ኖላዊ፡ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ፤ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ

በዓለ ኖላዊ

በቀደሙ አባቶቻችንና እናቶቻችን ድል የማትነሣ ረድኤት፣ ጥርጥር የሌለባት እምነት የተዋበች ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን የቀናች፣ የጸናች ሃይማኖትን የምትመሰክርበት አስተምህሮ በነቢያትና በሐዋርያት ትምህርት የተመሰረተ ሲሆን የማዕዘኑም ራስ የቤተክርስቲያን ልዩ ሊቀ ካህናት፣ አብሲዳማኮስ የተባለ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ (ኤፌ. 2፡20፣ ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤጲፋንዮስ 54፡21) ሰማያውያን ቅዱሳን ሰዎችና መላእክት በማይፈጸም ምስጋና የሚያመሰግኑትን ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ቅድስት ቤተክርስቲያን ከቅዱስ ያሬድና ከሌሎችም የቤተክርስቲያን መብራቶች በተማረችው መሰረት ወራትን፣ አዝማናትን ከፍላ ታመሰግነዋለች፣ የማዳኑን ሥራ ትመሰክራለች፡፡ በነቢያት ትንቢት መሰረትነት ቆማለችና ትንቢተ ነቢያትን ተስፋ አበውን ታዘክራለች፡፡ በሐዋርያት ስብከት ጸንታለችና መንፈሳዊ አገልግሎትን ለንግድና ለታይታ ከሚያደርጉ ምንደኞች ራሷን ለይታ ምዕመናን በብዙ መከራ የእግዚአብሔርን መንግስት ለመውረስ ፍጹማን እንዲሆኑ ታስተምራለች፡፡ (ሐዋ. 14፡22) ካህናቷም እንደ ጌታቸው፣ እንደ መምህራቸው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም እርሱን እንደመሰሉ ቅዱሳን እውነተኛ ጠባቂ፣ እውነተኛ እረኛ (ኖላዊ ኄር) እንዲሆኑ ታስተምራለች፡፡ ይህ የቸር ጠባቂነት (እውነተኛ እረኝነት) ነገር ጎልቶ ከሚነገርባቸው ዕለታት አንዱ በታኅሳስ ወር ከጌታችን በዓለ ልደት አስቀድሞ በሚውለው ሰንበት የሚከበረውና ከጌታችን ዘጠኝ ንዑሳን በዓላት አንዱ የሆነው “ኖላዊ” ይባላል፡፡

ከጌታችን በዓለ ልደት አስቀድሞ ከኅዳር 15 እስከ ታኅሳስ 28 ድረስ ቅድስት ቤተክርስቲያን የነቢያትን ጾም ትጾማለች፤ የነቢያትን ሱባኤ ታዘክራለች፤ የነቢያን ተስፋ፣ ጩኸት ታስባለች፡፡ ቅዱሳን ነቢያት ጾማቸው፣ ሱባኤያቸው፣ ተስፋቸውና ጩኸታቸው ዓለምን የሚመግብ፣ የሚጠብቅ እግዚአብሔር ለቀዳማዊ አዳም የገባለትን ቃል፣ የሰጠውን ተስፋ ፈጽሞ አንድያ ልጁን እንዲልክ መማጸን ነበር፡፡ ስለሆነም በዕለተ ኖላዊ ቅድስት ቤተክርስቲያን የነቢያትን ተስፋ ሊፈጽም የተገለጠ የኢየሱስ ክርስቶስን እውነተኛ እረኝነት (ጠባቂነት) ትመሰክራለች፡፡ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በኋላ የሐዲስ ኪዳንን ቤተክርስቲያን በእረኝነት (በጠባቂነት) እንዲመሩ የተሾሙ ካህናትና መምህራንን ክብር ታስረዳለች፡፡ ምዕመናንም ደገኞቹን (እውነተኞቹን) ካህናትና መምህራን አክብረው ቢቀበሉ የቅዱሳንን በከረት እንደሚወርሱ ታስተምራለች፡፡ (ማቴ. 10፡40) በአንጻሩ ደግሞ ለግል ጥቅም ሲሉ በመንፈሳዊ አገልግሎት ስም ከሚነግዱ ምንደኞች (ቅጥረኞች) እንዲለዩ ትመክራለች፡፡ በዚህች አጭር ጦማር በዕለተ ኖላዊ በቅድስት ቤተክርስቲያን ከሚነበቡ የመጽሀፍ ቅዱስ ምንባባት መካከል ከትንቢተ ነቢያት መዝሙረ ዳዊት 79፡1ን፣ ሐዋርያት ከመዘገቡት የጌታችን ትምህርት (ወንጌል) ዮሐንስ ወንጌል 10፡1-22ን በመጠኑ ለማብራራት እንሞክራለን፡፡

የኖላዊ ሰንበት ምስባክ

በዕለተ ኖላዊ በቅድስት ቤተክርስቲያናችን የሚሰበከው ምስባክ ከክቡር ዳዊት መዝሙር 79፡1 የተወሰደ ሲሆን ንባቡ፡-“ኖላዊሆሙ ለእስራኤል አጽምዕ፤ ዘይርእዮሙ ከመ አባግዐ ዮሴፍ፤ ዘይነብር ዲበ ኪሩቤል አስተርአየ/ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ፣ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ፤ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ/” የሚል ነው፡፡

የዮሴፍ በጎች በግብጽ ይጠበቁ እንደነበር፣ እስራኤል ዘሥጋ፣ እስራኤል ዘነፍስን የጠበቅካቸው፣ የምትጠብቃቸው፣ በኪሩቤል (በአርባእቱ እንስሳ) አድረኸ የምትኖር ጌታ ሆይ እባክህ ተገለጥ፤ ኀይልህን አንሣ፣ እኛንም ለማዳን ና፡፡ ከአዳም ጀምሮ የነበሩ አርዕስተ አበው ሁሉም ይህን ጸሎት ጸልየውታል፣ ይህን ልመና ለምነውታል፡፡ አዳምና ሄዋን በበደላቸው ቢፈረድባቸውም በንስሃቸው የመዳንን ተስፋ ተቀብለው ነበርና ጌታ ተስፋቸውን እንዲፈጽምላቸው ዘመናቸውን ሙሉ በፍጹም መንፈሳዊ መታዘዝ “የኀያላን አምላክ ሆይ መልሰን፣ ፊትህንም አብራ፣ እኛም እንድናለን” የሚለውን የመሰለ ጸሎት እየጸለዩ የተስፋ ዘመናቸውን ፍጻሜ፣ የሚቤዣቸውን የክርስቶስን ልደት (መገለጥ) በእምነት ይጠብቁ ነበር፡፡ ሌሎችም የብሉይ ኪዳን ነቢያትና ቅዱሳን እንዲሁ፡፡ የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ የተወደደ ሐዋርያ ፊልጶስ “ሙሴ በኦሪት፣ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው፡፡” (ዮሐ. 1፡46) በማለት እንደተናገረ ዮሴፍን እንደ መንጋ የሚመራ፣ እስራኤል ዘነፍስን የሚጠብቅ፣ የሚያሻግር (የጠበቀ፣ ያሻገረ) ታኦዶኮስ ከተባለች ከሐዲስ ኪዳን ኪሩቤል ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ነቢያት በረድኤት ሳይሆን በአካል (በሥጋ በመወለድ) ታወቀ፤ ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠ፡፡ እርሱም የሁሉም ጠባቂ፣ ቸር እረኛ ነው፡፡

ለእረኝነት የተመረጡት ምንደኛ ሲሆኑ የመረጣቸው ጌታ ተገለጠ

በበዓለ ኖላዊ የሚነበበው ወንጌል ጌታችን “ቸር ጠባቂ (መልካም እረኛ) እኔ ነኝ፡፡” ብሎ ያስተማረው በዮሐንስ ወንጌል 10፡1-22 ያለው አምላካዊ ቃል ነው፡፡ ጌታችን በዚህ ትምህርቱ ስለ እረኝነት ከማስተማሩ አስቀድሞ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 8 እና 9 ባሉ ሁለት አስተማሪ ታሪኮች ለእረኝነት የተሾሙ፣ በሙሴና በነቢያት ወንበር የተቀመጡ የአይሁድ ሊቃናትን የእረኝነትን አገልግሎት በማጉደፋቸው ነቅፏቸዋል፡፡ በምዕራፍ 8 በተጻፈው የዘማዊቷ ሴት ታሪክ ለእረኝነት የተሾሙት የአይሁድ አለቆች ኃጢአታቸውን ደብቆ የሕግ መምህራን ቢያደርጋቸው ለበጎ ከመጠቀም ይልቅ እንደነርሱ ኃጢአተኛ የሆነችን ሴት በተጣመመ ፍርድ ለማጥቃት አዋሉት፡፡ በምዕራፍ 9 በተጻፈው ዕውር ሆኖ የተወለደው ልጅ (ዘዕውሩ ተወልደ) ታሪክ እንደተገለጠው አይሁድ እንዲጠብቁት፣ እንዲያስጠብቁት የተሰጣቸውን ትዕዛዛተ እግዚአብሔር ለራሳቸው የማይረባ፣ የታይታ ክብር ሲሉ አቃልለውት ነበርና እነርሱን የሚያስጨንቃቸው የታሰሩት መፈታት፣ የታመሙት መፈወስ፣ የሕግጋተ እግዚአብሔር መፈጸም ጉዳይ አልነበረም፡፡ ከዚያ ይልቅ ማንኛውም መንፈሳዊ ምግባር የእነርሱን ክብርና ዝና የሚቃረን ከመሰላቸው ማሩን አምርረው፣ ወተቱን አጥቁረው ጻድቁን “ኃጢአተኛ”፣ የታወቀውን በደለኛ “ንጹህ” ነው በማለት የእረኝነትን (የመምህረ ሕግነትን) መመዘኛ አዛብተውት ነበር፡፡ “ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ ተመልሶ ተቆጣጠራቸው፡፡” (ማቴ. 24፡ 19) እንደተባለ ያላከበሩትን ክህነታቸውን የሚያሳልፍ፣ ለሚያከብሯት፣ ለሚያገለግሉባት ትሁታን ሐዋርያት አሳልፎ የሚሰጥ የእረኞች አለቃ ኢየሱስ ክርስቶስ መገለጡን አላወቁም ነበር፡፡

የሐዲስ ኪዳን ትሁታን እረኞች (ኖሎት ኄራን)

የካህናት፣ የመምህራን እረኝነት በብሉይ ኪዳን ዘመን ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ እውነተኛ፣ ቸር ጠባቂ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለበጎቹ ነፍሱን አሳልፎ ከሰጠ በኋላ የመሰረታትን ቤተክርስቲያን ይመሩ፣ ይጠብቁ ዘንድ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ኤጲስ ቆጶሳትንና ካህናትን ሾሞልናል፡፡ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 21፡15-17 ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚነሱ የሐዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ጠባቂዎች ካህናትና መምህራንን ወክሎ በጎችና ግልገሎችን እንዲጠብቅ፣ ጠቦቶችን እንዲያሰማራ የታዘዘው ለዚህ ነው፡፡ እነዚህ ካህናት እንዴት ቤተክርስቲያንን ማገልገል እንዳለባቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃል ትምህርት አስተምሯል፣ በአርዓያነት በትህትና፣ ራስን ዝቅ በማድረግ አገልግሎ አሳይቷል፣ እንዲሁም ከምንም በላይ እስከ መስቀል ሞት ድረስ በመከራ ታግሶ የካህናትን የአገልግሎት መከራ ባርኮላቸዋል፡፡

ትምህርቱ እንደ አይሁድ ሊቃነ ካህናት የእግዚአብሔርን ቃል ለራስ ጥቅም በማጣመም ሳይሆን ፊት አይቶ ሳያደላ እውነትን በመግለጥ፣ ቸርነትንም በማድረግ የተሞላ ነበር፡፡ አገልግሎቱ እንደ አይሁድ ሊቃነ ካህናት ክብርን በመፈለግ፣ ልብስና ሥምን በማሳመር፣ ራሱን እንደ ክፉ ባለስልጣን ከወገኖቹ በማራቅ ሳይሆን ወገቡን ታጥቆ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ የተገለጠ ነበር፡፡ በእርሱ ላይ ከሳሾቹ ያገኙበት በደል ባይኖርም ከአዳም ጀምሮ እስከ ዓለም ፍጻሜ ለሚነሱ ምዕመናንና ምዕመናት ኃጢአትና በደል ራሱን ለመከራ መስቀል በፈቃዱ አሳልፎ በመስጠት የሐዲስ ኪዳን ትሁታን እረኞች ፍለጋውን ይከተሉ ዘንድ አስተምሯል፡፡ ስለሆነም የሐዲስ ኪዳን ካህናት ልዩ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን መስለው እንደየአቅማቸው ካገለገሉ ክብራቸው እጅግ ልዩ ነው፡፡ በአንጻሩ እንደ አይሁድ ሊቃናት የእግዚአብሔርን ህዝብ በቅንነት ከማገልገል ይልቅ ለራሳቸው ጥቅምና ክብር ሲሉ አገልግሎታቸውን ካቀለሏት ግን መክሊቱን የሰጣቸው ጌታ በዘመኑ ፍጻሜ ሊቆጣጠራቸው በተገለጠ ጊዜ “አላውቃችሁም” ይላቸዋል፤ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ባለበት የዘላለም መከራም ይቀጣሉ፡፡

እውነተኛ መምህራን ከሐሰተኞች በምን ይለያሉ?

