ሰንደቅ ዓላማና ቤተክርስቲያን፡ የቄሳርን ለቄሳር!

flags_church
ምክንያተ ጽሕፈት

በአንዲት ኢትዮጵያውያን የሚኖሩባት የምዕራባውያን ሀገር ከተማ በቅርቡ የመጣውን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆኑ ጳጳሳት እርቅ ተከትሎ የጥምቀትን በዓል አጥቢያዎች ተለያይተው ማክበራቸው ቀርቶ “በአንድነት የማክበር ሀሳብ” በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ በዓሉን በአንድነት እናክብር ወይስ ላለፉት የተወሰኑ ዓመታት ልማድ እንደነበረው ተለያይተን እናክብር የሚል ውይይትም በካህናትም ሆነ በምዕመናን ዘንድ ጎልቶ ይሰማል፡፡ ሁሉም በየፊናው የየራሱን ሀሳብ ያቀርባል፡፡ በዚህ ሁኔታ ከቀረቡ ሀሳቦች ውስጥ አንዱ ባንዲራን ይመለከታል፡፡ አንዳንዱ “በጥምቀት በዓል መያዝ ያለበት ሀገራችን ኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት የተጠቀመችበት ልሙጡ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ ብቻ ነው፡፡ ኮከብ ያለበትን ባንዲራ የሚይዙ ካሉ ‘እንቃወማቸዋለን'”  ይላል፡፡ ሌላው ደግሞ “በጥምቀት በዓል መያዝ ያለበት የሀገራችን ኢትዮጵያ መደበኛ (ኦፊሴላዊ) ባንዲራ መሆን አለበት፡፡ ኮከብ የሌለበትን ባንዲራ የሚይዙ ካሉ ከእነርሱ ጋር ኅብረት የለንም፡፡” ይላል፡፡

ከዚህም በመነሳት መንፈሳዊ አንድነትን በሰንደቅ ዓላማ አረዳድ በመመዘን በዚህ ምድራዊ እይታ ከሚስማማቸው ጋር የሚውሉ፣ የማይስማማቸውን የሚያገሉ፣ አቅም ሲያገኙም የሚደበድቡ “የመንፈሳዊ በዓል አክባሪ ካህናትና ምዕመናን” አሉ፡፡ የሚገርመው እነዚህ ሁለት ቡድኖች የሚኖሩበትን ሀገር ባንዲራ ያለጭቅጭቅ ተሸክመው ሲዞሩ መዋላቸው ነው፡፡ የሚኖሩበት ሀገር ባንዲራም እንደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ባንዲራ የፖለቲካዊ ትርክት ማሳያ መሆኑን አይረዱም፡፡ የምድራዊ ባንዲራ ጉዳይ “ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ” ብለን የምንዘምርበት፣ የሰማያት ምሥጢር የተገለጠበትን የጥምቀት በዓል ሲያውክ ማየት ያሳዝናል፡፡ በመንፈሳዊ አውደ ምህረት ምድራዊ ባንዲራን የልዩነት (ወይም የአንድነት) ምንጭ አድርጎ የመሳል አባዜ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ቤተክርስቲያንን መለካት ባለባት መንፈሳዊ ሚዛን ሳይሆን መለካት በሌለባት ፖለቲካዊ (ሀገራዊ) ሚዛን እንድትለካ ያደርጋል፡፡  

በአጠቃላይ ከቅርብ ዘመናት ወዲህ በሕንፃ ቤተክርስቲያን ላይ፣ የበዓላት አከባበርን ለማድመቅ፣ በአልባሳትና አንዳንዴ ደግሞ ንዋየ ቅድሳት ላይ ጥቅም ላይ የሚውሉ ቀለማትን ከፖለቲካዊ ሰንደቅ ዓላማ ጋር ማያያዝ እንዲሁም ሰንደቅ ዓላማን በንግሥ በዓላት ላይ መያዝ ለብዙዎች አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኗል፡፡ አንዳንዶቹ ባለማወቅ፣ ሌሎችም በድፍረት (ዓለማዊ ዓላማን ከመንፈሳዊ ዓላማ በማስቀደም) ቤተክርስቲያንን የፖለቲካ ፉክክር አውድ እያደረጉ ኅማማተ ክርስቶስን የምናስብበትን ከበሮ “የእኔ ነው” የሚሉትን ባንዲራ አልብሰው “መዝሙር ሲዘምሩ” ይታያሉ፡፡ ሌሎቹም ሥርዓተ ቅዳሴን የሚያክል ሰማያዊ አምልኮ በሚፈጸምበት ሰዓት በመጾር መስቀል ላይ የሚንጠለጠለውን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፈዋሽ ሕማም የሚታሰብበትን መግነዝ መታሰቢያ “የእኔ ነው” በሚሉት ባንዲራ ተክተው “ሲቀድሱ” ይታያሉ፡፡ ይህን መሰል አሰራር በአንዳንዶቹ ዘንድ “ሀገር ወዳድነት” የሚል ካባ ተደርቦበት “በመተዳደሪያ ደንብ” ውስጥ  ሳይቀር የተካተተባቸው ቦታዎች አሉ፡፡

የሰንደቅ ዓላማ ፉክክር ከፖለቲካና ከፖለቲከኞች አውድ አልፎ የሁሉም እናት ወደሆነች ቅድስት ቤተክርስቲያን አውደምህረት መምጣቱ በርካታ ችግሮችን እያስከተለ ይገኛል፡፡ አንዳንዶች በአንድ የሃይማኖት ተቋም ውስጥ ‘ሰንደቅ ዓላማ’ መጠቀም ለምን አስፈለገ ብለው ሲጠይቁ፣ ሌሎች ደግሞ ቤተክርስቲያንን የተወሰነ የፖለቲካ ወገንተኝነት ያለው ቡድን ለፖለቲካ ዓላማው እየተጠቀመባት ነው ብለው ይከሳሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ እነርሱ ይህንን ‘ሰንደቅ’ ዓላማ በቤተክርስቲያን የሚጠቀሙ ከሆነ እኛም እኛን የሚወክለንን ሰንደቅ ዓላማ እንጠቀማለን ሲሉ ይደመጣሉ፤ መጠቀምም ጀምረዋል፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ቤተክርስቲያንን የፖለቲካ ፉክክር አውድ ሊያደርጋት ይችላል፡፡ ከዚህም የተነሣ የበዓላትን መንፈሳዊ ዓላማ ከመረዳት ይልቅ መንፈሳዊ በዓላትን ለምድራዊ ፉክክር ማዋል የሚያስደስታቸው ሰዎች በማወቅም ባለማወቅም መንፈሳዊውን አውድ ለፖለቲካዊ ዓላማ ስለሚጠቀሙበት መንፈሳዊ አንድነትን እየተፈታተነ ይገኛል፡፡

በዚህች አጭር የአስተምህሮ ጦማር ሰንደቅ ዓላማን (ባንዲራን) እና የሰንደቅ ዓላማ ቀለማትን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎችን ከኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ አንጻር እንዳስሳለን፡፡ የሰንደቅ ዓላማ ዓለማዊ (ሀገራዊ) እና ፖለቲካዊ ትንታኔዎች እንዲሁም በሀገራዊ ክዋኔዎች የቤተክርስቲያን ተቋማዊ ሚና እና የምዕመኖቿ ግላዊ አበርክቶት የኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ትኩረት ስላልሆኑ በዚህ ጽሁፍ በትኩረት አልተዳሰሱም፡፡

ለመሆኑ ሰንደቅ ዓላማ ምንድን ነው?

