አርዮስን ለማውገዝ በጉባዔ ኒቅያ የተሰበሰቡ ቅዱሳን አባቶች (ሠለስቱ ምዕት) ‹‹ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባዔ ዘሐዋርያት/ከሁሉ በላይ በምትሆን የሐዋርያት ጉባዔ በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን›› በማለት ቤተክርስቲያን አንዲት (አሐቲ) መሆንዋን ደንግገዋል፡፡ ለቤተክርስቲያናችንም ይህ የቤተክርስቲያን አንድነትን የሚያስረግጠውን ድንጋጌ የሃይማኖት ጸሎት (ጸሎተ ሃይማኖት) ዋና መመሪያዋ ነው፡፡ ቅድስት ቤተክርስተያን በቅዳሴዋም ‹‹ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተክርስቲያን አሐቲ ቅድስት ጉባዔ እንተ ሐዋርያት ርትዕት በኀበ እግዚአብሔር/በእግዚአብሔር ፊት የጸናች ስለምትሆን የሐዋርያት ጉባዔ አንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ጸልዩ›› እያለች ታውጃለች፡፡ በእነዚህና መሰል ጸሎቶች የቤተክርስቲያንን አንድ (አሐቲ) መሆን ስትመሰክር ትኖራለች፡፡ በዚህ የአስተምህሮ ጦማር ቤተክርስቲያን አንዲት ናት ሲባል የአንድነቷ መሠረትና መገለጫዎች ምን እንደሆኑ በአጭሩ እናቀርባለን፡፡
ቤተክርስቲያን መሪዋ አንድ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
የቤተክርስቲያን መሪዋ አንድ ነው፡፡ እርሱም መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስም ተጠሪነቱ ለአንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ በአንዱ መንፈስ ቅዱስ የምትመራ አንዲት ቤተክርስተያን እንጂ ከአንድ በላይ ቤተክርስቲያን የለችም፡፡ ያችውም ከቅዱሳን ሐዋርያት የተማረችውን ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ከሐሰት ትምህርትና ከመናፍቃን ቅሰጣ በመለየት በምድር ያለች የሰማያዊት ኢየሩሳሌም አምሳል የሆነች የክርስቶስ ቤተክርስቲያን፣ በቀጥተኛነቷና ክህደት ባለመቀላቀሏ ኦርቶዶክሳዊት የምትባል፣ በጌታችን ፍጹም አምላክነትና ፍጹም ሰውነት ተዋህዶ በማመኗ ደግሞ ተዋህዶ የምትባል ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመሠረተልን አንዲት ቤተክርስቲያንን ነው፡፡ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ቤተክርስቲያን አልመሠረተም፡፡ እንድንመሠረትም አላስተማረንም፡፡ ከዘመናት በኋላ ቤተክርስቲያን ተከፋፍላ እውነት ያልተዋጠላቸው ወገኖች ራሳቸውን እየለዪ የራሳቸውን ‘ቤተክርስቲያን’ በየዘመናቱ ቢመሠርቱም እውነተኛዋ ቤተክርስቲያን ግን አንዲት ናት፡፡ ስትመሠረትም፣ ከተመሠረተችም በኋላ፣ ዛሬም፣ እስከዓለም ፍጻሜም አንዲት ሆና ትኖራለች፡፡ በየዘመናቱ የሚነሱ ደገኛ አገልጋዮችም በመንፈስ ቅዱስ የተገለጠላቸውን እውነት እየመሰከሩ በዚች አሐቲ ቤተክርስቲያንም በመንፈስ ቅዱስ የሚከናወኑትን ምስጢራት ተካፍይ በመሆን በክርስትናቸው ጸንተው ለክብር ይበቃሉ፡፡
የቤተክርስቲያን ራሷ እና መሠረቷ አንዱ ክርስቶስ ነው፡፡
