ክርስቲያናዊ አንድነትና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት

ምክንያተ ጽሕፈት

በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው የውጭ ሀገር ከተሞች አብያተ ክርስቲያናት ከመንፈሳዊ ዐውድነት ባላነሰ (በአንዳንዶችም ዘንድ በበለጠ) መልኩ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ዐውድ እየሆኑ ሲሄዱ መታዘብ ችለናል። ከዚህም የተነሳ ፖለቲካዊ የአመለካከት ልዩነቶች መንፈሳዊውን አንድነት በእጅጉ ጎድተውታል። ይህ በአመዛኙ በውጭ ሀገራት ባሉ አጥቢያዎች ጎልቶ የሚታይ ችግር በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ኢትዮጵያ ካለው የፖለቲካ አሰላለፍ የተነሳ ያለ ከልካይ በሀገር ቤት ባሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና አገልግሎቶችም ላይ በብዛት መታየት ጀምሯል። በሩቅ እየታየ ይወገዝ የነበረው፣ በተደራጀ መንግስታዊ ጉልበትና የመንፈሳውያን አገልጋዮች ቅን ተጋድሎ ተገድቦ የቆየው መንፈሳዊውን ዐውድ የፖለቲካ ነጥብ ማወራረጃ የማድረግ ክፉ ልማድ በሙሉ ኃይሉ ቤተ ክርስቲያናችንን እየፈተናት እንዳለ እንረዳለን። ይሁንና የችግሩን ጥልቀትና ስፋት ተረድቶ በቤተ ክርስቲያን ዘላቂ አገልግሎት የሚኖረውን አሉታዊ ተፅዕኖ በውጤት ተኮር አስተዋይነት (pragmatic perspective) ተገቢ መፍትሄ የሚያመላክት የቤተ ክርስቲያን አካል አይስተዋልም። የዚህ ችግር አንዱ መነሻ ክርስቲያናዊ አንድነትን በፖለቲካዊ የአመለካከት ልዩነት የሚገድብ አርቆ የማያይ ምልከታ መስፈኑ ነው።

በምድራችን ላይ ብዙ አይነት የፖለቲካ አመለካከቶች እንዳሉ ይታወቃል። እያንዳንዱ ግለሰብም ይሻላል ብሎ የሚወስደውና የራሱ የሆነ ፓለቲካዊ አመለካከት ሊኖረው ይችላል። ተመሳሳይ ፖለቲካዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎችም ይህንን አመለካከታቸውን ለማራመድ በፖለቲካ ፓርቲነት ሊደራጁ ይችላሉ። ይህም በፖለቲካው ዘርፍ የራሱ የሆነ ሕጋዊ አሠራር አለው። በአንፃሩ ቤተ ክርስቲያን በምድራዊ የፖለቲካ ርዕዮት የማትገደብ ሁሉም ከጥፋት ውኃ የሚድንባት መርከብ እንጂ የፖለቲካዊ ርዕዮት መታገያ ዐውድ አይደለችም። ይሁንና በቤተ ክርስቲያን የተለያየ ዓይነት ፖለቲካዊ አመለካከት ያላቸው እና/ወይም በተለያዩ ፖለቲካዊ አደረጃጀቶች ውስጥ ያሉና ለሕዝብና ለሀገር ይበጃል ብለው የሚያምኑበትን ፖለቲካዊ አስተሳሰባቸውን የሚያራምዱ ሰዎች መኖራቸው የልዩነትና የክፍፍል ምንጭ ሲሆን ይታያል። በተለይም በዝርወት ዓለም (ዲያስፖራ) በአጥቢያ ደረጃ ሳይቀር የመንግስት (ወይም የተወሰነ ፖለቲካዊ ቡድን) ደጋፊና ተቃዋሚ ተብሎ መቧደን የተለመደ ሆኗል። የዚህም መነሻ የክርስቲያናዊ አንድነት መሠረቶችን በሚገባ ካለመረዳት ወይም የቤተ ክርስቲያንን መድረክ ለፖለቲካዊ ዓላማ ለመጠቀም ከማሰብ የሚመነጭ ነው። በዚህም የተነሳ የፖለቲካ አመላካከት ልዩነቶች ክርስቲያናዊ አንድነታችንን እየተፈታተኑት ይገኛሉ። እኛም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር የዚህን ችግር መሠረታዊ ምክንያቶች እንዳስሳለን፣ የመፍትሔ ሀሳቦችንም እንጠቁማለን።

ፖለቲካ ምንድን ነው? 

ከሁሉ አስቀድመን ፖለቲካ (ፖለቲከኛ መሆን) ሰው ሀገሩን እና ሕዝብን የሚያገለግልበት አንድ የሙያ/የሥራ ዘርፍ/ክህሎት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባዋል እንላለን። ይህም ሲባል ልክ እንደ ሕክምና፣ ምህንድስና ወይም የመምህርነት ሙያ ፍላጎትን፣ የትምህርት ዝግጅትንና ልምድን የሚጠይቅ ነው ማለት ነው። በቤተ ክርስቲያንም አስተምህሮ የፖለቲካው ዘርፍ እንደ አንድ የሙያ/የሥራ ዘርፍ/ክህሎት ሊታይ ይገባል እንጂ የተለየ የጽድቅም ሆነ የኩነኔ ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ አያስፈልገውም። ይህ ማኅበረሰቡ ውስጥም ሊሠርፅ የሚገባው አመለካከት ነው። ክርስቲያንም ፖለቲከኛ መሆንን በዚሁ አግባብ ሊመለከተው ይገባል። ፖለቲከኛ መሆንም የግለሰብ የሙያ ዘርፍ (career) እንጂ የቤተ ክርስቲያን ዐቢይ ጉዳይ ሆኖ ሊወሰድ አይገባውም። አንዳንድ አገልጋዮችም በፖለቲካ መሳተፋቸውና ለሥልጣን መብቃታቸው የተለየ የብቃት መለኪያ ወይም የመንፈሳዊ ልህቀት ከፍታ ተደርጎ መቆጠር የለበትም፣ አለመሳተፋቸውም የተለጠጠ ትርጉም ሊሰጠው አይገባም። የቤተ ክርስቲያን ዓላማዋ ይህ አይደለምና። ነገር ግን ጥንት የነበረው የቤተ ክህነትና የቤተ መንግስት ቁርኝት የፈጠረው ዳራ (legacy)፣ እንዲሁም በሀገራችን ሰፍኖ የሚታየው የጥቅመኝነትና የጥላቻ ፖለቲካ ይህን አስተሳሰብ ሲፈታተነው ይታያል።

ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያለው ምዕመን በእኩልነትና በነፃነት የሚገለገልበትንና የሚያገለግልበትን መንፈሳዊ ዐውድ መፍጠሩ ላይ ነው። ሌላው ዐቢይ ጉዳይ ደግሞ የፖለቲካ (የመንግስት አስተዳደር) እና የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ግንኙነት ነው። በተለይም በሴኩላሪዝም አስተሳሰብ የመንግስት አስተዳደርና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸው በሕግ የተደነገገ ቢሆንም ሁለቱ ተቋማት በትብብር/ተናበው የሚሠሩባቸው ብዙ ሀገራዊ ጉዳዮች አሉ። አንዳንድ መንግስት የሚሠራቸው ሥራዎችም በቤተ ክርስቲያን ላይ ተፅእኖ የሚያሳድሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ቤተ ክርስቲያን የምትሠራቸው ሥራዎችም እንዲሁ። በዚህም የተነሳ ነው የፖለቲካና የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ አንድ መወያያ ርዕስ ሆኖ የሚመጣው። ይህ በግልፅና በሥርዓት የሚመራበትን ሕጋዊ ማዕቀፍ ማበጀቱ በመንግስት በኩል የግለሰቦች፣ የፖለቲካዊ አመለካከት ወይም የፖለቲካ ድርጅቶች ሲቀየሩ ችግር እንዳይፈጠር ይረዳል።

የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት  

በአንዳንድ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ብዙ ውዝግብ የሚያስነሳው የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ነው፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ መታወቅ ያለበት ቤተ ክርስቲያን እንደ ተቋም ፖለቲካዊ ወገንተኝነት አይኖራትም፣ ሊኖራትም አይገባም፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችም በተለይም ካህናት በአገልግሎታቸው ይህንን የፖለቲካ ገለልተኝነት (neutrality) ሊያንጸባርቁ ይገባል፡፡ አገልግሎታቸው የተለያየ ዓይነት ፖለቲካዊ አመላከከት ላላቸው ምዕመናን ነውና፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያን የየራሱ ፖለቲካዊ አመለካከት ሊኖረው ይችላል፡፡ ይህም ክርስትና የማይገድበው መብቱ ነው፡፡ ክርስቲያንም ቤተ ክርስቲያን የሚመጣው ወንጌልን ለመማር፣ ለመጸለይ፣ ለማስቀደስ፣ ለመባረክ ነው። እነዚህም ከፖለቲካዊ አመለካከት ጋር የማይጋጩ፣ የምድርን ሳይሆን የሰማይን መንግስት የሚሰብኩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ክርስቲያን (ካህናትን ጨምሮ) በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት አንዱን የፖለቲካ አመለካከት ጽድቅ፤ ሌላውን ኩነኔ፤ አንዱን የፖለቲካ መሪ መልአክ፤ ሌላውን መሪ ሰይጣን አድርገው የሚያቀርቡ ከሆነ ድርጊቱ መንፈሳዊ ዓላማውን ከመሳቱም ባሻገር ምዕመናንን የሚከፋፍልና ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳ ይሆናል፡፡

የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መንፈሳዊ አንጂ ፖለቲካዊ ስላልሆነ ከማንኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ አመለካከት ጋር የማይጋጭ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አንዱን ፖለቲካዊ አመለካከት (ቡድን) ደግፋ ሌላውን አትኮንንም፡፡ ክርስቲያኖች ግን የየራሳቸው ፖለቲካዊ አመለካከት ሊኖራቸውና ይህንንም አመለካከታቸውን (ከቤተ ክርስቲያን ውጭና የቤተ ክርስቲያንን ስም ሳይጠቀሙ) ከማራመድ የሚከለክላቸው ነገር የለም፡፡ ይህንንም በማድረጋቸው በቤተ ክርስቲያን የተለየ ክብር ሊሰጣቸው ወይም የተለየ መገለል ሊደርስባቸው አይገባም፡፡ ፖለቲከኛም የቤተ ክርስቲያን አባል ስለሆነ የተለየ ነገር ለቤተ ክርስቲያን እንዲያደርግ ሊጠበቅበት አይገባም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በእምነት ስም ፖለቲካን ማራመድም ሆነ በፖለቲካ ስም እምነትን ለማራመድ መሞከር ቤተ ክርስቲያንን ሲጎዳት እንጂ ሲጠቅማት አላየንም።

ቤተ ክርስቲያንና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት

የክርስትና አስተምህሮ ለብዙ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እሴቶች መሠረት እንደሆነ ለማንም ግልፅ ነው። በዘመናችን ያለውም የክርስትና አስተምህሮም በዚህ ዘመን ያሉትና ወደፊት የሚኖሩትን ፖለቲካዊ አመለካከቶች በእውነት፣ በእኩልነትና በፍትህ ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ የራሱን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይገባል። በተጨማሪም በሕዝብ ዘንድ ሊኖር ስለሚገባው የመልካም አስተዳደር ሥርዓትም መሪዎችን የሚያስገኘውን የሕዝብ አመለካከትና ባህል በመቅረፅ ዘንድ ታላቅ ድርሻ አለው። በተቃራኒም የመልካም አስተዳደር እጦት መገለጫዎች የሆኑት ሙስናና የሰብአዊ መብት ረገጣዎች የክርስትና አስተምህሮ ሥር ያለመስደድ ምልክቶች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ። ነገር ግን የክርስትና አስተምህሮ ፖለቲካዊ አመለካከቶችን የማቃናት ሚና ይኖረዋል ሲባል ፖለቲካዊ ወገንተኝነት በሌለበት ዐውድ ልዕልና ያለውን ሀሳብ ከመቅረፅና የማኅበረሰቡ እሴት ከማድረግ ረገድ መሆኑን ማስተዋል ይገባል።

የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍለው አገልጋዮች (በተለይም ካህናትና ሰባክያን) የፖለቲካ አመለካከታቸውን በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ወይም በቤተ ክርስቲያን ስም ማንጸባረቅ ሲጀምሩ ነው፡፡ በተለይም የመንግስት ደጋፊና ተቃዋሚ በሚል ጎራ አንዳንድ አገልጋዮች የፖለቲካ መሪዎችን በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ሲያወድሱ ወይም ሲኮንኑ ቤተ ክርስቲያንን እየከፋፈሉ እንደሆነ አይረዱትም፡፡ አንዳንዶችም መንግስትን ሲያሞግሱ፣ ሌሎችም የተቃዋሚ ፓርቲዎችን አጀንዳ በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረትና በቤተ ክርስቲያን ስም ሲያራምዱ ያን ጊዜ በምዕመናን መካከል መለያየት ይፈጠራል፣ የክርስቶስ አካል ቤተ ክርስቲያንም በምድራዊ ልዩነት ትከፋፈላለች፡፡ ነገር ግን አገልጋዮች ወገንተኝነታቸውን ለክርስቶስ ብቻ አድርገው ቢያገለግሉ መከፋፈል አይኖርም፡፡ መከፋፈል የሚመጣው ቤተ ክርስቲያንን ለፖለቲካ ጥቅም ማዋል ሲታሰብ/ሲጀመር ነው፡፡

እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ውስጡን አንድ አይነት ፖለቲካዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎችን በቁልፍ ቦታዎች በማስቀመጥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሽጎ በሃይማኖት ስም የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብት በመጠቀም ፖለቲካዊ አመለካከትን ለማስፋፋት መሞከር ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ትልቅ እንቅፋት ነው፡፡ ይህ አይነቱ አካሄድ ምዕመናን ተስፋ በመቁረጥ ቤተ ክርስቲያንን በጥቅሉ እንዲጠሏትና በብዛት እየለቀቁ እንዲወጡ ያደርጋል፡፡ አቤት የሚባልበት አካል ራሱ የችግሩ ምንጭ ከሆነ ደግሞ ለእግዚአብሔር ካልሆነ ለማን አቤት ይባላል?! እነዚህ አካላት ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ምልክቶች ሳይቀር የቤተ ክርስቲያን በማስመሰል ምዕመናንን ለፖለቲካ ዓላማቸው ማስፈጸሚያነት ሲመለምሉ ማየት ያሳፍራል፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያንን የንትርክ መድረክ ያደርጋታል፡፡ ሁላችንም ቤተ ክርስቲያንን ለተቋቋመችበት ዓላማ ብቻ ብንጠቀምና የማኅበራዊ ማንነታችንን ጓዝ ማስፋፊያ ባናደርጋት ክርስቲያናዊ አንድነታችን ይጠናከራል፡፡

ሃይማኖትንና ፖለቲካን መቀላቀል
ማሳያ ምሳሌ

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉሥ የአፄ ኃይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ የሆነና “የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት” የተባለ ፖለቲካዊ ተቋምን የሚመራ ታዋቂ ሰው በተለያዩ የዓለማችን ከተሞች ይዘዋወር ነበር። ይህ ሰው የያዘው ዓላማ በፖለቲካዊ መነፅር ሊወደስም ሆነ ሊነቀፍ ይችላል። መንግስታዊ ስልጣንን ራሳቸውን “ባላባት” ብለው ለሚጠሩ ሰዎች ብቻ በዘር የማስተላለፍ ርዕዮት ደጋፊዎች ያሉትን ያህል በጥብቅ የሚኮንኑትም አሉ። ይሁንና ይህን አስተሳሰብ ለማስረፅ የሚንቀሳቀስ ተቋምና ግለሰብ እንደ ምዕመን ሳይሆን እንደ ልዩ መልእክተኛና ባለስልጣን በውጭ ሀገራት የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን ሲጎበኝ ካህናትና ምዕመናንም በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ሲያጎበድዱለት አስተውለናል። ከዚህ ጋር በተያያዘ  ቀላል ጥያቄ መጠየቅ ፓለቲካና ሃይማኖትን የመቀላቀልን ችግር ያሳያል ብለን እናስባለን። “ለመሆኑ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው ለዚህ ግለሰብና ለሚወክለው ፖለቲካዊ ርዕዮት ያጎበደዱ ካህናትና ምዕመናን ለሌሎች መሰል ፖለቲከኞች፣ ለልጅ ልጆቻቸውና ለሚወክሉት ፖለቲካዊ ርዕዮት በተመሳሳይ መልኩ ያጎበድዳሉ?” መልሱ “አዎ” በሚሆንባቸው ቦታዎች ቤተ ክርስቲያን የፖለቲካ ሸቀጥ ማራገፊያ ትሆናለች። መልሱ “አይደለም” በሚሆንባቸው ቦታዎች (በእኛ ግምት በአብዛኞቹ ቦታዎች) ደግሞ ከሚጎበደድለት ፖለቲካ የተለየ ርዕዮት ያላቸው ሰዎች “አሃ ይሄ ቦታ የእነ እገሌ ነው” ብለው እንዲገፉ ያደርጋቸዋል። ከመንፈሳዊ አስተሳሰብ ይልቅ ያልቦካ የፖለቲካ ሊጥ ይዘው ምዕመናንን ከቤተ ክርስቲያን የሚያርቁ ሞኞች በበዙበት ዘመን ይህ ሃይማኖትና ፖለቲካን የመቀላቀል አይሁዳዊ ልማድ የሚያመጣው መዘዝ ብዙ ነው።

ፖለቲካና ሃይማኖትን መለየት የሚጀመረው በመጀመሪያ በአእምሮ ውስጥ (ይህ ሀሳብ ሃይማኖታዊ ነው፣ ያ ደግሞ ፖለቲካ ነው ብሎ በማስተዋል) ሊሆን ይገባል። ቀጥሎም ሃይማኖትና ፖለቲካ መለየት ያለባቸው በንግግር (በጽሑፍ) ነው። ይህም ሁለቱን ለይቶ በመናገር ወይም በመጻፍ ነው። ሦስተኛም ሃይማኖትና ፖለቲካ የሚለዩት በተሳትፎ ነው። ይህም አቻችሎ በመሳተፍ ሊሆን ይችላል። ሌላውና ዋናው መለያቸው የዓላማ፣ አስተምህሮ፣ የሥርዓትና ተቋማዊ አወቃቀራቸው ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ በቤተ ክርስቲያን እና በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ዙሪያ የሚስተዋለው ችግር በክርስትና ልብስ/ሽፋን ወይም ስም የተወሰነ ፖለቲካዊ አመለካከትን ለማራመድ መሞከር ነው። ይህም በተለይ የራሳቸውን ፖለቲካዊ ወገንተኝነትን የሚያንጸባርቁ ወይም ለተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ብቻ የቆሙ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካህን እና ሰባኪ ወይም የማኅበረሰብ አንቂ (activist) የሆኑ ሰዎች ሲያደርጉት የሚታይ ነው። እነዚህ ግለሰቦች በግልፅ የሚታወቁት በቤተ ክርስቲያን ሰውነታቸው (ማዕረጋቸው) ወይም የመንፈሳውያን ማኅበራት አባልነታቸው ቢሆንም በስብከታቸውና በጽሑፎቻቸው ግን በሃይማኖት የተጠቀለለ ፖለቲካዊ አመለካከትን ወይም ለሌላው ወገን ያላቸውን የጥላቻና የንቀት ጥግ ሲያራምዱ ይስተዋላሉ። ይህ ዓይነቱ ጎራውን ያልለየ በእምነት ስምና ሽፋን የሚደረግና የትም የማያደርስ ሩጫ ክፋትንና ልዩነትን ከማስፋት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም።

በአንድ ወቅት በቤተ ክርስቲያን በሰባኪነታቸው የሚታወቁ ግለሰቦች በፖለቲካ መሳተፍ ሲጀምሩ ስብከቱንና ፖለቲካዊ ሥራቸውን ለይተው ለማራመድ ሲቸገሩ እናያለን። ፖለቲካው ስብከት፣ ስብከቱም ፖለቲካ ይሆንባቸዋል። ፖለቲካ ሃይማኖትን የማይለይ (ሁሉንም ሃይማኖት በእኩልነት ማየትን የሚጠይቅ)፣ ስብከት ደግሞ ፖለቲካዊ አመለካከትን የማይለይ (ሁሉንም ፖለቲካዊ አመለካከቶች በእኩልነት የሚያይ) መሆኑን ይዘነጉታል። እንደዚህ ዓይነት ግለሰቦች አንዱን አጥብቀው ቢይዙና ሌላውን ለሌላው ቢተዉ ሕዝብን ከማወዛገብ፣ ቤተ ክርስቲያንንም ከማስወቀስ ይድናሉ። በመንፈሳዊ አገልግሎት ያገኙትን ተሰሚነት ለፖለቲካ ዓላማ የተጠቀሙ ተብለው ከመወቀስም ይድናሉ። ምናልባት በሌሎች የሃይማኖት ድርጅቶች ያሉ ግለሰቦች ሁለቱን እያጣቀሱ መሄዳቸው እንደ መከራከሪያ የሚቀርብ ከሆነ ‘ሁለት ስህተት አንድ እውነት አይሆንም’ እንላለን። ምዕመናንንም ቢሆኑ ፖለቲከኛንና መንፈሳዊ አገልጋይን ለይተው ሁሉንም በሚገባው ሚዛን ሊመዝኑ ይገባል እንጂ አንድን ግለሰብ ‘ጥሩ ሰባኪ’ ስለነበር/ስለሆነ ጥሩ ፖለቲከኛም ይሆናል ከሚል ድምዳሜ ራሳቸውን ማራቅ ይገባቸዋል።