ሰንደቅ ዓላማ (‘Flag’ in English, ‘Bandiera’ in Italian) ከጀርባው ትልቅና ጥልቅ መልዕክትን ያዘለና አንድን ሀገራዊ ወይም ፖለቲካዊ ወይም ድርጅታዊ አስተሳሰብ የሚወክል ምልክት ነው። በዚህም መሠረት ሀገራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ድርጅቶች የራሳቸው ባንዲራ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ሰንደቅ ዓላማ  “በአብዛኛው የተወሰኑና የተለያዩ ቀለማት ካሏቸው ቁሶች የሚዘጋጅ የአንድ ሀገር የነፃነት ምልክትና መለያ፣ የአንድ ሀገርና ሕዝብ የሉዓላዊነቱ ምልክት ወይም ትዕምርት” ነው፡፡ ስለዚህ ሰንደቅ ዓላማ ሀገራዊ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የሰንደቅ ዓላማ ታሪካዊ አጀማመርን ያጠኑ ሰዎች (vexillologists) እንደሚሉት የሰንደቅ ዓላማ አጀማመር በጦርነት ጊዜ ወዳጅን ከጠላት የመለየት ዓላማ ነበረው፡፡ በጊዜ ሂደት ሀገራት መደበኛ ቅርጽ ያለቸውን ባንዲራዎች በመወሰን የባህል፣ የፖለቲካ አቋምና የግዛት አንድነት መለያ አድርገው መውሰድ ጀመሩ፡፡ በዓለማችን ያሉ አብዛኞቹ ባንዲራዎች በብዛት ጥቅም ላይ መዋል የጀመሩት ከብሔራዊ መንግስታት (Nation States) ምስረታ ጋር ተያይዞ ነው፡፡

የየትኛውም ሀገር ወይም ድርጅት ወይም የኅብረተሰብ ክፍል የሚጠቀመው ባንዲራ ከዚያ አገር ሕዝብ ወይም የኅብረተሰብ ክፍል ማንነትና ከሚከተለው የፖለቲካ ሥርዓት፣ ታሪክ፣ አስተሳሰብ ወይም ዓላማ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ትርጓሜና ውክልና ይሰጠዋል። ስለዚህ ሰንደቅ ዓላማ የባለቤቱን አስተሳሰብ፣ አመለካከት ወይም ዓላማ ይወክላል ማለት ነው፡፡ የሰንደቅ ዓላማ ልዩነት የምልክቱ (የቀለሙ) ልዩነት ብቻ አይደለም፡፡ በዋናነት ከሰንደቅ ዓላማው ጀርባ ያለው ጥልቅ መልእክት/ዓላማ ልዩነት እንጂ፡፡ ከዚህ አንጻር አንድ ሰው/ማኅበረሰብ/ “ይህ ሰንደቅ ዓላማ ይገልፀኛል” ሲል ሰንደቅ ዓላማው ሀገራዊ አመለካከቴን፣ ፖለቲካዊ ፍልስፍናዬን፣ ታሪካዊ ማንነቴን፣ ከሌሎች ወገኖቼ ጋር ያለኝን መስተጋብር… ይገልፃል ማለቱ ነው፡፡ እንዲሁም “ይህ ሰንደቅ ዓላማ አይገልፀኝም” ሲል ከላይ የተጠቀሱትን የእኔነት መገለጫዎቼን አያንጸባርቅም ማለቱ ነው እንጂ ቀለሙ ጠቆረ ወይም ቀላ ወይም ነጣ ማለቱ ብቻ አይደለም፡፡

የኖኅ ቀስተ ደመና ከሰንደቅ ዓላማ ጋር ይገናኛልን?

እግዚአብሔር በኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎችን በክፋታቸው ምክንያት በንፍር ውኃ ካጠፋቸው በኋላ ዳግመኛ የሰውን ልጅ በንፍር ውኃ ላያጠፋ ቃል ኪዳንን ሰጥቶታል፡፡ መጽሐፍ ይህንን ቃል ኪዳን ሲገልጽ “እግዚአብሔርም ለኖኅና ለልጆቹ እንዲህ ብሎ ተናገረ። እኔም እነሆ ቃል ኪዳኔን ከእናንተና በኋላ ከሚመጣው ከዘራችሁ ጋር አቆማለሁ፤ ከእናንተ ጋር ላሉትም ሕያው ነፍስ ላላቸው ሁሉ … ይሆናል። ቃል ኪዳኔንም ለእናንተ አቆማለሁ፤ ሥጋ ያለውም ሁሉ ዳግመኛ በጥፋት ውኃ አይጠፋም፤ ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም። እግዚአብሔርም አለ፡- በእኔና በእናንተ መካከል … ለዘላለም የማደርገው የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው፤ ቀስቴን በደመና አድርጌአለሁ፥ የቃል ኪዳኑም ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል። በምድር ላይ ደመናን በጋረድሁ ጊዜ ቀስቲቱ በደመናው ትታያለች… ሥጋ ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም። ቀስቲቱም በደመና ትሆናለች፤ በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል ያለውን የዘላለም ቃል ኪዳን ለማሰብ አያታለሁ። እግዚአብሔርም ኖኅን፡- በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው ሁሉ መካከል ያቆምሁት የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው አለው።” በማለት አስፍሮታል (ዘፍ 9፡8-17)፡፡

እግዚአብሔር ይህንን ቀስተ ደመና ነው የቃል ኪዳኑ ምልክት ያደረገው፡፡ ቃልኪዳኑም ዘላለማዊ ሲሆን እግዚአብሔር ዳግመኛ የሰውን ልጅ በንፍር ውኃ ላለማጥፋት የሰጠው ቃል ኪዳን ነው፡፡ ለሰው ብቻ ያይደለ ሥጋ ለለበሰ ፍጡር ሁሉ የተሰጠ ቃል ኪዳን ነው፡፡ ምልክቱም በእግዚአብሔርና በሰው መካከል በደመና ላይ የሚታይ ምልክት ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህንን ምልክት በደመና ላይ እንዲሆን ያደረበት የራሱ ምሥጢር አለው፡፡ የዚህ ምልክት ፍጻሜ ለሰው ልጅ ምክንያተ ድኂን የሆነችው ድንግል ማርያም ናት፡፡ ከልጇ ጽኑ ቃል ኪዳን የተቀበለች የአምላክ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም በኖኅ መርከብ እንደምትመሰል ሁሉ በኖኅ የቃል ኪዳን ምልክት በሆነችው በኖኅ ቀስተ ደመና ትመሰላለችና፡፡

እግዚአብሔር ይህንን የቀስተ ደመና ምልክት ለኖኅ ማሳየቱ ለጊዜው ከእንግዲህ ወዲህ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋና ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ የተፈጠረ ሰውን በንፍር ውሃ አላጠፋውም ሲለው ሲሆን ፍጻሜው ግን ደመና የቅድስት ድንግል ማርያም፤ ሕብረ ቀለማቱ የሰው ባሕርያት ምሳሌ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ይህንን የቃል ኪዳን ምልክት ማሳየቱ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቼ ተወልጄ ሰውን ከመርገም ውሃ (ከሲኦል) አድነዋለሁ ሲል ነው፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ይህን በማስመልከት በሰላምታ መጽሐፉ ላይ “ከልቅሶ ደመና የጥፋት ውሃ ዳግመኛ በምድር ፊት ላይ እንዳይዘንብ የኖኅ የመሐላው ምልክት የሆንሽ የተመሰገንሽ ማርያም ሰላምታ ላንቺ ይገባሻል” በማለት ድንቅ ምስጢርን አመስጥሯል፡፡ ሌሎች ቅዱሳን አባቶችም አማናዊት ቀስተ ደመና የድኅነት ምልክት የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም መሆኗን መስክረውላታል፡፡

ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴ ቀለማት (Pan-African Colours) (በብዙ ሀገራት ባንዲራ ላይ የሚገኘው) መነሻው የቀስተ ደመና ምልክት መሆኑ ቢታወቅም በሁለቱ መካከል መሠረታዊ ልዩነቶች እንዳሉ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ቀስተ ደመና በእግዚአብሔርና በሰው (በዓለም ላይ ያለው ሰው ሁሉ) መካከል ያለው ቃል ኪዳን ምልክት ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማ ግን የሀገር ፖለቲካዊ ምልክት ነው፡፡ ቀስተ ደመና በሰውና በእግዚአብሔር መካከል በደመና ላይ የሚታይ ምልክት ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማ ግን በጨርቅ ወይም መሰል ቁስ ላይ ተደርጎ የሚሰቀል ነው፡፡ ቀስተ ደመና ከሰባት የማያንሱ ቀለማት አሉት፡፡ በቀስተ ደመና ላይ ያሉት ቀለማት አቀማመጥም እንዲሁ ከሰንደቅ ዓላማ የተለየ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን የቃል ኪዳን ምልክት መነሻ ያደረጉ የብዙ ሀገራት ሰንቅ ዓላማዎች እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ይህ የቀስተ ደመና ቀለማት ያለው ምልክት የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን የሚደግፉና የሚፈጽሙ አካላት ምልክት ሆኗል፡፡ ይህ ቢሆንም ግን የቃል ኪዳን ምልክትነቱ የጸና ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ዓላማዋ “ነዋ ወንጌለ መንግስት/የመንግስት ወንጌል እነሆ” የሚለውን አምላካዊ ቃል መመሪያ በማድረግ ለሰው ልጅ ሁሉ ወንጌልን በመስበክ ለዘላለም ሕይወት ማብቃት ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” (1ኛ ቆሮ 1፡23) እንዳለው የቤተክርስቲያን ዓላማ ክርስቶስን መስበክ ነው፡፡ ይህንን ዓላማዋ ያደረገች ቤተክርስቲያን ማንኛውንም ምድራዊ አስተሳሰብ፣ አመለካከት ወይም ዓላማ በሚያንጸባርቅ ምልክት ልትገለጽ አይገባም፡፡ ስለዚህ ምድራዊ ዓላማ ያላቸው ሰዎች የራሳቸውን ዓላማ የሚገልጽ ምልክት ወደ ቤተክርስቲያን በማስገባት ከመንፈሳዊ ዓላማዋ ፈቀቅ እንድንል እንዲያደርጉ መፍቀድ አይገባም፡፡

አንዳንድ ወገኖች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ መያዝ/መጠቀም/ ቤተክርስቲያኒቱ “የኢትዮጵያ” መሆኗን ለመግለጽ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን” በሚለው ስያሜ ውስጥ “የኢትዮጵያ” የሚለው ቃል የቤተክርስቲያኒቱን “ሕጋዊ ሰውነትን፣ አስተዳደራዊ መዋቅርን፣ ታሪካዊ መሠረትን፣ ትውፊታዊ አመጣጥን…” የሚያሳይ እንጂ መንፈሳዊ ወሰንን ወይም ሃይማኖታዊ ባለቤትነትን የሚያመለክት አይደለም፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም” (ማቴ 16፡18) እንዳለ እንዲሁም ቅዱስ ጳውሎስ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ….”(ሐዋ 20፡28) ብሎ እንደመሰከረው ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ቤተክርስቲያን፣ የጸሎት ቤት፣ የክርስቲያኖች ቤት ናትና አምኖ ለመገልገልና ለማገልገል ለመጣ ሁሉ ናት፡፡ ከዚህ አንጻር እንደየፖለቲካው አስተሳሰብ በየዘመናቱ የሚቀያየሩ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ምልክቶች መንፈሳዊ ማንነቷና ምንነቷን ሊገልጹ አይችሉም፡፡

ቤተክርስቲያን ግዕዛን ያላቸው ፍጥረታት (ሰውና መላእክት) ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ኅብረት ናት፡፡ ስለዚህ ቀድሞ በዓለመ መላእክት ቀጥሎም በብሉይ ኪዳን ነበረች፡፡ የሐዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ደግሞ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ከመሠረታት ጀምሮ በሐዋርያት ስብከት በዓለም ላይ ከአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንስቶ የነበረች፣ ያለችና እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ የምትኖር ናት፡፡ ሰንደቅ ዓላማን አሁን ባለው መልኩ መጠቀም የቅርብ ዘመን ታሪክና ከብሔራዊ መንግስታት መመስረት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካለንበት ዘመን ድረስ የብዙ ሀገራት ሰንደቅ ዓላማ ለብዙ ጊዜያት ለውጥ ተደርጎበታል፡፡ ለወደፊትም እንደአስፈላጊነቱ ለውጥ ሊደረግበት ይችላል፡፡ ቤተክርስቲያን ግን ትናንትናም ዛሬም ነገም “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬና ነገ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ያው ነው” እንደተባለ እርሱን ስትሰብክ ትኖራለች እንጂ አትለዋወጥም፡፡

የሰው ልጅ ሙሉ ነጻነት ያለው ፍጡር ስለሆነ በተረዳውና ባወቀው መጠን በነፃ ፈቃዱ የፈለገውን ሃይማኖት የመከተል፣ የፈለገውን ፖለቲካዊ አመለካከት የማራመድ መብት አለው፡፡ ስለዚህም ሰው በሚከተለው ሃይማኖት የተነሳ ሃይማኖታዊ ማንነት፤ በሚኖርበት ሀገር ዜግነት፤ በሚያራምደው ፖለቲካዊ አቋም ደግሞ ፖለቲካዊ ማንነት አለው፡፡ እነዚህን ማንነቶች አስማምቶ መኖር የእያንዳንዱ ሰው ድርሻ ነው፡፡ አማናዊት ቤተክርስቲያን ግን ፖለቲካዊ ወገንተኝነት የላትም፡፡ “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች” እንደተባለ ሁሉም የሚጸልይባት፣ ከአምላኩ ጋር የሚገናኝባት፣ የእግዚአብሔር ቤት ናት፡፡

ዓለም አቀፋዊት ቤተክርስቲያን ሀገራዊ/አካባቢያዊ ምልክት ይገልጻታልን?

ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ሰማያዊት ከመሆኗም ባሻገር ኩላዊት (በሁሉ ያለች፣ ዓለም አቀፋዊት) ናት፡፡ ይህም ሲባል በየትኛውም ሀገር ለሚኖር፣ የትኛውንም ቋንቋ የሚናገር ሰው ተምሮ፣ አምኖና ተጠምቆ የቤተክርስቲያኒቱ አካል፣ የክርስቶስ አካል ሆኖ ከምስጢራት ይካፈላል ማለት ነው፡፡ ሰው በቤተክርስቲያን እምነቱ እንጂ ማንነቱን ወይም ሀገሩን አይጠየቅም፡፡ ሰው አምኖ ከተጠመቀ በኋላ ማንነቱ ክርስቲያን (የክርስቶስ አካል) ሀገሩም በሰማይ ነውና (ፊል 3፡20)፡፡  እንግዲህ በዓለም ላይ ሁሉ ላለችና ለሰው ልጆች ሁሉ መዳን የሚሆነውን ቅዱስ ወንጌልን ለምትሰብክ ቤተክርስቲያን የተወሰነ ሕዝብ ወይም ሀገር ወይም ቡድን የሚጠቀምበት ምድራዊ ዓላማን በሚገልጽ ምልክት እንዴት ልትወከል ትችላለች? ስለዚህ ብዙ ውስንነት ያለውንና የቤተክርስቲያንን ኩላዊነት የማይገልጽ ማንኛውንም ዓይነት ምድራዊ ምልክት በቤተክርስቲያን እንጠቀም ማለት ከቤተክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ዓላማ ጋር አብሮ የማይሄድ ከመሆኑ ባሻገር የቤተክርስቲያኒቱን ዓለም አቀፋዊነትም እንኳን የማይገልጽ ነው፡፡ ዓለም አቀፋዊት ናት ተብሎም ምድራዊ የሆኑ ዓለም አቀፋዊ ምልክቶች አይደረጉላትም፡፡

ታዲያ ቤተክርስቲያን ዓርማ/ምልክት ምንድን ነው?

