መዳንም በሌላ በማንም የለም: ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ

ምክንያተ ጽሕፈት

በመጽሐፍ ቅዱስ የተመዘገበው የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት በቅዱሳን ሰዎች የተጻፈ ነው፡፡ የሚተረጎመውም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ጥበብ መንፈሳዊን ከእውነተኛ ምንጭ በተማሩ ሰዎች ነው፡፡ ይሁንና የበጎ ነገር ጠላት ዲያብሎስ በሀሰተኛ መምህራን እያደረ የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብ ይቆነጻጽላል፣ ትርጓሜአቸውንም ያጣምማል፡፡ ሐዋርያዊ ውርስ የሌላቸው፣ ቅዱሳት መጻሕፍትንም እንደግለሰብ ድርሰት በልብ ወደድ የሚተረጉሙ ሰዎች ትርጓሜአቸውን አጣመው ያለአውዳቸው እየጠቀሱ ራሳቸው ግራ ተጋብተው ምዕመናንን ግራ ከሚያጋቡባቸው የተወደዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት አንዱ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ የጻፈልንና በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 4፡12 የተጻፈው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ያስተማረው ትምህርት “መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰው የተሰጠ ሌላ ስም ከቶ የለምና” በማለት ፣ የተናገረው ምስክርነት ነው፡፡

ይህ የቅዱስ ጴጥሮስ ምስክርነት ጥልቅ የክርስትና ሃይማኖት መሠረተ እምነትን የሚያስረዳ ቃል ነው፡፡ ይሁንና “እምነታቸውን” ቤተክርስቲያንን በመቃወም ላይ ብቻ የመሠረቱ ሰዎች ልዩ ልዩ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮዎችን ለመቃወም ያለ አውዱ ይጠቀሙታል፡፡ ስለ በሽተኞች ፈውስና ሌሎች ተዓምራት፣ ስለ ቅዱሳን ሰዎች አማላጅነት፣ ስለ ቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ሲነገር እንዲሁም ስለሌሎች ማንኛውም ዓይነት መንፈሳዊ ውይይት ሲነሳ ሁሉንም በራሳቸው አላዋቂነት ልክ እያሰቡ ሌሎች መንፈሳዊ ሀሳቦችን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ጋር ያለአግባብ እየቀላቀሉ “መዳንም በሌላ በማንም የለም” የሚለውን አምላካዊ ቃል መልዕክት ሰው እንዳይረዳው ያደርጋሉ፡፡ የዛሬ አስተምህሮ ጦማር ዓላማ የዚህን አምላካዊ ቃል ትርጉም ማብራራትና በግምት የሚደረጉ የአጽራረ ቤተክርስቲያንን ማሳሳቻዎች ለይቶ ማሳየት ነው፡፡

የሐዋርያት ሥራ (ገድለ ሐዋርያት)

“መዳንም በሌላ በማንም የለም” የሚለውን የቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት ለመረዳት የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን ዓላማ መረዳት እንዲሁም ለቅዱስ ጴጥሮስ ንግግር መነሻ የሆነውን ታሪክ ማንበብ ይጠቅማል፡፡ የሐዋርያት ሥራ በዋናነት ቅዱሳን ሐዋርያት ከጌታ ትንሣኤ በኋላ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዓመታት ያደረጉትን መንፈሳዊ ተጋድሎ፣ ያስተማሩትን ሐዋርያዊ ትምህርት እና የተቀበሉትን ልዩ ልዩ ሰማዕትነት የሚያትት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው፡፡ የባህርይ አምላክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ ሊቃናት ክፋት ለመስቀል ሞት ተላልፎ ቢሰጥም እርሱ ግን የመጣበት ዓላማ ነበርና በሞቱ ሞትን አጥፍቶ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን አውጇል፡፡ በልዩ ልዩ ተዓምራት የተገለጠው የክርስቶስ ትንሣኤ ግን ለአይሁድ ሊቃናት የሐሰተኝነታቸው ማረጋገጫ፣ የግፈኝነታቸው ማሳያ፣ ከቀናች የአባቶቻቸው ሃይማኖትና ተስፋ ተለይተው ራሳቸው በፈጠሩት ሃይማኖታዊ ካባ ባለው ምድራዊ ክብርና ዝናን ብቻ በሚፈልግ አሳፋሪ ማንነት መተብተባቸውን የገለጠ ነበር፡፡ ስለሆነም በማናቸውም መንገድ የክርስቶስን ትንሣኤ ማስተሀቀር (ማስተባበል) የተንኮላቸው ሁሉ ማዕከል ነበር፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመስቀል አይሁድ ከጠቀሱት የማስመሰል ክስ አንዱ የእግዚአብሔር ልጅ፣ እግዚአብሔር መሆኑን በመጽሐፋቸው የተጻፈውን እንኳ እንዳያምኑ ልባቸውን አክብደው ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይገባው “ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር በሀሰት ያስተካክላል” በማለት የፈጠሩት የክህደት ንግግራቸው ነው፡፡ የሰይጣንን ተንኮል በደቀመዛሙርቱ ትምህርትና የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የሆኑ ልዩ ልዩ ተዓምራት ማፍረስ ልማዱ የሆነ እግዚአብሔር ደግሞ አላዋቂና ፈሪ የነበሩ ሐዋርያቱን ሳይቀር አዋቂና ደፋሮች አደረጋቸው፤ በእነርሱም እያደረ እንድንበት ዘንድ የተሰጠንን የክርስቶስን ሥም (ማንነት) በይፋ በመግለጥ ሊቃናተ አይሁድን አሳፈራቸው፣ ቤተክርስቲያንንም አጸናት፡፡

