ሴቶች በቤተ ክርስቲያን (ክፍል ፫): አለባበስ

women in church_2የሰው ልጅ ሕግን ተላልፎ ጸጋውን ከተገፈፈ በኋላ ሰውነቱን መሸፈን አስፈልጎታል። ይህም በመጀመሪያ በቅጠል፣ ከዚያም ከቆዳ በተሠሩ ‘አልባሳት’ እና ቀጥሎም የሰው ልጅ የስልጣኔ ውጤት በሆኑት ከጨርቅ የተሠሩ አልባሳትን በመጠቀም ሲፈጸም ኖሯል። ልብስ የመልበስ ዋናው ዓላማ ሰውነትን መሸፈንና ከብርድና ከሐሩር መከላከል ቢሆንም በዘመናት ብዛት አለባበስ የባህልና የማንነት ነፀብራቅ እንዲሁም የውበት መገለጫ ሆኗል። በክርስትና ሃይማኖትም አለባበስ (በተለይም የሴቶች አለባበስ) አንዱ የሚያወያይ ጉዳይ ነው። የሴቶችን አለባበስ በተመለከተ ማስተማርም ይሁን መመካከር የሚገባቸው በዋናነት ሴቶች ራሳቸው መሆናቸውን እንገነዘባለን።  ይህን ታሳቢ በማድረግ በዚህች ጦማር የሴቶች አለባበስን የሚመለከቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮዎችንና ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮችን እንመለከታለን።

የጸሎት ጊዜ (የቤተክርስቲያን) አለባበስ

በቤተክርስቲያን ያለው የሁሉም ሰው አለባበስ ሥርዓት ያለውና በተለይም ለጸሎት የሚገባ መሆን እንዳለበት ቅዱሳት መጻሕፍትና የቤተክርስቲያን ትውፊት ያስረዳሉ። ይህም ወንዶችም ሴቶችም ነጭ ነጠላ ለብሰውና መላእክትን መስለው (ነጭ የነፃነትና የጽድቅ ምሳሌ ነውና)፣ ሴቶች ፀጉራቸውን ሸፍነው፣ ወንዶች ራሳቸውን ሳይሸፍኑ መጸለይ እንደሚገባቸው የተነገረው ነው። ሐዋርያው ይህን አብራርቶ ሲገልፅ “ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም ትንቢት የሚናገር ወንድ ሁሉ ራሱን ያዋርዳል። ራስዋን ሳትሸፍን ግን የምትጸልይ ወይም ትንቢት የምትናገር ሴት ሁሉ ራስዋን ታዋርዳለች፤ እንደ ተላጨች ያህል አንድ ነውና። ሴትም ራስዋን ባትሸፍን ጠጉርዋን ደግሞ ትቆረጥ፤ ለሴት ግን ጠጉርዋን መቆረጥ ወይም መላጨት የሚያሳፍር ከሆነ ራስዋን ትሸፍን። ወንድ የእግዚአብሔር ምሳሌና ክብር ስለ ሆነ ራሱን መከናነብ አይገባውም፤ ሴት ግን የወንድ ክብር ናት።… በእናንተ በራሳችሁ መካከል ፍረዱ፤ ሴት ራስዋን ሳትሸፍን ወደ እግዚአብሔር ልትጸልይ ይገባታልን? ወንድ ጠጉሩን ቢያስረዝም ነውር እንዲሆንበት፥ ሴት ግን ጠጉርዋን ብታስረዝም ክብር እንዲሆንላት ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁምን? ጠጉርዋ መጎናጸፊያ ሊሆን ተሰጥቶአታልና።” በማለት አስተምሯል፡፡ ነገር ግን ይህ ለጸሎት (በቤተክርስቲያን ለማስተማር ለመማር፣ ለመዘመር፣ ቅዳሴ ለማስቀደስ ፣ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል) ወቅት የተነገረ መሆኑን ማስተዋል ይገባል (1ኛ ቆሮ 11:4-15)።

በተጨማሪም ቤተክርስቲያን ቆጥራ፣ ለይታ ከምትቀበላቸው ከ81ዱ ቅዱሳት መጻሕፍት አንዱ በሆነው የሐዲስ ኪዳን የሥርዓት መጽሐፍ ‘ነገር ግን ላመኑ ሴቶች ራሳቸውን በንጽሕና ሊከናነቡ ይገባል፡፡ የፊታቸውን ውበት በማሳመርና ቀለም በመቀባት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በፈጠረው መልክ ውስጥ ጥቅም በሌለው ኩል መኳልና ማጌጥም አይደለም፡፡ እንደዚህ ያለውን ሁሉ አይሥሩ፡፡ ነገር ግን እነርሱ ተከናንበው ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ይሂዱ። (ዲድስቅልያ አንቀጽ 3)” በማለት ተገልጿል። ቅዱሳት መጻሕፍት “ራስን ዝቅ ስለማድረግ” የሚያስተምሩት ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም፣ ይልቁንም ከፍ ባለ አገልግሎት ለተሰማሩት ሁሉ መሆኑን ማስተዋል ይገባል እንጂ የመጻሕፍትን ንባብ ያለአውድ እየጠቀሱ ማኅበራዊ ኢፍትሃዊነትን ለማንበር መጠቀም አይገባም።

ሴቶች በሚገባ ልብስ ሰውነታቸውን ይሸልሙ!

ሴቶች በሚገባው መንገድ እንዲሸለሙ፣ እንዲዋቡና እንዲያጌጡ መጽሐፍ ያስተምረናል። ከዚህ አኳያ የወንድም ይሁን የሴት ክርስቲያን አለባበስ ሌሎችን በዝሙት ምኞት እንዳይፈትን መደበኛ ልብስ፣ የራሳቸውን ኢኮኖሚም እንዳይፈታተን በአቅማቸው ያለውን ልብስ ቢለብሱ መልካም ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን በሚመለከት “እንዲሁም ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤ እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ፥ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቍ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ። (1ኛ ጢሞ 2፡9-10) በማለት አስተምሯል።

ቅዱስ ጴጥሮስም “እንዲሁም፥ እናንተ ሚስቶች ሆይ፥ ከባሎቻችሁ አንዳንዱ ለትምህርት የማይታዘዙ ቢኖሩ፥ በፍርሃት ያለውን ንጹሑን ኑሮአችሁን እየተመለከቱ ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው ኑሮ እንዲገኙ ተገዙላቸው። ለእናንተም ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። እንዲህ በቀድሞ ዘመን በእግዚአብሔር ተስፋ ያደረጉት ቅዱሳት ሴቶች ደግሞ ለባሎቻቸው ሲገዙ ተሸልመው ነበርና” በማለት ስለአለባበስ አስተምሯል፡፡ 1ኛ ጴጥ 3፡2-5

የሴትና የወንድ ልብስ የተለያየ ነው!

በሴቶች አለባበስ ዙሪያ ከሚነሱ ነገሮች አንዱ ሱሪ የመልበስ ጉዳይ ነው። ብዙውን ጊዜ ስለ ወንዶች አለባበስ ባይነሳም የሴቶች አለባበስ ግን ታላቅ ርዕስ ነው የሚሆነውን ከዚህ የተነሳ ነው። አንዳንዶችም “ለምን የሴቶች አለባበስ ላይ ብቻ ታተኩራላችሁ? የወንዶች አለባበስስ ቅጥ እያጣ መጥቶ የለም ወይ?” ሲባሉ “የሴቶች አለባበስ ወንዶችን በዝሙት ስለሚፈትን ነው” ይላሉ። ምክንያቱ ይህ ከሆነ “ወንዶች በአለባበስ የማይፈተን ልብ እንዲኖራቸው፣ ስሜታቸውን እንዲቆጣጠሩ ለምን አታስተምሩም?” ሲባሉ መልስ የላቸውም። ችግሩ የዝሙት ፈተና ከሆነ የሚመለከተው ሁለቱንም እንጂ ሴቶችን ብቻ አይደለም። የዝሙት ሀሳብም ከሰው ልብና ሕሊና የሚመነጭ እንጂ አንድ አይነት አለባበስ ሲያዩ የሚከሰት ሌላ አይነት አለባበስ ሲያዩ የሚከስም ፍላጎት አይደለም። ከሌላም አንጻር ሲታይ ሴቶች የሚለብሱት የሚገባውን፣ ለሥራ የሚመቻቸውን፣ የሚወዱትንና የሚያምርባቸውን ልብስ ነው። ከዚህ በተቃራኒ ሴቶች የወንዶችን ትኩረት ለመሳብ ብለው ይለብሳሉ ማለት በጣም የተሳሳተ ጥቅል ፍረጃ (hasty generalisation) ነው። የዚህ ሁሉ ስሁት አስተሳሰብ መሠረታዊው መነሻ ግን ለሴቶች ያለው የተሳሳተ አመለካከት ነው።

በተለይም “ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ፣ ወንድ የሴት ልብስ አይልበስ”  (ዘዳ 22:5) የሚለውን በመጥቀስ “ሴት ሱሪ መልበስ የለባትም” ብለው የሚከራከሩ ወገኖች ቁጥር ጥቂት አይደለም። ይህ የመጽሐፍ ቃል ግን ለሚያስተውለው ሰው የሚያመለክተው የወንድና የሴት ልብስ የተለያየ መሆን እንዳለበትና ለአንዱ የተዘጋጀውን ወይም አንዱ የሚለብሰውን ልብስ ሌላው እንዳይለብስ ነው። ይህም የፆታ ልዩነት በአለባበስም ጭምር የሚገለጥ መሆኑን ያመለክታል። ከዚህ ባለፈ ግን “የወንድ ልብስ ይህ ነው፣ የሴት ልብስ ያ ነው” በሚል አስተሳሰብ ሊወሰን አይገባውም። የወንድና የሴት ልብስም እንደየባህሉ፣ የአየር ፀባይ፣ የሙያ ዘርፍና ሥልጣኔ ደረጃ የሚለያይ ስለሆነ ከዚህ ልብስ ውጭ ወይም ይህንን ልብስ ብቻ ልበሱ ማለት አስቸጋሪ ነው። በተለይም ወንዶችን ትቶ ሴቶችን ብቻ የማይለወጥ አለባበስ እንዲኖራቸው የሚጎተጉት እይታ ምንጩ ከመንፈሳዊነት ይልቅ በማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ሴቶችን አሳንሶ የማየትና የፆታ እኩልነትን ያለመቀበል ዝንባሌ የወለደው ይመስላል።

ክርስትና ክርስቶስን መልበስ ነው!