ቤተክርስቲያንም ሆነች ክርስቲያኖች የእምነት ምልክታቸው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ድኅነት ሲል የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ነው፡፡ ይህም ምልክት ብቻ ሳይሆን ኃይልም ጭምር ነው፡፡ ቅዱስ መስቀል በቤተክርስቲያኒቱ ሕንፃና በካህናቱ እጅ፣ በምዕመናኑ አንገት እንዲሁም በንዋየ ቅድሳት ላይ ያለ ክርስቶስ ስለመዳናችን የከፈለልንን ቤዛነት የምናስብበት ነው፡፡ ይህ የክርስትናችን ሃይማኖታዊ ምልክት ነው፡፡ ክርስትናችንን የሚገልጽ ከዚህ የሚበልጥ ምልክት የለንም፡፡ ምድራዊያን መንግስታት፣ ምድራዊ አስተሳሰብ፣ ምድራዊ ምልክቶችም ያልፋሉ፡፡ ቤተክርስቲያን ግን ዘላለማዊት ናት፡፡ ዘላለማዊት የሆነች ቤተክርስቲያን የሚያልፍ ምልክት ሊኖራት አይችልምና ዘላለማዊ ምልክቷ ቅዱስ መሰቀል ነው፡፡

በሌላም በኩል ቤተክርስቲያን በአካለ ሥጋ ያሉ ክርስቲያኖችና በአፀደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን ኅብረት ናት፡፡ የእነዚህ አንድነት ሁለቱም የክርስቶስ አካል መሆናቸው ነው፡፡ የክርስቶስ አካል የሆኑትም በስሙ አምነው፣ ከጎኑ በፈሰሰው ማየ ገቦ ተጠምቀው፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለው፣ ስለ ስሙ መስክረው፣ በስሙ መከራን ተቀብለው (ምግባር ትሩፋትን ሠርተው) ነው፡፡ ሰለዚህ የአንድነታቸው ምልክት ክርስቶስ የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ነው እንጂ ሌላ ምድራዊ ዓላማ ያለው ምልክት ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ አንጻር የክርስቲያኖች አንድነታችን መገለጫው በአንድ አምላክ ማመናችን፣ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት መዋጀታችን፣ በአንዱ በመንፈስ ቅዱስ መክበራችን፣ ለአንድ ተስፋ (ለመንግስተ ሰማያት) መጠራታችን፣ አንዲት ጥምቀትን መጠመቃችን፣ በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ከክርስቶስ ጋር አንድ አካል መሆናችንና ለቅዱሳን አንድ ጊዜ በተሰጠች ሃይማኖት በማመናችን ነው፡፡ የኑሮ ዘይቤ፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ፖለቲካዊ ፍልስፍና፣ ምድራዊ ሙያ/ጥበብ፣ ሰንደቅ ዓላማ…ወዘተ የምድራዊ አኗኗራችን ነፀብራቆች ናቸው እንጂ የክርስቲያናዊ አንድነት መስፈርቶች አይደሉም፡፡

አንድ መንፈሳዊ ተቋም ሰንደቅ ዓላማ ሊኖረው ይችላልን?

አንድ መንፈሳዊ ተቋም እንደ ማንኛውም ተቋም የራሱን መንፈሳዊና ሰማያዊ ዓላማ የሚገልጽ ምልክት ሊኖረው ይችላል፡፡ ይህም በመንፈሳዊ ተቋሙ የበላይ አካል የጸደቀና በተከታዮቹም የታመነበት ሊሆን ይገባል፡፡ ይህም መንፈሳዊ ዓላማን የሚገልጽና ለማንኛውም ዓይነት ምድራዊ ዓላማ ያልወገነ መሆን ይኖርበታል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴ ቀለማት ያለው ከጥንት ጀምሮ በቤተክርስቲያኒቱ የነበረ ምልክታችን ስለሆነ ዛሬ ላይ አንዳንድ ወገኖች ለፖለቲካ ዓላማ ቢጠቀሙበትም እኛ ጠብቀን ልናቆይ ያስፈልጋል ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ የባንዲራው ቀለማት መንፈሳዊ ታሪክና መነሻ እንዳላቸው ግልጽ ነው፡፡ ይሁንና እዚህ ላይ ግልጽ ማድረግ የሚያስፈልግ ዐቢይ ነገር አለ፡፡ ይህም በምልክቱና ምልክቱ በሚወክለው ዓላማ መካከል ያለው ልዩነት ነው፡፡ በቤተክርስቲያኒቱ ያሉ ሰዎች የቤተክርስቲያኒቱን ማንኛውንም ምልክት ለምድራዊ ዓላማ የሚጠቀሙ ከሆነ መንፈሳዊነታቸውን ያደበዝዘዋል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ማንኛውንም ምድራዊ ምልክት ለመንፈሳዊ ዓላማ የሚጠቀሙ ከሆነ ዓለማዊነታቸውን ያጎላዋል፡፡

ሃይማኖታዊ መሠረት ያላቸው ፖለቲካዊ ምልክቶችስ እንዴት ይታያሉ?

በዓለማችን ላይ ካሉ ሀገራት አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በሰንደቅ ዓላማቸው ላይ ሃይማኖታዊ መሠረት ያላቸው ምልክቶች አሏቸው፡፡ ጥቂት የማይባሉ ሀገሮችም በብሔራዊ መዝሙራቸው ውስጥ እንዲሁ “ሃይማኖታዊ ቃላት” አሏቸው፡፡ ይህም ሆኖ ግን የሰንደቅ ዓላማዎቹና የብሔራዊ መዝሙራቱ ዓላማ ፖለቲካዊ እንጂ ሃይማኖታዊ አይደለም፡፡ ስለዚህ የሀገራት መንግስታት ሃይማኖታዊ መነሻ ያለውን ምልክት ለሀገራዊ (ፖለቲካዊ) ዓላማ ሲጠቀሙበት የሚወስዱት ምልክቱን እንጂ ዓላማውን እንዳልሆነ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ ለምሳሌ የመስቀል ምልክት ያለባቸው ሰንደቅ ዓላማዎች ያላቸው ሀገራት አሉ፡፡ ይህ ማለት ግን የእነዚህ ሀገራት መንግስታት “ሃይማኖታዊ ዓላማ” ያላቸው ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ምናልባት አብዛኛው ሕዝባቸው ክርስቲያን ይሆናል ወይም የክርስትና ታሪክ ያለው ሕዝብ ይሆናል እንጂ፡፡

በእነዚህ ሀገራት ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ለመስቀል ምልክት የሚሰጡት ሃይማኖታዊ ትርጉምና የሚጠቀሙበት መንፈሳዊ ዓላማ እነዚህ መንግስታት ለመስቀሉ ምልክት ከሚሰጡት ፖለቲካዊ ትርጉምና ከሚጠቀሙበት ፖለቲካዊ ዓላማ የተለየ ነው፡፡ ይህንንም ማስተዋል ይገባል፡፡ በእነዚህ ሀገራት ያሉ አብያተ ክርስቲያናት የመስቀሉን ምልክት መንግስት ለፖለቲካ ዓላማ ተጠቅሞበታል ብለው ሃይማኖታዊ አገልግሎቱን አይተውም፡፡ መንፈሳዊ ትርጉሙን ጠብቀው ሃይማኖታዊ ዓላማውንም ጠንቅቀው ለመንፈሳዊ አገልግሎታቸው ይጠቀሙበታል እንጂ፡፡ ነገር ግን ሃይማኖታዊ ትርጉሙንና ሃይማኖታዊ ዓላማውን እንዲሁም መንፈሳዊ አጠቃቀሙን ለምእመናኑ በሚገባ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ፖለቲከኞቹም ቢሆኑ ፖለቲካዊ ትርጉሙን፣ ፖለቲካዊ ዓላማውንና ፖለቲካዊ አጠቃቀሙን ያሳውቃሉ፡፡ ምንም እንኳን ምልክቱ ተመሳሳይ ቢሆንም የተለያየ ትርጉም፣ ዓላማና አጠቃቀም ስላላቸው ሃይማኖትና ፖለቲካ የተለያዩ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡

ታዲያ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ምልክቶችን እንዴት እንለይ?

ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ምልክቶችን በዋናነት የምንለያቸው በቅርጻቸው፣ በመጠናቸው ወይም በቀለማቸው ሳይሆን ባላቸው ትርጉምና በሚወክሉት ዓላማ ነው፡፡ እነዚህ በግልፅ አለመለየታቸው ምዕመናን በመንፈሳዊ በዓላት ሳይቀር በመንፈሳዊ አስተምህሮ አንድ ከመሆን ይልቅ በምድራዊ ባንዲራ እየተቧደኑ ለመዘላለፍ ዳርጓቸዋል፡፡ ይህንን ክፍተትም ፖለቲከኞችና ሌሎች የቤተክርስቲያን መከፈል የሚያስደስታቸው ሰዎች ይጠቀሙበታል፡፡ ካህናትና ምዕመናን ተብለው በመንፈሳዊ አውደ ምህረት የሚሰበሰቡ ብዙ ግብዝ ሰዎችም በመንፈሳዊ ዓላማ ከሚመስላቸው ሰው ይልቅ በፖለቲካዊ ትንታኔና በሰንደቅ ዓላማዊ አንድነት የሚመስሏቸውን ሰዎች ሲያቀርቡ ይስተዋላል፡፡ በዚህም ሳናውቀው ሰቃልያነ እግዚእ አይሁድን እንመስላለን፡፡ እነርሱ አባቶቻቸው ከተውላቸው የነቢያት ተስፋ ይልቅ ለሚጠተ እስራኤል በመጨነቅ “ደሙ በእኛና በልጅ ልጆቻችን ላይ ይሁን” ብለው መድኃኒታቸውን የሰቀሉት በእግዚአብሔር ቤት ለሰማያዊ (ለመንፈሳዊ) ዓላማ ከመጨነቅ ይልቅ በምድራዊ ትብታብ ስለተያዙ ነበር፡፡ስለዚህ “የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር” (ማቴ 22፡21) እንደተባለ መንፈሳዊ/ሃይማኖታዊ ትርጉምና ዓላማ ያለውን ምልክት ለመንፈሳዊ አገልግሎት፣ ፖለቲካዊ ትርጉምና ዓላማ ያለውን ምልክት ደግሞ ለቆመለት ዓላማ ማዋል ይገባል፡፡ የሀገራዊ ምልክቶች ፖለቲካዊ ትርጉም፣ ፖለቲካዊ ዓላማና ፖለቲካዊ አጠቃቀም ለፖለቲከኞች ነው፡፡ የሃይማኖታዊ ምልክቶች መንፈሳዊ ትርጉም፣ ሃይማኖታዊ ዓላማና ክርስቲያናዊ አጠቃቀም ደግሞ ለሃይማኖት ሰዎች ነው፡፡ በአንድ ሳንቲም ላይ ‘የቄሳር’ እና ‘የእግዚአብሔር’ የሚል ጽሕፈት ቢኖርም ጌታችን “የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” እንዳለ ምልክቶች ቢመሳሳሉ እንኳን መንፈሳዊ ትርጉምን፣ ዓላማንና አጠቃቀምን ለቤተክርስቲያን፤ ፖለቲካዊ ትርጉምን፣ ዓላማንና አጠቃቀምን ደግሞ ለፖለቲከኞች መስጠት ይገባል፡፡ በፖለቲካው ንቁ ተሳትፎ ያላቸው ክርስቲያኖችም ቢሆኑ ፖለቲካውን በፖለቲካው አውድ፤ ሃይማኖታቸውን ደግሞ በመንፈሳዊው አውድ ማንጸባረቅ ይገባቸዋል፡፡ የተራራቀ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው የአንዲት ቤተክርስቲያን ልጆችም ቢሆኑ ይህን አመለካከታቸውን በቤተክርስቲያን ከሚኖራቸው ክርስቲያናዊ አንድነት ጋር ማያያዝ የለባቸውም፡፡ ከዚህ በተረፈ ፖለቲካዊ ዓላማ፣ ትርጉምና ትንታኔ ላለው ማንኛውም ምልክት ሃይማኖታዊ ካባ መደረብ አያስፈልግም፡፡ በዚህም ምክንያት የሚመጣው አላስፈላጊ ንትርክም ለቤተክርስቲያን ዕዳ እንጅ ጥቅም አይኖረውም፡፡

ስለዚህ ምን እናድርግ?

እያንዳንዱን አጥቢያ ቤተክርስቲያን ጨምሮ ቤተክርስቲያን እንደ ተቋም በባንዲራ ወገንተኝነት መተብተብ የለባትም፡፡ በዓላቶቿም በምድራዊ ቀለማት የሚደምቁ የፌሽታ ቦታዎች አይደሉም፡፡ ይሁንና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ብዙ ምዕመናን የባንዲራ ቀለማትን መጠቀም እንደሚወዱ ይታወቃል፡፡ ለዚህ መፍትሄው አንዱን መውቀስ፣ ሌላውን ማወደስ ሳይሆን ምዕመናን በየግላቸው የሚፈልጓቸው ቀለማትና አርማዎች የየራሳቸው ምርጫዎች እንጂ ቤተክርስቲያንን የሚወክሉ፣ አስተምህሮዋን የሚገልጹ አስመስሎ አለማቅረብ ነው፡፡ ምዕመናንን ይሄን ልበሱ፣ ይሄን አውልቁ የሚል አላስፈላጊ ንትርክም ቤተክርስቲያንን ጠላት ዲያብሎስ እንደሚመኘው የንትርክ አውድማ ያደርጋታል እንጂ ረብ የለውም፡፡ ይልቁንስ መንፈሳውያን መሪዎችና መምህራን በመንፈሳዊ ቦታ ምድራዊ የፖለቲካ ፉክክር እንዲፈጠር ያደረገውን መሰረታዊ ችግራቸውን መፍታት አለባቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቤት፣ የቤተክርስቲያን አውደ ምህረት፣ መንፈሳዊ በዓላት የከበረ ወንጌል የሚነገርባቸው፣ ለመንግስተ ሰማያት የሚያበቃ ምግባር የሚከብርባቸው እንጂ ሰዎች የወደዱትን የሚያሞግሱባቸው፣ የጠሉትን የሚኮንኑባቸው ምድራዊ አደባባዮች አይደሉም፡፡ ካህናትና መምህራን ትኩረታቸውን ቤተክርስቲያንን ወደሚወክለው አስተምህሮ በማድረግ ከጸኑ በጊዜ ሂደት ቤተክርስቲያን የምድራዊ ሰንደቆችና አርማዎች መፎካከሪያ ያደረጋትን መጤ አረም ማሸነፍና ለሁሉም ያለልዩነት መንፈሳዊ ዘርን መዝራቷን ትቀጥላለች፡፡

