ጌታችን በተራራው ስብከቱ የመጀመሪያውን ሕገ ወንጌል ሲያስተምር “ለቀደሙት አትግደል እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል” በማለት ከሕገ ኦሪት ነው የጀመረው (ማቴ 5:21-26)። “አትግደል” የሚለው ከአሠርቱ ትዕዛዛት አምስተኛው ሲሆን በሐዲስ ኪዳንም የጸና ሕግ ነው። ስለሆነም የገደለ (ሰውን የገደለ ወይም በመግደል የተሳተፈ) ፍርድ ይገባዋል። አዎን እግዚአብሔር በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረውን ሰው የገደለ ፍርድ ይገባዋል። ፍርዱም ምድራዊም (በምድራዊው ፍርድ ቤት) ሰማያዊም (የእግዚአብሔር መለኮታዊ ፍርድ) ነው። ግድያን ያስቻለ፣ የተባበረ ወይም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፈ እንዲሁም ማስቀረት ወይም መከላከል እየቻለ በቸልተኝነት ኃላፊነቱን ያልተወጣም ይጠየቃል። ሆኖም ሕገ ኦሪት ውጫዊ የሆነ አካላዊ ጥቃት (Physical violence) ከአካላዊ ጥቃትም የመጨረሻ ደረጃ የሆነው መግደል (homicide) ላይ የሚያተኩር ስለነበር ፍጹም ሕግ አልነበረም። ይህ ሕገ ኦሪት ከመግደል በመለስ ያሉት አካላዊ፣ ስነልቦናዊ፣ አእምሮአዊና ማኅበራዊ ጥቃቶች ላይ አያተኩርም ነበርና ፍጹም አልነበረም። አንድም ፈሪሳውያን ይናገሩታል፣ ይሰሙታል እንጂ ስለማይጠብቁት ወደ ጽድቅ አላደረሳቸውም ነበር። ስለዚህም ጌታችን አስቀድሞ “ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ካልበለጠ ወደ መንግሥተ ሰማያት አትገቡም” ብሏልና ጽድቃችን ከፈሪሳውያን እንዲበልጥ ይህ ሕግ ፍጹም ሊሆን ይገባዋል። ይህም የሚሆነው በሀሳብ (በሀልዮ)፣ በንግግር /በመናገርና በመጻፍ/ (በነቢብ) እና በድርጊት/በተግባር (በገቢር) የሚፈጸመውን ሁሉ ሲያካትት ነው።
ቁጣ (Anger) የአእምሮአዊም የአካላዊም ጥቃት መነሻ ዘር (seed) ነው።
ጌታችን “እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ በከንቱ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል” በማለት አትግደል የሚለውን ሕግ ጥልቅ፣ ጥብቅና ፍጹም አደረገው። በሲና ተራራ ሕገ ኦሪትን በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤል የሰጠ ራሱ እግዚአብሔር ዛሬም በተራራው ስብከቱ ሕጉን ፍጹም ሊያደርገው “እኔ ግን እላችኋለሁ” አለ (ማቴ 5:21-26)። የሕግ ምንጭ፣ የሕግ መገኛ፣ መምህረ ሕግ እርሱ ነውና። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው ጌታችን “እኔ ግን እላችኋለሁ” ሲል “የቀደመውን ሕግ ከመምህራነ ኦሪት ሰምታችኋል፣ እኔ ግን የሕጉን ስፋትና ጥልቀት እንዲሁም ፍጹምነት እገልጥላችኋለሁ” ማለቱ ነው። “እኔ ግን እላችኋለሁ” የምትለው ሐረግ ውስጥ ያለችው “ግን” የምታሳየው የኦሪቱን ሕግ መሻር ሳይሆን ወደ ፍጹምነት መሸጋገር ነው። የቀደሙት መምህራነ ኦሪት “አትግደል” ብለው ስለአካላዊ ጥቃት አስተምረዋል፣ እናንተም ያንን ሰምታችኋል፣ እኔ ግን እላችኋለሁ ፍጹም ትሆኑ ዘንድ ከአእምሮአዊና ከስነልቦናዊ ጥቃት ጭምር ተከልከሉ ሲለን ነው።
