በዓለ ኖላዊ
በቀደሙ አባቶቻችንና እናቶቻችን ድል የማትነሣ ረድኤት፣ ጥርጥር የሌለባት እምነት የተዋበች ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን የቀናች፣ የጸናች ሃይማኖትን የምትመሰክርበት አስተምህሮ በነቢያትና በሐዋርያት ትምህርት የተመሰረተ ሲሆን የማዕዘኑም ራስ የቤተክርስቲያን ልዩ ሊቀ ካህናት፣ አብሲዳማኮስ የተባለ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ (ኤፌ. 2፡20፣ ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤጲፋንዮስ 54፡21) ሰማያውያን ቅዱሳን ሰዎችና መላእክት በማይፈጸም ምስጋና የሚያመሰግኑትን ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ቅድስት ቤተክርስቲያን ከቅዱስ ያሬድና ከሌሎችም የቤተክርስቲያን መብራቶች በተማረችው መሰረት ወራትን፣ አዝማናትን ከፍላ ታመሰግነዋለች፣ የማዳኑን ሥራ ትመሰክራለች፡፡ በነቢያት ትንቢት መሰረትነት ቆማለችና ትንቢተ ነቢያትን ተስፋ አበውን ታዘክራለች፡፡ በሐዋርያት ስብከት ጸንታለችና መንፈሳዊ አገልግሎትን ለንግድና ለታይታ ከሚያደርጉ ምንደኞች ራሷን ለይታ ምዕመናን በብዙ መከራ የእግዚአብሔርን መንግስት ለመውረስ ፍጹማን እንዲሆኑ ታስተምራለች፡፡ (ሐዋ. 14፡22) ካህናቷም እንደ ጌታቸው፣ እንደ መምህራቸው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም እርሱን እንደመሰሉ ቅዱሳን እውነተኛ ጠባቂ፣ እውነተኛ እረኛ (ኖላዊ ኄር) እንዲሆኑ ታስተምራለች፡፡ ይህ የቸር ጠባቂነት (እውነተኛ እረኝነት) ነገር ጎልቶ ከሚነገርባቸው ዕለታት አንዱ በታኅሳስ ወር ከጌታችን በዓለ ልደት አስቀድሞ በሚውለው ሰንበት የሚከበረውና ከጌታችን ዘጠኝ ንዑሳን በዓላት አንዱ የሆነው “ኖላዊ” ይባላል፡፡
ከጌታችን በዓለ ልደት አስቀድሞ ከኅዳር 15 እስከ ታኅሳስ 28 ድረስ ቅድስት ቤተክርስቲያን የነቢያትን ጾም ትጾማለች፤ የነቢያትን ሱባኤ ታዘክራለች፤ የነቢያን ተስፋ፣ ጩኸት ታስባለች፡፡ ቅዱሳን ነቢያት ጾማቸው፣ ሱባኤያቸው፣ ተስፋቸውና ጩኸታቸው ዓለምን የሚመግብ፣ የሚጠብቅ እግዚአብሔር ለቀዳማዊ አዳም የገባለትን ቃል፣ የሰጠውን ተስፋ ፈጽሞ አንድያ ልጁን እንዲልክ መማጸን ነበር፡፡ ስለሆነም በዕለተ ኖላዊ ቅድስት ቤተክርስቲያን የነቢያትን ተስፋ ሊፈጽም የተገለጠ የኢየሱስ ክርስቶስን እውነተኛ እረኝነት (ጠባቂነት) ትመሰክራለች፡፡ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በኋላ የሐዲስ ኪዳንን ቤተክርስቲያን በእረኝነት (በጠባቂነት) እንዲመሩ የተሾሙ ካህናትና መምህራንን ክብር ታስረዳለች፡፡ ምዕመናንም ደገኞቹን (እውነተኞቹን) ካህናትና መምህራን አክብረው ቢቀበሉ የቅዱሳንን በከረት እንደሚወርሱ ታስተምራለች፡፡ (ማቴ. 10፡40) በአንጻሩ ደግሞ ለግል ጥቅም ሲሉ በመንፈሳዊ አገልግሎት ስም ከሚነግዱ ምንደኞች (ቅጥረኞች) እንዲለዩ ትመክራለች፡፡ በዚህች አጭር ጦማር በዕለተ ኖላዊ በቅድስት ቤተክርስቲያን ከሚነበቡ የመጽሀፍ ቅዱስ ምንባባት መካከል ከትንቢተ ነቢያት መዝሙረ ዳዊት 79፡1ን፣ ሐዋርያት ከመዘገቡት የጌታችን ትምህርት (ወንጌል) ዮሐንስ ወንጌል 10፡1-22ን በመጠኑ ለማብራራት እንሞክራለን፡፡