የመፍትሔ ሀሳቦች
ክርስቲያናዊ ስነ-ምግባርን ማስተማር

በፖለቲካዊ አመለካከት ልዩነቶች ምክንያት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈጠረውን ችግር ከመሠረቱ ለመፍታት ለሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ክርስቲያናዊ ስነ-ምግባራትን በሚገባ ማስተማር ሊቀድም ይገባዋል። ይህም ሰው የክርስቲያናዊ አንድነት መሠረቶችን እንዲያውቅና የሰዎችን የተለያየ አስተሳሰብና አመለካከትም እንዲያከብር ያደርገዋል። ከዚህ በተጨማሪም ፖለቲካ ራሱን የቻለ የሙያ ዘርፍ መሆኑን በሚገባ በማሳወቅ ሰዎች በፍላጎታቸውና በክህሎታቸው በድብቅ (በሃይማኖት ስም) ሳይሆን በግልፅ በአደባባይ፣ በፍርሃትና በመሸማቀቅ ሳይሆን በልበ ሙሉነት፣ በሃይማኖት ተከልለው ሳይሆን ራሳቸውን ሆነውና ራሳቸውን ችለው እንዲያራምዱ ማኅበረሰቡ ሊያበረታታቸው ይገባል። ይህ ሲሆን ለእምነቱም ለፖለቲካውም ይበጃል።

ግለሰብንና ተቋምን መለየት

ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አንፃርም የግለሰብና የተቋምን (የቤተ ክርስቲያንን) አቋም ለይቶ የሚያይ አገልጋይና ምዕመን መፍጠር ያስፈልጋል። በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት የሚቆሙ አገልጋዮች የራሳቸውን አመለካከት ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ሊሰብኩ ይገባል። የራሳቸውን አመለካከትና የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ የሚቀላቅሉ ከሆነ ምዕመናንን ይጎዳሉ። የግለሰቦች ፖለቲካዊ አመለካከት የየራሳቸው እንጂ የቤተ ክርስቲያን አይደለምና። ምዕመናንም ወደ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡት በክርስትናቸው እንጂ በፖለቲካዊ አመለካከታቸው አይደለም። የሰባኪን ፖለቲካዊ ትንታኔ ሊሰማ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጣ ምዕመን የለም፣ ካለም የክርስትናን አስተምህሮ ያልተረዳ ነው። ቤተ ክርስቲያንም የክርስቲያኖች አንድነት/ኅብረት እንጂ ተመሳሳይ ፖለቲካዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ኅብረት አይደለችም።

የአገልግሎት መመሪያመተግበር

ከመንፈሳዊ አገልግሎት አንፃርም የመንፈሳዊ አገልግሎት መመሪያ (code of conduct) ማዘጋጀትና ትግበራውንም ማጠናከር ይገባል። ይህም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መንፈሳዊ አገልግሎትን እና የራሳቸውን ፖለቲካዊ አመለካከት ለይተው በመንፈሳዊው ዐውድ መንፈሳዊ መልእክትን ብቻ እንዲያስተላልፉ ይረዳል። ከሥርዓት ሲወጡም እንዲታረሙ ያደርጋል። በተለይ ካህናት ሁሉንም ያለ ልዩነት በእኩልነት እንዲያገለግሉ ያደርጋል። ከዚህ ጎን ለጎን ቤተ ክርስቲያን ፖለቲካዊ ወገንተኝነት እንደሌላት ማረጋገጥና በቤተ ክርስቲያን ፖለቲካዊ አዝማሚያ ሲታይ ቶሎ መከላከልና የእርምት እርምጃ መውሰድም ያስፈልጋል። ይህም በምዕመናን መካከል በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት የተነሳ መከፋፈል እንዳይፈጠር ይረዳል። ግለሰቦች በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ሳይቀር የራሳቸውን ፖለቲካዊ አመለካከት ሲስብኩ ዝም ማለት ግን መንፈሳዊውን ዐውደ ምሕረት መንፈሳዊ ረብ ለሌለው አላፊና ጠፊ የሰዎች ፍልስፍና ማስፋፊያነት መፍቀድ ነው።

ትርክትንና አስተምህሮን መለየት

በስተመጨረሻም ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ በየጊዜው የሚነሱ የሐሰት ትርክቶችም ሆኑ የቀድሞ መሪዎችና የግለሰቦች ድርጊቶች (ያራምዱት የነበረው የፖለቲካዊ አመራር ዘዴዎች) ቤተ ክርስቲያንን እንደማይወክሉ በግልፅ ማሳወቅ ይገባል። የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮንና የተለያዩ ግለሰቦችና ጸሐፍያን በተለያዩ ዘመናት የጻፏቸውን መጻሕፍትና የተናገሯቸውን ንግግሮች ለይቶ ማየት ይገባል። በዚህም የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር እየሰጠን ሁሉንም በአግባቡና በተሠራለት ሥርዓት መሠረት እየፈጸምን በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት የተነሳ ክርስቲያናዊ አንድነታችን ሳይፈተን ጸንተን ልንቆም ይገባል።

ማጠቃለያ

የክርስትና አስተምህሮና የፖለቲካ አመለካከት ፍጭትና ግጭት ከጥንት ጀምሮ የነበረና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አንዱ አካል ነው። በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን እንኳን ብንመለከት ንጉሥ ሄሮድስ ጌታችንን ማሳደዱ፣ ሌላው ሄሮድስ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ማስገደሉ፣ አይሁድ ጌታችንን ከቄሳር ጋር ለማጋጨት ያደረጓቸው ሙከራዎች፣ በመጨረሻም ጌታችን በጲላጦስ ፊት መቅረቡንና ለመስቀል ተላልፎ መሰጠቱ ልዩ መገለጫዎች ናቸው። ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ሰማዕታትና ሊቃውንትም በየዘመኑ በነበሩት ነገሥታት መከራን መቀበላቸው የዚሁ አካል ነው። እነርሱ የተፈተኑት ለእውነተኛይቱ እምነት ብቻ ሲሉ መሆኑ ግን ሊሠመርበት ይገባል። ይህ በክርስትና ላይ የሚደርሰው እንዲህ ዓይነት ፈተናም መልኩንና ይዘቱን እየቀያየረ የሚቀጥል መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