ክርስቶስ የቤተክርስቲያን ራስ ነው፡፡ እርሱ የቤተክርስቲያን መሠረትም ነው (ማቴ 16፡16)፡፡ በክቡር ደሙ የዋጃትም እርሱ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር ወልድ ሰው በመሆኑ ከሰው ባህርይ ጋር በተዋሕዶ አንድ ሆኖ የመሠረታት ናት፡፡ ክርስቶስ ትናንት ዛሬና ነገ እስከ ዘለዓለም ድረሰ ያው ነውና የመሠረታት ቤተክርስቲያንም አንዲት ሆና ትኖራለች፡፡ ”እኔ የወይን ግንድ ነኝ፣ እናንተም ቅርጫፎች ናችሁ’ እንዳለው ሁላችን በአንዱ ግንድ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተመሠረትን ቅርጫፎች ነን፡፡ ቤተክርስቲያንም በዚህ አንድ ግንድ ላይ የተመሠረቱ ክርስቲያኖች ኅብረት ስለሆነች አንዲት ናት፡፡ በአንድ ግንድ ላይ የተመሠረትን ልንለያይና ልንከፋፈል አይገባም፡፡ ‹‹ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (1ኛ ቆሮ 3 : 11)›› እንደተባለው አሐቲ ቤተክርስቲያን በዚህ መሠረት ላይ የተመሠረተች ስለሆነች ሌላ አዲስ መሠረት ወይም እንደ አዲስ መመሥረት አያስፈልጋትም፡፡ አንዳንዶች ባለማወቅ አንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ሲተክሉ ራሳቸውን ‹‹መሥራች›› ብለው ይጠራሉ፡፡ ይህ አባባል ከምድራዊ ሕግ አሰራር የተቀዳ፣ በአብዛኛውም ቤተክርስቲያንን ለግል ጥቅምና ዝና መጠቀሚያነት የሚያስቡ የብኩን ትውልድ አካላት የሚጠቀሙበት ነው፡፡ የአሐቲ ቤተክርስቲያን መሥራች ራሱ ክርስቶስ ስለሆነ ይህ አባባል ለስሕተት ይዳርጋል፡፡
የቤተክርስቲያን ዓላማዋ አንድ ነው፡፡
የአሐቲ ቤተክርስቲያን ዓላማዋ አንድ ብቻ ነው፡፡ እርሱም ለሰው ልጅ ሁሉ ቅዱስ ወንጌልን በማዳረስ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምኖ፣ በስሙም ተጠምቆ፣ ምግባር ትሩፋትን ሠርቶ የእግዚአብሔርን መንግስት እንዲወርስ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ የተለየ ዓላማ ያላት ቤተክርስቲያን የለችም፡፡ ከዚህ የተለየ ምድራዊ ዓላማ ይዘው በቤተክርስቲያን ስም የሚጠሩ ስብስቦች ሐሰተኛ እንጂ እውተኛ፣ ምድራዊ እንጂ ሰማያዊ ቤተክርስቲያን ሊባሉ አይችሉም፡፡ እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ተቋም ስለሆነች ዓላማዋም ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን አንዳንድ ምድራዊ ዓላማ ያላቸው ‘አገልጋዮች’ በቤተክርስቲያን ቢኖሩም የቤተክርስቲያንን ዓላማ ግን ምድራዊ አያደርጉትም፡፡ በምድር ያለችው ቤተክርስቲያን ምሳሌ የሆነቻት ሰማያዊት ኢየሩሳሌምም አንዲት ናት፡፡ በምድር ባለችው አንዲት ቤተክርስቲያን የጸኑት ክርስቲያኖች እንደሚሰበሰቡ ሁሉ ነጻ በምታወጣ በኢየሩሳሌም ሰማያዊትም የጸደቁት፣ በጌታ ቀኝ የሚቆሙት ይሰበሰባሉ፡፡
ቤተክስቲያን የአንድነት ጉባዔ ናት፡፡
