ቅዱስ መስቀል፡ እግዚአብሔርን ለሚፈሩ የተሰጠ ምልክት!

ግሸን

እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን፡፡

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ታላቅ ክብር ይሰጠዋል፡፡ የመስቀል በዓልም ከዘጠኙ የጌታችን ንዑሳን በዓላት አንዱ ሲሆን በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን ይከበራል፡፡  በዓሉም ከዋዜማው መስከረም 16 ጀምሮ ደመራ በመደመር ይከበራል፡፡ የመስቀል ደመራ በዓል ቅድስት ቤተክርስቲያን በደማቅ ሁኔታ በአደባባይ ከምታከብራቸው በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህንን ታላቅ በዓል በማስመልከት በዚህች የአስተምህሮ ጦማር የመስቀልን ምንነት፣ የመስቀልን አገልግሎት፣ የመስቀልን ታሪክ፣ የመስቀልን ክብርና አንዳንድ ተያያዥ ጉዳዮች እንዳስሳለን፡፡

የቅዱስ መስቀል ምንነት: መከራ ክርስቶስ፣ መከራ ክርስትና፣ ዕፀ መስቀል

በቤተክርስቲያን አስተምህሮ “መስቀል” የሚለው ቃል ሦስት መሠረታዊ ቁም ነገሮችን ያመለክታል፡፡ የመጀመሪያው ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከሞተ ነፍስ ለማዳን ሲል የተቀበለው መከራና የከፈለው መሥዋዕትነት (የክርስቶስ መከራ መስቀል) ነው፡፡  ሁለተኛው  ደግሞ በክርስትና ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥም ልዩ ልዩ ዓይነት መከራም (መከራ መስቀለ ክርስቲያን) ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕፀ መስቀል ነው፡፡ በሦስቱም ቁም ነገሮች ነገረ መስቀል (የመስቀሉ ነገር) ከክርስትና ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡ መስቀል የሰላማችንና የድኅነታችን የመቀደሳችን ዓርማ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጆች ለማዳን፥ የዘላለም ሕይወትን ለመስጠት መስዋዕትነት የከፈለበት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት መንበር፥ ሲሆን አምላካችንን የምንመለከትበት መስታወት ነው።

የቅዱስ መስቀል አገልግሎት:  የድኅነት ኃይል፣ የእምነት ዓርማ

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋጋ የከፈለበት ቤዛ ዓለም የተከናወነበት እንደመሆኑ መስቀል በቤተ ክርስቲያናችን በሁሉ አገልግሎት ሰፊ ድርሻ ያለውና እንዲሁም በንዋያተ ቅድሳት ላይ የሚውል አቢይ ምልክት ነው:: በነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት “ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው (መዝ 59:4) እንደተባለ ለክርስቲያኖች መስቀል የጠላት ሰይጣን ተንኮል የከሸፈበት ስለሆነ ከአንገታችን፣ ከእጃችን ሳይለይ የክርስቶስን ቤዛነት የምንመሰክርበት የድኅነታችንም ኃይል የተገለጠበት ነው:: አጋንንት የመስቀሉን ምልክት ባዩ ጊዜ ይንቀጠቀጣሉ፤ ካደሩበት ሰው ላይም በፍጥነት ይወጣሉ፡፡ ምእመናን በመስቀሉ ስንዳሰስ ከልዩ ልዩ ደዌ እንፈወሳለን፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋል የሚያስፈልግ ነገር አለ፡፡ ቤተክርስቲያንና ክርስቲያኖች ቅዱስ መስቀል ስንገለገልበት የሕሊናችን ትኩረት በመስቀሉ ላይ ተሰቅሎ ቤዛ የሆነን ኢየሱስ ክርስቶስን በማሰብ የመስቀሉ ምልክትነት (ዓርማነት) ላይ ነው እንላለን እንጂ የመስቀሉን ቁሳዊ አካል (Physical structure) ላይ አይደለም የሚሆነው፡፡ መስቀል ከእንጨትም ተሠራ ከእንቁ ትኩረታችን መሆን ያለበት ምልክትነቱ፣ ዓርማነቱ ላይ ነው፡፡ ይህም በቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችን ህይወት የተገለጠ ህያው ምስክር ነው፡፡ መስቀልም የድኅነታችን ኃይል፣ የእምነታችን ዓርማ፣ የቤተክርስቲያናችን ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ ስለዚህም የመስቀል ምልክት የሃይማኖታችን መገለጫ እንጂ ለሥጋዊ ሰውነታችን ማጌጫ አይደለም፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያ ክርስቲያናዊ ባህል የመድኀኒታችን የክርስቶስ መስቀል በብዙ ተግባራት ላይ በምልክትነት ጥቅም ላይ ሲውል ይታያል፡፡ ለምሳሌ በየሸማ ልብሶች፤ እንደዚሁም በጆሮ፣ በአንገት፣ በእጅና ሌሎችም ጌጣጌጦች ላይ የመስቀል ምልክት አለ፡፡ ክርስቲያን ልጃገረዶች (በተለይ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል) በግንባራቸው፣ በጉንጫቸው፣ በአንገታቸው፣ በደረታቸውና በእጃቸው ላይ በመስቀል ቅርፅ እየተነቀሱ እምነታቸውን ይመሰክሩበታል፡፡ ክርስቲያኖች ከዚህ ዓለም በሞት ስንለይም በመቃብር ሣጥናችን ወይም በሐውልቶቻችን ላይ የመስቀል ምልክት ይቀመጣል፡፡ በቤት ውስጥም ስንተኛና ከእንቅልፋችን ስንነቃ ፊታችንንና መላ ሰውነታችንን በትእምርተ መስቀል እናማትባለን፤ አባቶችና እናቶችም ውሃ ሲቀዱ፣ ሊጥ ሲያቦኩ፣ እንጀራ ሲጋግሩ፣ ምግብ ሲቈርሱ፣ ወዘተ በመስቀል አማትበው ነው፡፡ በአጠቃላይ መስቀል ብዙ ነገር ነው፤ መስቀል በክርስትና ሕይወት ውስጥ በሚደረጉ ተግባራት ኹሉ ያለው ድርሻ ጕልህ ነው፡፡

የቅዱስ መስቀል ታሪክ: ከደብረ ቀራንዮ እስከ ደብረ ከርቤ

የቅዱስ መስቀሉ መቀበር በብሉይ ኪዳን መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ መሣርያ ነበር፡፡ በደላችንን ሊያጠፋ የመጣው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ33 ዓ.ም ለሰው ልጆች ሲል በመስቀል ተሰቀለ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ሕሙማንን በመፈወሱ ምክንያት በርካታ አሕዛብ ክርስቲያን እንዲሆኑ አስችሏል፡፡ በተአምራዊነቱና በክርስቲያኖች ዘንድ ከፍተኛ ክብር የተሰጠው በመሆኑ ይህን የተመለከቱ አይሁድ ቅዱስ መስቀሉን በአንድ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ እንዲቀበር አደረጉ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በየቀኑ ቆሻሻ ስለሚጥሉበት ቦታው ወደ ተራራነት ተቀየረ፡፡ ምንም እንኳን መስቀሉን ለማውጣት ባይችሉም በኢየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖች ቦታውን ያውቁት ነበር፡፡ በሰባ ዓመተ ምሕረት በጥጦስ ወረራ ኢየሩሳሌም ስለጠፋች በዚያ የነበሩ ክርስቲያኖች ተሰደዱ፡፡ የተቀበረበትን ቦታ የሚያውቅ ባለመገኘቱ መስቀሉ ከ300 ዓመታት በላይ ተዳፍኖ /ተቀብሮ/ ኖረ፡፡

የቅዱስ መስቀሉ ከተቀበረበት መውጣት፡ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (በ327 ዓ.ም) የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ቅድት እሌኒ መስቀሉን ለማግኘት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡ ቅድት ዕሌኒ በዕጣን ጢስ አመልካችነት መስቀሉን ከተቀበረበት ቦታ ለማውጣት ቍፋሮ ያስጀመረችበትን የመታሰቢያ በዓል የደመራ በዓል ተብሎ ይከበራል፡፡ በሀገራችን መስቀል የሚከበርበትን ጊዜ በማስመልከት ሁለት አይነት ትውፊት አለ፡፡ ጎንደር ትግራይና ኤርትራ እንዲሁም በገጠራማው የጎጃምና የወሎ ክፍሎች ደመራ የሚለኮሰው መስከረም 17 ሲሆን በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ መስከረም 16 ቀን ለ17 ዋዜማ ምሽት ላይ ይከበራል፡፡ የዚህን ልዩነት መነሻ መተንተን የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ባይሆንም ቅዱስ መስቀልን ለማግኘት ደመራ ተሰርቶ የተለኮሰው መስከረም 16 ለ 17 አጥቢያ እንደሆነ አባቶቻችን ያስተምራሉ፡፡ ከዚህም በመነሳት አንዳንዱ አካባቢ በዋዜማው ሌላ አካባቢ ደግሞ በዕለቱ ያከብራሉ፡፡ በየዓመቱ መስከረም 16 ቀን ደመራ ደምረው በመለኮስ በታላቅ መንፈሳዊ ሥርዓት በዐደባባይ ያከብሩታል፡፡

ቅድስት እሌኒ ከመስከረም 17 ቀን አስጀምራ እስከ መጋቢት 10 ቀን ሌሊትና ቀን ለሰባት ወራት ያህል የጉድፍን ኮረብታ ቆፍረው ቆሻሻውንም ካስወገዱ በኋላ ሦስት መስቀሎች ተገኙ ፡፡ የጌታም መስቀል ሙት በማስነሣቱ ተለይቶ ታውቋል፡፡ መስቀሉ የተገኘው መጋቢት 10 ቀን 326 ዓ. ም. ነበር፡፡ በተመሳሳይ መልኩ መስቀሉ ከተቀበረበት ተራራ ተቈፍሮ የወጣበት መጋቢት 10 ቀንም በቤተ ክርስቲያን በደማቅ ሥርዓት ይከበራል፡፡ በተጨማሪም መስከረም 17 ቀን ንግሥት ዕሌኒ ቅዳሴ ቤቱን ያከበረችበትን የመታሰቢያ በዓል ታቦት አውጥተው ዑደት በማድረግ በቤተ ክርስቲያን ያከብሩታል፡፡ በ327 ዓ.ም የጌታን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ መስቀል በቅድስት እሌኒ ከተቀበረበት ከወጣና በክብር ለረጅም ዓመታት በኢየሩሳሌም ከተቀመጠ በኋላ ዐረቦች ኢየሩሳሌምን በመውረራቸው ምክንያት በአረማውያን እጅ እየተማረከ ከአንዱ ሀገር ወደ አንዱ ሀገር ሲንከራተት ቆይቷል፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ክርስቲያኖችም በመስቀሉ መማረክ ያዝኑና ይበሳጩ ስለነበር ጦራቸውን አሰልፈው መስቀሉ ወደሔደበት ሀገር በመዝመት ጦርነት ያካሔዱ ነበር፡፡