በዘመናችን የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦችና ፖለቲካዊ ድርጅቶች አሉ። የቤተ ክርስቲያን ልጆችም ይበጀናል ያሉትን ፖለቲካዊ አመለካከት ሊደግፉ፣ አይበጀንም ያሉት ላይም አስተያየት ሊሰጡ ይችላሉ። ፖለቲካም አንድ የሙያ ዘርፍ እስከሆነ ድረስ በግልም በቡድን ተሳትፈውበት ለሀገርና ለሕዝብ የራሳቸውን ድርሻ ማበርከት ይችላሉ፣ ይገባቸዋልም። ይሁንና ቤተ ክርስቲያን እንደ መንፈሳዊ ተቋም የሁሉም ስለሆነች ለፖለቲካዊ አመለካከትም ይሁን ድርጅት ወገንተኝነት የላትም። የክርስትና አስተምህሮም ሁሉንም ፖለቲካዊ አመለካከቶች በአንድ መነጽር የሚመለከት እምነትን፣ ተስፋን እና ፍቅርን የሚሰብክ ነው። የክርስቲያናዊ አንድነት መሠረቶችም የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ ሥርዓትና ትውፊት አንድነት ናቸው። የቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረትም ክርስቲያኖች ከአምላካቸው ጋር የሚገናኙበት ሰገነት ነው። በቅዱሳን ጸሎት የከበረው ዐውደ ምሕረት መንፈሳዊው ጸሎትና ትምህርት ብቻ ሊከናወንበት ይገባል። ፖለቲካዊ ጉዳዮችም በተገቢ ቦታቸው ሊፈጸሙ ይገባል። ነገሮችን ያለ ዐውዳቸው በመጥቀስ፣ በማጣቀስና በማምታታት በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች መካከል ያለ የፖለቲካዊ አመለካከት ልዩነት ክርስቲያናዊ አንድነታችንን ሊፈትነው አይገባም፣ ለዚህም ሁሉም በእውቀት፣ በማስተዋልና ለሌላው በማሰብ የተመላ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል እንላለን።

 

በየቋንቋው ማ(መ)ገልገል: ሐዋርያዊነትን ከብሔርተኝነት እንለይ!

ምክንያተ ጽሕፈት

በዓለማችን ላይ ብዙ ቋንቋዎች ይነገራሉ። ቅዱስ ወንጌል ለሁሉም ይዳረስ ዘንድ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን ሐዋርያትን አሰረ ፍኖት በመከተል ሰዎች በሚናገሯቸው ቋንቋዎች ሁሉ ስታስተምር ኖራለች፣ አሁንም እያስተማረች ትገኛለች። ይህም በሐዋርያት ዘመን መንፈስ ቅዱስ በገለጠላቸው ልሳናት (ቋንቋዎች) የተፈጸመ ሲሆን በዘመናችን ደግሞ የየቋንቋውን ተናጋሪ ካህናትና አገልጋዮችን በማፍራት እንዲሁም ሌሎች አገልጋዮችም ተጨማሪ ቋንቋን ተምረው እንዲያገለግሉ በማድረግ ሊፈጸም ይችላል። ይሁንና በተለያየ ቋንቋ የማስተማር ነገር በሰፊው ሊሠራበት የሚገባ ሆኖ ሳለ አንዳንድ ወገኖች ይህ አካሄድ “ብሔርተኝነትን በማስፋት ቤተ ክርስቲያንን ይከፋፍላል” የሚል ስጋት አላቸው።

በሌላም በኩል ቤተ ክርስቲያን በአንድ ቋንቋ አገልግሎት መስጠቷ “የሌላ ብሔርን ባሕል በማስፋፋት የባሕል ወረራ እያደረሰችብን ነው” የሚሉ ወገኖች አሉ። ለእነዚህ የተቃረኑ አመለካከቶች ምንጭ ከሆኑት ነገሮች ዋነኞቹ ብሔርና ብሔርተኝነት በሚባሉት አስተሳሰቦች ላይ ያለ አለመግባባትና የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለፖለቲካዊ ዓላማ ለማስገዛት የሚደረግ እሽቅድምድም ናቸው ብለን እናምናለን። ስለሆነም እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያን የየብሔሩን (የየሀገሩን) ቋንቋ በጸጋ የገለጠበትን በዓለ ጰራቅሊጦስን በምናከብርበት ሳምንት፣ በዚህች የአስተምህሮ ጽሑፍ በየብሔሩ ቋንቋ ማስተማር/ማገልገልና ብሔርተኝነት ያላቸውን ልዩነት እንዳስሳለን።

‘ብሔር’ ምንድን ነው?

‘ብሔር’ የሚለው ቃል ‘ዓለም’ የሚለውን ትርጉም ሊይዝ ይችላል። ይህም እግዚአ-ብሔር የሚለው ቃል ‘የዓለም ጌታ’ ተብሎ በመተርጎሙ ይታወቃል። ‘ብሔረ ሕያዋን’ እና ‘ብሔረ ብፁዓን’ በመባል የሚታወቁት የስውራን ቅዱሳን መኖሪያ የሆኑት የዓለመ መሬት ክፍሎች ስያሜም ይህንኑ የሚያስረዳ ነው። ብሔር ‘ሀገር’ ተብሎ ሊተረጎምም ይችላል። ‘አይቴ ብሔራ ለጥበብ’ የሚለውን ‘የጥበብ ሀገሯ ወዴት ነው?’ እንዲል። እንዲሁም የራሱ የሆነ ቋንቋ፣ ባሕል፣ የሕዝብ አሰፋፈርና ሌሎች ማኅበራዊ እሴቶች ያለው ወገን/ማኅበረሰብ ‘ብሔር (Ethnic group)’ ይባላል። ከኖኅ ልጆች ጀምሮ፣ በባቢሎን ቋንቋ መደበላለቁን ይዞ፣ አሥራ ሁለቱን ነገደ እሥራኤል ጨምሮ፣ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ብዙ ልሳናትን መግለጡን ስንገነዘብ የብሔር ምንነትና ልዩነት መኖሩን ማንም ሊክደው የማይችልና በምድር ላይ የሚታይ ሐቅ መሆኑን እንረዳለን።

ብሔር የሚለው ቃል ለአንዳንዱ ሀገር ማለት ሲሆን፣ ለሌላው በቋንቋና በባሕል የተሳሰረ በአንድ ወይም ከዚያ በላይ ሀገራት ውስጥ የሚኖር (የግድ ራሱን የቻለ ፖለቲካዊ ድንበር ሊኖረው ይገባል የማይባል) የኅብረተሰብ ክፍል ማለት ነው። ብሔር ከሀገር ጋር የሚመሳሰልባቸው ሀገራት ያሉትን ያህል በሀገራት ውስጥ የየራሳቸው (ተወራራሽ) ባሕል፣ ቋንቋና ልዩ ልዩ ማኅበረሰባዊ አንድነቶች ያሏቸው ሕዝቦች በብዙ ሀገራት አሉ። “ብሔር የፖለቲካ ድንበርን መወሰን አለበት ወይስ የለበትም?” በሚለው ሀሳብ ላይ ፖለቲካዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ልዩነት እንዳለ ይታወቃል። ይሁንና በቋንቋና በባሕል የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በየሀገራቱ አሉ። እነዚህ ብሔሮችም የሚያመሳስሏቸው መገለጫዎች እንዳሏቸው ሁሉ፣ የሚለያዩአቸው መገለጫዎችም አሉ።

