በዲያቆን ሙሉነህ ጌቴ
መግቢያ
በታቦርሂ አመ ቀነጸ መለኮትከ ፈረስ፤ ኢክህሉ ስሒቦቶ ሙሴ ወኤልያስ፡፡ የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ ቄሰ ገበዝ ሐዲስ ኪዳናት እና ልጃቸው የቅኔዋ ንግሥት እሙሐይ ገላነሽ ሐዲስ በደብረ ጽላሎ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ለደብረ ታቦር በዓል የተቀኙት የመወደስ ቅኔ ሲሆን “ለዓለም” በመባል ከሚጠራው የአንድ መወድስ ቅኔ ክፍል ውስጥ አንደኛውና ኹለተኛው ቤት ቅኔ ነው፡፡ ቄሰ ገበዝ ሐዲስ ኪዳናት በቅኔ ማኅሌት ሆነው “በታቦርሂ” ብለው ቤቱን ሲጨርሱ በምቅዋመ አንስት (በሴቶች መቆሚያ) ያለችው በቅኔ የሰከረችው ሕጻኒቱ ልጃቸው ገላነሽ “ኢክህሉ ስሒቦቶ ሙሴ ወኤልያስ” ብላ ቅኔውን ከአባቷ ነጥቃ (ዘርፋ) ተቀኘች፡፡ የቅኔው ትርጉምም በደብረ ታቦር ተራራ የመለኮትህ መገለጥ ፈረስ በዘለለ ጊዜ ሙሴና ኤልያስ ሊገቱት አልቻሉም ማለት ሲሆን ምሥጢሩም ሙሴና ኤልያስ ታቦር ተብሎ በሚጠራው ተራራ የተገለጠውን ግርማ መለኮትህን ማየት ተሳናቸው ማለት ነው፡፡ ይኸውም መለኮት ብርሃኑን ብልጭ ባደረገ ጊዜ ፍጡሩ ዐይን ግርማ መለኮትን የማየት አቅም ስለተሳነው ሙሴ “ይኄይሰኒ መቃብርየ/መቃብሬ ይሻለኛል/” ብሎ ወደ መቃብሩ ኤልያስም በሠረገላው ወደ መኖሪያው /ወደ ተሰወረበት ቦታ ማለትም ብሔረ ሕያዋን/ ተመልሰዋል፡፡
ታቦር የተራራ ስም ሲሆን ከገሊላ ባሕር በምዕራባዊ ደቡብ በኩል 10 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቆ በመገኘት 572 ሜትር ከባሕር ጠለል (ወለል) ከፍ ይላል፡፡ በዚህ ተራራም ባርቅ ሲሳራን አሸንፎበታል፤ ጌታችንና አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው በሚያስተምርበት ወቅት ምሥጢረ መንግሥቱን እና ብርሃነ መለኮቱን ለነቢያት እና ለሐዋርያት ገልጦበታል፡፡ በመሆኑም ይህ ተራራ የምሥጢራት ተራራ ተብሎ ይጠራል፡፡ ከባሕረ ዮርዳኖስ ቀጥሎ ምሥጢረ መለኮት የተገለጠበት ዐምደ ምሥጢራት የሆነ ተራራ ነው፡፡ ስለዚህ የምሥጢራት መገለጫ ኾኖ ያገለገለ ተራራም ነቢያት ትንቢት ተናግረዋል፡፡ ልበ አምላክ ዳዊት “ደብረ እግዚአብሔር ደብር ጥሉል፤ደብር ርጉዕ ወደብር ጥሉል/የእግዚአብሔር ተራራ (ታቦር) የለመለመ /በምሥጢር/ ነው፤የረጋና የለመለመ /በምሥጢራት መገለጫነት/ ነው”፡፡ በሌላም ቦታ “ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌስሑ፤ወይሴብሑ ለስምከ/ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል፤ስምህንም ያመሰግናሉ” ይላል፡፡ /መዝ 88፣12/
ከአራቱ ዐበይት ነቢያት አንዱ የኾነው ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም “ኑ ወደ እግዚአብሔር ተራራ/ታቦር/ ፣ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፤ በጎዳናውም እንሄዳለን፡፡” /ኢሳ 2፣3/ ከላይ የተጠቀሱት ነቢያት አበው የታቦርን ተራራ “የእግዚአብሔር ተራራ” /ምሥጢራተ እግዚአብሔር የተገለጠበት/ በማለት ሲጠሩት ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ “ቅዱሱ ተራራ” ሲል ይጠራዋል፡፡ 2ጴጥ1÷18 ደብረ ታቦር የሚለው ቃል የተራራውም ኾነ የብርሃነ መለኮት መገለጥ በዓል መጠሪያ ኾኖ ያገለግላል፡፡ በተራራነቱ የታቦር ተራራ ወይም ታቦር የተባለ ተራራ ተብሎ ሲተረጎም በበዓልነቱ ሲጠራ ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮት የተገለጠበት ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ዐበይት/ታላላቅ/ በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡ በዚህች አጭር የአስተምህሮ ጦማር የደብረ ታቦርን በዓል የአከባበር ታሪካዊ አመጣጥና ባሕላዊ አከባበር ሳይኾን በቅዱሱ ተራራ የተገለጡትን ትምህርታተ እግዚአብሔር መጠነኛ ዳሰሳ እናደርጋለን፡፡
ትምህርተ እግዚአብሔር (Apophatic Theology)