የመግደል ኃጢአት ዘሩ (መጀመሪያው) በወንድም ወይም በእኅት ላይ መናደድና መቆጣት ነው። መቆጣት የገነፈለ (aggressive)፣ የታፈነ (suppressed/passive) ወይም በአግባቡ የተገለጠ (assertive) ሊሆን ይችላል። ኃጢአትን ከሥሩ (ከመነሻው) ለመንቀል ቁጣን መተው ይገባል። ነገር ግን ቁጣ ሁለት አይነት ነው። ለበጎ ከመቅናት ወይም ከቁጭት የሚመነጭ ቁጣ አለ። ለምሳሌ ሕግ ተጣሰ፣ ሥርዓት ፈረሰ፣ ደኃ ተበደለ፣ ፍርድ ተጓደለ ብሎ መቆጣት ለመልካም ለውጥ ሊያነሳሳ ይችላል። የዚህ ዓይነቱ ቁጣ ማንንም በማይጎዳ መልክ ከተያዘ ለበለጠ ሥራ ያስጨክናል። ነገር ግን ምንም በጎ አመክንዮ የሌለው ከንቱ ቁጣ ከክፉ ቅናት፣ ከጥላቻ፣ ለመጉዳት ከመሻት ይመነጫል። እንዲህ አይነቱን ቁጣ ነው ጌታችን “በወንድሙ ላይ በከንቱ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል” ያለው። ይህ አይነቱ ቁጣ ወንድምን መታደግን ሳይሆን ወንድምን መጉዳትን ዒላማ ያደረገ ቁጣ ነው። ስለዚህ ለቃላዊ ጥቃት (ስድብ) እና አካላዊ ጥቃት (ድብደባ) ዘር ስለሆነ ከልባችን ልናስወግደው ይገባል።
ስለዚህም ነው ክቡር ዳዊት አስቀድሞ “ከቁጣ ራቅ መዓትንም ተው፤ እንዳትበድል አትቅና (መዝ 37:8)” በማለት የተናገረው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም “ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት (ኤፌ 4:26-27)” በማለት ቁጣን በፍጥነት አለመግታት ለዲያብሎስ ፈንታ መስጠት መሆኑን አስተምሯል። እንዲሁም “አሁን ግን እናንተ ደግሞ ቍጣንና ንዴትን ክፋትንም፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ (ቆላ 3:8)” በማለት እንድናስወግደው አስተምሯል። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም “ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤ የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና (ያዕ 1:19-20)” በማለት ቁጣ ኃጢአትን እንጂ ጽድቅን እንደማይሠራ ተናግሯል። ሰዎች ቢያናድዱን እንኳ የስነልቦና ባለሙያዎችም እንደሚነግሩን (Control your emotions, and do not let your emotions control your actions) ስሜታችንን ልንቆጣጠረው ይገባል እንጂ ስሜታችን ሊቆጣጠረን አይገባም።
በአዕምሮ ጤና ጉድለት (mental health disorder) ምክንያት የሚደረገውንና በነፃ ፈቃድ የሚፈፀም ኃጢአትን ለይተን ማወቅ ይኖርብናል። ኃጢአት የስነምግባር ውድቀት (moral failure) ነው። አንድን ድርጊት የስነምግባር ውድቀት የሚያደርጉት ዕውቀት (knowledge) (ድርጊቱ ትክክል እንዳልሆነ ማወቅ)፣ ዓላማ (Intention) (ድርጊቱን እንዲጎዳ አስቦ ማድረግ) እና ነፃነት (Freedom) (በነፃ ፈቃድ ወስኖ ማድረግ) ናቸው። አዳም ዕፀ በለስን ሲበላ “አትብላ” የተባለውን ሕግ ያውቅ ነበር። ይህንን ሕግ መተላላፍም ሞትን እንደሚያስከትል ያውቅ ነበር። የበላበትም ዓላማ ሌላ የሚበላው ነገር አጥቶ ተርቦ ሳይሆን አምላክ ለመሆን ነበር። የበላውም ማንም ሳያስገድደው በራሱ ነፃ ፈቃድ ነበር። ዲያብሎስም መከራቸው እንጂ አስገድዶ አላበላቸውም፣ ቀጥፎም አላጎረሳቸውም። ዛሬም እንዲሁ ነው። አውቀን፣ አልመንና በነፃ ፈቃዳችን ወስነን የምናደርገው ኃጢአት ለፍርድ ይዳርገናል። በአዕምሮ ጤና ጉድለት ያለበት ሰው የሚያደርገው ከዚህ ተለይቶ መታየት ይኖርበታል። ትኩረታችንም የአእምሮው ጤንነት እንዲመለስ/እንዲሻሻል ማድረግ ላይ ሊሆን ይገባል። ዘመናዊ ህግም በአእምሮአዊ ጤንነታቸው ጉድለት የተነሳ የወንጀል ኃላፊነት ስለማይኖርባቸው ሰዎች ያስረዳናል።
በሰው ችሎታ (Intelligence) ላይ የሚሰነዘር ስድብ ፍርድን ያመጣል።