ከዚህም የተነሳ ለየራሳቸው መጠሪያና መገለጫ ያላቸው፣ በዘመናት ሂደት የዳበረ ተመሳሳይ ቋንቋና ባሕል የሚያንፀባርቁ የማኅበረሰብ ክፍሎች “ብሔር” ሊባሉ ይችላሉ፣ በተግባርም ይባላሉ። ብሔር የሰዎች ስብስብ እንደመሆኑ “ብሔር” የሚለውን ቃል “ብሔረሰብ” ከሚለው ተመሳሳይ ቃል ጋር በተለዋጭነት እንጠቀማለን። አንድ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ወንጌልን እየተማረ እንደሚያድገው ሁሉ በማኅበረሰቡ ውስጥም ቋንቋን ባሕልንና የተለያዩ የማኅበረሰቡ መገለጫ የሚሆኑ እሴቶችን እየተማረ ያድጋል፡፡ በዚህም ሰው ካደገበት ማኅበረሰብ ወይም ከትውልድ ሐረጉ የተነሳ የራሱ ‘ብሔር (ባሕልና ቋንቋ) ይኖረዋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም ብዙ የብሔር ስም ተጠቅሷል። ክርስቲያንም እንዲሁ የማኅበረሰቡ አካል ስለሆነ የራሱ ‘ብሔር’ ይኖረዋል፡፡ 

ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት!

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡ ይህም ማለት “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረትነት ላይ ታንጻችኋል (ኤፌ 2:20)” እንደተባለ የሐዋርያትን አስተምህሮና ትውፊት የምትከተል፣ ሐዋርያት ባስተማሩበት መንገድ በተለያየ ቋንቋ ወንጌልን የምትሰብክ፣ ከሐዋርያት ቀጥታ የመጣ የሢመት ሐረግ ያላት ናት ማለት ነው፡፡ አገልጋዮችም እንዲሁ አገልግሎትን የሚፈጽሙት የሐዋርያትን ፈለግ ተከትለው ስለሆነ አገልግሎታቸው ሐዋርያዊ አገልግሎት ይባላል፡፡ ሐዋርያዊነት የምንለውም ለዚህ ዓላማ መታመንንና መቆምን ነው፡፡ የሐዋርያነት ዋናው ተግባርም ለሁሉም ሰው በሚናገረው ቋንቋ የክርስቶስ ወንጌልን መስበክ ነው፡፡

በማኅበራዊና በመደበኛ መገናኛ ብዙኃን በየብሔረሰቡ ቋንቋ ማስተማር እንዳለ ሆኖ በየአካባቢው የሚተከሉ አብያተ ክርስቲያናትም ሆኑ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ተቋማት የየአካባቢውን ማኅበረሰብ ቋንቋ የሚጠቀሙና የየማኅበረሰቡን የአኗኗር ባህል የዋጁ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህ ማለት ግን በቤተ ክርስቲያን ወንጌል በሕዝቡ ቋንቋ ይሰበክ ማለት ነው እንጂ በቋንቋ በመ(ማ)ግልገል ሽፋን ከወንጌል ይልቅ ብሔርተኝነት ይሰበክ ማለት አይደለም፡፡ የተለያየ የብሔረሰብ ስብጥር ባለባቸው አካባቢዎችም አብዛኛው ማኅበረሰብ በሚረዳው ቋንቋ እያገለገሉ ቋንቋውን ለማይናገሩ ሰዎች ደግሞ የተለየ መርኃግብር ማዘጋጀት ይገባል፡፡ ከዚህ ውጭ ቤተ ክርስቲያን በአንድ ቋንቋ ብቻ አገልግሎት ትስጥ የሚል በሀሳብም ሆነ በተግባር የሚገለጥ አስተሳሰብ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በእጅጉ የሚገድብ ነው፡፡ አንዳንዶች ይህን አስተሳሰብ መያዛቸውን ሳያውቁ፣ ሌሎች ደግሞ በፖለቲካዊ ዓላማ የቤተ ክርስቲያንን በየቋንቋው የማስተማር ተልዕኮ ይቃወማሉ ወይም ለሚፈልጉት ፖለቲካዊ ዓላማ ግብዓት በሚሆን መልኩ “ከአንድ ቦታ እየተቆረሰ የሚሰጥ ምጽዋት” ያስመስሉታል።

ቤተ ክርስቲያን በየማኅበረሰቡ ቋንቋ ልታስተምር ይገባል ሲባል በመዋቅር፣ በመመሪያ እና በዕቅድ በተደገፈና ወጥነት ባለው መልኩ እንጂ አንዳንድ ጊዜ እንደምናየው የተወሰኑ ሰባክያን በሚዲያ ብቅ እያሉ በተለያየ ቋንቋ ስለሰበኩ ብቻ ወይም የተወሰኑ መምህራን አንዳንድ መጻሕፍትን በተለያየ ቋንቋ ስላሳተሙ ብቻ ቤተ ክርስቲያን በተሟላ ተቋማዊ አቅም ምዕመናንን በየቋንቋቸው እያስተማረች ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ዓለማዊ መንግሥታት እንኳን ሕዝቡ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድርና በየቋንቋዉ አገልግሎት እንዲያገኝ ባደረጉበት በዚህ ወቅት ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንን በቋንቋቸው ለማገልገል ሳትችል ስትቀር ማየት አሳዛኝ ነው፡፡ ይህ የሆነው የተለያየውን ቋንቋ የሚናገር አገልጋይ ጠፍቶ ሳይሆን በአስተዳደር ብልሽትና በዘረኝነት መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ ገና ብዙ መሥራት እንደሚቀረን ያመለክታል፡፡ ከዚህም አልፎ በአንድ ቋንቋ መገልገልን (ማገልገልን) የመንፈሳዊ አንድነት ማሳያ በማስመሰል ምድራዊ ፍላጎታቸውን በሌሎች ላይ ለመጫን የሚሯሯጡትን ማየትም ያሳፍራል።  

የቋንቋ መለያየት ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍላት አድርጎ ማሰብም ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ይልቁንስ ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍላት አንድ ቋንቋ ብቻ ለመጠቀም መሞከር ነው፡፡ አንድ ዓይነት ምድራዊ አስተሳሰብና ቋንቋ በቤተ ክርስቲያንን የበላይ ለመሆን ሲሞክር፣ ሌላው ደግሞ ‘በሥርዓት እንመራ’ በማለቱ ሲገለል ቤተ ክርስቲያን የሁሉም መሆኗ ይዘነጋና መከፋፈል ይፈጠራል፡፡ በተለይም የብሔር ብዙኅነት ባለበት ሀገር ሁሉም በቋንቋው መገልገል ይፈልጋል፣ ይገባዋልም፡፡ ምዕመናን በቋንቋቸው መገልገል እየፈለጉ ይህንን የማይፈጽም አስተዳደር ሲኖር ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን ባይተዋርነት እንዲሰማቸው ያደርጋል፣ ያልጸኑትም እየተው ይሄዳሉ፡፡ ምክንያቱም አገልግሎቱ ለእነርሱ ተደራሽ አይደለምና፡፡

በአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ከአንድ ቋንቋ በላይ ለመንፈሳዊ አገልግሎት መጠቀም የሚያመጣው ችግር የለም፡፡ በተለያዩ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በተለያየ ቋንቋ ማገልገልም እንዲሁ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ተደራሽነት ያሰፋዋል እንጂ ቤተ ክርስቲያንን አይከፋፍልም፡፡ ለምሳሌ በግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በአንድ አጥቢያ በሁለት መቅደስ በተለያየ ቋንቋ ይቀደሳል፡፡ በሁለት አጥቢያም በአንድ ጊዜ በተለያየ ቋንቋ ይቀደሳል፡፡ ምዕመናንም የተሻለ በሚሰሙት ቋንቋ የሚቀደሰው ጋር ሄደው ያስቀድሳሉ፡፡ ስብከተ ወንጌልና ሰንበት ትምህርት ቤትም እንዲሁ ነው። ይህ ቤተ ክርስቲያኗን አጠናክራት እንጂ አልከፋፈላትም፡፡ በሌሎችም አኃት አብያተ ክርስቲያናት ያለው አሠራር ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ ሐዋርያዊነት በእኛም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሊለመድ ይገባዋል፡፡

ብሔርተኝነት ፖለቲካዊ ርዕዮት ነው!

