ራሳችንን አናታልል: ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም!

መግቢያ

በዚህ ዘመን ከገጠሙን የክርስትና ሕይወት ፈተናዎች መካከል ዋነኛው በኅሊና የሚታሰበው፣ በልብ የሚመላለሰው፣ በአንደበት የሚነገረውና በእጅ የሚተገበረው ከክርስትና አስተምህሮ ጋር እየተራራቀ መሄዱ ነው። የክርስትናን አስተምህሮ በተደጋጋሚ ሰምተነዋል፣ እንደየ አቅማችንም በተገለጠልን መጠን አውቀነዋል። ነገር ግን ኅሊናችን መልካም ነገርን ብቻ ማሰብ ሲኖርበት የጥላቻ አስተሳሰብ ሲንሸራሸርበት ይውላል። ልባችን ትህትናንና ፍቅርን ገንዘብ ማድረግ ሲገባው ትዕቢትና ንቀት ሲነግስበት ይታያል። አንደበታችን እውነትና ሕይወት የሆነውን የወንጌል ቃል ተናግሮ የሰውን መንፈሳዊ ሕይወት ማነጽ ሲገባው በስድብ፣ በውሸትና በሽንገላ ያለዚያም እውነትን ከመናገር በመቆጠብ መንፈሳዊ ሕይወታችንን ሲገዘግዘው ይስተዋላል። ሰውን ለመርዳት መዘርጋት የነበረባቸው ብዙ እጆችም ሰውን ለመጉዳት ሲዘረጉ ማየት ልብን ይሰብራል።

እነዚህ መሰል ግብዝነቶች በአሁኑ ወቅት ሀገራችንን ኢትዮጵያን ለማያባራ ችግር ካጋለጡት ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ፣ ከዚህም የከፋ መከራ እንዳይመጣ የሚከለክል ማኅበረሰባዊ ቁመናችን በእጅጉ እየተዳከመ ነው። ምንም እንኳ ለዚህ መሰሉ ችግር የመንግስትና የሌሎች ፖለቲካዊ ኃይሎች ተጠያቂነት ጉልህ ቢሆንም ችግሩም ሆነ መፍትሔው ከፖለቲካዊ ኃይሎች አቅምና ቁጥጥር ውጭ መሆኑ ግልፅ ነው። ወደ መፍትሄ የሚደረግ ጉዞ ከአስመሳይነት የተላቀቀ፣ ለእውነት የሚቆምና ራስን በማታለል በእውነት ላይ የማይሸቅጥ ማኅበረሰባዊ ስነ-ልቦና ይፈልጋል። እንደ ክርስቲያን ከበጎ ነገር ጋር ብቻ መተባበር፣ ክፉውንም ያለግብዝነት መቃወም ይኖርብናል። ስለሆነም በዚህች የአስተምህሮ ጽሑፍ እነዚህን በክርስትና ሕይወታችን ላይ የተደቀኑ አሁናዊ ፈተናዎች ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አንጻር እንዳስሳለን። ለቅዱሳን ሐዋርያት፣ ለክቡራን ሊቃውንት ጦማር ኃይልን የሰጠ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለሁላችንም ማስተዋሉን ያድለን።

ጥላቻን ከኅሊናችን እናስወግድ!

ከኅሊና የሚመነጭ ሀሳብ የማንኛውም ድርጊት መነሻ ነው። ሀሳብ የፍቅርም የጥላቻም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የክርስትና አስተምህሮ ለጥላቻ አስተሳሰብ አንዳች ቦታ አይሰጥም። የክርስትና አስተምህሮ መጀመሪያውም ማሠሪያውም ፍቅር ነው። የእግዚአብሔር ልጅ (እግዚአብሔር) ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነው ስለ ሰው ልጅ ፍቅርና ለሰው ልጅ ፍቅርን ለማስተማር ነው። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ‘ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፣ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና’ ያለው ለዚህ ነው (1ኛ ዮሐ 4:7-21)። ጌታችንም በመዋዕለ ስብከቱ ‘ከትዕዛዛት ሁሉ የትኞቹ ይበልጣሉ?’ ተብሎ ሲጠየቅ ፍቅረ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን መውደድ) እና ፍቅረ ቢፅ (ባልንጀራን መውደድ) እንደሆኑ በግልፅ ተናግሯል (ማቴ 22:37)። ሕግንና ነቢያትን የሚገልፃቸው ቃልም ‘ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን እናንተም አድርጉላቸው’ የሚለው ቃል መሆኑን አስተምሮናል (ማቴ 7:12)። ከሁሉም የሚበልጠው ፍቅሩ ግን “ነፍሱን ለወዳጁ የሚሰጥ ቢኖርም ለጠላት የሚሞት ከቶ አይገኝም” እንዳለው ራሱን ስለእኛ በመስቀል ላይ ቤዛ አድርጎ መስጠቱ ነው።

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የሚያጠነጥነው ፍቅርን በኅሊናችን እንድናኖርና ጥላቻን ከኅሊናችን እንድናርቅ በማስገንዘብ ላይ ነው። ወንድምን/እህትን በምንም ምክንያት መጥላት ተቀባይነት እንደሌለው ለማረጋገጥ ነው “እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጆች ትባሉ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ” (ማቴ 5:44) የተባልነው። ታዲያ እኛ እንኳን ጠላቶቻችንን ይቅርና ወዳጆቻችንስ በአግባቡ እንወዳለንን? አስተሳሰቡን፣ አመለካከቱንና ስነ-ምግባሩን እንኳን ጠንቅቀን የማናውቀውን ሰው በሚጠራበት ስም፣ በሚናገረው ቋንቋ፣ በተወለደበት አካባቢ፣ በሚደግፈው የፖለቲካ ቡድን ብቻ ተነስተን የምንጠላና የምናሳድድ የለንምን? የሞተውን ወንድማችንን እንኳ ከእኛ የተለየ ሀሳብ ስላለው ብቻ በጥላቻ ተሞልተን ድጋሚ መግደል ባንችል “አስከሬኑን ወይም ሀውልቱን እንዲህና እንዲያ እናድርግ” እያልን የጥላቻን ጥግ የምናንፀባርቅ የለንምን? በሃይማኖትም በባሕልም ለማይመስሉን የሌሎች ሀገራት ዜጎች ጠብ-እርግፍ እያልን የምንሰጠውን ክብር ለገዛ ወንድማችን የምንነሳ ‘የስም ክርስቲያኖች’ አይደለንምን? ይህንን ሳናደርግ ‘ክርስትና ፍቅር ነው’ እያልን በየአደባባዩ ስንለፍፍ ብንውል ከእንግዲህ ማን ይሰማናል? እኛ ከሀሳባችን የተለዩት ላይ የምናደርገውን ክፋት ሌሎች በእኛ ላይ ሲያደርጉት “የእውነት አምላክ ሆይ ፍረድ!” ብንል በፍርዱ ሐሰት የሌለበት ጌታ በሚዲያና በምድራዊ ማዕረግ ወይም በመንፈሳዊ ስልጣን ተከልለን እንደምናነሆልለው ጭፍን ተከታይ የሚታለል ይመስለናልን? ይልቁንስ በመጀመሪያ ጥላቻን ከኅሊናችን እናስወግድ! ኅሊናችንንም ለፍቅር እናስገዛ!

በሰዎች መካከል ጥላቻ እንዲነግሥ ዲያብሎስ የሚያማክራት በሚመስል መልኩ በመጥፎ ሀሳብ ስትብሰለሰል የምትውልና የምታድር ኅሊናን ይዘን ክርስቲያን ነን ማለት ራስን ማታለል ነው። ይልቁንስ ‘ምን ብናደርግ ነው በወንድሞች መካከል ያለው ፍቅር ወደላቀ ደረጃ የሚደርሰው?’ የሚለውን መልካም ሀሳብ የምታስብ ኅሊና ልትኖረን ይገባናል። ሌሎች ወገኖቻችን ሲሳካላቸው የምትከፋ፣ ሳይሳካላቸው ሲቀር ደግሞ የምትደሰት ኅሊና ካለችን ራሳችንን እንመርምር። ራሷን እየጎዳችም ቢሆን ሌላውን ወገን መቀመቅ ለመክተት የምትውተረተር ነፍስ ምንኛ የቆሸሸች ናት?! በዚህች ፈንታ ሰዎች ሲሳካላቸው አብራ የምትደሰት፣ ሳይሳካላቸው ሲቀር ደግሞ ስሜታቸውን በመረዳት በቀጣይ እንዲሳካላቸው የሚረዳ ሀሳብን የምታመነጭ ኅሊናን እንያዝ። ‘የሌሎች ኅሊና የሚያስበው ሁሉ ተንኮል ነው!’ ብላ የምትፈርጅ ኅሊና አትኑረን። ይልቁንስ የሌሎች አስተሳሰብ ከቅንነት የመነጨ ነው፣ ክፋት ቢገኝበት እንኳን ካለማወቅ የመጣ ነው ብላ የምትገነዘብና ለማስረዳት የምትጥር ኅሊና ትኑርልን። ኅሊናችንን የመልካም ሀሳብ መፍለቂያና ማብለያ እንጂ የተንኮልና የክፋት ማምረቻና ማከፋፈያ ከመሆን ይጠብቅልን!