ጠቢቡ ሰሎሞንም “የወርቅ ቀለበት በእርያ አፍንጫ እንደ ሆነ፥ ከጥበብ የተለየች ቆንጆ ሴትም እንዲሁ ናት (ምሳ 11፡22)” በማለት ሴት ውብ ብቻ ሳይሆን በልቧም ጥበበኛም መሆን እንደሚገባት ተናግሯል፡፡ እንዲሁም ስለልባም ሴት ሲናገር “ብርታትና ከበሬታ ልብስዋ ነው፤ በኋላም ዘመን ላይ ትስቃለች (ምሳ 31፡25)” በማለት ገልጿታል፡፡ ይህም ሴቶች ከውጭ ውበት ጋር ውስጣዊ ጥበብን ገንዘብ ማድረግ እንዳላባቸው ያስተምረናል። ከዚህም አንጻር በክርስትና ሕይወት ዋናው ጉዳይ ክርስቶስን መልበስ ነው እንጂ የሚያረጅ ልብስን መልበስ አይደለም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲገልፅ “ክርስቶስን ልበሱት” (ሮሜ 13:14) ነው ያለው። ስለዚህ ክርስትናችን በልብስ ጉዳይ ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ የሕይወታችን መሠረት የሆነው ክርስቶስን የመልበስ ጉዳይ ላይ ሊያተኩር ይገባል። ክርስቶስን መልበስ በምን ይገለፃል? በማኅበረሰባችን ዘንድ ያለው የሴቶችን አለባበስ ብቻ ነጥሎ የሚያጠቃ መንፈሳዊ መሠረት የሌለው ፍረጃ የአስተሳሰብ ምንጮቹ ምንድን ናቸው? የሚከተሉትን ማሳያዎች ተጠቅመን እነዚህን ሀሳቦች እንመርምር።

ማሳያ 1: ቀሚስ ዋነኛ የአገልግሎት መመዘኛ?

መንፈሳዊ አገልግሎት ራስን ከማሳየት እግዚአብሔርን ወደማሳየት ለማደግ የሚደረግ ጉዞ ነው ልንለው እንችላለን። ስለሆነም ለአገልግሎት ቅድሚያ የሚሰጡ መንፈሳውያን አገልጋዮች በኑሮአቸው ሁሉ የግል ፍላጎታቸውን በመጫን፣ ራስን መግዛትን በሚያሳይ አለባበስ መታየታቸው የሚያስመሰግናቸው ነው። ለመንፈሳዊ ዓላማ ሥጋዊ ውበትና ምቾትን መተው ዋጋ ያለው ሰማዕትነት ነው። ይሁንና በተደጋጋሚ እንደታዘብነው ቀሚስ መልበስን ብቸኛ (ዋነኛ) የመንፈሳዊነት ማሳያ እና ለመንፈሳዊ አገልግሎት የመመረጥ የይለፍ ኮድ (pass code) ሲሆን ይታያል። ቀሚስ መልበስ በሰንበት ት/ቤቶች፣ በግቢ ጉባኤያትና መሰል የአገልግሎት ማኅበራት ሴቶችን ወደአገልግሎት ለማቅረብ በታዋቂም በውስጠ ታዋቂም እይታ እንደ ዋነኛ መመዘኛ የሚቀርብባቸው ቦታዎች ብዙ ናቸው። በብዙዎች ዘንድ ሊታወቁ የሚችሉ ውሳጣዊ የመንፈሳዊነት ማሳያዎችን እንደአቅም ከመመርመር ይልቅ በቀሚስ መልበስ ላይ የተንጠለጠለ የአገልግሎት ምርጫ ይደረጋል።

ስለሆነም ከላይ በተጠቀሱት መስኮች ሴቶችን ወክለው በአገልግሎት ኃላፊነት የሚቀመጡት እህቶቻችን በቁጥር በጣም አነስተኛ ይሆናሉ። በአንፃሩ ሌሎች በልዩ ልዩ ማሳያ እውነትም ክርስቶስን የለበሰ ማንነት ያላቸው እህቶቻችን ከሚወዱት፣ ከሚፈልጉት አገልግሎት በቀሚስ ምክንያትነት በአፍአ ይቀራሉ። ለወንዶች ሲሆን እምብዛም የማይተኮርበት አለባበስ በቤተክርስቲያን አገልግሎት በቂ ሱታፌ እንዳይኖራቸው ባህልና ልማድ የከለከላቸውን ሴቶች የበለጠ ያርቃል። በተለይም ለራሳቸው ከቤተክርስቲያን ትውፊትና ሥርዓት በሚጣላ ሁኔታ ቀሳውስቱ እንደመነኮሳት፣ እንደ ጳጳሳት፣ መምህራኑና ዘማርያኑም እንደቤተክርስቲያን ውርስ ሳይሆን እንደ ምዕራባውያን ሴሚናሪ ሰዎች በማስመሰል በዓለማዊ አሸንክታብ የተሞሉ የማስመሰል ቀሚሶችን የሚለብሱ የዘመናችን ተርእዮ (ታይታ) ወዳጅ ካህናትና መምህራን ይህን መሰሉን ያልተመጠነ ትችት በሴቶች አገልጋዮች ላይ ማቅረባቸው መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን ሞራላዊ መሰረትም የለውም።

ማሳያ 2: ቀሚስ ሲወልቅ አብሮ የሚወልቅ መንፈሳዊነት

ከላይ በተጠቀሰው መልኩ የሚገለፀውbምክንያት ቀሚስ ብቻ መልበስን ሲተው በሚገርም ሁኔታ በርካታ የመንፈሳዊነት መገለጫዎችንም አብረው ያወልቋቸዋል። ይህም ቢቻል በፈሪሐ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን በመፍራት) ባይቻል ደግሞ በአክብሮተ ሰብዕ (ሰዎችን በማክበር) የሚፈፀሙ መንፈሳዊ ፍሬዎችን ከአለባበስ ለውጥ ጋር በመተው “ከታሰረበት እንደተፈታ” የመሆን ውጤት ሲያመጣ ታዝበናል። ለሴቶች ቀሚስ መልበስ ብቻውን የጥሩ ክርስቲያንነት መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም። ቀሚስ አለመልበስም ብቻውን የኃጢአተኝነት መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም። ነጭ ነጠላን መልበስም እንዲሁ ነው። ሥርዓት ያለው አለባበስ አስፈላጊ ቢሆንም ብቸኛ የጥሩ ክርስቲያንነት መስፈርት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። መንፈሳዊ ሕይወት በልብስ ብቻ ሳይሆን በልብ፣ በሀሳብ፣ በንግግርና በተግባር የሚገለጥ ነውና። ይሁንና በአንዳንዶች ዘንድ ልማድ እንደሆነው “አለባበስ ከመንፈሳዊነት ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና የለውም” ወደሚል የተሳሳተ ፅንፍ መሄድ አይገባም። የዚህ ጦማር ዓላማም ሴቶች ላይ ብቻ የሚያተኩሩ የአለባበስ እሳቤዎች ከመንፈሳዊ ይልቅ የተዛባ ማኅበራዊ እይታን እንደሚያሳዩ መተንተን እንጂ “ችግር የለውም፣ ያለ ገደብ ያሰኛችሁን ሁሉ ልበሱ” ለማለት አይደለም።

መልእክተ አስተምህሮ

በአለባበስ ጉዳይ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችና የሚደረጉ ክርክሮች ሴቶች ላይ ብቻ የሚያተኩሩት በማኅበረሰቡ ውስጥ ለሴቶች ባለው የተዛባ አመለካከት የተነሳ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህንን የምንለው የአለባበስ ችግሮች የሚታዩት በሁለቱም ፆታዎች ስለሆነ ነው። ከአለባበስ አንጻር የቤተክርስቲያን አስተምህሮ የሚመለከተው በቤተክርስቲያን (በጸሎት ጊዜ) ያለውን አለባበስ ነው። ይህም በዋናነት በጸሎት ጊዜ ሴቶች ጸጉራቸውን ይሸፍኑ፣ ወንዶች ጸጉራቸውን አያሳድጉ (አይሸፍኑ) የሚል ነው። ቤተክርስቲያን እንደተቋምም ቢሆን የራሷን የአለባበስ ሥርዓት ማስቀመጧ የተገባ ነው። እንኳን በሰማያዊ ንጉሥ በእግዚአብሔር ፊት ለሚደረግ አምልኮና አገልግሎት ምድራዊ ዓላማ ያላቸው ተቋማትም የራሳቸው የአለባበስ መመሪያ (dressing code) አላቸውና። በምድራዊ መሥሪያ ቤት እንኳን የአለባበስ መመሪያ ተግባራዊ ከሆነ ሰማያዊት በሆነችው ቤተክርስቲያን እንዴት አብዝቶ አይከበር?! የቤተክርስቲያን የአለባበስ ስርዓት እንዳለ ሆኖ ከቤተክርስቲያን (ከጸሎት ውጭ) ያለው አለባበስ ግን የየማኅበረሰቡን የአለባበስ ባህል (norm) ያማከለ ሊሆን ይገባዋል። ክርስቲያን በሥራ ቦታም የየመስሪያ ቤቱ መመሪያ በሚያዘው ወይም የሥራው ፀባይ (dressing code) መከተል አስገዳጅ ሊሆን ይችላል።