‘ብሔርተኝነት (nationalism)’ በቀጥታ ትርጉሙ ለአንድ ሀገር/ብሔር መብት መከበር መታገል፣ ለብሔር/ለዜጎች እኩልነትንና ራስን በራስ ለማስተዳደር ይችሉ ዘንድ (የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት እንዲሆኑ) የብሔረሰቡን አባላት በማደራጀት አብሮ መሥራት ነው። በዚህ ትርጉሙም ለብሔረሰቡ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ብልፅግና መቆምን ያመለክታል። ብሔርተኝነት በተለይም አንድ ሀገር/ብሔር ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች ሲጋረጡበት ተደራጅቶ ችግሮችን የሚፈታበትና በቀጣይም ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥበት ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም (Political ideology) ነው። በጥቅሉ ብሔርተኝነት ለአንድ ብሔር/ሀገር በታማኝነት መቆምን ያመለክታል፣ አጠቃላይ ዓላማውም ምድራዊ ነው።

ከፖለቲካ ሳይንስ አንጻር ሁለት አይነት ብሔርተኝነት አለ ማለት ይቻላል። እነዚህም ሀገርን፣ ዜግነትን ወይም ሕገ መንግስትን መሠረት ያደረገ “ሀገራዊ ብሔርተኝነት” (Civic nationalism) እና ቋንቋን፣ ባሕልን እና የሕዝብ አሠፋፈርን መሠረት ያደረገ “ብሔር-ተኮር ብሔርተኝነት” (Ethnic nationalism) ናቸው። ምንም እንኳ “ከዶሮና ከእንቁላል ማን ይቀድማል?” እንደሚለው ውል አልባ አመለካከት ለመበየን የሚያስቸግር ቢሆንም በግርድፉ ስንመለከተው የመጀመሪያው ሀገርን የሚያስቀድም ሲሆን ሁለተኛው ብሔርን የሚያስቀድም ነው ሊባል ይችላል። የብሔርተኝነትንም ሆነ ሌላ ዓይነት ርዕዮተ ዓለም ጥቅሙንና ጉዳቱን አመዛዝኖና ተንትኖ ለመከተል ወይም ላለመከተል መወሰን የፖለቲካ መሪዎችና የሚመሩት ማኅበረሰብ ድርሻ ነው፡፡

በመሠረታዊ አስተሳሰቡ ብሔርተኝነት ከብዙ ፖለቲካዊ ርዕዮቶች አንዱ ነው። በቅርብ ጊዜ የጽሁፍ ታሪክ ምንጭነት ከተመለከትነው ብሔርተኝነት እንደ ፖለቲካዊ ርዕዮት የተጀመረው በአውሮፓ ሲሆን ኋላ ወደ አፍሪካና ኤስያ ሀገራት ተሰራጭቷል። ማንኛውም ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም የራሱ በጎና ደካማ ጎኖች እንዳለው ሁሉ ብሔርተኝነትም የራሱ የሆኑ በጎና ደካማ ጎኖች አሉት። በተለይም በአንድ ብሔርና በሌላው መካከል ለባህል፣ ለስልጣን ወይም ለሀብት ፉክክር ባለበት ሀገር የአንዱ ብሔር መጠናከር በሌላው ዘንድ በመልካም ላይታይ ይችላል። በተጨማሪም አንዱ የራሱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት ሌላውን ሊጎዳ ይችላል። በዚህም የተነሳ ግጭቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ።

ክርስትና ምድራዊ ‘ብሔር’ የለውም፣ ራሱን የቻለ ምድራዊ ‘ብሔርም’ አይደለም። ቤተ ክርስቲያንም ለሁሉም ብሔረሰብ በእኩልነት መንፈሳዊ አገልግሎት የምትሰጥ መንፈሳዊት ተቋም ናት፡፡ ከዚህም የተነሳ የክርስትና አስተምህሮ ሁለቱንም የብሔርተኝነትን ርዕዮቶች እንደ ማንኛውም ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ሊመለከታቸው ይገባል። የክርስትና አስተምህሮ መሠረታዊ ዓላማው መንፈሳዊ/ሰማያዊ ስለሆነ አንዱን ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም የሚደግፍበት ሌላውን ደግሞ የሚቃወምበት አግባብ የለም። ይህ የመንግስት አስተዳደር እና የሚመሩት ሕዝብ ምርጫ እንጂ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት አይደለምና። ይሁንና በማንኛውም ርዕዮተ ዓለም ተፈጥሮአዊ ጠባይም ይሁን በአፈፃፀም ችግር ምክንያት በሰው ልጆች ላይ በደል ሲደርስ ቤተ ክርስቲያን በደልን በቸልታ ማለፍ የለባትም። የዚህም ዋና ዓላማው የመንግሥትን ሥርዓት (ርዕዮተ ዓለም) ለማስቀየር ሳይሆን በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው ችግር እንዲቆምና የተበደለው እንዲካስ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

‘ኦርቶዶክሳዊ ብሔርተኝነት’

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን ፈተና እንደ ምክንያት በመጠቀም “ኦርቶዶክሳዊ ብሔርተኝነት” የሚል ሀሳብን ሲያነሱ አስተውለናል። በመሠረታዊ ባሕርይው ብሔርተኝነት ፖለቲካዊ ርዕዮት እንደሆነ ከላይ ተመልክተናል። ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ እምነት ደግሞ ሰማያዊት ስለሆነች ምድራዊ የሆነው ፖለቲካዊ ፍልስፍና ሊደረትባት አይገባም። በአጭር አገላለጽ ፖለቲካዊ ርዕዮት ለክርስትና አይስማማም። የብሔርተኝነት ግብ የአንድ ‘ብሔርን’ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መብቶችን በማረጋገጥ ራሱን ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ በግልጽ በብሔር የተደራጀ የፖለቲካ ፓርቲ ዓላማ ነው። ከዚህ አንፃር የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንን በብሔርተኝነት አስተሳሰብ ለማንቀሳቀስ ማሰብም በሃይማኖት ካባ ፖለቲካን ማራመድ ነው፡፡

የኦርቶዶክሳዊ ብሔርተኝነት ዋናው መነሻ ሀሳቡ የቤተ ክርስቲያንን መብት ለማስከብር ከሆነ የሀገሪቷን ሕግ በመጠቀም ማስከበር ይገባል። ይህ የማያሰራ ከሆነ በጠራ አስተሳሰብ በግልም ይሁን በቡድን ለሁሉም ሰው ፍትህን ሊሰጥ የሚችል ፖለቲካዊ ፕሮግራም ያለው ፓርቲን በመፍጠር፣ በመደገፍ፣ ገብቶ በመሳተፍ መምረጥና/መመረጥ ይገባል እንጂ ቤተ ክርስቲያንን ተጠግቶ ፖለቲካዊ ርዕዮትን መጎተት ቤተ ክርስቲያንን ይጎዳታል፣ አንዳችም አይጠቅማትም። ስንዱ እመቤት የሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንስ ምን ጎድሎባት ነው የብሔርተኝነት ፖለቲካዊ ፍልስፍናን የምትዋሰው? በምድራዊ የብሔርተኝነት ቁርቁስ በጥላቻ ተሞልተው፣ ብሔር ተኮር ፖለቲካዊ ቅስቀሳና ቀረርቶ በማቅረብ የሚታወቁ ሰዎች ሳይቀሩ እንደ “ባጣ ቆየኝ” ስሌት ቤተ ክርስቲያን የእነርሱን “ገዥ ያጣ ፖለቲካዊ ሸቀጥ” እንድትሸከም የሚፈልጉት አዝነውላት ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንን ተጠግተው “ጠላት” ያሉትን ለመውጋት ነው። ይህ ደግሞ ሌላ በደል ነው።

ሐዋርያዊነት በብሔር አይወሰንም!

የክርስቶስ አካል የሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምድራዊ ብሔር የላትም። እግዚአብሔር የዓለም ሁሉ ጌታ ስለሆነ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንም ዓለም ዓቀፋዊትና የሁሉም ናት። በአገልግሎት ውስንነት ምክንያት በሁሉም ብሔረሰብ ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ባትስፋፋ እንኳን ቤተ ክርስቲያን የብሔር ወሰን የላትም፣ በፖለቲካዊ አስተሳሰብም ሆነ በታሪክ ትንታኔ ልዩነት አትገደብም፡፡ ዶግማዋ፣ ሥርዓቷና አስተምህሮዋ መልክአ ምድራዊም ሆነ ማኅበራዊ ድንበር የለውም። ይህን መንፈሳዊ የአስተሳሰብ ልዕልና የሚያጠፉና ቤተ ክርስቲያንን የሚያስነቅፉትን አሰራሮችና ልማዶችን ለይቶ አውቆ ማረም ያስፈልጋል። ከእነዚህም ውስጥ በተወሰነ ቋንቋ ብቻ መጠቀም፣ ካህናትን ከተወሰኑ ብሔሮች ብቻ በብዛት ማፍራት፣ የተወሰኑ ብሔሮችን ባሕላዊ፣ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መገለጫዎች ብቻ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማዘውተርና የቤተ ክርስቲያን እንደሆኑ አድርጎ ማቅረብ ቤተ ክርስቲያንን የተወሰነ ብሔር/ወገን የሆነች ሊያስመስሏት ይችላሉ።

ከውጭም ቢሆን አንዳንድ አካላት በሚያራምዱት ጽንፍ የረገጠ የብሔርተኝነት ፖለቲካ የቀድሞ ነገሥታት ወይም የቀድሞ ሥርዓቶች የፈጸሙትን ስህተት ለቤተ ክርስቲያን በመስጠት ቤተ ክርስቲያንን “የዚህ ወገን መገልገያ መሣርያ ናት” ብለው የፖለቲካ ነጥብ ሊያስቆጥሩ ይሞክራሉ። ይህ ፍጹም ስህተትና መታረም የሚያስፈልገው ነው። በተመሳሳይም ቀድሞ የነበሩት ክርስቲያን ነገሥታት የሠሩትን መልካም ነገር ሁሉ የቤተ ክርስቲያን አድርጎ ማቅረብ ቤተ ክርስቲያንን የነገሥታቱ ብቻ፣ ነገሥታቱም የቤተ ክርስቲያን ብቻ የነበሩ ያስመስልና ቤተ ክርስቲያን የተወሰነ ወገን ብቻ የነበረች ያስመስላታል። መታወቅ ያለበት እውነት ምንም እንኳን በጥንት ዘመን ቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥት የተቆራኙ የነበሩ ቢሆንም የነገሥታቱ አገዛዝና የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ግን በመሰረተ ሀሳብ የተለያየ የነበረ መሆኑ ነው። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ነገሥታቱ ለሠሩት መልካም ነገር ሁሉ የምትወደስበት፣ ለበደሉት በደል የምትወቀስበት ሁኔታ መጤን ይኖርበታል። 

የሐዋርያዊነት ዓላማ ተስፋ መንግስተ ሰማያት ናት!

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እኛስ ሀገራችን በሰማይ ያለችው ናት” (ፊልጵ 3:20) እንዳለው የእኛ ክርስቲያኖች ሀገራችን በሰማይ ነው። “ሀገራችን በሰማይ ነው” ማለት ከቁሳዊ እይታ፣ ከምድራዊ ደስታ በላይ የምንታመንለት እምነት፣ ከምንም በላይ ተስፋ የምናደርጋት መንግስተ ሰማያት አለችን ማለት እንጂ በምድር ኑሯችን ማኅበረሰባዊ ልዩነቶች የሉንም ማለት አይደለም። በተጨማሪም የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና (ገላ 3:28)” ሲል ለገላቲያ ክርስቲያኖች የጻፈው በተለያዩ ማኅበራዊ ልዩነቶች የተነሳ እንዳይከፋፈሉ ነበር። ይህ ቃል ዛሬም ሕያው ነው።  ይህች ምድር በእንግድነት የምንቆይባት፣ ነገር ግን ለማያልፈው ሕይወታችን ቁም ነገር ሠርተን የምናልፍባት ሥፍራ ናት። ሀገራችን በሰማይ፣ አምላካችንም እግዚአብሔር፣ አንድነታችንም ከቅዱሳን ጋር ነው (ፊልጵ 3:20)።

በምድር ላይ ስንኖር ከማንኛውም ብሔር ጋር ብንመደብ፣ የትኛውንም ቋንቋ ብንናገር የመጨረሻው ዓላማችን በእምነታችን ጸንተን መንግስተ ሰማያትን መውረስ ነው። መጽሐፍ በግልፅ ከሁሉም ነገድ ወደ መንግስተ ሰማያት መግባት እንደሚችል ይነግረናል። ይህም ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ (ራእይ 7:9-10) “ከዚህ በኋላ አየሁ፥ እነሆም፥ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮሁ፡- በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው፡ አሉ” በማለት ገልጾታል። በምድር ላይ ስንኖርም “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ (ሮሜ 12:18)” እንደተባልን በሥላሴ አምሳል ከተፈጠረ ሰው ጋር ሁሉ በሰላም ልንኖር ይገባናል። የቋንቋና የባህል ልዩነትም ክርስትናችንን ሳይከፋፍለው ሁሉም በቋንቋው እየተማረና እየተገለገለ ለመንግስተ እግዚአብሔር ልንበቃ ያስፈልጋል።