ትዕቢትና ንቀት ከልባችን ይወገድ!

የሰውን ልጅ ሁሉ በእኩልነት ማየትና ራስን በትሁት ልብ ዝቅ ማድረግ የክርስትና መሠረታዊ መርሆዎች ናቸው። ሁሉም የሰው ልጅ በሥላሴ አምሳል የተፈጠረ ነው። በሰዎች መካከል በአፈጣጠር መበላለጥ የለም። ከዚህ አንጻር መሠረታዊው የክርስትና መርህ የሰዎችን እኩልነት ማመን ነው። ‘የእኛ ወገን ከሌላው ይበልጣል’ ብለን የምናስብ ከሆነና ለሰውነት ደረጃ የምንሰጥ ከሆነ እንኳን የክርስትናን አስተምህሮ የዓለምን ሕግ አላወቅንም። የሰው ልጅ የትም ቢወለድ፣ የትኛውንም ቋንቋ ቢናገር፣ የፈለገውን ማኅበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ አቋም ቢይዝ፣ በጫካም ይሁን በተንጣለለ ፎቅ ቢኖር፣ ወርቅ ቢለብስ ወይም ራቁቱን ቢሄድ፣ ድንጋይ ወይም ዛፍ ቢያመልክ፣ በዶማ ቢቆፍር ወይም በትራክተር ቢያርስ፣ የሀገር መሪ ወይም የከብቶች እረኛ ቢሆን፣ ቢማር ወይም ጭራሽ ባይማር በሰውነቱ እኩል ነው። ሁሉም በሥላሴ አምሳል የተፈጠረ፣ በዚህች ዓለም ሲመጣ ራቁቱን የተወለደ፣ ሲሞትም ሥጋው ወደ አፈር የሚመለስ፣ በመጨረሻው ዘመንም በእግዚአብሔር ፊት እንደ ሥራው ሊሰጠው ለፍርድ የሚቀርብ ፍጡር ነው። በምድር ላይ ስንኖር በፆታ፣ በቋንቋ፣ በዕድሜ፣ በዕውቀት፣ በአመለካከት፣ በሃይማኖት፣ በጉልበት፣ በሥልጣን፣ በሥልጣኔ፣ በሀብት፣ በመኖሪያ ቦታ ብንለያይም ሁላችንም እኩል ሰዎች ነን።

ትዕቢት ራስን የበላይ አድርጎ የመመልከትና ሌሎችን ዝቅ አድርጎ የማየት ልክፍት ናት። ከትዕቢት ሁሉ አስቀያሚዋ “ጊዜ ሰጠን” ብለን የሀሳብ ተቀናቃኞቻችንን በሀሰት እያሸማቀቅን “እነርሱ ካልጠፉ ሰላም አይኖረንም” የምትል የሀሳብ ልምሾ ያጠቃቸው ደካሞች ሾተል ናት። እርሷም የውድቀት ሁሉ የመጀመሪያ እርምጃ ናት። ሳጥናኤል ከክብሩ ለመውረድና ለመዋረድ ሲጀምር በትዕቢት ነበር (ኢሳ  14:12)። በትዕቢት የጀመረውን የውርደት ጉዞ በውድቀት ፈፅሞታል። የፈርዖን ከልክ ያለፈ ትዕቢትም በኤርትራ ባሕር ከመስጠም ውጭ ያተረፈለት አንዳች ነገር አልነበረም። የጎልያድ ትዕቢትም እንዲሁ በአንዲት ጠጠር ፍጻሜውን አግኝቷል። በተለይም በጎ አሳቢ መስላ በሌሎች ላይ መዓትን የምትጠራ አንደበት ሰውን እንጂ እግዚአብሔርን ማታለል አትችልም። ለእያንዳንዷ የግፍ ንግግራችንና ተግባራችን ከእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ እንከፍልባታለን። በዚህ ምክንያት ነው ትዕቢት የውድቀት የመጀመሪያ ምዕራፍ ነው የምንለው። ትዕቢት የምንይዘው እሴት ሳይሆን ታግለን የምናሸንፈው ፈተና መሆኑን ሲያስተምረን ነው ጌታችንም በገዳመ ቆሮንቶስ ድል ካደረጋቸው ሦስት ፈተናዎች አንዱ ያደረገው። (ማቴ 4:1)

በጥበብ የተመላች ትህትና ግን የብልህነት ውጤትና የሰው ልጅ መንፈሳዊ ሕይወት ዕድገት የመጀመሪያ ምዕራፍ ናት። ስለዚህ ነው ጌታችን እርሱ ከሁሉ በላይና የሁሉ ፈጣሪ ሲሆን ራሱን ዝቅ አድርጎ በፍጹም ትህትና በበረት የተወለደው (ሉቃ 2:10)፣ የሰማያውያን ሠራዊት ጌታ ሲሆን በሄሮድስ ሠራዊት ወደ ግብፅ የተሰደደው (ማቴ 2:13)፣ በተናቀችው ናዝሬት ያደገው (ዮሐ 1:47)፣ የደቀ መዛሙርቱን እግር ዝቅ ብሎ ያጠበው (ዮሐ 13:1)፣ ፈጣሪ ሲሆን በፍጡር እጅ የተጠመቀው (ማቴ 3:15)። ፈራጅ ሲሆን በጲላጦስ ፊት ለፍርድ የቀረበው። መላእክቱን ልኮ ሰዎችን ከመከራ የሚያድን ሆኖ ሳለ እርሱ ሰው ሆኖ በመስቀል ላይ መከራን የተቀበለው። ትህትናን በቃልና በተግባር ለማስተማር መጥቷልና “ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደግ ይዋረዳል፣ ራሱን ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ከፍ ከፍ ይላል” (ሉቃ 14:11) በማለት ያስተማረውም ለዚሁ ነው። ይህች ትህትና ራስን ዝቅ በማድረግ ከሁሉም ጋር በጥበብ የምታኖር ምሥጢር ናት።  ይህች ትህትና በጥበብ ላይ የተመሠረተችና የትዕቢተኞችን የሞኝነት ትምክህት የምትንድ እንጂ በድክመትና በድንዙዝ አስተሳሰብ የበታችነትን ተቀብላ ለትዕቢተኞች ክፉ ሀሳብ ተገዢ ልትሆን አይገባም።

በልባችን ‘እኔ ታላቅ ነኝ፣ እኔ ኃያል ነኝ፣ እኔ አዋቂ ነኝ፣ እኔ ብልህ ነኝ፣ እኔ ባለሥልጣን ነኝ፣ እኔ ውብ ነኝ፣ እኔ ባለሀብት ነኝ፣ እኔ መንፈሳዊ ነኝ፣ እኔ ስልጡን ነኝ ወዘተ’ በማለት ራሳችንን ከሌላው ሰው ከፍ ባለች ማዕረግ ላይ ማስቀመጥ የውድቀታችን መጀመሪያ መሆኗን እናስተውል። ይልቁንስ እኛ ከሌላው መካከል እንደ አንዱ መሆናችንን እንቀበል። እኛ የተለየን መሆናችንን ለማሳየትና አድናቆትን ለማትረፍ አንድከም።  ይልቁንም እኛ አንድ የተለየ ነገር ቢኖረን እንኳን ሌላው ቢያንስ እንደ እኛ የራሱ የተለየ ነገር እንዳለው እናስተውል። ሌሎች በከፍታ አስቀምጠውን ወደላይ አሻቅበው እንዲያዩን፣ እኛም በከፍታ ተቀምጠን ሁሉንም ቁልቁል ለማየት አንመኝ። ይህ ሳጥናኤል ከመጨረሻው የፍጡራን ልዕልና ወደ መጨረሻው የፍጡራን ውርደት የወደቀበት ነውና። ይልቁንም ለሌሎች ከልባችን ክብርን በመስጠት ዝቅ ብለን በትህትና እናገልግላቸው። ያን ጊዜ ከፍ ከፍ እንላለን።

የስድብ ቃል ከአንደበታችን ይራቅ!

ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ እንደተናገረው አንደበት እሳት ነው (ያዕ 3:1)። እሳት በአግባቡ ካልተያዘ ሀገርን ያቃጥላል፣ ዓለምንም ወደ አመድነት ሊቀይራት ይችላል። እሳት በአግባቡ ስንጠቀምበት ደግሞ ምግብ ያበስልልናል፣ ለሰውነታችን ሙቀትን በመስጠት ብርድን ያስወግድልናል፣ ነበልባሉም በጨለማ ብርሃን ይሆንልናል። አንደበትም እንዲሁ ነው። የምንናገረውን ካልመረጥን ንግግራችን ጥፋትን ያስከትላል። መርጠንና መጥነን ስንናገር ሰውን፣ ማኅበረሰብንና ሀገርን እንገነባለን። ስለዚህ አንደበታችን ለእኛ የሚጠቅመንን ብቻ ሳይሆን ለሚሰማን ሰው የሚጠቅመውን ነገር ጭምር ልትናገር ይገባታል።

የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ከሚያክል ጌታ ገነትን ከምታክል ቦታ ተለይቶ ወደ ምድረ ፋይድ የተጣለው ዲያብሎስ ካደረባት እባብ አንደበት የወጣውን ቃል ሰምቶ ነው እንጂ ዲያብሎስ እጁን ይዞ ዕፀ በለስን አላስቆረጠውም፣ ቆርጦም አላጎረሰውም። በእባብ አንደበት “ዕፀ በለስን ብትበሉ ሞትን አትሞቱም፣ ይልቁንም አምላክ ትሆናላችሁ” (ዘፍ 3:4) ብሎ ምክር በመስጠት ብቻ አሳሳተው እንጂ። ዛሬም ብዙዎችን በወንድም እህቶቻቸው ላይ በጭካኔ የሚያነሳሳቸው፣  ከእውነተኛ የሃይማኖት መንገድ የሚያስወጣቸው፣ ከጽድቅ ይልቅ ኃጢአትን የሚያሠራቸው ከአንደበት የሚወጣው ክፉ ቃል ነው። ስለዚህም ነው ጌታችን “ከአፍ የሚወጣው እንጂ ወደ አፍ የሚገባው ሰውን አያረክሰውም (ማቴ 15:1)” በማለት ያስተማረው። ከአንደበት የሚወጣው ክፉ ንግግር ተናጋሪውንም ሰሚውንም የማርከስ አቅም አለው። ከዚህ በተቃራኒውም የሰው ልጅ የወንጌልን ቃል የተቀበለውና የሚቀበለው ከአንደበት በሚወጣው ቃል (ስብከት) ነው። ጌታችን በምድር ላይ ሐዋርያትን የጠራቸው፣ ያስተማራቸውም በአንደበቱ ነው። ቅዱሳን ሐዋርያትም ክርስትናን ወደ ዓለም ያዳረሱት በአንደበታቸው በመስበክ ነው። በየዘመናቱ የነበሩ ቅዱሳን ሁሉ ለጽድቅ የበቁት የእግዚአብሔርን ወንጌል በጆሮአቸው ሰምተው፣ በልባቸው አምነው፣ በአንደበታቸው መስክረው ነው። ሰውና እግዚአብሔር የሚገናኙባት ጸሎትም የምትደረገው (እግዚአብሔር የልብን ቢያውቅም) በአንደበት በመናገር ነው።

ከአንደበታችን ምስጋናና መልካም ነገር እንጂ የስድብ ቃል ሊወጣ አይገባም። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብ በስድብ ፈንታ አትመልሱ፣ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፣ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና” (1ኛ ጴጥ 4:9) እንዳለው አንደበታችን እውነተኛ እምነትን፣ ፍቅርና ተስፋን የምትሰብክ ልትሆን ይገባል። ወንድሙን የሚሳደብ በሰማይም በምድርም ፍርድ እንደሚገባው የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል (ማቴ 5:22)። በዘመናችን ግን ከወንድሞቻችንም አልፎ አባቶቻችን በአደባባይ በዱርየ ቋንቋ ሲሰደቡ እያየን ነው። የሚያሳዝነው በፖለቲካ አቋም የሚመስሏቸውን በሃይማኖት ግን ምንፍቅናቸው የታወቀውን ‘አገልጋዮች’ እያሞገሱ፣ በሃይማኖት አቋም የማይለዩትን በፖለቲካ አስተሳሰብ የተለዩትን አባቶች እጅግ በወረደ ጸያፍ ቋንቋና በውሸት ስማቸውን የሚያጠፉ፣ ራሳቸውን ግን “ታላላቅ” እንደሆኑ የሚቆጥሩ መንፈሳውያን አገልጋዮች ለምዳቸውን እየገፈፉ ያለሀፍረት መገለጣቸው ነው። ይህም የክርስትና ሕይወታችን ምን ያህል እየተጎዳ እንደመጣ ያመለክታል። በዓለማዊ አስተሳሰብ እንኳን ቢሆን አንደበታችን ሰላምን፣ እኩልነትን፣ ፍትሕን፣ ዕድገት፣ ብልጽግናን የምትሰብክ መሆን ይጠበቅባታል። ሲቻል በግልፅ ሳይቻል በአሽሙር የሰውን ልጅ በጅምላም ይሁን በተናጥል በተወሰነ ሳጥን ውስጥ እያስገባች የምትፈርጅ አንደበትን እናርቅ። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “ልጆቼ ሆይ:- በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ” (1ኛ ዮሐ 3:18) ብሎ እንዳስተማረው የሽንገላ ፍቅርን ከልባችን እና ከአንደበታችን እናስወግድ። እኔ የምናገረው ብቻ እውነት፣ እኔ የምናገረው ብቻ አዋጭ፣ ሌሎች የሚናገሩት አፍራሽ ነው ብላ የምትናገር አንደበትም ትታረም።

በፍጹም ትዕቢት ‘አንተ የተመረጥክ ዘር ነህ፣ ከሌላው ጋር ለመሥራት አትውረድ’ እያለች በሰዎች መካከል የሰውነት ደረጃን የምትሰብክ አንደበት አታስፈልገንም። ይልቁንስ ሁላችንም ወንድማማቾች/እህትማማቾች ነን፣ አብረን እንኑር እያለች ፍቅርን የምትሰብክ አንደበት ትለምልምን። ወንድም ወንድሙን እንዲጠላ፣ ወንድም ከወንድሙ እንዲጣላ በሐሰት የምትሠራ አንደበት አትኑረን። ይልቁንስ ወንድማማቾች እንዲተባበሩ ፍቅርን የምትሰብክ አንደበት ትኑረን እንጂ። በኢንተርኔት መስኮት ብቅ ብላ ‘እገሌ የሚባል ወገን በድሎሃል፣ ገድሎሃል፣ ሰብሮሃል፣ አሁንም ተገዢ ሊያደርግህ ነውና ተባብረህ ስበረው፣ በለው፣ ግደለው’ እያለች በሰዎች መካከል መገዳደልን የምትሰብክ አንደበት አትኑር። መቶ አመታትን ወደኋላ ተጉዛ በእውነትም ሆነ በሐሰት የተደረተ የታሪክ ምራጭን ለማጋጨት የምትጠቀም አንደበት አትኑረን። እንዲሁም “ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ አንይ” በሚል ምክንያታዊ ትንታኔ ታጅባ የሌሎችን የታሪክ ምልከታ የምትወቅስ ለራሷ ሲሆን ግን ምዕተ ዓመታትን ወይም አስርት ዓመታትን ወደ ኋላ ተጉዛ የሚጠቅማት የመሰላትን የእውነትም ሆነ የፈጠራ ታሪክ ለመሰብሰብ የምትሮጥ አንደበት አትኑር።