ቅዱስ መስቀሉን እንደተከፋፈሉት በ778 ዓ.ም አራቱ አኅጉራት ለበረከት ይሆናቸው ዘንድ በአራቱ የመስቀሉ ክንፍ የተያያዙት ምልክቶችን በማንሳት የተከፋፈሉ ሲሆን በወቅቱ በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ዐረቦች በእስክንድርያ ለሚኖሩ አባቶች የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግሮቹ እና እጆቹ ተቸንክረው የተሰቀለበትን ሙሉ መስቀል ላኩላቸው፡፡ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስም በክብርና በጥንቃቄ እንዲቀመጥ አድርጓል፡፡ ይህም የመስቀሉ ክፋይ (ግማደ መስቀል) በእስክንድያ እስከ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ በክብር ተቀምጦ ነበር፡፡

የግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ መግባት፡ የጌታችን ቅዱስ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ የቻለበት 1394 ዓ.ም. ዐፄ ዳዊት ሁለተኛ በነገሡ በ29ኛ ዓመታቸው የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን 47ኛው ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል  በወቅቱ የነበረው የግብጽ ፈርዖን አሠራቸው ክርስቲያን የሆኑ ዜጎቹን “የእኔን ሃይማኖት ካልተከተላችሁ መኖር በግብጽ መኖር አትችሉም” ብሎ ከአቅማቸው በላይ ግብር ጣለባቸው፡፡ መከራው የጸናባቸው የግብጽ ክርስቲያኖች “ከደረሰብን መከራና ሊቀጳጳሳችንን ታስፈታልን ዘንድ በእግዚአብሔር ስም ተማጽነናል” ሲሉ ለአፄ ዳዊት መልእክት ላኩባቸው፡፡ አጼ ዳዊትም ወታደራቸውን ወደ ግብፅ አዘመቱ፡፡ በወታደሩም ኃይል የዓባይን ወንዝ ለመገደብ ተነሱ፡፡ ይህን የሰሙ የወቅቱ የግብጽ መሪ መርዋን እልጋዴን መኳንቱን ሰብስበው “ምን ይሻለናል ብለው ምክር ያዙ” የዐባይን ወንዝ ከምናጣ “ሊቀጳጳሱን አቡነ ሚካኤልን እንፈታለን በክርስቲያኖችም ላይ መከራ አናደርስም” ብለው ቃል በመግባት ብፁዕ አቡነ ሚካኤልን ሁለት እልፍ ወቂት ወርቅ እጅ መንሻ አስይዘው ለዐፄ ዳዊት አማላጅ ላኩ፡፡

ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም “ብርና ወርቅ አልፈልግም ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ነው የምፈልገው” አሏቸው፡፡ የሀገራችን ሕዝብ በውኃ ጥም ከሚያልቅ ብንስማማ ይሻለናል ብለው መስከረም 10 ቀን 1395 ዓ.ም. ከመስቀሉ ጋር ቅዱስ ሉቃስ የሳላት የእመቤታችን ሥዕል ጨምረው ሰጧቸው፡፡ መስከረም 10 ቀን በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ግማደ መስቀሉ ከእስክንድርያ ወደ ኢትዮጵያ የመጣበትን የመታሰቢያ በዓል በየዓመቱ ይከበራል፡፡ ዐፄ ዳዊት መስከረም 10 ቀን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ከግብፃውያን የተቀበሉበት ቀን በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ተቀጸል ጽጌ በመባል የሚታወቅ ሲሆን በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡

የመስቀሉ በመስቀለኛ ቦታ መቀመጥ ከዐፄ ዳዊት በኋላ በቦታቸው የተተኩት ዐፄ ዘርዐያዕቆብ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል” የሚል ራዕይ በማየታቸው መስቀሉን በ1443 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት በተለያዩ ቦታዎች ለማሳረፍ ጥረት አድርገዋል፡፡ በደብረ ብርሃን፤ በሸዋ ደርሄ ማርያም፤ በጨጨሆ፤ በአንኮበር፤ በመናገሻ አምባ፤ በእንጦጦ፤ ወዘተ አሳርፈውት አልተሳካላቸውም፡፡ በመጨረሻም መስከረም 21 ቀን 1446 ዓ.ም. በራዕይ በተነገራቸው ቅዱስ ስፍራ በግሸን ደብረ ከርቤ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አኑረውታል፡፡ መስከረም 21 ቀን ግማደ መስቀሉ በሚገኝበት በግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም በታላቅ በዓለ ንግሥ ያከብሩታል፡፡  በአጼ ዳዊት እግር የተተኩት ልጃቸው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል /መስቀሌን በመስቀልያ ስፍራ አስቀምጥ/” የሚል ራእይ በተደጋጋሚ እግዚአብሔር አሳያቸው፡፡ በኢትዮጵያ ካሉት መልከዐ ምድር ውስጥ የመስቀል ቅርጽ ያለው የቀራንዮ አምሳል የሆነ ቦታ ከፈለጉትና ካጠኑ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ በቀራንዮ የተሰቀለበት ቀኝ እጁ ያረፈበት ግማደ መስቀል አሁን ግሼ አምባ በሚባለው ሥፍራ ላይ መስከረም 21 ቀን 1446 ዓ.ም ደብረ ከርቤ አሁን እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን የታነጸበት ቦታ ላይ እንዲያርፍ አደረጉ፡፡

አንዳንድ ወገኖች “መስቀሉን ለምን በዚያ አሳረፉት? ለምን ዛሬ ለሰዎች እንዲታይ ሆኖ አልተቀመጠም?” ብለው ይጠይቃሉ፡፡  የመስቀሉ ጠላቶች የሆኑት አይሁድ መስቀሉ ድውይን ስለፈወሰ ሙታንን ስላስነሳ ሰዎች እንዳይድኑበት በተንኮል ነበር የቀበሩት፡፡ የክርስቶስ የክብር ዙፋኑ በሆነው መስቀል ላይም ቆሻሻ እንዲደፋበት አድርገዋል፡፡  የመስቀሉ ወዳጆች የሆኑት ኢትዮጵያውያን አባቶች ግን መስቀሉን በመስቀለኛ ቦታ በክብር ነው ያሳረፉት፡፡ በመስቀለኛው ስፍራም ያሳረፉት በየአድባራቱ አዙረው ምድሪቱን ካስባረኩ በኋላ ከፈጣሪ በተሰጣቸው ትዕዛዝ ለመስቀሉ በተፈቀደው ቦታ በግሸን በደብረ ከርቤ ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ብዙ ጊዜ ሲማረክ የነበረው መስቀልን በክብር ተጠብቆ እንዲቆይ በመስቀለኛው ቦታ አሳረፉት፡፡

የቅዱስ መስቀል ክብር

በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኘን ክርስቲያኖች መስቀልን የምናከብረው በመስቀሉ ላይ በተፈጸመው ቤዛነት ብዙ ነገሮችን ስላገኘን ነው። በክርስቶስ ቤዛነት ሞት ስለተሻረ አጥተነው የነበረውን ሕይወት አግኝተናል። ስለዚህ ነው “ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና፤” የተባለው። 1ኛ ቆሮ.15፥22። የሰው ልጅ ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ክርስቶስ ሥጋውን የሕይወት እንጀራ አድርጎ በመስቀል ላይ ሰጠን። ይህንንም “እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ /የወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስን/ ሥጋውን ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፤” ሲል አረጋግጦልናል። ዮሐ.6፥53-54። 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም፤” ብሎ እንደተናገረ ፍጹም የሆነውን ሰላም የሰጠን በመስቀል ላይ ነው። ይህንንም፡- ሞትን በኃይሉ ድል አድርጎ በተነሣ ጊዜ “ሰላም ለእናንተ ይሁን፤” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ አረጋግጦላቸዋል። ዮሐ.14፥27፤ 20፥19፣26። በመርገመ ሥጋ በመርገመ ነፍስ አርጅቶ የነበረው ሰውነታችን አዲስ የሆነው በመስቀል ላይ በተፈጸመው ቤዛነት ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ከእንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን /ሰውነታችን/ ከእርሱ ጋር እንደተሰቀለ እናውቃለን።” ያለው ሮሜ.6፥6። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርቶስ በመስቀሉ ላይ በከፈለው ቤዛነት ከራሱ ጋር አስታረቀን (ታረቀን)፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ “በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷል፤” ብሏል። ቆላ.1፥20።

መስቀልን ስናከብር አንዳንዶች ባለማወቅ ወይም እውነተኛውን የወንጌል አስተምህሮ ባለመረዳት “አባትህ የተገደለበትን መሣርያ እንዴት ታከብራለህ?” የሚል አንድምታ ያለው ሀሳብ ያነሳሉ፡፡ ይህም ስለክርስቶስ ስቀለት ያላቸውን ትክክለኛ ያልሆነ ግንዛቤ ያነፀባርቃል፡፡ ምክንያቱም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሰው ልጆች ሲል በመስቀል ላይ የተሰቀለው በራሱ ፈቃድ (በፍቅር) እንጂ እነዚህ ወገኖች እንደሚያስቡት አይሁድ አስገድደውት አይደለም፡፡ መስቀሉም ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስና በእርሱ ምክንያት የመጣብን ሞት የተሸነፉበት ነው፡፡ መስቀሉ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሰላምን ያደለበት ነው፡፡ መስቀሉ የክርስቶስ የክብር ዙፋኑ ለእኛም የድል ዓርማችን ነው የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ለአርአያነትና ለቤዛነት የመጣው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ጠላትን ድል አድርጎ ቤዛ የሆነን እናንተም በዚህ መስቀል ጠላታችሁ ዲያብሎስን ድል አድርጉበት ብሎ አርአያ ሊሆነንም ጭምር ነው፡፡ እውነተኛዋ ክርስትናም የምታሸንፈው በመግደል ሳይሆን በመሞት፣ በማጥቃት ሳይሆን መከራ በመቀበል፣ በማሳደድ ሳይሆን በመሰደድ፣ በማስገደድ ሳይሆን በማስወደድ፣ በክርክር ሳይሆን በፍቅር ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝሙሩ “ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሀቸው ወዳጆችህም እንዲድኑ” (መዝ. 59፡4) እንዳለ ቅዱስ መስቀል እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ምዕመናን የተሰጠ ልዩ የድኅነት ምልክት ነው፡፡