የሴቶችን አለባበስ ስናነሳ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ስለሴቶች አለባበስ ጥናት በማድረግ፣ በማስተማር፣ ምክረ ሀሳብ በማቅረብ ሴቶች መሪ ተዋናይ መሆን እንደሚገባቸው ነው። ለዚህም ሴቶችን በዕውቀትና በክህሎት ማብቃትና የውሳኔ ሰጭነት ኃላፊነት መስጠት ያስፈልጋል። ከዚህ ውጭ (የቤተክርስቲያን ሥርዓት የተጠበቀ ሆኖ) ‘እኛ እናውቅላችኋለን፣ እኛ የምንላችሁን ብቻ አድርጉ’ አይነት አካሄድ የትም አያደርስም፣ ይልቁንም ቤተክርስቲያንን በሂደት ያደክማታል እንጂ አይጠቅማትም። በአጠቃላይ ሲታይ ግን የክርስቲያን በተለይም የሴቶችን አለባበስን በሚመለከት የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ በአራት መልእክቶች ላይ ያተኩራል።

መልእክት 1: የማይፈትን አለባበስ

የቤተክርስቲያን አስተምህሮ እያንዳንዱ ክርስቲያን (ወንድም ሴትም) የራሱን እና የሌላውን ሰው ክርስቲያናዊ ሕይወት የማይጎዳ አለባበስን እንዲያዘወትር ይመክራል። ክርስቲያን ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ሕይወት ያስባልና አለባበሱ ሌላውን የሚፈትን ከሆነ የሚወደው አለባበስ እንኳን ቢሆን በማይፈትን መልኩ ሊያደርገው ይገባል። ቅዱስ ጳውሎስ “ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ ከእንግዲህ ሥጋ አልበላም” ባለው መሠረት አለባበሳችንም ሌላውን የሚያሰናክል ከሆነ “የራሱ ጉዳይ” ማለት ሳይሆን ለሌላውም ሊያስብ ይገባዋል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በተለይ በአለባበስ ሰውን መፈተን እንደሚያስጠይቅ አስተምሯል። ነገር ግን ሰውን የሚፈትን ወይም ከቤተክርስቲያን ሥርዓት የወጣ አለባበስ ለብሰው ወደ ቤተክርስቲያን የሚመጡ ምዕመናንን በፍቅር ቀርቦ ማስተማር ይገባል እንጂ በመፍረድ፣ በማንጓጠጥ፣ በመሳደብ፣ በመተቸት፣ በማጥላላት፣ በማግለል፣ በሐሜት ወይም ሌሎች ኢ-ክርስቲያናዊ የሆኑ ጸባያትን በማሳየት ከቤተክርስቲያን ማራቅ አይገባም።

መልእክት 2: በአቅም መልበስ

የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ክርስቲያኖች ከኢኮኖሚ አቅማቸው በላይ ውድ የሆኑ ልብሶችን መልበስ ጉዳት እንዳለው ያስተምራል። ከአቅም በላይ ውድ የሆኑ ልብሶችን መልበስ የኢኮኖሚ አቅምን አቃውሶ ለድህነት ከመዳረጉም በላይ ለጥፋት በሚታትሩ ሰዎች ትኩረት ውስጥ መግባትን እና በክርስትና ሕይወትም መፈተንን ያመጣልና። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “በመጠን ኑሩ” ብሎ ያስተማረው በአለባበስም ጭምር መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል። ይልቁንም ክርስቲያን ለራሱ በመጠን እየለበሰ የታረዙትን ሊያለብስ ይገባዋል እንጂ ለራሱ ብቻ ውድ ልብስን መልበስ ላይ ሊያተኩር አይገባውም።

መልእክት 3: ባህልን መዋጀት

ክርስትናን በተወሰነ ባህላዊ ማንነት አጥረው “ክርስትና የራሱ ባህል ስላለው ክርስቲያን ባህልን መዋጀት አያስፈልገውም” በሚል እሳቤ የሚያምኑ ወገኖች ቢኖሩም ከተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ግን ክርስቲያን ሴቶችም ሆኑ ወንዶች በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ያለውን የአለባበስ ባህል ከክርስትናቸው ጋር አጣጥመው ሊዋጁ ይገባል እንላለን። ክርስቲያን በሕይወቱ ክርስቶስን መምሰል እንዳለበት ግልጽ ነው። ከክርስትናው ጋር በሚጣጣም (በማይጋጭ) መልኩ የአካባቢውንም ባህል መዋጀትም መልካም ነው። ይህም ቅዱሳን ሐዋርያት ጭምር የሚያስተምሩትን ሕዝብ አለባበስ ለብሰው በማስተማራቸው ተገልጧል። ክርስቲያንም በአካባቢው ባህል መሠረት መልበሱ ራሱንም ሆነ ሌሎችን ፈተና ላይ ከመጣል ያድነዋል። በማኅበረሰቡም “አፈንጋጭ” ተብሎ ከመገለልም ይተርፋል። በሌላ በኩል በክርስቲያናዊ አለባበስ ስም የአንድን ማኅበረሰብ የአለባበስ ባህል በሌላው ላይ መጫን አይገባም። ይህንን ማድረግ የአንድን ማኅበረሰብ ባህል ካለማክበሩም ባሻገር ቤተክርስቲያንን በዚያ ማኅበረሰብ ዘንድ ባዕድ እንድትሆን ያደርጋታል። ሁሉም በራሱ መንገድ የቤተክርስቲያንን መንፈሳዊ መልክ እንዲያንፀባርቅ ማድረግ እንጂ “ቀድሞ የተንፀባረቀውን ብቻ እንከተል” ማለት አይገባም።

መልእክት 4: የቤተክርስቲያንን ሥርዓት መጠበቅ

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን እና ካህናት የቤተክርስቲያኒቱን አስተምህሮ፣ ሥርዓትና ትውፊት የሚያንጸባርቅ አለባበስ ሊኖራቸው እንደሚገባ እሙን ነው። ይህ በተለይም በቤተክርስቲያን እና መንፈሳዊ አገልግሎቶች በሚፈጸሙባቸው መርኃግብሮች ሊተገበሩ ይገባል። የቤተክርስቲያን መምህራንም ይህንን በሰፊው ማስተማር ይገባቸዋል። እናቶች ለሴት ልጆቻቸው፣ እህቶችም ለሌሎች በዕድሜ ታናናሽ ለሚሆኗቸው እህቶቻቸው በመንፈሳዊ አገልግሎት የቤተክርስቲያንን የአለባበስ ሥርዓት ማስተዋወቅና ማስተማር ይገባቸዋል። ነገር ግን ሁሉም አስተምህሮ በመጻሕፍትና በትውፊት ባለው ላይ ሊመሠረት ይገባዋል እንጂ በተወሰነ ማኅበረሰብ ባህል ወይም በተወሰኑ ግለሰቦች የወግ አጥባቂነት አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ መሆን የለበትም። ይህን መሰሉ አካሄድ ቤተክርስቲያንን የአልባሳት ፉክክር መድረክ ከማድረግ አያልፍም።

ስለዚህም ሁሉም ክርስቲያን በጸሎት ወቅት (በቤተክርስቲያን) የክርስቶስን ትንሣኤ ምስክርነት የሚገልጸውን ነጭ ልብስ መልበስ ይገባዋል። ከሥርዓት የወጣ አለባበስ በቤተክርስቲያን ሲታይም ስለ መልካም አለባበስ ቀስ በቀስ በማስተማር እንጂ ሰውን በማንጓጠጥ፣ ማሸማቀቅና በማግለል በሰው ላይ በደል መፈጸም አይገባም። ማሸማቀቅና ማግለል ሰውን ከቤተክርስቲያን ያርቀዋል እንጂ አያቀርበውም። ሰውን በመፍራት ብቻ የምንከተለው አለባበስም ዘለቄታ የለውም። ሰው ተምሮ፣ እውቆ፣ ተረድቶና አምኖበት አለባበሱን እንዲያስተካክል ዕድል ሊሰጠው ይገባል። በመጨረሻም የክርስትናችን ዋናው ትኩረት በውጭ በሚታየው አለባበስ ላይ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ መንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ ሊሆን ይገባል እንላለን። በልጅነት ጥምቀታችን የለበስነው ክርስቶስ በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ጸንተን መንግስቱን ለመውረስ ያብቃን። አሜን!