ዘመናችን ከምንም ጊዜ በላይ ምዕመናንን ከቀናች ሃይማኖት የሚለዩ፣ ለራሳቸው ጥቅም ትምህርተ ወንጌልንና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የሚያጣምሙ ሐሰተኛ መምህራን የበዙበት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እውነተኛ እረኛ እንዳስተማረው ሁሉ በተነጻጻሪ ስለ ሐሰተኛ መምህራንም አስተምሯል፡፡ ጌታችን በአንቀጸ ኖላዊ ያስተማረውን የሚተረጉሙ ሊቃውንት እውነተኛ መምህራንን ከሐሰተኞች እንደሚከተለው ይለያሉ፡፡

እውነተኛ መምህራን ቅዱሳት መጻህፍት ይመሰክሩላቸዋል፤ እነርሱም በቅዱሳት መጻሕፍት አጥርነት፣ በሥርዓተ ቤተክርስቲያን ጋሻነት ተጠብቀው ቅዱስ ቃሉን ያስተምራሉ፡፡ ሐሰተኛ መምህራን ግን በልብ ወደድ ይጓዛሉ፤ በስህተት ትምህርትም ምዕመናንን ከቤተክርስቲያን (ቤተክርስቲያንን ከምዕመናን) ይለያሉ፡፡ ህገ ሃይማኖትን፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ይንቃሉ፣ ያቃልላሉ፡፡

እውነተኛ መምህራን በጽኑ አገልግሎት፣ በፍጹም አርዓያነት ደቀመዛሙርትን ያፈራሉ፤ ስለ ራሳቸው ክብርም አይናገሩም፣ አያስነግሩም፡፡ እግዚአብሔርም ከሞታቸው በኋላ መታሰቢያቸውን እንዳይጠፋ ያደርጋል፣ በረከታቸውም ለትውልድ ይተርፋል፡፡ ሐሰተኛ መምህራን ግን ስለ ራሳቸው የሚናገሩ (የሚመሰክሩላቸውን)፣ በእግዚአብሔር ቃል ሳይሆን በወገንተኝነትና በድጋፍ የእግዚአብሔርን ቃል የሚያጣምሙ መሰሎቻቸውን ያፈራሉ፡፡ ደቀ መዛሙርት ይጠይቃሉ፣ ይሞግታሉ፣ ያምናሉ፣ ያሳምናሉ፡፡ የሐሰተኛ መምህራን ደጋፊዎች ግን እንዲህ አይደሉም፤ ቢጠይቁ፣ ቢሞግቱ እንኳ ለማመን ለማሳመን ሳይሆን ለክብርና ለዝና እንዲሁም ለወገንተኝነት ብቻ ነው፡፡ ለጊዜው ብዙዎች ይከተሏቸዋል፡፡ በኋላ ግን ማንነታቸው ይገለጣል፤ እንደ ቴዎዳስ ዘግብፅ እና ይሁዳ ዘገሊላ ተከታዮቻቸው ይጠፋሉ፣ እነርሱም መታሰቢያቸው ይረሳል፡፡

እውነተኛ መምህራን ስለ ምዕመናን መጠበቅ፣ ስለ ሕገ ሃይማኖትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ሲሉ ያለበደላቸው ልዩ ልዩ መከራን ይቀበላሉ፤ መከራን ይቀበሉታል እንጂ እነርሱ ሸሽተው ምዕመናንን በተኩላ አያስበሉም፡፡ ሐሰተኛ መምህራን ግን ቤተክርስቲያንን (ምዕመናንን) የሚፈልጓቸው በደስታ ወቅትና በጥቅማቸው ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ከሀዲ ባለስልጣን፣ መናፍቅ ጳጳስ ሲመጣ ወገንተኝነታቸው ለጥቅማቸው እንጂ ለቤተክርስቲያን አይደለም፡፡

እውነተኛ የበጎች እረኛ እንደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቶ በጎች ቢኖሩትና ከእነርሱ አንዱ ቢባዝን ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ትቶ ይባዘነውን ይፈልገዋል፡፡ (ማቴ. 18፡12-14፣ ሉቃስ 15፡4-5) የጠፋው አንድ ነው ብሎ ንቆ አይተወውም፡፡ የጠፋውን ሲፈልግም ያሉትን በትኖ ሳይሆን በተራራ ትቷቸው (አስጠብቋቸው) ይሄዳል፡፡ ቸር ጠባቂ ለደመወዝ (የግብር ይውጣ አገልግሎት) ሳይሆን በመክሊቱ ለማትረፍ በቅንነት ስለሚሰራ ስለ በጎቹ ይገደዋልና፡፡ በአንፃሩ በጎቹ ገንዘቡ ያይደሉ ምንደኛ፣ ሐሰተኛ እረኛ (መምህር) ግን ስለበጎቹ አይገደውም፡፡ የጠፋውን አይፈልግም፣ ቢፈልገውም ለጥቅሙ ብቻ ይፈልገዋል፡፡ ያልባዘኑትንም አያጸናም፣ የሚያጸና ቢመስል እንኳ የበጎቹን ጸጉር እየላጨ ለመሸጥ፣ ሥጋቸውን ወተታቸውን ለመብላት ለመጠጣት ይፋጠናል እንጂ እዳሪያቸውን ለመጥረግ (መከራቸውን ለመጋራት) አይፈልግም፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ እረኝነትና የተሾሙ ካህናት እረኝነት ልዩነት

የእግዚአብሔር ቤተሰቦች በዓለ ኖላዊን ስናከብር ሁላችንም ልናስተውለው የሚገባው ነቢያት በተስፋ የተናገሩለት በኪሩቤል ላይ የሚቀመጥ የነፍሳችን እረኛና ጠባቂ ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላችን አለ፡፡ (1ኛ ጴጥ. 2፡25) ይጠብቀናል፡፡ (መዝ. 22፡1-6) ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ (ያስወገደ) የእግዚአብሔር በግ ነው፡፡ (ዮሐ. 1፡29) በቤዛነቱ የእግዚአብሔር በግ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጋቢነቱ፣ በጠባቂነቱ፣ በመምህርነቱ በጎች የተባሉ የምዕመናን ሁሉ ጠባቂያቸው ነው፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ጠባቂነት፣ መጋቢነት፣ መምህርነት በሹመት በትምህርት የተገኜ ሳይሆን የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ የማዳን ተስፋውን በቅዱሳን አድሮ የሚገልጥ ጌታ በሥጋ የተገለጠበት ዘመን ከተፈጸመ በኋላ ዳግመኛ ተገልጦ ወደ መንግስቱ እስኪወስደን ድረስ ካህናትን መምህራንን እንደራሴዎቹ አድርጎ ሰጥቶናል፡፡ እነርሱም ትምህርተ ኖሎትን በሚገባ ተረድተው በቅንነት ምዕመናንን ሊያገለግሉ ይገባል፡፡ (1ኛ ጴጥ. 5፡2፣ ሐዋ. 20፡28) የካህናት የመምህራን ጠባቂነት በሹመት፣ በትምህርት የሚገኝ እንጅ የራሳቸው አይደለም፡፡ በጎች የተባሉ ምዕመናንም በአደራ የሚጠብቋቸው (የሚንከባከቧቸው፣ የሚያገለግሏቸው) ናቸው እንጅ የግል ገንዘቦቻቸው አይደሉም፡፡ እግዚአብሔር የሰጠንን የተሾሙ እውነተኛ ካህናት አክብረን በመያዝና ከሐሰተኞች በመራቅ እውነተኛ እረኞች እንዲበዙልን የአቅማችንን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል፡፡

“እኔም የወንድሜ (የእህቴ) ጠባቂ ነኝ!” እንበል

ምንም እንኳ እረኝነት (ጠባቂነት) በዋናነት ለካህናት ብቻ የተሰጠ ቢሆንም ሁላችንም እንደየአቅማችን የወንድሞቻችን፣ የእህቶቻችን ጠባቂዎች መሆናችንን መዘንጋት አይገባም፡፡ ስለሆነም “እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” (ዘፍጥ. 4፡9) በማለት በትዕቢት እንደተናገረ እንደ ቃየል ሆነን ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን ከቀናች ሃይማኖት፣ ከበጎ ምግባር ሲራቆቱ “አያገባንም” ልንል አይገባም፡፡ ይልቁንስ የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ “በሥጋ ዘመዶቼና ወንድሞቼ ስለሚሆኑ እኔ ከክርስቶስ እለይ ዘንድ እጸልያለሁ፡፡” (ሮሜ. 9፡3) እንዳለ እኛም ለወንድሞቻችንና እህቶቻችን ልንራራላቸው ቸር ጠባቂ ወደ ሆነ እግዚአብሔር ለማድረስም የአቅማችንን ልናደርግ ይገባል፡፡ እኛ እያንዳንዳችን በየደረጃችን እረኝነታችንን ሳንወጣ በዓለ ኖላዊን ብናከብር፣ ስለ እውነተኛና ሐሰተኛ መምህራንም ብንተርክ ምናልባት ለእውቀት እንጂ ለጽድቅ አይሆንልንም፡፡ ራስን ሳይጠብቁ ለሌላው መትረፍ አይቻልምና ስለሌሎች ከማሰባችን አስቀድመን ግን እያንዳንዳችን ራሳችንን ልንጠብቅ (በሃይማኖት፣ በምግባር ልንጸና) ይገባል፡፡ ዮሴፍን እንደመንጋ የጠበቀ (የሚጠብቅ)፣ ከሐዲስ ኪዳን ኪሩቤል ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ሥጋና ነፍስን ነስቶ እኛን ለመጠበቅ (ለማዳን) የተገለጠ የሥጋችንና የነፍሳችን እረኛና ጠባቂ ልዩ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ እያንዳንዳችን የወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን ጠባቂዎች የምንሆንበትን ጥበብ መንፈሳዊ እንዲያድለን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ አሜን፡፡

ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን፡ የሙታንን መነሣት ተስፋ እናደርጋለን የሚመጣውንም ሕይወት ለዘለዓለሙ!

coming again
የትንሣኤ ሙታን ትርጉም

ትንሣኤ የሚለው ቃል ተንሥአ ካለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን መነሣት ማለት ነው፡፡ ትንሣኤ ሙታን ማለት የሙታን መነሣት ማለት ነው፡፡ ይህም ተለያይተው በተለያየ ስፍራ ይኖሩ የነበሩ ነፍስና ሥጋ ተዋሕደው መነሣት፣ ከሞት በኋላ በነፍስና በሥጋ ሕይወት ማግኘት ማለት ነው፡፡ በመጀመሪያው ሞት ምክንያት የተለያዩት ነፍስና ሥጋ በመጨረሻው ዘመን ዳግመኛ የሚኖራቸው ኅብረት ትንሣኤ ሙታን ይባላል፡፡ ሙታን በመጨረሻው ቀን ዳግመኛ በማይሞት ሥጋ ሕያዋን የሚሆኑበት አምላካዊ ጥበብ ትንሣኤ ሙታን ይባላል፡፡ ይህ የሙታን መነሣት ሁኔታ በሰው ልጅ አእምሮ ሊደርስበትና ሊታወቅ የማይችል ረቂቅ ጥበብ ስለሆነ ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ምስጢር ተስፋ የምናደርገው ሲሆን ክርስቶስ ዳግመኛ ከመጣ በኋላ ለሚኖረው ዘላለማዊ ሕይወት መጀመሪያ ነው፡፡ ትንሣኤ ሙታን በአዳምና በልጆቹ ላይ የተፈረደው የሞት ፍርድ ለመጨረሻ ጊዜ የሚጠፋበት ነው፡፡