በምድራዊ አመለካከትም ቢሆን የአንዱን አመለካከት ርኩስ የሌላውን ቅዱስ፣ የአንዱን የሰይጣን የሌላውን የመልአክ፣ ያንዱ እንጦሮጦስ መግባት ያለበት የሌላው ወደ ቤተ መንግስት መግባት ያለበት አድርጋ ለምትናገር አንደበት ማስተዋልን ይስጥልን። የተለየ ሀሳብ የሚያነሳን ወገን ፀረ-ሰላም፣ ፀረ-ሀገር፣ ፀረ-ልማት፣ ፀረ-ኦርቶዶክስ፣ ፀረ-ሙስሊም፣ ፀረ-ሕዝብ ወዘተ እያለች በመፈረጅ ምክንያታዊ ተዋስኦን ለምትዘጋ አንደበት ማስተዋልን ይስጥልን። ይልቁንም የሁሉንም አመለካከት በማክበር ኑ እንመካከር፣ እንነጋገር፣ ሀሳቦችን እንሞግት፣ ለሁላችንም የሚበጀውን እንያዝ የምትል አንደበት ትስፋፋ! ‘እነርሱ ይጥፉ እኛ እንስፋ’ የምትል ፀረ-ሰው አንደበት አታስፈልገንም። ይልቁንስ ‘እኛ እና እነርሱ’ ሳይሆን ሁሉም እንዲሰፋ የምትሰብክ አንደበት ትብዛ።

አንዱ ወገን ሲበድል ምንም እንዳልሰማ ጆሮ ዳባ ልበስ ብላ፣ አንዳንዴም አሞግሳ፣ ሌላው ሲበድል ግን ሀገር ይያዝልኝ ብላ እሪሪሪ የምትል አንደበት ፍትሐዊነት የጎደላት ስለሆነች ትታረም። አንዱ ወገን ላይ መከራ ሲደርስበት በግልፅ በመናገር፣ በደስታ በመጨፈር ወይም በልቧ ‘እሰይ፣ እንኳን፣ ይበለው፣ የእጁ ነው’ እያለች ሌላው ወገን በተራው ተመሳሳይ መከራ ሲደርስበት ደግሞ ዋይ ዋይ በማለት አጥፊዎችንም ንፁሐንንም ይጥፉ የምትል አንደበት በክርስትና መዶሻ ተስተካክላ ሁሉንም በእኩልነት ትመልከት። አንዱ ወንድም ወይም እህት በአንዲት ሀሳብ ብቻ ስለተለየ እንመካከር፣ እነጋገር፣ እንወያይና የተሻለውን እንያዝ ከማለት ይልቅ “ይታሰር፣ ይገረፍ፣ ይሰቀል!” እያለች ያለ ፍትሕ በሰው ላይ የምትፈርድ አንደበት በክርስትና አስተምህሮ ትታረቅ! ያለ አንዳች ገደብ ሌላውን ወገን በመናቅና በመሳደብ ለምዕመናንና ለቤተ ክርስቲያን ጥላቻን የምታተርፍ፣ በቀለኛውም ወገን በአስመሳይ አንደበተኞች ጥፋት ተነስቶ በንፁሐን ምዕመናንና በቤተ ክርስቲያን ላይ ጥቃት እንዲፈጽም ምክንያት የምትሆን አንደበት ከዚህ ድርጊቷ ትታቀብ።

እጆቻችን ለመጉዳት ሳይሆን ለመርዳት ይዘርጉ!

እጆቻችን እርዳታን የሚሻ ሰውን ለመርዳት ሊዘረጉ ይገባል። የሰውን ንብረት ለመውሰድ ሳይሆን የእኛን ለተቸገረ ሰው ለመስጠት ሊዘረጉ ይገባል። ያለውን በመስጠት እንጂ የሌላውን በመውሰድ የተጠቀመ የለምና። የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችም በሰው ላይ ለማትረፍ፣ ገንኖ ለመታየት፣ ሳይሆን የሰውን ሕይወት ለማትረፍ ሊተጉ ይገባል። ከእውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን የጠፉትንም ቢሆን የፍቅርን እጅ በመዘርጋት መፈለግ ይገባል እንጂ የጠብና የክርክርን ሰይፍ በመምዘዝ በማሳደድ መመለስ እንደማይቻል የታወቀ ነው። ክርስቶስ የጠፋውን አዳም በፍቅር እንደፈለገው ማስተዋል ይገባናል። በቤተ ክርስቲያን ያሉትን ለማስወጣት ሳይሆን የወጡትን ለመመለስ እጃችን ይዘርጋ። ያን ጊዜ ክርስቶስ ይሰማናል።

ሰዎች ብዙ ደክመው ያፈሩትን ንብረት ለማጥፋት የምትዘረጋ እጅ አትኑር። ይልቁንስ ሰዎች ደክመው ያፈሩትን የምትጠብቅና በዚያም ላይ ሠርታ የምትጨምር እጅ ትዘርጋ። የሰው አካል ላይ ጉዳትን ለማድረስ የምትዘረጋ ክፉ እጅ አትኑር። ይልቁንስ እንደ ደጉ ሳምራዊ የተጎዳውን ለማከም መልካም እጆች ሁሉ ይዘርጉ እንጂ። ሰዎች ተወልደው ካደጉበት፣ ለወግ ለማዕረግ ከበቁበት፣ ወልደው ከከበዱበት ቤታቸውና ሠፈራቸው ለማፈናቀል የምትዘረጋ እጅ አትኑር። ይልቁንስ ማደሪያ ማረፊያ ለሌላቸው ወገኖች መኖሪያን ለመሥራት እጆች ሁሉ ይዘርጉ እንጂ። የመገፋትን፣ የመበዝበዝንና የመፈናቀልን ክፉነት ለመረዳት በየግላችን እስኪደርስ አንጠብቅ። የራሳችን በምንለው ወገን ላይ የደረሰው ወይም የሚደርሰው መሰል በደል እንደሚያመን “የእኛ” የምንለው ወገን በሌሎች ላይ መሰል በደል ሲያደርስ ብንችል እናስቁመው፣ ቢያንስ ግን አንተባበረው፣ ለጥቅማችን አንሸፋፍነው። ለተበደሉት ካልቆምንላቸው፣ በተለይም በጉዳታቸው ከተባበርን፣ ከተሳለቅን እንዴት በመከራችን ወቅት አምላካችንን “አቤቱ የደረሰብንን እይ!” ማለት እንችላለን?!

የጦር መሣሪያን በወገን ላይ ለማንሳት የምትጣደፍ እጅ አትበርታ። በተለይም ገዳይነትን “ባሕል” አድርጋ የምታንቆለጳጵስ አላዋቂነት ከእኛ የተለየች ትሁን።  ይልቁንስ ለልማት ሥራ የሚውሉ የተለያዩ መሣሪያዎችን የምታነሳ እጅ ትበርታ። ለእግዚአብሔር ምስጋናን ለማቅረብ የዜማ መሣርያን የምታነሳ እጅም ትጠንክር። ጸሎትና ልመናን ለማቅረብ ወደ እግዚአብሔር የምትዘረጋ እጅም መሻቷን ታግኝ። ከዚህም በላይ ሰውን ለመባረክ፣ አጋንንትን ለማንበርከክ የክርስቶስን መስቀል የምታነሳ የካህናት እጅ ትጽና። በደለኞችን ለማበረታታት፣ ንፁሐንን በሐሰት ለመርገም የከበረውን የክርስቶስ መስቀል በሽንገላ የሚያነሱ ፍኖተ በለዓምን የተከተሉ ነቢያተ ሐሰት (የሀሰት ካህናት) እጆች ከአህዮቻቸው ይማሩ። የካህናት እጆች በረከትን ለማውረስ እንጂ ከጥላቻ ፖለቲከኞች ጎን ተሰልፈው “የግፋ በለው” መፈክር አንጋቢዎች መሆን የለባቸውም። እጆች ለሰው ልጅ የተሰጡት የሚጠቅምና እግዚአብሔርን የሚያስደስት ሥራን ለማከናወን ነውና።