 

 

ሴቶች በቤተ ክርስቲያን (ክፍል ፪): የፆታ እኩልነት

women in church_2

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምኖ የተጠመቀ ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ባገኘው የሥላሴ ልጅነት ያለምንም ልዩነት አንድ ነው። ይሁንና በአንዳንድ ወገኖች በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለውን የተፈጥሮ ልዩነት መነሻ በማድረግና በመጽሐፍ ቅዱስ የተቀመጡ አንዳንድ ታሪኮችንና ትምህርቶችን የተለያየ ትርጓሜ በመስጠት ወንዶችን ከሴቶች አስበልጦ የመመልከት (ሴቶችን ከወንዶች አሳንሶ የማየት) ነገር ይስተዋላል። በዚህም የተነሳ  በተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት የፆታ እኩልነትን የማረጋገጥ እንቅስቃሴ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። የእኛ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ የሴቶችን ድርሻ በጉልህ ቢገልጽም አሁንም ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ያለመስጠት ሁኔታ ከመታየቱም በላይ በዚህ ዘመንም ሴቶችን አግላይ የሆኑ አገልግሎቶችና በሴቶችም ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች አሉ። ሴቶች በቤተክርስቲያን በሚለው ዋና ርዕሰ ጦማር የመጀመሪያ ክፍል በቅዱሳት መጻሕፍትና በቤተክርስቲያን የኋላ ዘመን ታሪክ የቅዱሳት አንስት(ሴቶች)ን አገልግሎት በመጠኑ አሳይተናል። በዚህች የአስተምህሮ ጦማር “ሴቶች በቤተክርስቲያን” በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ሥር ሁለተኛ የሆነውን የፆታ እኩልነትን (Gender Equality) የሚመለከቱ ሀሳቦችን እንዳስሳለን።

ሔዋን ከአዳም መፈጠሯ ከአዳም አያሳንሳትም!

እግዚአብሔር “ሰውን በመልካችን፣ እንደምሳሌያችን እንፍጠር” ካለ በኋላ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። አስቀድሞ አዳምን ከመሬት አበጀው። የሕይወትንም እስትንፋስ እፍ አለበትና ሕያዊት ነፍስ ያለው ሆነ። ለአዳምም እንደርሱ ያለ ረዳት ስላልተገኘለት እግዚአብሔር ከአዳም ጎን አንዲት አጥንት ወስዶ ሴት አድርጎ ሠራት። ይህችም ሴት የሁሉ እናት የሆነችው ሔዋን ናት። አንዳንድ ወገኖች ሔዋን ከአዳም ተገኝታለችና “ወንድ ከሴት ይበልጣል፣ ሴትም ከወንድ ታንሳለች” ሲሉ ይከራከራሉ። የመጽሐፉን ቃል በሚገባ ላስተዋለው ግን ወንድ ከሴት ይበልጣል፣ ሴትም ከወንድ ታንሳለች የሚል መልእክት የለውም። በመጀመሪያ “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረው፣ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው (ዘፍ 1:28)” የሚለው ሁለቱንም በምሳሌውና በመልኩ እኩል አድርጎ መፍጠሩን ያሳያል። የሰጣቸው በረከትና ስልጣንም እንዲሁ አንድ ዓይነት ነው። ለአዳም ትልቅ ስልጣን፣ ለሔዋን ትንሽ ስልጣን ወይም ለአዳም ትልቅ በረከት ለሔዋን ትንሽ በረከትን አልሰጠም። ሁለቱንም ባረካቸው፣ በምድር ላይ ይበዙ ዘንድ፣ በምድርም ያሉትንም ሁሉ ይገዙ ዘንድ ስልጣንን ሰጣቸው እንጂ።

አዳም ከእርሱ የተፈጠረችውን ሔዋን “ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል” ያለው፣ እንዲሁም “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ (ዘፍ 2:23-24 ማቴ 19:4-6)” የተባለው አዳምና ሔዋን አንድ እና እኩል መሆናቸውን ያረጋግጣል። አንድ አካል የሆኑ አዳምና ሔዋን እኩል እንጂ የሚበላለጡ አይደሉም። ሌላው ማስተዋል ያለብን ግን አዳም ከመሬት፣ ሔዋንም ከአዳም ቢገኙም ከእነርሱ በኋላ ያሉ ሴቶችም ወንዶችም በእኩልነት ከእናትና ከአባት የተወለዱ መሆናቸውን ነው። ይህም ከእናትና ከአባት ነፍስና ሥጋ ነስተው መወለዳቸው እኩልነታቸውን ያረጋግጣል።

አዳም ከሔዋን ቀድሞ መፈጠሩ ከሔዋን አያስበልጠውም!

ሔዋን ከአዳም ጎን መፈጠሯ የታወቀ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ነው። ይህን መነሻ በማድረግ ማኅበራዊ ብዥታ በፈጠረው አስተሳሰብ በመገፋት ያልተፃፈ እያነበቡ አዳም ከሔዋን ቀድሞ መፈጠሩ ከሔዋን እንደሚያስበልጠው የሚናገሩ አሉ። ይሁንና በአፈጣጠራቸው አዳምን ከመሬት፣ ሔዋንንም ከአዳም አጥንት የሠራቸው እግዚአብሔር ነው። በዚህም ሁለቱም የእጆቹ ሥራዎች ናቸው። አዳም ከሔዋን ቀድሞ መፈጠሩ መቀዳደምን እንጂ መበላለጥን አያመለክትም። “አዳም ቀድሞ ስለተፈጠረ ከሔዋን ይበልጣል” የምንል ከሆነ እንስሳት ከሰው ቀድመው ተፈጥረዋልና “ይበልጣሉ” ወደሚል ስህተት ይመራናል። የሔዋን ከአዳም አጥንት መሠራትም እንዲሁ መገኛዋን ያመለክታል እንጂ ማነስዋን አያሳይም። ይልቁንስ የቤተክርስቲያናችን ሊቃውንት እንዳስተማሩን ከፍ ብሎ ከራሱ ወይም ዝቅ ብሎ ከባቱ ሳይሆን ከመካከል ጎኑ መገኘቷ ከእርሱ የማታንስ ወይም የማትበልጥ መሆኗን ያመለክታል። ለዚህም ነው እግዚአብሔር “እንደ እርሱ ያለ ረዳት እንፍጠርለት” ያለው። “እንደ እርሱ ያለ” ሲል ከእርሱ እኩል የሆነ ነገር ግን የሚረዳው አጋር እንፍጠርለት ማለቱን ልብ ይሏል።

ሔዋን ቀድማ መሳሳቷ ከአዳም አያሳንሳትም!

“ሴቶች ከወንዶች ያንሳሉ” ብለው የሚያስቡ አንዳንድ ወገኖች ሌላ የሚያነሱት ምክንያት “ሔዋን ቀድማ ተሳስታለች፣ አዳምንም አሳስታለች፣ ስለዚህ ከአዳም ታንሳለች” የሚል ነው። ሔዋን በእባብ፣ አዳምም በሔዋን ምክንያት ሕግ ማፍረሳቸው መበላለጥን አያሳይም። ሁለቱም ተሳስተው ሕግን አፍርሰዋልና። ይልቁንም አባታችን አዳም ቀድማ የተሳሳተችውን ሔዋንን ከመርዳት ይልቅ ራሱም ተሳሳተ። የተሳሳተችውን ሔዋንን ወደ ንስሐ ከመምራት ይልቅ በነፃ ፈቃዱ እርስዋን ለመከተል ወሰነ። ስለዚህ ነው ለአዳም መሳሳት ሔዋን ምክንያት ናት እንጂ ተጠያቂ አይደለችም የምንለው። ይልቁንም ሁለቱም መሳሳታቸውና ሕግን ማፍረሳቸው፣ ሁሉቱም በሕግ መቀጣታቸው እኩልነታቸውን ያሳያል። ምክንያቱ ቢለያይም፣ በመሳሳት ቢቀዳደሙም፣ የቅጣታቸው ይዘት በጥቂቱ ቢለያይም በሰው ደረጃ ግን የሚያበላልጣቸው አልነበረም። የመጀመሪያዋ ሴት (ሔዋን) ቀድማ ተሳስታለችና ሁሉም ሴቶች እንደ እርስዋ ናቸው ብሎ ማጠቃለልም አይቻልም።

ይልቁንም የዓለማትን ፈጣሪ በመውለዷ ለሰው ልጆች ሁሉ የድኅነት ምክንያት የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ከፍጡራን ሁሉ የሚበልጥ ክብር አላት። በዚህም “ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ የሆነች” ትባላለች። ክብሯም በቃላት የማይገለፅና ዕፁብ ድንቅ ተብሎ የሚታለፍ ነው። ስለዚህም ቅድስት ድንግል ማርያም አይደለም የአዳም ልጆች ከሆኑት ከወንዶች ይቅርና ከሱራፌልና ከኪሩቤልም ትበልጣላች። ይህ ማለት ግን ሴቶች ከወንዶች ይበልጣሉ ማለት አይደለም። በተመሳሳይ ሔዋን ቀድማ ስለተሳሳተች ሴቶች ከወንዶች ያንሳሉ አይባልም።

“ባልሽ ገዥሽ ይሆናል” የሚለው እኩልነትን ይፃረራልን?