“ወተወለጠ ራእዩ በቅድሜሆሙ ወአብርሀ ገጹ ከመ ፀሐይ ወአልባሲሁኒ ኮነ ጸዐዳ ከመ ብርሃን /መልኩም በፊታቸው ተለወጠ ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ኾነ (ሜቴ 17÷2)፡፡” በደብረ ታቦር በጉልህ ከተቀመጡት ምሥጢራት አንዱ የእግዚአብሔር አይገለጤነት ትምህርተ መለኮት (Apophatic Theology) ነው፡፡ ቅዱሳን አበው በእግዚአብሔር የባሕርይ ግብራት ጋር በሚያደርጉት ተዋሕዶ እግዚአብሔርን በተምሳሌት ይገልጡታል፡፡ ምክንያቱም ፍጡሩ አንደበታችን እና ቋንቋችን የተገደበው በተፈጠሩ ነገሮች ላይ ብቻ ነው፡፡ ንግግራችን ከጊዜ እና ከቦታ ውጭ አልፎ መናገር እና መግለጽ ፈጽሞ አይችልም፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ከጊዜና ከቦታ ውጪ ነው፡፡ ዘላለማዊውንና መጠንና ወሰን የሌለውን እግዚአብሔርን በጊዜ የተፈጠረውና በተፈጠረው ዓለም የተወሰነው ሰውና ቋንቋው የነጥብና የፍንጭ ያክል ካልሆነ በስተቀር አከናውኖ ሊጠራውና ሊገልጸው ፈጽሞ አይቻለውም፡፡ እግዚአብሔር እኛ ስለ እሱ /እግዚአብሔር/ ከምንናገረውና ከምናስበው ማንኛውም ነገር በማይነጻጸር ሁኔታ ይበልጣል፡፡ ስለዚህ ስለ እግዚአብሔር የምንናገረው ትምህርተ መለኮታችን በአብዛኛው ስዕላዊ እና ተምሳሌታዊ ነው፡፡ ይህ ስዕላዊና ተምሳሌታዊ አገላለጽም ቢሆን እግዚአብሔርን የፍንጭ ወይም የነጥብ ካልኾነ በቀር ሊገልጸው አይችልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እና ቅዱሳን አበው እግዚአብሔርን ከሚገልጡባቸው ስዕላዊና ተምሳሌታዊ መግለጫዎች መካከል ጨለማና ብርሃን ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ብርሃን ነው ወይም ጨለማ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ ኹለቱም እግዚአብሔርን እንደየአቅማቸው ለማስረዳት ይሞክራሉ እንጂ አንዳቸውም እግዚአብሔርን ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር ብርሃን ነው ሲባል ብርሃን መገለጫው ነው ማለት እንጂ ገልብጠን ብርሃን እግዚአብሔር ነው ብንል የሚያስኬድ አይደለም፡፡
ጨለማ፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ጨለማ የሚለውን ቃል የእግዚአብሔርን አይደረሴነት ለመግለጥ ተጠቅሞበታል፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በሲና በረሃ ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር በተዘጋጀ ጊዜ እግዚአብሔር ወዳለበት ጨለማ እንደገባ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ያስረዳናል ‹‹ሕዝቡም ርቀው ቆሙ፤ ሙሴም እግዚአብሔር ወዳለበት ጨለማው ቀረበ›› (ዘጸ 20÷21)፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊትም ‹‹ወረሰየ ጽልመተ ምስዋሮ /መሰወሪያውን ጨለማ አደረገ›› (መዝ. 17፡11) በማለት የሊቀ ነቢያት ሙሴን ኀይለ ቃል ያጸናዋል፡፡ ኹለቱም በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው የተናገሩት አበው ነቢያት እግዚአብሔር ጨለማ ሳይሆን በጨለማ እንደሚያድር ያረጋግጡልናል፡፡ በጨለማ ያድራል መባሉም አእምሮዋት/ኅሊናት ተመራምረው ሊደርሱበት የማይችሉ ምጡቀ ልቡና፣ረቂቀ ኅሊና መሆኑን ያመለክታል፡፡ ጨለማነቱም ያለው በእግዚአብሔር ዘንድ ሳይሆን በእኛ አእምሮ ውስጥ ነው፡፡ ለምሳሌ የፀሐይን ብርሃን ማየት የተሳነው ዐይነ ስውር ሰው ጨለማው ያለው ከእሱ ነው እንጂ ከፀሐይ እንዳልሆነ ኹሉ ጨለማነቱ ያለው በእግዚአብሔር ዘንድ ሳይሆን በእኛ ውስጥ ነው፡፡ በነቢዩ ሙሴና በልበ አምላክ ክቡር ዳዊት ጎራ ሆነው እግዚአብሔርን በተምሳሌታዊ አገላለጥ ከሚገልጡት ቅዱሳን አበው መካከል ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ አንዱ ነው፡፡