በሐዋርያት እግር የተተኩና የእነርሱንም አሠረ ፍኖት የተከተሉ ሃይማኖታቸው የቀና ቅዱሳን አባቶች መናፍቃንን ባወገዙባቸውና ርትዕት ሃይማኖትን ባጸኑባቸው ጉባዔያት ሌሎቹን አንቀጾች ‹‹እናምናለን›› በማለት ካስቀመጡ በኋላ ‹‹የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን፤ የሚመጣውንም ሕይወት ለዘላለሙ›› ብለው ደንግገዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው ሌሎቹ አንቀጾች ‹‹እምነት›› ላይ ሲያተኩሩ ይህ ግን ‹‹ተስፋ›› መሆኑን ነው፡፡ ይህ የጌታችንና የሐዋርያትን አስተምህሮ መሠረት ያደረገው የቤተክርስቲያናችን ጸሎተ ሃይማኖት (የሃይማኖት ጸሎት) የመጨረሻው አንቀጽ ነው፡፡ ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹ልጁንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው። እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ» (ዮሐ 6፡40) እንዳለው ትንሣኤ ሙታን የእምነታችን አንዱ መሠረት ነው፡፡

ከትንሣኤ በኋላ የሚኖረውም ዘላለማዊ ሕይወት ታላቅ ተስፋችን ስለሆነ ቅዱሳን አበው ‹‹የሚመጣውንም ሕይወት ለዘላለሙ አሜን›› በማለት የሃይማኖት ድንጋጌውን ፈጽመውታል፡፡ ስለዚህ የዘላለም ሕይወት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ «ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን» (2ጴጥ 3፡13) በማለት ሲናገር ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም «እኛ አገራችን በሰማይ ነውና። በዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርቶስን እንጠብቃለን። እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደ ሚችልበት አሠራር ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል» (ፊል 3፡20-21) ብሎ ዘላለማዊ ተስፋችንን አጽንቶልናል፡፡ ባለራዕዩ ዮሐንስም «አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርንም አየሁ፤ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና። ባሕርም ወደ ፊት የለም። ቅድስቲቱ ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ» (ራዕ 21፡1-2) በማለት ተስፋ መንግስተ ሰማያት አዲሲቱ ኢየሩሳሌም መሆኗን ተራግሯል፡፡

ሞት ምንድን ነው?

ሰው ከመሬት የተሠራ ሥጋና ዘላለማዊት ነፍስ ያለው ፍጡር ነው፡፡ ሰው አራት ባህርያተ ሥጋ (አፈር፣ እሳት፣ ነፋስና ውኃ) እንዲሁም ሦስት ባህርያተ ነፍስ (ለባዊት፣ ነባቢት፣ ሕያዊት) ያለው ፍጡር ነው፡፡ ዘላለማዊ ሆኖ በገነት እንዲኖር የተፈጠረው ሰው የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በመሻሩ ሞት መጣበት፡፡ በሃይማኖታዊው ትርጉም ሞት ማለት የሥጋና የነፍስ መለያየት ነው (ያዕ 2፡26 ማቴ 10፡28 መዝ 30፡5 ሉቃ 23፡46 ሐዋ 7፡59 ራዕ 6፡9)፡፡ ሞት ተዋሕደው የሚኖሩት ነፍስና ሥጋ ተለያይተው ነፍስ ከእግዚአብሔር እስትንፋስ የተገኘች ናትና ወደ እግዚአብሔር፣ ሥጋ ደግሞ ወደ ተገኘበት ወደ መሬት የሚሄድበት ሁኔታ ነው፡፡ በሳይንሳዊ ትርጉሙ ደግሞ ሞት ማለት ለሕይወት መቀጠል አስፈላጊ የሆኑት ሕዋሳት ሥራ ማቆም ነው፡፡ በሌላ በኩል ሁለተኛ/ዳግመኛ ሞት የሚባለው ከእግዚአብሔርና ከእግዚአብሔር መንግስት መለየት (ወደ ዘላለም ቅጣት መግባት) ነው፡፡

የትንሣኤ ሙታን የብሉይ ኪዳን ማስረጃዎች

ትንሣኤ ሙታን አስቀድሞ ነቢያት ያስተማሩት ተስፋ ነው፡፡ ነቢዩ ዳንኤል ‹‹በምድር ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች ይነሣሉ እኩሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት እኩሌቶቹ ወደ እፍረትና ጉስቁልና›› (ዳን 12፡2) በማለት የሙታን ትንሣኤ መኖሩን ተናግሯል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስም ‹‹ሙታን ሕያዋን ይሆናሉ ሬሳዎችም ይነሣሉ በምድርም የምትኖሩ ሆይ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና ምድርም ሙታንን ታወጣለችና ንቁ ዘምሩም›› (ኢሳ 26፡19) ብሎ በመጨረሻ ያንቀላፉት ሁሉ እንደሚነሱ በትንቢቱ አስተምሯል፡፡ በተጨማሪም ነቢዩ ሕዝቅኤል ‹‹ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ትንፋሽን አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ። ጅማትም እሰጣችኋለሁ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ በእናንተም ላይ ቁርበትን እዘረጋለሁ ትንፋሽንም አገባባችኋለሁ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ›› (ሕዝ 37፡1-10) በማለት ሙታን እንደሚነሱ አብራርቶ ተናግሯል፡፡ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊትም እንዲሁ ‹‹ብዙ መከራና ጭንቀት አሳይተኸኛልና ተመልሰህ ሕያውም አደረከኝ ከምድር ጥልቅም እንደገና አወጣኝ›› (መዝ 70፡20) በማለት ስለ ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን ዘምሯል፡፡

የትንሣኤ ሙታን የሐዲስ ኪዳን ማስረጃዎች

በሐዲስ ኪዳንም እንዲሁ ስለትንሣኤ ሙታን ጌታችን በወንጌል ሐዋርያትም በመልእክቶቻቸውና በስብከታቸው አጽንተው አስተምረዋል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ››(ዮሐ 5፡ 28-29) በማለት ሙታን ለክብርና ለአሳር እንደሚነሱ አስተምሯል፡፡ ስለነገረ ምጽአቱ በተናገረበት ክፍልም ‹‹የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል›› (ማቴ 25፡31-32) ብሎ ስለሙታን መነሳትና ስለመጨረሻው ፍርድ ነግሮናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹እነሆ፥ አንድ ምሥጢር እነግራችኋለሁ፤ ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበት ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን።›› (1ኛ ቆሮ 15፡52) በማለት የሰው ልጅ በማይበሰብስ ሥጋ እንደሚነሳ በመልእክቱ ጽፎታል፡፡

ለጊዜው ከሞት የተነሱ ሰዎች

ነፍሳቸው ከሥጋቸው ከተለየች በኋላ በቅዱሳን ጸሎት፣ በጌታችን ተዓምራት ለጊዜው ከሙታን የተነሱ ሰዎች የትንሣኤ ሙታን ምሳሌዎች ናቸው፡፡ የእነርሱ መነሳት ነፍስና ሥጋ ዳግመኛ መዋሐድ እንደሚችሉ ያሳያሉና፡፡ በብሉይ ኪዳን ለጊዜው ከሙታን የተነሡ ነቢዩ ኤልያስ ያስነሣው ብላቴና (1ኛ ነገ 17፡ 21) እና ነቢዩ ኤልሳ ያስነሣው ብላቴና (2ኛ ነገ 4፡18)፣ በነቢዩ ኤልሳ አጽም የተነሳው እስራኤላዊ ሰው (2ኛ ነገ 13-20) ይገኙበታል፡፡ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ ያለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዘመነ ሥጋዌው የመበለቲቱን ልጅ (ሉቃ 7፡11)፣ የኢያኢሮስን ልጅ (ሉቃ 8፡49)፣ አልዓዛርን (ዮሐ 11፡1-44) እና የኢየሩሳሌም ቅዱሳንን (ማቴ 27፡50)  ከሞት አስነስቷል፡፡ የሐዋርያት አለቃ የነበረው ቅዱስ ጴጥሮስም ጣቢታን ከሞት አስነስቷል (ሐዋ 9፡ 36)፡፡ የእነዚህ ሁሉ ትንሣኤ ግን ዳግመኛ መሞት የነበረበት ጊዜያው ትንሣኤ ነበር፡፡

ዘላለማዊ ትንሣኤ

መድኃኒዓለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአባታችን ለአዳም በገባው ቃልኪዳን መሠረት: በአይሁድ እጅ መከራ መስቀልን ከተቀበለ በኋላ ነፍሱን በራሱ ስልጣን አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ዐርብ በ11 ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ መስፍኑ ጲላጦስን አስፈቅደው ከመስቀል አውርደው ዮሴፍ ራሱ ባሰራው መቃብር በንጹህ በፍታ ገንዘው ቀብረውት ገጥመው ሲሄዱ ጸሐፍት ፈሪሳውያንና መስፍኑ በመቃብሩ ላይ ማኅተማቸውንና ጠባቂዎችን አኖሩ (ማቴ 27÷57-66 ማር 15÷42 ሉቃ 23÷50 ዮሐ 19÷38-42) ፡፡ በሦስተኛው ቀን እሑድ በእኩለ ሌሊት መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በታላቅ ኃይል ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ተነሣ ይጠብቁ የነበሩ ጠባቂዎችም ደንግጠው ተበታተኑ በመቃብሩ ዙሪያ ቅዱሳን መላዕክት ታዩ (ማቴ 28÷1-15 ማር 16÷11-15 ሉቃ 24÷1-43 ዮሐ 20÷1-25 1ኛ ቆሮ 15-1 ሮሜ 6÷9-15)፡፡ ለሰው ልጆች ዘላለማዊ ትንሣኤ በኩር የሆነው የክርስቶስ ትንሣኤ ነው፡፡ ከክርስቶስ ትንሣኤ ቀጥሎ ዘላለማዊ ትንሣኤን የተነሣችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ የድንግልም ትንሳኤ ዘላለማዊ ስለሆነ እንደሌሎች ሰዎች የመጨረሻውን ትንሣኤ አልጠበቀችም፡፡  በመጨረሻው ቀን ሁላችን የምንነሳው ትንሣኤ እንዲሁ ዳግመኛ ሞት የሌለበት ዘላለማዊ ትንሣኤ ነው፡፡

ትንሣኤ ዘለክብር፡- የሚነሡት ጻድቃን የሚወርሱት መንግሥተ ሰማያትን ሲሆን ሲነሡ ብርሃን ለብሰው ብርሃን ተጎናጽፈው እንደ ፀሐይ እያበሩ ወንዶች የ30 ዓመት ጎልማሳ ሴቶች የ15 ዓመት ቆንጆ ሆነው ለዘላለም በደስታ በሕይወት ለመኖር የሚነሡት ትንሣኤ ነው፡፡ (ራዕ 21÷1-5 ፤ 2ተኛ መቃ 13÷8-14) የ30 ዓመትና የ15 ዓመት መባሉ አዳምና ሄዋን ሲፈጠሩ የ30 ዓመትና የ15 ዓመት ሆነው ተፈጠሩ ብለው ሊቃውንት ከሚያስተምሩት ጋር በተመሳሳይ መልኩ ለሰው በሚገባ ቋንቋ ሙሉ ሰው መሆናቸውን ለማስገንዘብ እንጅ ከትንሣኤ በኋላ የሚቆጠር እድሜ ኖሮ አይደለም፡፡ እድሜ የሚቆጠረው በፀሐይ፣ በጨረቃ፣ በከዋክብት ነው፡፡ ከዳግም ምጽዓት በኋላ እነዚህ ሁሉ ፍጥረታት ስለሚያልፉ በማይቆጠር እድሜ እንኖራለን፡፡  

