የሕገ እግዚአብሔር አመጣጥ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ተከፍሎ ይታያል። እነዚህም ሕገ ልቡና (ሕገ ሕሊና)፣ ሕገ ኦሪት (ሕገ ብሉይ) እና ሕገ ወንጌል (ሕገ ሐዲስ/ሕገ ትሩፋት/የፍቅር ሕግ) ናቸው። ሕገ ልቡና ያልተጻፈና በልቡና (በሕሊና) ያለ ሕግ ሲሆን ከአዳም እስከ ሙሴ የነበረውን ትውልድ ከእግዚአብሔር ጋር ሲያገናኝ የነበረ ሕግ ነው። እግዚአብሔር “እኔ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ” ብሎ የተናገረላቸው ቅዱሳን አበው በሕገ ልቡና ዘመን የነበሩ ናቸው። በአጠቃላይም በዘፍጥረት የሰፈረው የአምልኮ ሥርዓት በሕገ ልቡና የሚመራ ነበር። ሕገ ኦሪት (ሕገ ብሉይ) ደግሞ እግዚአብሔር ለሙሴ ሕግን በሲና ተራራ ላይ ከሰጠበት ጀምሮ እስከ ክርስቶስ መወለድ ድረስ ያለው ሲሆን አምልኮተ እግዚአብሔር በተጻፈ ሕግ የተመራበት፣ ብዙ ነቢያትም ያስተማሩበት ዘመን ነው። ይህም “ሕግና ነቢያት” ተብሎ የሚገለጸው ነው። ከሕግጋተ ኦሪት ጎልተው የሚታዩትም አሠርቱ ትዕዛዛት ናቸው።
ሙሴም እስራኤልን ሁሉ ጠርቶ ስለ ሕገ ኦሪት ሲነግራቸው “እስራኤል ሆይ፥ እንድትማሩአት በማድረግም እንድትጠብቁአት ዛሬ በጆሮአችሁ የምናገራትን ሥርዓትና ፍርድ ስሙ። አምላካችን እግዚአብሔር በኮሬብ ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ (ዘዳ 5:1-2)” ነበር ያላቸው። እንዲሁም “እግዚአብሔርም በእግዚአብሔር ጣት የተጻፋትን ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ሰጠኝ፤ …እግዚአብሔር በተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ የነገራችሁ ቃል ሁሉ ተጽፎባቸው ነበር። ከአርባ ቀንና ከአርባ ሌሊትም በኋላ እግዚአብሔር ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶች፥ የቃል ኪዳኑን ጽላቶች፥ ሰጠኝ (ዘዳ 9:10-11)” በማለት አሠርቱ ትዕዛዛት (ሕገ ኦሪት) በሁለቱ ጽላቶች ላይ ተጽፈው መሰጠታቸውን ተናግሯል። ሶሪያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ስለ ሕግጋተ ኦሪት “ወደ ደብረ ሲና የወረደ ለሙሴ ሕግን የሰጠ የተራራውን እራስ በጽጋግ በጢስ በጨለማና በነፋስ የሸፈነ ፈርተው የቆሙትንም በነጋሪቶች ድምፅ የገሠፀ የአብ አካላዊ ቃል ነው” በማለት ሕገ ኦሪት የተሰጠበትን ሁኔታ ተናግሯል (ውዳሴ ማርያም ዘሠሉስ)።

እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ!