የኖላዊ ሰንበት ምስባክ
በዕለተ ኖላዊ በቅድስት ቤተክርስቲያናችን የሚሰበከው ምስባክ ከክቡር ዳዊት መዝሙር 79፡1 የተወሰደ ሲሆን ንባቡ፡-“ኖላዊሆሙ ለእስራኤል አጽምዕ፤ ዘይርእዮሙ ከመ አባግዐ ዮሴፍ፤ ዘይነብር ዲበ ኪሩቤል አስተርአየ/ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ፣ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ፤ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ/” የሚል ነው፡፡
የዮሴፍ በጎች በግብጽ ይጠበቁ እንደነበር፣ እስራኤል ዘሥጋ፣ እስራኤል ዘነፍስን የጠበቅካቸው፣ የምትጠብቃቸው፣ በኪሩቤል (በአርባእቱ እንስሳ) አድረኸ የምትኖር ጌታ ሆይ እባክህ ተገለጥ፤ ኀይልህን አንሣ፣ እኛንም ለማዳን ና፡፡ ከአዳም ጀምሮ የነበሩ አርዕስተ አበው ሁሉም ይህን ጸሎት ጸልየውታል፣ ይህን ልመና ለምነውታል፡፡ አዳምና ሄዋን በበደላቸው ቢፈረድባቸውም በንስሃቸው የመዳንን ተስፋ ተቀብለው ነበርና ጌታ ተስፋቸውን እንዲፈጽምላቸው ዘመናቸውን ሙሉ በፍጹም መንፈሳዊ መታዘዝ “የኀያላን አምላክ ሆይ መልሰን፣ ፊትህንም አብራ፣ እኛም እንድናለን” የሚለውን የመሰለ ጸሎት እየጸለዩ የተስፋ ዘመናቸውን ፍጻሜ፣ የሚቤዣቸውን የክርስቶስን ልደት (መገለጥ) በእምነት ይጠብቁ ነበር፡፡ ሌሎችም የብሉይ ኪዳን ነቢያትና ቅዱሳን እንዲሁ፡፡ የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ የተወደደ ሐዋርያ ፊልጶስ “ሙሴ በኦሪት፣ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉለትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው፡፡” (ዮሐ. 1፡46) በማለት እንደተናገረ ዮሴፍን እንደ መንጋ የሚመራ፣ እስራኤል ዘነፍስን የሚጠብቅ፣ የሚያሻግር (የጠበቀ፣ ያሻገረ) ታኦዶኮስ ከተባለች ከሐዲስ ኪዳን ኪሩቤል ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ነቢያት በረድኤት ሳይሆን በአካል (በሥጋ በመወለድ) ታወቀ፤ ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠ፡፡ እርሱም የሁሉም ጠባቂ፣ ቸር እረኛ ነው፡፡
ለእረኝነት የተመረጡት ምንደኛ ሲሆኑ የመረጣቸው ጌታ ተገለጠ