ቁጣ ገና በልባችን ሳለ በቶሎ ካልተገታ አድጎ መጥፎና ሰውን የሚጎዱ ቃላትን ወደ መናገር (መሳደብ – Verbal Abuse) ያደርሳል። ስድብም በሰው ላይ ስነልቦናዊና አእምሯዊ ጉዳትን የሚያደርስ ጥቃት ነው። ስድብ የሚባለው በሌላ አገላለጽ ሰውን በቃላት ማጥቃት (መውገር) ነው። ስድብም ከንቀት (contempt)፣ ከበቀል ፍላጎት (Revenge)፣ ከትዕቢትና (pride/arrogance) ከጥላቻ (hate) ይመነጫል። ጌታችን ስለመጀመሪያው ደረጃ ስድብና ውጤቱ ሲያስተምር “ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል” በማለት ነው። በአማርኛ ‘ጨርቃም’፣ በግእዝ ‘ኅሡር ዘፀርቅ’ ተብሎ የተገለጸው ቃል ጥንተ ቃሉ “ራካ (Raca)” ሲሆን የአረማይክ ቃል ነው። ቀጥታ ትርጉሙም ዕውቀት፣ ችሎታ፣ ክህሎት፣ ጥበብ የሌለው ማለት ነው። ይህም ሰው ተምሮ ሊያውቀው፣ ሠርቶ ሊያዳብረው የሚችለውን ሥጋዊ ጥበብን የሚመለከት ነው። ለዚህም ነው ለዚህ ዓይነቱ ኃጢአት ፍርዱ የሰው ፍርድ (የሸንጎ ፍርድ፣ የዐውድ ፍርድ) የሆነው። የተሰደበው (ለጉዳት የተጋለጠው) የሥጋ ጥበብ ነውና የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል የተባለው። በዚህም ፍርድ የበደለው (ሰውን የተሳደበው) አካል ኃጢአቱን በንስሐ፣ በደሉን በካሳ (የተፈረደበትን ቅጣት በመቀበል) ሊቋጨው ይገባል።
“አንድን ቃል ስድብ የሚያደርገው ምንድን ነው?” ብለን እንጠይቅ ይሆናል። በመጀመሪያ አንድን ቃል ስድብ የሚያደርገው ተናጋሪው የሚናገርበት ዓላማ (Intention) ነው። ሰውን ለመጉዳት፣ ለማሳነስ፣ ለማጥቃት፣ ለማግለል ታስቦ የሚነገር ማንኛውም ቃል ስድብ ነው። ይህም ጌታችን “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና (ማቴ 12:34)” እንዳለው ቃል በልብ ያለውን ስለሚገልጽ ነው። በሁለተኛ ደረጃ አንድን ቃል ስድብ የሚያደርገው ሰሚው የሚረዳበት መንገድ (Perception/Interpretation) ነው። የተናጋሪው ዓላማ ምንም ይሁን ምን ሰሚው ቃሉን የሚጎዳ አድርጎ ከተረዳው ያ ቃል ስድብ ነው። ጠቢቡ ሰሎሞን “ከሰው አንደበት የሚወጣ ቃል እንደሚዋጋ ሰይፍ ነው” እንዳለው (ምሳ 12:18) ከአፋችን የሚወጣ ቃል ለሚሰማው አዕምሮን የሚያቆስል ሊሆን ይችላል። ስለዚህ መናገራችንን ብቻ ሳይሆን የሚሰሙን እንዴት ይረዱታል የሚለውን ማጤን ይገባናል። በሦስተኛ ደረጃ ማኅበረሰቡ ቃሉን የሚበይንበት መንገድ/በማኅበረሰቡ የሚሰጠው ትርጉም (community norm) ነው። አንድ ቃል ማኅበረሰቡ የሚሰጠው ሞራላዊ ትርጉም አሉታዊ (negative/derogatory) ከሆነ ስድብ ነው።
ትችትንና (criticism) ስድብን ማምታታት የለብንም። ስድብንም ትችት ነው እያልን ራሳችንን ማታለል የለብንም። ትችትና ስድብ በትኩረት (focus)፣ በዓላማ (objective) እና በውጤት (outcome) ይለያያሉ። የትችት ትኩረት ፀባይ (behavior)፣ ሂደት (Process/activity)፣ ወይም ውጤት (product) ላይ ነው። ዓላማውም ድክመቶችንና ጠንካራ ጎኖችን በማመላከት እንዲሻሻል መርዳት ነው። ውጤቱም የተሻለን ፀባይ፣ ሂደት ወይም ውጤትን ማየት ነው። የስድብ ትኩረት ግን ሰው ነው። ዓላማውም ሰውን በቃላት መሣርያነት ማጥቃት (መጉዳት) ነው። ውጤቱም ጥል፣ መለያየትና ግጭት እንዲሁም ሞት ናቸው። ትችትን የበለጠ ለመረዳት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቅዱስ ጴጥሮስ (ኬፋ) ድርጊት ላይ ያቀረበው ትችት ጥሩ ምሳሌ ይሁነን (ገላ 2:11-14)። የስድብን ውጤት ለማወቅ ደግሞ ነቢዩ ኤልሳዕ ከቤቴል ሲወጣ የሰደቡት ብላቴኖች የደረሰባቸውን ማስታወስ በቂ ነው (2ኛ ነገሥት 2:22 )።