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከተጻፈባቸው ዓላማዎች ዋናው አይሁድ ጌታችን በሰው ባህርይ መገለጡን አይተው አምላክነቱን ይክዱ ያስክዱ ነበርና ስለእኛ በፈቃዱ ሰው መሆኑ፣ በመካከላችን መመላለሱ፣ መከራ መቀበሉ ከአብ ከመንፈስቅዱስ በክብር እንደማያሳንሰው ማስረዳት ነው፡፡ ለዚህም ነው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በተዓምራትና በትምህርት ነገረ ክርስቶስን በማጉላት የትንሣኤውን ኃይል የሚመሰክረው፡፡ የጌታችን የትንሣኤው ኃይል ከተገለጠባቸው ሐዋርያዊ አስተምህሮዎችና ተዓምራትና መካከል በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ሦስት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ያደረጉት ተዓምርና በተዓምሩ ምክንያት ቅዱስ ጴጥሮስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ አራት ያስተማረው የጌታችንን ትንሣኤ የሚያስረግጥ አስተምህሮ ይጠቀሳሉ፡፡

የቤተክርስቲያን የጸሎት ሰዓት

ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና ፍቁረ እግዚእ (የጌታ ወዳጅ) ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ “በጸሎት ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት ወደ መቅደስ ይወጡ ነበር፡፡” (ሐዋ. 3፡1) ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ስለ እውነት ፍርድህ ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ” (መዝ. 118፡ 164) እንዳለ በነቢያትና በሐዋርያት መሰረትነት በጸናች (ኤፌ. 2፡20) ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ከሚታወቁት ሰባቱ የጸሎት ጊዜያት አንዱ የተሰዓት (የቀኑ ዘጠኝ ሰዓት) ጸሎት ነው፡፡ ዘጠኝ ሰዓት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ተፈጸመ” ብሎ ቅድስት ነፍሱን ከክቡር ሥጋው የለየባት ሰዓት ስለሆነች ቅድስት ቤተክርስቲያን በተለየ ሁኔታ በጸሎት የምታስባት ሰዓት ነች፡፡ በአጽዋማት ጊዜ ቅዳሴ ተቀድሶ ሥጋውና ደሙ ለምዕመናን የሚሰጥባት የከበረች የጸሎት ሰዓት ነች፡፡ በሐዋርያት ሥራ 10፡3 እንደተመለከተው ቅዱሳን መላእክት የሰዉ ልጆችን ጸሎት ወደ መንበረ ጸባኦት የሚያሳርጉባት የከበረች የጸሎት ሰዓት ነች፡፡ የኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ትውፊት ምንጮች የሆኑ ቅዱሳን ሐዋርያትም በዘጠኝ ሰዓት ወደ ቤተ መቅደስ ይወጡ ነበር፡፡

በመቅደስ ደጅ ምጽዋት የሚለምን በሽተኛ

ቅዱሳን ሐዋርያት ወደ ቤተመቅደስ ሲሄዱ “ከእናቱ ማኅፀንም ጀምሮ እግሩ ሽባ ሆኖ የተወለደ…ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ ሁልጊዜ እየተሸከሙ መልካም በሚልዋት በመቅደስ ደጃፍ [ያስቀምጡት የነበረ በሽተኛ] ጴጥሮስና ዮሐንስንም ምጽዋት ይሰጡት ዘንድ ለመናቸው፡፡” (ሐዋ. 3፡2-3) የድኅነትን ነገር መቀለጃ የሚያደርጉ ሰዎች ድኅነት “በእምነት ብቻ” እንደሆነ አስመስለው ቅዱሳት መጻሕፍትን በማጣመም ፆም፣ ጸሎት፣ ምጽዋት፣ ስግደትና ሌሎችም በጎ ምግባራት ከድኅነት ጋር የማይገናኙ እንደሆኑ አስመስለው ምዕመናንን ከጽድቅ መንገድ ለመለየት ይደክማሉ፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ግን እምነት ያለምግባር ከነፍስ እንደተለየ ሥጋ የሞተ መሆኑን (ያዕ. 2፡14-26) በማስተማር ምዕመናን እንደ አቅማቸው ምጽዋትን ለተቸገሩት እንዲሰጡ፣ የተቸገሩትን የማይረዳ ምዕመንም በዕለተ ምጽአት እንደሚፈረድበት በአጽንኦት ታስተምራለች፡፡ (ማቴ. 25፡31-46) ከዚህም የተነሳ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ዘመን ምጽዋትን የሚፈልጉ ችግረኞች መጠለያ መሆኗ የታወቀ ነው፡፡ ከሐዋርያት የተማረችው ነውና፡፡