ብርሃን፡ ይህን መንገድ ተከትለው ስለ እግዚአብሔር አይደረሴነት ከሚያስተምሩት ቅዱሳን አበው መካከል ቅ/ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት ይገኝበታል፡፡ እግዚአብሔርን ብርሃን በሚለው ቋንቋ ለመግለጥ መሠረቱ ነባቤ መለኮት ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ጨለማም በእርሱ ዘንድ ጥቂትስ እንኳን የለም›› (1ኛ ዮሐ 1÷5)፡፡ እግዚአብሔር ብርሃን እንደሆነ በይበልጥ የተገለጠው ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ባደረገው ብርሃናዊ አስተርእዮ ነው፡፡ ስለዚህ ብርሃናዊ አስተርእዮ ከጻፉት ሦስቱ ወንጌላውያን አንዱ የሆነው ቅዱስ ማቴዎስ “ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ ፤ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ” በማለት የእግዚአብሔርን ብርሃናዊነት ገልጧል (ማቴ 17÷2)፡፡ ይህ እግዚአብሔርን በብርሃን ወክሎ መግለጥ በብዙ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የሚዘወተር ሲሆን የሊቃውንት ቅዱሳን ፈጣሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነስቶ እስከሚያርግበት ጊዜ ባሉት አርባ ቀናት ውስጥ ካስተማረውና ኪዳን ተብሎ ከሚጠራው ትምህርት ውስጥ “እግዚአብሔር ዘብርሃናት” በሚባለው የጸሎት ክፍል ውስጥ ይህ አገላለጥ ጎልቶ ይታያል፡፡ “ዘመንጦላዕቱ ብርሃን ወቅድመ ገጹ እሳት ወመንበረ ስብሐቲሁ ዘኢይተረጐም ወምዕራፈ ተድላሁ ዘኢይትነገር ዘአስተዳለወ ለቅዱሳን ወበመልበስቱ መዛግብተ ብርሃን / መጋረጃው ብርሃን፣ በፊቱ እሳት የሚቦገቦግ፣ የጌትነቱ መንበር የማይተረጎም፣ ለቅዱሳን ያዘጋጀው የደስታ ማረፊያ የማይነገር፣ መጎናጸፊያው የብርሃን መጎናጸፊያ የሆነ እግዚአብሔር ….”፡፡
ኪዳን በተባለው መጽሐፍም “ፀሐይ ዘኢየዐርብ ወማኅቶት ዘኢይጠፍእ ፀሐይ ዘዘልፈ ያበርህ ዲበ ቅዱሳን/የማይጠልቅ ፀሐይ፣ የማይጠፋ ብርሃን፣ በቅዱሳን ላይ ዘወትር የሚያበራ ፀሐይ” ሲል እግዚአብሔርን ተምሳሌታዊ በሆነ አገላለፅ ይገልጠዋል፡፡ በደብረ ታቦር /በምሥጢሩ ተራራ/ የታየው ብርሃን ግን በዕለተ እሑድ የተፈጠረ ብርሃን አይደለም፡፡ ይህ ብርሃን መለኮታዊ ብርሃን፣ ያልተፈጠረና ለሌሎች ብርሃናት ምንጭ የሆነ ብርሃን ነው፡፡ ይህ ብርሃን ኖኅና ሙሴ ሲወለዱ እንደከበባቸው፣ ሙሴ ከ40 ቀን የደብረ ሲና ቆይታ በኋላ ኹለቱን ጽላት ተቀብሎ ሲመጣ እስራኤላውያን በሙሴ ላይ ያለውን ብርሃን ማየት ተስኗቸው ‹‹ሙሴ ተገልበብ ለነ/ ሙሴ ሆይ የፊትህን ብርሃን ማየት ተስኖናልና ፊትህን ተሸፈንልን” (ዘፀ. 34፡29-30) እንዳሉት ቅዱሳን ሲበቁ እንደሚጎናጸፉት ያለ ብርሃን አይደለም:: ይህ ብርሃን መለኮታዊ በመሆኑና ሌላ መግለጫ ቃል በመጥፋቱ ብርሃን በሚለው ተምሳሌት ተጠራ እንጂ ከብርሃን በላይ የሆነ ነው፡፡ የሰው ዐይን ፍጡሩን ብርሃን እንጂ ያልተፈጠረውን ብርሃን መመልከት አይችልም፡፡ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የተሟሸ ዐይን መለኮታዊውን ብርሃን በመለኮትነቱ ልክ ማየት ፈጽሞ የማይቻል ቢሆንም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የተወሰነለትን ያህል መመልከት መቻሉን በደብረ ታቦር አየን፡፡
“ወእም ከመ ጥቀ ታሤንዩ ግብረ ወትኔጽርዎ ይከውን ለክሙ ከመ ማኅቶት እንተ ታበርህ ውስተ መካነ ጽልመት እስከ ታበርህ ለክሙ ዕለት ወይሠርቅ ለክሙ ቤዝ ውስተ ልብክሙ ዘያበርህ / በአንብቦ መጻሕፍት ጽሙዳን ብትሆኑ ፀሐይ እስኪያበራላችሁ ድረስ ያጥቢያ ኮከብ እስኪወጣላችሁ/ አእምሮ መንፈሳዊ በልቡናችሁ እስኪሳልባችሁ/ ድረስ በጨለማ ቦታ እንደሚያበራ ፋና ይሆንላችኋል” (2ጴጥ 1÷19) ቅዱስ ጴጥሮስ በዚህ አገላለጹ ከሰው የሚገኘውን ዕውቀት በፋና፣ ከእግዚአብሔር የሚገኘውን ዕውቀት ደግሞ በፀሐይ መስሎ ተናግሯል፡፡ ‹‹ሃይማኖት እንተ ትጠረይ እም ተምህሮ ኢታግዕዞ ለሰብእ እምኑፋቄ ወእምትሕዝብት / ከመማር የምትገኝ ሃይማኖት ሰውን ከጥርጣሬ ነጻ አታወጣውም›› እንዳለ መጸሐፍ በምርምርና በአስተውሎት /Knowledge of Empiricism and Reason/ ከሚገኝ የዕውቀት ብርሃን ይልቅ እግዚአብሔር በልባችን የሚያትምልን የዕውቀት ብርሃን /Knowledge of Revelation/ እንደ ፀሐይ ያበራል፡፡ (መዝ118÷105)፤2ቆሮ 4÷6)፡፡ ይህ እግዚአብሔር ጸጋውን አሳድሮ ዐይነ ሥጋችንንና ዐይነ ልቡናችንን የሚያበራው ብርሃን ያልተፈጠረውን መለኮታዊውን ብርሃን ለማየት ያስችላል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ኹለንተናቸው የበራላቸው ኹለቱ ነቢያት አበው /ሙሴና ኤልያስ/ እና ሦስቱ የምሥጢር ሐዋርያት /ቅ/ጴጥሮስ፣ቅ/ዮሐንስና ቅ/ያዕቆብ/ መለኮታዊውን ብርሃን እንደ ዐቅማቸው ለማየት ደረሱ፡፡