ሕገ ወንጌል የምንለው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ “እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ። እንግዲህ ከነዚህ ከሁሉ ካነሱት ትእዛዛት አንዲቱን የሚሽር ለሰውም እንዲሁ የሚያስተምር ማንም ሰው በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ ታናሽ ይባላል፤ የሚያደርግ ግን የሚያስተምርም ማንም ቢሆን እርሱ በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይባላል። እላችኋለሁና። ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም (ማቴ 5:17-20)” በማለፍ ፍጹማን ያደረጋቸው ሕግጋትን ነው።
ጌታችን “ልፈጽም እንጂ ለመሻር አለመጣሁም” ያለውን ሊቃውንት ሲያብራሩት አንድም ሕግጋቱን ፍጹማን (Perfect) ሊያደርጋቸው ነው ብለዋል። ይህም “አድርግ አታድርግ” የሚሉ ሕግጋተ ኦሪትን በፍቅር ፍጹም ሊያደርጋቸው ነው። አንድም እርሱ ፈጽሟቸው ለእኛ ፍጹም አብነት (perfect example) ሊሆነን ነው ብለው አስተምረዋል። አንድም በነቢያት የተነገረውን የማዳኑን ተስፋ (የቤዛነቱን ሥራ) ለመፈጸም መምጣቱን ያመለክታል። ስለዚህም ለሕገ ወንጌል ጥላ የነበረችው ሕገ ኦሪት በጌታችን ወደ ፍጽምት ሕገ ወንጌል ተሸጋገረች እንጂ አልተሻረችም። በዝርዝር ያሉት ትዕዛዛትን ማክበር እንደሚገባም ጌታችን በማቴ 19:16-22 ማር 10:17-30 ሉቃ 18:18-30 አስተምሯል። ሐዋርያትም አሠርቱን ትዕዛዛት ማክበር እንደሚገባ በሰፊው አስተምረዋል። ለምሳሌም ያህል ሌሎች አማልክትን አታምልኩ ( 1ኛ ቆሮ 8: 6 ፤ 1ኛ ጢሞ 2: 5)፣ ጣዖታትን አታድርጉ (1ኛ ዮሐ 5: 21)፣ የጌታን ስም አላግባብ አትጥራ (1ኛ ጢሞ 6: 1)፣ የሰንበትን ቀን ቀድሰው (ቆላ 2፡16 ዕብ 4:1–11)፣ አባትህንና እናትህን አክብር ( ኤፌ 6:1–2)፣ አትግደል (ሮሜ 13:9 ፤ 1 ጴጥ 4:15)፣ አታመንዝር (1ኛ ቆሮ 6:9–10)፣ አትስረቅ ( ኤፌ 4 :1-2 ራእይ 9:28)፣ በሐሰት አትመስክር (ራዕይ 21:8)፣ የባልንጅራህን ቤት አትመኝ (ቆላ 3:5) ያሉትን ማየት ይቻላል።
በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል
ሕገ ወንጌል ፍጽምት የሆነች የፍቅር ሕግ ናት። ይህም ጌታችን ሁለቱን ዐበይት ትዕዛዛት (ፍቅረ እግዚአብሔርንና ፍቅረ ቢጽን) ያስተማረበትን ክፍል የሚያጠይቅ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ ይህንን ሲጽፍ “ፈሪሳውያንም ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው በሰሙ ጊዜ አብረው ተሰበሰቡ። ከእነርሱም አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው “መምህር ሆይ፥ ከሕግ ማንኛይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ አለው:- ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል (ማቴ 22:34-40)” አለው በማለት አስፍሮልናል። እነዚህ ሁለቱ ዐበይት ትዕዛዛት (Fundamental Commandments) ሁሉንም ሕግጋተ ኦሪትንና ሕግጋተ ወንጌልን የሚያጠቃልሉ ናቸው። የእነዚህ ታላላቅ ሕግጋት መሠረት ፍቅር ነው። ነገር ግን ፍቅር ምንድን ነው? በምንስ ይገለጣል?