የቅዱሳን ሐዋርያት ተዓምር

ከእናቱ ማኅጸን ጀምሮ ሽባ ሆኖ የተወለደው ሰው ቅዱሳን ሐዋርያት ወደ ቤተ “መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ይሰጡት ዘንድ ለመናቸው፡፡” እነርሱ ግን እርሱ ከጠበቀው የገንዘብ ምጽዋት የበለጠውን የፈውስ ምጽዋት ሰጡት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ወርቅና ብር የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ ሂድ” አለው፡፡ (ሐዋ. 3፡3-6) አይሁድ ናዝሬትንና ከናዝሬት የሚወጡ ሰዎችን ይንቋቸው ነበር፣ ናዝሬት የወንበዴዎች ከተማ ነበረችና፡፡ ለዚያ ነው ምሁረ ኦሪት የነበረው ናትናኤል ቅዱስ ፊልጶስ ሙሴና ነቢያት የተናገሩለትን “የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው” ባለው ጊዜ “በውኑ ከናዝሬት ደግ ሰው ሊወጣ ይቻላልን?” ያለው፡፡ (ዮሐ. 1፡46-47) ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም” ሽባውን ማዳኑ ለአይሁድ ልዩ መልእክት ነበረው፡፡ “እናንተ ከናዝሬት በመገኘቱ (ናዝሬት በማደጉ) የናቃችሁት፣ በሀሰት ፍርድ ለመስቀል ሞት አሳልፋችሁ የሰጣችሁት፣ ትንሣኤውን ለመደበቅ የሀሰት ምስክር ገዝታችሁ ከወቀሳ ለመዳን የምትደክሙበት ኢየሱስ ክርስቶስ የክብር ትንሣኤው ማሳያ የሆነ ይህን ተዓምር በእኛ እጅ አደረገ” ማለቱ ነው፡፡

የትንሣኤው ኃይልና የኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት

ቅዱሳን ሐዋርያት ተዓምራቱን የማድረጋቸው ዓላማ የክርስቶስን የትንሣኤ ኃይል መግለጥ ነበር፡፡ የእስራኤል ሰዎች ከእናቱ ማኅጸን ጀምሮ ሽባ ሆኖ የተወለደውን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ሥም፣ በደቀመዛሙርቱ አማካኝነት መፈወስ ባዩ ጊዜ ተደነቁ፡፡ ቅዱሳን ተዓምራትን የሚያደርጉት እንደዘመናችን ጋጠወጥ መናፍቃን፣ ጠንቋዮች፣ መተተኞችና ከንቱ ውዳሴ ፈላጊዎች ለራሳቸው አንዳች ክብር ወይም ጥቅም ፈልገው አይደለም፡፡ ስለሆነም ሰዎች ሁሉ በተደነቁ ጊዜ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “እናንት የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ ይህን ለምን ታደንቃላችሁ? እኛንስ በኀይላችንና በጽድቃችን ይህን ሰው በእግሩ እንዲሄድ እንዳደረግነው አስመስላችሁ ለምን ታዩናላችሁ?…የሕይወትን ባለቤት ግን ገደላችሁት፤ እግዚአብሔርም ከሙታን ለይቶ አስነሣው፤ ለዚህም እኛ ምስክሮቹ ነን፡፡ ስሙን በማመን ይህን የምታዩትንና የምታውቁትን እርሱ ስም አጸናው፤ እርሱንም በማመን በፊታችሁ ይህን ሕይወት ሰጠው፡፡” (ሐዋ. 3፡12-16) በማለት መሰከረ፡፡

ይህ ምስክርነት የክርስቶስን እውነተኛ አምላክነት (ሞትን በስልጣኑ ድል ማድረጉን) እንደገለጠው ሁሉ የአይሁድ ሊቃናት (አለቆችን) ሀሰተኛነት የገለጠ ነበርና የአይሁድ የቤተመቅደስ አለቆች፣ በተለይም “ትንሣኤ ሙታን የለም” ብለው የሚያስተምሩትን የምንፍቅና አስተምህሮ ያፈረሰባቸው ሰዱቃውያን መከራ ሊያጸኑባቸው ተሰበሰቡ፤ ቅዱሳን ሐዋርያትንም በማን ስምና በማን ኀይል ተዓምራቱን እንዳደረጉ ጠየቋቸው፡፡(ሐዋ. 4፡1-7) በአይሁድ ሀሳብ ሐዋርያት ማስፈራራታቸውን አይተው የተዓምራቱን ባለቤት፣ የትንሣኤያችን በኩር የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ከመስበክ (አምላክነቱን፣ አዳኝነቱን፣ ቤዛነቱን ከመመስከር) የሚቆጠቡ መስሏቸው ነበር፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ግን አይሁድን በኃጢአታቸው ወቅሶ፣ የክርስቶስን ትንሣኤ መስክሮ፣ በሽተኛውም የተፈወሰው በክርስቶስ ሥም በማመን መሆኑን ነገራቸው፡፡

ይልቁንም “መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰው የተሰጠ ሌላ ስም ከቶ የለምና” (ሐዋ. 4፡12) በማለት ሰቃልያነ እግዚእ አይሁድን አሳፈራቸው፡፡ አይሁድ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥም (የክርስቶስን አምላክነት፣ ትንሣኤውን ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱን) እንዳያስተምሩ በከለከሏቸው ጊዜም ቅዱሳን ሐዋርያት “እግዚአብሔርን ያይደለ እናንተን ልንሰማ በእግዚአብሔር ፊት ይገባልን? እስኪ እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ፡፡ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም እንል ዘንድ አንችልም፡፡” (ሐዋ. 4፡19-20) በማለት በጽናት ቆመዋል፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ሳያምኑ፣ ይልቁንም ትንሣኤውን እየካዱ መዳን በሌላ በማንም የለምና፡፡

መዳን ማለት ምን ማለት ነው?

በቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ መዳን ማለት በዋናነት የዘላለምን ሕይወት ማግኘት ማለት ነው፡፡ ከዚያም ባሻገር ግን መዳን ማለት እንደ አገባቡ ከስጋ ደዌ፣ ከአጋንንት እስራት መፈወስንም ያሳያል፡፡ ጌታ በወንጌል “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ትሻለች” (ማቴ. 16፡4) እንዳለ በእምነት የደከሙ ሰዎች ተዓምር ናፋቂ ስለሆኑ መዳን ሲባል የሚታያቸው ሥጋዊ ድህነት ብቻ ነው፡፡ ከበሽታ መዳን፣ ሀብትና ንብረት ማግኘት፣ በምድር በሰዎች ዘንድ ከፍ ብሎ መታየት መዳን ይመስላቸዋል፡፡ ለዚያ ነው በዘመናችን ያሉ መናፍቃንና መሰሎቻቸው የትምህርታቸው ሁሉ መሰረት የሀሰት ተዓምራት የሆነው፡፡ እነዚህ ደካሞች “መዳንም በሌላ በማንም የለም” የሚለውን ቅዱስ ቃል ከምድር ከፍ በማይል ሀሳባቸው ለልዩ ልዩ የሥጋ  ደዌ የተነገረ ይመስላቸዋል፡፡ ምዕመናንና ምዕመናት በቅዱሳን ቃልኪዳን፣ በቤተክርስቲያን ጸሎት ከደዌ ሥጋ ሲድኑም ብርቅ ይሆንባቸዋል፡፡ በውስጣቸው ያደረ የበጎ ነገር ጠላት ዲያብሎስም ከምድራዊ ሀሳባቸው ከፍ እንዳይሉ ስለሚፈልግ በደካማ አመክንዮ በቅዱሳን ቃል ኪዳን ሰዎች ከደዌ ሥጋ መዳናቸው “መዳንም በሌላ በማንም የለም” በማለት ቅዱስ ጴጥሮስ ከተናገረው ጋር የሚጋጭ አስመስለው ይከራከራሉ፡፡

እንግዲህ ምን እንላለን? ለእነዚህ ሰዎች የቅዱሳንን ቃል ኪዳን ከማስረዳት በዓይናቸው የሚያዩትን የዓለም ስርዓት ዓይናቸውን ገልጠው እንዲያዩ ማገዝ ይቀላል፡፡ ተፈጥሮ እንኳ አያስተምራችሁም? የእግዚአብሔር ሥጋዊ መግቦት በእምነት የማይገደብ እንደሆነ፣ ቸር የሆነ አምላክ ለክፉዎቹም ለደጎቹም የምህረት ዝናብን እንደሚያዘንብ፣ የቸርነት ፀሐይን እንደሚያወጣ መረዳት አትችሉም? እናንተ አላዋቂዎች አንድ እግዚአብሔርን የካደ ሰው እንኳ በክፉ ሥጋዊ ደዌ ቢታመም እግዚአብሔርን የማያውቁ ምድራውያን ጠበብት ሲያድኑት አላያችሁም? በስጋዊ ደዌ የታመመን ሰው ምድራውያን ጠበብት በህክምና ሲያድኑት የእግዚአብሔር የማዳን እጅ የሌለችበት ይመስላችኋል? ምንም እንኳ ምድራዊ ጥበብና በቅዱሳን የሚገለጥ ተዓምር የተለያዩ ቢሆኑም ምሳሌው በተዓምራት የሚፈጸም ስጋዊ ድህነትን ለመረዳት ይጠቅመናል፡፡ በዚህ ጊዜም ከምድር ከፍ ያላለ ቅዱሳት መጻሕፍትን በግምት የሚተረጉም፣ የሐዋርያትን የሕይወትና የትምህርት ውርስ የማይከተል የማያስተውል ልቦናችሁ “መዳንም በሌላ በማንም የለም” እያለ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጉም እንዳትረዱ ሲጋርድባችሁ ለምን መንቃት አትችሉም? እስኪ ከአይሁድ ተማሩ፡፡

ሊቃናተ አይሁድ ሽባውን ሰው ቅዱሳን ሐዋርያት ድኅነተ ሥጋ ስለሰጡት ተደንቀው “በማን ስምና በማን ኀይል” (ሐዋ. 4፡7) ተዓምራቱ እንደተደረገ ለማወቅ ጓጉተው ነበር ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ የመጡት፡፡ ሥጋዊ ሰው ምንጊዜም የሚታየው ሥጋዊ ክብር፣ ሥጋዊ ድህነት፣ ሥጋዊ ደስታ ብቻ ስለሆነ መንፈሳዊው ክብር፣ መንፈሳዊው ድህነት፣ መንፈሳዊው ደስታ አይታሰበውም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ሽባውን ከአካላዊ በሽታ ያዳኑት እርሱና ተዓምራቱን ያዩ ሁሉ ወደ እውነተኛው ድኅነት (ዘላለማዊ ሕይወት) እንዲመለሱ የዘላለም ሕይወት ምንጭ የሆነውን አይሁድ በናዝራዊነቱ ያቃለሉትን የመዳናችንን ራስ ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያምኑበት ምልክት እንዲሆናቸው ነው፡፡ ስለሆነም አይሁድ ለሥጋዊ ተዓምር ሲሰበሰቡ ቅዱስ ጴጥሮስ ልባቸውን ከፍ አደረገው “መዳንም በሌላ በማንም የለም” በማለት መንፈሳዊውን ተዓምር የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው መሆን፣ በዚህም ሰውም አምላክም ሆኖ በሐዲስ ኪዳን መካከለኛነቱ የሰውን ባሕርይ ተዋህዶ በአምላካዊ ስልጣኑ ከኃጢአት ፍርድ የተቤዠን መሆኑን እንዲያምኑ አስተማራቸው፡፡