የሰውን ልጅ እርስ በእርስ እንዲጋጭ ወይም ሰውን ወደ ኃጢአት የሚመራን ጽሑፍ የሚጽፉ እጆች ይህንን ትተው ለሕዝብና ለሀገር የሚጠቅም፣ ሰውን ከሰው የሚያቀራርብ፣ ሰውን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ ጽሑፍን ለመጻፍ ይትጉ። የተዛባ ትርክትን እየጻፉ ለትውልድ ጥላቻን ከማትረፍ እውነተኛውን ታሪክ ጽፈው የሰውን አዕምሮ ለማነጽ ይትጉ። አንዱን ወገን የሚያንቋሽሽና የሚያሳንስ፣ ሌላውን ብቻ የሚያኩራራና የሚኮፍስ ጽሑፍን የሚጽፉ እጆች ክብር ለሚገባው ክብርን ሰጥተው ፍቅርን ለማፅናት ይጽፉ ዘንድ እንጸልይ። ለትውልድ የሚተርፍ ዕውቀትንና ጥበብን በጽሑፍና በስዕል ማስቀረት የሚችሉ እጆች ከዚህ በተቃራኒ ለድንቁርናና ለተንኮል የሚዳርግን ጽሑፍ እየጻፉ ለትውልድ የሚተርፍ ጠባሳን እንዳያስተላልፉ እንጸልይ። መጸለይም ብቻ ያይደለ የበኩላችንን ድርሻም እናበርክት።

ማጠቃለያ

ጥላቻን በኅሊናችን ይዘን፣ ትዕቢትና ንቀትን በልባችን አኑረን፣ አንደበታችን ስድብን እያፈለቀና እጆቻችን ሰውን ለመጉዳት ያለመከልከል እየተዘረጉ ፍቅር በእኛ ዘንድ አለ ብንል ራሳችንን እናታልላለን፣ እግዚአብሔርም ያዝንብናል። በመርህ ሳይሆን በወገንተኝነት እየመረጥን የምናሞግስና፣ እየመረጥን የምናወግዝ ከሆንንም ፍትሐዊነት በእኛ ዘንድ የለችም። እውነትን እየሸሸግንና በሐሰት መነገድን እንደ ስልት እየቆጠርን ራሳችንን የእውነት ጠበቃ አድርገን ብናቀርብ ድንጋዮች ሳይቀሩ ይታዘቡናል። መስደብንና ማሸማቀቅን አፋችን ገንዘብ ካደረገው በምን አንደበታችን ጸሎትን እናቀርባለን? መጽሐፍ “ከእንግዲህ ወዴት እንደወደቅህ አስብ፣ ፈጥነህም ንስሐ ግባ፣ ያለዚያ እመጣብሃለሁ (ራዕይ 2:16)” እንዳለ በደላችንንና ኃጢአታችንን አምነን ንስሐ እንግባ። በፍትሕና በእውነት ሳይሆን በወገንተኝነት ተይዘን “አገልጋዮች” እየተባባልን “ጠላት” ያልነውን ወገን ለማጥፋት በአንደበት ስንዘላብድ፣ በተግባር እኩይ አስተሳሰብን ስናራምድ እየዋልን ስለ ፍቅር ብንደሰኩር ሰው የፍቅር ትርጉም እንዲጠፋበት እናደርግ እንደሆን እንጂ ቅድመ እግዚአብሔር የሚደርስ ጸሎት የለንም። ስለሆነም ፍቅራችን ያለ ግብዝነት ይሁን፣ ክፉውን እንጸየፍ፣ ከበጎ ጋር እንተባበር (ሮሜ 12:9)። ፍቅርን ገንዘብ ሳናደርግ እግዚአብሔርን እናውቀዋለን ብንል ራሳችንን እናስታለን። ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅምና።

ኢታርዕየነ እግዚኦ ሙስናሃ ለቤተ ክርስቲያን!

ስብሃት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን።

በሥራ መትጋት: ሊሠራ የማይወድ አይብላ!

መጽሐፍ ቅዱስ ገና ሲጀምር “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ (ዘፍ 1:1)” በማለት የእግዚአብሔርን ሥራ ይናገራል። በዕቅዱ መሠረት ለስድስት ቀናት ከፈጠረ በኋላ  “እግዚአብሔርም የሠራውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ፈጸመ፤ በሰባተኛውም ቀን ከሠራው ሥራ ሁሉ ዐረፈ (ዘፍ 2:2)” እንደተባለ ሥራውን ሲፈጽም ዐርፏል። ጌታችንም “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ (ዮሐ 5:16)” ብሎ እንዳስተማረን እግዚአብሔር ድንቅ ነገርን ሲሠራ ይኖራል። በሥራ አንቀፅ የጀመረው መጽሐፍ ቅዱስ “እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ (ራዕ 22:12)” በማለት በመጨረሻው ቀን እግዚአብሔር ለሁሉም እንደ ሥራው ሊሰጠው እንደሚመጣ አበክሮ በመግለጽ መልእክቱን ያጠቃላል። ይሁንና በአንዳንድ ኦርቶዶክሳዊያን ዘንድ ለሥራ ያለው አመላካከት ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ጋር የማይስማማና ወገኖቻችንንም ለድህነት የሚዳርግ ነው፡፡ በዚህች የአስተምህሮ ጽሑፍ ሥራን የሚመለከተውን አስተምህሮ ቅዱሳት መጻሕፍትን ዋቢ በማድረግ እንዳስሳለን፡፡

ሰው የተፈጠረው ለሥራ ነው!

የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ዓላማ ዋነኛው ሥራን ለመሥራት ነው። እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከፈጠረ በኋላ “እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው። ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው (ዘፍ 1:28)” ብሎ እንዳዘዘው የሰው ልጅ ለሥራ ነው የተፈጠረው። በዓለም የተፈጠረውን ሁሉ መግዛት (ማስተዳደር)  ለሰው ልጅ የተሰጠው የሥራ ድርሻ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከፈጠረው በኋላ ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔደን ገነት ያኖረውም (ዘፍ 2:15) ለሥራ መሆኑን ማስተዋል ይገባል። የሰው ልጅ ዕፀ በለስን በልቶ ከተሳሳተ በኋላ ግን ሥራ እንዲከብድበት ሆኗል። “አዳምንም አለው። የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህእሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ።ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህና (ዘፍ 3:17-19)” እንደተባለ በሥራ ደክሞ የላቡን ዋጋ እንዲበላ ተፈርዶበታል። በክርስቶስ ቤዛነት ወደ ቀደመው ክብሩ ቢመለስም በምድር ላይ እስካለ ድረስ ግን እየሠራ ይኖራል።

ሥራ የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ነው!

ሥራን መሥራት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ትዕዛዛት መካከል አንዱ ነው። “ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤ ስድስት ቀን ትሠራለህ፥ በሰባተኛውም ቀን ታርፋለህ፤ በምታርስበትና በምታጭድበት ዘመን ታርፋለህ (ዘፍ 20:9 34:21)” እንዳለው የሰው ልጅ ስድስቱን ቀን ሠርቶ በሰባተኛው ቀን ሰንበትን ሊያከብር ይገባል። “ሰንበትን አክብር” የሚለውም ሰው በሰንበት ቀን በተለየ ሁኔታ ምስጋናን እንዲያቀርብና ትሩፋትን እንዲሰራባት እንጂ ተቀምጦ ወይም ተኝቶ እንዲውል አለመሆኑን ልብ ማለት ይገባል። የበዓል ቀናትም እንዲሁ መንፈሳዊ ሥራ የሚከናወንባቸው ናቸው፡፡ የበዓል ቀናት ማኅሌት፣ ኪዳን፣ ቅዳሴና የመሳሰሉት መንፈሳዊ አገልግሎቶች የሚከናወኑባቸው፣ እኛም ምስጋናን የምናቀርብበት፣ ወገኖቻችንን የምንጎበኝባቸው (የምናስብባቸው) እንጂ ሳንሠራ የምንውልባቸው የዕረፍት ቀናት አይደሉም፡፡

ይህንን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በማክበር በገዳም ያሉ አባቶችና እናቶች ከጸሎት ሰዓት በስተቀር ሙሉ ጊዜያቸውን በሥራ ተጠምደው ያሳልፋሉ፡፡ ይህም ትጋታቸው ገዳማቸውን ከመጥቀሙ ባሻገር የመንፈሳዊ ትጋታቸው አንዱ አካል መሆኑን የቅዱሳን ገድላትና በዘመናችን የምናውቃቸው ደገኛ ገዳማውያን ተጋድሎ ይመሰክራሉ፡፡ በገጠሪቱ የሀገራችን ክፍል ያሉ ካህናትም እንዲሁ የቤተ መቅደሱን አገልግሎት ከሚፈጽሙበት ሰዓት ውጭ ያለውን ጊዜ የግብርና ሥራቸውን በመሥራት ይተጋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ትጋት አንዳንድ በከተማዎች ለሚኖሩ ካህናትና አገልጋዮችም ትምህርት ሊሆናቸው ይገባል፡፡ ልበ አምላክ የተባለ ንጉስ ዳዊት “የድካምህንም ፍሬ ትመገባለህ፤ ምስጉን ነህ መልካምም ይሆንልሃል (መዝ 128:2)” እንዳለው ሁሉም መልካም እንዲሆንልን በሥራ ልንተጋ ይገባናል፡፡ በከተማና በውጭ ሀገራት ባሉ አጥቢያዎች መንፈሳዊ አገልግሎት ቁሳዊ ከሆነባቸው፣ አብያተ ክርስቲያናትም የግለሰቦችና የቡድኖች መነታረኪያ ከሆኑባቸው ምክንያቶች አንዱ ከስራ ይልቅ በአሉባልታ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ምንደኛ ሰዎች አገልግሎትን እንደ ተራ ስራ መያዛቸውና በጥቅም መነፅር መመልከታቸው መሆኑን መታዘብ ይቻላል።

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ “ደግሞ ከእናንተ ጋር ሳለን:- ሊሠራ የማይወድ አይብላ ብለን አዘናችሁ ነበርና:- ሥራ ከቶ ሳይሠሩ፥ በሰው ነገር እየገቡ፥ ያለ ሥርዓት ከእናንተ ዘንድ ስለሚሄዱ ስለ አንዳንዶች ሰምተናልና (ተሰሎ 3:10)” በማለት ሥራን የማይወዱትንና በማያገባቸው ነገር የሚገቡትን ገስጿቸዋል፡፡ ‘ሊሠራ የማይወድ አይብላ’ የሚል ታላቅ ትዕዛዝንም አስተላልፎ ነበር፡፡ ሰው የተፈጠረው ለመሥራት ነውና ሊሠራ የማይወድ ሰው አይብላ አለ፡፡ ሰው ሠርቶ የላቡን ዋጋ እንዲበላ ተፈርዶበታልና ሊሠራ የማይወድ አይብላ ማለቱም ለዚህ ነው፡፡ ነገር ግን ሐዋርያው የሰጣቸው ትዕዛዝ ‘የማይሠራ አይብላ’ ሳይሆን ‘ሊሠራ የማይወድ አይብላ’ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰዎች መሥራት እየፈለጉ ነገር ግን መሥራት የማይችሉባቸው የተለያዩ ሁኔታዎች አሉና ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች መሥራት እየወደዱ/እየፈለጉ መሥራት ባለመቻላቸው ልንረዳቸው ይገባል እንጂ አይሠሩም ተብለው ሊገለሉ አይገባም፡፡

ለመልካም ሥራ እንትጋ!

ሥራን ለመሥራት የተፈጠረው የሰው ልጅ ሥራውን ተግቶ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች በሥራ መትጋት እንዳለባቸው ሲያስተምር “ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት (ገላ 6:9)” በማለት ነበር ያሳሰባቸው፡፡ በሮሜ ይኖሩ ለነበሩ ክርስቲያኖችም በጻፈው መልእክቱ “ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ (ሮሜ 12:11)” በማለት በሥራ እንዳይለግሙ ጽፎላቸዋል፡፡ በሥራ መለገም፣ በሥራም የተነሳ ማንጎራጎር የሚያስነቅፍ ተግባር ነውና ስለዚህም ለፊልጵስዮስ ሰዎች ሲጽፍ “በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ (ፊልጵ 2:14)” በማለት አስተምሯቸዋል፡፡

ይኸው የተወደደና ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን የሚባለው ሐዋርያ ለደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስም በምድር ላይ ያለውን አገልግሎትና ሥራ በትግል መስሎ ሲያስተምረው “ደግሞም በጨዋታ የሚታገል ማንም ቢሆን፥ እንደሚገባ አድርጎ ባይታገል፥ የድሉን አክሊል አያገኝም። የሚደክመው ገበሬ ፍሬውን ከሚበሉት መጀመሪያ እንዲሆን ይገባዋል (2 ጢሞ 2:6-7)” በማለት የሰው ልጅ በተሰማራበት ዘርፍ ጸንቶ መታገል (መሥራት) እንዳለበት በአጽንኦት መክሮታል፡፡ ራሱም በሰው ላይ ላለመክበድ እየሠራና እየደከመ ይኖር እንደነበር ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች “በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን፤ ሲሰድቡን እንመርቃለን፥ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፥ ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን (1 ቆሮ 4:12-13)” በማለት ምሳሌ ሆኗቸዋል፡፡ ይህ አምደ ቤተ ክርስቲያን የተባለ ሐዋርያ ወንጌልን ከመስበክ ጎን ለጎን ድንኳን ይሰፋ እንደነበር ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ (ሐዋ 18፡1-4)፡፡

ስለዚህም ሲናገር “እነዚህ እጆቼ በሚያስፈልገኝ ነገር ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት እንዳገለገሉ እናንተ ታውቃላችሁ” (ሐዋ 20፡33-35) ብሏል፡፡ ሌሎችንም ማስቸገር እንደሌለበት ሲናገር “ከእናንተ ዘንድ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት፥ ሌሊትና ቀን በድካምና በጥረት እየሠራን እንኖር ነበር እንጂ፥ ከማንም እንጀራን እንዲያው አልበላንም” ( 2ኛ ተሰሎ 3፡8) በማለት አስገንዝቦናል፡፡ ለፊልጵስዮስ ቤተ ክርስቲያንም ያለ አንዳች ክፍያ እንዳገለገላቸው ሲናገር  “የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ” (ፊልጵ 4፡14-16) ብሏል፡፡ ይህም ለዘመናችን አገልጋዮች ሁሉ አርአያ ሊሆናቸው ይገባል፡፡ የእግዚአብሔር ምርጥ ዕቃ የተባለ ሐዋርያ ከሰፊው ስብከቱ በተጨማሪ ድንኳን ይሰፋ ከነበር የዘመናችን አገልጋዮችማ እንደምን ሥራቸውን በመደበኛነት አይሠሩ?!

በተለይም በዝርወት ዓለምና በታላላቅ ከተሞች ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ያሉ ካህናትና ሌሎችም አገልጋዮች (አረጋውያኑን ሳይጨምር) ለሥራ የሚሆን በቂ ጊዜና ጥሩ የሥራ ዕድልም ስላላቸው ሠርተውበት ራሳቸውን፣ ቤተ ክርስቲያናቸውንና ሀገራቸውን በብዙ መጥቀም ይችላሉ። እንደሚታወቀው በአብዛኞቹ የውጭው ዓለም አብያተ ክርስቲያናት አብዛኛው (አንዳንዴም ሙሉው) መንፈሳዊ አገልግሎት የሚከናወነው በሰንበተ ክርስቲያን (እሁድ) ነው። ምንም እንኳን ከቤተ መቅደስ ውጭ የሚሰጡ ሌሎች መንፈሳዊ አገልግሎቶች ቢኖሩም እነዚህ አገልጋዮች ቢያንስ በከፊል (part-time) መሥራት ይችላሉ። ብዙዎቹም የመሥራት ፍላጎቱ ያላቸውና ቤተ ክርስቲያንንም ያለ ክፍያ ማገልገል የሚፈልጉ እንደሆኑ እንረዳለን። ምዕመናንንም ይህንን የማበረታታት፣ የሥራ ዕድሎችንም የማመቻቸት ኃላፊነት አለባቸው። ሥራ የማይሰራ አእምሮ የተንኮል፣ የክፋትና የአሉባልታ ተጠቂ ስለሚሆን ከአገልጋዮቹ ግላዊ ሕይወት አልፎ ቤተ ክርስቲያንንም እንደሚያውክ በየቦታው የምናየው እውነታ ነው።

በሌላ በኩል በ(ለ)ሥራ መትጋት ማለት ሥራ ቦታ በተመደበው ሰዓት መግባት፣ በተመደበው ሰዓት መውጣት ወይም ለተወሰነው ሰዓት ሥራ ላይ መቆየት ማለት ብቻ አይደለም። ለሥራ መትጋት ማለት ሙሉ አቅምን ተጠቅሞ መሠራት ያለበትን ሥራ በጊዜው ማከናወን ነው። ለሥራ መትጋትም የሚባለው አለቃን ለማስደሰት የሚደረግ ሳይሆን ለኅሊናና ለእግዚአብሔር ብሎ የሚገባውን በጥራት ማከናወን ነው። ለሥራ መትጋት የሚባለውም የሚከፈለንን ያህል ብቻ መሥራት አይደለም፣ ሊሠራ የሚገባውን ያህል መሥራት እንጂ። ለሥራ የሚተጋ ክርስቲያን ስለ ሠራ ይከፈለዋል እንጂ የሚከፈለውን ያህል ብቻ አይሠራም። ገንዘብ ለሥራ ከሚያተጉን ብዙ ምክንያቶች አንዱ ምክንያት እንጂ ብቸኛው ምክንያት አይደለም። ለገንዘብ ብቻ ብለን በሥራችን የምንተጋ ከሆነ ጉልበታችንን እየሸጥን እንጂ ለሥራ እየተጋን አይደለም፣ ገንዘብ ብቻውን የመንፈስም ሆነ የኅሊና ዕረፍትን አይሰጥምና። ይልቅስ የምንሠራው ሥራ ለማኅበረሰቡ ሕይወት ያለውን ጠቀሜታ እያየን ልንተጋ ይገባናል።

ታካችነትን እናስወግድ!