ወንጌላውያኑ መለኮታዊውን ብርሃን የሚገልጡበት ነገር ቢያጡ በተፈጠረው ብርሃን መስለው ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ ብለው ተናገሩ፡፡ ቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት የተገለጠውን መለኮታዊ ብርሃን አይቶ መቋቋም የሚችል ዐይን ስላልነበራቸው “ወወድቁ በገጾሙ ዲበ ምድር /በግንባራቸው ወደ ምድር ወደቁ፡፡” ይህን አይደረሴ መለኮታዊ ብርሃን የትምህርተ መለኮት ሊቃውንት ከጨለማ ጋር አብረው በማጣመር “Dazzling Darkness, Radiance of Divine Darkness, Blinding Light” ብለው ይጠሩታል፡፡ ከዚህ የማይገለጥ አንጸባራቂ መለኮታዊ ብርሃን የተነሳ ቅዱስ ጴጥሮስ የሚናገረው ነገር እንዳጣ፣ያየውንም ነገር መሰየሚያ ቃል እንዳጣ፡ “ወኢየአምር ዘይብል / የሚለውን /የሚናገረውን አያውቅም/” በማለት ኹለቱ ወንጌላውያን አስቀምጠውታል (ማር 9÷6 ፤ሉቃ 9÷33)፡፡ ለዚህ ብርሃነ መለኮት መገለጥና በተገለጠው ብርሃነ መለኮት ፊት ለመቆም አለመቻልን ነበር ባለ ቅኔው ሐዲስ ኪዳናትና ልጃቸው እሙሐይ ገላነሽ ሙሴና ኤልያስ መለኮት ፈረስን መግታት ተሳናቸው ያሉት፡፡
በደብረ ታቦር የተገለጠው ብርሃን ያልተፈጠረ መለኮታዊ ብርሃን ነው፡፡ ፍጡሩን ብርሃንና መለኮታዊውን ብርሃን ስም እንጅ ግብርና ባሕርይ ፈጽሞ አያገናኛቸውም፡፡ መለኮታዊው ብርሃን ዘላለማዊ ብርሃን ነው፡፡ “ብርሃን ዘእምቅድም / ቅድመ ዓለም የነበረ ብርሃን /ባሕርይ/” እንዲል (መጽሐፈ ኪዳን)፡፡ ፍጡሩን፣ ለሰው ልጆች በሥጦታ /በጸጋ/ የሚታደለውን ብርሃን ደግሞ መጻሕፍት በተለያየ አገላለጽ ይገልጡታል፡፡ “አምላከ ብርሃን፣ ወሀቤ ብርሃን / ረቂቁን ብርሃን የሰጠ፣ ግዙፉን ብርሃን የፈጠረ” በማለት ግዙፋኑ ብርሃናት ፀሐይ፣ጨረቃ፣ከዋክብትና ከእነርሱ የሚመነጨው ረቂቁ ብርሃን ለሰው ልጆች በሥጦታ የተበረከተ እንደሆነ መጻሕፍት ይገልጣሉ (መጽሐፈ ኪዳን)፡፡ ከዚህ ግዙፍ ብርሃን ባሻገር ግን በተጋድሎ ብዛት ቅዱሳን የሚታደሉት ረቂቅ ብረሃን አለ፡፡ ይህን ብርሃን “ብርሃን ዘኢይትረከብ / ያለ በጎ ሥራ የማይገኝ ብርሃን” ሲል ይገልጠዋል (መጽ.ኪዳን)፡፡
የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ለማየት የሚያደርሰውን ብርሃን ለማግኘት ተስፋ አድርጎ ይኖራል፡፡ ይህን አስመልክቶ “ወብርሃነ ለነ ዘኢይጠፍእ አሰፎከነ / የማይጠፋ ብርሃንን ለእኛ ተስፋ አስደረግከን” (መጽሐፈ ኪዳን)፡፡ ይህ ብርሃን ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለመላእክትም ጭምር በጥንተ ተፈጥሮ ዕውቀት ሆኗቸው መለኮታዊውን ብርሃን እንዲረዱ አድርጓቸዋል፡፡ “ዝንቱ ብርሃን ኮኖሙ ጥበበ ወአእምሮ” እንዲል መጽሐፍ፡፡ ይህን ፍጡር ብርሃን ዕውቀት አድርገው መላእክት መለኮታዊውን ብርሃን እንደጎበኙት መጽሐፈ ኪዳን “ዘያፈትዎሙ ለመላእክት የሐውጽዎ ለዘእምቅድመ ዓለም ብርሃን / ዓለም ሳይፈጠር የነበረውን ብርሃን ያዩት ዘንድ መላእክትን ደስ የሚያሰኛቸው” በማለት ያስረዳል፡፡
ትምህርተ ሥላሴ /Doctrine of Holy Trinity/