ክቡር ዳዊት “አቤቱ፥ ለአፌ ጠባቂ አኑር፥ የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ (መዝ 141:3)” በማለት ጸሎትን ያቀረበው እግዚአብሔር ከእንደዚህ ዓይነቱ ኃጢአት ይጠብቀው ዘንድ ነው። ጠቢቡ ሰሎሞንም “ሰነፍ ሰው ቍጣውን ሁሉ ያወጣል፤ ጠቢብ ግን በውስጡ ያስቀረዋል (ምሳ 29:11)” በማለት በተናደድን ጊዜ ራሳችንን መቆጣጠር እንደሚገባን ነገሮናል። እንዲሁም “በነፍስህ ለቍጣ ችኩል አትሁን ቍጣ በሰነፍ ብብት ያርፋልና (መክ 7:9)” በማለት ይመክረናል። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም “ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ..መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ (ኤፌ 4:29-31)” ብሎ ያስተማረው በቃላችን ሰውን ልናንጽበት እንጂ ሰውን ልንጎዳበት እንደማይገባ ሊያስገነዝበን ነው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስም “ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና። ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል (1ኛ ጴጥ 3:9-10)” በማለት ብንሰደብ እንኳን መልሰን መሳደብ እንደማይገባ አስተምሯል። ፍጹም ምሳሌያችን የሆነው ክርስቶስ ሲሰድቡት አልተሳደበምና (1ኛ ጴጥ 2 ፡23)።
በተለይም በዘመናችን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተንሰራፍቶ የሚታየው ሰውን የሚመለከት ጽሑፍና ንግግር ነው። ይህም ሁለት አይነት ነው። አንዱ በተጋነነ መረጃ ወይም በፍጹም ሐሰት ሰውን መልአክ አስመስሎ ማወደስ ነው። የመጀመሪያው የዚህ ጦማር ትኩረት አይደለም። ሁለተኛው በተጋነነ መረጃ ወይም በፍጹም ሐሰት ሰውን ሰይጣን አስመስሎ ማቅረብ ነው። ከልብ ካለ ጥላቻ የሚመነጭ ሲሆን ሰውን ለመጉዳት ታልሞ የሚደረግ ክፉ ድርጊት ነው። አንድም የተጠቀሰው ሰው ጽሑፉን አይቶ ወይም የተባለውን ሰምቶ አእምሮው እንዲጎዳ፣ ወይም ሌላ ሰው ያንን ጽሑፍ አንብቦ ወይም ስለዚያ ሰው የተነገረውን ሰምቶ እንዲጠላው ወይም ጉዳት እንዲያደርስበት። እንዲህ አይነቱ ድርጊት በመጨረሻው ቀን ለቅጣት የሚዳርግ መሆኑን ተገንዝበን ማኅበራዊ ሚዲያን ለማኅበራዊ መስተጋብር በኃላፊነት ልንጠቀም ይገባል። እያንዳንችንም እንዲህ አይነት ሰውን የሚጎዳ ነገር ባለመጻፍ ወይም ባለመናገር እንዲሁም ባለማጋራት፣ ባለመውደድ፣ ይልቁንም በመገሰፅ የየራሳችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል። የሰው ሠራሽ አስተውሎትን ጨምሮ ማንኛውንም የቴክኖሎጂ ውጤት ሰውን ለመጥቀም እንጂ ለመጉዳት አንጠቀም።
አንዳንዶች በማኅበራዊ ሚዲያ በስውር ስም (መለያ) ተከልለው ወንድማቸውን ሲሳደቡና ሲያዋርዱ ይታያል። በዚህም ከሰው እይታ የሚደበቁ፣ ከቅጣትም የሚያመልጡ ይመስላቸዋል። ነገር ግን ይህ ራስን ማታለል መሆኑን ሊረዱ ይገባል። ምክንያቱም በመጀመሪያ ደረጃ እግዚአብሔር ያውቃቸዋል፣ ያያቸዋልም። በሁለተኛ ደረጃ ህሊናቸው ያውቀዋል፣ ይፈርድባቸዋልም። በሰውም ዘንድ ቢሆን በዚህ በዲጂታል ዘመን የሚሰወር ነገር ስለማይኖር IP addressን በመሳሰሉ የመለያ ቁጥሮችና በተመሳሳይ ጥልቅ ምርመራዎች በቀላሉ ሊገኙ እንደሚችሉ ማወቅ አለባቸው። የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንታቸውን ካጠፉት (Delete ካደረጉት) በኋላ ጭምር ይህ መለያ እንደሚቆይ ማወቅ ይኖርባቸዋል። ሆኖም ዋናው የእግዚአብሔርና የህሊና ፍርድ ነውና ራሳችንን ከእንደዚህ አይነት አፀያፊ ድርጊት መጠበቅ ይኖርብናል። በዲጂታል ሚዲያ የሚወረወር ስድብ ተሳዳቢውን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ሊከተለው ይችላል። በባለፉት ዘመናት ስድብ በጥቂት ሰዎች ብቻ አንድ ጊዜ ተሰምቶ ያልፍ ነበር። በዚህ ዘመን ግን በዓለም ላይ ያለ ማንኛውም ሰው ያየዋል፣ ይሰማዋል፣ በዲጂታል ሚዲያው ተሰንዶ ይቀመጣል፣ የማንነታችን መገለጫ፣ የታሪካችንም አካል ሆኖ ይኖራል። እናጥፋው ብንልም አንችልም። ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ንስሐ እንደምንገባው ሁሉ ይቅርታ መጠየቃችንም አብሮ ተሰንዶ ካልተቀመጠ በማንኛውም ጊዜ በሕግም ጭምር ተጠያቂ ልንሆን እንችላለን።