ታዲያ “ፈቃድሽ ወደ ባልሽ ይሆናል፣ እርሱም ገዥሽ ይሆናል (ዘፍ 3:16)” ለምን ተባለ? እንል ይሆናል። ይህም ቢሆን ሕግን ከመተላለፋቸው አንጻር የተነገረ ነው እንጂ እግዚአብሔር እኩል ሰው አድርጎ የፈጠራቸውን አዳምን እና ሔዋንን ለማበላለጥ የተናገረው አይደለም። ሔዋንን “ፈቃድሽ ወደ ባልሽ ይሆናል” ያላት አንዳንዶች እንደሚሉት ጾታዊ ፍላጎትን (ፈቃድን) የሚያመለክትም አይደለም። ይልቁንም የእባብን ምክር ሰምታ በራስዋ ፈቃድ ብቻ ሕግን አፍርሳ ነበርና ከዚህ በኋላ ከባልዋ ጋር በትዳር ስትኖር በአንድነት መወሰን እንደሚገባት የሚገልፅ ነው። ለአዳምም “እርሱም ገዥሽ ይሆናል” የተባለው የአንቺን ምክር ብቻ ሰምቶ አትብላ የተባለውን እንደበላው ሳይሆን ከዚህ በኋላ ሀሳብሽን ምክርሽን የሚሞግትና ያለ እርሱ ተሳትፎ በትዳር ውስጥ ብቻሽን አትወስኝም ሲል ነው። “ይገዛሻል” የተባለውም በፍቅር በትዳር አንዱ ለአንዱ እንደሚገዛው ‘በፍቅሩ ይገዛሻል’ የሚል እንጂ እንደ ምድር ነገሥታት ምርኮ በባርነት መግዛትን አያመለክትም።

እግዚአብሔር ፍትሐዊ አምላክ ስለሆነ ሁሉቱም እኩል ሕግን አፍርሰው የበደሉትን አንዱን ገዥ ሌላውን ተገዥ (አንዱን የበላይ ሌላውን የበታች) አያደርግምና። እዚህ ላይ ማስተዋል የሚሻው ሌላው ነገር ለይቶ “ባልሽ” አለ እንጂ “ወንድ” አላለም። እንዲህም ማለቱ በትዳር ውስጥ ያለውን ለይቶ ለማሳየት ነው። አንድም “ፈቃድሽ” የተባለው ሔዋን አምላክ ለመሆን የፈለገችውና ሕግን ለመተላለፍ ያበቃት መሻት/ፍላጎት ነው። ይህም ፈቃድ ዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ በመሆኑ ተፈጽሟል። ይህም እግዚአብሔር “እነሆ አዳም መልካሙንና ክፉውን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” በማለቱ ይታወቃል (ዘፍ 3:21)። ያ አምላክ የመሆን ፈቃድ በእርሱ ተፈጸመ። “እርሱም ገዥሽ ይሆናል” የተባለውም በመስቀል ተሰቅሎ በፍቅሩና በደሙ የገዛን መሆኑን የሚያመለክት ነው። ስለዚህ ይህ ቃል ለጊዜው ለአዳምና ለሔዋን ይነገር እንጂ ፍጻሜው በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን፣ ሞትን ድል አድርጎ በመነሳቱ በደሙ የተገዛን መሆናችንን የሚያሳይ ነው።

“የሴት ራስ ወንድ ነው” የሚለውስ እንዴት ይገለጻል?

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴት ራስም ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደሆነ ልታውቁ እወዳለሁ።” (1ኛ ቆሮ 11:3) ያለውም ቢሆን መበላለጥን አያሳይም። ይልቁንም አዳም መገኛው ከእግዚአብሔር፣ የሔዋን መገኛዋ ከአዳም፣ የወልድም መገኛው (የተወለደው) ከአብ መሆኑን ያረጋግጣል እንጂ። “የሴት ራስ ወንድ ነው” የሚለውን ይዘን ‘ወንድ ከሴት ይበልጣል’ የምንል ከሆነ “የክርስቶስ ራስ እግዚአብሔር ነው” የሚለውንም ወስደን ‘አብ ከወልድ ይበልጣል’ ልንል ነው? ይህ ደግሞ ወደ አርዮስ ክህደት ያስገባናል። ስለዚህ የሴት ራስ ወንድ ነው የሚለው ሔዋን ከአዳም አጥንት መገኘቷን የሚያሳይ ነው እንጂ ወንድ የሴት የበላይ (አለቃ) ነው ማለት አይደለም። በሌላም ትርጓሜ የሴት ራስ ወንድ ነው የሚለው የቤተሰቡ ተጠሪ እርሱ ነው ለማለት ነው። እግዚአብሔር አዳም ወይም አብርሃም ወይም ይስሐቅ ወይም ያዕቆብ ብሎ ሲጠራ መላውን ቤተሰብ መጥራቱ እንጂ አንድን ወንድ ብቻ መጥራቱ አይደለም። ይህም ድርሻን እንጂ የበላይነትን የሚያሳይ አይደለም።

“ሚስቶች ሆይ ለባሎቻችሁ ተገዙ” የሚለውስ?

ይህን ቃል በመያዝ “የወንዶች የበላይነት በመጽሐፍ ቅዱስ ተነግሯል” የሚሉ ወገኖች አሉ። ቃሉን ላስተዋለው ግን ይህ ስለትዳር ጉዳይ እንጂ ስለፆታዊ መበላለጥ የተነገረ አይደለም። ሐዋርያው ያለው “ሴቶች ሆይ ለወንዶች ተገዙ” ሳይሆን ለይቶ “ሚስቶች ሆይ ለባሎቻችሁ ተገዙ” ነው (ኤፌ 5:22-24)። ይህም እንደቀደመው “ገዥሽ ይሆናል” ብሎ እንደተነገረው ነው። በትዳር ያሉ ጥንዶች አንድ እንጂ ሁለት ስላልሆኑ አንዳቸው ለሌላው በፍቅር ሕግ መገዛት እንደሚገባቸውና ትዳራቸውን በግል ፈቃድ ሳይሆን በጋራ እየተመካከሩ መምራት እንደሚገባቸው ለማስረዳት የተነገረ ነው። ለዚህም ነው በዚሁ ክፍል “ባሎች ሆይ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን እንደወደዳት ስለእርሷም ራሱንም አሳልፎ እንደሰጠ ሚስቶቻችሁን ውደዱ” የተባለው። በዚህ መልእክት ሐዋርያው በትዳር ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው ፍቅር፣ መተሳሰብና አንድነት አስተማረ እንጂ የወንድ የበላይነትን አላስተማረም።

ወንዶችና ሴቶች መለየታቸው

በቤተክርስቲያን ወንዶች በግራ ሴቶች በቀኝ በኩል ሆነው ያስቀድሳሉ። በሌሎች መርኅግብሮችም እንዲሁ ተለይተው ይቀመጣሉ። ቅዱስ ቁርባንንም ሲቀበሉ እንዲሁ በቅደም ተከተል ነው። ይህ ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ የነበረ ሥርዓት ነው። ሥርዓቱም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ነው። ኖኅና ቤተሰቡ በመርከብ ሲገቡ ወንዶችና ሴቶች ለየብቻ ነበሩ። ይህንንም መነሻ በማድረግ ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም ወንዶች ከወንዶች ጋር ሴቶችም ከሴቶች ጋር እንዲቆሙ፣ በቅዳሴም ጊዜ ሰላምታ እንዲሰጣጡ በማዘዝ ይህም በቤተክርስቲያን በተመስጦ ለመጸለይ እንደሚረዳ አስተምሯል። ይህም ለሁሉም ተገቢውን ቦታ የመስጠት እንጂ የሚያበላልጥ ሥርዓት አይደለም። የቅዱስ ቁርባን ሥርዓትም እንዲሁ ምስጢራትን በተገቢው መንገድ ያላንዳች ልዩነት ለመፈጸም የተሠራ ነው። መቀዳደሙም መበላለጥን አያሳይም። እንደዚያ ቢሆን የሚበላውን እና የሚጠጣውን ያስገኘችልን ድንግል ማርያም ስለሆነች ከምስጢረ ቁርባን አንጻር ሴቶች ይበልጣሉ በተባለ ነበር።

የሴቶችና የወንዶች ተፈጥሮአዊ ልዩነት

ወንዶችና ሴቶች ተፈጥሮአዊ ልዪነት (biological difference) እንዳላቸው ሁሉም የሚገነዘበው እውነታ ነው። ይህም በዋናነት ትውልድን ከማስቀጠል አንጻር ዘርን ለመተካት ካላቸው ድርሻ ጋር የተያያዘ ነው። ነገር ግን በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ወንዶችና ሴቶች ነገሮችን የሚመለከቱበት መንገድ፣ የሚረዱበት ሁኔታ፣ ምላሽ የሚሰጡበት መንገድ፣ ለችግሮች መፍትሔ የሚሰጡበት አካሄድ ይለያያል። ይህም ጠንካራ ጎኖቻቸውን እንዲያስተባብሩ፣ በደካማ ጎኖቻቸው ደግሞ እንዲረዳዱ ያግዛል። ከፆታ ጋር የተያያዘ ተፈጥሮአዊ ልዩነት የመከባበር እንጂ የመበላለጥ ምንጭ ሊሆን አይችልም። ከአባታችን ከአዳም በቀር ሁሉም ሰው በእኩልነት ከሴት (ከእናት) የተወለደ ነው። የሰው ዘርም የሚቀጥለው በዚሁ መልክ ነው። በተፈጥሮ ልዩነት ቢሆንማ ይልቁንም ዘጠኝ ወር በማህፀን የሚንከባከቡት፣ ቀጥሎም ጡት እያጠቡ የሚያሳድጉት፣ በእያንዳንዱ ሰው ሕይወትም ጉልህ ድርሻ ያላቸው እናቶች በበለጡ ነበር።

መደምደሚያ

በአጠቃላይ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚመሰክሩት እውነትና የቀደሙት ቅዱሳን ያስተማሩት በሴቶችና ወንዶች መካከል መበላለጥን ሳይሆን አንድነትንና ፍቅርን ነው። ሴቶችና ወንዶች የተለያየ ድርሻ (different roles) ቢኖራቸውም እኩል መብት (equal rights) አላቸው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ለገላቲያ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ “ሴት የለም፣ ወንድ የለም፣ ሁሉም በክርስቶስ አንድ ነው” በማለት እኩልነትን አስተምሯል (ገላ 3:28)። የክርስትናችን መርህም ይህ ነው። ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ የተወለደ ሁሉ በክርስቶስ አንድ ነው። የተሰጠው ጸጋ ሊለያይ ይችላል። ጽድቅም በእምነት፣ በምግባርና በእግዚአብሔር ቸርነት እንጂ በፆታ ወይም በሥጋዊ ክህሎት የሚገኝ አይደለም። በመንፈሳዊ ሕይወትም ሰው ሁሉ በአንድ መንፈስ ሆኖ የሚያገለግለው አንድ እግዚአብሔርን ነው። በሥጋዊ ተፈጥሮ ወንድና ሴት የሚለያዩባቸው ነገሮች እንዳሉ ግልፅ ነው። ይህ የሆነው ዘርን በመተካት ሂደት የየራሳቸው ተመጋጋቢ ድርሻ ያላቸው ስለሆነ ነው። የግል ክህሎት ግን ሁሉም ሰው ያሉትን ዕድሎች ተጠቅሞ የሚያዳብረው እንጂ በተፈጥሮ ለወንድና ለሴት ተብሎ የተከፈለ አይደለም።