በምሥጢራዊው ቅዱስ ተራራ በታቦር ከምናገኛቸው መሠረታዊ ትምህርቶች መካከል ትምህርተ ሥላሴ ዋነኛው ነው፡፡ የምሥጢሩ ተራራ ታቦር በእግዚአብሔር አይገለጤነት ትምህርተ እግዚአብሔር (Apophatic Theolgy) ጀምሮ የእግዚአብሔርን የባሕርይ አንድነትና የባሕርዩ ግርማ መገለጫ ከሆኑት መካከል ብርሃን አንዱ መሆኑን ካስረዳ በኋላ ይህ በባሕርይ አንድ የሆነ እግዚአብሔር አካል ስንት እንደሆነ ወደ ማመላከት ያመራል፡፡ ይህ ትምህርት ወደ ጥልቁና አይመረመሬው ትምህርተ ሥላሴ ይወስደናል፡፡ በደብረ ታቦር ጌታችንና አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮታዊ ግርማ የመገለጡ ዋነኛ ምክንያት በብሉይ ኪዳን ስለ እግዚአብሔር አንድ ገጽነት ይታመን የነበረውን የስህተት አስተምህሮ አርሞ እግዚአብሔር በአካል እና በገጽ ሦስት እንደሆነ ለምዕመናነ እግዚአብሔር በሰፊው ለማስረዳት ነው፡፡ ይህ የምሥጢረ ሥላሴ አስተምህሮ በብሉይ ኪዳን በስውር ሁኔታ በብዙ ስፍራዎች ላይ የተገለጠ ሲሆን በአዲስ ኪዳን ግን በአገላለጥ ብቻ ሳይሆን በእይታም በሚረዳ መልኩ ተገልጧል፡፡ ከእነዚህ አስተርእዮታት (መገለጦች) መካከል ከባሕረ ዮርዳኖስ ቀጥሎ ደብረ ታቦር አንዱ የምሥጢረ ሥላሴ የምሥጢር ቁልፍ ነው፡፡
በባሕረ ዮርዳኖስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲጠመቅ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት ባለመገለጥ ቁልፍ ተዘግቶ የኖረው ምሥጢረ ሥላሴ “ተርህወ ሰማይ/ ሰማይ ተከፈተ” በሚል አንቀጽ የመገለጡን ምስራች እንደ ሰማን ምሥጢረ ሥላሴ በአንድ መገለጥ የሚረዳ አይደለምና በታላቁ የምሥጢራት ተራራ በደብረ ታቦር ይህ የሰማይ መከፈት ምሥጢር ተደገመ፡፡ በኹለቱ ታላላቅ የምሥጢር መካናት እግዚአብሔር አንድነት ሦስትነቱን በምንረዳው ልክና መጠን ገለጠልን፡፡ በታቦር ተራራ ብርሃነ መለኮቱ ለተገለጠ ለኢየሱስ ክርስቶስ “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ወሎቱ ስምዕዎ / የምወደው ልጄ ይህ ነው እሱንም ስሙት” የሚል መለኮታዊ ቃል ከባሕርይ አባቱ ከአብ ዘንድ ተሰማ፡፡ እጅግ በጣም ታላቅና ድንቅ ድምፅ ነው! ኢየሱስ ክርስቶስ “እኔ እና አብ አንድ ነን፤ እኔን ያየ አብን አየ፤ እግዲህ ሂዱና በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ እያጠመቃችኋቸው አሕዛብን ኹሉ አስተምሩ” (ዮሐ 10፣30፣ ዮሐ 14፣9፣ ማቴ 28፣19) እያለ ስለ እግዚአብሔር የባሕርይ አንድነትና የአካል ሦስትነት የሚያስተምራችሁን ትምህርተ እግዚአብሔር ስሙት፣ተቀበሉት፣እመኑበት በማለት እግዚአብሔር አብ የግርማው መገለጫ በሆነው በደመናው ውስጥ ሆኖ አዘዘን፡፡ በመሆኑም የታቦር ተራራ የምጢራት ኹሉ መሠረት የሆነው ምሥጢረ ሥላሴ ለኹለተኛ ጊዜ በጉልህ የተገለጠበት የምሥጢራተ መለኮት ዐደባባይ ነው፡፡
ትምህርተ ተዋሕዶ/አንድ አካል አንድ ባሕርይ/
በአንድ ብርሃነ መለኮት መገለጥ የሥላሴን የባሕርይ አንድነት፣አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ብሎ በመግለጥ የሥላሴን የአካል ሦስትነት ከተረዳን በኋላ የወልድን በተዋሕዶ ሰው መሆን የምንረዳበት ትምህርት በምሥጢሩ ተራራ በታቦር የተገለጠው ትምህርተ እግዚአብሔር ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስቱ የምሥጢር ሐዋርያት ጋር ወደ ረጅም ተራራ ወጥቷል፡፡ ከሐዋርያቱ ጋርም ቃል በቃል በአካል ተነጋግሯል፡፡ በእነዚህ ድርጊቶች የኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም ሰውነት በፍጽምና እንረዳለን፡፡ ይህ ፍጹም ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን በመግለጥ ነቢያትንና ሐዋርያትን በግርማ መለኮቱ ፍጹም ማስፈራቱም፣ “ይህ የባሕርይ ልጄ ነው” የሚል መለኮታዊ ድምጽ ከአብ መሰማቱ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም አምላክነት በተገለጠ ሁኔታ ያስረዳል፡፡ አንዱ አካል በአንድ ጊዜ በተዋሕዶ ሰውም አምላክም መሆኑን በምሥጢሩ ተራራ በታቦር ተረድተናል፡፡ በአዳም ፍዳ መነሻነትና በግሉ በሚሰራው ኀጢአት ምክንያት የቀደመ የገዢነት፣ የተፈሪነት ክብርን አጥቶ በፍጥረታት ኹሉ ሲረገጥና ሲቀጠቀጥ የኖረ ሥጋ /ባሕርየ ሰብእ/ በተዋሕዶ የመለኮት ገንዘብ ኹሉ ገንዘቡ ኾኖለት በመለኮታዊ ግርማው በቅዱሱ ተራራ የነበሩትን ቅዱሳን ፍጹም አስደነገጠ፤ በብርሃኑ ዓለምን አበራ፤ የአብ የባሕርይ ልጅ ለመባል በቃ፤ ሙታንን በሥልጣኑ ከያሉበት ማስነሳትና ከሕያዋን ጋር ማነጋገር ቻለ፤ጌታ፣ እግዚአብሔር፣አምላክ ለመኾን በቃ፡፡ ረቂቁ መለኮትም ከሥጋ ጋር ባደረገው ፍጹም ተዋሕዶ የሥጋን ገንዘብ ኹሉ ገንዘቡ በማድረጉ ወደ ምሥጢሩ ተራራ ሲወጣ ታየ፤ ተዳሰሰ፤ ወጣ፤ ተለወጠ፤ ወዘተ የሚሉ ሰውኛ ግሶች ተነገሩለት፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት
ዓለም የተፈጠረው በእግዚአብሔር ቃል /ወልድ እንደሆነ የሚድነውና የሚጠፋው በእግዚአብሔር ቃል /ወልድ/ ነው፡፡ “ዘየአምን በወልድ ቦ ሕይወት ዘለዓለም / በወልድ ያመነ የዘላለም ሕይወት አለው” (1ኛ ዮሐ. 5፡12) እንዳለ ወንጌላዊው ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ነው ብለው ካላመኑ በስተቀር ድኅነት ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ አረጋዊው ስምዖን “እነሆ ይህ ሕጻን ከእስራኤል መካከል ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሳታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ይሆን ዘንድ የተሠየመ ነው” (ሉቃ 2÷34) እንዳለ ለዓለም ድኅነትም ሆነ ሞት ምክንያቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ዓለም ለምንፍቅናዋና ውድቀቷ መሠረት የምታደርገው የኢየሱስ ክርስቶስን እግዚአብሔርነት መካድ ነው፡፡ በምሥጢሩ ተራራ በታቦር ግን ለዓለም መውደቅና መነሳት ምልክት የኾነው የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትን ማመን ለዓለም በግልጥና በሚረዳ ቦታ፣በሚረዳ ቋንቋ ተገልጧል፡፡ “የምወደው ልጄ ይህ ነው” ከማለት በላይ ለኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት ሌላ ምስክርነት አያሻም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ አይደለም ብሎ መካድ እግዚአብሔር አብ የባሕርይ አምላክ አይደለም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ፍጡር ፍጡርን ፣ፈጣሪ ፈጣሪን በባሕርያቸው ይወልዳሉ እንጅ ፍጡር ከፈጣሪ በባሕርይ ሊወለድ አይቻለውም፡፡ ወይም ፈጣሪ ፍጡርን በባሕርይው ወለደ ማለት ለባሕርዩ አይስማማውም፡፡
በሌላ አገላለጽ የፍጡር የባሕርይ ልጅ ፍጡር፣ የፈጣሪ የባሕርይ ልጅ ፈጣሪ ነው፡፡ ታዲያ ራሱ አብ ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ ልጄ ነውና እሱ የሚላችሁን ኹሉ አምናችሁ ተቀበሉት ብሎ ካዘዘን፣ እንዲሁም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ “እምቅድመ ይትፈጠር አብርሃም ሀሎኩ አነ / አብርሃም ሳይፈጠር በቅድምና ነበርሁ” (ዮሐ. 8፡58) እያለ ዘላለማዊነቱን የሚነግረንን ኢየሱስ ክርስቶስን እግዚአብሔርነቱን አለመቀበልና በእግዚአብሔርነቱ አለማመን የአብን ቃል መካድና የአብንም እግዚአብሔርነት ፈጽሞ መካድ አይደለምን?! ሊቃውንት አባቶቻችን “ወልድ ሲነካ አብ ይነካል” ብለው እንዳስቀመጡት በኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት አለማመንና አለመታመን በኢየሱስ ክርስቶስ ተጠግቶ የእግዚአብሔር አብንም እግዚአብሔርነት ፍጹም መካድ ነው፡፡ ይህ ድርጊት ደግሞ ወደ እግዚአብሔር የለሽነት ጥልቅ አዘቅት የሚከት ወደር የለሽ ክህደት ነው፡፡ በምሥጢሩ ተራራ ግን የኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት በግልጥ ቀርቧል፡፡ ብርሃነ መለኮቱ ስለታየበት፣ምሥጢረ ሥላሴ ስለተገለጠበት፣የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ስለተነገረበት ከዓለም ተራራዎች ኹሉ ለይቶ ቅዱስ /ልዩ/ በማለት በሚጠራው በቅዱሱ ተራራ በታቦር ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በዐይኑ የተመለከተውን፣በልቡናው ያስተዋለውን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርነት ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር እንዳገኘው እንዲህ በማለት መስክሮልናል፡፡