የኪስኪስ ኤጲስ ቆጶስ ሊቁ አባታችን ቅዱስ ኤራቅሊስ በሃይማኖተ አበው “እግዚአብሔር ያገለገለባት መቅደስ ወዮ እንደምን ያለች ናት?!” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤራቅሊስ 48፡17) ብሎ እንዳመሰገናት እንደ እመቤታችን ድንግል ማርያም እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ያገለገለበት ወገኖቹንም ወደ ጽድቅ የመለሰበት የክብር ዙፋኑ (ማቴ. 20፡21) ቅዱስ መስቀል ወዮ እንደምን የከበረ ነው?! ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “ወንሰግድ ውስተ መካን ኀበ ቆመ እግረ እግዚእነ/ የጌታችን እግሮቹ በሚቆሙበት (በቆሙበት) ቦታ እንሰግዳለን” (መዝ. 131፡7) እንዳለ ለኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የጸጋ ስግደትን እንሰግዳለን፡፡ የእግዚአብሔር ማደሪያ በመሆኗ ምድራዊት ጽዮን በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተመሰገነችና የጸጋ ስጦታ ምንጭ መሆኗ እንደተነገረ፣ ተራሮችም የእግዚአብሔር ክብር ሲገለጥባቸው “ቅዱስ” (2ኛ ጴጥ 1፡18) እንደተባሉ ከዚያ በበለጠ ክብር የድኅነታችን ምስጢር የተፈጸመበትን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት መገለጫና ዘላለማዊ መቅደስ ቅዱስ መስቀልን እናከብረዋለን፡፡ ምልክታችን፣ አርማችን አድርገነው እንኖራለን፡፡ ምልክትና አርማ ሲባል ግን እንደምድራውያን ሰንደቆች ኃይል የሌለው ተዓምራትን የማያደርግ ሳይሆን እንደ ሙሴ በትር ሰይጣንን የሚረታ (ዘፀ. 14፡16)፣  ቅዱሳን መላእክት ከመስቀሉ ደመ ማኅተም የተነሳ ጠላት ዲያብሎስን እንዳሸነፉት ምዕመናንን የሚያጸና፣ የሚረዳ (ራዕይ 12፡11) ሰማያዊ አርማ ነው፡፡ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለቅዱስ መስቀል ልዩ ክብር ትሰጣለች፡፡ በጸሎቷ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ የባህርይ፣ አምላክን በድንግልና ለወለደች ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የጸጋ ምሥጋና ካቀረበች በኋላ “…ለኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልም ምሥጋና ይገባል፡፡” እያለች ታከብረዋለች፡፡ የመስቀሉ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር ልዑል ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ፡ የአዲስ ዘመን ምልክት

በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የበዓላት ቀኖና መሰረት የአዲስ ዓመት ዘመን መለወጫ በዓል የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በዓል ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ቅዱስ ዮሐንስ የአሮጌ (ብሉይ) ዘመን ማብቃት ብስራት፣ የአዲስ ዘመን መምጣት ማሳያ ሆኖ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለሚታወቅ ነው፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን መካከል ከነበሩት ቅዱሳን አበው አንዱ የሆነ፣ ከነቢያት እነ ነቢዩ ኢሳይያስ፣ ከመላእክት ቅዱስ ገብርኤልና ከካህናት አባቱ ዘካርያስ ትንቢት የተናገሩለት ነቢይና ሐዋርያ ነው፡፡ ገና ከሕፃንነቱ ጀምሮ ቅኑት እንደ ገበሬ፣ ጽሙድ እንደ በሬ ሆኖ እግዚአብሔርን ያገለገለ፣ በፍጹም ልቡ ዓለምን የናቀ፣ ከተድላዋና ከደስታዋም የተለየ፣ አምላክን ለማጥመቅ የታደለ ሐዋርያ፣ መምህር፣ ሰማዕት፣ ባሕታዊ፣ ነቢይ፣ ጻድቅ ነው፡፡ በዚህች የአስተምህሮ ጦማር የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስን ሕይወቱን፣ ትምህርቱን፣ አገልግሎቱንና ሰማዕትነቱን እንዳስሳለን፡፡

ትንቢቱና ብሥራቱ፡ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል።

ካህኑ ዘካርያስ እና ከካህኑ ከአሮን ወገን የሆነች ኤልሳቤጥ ሁለቱም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፡፡ ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም /ሉቃ.፩፥፭-፯/፡፡ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድም እግዚአብሔርን ዘወትር ይማጸኑት ነበር፡፡ ካህኑ ዘካርያስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ዕጣን በማሳረግ ላይ ሳለም የእግዚአብሔር መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ “ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፥ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል፤ ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል። እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።” ብሎ አበሠረው (ሉቃ.፩፥፰-፲፯)፡፡

ካህኑ ዘካርያስም “እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜዋ አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ?” አለው፡፡ መልአኩም “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፡፡ እነሆም በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ ይህ ነገር እስከሚኾን ቀን ድረስ ዲዳ ትኾናለህ፤ መናገርም አትችልም፤” አለው፡፡ ከውጪ ቆመው ጸሎት ሲያደርጉ የነበሩት ሕዝብም ዘካርያስን ከቤተ መቅደስ እስኪወጣ ይጠብቁት ነበር፤ በመዘግየቱም ይደነቁ ነበር (ሉቃ.፩፥፲፰-፳፩)፡፡ ከቤተ መቅደስ በወጣም ጊዜ ሊያናግራቸው ባለመቻሉ ይጠቅሳቸው ነበር፡፡ በዚህም በቤተ መቅደስም ራእይ እንዳየ አስተዋሉ፡፡ ከመልአኩም ቃል ተነሳ ካህኑ ዘካርያስ ልጁ ቅዱስ ዮሐንስ እስኪወለድ ድዳ ኾኖ ኖረ፡፡ የማገልገሉም ወራት ሲፈጸምም ወደ ቤቱ ሔደ፤ ከሁለት ቀን በኋላም አረጋዊቷ ቅድስት ኤልሳቤጥ ፀነሰች፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥም በመካንነቷ ከሰዎች የሚደርስባት ሽሙጥ ተወግዷላታልና “እግዚአብሔር በዚህ ወራት ከሰው ስድቤን ያርቅ ዘንድ እንዲህ አደረገልኝ” ስትል ለአምስት ወራት ተሸሸገች (ሉቃ.፩፥፳፪-፳፭)፡፡ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችን ጌታችንን በድንግልና እንደምትወልድ ሲያበሥራት “ወንድ ሳላውቅ ይህ እንዴት ሊኾን ይችላል?” ባለችው ጊዜ እግዚአብሔር ኹሉን ማድረግ እንደሚቻለው ለማስረዳት መካኗ ቅድስት ኤልሳቤጥ በስተእርጅና መውለዷን ጠቅሶላታል፡፡

ጽንሰቱና ልደቱ፡ አንተ ሕፃን ሆይ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፡፡

ቅድስት ኤልሳቤጥ መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው:: አስቀድሞ በነቢዩ በኢሳይያስ የአዋጅ ነጋሪ ቃል ተብሎ እንደተነገረው የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካክሉ በማለት ፊት አውራሪ ሆኖ የሚላከውን ቅዱስ ዮሐንስን የፀነሰችው ቅድስት ኤልሳቤጥ በፀነሰች በስድስተኛው ወር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ልትጠይቃት ወደ እርሷ በሔደች ጊዜ እጅግ የሚያስገርም ሁኔታ ተፈጠረ። ይኸውም ቅዱስ ዮሐንስ በማኅፀን ውስጥ ኾኖ ለቅድስት ድንግል ማርያም እና በማኅፀኗ ላለው ለዓለም መድኃኒት ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰግዷል (ሉቃ. ፩፥፳፮-፵፩) ። ቅድስት ኤልሳቤጥም ድምጿን ከፍ አድርጋ “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፡፡ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይኾንልኛል? እነሆ የሰላምታሽን ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሏልና፡፡ ከጌታ የተነገረላት ቃል እንደሚፈጸምላት ያመነች ብፅዕት ናት፤” በማለት እመቤታችንን አመስግናታለች (ሉቃ.፩፥፵፪-፵፭)፡፡

የመውለጃዋ ቀን ሲደርስም ሰኔ ፴ ቀን ንዑድ፣ ክቡር የኾነው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ተወለደ። ዘመዶቹ የሕፃኑን ስም በአባቱ መጠሪያ “ዘካርያስ” ሊሉት ቢወዱም እናቱ ግን “ዮሐንስ ይባል” አለች፡፡ የመልአኩን የብሥራት ቃል ባለመቀበሉ አንደበቱ ተይዞ የነበረው ካህኑ ዘካርያም ስሙ “ዮሐንስ” ይባል ብሎ ሲጽፍ አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱም ተፈታና በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ “… አንተ ሕፃን ሆይ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሔዳለህና፡፡ የኃጢአታቸው ስርየት የኾነውን የመዳን ዕውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፡፡ ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፡፡ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል፤ እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል፤” ብሎ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ነቢይነትና አጥማቂነት፣ እንደዚሁም የክርስቶስን የማዳን ትምህርት እንደሚያበሥር አስቀድሞ ትንቢት ተናገረ (ሉቃ.፩፥፶፯-፸፱)፡፡