የተቀደሰ ሐዋርያ ጳውሎስ “አሁንም ወንድሞቼ ሆይ ዘወትር እንደምትሰሙኝ ሳለሁ ብቻ ሳይሆን ሳልኖርም በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ሆናችሁ ለድኅነታችሁ ሥሩ [መዳናችሁን ፈጽሙ]” (ፊልጵ. 2፡12) እንዳለ መዳን ማለት የዘላለምን ሕይወት መውረስ፣ ጌታችን በዳግም ምጽዓት በክበበ ትስብእት፣ በግርማ መለኮት በተገለጠ ጊዜ በቀኙ ከሚቆሙት፣ የሕይወትን ቃል ከሚሰሙት ቅዱሳን ወገን (ማቴ. 25፡31-46) ለመሆን መብቃት (መታደል) ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “መዳንም በሌላ በማንም የለም” ሲል በኢየሱስ ክርስቶስ ሳያምኑ የዘላለም ሕይወት አይገኝም ማለቱ ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዳያስተምሩ ይከለክሏቸው የነበሩ አይሁድ ራሳቸውን የነቢያት ወራሾች፣ እውነተኛ ሃይማኖተኞች አስመስለው ያቀርቡ ነበርና ቅዱስ ጴጥሮስ “በኢየሱስ ክርስቶስ ሳታምኑ ስመ እግዚአብሔርን ብትጠሩ፣ በነቢያት ብትመኩ መዳን አትችሉም” ሲላቸው ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ

በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን መሰረታዊ አስተምህሮ ለድኅነት መሠረት የሆኑ አምስት ዋና ዋና መሠረተ እምነቶች (ዶግማዎች) አሉ፤ እነርሱም አምስቱ አዕማደ ምስጢራት ተብለው ይታወቃሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ እንኳ ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቆም አይችልም፡፡

  1. በምስጢረ ሥላሴ ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ህይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ባለው ፍጹም አንድነትና ልዩ ሦስትነት ያላመነ ሰው መዳን በሌላ በማንም አያገኝም፡፡
  2. በምስጢረ ሥጋዌ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ለማዳን ንጽሕት፣ ቅድስት ከሆነች፣ ከአዳም ተስፋ፣ ከዳግሚት ሄዋን፣ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ መወለዱን፣ በመወለዱም ከአምላካዊ ክብሩ እንዳልተለየ የማያምን ሰው መዳን በሌላ በማንም አያገኝም፡፡
  3. በምስጢረ ጥምቀት ጥምቀትን በባህረ ዮርዳኖስ ከመሠረተ፣ በመስቀል በተሰቀለ ጊዜ ሌንጊኖስ የተባለ ሮማዊ ወታደር ጎኑን በጦር ሲወጋው ለልጅነት ጥምቀት፣ ለድህነት ጥምቀት ንፁህ ውሃና ደም በፈሰሰው በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት አምኖ፣ መስክሮ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ያልተጠመቀ ሰው መዳን በሌላ በማንም አያገኝም፡፡
  4. በምስጢረ ቁርባን ሕብስቱን ለውጦ ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሀደው  ሥጋ፣ ወይኑን ለውጦ ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሀደው ደም ባደረገ (በሚያደርግ)፣ ለዘላለምም በቤተክርስቲያን አድሮ ይህን አምላካዊ ተዓምር በሚፈጽም በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ የጌታን ቅዱስ ሥጋውን፣ ክቡር ደሙን ለልጅነት፣ ለስርየተ ኀጢአት የማይቀበል (የማይበላ የማይጠጣ) ሰው መዳን በሌላ በማንም አያገኝም፡፡
  5. በምስጢረ ትንሣኤ ሙታን አስቀድሞ ለዓለም ቤዛነትና አርአያነት በትህትና ከመጣበት አመጣጥ በተለየ በክበበ ትስብእት (በሰው ሥጋና አካል)፣ በግርማ መለኮት (በደብረታቦር ተራራ እንደተገለጠው ያለ መለኮታዊ ግርማ) በሚገለጥ በቀናች ሃይማኖት፣ በደገኛ ምግባር ጸንተው የሚጠብቁትን ወደ ዘላለማዊ ሕይወት፣ በሰይጣን ማታለል በመናፍቃን ማጭበርበር ተታለው ከቀናች ሃይማኖት፣ ከደገኛ ምግባር የራቁትን ወደ ዘላለም ቅጣት የሚልክ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመጣ የማያምን፣ ለዚያች የፍርድ ቀንም በአካለ ሥጋ እያለ የማይዘጋጅ ሰው መዳን በሌላ በማንም አያገኝም፡፡

ስለሆነም “መዳንም በሌላ በማንም የለም” ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የቤተክርስቲያን ራስና መሰረት መሆኑን፣ እምነትም ምግባርም ያለእርሱ ዋጋ ቢስ መሆኑን ማመን፣ መቀበል፣ በሕይወትም መኖር ማለት ነው እንጂ በመዳን ጉዞ ከእያንዳንዱ ምዕመን እምነትና ምግባር፣ በአጸደ ስጋና በአጸደ ነፍስ ካሉ ቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ፣ እንዲሁም ከቅዱሳን መላእክት ረዳትነት ጋር የሚነጻጸር ወይም የሚምታታ አይደለም፡፡