በግእዝ፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ፍቅር (Love) ተብሎ በአንድ ቃል የሚገለጠው በግሪክ ቋንቋ አራት የፍቅር አይነቶችን ሊያመለክት ይችላል። የመጀመሪያው “ፍጹም ፍቅር” (Agape) ሲሆን ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በተለይም ሐዲስ ኪዳን ላይ በሰፊው የሚገኘው ቃል ነው። ይህ መንፈሳዊ (መለኮታዊ)፣ ቅድመ ሁኔታ የሌለውና መስዋእትነትን እስከመክፈል ድረስ የሚደርስ መውደድ ነው። እግዚአብሔር ሰውን የወደደበት ፍቅር ይህ ነው። ቅዱስ ጳውሎስም “ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ (1ኛ ቆሮ 13:1)” በማለት የተናገረው ስለዚህ ፍቅር ነው። ሁለተኛው የፍቅር አይነት “ወንድማዊ ፍቅር” (Philia) ሲሆን ይህም በወንድማማች፣ በእኅትማማች መካከል ያለ ፍቅር ነው። ጌታችን ሦስት ጊዜ ክዶት የነበረውን ቅዱስ ጴጥሮስን “የዮና ልጅ ጴጥሮስ ሆይ ትወደኛለህን (በፍጹም ፍቅር)” ብሎ ሲጠይቀው ቅዱስ ጴጥሮስ የመለሰው በዚህ አይነቱ ፍቅር (Philia) ነበር። ዳዊትና ዮናታንን ያስተሳሰራቸው ይህ ፍቅር ነበር። ሦስተኛው “ቤተሰባዊ ፍቅር” (Storge) ሲሆን በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ያሉ የቤተሰብ አባላት (parents and siblings) መካከል ያለ ፍቅርን ያመለክታል። አራተኛው “ጾታዊ ፍቅር” (Eros) ሲሆን በተቃራኒ ጾታ (በእጮኛሞችና በባለትዳሮች) መካከል የሚኖረው ፍቅር ነው። ይህ ያዕቆብ ለራሄል የነበረው ፍቅር አይነት ነው (ዘፍ 29:20)።
ጌታችን ያስተማራት ሕገ ወንጌል በፍጹም ፍቅር (Agape) ላይ የተመሠረተች ናት። “በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ጌታ አምላክህን ወደድ” ያለው ይህንን ፍጹም ፍቅር ያመለክታል። ይህም በሙሉ ኃይላችን (with all our powers)፣ በሙሉ መውደድ (complete love)፣ እስከመጨረሻው ደረጃ (strongest love)፣ በሕይወታችን ዘመን ሁሉ መውደድንም ያጠይቃል። አንድም በፍጹም ልባችን (በሙሉ ፈቃዳችን)፣ በፍጹም ነፍሳችን (በሙሉ ስሜታችን)፣ በፍጹም ሀሳባችን (በሙሉ መረዳትና ዕውቀት) መውደድ እንዳለብን ያመለክታል። አንድም በፍጹም ልባችን (ከልብ በመነጨ በእውነተኛ መውደድ)፣ በፍጹም ነፍሳችን (ከሁሉ በበለጠና የሚተካከለው በሌለ፣ ውስጣዊ ስሜታችንን በነካ መውደድ)፣ በፍጹም ሀሳባችን (በሚገባ አውቀን፣ ተረድተን በምንወደው መውደድ) ለማለት እንደሆነ ቀደምት ሊቃውንት ያስተምራሉ። ይህ ፍጹም ፍቅር የሚገለጠው ደግሞ እርሱን በማመንና ለእርሱ በመታመን ትዕዛዛቱን በማክበር ነው። ብትወዱኝ ትዕዛዛቴን ጠብቁ (ዮሐ 14:15) ብሏልና።
ሁለተኛይቱም ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። ይህችም የመጀመሪያይቱን ትዕዛዝ ትመስላለች። የቀደመችውን ትዕዛዝ የምትመስለው እንዴት ነው ቢሉ በመጀመሪያዋ ትዕዛዝ ላይ የተመሠረተችና ከመጀመሪያዋ ትዕዛዝ የምትወጣ መሆኗ ነው። አንድም እንደመጀመሪያዋ ባለች ፍጹም ፍቅር የምናየውን ባልንጀራችንን በመውደድ የማናየውን እግዚአብሔርን እንደምንወድ ማሳያ ስለሆነች ነው። በዚህች ትዕዛዝ ሥር “እንደራስህ ወደድ” በምትለዋ ሐረግ ውስጥ ራስን መውደድ እንደሚገባ እንረዳለን። ነገር ግን ይህች ራስን መውደድ ከራስ ወዳድነት (ራስን ብቻ ከመውደድና ሌላውን ካለመውደድ) የተለየች ስትሆን ተፈጥሯዊ ለራሳችን ሊኖረን የሚገባውን ክብር የምታሳይ ናት። “ባልንጀራ” ተብሎ የተገለጸውም የሰው ልጅ ሁሉ ነው። ምክንያቱም ሰውን ለይታ የምትወድ ፍቅር ፍጹም ፍቅር አይደለችምና።