“እስመ ኢኮነ መሐድምተ ጥበብ ዘተሎነ ወአመርናክሙ ቦቱ ኀይሎ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወምጽአቶ ወሀልዎቶ…. /ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ዓለም መኖሩን፣አምጻኤ አለማትነቱን፣ በሥጋ መምጣቱን ስናስተምራችሁ የተከተልነው የፍልስፍና ተረት አይደለምና፣ የእርሱን ገናናነት እኛ ራሳችን አይተን ነው እንጅ ከገናናው ክብር ‘በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው’ የሚል ያ ደምፅ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ገንዘብ አድርጓልና፡፡ ይህንም ቃል እኛ በተቀደሰው ተራራ አብረነው ሳለን ከሰማይ እንደወረደለት ሰምተነዋል›› (2ጴጥ 1÷16-18)
ነገረ ቤተክርስቲያን
በምሥጢሩ ተራራ በታቦር ከተገለጡት ምሥጢራት ነገረ ቤተ ክርስቲያን ይገኝበታል፡፡ በደብረ ታቦር በሕይወተ ሥጋና በሕይወተ ነፍስ ያሉ ምእመናን በአንድ ላይ ተገኝተው ምሥጢረ መለኮትን ተመልክተዋል፡፡ አንዱ ለአንድ ሲጸልይ ተስተውለዋል፡፡ አንድነትን፣ አብሮ መኖርን ሲመኙ ታይተዋል፡፡ ይህ የቤተክርስቲያን ጠባይ ነው፡፡ በደብረ ታቦር የተገለጠው ምሥጢር ዛሬም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እየተገለጠ ይኖራል፡፡ ቤተክርስቲያን የኹለት ዓለማት ምእመናን አንድነት ናት፡፡ ምሥጢረ መለኮት የሚገለጥባት፣ አንዱ ለሌላው የሚኖርባት፣ አንዱ ለሌላው የሚጸልይባት፣ በዐፀደ ሥጋና በዐፀደ ነፍስ ያሉ ምእመናንና የመላእክት ተዋሕዶ /አንድነት/፣ የምሕረት ዐደባባይ ናት፡፡
ትምህርተ ትንሣኤ ምውታን
ነገረ ትንሣኤ ምውታን ከጥንት ጀምሮ ለብዙ ሰዎች የክህደታቸው መነሻ ሆኖ የቆየ ዐቢይ ምሥጢር ነው፡፡በክርስቶስ ዘመነ ሥጋዌ ወቅት ሰዱቃውያን የሚባሉ ቡድኖች ሰው ከሞተ በኋላ ነፍሱና ሥጋው ተዋሕደው ይነሳል የሚለውን የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስን አስተምህሮ አምርረው ይቃወሙ ነበር፡፡ኢየሱስ ክርስቶስም ሰው ዘላለማዊ ፍጡር እንደሆነና ከሞት በኋላ መልአካዊ ህላዌ እንደሚኖረው ገሥጾ አስተምሯቸዋል፡፡በዘመነ ሐዋርያት ጊዜም ብዙ ተረፈ ሰዱቃውያንና አሕዛባውያን ተነስተው ስለ ትንሣኤ ምውታን በጥልቀት ያስተምር የነበረውን ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስን ተቃውመውታል፡፡ቅዱስ ጳውሎስም “ሀሎኑ ዘይብል እፎኑ ይትነሥኡ ምውታን ወበአይ ነፍስቶሙ የሐይዉ ኦ አብድ አንተ ዘትዘርእ አኮኑ ዝንቱ ነፍስት ዘይትወለድ ዘትዘርእ ዳእሙ ሕጠተ እመኒ ዘሥርናይ ወእመኒ ዘባዕድ ወእግዚአብሔር ይሁቦ ነፍስተ ዘከመ ፈቀደ/ ሙታን እንዴት ይነሳሉ? በየትኛው ሰውነታቸውስ ይነሳሉ? የሚል አለን አንተ ሰነፍ አንተ የምትዘራው ቅንጣት የሥንዴም ቢሆን ሌላም ቢሆን እግዚአብሔር እንደወደደ አካልን ይሰጠዋል፡፡” (1ቆሮ15፡35-38)
ዛሬም በዘመናችን ለሚኖሩ ለብዙ ከሃድያን ፈላስፎችና ባለ ሳይንሶች/ሳይንቲስቶች የክህደታቸው ዋና መነሻ ትንሣኤ ምውታንን መካድ ነው፡፡ ከሞት በኋላ ስላለው ዘላለማዊ ሕይወት መስማት ፈጽመው አይፈልጉም፡፡ የምሥጢረ ትንሣኤ አስተምህሮ ሰነፎች የፈጠሩት ተረት ተረት እንደሆነ አድርገውም ይገምታሉ፡፡በቅዱሱ መጽሐፍ እንደተጻፈልን ግን በመዝገበ ምሥጢራቱ በታቦር ተራራ ትንሣኤ ምውታን በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባር ተገልጧል፡፡ ከሞተ አንድ ሽህ አምስት መቶ ዓመት ገደማ የሚሆነው ሊቀ ነቢያት ሙሴ በቅዱሱ ተራራ በታቦር በሕይወተ ሥጋ ተገልጦ ሕይወትን ከሰጠው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በግልጥ ተነጋግሯል፡፡ በዚህ የምሥጢራት ተራራ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ማዕከል የሆነው የምሥጢረ ምውታን አስተምህሮ በቃል ብቻ ሳይወሰን በተግባር ተገለጠ፡፡ ትምህርተ ትንሣኤ ምውታን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አምስቱ አእማደ ምሥጢራት ብላ ከምታስተምረው የሃይማኖቷ መሠረት ከቆመባቸው ምሰሶዎች አንዱ ሲሆን መነሻዋም መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ የነገረ ተዋሕዶው ሊቅ ቅዱስ ቄርሎስ የትስብእት ምሳሌ አድርጎ በተረጎመው ዕፀ ጳጦስ ላይ አድሮ በጊዜያዊው ሥጋዊ ሞት ከሥጋዊው ዓለም ለተለዩት አብርሃም፣ይስሐቅና ያዕቆብ አምላክ እንደሆነ የነገረው እግዚአብሔር ራሱን ሙሴን ነፍስና ሥጋውን አዋሕዶ ከመቃብር አስነስቶ በቃል ያስተማረውን በተግባር አሳይቶታል፡፡
መቼም ቢሆን አንድን ነገር/ድርጊት/ በተግባር ከማሳየት የሚበልጥ ነገሩን/ድርጊቱን/ የሚያስረዳ ስልት አይገኝም፡፡ የታቦርን ተራራ የትምህርተ ትንሣኤ ምውታን ማሳያ ቤተ ሙከራ አድርጎ መመልከት ይቻላል፡፡ በብሉይና4 በአዲስ ኪዳን ሲነገርና ሲተረጎም ላለውና ለነበረው ምሥጢረ ትንሣኤ ምውታን ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ ከመቃብር፣ነቢዩ ኤልያስ ደግሞ ከተሰወረበት መምጣታቸውና በደብረ ታቦር ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መነጋገራቸው የትንሣኤ ምውታን ማረጋገጫ ማኅተም ነው፡፡ አምላከ አማልክት ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዱቃውያንን “አነ ውእቱ እግዚአብሔር አምላከ አብርሃም ወአምላከ ይስሐቅ ወአምላከ ያዕቆብ ኢኮነኬ አምላከ ምውታን አላ አምላከ ሕያዋን ውእቱ/ እኔ እግዚአብሔር የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅም አምላክ፣ የያዕቆብም አምላክ ነኝ፤ እንግዲህ የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም” (ማቴ. 22፡32) በማለት ስለ ትንሣኤ ምውታን በጎላ በተረዳ መልኩ አስተምሯቸዋል፡፡
በዮሐንስ ወንጌልም “በመቃብር ያሉ ቃሉን የሚሰሙባት ጊዜ ትመጣለችና ስለዚህ አታድንቁ፡፡ መልካም የሰሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሰሩም ለፍርድ ትንሣኤ ይነሳሉ በማለት ስለ ምሥጢረ ትንሣኤ መውታን አስተምህሮ አስረድቷል (ዮሐ 5፡28-29)፡፡” በአጠቃላይ ሞት የሥጋ፣የኅሊናና የነፍስ ሞት ተብሎ የሚመደብ ሲሆን የሥጋ ሞት የነፍስ ከሥጋ ጊዜያዊ መለየት ሆኖ ከጊዜያዊነት ወደ ዘላለማዊነት የምንሸጋገርበት መሻጋገሪያ ድልድይ፣ከምድራዊነት ወደ ሰማያዊነት ከፍ የምንልበት መወጣጫ መሰላል፣ከእንስሳዊነት ግብር ወደ መላእክታዊነት ግብር የምናድግበት፣ለዘላለማዊነት የምንጸነስበት ማኅፀን ነው፡፡ በአንድ በአዳም በደል ኀጢአትና ሞት ወደ ዓለም እንደገቡ በአንድ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ትንሣኤና ሕይወት ወደ ዓለም ገብተዋል፡፡(ሮሜ 5፡12-21፣ 1ቆረ15፡51-56፣ ሕዝ 37፣1-14)
ይህ ታላቁ የምሥጢረ ትንሣኤ አስተምህሮ በታላቁ የታቦር ተራራ ለዓለም ኹሉ ተገልጧል፡፡ ስለ ምሥጢረ ትንሣኤ ምውታን ቅዱሳት መጻሕፍት የተናገሩትን ምስክርነት ስለማይቀበሉ ሰነፎች ሰዎች የትምህርተ እግዚአብሔር ሊቁ አባታችን አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የተናገረውን ግሣጼያዊ ትምህርት እንደወረደ በማቅረብ የያዝነውን ንኡስ ርእሰ ጉዳይ ለማጠቃለል እንወዳለን፡፡ “እንግዲህስ ስለ ሙታን መነሣት የሚናገሩ የመጻሕፍት ምስክርነት ይበቃናል፡፡ በእነዚህ ጥቂት የመለኮት ቃሎች ካላመኑ ከዚህ የበዛም ብንናገር አያምኑም፡፡ መስማት ለተሳነው ሰው የመለከት ድምፅ በጆሮዎቹ አይገባም፤ ማየት የተሳነውም የፀሐይ ብርሃን አይታጠውም፤ ሰነፍም ስንፍናው ጥበብ ይመስለዋል፤ የጥበበኞችንም ነገር እንደ ጥራጊ ይጥለዋል፡፡ የምድርን አፈር በውሃ ብታጥባት በጭቃ ላይ ጭቃን ትጨምራለህ፤ማንጻትም አትችልም፤ሰነፍንም በጥበብ ቃል ብትገሥጸው በስንፍናው ላይ ስንፍናን ይጨምራል፤ዐዋቂም ልታደርገው አትችልም” (መጽሐፈ ምሥጢር ገጽ 358-359)፡፡
ስብሃት ለአብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡ ይቆየን፡፡