ስደቱና ገዳማዊ ሕይወቱ፡ የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካከሉ።

በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈ ሄሮድስ የመድኀኒታችን የክርስቶስን መወለድ ከሰብአ ሰገል ሲሰማ መንግሥቴን ይወስድብኛል ብሎ ስለ ሰጋ ጌታችንን ያገኘ መስሎት የቤተልሔም ሕፃናትን መግደል ጀመረ (ማቴ.፪፥፩-፲፮)፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሄሮድስ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሄሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: “ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ ‘ዮሐንስ’ የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል” አሉ:: እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን ገድለውታል:: የሄሮድስ ጭፍሮችም ዮሐንስን ፈልገው ባጡት ጊዜ ዘካርያስን በቤተ መቅደስ ውስጥ በሰይፍ ገደሉት፤ ካህናቱም በንጹሕ ልብስ ገንዘው በአባቱ በበራክዩ መቃብር ቀበሩት፡፡ ደሙም እስከ ፸ ዓመት ድረስ ሲፈላ ኖረ። ጌታችንም የዘካርያስ ደም እንደሚፋረዳቸው ሲያስረዳ “ከአቤል ደም ጀምሮ በመሠዊያውና በቤተ መቅደስ መካከል እስከ ጠፋው እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ ከዚህ ትውልድ ይፈለጋል” በማለት ጸሐፍት ፈሪሳውያንን ገሥጿቸዋል (ሉቃ.፲፩፥፶፩)፡፡

በዚህ ጊዜ ቅድስት ኤልሳቤጥ ልጇን ከሞት ለማዳን ስትል ሕፃኑ ዮሐንስን ይዛ ወደ በረሃ ተሰደደች። በበረሃም ድንጋይ ቤት ኾኖላቸው፣ እግዚአብሔርም ከብርድ፣ ከፀሐይና ከአራዊቱ አፍ እየጠበቃቸው መኖር ጀመሩ፡፡ ወደ በረሃ ሲገቡ ቅዱስ ዮሐንስ የሁለት ዓመት ከመንፈቅ ሕፃን ነበር፡፡ አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: “ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤል እስከታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ” (ሉቃ.፩፥፹)፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥ ወደ በረሃ በገባች በአምስተኛ ዓመቷ፤ ቅዱስ ዮሐንስም ሰባት ዓመት ሲሞላው ሕፃኑን በበረሃ ትታ ከዚህ ዓለም ድካም ዐረፈች፡፡ በገድሉ እንደተጻፈው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ቅድስት ድንግል ማርያምና ሰሎሜ እንዲሁም ቅዱሳን መላእክት፣ካህኑ ዘካርያስና ሰምዖን በአካለ ነፍስ ተገኝቶ ገንዘው ቀብረዋታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም እግዚአብሔር ከአራዊት አፍ እየጠበቀው፤ ሲርበው ሰማያዊ ኅብስትን እየመገበው ሲጠማውም ውኃ እያፈለቀ እያጠጣው፤ አናብስቱና አናምርቱ እንደ ወንድምና እኅት ኾነውለት በበረሃ መኖር ጀመረ፡፡ በበረሃ ሲኖርም የግመል ጠጉር ይለብስ፣ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ፣ አንበጣ (በአቴና ቀምሲስ፣ በኢትዮጵያ ሰበቦት /የጋጃ ማር/) የሚባል /የበረሃ ቅጠል/ እና መዓረ ጸደንያ /ጣዝማ ማር/ ይመገብ ነበር (ኢሳ.፵፥፫-፭)። ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በሁዋላ በዚያ በረሀ የግመል ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ፡፡ ለሃያ ሦስት ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም፡፡ ይህችን አመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም::

ኤልያስ ፀጉራም እንደ ኾነ ኹሉ ዮሐንስም ልብሱ የግመል ፀጉር መኾኑ፤ ሁለቱም መናንያን፣ ጸዋምያን፣ ተሐራምያን (ፈቃደ ሥጋን የተዉ)፣ ዝጉሐውያን (የሥጋን ስሜት የዘጉ)፣ ባሕታውያን መኾናቸው፤ በተጨማሪም ኤልያስ አክአብና ኤልዛቤልን፣ ዮሐንስ ደግሞ ሄሮድስና ሄሮድያዳን መገሠፃቸው፤ ኤልያስ ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት ቀድሞ እንደሚመጣ ኹሉ ዮሐንስም ከክርስቶስ ቀዳሚ ምጽአት (በአካለ በሥጋ መገለጥ) ቀድሞ ማስተማሩ ያመሳስላቸዋልና ጌታችን ዮሐንስን ኤልያስ ብሎታል። “እነርሱም ስለ ዮሐንስ እንደ ነገራቸው አስተዋሉ፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ማቴ.፲፩፥፪-፲፱)። ቅዱስ ዮሐንስ በብሕትውና በበረሃ/በገዳም የኖረ፣ የብሉይና የሐዲስ መሸጋገሪያ፣ የመጨረሻው ነቢይና የመጀመሪያው ሐዋርያ ነው፡፡

ስብከቱና ጥምቀቱ፡ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ!

ሠላሳ ዓመት ሲሞላውም በነቢዩ በኢሳይያስ ቃል “… የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አቅኑ፤ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፡፡ ዐዘቅቱ ሁሉ ይሙላ፤ ተራራውና ኮረብታውም ኹሉ ዝቅ ይበል፡፡ ጠማማውም የቀና መንገድ ይኹን፤ ሸካራውም መንገድ ትክክል ይኹን፡፡ ሥጋም የለበሰ ኹሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ፤” ተብሎ እንደ ተነገረ ቅዱስ ዮሐንስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!” እያለ እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለው አገር ኹሉ ወጣ (ሉቃ.፫፥፫-፮)። ዮሐንስ ወንጌላዊም ይህንን “ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ። ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም።” በማለት ገልጾታል፡፡

በዚያም ወቅት የይሁዳ አገር ሰዎች ኹሉ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር። እርሱም፡- “… እናንተ የእፉኝት ልጆች ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ኹሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል፤” ይላቸው ነበር፡፡ “ምን እናድርግ?” ብለው ሲጠይቁት “ሁለት ልብስ ያለው ለሌለው ያካፍል፤ ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ” ይላቸው ነበር። ቀራጮችን፡- “ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ” ጭፍሮችንም፡- “በማንም ላይ ግፍ አትሥሩ፤ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፤ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ” እያለና ሌላም ብዙ ምክር እየመከረ ወንጌልን ይሰብክላቸው ነበር /ሉቃ.፫፥፯-፲፬/፡፡

በተጨማሪም “በዚያን ጊዜ በይሁዳ፣ በኢየሩሳሌምና በዮርዳኖስ አውራጃ ያሉ ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይሄዱ ነበር፡ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ ሁሉም በዮርዳኖስ ወንዝ ይጠመቁ ነበር፡፡ ማቴ. ፫ ፥ ፮ ከሰዱቃውያንና ከፈሪሳውያን ወገን መጥተው ሲጠመቁ አይቶ እናንተ የእፉኝት ልጆች ከሚመጣው ቁጣ ትሸሹ ዘንድ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህስ ለንስሐ የሚያበቃችሁን በጎ ሥራ ሥሩ፡፡ አብርሃም አባት አለን በማለት የምታመልጡ አይምሰላችሁ …ምሳር በዛፎች ግንድ ላይ ሊቆርጥ ተዘጋጅቷልና መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል፡፡ ማቴ. ፫ ፥ ፱ ጥምቀቱንም በተመለከተ እኔ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እሱ ከእኔ አስቀድሞ የነበረ ነው ከእኔ ይበልጣል፤ እርሱ በእሳት ያጠምቃችኋል፤ የጫማውን ጠፍር ልፈታ አይገባኝም (ማቴ. ፫ ፥ ፲፩) እያለ ያስተምር ነበር፡፡ እኔ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ፣ ከእኔ በኋላ የሚመጣውና ከእኔ ይልቅ የሚበረታው እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ መንሹም በእጁ ነው፤ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፤ ሥንዴውንም በጎተራው ይከታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል” በማለት የክርስቶስን በሥጋ መገለጥ እና አምላክነት ነግሯቸዋል (ማቴ.፫፥፩-፲፪፤ ሐዋ.፲፫፥፳፬-፳፰)። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” በማለት ታላቅ ምስክርነትን የሰጠ ሐዋርያ ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ከፈሪሳውያን ወገን የኾኑ ካህናትና ሌዋውያን ‹‹ስለ ራስህ ምን ትላለህ?›› ብለው በጠየቁት ጊዜም እርሱ ክርስቶስ እንዳልኾነና “የጌታን መንገድ አቅኑ” ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ቃለ ዐዋዲ (ዐዋጅ ነጋሪ) መኾኑን ተናግሯል (ሉቃ. ፫፥፲፭-፲፰፤ ዮሐ.፩፥፲፱-፳፫)። ቅድስት ኤልሳቤጥ “የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይኾንልኛል?” (ሉቃ.፩፥፵፫) ስትል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ መኾኗን እንደ መሰከረችው ኹሉ፣ ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችን ሊጠመቅ ወደ እርሱ በሔደ ጊዜ “እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል፤ አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ባሪያ ወደ ጌታው ይሔዳል እንጂ እንዴት ጌታ ወደ ባሪያው ይመጣል?” በማለት የጌታችንን አምላክነት በትሕትና ተናግሯል (ማቴ.፫፥፲፬)፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን “… ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለሁ፤ አንተንስ በማን ስም ላጥምቅህ?” ሲለው “እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሥልጣንህ ዘለዓለማዊ የኾነ የዓለሙ ካህን፤ የዓለምን ኃጢአት የምታስወግደው የእግዚአብሔር በግ፤ ብርሃንን የምትገልጽ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ይቅር በለን?” እያልህ አጥምቀኝ ብሎት እንደታዘዘው አድርጎ ጥር ፲፩ ቀን ጌታችንን አጥምቆታል፡፡ ቅዱስ ጌታችንን ባጠመቀው ጊዜ ከሰማይ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚለውን የእግዚአብሔር አብ ቃል መስማቱንና መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል መውረዱን በመመስከር ምሥጢረ ሥላሴን አስተምሯል (ማቴ.፲፯፥፭፤ ዮሐ.፩፥፴፬)፡፡