ማነጻጸሪያ ምሳሌዎች

የመዳን እውነተኛ መንፈሳዊ ትርጉም ከላይ እንደተብራራው መሆኑን ካየን እያንዳንዱ ሰው ለድኅነት እንዲበቃ የተለያዩ አካላትን ተመጋጋቢ ድርሻ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ሀሰተኞች በሰው ልጅ መዳን የእግዚአብሔርን ድርሻና የቅዱሳን ሰዎችና መላእክትን ድርሻ ባለመረዳት ወይም ሆነ ብሎ በማምታታት ብዙ ምዕመናንን ግራ እንደሚያጋቡ ይታወቃል፡፡ የቤተክርስቲያን መሰረታዊ ትምህርት ግልጽ ነው፡፡ በአጸደ ሥጋ ያሉ ክርስቲያኖች ጸሎትና ትምህርት፣ በአጸደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን ምልጃ፣ የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት በቅዱሳት መጻሕፍት በተገለጠችው የቀናች ሃይማኖትና ደገኛ ምግባር እንድንጸና የሚረዳን በቤተክርስቲያን በኩልም ወደ ሕይወት ባለቤት እግዚአብሔር የሚያቀርበን አጋዥ እንጅ መሠረተ እምነትን የሚተካ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት፣ ከእግዚአብሔር ቸርነት የተለየ ሌላ መንገድ አይደለም፡፡

ቤተክርስቲያን (እያንዳንዱ ምዕመን እንዲሁም ማኅበረ ምዕመናንን የሚወክሉ የቤተክርስቲያን አካላት) ያላስተማረችው፣ ወንጌልን ያላስረዳችው ሰው ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ሊያውቅ ይችላል? (ሮሜ 10፡14) ቅዱሳን ሰዎች በቃልኪዳናቸው ያልረዱት፣ ቅዱሳን መላእክት በጥበቃቸው ከሰይጣን ፈተና፣ ከኃጢአት  እስረኝነት ተላቆ መንፈሳዊ ፍሬን አፍርቶ በሕይወቱ ጌታን እንዲያስደስት ያላገዙት ሰው እንዴት ትምህርተ ወንጌልን ሊፈጽማት ይችላል? (መዝ. 105፡23፣ ሉቃ. 13፡6-9) የቤተክርስቲያን ጥረት፣ የቅዱሳን ጸሎት፣ የመላእክት ርዳታ ከእግዚአብሔር ቸርነት የተለየ የሚመስለው ሰውስ በእውነት መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ሊረዳ ይችላል? እነዚህን ጥያቄያዊ ማብራሪያዎች የበለጠ ለመረዳት ሁለት ማነጻጸሪያ ታሪኮችን በምሳሌነት እናንሳ፡፡

ምሳሌ 1: የእስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ ወደ ከነአን ጉዞ

በኦሪት ዘፀዓት እንደተመዘገበው እግዚአብሔር አምላካችን በስሙ ያመኑትን፣ በምግባራቸው ያስደሰቱትን ሰዎች ከእስራኤል ዘሥጋ መካከል ለይቶ ከግብጽ ወደ ከነአን አሻግሯቸዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ የእስራኤል ዘሥጋ ታሪክ የሚነግረን ምድራዊ የታሪክ ሽኩቻዎች ዋና ዓላማዎቹ ስለሆኑ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ (በ1ኛ ቆሮ 10፡1-13) መልእክቱ እንዳስተማረን እስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ ወደ ከነአን ያደረጉት ምድራዊ ጉዞ እኛ ከምድር ወደ መንግስተ እግዚአብሔር የምናደርገው መንፈሳዊ ጉዞ ምሳሌ ስለነበረ ነው፡፡ በእስራኤል ጉዞ ከተደረጉት ድንቅ ተዓምራት አንዱ ያስቸግራቸው የነበረ ፈርኦን ሰራዊትን በባህረ ኤርትራ አስጥሞ እነርሱን በደረቅ ያሻገራቸው የእግዚአብሔር የቸርነት ስራ ነው፡፡