በነፍስ ለባዊነት (Conscience) ላይ የሚሰነዘር ስድብ የገሃነም እሳት ፍርድ ያመጣል።
ጌታችን ከሁሉ ስለሚከፋው ስድብና ጉዳቱ ሲያስተምር “ወንድሙን ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል” ብሏል። ይህ ዓይነቱ ስድብ የነፍስ ባህርይ በሆነው ለባዊነት ላይ የሚሰነዘር ስድብ፣ ሰውንም ከሰብአዊነት ክብር የሚያጎድል (dehumanization) ነው። ነፍስ ለባዊት ናት ስንል ልባም፣ ልብ አድራጊ፣ ተመልካች፣ አስተዋይ፣ ብልኅ፣ ዐዋቂ፣ ጠንቃቂ ናት ማለታችን ነው። በዚህም እግዚአብሔር ነፍስን ሲፈጥራት ለባዊት አድርጎ፣ ሕገ ልቡናንም በውስጧ አትሞ ነው የፈጠራት። እንግዲህ በሰው ውስጥ ያለችን ይህችን ለባዊት ነፍስ ደንቆሮ (ክፉንና ደጉን (Moral values) የማትለይ) ብሎ መሳደብ ለባዊት አድርጎ የፈጠራትን እግዚአብሔርን መሳደብ ነው። በነፍስ ላይ ሁሉ ስልጣን ያለው እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ በእርሱ ሥራ ገብቶ ፍርድ እንደመስጠት ይቆጠራል። ስለዚህ ይህ ከስድብም አልፎ ክህደት ነው። ስለዚህ ነው “የገሃነመ እሳት ፍርድ” ይገባዋል የተባለው።
ጌታችን እንዲህ አይነቱ ከንቱና የክህደት ንግግር በመጨረሻው ቀን ለፍርድ እንደሚያቀርብ ሲያስተምርም “እኔ እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤ ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህና ከቃልህም የተነሣ ትኰነናለህ (ማቴ 12:37-37)” ብሏል። ጌታችን በሌላው ትምህርቱም “ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባ አይደለም፥ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው” (ማቴ 15:11) በማለት ከአፍ የሚወጣ ስድብ ሰውን (ተሳዳቢውን) በኃጢአት እንደሚያረክሰው በግልፅ አስተምሯል። ይህን ቃል እያነበብን በተለይም በዘመናችን በማኅበራዊ ሚዲያ ጭምር ያለውን ሰውን ከሰውነት ክብር በሚያሳንስ ሁኔታ በክፉ እንስሳት፣ በዱር በአራዊት፣ በሰይጣን፣ በአረም፣ በካንሰርና በመሳሰሉት እየመሰሉ የሚሰነዝሩትን ስድብ ስናስብ ዘመኑ ኃጢአት የሰለጠነበትና የሚያስጨንቅ መሆኑን እናስተውላለን። ይባስም ብሎ (ሰባክያን ተብለው ጭምር) ሃይማኖትን ለመጠበቅ በሚል ሽፋን የሰውን ልጅ የሚሳደቡትን ስናይ ለእግዚአብሔር ቀንተው ክርስቶስን የሰቀሉትን አይሁድን ያስታውሰናል። በመሳደብ የሚፈፀም ኃጢአት፣ የሚጠብቀን ቅጣት እንጂ የምንጠብቀው ሃይማኖት የለም።
በሌላ በኩል ኃጢአትን አለመሥራት ብቻውን ጽድቅ አይደለምና በልባችን፣ በአንደበታችን፣ በተግባራችንም ሰውን የሚጠቅም ነገርን ልናደርግ ይገባናል። በሀሳባችን(በልባችን) ወንድማችንን ወይም እኅታችንን በነፍስና በሥጋ የሚጠቅም ነገርን እናስብ። በአንደበታችንም (በቃላችን) ሰውን የሚጠቅመውን ይልቁንም ወደ ጽድቅ መንገድ የሚያደርሰውን መልካሙን ቃል ብቻ እንናገር። ማኅበራዊ ሚዲያውንም ለተሠራለት ዓላማ (ማኅበራዊ መስተጋብርን ለማጠናከር) እንጠቀምበት። በዚህ መስተጋብርም ለሰው የሚበጀውን አብሮ በሰላም መኖርን እንስበክበት። በተግባርም ሰውን የሚጠቅመውን ነገር አብዝተን እንሥራ። የተቸገሩትን እንርዳ። አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸውን እናክም። ይህን ስናደርግ የብርሃን ልጆች እንሆናለን።