ሰማዕትነቱና ዕረፍቱ፡ በሕፃንነቱ ያለፈችውን የሰማዕትነት ጽዋ በሠላሳ ዓመቱ ተቀበላት፡፡

በመጨረሻም መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ “ድንበር አታፍርሱ፤ ዋርሳ አትውረሱ” እያለ ንጉሡ ሄሮድስንና ሄሮድያዳን በመገሠፁ ምክንያት አንገቱን በሰይፍ ተቈርጦ በሰማዕትነት ካረፈ በኋላ የራስ ቅሉ ክንፍ አውጥቶ በዓለም እየተዘዋወረ ፲፭ አምስት ዓመት ወንጌልን አስተምሯል፡፡ የሰማዕትነቱ ዜናም እንዲህ ነበር፡፡

“የሄሮድያዳ ልጅ ንጉሥ ሄሮድስን በዘፈኗ በጣም አድርጋ ስላስደሰተችው እርሱም በተራው ሊያስደስታት ፈለገ፡፡ ‹እስከ መንግሥቱ እኩሌታ ድረስም ቢሆን የለመነችውን ይሰጣት ዘንድ በሕዝቦቹና በመኳንንቱ ሁሉ ፊት እንዳይከዳት በፅኑ ቃልኪዳን ማለላት፡፡” እንዲህም እያለ ‘የፈለግሽውን ጠይቂኝ፣ የመንግሥቴንም እኩሌታ ቢሆን እሰጥሻለሁ ምን ላድርግልሽ?’ እያለ በመሐላ ባላት ጊዜ በእናቷ ምክር የዮሐንስን አንገት ቆርጦ ይሰጣት ዘንድ ለመነችው፡፡ ንጉሥ ሄሮድስም ይህን ልመና ከአፏ በሰማ ጊዜ ‹የፈለግሽውን እሰጥሻለሁ› ብሎ በሕዝቡ ፊት ስለማለ ለሰው ይምሰል አዘነ፣ ተከዘ፡፡ ኃዘኑም ስለ ዮሐንስ መሞት አይደለም፣ ዮሐንስን ሕዝቡ ይወደው ስለነበር እነርሱን ስለ መፍራቱና መሐላ ምሎ ከዳ እንዳይባል ነው እንጂ፡፡ ስለ ዮሐንስ አዝኖ ቢሆን ኖሮ ቀድሞውንም በግፍ እንዲታሰር ባላደረገው ነበር፡፡ ‹የለመንሽውን ሁሉ እሰጥሻለሁ› ብሎ ስለማለ ሄሮድስ የዮሐንስን አንገት እንድትቆረጥ አደረገ፡፡ መስከረም ፪ ቀን ሰማዕትነት የተቀበለበት ዕለት ነው፡፡

ከዚህ በኋላ ወታደሮች ሠይፍ ይዘው የዮሐንስን አንገት ይቆርጡ ዘንድ ወደ መኅኒ ቤት ሄዱ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም የሄሮድስ ጭፍሮች ሊገድሉት እንደመጡ በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ስላወቀ ከጨለማው ቤት ውስጥ አንገቱን በመስኮት አውጥቶ እንደሚመቻቸው አድርጎ ጠበቃቸው፡፡ የሄሮድስን ቃል እንዳያቃልሉ ጭፍሮቹም የመጥምቀ መለኮት ዮሐንስን አንገት ስለ መሐላው ቆረጡት፡፡ አስቀድሞ በሕፃንነቱ ስለጌታ ከተሰየፉት ሕፃናት መካከል በስደት ምክንያት ባይኖርም ከሠላሳ ዓመት በኋላ ግን እውነትን መስክሮ የሰማዕትነትን ጽዋ ተቀበለ፡፡  በመሐላ ምክንያት ባይሆን ኖሮ ሄሮድስ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ባላስገደለው ነበር፡፡ ስካርና ዘፈን ከሚገኙበት ቦታ አጋንንትና ኃጢአት ከዚያ አሉ፤ አለልክ መብላና መጠጣት ካለበት ቦታ እግዚአብሔርን መበደል፣ ማስቀየምና ማስቆጣት ይገኝበታል፡፡ ስካር ከሚገኝበት ቦታ አጋንንትና ኃጢአት ከዚያ አሉ፡፡ ስካርና ዘፈን ከሚገኝበት ቦታ የእግዚአብሔር መቅሰፍት የፈጣሪያችን ቁጣና በቀል ይፈጸምበታልና፡፡ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ያስገደለው ዘፈን፣ ስካርና የዘማ ፍቅር መሆኑን ልብ በማለት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ርጉም ሔሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በሁዋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት ደብረ ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች:: ቅዱሳን ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት:: ከዚሕ በሁዋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ስልጣን ሰጥቶ አሰናበታት:: በመላው ዓለም ለአሥራ አምስት ዓመታት ስትሰብክ ኑራ ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች:: የካቲት ፴ ቀን ራሱ የተገኘችበት፤ ሚያዝያ ፲፭ ቀን ራሱ ያረፈችበት (ነፍሱ የወጣችበት) ዕለት ነው፡፡ ሰኔ ፪ ቀን ደግሞ ፍልሰተ ዐፅሙ (ዐፅሙ የፈለሰበት) በዓል በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡

ስሞቹና ትርጉማቸው፡ ፍስሐ ወሐሴት፣ ጸያሔ ፍኖት፣ ቃለ ዓዋዲ… ይባላል፡፡

ዮሐንስ ማለት “እግዚአብሔር ጸጋ ነው” ማለት ነው፡፡ ትርጓሜ ወንጌልም መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ፍሥሐ ወሐሴት (ተድላና ደስታ) ይለዋል፤ ወላጆቹ በእርሱ መወለድ ተደስተዋልና (ሉቃ.፩፥፲፬)፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የቅዱሳኑ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ልጅ፣ በማሕጸን ሳለ መንፈስ ቅዱስ የሞላበት፣ በበርኀ ያደገና በገዳማዊ ቅድስና ያጌጠ፣ እሥራኤልን ለንስሃ ያጠመቀ፣ የጌታችንን መንገድ የጠረገ፣ ጌታውን ያጠመቀና፣ ስለ እውነት አንገቱን የተቆረጠ ታላቅ ሰው ነው:: ስለዚሕም ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስን ነቢይ፣ ሐዋርያ፣ ሰማዕት፣ ጻድቅ፣  ካሕን፣ ባሕታዊ/ገዳማዊ፣  መጥምቀ መለኮት፣ ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ)፣ ድንግል፣ ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ)፣ ቃለ አዋዲ (አዋጅ ነጋሪ)፣ መምሕር ወመገሥጽ፣ ዘየዐቢ እምኩሉ (ከሁሉ የሚበልጥ) ብላ ታከብረዋለች::

ስለዮሐንስ የተሰጠ ምስክርነት፡ እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፡፡

መጥምቁ ዮሐንስ በነብዩ በኢሳይያስ አስቀድሞ ቃለ ዓዋዲ ዘይሰብክ በገዳም፤ በምድረ በዳ የሚያስተምር የአዋጅ ነጋሪ ቃል ኢሳ. ፲፩ ፥ ፩ ተብሎ የተነገረለት ነው፡፡ ጌታችንም፡- “ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? … ነቢይን? አዎን ይህ ከነቢይም ይበልጣል። (እነሆ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ) ተብሎ የተጻፈለት እርሱ ነው፤ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው፤ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” በማለት የቅዱስ ዮሐንስን ታላቅነት ተናግሯል (ማቴ.፲፩፥፱-፲፩)።

ጌታችን በቅዱስ ወንጌሉ ስለ ዮሐንስ ሲናገር “ወዝንቱ ውእቱ ማኅቶት ዘየኃቱ ወያበርህ – እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ” ነው ያለው (ዮሐ ፭፡፴፭)፡፡ ዮሐንስን የሚነድና የሚያበራ ፋና (መብራት) ብሎ ገለጸው፡፡ ይህን ለጨለማው ዓለም ታላቅ ብርሀን ነበረ፡፡ እርሱ ሰማዕትነትን እየተቀበለ (እየነደደ) ለሌላው አበራ፡፡ ፀሐይ  በወጣ ጊዜ የፋናን ብርሀን የሚሻው እንደሌለ ጌታም ባስተማረ ጊዜ የዮሐንስን ትምህርት የሚሻው የለምና የዮሐንስን ትምህርት በፋና፣ የጌታን ትምህርት በፀሐይ መስሎ ተናገረ፡፡ በሌላም መልኩ ፋና ለመጣለት ነው የሚያበራው፡፡ ፀሐይ ግን ለሁሉም ነው፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ዮሐንስ ያስተማረው ለመጣለት ሕዝብ ነው፡፡ ጌታ ያስተማረው ለሁሉም ነውና የዮሐንስን ትምህርት በፋና፣ የጌታን ትምህርት ደግሞ በፀሐይ መስሎ አስተማረ፡፡

የመልክአ ዮሐንስ መጥምቅ ፀሐፊም  ከመላእክት፣ ከነቢያት፣ ከካህናት፣ ከሐዋርያት መካከል እንደርሱ መለኮትን ለማጥመቅ የተመረጠ አለመኖሩን በመጥቀስ “ዮሐንስ ከማከ ሶበ ፈተዉ ወጽሕቁ፤ እሳተ ነዳዴ ኢተክህሎሙ ያጥምቁ፤ ራጉኤል በትጋሁ ወኢዮብ በጽድቁ /ዮሐንስ ሆይ ራጉኤል በትጋቱ፣ ኢዮብም በጽድቁ ቢመኙም ሆነ ቢጨነቁ እንደ አንተ የሚነድ እሳትን (መለኮትን) ሊያጠምቁ አልተቻላቸውም/” ሲል መስክሮለታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ መስከረም ፩ ቀን ቃል ኪዳን የተቀበለበት ዕለት ነው፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ሕይወቱና ትምህርቱ፣ ያደረጋቸው ድንቆችና ተአምራት፣ እንዲሁም እግዚአብሔር የሰጠው ቃል ኪዳንና ሰማዕትነቱ በገድሉ በሰፊው ተጽፏል፡፡ በዚህች አጭር የአስተምህሮ ጦማር ክብሩን ለማስታወስ ያህል በጥቂቱ አቀረብን፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በቅዱስ ዮሐንስ ጸሎት ይማረን፡፡ በረከቱም ትጠብቀን፡፡አሜን!