በበዓለ ኖላዊ የሚነበበው ወንጌል ጌታችን “ቸር ጠባቂ (መልካም እረኛ) እኔ ነኝ፡፡” ብሎ ያስተማረው በዮሐንስ ወንጌል 10፡1-22 ያለው አምላካዊ ቃል ነው፡፡ ጌታችን በዚህ ትምህርቱ ስለ እረኝነት ከማስተማሩ አስቀድሞ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 8 እና 9 ባሉ ሁለት አስተማሪ ታሪኮች ለእረኝነት የተሾሙ፣ በሙሴና በነቢያት ወንበር የተቀመጡ የአይሁድ ሊቃናትን የእረኝነትን አገልግሎት በማጉደፋቸው ነቅፏቸዋል፡፡ በምዕራፍ 8 በተጻፈው የዘማዊቷ ሴት ታሪክ ለእረኝነት የተሾሙት የአይሁድ አለቆች ኃጢአታቸውን ደብቆ የሕግ መምህራን ቢያደርጋቸው ለበጎ ከመጠቀም ይልቅ እንደነርሱ ኃጢአተኛ የሆነችን ሴት በተጣመመ ፍርድ ለማጥቃት አዋሉት፡፡ በምዕራፍ 9 በተጻፈው ዕውር ሆኖ የተወለደው ልጅ (ዘዕውሩ ተወልደ) ታሪክ እንደተገለጠው አይሁድ እንዲጠብቁት፣ እንዲያስጠብቁት የተሰጣቸውን ትዕዛዛተ እግዚአብሔር ለራሳቸው የማይረባ፣ የታይታ ክብር ሲሉ አቃልለውት ነበርና እነርሱን የሚያስጨንቃቸው የታሰሩት መፈታት፣ የታመሙት መፈወስ፣ የሕግጋተ እግዚአብሔር መፈጸም ጉዳይ አልነበረም፡፡ ከዚያ ይልቅ ማንኛውም መንፈሳዊ ምግባር የእነርሱን ክብርና ዝና የሚቃረን ከመሰላቸው ማሩን አምርረው፣ ወተቱን አጥቁረው ጻድቁን “ኃጢአተኛ”፣ የታወቀውን በደለኛ “ንጹህ” ነው በማለት የእረኝነትን (የመምህረ ሕግነትን) መመዘኛ አዛብተውት ነበር፡፡ “ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ ተመልሶ ተቆጣጠራቸው፡፡” (ማቴ. 24፡ 19) እንደተባለ ያላከበሩትን ክህነታቸውን የሚያሳልፍ፣ ለሚያከብሯት፣ ለሚያገለግሉባት ትሁታን ሐዋርያት አሳልፎ የሚሰጥ የእረኞች አለቃ ኢየሱስ ክርስቶስ መገለጡን አላወቁም ነበር፡፡
የሐዲስ ኪዳን ትሁታን እረኞች (ኖሎት ኄራን)
የካህናት፣ የመምህራን እረኝነት በብሉይ ኪዳን ዘመን ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ እውነተኛ፣ ቸር ጠባቂ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለበጎቹ ነፍሱን አሳልፎ ከሰጠ በኋላ የመሰረታትን ቤተክርስቲያን ይመሩ፣ ይጠብቁ ዘንድ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ኤጲስ ቆጶሳትንና ካህናትን ሾሞልናል፡፡ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 21፡15-17 ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚነሱ የሐዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ጠባቂዎች ካህናትና መምህራንን ወክሎ በጎችና ግልገሎችን እንዲጠብቅ፣ ጠቦቶችን እንዲያሰማራ የታዘዘው ለዚህ ነው፡፡ እነዚህ ካህናት እንዴት ቤተክርስቲያንን ማገልገል እንዳለባቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃል ትምህርት አስተምሯል፣ በአርዓያነት በትህትና፣ ራስን ዝቅ በማድረግ አገልግሎ አሳይቷል፣ እንዲሁም ከምንም በላይ እስከ መስቀል ሞት ድረስ በመከራ ታግሶ የካህናትን የአገልግሎት መከራ ባርኮላቸዋል፡፡