ይህን ታሪክ “መዳንም በሌላ በማንም የለም” ከሚለው ንባብ ጋር በተነጻጻሪ መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ እግዚአብሔር ምንም ቸር ቢሆንም የነጻነት አምላክ ነውና ማንንም በማስገደድ ከነጻ ፈቃዱ ውጭ አያድነውም፡፡ በባህረ ኤርትራ በተደረገው ተዓምር እያንዳንዱ እስራኤላዊ፣ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴና ሌሎች እስራኤልን ይመሩ የነበሩ ሰዎች፣ በደመና ይመራቸው የነበረ የእግዚአብሔር መልአክ (ቅዱስ ሚካኤል)፣ የሙሴ በትር የየራሳቸው ድርሻ ነበራቸው፡፡ የማናቸውም ድርሻ ግን ከእግዚአብሔር ቸርነት ጋር የሚጋጭ ወይም የሚወዳደር አልነበረም፡፡ የእያንዳንዳቸው ጥረት ፈቃደ እግዚአብሔር እንዲፈጸም በማድረጉ ሁሉም በየድርሻቸው ይመሰገናሉ፡፡ የሙሴ በትር ከሌሎች በትሮች የተለየችው ለዚያ ነው፡፡ ባሕረ ኤርትራን ተሻግረው ምድረ ርስት የደረሱት እስራኤል በመንገድ ከተቀሰፉት የተለዩትና የተመሰገኑት ለዚያ ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ፣ ኢያሱና ካሌብ እስከ አሁን ድረስ ለቀናች አገልግሎታቸው የሚመሰገኑት ለዚህ ነው፡፡ በወቅቱ በአካለ ሥጋ ያልነበሩት፣ በጸሎታቸው በቃልኪዳናቸው እስራኤል እንዲሻገሩ የረዱ ቀደምት አበው (ለምሳሌ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ) በተለየ ሁኔታ የሚመሰገኑት ለዚህ ነው፡፡ እስራኤልን ቀን በደመና፣ ሌሊት በብርሃን እየመራ የድኅነት ምሳሌ ወደሆነች ከነአን ያደረሳቸው የእግዚአብሔር  መልአክ መጋቤ ብሉይ ቅዱስ ሚካኤልም በእስራኤል ረዳትነቱ በልዩ ሁኔታ የሚመሰገነው ለዚህ ነው፡፡ (ዘፀ. 23፡20-23)

እነዚህ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደየድርሻቸው ተለይተው ተወስተዋል፣ ተመስግነዋል፡፡ ነገር ግን የአንዳቸውም ድርሻ ከእግዚአብሔር ማዳን ጋር እንደማይጋጭ ይልቁንም የእግዚአብሔር የማዳን ስራ መገለጫዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት  “እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፣ ቤትን የሚሠሩ በከንቱ ይደክማሉ፤ እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፣ የሚጠብቁ በከንቱ ይተጋሉ” (መዝ. 126፡1) እንዳለ የእግዚአብሔር ቸርነትና የሰው ልጆች ጥረት እርስ በርስ የሚፎካከሩ ሳይሆኑ የሚመጋገቡ፣ የተያያዙ መሆናቸውን መረዳት ይገባል፡፡ አንተ የዋህ ቤትን የሚሰራው፣ ከተማን የሚጠብቀው እግዚአብሔር እንደሆነ ታምናለህ? በዚህ እምነት የተነሳ ግን  ያለ እግዚአብሔር ቤትን መስራት፣ ከተማን መጠበቅ አይቻልም ብለህ እጅህን አጣጥፈህ ትቀመጣለህ? የሚሰሩትንስ “አትድከሙ ቤትን የሚሰራው፣ ከተማን የሚጠብቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው” ትላለህ? እርግጠኛ ነኝ ቢያንስ ለሆድህና ለኑሮህ ስትል እንደዚያ አትልም፡፡ ታዲያ በተመሳሳይ አመክንዮ ሰይጣን ከጽድቅ መንገድ ሊያወጣህ “መዳንም በሌላ በማንም የለም” የሚለውን ያለቦታው ያለትርጉሙ እየጠቀሰ ሲያታልልህ ለምን ትወናበዳለህ? የሰው ድርሻ ሌላ፣ የመላእክት ድርሻ ሌላ፣ የሌሎች ፍጥረታት ድርሻ ሌላ፣ እግዚአብሔር ድርሻ ሌላ መሆኑን እንዳትረዳ “ብቻ፣ ብቻ፣ ብቻ” በሚል ሰይጣናዊ ማዘናጊያ አዚም ያደረገብህ ማን ነው?

ምሳሌ 2: በወይኑ ቦታ የተተከለችው በለስ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በነገረ ድህነት የቅዱሳን መላእክትን ድርሻ በምሳሌ ካስረዳባቸው ትምህርቶች አንዱ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 13፡6-9 የተመዘገበው ምሳሌአዊ ታሪክ ነው፡፡ ከታሪኩ እንደምንረዳው አንድ ሰው በወይኑ ቦታ የተተከለች በለስ ነበረችው፡፡ ከበለሷም ፍሬ ፈልጎ በተደጋጋሚ (ሦስት ጊዜ) ቢመጣም ፍሬ ሊያገኝባት አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ የወይኑን ጠባቂ ጠርቶ ፍሬ ያላገኘባትን በለስ እንዲቆርጣት አዘዘው፡፡ የበለሷ ጠባቂ ግን “አቤቱ አፈር ቆፍሬ በሥሯ እስከ አስታቅፋት፣ ፍግም እስካፈስባት ድረስ የዘንድሮን እንኳ ተዋት፡፡ ምናልባትም ለከርሞ ታፈራ እንደ ሆነ፣ ያለዚያ ግን እንቆርጣታለን፡፡” በማለት ስለ በለሷ አዝኖ ተሟገተላት፡፡