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር፣ ትርጓሜ ወንጌል (ወንጌለ ሉቃስ)፣ ገድለ ዮሐንስ መጥምቅ፣ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ

ወርኃ ጳጉሜ፡ ሩፋኤል አሳድገን

ሩፋኤል

ጳጉሜ የሚለው ስያሜ “ኤፓጉሜኔ” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም “ጭማሪ” ማለት ነው ፡፡ በግእዝ “ወሰከ – ጨመረ” ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ተውሳክ (ተጨማሪ) ማለት ነው፡፡ ምዕራባዊያኑ ጳጉሜን የወር ተጨማሪ ቀን አድርገዋታል፡፡ እኛ ግን የዓመት ተጨማሪ ወር አድርገናታል፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ወርኃ ጳጕሜን የዓለም ፍጻሜ መታሰቢያ ተደርጋ ትታሰባለች፡፡ ይህም ጳጉሜ ከአሮጌው ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት፣ ከክረምት ወቅት ወደ ጸደይ መሸጋገሪያ እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ከጊዜያዊው ወደ ዘላለማዊ፣ ከምድራዊ ወደ ሰማያዊ፣ ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው መሸጋገሪያ ነትና ነው፡፡ ጳጉሜ የክረምቱ ማብቂያ እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም በመጨረሻው ዘመን መከራ የሚበዛበት የዚህ ዓለም ማብቂያ ናት፡፡ ወርኃ ጳጉሜ አዲሱን ዓመት ለመቀበል የዝግጅት ጊዜ እንደሆነች ሁሉ ምጽአትም ጻድቃል አዲሲቷን ምድር (መንግስ ሰማያትን) ለመውረስ ተዘጋጅተው “ኑ የአባቴ ብሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግስት ውረሱ” የሚባሉባት ናት፡፡

በዚህም የተነሣ ብዙ ምእመናን በጾምና በጸሎት (በሱባዔ) ያሳልፏታል፡፡ በተለይም በቅዱስ ሩፋኤል ዕለት ሰማያት የሚከፈቱበት (ርኅዎተ ሰማይ) መኾኑን በማመን ምእመናን የጸሎታቸውን ማረጊያ (ማሳረጊያ) መሆኑን በማመን ከምንጊዜውም በበለጠ በእምነት ይጸልያሉ፡፡ ርኅወተ ሰማይ የስሙ ትርጉም የሰማይ መከፈት እንደማለት ሲሆን በክርስቶስ ክርስቲያን የተባሉ ሁሉ ፀሎት፣ ልመናቸው ምልጃቸው የሚያርግበት ዕለት ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት የምእመናንን ልመና መስዋእቱን የሚያሳርጉበት እና የአምላካችንን ምህረት ቸርነት ለሰው ልጆች የሚያወርዱበት ዕለት ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ውኆች እንደሚባረኩ በሚረዳ ጽኑ እምነት ምዕመናን ወደ ወንዞች በመሔድና በሚዘንበው ዝናብ ይጠመቃሉ፡፡

በቅድስት ቤተክርስቲያን ካሉት ሁለት የፈቃድ አጽዋማት መካከል አንዱ በዚህ በጳጉሜ ወር የምንጾመው ጾመ ዮዲት ነው፡፡ የዮዲት ጾም የሚባለውም እርሷ ስለ ጾመችው ነው፡፡ የፋርስ ንጉስ ናቡከደነጾር በሠራዊቱ ተመክቶ ጠላት አጥፋ ድንበር አስፋ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበልህ ያላመነውን እያሳመንህ ና ብሎ ለጦር አበጋዙ ለሆሎፎርኒስ ትዕዛዝ ሰጠ (ዮዲ ፪፡-፪)፡፡ እርሱም እንደታዘዘው በኃይላቸው የታመኑ ፲፪ ሺህ እግረኞችንና በፈረስ የተቀመጡ ፲፪ ሺህ ጦረኞችን እየመራ ዘምቶ ካመነው እጅ መንሻ እየተቀበለ ያላመነውን እያሳመነ ብዙ ሀገሮችን እያጠፋ ሲሔድ ከአይሁድ ከተማ ደረሰ በዚህም ብዙ ጥፋት በመድረሱ የእስራኤል ልጆች አለቀሱ፡፡

ዮዲት ባለቤቷ ምናሴ ሞቶባት ከወንድ ርቃ ንጽሕናዋን ጠብቃ በጾም በቀኖና በሀዘን ተወስና ትኖር ነበር:: በተፈጠረው ጥፋት ህዝቡ ላይ ለመጣው መከራ ማቅ ለብሳ በራስዋ ላይ ትብያ ነስንሳ ወደ እግዚአብሔር አለቀሰች፡፡ የፍጥረቱን ጥፋት የማይሻ እግዚአብሔር አምላክም ሕዝቡን የሚያድኑበትን መንገድ ለመጠየቅ ሱባኤ በገባች በሦስተኛው ቀን ገለጸላት (ዮዲ ፰፡፪)፡፡ ከዚህ በኋላ ጠላታቸውን በዮዲት ምክንያት እስራኤላውያን እስከ ዮርዳኖስ እየተከተሉ አጥፍተዋቸዋል፡፡ ዮዲት ጠላቷን ለማጥፋት የቻለችው በጾምና በጸሎት ከእግዚአብሔር አምላክ ኃይል አግኝታ ነው፡፡ ስለዚህ ምዕመናን ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንንና ፈቃደ ሥጋን ለማሸነፍ በጾም ከፈጣሪያችን ኃይልን መጎናጸፍ አለብን ብለው ጳጉሜን በፈቃድ ይጾማሉ፡፡

በወርኀ ጳጉሜን ከሚታሰቡ እና ከሚከበሩ በዓላት መካከል በየዓመቱ ጳጕሜን ፫ ቀን የሚከበረው የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በታላቅነቱ በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ይከበራል፡፡ “ሩፋኤል” የሚለው የስሙ ትርጓሜ “ደስ የሚያሰኝ፣ ቸር፣ መሐሪ፣ ቅን የዋህ” ማለት ነው፡፡ በሌላም መልኩ ይህ የከበረ ታላቅ መልአክ ሰሙ የዕብራይስጥ ሁለት ቃላት ጥምረት ውጤት ነው፡፡ “ሩፋ” ማለት ጤና፣ ፈውስ፣ መድኃኒት ማለት ሲሆን “ኤል” ሚለው በሌሎቹም መላእክት ስም ላይ የሚቀጠል ስመ አምላክ ነው:: ይህም “መልአኬን በፊትህ እሰዳለሁ….. ስሜ በእርሱ ስለሆነ አታስመርሩት” (ዘጸ.23÷20-22) እንዳለው ነው፡፡ ታዲያ “ሩፋኤል” የሚለው በጥምረት “ከአምላክ ለሰዎች የተሰጠ ፈውስ” የሚለውን ይተካል፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን ስሙም ከሚካኤልና ከገብርኤል ቀጥሎ በሦስተኛ ደረጃ ይቀመጣል፡፡ “ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ” እንዲል (ጦቢት ፲፪፥፲፭)፡፡ ይህ መልአክ እንደሌሎቹ ሊቃነ መላእክት ሁሉ የሰው ልጆችን ይጠብቃቸዋል (ዳን.4÷13 ዘጸ. 23÷20 መዝ. 90÷11-13 ) ያማልዳል፣ ከፈጣሪ ያስታርቃቸዋል፡፡ (ሉቃ. 13፡6-9፣ ዘካ.1÷12) ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ያለ ማቋረጥ ፈጣሪያቸው ልዑል እግዚአብሔርን ከሚያመሰግኑ ቅዱሳን መላእክት አንዱ ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት አድርገው መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልን በሚከተሉት ሰባት አንኳር ነጥቦች ይገልጡታል፡፡

 ፈዋሴ ዱያን፡ ሕሙማንን የሚፈውስ

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህች ምድር ላይ እየተመላለሰ ሲያስተምር ድውያነ ሥጋን በተአምራት ድውያነ ነፍስን ደግሞ በትምህርቱ ይፈውስ ነበር፡፡ ለምሳሌ ለሠላሳ ስምንት ዘመን በአልጋ ላይ የነበረውን መጻጉዕን ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሄድ በማለት ከደዌው ፈውሶታል (ዮሐ ፭፡í-፲)፡፡ ማዳን (መድኃኒትነት) ለእርሱ የባህሪው ነው፡፡ የማዳንን ጸጋ ለቅዱሳን ሰጥቷል፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ድውያንን ሲፈውሱ የነበረው፡፡ ከቅዱሳን መላእክትም  ቅዱስ ሩፋኤል የሰው ልጆች ከተያዙበት የኃጢአት ቍስል ይፈወሱ ዘንድ በአማላጅነቱና በጸሎቱ የሚረዳ መልአክ ነው፡፡ “በበሽታ ዅሉ ላይ በሰው ልጆችም ቍስል ላይ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው” በማለት ሄኖክ ከእግዚአብሔር መልአክ ያገኘውን የምስክርነት ቃል ጽፏል (ሄኖክ ፲፥፲፫)፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል በሰውነታችን ላይ የሚወጣውን ደዌም ኾነ ቍስል ይፈውስ ዘንድ ከልዑል እግዚአብሔር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ “በሰው ቍስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው” እንዳለ ሄኖክ (ሄኖክ ፮፥፫)፡፡ ለቈሰሉ ፈውስን የሚያሰጣቸው መልአክ ነው፡፡ ዛሬም ሁላችንን በአማላጅነቱ ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ይፈውሰናል፣ ይጠብቀናልም፡፡

ፈታሔ ማኅፀን፡ ማኅፀንን የሚፈታ

በብሉያና በአዲስ ኪዳን ብዙ እናቶች ከመካንነት የተነሳ ሀዘን ጸንቶባቸው ቢቆይም ምንም የማይሳነው አምላክ እጅግ ድንቅን ያደረጉ የተባረኩ ልጆችን ሰጥቷቸዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የይስሐቅ እናት ሣራ፣ የያዕቆብ እናት ርብቃ፣ የዮሴፍ እናት ራሄል፣ የሶምሶን እናት እንትኩን፣ የነቢዩ ሳሙኤል እናት ሐና፣ የመጥምቀ መለኮት የዮሐንስ እናት ኤልሳቤጥ፣ የድንግል ማርያም እናት ሐና ይገኙበታል፡፡ እግዚአብሔር የመካኒቱን ማኅፀን ፈትቶ የተባረከ ልጅን የሚሰጥ አምላክ ነው፡፡ ይህንንም ጸጋ ለቅዱሳን መላእክት ሰጥቷል፡፡ ይህም ስልጣን ከተሰጣቸው ቅዱሳን መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል አንዱ ነው፡፡