በመጽሐፍ ያሉትን ጥቅሶች ባልተገባ መንገድ በመተርጎም ሴቶችን የበታች አድርጎ መመልከትም ሆነ እንደዚህ ማስተማር ሁለት መሠረታዊ ስህተቶችን መፈጸም ነው። የመጀመሪያው የመጽሐፍን ቃል ባልተገባ መንገድ መተርጎም፣ ሁለተኛው ደግሞ በተሳሳተ ትርጉም በደልን ለማድበስበስ መሞከር። ይህ በተለይም “ወንዶች ብቻ በሚያዙበት” ነገር ግን ሴቶች በብዛት በየጉባዔው በሚሳተፉበት በእኛው ቤተክርስቲያን ሲሆን ችግሩን ውስብስብ ያደርገዋል። ከዚህ አንጻር ቤተክርስቲያን በፆታ እኩልነት ዙሪያ የሚታዩ ሥር የሰደዱ ስሁት አመለካከቶችን በማፅዳትና ሴቶችን ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ባከበረ መልኩ ቁልፍ በሆኑ የቤተክርስቲያን አገልግሎቶችና ውሳኔዎች በበቂ ሁኔታ ከማሳተፍ አንጻር ብዙ ይጠበቅባታል። እኩልነትንም ለማረጋገጥ ከቃልና ከመመሪያ በተጨማሪ በተግባር ሊገለጥ ይገባዋል እንጂ ቁጭ ብሎ መማርም ታላቅ አገልግሎት ነው በሚል መሸንገያ ሊታለፍ አይገባውም። በባህል ተፅእኖ ምክንያትም የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብና ትርጓሜ እያጣመሙ ሴቶችን አሳንሶ የማየትን ልማድ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ድጋፍ በመስጠት (ወይም በዝምታ በማለፍ) የቤተክርስቲያንን አገልግሎት የሚያዳክሙትን ሰዎችም በትምህርት፣ በምክርና በተግሳጽ ማስተካከል ይገባል እንላለን።

ሴቶች በቤተ ክርስቲያን (ክፍል ፩): የቅዱሳት አንስት (ሴቶች) አገልግሎት

women in church_2
መግቢያ

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ የክርስቲያኖችን አንድነት በሦስት “ፆታ ምዕመናን” ይከፍላቸዋል። እነርሱም ወንዶች፣ ሴቶችና ካህናት ናቸው። እግዚአብሔር በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተናገረን በመንፈሳዊ ህይወት የሁሉም ፆታ ምዕመናን ዓላማ መስዋዕትነትና ከራስ በላይ ለሌሎች መኖር ነው። ወንዶች የቤተሰብ ራስ (ተጠሪ) መባላቸው እንደ ክርስቶስ ራሳቸውን ስለቤተሰባቸው ቤዛ እስከማድረግ የሚገለጥ ነው። ሴቶች የሕይወት ምንጭ (እናት) በመሆናቸው በብዙ መከራ እየተፈተኑ የቤተክርስቲያንን ሕይወት ያስቀጥላሉ። ካህናትም ክህነታቸው “እናንተም እንዲሁ አድርጉ” ብሎ አብነት እንደሆናቸው ጌታ ዝቅ ብለው ምዕመናንን እንዲያገለግሉ ነው።

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎት ሁሉም ምዕመን እንደየድርሻው ይሳተፋል። ይሁንና በታሪክ ሂደት ከሦስቱ ፆታ ምዕመናን መካከል ሴቶች በልዩ ልዩ ምክንያቶች በተፈጠሩ መንፈሳዊ ሱታፌአቸውን በሚያቀጭጩ ችግሮች ተይዘዋል። ስለሆነም “ሴቶች በቤተክርስቲያን” በሚል መሪ ርዕስ ሥር በተከታታይ በምናወጣቸው የአስተምህሮ ጦማሮች በመንፈሳዊ ከቅዱሳት መጻሕፍት ሳይሆን ከሌሎች ልማዶች የፈለቁ ሴቶች በቤተክርስቲያን ያላቸውንና ሊኖራቸው የሚገባውን ሱታፌ የሚያደበዝዙ ልማዶችና ዘልማዳዊ ትንተናወችን በቅዱሳት መጻሕፍትና የቤተክርስቲያን ትውፊት ሚዛንነት እንዳስሳለን። ለዚህም እንዲረዳን በቅድሚያ የሴትቶች (የእናትነት) አገልግሎት በቅድስት ቤተክርስቲያን የሚሰጠውን ክብር በአጭሩ እናቀርባለን።

የሴትነት (የእናትነት) አገልግሎት ክብር

የሴቶች መንፈሳዊ አገልግሎት በቤተክርስቲያን አስተምህሮ ታላቅ ቦታ ይሰጠዋል። ይህም ከሚገለጥባቸው ነገሮች አንዱ የፈጠረንን አምላክ “ድስት ሥላሴ” ብለን በእናት አንቀፅ መጥራታችን ነው። ይህም ከእናት በሥጋ እንደተወለድን ከሥላሴም በጥምቀት መወለዳችንን ለማጠየቅና ሥላሴም እናትም አባትም እንደሆኑን ለመመስከር ነው። በተጨማሪም የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም “እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም” ብለን የምናከብራትና የምልጃዋን በረከት የምንማፀነው ለእናትነቷ ካለን ታላቅ አክብሮት የተነሳ ነው።  እርስዋ “ሰው ሁሉ እናታችን ጽዮን ይላል (መዝ 86:5)” ተብሎ በትንቢት የተነገረላት፣ “እነኋት እናትህ (ዮሐ 19:38)” ብሎ በአካል የሰጠን እናታችን ናት። የእርስዋን እናትነት መሠረት በማድረግ ቤተክርስቲያን የእናትነትን አገልግሎት አመስጥራ ታስተምርበታለች።

እንዲሁም ዕለት ዕለት ቅዱስ ቃሉን፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የምትመግበንን አማናዊት ቤተክርስቲያን “እናት ቤተክርስቲያን” እንላታለን። ሥጋዊት እናት ከምድራዊ አባት ዘርን ተቀብላ ልጆችን በምጥ፣ በህማም እንደምትወልድ ሁሉ መንፈሳዊት እናት ቅድስት ቤተክርስቲያንም መንፈሳዊ ዘርን (ቅዱስ ቃሉን፣ ምስጢራተ ቤተክርስቲያንን) ከሰማያዊ አባት ከእግዚአብሔር ዘንድ ተቀብላ ምዕመናንን በመከራ በሚገለጥ ሰማዕትነት አልፋ ምዕመናንን ወልዳ ታሳድጋለች። ይህም የቤተክርስቲያን አስተምህሮና ሥርዓት ለሴቶች የእናትነት ድርሻ ምን ያህል ታላቅ ቦታን እንደሚሰጥ ሌላው ማሳያ ነው። 

የሴቶች አገልግሎት በብሉይ ኪዳን

እናት ቤተክርስቲያን ጠብቃ ባቆየችልን የክርስትና ታሪክና አስተምህሮ ቅዱሳንን ከመውለድና በመንፈሳዊ ጥበብ ከማሳደግ ባሻገር ታላላቅና ድንቅ ተጋድሎን የፈጸሙ፣ በሕይወታቸው አርአያና ምሳሌ ሆነው ያስተማሩ ብዙ ቅዱሳት አንስት አሉ። የእናትነት አገልግሎት የጀመረው የሰው ሁሉ እናት በሆነችው በመጀመሪያዋ ሴት በሔዋን ነው (ዘፍ 3:20)። የአብርሃም ባለቤት የተቀደሰች እናታችን ሣራ ደግሞ የእስራኤል ዘሥጋ እናት ተብላ ትታወቃለች (ዘፍ 17:16)። ያዕቆብ በረከትን እንዲያገኝ ያደረገችው ርብቃና የዮሴፍ እናት ራሄል እንዲሁ እግዚአብሔር የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ ተብሎ ሲጠራ (ቤተሰቡን እንደሚጠራ ልብ ይሏል) አብረው የሚነሱ የመጀመሪያዎቹ ቅዱሳት አንስት ናቸው። ታላቁን የእስራኤል መሪ ሙሴን በፈርኦን ቤት በጥበብ ያሳደገችው የሙሴ እናት (ዮካቤድ) ሴቶች መሪዎችን ቀርፀው በማሳደግ ረገድ ያላቸውን እጅግ ታላቅ ሚና ያሳየች ታላቅ እናት ናት (ዘፀ 1:28)።

ሕዝበ እስራኤል ባህረ ኤርትራን ከተሻገሩ በኋላ ከበሮን ይዛ ምስጋናውን ስትመራ የነበረችው የሙሴ እህት ማርያምም ሴቶች በዝማሬ እና በምስጋና ዘርፍ ለሚያበረክቱት ድርሻ አብነት ሆናለች (ዘጸ 15:20)። የእስራኤልን ሰላዮች ተቀብላ ያተረፈቻቸው በኢያሪኮ ትኖር የነበረችውና በኋላም በዳዊትና በክርስቶስ የዘር ሀረግ ለመቆጠር የበቃችው ረዓብ ሌላዋ ታላቅ ሴት ነበረች። እግዚአብሔር በገለጠላት ጥበብ የጠላትን መሪ ድል ያደረገችው ዮዲት (መጽሐፈ ዮዲት 1)፣ በድንቅ እምነቷ እግዚአብሔር ከሐሰት ፍርድ ያዳናት ሶስና (መጽሐፈ ሶስና 1) ሴቶች በእምነትም ሆነ በጦርነት የመጣውን ፈተና ድል ማድረግ እንደሚችሉ ልዩ ማሳያዎቻችን ናቸው። 

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ስለ ተአምራት ሲያስተምር “ንግሥተ ዓዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፥ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ (ማቴ 12:42)” በማለት የተናገረላት ንግሥተ ዓዜብ በመንግሥት አመራርና በመንፈሳዊውም ጥበብ ምንኛ ታላቅ እንደነበረች ከታሪክ ድርሳናት መማር ይቻላል። አስቴር ለእስራኤል ድኅነት ምክንያት የሆነች ታላቅ ሴት እንደነበረች መጽሐፍ ይናገራል (አስቴር 4:14)። አቢጊያ ከባልዋ ከናባል ይልቅ ባለታላቅ አእምሮ ስለነበረች ከዳዊት ጦር የታዘዘውን የሞት ቅጣት በጥበብ መመለስ ችላለች (1ኛ ሳሙ 25:3)።

ጌታችንን በመቅደስ ያመሰገነችው (በሉቃ 2:36-38) ነቢይት ሐና ሴቶች ነቢያት ሆነው (በፆም በጸሎት ተወስነው መጻዕያትን እየተናገሩ፣ የእግዚአብሔርን ድንቅ ስራ እየመሰከሩ) ሲያገለግሉ እንደነበር ጥሩ ማሳያ ናት። በተጨማሪም ልዳ እና ኖአዲያ እንዲሁ ነቢያት ነበሩ (2ኛ ነገ 22:14 ነህምያ 6:14)። እንዲሁም በነቢዪ ኢሳይያስ የተነገረላቸው ሴት ነቢያት ነበሩ (ኢሳ 8:3)። በእስራኤል የፍርድ ወንበር ተቀምጣ ትፈርድ የነበረችው ዲቦራም (መሳፍ 4:4-5) ሴቶች በኃላፊነት ደረጃ ተቀምጠው ለሕዝብና ለቤተክርስቲያን የሚጠቅም ሥራን መሥራት እንደሚችሉ ጥሩ ምሳሌ ናት። የእምነቷ ጽናት በልዩ ሁኔታ የተመሰከረላትና ከክርስቶስ የትውልድ ሀረግ የተቆጠረችው ሞአባዊቷ ሩት እንዲሁ ልዩ ምሳሌያችን ሆና ትኖራለች። የታላቁ ነቢይ የሳሙኤል እናት ሐና እና የጠቢቡ ሰሎሞን እናት ቤርሳቤህ  በታላቅ የእናትነት ሥራቸው ሲታወሱ የሚኖሩ እናቶች ናቸው። እነዚህን እናቶች ለምሳሌ ያህል አነሳን እንጂ ሌሎችም ዘርዝረን የማንጨርሰውን ድንቅ የእናትነት አገልግሎትን ያስተማሩ ታላላቅ እናቶች በብሉይ ኪዳን ነበሩ።

የሴቶች አገልግሎት በዘመነ ሥጋዌ

ከሁሉም በላይ ወልደ እግዚአብሔርን ያስገኘችልን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሴቶች ሁሉ የተለየች ናት (ሉቃ 1:26-30)። በሔዋን አለመታዘዝ የተዋረደው ሴትነት በእመቤታችን ትህትና እና መታዘዝ ፍፁም ከብሯልና። ከመልአኩ ከቅዱስ ገብርኤል ቀጥላ ድንግል ማርያምን ያመሰገነችውና መጥምቁ ዮሐንስን በበረሀ ያሳደገችው ቅድስት ኤልሳቤጥም በሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ የነበረች ታላቅ ቅድስት እናት ነበረች (ሉቃ 1:39-44)። ከጌታችን እና ከእናቱ ጋር አብራ ግብፅ ድረስ የተሰደደችው ሰሎሜም የክርስትና ታሪክ ሲያስታውሳት ይኖራል። ለሰማርያ ሐዋርያ የሆነችው ሳምራዊቷ ሴትም (ቅድስት ፎቲና) ቀጥላ ተጠቃሽ ናት (ዮሐ 4:4-26)። ጌታችን በዚህ ምድር ላይ በሚያስተምርበት ጊዜም ከ12ቱ ደቀመዛሙርትና ከ72 አርድዕት ጋር 36 ቅዱሳት አንስትን ለአገልግሎት መምረጡ በክርስትና አገልግሎት ሴቶች ታላቅ ቦታ እንዳላቸው የሚያሳይ ነው።

ጌታችን በሚያስተምርበት ወቅትም ተቀምጣ ቃሉን ትማር የነበረችውና “ማርያምስ የማይቀሟትን መልካሙን መረጠች” ተብሎ የተነገረላት፣ በመስተንግዶ ትደክም የነበረችውና ኋላም ወንድሟ አልዓዛር እንደሚነሳ ታላቅ እምነቷን የገለጸችው እህቷ ማርታ የእህቶች እምነትና አገልግሎት ድንቅ ምሳሌዎች ናቸው (ዮሐ 10:38):። ያላትን አንዲት ዲናር ሰጥታ ጌታችን እምነቷን ያደነቀላት ሴት፣ የልብሱን ጫፍ ብነካ እድናላሁ ብላ በማመን ልብሱን ነክታ የዳነችው ደም ይፈሳት የነበረችው ሴት (ዮስቃና)፣ በብዙ ገንዘብ ሽቱን ገዝታ በራሱ ላይ ያፈሰሰችውና እግሩን በእንባዋ እያጠበች በፀጉሯ ያበሰችውና ያም ታሪኳ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚነገርላት ማርያም በእንተ ዕፍረት፣ ጌታችን መስቀል ተሸክሞ በጎልጎታ መከራን ሲቀበል አይሁድን ሳትፈራ ላቡን እንዲጠርግበት መጎናጸፊያዋን የሰጠችው ቅድስት ቬሮኒካ፣ የጌታችንን ትንሣኤ ከሁሉ በፈት አይታ ለደቀመዛሙርቱ ያበሰረችው ማርያም መግደላዊት (ማቴ 28:1) ሴቶች በመንፈሳዊ አገልግሎት እጅግ ታላቅ ድርሻ እንዳላቸው ድንቅ ማሳያዎቻችን ናቸው።

የሴቶች አገልግሎት በዘመነ ሐዋርያት

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ (ሮሜ 16:1-7) የጻፈላቸው ፌቤንና፣ ጵርስቅላና አቂላ ሌሎችም ቅዱሳት ሴቶች እንዲሁ የጎላ መንፈሳዊ አገልግሎትን ፈፅመዋል። ይህንንም ሲናገር “በክንክራኦስ ባለች ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የምትሆን እኅታችንን ፌቤንን አደራ ብያችኋለሁ፤ ለቅዱሳን እንደሚገባ በጌታ ተቀበሉአት፥ እርስዋ ለብዙዎች ለእኔም ለራሴ ደጋፊ ነበረችና፥ ከእናንተም በምትፈልገው በማናቸውም ነገር እርዱአት። በክርስቶስ ኢየሱስ አብረውኝ ለሚሠሩ ለጵርስቅላና ለአቂላ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ እነርሱም ስለ ነፍሴ ነፍሳቸውን ለሞት አቀረቡ፥ የአሕዛብም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የሚያመሰግኑአቸው ናቸው እንጂ እኔ ብቻ አይደለሁም፤ በቤታቸውም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከእስያ ለክርስቶስ በኵራት ለሆነው ለምወደው ለአጤኔጦን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ስለ እናንተ ብዙ ለደከመች ለማርያ ሰላምታ አቅርቡልኝ። በሐዋርያት መካከል ስመ ጥሩዎች ለሆኑ፥ ደግሞም ክርስቶስን በማመን ለቀደሙኝ፥ አብረውኝም ለታሰሩ ለዘመዶቼ ለአንዲራኒቆንና ለዩልያን ሰላምታ አቅርቡልኝ” በማለት ገልጿቸዋል።

ወንጌላዊው ዮሐንስም (2ኛ ዮሐ 1:1) “በእኛ ስለሚኖርና ከእኛ ጋር ለዘላለም ስለሚሆን እውነት፥ እኔ ሽማግሌው በእውነት ለምወዳቸውና እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን የሚያውቁ ሁሉ ደግሞ ለሚወዱአቸው ለተመረጠች እመቤትና ለልጆችዋ፤ ከእግዚአብሔር አብና ከአብ ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም በእውነትና በፍቅር ከእኛ ጋር ይሆናሉ።” በማለት ያገለግሉ ከነበሩ ቅዱሳት ሴቶች መካከል ለነበረችው ሮምናን “እመቤቴ” ይላት ነበር።

ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስተምር የነበረችውና (ሐዋ 16:13-15) “በሰንበት ቀንም ከከተማው በር ውጭ የጸሎት ስፍራ በዚያ መሆኑን ስላሰብን ወደ ወንዝ አጠገብ ወጣን፤ ተቀምጠንም ለተሰበሰቡት ሴቶች ተናገርን። ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት። እርስዋም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ፥ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ ብላ ለመነችን፤ በግድም አለችን።” ተብሎ የተነገረላት ልዲያም ለቤተሰቦቿ ሐዋርያ ሆና አስተምራለች።

እንዲሁም በሐዲስ ኪዳን የፊሊጶስ አራቱ ደናግል ሴት ልጆቹ ነቢያት እንደነበሩ መገለጹ ሴቶች በሐዲስ ኪዳን የነበራቸውን እና ያላቸውን ድርሻ ያጠናክረዋል (ሐዋ 21:9)። በትንቢትም “እግዚአብሔር ይላል፡- በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ (ሐዋ 2:17)” ተብሎ የተነገረው ሴቶች ትንቢትን ከመናገር (ቃለ እግዚአብሔርን ከመመስከር) አንጻር ከወንዶች ተመሳሳይ ድርሻ እንዳላቸው ያሳያል። በዚህ ረገድ በሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያ ክርስቲያኖችም በጸሎት ሲተጉ ያለ ልዩነት እንደነበር ወንጌላዊው ሉቃስ ሲጽፍ “እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ከማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር (ሐዋ 1:14)” ብሏል። 

የሴቶች አገልግሎት በዘመነ ሰማዕታትና ሊቃውንት

በእምነት ጸንታ የሰማዕትነት አክሊልን የተቀበለችው በዚህም ስትዘከር የምትኖረው ቅድስት አርሴማ (ስንክሳር መስከረም 29)፣ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከ50 ቅዱሳት አንስት ጋር በንጉሥ ዑልያኖስ ሰማዕትነትን የተቀበለችው ቅድስት ሶፊያ፣ በንጉሥ ዴሲየስ ዘመን ሰማዕትነትን የተቀበለችው ቅድስት አንስጣስያ፣ ገድላቸው ሲዘከር የሚኖረው ቅድስት ባርባራ ቅድስት ዮልያና እና ቅድስት ዮስቲና፣ በጽኑ ተጋድሎ ክብርን ያገኘች ቅድስት ዕንባ መሪና (ስንክሳር ነሐሴ 25)፣ ገዳማዊ ሕይወትን ለእናቶች ያስተማረች ሰማዕቷ ዴምያና፣ ከልጇ ጋር ሰማዕትነትን የተቀበለችው ቅድስት እየሉጣና (ስንከሳር ሐምሌ 19) ሌሎችም ሰማዕታት ታሪካቸውን በደም የጻፉ ቅዱሳት አንስት ናቸው።

ለ25 ዓመታት በገዳም የተጋደለችው ቅድስት ማርታ ተሐራሚት (ስንክሳር ሰኔ 3)፣ በዘመነ ሰማዕታት ልጇን በደም ያጠመቀችው ቅድስት ሣራ፣ የጌታችን ቅዱስ መስቀል ከ300 ዓመታት በላይ ከተቀበረበት እንዲወጣ ያደረገችው ንግሥት ኢሌኒ የክርስትና ታሪክ ፈርጦች ናቸው። የቤተክርስቲያን ወርቃማ ዘመን በሚባለው በ4ኛው መቶ ከፍለ ዘመን የነበሩት የቅዱስ አውግስቲን እናት ቅድስት ሞኒካ፣ የቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ እህት ቅድስት ማክሪና እና የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ረዳት የነበረችው ቅድስት ኦሊምፒያ የቤተክርስቲያን ታሪክ ሲዘክራቸው ይኖራል፡፡ ከዚህም ባሻገር ታላላቅ ቅዱሳንን ያስገኙልን እንደ ቅድስት እግዚእ ኃረያና ቅድስት አቅሌስያ ያሉትም ቅዱሳት እናቶች ሲታሰቡ ይኖራሉ። እነዚህን ለምሳሌ ያህል አነሳን እንጂ ሌሎችም ስማቸውን ዘርዝረን የማንጨርሰው ቅዱሳት አንስት ያደራጉት ተጋድሎና ያገኙት ክብር በስንክሳርና በተለያዩ የቤተክርስቲያን መጻሕፍት ይገኛል።

የሴቶች አገልግሎት በቅርብ ዘመን

ዲያብሎስን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ ምህረትን የጠየቀችለት ጻድቋ ክርስቶስ ሠምራ (ስንክሳር ነሐሴ 24)፣ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት በመዐርግ የተስተካከለችውና ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አንዱን ያነፀችው ቅድስት መስቀል ክብራ (ስንክሳር ሐምሌ 28)፣በቅድስናና በንጽሕና ኖራ ሰማዕትነትን የተቀበለችው ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ (እመ ምዑዝ) (ስንክሳር የካቲት 29)፣  ካቶሊካውያን ቅኝ ገዥዎች በሀገራችን ኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያንን አስገድደው እምነት በማስለወጥ ላይ በነበሩበት  ዘመን በቅድስናና በጥብዓት ሰማዕትነትን የተቀበለችው ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ (ስንክሳር ህዳር 17) በሀገራችን ኢትዮጵያ የክርስትና ታሪክ ልዩ ሥፍራ ያላቸው ቅዱሳት አንስት ናቸው። በአንድነት ቆመው የህንድን ቤተክርስቲያን ከተሃድሶ ጥፋት የታደጓት የህንድ እናቶች ተጋድሎም የቅርብ ትዝታችን ነው።

በቅርብ ዘመን በቅኔው ዘርፍም ድንቅ ታሪክን ያስመዘገበችው እሙሐይ ሐይመትእሙሐይ ገላነሽ፣ ቀጥሎም የመጡት ሴት የቅኔ መምህራን እሙሐይ ኅርይትና እሙሐይ ወለተ ሕይወት ያሳዩት አርአያነት ሴቶች ከባድ በሚባለው የቅኔ ዘርፍ ሳይቀር በማስተማር ጉልህ ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚችል ማረጋገጫዎቻችን ናቸው። ብዙ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለቤተክርስቲያን ያበረከቱት እቴጌ ኢሌኒም እንዲሁ የቤተክርስቲያን ባለውለታ ናቸው።  በዘመናችንም ያሉት መምህርት ጥዕምተ ዜማመምህርት ሶስና በላይመምህርት ሕይወት ፀሐይ ሴቶች በመንፈሳዊው ዕውቀትና በማስተማሩም ሥራ ታላቅ ድርሻ ማበርከት እንደሚችሉ አርአያዎች ናቸው።

መልእክተ አስተምህሮ

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሴቶች ገዳማት ለሴቶች ገዳማዊ ሕይወትና የመንፈሳዊ ትምህርት የልህቀት ማዕከል ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወቃል። እነዚህ ገዳማት ለሴት ሊቃውንትና ቅዱሳት ሴቶች መፍለቂያ ናቸው። በዘመናችንም ይህንን አገልግሎት የሚሰጡና በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚገኙ የሴቶች ገዳማት ልዩ እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል። በአንጻሩም ሴቶች በዘመናዊው የቤተክርስቲያን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ገብተው ተምረው ለቤተክርስቲያን አገልግሎት በተለያዩ ዘርፎች የራሳቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ሊበረታቱ ይገባል።

በተጨማሪም ሴቶች ከእልልታ ባለፈ በመዝሙርና እና በዜማ መሣሪያዎች (ለምሳሌ በገና በመደርደር) ዘርፍ የሚያበረክቱት አገልግሎት በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እየታገዘ ሊጎለብት ይገባዋል። የቤተክርስቲያን አልባሳትንና የተለያዩ ንዋየ ቅድሳትን በእጃቸው ሠርተው በማዘጋጀት፣ ቅፅረ ቤተክርስቲያንን በማፅዳት፣ መገበሪያውን መርጠው በማዘጋጀት፣ የአብነት ተማሪዎችን እና ካህናቱን በመመገብ፣ በእንግዶች መስተንግዶ፣ በአስተዳደር ሥራዎችና በመሳሰሉት ዘርፎችም ሴቶች የሚያበረክቷቸው አገልግሎቶች ታላቅ ዋጋ እንዳላቸውና ሰማያዊ ክብርን እንደሚያሰጧቸውም ማስተዋል ያስፈልጋል። በበጎ አድራጎት ዘርፍም ገዳማትን፣ የገጠር አብያተ ክርስቲያናትን፣ የአብነት ትምህርት ቤቶችን በመርዳት ሴቶች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ታላቅ ነው። ይህም ሊበረታታ ይገባዋል።

ሴቶች (እናቶች) የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ጀምሮ እስካላንበት ዘመን ድረስ ተነግሮ የማያልቅ ድንቅና ታላላቅ መንፈሳዊ አገልግሎትን ሲፈጽሙ ኖረዋል። በዚህም ለራሳቸው የጽድቅ አክሊልን አግኝተዋል፣ ለትውልድም አርአያ የሚሆን የተጋድሎ ታሪክን አቆይተዋል። በዚህ ዘመንም በዓለምና በገዳም ሃይማኖትን በመጠበቅና ለቀጣዩ ትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ወሳኝ የሆነ የመንፈሳዊ አገልግሎት ድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። ስለዚህም ቅዱሳት መጻሕፍትና የቤተክርስቲያን የታሪክ መዛግብት ያሰፈሩትን የእናትነት አገልግሎት በዘመናችን ላለው ትውልድ በበቂ ሁኔታ ማስተማርና ጽፎም ማሰራጨት ያስፈልጋል። በዘመናችን ላሉት ሴቶች እህቶቻችን አብነት ይሆን ዘንድ የቤተክርስቲያን አውደምሕረትም አሁን ከሚደረገው በበለጠ የእነዚህ ቅዱሳት አንስት ተጋድሎ የሚሰበክበት፣ ስለእነርሱም የሚዘመርበት፣ ገድላቸው የሚነበበት ሊሆን ይገባል እንላለን። የእነዚህ ደጋግ ቅዱሳን እናቶች በረከታቸው ይደርብን። አሜን!