ቤተክርስቲያን በምድር ያሉ ክርስቲያኖች፣ በሰማይ በአፀደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን፣ እንዲሁም ቅዱሳን መላእክት በአንድነት ለምስጋና የሚተጉባት የሰማይ ደጅ ናት (ዘፍጥረት 28፡17)፡፡ እነዚህ ሁሉ ቅዱሳን ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው አንድነት (ውህደት) ነው ቤተክርስቲያን የሚባለው፡፡ በዚህም መሠረት ቤተክርስቲያን ሁሉም ሰውና መላእክት በአንድነት የሚያመሰግኑባት እንጂ ሰው በየወገኑ እየተከፋፈለ የሚወነጃጀልባት አውድ አይደለችም፡፡ አንድነትን በአደባባይ ለይምሰል እየሰበኩ በተግባር ግን ልዩነትን የሚያስፋፉ ወገኖችም በንስሐ እስካልተመለሱ ድረስ ከቤተክርስቲያን ወገን አይደሉም፡፡ ራሳቸውን ቤተክርስቲያን (የክርስቶስ ቤተመቅደስ) ሳያደርጉ በሕንጻ ቤተክርስቲያን አካባቢ ስለተመላለሱ ብቻ የቤተክርስቲያን አካል አይሆኑም፡፡ እውተነኞቹ ክርስቲያኖች በቤተክርስቲያን ያላቸው አንድነት በፍቅር የተገነባ የመንፈስ አንድነት ስለሆነ አንዱ ለሌላው ስለመልካም ነገር የሚጸልይበት አንድነት ነው፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋል የሚያስፈልገን ቤተክርስቲያን የአንድነት ጉባዔ ናት ሲባል የአምልኮ፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የመተሳሰብ፣ የመተባበር፣ የመደጋገፍ ጉባዔ ናት ማለት ነው፡፡
የቤተክርስቲያን አስተምህሮ አንድ ነው፡፡
ቤተክርስቲያን በየትኛውም የዓለም ክፍል ብትኖር፣ በየትኛውም ዘመን ብታስተምር፣ በየትኛውም ቋንቋ ብትሰብክ መሰረታዊ አስተምህሮዋ አንድ ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ፣ ስለሰው ልጅም መከራን ተቀብሎ ሞትን ድል አድርጎ እኛን ከሲኦል ወደገነት እንደመለሰን የሚመሰክርና ሰውም ይህንን አምኖና ተጠምቆ መልካም ምግባርን ሠርቶ እንዲድን የሚያስተምር አስተምህሮ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‘እኛ ከሰበክንላችሁ ወንጌል ውጭ የሚሰብክላችሁ የሰማይ መልአክም ቢሆን የተወገዘ ይሁን’ ያለው የቤተክርስቲያን አስተምህሮ አንድ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ እርሱም ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ ማስተማር፣ እንዲሁም እርሱ ባስተማረው፣ ሐዋርያት በሰበኩት፣ ሐዋርያነ አበውና ደጋግ ሊቃውንት በመንፈስ ቅዱስ ምሪት አጽንተው በጠበቁት ኦርቶዶክሳዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት ያለመወላወል መጽናት ነው፡፡ ሁሉም ሐዋርያት ያስተማሩት ይህንኑ አንዱን የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ነው፡፡ በዘመናችን ያሉት ስድስቱ ኦሪየንታል አብያተ ክርስቲያናትም (ማለትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ የግብፅ ኦርቶዶክስ፣ የሶርያ ኦርቶዶክስ፣ የአርመን ኦርቶዶክስ፣ የሕንድ ኦርቶዶክስና የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት) አንድ ናቸው ስንል በአስተምህሮ (በዶግማ) ነው፡፡ በተለያየ ሀገር ሆነው የየራሳቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ቢኖራቸውም በአስተምህሮ አንድ ስለሆኑ የአንዲት ቤተክርስቲያን አካል ናቸው እንጂ የተለያዩ አይደሉም፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በአንዲት ቤተክርስቲያን ውስጥ ሆነው አስተምህሮዋን የማይቀበሉና የየራሳቸውን ፍልስፍና የሚያስተምሩ የውስጥ መናፍቃን የአንዲት ቤተክርስቲያን አካል አይደሉም፡፡