የወላድ ማኅፀን እንዲፈታ ስለተሾመ ከጌታ አዋላጅ ብትኖር ባትኖርም ሐኪም ሩፋኤል አይታጣም በምጥ ጊዜ ሲጨነቁ ሴቶች ሁሉ የመልአኩን መልክ አንግተው ማርያም ማርያም ይላሉ ማየጸሎቱን ጠጥተው ቶሎ ፈጥነው ይወልዳሉ፡፡ የይስሐቅን እናት ሣራን፣ የሶምሶንን እናት (እንትኩይን) ምክነታቸውን የቆረጠ ወልዶ ለመሳም ያበቃቸው ይኸው ፈታሔ ማኅጸን የልዑል እግዚአብሔር መልአክተኛ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ለነፍሰጡር ሴቶች ረዳታቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ሴት በፀነሰችበት ወቅት ቅዱስ ሩፋኤል አይለያትም፡፡ ሕፃኑ (ኗ) በማኅፀን እያለ (ች) ተሥዕሎተ መልክዕ (በሥላሴ አርአያ መልኩ /ኳ/ መሳል) ከጀመረበት ቀን አንሥቶ እስከሚወለድበት ቀን ድረስ ቅዱስ ሩፋኤል በጥበቃው አይለያቸውም፡፡ በመውለጃቸው ቀን ሴቶች ከሚደርስባቸው ጭንቀትና ሕመም ስሙን ጠርተው ይማጸኑታል፡፡ ፈታሔ ማኅፀን ነውና ቅዱስ ሩፋኤልም ጭንቀታቸውን ያቀልላቸዋል፡፡ ሕጻናትን በእናታቸው ማኅፀን የሚጠብቃቸው እናቶችንም ከመፅነስ እስከ መውለድ የሚራዳቸው፣ የመካኖችንንም ማኅፀን የመፍታት ጸጋ የተሰጠው መልአክ ነው፡፡

ሰዳዴ አጋንንት፡ አጋንንትን የሚያሳድድ

ከጌታችን ሠላሳ ሦስት ታላላቅ ተአምራት ውስጥ አራቱ አጋንንትን ማስወጣት ነበሩ፡፡ ይህ ስልጣን ለቅዱሳን ሰዎችና መላእክት በጸጋ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ቅዱስ ሩፋኤልም በተሰጠው ስልጣን አጋንንትን የሚያሳድድ መልአክ ነው፡፡ አስማንድዮስ የተባለ ጋኔን በሣራ (ወለተ ራጉኤል) ላይ አድሮ ባሎቿን እየገደለ ቢያሰቃያት ቅዱስ ሩፋኤል ጋኔኑን አስጨንቆ አስወጥቶላታል (ጦቢት ፫፥፰-፲፯)፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል “ዳግመኛም እግዚአብሔር ሩፋኤልን፣ አዛዝኤልን እጁን እግሩን አስረህ በጨለማ ውስጥ ጣለው አለው” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሄኖክ ፫፥፭-፯) ለቃየን ልጆች ሰይፍና ሾተል መሥራትን፣ የምንዝር ጌጥ ማጌጥን፣ መቀንደብን ያስተማረ አዛዝኤል የተባለውን ጋኔን በእሳት ሰይፍ እየቀጣ በረቂቅ አስሮ ወደ ጥልቁ የጣለው ይኸው መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ነው (ሄኖክ ፪፥፲፰)፡፡ ዛሬም ከእግዚአብሔር ተልኮ ለሰው ልጆች የተንኮልን፣ የጥላቻን፣ የመገዳደልን ሀሳብ እንዲያፈልቁ የሚያደርገውን የመልካም ነገር ጠላት የሆነውን ጠላታችንን አስጨንቆ የሚያባርር መልአክ ነው፡፡

አቃቤ ኆኅት፡ የምህረትን ደጅ የሚጠብቅ

ቅዱሳን መላእክት የሰውን ልጅን ጸሎት ከምድር ወደ ሰማይ የእግዚአብሔርን ምህረት ደግሞ ከሰማይ ወደ ምድር የሚያደርሱ መልእክተኛች ናቸው (ራዕ ፰፡፪)፡፡ ቅዱስ ሩፋኤልም ስለራሱ ማንነት በሰጠው ምስክርነት የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ ከበረ ወደ ገነነ ወደ እግዚአብሔር ጌትነትም ከሚያገቡ ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ አላቸው” (ጦቢት ፲፪፥፲፭)፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ሩፋኤል መዝገበ ጸሎት እና አቃቤ ኆኅት ይባላል፡፡ ከዚህ ጋርም በቅዱስ ሩፋኤል ተራዳዒነት ከተደረጉ ተአምራት መካከል በእስክንድርያ አቅራቢያ በምትገኝ ደሴት በታነጸች ቤተ ክርስቲያኑ ያደረገው ተአምር አንደኛው ነው፡፡ በመጽሐፈ ስንክሳር እና በድርሳነ ሩፋኤል እንደ ተጻፈው በሊቀጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን አባቶች ለሊቀመናብርቱ ክብር በአሣ አንበሪ ጀርባ ላይ ያሳነጹትን መታሰቢያ ቤተ መቅደስ በወደቡ አጠገብ በእስክንድሪያ ነበረች፡፡

ብዙ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያሉ ጠላት ዲያቢሎስ አነዋውጾ ለምስጋና የታደሙትን ምዕመናን ሊያጠፋ አሣ አንበሪውን ቢያውከው ቤተክርስቲያኒቱ ፈጽማ ተናወጠች፤ ያቺ ደሴት በታላቅ አንበሪ ጀርባ ላይ የቆመች ናትና፡፡ የሰዎች ብዛትም በከበደው ጊዜ ዓሣ አንበሪው ቤተ ክርስቲያኒቱን ያፈርሳት ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው፡፡ ምእመናኑም ወደ ክብር ባለቤት እግዚአብሔር በከበረ መልአክ ሩፋኤል ስም ጮኹ፡፡ ያን ጊዜ ቅዱስ ሩፋኤል ያንን አንበሪ በበትረ መስቀሉ (ዘንጉ) ገሥጾ “እግዚአብሔር አዝዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጥ ጸጥ ብለህ ቁም!” ባለው ጊዜ አንበሪው ጸጥ ብሎ ቆሟል፡፡ ምዕመናኑንም ከጥፋት ታድጓቸዋል፡፡

መራኄ ፍኖት፡ መንገድ መሪ

ጦቢት በፋርስ ንጉሥ በስልምናሶር ዘመን የተማረከ ከነገደ ንፍታሌም የተወለደ ጽኑዕ እሥራኤላዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር በስልምናሶር ፊት የመወደድን ግርማና ባለሟልነትን ስለ ሰጠው አለቃ አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ ለወገኖቹ ምጽዋት በመስጠት ሕገ ርትዕን በመሥራት የተጋ ሰው ነበር፡፡ ሐና የምትባል ሚስት አግብቶ አንድ ልጅ ወልዷል፡፡ ስልምናሶር ሞቶ ሰናክሬም በነገሠ ጊዜ ከሹመቱ ስለሻረው ደግሞ ወደ ምድያም መሔድ አልቻለም፡፡

ሣራ ወለተ ራጉኤል ከፍተኛ ችግር ደርሶባት ነበር፡፡ ችግሯም ሕፃናት ወልጄ ቤት ንብረት ይዤ እኖራለሁ በማለት ባል አገባች ነገር ግን በዚች ሴት አስማንድዮስ የሚባል ጋኔን አድሮ ያገባችውን ሰው ገደለባት ሌላም ባል ብታገባ ሞተባት እንደዚህ እየሆነ በጠቅላላ ሰባት ድረስ ያሉትን ባሎችን ገደለባት፡፡ የራጉኤል ልጅ ሣራ በዚህ ሁኔታ በኀዘን ተውጣ ስትኖር በነበረበት ጊዜ ጦቢት ሸምግሎ ስለ ነበር ልጁ ጦብያን ጠርቶ በዚህ ዓለም እስካለ ድረስ ሊሠራው የሚገባውን መንፈሳዊ ሥራ እንዲሠራ በጥብቅ ከመከረው በኋላ በመጨረሻ ልጄ እኔ ሳልሞት የኑሮ ጓደኛህን ፈልግ፣ ስትፈልግም ዕወቅበት፣ እኛ የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ ዘሮች ነን ስለዚህ ከእነርሱ ወገን የሆነችውን እንድታገባ ከዚህም ሌላ ከገባኤል ዘንድ በአደራ ያስቀመጥኩት ገንዘብ አለና እኔ በሕይወት እያለሁ ብታመጣው የተሻለ ነው አለው፡፡

“በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ (ዘጸ ፳፫፡፳)።” ተብሎ ለመላእክት ሰውን መንገድ የመምራትና የመጠበቅ ስልጣን እንደተሰጣቸው የጦቢትን ልጅ ጦቢያን ከነነዌ የሜዶን ክፍል ወደ ምትሆነውና ራጌስ ወደምትባለው ሀገር ሲሄድ አዛርያስ  (ቅዱስ ሩፋኤል) በመንገድ ይመራው ነበር፡፡ በዚህም ቅዱስ ሩፋኤል መራኄ ፍኖት (መንገድ መሪ) ይባላል፡፡ ጦቢያና አዛርያስ ሲሄዱ ውለው ማታ ጤግሮስ ከተባለው ታላቅ ወንዝ ደረሱና ከዚያም ለማደር ወሰኑ፡፡ በዚህ ጊዜ ከድካሙ ጽናት የተነሣ ጦብያ ሊታጠብ ወደ ወንዙ ወረደና ልብሱን አውልቆ መታጠብ ሲጀምር አንድ ዓሣ ሊውጠው ከባሕር ወጣ፡፡ ወዲያውም መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን ያዘው፤ ዓሣውን እንዳትለቀው አለው፤ ጦቢያም ከዓሳው ጋር ግብ ግብ ገጥሞ እየጐተተ ወደ የብስ አወጣው፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሩፋኤል ጦብያን እንዲህ ሲል አዘዘው፡፡ ዓሣውን እረደው ጉበቱንና ሐሞቱን ተጠንቅቀህ ያዘው ሌላውን ግን ጠብሰን እንበላዋለን አለው፡፡ ዛሬም በመንገዳችን እንዲመራን በጉዞአችንም ፈተና ሲገጥመን እንዲራዳን መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልን ሊልክልን አምላካችን የታመነ ነው፡፡