 

ክርስቲያናዊ አንድነታችን በእምነት መሠረቶቻችን ላይ የታነጸ መሆን አለበት እንጂ በሰንደቅ ዓላማ ወይም በፖለቲካዊ አመለካከት ልዩነት የተነሳ የሚፈረካከስ የአሸዋ ክምር መሆን የለበትም፡፡ በመንፈሳዊ በዓላትና ጉባኤያት ላይ የባንዲራ ፉክክር ማድረግ እንደ አይሁድ ሰማያዊ ተስፋን በምድራዊ፣ ውል አልባ የፖለቲካ ፍላጎት መተካት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቤተክርስቲያንን ያከስራታል እንጂ አይጠቅማትም፡፡ መንፈሳዊ አውዶች በምድራዊ ልዩነት በታጀበ ፉክክራዊ የሰንደቅ ዓላማ እሽቅድምድም ሲሞሉ ለጊዜው በስሜታዊነት የሚሰበሰቡ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ይሁንና የመሰባሰባቸው ምክንያት ፖለቲካዊ እንጂ መንፈሳዊ አይደለም፡፡ በመንፈሳዊ ቦታ ከመንፈሳዊ ሀሳብ ይልቅ ባንዲራ ማውለብለብን እና ለሚወዷቸው ፖለቲከኞች ደርዝ የሌለው ውዳሴ ማቅረብን ቁም ነገር አድርገው የሚያስቡ መለካውያን (ፈጻምያነ ፈቃደ ንጉስ፣ የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ ለመሪዎች ጥቅም ሲሉ የሚበርዙ አድርባይ አገልጋዮች) እንደሚሉት ቤተክርስቲያንን የሚወዷት ከሆነ ከዚህ መሰል አላስፈላጊና መንፈሳዊ ረብ የሌለው እሽቅድምድም መራቅ ይገባቸዋል፡፡ ቤተክርስቲያን በምታምንበት፣ በምትታመንበት ሰማያዊ ሰንደቅ፣ በቅዱስ መስቀል እንጂ በምድራዊ ምልክት አትወከልምና፡፡

ስብሃት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር፡፡ አሜን፡፡

 

መድኅን ተወልዶላችኋል!

lidet photo

“እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኽውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው፡፡” ሉቃ 2፡11

አዳም ከተሳሳተ ከገነትም ከወጣ በኋላ 5,500 ዘመን ሲፈፀም፣ ሕገ ኦሪት ከተሰጠች 1,800 ዘመን በኋላ፣ የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ከተሠራ 1,000 ዓመት በኋላ፤ በልደተ ሥጋዌ (ማቴዎስ) ተቆጥሮ ከአብርሃም 42 ትውልድ በኋላ፣ በልደተ ሕጋዊ (ሉቃስ) ተቆጥሮ ከአዳም 77 ትውልድ በኋላ፣  ከዛሬ 2011 ዓመት በፊት በዓለማችን ላይ አንድ ታላቅ ተአምር ተከናወነ፡፡

አውግስጦስ ቄሳር የሮም ገዥ፣ ሄሮድስ የይሁዳ ንጉስ፣ እንዲሁም ቄሬኔዎስ የሶርያ ገዥ በነበሩበት ወቅት የሰውን ልጅ ሕይወት ወደ ታላቁ የድኅነት ምዕራፍ ያሸጋገረ ታላቅ ክስተት በማዕከለ ምድር፣ በሀገረ እስራኤል ተከሰተ፡፡ ይህም የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ነው (ማቴ 1፡17)፡፡ የእርሱ ልደት ከሌሎች ልደታት ሁሉ ልዩ ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በነቢያት ትንቢት ተነግሮለት፣ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤልም ብስራት ተነግሮለት በህቱም ድንግልና ስለተወለደ የእርሱ ልደት እጅግ ልዩ ነው፡፡

በዚያ ወራት  ለግብር አሰባሰብ እንዲያመች በማሰብ ሰው ሁሉ እንዲቆጠር (እንዲፃፍ) ከአውግስጦስ ቄሳር ትዕዛዝ ወጣች፡፡ የእመቤታችን ጠባቂ የነበረው ዘመዷ አረጋዊው ዮሴፍም ከዳዊት ወገን ነበርና ፀነሳ ከነበረችው ከድንግል ማርያም ጋር ሊቆጠር ከገሊላ ናዝሬት ከተማ ተነስቶ ቤተልሔም ወደምትባል ከተማ ወደ ይሁዳ ሄደ፡፡ሁሉም በየወገኑ ይቆጠር ስለነበር ዮሴፍም ከዳዊት ወገን ስለነበር ወደቤተልሔም ሄዱ፡፡ ጌታም ከአሕዛብ ጋር (እነርሱን ሊያድን መጥቷልና) አብሮ ይቆጠር ዘንድ ወደዚያው አመሩ፡፡

በዚያም (በቤተልሔም) እያሉ የድንግል ማርያም የመውለጃዋ ወራት (9 ወር ከ 5ቀን) ደረሰ፡፡ የበኩር ልጅዋንም ወለደችው፡፡ ‹‹እኔም ደግሞ በኩሬ አደርገዋለሁ፤ ከምድር ነገስታትም ከፍ ይላል (መዝ 88፡27) ፡፡›› እንደተባለ የበኩር ልጅዋን ወለደችው፡፡ አውራ ነህ ስትል እንዲሁም እንደዚህ በዮሴፍና በኒቆዲሞስ ትገነዛለህ ስትልአውራ ጣቱን አሠረችው፡፡  በድርብ በፍታ ትገነዛለህ ስትል፤ ካህናት ሥጋህን ይጠቀልሉታል ስትል በጨርቅም ጠቀለለችው፡፡ በግርግምም አስተኛችው፤ በእንግዶች ማረፊያ ቦታ ስላልነበራቸው ህፃኑ በግርግም ተኛ፡፡

በዚህች ዕለት የመወለዱ ትንቢት ተፈፀመ፡፡ የመወለዱ ብስራትም ተፈፀመ፡፡ በነቢይ ‹‹ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች›› የተባለው (ኢሳ 7፡14) ተፈፀመ፡፡ ‹‹በጨለማ የሄደ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ በሞት ጥላና በጨለማ ሀገርም ለነበሩ ብርሃን ወጣላቸው (ኢሳ 9፡2)››እንደተባለም ያ ብርሀን ወጣ፡፡ እንዲሁም ‹‹ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኀያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።›› ኢሳ 9፡6 ተብሎ እንተተነበየም ሕፃን ተወለደ፡፡ ‹‹ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች ›› (ኢሳ 7፡15) እንደተባለም ስሙን አማኑኤል አለችው፡፡ አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ ማለት ነው፡፡ ‹‹ ከጽዮን ታዳጊ ይመጣል፤ ከያዕቆብም ኃጢአትን ያርቃል፡፡››(ኢሳ 59፡20)ተብሎ እንደተፃፈ መድኃኒት ክርስቶስ፣ አዳኝ ክርስቶስ፣ ወገኖቹን እስራኤል ዘነፍስን የሚታደግ (የታደገ) ክርስቶስ ከአማናዊት ጽዮን ከድንግል ማርያም ወጣ፣ ተወለደ፡፡ ለድንግል ማርያም ‹‹ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ›› እንዲሁም ለዮሴፍ ‹‹ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ” (ሉቃ 1፡31 ማቴ 1፡21) ተብሎ በመልአኩ እንደተነገረም ስሙን ኢየሱስ አሉት፡፡