የወይን ባለቤት የተባለ አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ወይን የተባልን በስሙ አምነን ፍሬ (በጎ ምግባር) ማፍራት እንዳለብን የታዘዝን ምዕመናን ነን፡፡ (ኢሳ. 5፡1፡19) የወይን ጠባቂ የተባለው እያንዳንዱን ምዕመን ከሚጠብቁ ቅዱሳን መላእክት አንዱ ነው፡፡ (ማቴ. 18፡10፣ ራዕይ. 4፡1-11) ቅዱሳን መላእክት በቀናች ሃይማኖት ጸንተን፣ በበጎ ምግባራት ፍሬ አፍርተን መዳን የሚገኝበትን ሕይወት እንድንይዝ ይረዱናልና፡፡ (ዕብ. 1፡14) በበለሷ ምሳሌ ለበለሷ መዳን የበለሷ ድርሻ እንክብካቤውን ተጠቅማ የሚጠበቅባትን ፍሬ ማፍራት ነው፡፡ የመልአኩ ድርሻ በለሷን በሚያስፈልጋት ሁሉ እየረዳ ፍሬ እንድታፈራ ማድረግ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ድርሻ በለሷ ፍሬ እንድታፈራ መልአኩን እየላከ፣ ተፈጥሮን እየገሰፀ ኃይል ብርታት መሆን ነው፡፡ የበለሷ ፍሬ ማፍራት የመዳን ምሳሌ ነው፡፡ አንተ የዋህ አንተ በለሷን ስትሆን  “መዳንም በሌላ በማንም የለም” የሚለውን ቅዱስ ቃል እንደሰይጣን ያለቦታው፣ ያለትርጉሙ እየጠቀስክ እግዚአብሔር የሾመልህን ቅዱሳን መላእክት የምታቃልል፣ ለመዳንህ ያላቸውን ድርሻ የምታጥላላ ከማን ተምረኸው ነው?

ማጠቃለያ

የጸጋ ሁሉ ምንጭ አምላካችን እግዚአብሔር የማዳን ስራውን በቅዱሳን ሰዎችና መላእክት አማካኝነት ይገልጣል፡፡ በስሙ አምነን ህይወትን የምናገኝበት አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማዳን የባህርይ ገንዘቡ እንጅ ከማንም የተቀበለው አይደለም፡፡ በአንጻሩ ቅዱሳን ሰዎችና መላእክት ከጌታ በተቀበሉት ጸጋ ሰዎችን ከደዌ ስጋ ያድናሉ ወደዘላለማዊ ሕይወት በሚደረገው የመዳን ጉዞም በትምህርታቸው፣ በተዓምራታቸው፣ በጥበቃቸው፣ በአማላጅነታቸው እያገዙ በክርስቶስ ቤዛነት ያመኑ ሰዎችን ይረዳሉ፡፡ ለምሳሌ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፣ ያድናቸውማል” (መዝ. 33፡7) ማለቱ ለቅዱሳን የተሰጠውን የማዳን ጸጋ ያስረዳናል፡፡ በአጸደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን ሰዎች፣ ሰዎችን ወደ ጽድቅ መንገድ የሚመሩ ቅዱሳን መላእክት እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው በመዳን ጉዞ ያላቸውን ሱታፌ ከማይነጻጸረው የእግዚአብሔር ማዳን ጋር ማምታታት አይገባም፡፡ “መዳንም በሌላ በማንም የለም” የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል ያለ አውዱ እየጠቀሱ ለዘላለም ሕይወት ለመብቃት በምናደርገው ጉዞ የእያንዳንዱን ምዕመን እምነትና ምግባር፣ በአጸደ ስጋም ሆነ በአጸደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳንን ጸሎትና አማላጅነት፣ የቅዱሳን መላእክትን ረዳትነት ከኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ጋር ተነጻጻሪ ወይም ተፎካካሪ አስመስለው የሚያቀርቡ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ሳይረዱ አለማወቃቸውን በጩኸት ብዛት ለመሸፈን የሚሞክሩ ደካሞች ናቸው፡፡

እነዚህን ሰዎች ስናይ ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ጆርጅ ኦርዌል የተባለ ደራሲ “የእንስሳት እድር” (Animal Farm) በተባለ ድርሰቱ በሞኝነትና አላዋቂነት ገጸባሕርይ የጠቀሳቸው  በጎች ሊታወሱን ይችላሉ፡፡ በድርሰቱ የተጠቀሱት በጎች አንድ አስቂኝ ጠባይ ነበራቸው፡፡ በጎቹ ያሰባሰቧቸውን ሕግጋት በሙሉ የመረዳት አቅም የላቸውም፡፡ እነርሱ የሚያውቁት አለቆቻቸው የሆኑት አሳማዎች በተንኮል ቀባብተው የሚሰጧቸውን ነገር ሁሉ ያለመገምገም እየተቀበሉ ጉሮሮአቸው እስኪንቃቃ ድረስ “Four legs good; two legs bad” (አራት እግር ጥሩ ነው፤ ሁለት እግር መጥፎ ነው) እያሉ መጮህና ልሂቃኑ ከፍ ያለ መረዳት የሚጠይቀውን ትምህርት እንዳያስተምሩ፣ ሌሎችም እንዳይረዱ መረበሽ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን የምታስተምረውን የነገረ ድኅነት ምስጢር የማይረዱ ደካሞችም የማያውቁትን ይቃወማሉ፤ ደርዝ በሌለው የአላዋቂነት ድፍረታቸውም ራሳቸው ክደው ሌሎችን ያስክዳሉ፣ የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብና ትርጉም ያጣምማሉ፡፡ የቅዱሳን አምላክ፣ የሰራዊት (ቅዱሳን መላእክት) ጌታ አምላካችን እግዚአብሔር ከሰይጣን ማታለል፣ ከመናፍቃን ክህደት ተጠብቀን በቀናች ሃይማኖት በበጎ ምግባር ጸንተን እንድንኖር ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

“መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰው የተሰጠ ሌላ ስም ከቶ የለምና”

ስብሃት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር፡፡ አሜን፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s