ትምህርቱ እንደ አይሁድ ሊቃነ ካህናት የእግዚአብሔርን ቃል ለራስ ጥቅም በማጣመም ሳይሆን ፊት አይቶ ሳያደላ እውነትን በመግለጥ፣ ቸርነትንም በማድረግ የተሞላ ነበር፡፡ አገልግሎቱ እንደ አይሁድ ሊቃነ ካህናት ክብርን በመፈለግ፣ ልብስና ሥምን በማሳመር፣ ራሱን እንደ ክፉ ባለስልጣን ከወገኖቹ በማራቅ ሳይሆን ወገቡን ታጥቆ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ የተገለጠ ነበር፡፡ በእርሱ ላይ ከሳሾቹ ያገኙበት በደል ባይኖርም ከአዳም ጀምሮ እስከ ዓለም ፍጻሜ ለሚነሱ ምዕመናንና ምዕመናት ኃጢአትና በደል ራሱን ለመከራ መስቀል በፈቃዱ አሳልፎ በመስጠት የሐዲስ ኪዳን ትሁታን እረኞች ፍለጋውን ይከተሉ ዘንድ አስተምሯል፡፡ ስለሆነም የሐዲስ ኪዳን ካህናት ልዩ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን መስለው እንደየአቅማቸው ካገለገሉ ክብራቸው እጅግ ልዩ ነው፡፡ በአንጻሩ እንደ አይሁድ ሊቃናት የእግዚአብሔርን ህዝብ በቅንነት ከማገልገል ይልቅ ለራሳቸው ጥቅምና ክብር ሲሉ አገልግሎታቸውን ካቀለሏት ግን መክሊቱን የሰጣቸው ጌታ በዘመኑ ፍጻሜ ሊቆጣጠራቸው በተገለጠ ጊዜ “አላውቃችሁም” ይላቸዋል፤ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ባለበት የዘላለም መከራም ይቀጣሉ፡፡
እውነተኛ መምህራን ከሐሰተኞች በምን ይለያሉ?
ዘመናችን ከምንም ጊዜ በላይ ምዕመናንን ከቀናች ሃይማኖት የሚለዩ፣ ለራሳቸው ጥቅም ትምህርተ ወንጌልንና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የሚያጣምሙ ሐሰተኛ መምህራን የበዙበት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እውነተኛ እረኛ እንዳስተማረው ሁሉ በተነጻጻሪ ስለ ሐሰተኛ መምህራንም አስተምሯል፡፡ ጌታችን በአንቀጸ ኖላዊ ያስተማረውን የሚተረጉሙ ሊቃውንት እውነተኛ መምህራንን ከሐሰተኞች እንደሚከተለው ይለያሉ፡፡
እውነተኛ መምህራን ቅዱሳት መጻህፍት ይመሰክሩላቸዋል፤ እነርሱም በቅዱሳት መጻሕፍት አጥርነት፣ በሥርዓተ ቤተክርስቲያን ጋሻነት ተጠብቀው ቅዱስ ቃሉን ያስተምራሉ፡፡ ሐሰተኛ መምህራን ግን በልብ ወደድ ይጓዛሉ፤ በስህተት ትምህርትም ምዕመናንን ከቤተክርስቲያን (ቤተክርስቲያንን ከምዕመናን) ይለያሉ፡፡ ህገ ሃይማኖትን፣ ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ይንቃሉ፣ ያቃልላሉ፡፡
እውነተኛ መምህራን በጽኑ አገልግሎት፣ በፍጹም አርዓያነት ደቀመዛሙርትን ያፈራሉ፤ ስለ ራሳቸው ክብርም አይናገሩም፣ አያስነግሩም፡፡ እግዚአብሔርም ከሞታቸው በኋላ መታሰቢያቸውን እንዳይጠፋ ያደርጋል፣ በረከታቸውም ለትውልድ ይተርፋል፡፡ ሐሰተኛ መምህራን ግን ስለ ራሳቸው የሚናገሩ (የሚመሰክሩላቸውን)፣ በእግዚአብሔር ቃል ሳይሆን በወገንተኝነትና በድጋፍ የእግዚአብሔርን ቃል የሚያጣምሙ መሰሎቻቸውን ያፈራሉ፡፡ ደቀ መዛሙርት ይጠይቃሉ፣ ይሞግታሉ፣ ያምናሉ፣ ያሳምናሉ፡፡ የሐሰተኛ መምህራን ደጋፊዎች ግን እንዲህ አይደሉም፤ ቢጠይቁ፣ ቢሞግቱ እንኳ ለማመን ለማሳመን ሳይሆን ለክብርና ለዝና እንዲሁም ለወገንተኝነት ብቻ ነው፡፡ ለጊዜው ብዙዎች ይከተሏቸዋል፡፡ በኋላ ግን ማንነታቸው ይገለጣል፤ እንደ ቴዎዳስ ዘግብፅ እና ይሁዳ ዘገሊላ ተከታዮቻቸው ይጠፋሉ፣ እነርሱም መታሰቢያቸው ይረሳል፡፡