መልአከ ከብካብ: ጋብቻን የሚባርክ መልአክ

የራጉኤል ልጅ ሣራ ሰባት ሰዎች አግብተዋት ሰባቱም ባገቧት ሌሊት ደርቀው /ሞተው/ አድረዋል፡፡ ይህንንም ከነነዌ ወደ ራጌስ የመጣው የጦቢት ልጅ ጦቢያ ያውቅ ነበር፡፡ ለአዛርያስም “ስለዚህ እኔ ላባቴና ለእናቴ አንድ ልጅ ነኝ እርስዋን አግብቼ ከዚህ በፊት እንዳገቧት ሰዎች እኔም የሞትኩ እንደሆነ አባቴንና እናቴን የሚረዳቸው የለም ቢሞቱም የሚቀብራቸው አያገኙምና እፈራለሁ” አለው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ግን ‹አባትህ ከዘመዶችህ ወገን ካልሆኑ በስተቀር ሌላ ሴት እንዳታገባ ሲል የነገረህን ረሳኸውን? በል ሰባት ባሎቿ ሙተውባታል ስለምትለው እኔ መድኃኒቱን አሳይሃለሁ ፤ አይዞህ አትፍራ አትሞትም የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ለምን ያዘው ያልኩህ ለምን ይመስልሃል? እንግዲህ ሐሞቱንና ጉበቱን ከዕጣን ጋር ጨምረህ ስታጤስበት በሣራ አድሮ የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ወጥቶ ይሄዳል ፈጽሞም ወደ እርሷ በገባህም ጊዜ ሁለታችሁ ይቅር ባይ ወደ ሆነው እግዚአብሔር ጸልዩ እርሷም የተዘጋጀች ናት፡፡ ከእኛ ጋርም ወደ ሀገርህ ይዘናት እንሄዳለን› አለው፡፡ ጦብያም ይህንን ቃል በሰማ ጊዜ ደስ አለውና ከእርሷ በስተቀር ሌላ እንዳያገባ በሙሉ አሳቡ ወሰነ፡፡

ከዚህ በኋላ ወደ ራጉኤል ቤት እንደ ደረሱ ሣራ በደስታ ተቀበለቻቸው የሣራ አባትም ጦብያን ገና እንዳየው ሚስቱ አድናን “ይህ ልጅ የእኔ ዘመድ ጦቢትን ይመስላል” አላት ከዚያም ጋር አያይዞ “ልጆች ከየት ሀገር መጣችሁ?” አላቸው፡፡ እነሱም “ከነነዌ ሀገር ነው የመጣን” አሉት፡፡ “ከዚያም ሀገር ጦቢት የሚባል ወንድም ነበረኝ ታውቁት ይሆን?” ሲል ጠየቃቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ጦቢያ አባቱን ሲጠራለት “እናውቀዋለን፡፡ እኔም ራሴ የጦቢት ልጅ ነኝ” አለው፡፡ ከዚያ በኋላ ራጉኤል “የወንድሜ ልጅ ነህን?” ብሎ እቅፍ አድርጐ ሳመው፡፡ አድናም ሳመችውና ሁሉም ተያይዘው የናፍቆት ልቅሶ ተላቀሱ፡፡ ከወንድሙ እንደ መጡም ሲገነዘብ በግ አርዶ በጥሩ ሁኔታ ጋበዛቸው፡፡

እራትም ከበሉ በኋላ ጦብያ ቅዱስ ሩፋኤል በመንገድ የነገረውን በልቡ ሲያወጣ ሲያወርድ ስለ ዋለ ቅዱስ ሩፋኤልን ያንን በመንገድ የነገርከኝን አሁን ፈጽምልኝ ሲለው ሰምቶ ስለ ልጅቷ መሆኑን ስለ ገባው ራጉኤል ጦብያን ‹ልጄ ይህች ልጅ ላንተ የምትገባ ናት ሰጥቸሃለሁ አይዞህ አትጠራጠር አሁንም ብላ ጠጣ ለዛሬም ደስ ይበልህ አለውና ሣራ ካለችበት የጫጉላ ቤት አግብተው ዘጉት፡፡ ጦብያም ሣራን በይ እኅቴ ኑሮዋችን እንዲቃናልንና ጋብቻችን እንዲባረክልን አስቀድመን ወደ ፈጣሪያችን ጸሎት እናድርግ› አላትና አብረው ጸሎት ካደረጉ በኋላ ያንን የያዘውንና የዓሣ ጉበትና ሐሞት ከዕጣን ጋር ጨምሮ ቢያጤስበት በሣራ አድሮ ባሎችዋን ይገድልባት የነበረው አስማንድዮስ የተባለው ጋኔን ከሣራ ለቆ ወጥቶ ሄደ ሁለተኛም ሊመለስ አልቻለም፡፡ እነርሱም በሰላምና በጤና አደሩ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያምና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተገኝቶ በዶኪማስ ቤት የነበረውን ሠርግ ባርኮታል፡፡ የወይን ጠጅ ቢያልቅባቸውም ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ ለውጦ ቤቱን በበረከት ሞልቶታል (ዮሐ ፪፡í)፡፡ ቅዱሳንም ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ጸጋ ጋብቻን በጸሎታቸው ይባርካሉ፡፡ በመሆኑም  የጦብያንና የሣራን ጋብቻ የባረከ ቅዱስ ሩፋኤል ስለሆነ መልአከ ከብካብ ይባላል፡፡ ዛሬም በምልጃው ላመኑት ጋብቻን ይባርካል፣ ትዳርንም ያጸናል፡፡

ከሳቴ እውራን፡ ዓይነ ስውራንን የሚያበራ

ራጉኤልና ሐና የሣራንና የጦቢያን የጤንነታቸውን ነገር ሲረዱ የሰርጉ ቀን የሚሆን የአሥራ አራት ቀን በዓል እስኪፈጸም ድረስ ጦብያ ወደ ሀገሬ እሄዳለሁ ብሎ እንዳያውከው በማለት አማለው፡፡ የአሥራ አራት ቀን በዓለ መርዓ ከተፈጸመ በኋላ ግን ጥሬ ገንዘብና የከብት ስጦታ አድርጐ መርቆ ወደ ሀገሩ ሰደደው፡፡ ወላጆቹ ጦቢትና አድና ግን በመዘግየቱ ልጃችን ምን አግኝቶት ይሆን? እያሉ ለጊዜው ሳያዝኑ አልቀሩም፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሚስቱንና ግመሎቹን ይዞ ሲመጣ በክብርና በደስታ ተቀበሉት፡፡ የጦብያ አባት ጦቢትም ልጅህ መጣ ሲሉት ዓይነ ሥውር ስለ ነበር እርሱን እቀበላለሁ ሲል ስለ ወደቀ ወዲያው ጦብያ የዓሣውን ሐሞትና ጉበቱን ይዞ ስለ ነበር የአባቱን ዓይን ቀባው ወዲያውም ዓይኖቹ ተከፈቱ፡፡ በምራቁ አፈር ለውሶ በደረቅ ግንባር ላይ ዓይንን የሚሠራው እግዚአብሔር (ዮሐ ፰) በመልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል አማካኝነት የጦቢያን አባት የጦቢትን ዓይን በራለት፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል ዛሬም በምልጃው ለሚያምኑት ሥጋዊ ዓይንና መንፈሳዊ ዓይንን (ዓይነ ልቡናን) የሚያበራ መልአክ ነው፡፡

ማጠቃለያ

በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የበዓላት ቀኖና መሰረት ወርኃ ጳጉሜ የዕለተ ምጽአት መታሰቢያ ተደርጋ ትታሰባለች፡፡ በወርኃ ጳጉሜ የአሮጌውን ዘመን የኃጢአት ቆሻሻ በንስሃ አጥበን ከዕለተ ምጽዓት በኋላ ለምትገለጠው የእግዚአብሔር መንግስት ምሳሌ ለሆነ አዲስ የምህረት ዓመት እንዘጋጅባታለን፡፡ የታደሉትም በፈቃድ ጾምና በሱባኤ እንደሚያሳልፏት ይታወቃል፡፡ በወርኃ ጳጉሜ በገናንነት የሚከበረው የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል በዓል የአሮጌው ዘመን በዓላት መዝጊያ ለአዲሱ ዘመን ርዕሰ አውደ ዓመት ለቅዱስ ዮሐንስ በዓልም መሸጋገሪያ ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የሊቀ መልአኩን የቅዱስ ሩፋኤልን በዓል በማሰብ በወርኃ ጳጉሜ ውኆች እንደሚባረኩ በእምነት በመረዳት “ሩፋኤል አሳድገን (እርዳን፣ ጠብቀን)” እያልን በሃይማኖት እንጠራዋለን፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን በመጽሐፈ ጦቢት፣ በመጽሐፈ ሄኖክ፣ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በጻፈው አክሲማሮስ በተባለው መጽሐፍና በድርሳኑ ላይ እንደተገለጠው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ጸጋ ድውያነ ሥጋንና ድውያነ ነፍስን የሚፈውስ፣ የሚካኒቱን ማኅፀን የሚያለመልም፣ ሕጻናትንም በእናታቸው ማኅፀን ሳሉ የሚጠብቃቸው፣ የክፋት አባት የሆነውን ጠላት ሰይጣንን የሚያሳድድ፣ በመንገድ ያሉትን የሚመራ፣ ምህረትን ለሚሹ ፈጥኖ የሚደርስ፣ በጋብቻና በትዳር የሚፈተኑትን የሚረዳ መልአክ ነው፡፡ የሊቀ መልአኩ የቅዱስ ሩፋኤል ጸሎትና አማላጅነት ልጅ በማጣት ለተጨነቁ መልካም ፍሬን፣ ለተወለዱት በሃይማኖት ማደግን፣ ለታመሙት ፈውስን፣ ለባለትዳሮች እግዚአብሔር የሚደሰትበት ትዳርን እንዲሰጥልን የሰራዊት ጌታ የአምላካችን እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ አሜን ሩፋኤል አሳድገን፡፡