ሰውን በማንነቱ መጥላት/ማግለል/መስደብ የክህደት ተግባር ነው።
ሰው እግዚአብሔር በአርአያውና በአምሳሉ አክብሮ የፈጠረው ፍጡር ነው (ዘፍ 1:28)። ስለዚህም የሰው ዘር ሁሉ ከአዳምና ከሔዋን የተገኘ ሲሆን ሁሉም ሰው በእግዚአብሔር ፊት እኩል ነው። በሳይንስም ቢሆን የሰው ዘር (Human race) አንድ ሲሆን እርሱም Homo Sapiens ነው። የሰው ልጅ የቆዳ ቀለም በአካባቢያዊ ሁኔታዎችና በአየር ንብረት ተጽዕኖ ምክንያት የተለያየ ሲሆን ባህሉ(Culture) ደግሞ በማኅበራዊ መስጋብር በዘመናት የዳበረ ነው። በዚህም አንድ ወይም ተመሳሳይ ባህል ያላቸውና አብረው የሚኖሩ ማኅበረሰብ ብሔር (Ethnic group) ተብሎ ይታወቃል። ሰውም በተፈጥሮው በመጀመሪያ ቤተሰቡን፣ ቀጥሎ ጎረቤቱንና ጓደኞቹን፣ ቀጥሎ የሚኖርበትን ማኅበረሰብ፣ ቀጥሎም የተቀረውን ዓለም ይቀርባል፣ ያውቃል፣ ይግባባል፣ ይወዳል። ይህ ሌላውን ከመጥላት የሚመነጭ ሳይሆን ከመቀራረብ (Intimacy) የሚመነጭ መሆኑን ሁሉም ሊረዳው ይገባል። ሰው የራሴ ብሎ የሚያስበውን መውደዱ ሌላውን መጥላቱ አይደለም። ሲቀርብና ሲያውቅ ሌላውንም ይወዳልና። ነገር ግን ሰውን እየጠላነውና ‘ይጠላናል’ ብለን እየተናገርን እንዲወደን መጠበቅ የለብንም። ፍቅርን በማድረግ አርአያ ልንሆን ይገባናል እንጂ።
ሊቀ ነቢያት ሙሴ በቆዳ ቀለም (Skin colour) ጥቁር የሆነችውን በማግባቱ እኅቱ ማርያምና ወንድሙ አሮን ተቃውመውት ነበር። በዚህም ከእግዚአብሔር ተግሳፅን ተቀብለዋል (ዘኁ 12)። ቅዱስ ጳውሎስም በገላቲያ መልእክቱ “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና። እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ። (ገላ 3:28-29)” በማለት ሁሉም በክርስቶስ አንድ እንደሆነ አስተምሯል። ሐዋርያው ያዕቆብም ለሰው ማዳላት እንደሌለብን አስተምሮናል (ያዕ 2:1-9)። ወንጌላዊ ዮሐንስም በራእዩ “ከዚህ በኋላ አየሁ፥ እነሆም፥ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮሁ። በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ። (ራእ 7:9-10)” በማለት የሰው ልጆች ሁሉ ያለ ልዩነት እግዚአብሔርን በአንድነት እንደሚያመሰግኑት ተናግሯል።
እግዚአብሔር እንደዚህ አክብሮ የፈጠረውን የሰው ልጅ በማንነቱ መስደብ የክህደት ተግባር ነው። እግዚአብሔር አንተንም ወንድምህንም እኩል አክብሮ ፈጥሯችሁ ሳለ (ከአንድ የሰው ዘር ተገኝታችሁ) አይ እኔን አብልጦ እርሱን ደግሞ አጉድሎ ወይም አሳንሶ ነው የፈጠረው ብሎ ማሰብ፣ መናገር ክህደት ነው። ክርስቶስ የሞተለትን፣ በደሙ ዋጋም የገዛውን ሰውን መናቅ፣ መጥላት፣ መስደብ ክርስቶስ ለሰው ልጅ መዳን የከፈለውን ቤዛነት መካድ ነው። ይህ ኃጢአት ከሰውነት ክብር ጭምር የሚያወርድ ከባድ ኃጢአት ነው። ሳጥናኤል የተዋረደው እርሱም ልክ እንደ ሌሎቹ መላእክት መልአክ ሆኖ ሳለ ራሱን ከሌሎች መላእክት በማስበለጡና ሌሎች መላክትን አሳንሶ እርሱ እንደፈጣሪ እንዲመለክ በመሻቱ ነው። ዛሬም ራሳቸውን ከፍ የሚያደርጉ፣ ሌሎችን የሚዋርዱ ዕጣ ፈንታቸው ውርደት ብቻ ነው። አንዳንዶች ለዘረኝነት ክፋታቸው ኖኅ “ከነዓን ርጉም ይሁን፤ ለወንድሞቹም የባሪያዎች ባሪያ ይሁን (ዘፍ 9:20-27)” የሚለውን የመጽሐፍ ቃል ለሀም የተነገረ አድርገው አጣመው ይጠቅሳሉ። ይህም ሌላ ክህደታቸው ነው። አንደኛ ኖኅ የረገመው ሀምን ሳይሆን ልጁን ከነዓንን ነው። ሀም አስቀድሞ በእግዚአብሔር ተባርኮ ነበርና (ዘፍ 9:1)። የከነዓንም ርግማን ትንቢታዊ እንጂ ቀጥታ ባርነት አልነበረም። ይህም ትንቢት የሴም ልጆች የሆኑት ሕዝበ እስራኤል ወደ ተስፋይቱ ምድር ከነዓን ሲገቡ የተፈፀመ ነው።