ትንሣኤ ዘለኃሣር ፡-ይህን ትንሣኤ የሚነሡት ሰዎች በዚህች ምድር ሳሉ እግዚአብሔርን ሲበድሉ በክህደት በምንፍቅና የሚኖሩ ትንሣኤ ልቡና ያላገኙ ሰዎች የሚነሡት ትንሣኤ ነው፡፡ ትንሣኤ ዘለኃሣር የሚነሡት ኃጥአን ከቁራ ሰባት እጅ ጠቁረው የግብር አባታቸውን ሰይጣንን መስለው ለዘላለም ትሉ በማያንቀላፋበት እሳቱ በማይጠፋበት በገሃነመ እሳት ውስጥ ይኖራሉ፡፡ (1ኛ መቃ 13÷9-11′ ማቴ 13÷-42)

ዳግም ምጽዓት

ዕለተ ምጽአት /ዳግም ምጽአት/ የምትባለው ዕለት ጌታችን በግርማ መለኮት በክበበ ትስብዕት ሆኖ ዳግመኛ ይመጣል፡፡ የተወጋ ጎኑን የተቸነከረ እጅና እግሩን እያሳየ ለጻድቃን ሊፈርድላችው ለኃጥአንና ለሰይጣን ሊፈርድባቸው ዓለምን ለማሳለፍ የሚመጣባት ዕለት ናት (መዝ 49/50÷2-3′ ራዕ 22÷12)፡፡ ጌታችን በዓለም ፍጻሜ ዳግመኛ እንደሚመጣ በደብረ ዘይት ተራራ በሰፊው አስተምሯል፡፡  አመጣጡም ‹‹መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፡፡››(ማቴ 24፡ 27) እንዳለው ለሁሉም በአንድ ጊዜ የሚታይ ነው፡፡ ከመምጣቱ አስቀድሞ ግን ብዙ ምልክቶች ይታያሉ፡፡ የመምጣቱም ነገር አስጨናቂ እንደሆነ ሲናገር ‹‹በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል››(ማቴ 24፡30) በማለት ገልጾታል፡፡ ‹‹የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል።›› (ማቴ 16፡27) ጌታችን ስለ ነገረ ምጽዓት ሲናገር “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ወልድም ቢሆን የሚያውቃት የለም፡፡ በኖኅ ዘመንም እንደ ሆነ የሰው ልጅ አመጣጡ እነዲሁ ይሆናል፡፡” (ማቴ. 24፡36) በማለት አስተምሯል፡፡ የዚህም ዓላማ የጌታ መምጫው ድንገት መሆኑን ለማስረዳትና ያችም ዕለት በአብ ልብ ታስባ እንደምትኖር (ሥላሴ በአብ ልብነት ያስባሉና) የሚያስረዳ ድንቅ ምሥጢር ነው፡፡ ለአንዳንዶች እንደሚመስላቸው ለአብ የሚታወቅ ከወልድ ግን የተሰወረ ሆኖ አይደለም፡፡ የተናገረው ራሱ ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን፣ የተናገረበት አውድም ዳግመኛ ስለ ሚመጣበት ሰዓትና ዕለት ደቀመዛሙርቱ ጠይቀውት ሲመልስ መሆኑን ማስተዋል ከደካማ እይታ ሊሰውረን ይችላል፡፡ በተጨማሪም (ሉቃ 17፡28-30 ሉቃ 21፡34-36 ማቴ 25፡1-12 ሉቃ 12፡37-38 ዮሐ 14፡1-3 ሉቃ 12፡40 ማር 8፡38) ያሉት ነገረ ምጽአቱን ያስረዳሉ፡፡

የሙታን አነሳስ

የሞትህ ተነሥ የሚል አዋጅ በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል ይታወጃል፡፡ ሦስት ረቂቃን ነጋሪት አሉ፡፡ ነጋሪት ሲባል ነጋሪት አይደለም የጌታ ትዕዛዝ ነው ጌታ ራሱ በትዕዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምጽ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና (1ና ተሰ 4÷16) እንደተባለ የመጀመሪያው ረቂቅ ነጋሪት ሲመታ አውሬ የበላው ነፋስ የበተነው ያለቀው የደቀቀው ሁሉ ራስ በፈረሰበት ቦታ ላይ ይሰበሰባል (ያዕቆብ ዘሥሩግ ቁ.91)፡፡ ሁለተኛው ረቂቁ ነጋሪት ሲመታ አጥንትና ሥጋ ተዋሕደው ሳይንቀሳቀስ ትኩስ ሬሳ ይሆናል፡፡ አጥንትና ጅማቶች ከሥጋ ከደም ጋር ይያያዛሉ እስኪነሡ ያለመንቀሳቀስ ፍጹም በድን ይሆናሉ፡፡ ሦስተኛው ረቂቁ ነጋሪት ሲመታ በቀዋሚ አካል የምትናገር አንደበት ከራስ ጸጉራቸው ሳይከፈሉ በአርባ ቀን በእናቱ ማህጸን ደም ሆኖ የወረደው ጽንስ ሳይቀር በጎም ሆነ ክፉ ሥራቸውን ይዘው ይነሣሉ፡፡ በዳግም ትንሣኤ ሴቶች የ15 ዓመት ወንዶች የ30 ዓመት (ሙሉ ሰው ሆነው) ሆነው ይነሳሉ፡፡ ሲፈጠሩም ሙሉ ሰው ሆነው የ15 እና የ30 ዓመት ሆነው ስለነበር በዚያው ሰውነት ይነሳሉ፡፡ በምድር ላይ ስንኖር እንዳለው በሚበሰብስ ሥጋ ሳይሆን ዘላለማዊ በሆነው ሥጋ ሁላችን እንነሳለን፡፡

የመጨረሻው ፍርድ

ሁሉም እንደየሠራው የሚያገኝበት የመጨረሻው ቀን ፍርድ አለ፡፡ ይህም ከጌታችን ምጽአትና ያንቀላፉት ሁሉ ከተነሱ በኋላ ይከናወናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹የሚጥለኝ ቃሌንም የማይቀበለው እርሱ የሚፈርድበት አለው፤ እኔ የተናገርሁት ቃል እርሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል›› (ዮሐ 12፡48) በማለት ሰው በመጨረሻው ቀን የሰማው የእግዚአብሔር ቃል እንደሚፈርድበት ተናግሯል፡፡ እንዲሁም ‹‹እኔ እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል›› (ማቴ 12፡36) ብሎ ዛሬ ለምንናገራቸው ከንቱ ነገሮች ሁሉ በዚያ በፍርድ ቀን መልስ የምንሰጥበት ይሆናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በራዕዩ ስለመጨረሻው ቀን ፍርድ ሲናገር ‹‹ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ›› (ራዕ 20፡11-15) በማለት ሁሉም እንደ ሥራው የሚከፈልበት ፍርድ መሆኑን መስክሯል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ሰለዚህ ቀን ‹‹መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፥ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና›› (2ኛ ቆሮ 5፡10) ብሏል፡፡ እንዲሁም ለአቴና ሰዎች ‹‹ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል›› (ሐዋ 17፡31) በማለት እውነትን መስክሮላቸዋል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም ስለዚች ቀን ‹‹እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፥ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፥ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና›› (መክ 12፡14) ብሏል፡፡  ገነትና ሲኦል ጊዜያዊ የነፍሳት መቆያ ናቸው፡፡ መልካም የሠሩ ነፍሳት እስከ ትንሣኤ ሙታን ድረስ በገነት ይቆያሉ፡፡ ክፉ የሠሩ ደግሞ በሲኦል ይቆያሉ (2ኛ ጴጥ 3፡13 ራዕ 21፡1-5 2ኛ ቆሮ 5፡1 2ኛ ጴጥ 1፡14 ፊልጵ 3፡20-21)፡፡ መንግስተ ሰማያትና ገሀነመ እሳት፡ በመጨረሻው ፍርድ ጻድቃን ወደ መንግስተ ሰማያት፣ ኃጥአን ደግሞ ወደ ገሀነመ እሳት ይገባሉ (ማቴ 10፡28 ራዕ 20፡14-15 ራዕ 19፡20 ማር 9፡43)፡፡

ቀኝና ግራ 

አባታችን አባ ሕርያቆስ እንደተናገረ ለመለኮት ቀኝና ግራ የለውም፡፡ ቀኝና ግራ የተባለውም ምሳሊያዊ ነው፡፡ ጻድቃን በቀኝ የሚቆሙት ምሣሌያቸው ስለሆነ ነው፡፡ቀኝ ቅን ነው፡፡ ጻድቃንም ለምግባር ለሃይማኖት ቅን ናቸው፡፡ ቀኝ ፈጣን ነው፡፡ ጻድቃንም ለምግባር ለሃይማኖት ፈጣን ናቸው፡፡ ቀኝ ብርቱ ነው፡፡ ጻድቃንም ለምግባር ለሃይማኖት ብርቱ ናቸው፡፡ ኃጥአን በግራ የሚቆሙት ምሣሌያቸው ስለሆነ ነው፡፡ ግራ ጠማማ ነው፡፡ ኃጥአንም ሃይማኖት ምግባር ለመሥራት ጠማማ ናቸው፡፡ ግራ ዳተኛ ነው፡፡ ኃጥአንም ሃይማኖት ምግባር ለመስራት ዳተኞች ናቸውና፡፡ ቤተክርስቲያን ለምን አትሄዱም ሲሏቸው እዚህ ቦታ ደርሼ መጥቼ ደከመኝ ጸልዩ ሲባሉ ራሱ እግዚአብሔር ፍላጎቴን ያውቅ የለ ስገዱ ጹሙ ሲባሉ ምክንያት አያጣቸውምና፡፡ ግራ ሰነፍ ነው፡፡ ኃጥአንም በምግባር በሃይማኖት በኩል ሰነፎች ናቸው፡፡ ጠንከር ያለ ሥራ መሥራት አይችልም ኃጥአንም በምግባር በሃይማኖት በኩል ጠንከር ያለ ነገር ሲገጥማቸው ደከመን ሰለቸን ብለው ይተውታል፡፡ ለኃጢአት ግን አይደክሙም ሌሊት ጨለማን ተገን አድርገው ሲዘርፉ ሲዘሙቱ ይዉላሉና፡፡

በጎችና ፍየሎች

ጻድቃን በበግ ኃጥአን በፍየል ለምን ይመሰላሉ፡፡ ጻድቃን በበግ ኃጥአን በፍየል ለምን ተመሰሉ ቢባል የበጎች ተፈጥሮ ከጻድቃን ሥራ ጋር የፍየል ተፈጥሮ /ግብር/ ከኃጥአን ጋራ ስለሚመሳሰል ነው፡፡ በጎች በደጋ እንጂ በቆላ አይኖሩም፡፡ ተስማሚያቸው ደጋ ነው ጻድቃን በመከራ ሥጋ እንጂ በተድላ ደስታ ለመኖር ሲሉ ሃይማኖታቸውን ክደው በምግባር ብልሹነት አይገኙም፡፡ ፍየሎች በቆላ እንጂ በደጋ አይኖሩም፤ ኃጥአንም በተድላ ደስታ ለመኖር ሲሉ ሃይማኖታቸውን በወርቅ በብር ይለውጣሉና፡፡

በጎች እረኛቸው ባሰማራቸው ሥፍራ ጸንተው ይኖራሉ፡፡ ጻድቃንም እረኛቸው ክርስቶስ ባሰማራቸው በአንዲት ሃይማኖት ጸንተው ይኖራሉ፡፡ ፍየሎች እረኛቸው ባሰማራቸው ቦታ ጸንተው እንደማይኖሩ ኃጥአንም እንዲሁ በሃይማኖት ጸንተው መኖር አይቻላቸውምና፡፡ በጎች ጥቂት ሳር ካገኙ ተፋቅረው አብረው ይበላሉ ጻድቃንም ያለቻቸውን ተካፍለው ይኖራሉና፡፡ ፍየሎች ግን ሣር ቅጠሉ ሞልቶ ለሁላቸው ሲበቃ ሳለ ይጣላሉ፡፡ ኃጥአንም ሀብት ንብረት ተትረፍርፎላቸው ለወገናቸው አያካፍሉም፡፡ ለገንዘብ ብለው እርስ በእርሳቸው ይጣላሉ ዘለው የሌላውን ሀብት ንብረት ለማግኘት ሲሉ የማይገባ ሥራ ይሠራሉና፡፡