ቤተክርስቲያን የአንድ እግዚአብሔር ቤት ናት፡፡
በአንዲት ቤተክርስቲያን ያሉት ክርስቲያኖች የሚያምኑትና የሚያመልኩት፣ ቤተክርስቲያንም የምትሰብከው በዘመናት የማይቀየር የማይጨመርበት በፍጹም አንድነት በልዩ ሦስትነት የሚመሰገን አንድ አምላክ ነው፡፡ እርሱም አንድ እግዚአብሔር ነው፡፡ ቤተክርስቲያንም የእግዚአብሔር ቤት ናት፡፡ ጌታችን ‹‹ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች (ማቴ 21፡13)›› ያለውም ለዚህ ነው፡፡ አንዲት ቤተክርስቲያን የአንዱ የእግዚአብሔር ቤት ናትና ‘የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን’ ትባላለች (ሐዋ 20፡23)፡፡ አንዱን እግዚአብሔርን የምታመልክ ቤተክርስቲያን የሰው ዘር ሁሉ እርሱን ስም ቀድሶ ክብሩን እንዲወርስ ታስተምራለች፡፡ ‹‹ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ (ዘጸ 20፡3)›› ብሎ ለሙሴ ትዕዛዝን የሰጠውም በቤተክርስቲያን የሚመለከው እርሱ ብቻ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ቤት ናት ማለት የሰው ፈቃድ (ፍላጎት) ሳይሆን ፈቃደ እግዚአብሔር የሚፈጸምባት ናት ማለት ነው፡፡ የሰው ዝና ወይም ሥራ ሳይሆን የእግዚአብሔር ቸርነቱ፣ መግቦቱና ከሀሊነቱ የሚነገርባት ናት ማለት ነው፡፡ በቤተክርስቲያን የሚሰበሰበው ሰው እግዚአብሔርን ብሎ የመጣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ነው ማለት ነው፡፡ በቤተክርስቲያን የሚፈጸመው አገልግሎትም ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መስዋዕት እንጂ ምድርዊ ትርፍን ለማግኘት የሚደረግ አይደለም ማለት ነው፡፡ አሐቲ ቤተክርስቲያን የአንዱ የእግዚአብሔር ቤት ናት ስንል ይህንን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡
ቤተክርስቲያን ክርስቲያኖች ከአንድ ምስጢር የሚካፈሉባት ናት፡፡
ቤተክርስቲያን ያመንን ሁሉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ (ማየ ገቦ) አንዲት ጥምቀትን ተጠምቀን የስላሴ ልጅነትን የምናገኝባት፣ የአንዱን ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በአንድነት ተካፍለን፣ ተቀብለን የዘላለም ሕይወትን የምንወርስባት ቤት ናት፡፡ በቤተክርስቲያን ሁላችንም የተጠመቅነው ጥምቀት ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የሁላችንም ጥምቀት የስላሴን ልጅነት የምታሰጥ ጥምቀት ናት፡፡ ይህም በጥምቀታችን አንድ መሆናችንን ያሳያል፡፡ በአሐቲ ቤተክርስቲያን የሚፈተተው የአንዱ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ነው፡፡ ሁላችንም የምንቀበለው ይህንን የአንዱን የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ነው፡፡ በዚህም ሁላችንም የዘላለም ሕይወትን እንወርሳለን፡፡ ይህም በቤተክርስቲያን ያለንን የመንፈስ አንድነት ያሳያል፡፡ እነዚህ ምሥጢራት በየትም