ይህም በመሆኑ ነው ጌታችን በተለምዶ “ወርቃማ ሕግ” (Golden rule) ተብሎ በሚታወቀው ትዕዛዝም “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና (ማቴ 7:12)” በማለት ያስተማረው። ይህም ባልንጀራን መውደድ ማለት ለራሳችን ሊደረግልን የምንወደውን ለሌላው ማድረግ፣ በእኛ ሊደረግብን የማንወደውን ለሌላውን አለማድረግ መሆኑን ያስረዳናል። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ “ልጆቼ ሆይ፥ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ(1ኛ ዮሐ 3:18)” በማለት ያስተማራትም ይህች በተግባር የምትገለጠው እውነተኛዋ ፍቅር ናት። በግሪክ ቋንቋ የተጻፈውን ቅዱስ ወንጌልን ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበበው ቶማስ ሊናክር (Thomas Linacre, 1460–1524) የወቅቱ ‘ክርስቲያኖች’ ይኖሩት የነበረው የክርስትና ሕይወት ክርስቶስ ካስተማረው ወንጌል በእጅጉ ቢለይበት “ወይ ይህ ወንጌል አይደለም፣ ወይም እነዚህ ክርስቲያኖች አይደሉም – Either this is not the gospel, or these are not Christians” በማለት ነበር የተናገረው። ይህም የክርስትና ሕይወታችን የሚዳኝበትን መንገድ ያመላክተናል።
ጌታችን የእነዚህ ሁለቱን ትዕዛዛት ታላቅነት ሲያመለክተን “በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል” ነው ያለው። ምክንያቱም እነዚህ ሁለቱ መሠረታዊ ትዕዛዛት በሕገ ልቡና የነበረው፣ በኦሪት የተጻፈው፣ ነቢያት ያስተማሩት፣ ሐዋርያት የሰበኩት ሕግ ሁሉ ፍጻሜ ናቸውና። እግዚአብሔር ለሊቀ ነቢያት ሙሴ አሠርቱን ትዕዛዛት ሲሰጠው የመጀመሪያዎቹን አራቱን ማለትም ፍቅረ እግዚአብሔርን የሚመለከቱትን በመጀመሪያው ጽላት ላይ፣ ሌሎቹን ስድስቱን ማለትም ፍቅረ ቢጽን የሚመለከቱትን በሁለተኛው ጽላት ላይ ጽፎ ነበር። ይህም ሕገ ኦሪት በእነዚህ በሁለቱ ዐበይት ትዕዛዛት እንደምትጠቃላል ያስረዳናል። አቡነ ዘበሰማያት (አባታችን ሆይ) ብለን በምንጽልየው ጽሎትም ስምህ ይቀደስ፣ መንግሥትህ ትምጣ፣ ፈቃድህ በሰማያት እንደሆነች የሚለው የመጀመሪያው ክፍል ፍቅረ እግዚአብሔርን ቀጥሎ ያለው ሰውን የሚመለከተው ክፍል ደግሞ ፍቅረ ቢጽን የሚያሳይ ነው። በዚህም ሁለቱ ዐበይት ትዕዛዛት ይገለጣሉ።
እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ
የፍቅር ሕግ የሆነችው ሕገ ወንጌል ጌታችን የሰጠን አዲስ ትዕዛዝ ናት። ወንጌላዊ ዮሐንስ እንደጻፈው ጌታችን “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ (ዮሐ 13:34-35)” በማለት አዲስ ትዕዛዝ ሰጥቶናል። አዲስ (New) ያሰኛትም “እንደ ራስህ ውደድ” ከሚለው ሕገ ኦሪት “እኔ እንደወደድኳችሁ” ብሎ ፍጹም ፍቅር ማድረጉ ነው። ይህች አዲስ ትዕዛዝ “እኔ እንደወደድኳችሁ” ብሎ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ፣ በመስቀል ላይ ቤዛ በመሆን አብነት ሆኖ ፈጽሞ ያሳየን ትዕዛዝ ናት። የክርስትና ዋነኛ መታወቂያችንም ይህችን የፍቅር ሕግ መፈጸም መሆኑን ሲያስረዳን “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። በተጨማሪም “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት። ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም። እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ (ዮሐ 15:12-14)” በማለት ትዕዛዙ ይህች ፍቅር መሆኗንና ከእርሱ ጋር የምንወዳጀውም ፍቅር ሲኖረን መሆኑን አስተምሮናል።
ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም በመልእክቱ “ክርስቶስ ነው ብሎ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፥ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል። እግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድ በዚህ እናውቃለን። ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም (1ኛ ዮሐ 5:1-3)” በማለት ስለአዲሲቷ ትዕዛዝ ጽፎልናል። አዎን! እግዚአብሔርን የሚወድ በውኃና ከመንፈስ ከእግዚአብሔር የተወለደውን ወንድሙን ሁሉ ይወዳል። ይህ የተወደደ ሐዋርያ “ማንም እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን(1ኛ ዮሐ 4:20-21)” በማለትም ስለፍቅር ሕግ አስተምሯል። እንዲሁም “ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለሆነ፥ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ። ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና (1ኛ ዮሐ 4:8)” በማለት ስለአዲሲቱ ትዕዛዝ አስተምሯል። እንዲሁም “ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም (1ኛ ዮሐ 4:10)” በማለት ፍጹም ፍቅር ምን እንደሆነ አስተምሮናል።።
ይህ በእንዲህ እያለ ሕግጋተ ወንጌል ተብለው ስለሚታወቁትና ጌታችን በተራራው ስብከቱ ስላስተማራቸው የፍቅር ሕግጋት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አስፍተውና አምልተው ቢያስተምሩም ይህ ትምህርት በዘመናችን ከመጻሕፍት ውስጥ በቀር በተደራጀና ተከታታይነት ባለው መልኩ በዲጂታል ሚዲያው ብዙም አይገኝም። በዲጂታል ሚዲያው ያሉት ጥቂት ጽሑፎችም ቢሆኑ “ስድስቱ ሕግጋተ” ወንጌል እያሉ ከመዘርዘር ባለፈ ጠለቅ ያለና የተብራራ ግንዛቤን የሚያስጨብጡ ሆነው አላገኘናቸውም። በክርስቲያናዊ ስነ-ምግባራት ሥር ስለ ሕግጋተ ወንጌል የሚሰጠው ትምህርትም ቢሆን ሕግጋቱን ከመጥቀስና የክርስቲያናዊ ስነ-ምግባራት ምንጭ መሆናቸውን አበክሮ ከመግለጽ ያለፈ አለመሆኑን አስተውለናል። በተግባርም በብዛት የሚታየው የሕግጋቱን ቁጥር የመጥቀስ (superficial እውቀት) እንጂ በሕይወት የመተርጎም ነገር አይደለም። ምክንያቱም ሕግጋቱን እናስተምራለን የሚሉት ጭምር በተግባር ተቃራኒውን ሲያደርጉ ይስተዋላልና። ስለዚህም ለክርስትና ሕይወታችን ዕድገት ይረዳን ዘንድ ቅዱሳት መጻሕፍትንና የአባቶቻችንን ትምህርቶች መሠረት በማድረግ በዚህ “ሕግጋተ ወንጌል” በሚል ዐቢይ ርዕስ ሥር በተከታታይ በምናቀርባቸው ትምህርታዊ ጽሑፎች ሕግጋቱን አንድ በአንድ በተብራራ መልኩ እንዳስሳለን።