የበጎች ላታቸው የተከደነ ሐፍረተ ሥጋቸው የተሸፈነ ነው፡፡ የጻድቃንም ኃጢአታቸው በሰው ዘንድ የተጋለጠ አይደለም፡፡ ኃጢአት ቢሰሩ ሌላ ሰው ሳይሰናከልባቸው ንስሐ ይገባሉ፡፡ የፍየሎች ላታቸው የተሰቀለ ሐፍረተ ሥጋቸው የተጋለጠ ነው፡፡ የኃጢአተኞችም ሥራ በሰው ዘንድ የተጋለጠ ለሚሰሩት እኩይ ሥራ የማያፍሩ በየአደባባዩ ኃጢአትን የሚፈጽሙ ናቸውና፡፡ በጎች አቀርቅረው እንጂ አሻቅበው አያዩም ጻድቃንም ሁልጊዜ ዕለተ ሞታቸውን በማሰብ ወደ አፈር እንደሚመለሱ እያሰቡ በትህትና ሕይወታቸውን ይመራሉ፡፡ ሀብት’ ንብረት’ ዕውቀት እያላቸው ራሳቸውን ዝቅ ያደርጋሉ፡፡ ፍየሎች አሻቅበው ነው የሚያዩት አንገታቸውን ያንጠራራሉ ኃጥአንም ደካማ ሆነው ሳሉ ብርቱ ነን ይላሉ ባገኙበት ሀብት ዕውቀት ይመካሉ ትዕቢተኞች ናቸው፡፡ ትሕትና በእነርሱ ዘንድ የበታችነት ምልክት ነው፡፡

ከበጎች ውስጥ አንዲቱ ተኩላ ቢነጥቃት ሁለተኛ ወደዚያ ቦታ ተመልሰው አይመጡም፡፡ ጻድቃንም እኩይ ሞት ከእነርሱ አንዱን ከወሰደ ነገም የእነርሱ ተራ እንደሆነ ተረድተው ከኃጢአት ሥራቸው በንስሐ ይመለሳሉ ወደ እግዚአብሔር ይቀርባሉ፡፡ ፍየሎች ግን ከመካከላቸው ነብር አንዲቱን ቢወስድ ለጊዜው ደንብረው ይሄዳሉ፡፡ ኋላ ግን ተመልሰው እዚያው ቦታ ይመጣሉ ኃጥአንም ከመካከላቸው አንዱ ሳያስቡት በሞት ቢወሰድ ለጊዜው ደንግጠው ከኃጥአት ሥራቸው ይታቀባሉ በኋላ ግን የሞተው ሰው ከህሊናቸው ሲጠፋና የዓለም ሁኔታ ሲማርካቸው ወደ ኃጢአት ግብራቸው ይመለሳሉና፡፡

የፍርድ ቀን ጥያቄዎች

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መጨረሻው የፍርድ ቀን ሲናገር ‹‹ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል። እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና። ጻድቃንም መልሰው ይሉታል። ጌታ ሆይ፥ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን? ንጉሡም መልሶ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል። በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል። እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና። እነርሱ ደግሞ ይመልሱና። ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም? ይሉታል። ያን ጊዜ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም ብሎ ይመልስላቸዋል። እነዚያም ወደ ዘላለም ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።›› (ማቴ 25፡34-46) በማለት ሰው በመጨረሻው ቀን የሚጠየቀው እነዚህን ጥያቄዎች መሆኑን ተናግሯል፡፡ ይህም እምነት ያለ ምግባር ከንቱ መሆኑን ያስረዳናል፡፡

ከትንሣኤ በላ ያለው ሕይወት

ከትንሣኤ ሙታን በኋላ ስለሚኖረው ሕይወት ቅዱሳት መጻሕፍት ብዙ እውነታዎችን አስፍረዋል፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሁላችን አናንቀላፋም ነገር ግን የኋለኛው መለከት ሲነፋ ሁላችን በድንገት በቅጽበት ዓይን እንለወጣለን፤ መለከት ይነፋልና ሙታንም የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ እኛም እንለወጣለን›› (1ኛ ቆሮ 15፡ 52) በማለት ሙታን የማይበሰበሱ ሆነው እንደሚነሱ በመልእክቱ ጽፎታል፡፡ ጌታችንም ትንሣኤ ሙታንን የማያምኑ ሰዱቃውያን ለጠየቁት ጥያቄ ‹‹ያን ዓለምና ከሙታን ትንሣኤ ሊያገኙ የሚገባቸው እነዚያ ግን አያገቡም አይጋቡምም፥ እንደ መላእክት ናቸውና፥ ሊሞቱም ወደ ፊት አይቻላቸውም፥ የትንሣኤም ልጆች ስለ ሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው።›› (ሉቃ 20፡35) በማለት ከትንሣኤ በኋላ ማግባት መጋባት እንደሌለና ሰዎች እንደመላእክት ሆነው እንደሚኖሩ ነግሯቸዋል፡፡

ሙታን የማይነሱ ከሆነ…

ትንሣኤ ሙታን ከሌለ (ሙታን የማይነሱ ከሆነ) እምነታችን ሁሉ ከንቱ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገር ‹‹ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤ክርስቶስን አስነሥቶታል ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለ መሰከርን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ። እንግዲያስ በክርስቶስ ያንቀላፉት ደግሞ ጠፍተዋላ። በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን›› (1ኛ ቆሮ 15፡ 12-19) በማለት አረጋግጦታል፡፡ በተጨማሪም ‹‹እንዲያማ ካልሆነ፥ ስለ ሙታን የሚጠመቁ ምን ያደርጋሉ? ሙታንስ ከቶ የማይነሡ ከሆነ፥ ስለ እነርሱ የሚጠመቁ ስለ ምንድር ነው? እኛስ ዘወትር በሚያስፈራ ኑሮ የምንኖር ስለ ምንድር ነው?…እንደ ሰው በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ከታገልሁ፥ ሙታንስ የማይነሡ ከሆነ፥ ምን ይጠቅመኛል? ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ›› (1ኛ ቆሮ 15፡ 29-34) በማለት ትንሣኤ ሙታን ከሌለ ድካማችን ሁሉ ከንቱ መሆኑን አብራርቷል፡፡

ሳይሞቱ በብሔረ ሕያዋን ያሉትስ?

ነቢዩ ሚልክያስ ‹‹እነሆ፥ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ። መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል››(ሚል 4፡5-6) ብሎ እንደተነበየው፤ ጌታችንም በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹ኢየሱስም መልሶ። ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናል፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ኤልያስ ከዚህ በፊት መጣ፤ የወደዱትንም ሁሉ አደረጉበት እንጂ አላወቁትም፤ እንዲሁም ደግሞ የሰው ልጅ ከእነርሱ መከራ ይቀበል ዘንድ አለው አላቸው››(ማቴ 17፡11-13) ብሎ እንዳረጋገጠው ከሰው ልጆች ሞትን የማይቀምስ አይኖርም፡፡ በዚያን ዘመን በምድር ላይ ያሉትም ቢሆኑ፣ በብሔረ ሕያዋንም ያሉት ቢሆኑ እንዲሁ ሞትን ይቀምሳሉ፤ ሳይሞቱ ትንሣኤ ሙታን የለምና፡፡

መሐሪ የሆነው አምላክ ኃጥአንን በዘላለም ሞት ይቀጣልን?

ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያስረዱት እግዚአብሔር ኃጥአንን በዘላለም ሞት ይቀጣልን፡፡ እግዚአብሔር ፈታሂ ነው፡፡ ክፉዎች ካልተቀጡ ግን ፍትህ እንዴት ይኖራል? እግዚአበሔር የኖኅ ዘመን ሰዎችን በኃጢአታቸው ምክንያት የቀጣቸው መሐሪ ስላልሆነ ሳይሆን ፈታሂ ስለሆነ ነው (ዘፍ 7፡1)፡፡ በአዳም ላይ የሞት ቅጣትን የፈረደበትም እንዲሁ ፈታሂ ስለሆነ ነው፡፡ መሐሪ ስለሆነ ደግሞ ቤዛ ሆኖ አዳነው፡፡ ክፉዎች ካልተቀጡ እግዚአብሔር እንዴት ፈታሂ ይባላል? ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በገላቲያ መልእክቱ ‹‹አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል። ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት›› (ገላ 6፡7) እንዳለው በመጨረሻው ዘመን ሁሉም የዘራውን ያጭዳል:: እግዚአብሔር መሐሪም ፈታሂም ስለሆነ ጻድቃን የዘላለም ሕይወት ኃጥአን ደግሞ እንደሥራቸው የዘላለም ሞትን ያገኛሉ፡፡ ስለዚህ ‹‹የዘላለም ቅጣት ከእግዚአብሔር ባሕርይ ጋር አይሄድም›› የሚለው አስተሳሰብ የዘላለም ቅጣትን የሚያስቀር አይደለም፡፡

ፍትሐትና ተዝካር

ሰው በሥጋው ለጊዜው ቢሞትም በነፍስ ግን ሕያው ነው፡፡ ጸሎተ ፍትሐት በአፀደ ሥጋና በአፀደ ነፍስ በሚኖሩ ክርስቲያኖች መካከል ያለውን የዕምነት አንድነት ይገልፃል፡፡ ነብዩ ሄኖክ ‹‹ህያዋን ለሙታን ሙታን ለህያዋን ይጸልያሉ›› (12 ÷34) በማለት እንደተናገረው በአፀደ ነፍስ የሚገኙ ሙታን በአፀደ ስጋ ለሚገኙ እንደሚፀልዩ ሁሉ በአፀደ ስጋ ያሉትም በሞት ለተለዩት ይፀልዩላቸዋል፡፡ ይህም የክርስቲያኖችን አንድነት ይገልጣል፡፡ ጸሎተ ፍትሐትም ሆነ ተዝካር (መታሰቢያ) ጸሎት እንጂ ድግስ አይደሉም፡፡ አንዳንዶች ሟች ፍርዱን ከተቀበለ በኋላ ጸሎት ምን ያደርግለታል እንደሚሉት አይደለም፡፡ ሥርዓተ ፍትሐትም ጸሎት እደመሆኑ መጠን ኃጥያት ማስተሰረያ ይሆን ዘንድ ይቀርባል፡፡ ‹‹ኃጥአት የለብንም ብንል እራሳችንን እናታልላለን›› (ዮሐ 1፡8) በማለት ወንጌላዊው እንዳስተማረው ሐጥያት የለብኝም ፍትሐት አያስፈልገኝም ማለት የሚችል ሰው የለም፡፡

 ተዝካር የሚለው ቃል ዘከረ አሰበ ከሚለው የግዕዝ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም መታሰቢያ ማለት ነው። መታሰቢያውም የሚደረገው ለሙታን ሲሆን የሚቀርበውም በጸሎት፣ በመሥዋእት፣ በመብራትና በማዕጠንት ነው። ስለተዝካር ጥበበኛው ሲራክ ‹‹ልጄ ለሞተ ሰው አልቅስለት እዘንለት፤ እደአገሩ ተዝካር አውጣለት ። የሞተ ሰውስ ዓረፈ ነገር ግን ነፍሱ ታርፍ ዘንድ ተዝካር አውጣለት ከዚህ በሁላ ለቅሶህን ተው›› (ሲራክ 38፡16) በማለት በሃይማኖት ኖረው ለሞቱ ወገኖች ተዝካር ማውጣት ተገቢ መሆኑን ያመለክታል። ጠቢቡ ሰሎሞንም ‹‹የጻድቅ መታሰቢያ (ተዝካር) ለበረከት ነው›› በማለት ተናግሯል (ምሳ 10፡7)፡፡ ይህም በእግዚአብሔር ቤት ኖረው ላረፉ ወገኖች መታሰቢያን ማድረግ ለሚያደርገው ሰው በረከት ነው።

ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን ከሌሎች አምስቱ አዕማደ ምስጢራት በመጨረሻ የሚገኝ ተስፋ ነው፡፡ ሌሎቹ አምነን የምንጠብቃቸው ወይም አምነን የምንፈጽማቸው ሲሆኑ ምስጢረ ትንሣኤ ሙታን ግን አምነን ተስፋ የምናደርገው ነው፡፡ በመጨረሻው ዘመን ክርስቶስ ዳግመኛ ይመጣል፤ ሙታንም እንደ ዓይን ጥቅሻ ፈጥነው ይነሳሉ፤ ለሁሉም እንደየሥራው ዋጋው ይከፈለዋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ ፍጻሜ ላይ ‹‹እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ›› (ራዕ 22፡12) ብሎ እንደጻፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይመጣል፤ ለሁሉም እንደሥራው ዋጋውን ይከፍለዋል፡፡ ስለዚህ ሃይማኖታቸው የቀና ቀደምት አበው ቅዱሳን በሃይማኖት ድንጋጌ ‹‹ዳግመኛም የሞቱ የጻድቃንና የኃጥአን ትንሣኤ እንዳለ እናምናለን᎓᎓ ሁሉ እንደ ሥራው ፍዳውን የሚቀበልበት የፍርድ ቀንም እንዳለ እናምናለን᎓᎓›› በማለት እንዳስተማሩን እኛም ምስጢረ ሥላሴንና ምስጢረ ሥጋዌን አምነንና ጠብቀን፣ ምስጢረ ጥምቀትንና ምስጢረ ቁርባንን አምነንና ፈጽመን፣ ምስጢረ ትንሣኤ ሙታንን ደግሞ አምነንና ተስፋ አድርገን እምነታችንን በአምስቱ አዕማደ ምስጢራት ላይ አጽንተን ዘላለማዊ ሕይወትን እንወርስ ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የቅድስተ ቅዱሳን የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡

ምስጢረ ቁርባን፡ የቤተክርስቲያን ምስጢራት አክሊል (ክፍል 2)

ምስጢረ ቁርባን በክርስቶስ ቤዛነት ያመንን ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ የምንሆንበት፣ ስርየተ ኃጢአትን የምናገኝበት፣ በመዳን ጉዞ ውስጥ ሰይጣንን ድል የምናደርግበት፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑ የሚታወቅበት፣ በእምነት ካልሆነ በቀር በፍጥረታዊ አዕምሮ የማይታወቅ ሰማያዊ ጸጋን የሚሰጥ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ የበጎ ነገር ጠላት ዲያብሎስ ምዕመናን በቀናች ሃይማኖት ጸንተው ከዚህ ጸጋ እንዳይካፈሉ በመናፍቃን እያደረ የማሳሳቻ ትምህርቶችን ያመጣል፡፡ ስለሆነም ምስጢረ ቁርባን እጅግ ብዙ ጥያቄዎች የሚነሱበት የቤተክርስቲያን ምስጢር ነው፡፡ ሰዎች በዚህ ምስጢር ላይ ጥያቄዎችን የሚያነሱት ስለ ምስጢሩ ካላቸው ግነዛቤ ማነስና ምስጢሩም ከሰው አዕምሮ በላይ ከመሆኑ የተነሳ ነው፡፡ በተጨማሪም ዘመኑ የወለዳቸው መናፍቃንም ራሳቸው ክደው ሌላውንም ለማስካድ በተለያየ መንገድ የሚረጩት የሐሰት ትምህርት በምዕመናን አዕምሮ ውስጥ ብዙ ጥያቄዎች እንዲፈጠሩ ያደርጋል፡፡ ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት በአስተምህሮ የጡመራ መድረክ በዚህ ርዕስ ክፍል አንድ ጦማር በምስጢረ ቁርባን ዙሪያ የሚነሱ 12 ዋና ዋና ጥያቄዎች ተዳስሰዋል፡፡ በዚህ በሁለተኛውና የመጨረሻው ክፍል ደግሞ ሌሎች በምስጢረ ቁርባን ላይ የሚነሱ 13 ተጨማሪ ጥያቄዎች ይዳሰሳሉ፡፡

13. ቅዱስ ቁርባንን በምንቀበልበት ጊዜ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?

ጌታችን በቃሉ እንዳስተማረን ቅዱስ ቁርባን ደካማ ስጋችን በእግዚአብሔር ፀጋ ከብሮ የሚኖርበት ድንቅ ምሥጢር ነው፡፡ በኃጢአት የደከመ ሰውነታችን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለመሆን፣ የክርስቶስን ሥጋና ደም ለመቀበል በንስሐ መታጠብ አለበት፡፡ ንስሐውም እንደ ሮማዊው መቶ አለቃ ፍፁም ራስን ዝቅ በማድረግ፣ በትህትና የሚፈጸም መሆን አለበት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቅፍርናፎም በገባ ጊዜ አንድ መቶ አለቃ ቀርቦ ልጁን እንዲያድንለት ለመነው፤ ጌታችን ወደ መቶ አለቃው ቤት ሄዶ ልጁን እንደሚፈውስለት በነገረው ሰዓት ትሁት፣ ተነሣሂ ልቦና ነበረው መቶ አለቃ “አቤቱ! አንተ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፡፡” (ማቴ. 8፡8) በማለቱ ጌታችን አመስግኖታል፡፡ እኛም የከበረ የክርስቶስ አካል ቤት በተባለ ሰውነታችን በቅዱስ ቁርባን አማካኝነት እንደሚገባ ሲነገረን እንደ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን በትዕቢት ሳይሆን እንደ መቶ አለቃው በትህትና፣ ኃጢአታችንን በመናዘዝ “አቤቱ! አንተ በእኔ በኃጢአት በከረሰ ሰውነት ልታድር አይገባህም፣ እንደ ቸርነትን አንጻኝ፣ ቀድሰኝ” ልንል ይገባል፡፡ ለዚህም እንዲረዳን በመንፈስ ቅዱስ የተቃኙ አባቶቻችን ወደ ቅዱስ ቁርባን ለመቅረብ የሚጸለዩ ልቦናን ከምድራዊ ሀሳብ ከፍ የሚያደርጉ፣ ትምህርተ ሃይማኖትን የጠነቀቁ ጸሎቶችን አዘጋጅተውልናል፡፡

ስለሆነም የሚቆርቡ ምዕመናን ከመቁረባቸው በፊት የሚጸለየውን ጸሎት ይጸልዩ ዘንድ ይገባል፡፡ ቅዱስ ቁርባንን ካህናት፣ ሕጻናት፣ ደናግል፣ ሕዝባዊያንና ምዕመናን ቤተክርስቲያን የሠራችላቸውን ቅደም ተከተል ጠብቀው ይቆርባሉ፡፡ ሥጋውን ካህኑ በእጁ ሲያቀብል ደሙን ንፍቅ ካህኑ በዕርፈ መስቀል ለካህናት እንዲሁም ዲያቆኑ ለምዕመናን በዕርፈ መስቀል ያቀብላል፡፡ ንፍቅ ካህን ሥጋውን አያቀብልም፡፡ ንፍቅ ዲያቆንም ደሙን ለማቀበል አይችልም፡፡  የአቆራረብ ቅደም ተከተላቸውም ቅድሚያ በመቅደስ ውስጥ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት፣ ቆሞሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት ሲቆርቡ በቅድስት ደግሞ የሚጠቡ ሕጻናት፣ ወንድ ልጆች፣ ሴቶች ልጆች፣ አዋቂ ወንዶችና አዋቂ ሴቶች ይቆርባሉ፡፡ በመጨረሻም ማየ መቁርር (የቅዳሴ ጠበል) ቅዱስ ቁርባንን ለተቀበሉ ወዲያውኑ ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚያም ከቁርባን በኋላ የሚጸለየውን ጸሎት ይጸልያሉ፡፡

14. ቅዱስ ቁርባን ከተቀበልን በኋላ ምን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል?

ቅድስት ቤተክርስቲያን የሰርግ ቤት ትባላለች፡፡ በሰርግ ቤት የሙሽራና የሙሽሪት ተዋሕዶ (አንድነት) እንደሚፈጸም በቅድስት ቤተክርስቲያንም የሙሽራው የክርስቶስና የሙሽራይቱ የቤተክርስቲያን ተዋሕዶ (አንድነት) ይነገርባታል፣ ይፈጸምባታል፡፡ (ኤፌ. 5፡21-33) የሰው ልጅ በልማዱ ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚሆንበት ጊዜ ራሱን ባማረ ልብስ ያስውባል (ታስውባለች)፡፡ በተለይም ደግሞ ወደ ሰርግ ቤት የተጠራ እንደሆነ ልዩና ያማረ ሰርግ ልብስ መልበስ ይገባል፡፡ በወንጌል ትርጓሜ የሰርግ ቤት የተባለች ቅድስት ቤተክርስቲያን ነች፡፡ የሰርጉ ማዕድም የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ፣ ክቡር ደም ነው፡፡ ጌታችን በወንጌል እንዳስተማረ ሙሽራው ባለበት የሰርግ ቤት የሰርግ ልብስ ሳይለብሱ በአልባሌ አለባበስ መገኘት ያስወቅሳል፣ ያስቀጣል፡፡ (ማቴ. 22፡11-13)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲህ የክርስቶስን አካል ወስዳችሁ የአመንዝራ አካል ታደርጉታላችሁን? አይገባም፡፡” (1ኛ ቆሮ. 6፡15) እንዳለ የክርስቲያን ሰውነት በክርስቶስ ሥጋና ደም የከበረ ነውና ሁልጊዜም በንጽሕና፣ ከኃጢአት በመራቅ መጠበቅ አለበት፡፡ በተለይም በቅዱስ ቁርባን ከክርስቶስ ጋር በምንዋሐድባቸው ዕለታት ከሌሎች ጊዜያት በበለጠ ጥንቃቄ ራሳችንን ከኃጢአት ልንጠብቅ ይገባል፡፡ ይህም ባሏን የምትጠብቅ ንጽሕት ሙሽራን ይመስላል፡፡ አንዲት ሴት ምንጊዜም ራሷን በንጽሕና መጠበቅ እንዳለባት ቢታወቅም ባሏን ለተዋሕዶ በምትጠብቅበት ዕለት ግን በተለየ ሁኔታ ራሷን ትጠብቃለች፡፡ እኛም ራሳችንን የክርስቶስ ሙሽራ አድርገን በንስሐ ተጸጽተን ሥጋውን ከበላን ደሙን ከጠጣን በኋላ ልናደርጋቸው የሚገቡንን ጥንቃቄዎች የክርስቶስ አካል ቅድስት ቤተክርስቲያን ደንግጋልናለች፡፡

በፍርድ በሙግት ጠብና ክርክር አይታጣምና ከዚያ ለመራቅ ከቆረቡ በኋላ በዚያው ዕለት ወደ ፍርድ ቤት መሄድና መሟገት ክልክል ነው፡፡ ከመንፈሳዊ ሀሳብ ይልቅ ለስጋዊ ደስታ የተመቸ ነውና በዚሁ ዕለት ለባለትዳሮች ሩካቤ፣ አብዝቶ መብላትና መጠጣት አየይገበባመም፡፡ ጥፍር መቁረጥ፣ ጸጉር መላጨት፣ በውኃ መታጠብና ከልብስ መራቆት ክልክል ነው፡፡ ግብፃውያን ክርስቲያኖች በቆረቡበት ዕለት በባዶ እግር አይሄዱም፡፡ እንቅፋት እንዳያገኛቸውና እግራቸው እንዳይደማ ነው፡፡ እንዲሁም ከቁርባን በኋላ የጸሎት መጻሕፍትን ያነባሉ፡፡ ተረፈ ዕለቱንም ከሰዎች ጋር ባለመገናኘት፣ በሰላምና ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ያሳልፋሉ፡፡

ከቆረቡ በኋላ በተለይም ከጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ እንቅፋት (መሰናክል) እክል ቢያጋጥመን ለምሳሌ. ነስር፣ እንቅፋት፣ ትውከት፣ ወደ አፍ የሚገባ ትንኝ፣ ዝንብ… ቢያጋጥመን፤ ንስሃ ልንገባና ያጋጠሙንን እክሎች በሙሉ ለካህን (ለንስሃ አባታችን) ልንናገር ይገባል፡፡የተሰጠንን ንስሃም ሳንፈጽም ዳግም መቁረብ አይፈቀድም (አይገባም)፡፡ ሩቅ መንገድ መሔድ፣ መስገድ፣ አይገባም፡፡ ይህም ምስጢሩ በሥጋ ወደሙ ድካም የለበትምና፡፡ አንድም በመንግስተ ሰማይ ከገቡ በኋላ ድካም የለምና አንድም ድኀነት በሥጋና በደሙ ሳይሆን በትሩፋት ነው እንዳያሰኝ ነው፡፡

15. ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስለምስጢረ ቁርባን የምታምነው እምነት ከሌሎች የሚለየው እንዴት ነው?