ከመስዋእት በፊት ይቅር መባባልና እርቅ ይቅደም።
ጌታችን በዚሁ በመጀመሪያው ሕገ ወንጌል ሥር ከጸሎት፣ ከምስጋና፣ ከምጽዋት፣ ከሌሎችም መስዋእቶች በፊት ይቅር መባባል፣ እርቅን መፈጸም እንደሚገባ አስተምሯል። ይህንንም “እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፥ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፥ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፥ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ” በማለት ነው የተናገረው። ይህም ከሁሉም አገልግሎት በፊት እርቅ መቅደም እንዳለበትና ያለ እርቅ የሚቀርብ አገልግሎትም ይሁን መስዋእት በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ እንደማይሆን ያስረዳናል። ስለዚህም ነው ‘በደላችንን ይቅር በለን እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል’ ብለን እንድንጸልይ ያስተማረን። በተጨማሪም “ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና፤ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም (ማቴ 6:14-15)” ብሎ ወንድማችንን (እኅታችንን) ይቅር ሳንል ይቅርታን ከእግዚአብሔር እንደማናገኝ አስተምሮናል።
እግዚአብሔር ከመስዋእትና ከአገልግሎት በፊት የሚፈልገው ንጹሕ ልብን ነው። ልባችን ንጹሕ ሳይሆን መስዋእትን ብናቀርብ እግዚአብሔር አስቀድሞ የልባችን ነው የሚያየው። መጽሐፍ እግዚአብሔር ወደ አቤልና (የአቤል ልብ) ወደ መስዋእቱ ተመለከተ እንዲል(ዘፍ. 4:4)። አንድም ልባችን ንጹሕ ካልሆነ ንጹሕና እውነተኛ መስዋእትን (አምልኮን) ልናቀርብ አንችልምና። በሌላም መልኩ ያዘነብንን ወንድም ወይም እኅት ይቅርታ ሳንጠይቅ መስዋእትን ብናቀርብ እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ ስለሆነ ፍቅርም ከመስዋእት ሁሉ ይቀድማልና መስዋእታችንን አይመለከተውም። ስለዚህን ጸሎታችንን፣ ምስጋናችንን፣ መባችንን ከማቅረባችን በፊት የበደልናቸውን ሁሉ ይቅርታ ጠይቀን፣ የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለን ሊሆን ይገባል።
እርቅንና ሰላምን ሳንዘገይ በፍጥነት እናድርግ
ጌታችን በዚሁ በመጀመሪያው ሕገ ወንጌል እርቅን በቶሎ ማደረግ እንደሚገባን አስተምሮናል። ይህንንም ሲናገር “አብረኸው በመንገድ (ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ) ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ፤ ባላጋራ ለዳኛ እንዳይሰጥህ ዳኛም ለሎሌው፥ ወደ ወህኒም ትጣላለህ፤ እውነት እልሃለሁ፥ የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከቶ ከዚያ አትወጣም (ማቴ 5:21-26)” ብሏል። ከሰው ጋር ያለን ያለመግባባት ሳይፈታ ቆይቶ ሌላው ወገን ወደ ምድራዊ ፍርድ ቤት ሊወስደው ቢነሳ ወደ ፍርድ ከመድረሱ በፊት በመንገድ ሳላችሁ እርቅን አድርጉ ሲለን ነው። አንድም በምድራዊ ፍርድ ቤት ከቅጣት እናመልጥ ዘንድ ይህንን ጥበብ አስተማረን። ይቅርታ የምንጠይቀው ወይም ይቅርታ የምናደርገው ፍርድ ቤት ሄደን ከተፈረደብ(ል)ን በኋላ ሳይሆን ቀደሞውኑ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ሳያመራ መሆን እንዳለበት አስተማረን። ፍጻሜው ግን ከወንድምህ ጋር እንደተጣላህ ሞት እንዳይወስድህና እንዳይፈረድብህ ፈጥነህ ይቅር ተባባል (ኃጢአትን አታሳድር)፣ ሰላምን አድርግ ማለቱ ነው። መንገድ የተባለ የሰው ልጅ ምድራዊ ሕይወት ነውና። ባላጋራ የተባለውም ለቅጣት ፍርድ የሚያደርስ ኃጢአት ነው።
መደምደሚያ
በዘመናችን መሳደብ እንደ ልማድ ተወስዶ በተለይም በዲጂታል ሚዲያው ኃጢአት እስከማይመስል ድረስ ተንሰራፍቶ የሚታይበት ሁኔታ ነው የሚስተዋለው። አንዳንዶችም ስድብን ምክንያታዊና ሕጋዊ ለማስመሰል የሚሄዱበትን ርቀት ማየት ያሳዝናል፣ ያሳፍራልም። ታዋቂነት በተሳዳቢነት ውድድር የሚገኝ ይመስል ግለሰቦችንና ማኅበረሰብን ብዙ የተሳደቡና ያሰደቡ ደግሞ ብዙ እይታና (View) መውደድ (Like) አግኝተው፣ እንደ ታላቅ ተፅዕኖ ፈጣሪና ጀግና ተቆጥረው ታላቅ ቦታ ሲሰጣቸው ማየት ያስፈራል። ይባስ ብሎም ‘ለምን ሰውን ትሳደባላችሁ?’ ሲባሉ ‘እኔ አልተሳደብኩም፣ በሆነው ልክ ነው የገለፅኩት፣ እንትንን እንትን ማለት ስድብ አይደለም’ እያሉ መሳደባቸውንም ሆነ ብለው ይክዳሉ። ሌላውም እነርሱን ምሳሌ አድርጎ የእነርሱን ክፋት ለመድገም ሲታትር ማየት ልብን ይሰብራል። ነገር ግን ጌታችን ያስተማራቸው ፍጹማን ሕግጋት ዘመን የማይሽራቸው ዘላለማዊ ናቸው። ስለዚህም ቁጣና ስድብ ከአካላዊ ጥቃት በመለስ ያሉ ለፍርድ የሚያደርሱ ኃጢአቶች መሆናቸውን በሰፊው ማስተማር የሚገባን ዘመን ላይ እንገኛለን። እነዚህን መግታት ካልተቻለም ‘አትግደል’ የሚለውን ሕግ ማስጠበቅ ይከብዳል። የተዘራ ክፉ ዘር ክፉ ፍሬን ማፍራቱ አይቀርምና። ክፉ ዘርን በቃላት የዘራነውም ያንኑ የዘራነውን በተግባር እናጭዳለን።
ስለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ “እነሆ፥ ፈረሶች ይታዘዙልን ዘንድ ልጓም በአፋቸው ውስጥ እናገባለን፥ ሥጋቸውንም ሁሉ እንመራለን። “እነሆ፥ መርከቦች ደግሞ ይህን ያህል ታላቅ ቢሆኑ በዐውሎ ነፋስም ቢነዱ፥ የመሪ ፈቃድ ወደሚወደው ስፍራ እጅግ ታናሽ በሆነ መቅዘፊያ ይመራሉ። እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል። እነሆ፥ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል። አንደበትም እሳት ነው። አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል፤ ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና፥ የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል፥ በገሃነምም ይቃጠላል (ያዕ 3:5-6)” በማለት ያስተማረውን በማስተዋል አንደበታችንን ልንገራው ይገባል። ከምድራዊና ከሰማያዊው ፍርድ የምንድነው በዚህ ነውና። ከምንም በላይ አንደበታችንን ባለመግራታችን የበለጠ የምንጎዳው ራሳችን መሆናችንን ልናስተውል ይገባናል። አንደበቱን ያልገራ በምድር ላይም ሰዎች ርቀውት ብቻውን ይቀራል፣ ፈጥኖ ንስሐ ካልገባም በሰማይም ቅድስና ርቆት ክመንግስተ ሰማያት በአፍአ ይቀራል።
መጽሐፍ “አንደበቱን ሳይገታ፣ ልቡን እያሳተ ሃይማኖተኛ ነኝ የሚል ሰው፣ ራሱን ያታልላል፤ ሃይማኖቱም ከንቱ ነው(ያዕ 1:26)” ይላልና አንደበታችንን ልንቆጣጠረው ይገባል። ክርስቶስ የፍቅር አምላክ ነውና፣ ክርስትናም የፍቅር እምነት ናትና አንደበታችንን ለፍቅር እንጂ ለስድብ አገልግሎት ልናውለው አይገባም። ስለዚህ በዕውቀትም ይሁን ያለ ዕውቀት፣ በነፃ ፈቃድም ይሁን በሰዎች ግፊት ለተቆጣነው፣ በቃላት በሰው ልጅ ላይ ለፈፀምነው ጥቃት፣ በድርጊትም ሰውን ለጎዳነው፣ ጥቃትን መከላከል፣ማውገዝ ወይም አለመተባበር ስንችል ላልተከላከልነው ይልቁንም በተቃራኒው ጥቃትን ለደገፍነው፣ ጥቃት ለደረሰባቸው ወገኖች ርኅራሄን ላላሳየነው ፈጥነን ንስሐ ልንገባ ይገባል። ለወደፊት መንፈሳዊ ሕይወታችንም ከእነዚህ ኃጢአቶች ለመለየት መወሰን አለብን። የፍቅር አምላክ ይህንን ለማድረግ ይርዳን። አሜን!