አስቀድሞ በነቢያት ስለመወለዱ ብቻ ሳይሆን ስለሚወለድበትም ቦታም፡-‹‹አንቺም የኤፍራታ ምድር ቤተልሔም ሆይ! አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ነገር ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘለዓለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ከአንቺ ይወጣልኛል።››(ሚክ 5፡2) እንደተባለ ታላቁ የሰማይና የምድር ንጉስ በቤተልሔም ተወለደ፡፡ ‹‹ እነሆ በኤፍራታ ሰማነው፤ ዛፍ በበዛበትም ቦታ አገኘነው፡፡››(መዝ 131፡6)ተብሎ እንደተፃፈም የሕይወት እንጀራ የሆነው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእንጀራ ቤት  በተባለችው በቤተልሔም ተወለደ፡፡

የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት የተለያዩ አካላት በተለያየ መልክ ተቀበለውታል፡፡

  1. እንስሳት

እንስሳት ትንፋሻቸውን ገበሩለት፤ በዚያ የነበሩ እንግዶች ግን ሥፍራ አልሰጡትም፡፡ ‹‹በሬ ገዢውን አህያም የጌታውን ጋጥ አወቀ፤ እስራኤል ግን አላወቁኝም፥ ሕዝቤም አላስተዋሉኝም።››(ኢሳ 1፡3) እንደተባለ እንስሳት (አድግና ላህም) አወቁት፤ ሰዎች ግን አራቁት፡፡ በእንስሳት በግርግም መተኛቱ የትህትናው ጥግ ነው፡፡ ‹‹ወራሹ ሕፃን ሳለ ለሁሉ ጌታ ሲሆን ከአገልጋይ የሚለይ አይደለም ››(ገላ 4፡1) እንደተባለ ንጹሐ ባህርይ የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎች በሚያድሩበት በበረት ተኛ፡፡በቀዝቃዛ (ተስፋ በቆረጠ ልብ)፤ በጨለማ (ብርሀን በሌለው ኃጢአተኛ ልብ)፤ ንፁህ ባልሆነ (ኃጢአት ባጎሰቆለው ልብ) ቦታ ተወለደ (አደረ)፡፡

  1. መላእክት

የሰማይ መላእክት ልደቱን ለእረኞች አበሰሩ፤ ነገስታትን (ጥበበኞችን) ወደ ቤተልሔም መሩ፡፡ በጌታ ልደት መላእክት ከሰው ልጅ ጋር አብረው ዘመሩ፡፡ ‹‹በዚያ ሀገር እረኞች ነበሩ፤ ሌሊቱንም ተግተው መንጋቸውን ይጠብቁ ነበር፡፡ እነሆም፥ የእግዚአብሔር መልአክ በአጠገባቸው ቆመ፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅ ፍርሃትንም ፈሩ፡፡ መልአኩም እንዲህ አላቸው፣ “እነሆ፣ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን  ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፡፡ እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኽውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።›› ሉቃ 2፡8-13 ይህ ለእረኞቹ የተነገረው የልደቱ ብስራት ነው፡፡የተወለደው ለመላእክት ሳይሆን ለሰው ልጆች ነውና መላእክት ተወልዶልናል ሳይሆን ተወልዶላችኋል አሉ፡፡

ይህ ታላቅ የምሥራች የእምነታችን መሠረት ነው፡፡ እምነታችን ከእግዚአብሔር ስለመሆኑ መገለጫው ይህ ነው፡፡‹‹ ወንድሞቻችን ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፤ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም መጥተዋልና። የእግዚአብሔርን መንፈስና የሐሰትን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚያምን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማያምን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም እንደሚመጣ የሰማችሁት ሐሳዊ መሲህ ነው፤ አሁንም እንኳ በዓለም ውስጥ አለ።›› እንደተባለው የጌታችን ልደት የተዋህዶ መሠረቷ ነው፡፡ 1ኛ ዮሐ 4፡1-3

መልአኩ አስቀድሞ ለተናቁት ለእረኞች ልደቱን አበሰረ፡፡ ‹‹ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ ሠራዊት  እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ። “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ ” ይሉ ነበር።›› ሉቃ 2፡14 አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰውም አምላክ ሆነ፡፡ በመላእክት ዘንድ ምስጋና ተደረገ፤ በደቂቀ አዳምም ዘንድ አንድነት ሆነ፡፡ የሰው ፍቅር አገብሮት አምላክ ሰው ሆነ፡፡

የእግዚአብሔር መልአክ የሩቅ ነገስታትን ጌታ ወደተወለደበት ቦታ ወደ ቤተልሔም በብርሀን መራቸው፡፡ ነገስታቱ በምስራቅ ያዩት ኮከብ ሕጻኑ ባለበት ቦታ መጥቶ እስኪቆም ድረስ በሰው ቁመት ልክ ዝቅ ብሎ ይመራቸው ነበር፡፡ ይህ ኮከብ የእግዚአብሔር መልአክ ነበር፡፡ እስራኤልን በብርሃን ፋና የመራ ጥበበኞችን በኮከብ አምሳያ መርቶአቸዋል፡፡በቀን የሚያበራ፤ ወደ ምስራቅ የሚሄድ፤ ቆሞ በሰው ቁመት ወደታች የሚጠቁም መልአክ እንጂ ኮከብ አይደለም፡፡

  1. እረኞች

እረኞች የመወለዱን ብስራት ከመልአኩ ሰምተው ከመላእክት ጋር አመሰገኑ (ዘመሩ)፡፡  መልካም እረኛ እርሱ ነውና ልደቱም ቀድሞ ለእረኞች ደረሰ፡፡ ዮሐ 10፡11 እረኞቹ አመስግነውም አልቀሩም፡-‹‹እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ ተባባሉ። ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገረላቸውን ነገር ገለጡ። የሰሙትን ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር አደነቁ፡፡›› ሉቃ 2፡15-18 እረኞች ልደቱን ሰሙ፤ አመሰገኑ፤ ፈጥነው ሄዱ (በሌሊት መንጋቸውን ትተው)፤ አዩ፤ ያዩትንም ለሌሎች ገለጡ፡፡ እረኞችም እንደ ተባለላቸው ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ። የእውነተኛው እረኛ ልደት ለትጉሀን እረኞች ተበሰረ፡፡ በግርግም ተኝቶ ከካህናቱ ከጸሀፍቱ ሳይሆን ከእረኞች ምስጋናን ተቀበለ፡፡ የበጎች እረኞች የበጉን ልደት ከሊቃውንት ከመምህራን ከነገስታቱም ቀድመው ሰምተው አመሰገኑት፡፡

  1. የጥበብ ሰዎች

የሩቅ (የምስራቅ) ነገስታት – የጥበብ ሰዎች – ሊሰግዱለት ስጦታንም ሊያበረክቱለት መጡ፡፡ በቅርቡ የነበሩት ነገስታት በመጣው ሠራዊት ብዛትና ‹‹የተወለደው ንጉስ›› በመባሉ ደነገጡ፡፡የጥበብ ሰዎች በኮከብ (በመልአክ) ተመርተው፤ ሁለት ዓመት ተጉዘው መጥተው፤ ሰግደውለት (የነገስታት ንጉስ ነውና)፤ ወርቅን ለመንግስቱ፣ እጣንን ለክህነቱ፣ ከርቤንም ለሞቱ ገበሩለት፡፡ በነቢይ ‹‹የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤ የዓረብ ነገሥታት እጅ መንሻን ያመጣሉ” መዝ 71፡10። እንደተባለ የልደት (የገና) በዓል የስጦታ ቀን የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ የጥበብ ሰዎች ‹‹የተወለደው የአይሁድ ንጉስ ወዴት ነው?›› አሉ፡፡ ንጉስ ሆኖ የተወለደ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሌሎች ተወልደው ይነግሳሉ እንጂ ንጉስ ሆነው ሊወለዱ አይቻላቸውም፡፡ የጥብበ ሰዎች መወለዱንም አውቀው ስለነበር ‹‹የሚወለደው›› ሳይሆን ‹‹የተወለደው›› አሉ፡፡