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስለምስጢረ ቁርባን የምታምነው እምነት አማናዊ ለውጥ (Definitive change) ሲሆን ይህም ‹ፍጹም በሆነ አምላካዊ ምስጢር ኅብስቱ ተለውጦ አማናዊ የክርስቶስ ሥጋ፣ ጽዋውም ተለውጦ አማናዊ የክርስቶስ ደም ይሆናል›› የሚል ነው፡፡ ይህም የሰው አእምሮ ተመራምሮ የማይደርስበት አምላካዊ ምስጢር ነው፡፡ ከተለወጠም በኋላ ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሐደው ሥጋና ደም ይሆናል፡፡ ይህንንም ተቀብለን ከክርስቶስ ጋር አንድ አካል እንሆናለን፡፡ የካቶሊክ እምነት ደግሞ ‹‹ተፈጥሮአዊ በሆነ ለውጥ (Transubstantiation) የኅብስቱና የወይኑ ተፈጥሮ ወደ ሥጋና ደም ይቀየራል›› የሚል ነው፡፡ በእነርሱ እምነት ለውጡ በውጫዊ ገጽታውና በውስጣዊ ይዘቱ ላይ አይታይም፡፡ ተቀይሮም ሙሉ ክርስቶስን (ሥጋ፣ ደም፣ ነፍስና መለኮት ያለው) ይሆናል ብለው ያምናሉ፡፡ በሌላ በኩል ሉተራንስ ብሎ ራሱን የሚጠራው ዋናው የፕሮቴስታንት ክንፍ ስለ ቁርባን የሚያራምደው እምነት ‹‹ምስጢራዊ ኅብረት (Sacramental Union)›› ይባላል፡፡ ይህም የክርስቶስ ሥጋና ደም ከኅብስቱና ከወይኑ ጋር አብሮ በኅብረት ይገኛል የሚል ሲሆን የሚቀበሉትም ሥጋውና ደሙን እንዲሁም ኅብስቱንና ወይኑን አብረው ይቀበላሉ ብለው ያምናሉ፡፡

በአንጻሩ ተሃድሶአውያኑ ደግሞ ‹‹በመንፈስ መገኘት (Spiritual Presence)›› የሚል አስተምህሮ አላቸው፡፡ ይህም በቁርባኑ ላይ ክርስቶስ በአካል አይገኝበትም፤ በመንፈስ እንጂ የሚል ነው፡፡ ስለዚህም በኅብስቱና በወይኑም የሚካሄድ የተፈጥሮ/ይዘት ለውጥ የለም ብለው የሚያምኑ ሲሆን ከቁርባኑ ጋር ያለው መንፈስም የሚቀበሉትን ክርስቲያኖችን ከክርስቶስ ጋር ያገናኛቸዋል ይላሉ፡፡ ሌላው በቁርባን ላይ ያለው እምነት የተለያዩ አዳዲስ የእምነት ድርጅቶች የሚያራምዱት ‹‹መታሰቢያነት (Memorialism)›› የሚለው ነው፡፡ ይህም ኅብስቱና ወይኑ የክርስቶስ ሥጋና ደም መታሰቢያ ምልክቶች ብቻ ናቸው የሚል ትምህርት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ኅብስቱንና ወይኑን የሚቀበል የክርስቶስን መታሰቢያ ያደርጋል የሚሉ ሲሆን ክርስቶስ በክርስቲያኖቹ ኅሊና እንጂ በኅብስቱና በወይኑ አይገኝም ብለውም ያስተምራሉ፡፡ በእነርሱ እምነት የቁርባን ሥርዓቱ ምልክትና መታሰቢያ ብቻ ነው፡፡ በመጨረሻም ቁርባን የሚባለው የእግዚአብሔር ቃል እንጂ የሚበላና የሚጠጣ አይደለም (Real Absence) የሚል አስተሳሰብ ያላቸው ወገኖችም አሉ፡፡ እኛ ግን አምላካችን ክርስቶስ ያስተማረውንና የሠራልንን የምስጢረ ቁርባን ሥርዓት መሠረት አድርገን በአማናዊው የክርስቶስ ሥጋና ደም (ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሐደው) እናምናለን፡፡

16. ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ለምን ለየብቻ ይዘጋጃል?

ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ለየብቻ እንጂ ተቀላቅሎ አይዘጋጅም፡፡ ይህም የጌታችንን የምስጢረ ቁርባን ትምህርትና የሠራውን ሥርዓት መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ጌታችን “ሥጋዬን የሚበላ” ሲል ቅዱስ ሥጋውን እንድንበላ፣ ከዚያም “ደሜን የሚጠጣ” ሲል ደሙን እንድንጠጣ መናገሩ ነው፡፡ እንዲሁም “ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነው” ብሎ ለይቶ የተናገረው ተለያይቶ እንዲዘጋጅ ነው፡፡ ሥርዓተ ቁርባንን በሠራባት በጸሎተ ሐሙስም በመጀመሪያ ኅብስቱን አንስቶ ባረከና ቆርሶ ሰጣቸው፤ ከዚም ጽዋውን አንስቶ አመስግኖ ስጣቸው፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ለየብቻ ተዘጋጅቶ በመጀመሪያ ቅዱስ ሥጋውን ቀጥሎ ክቡር ደሙን እንቀበላለን፡፡

17.  ሳይገባው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን የሚቀበል ቅጣቱ ምንድን ነው?

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው ሳይገባው (ሳይዘጋጅ) የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም የሚቀበል ዕዳ አለበት፡፡  ካህኑ እንዳወጀው ተጠያቂው ራሱ በድፍረት የተቀበለው ሰው ነው፡፡ የካህኑ አዋጅ የሚጠቅመው “ባለማወቅ ነው የተቀበልኩት” እንዳንልም ነው፡፡ እዚያው ካህኑ ተናግሮታልና፡፡ ይህንን የካህኑን ቃል ተዳፍሮ የሚቀበል ግን ዲያቆኑ እንደተናገረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያሳዝናል፡፡ “ስለበረከት ፈንታ መርገምን ስለኃጢአት ሥርየት ፈንታ ገሃነመ እሳትን ይቀበላል” የድፍረት ኃጢአት ከሁሉ የከፋ ነውና፡፡

18. ጌታችን ሥጋውና ክቡር ደሙን “ለመታሰቢያ አድርጉት” ያለው ምን ማለት ነው?

የድኅነትን ነገር መቀለጃ የሚያደርጉ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ምስጢር ከእምነት በተለየ ደካማ ፍጥረታዊ አዕምሮ ለመረዳት የሚሞክሩ የወንጌል ጠላቶች በወንጌል ያልተጻፈውን አንብበው፣ የተጻፈውን አዛብተው እውነተኛ የክርስቶስ ሥጋና ደም “መታሰቢያ ብቻ” ነው በማለት የማይገባቸውን ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ጌታችን ኅብስቱን ባርኮ ሲሰጣቸው ‹‹ይህ ሥጋዬ›› ነው በማለት ነው እንጂ መታሰቢያ ነው በማለት አይደለም፡፡ ጽዋውንም አንስቶ አመስግኖ ሲሰጣቸው ‹‹ይህ ደሜ ነው›› አላቸው እንጂ መታሰቢያ ነው አላለም፡፡ ሐዋርያት የእምነታችው ጽናት የሚደነቀው ኅብስቱን እያዩት ‹‹ሥጋዬ ነው›› ወይኑንም እያዩት ‹‹ደሜ ነው›› ቢላቸው የሚሳነው ነገር እንደሌለና በግብር አምላካዊ ‹‹አማናዊ ሥጋና ደም›› እንደሚሆን ያለጥርጥር መቀበላቸው ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ለመታሰቢያዬ አድርጉት›› ያለው ዘወትር ምዕመናን ለምስጋና ለመስዋዕት (ሊቆርቡ) በተሰበሰቡ ጊዜ ሞቱን ግርፋቱን ትንሣኤውንና ዕርገቱን እንዲያስታውሱ ለማሳሰብ ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይህንን የሐዋርያትን ትምህርት ሳታፋልስ፣ ሳትጨምርና ሳትቀንስ በቅዳሴ ጊዜ ‹‹ንዜኑ ሞተከ እግዚኦ ወትንሣኤከ ቅድስት/አቤቱ ሞትህንና ቅድስት ትንሣኤህን እንናገራለን›› እያለች ማንሳቷ ለዚህ ጽኑ ምስክር ነው፡፡ ጌታችን ለመታሰቢያዬ አድርጉት ሲል ‹‹ቅዱስ ቁርባንን በተቀበላችሁ ጊዜ የተደረገላችሁን ሰማያዊ ፍቅር አስቡ›› ማለቱ ነው እንጂ ‹‹ቁርባን መታሰቢያ ነው›› ማለቱ አይደለም፡፡ መታሰቢያዬ አድርጉት ማለትና መታሰቢያ ነው ማለት የተለያየ ነው፡፡ ደካማ አዕምሮ ባላቸው ሰዎች አነባበብ ከተወሰደ “መታሰቢያ” የሚል ስያሜ ያላቸው ሰዎች “እውነተኛ አይደሉም” ይባል ይሆን? መታሰቢያ ብቻ ቢሆን ኖሮ ሳይገባው የተቀበለ ሁሉ ዕዳ አለበት አይባልም ነበር፡፡ ብዙዎች ታመዋል፣ አንቀላፍተዋል የተባለው መታሰቢያ የሆነውን ሳይገባቸው ስለተቀበሉ ይሆንን? ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ለመታሰቢያዬ አድርጉት›› የሚለውን ሲያብራራ ‹‹ይህንን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፣ ይህንንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስሚኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና›› በማለት ገልጾታል፡፡ 1ኛ ቆሮ 11፡25-26

19. ካህናት አባቶች ለምን ሥጋውና ክቡር ደሙን ይሸፍኑታል?

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት የጌታችን ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ይሸፈናል፡፡ ይህም ቅዱስ ዮሐንስ የጌታችንን ስዕል ለጢባርዮስ ቄሳር ሲሥል በመጀመሪያ ጌታችንን ልክ እንደተሰቀለ አድርጎ ራቁቱን ነበር የሳለው፡፡ ዮሐንስ የሳለው የጌታችን ሥዕልም አፍ አውጥቶ “በመጀመሪያ አይሁድ በኢየሩሳሌም ራቁቴን ሰቀሉኝ፣ አሁን ደግሞ አንተ ድጋሚ በሮም ራቁቴን ትሰቅለኝን?” ብሎ ተናገረው፡፡ ዮሐንስም እጅግ ደንግጦ ‹‹እንዴት አድርጌ ልሳልህ?›› ብሎ የሳለውን ሥዕል ቢጠይቀው ሥዕሉም “ከለሜዳ አልብሰህ ሳለኝ” አለው፡፡ ዮሐንስም እንዳለው ከለሜዳ አልብሶ ሳለው፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ በከለሜዳ ምሳሌ ይሸፈናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ የፈጣሪያቸውን እርቃን ላለማሳየት ፀሐይ ጨልማ ጨረቃም ደም ለብሳ ነበር፡፡ ይህንንም አብነት በማድረግ ካህናት ሥጋና ደሙን ይሸፍኑታል፡፡

20. ስለምን ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን ደጋግመን እንድንቀበል አስፈለገ? ስንት ጊዜስ እንቁረብ?

ምስጢረ ቁርባን የሚደገም ምስጢር ስለሆነ አንድ ክርስቲያን በሕይወቱ ይህን ያህል ጊዜ ይቁረብ ባይባልም በየጊዜው ግን ንስሐ እየገባ ከመምህረ ንስሐው ጋርም እየተማከረ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሊቀበል ይገባዋል፡፡ ሁሉም ክርስቲያን ሲጠመቅ ቅዱስ ቁርባንን ቢቀበልም ከተጠመቀ በኋላ ለሚሠራው ኃጢአት ማስተስረያ ንስሐ ገብቶ ቅዱስ ቁርባንን መቀበል ያስፈልገዋል፡፡ ባለትዳሮችም በተክሊል ሥርዓታቸው ወቅት ቅዱስ ቁርባንን ቢቀበሉም በትዳር ሕይወታቸውም በየወቅቱ ከመምህረ ንስሐቸው ጋር እየተመካከሩ ንስሐ እየገቡ ቅዱስ ቁርባንን ይቀበላሉ፡፡ ሰው በንስሐ ታጥቦ ቅዱስ ቁርባንን ከተቀበለም በኋላ መልሶ ኃጢአትን ይሠራልና ምስጢረ ቁርባንን ደጋግሞ ይፈጽማል፡፡ ይህንን ያህል ጊዜ ባይባልም በዓመት ውስጥ ክርስቲያኖች ቢያንስ በታላላቅ በዓላት (ልደት፣ ጥምቀት፣ ትንሣኤ…..) መቁረብ ይኖርባቸዋል፡፡

21. ሐዋርያት የቆረቡት ከምግብ በኋላ ምሽት ላይ ሆኖ ሳለ ለምን እኛ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል እንጾማለን?

የዚህ ጥያቄ መንፈስ “ከሐዋርያት ጋር ፉክክር” ያለ ያስመስላል፡፡ በመሠረቱ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንደሚያስተምሩት ‹‹የጸሎተ ሐሙስ ዕለት አስቀድመው የፋሲካውን በግ ከበሉ በኋላ በግብር አምላካዊ አስቀድመው የበሉትን አጥፍቶ ለበረከት ካመጡለት ከኅብስቱና ከወይኑ ከፍሎ “ይህ ሥጋዬ ነው፣ ይህ ደሜ ነው” ብሎ ለውጦ ትኩስ ሥጋ ትኩስ ደም አድረጎ አቁርቧቸዋል›› በማለት አመስጥረው ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሐደው አድርጎ እንደሰጠን አስተምረውናል፡፡ በወንጌል እንደተጻፈ ቅዱስ ዮሴፍ ዘአርማትያስ ጌታችን እንዲቀበርበት የመረጠው መቃብር “በውስጡ ሰው ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበር፡፡” (ዮሐ. 19፡41)  እኛ ደግሞ ስንቆርብ የምንቀበለው ዮሴፍና ኒቆዲሞስ እንደገነዙት ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሐደውን የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም እንደሆነ ቅድስት ቤተክርስቲያን ታስተምራለች፡፡ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በአዲስ መቃብር ጌታችንን እንደቀበሩት ከቅዱስ ቁርባን የሚቀበሉ ምዕመናንንም አፋቸውን ምሬት እስኪሰማቸው (ሆዳቸው ባዶ እስኪሆን) ለ18 ሰዓታት በመፆም እንዲቆርቡ ቅዱሳን አባቶቻችን ሥርዓትን ደንግገውልናል፡፡

22. መስዋዕት የሚባለው ራሱን ቤዛ አድርጎ የተሰቀለው መድኃኔዓለም ወይስ ቅዱስ ቁርባን?

የዚህ ዓይነት ጥያቄ የሚመነጨው በኢየሱስ ክርስቶስና በቅዱስ ቁርባን መካከል ያለውን ግንኙነት ካለመረዳት ነው፡፡ ሥጋ ወደሙን ከኢየሱስ ክርስቶስ ለይቶ ማየት ደግሞ ምስጢረ ተዋሕዶን ያለመረዳት ነው፡፡ በመሠረቱ በሥጋ ወደሙና በጌታችን መካከል ስላለው ግንኙነት ያስተማረን ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እንዲህ ሲል ‹‹እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፡፡ ጽዋውንም አንስቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፡- ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈሰ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፡፡›› ማቴ 26፡ 26 ታዲያ ራሱ ጌታችን የነገረንን ትተን የሰዎችን ፍልስፍናና ተረት እንቀበልን? እኛስ የምንቀበለው ቅዱስ ቁርባን ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ሆኖ የተገለጠ የመድኃኔዓለም የኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊ መሥዋዕት መሆኑን በፍጹም ሃይማኖት እንቀበላን፡፡ ይህ ግን የምንመገበው የተሰዋው አንድ ጊዜ ነው፡፡ አሁንም የምንሳተፈው ከዚያው አንድ ጊዜ በርሱ በራሱ ከቀረበው ሆኖ አምነው በመቅረብ ግን ዘወትር ለሚመገቡትም የዘላለም ሕይወትን የሚያስገኝ ነው፡፡

23. ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰው የነሳውን ሥጋ እንዴት ‹‹እንዴት የአምላክ ሥጋ የአምላክ ደም›› እንለዋለን?

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ነፍስን የነሣው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ረቂቅ የሆነው መለኮት የሰውን ሥጋና ነፍስ ፍጹም ስለተዋሐደና በተዋሕዶ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ስለሆነ የሥጋ ገንዘብ የመለኮት ሆነ፤ የመለኮትም ገንዘብ ለሥጋ ሆነ፡፡ ቃል ሥጋ ሆኖአልና፡፡  ስለዚህ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነፍስ ስለተለየው እንደሚፈርስ፣ እንደሚበሰብስ የፍጡር አካል አይደለምና፡፡ ‹‹የአምላክ ሥጋ የአምላክ ደም›› እንለዋለን፡፡

24. “ኢየሱስ ይፈርዳል፣ ሥጋውና ደሙ ያማልደናል” የሚሉትስ እንዴት ይታያል?

በፕሮቴስታንታዊ አስተምህሮ የደነዘዙ ሰዎች ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከማዳን፣ ከቤዛነት ስራው ፍጻሜ በኋላም “አማላጅ”  እንደሆነ አድርገው ይናገራሉ፣ ያስተምራሉ፡፡ ለዚህም እንዲረዳቸው የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብና ያበላሻሉ፣ ትርጓሜውን ይለውጣሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ከሚታወቁባቸው አስተምሮዎቻቸው መካከል ቀደምት አበው ያቆዩዋቸውን አዋልድ መጻሕፍት በውኃ ቀጠነ መተቸት  አንዱ ነው፡፡ ምንም እንኳ አዋልድ መጻሕፍትን የሚጠሉና የሚንቁ ቢሆኑም “ሰይጣን ላመሉ መጽሐፍ ቅዱስን ይጠቅሳልና” እነርሱም ለክህደታቸው የሚመች ከመሰላቸው የአዋልድ መጻሕፍትንም አጣምመው ለመጠቀም ይሞክራሉ፡፡ በዚህ አግባብ ከሚጠቅሷቸው ደገኛ የቤተክርስቲያን መጻሕፍት አንዱ ቅዳሴ ሐዋርያት ነው፡፡ “ኢየሱስ ያማልዳል” የሚለውን አዘምነው “ኢየሱስ በዙፋኑ ተቀምጦ እንደሚፈርድ እናውቃለን፤ያማልዳል የምንለው በሥጋውና በደሙ(በቅዱስ ቍርባን) ነው” ይላሉ

ለዚህም የሚጠቅሱት ንባቡን እንጂ ትርጓሜውን ሳይመለከቱ “ስለ እኔ በቀራንዮ የፈሰሰ ንጹሕ የሚሆን የመሢሕም ደም እነሆ ስለ እኔ ይጮኻል፤ ይህ የሚናገር ደም የእኔን የባሪያህን ኃጢአት የሚያስተሰርይ ይሁን” የሚለውን ነው። ይህ ገጸ ንባብ የሚገኘው በቅዳሴ ሐዋርያት ቍጥር 106 ላይ ነው። የቅዳሴው አንድምታ ትርጓሜ ግን “የሚጮህ የሚካሰስ ዋጋ እንደሚያሰጥ ዋጋዬን (የዘለዓለም ሕይወትን) ይሰጠኛል ማለት ነው” ብሎ ምሥጢራዊ መልእክቱን ነግሮናል። ምክንያቱም ጌታችን “ሥጋዬን የሚበላ፥ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው”ብሎናልና ነው (ዮሐ 6፡53)።  በቅዳሴው “የሚጮህ ደም የሚናገር ደም”ተብሎ የተነገረው ሥጋውና ደሙ (ቅዱስ ቍርባን) ነፍስ የተለየው መለኮት ግን የተዋሐደው ሕያውና ዘለዓለማዊ መሆኑን ለመመስከር ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ “በሥጋ ሞተ በመንፈስ (በመለኮት) ግን ሕያው ሆነ (ነፍስ ሥጋን እንደተለየችው ሕያው መለኮት አልተለየውም)” ያለው ይኼንን ነው (1ኛ ጴጥ 3፡18)።  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡-የክርስቶስ ሥጋውና ደሙ መለኮት የተዋሐደው መሆኑን ሲመሰክር “የእግዚአብሔር ደም” ብሎአል (የሐዋ፡20፡28)።

ለመሆኑ “ኢየሱስ ይፈርዳል፥ ሥጋውና ደሙ ያማልዳል፤” ማለት ምን ማለት ነው? በእርሱና በሥጋ ወደሙ መካከል ልዩነት አለ እንዴ? እርሱ ሌላ፥ሥጋውና ደሙ ደግሞ ሌላ ነው? እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ አንዱን ክርስቶስ ለሁለት ከፍለው (በተዋህዶ ከሁለት አካል አንድ አካል፥ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ የሆነውን አንዱን ክርስቶስ ሁለት ባሕርይ አድርገው) በሥጋው ወደ ሠርግ ቤት ተጠራ፤ በመለኮቱ ደግሞ በተአምር ውኃውን ወደ ወይን ጠጅነት ለወጠ” እንደሚሉ ውጉዛን ካቶሊካውያን መሆን ነው። ምክንያቱም ወደ ሠርግ ቤት የተጠራውም ተአምር ያደረገውም ከተዋህዶ በኋላ መለየት የሌለበት አንዱ ክርስቶስ ነው። እኛም የምንቆርበው በተዋህዶተ መለኮት የከበረውን፥ የአንዱን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋና ደም ነው፤ እርሱም የዘለዓለምን ሕይወት የሚሰጥ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡-“የምንቆርበው ቅዱስ ቍርባንበዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ ከተቆረሰው የክርስቶስ ሥጋና ደም ጋር አንድ ነው” ያለው ለዚህ ነው። 1ኛ ቆሮ 11፡29

25. ሰዎችን ሥጋውንና ደሙን እንዳይቀበሉ የሚያደርጓቸው ምክንያቶችና መፍትሔዎቻቸው ምንድን ናቸው?

ክርስቲያኖችን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እንዳይቀበሉ የሚያደርጓቸው ብዙ ምክንቶች ቢጠቀሱም ባለመቀበል የቀረውን ዋጋ ግን ሊመልሱት አይችሉም፡፡ ብዙውን ጊዜ የሚጠቀሱት ምክንያቶች ስለቅዱስ ቁርባን በሚገባ አለመረዳት፣ መቅሰፍት ያመጣብኛል ብሎ መፍራት፣ ከኃጢአት አልተለየሁም (አልበቃሁም) ማለት፣ ከቆረብኩ በኋላ መልሼ ኃጢአት እሠራለሁ ማለት፣ እንዲሁም ስሸመግል እቀበላለሁ ማለት እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ኢየሱስም በሰማ ጊዜ አላቸው። የታመሙ እንጂ ጤነኞች ባለ መድኃኒትን አይሹትም። ነገር ግን ሂዱ እወቁትም ይህ ምንድር ነው ኃጥአንን ወደ ንስሓ ልጠራ መጣሁ እንጂ ጻድቃንን ለመጥራት አልመጣሁምና” (ማቴ.9:12-13) እንደተባለው ይህ መድኃኒት ለታመሙት ነውና ከምክንያተኝነት ወጥተን ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን ልንቀበል ይገባል፡፡

ክርስቲያን ስለ ምስጢረ ቁርባን የሚማረውና የሚያውቀው በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ ራሱን እንዲያዘጋጅና ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብሎ የዘላለም ሕይወትን እንዲወርስ ነው፡፡ “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው” እንደተባለ ሥጋውን የሚበላ ደሙንም የሚጠጣ በክርስቶስ ይኖራል፡፡ ሥጋውን ያልበላ ደሙንም ያልጠጣ ግን ለዘለዓለም የዘላለም ሕይወትን አያይም፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል እንጂ ላለመቀበል ምክንያትን ማቅረብ የዘላለም ሕይወትን አያሰጥምና ሁሉም ክርስቲያን ንስሐ እየገባ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሊቀበል ይገባዋል፡፡ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ቤዛ ያደረገ፣ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ያዳነን፣ በዕለተ አርብ በቀራንዮ አደባባይ ራሱን ከአዳም ጀምሮ እስከ ዓለም ፍጻሜ ላሉ ሰዎች ሁሉ ቤዛ፣ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበ፣ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በቤተክርስቲያን  መሥዋእት ህልው ሆኖ የሚኖር፣ በደላችንን የሚያጠፋ፣ መሥዋዕታችንን የሚቀበል ልዩ የሐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን በዘላለም ሕይወት ለመኖር ርስታችን መንግስተ ሰማያትን እንወርስ ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ አሜን፡፡