በሥራ ታካች መሆን በምድር ድህነትን ሲያስከትል በሰማይ ደግሞ ድኅነትን ያሳጣል፡፡ ታካችነት በሥጋም በነፍስም እንደሚጎዳ መጽሐፍ ያስተምረናል፡፡ ስለሥራ በልዩ ሁኔታ የተሰጠውን ሀብተ ጥበብ ተጠቅሞ የጻፈው ጠቢቡ ሰሎሞን ታካችነትን እናስወግድ ዘንድ በብዙ ምሳሌ አስተምሮናል፡፡ በመጽሐፈ ምሳሌ ታካቾችንና ታካችነትን ሲገስፅ “አንተ ታካች፥ እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ? ጥቂት ትተኛለህ፥ ጥቂት ታንቀላፋለህ፥ ትተኛም ዘንድ ጥቂት እጅህን ታጥፋለህ፤ እንግዲህ ድህነትህ እንደ ወንበዴ፥ ችጋርህም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል (ምሳሌ 6:7-11)” እያለ ታካችነት ለድህነትና ለረሃብ እንደሚያጋልጥ በግልፅ ነግሮናል፡፡ ይኸው ጠቢብ ስለታካች እጅ ሲናገርም “የትጉ እጅ ትገዛለች፤ የታካች እጅ ግን ትገብራለች (ምሳሌ 12:24)” ይልና  “የታካች እጅ ችግረኛ ታደርጋለች፤ የትጉ እጅ ግን ባለጠጋ ታደርጋለች። በበጋ የሚያከማች ልጅ አስተዋይ ነው፤ በመከር የሚተኛ ግን እርሱ ራሱን ያስነውራል (ምሳሌ 10:4-5)” በማለት የታካችነትን አስከፊነት አጉልቶ ያስረዳል፡፡

ከእግዚአብሔር በተሰጠው ጥበብ ድንቅ ምሳሌዎችን እየመሰለ ነገረ ሃይማኖትን ያስተማረው ይህ ጠቢቡ ሰሎሞን ስለታካችነትና አስከፊነቱ ብዙ ተናግሯል፡፡ በተለይም ሥራን የማይወዱና በምኞት ብቻ የሚፈልጉትን የሚያገኙ ሰለሚመስላቸው ሰነፎች ሲናገር “ታካችን ምኞቱ ትገድለዋለች፥ እጆቹ ይሠሩ ዘንድ አይፈቅዱምና (ምሳሌ 21:25)” በማለት ታካችን ክፉ ምኞቱ እንደምትገድለው በመጽሐፈ ምሳሌ ተናግሯል፡፡ በተጨማሪም “የታካች ሰው ነፍስ ትመኛለች፤ አንዳችም አታገኝም፤ የትጉ ነፍስ ግን ትጠግባለች (ምሳሌ 13:4)” በማለት ጠንክሮ መሥራትን ወደጎን በመተው ምኞታቸውን በአቋራጭ ለማግኘት የሚያስቡ ይህ ምኞታቸው እንደሚያጠፋቸው በማያወላዳ መልኩ አስረድቶናል፡፡በሌላም አገላለጽ ሥራን ለመሥራት የሚሰንፍ ሰውን ሲገስፅ “በሥራው ታካች የሚሆን የሀብት አጥፊ ወንድም ነው (ምሳሌ 18:9-10)” በማለት ታካችነት ከሀብት አጥፊነት ተርታ እንደሚቆጠር በግልጽ አስተምሯል፡፡ ይህንንም ያለው ታካችነት በሥራ ለወደፊት ሊገኝ የሚችል ሀብትን ማምከን ስለሆነ ነው፡፡ አጥፊነት ደግሞ አሁን ያለውን ሀብት ማጥፋት ስለሆነ ሁለቱን ወንድማማች አድርጎ በምሳሌ አስተምሮናል፡፡

ክርስቲያን በሥራ መትጋትን በምንም ሊተካው አይችልም፡፡ ምድራዊ ሀብትም ይሁን ሰማያዊ ጽድቅ በመትጋት እንጂ በመታከትና በመተኛት አይገኝም፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን “በድካም ሁሉ ልምላሜ ይገኛል፤ ብዙ ነገር በሚናገር ከንፈር ግን ድህነት ብቻ አለ (ምሳሌ 14:23-24)” በማለት ልምላሜ (ትርፍ) በድካም (በመሥራት) እንጂ በከንፈር (በማውራት) እንደማይገኝ አስገንዝቦናል፡፡ በተጨማሪም “ምድሩን የሚያርስ እንጀራ ይጠግባል፤ ምናምንቴዎችን የሚከተል ግን ድህነት ይሞላበታል። የታመነ ሰው እጅግ ይባረካል፤ ባለጠጋ ለመሆን የሚቸኵል ግን ሳይቀጣ አይቀርም (ምሳሌ 28: 19-20)” ብሎ መትጋትን ገንዘብ እንድናደርግ አስተምሮናል፡፡ እንቅልፍን መውደድም እንዲሁ ለድህነት እንደሚዳርግ ሲናገር “ድሀ እንዳትሆን እንቅልፍን አትውደድ (ምሳሌ 20:13)” ብሏል፡፡

በሥራችን እግዚአብሔርን እናስቀድም!

ሥራም ሆነ ለሥራ የሚያስፈልጉን ዕውቀትና ክህሎት የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው። የሰው ልጅ የሚሠራውን ሥራ በዕውቀቱና በጉልበቱ የሚያከናውነው ቢሆንም ዕውቀትን እና ጤነትን የሠጠውን እግዚአብሔርን በሥራው ሁሉ ሊያስቀድም ይገባል። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገር “እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት (ቊላ 3:17)” ብሏል። በተጨማሪም ክርስቲያን ሥራን ሲሠራ በትጋትና ያለ አንዳች ልግመት መሆን እንዳለበት ሲያስተምር “ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፥ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት (ቆላ 3:23)” በማለት አስተምሯል። ጠቢቡ ሰሎሞንም ሥራችንን ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ ማከናወን እንዳለብን ሲነግረን “ሥራህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፥ አሳብህም ትጸናለች (ምሳሌ 16:3)” ብሏል።

የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሌለበት የሰዎች ድካም ብቻውን ፍሬ ሊያፈራ አይችልም፡፡ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ የሠራተኞች ድካምም ከንቱ ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት ስለዚህ “እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፥ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ፤ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፥ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል። በማለዳ መገሥገሣችሁም ከንቱ ነው። ለወዳጆቹ እንቅልፍን በሰጠ ጊዜ፥ እናንተ የመከራን እንጀራ የምትበሉ፥ ከተቀመጣችሁበት ተነሡ (መዝ 127:1-2)” በማለት በሥራችን ሁሉ እግዚአብሔርን እንድናስቀድም በመዝሙሩ አስተምሮናል፡፡   ይህንንም ዘወትር በጸሎታችን እግዚአብሔርን “የአምላካችን የእግዚአብሔር ብርሃን በላያችን ይሁን። የእጆቻችንንም ሥራ በላያችን አቅና (መዝ 90:17)” እያልን ልንለምንና ሥራችንም ሲከናወንልን ምስጋናን ልናቀርብ ይገባናል፡፡

ክርስትናን በሥራ እንመስክር!