  1. ሄሮድስና ኢየሩሳሌም

የሩቅ ሀገር ነገስታት በልደቱ ተደስተው አምሐ ሲያቀርቡ የቅርብ ነገስታትና ኢየሩሳሌም ግን ደነገጡ (ተረበሹ)፤ የቅርቡ ንጉስ ሄሮድስ ግን ‹‹የአይሁድ ንጉስ ተወለደ›› ሲባል ደነገጠ፡፡‹‹ የካህናት አለቆችንና የሕዝቡን ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ “ክርስቶስ በየት ይወለዳል?” ብሎ ጠየቃቸው። እንዲህም አሉት “በይሁዳ ክፍል ቤተ ልሔም ነው፤ በነቢይ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና…›› አሉት ። ከዚህምበኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠራቸው፤ ኮከቡ የታየበትንም ዘመን ከእነርሱ ተረዳ፡፡ “ሂዳችሁ የዚያን ሕፃን ነገር ርግጡን መርምሩ፤ ያገኛችሁትም እንደ ሆነ እኔም መጥቼ እሰግድለት ዘንድ በእኔ በኩል ተመልሳችሁ ንገሩኝ” ብሎ ወደ ቤተ ልሔምም ሰደዳቸው። › ማቴ 2፡4-9 ሄሮድስ ይህን ያለው እንደ ቃሉ ሊሰግድለት ሳይሆን ሊገድለው አስቦ ነበር፡፡ የጌታን ልደት የቅርቡ ንጉስ ሄሮድስ ሳይሆን የሩቆቹ ነገስታት ሰብአ ሰገል ሰሙ፤ እርሱ ሲሰማ ተረበሸ፤ እነርሱ ግን ሲያገኙት ተደሰቱ፡፡

ይህንን የጌታን ልደት እኛስ እንዴት እንቀበለዋለን? እንደ ቤተልሔም ሰዎች ወይስ እንደ እረኞቹ? እንደ ጥበብ ሰዎች ወይስ እንደ ሄሮድስ? የቤተልሔም ሰዎች በምድራዊ ተግባር ተጠምደው ሌሎች እንግዶችን በማስተናገድ ሲባክኑ ጌታቸው ሲወለድ ማደሪያ መስጠት አልቻሉም፡፡ ትጉሃን እረኞች ግን ከብቶቻቸውን በትጋት ሲጠብቁ የራሳቸውን ጠባቂ አገኙት፡፡ እኛም በተግባረ ሥጋ ብቻ ተጠምደን ቤተመቅደስ የተባለ ሰውነታችንን ለጌታችን ማደሪያ ከመሆን ከልክለን እንግዳ የተባለ ኃጢአት፣ እንግዳ የተባለ የዲያብሎስ ፍሬ እንዲሰለጥንብን መፍቀድ የለብንም፡፡ የጥበብ ሰዎች አባቶቻቸው የነገሯቸውን ተስፋ አስበው፣ ሩቅ መንገድ ተጉዘው፣ አምሐ ይዘው በመምጣታቸው ከመጡበት ያለማመን መንገድ ይልቅ በሌላ የእምነት መንገድ (የክርስቶስን ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆንን አምነው) ተመለሱ፡፡ (ማቴ. 2፡12)

በኢየሩሳሌም የነገሰ ሄሮድስና እረኝነታቸውን ረስተው፣ በምድራዊ ተንኮል ተጠምደው ሰማያዊ ተግባራቸውን የረሱት የአይሁድ አለቆች ግን በተስፋይቱ ምድር ተቀምጠው የጌታቸውን መወለድ ለመስማት አልታደሉም፡፡ ሲሰሙም ለክፋት እንጅ ለድኅነት አልተጠቀሙበትም፡፡ እኛም እንደ ጥበብ ሰዎች አባቶቻችን ያስተማሩንን የክርስቶስን ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆኖ በሥጋ ማርያም የመገለጥ ፍቅር እያሰብን እንደ ጥበብ ሰዎች አምሐ ልናቀርብለት ይገባል፡፡ ለእግዚአብሔር የምናቀርበው አምሐም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን ቤተመቅደስ የተባለ ሰውነታችንን እንዲሁም በዕውቀትና በእምነት የታነጸ አገልግሎታችንን ነው፡፡ (ሮሜ. 12፡1)

እንደ ሄሮድስና የአይሁድ አለቆች በተስፋይቱ ምድር በቅድስት ቤተክርስቲያን ተቀምጠን ከእግዚአብሔር ጸጋ ተለይተን እንዳንጣል ልንተጋ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም አብነታችን የጌታችን፣ የመድኃኒታችን እናት፣ የቅዱሳን ነቢያት ተስፋ ፍፃሜ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ናት፡፡ እርሷ የተደረገውን ሁሉ በልብዋ እያሰበች በአንክሮ ትጠብቀው ነበርና፡፡ (ሉቃ 2፡9)፡፡ የዓለም መድኃኒት መወለዱን፣ የነቢያት ትንቢት መፈፀሙን፣ የመላእክትን ምስጋና፣ የእረኞችን ምስጋና፣ የጥበብ ሰዎችን ምስጋና፣ ስግደትና ስጦታ በልብዋ አኖረችው፡፡ የምስጢር መዝገብ ናትና፡፡ እርስዋ በልብዋ ያኖረችው ነው ለእኛም የደረሰን፡፡

በዚህ ሁሉ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እንረዳለን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። 1ኛ ዮሐ 4፡9 እንዳለ፡፡ ይህን የእግዚአብሔርን ፍቅር መርምረን መፈጸም አንችልምና በአንክሮ እናደንቃለን፡፡

ይህን አስመልክቶ የደገኛው የባስልዮስ ወንድም፣ የኑሲስ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ እንዲህ አለ፡- “ለእኛም በሥጋ መገለጡን እንደሚገባው መርምረን ልናውቀው አይቻለንም፤ ጸጋን ለመስጠት ያደረገውን ተዋሕዶ የሚያምኑት ሰዎች ከእነርሱ ትምህርትን ይቀበሉ ዘንድ ይገባል ብሎ ቃል ስለእነርሱ ከተናገረላቸው ከመምህራን እንማር ዘንድ ያሻናል፡፡” ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ጎርጎርዮስ 35፡10፡፡ ስለዚህ ሁላችንም የተደረገልንን ድንቅ ተዓምር፣ የተሰጠንን ድንቅ ስጦታ እያሰብን ከቅዱስ ኤፍሬም ጋር እናመስግን፡- “በቅዱሳን ላይ የሚያድር እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ልዩ ከሆነች ድንግል ሰው ሆኗልና፣ ኑ ይህን ድንቅ እዩ፣ ስለተገለጠልን ምስጢር ምስጋና አቅርቡ፣ ሰው የማይሆን ሰው ሆኗልና፣ ቃል ተዋህዷልና፣ ጥንት የሌለው ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊ ሆነ፣ ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት፣ የማይታወቅ ተገለጠ፣ የማይታይ ታየ፣ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ በእርግጥ ሰው ሆነ” የረቡዕ ውዳሴ ማርያም፡፡

የተደረገልንን አስበን የጌታችንን ልደት እንደ ዮሴፍና ሰሎሜ በአንክሮ፣ እንደ ጥበብ ሰዎች በአምሐ፣ እንደ ቤተልሔም እረኞች አገልግሎታችንን በትጋት በመፈጸም፣ እንደ ቅዱሳን መላእክት በሰማያዊ ምስጋና እንድናከብር የቅዱሳን አምላክ፣ የአብ የባህርይ ልጅ፣ የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱ ይጎብኘን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር