መዳንም በሌላ በማንም የለም: ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ

ምክንያተ ጽሕፈት

በመጽሐፍ ቅዱስ የተመዘገበው የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት በቅዱሳን ሰዎች የተጻፈ ነው፡፡ የሚተረጎመውም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ጥበብ መንፈሳዊን ከእውነተኛ ምንጭ በተማሩ ሰዎች ነው፡፡ ይሁንና የበጎ ነገር ጠላት ዲያብሎስ በሀሰተኛ መምህራን እያደረ የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብ ይቆነጻጽላል፣ ትርጓሜአቸውንም ያጣምማል፡፡ ሐዋርያዊ ውርስ የሌላቸው፣ ቅዱሳት መጻሕፍትንም እንደግለሰብ ድርሰት በልብ ወደድ የሚተረጉሙ ሰዎች ትርጓሜአቸውን አጣመው ያለአውዳቸው እየጠቀሱ ራሳቸው ግራ ተጋብተው ምዕመናንን ግራ ከሚያጋቡባቸው የተወደዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት አንዱ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ የጻፈልንና በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 4፡12 የተጻፈው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ያስተማረው ትምህርት “መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰው የተሰጠ ሌላ ስም ከቶ የለምና” በማለት ፣ የተናገረው ምስክርነት ነው፡፡

ይህ የቅዱስ ጴጥሮስ ምስክርነት ጥልቅ የክርስትና ሃይማኖት መሠረተ እምነትን የሚያስረዳ ቃል ነው፡፡ ይሁንና “እምነታቸውን” ቤተክርስቲያንን በመቃወም ላይ ብቻ የመሠረቱ ሰዎች ልዩ ልዩ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮዎችን ለመቃወም ያለ አውዱ ይጠቀሙታል፡፡ ስለ በሽተኞች ፈውስና ሌሎች ተዓምራት፣ ስለ ቅዱሳን ሰዎች አማላጅነት፣ ስለ ቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ሲነገር እንዲሁም ስለሌሎች ማንኛውም ዓይነት መንፈሳዊ ውይይት ሲነሳ ሁሉንም በራሳቸው አላዋቂነት ልክ እያሰቡ ሌሎች መንፈሳዊ ሀሳቦችን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ጋር ያለአግባብ እየቀላቀሉ “መዳንም በሌላ በማንም የለም” የሚለውን አምላካዊ ቃል መልዕክት ሰው እንዳይረዳው ያደርጋሉ፡፡ የዛሬ አስተምህሮ ጦማር ዓላማ የዚህን አምላካዊ ቃል ትርጉም ማብራራትና በግምት የሚደረጉ የአጽራረ ቤተክርስቲያንን ማሳሳቻዎች ለይቶ ማሳየት ነው፡፡

የሐዋርያት ሥራ (ገድለ ሐዋርያት)

“መዳንም በሌላ በማንም የለም” የሚለውን የቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት ለመረዳት የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን ዓላማ መረዳት እንዲሁም ለቅዱስ ጴጥሮስ ንግግር መነሻ የሆነውን ታሪክ ማንበብ ይጠቅማል፡፡ የሐዋርያት ሥራ በዋናነት ቅዱሳን ሐዋርያት ከጌታ ትንሣኤ በኋላ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዓመታት ያደረጉትን መንፈሳዊ ተጋድሎ፣ ያስተማሩትን ሐዋርያዊ ትምህርት እና የተቀበሉትን ልዩ ልዩ ሰማዕትነት የሚያትት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው፡፡ የባህርይ አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ ሊቃናት ክፋት ለመስቀል ሞት ተላልፎ ቢሰጥም እርሱ ግን የመጣበት ዓላማ ነበርና በሞቱ ሞትን አጥፍቶ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን አውጇል፡፡ በልዩ ልዩ ተዓምራት የተገለጠው የክርስቶስ ትንሣኤ ግን ለአይሁድ ሊቃናት የሐሰተኝነታቸው ማረጋገጫ፣ የግፈኝነታቸው ማሳያ፣ ከቀናች የአባቶቻቸው ሃይማኖትና ተስፋ ተለይተው ራሳቸው በፈጠሩት ሃይማኖታዊ ካባ ባለው ምድራዊ ክብርና ዝናን ብቻ በሚፈልግ አሳፋሪ ማንነት መተብተባቸውን የገለጠ ነበር፡፡ ስለሆነም በማናቸውም መንገድ የክርስቶስን ትንሣኤ ማስተሀቀር (ማስተባበል) የተንኮላቸው ሁሉ ማዕከል ነበር፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመስቀል አይሁድ ከጠቀሱት የማስመሰል ክስ አንዱ የእግዚአብሔር ልጅ፣ እግዚአብሔር መሆኑን በመጽሐፋቸው የተጻፈውን እንኳ እንዳያምኑ ልባቸውን አክብደው ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይገባው “ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር በሀሰት ያስተካክላል” በማለት የፈጠሩት የክህደት ንግግራቸው ነው፡፡ የሰይጣንን ተንኮል በደቀመዛሙርቱ ትምህርትና የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የሆኑ ልዩ ልዩ ተዓምራት ማፍረስ ልማዱ የሆነ እግዚአብሔር ደግሞ አላዋቂና ፈሪ የነበሩ ሐዋርያቱን ሳይቀር አዋቂና ደፋሮች አደረጋቸው፤ በእነርሱም እያደረ እንድንበት ዘንድ የተሰጠንን የክርስቶስን ሥም (ማንነት) በይፋ በመግለጥ ሊቃናተ አይሁድን አሳፈራቸው፣ ቤተክርስቲያንንም አጸናት፡፡

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከተጻፈባቸው ዓላማዎች ዋናው አይሁድ ጌታችን በሰው ባህርይ መገለጡን አይተው አምላክነቱን ይክዱ ያስክዱ ነበርና ስለእኛ በፈቃዱ ሰው መሆኑ፣ በመካከላችን መመላለሱ፣ መከራ መቀበሉ ከአብ ከመንፈስቅዱስ በክብር እንደማያሳንሰው ማስረዳት ነው፡፡ ለዚህም ነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በተዓምራትና በትምህርት ነገረ ክርስቶስን በማጉላት የትንሣኤውን ኃይል የሚመሰክረው፡፡ የጌታችን የትንሣኤው ኃይል ከተገለጠባቸው ሐዋርያዊ አስተምህሮዎችና ተዓምራትና መካከል በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ሦስት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ያደረጉት ተዓምርና በተዓምሩ ምክንያት ቅዱስ ጴጥሮስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ አራት ያስተማረው የጌታችንን ትንሣኤ የሚያስረግጥ አስተምህሮ ይጠቀሳሉ፡፡

የቤተክርስቲያን የጸሎት ሰዓት

ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና ፍቁረ እግዚእ (የጌታ ወዳጅ) ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ “በጸሎት ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት ወደ መቅደስ ይወጡ ነበር፡፡” (ሐዋ. 3፡1) ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ስለ እውነት ፍርድህ ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ” (መዝ. 118፡ 164) እንዳለ በነቢያትና በሐዋርያት መሰረትነት በጸናች (ኤፌ. 2፡20) ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ከሚታወቁት ሰባቱ የጸሎት ጊዜያት አንዱ የተሰዓት (የቀኑ ዘጠኝ ሰዓት) ጸሎት ነው፡፡ ዘጠኝ ሰዓት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ተፈጸመ” ብሎ ቅድስት ነፍሱን ከክቡር ሥጋው የለየባት ሰዓት ስለሆነች ቅድስት ቤተክርስቲያን በተለየ ሁኔታ በጸሎት የምታስባት ሰዓት ነች፡፡ በአጽዋማት ጊዜ ቅዳሴ ተቀድሶ ሥጋውና ደሙ ለምዕመናን የሚሰጥባት የከበረች የጸሎት ሰዓት ነች፡፡ በሐዋርያት ሥራ 10፡3 እንደተመለከተው ቅዱሳን መላእክት የሰዉ ልጆችን ጸሎት ወደ መንበረ ጸባኦት የሚያሳርጉባት የከበረች የጸሎት ሰዓት ነች፡፡ የኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ትውፊት ምንጮች የሆኑ ቅዱሳን ሐዋርያትም በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ ይወጡ ነበር፡፡

በመቅደስ ደጅ ምጽዋት የሚለምን በሽተኛ

ቅዱሳን ሐዋርያት ወደ ቤተመቅደስ ሲሄዱ “ከእናቱ ማኅፀንም ጀምሮ እግሩ ሽባ ሆኖ የተወለደ…ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ ሁልጊዜ እየተሸከሙ መልካም በሚልዋት በመቅደስ ደጃፍ [ያስቀምጡት የነበረ በሽተኛ] ጴጥሮስና ዮሐንስንም ምጽዋት ይሰጡት ዘንድ ለመናቸው፡፡” (ሐዋ. 3፡2-3) የድኅነትን ነገር መቀለጃ የሚያደርጉ ሰዎች ድኅነት “በእምነት ብቻ” እንደሆነ አስመስለው ቅዱሳት መጻሕፍትን በማጣመም ፆም፣ ጸሎት፣ ምጽዋት፣ ስግደትና ሌሎችም በጎ ምግባራት ከድኅነት ጋር የማይገናኙ እንደሆኑ አስመስለው ምዕመናንን ከጽድቅ መንገድ ለመለየት ይደክማሉ፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ግን እምነት ያለምግባር ከነፍስ እንደተለየ ሥጋ የሞተ መሆኑን (ያዕ. 2፡14-26) በማስተማር ምዕመናን እንደ አቅማቸው ምጽዋትን ለተቸገሩት እንዲሰጡ፣ የተቸገሩትን የማይረዳ ምዕመንም በዕለተ ምጽአት እንደሚፈረድበት በአጽንኦት ታስተምራለች፡፡ (ማቴ. 25፡31-46) ከዚህም የተነሳ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ዘመን ምጽዋትን የሚፈልጉ ችግረኞች መጠለያ መሆኗ የታወቀ ነው፡፡ ከሐዋርያት የተማረችው ነውና፡፡

የቅዱሳን ሐዋርያት ተዓምር

ከእናቱ ማኅጸን ጀምሮ ሽባ ሆኖ የተወለደው ሰው ቅዱሳን ሐዋርያት ወደ ቤተ “መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ይሰጡት ዘንድ ለመናቸው፡፡” እነርሱ ግን እርሱ ከጠበቀው የገንዘብ ምጽዋት የበለጠውን የፈውስ ምጽዋት ሰጡት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ወርቅና ብር የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ ሂድ” አለው፡፡ (ሐዋ. 3፡3-6) አይሁድ ናዝሬትንና ከናዝሬት የሚወጡ ሰዎችን ይንቋቸው ነበር፣ ናዝሬት የወንበዴዎች ከተማ ነበረችና፡፡ ለዚያ ነው ምሁረ ኦሪት የነበረው ናትናኤል ቅዱስ ፊልጶስ ሙሴና ነቢያት የተናገሩለትን “የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው” ባለው ጊዜ “በውኑ ከናዝሬት ደግ ሰው ሊወጣ ይቻላልን?” ያለው፡፡ (ዮሐ. 1፡46-47) ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” ሽባውን ማዳኑ ለአይሁድ ልዩ መልእክት ነበረው፡፡ “እናንተ ከናዝሬት በመገኘቱ (ናዝሬት በማደጉ) የናቃችሁት፣ በሀሰት ፍርድ ለመስቀል ሞት አሳልፋችሁ የሰጣችሁት፣ ትንሣኤውን ለመደበቅ የሀሰት ምስክር ገዝታችሁ ከወቀሳ ለመዳን የምትደክሙበት ኢየሱስ ክርስቶስ የክብር ትንሣኤው ማሳያ የሆነ ይህን ተዓምር በእኛ እጅ አደረገ” ማለቱ ነው፡፡

የትንሣኤው ኃይልና የኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት

ቅዱሳን ሐዋርያት ተዓምራቱን የማድረጋቸው ዓላማ የክርስቶስን የትንሣኤ ኃይል መግለጥ ነበር፡፡ የእስራኤል ሰዎች ከእናቱ ማኅጸን ጀምሮ ሽባ ሆኖ የተወለደውን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ሥም፣ በደቀመዛሙርቱ አማካኝነት መፈወስ ባዩ ጊዜ ተደነቁ፡፡ ቅዱሳን ተዓምራትን የሚያደርጉት እንደዘመናችን ጋጠወጥ መናፍቃን፣ ጠንቋዮች፣ መተተኞችና ከንቱ ውዳሴ ፈላጊዎች ለራሳቸው አንዳች ክብር ወይም ጥቅም ፈልገው አይደለም፡፡ ስለሆነም ሰዎች ሁሉ በተደነቁ ጊዜ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “እናንት የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ ይህን ለምን ታደንቃላችሁ? እኛንስ በኀይላችንና በጽድቃችን ይህን ሰው በእግሩ እንዲሄድ እንዳደረግነው አስመስላችሁ ለምን ታዩናላችሁ?…የሕይወትን ባለቤት ግን ገደላችሁት፤ እግዚአብሔርም ከሙታን ለይቶ አስነሣው፤ ለዚህም እኛ ምስክሮቹ ነን፡፡ ስሙን በማመን ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን እርሱ ስም አጸናው፤ እርሱንም በማመን በፊታችሁ ይህን ሕይወት ሰጠው፡፡” (ሐዋ. 3፡12-16) በማለት መሰከረ፡፡

ይህ ምስክርነት የክርስቶስን እውነተኛ አምላክነት (ሞትን በስልጣኑ ድል ማድረጉን) እንደገለጠው ሁሉ የአይሁድ ሊቃናት (አለቆችን) ሀሰተኛነት የገለጠ ነበርና የአይሁድ የቤተመቅደስ አለቆች፣ በተለይም “ትንሣኤ ሙታን የለም” ብለው የሚያስተምሩትን የምንፍቅና አስተምህሮ ያፈረሰባቸው ሰዱቃውያን መከራ ሊያጸኑባቸው ተሰበሰቡ፤ ቅዱሳን ሐዋርያትንም በማን ስምና በማን ኀይል ተዓምራቱን እንዳደረጉ ጠየቋቸው፡፡(ሐዋ. 4፡1-7) በአይሁድ ሀሳብ ሐዋርያት ማስፈራራታቸውን አይተው የተዓምራቱን ባለቤት፣ የትንሣኤያችን በኩር የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ከመስበክ (አምላክነቱን፣ አዳኝነቱን፣ ቤዛነቱን ከመመስከር) የሚቆጠቡ መስሏቸው ነበር፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ግን አይሁድን በኃጢአታቸው ወቅሶ፣ የክርስቶስን ትንሣኤ መስክሮ፣ በሽተኛውም የተፈወሰው በክርስቶስ ሥም በማመን መሆኑን ነገራቸው፡፡

ይልቁንም “መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰው የተሰጠ ሌላ ስም ከቶ የለምና” (ሐዋ. 4፡12) በማለት ሰቃልያነ እግዚእ አይሁድን አሳፈራቸው፡፡ አይሁድ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥም (የክርስቶስን አምላክነት፣ ትንሣኤውን ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱን) እንዳያስተምሩ በከለከሏቸው ጊዜም ቅዱሳን ሐዋርያት “እግዚአብሔርን ያይደለ እናንተን ልንሰማ በእግዚአብሔር ፊት ይገባልን? እስኪ እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ፡፡ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም እንል ዘንድ አንችልም፡፡” (ሐዋ. 4፡19-20) በማለት በጽናት ቆመዋል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ሳያምኑ፣ ይልቁንም ትንሣኤውን እየካዱ መዳን በሌላ በማንም የለምና፡፡

መዳን ማለት ምን ማለት ነው?

በቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ መዳን ማለት በዋናነት የዘላለምን ሕይወት ማግኘት ማለት ነው፡፡ ከዚያም ባሻገር ግን መዳን ማለት እንደ አገባቡ ከስጋ ደዌ፣ ከአጋንንት እስራት መፈወስንም ያሳያል፡፡ ጌታ በወንጌል “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ትሻለች” (ማቴ. 16፡4) እንዳለ በእምነት የደከሙ ሰዎች ተዓምር ናፋቂ ስለሆኑ መዳን ሲባል የሚታያቸው ሥጋዊ ድህነት ብቻ ነው፡፡ ከበሽታ መዳን፣ ሀብትና ንብረት ማግኘት፣ በምድር በሰዎች ዘንድ ከፍ ብሎ መታየት መዳን ይመስላቸዋል፡፡ ለዚያ ነው በዘመናችን ያሉ መናፍቃንና መሰሎቻቸው የትምህርታቸው ሁሉ መሰረት የሀሰት ተዓምራት የሆነው፡፡ እነዚህ ደካሞች “መዳንም በሌላ በማንም የለም” የሚለውን ቅዱስ ቃል ከምድር ከፍ በማይል ሀሳባቸው ለልዩ ልዩ የሥጋ  ደዌ የተነገረ ይመስላቸዋል፡፡ ምዕመናንና ምዕመናት በቅዱሳን ቃልኪዳን፣ በቤተክርስቲያን ጸሎት ከደዌ ሥጋ ሲድኑም ብርቅ ይሆንባቸዋል፡፡ በውስጣቸው ያደረ የበጎ ነገር ጠላት ዲያብሎስም ከምድራዊ ሀሳባቸው ከፍ እንዳይሉ ስለሚፈልግ በደካማ አመክንዮ በቅዱሳን ቃል ኪዳን ሰዎች ከደዌ ሥጋ መዳናቸው “መዳንም በሌላ በማንም የለም” በማለት ቅዱስ ጴጥሮስ ከተናገረው ጋር የሚጋጭ አስመስለው ይከራከራሉ፡፡

እንግዲህ ምን እንላለን? ለእነዚህ ሰዎች የቅዱሳንን ቃል ኪዳን ከማስረዳት በዓይናቸው የሚያዩትን የዓለም ስርዓት ዓይናቸውን ገልጠው እንዲያዩ ማገዝ ይቀላል፡፡ ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁም? የእግዚአብሔር ሥጋዊ መግቦት በእምነት የማይገደብ እንደሆነ፣ ቸር የሆነ አምላክ ለክፉዎቹም ለደጎቹም የምህረት ዝናብን እንደሚያዘንብ፣ የቸርነት ፀሐይን እንደሚያወጣ መረዳት አትችሉም? እናንተ አላዋቂዎች አንድ እግዚአብሔርን የካደ ሰው እንኳ በክፉ ሥጋዊ ደዌ ቢታመም እግዚአብሔርን የማያውቁ ምድራውያን ጠበብት ሲያድኑት አላያችሁም? በስጋዊ ደዌ የታመመን ሰው ምድራውያን ጠበብት በህክምና ሲያድኑት የእግዚአብሔር የማዳን እጅ የሌለችበት ይመስላችኋል? ምንም እንኳ ምድራዊ ጥበብና በቅዱሳን የሚገለጥ ተዓምር የተለያዩ ቢሆኑም ምሳሌው በተዓምራት የሚፈጸም ስጋዊ ድህነትን ለመረዳት ይጠቅመናል፡፡ በዚህ ጊዜም ከምድር ከፍ ያላለ ቅዱሳት መጻሕፍትን በግምት የሚተረጉም፣ የሐዋርያትን የሕይወትና የትምህርት ውርስ የማይከተል የማያስተውል ልቦናችሁ “መዳንም በሌላ በማንም የለም” እያለ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጉም እንዳትረዱ ሲጋርድባችሁ ለምን መንቃት አትችሉም? እስኪ ከአይሁድ ተማሩ፡፡

ሊቃናተ አይሁድ ሽባውን ሰው ቅዱሳን ሐዋርያት ድኅነተ ሥጋ ስለሰጡት ተደንቀው “በማን ስምና በማን ኀይል” (ሐዋ. 4፡7) ተዓምራቱ እንደተደረገ ለማወቅ ጓጉተው ነበር ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ የመጡት፡፡ ሥጋዊ ሰው ምንጊዜም የሚታየው ሥጋዊ ክብር፣ ሥጋዊ ድህነት፣ ሥጋዊ ደስታ ብቻ ስለሆነ መንፈሳዊው ክብር፣ መንፈሳዊው ድህነት፣ መንፈሳዊው ደስታ አይታሰበውም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ሽባውን ከአካላዊ በሽታ ያዳኑት እርሱና ተዓምራቱን ያዩ ሁሉ ወደ እውነተኛው ድኅነት (ዘላለማዊ ሕይወት) እንዲመለሱ የዘላለም ሕይወት ምንጭ የሆነውን አይሁድ በናዝራዊነቱ ያቃለሉትን የመዳናችንን ራስ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያምኑበት ምልክት እንዲሆናቸው ነው፡፡ ስለሆነም አይሁድ ለሥጋዊ ተዓምር ሲሰበሰቡ ቅዱስ ጴጥሮስ ልባቸውን ከፍ አደረገው “መዳንም በሌላ በማንም የለም” በማለት መንፈሳዊውን ተዓምር የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው መሆን፣ በዚህም ሰውም አምላክም ሆኖ በሐዲስ ኪዳን መካከለኛነቱ የሰውን ባሕርይ ተዋህዶ በአምላካዊ ስልጣኑ ከኃጢአት ፍርድ የተቤዠን መሆኑን እንዲያምኑ አስተማራቸው፡፡

የተቀደሰ ሐዋርያ ጳውሎስ “አሁንም ወንድሞቼ ሆይ ዘወትር እንደምትሰሙኝ ሳለሁ ብቻ ሳይሆን ሳልኖርም በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ሆናችሁ ለድኅነታችሁ ሥሩ [መዳናችሁን ፈጽሙ]” (ፊልጵ. 2፡12) እንዳለ መዳን ማለት የዘላለምን ሕይወት መውረስ፣ ጌታችን በዳግም ምጽዓት በክበበ ትስብእት፣ በግርማ መለኮት በተገለጠ ጊዜ በቀኙ ከሚቆሙት፣ የሕይወትን ቃል ከሚሰሙት ቅዱሳን ወገን (ማቴ. 25፡31-46) ለመሆን መብቃት (መታደል) ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “መዳንም በሌላ በማንም የለም” ሲል በኢየሱስ ክርስቶስ ሳያምኑ የዘላለም ሕይወት አይገኝም ማለቱ ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዳያስተምሩ ይከለክሏቸው የነበሩ አይሁድ ራሳቸውን የነቢያት ወራሾች፣ እውነተኛ ሃይማኖተኞች አስመስለው ያቀርቡ ነበርና ቅዱስ ጴጥሮስ “በኢየሱስ ክርስቶስ ሳታምኑ ስመ እግዚአብሔርን ብትጠሩ፣ በነቢያት ብትመኩ መዳን አትችሉም” ሲላቸው ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ

በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን መሰረታዊ አስተምህሮ ለድኅነት መሠረት የሆኑ አምስት ዋና ዋና መሠረተ እምነቶች (ዶግማዎች) አሉ፤ እነርሱም አምስቱ አዕማደ ምስጢራት ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ እንኳ ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቆም አይችልም፡፡

  1. በምስጢረ ሥላሴ ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ህይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ባለው ፍጹም አንድነትና ልዩ ሦስትነት ያላመነ ሰው መዳን በሌላ በማንም አያገኝም፡፡
  2. በምስጢረ ሥጋዌ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ለማዳን ንጽሕት፣ ቅድስት ከሆነች፣ ከአዳም ተስፋ፣ ከዳግሚት ሄዋን፣ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ መወለዱን፣ በመወለዱም ከአምላካዊ ክብሩ እንዳልተለየ የማያምን ሰው መዳን በሌላ በማንም አያገኝም፡፡
  3. በምስጢረ ጥምቀት ጥምቀትን በባህረ ዮርዳኖስ ከመሠረተ፣ በመስቀል በተሰቀለ ጊዜ ሌንጊኖስ የተባለ ሮማዊ ወታደር ጎኑን በጦር ሲወጋው ለልጅነት ጥምቀት፣ ለድህነት ጥምቀት ንፁህ ውሃና ደም በፈሰሰው በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት አምኖ፣ መስክሮ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ያልተጠመቀ ሰው መዳን በሌላ በማንም አያገኝም፡፡
  4. በምስጢረ ቁርባን ሕብስቱን ለውጦ ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሀደው  ሥጋ፣ ወይኑን ለውጦ ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሀደው ደም ባደረገ (በሚያደርግ)፣ ለዘላለምም በቤተክርስቲያን አድሮ ይህን አምላካዊ ተዓምር በሚፈጽም በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ የጌታን ቅዱስ ሥጋውን፣ ክቡር ደሙን ለልጅነት፣ ለስርየተ ኀጢአት የማይቀበል (የማይበላ የማይጠጣ) ሰው መዳን በሌላ በማንም አያገኝም፡፡
  5. በምስጢረ ትንሣኤ ሙታን አስቀድሞ ለዓለም ቤዛነትና አርአያነት በትህትና ከመጣበት አመጣጥ በተለየ በክበበ ትስብእት (በሰው ሥጋና አካል)፣ በግርማ መለኮት (በደብረታቦር ተራራ እንደተገለጠው ያለ መለኮታዊ ግርማ) በሚገለጥ በቀናች ሃይማኖት፣ በደገኛ ምግባር ጸንተው የሚጠብቁትን ወደ ዘላለማዊ ሕይወት፣ በሰይጣን ማታለል በመናፍቃን ማጭበርበር ተታለው ከቀናች ሃይማኖት፣ ከደገኛ ምግባር የራቁትን ወደ ዘላለም ቅጣት የሚልክ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመጣ የማያምን፣ ለዚያች የፍርድ ቀንም በአካለ ሥጋ እያለ የማይዘጋጅ ሰው መዳን በሌላ በማንም አያገኝም፡፡

ስለሆነም “መዳንም በሌላ በማንም የለም” ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የቤተክርስቲያን ራስና መሰረት መሆኑን፣ እምነትም ምግባርም ያለእርሱ ዋጋ ቢስ መሆኑን ማመን፣ መቀበል፣ በሕይወትም መኖር ማለት ነው እንጂ በመዳን ጉዞ ከእያንዳንዱ ምዕመን እምነትና ምግባር፣ በአጸደ ስጋና በአጸደ ነፍስ ካሉ ቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ፣ እንዲሁም ከቅዱሳን መላእክት ረዳትነት ጋር የሚነጻጸር ወይም የሚምታታ አይደለም፡፡

ማነጻጸሪያ ምሳሌዎች

የመዳን እውነተኛ መንፈሳዊ ትርጉም ከላይ እንደተብራራው መሆኑን ካየን እያንዳንዱ ሰው ለድኅነት እንዲበቃ የተለያዩ አካላትን ተመጋጋቢ ድርሻ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ሀሰተኞች በሰው ልጅ መዳን የእግዚአብሔርን ድርሻና የቅዱሳን ሰዎችና መላእክትን ድርሻ ባለመረዳት ወይም ሆነ ብሎ በማምታታት ብዙ ምዕመናንን ግራ እንደሚያጋቡ ይታወቃል፡፡ የቤተክርስቲያን መሰረታዊ ትምህርት ግልጽ ነው፡፡ በአጸደ ሥጋ ያሉ ክርስቲያኖች ጸሎትና ትምህርት፣ በአጸደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን ምልጃ፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት በቅዱሳት መጻሕፍት በተገለጠችው የቀናች ሃይማኖትና ደገኛ ምግባር እንድንጸና የሚረዳን በቤተክርስቲያን በኩልም ወደ ሕይወት ባለቤት እግዚአብሔር የሚያቀርበን አጋዥ እንጅ መሠረተ እምነትን የሚተካ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት፣ ከእግዚአብሔር ቸርነት የተለየ ሌላ መንገድ አይደለም፡፡

ቤተክርስቲያን (እያንዳንዱ ምዕመን እንዲሁም ማኅበረ ምዕመናንን የሚወክሉ የቤተክርስቲያን አካላት) ያላስተማረችው፣ ወንጌልን ያላስረዳችው ሰው ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ሊያውቅ ይችላል? (ሮሜ 10፡14) ቅዱሳን ሰዎች በቃልኪዳናቸው ያልረዱት፣ ቅዱሳን መላእክት በጥበቃቸው ከሰይጣን ፈተና፣ ከኃጢአት  እስረኝነት ተላቆ መንፈሳዊ ፍሬን አፍርቶ በሕይወቱ ጌታን እንዲያስደስት ያላገዙት ሰው እንዴት ትምህርተ ወንጌልን ሊፈጽማት ይችላል? (መዝ. 105፡23፣ ሉቃ. 13፡6-9) የቤተክርስቲያን ጥረት፣ የቅዱሳን ጸሎት፣ የመላእክት ርዳታ ከእግዚአብሔር ቸርነት የተለየ የሚመስለው ሰውስ በእውነት መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ሊረዳ ይችላል? እነዚህን ጥያቄያዊ ማብራሪያዎች የበለጠ ለመረዳት ሁለት ማነጻጸሪያ ታሪኮችን በምሳሌነት እናንሳ፡፡

ምሳሌ 1: የእስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ ወደ ከነአን ጉዞ

በኦሪት ዘፀዓት እንደተመዘገበው እግዚአብሔር አምላካችን በስሙ ያመኑትን፣ በምግባራቸው ያስደሰቱትን ሰዎች ከእስራኤል ዘሥጋ መካከል ለይቶ ከግብጽ ወደ ከነአን አሻግሯቸዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ የእስራኤል ዘሥጋ ታሪክ የሚነግረን ምድራዊ የታሪክ ሽኩቻዎች ዋና ዓላማዎቹ ስለሆኑ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ (በ1ኛ ቆሮ 10፡1-13) መልእክቱ እንዳስተማረን እስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ ወደ ከነአን ያደረጉት ምድራዊ ጉዞ እኛ ከምድር ወደ መንግስተ እግዚአብሔር የምናደርገው መንፈሳዊ ጉዞ ምሳሌ ስለነበረ ነው፡፡ በእስራኤል ጉዞ ከተደረጉት ድንቅ ተዓምራት አንዱ ያስቸግራቸው የነበረ ፈርኦን ሰራዊትን በባህረ ኤርትራ አስጥሞ እነርሱን በደረቅ ያሻገራቸው የእግዚአብሔር የቸርነት ስራ ነው፡፡

ይህን ታሪክ “መዳንም በሌላ በማንም የለም” ከሚለው ንባብ ጋር በተነጻጻሪ መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ እግዚአብሔር ምንም ቸር ቢሆንም የነጻነት አምላክ ነውና ማንንም በማስገደድ ከነጻ ፈቃዱ ውጭ አያድነውም፡፡ በባህረ ኤርትራ በተደረገው ተዓምር እያንዳንዱ እስራኤላዊ፣ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴና ሌሎች እስራኤልን ይመሩ የነበሩ ሰዎች፣ በደመና ይመራቸው የነበረ የእግዚአብሔር መልአክ (ቅዱስ ሚካኤል)፣ የሙሴ በትር የየራሳቸው ድርሻ ነበራቸው፡፡ የማናቸውም ድርሻ ግን ከእግዚአብሔር ቸርነት ጋር የሚጋጭ ወይም የሚወዳደር አልነበረም፡፡ የእያንዳንዳቸው ጥረት ፈቃደ እግዚአብሔር እንዲፈጸም በማድረጉ ሁሉም በየድርሻቸው ይመሰገናሉ፡፡ የሙሴ በትር ከሌሎች በትሮች የተለየችው ለዚያ ነው፡፡ ባሕረ ኤርትራን ተሻግረው ምድረ ርስት የደረሱት እስራኤል በመንገድ ከተቀሰፉት የተለዩትና የተመሰገኑት ለዚያ ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ፣ ኢያሱና ካሌብ እስከ አሁን ድረስ ለቀናች አገልግሎታቸው የሚመሰገኑት ለዚህ ነው፡፡ በወቅቱ በአካለ ሥጋ ያልነበሩት፣ በጸሎታቸው በቃልኪዳናቸው እስራኤል እንዲሻገሩ የረዱ ቀደምት አበው (ለምሳሌ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ) በተለየ ሁኔታ የሚመሰገኑት ለዚህ ነው፡፡ እስራኤልን ቀን በደመና፣ ሌሊት በብርሃን እየመራ የድኅነት ምሳሌ ወደሆነች ከነአን ያደረሳቸው የእግዚአብሔር  መልአክ መጋቤ ብሉይ ቅዱስ ሚካኤልም በእስራኤል ረዳትነቱ በልዩ ሁኔታ የሚመሰገነው ለዚህ ነው፡፡ (ዘፀ. 23፡20-23)

እነዚህ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደየድርሻቸው ተለይተው ተወስተዋል፣ ተመስግነዋል፡፡ ነገር ግን የአንዳቸውም ድርሻ ከእግዚአብሔር ማዳን ጋር እንደማይጋጭ ይልቁንም የእግዚአብሔር የማዳን ስራ መገለጫዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት  “እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፣ ቤትን የሚሠሩ በከንቱ ይደክማሉ፤ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፣ የሚጠብቁ በከንቱ ይተጋሉ” (መዝ. 126፡1) እንዳለ የእግዚአብሔር ቸርነትና የሰው ልጆች ጥረት እርስ በርስ የሚፎካከሩ ሳይሆኑ የሚመጋገቡ፣ የተያያዙ መሆናቸውን መረዳት ይገባል፡፡ አንተ የዋህ ቤትን የሚሰራው፣ ከተማን የሚጠብቀው እግዚአብሔር እንደሆነ ታምናለህ? በዚህ እምነት የተነሳ ግን  ያለ እግዚአብሔር ቤትን መስራት፣ ከተማን መጠበቅ አይቻልም ብለህ እጅህን አጣጥፈህ ትቀመጣለህ? የሚሰሩትንስ “አትድከሙ ቤትን የሚሰራው፣ ከተማን የሚጠብቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው” ትላለህ? እርግጠኛ ነኝ ቢያንስ ለሆድህና ለኑሮህ ስትል እንደዚያ አትልም፡፡ ታዲያ በተመሳሳይ አመክንዮ ሰይጣን ከጽድቅ መንገድ ሊያወጣህ “መዳንም በሌላ በማንም የለም” የሚለውን ያለቦታው ያለትርጉሙ እየጠቀሰ ሲያታልልህ ለምን ትወናበዳለህ? የሰው ድርሻ ሌላ፣ የመላእክት ድርሻ ሌላ፣ የሌሎች ፍጥረታት ድርሻ ሌላ፣ እግዚአብሔር ድርሻ ሌላ መሆኑን እንዳትረዳ “ብቻ፣ ብቻ፣ ብቻ” በሚል ሰይጣናዊ ማዘናጊያ አዚም ያደረገብህ ማን ነው?

ምሳሌ 2: በወይኑ ቦታ የተተከለችው በለስ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በነገረ ድህነት የቅዱሳን መላእክትን ድርሻ በምሳሌ ካስረዳባቸው ትምህርቶች አንዱ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 13፡6-9 የተመዘገበው ምሳሌአዊ ታሪክ ነው፡፡ ከታሪኩ እንደምንረዳው አንድ ሰው በወይኑ ቦታ የተተከለች በለስ ነበረችው፡፡ ከበለሷም ፍሬ ፈልጎ በተደጋጋሚ (ሦስት ጊዜ) ቢመጣም ፍሬ ሊያገኝባት አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ የወይኑን ጠባቂ ጠርቶ ፍሬ ያላገኘባትን በለስ እንዲቆርጣት አዘዘው፡፡ የበለሷ ጠባቂ ግን “አቤቱ አፈር ቆፍሬ በሥሯ እስከ አስታቅፋት፣ ፍግም እስካፈስባት ድረስ የዘንድሮን እንኳ ተዋት፡፡ ምናልባትም ለከርሞ ታፈራ እንደ ሆነ፣ ያለዚያ ግን እንቆርጣታለን፡፡” በማለት ስለ በለሷ አዝኖ ተሟገተላት፡፡

የወይን ባለቤት የተባለ አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ወይን የተባልን በስሙ አምነን ፍሬ (በጎ ምግባር) ማፍራት እንዳለብን የታዘዝን ምዕመናን ነን፡፡ (ኢሳ. 5፡1፡19) የወይን ጠባቂ የተባለው እያንዳንዱን ምዕመን ከሚጠብቁ ቅዱሳን መላእክት አንዱ ነው፡፡ (ማቴ. 18፡10፣ ራዕይ. 4፡1-11) ቅዱሳን መላእክት በቀናች ሃይማኖት ጸንተን፣ በበጎ ምግባራት ፍሬ አፍርተን መዳን የሚገኝበትን ሕይወት እንድንይዝ ይረዱናልና፡፡ (ዕብ. 1፡14) በበለሷ ምሳሌ ለበለሷ መዳን የበለሷ ድርሻ እንክብካቤውን ተጠቅማ የሚጠበቅባትን ፍሬ ማፍራት ነው፡፡ የመልአኩ ድርሻ በለሷን በሚያስፈልጋት ሁሉ እየረዳ ፍሬ እንድታፈራ ማድረግ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ድርሻ በለሷ ፍሬ እንድታፈራ መልአኩን እየላከ፣ ተፈጥሮን እየገሰፀ ኃይል ብርታት መሆን ነው፡፡ የበለሷ ፍሬ ማፍራት የመዳን ምሳሌ ነው፡፡ አንተ የዋህ አንተ በለሷን ስትሆን  “መዳንም በሌላ በማንም የለም” የሚለውን ቅዱስ ቃል እንደሰይጣን ያለቦታው፣ ያለትርጉሙ እየጠቀስክ እግዚአብሔር የሾመልህን ቅዱሳን መላእክት የምታቃልል፣ ለመዳንህ ያላቸውን ድርሻ የምታጥላላ ከማን ተምረኸው ነው?

ማጠቃለያ

የጸጋ ሁሉ ምንጭ አምላካችን እግዚአብሔር የማዳን ስራውን በቅዱሳን ሰዎችና መላእክት አማካኝነት ይገልጣል፡፡ በስሙ አምነን ህይወትን የምናገኝበት አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማዳን የባህርይ ገንዘቡ እንጅ ከማንም የተቀበለው አይደለም፡፡ በአንጻሩ ቅዱሳን ሰዎችና መላእክት ከጌታ በተቀበሉት ጸጋ ሰዎችን ከደዌ ስጋ ያድናሉ ወደዘላለማዊ ሕይወት በሚደረገው የመዳን ጉዞም በትምህርታቸው፣ በተዓምራታቸው፣ በጥበቃቸው፣ በአማላጅነታቸው እያገዙ በክርስቶስ ቤዛነት ያመኑ ሰዎችን ይረዳሉ፡፡ ለምሳሌ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፣ ያድናቸውማል” (መዝ. 33፡7) ማለቱ ለቅዱሳን የተሰጠውን የማዳን ጸጋ ያስረዳናል፡፡ በአጸደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን ሰዎች፣ ሰዎችን ወደ ጽድቅ መንገድ የሚመሩ ቅዱሳን መላእክት እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው በመዳን ጉዞ ያላቸውን ሱታፌ ከማይነጻጸረው የእግዚአብሔር ማዳን ጋር ማምታታት አይገባም፡፡ “መዳንም በሌላ በማንም የለም” የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል ያለ አውዱ እየጠቀሱ ለዘላለም ሕይወት ለመብቃት በምናደርገው ጉዞ የእያንዳንዱን ምዕመን እምነትና ምግባር፣ በአጸደ ስጋም ሆነ በአጸደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳንን ጸሎትና አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክትን ረዳትነት ከኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ጋር ተነጻጻሪ ወይም ተፎካካሪ አስመስለው የሚያቀርቡ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ሳይረዱ አለማወቃቸውን በጩኸት ብዛት ለመሸፈን የሚሞክሩ ደካሞች ናቸው፡፡

እነዚህን ሰዎች ስናይ ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ጆርጅ ኦርዌል የተባለ ደራሲ “የእንስሳት እድር” (Animal Farm) በተባለ ድርሰቱ በሞኝነትና አላዋቂነት ገጸባሕርይ የጠቀሳቸው  በጎች ሊታወሱን ይችላሉ፡፡ በድርሰቱ የተጠቀሱት በጎች አንድ አስቂኝ ጠባይ ነበራቸው፡፡ በጎቹ ያሰባሰቧቸውን ሕግጋት በሙሉ የመረዳት አቅም የላቸውም፡፡ እነርሱ የሚያውቁት አለቆቻቸው የሆኑት አሳማዎች በተንኮል ቀባብተው የሚሰጧቸውን ነገር ሁሉ ያለመገምገም እየተቀበሉ ጉሮሮአቸው እስኪንቃቃ ድረስ “Four legs good; two legs bad” (አራት እግር ጥሩ ነው፤ ሁለት እግር መጥፎ ነው) እያሉ መጮህና ልሂቃኑ ከፍ ያለ መረዳት የሚጠይቀውን ትምህርት እንዳያስተምሩ፣ ሌሎችም እንዳይረዱ መረበሽ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን የምታስተምረውን የነገረ ድኅነት ምስጢር የማይረዱ ደካሞችም የማያውቁትን ይቃወማሉ፤ ደርዝ በሌለው የአላዋቂነት ድፍረታቸውም ራሳቸው ክደው ሌሎችን ያስክዳሉ፣ የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብና ትርጉም ያጣምማሉ፡፡ የቅዱሳን አምላክ፣ የሰራዊት (ቅዱሳን መላእክት) ጌታ አምላካችን እግዚአብሔር ከሰይጣን ማታለል፣ ከመናፍቃን ክህደት ተጠብቀን በቀናች ሃይማኖት በበጎ ምግባር ጸንተን እንድንኖር ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

“መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰው የተሰጠ ሌላ ስም ከቶ የለምና”

ስብሃት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር፡፡ አሜን፡፡

ደብረ ምሥጢራት ታቦር

Debretabor2.1

በዲያቆን ሙሉነህ ጌቴ

መግቢያ

በታቦርሂ አመ ቀነጸ መለኮትከ ፈረስ፤ ኢክህሉ ስሒቦቶ ሙሴ ወኤልያስ፡፡ የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ ቄሰ ገበዝ ሐዲስ ኪዳናት እና ልጃቸው የቅኔዋ ንግሥት እሙሐይ ገላነሽ ሐዲስ በደብረ ጽላሎ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ለደብረ ታቦር በዓል የተቀኙት የመወደስ ቅኔ ሲሆን “ለዓለም” በመባል ከሚጠራው የአንድ መወድስ ቅኔ ክፍል ውስጥ አንደኛውና ኹለተኛው ቤት ቅኔ ነው፡፡ ቄሰ ገበዝ ሐዲስ ኪዳናት በቅኔ ማኅሌት ሆነው “በታቦርሂ” ብለው ቤቱን ሲጨርሱ በምቅዋመ አንስት (በሴቶች መቆሚያ) ያለችው በቅኔ የሰከረችው ሕጻኒቱ ልጃቸው ገላነሽ “ኢክህሉ ስሒቦቶ ሙሴ ወኤልያስ” ብላ ቅኔውን ከአባቷ ነጥቃ (ዘርፋ) ተቀኘች፡፡ የቅኔው ትርጉምም በደብረ ታቦር ተራራ የመለኮትህ መገለጥ ፈረስ በዘለለ ጊዜ ሙሴና ኤልያስ ሊገቱት አልቻሉም ማለት ሲሆን ምሥጢሩም ሙሴና ኤልያስ ታቦር ተብሎ በሚጠራው ተራራ የተገለጠውን ግርማ መለኮትህን ማየት ተሳናቸው ማለት ነው፡፡ ይኸውም መለኮት ብርሃኑን ብልጭ ባደረገ ጊዜ ፍጡሩ ዐይን ግርማ መለኮትን የማየት አቅም ስለተሳነው ሙሴ “ይኄይሰኒ መቃብርየ/መቃብሬ ይሻለኛል/” ብሎ ወደ መቃብሩ ኤልያስም በሠረገላው ወደ መኖሪያው /ወደ ተሰወረበት ቦታ ማለትም ብሔረ ሕያዋን/ ተመልሰዋል፡፡

ታቦር የተራራ ስም ሲሆን ከገሊላ ባሕር በምዕራባዊ ደቡብ በኩል 10 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቆ በመገኘት 572 ሜትር ከባሕር ጠለል (ወለል) ከፍ ይላል፡፡ በዚህ ተራራም ባርቅ ሲሳራን አሸንፎበታል፤ ጌታችንና አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው በሚያስተምርበት ወቅት ምሥጢረ መንግሥቱን እና ብርሃነ መለኮቱን ለነቢያት እና ለሐዋርያት ገልጦበታል፡፡ በመሆኑም ይህ ተራራ የምሥጢራት ተራራ ተብሎ ይጠራል፡፡ ከባሕረ ዮርዳኖስ ቀጥሎ ምሥጢረ መለኮት የተገለጠበት ዐምደ ምሥጢራት የሆነ ተራራ ነው፡፡ ስለዚህ የምሥጢራት መገለጫ ኾኖ ያገለገለ ተራራም ነቢያት ትንቢት ተናግረዋል፡፡ ልበ አምላክ ዳዊት “ደብረ እግዚአብሔር ደብር ጥሉል፤ደብር ርጉዕ ወደብር ጥሉል/የእግዚአብሔር ተራራ (ታቦር) የለመለመ /በምሥጢር/ ነው፤የረጋና የለመለመ /በምሥጢራት መገለጫነት/ ነው”፡፡ በሌላም ቦታ “ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌስሑ፤ወይሴብሑ ለስምከ/ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል፤ስምህንም ያመሰግናሉ” ይላል፡፡ /መዝ 88፣12/

ከአራቱ ዐበይት ነቢያት አንዱ የኾነው ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም “ኑ ወደ እግዚአብሔር ተራራ/ታቦር/ ፣ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፤ በጎዳናውም እንሄዳለን፡፡” /ኢሳ 2፣3/ ከላይ የተጠቀሱት ነቢያት አበው የታቦርን ተራራ “የእግዚአብሔር ተራራ” /ምሥጢራተ እግዚአብሔር የተገለጠበት/ በማለት ሲጠሩት ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ “ቅዱሱ ተራራ” ሲል ይጠራዋል፡፡  2ጴጥ1÷18  ደብረ ታቦር የሚለው ቃል የተራራውም ኾነ የብርሃነ መለኮት መገለጥ በዓል መጠሪያ ኾኖ ያገለግላል፡፡ በተራራነቱ የታቦር ተራራ ወይም ታቦር የተባለ ተራራ ተብሎ ሲተረጎም በበዓልነቱ ሲጠራ ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮት የተገለጠበት ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ዐበይት/ታላላቅ/ በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡ በዚህች አጭር የአስተምህሮ ጦማር የደብረ ታቦርን በዓል የአከባበር ታሪካዊ አመጣጥና ባሕላዊ አከባበር ሳይኾን በቅዱሱ ተራራ የተገለጡትን ትምህርታተ እግዚአብሔር መጠነኛ ዳሰሳ እናደርጋለን፡፡

ትምህርተ እግዚአብሔር (Apophatic Theology)

ወተወለጠ ራእዩ በቅድሜሆሙ ወአብርሀ ገጹ ከመ ፀሐይ ወአልባሲሁኒ ኮነ ጸዐዳ ከመ ብርሃን /መልኩም በፊታቸው ተለወጠ ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ኾነ (ሜቴ 17÷2)፡፡” በደብረ ታቦር በጉልህ ከተቀመጡት ምሥጢራት አንዱ የእግዚአብሔር አይገለጤነት ትምህርተ መለኮት (Apophatic Theology) ነው፡፡ ቅዱሳን አበው በእግዚአብሔር የባሕርይ ግብራት ጋር በሚያደርጉት ተዋሕዶ እግዚአብሔርን በተምሳሌት ይገልጡታል፡፡ ምክንያቱም ፍጡሩ አንደበታችን እና ቋንቋችን የተገደበው በተፈጠሩ ነገሮች ላይ ብቻ ነው፡፡ ንግግራችን ከጊዜ እና ከቦታ ውጭ አልፎ መናገር እና መግለጽ ፈጽሞ አይችልም፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ከጊዜና ከቦታ ውጪ ነው፡፡ ዘላለማዊውንና መጠንና ወሰን የሌለውን እግዚአብሔርን በጊዜ የተፈጠረውና በተፈጠረው ዓለም የተወሰነው ሰውና ቋንቋው የነጥብና የፍንጭ ያክል ካልሆነ በስተቀር አከናውኖ ሊጠራውና ሊገልጸው ፈጽሞ አይቻለውም፡፡ እግዚአብሔር እኛ ስለ እሱ /እግዚአብሔር/ ከምንናገረውና ከምናስበው ማንኛውም ነገር በማይነጻጸር ሁኔታ ይበልጣል፡፡ ስለዚህ ስለ እግዚአብሔር የምንናገረው ትምህርተ መለኮታችን በአብዛኛው ስዕላዊ እና ተምሳሌታዊ ነው፡፡ ይህ ስዕላዊና ተምሳሌታዊ አገላለጽም ቢሆን እግዚአብሔርን የፍንጭ ወይም የነጥብ ካልኾነ በቀር ሊገልጸው አይችልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እና ቅዱሳን አበው እግዚአብሔርን  ከሚገልጡባቸው ስዕላዊና ተምሳሌታዊ መግለጫዎች መካከል ጨለማና ብርሃን ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ብርሃን ነው ወይም ጨለማ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ ኹለቱም እግዚአብሔርን እንደየአቅማቸው ለማስረዳት ይሞክራሉ እንጂ አንዳቸውም እግዚአብሔርን ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር ብርሃን ነው ሲባል ብርሃን መገለጫው ነው ማለት እንጂ ገልብጠን ብርሃን እግዚአብሔር ነው ብንል የሚያስኬድ አይደለም፡፡

ጨለማ፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ጨለማ የሚለውን ቃል የእግዚአብሔርን አይደረሴነት ለመግለጥ ተጠቅሞበታል፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በሲና በረሃ ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር በተዘጋጀ ጊዜ እግዚአብሔር ወዳለበት ጨለማ እንደገባ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ያስረዳናል ‹‹ሕዝቡም ርቀው ቆሙ፤ ሙሴም እግዚአብሔር ወዳለበት ጨለማው ቀረበ›› (ዘጸ 20÷21)፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊትም ‹‹ወረሰየ ጽልመተ ምስዋሮ /መሰወሪያውን  ጨለማ አደረገ›› (መዝ. 17፡11) በማለት የሊቀ ነቢያት ሙሴን ኀይለ ቃል ያጸናዋል፡፡ ኹለቱም በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው የተናገሩት አበው ነቢያት እግዚአብሔር ጨለማ ሳይሆን በጨለማ እንደሚያድር ያረጋግጡልናል፡፡ በጨለማ ያድራል መባሉም አእምሮዋት/ኅሊናት ተመራምረው ሊደርሱበት የማይችሉ ምጡቀ ልቡና፣ረቂቀ ኅሊና መሆኑን ያመለክታል፡፡ ጨለማነቱም ያለው በእግዚአብሔር ዘንድ ሳይሆን በእኛ አእምሮ ውስጥ ነው፡፡ ለምሳሌ የፀሐይን ብርሃን ማየት የተሳነው ዐይነ ስውር ሰው ጨለማው ያለው ከእሱ ነው እንጂ ከፀሐይ እንዳልሆነ ኹሉ ጨለማነቱ ያለው በእግዚአብሔር ዘንድ ሳይሆን በእኛ ውስጥ ነው፡፡ በነቢዩ ሙሴና በልበ አምላክ ክቡር ዳዊት ጎራ ሆነው እግዚአብሔርን በተምሳሌታዊ አገላለጥ ከሚገልጡት ቅዱሳን አበው መካከል ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ አንዱ ነው፡፡

ብርሃን፡ ይህን መንገድ ተከትለው ስለ እግዚአብሔር አይደረሴነት ከሚያስተምሩት ቅዱሳን አበው መካከል ቅ/ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት ይገኝበታል፡፡ እግዚአብሔርን ብርሃን በሚለው ቋንቋ ለመግለጥ መሠረቱ ነባቤ መለኮት ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ጨለማም በእርሱ ዘንድ ጥቂትስ እንኳን የለም›› (1ኛ ዮሐ 1÷5)፡፡ እግዚአብሔር ብርሃን እንደሆነ በይበልጥ የተገለጠው ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ባደረገው ብርሃናዊ አስተርእዮ ነው፡፡ ስለዚህ ብርሃናዊ አስተርእዮ ከጻፉት ሦስቱ ወንጌላውያን አንዱ የሆነው ቅዱስ ማቴዎስ “ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ ፤ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ” በማለት የእግዚአብሔርን ብርሃናዊነት ገልጧል (ማቴ 17÷2)፡፡ ይህ እግዚአብሔርን በብርሃን ወክሎ መግለጥ በብዙ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የሚዘወተር ሲሆን የሊቃውንት ቅዱሳን ፈጣሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነስቶ እስከሚያርግበት ጊዜ ባሉት አርባ ቀናት ውስጥ ካስተማረውና ኪዳን ተብሎ ከሚጠራው ትምህርት ውስጥ “እግዚአብሔር ዘብርሃናት” በሚባለው የጸሎት ክፍል ውስጥ ይህ አገላለጥ ጎልቶ ይታያል፡፡ “ዘመንጦላዕቱ ብርሃን ወቅድመ ገጹ እሳት ወመንበረ ስብሐቲሁ ዘኢይተረጐም ወምዕራፈ ተድላሁ ዘኢይትነገር ዘአስተዳለወ ለቅዱሳን ወበመልበስቱ መዛግብተ ብርሃን / መጋረጃው ብርሃን፣ በፊቱ እሳት የሚቦገቦግ፣ የጌትነቱ መንበር የማይተረጎም፣ ለቅዱሳን ያዘጋጀው የደስታ ማረፊያ የማይነገር፣ መጎናጸፊያው የብርሃን መጎናጸፊያ የሆነ እግዚአብሔር ….”፡፡

ኪዳን በተባለው መጽሐፍም “ፀሐይ ዘኢየዐርብ ወማኅቶት ዘኢይጠፍእ ፀሐይ ዘዘልፈ ያበርህ ዲበ ቅዱሳን/የማይጠልቅ ፀሐይ፣ የማይጠፋ ብርሃን፣ በቅዱሳን ላይ ዘወትር የሚያበራ ፀሐይ” ሲል እግዚአብሔርን ተምሳሌታዊ በሆነ አገላለፅ ይገልጠዋል፡፡ በደብረ ታቦር /በምሥጢሩ ተራራ/ የታየው ብርሃን ግን በዕለተ እሑድ የተፈጠረ ብርሃን አይደለም፡፡ ይህ ብርሃን መለኮታዊ ብርሃን፣ ያልተፈጠረና ለሌሎች ብርሃናት ምንጭ የሆነ ብርሃን ነው፡፡ ይህ ብርሃን ኖኅና ሙሴ ሲወለዱ እንደከበባቸው፣ ሙሴ ከ40 ቀን የደብረ ሲና ቆይታ በኋላ  ኹለቱን ጽላት ተቀብሎ ሲመጣ እስራኤላውያን በሙሴ ላይ ያለውን ብርሃን ማየት ተስኗቸው ‹‹ሙሴ ተገልበብ ለነ/ ሙሴ ሆይ የፊትህን ብርሃን ማየት ተስኖናልና ፊትህን ተሸፈንልን” (ዘፀ. 34፡29-30) እንዳሉት ቅዱሳን ሲበቁ እንደሚጎናጸፉት ያለ ብርሃን አይደለም:: ይህ ብርሃን መለኮታዊ በመሆኑና ሌላ መግለጫ ቃል በመጥፋቱ ብርሃን በሚለው ተምሳሌት ተጠራ እንጂ ከብርሃን በላይ የሆነ ነው፡፡ የሰው ዐይን ፍጡሩን ብርሃን እንጂ ያልተፈጠረውን ብርሃን መመልከት አይችልም፡፡ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የተሟሸ ዐይን መለኮታዊውን ብርሃን በመለኮትነቱ ልክ ማየት ፈጽሞ የማይቻል ቢሆንም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የተወሰነለትን ያህል መመልከት መቻሉን በደብረ ታቦር አየን፡፡

“ወእም ከመ ጥቀ ታሤንዩ ግብረ ወትኔጽርዎ ይከውን ለክሙ ከመ ማኅቶት እንተ ታበርህ ውስተ መካነ ጽልመት እስከ ታበርህ ለክሙ ዕለት ወይሠርቅ ለክሙ ቤዝ ውስተ ልብክሙ ዘያበርህ / በአንብቦ መጻሕፍት ጽሙዳን ብትሆኑ ፀሐይ እስኪያበራላችሁ ድረስ ያጥቢያ ኮከብ እስኪወጣላችሁ/ አእምሮ መንፈሳዊ በልቡናችሁ እስኪሳልባችሁ/ ድረስ በጨለማ ቦታ እንደሚያበራ ፋና ይሆንላችኋል” (2ጴጥ 1÷19) ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ አገላለጹ ከሰው የሚገኘውን ዕውቀት በፋና፣ ከእግዚአብሔር የሚገኘውን ዕውቀት ደግሞ በፀሐይ መስሎ ተናግሯል፡፡ ‹‹ሃይማኖት እንተ ትጠረይ እም ተምህሮ ኢታግዕዞ ለሰብእ እምኑፋቄ ወእምትሕዝብት / ከመማር የምትገኝ ሃይማኖት ሰውን ከጥርጣሬ ነጻ አታወጣውም›› እንዳለ መጸሐፍ በምርምርና በአስተውሎት /Knowledge of Empiricism and Reason/ ከሚገኝ የዕውቀት ብርሃን ይልቅ እግዚአብሔር በልባችን የሚያትምልን የዕውቀት ብርሃን /Knowledge of Revelation/  እንደ ፀሐይ ያበራል፡፡ (መዝ118÷105)፤2ቆሮ 4÷6)፡፡ ይህ እግዚአብሔር ጸጋውን አሳድሮ ዐይነ ሥጋችንንና ዐይነ ልቡናችንን የሚያበራው ብርሃን ያልተፈጠረውን መለኮታዊውን ብርሃን ለማየት ያስችላል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ኹለንተናቸው የበራላቸው ኹለቱ ነቢያት አበው /ሙሴና ኤልያስ/ እና ሦስቱ የምሥጢር ሐዋርያት /ቅ/ጴጥሮስ፣ቅ/ዮሐንስና ቅ/ያዕቆብ/ መለኮታዊውን ብርሃን እንደ ዐቅማቸው ለማየት ደረሱ፡፡

ወንጌላውያኑ መለኮታዊውን ብርሃን የሚገልጡበት ነገር ቢያጡ በተፈጠረው ብርሃን መስለው ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ ብለው ተናገሩ፡፡ ቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት የተገለጠውን መለኮታዊ ብርሃን አይቶ መቋቋም የሚችል ዐይን ስላልነበራቸው “ወወድቁ በገጾሙ ዲበ ምድር /በግንባራቸው ወደ ምድር ወደቁ፡፡” ይህን አይደረሴ መለኮታዊ ብርሃን የትምህርተ መለኮት ሊቃውንት ከጨለማ ጋር አብረው በማጣመር “Dazzling Darkness, Radiance of Divine Darkness, Blinding Light” ብለው ይጠሩታል፡፡ ከዚህ የማይገለጥ አንጸባራቂ መለኮታዊ ብርሃን የተነሳ ቅዱስ ጴጥሮስ የሚናገረው ነገር እንዳጣ፣ያየውንም ነገር መሰየሚያ ቃል እንዳጣ፡ “ወኢየአምር ዘይብል / የሚለውን /የሚናገረውን አያውቅም/” በማለት ኹለቱ ወንጌላውያን አስቀምጠውታል (ማር 9÷6 ፤ሉቃ 9÷33)፡፡ ለዚህ ብርሃነ መለኮት መገለጥና በተገለጠው ብርሃነ መለኮት ፊት ለመቆም አለመቻልን ነበር ባለ ቅኔው ሐዲስ ኪዳናትና ልጃቸው እሙሐይ ገላነሽ ሙሴና ኤልያስ መለኮት ፈረስን መግታት ተሳናቸው ያሉት፡፡

በደብረ ታቦር የተገለጠው ብርሃን ያልተፈጠረ መለኮታዊ ብርሃን ነው፡፡ ፍጡሩን ብርሃንና መለኮታዊውን ብርሃን ስም እንጅ ግብርና ባሕርይ ፈጽሞ አያገናኛቸውም፡፡ መለኮታዊው ብርሃን ዘላለማዊ ብርሃን ነው፡፡ “ብርሃን ዘእምቅድም / ቅድመ ዓለም የነበረ ብርሃን /ባሕርይ/” እንዲል  (መጽሐፈ ኪዳን)፡፡ ፍጡሩን፣ ለሰው ልጆች በሥጦታ /በጸጋ/ የሚታደለውን ብርሃን ደግሞ መጻሕፍት በተለያየ አገላለጽ ይገልጡታል፡፡ “አምላከ ብርሃን፣ ወሀቤ ብርሃን / ረቂቁን ብርሃን የሰጠ፣ ግዙፉን ብርሃን የፈጠረ” በማለት ግዙፋኑ ብርሃናት ፀሐይ፣ጨረቃ፣ከዋክብትና ከእነርሱ የሚመነጨው ረቂቁ ብርሃን ለሰው ልጆች በሥጦታ የተበረከተ እንደሆነ መጻሕፍት ይገልጣሉ (መጽሐፈ ኪዳን)፡፡ ከዚህ ግዙፍ ብርሃን ባሻገር ግን በተጋድሎ ብዛት ቅዱሳን የሚታደሉት ረቂቅ ብረሃን አለ፡፡ ይህን ብርሃን “ብርሃን ዘኢይትረከብ / ያለ በጎ ሥራ የማይገኝ ብርሃን” ሲል ይገልጠዋል (መጽ.ኪዳን)፡፡

የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ለማየት የሚያደርሰውን ብርሃን ለማግኘት ተስፋ አድርጎ ይኖራል፡፡ ይህን አስመልክቶ “ወብርሃነ ለነ ዘኢይጠፍእ አሰፎከነ / የማይጠፋ ብርሃንን ለእኛ ተስፋ አስደረግከን” (መጽሐፈ ኪዳን)፡፡ ይህ ብርሃን ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለመላእክትም ጭምር በጥንተ ተፈጥሮ ዕውቀት ሆኗቸው መለኮታዊውን ብርሃን እንዲረዱ አድርጓቸዋል፡፡ “ዝንቱ ብርሃን ኮኖሙ ጥበበ ወአእምሮ” እንዲል መጽሐፍ፡፡ ይህን ፍጡር ብርሃን ዕውቀት አድርገው መላእክት መለኮታዊውን ብርሃን እንደጎበኙት መጽሐፈ ኪዳን “ዘያፈትዎሙ ለመላእክት የሐውጽዎ ለዘእምቅድመ ዓለም ብርሃን / ዓለም ሳይፈጠር የነበረውን ብርሃን ያዩት ዘንድ መላእክትን ደስ የሚያሰኛቸው” በማለት ያስረዳል፡፡

ትምህርተ ሥላሴ /Doctrine of Holy Trinity/

በምሥጢራዊው ቅዱስ ተራራ በታቦር ከምናገኛቸው መሠረታዊ ትምህርቶች መካከል ትምህርተ ሥላሴ ዋነኛው ነው፡፡ የምሥጢሩ ተራራ ታቦር በእግዚአብሔር አይገለጤነት ትምህርተ እግዚአብሔር (Apophatic Theolgy) ጀምሮ የእግዚአብሔርን የባሕርይ አንድነትና የባሕርዩ ግርማ መገለጫ ከሆኑት መካከል ብርሃን አንዱ መሆኑን ካስረዳ በኋላ ይህ በባሕርይ አንድ የሆነ እግዚአብሔር አካል ስንት እንደሆነ ወደ ማመላከት ያመራል፡፡ ይህ ትምህርት ወደ ጥልቁና አይመረመሬው ትምህርተ ሥላሴ ይወስደናል፡፡ በደብረ ታቦር ጌታችንና አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮታዊ ግርማ የመገለጡ ዋነኛ ምክንያት በብሉይ ኪዳን ስለ እግዚአብሔር አንድ ገጽነት ይታመን የነበረውን የስህተት አስተምህሮ አርሞ እግዚአብሔር በአካል እና በገጽ ሦስት እንደሆነ ለምዕመናነ እግዚአብሔር በሰፊው ለማስረዳት ነው፡፡ ይህ የምሥጢረ ሥላሴ አስተምህሮ በብሉይ ኪዳን በስውር ሁኔታ በብዙ ስፍራዎች ላይ የተገለጠ ሲሆን በአዲስ ኪዳን ግን በአገላለጥ ብቻ ሳይሆን በእይታም በሚረዳ መልኩ ተገልጧል፡፡ ከእነዚህ አስተርእዮታት (መገለጦች) መካከል ከባሕረ ዮርዳኖስ ቀጥሎ ደብረ ታቦር አንዱ የምሥጢረ ሥላሴ የምሥጢር ቁልፍ ነው፡፡

በባሕረ ዮርዳኖስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲጠመቅ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት ባለመገለጥ ቁልፍ ተዘግቶ የኖረው ምሥጢረ ሥላሴ “ተርህወ ሰማይ/ ሰማይ ተከፈተ” በሚል አንቀጽ የመገለጡን ምስራች እንደ ሰማን ምሥጢረ ሥላሴ በአንድ መገለጥ የሚረዳ አይደለምና በታላቁ የምሥጢራት ተራራ  በደብረ ታቦር ይህ የሰማይ መከፈት ምሥጢር ተደገመ፡፡ በኹለቱ ታላላቅ የምሥጢር መካናት እግዚአብሔር አንድነት ሦስትነቱን በምንረዳው ልክና መጠን ገለጠልን፡፡ በታቦር ተራራ ብርሃነ መለኮቱ ለተገለጠ ለኢየሱስ ክርስቶስ “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ወሎቱ ስምዕዎ / የምወደው ልጄ ይህ ነው እሱንም ስሙት” የሚል መለኮታዊ ቃል ከባሕርይ አባቱ ከአብ ዘንድ ተሰማ፡፡ እጅግ በጣም ታላቅና ድንቅ ድምፅ ነው! ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔ እና አብ አንድ ነን፤ እኔን ያየ አብን አየ፤ እግዲህ ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ እያጠመቃችኋቸው አሕዛብን ኹሉ አስተምሩ” (ዮሐ 10፣30፣ ዮሐ 14፣9፣ ማቴ 28፣19) እያለ ስለ እግዚአብሔር የባሕርይ አንድነትና የአካል ሦስትነት የሚያስተምራችሁን ትምህርተ እግዚአብሔር ስሙት፣ተቀበሉት፣እመኑበት በማለት እግዚአብሔር አብ የግርማው መገለጫ በሆነው በደመናው ውስጥ ሆኖ አዘዘን፡፡ በመሆኑም የታቦር ተራራ የምጢራት ኹሉ መሠረት የሆነው ምሥጢረ ሥላሴ ለኹለተኛ ጊዜ በጉልህ የተገለጠበት የምሥጢራተ መለኮት ዐደባባይ ነው፡፡

ትምህርተ ተዋሕዶ/አንድ አካል አንድ ባሕርይ/

በአንድ ብርሃነ መለኮት መገለጥ የሥላሴን የባሕርይ አንድነት፣አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ብሎ በመግለጥ የሥላሴን የአካል ሦስትነት ከተረዳን በኋላ የወልድን በተዋሕዶ ሰው መሆን የምንረዳበት ትምህርት በምሥጢሩ ተራራ በታቦር የተገለጠው ትምህርተ እግዚአብሔር ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስቱ የምሥጢር ሐዋርያት ጋር ወደ ረጅም ተራራ ወጥቷል፡፡ ከሐዋርያቱ ጋርም ቃል በቃል በአካል ተነጋግሯል፡፡ በእነዚህ ድርጊቶች የኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም ሰውነት በፍጽምና እንረዳለን፡፡ ይህ ፍጹም ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን በመግለጥ ነቢያትንና ሐዋርያትን በግርማ መለኮቱ ፍጹም ማስፈራቱም፣ “ይህ የባሕርይ ልጄ ነው” የሚል መለኮታዊ ድምጽ ከአብ መሰማቱ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም አምላክነት በተገለጠ ሁኔታ ያስረዳል፡፡ አንዱ አካል በአንድ ጊዜ በተዋሕዶ ሰውም አምላክም መሆኑን በምሥጢሩ ተራራ በታቦር ተረድተናል፡፡ በአዳም ፍዳ መነሻነትና በግሉ በሚሰራው ኀጢአት ምክንያት የቀደመ የገዢነት፣ የተፈሪነት ክብርን አጥቶ በፍጥረታት ኹሉ ሲረገጥና ሲቀጠቀጥ  የኖረ ሥጋ /ባሕርየ ሰብእ/ በተዋሕዶ የመለኮት ገንዘብ ኹሉ ገንዘቡ ኾኖለት በመለኮታዊ ግርማው በቅዱሱ ተራራ የነበሩትን ቅዱሳን ፍጹም አስደነገጠ፤ በብርሃኑ ዓለምን አበራ፤ የአብ የባሕርይ ልጅ ለመባል በቃ፤ ሙታንን በሥልጣኑ ከያሉበት ማስነሳትና ከሕያዋን ጋር ማነጋገር ቻለ፤ጌታ፣ እግዚአብሔር፣አምላክ  ለመኾን በቃ፡፡ ረቂቁ መለኮትም ከሥጋ ጋር ባደረገው ፍጹም ተዋሕዶ የሥጋን ገንዘብ ኹሉ ገንዘቡ በማድረጉ ወደ ምሥጢሩ ተራራ ሲወጣ ታየ፤ ተዳሰሰ፤ ወጣ፤ ተለወጠ፤ ወዘተ የሚሉ ሰውኛ ግሶች ተነገሩለት፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት

ዓለም የተፈጠረው በእግዚአብሔር ቃል /ወልድ እንደሆነ የሚድነውና የሚጠፋው በእግዚአብሔር ቃል /ወልድ/ ነው፡፡ “ዘየአምን በወልድ ቦ ሕይወት ዘለዓለም / በወልድ ያመነ የዘላለም ሕይወት አለው” (1ኛ ዮሐ. 5፡12) እንዳለ ወንጌላዊው ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ነው ብለው ካላመኑ በስተቀር ድኅነት ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ አረጋዊው ስምዖን “እነሆ ይህ ሕጻን ከእስራኤል መካከል ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሳታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ይሆን ዘንድ የተሠየመ ነው” (ሉቃ 2÷34) እንዳለ ለዓለም ድኅነትም ሆነ ሞት ምክንያቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ዓለም ለምንፍቅናዋና ውድቀቷ መሠረት የምታደርገው የኢየሱስ ክርስቶስን እግዚአብሔርነት መካድ ነው፡፡ በምሥጢሩ ተራራ በታቦር ግን ለዓለም መውደቅና መነሳት ምልክት የኾነው የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትን ማመን ለዓለም በግልጥና በሚረዳ ቦታ፣በሚረዳ ቋንቋ ተገልጧል፡፡ “የምወደው ልጄ ይህ ነው” ከማለት በላይ ለኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት ሌላ ምስክርነት አያሻም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ አይደለም ብሎ መካድ እግዚአብሔር አብ የባሕርይ አምላክ አይደለም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ፍጡር ፍጡርን ፣ፈጣሪ ፈጣሪን በባሕርያቸው ይወልዳሉ እንጅ ፍጡር ከፈጣሪ በባሕርይ ሊወለድ አይቻለውም፡፡ ወይም ፈጣሪ ፍጡርን በባሕርይው ወለደ ማለት ለባሕርዩ አይስማማውም፡፡

በሌላ አገላለጽ የፍጡር የባሕርይ ልጅ ፍጡር፣ የፈጣሪ የባሕርይ ልጅ ፈጣሪ ነው፡፡ ታዲያ ራሱ አብ ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ ልጄ ነውና እሱ የሚላችሁን ኹሉ አምናችሁ ተቀበሉት ብሎ ካዘዘን፣ እንዲሁም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ “እምቅድመ ይትፈጠር አብርሃም ሀሎኩ አነ / አብርሃም ሳይፈጠር በቅድምና ነበርሁ” (ዮሐ. 8፡58) እያለ ዘላለማዊነቱን የሚነግረንን ኢየሱስ ክርስቶስን እግዚአብሔርነቱን አለመቀበልና በእግዚአብሔርነቱ አለማመን የአብን ቃል መካድና የአብንም እግዚአብሔርነት ፈጽሞ መካድ አይደለምን?! ሊቃውንት አባቶቻችን “ወልድ  ሲነካ አብ ይነካል” ብለው እንዳስቀመጡት በኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት አለማመንና አለመታመን በኢየሱስ ክርስቶስ ተጠግቶ የእግዚአብሔር አብንም እግዚአብሔርነት ፍጹም መካድ ነው፡፡ ይህ ድርጊት ደግሞ ወደ እግዚአብሔር የለሽነት ጥልቅ አዘቅት የሚከት ወደር የለሽ ክህደት ነው፡፡ በምሥጢሩ ተራራ ግን የኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት በግልጥ ቀርቧል፡፡ ብርሃነ መለኮቱ ስለታየበት፣ምሥጢረ ሥላሴ ስለተገለጠበት፣የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ስለተነገረበት ከዓለም ተራራዎች ኹሉ ለይቶ ቅዱስ /ልዩ/ በማለት በሚጠራው በቅዱሱ ተራራ በታቦር ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ  በዐይኑ የተመለከተውን፣በልቡናው ያስተዋለውን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር እንዳገኘው እንዲህ በማለት መስክሮልናል፡፡

“እስመ ኢኮነ መሐድምተ ጥበብ ዘተሎነ ወአመርናክሙ ቦቱ ኀይሎ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወምጽአቶ ወሀልዎቶ…. /ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ዓለም መኖሩን፣አምጻኤ አለማትነቱን፣ በሥጋ መምጣቱን ስናስተምራችሁ የተከተልነው የፍልስፍና ተረት አይደለምና፣ የእርሱን ገናናነት እኛ ራሳችን አይተን ነው እንጅ ከገናናው ክብር ‘በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው’ የሚል ያ ደምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ገንዘብ አድርጓልና፡፡ ይህንም ቃል እኛ በተቀደሰው ተራራ አብረነው ሳለን ከሰማይ እንደወረደለት ሰምተነዋል›› (2ጴጥ 1÷16-18)

ነገረ ቤተክርስቲያን

በምሥጢሩ ተራራ በታቦር ከተገለጡት ምሥጢራት ነገረ ቤተ ክርስቲያን ይገኝበታል፡፡ በደብረ ታቦር በሕይወተ ሥጋና በሕይወተ ነፍስ ያሉ ምእመናን በአንድ ላይ ተገኝተው ምሥጢረ መለኮትን ተመልክተዋል፡፡ አንዱ ለአንድ ሲጸልይ ተስተውለዋል፡፡ አንድነትን፣ አብሮ መኖርን ሲመኙ ታይተዋል፡፡ ይህ የቤተክርስቲያን ጠባይ ነው፡፡ በደብረ ታቦር የተገለጠው ምሥጢር ዛሬም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እየተገለጠ ይኖራል፡፡ ቤተክርስቲያን የኹለት ዓለማት ምእመናን አንድነት ናት፡፡ ምሥጢረ መለኮት የሚገለጥባት፣ አንዱ ለሌላው የሚኖርባት፣ አንዱ ለሌላው የሚጸልይባት፣ በዐፀደ ሥጋና በዐፀደ ነፍስ ያሉ ምእመናንና የመላእክት ተዋሕዶ /አንድነት/፣ የምሕረት ዐደባባይ ናት፡፡

ትምህርተ ትንሣኤ ምውታን

ነገረ ትንሣኤ ምውታን ከጥንት ጀምሮ ለብዙ ሰዎች የክህደታቸው መነሻ ሆኖ የቆየ ዐቢይ ምሥጢር ነው፡፡በክርስቶስ ዘመነ ሥጋዌ ወቅት ሰዱቃውያን የሚባሉ ቡድኖች ሰው ከሞተ በኋላ ነፍሱና ሥጋው ተዋሕደው ይነሳል የሚለውን የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስን አስተምህሮ አምርረው ይቃወሙ ነበር፡፡ኢየሱስ ክርስቶስም ሰው ዘላለማዊ ፍጡር እንደሆነና ከሞት በኋላ መልአካዊ ህላዌ እንደሚኖረው ገሥጾ አስተምሯቸዋል፡፡በዘመነ ሐዋርያት ጊዜም ብዙ ተረፈ ሰዱቃውያንና አሕዛባውያን ተነስተው ስለ ትንሣኤ ምውታን በጥልቀት ያስተምር የነበረውን ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስን ተቃውመውታል፡፡ቅዱስ ጳውሎስም “ሀሎኑ ዘይብል እፎኑ ይትነሥኡ ምውታን ወበአይ ነፍስቶሙ የሐይዉ ኦ አብድ አንተ ዘትዘርእ አኮኑ ዝንቱ ነፍስት ዘይትወለድ ዘትዘርእ ዳእሙ ሕጠተ እመኒ ዘሥርናይ ወእመኒ ዘባዕድ ወእግዚአብሔር ይሁቦ ነፍስተ ዘከመ ፈቀደ/ ሙታን እንዴት ይነሳሉ? በየትኛው ሰውነታቸውስ ይነሳሉ? የሚል አለን አንተ ሰነፍ አንተ የምትዘራው ቅንጣት የሥንዴም ቢሆን ሌላም ቢሆን እግዚአብሔር እንደወደደ አካልን ይሰጠዋል፡፡” (1ቆሮ15፡35-38)

ዛሬም በዘመናችን ለሚኖሩ ለብዙ ከሃድያን ፈላስፎችና ባለ ሳይንሶች/ሳይንቲስቶች የክህደታቸው ዋና መነሻ ትንሣኤ ምውታንን መካድ ነው፡፡ ከሞት በኋላ ስላለው ዘላለማዊ ሕይወት መስማት ፈጽመው አይፈልጉም፡፡ የምሥጢረ ትንሣኤ አስተምህሮ ሰነፎች የፈጠሩት ተረት ተረት እንደሆነ አድርገውም ይገምታሉ፡፡በቅዱሱ መጽሐፍ እንደተጻፈልን ግን በመዝገበ ምሥጢራቱ በታቦር ተራራ ትንሣኤ ምውታን በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባር ተገልጧል፡፡ ከሞተ አንድ ሽህ አምስት መቶ ዓመት ገደማ የሚሆነው ሊቀ ነቢያት ሙሴ በቅዱሱ ተራራ በታቦር በሕይወተ ሥጋ ተገልጦ ሕይወትን ከሰጠው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በግልጥ ተነጋግሯል፡፡ በዚህ የምሥጢራት ተራራ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ማዕከል የሆነው የምሥጢረ ምውታን አስተምህሮ በቃል ብቻ ሳይወሰን በተግባር ተገለጠ፡፡ ትምህርተ ትንሣኤ ምውታን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አምስቱ አእማደ ምሥጢራት ብላ ከምታስተምረው የሃይማኖቷ መሠረት ከቆመባቸው ምሰሶዎች አንዱ ሲሆን መነሻዋም መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ የነገረ ተዋሕዶው ሊቅ ቅዱስ ቄርሎስ የትስብእት ምሳሌ አድርጎ በተረጎመው ዕፀ ጳጦስ ላይ አድሮ በጊዜያዊው ሥጋዊ ሞት ከሥጋዊው ዓለም ለተለዩት አብርሃም፣ይስሐቅና ያዕቆብ አምላክ እንደሆነ የነገረው እግዚአብሔር ራሱን ሙሴን ነፍስና ሥጋውን አዋሕዶ ከመቃብር አስነስቶ በቃል ያስተማረውን በተግባር አሳይቶታል፡፡

መቼም ቢሆን አንድን ነገር/ድርጊት/ በተግባር ከማሳየት የሚበልጥ ነገሩን/ድርጊቱን/ የሚያስረዳ ስልት አይገኝም፡፡ የታቦርን ተራራ የትምህርተ ትንሣኤ ምውታን ማሳያ ቤተ ሙከራ አድርጎ መመልከት ይቻላል፡፡ በብሉይና4 በአዲስ ኪዳን ሲነገርና ሲተረጎም ላለውና ለነበረው ምሥጢረ ትንሣኤ ምውታን ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ ከመቃብር፣ነቢዩ ኤልያስ ደግሞ ከተሰወረበት መምጣታቸውና በደብረ ታቦር ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መነጋገራቸው የትንሣኤ ምውታን ማረጋገጫ ማኅተም ነው፡፡ አምላከ አማልክት ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዱቃውያንን “አነ ውእቱ እግዚአብሔር አምላከ አብርሃም ወአምላከ ይስሐቅ ወአምላከ ያዕቆብ ኢኮነኬ አምላከ ምውታን አላ አምላከ ሕያዋን ውእቱ/ እኔ እግዚአብሔር የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅም አምላክ፣ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፤ እንግዲህ የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም” (ማቴ. 22፡32) በማለት ስለ ትንሣኤ ምውታን በጎላ በተረዳ መልኩ አስተምሯቸዋል፡፡

በዮሐንስ ወንጌልም “በመቃብር ያሉ ቃሉን የሚሰሙባት ጊዜ ትመጣለችና ስለዚህ አታድንቁ፡፡ መልካም የሰሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሰሩም ለፍርድ ትንሣኤ ይነሳሉ በማለት ስለ ምሥጢረ ትንሣኤ መውታን አስተምህሮ አስረድቷል (ዮሐ 5፡28-29)፡፡” በአጠቃላይ ሞት የሥጋ፣የኅሊናና የነፍስ ሞት ተብሎ የሚመደብ ሲሆን የሥጋ ሞት የነፍስ ከሥጋ ጊዜያዊ መለየት ሆኖ ከጊዜያዊነት ወደ ዘላለማዊነት የምንሸጋገርበት መሻጋገሪያ ድልድይ፣ከምድራዊነት ወደ ሰማያዊነት ከፍ የምንልበት መወጣጫ መሰላል፣ከእንስሳዊነት ግብር ወደ መላእክታዊነት ግብር የምናድግበት፣ለዘላለማዊነት የምንጸነስበት ማኅፀን ነው፡፡ በአንድ በአዳም በደል ኀጢአትና ሞት ወደ ዓለም እንደገቡ በአንድ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ትንሣኤና ሕይወት ወደ ዓለም ገብተዋል፡፡(ሮሜ 5፡12-21፣ 1ቆረ15፡51-56፣ ሕዝ 37፣1-14)

ይህ ታላቁ የምሥጢረ ትንሣኤ አስተምህሮ በታላቁ የታቦር ተራራ ለዓለም ኹሉ ተገልጧል፡፡ ስለ ምሥጢረ ትንሣኤ ምውታን ቅዱሳት መጻሕፍት የተናገሩትን ምስክርነት ስለማይቀበሉ ሰነፎች ሰዎች የትምህርተ እግዚአብሔር ሊቁ አባታችን አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የተናገረውን ግሣጼያዊ ትምህርት እንደወረደ በማቅረብ የያዝነውን ንኡስ ርእሰ ጉዳይ ለማጠቃለል እንወዳለን፡፡ “እንግዲህስ ስለ ሙታን መነሣት የሚናገሩ የመጻሕፍት ምስክርነት ይበቃናል፡፡ በእነዚህ ጥቂት የመለኮት ቃሎች ካላመኑ ከዚህ የበዛም ብንናገር አያምኑም፡፡ መስማት ለተሳነው ሰው የመለከት ድምፅ በጆሮዎቹ አይገባም፤ ማየት የተሳነውም የፀሐይ ብርሃን አይታጠውም፤ ሰነፍም ስንፍናው ጥበብ ይመስለዋል፤ የጥበበኞችንም ነገር እንደ ጥራጊ ይጥለዋል፡፡ የምድርን አፈር በውሃ ብታጥባት በጭቃ ላይ ጭቃን ትጨምራለህ፤ማንጻትም አትችልም፤ሰነፍንም በጥበብ ቃል ብትገሥጸው በስንፍናው ላይ ስንፍናን ይጨምራል፤ዐዋቂም ልታደርገው አትችልም” (መጽሐፈ ምሥጢር ገጽ 358-359)፡፡

ስብሃት ለአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡ ይቆየን፡፡