ለሥራ ስንተጋ በሥራ ቦታ ሊኖረን የሚገባው መንፈሳዊነት (ክርስትና) በብዙዎች ዘንድ አነጋጋሪ ሲሆን ይታያል። አንዳንዶችም ክርስትናን በሥራና በእውነት ከመግለፅ ይልቅ የማስመሰል ሕይወት ውስጥ በመግባት ራሳቸውንም ሌሎችንም ይጎዳሉ። ሃይማኖታዊ ግብ በሌላቸው ተቋማት ውስጥ ማንኛውም ዓይነት እምነት ያለው (እምነት የሌለውም ጭምር) በሙያው ሊሠራ ይችላል፡፡ እነዚህ ተቋማትም የሚመሩት በየራሳቸው የሥራ ቦታ መመሪያ ነው፡፡ በቅጥርም ሂደት ሰውን በእምነቱ ምክንያት ማግለልና አድልኦ መፈጸም እንደሌለባቸው ይታመናል፡፡ በሥራ ቦታም የየራሳቸው የአለባበስ ሥርዓት ይኖራቸዋል፡፡ በመሠረታዊነት እነዚህ ተቋማት የእምነት መገለጫ (እምነትን መግለጫ) ቦታዎች ስላልሆኑ ሁሉም ሠራተኛ አለባበሱም ሆነ አነጋገሩ የየተቋማቱን ሥርዓትና መመሪያ ያከበረ ሊሆን ይገባዋል፡፡ እውነተኛ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ እምነቱን የሚገልጸው በመልካም ስነ-ምግባሩ ነው፡፡ በእነዚህ ተቋማትም በሥራ በመትጋት፣ የተቋሙን መመሪያ በማክበር፣ ከሌሎች ሠራተኞች ጋር መልካም ግንኙነትን በመፍጠር፣ ተቋሙ የቆመለትን ዓላማ እንዲያሳካ የሚችለውን ሁሉ በማድረግና ለሌሎችም መልካም አርአያ በመሆን ነው ክርስትናውን የሚገልጠው፡፡ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ያለው እንዲሁ ነው፡፡ ክርስትናችን የሚገለጠው በአስተሳሰባችን፣ በአነጋገራችንና በምግባራችን መልካምነት ሊሆን ይገባል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በአንዳንዶች ዘንድ ነጠላ ለብሶ ወደ መሥሪያ ቤት ወይም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መግባት መከልከሉ ትልቅ መነጋገሪያ ጉዳይ ሲሆን አስተውለናል፡፡ መሥሪያ ቤቶችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሴኩዩላር እስከሆኑ ድረስ የራሳቸው የአለባበስ ደንብ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ይህም ለማንኛውም ወገን የማያዳላ፣ ማንንም የማያገልል ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይህንን ወደጎን ትተን እኛ እምነታችንን የሚገልጽ ነገር እንልበስ የምንል ከሆነ መመሪያውን እንተላለፋለን፡፡ ይሁንና ብዙ ተቋማት አካታች ስለሆኑ እንደሁኔታው ለሠራተኞቻቸው የሚጸልዩበት ቦታና ሰዓት ሁሉ እስከመፍቀድ ሲደርሱ አስተውለናል፡፡ በተቋም ውስጥ ነጠላ መልበስ የሚከለከል ከሆነ አለመልበስ ይመረጣል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በሌሎች ተቋማት ውስጥ ነጠላ ልበሱ የሚል ትዕዛዝ የላትም፡፡ ሌሎች እምነትን የሚገልጡ ነገሮችንም ሴኪዩላር በሆኑ ተቋማት ውስጥ አጉልቶ ማሳየት እንዲሁ ተቋማቱን የሃይማኖታዊ ምልክቶች መፎካከሪያ ዐውድ በማድረግ ከቆሙለት ዓላማ ያዘናጋቸዋል፡፡ ይህንን በማድረግ ከምናተርፈው ይልቅ የምናጠፋው ይበልጣልና ጥንቃቄ ማድረጉ አይከፋም፡፡ የሌላ እምነት ተከታዮች ይህንን ሲያደርጉ ብናይ ህግን እንጂ ህግ ተላላፊዎችን መከተል የለብንም፡፡

የማዕተብ ጉዳይ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ማዕተብ የሥላሴ ልጅነትን ስናገኝ የተሰጠን የክርስትናችን ምልክት ነው። በአንገታችን የምናስረው ስለሆነ ብዙውን ጊዜ በግልፅ ከሩቅ የሚታይ ምልክት አይደለም። ዓላማውም የእምነት (የጥምቀት) ምልክት እንጂ ለጌጥ፣ ለታይታ ወይም ለፉክክር የሚደረግ አይደለም። በሴኪዩላር ተቋማትም ቢሆን ከአብዛኛው የአለባበስ ሥርዓት ጋር የሚስማማ ነው። ይልቁንም የተለያዩ ጌጣጌጦችን በአንገት ላይ ማሰር የተለመደ ነገር በሆነበት ዘመን በመመሪያውም ሆነ በአመራሩ ‘ማዕተብ አትሠሩ’ የሚል ተቋም ካለ ልንሞግተው ይገባል። በተጨማሪም የሌሎች እምነት ተከታዮች የሚመሯቸው ሴኪዩላር ተቋማት በእምነት ምክንያት በግልፅ አድሎና ማግለል የሚፈፀምበት ሁኔታ ሲያጋጥም ችግሩ በህግ አግባብ እንዲታይ ማድረግ ይኖርብናል። በራሳችን የክህሎትና የአፈፃጸም ማነስ ወይም በተቋማቱ ሌሎች ሁኔታዎች ምክንያት ሳንቀጠር ስንቀር ወይም ተቋማቱን ስንለቅ ‘ማዕተብ በማድረጌ ነው’ ወይም ‘ኦርቶዶክስ ስለሆንኩ ነው’ ማለት ግን በምድራዊም በሰማያዊም ህግ ያስጠይቃል።

ማጠቃለያ

ሥራን በመሥራት የምናገኛቸው ብዙ ትሩፋቶች አሉ፡፡ ተግተን ስንሠራ ለራሳችን ሕይወት የሚያስፈልገንን ማሟላት እንችላለን፣ ለሌሎችም አንከብድባቸውም፡፡ በመሥራታችን ለማኅበረሰባችንና ለሀገራችን ዕድገትና ልማት የበኩላችንን ድርሻ ማበርከት እንችላለን፡፡ ጠንክረን ስንሠራ አዕምሮአችን በሙሉ አቅሙ ሥራ ላይ ስከሚያተኩር ኃጢአትን ከምትወልድና ለሞት ከምታደርስ ክፉ ሀሳብ እንርቃለን፣ ኃጢአትንም አንሠራም፡፡ በሥራ ስንተጋ ከሥራችን በምናገኘው ገንዘብ፣ እውቀትና ልምድ ሌሎች ወገኖቻችንን መርዳት እንችላለን፣ ለእነርሱና ለቀጣዩ ትውልድም መልካም አርአያና ምሳሌ መሆን እንችላለን፡፡ በርትተን ስንሠራ ለቤተ ክርስቲያንም በገንዘብ፣ በዕውቀት/በልምድ፣ በምሳሌነት አለኝታ እንሆናታለን፡፡ የቀደሙት ቅዱሳንም ለመንፈሳዊውም ለምድራዊውም ሥራ በመትጋታቸው ነው ለሁላችንም አብነት ሆነው ያለፉት፡፡ በሥራ ከመትጋት ውጭ ለሰው ልጅ ሌላ የሚበጀው ነገር እንደሌለም ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡

ስለዚህም የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንና አገልጋዮች የሚያምኑት እውነተኛ እምነት በሥራ የሚገለጥ መሆኑን በማስተዋል ለሥራ መትጋትን ገንዘብ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በአንዳንዶች ዘንድ እንደሚታየውም “በአቋራጭ የመክበርን” አስተሳሰብ ከልባቸውና ከህሊናቸው ማራቅ አለባቸው። እውነተኛ እምነት ጭብጥ በሌለው ልፍለፋና በየቀኑ በሚቀያየር የፋሽን ልብስ፣ በሰው ዘንድ ልታይ ልታይ በማለት ሳይሆን በፍጹም ነፍስ፣ በፍጹም ሀሳብና በፍጹም ልብ ውስጥ ተዋሕዶ በመንፈሳዊና በምድራዊ ሥራ የሚገለጥ ስለሆነ ለሥራ መትጋትን ሁሉም ገንዘብ ሊያደርገው ይገባል እንላለን፡፡