እውነተኛ መምህራን ስለ ምዕመናን መጠበቅ፣ ስለ ሕገ ሃይማኖትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ሲሉ ያለበደላቸው ልዩ ልዩ መከራን ይቀበላሉ፤ መከራን ይቀበሉታል እንጂ እነርሱ ሸሽተው ምዕመናንን በተኩላ አያስበሉም፡፡ ሐሰተኛ መምህራን ግን ቤተክርስቲያንን (ምዕመናንን) የሚፈልጓቸው በደስታ ወቅትና በጥቅማቸው ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ከሀዲ ባለስልጣን፣ መናፍቅ ጳጳስ ሲመጣ ወገንተኝነታቸው ለጥቅማቸው እንጂ ለቤተክርስቲያን አይደለም፡፡
እውነተኛ የበጎች እረኛ እንደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቶ በጎች ቢኖሩትና ከእነርሱ አንዱ ቢባዝን ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ትቶ ይባዘነውን ይፈልገዋል፡፡ (ማቴ. 18፡12-14፣ ሉቃስ 15፡4-5) የጠፋው አንድ ነው ብሎ ንቆ አይተወውም፡፡ የጠፋውን ሲፈልግም ያሉትን በትኖ ሳይሆን በተራራ ትቷቸው (አስጠብቋቸው) ይሄዳል፡፡ ቸር ጠባቂ ለደመወዝ (የግብር ይውጣ አገልግሎት) ሳይሆን በመክሊቱ ለማትረፍ በቅንነት ስለሚሰራ ስለ በጎቹ ይገደዋልና፡፡ በአንፃሩ በጎቹ ገንዘቡ ያይደሉ ምንደኛ፣ ሐሰተኛ እረኛ (መምህር) ግን ስለበጎቹ አይገደውም፡፡ የጠፋውን አይፈልግም፣ ቢፈልገውም ለጥቅሙ ብቻ ይፈልገዋል፡፡ ያልባዘኑትንም አያጸናም፣ የሚያጸና ቢመስል እንኳ የበጎቹን ጸጉር እየላጨ ለመሸጥ፣ ሥጋቸውን ወተታቸውን ለመብላት ለመጠጣት ይፋጠናል እንጂ እዳሪያቸውን ለመጥረግ (መከራቸውን ለመጋራት) አይፈልግም፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ እረኝነትና የተሾሙ ካህናት እረኝነት ልዩነት
የእግዚአብሔር ቤተሰቦች በዓለ ኖላዊን ስናከብር ሁላችንም ልናስተውለው የሚገባው ነቢያት በተስፋ የተናገሩለት በኪሩቤል ላይ የሚቀመጥ የነፍሳችን እረኛና ጠባቂ ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላችን አለ፡፡ (1ኛ ጴጥ. 2፡25) ይጠብቀናል፡፡ (መዝ. 22፡1-6) ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ (ያስወገደ) የእግዚአብሔር በግ ነው፡፡ (ዮሐ. 1፡29) በቤዛነቱ የእግዚአብሔር በግ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጋቢነቱ፣ በጠባቂነቱ፣ በመምህርነቱ በጎች የተባሉ የምዕመናን ሁሉ ጠባቂያቸው ነው፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ጠባቂነት፣ መጋቢነት፣ መምህርነት በሹመት በትምህርት የተገኜ ሳይሆን የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ የማዳን ተስፋውን በቅዱሳን አድሮ የሚገልጥ ጌታ በሥጋ የተገለጠበት ዘመን ከተፈጸመ በኋላ ዳግመኛ ተገልጦ ወደ መንግስቱ እስኪወስደን ድረስ ካህናትን መምህራንን እንደራሴዎቹ አድርጎ ሰጥቶናል፡፡ እነርሱም ትምህርተ ኖሎትን በሚገባ ተረድተው በቅንነት ምዕመናንን ሊያገለግሉ ይገባል፡፡ (1ኛ ጴጥ. 5፡2፣ ሐዋ. 20፡28) የካህናት የመምህራን ጠባቂነት በሹመት፣ በትምህርት የሚገኝ እንጅ የራሳቸው አይደለም፡፡ በጎች የተባሉ ምዕመናንም በአደራ የሚጠብቋቸው (የሚንከባከቧቸው፣ የሚያገለግሏቸው) ናቸው እንጅ የግል ገንዘቦቻቸው አይደሉም፡፡ እግዚአብሔር የሰጠንን የተሾሙ እውነተኛ ካህናት አክብረን በመያዝና ከሐሰተኞች በመራቅ እውነተኛ እረኞች እንዲበዙልን የአቅማችንን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል፡፡
“እኔም የወንድሜ (የእህቴ) ጠባቂ ነኝ!” እንበል
ምንም እንኳ እረኝነት (ጠባቂነት) በዋናነት ለካህናት ብቻ የተሰጠ ቢሆንም ሁላችንም እንደየአቅማችን የወንድሞቻችን፣ የእህቶቻችን ጠባቂዎች መሆናችንን መዘንጋት አይገባም፡፡ ስለሆነም “እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” (ዘፍጥ. 4፡9) በማለት በትዕቢት እንደተናገረ እንደ ቃየል ሆነን ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን ከቀናች ሃይማኖት፣ ከበጎ ምግባር ሲራቆቱ “አያገባንም” ልንል አይገባም፡፡ ይልቁንስ የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ “በሥጋ ዘመዶቼና ወንድሞቼ ስለሚሆኑ እኔ ከክርስቶስ እለይ ዘንድ እጸልያለሁ፡፡” (ሮሜ. 9፡3) እንዳለ እኛም ለወንድሞቻችንና እህቶቻችን ልንራራላቸው ቸር ጠባቂ ወደ ሆነ እግዚአብሔር ለማድረስም የአቅማችንን ልናደርግ ይገባል፡፡ እኛ እያንዳንዳችን በየደረጃችን እረኝነታችንን ሳንወጣ በዓለ ኖላዊን ብናከብር፣ ስለ እውነተኛና ሐሰተኛ መምህራንም ብንተርክ ምናልባት ለእውቀት እንጂ ለጽድቅ አይሆንልንም፡፡ ራስን ሳይጠብቁ ለሌላው መትረፍ አይቻልምና ስለሌሎች ከማሰባችን አስቀድመን ግን እያንዳንዳችን ራሳችንን ልንጠብቅ (በሃይማኖት፣ በምግባር ልንጸና) ይገባል፡፡ ዮሴፍን እንደመንጋ የጠበቀ (የሚጠብቅ)፣ ከሐዲስ ኪዳን ኪሩቤል ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ሥጋና ነፍስን ነስቶ እኛን ለመጠበቅ (ለማዳን) የተገለጠ የሥጋችንና የነፍሳችን እረኛና ጠባቂ ልዩ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ እያንዳንዳችን የወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን ጠባቂዎች የምንሆንበትን ጥበብ መንፈሳዊ እንዲያድለን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ አሜን፡፡