ቦታ፣ በማንኛውም ጊዜ፣ ለማንኛውም ሰው፣ በማንኛውም ካህን ቢፈጸሙ ዋጋቸው አንድ መሆኑ የቤተክርስቲያንን አንድነት ያመለክታል፡፡ በአንዲት ቤተክርስቲያን (በአባታችን በእግዚአብሔር ቤት) ከአንድ ምስጢር የተካፈልንና የምንካፈል የአንድ አባትና የአንድ እናት ልጆች ከማንም በላይ አንድ መሆን ይጠበቅብናል፡፡ እንደ ጠዋት ጤዛ ረግፎ ለሚጠፋው የሥጋ ፍላጎታችን ብቻ ስንል ከአንድ አባትና እናት የተወለዱት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከአባታቸው ቤት ከእናት ቤተክርስቲያን እንዲርቁ ምክንያት ብንሆን ግን በፍርድ ቀን ዋጋችን ይጠብቀናል፡፡
አንዲት (አሐቲ) ቤተክርስቲያን ማለት ‘በአንድ ሲኖዶስ እንመራለን’ ማለት ብቻ አይደለም፡፡ የቤተክርስቲያን አንድነት በአስተዳዳር መነጽር ብቻ መታየት የለበትም፡፡ በአስተዳደር አንድነት ከሆነ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዓለም አቀፍ የአስተዳዳር አንድነት ያለው ነው፡፡ በሁሉም ዓለም ያሉት ካቶሊካዊያን በአንድ ፖፕ ይመራሉና፡፡ የቤተክርስቲያን አንድነት ግን ከአስተዳደር አንድነት በላይ ነው፡፡ በአንድ ሲኖዶስ ስር ሆነው በቋንቋ፣ በዘር፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በመንደርተኝነትና በምድራዊ ጥቅም የተሳሰሩ ወገኖች የየራሳቸው ‘ቤተክርስቲያን’ ይዘውና ደሴት ሠርተው የሚኖሩበት ሁኔታ የአሐቲ ቤተክርስቲያንን ጽንሰ ሐሳብ ምሉዕ አያደርገውም፡፡ አንዱ የሌላውን መልካም ካልተመኘ፣ ሁሉ ስለሰው ሁሉ ድኅነት ካልሠራ፣ አንዱ ስለሌላው ካልጸለየ፤ በአንጻሩ መደጋገፍ ሳይሆን መነቃቀፍና መፎካከር ከነገሠ አሐቲ ቤተክርስቲያን ነን የሚለውን የቃል ብቻ ያደርገዋል፡፡ ይህ በሽታ በተለይም በዝርወት ምድር በሚገኙ ቤተክርስቲያንን በዋናነት የባህልና የማኅበረሰባዊ ትስስር ማጠንከሪያ፣ የእውቅና ፈላጊ አጭበርባሪዎች ዋሻ ባደረጉ ቦታዎች ይስተዋላል፡፡
አሐቲ (አንዲት) ቤተክርስቲያን ስንል ሕይወታችን የአንድ አባትና የአንድ እናት ልጆች መሆናችንን፣ እንዲሁም በአንድ አምላክ የምናምን፣ አንዲት መንግስተ ሰማያትን ተስፋ የምናደርግ የክርስቶስ ቤተሰቦች (ክርስቲያኖች) መሆናችንን በእምነትና በተግባር የሚመሰክር ሊሆን ይገባል፡፡ በአጠቃላይ የቤተክርስቲያን አንድነት በእምነት (በአንድ አምላክ በማመን)፣ በፍቅር (የአንድ አባትና የአንድ እናት ልጆች መሆናችንና በአንድ በክርስቶስ ፍቅር መዋደዳችን) እንዲሁም በተስፋ (አንዲት መንግስተ ሰማያትን ተስፋ የምናደርግ መሆናችንን) የሚገለጥ ነው እንጂ በቃላት ‘አንድ ነን’ ወይም ‘አንድ ሆነናል’ በማለት ብቻ የምናረጋግጠው አይደለም፡፡ የቤተክርስቲያን አምላክ እግዚአብሔር የሰይጣንን ተንኮል ያፍርስልን፣ አንድነታችንንም ያጽናልን፡፡ አሜን፡፡
Melkamu ebalalehu bizu gize kante meseretawi yehone kidem teketelun yetebeke timihirt lememar efeligi neber gin endet endemagegnih alawekum
Wendime Protestant nw ena metsaf kidus anibiboal ena hule eyeteyeke yaschegregnal bichalik bitagegnegn
0777317070
LikeLike