ሕግጋተ ወንጌል (ክፍል ፪): በልብህም፣ በሀሳብህም፣ በግብርህም አታመንዝር

ጌታችን በሁለተኛው ሕገ ወንጌል ከአሠርቱ ትዕዛዛት ስድስተኛው ስለሆነው አታመንዝር (ዘጸ 20:14) ስለሚለው ትዕዛዝ ሲናገር “አታመንዝር እንደ ተባለ ሰምታችኋል” በማለት ነው የጀመረው። በኦሪት ሕግ ሲያመነዝር የተገኘ እንዲገደል “ማናቸውም ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ወይም ከባልንጀራው ሚስት ጋር ቢያመነዝር አመንዝራውና አመንዝራይቱ ፈጽመው ይገደሉ (ዘሌ 20:10)” የሚል ትዕዛዝ ነበር። ጠቢቡ ሰሎሞንም በመጽሐፈ ምሳሌ “ከሴት ጋር የሚያመነዝር ግን አእምሮው የጎደለ ነው፤ እንዲሁም የሚያደርግ ነፍሱን ያጠፋል። ቁስልንና ውርደትን ያገኛል፥ ስድቡም አይደመሰስም (ምሳሌ 6:32-33)” በማለት የዚህን ትዕዛዝ መተላለፍ አስከፊነት ተናግሯል። ነገር ግን በሕገ ኦሪት የነበረው አታመንዝር የሚለው ትዕዛዝ ጾታዊ (አካላዊ (Physical act) – በግብር/በተግባር ከትዳር ውጭ ያለ ጾታዊ ግንኙነት) ማመንዘርን ብቻ መከልከል ላይ ያተኮረ ስለነበር ፍጹም አልነበረም።

ዝሙት ማለት ፍቅረ ተራክቦ ማለት ነው፡፡ ይህም ተራክቦን (ሩካቤ ሥጋን) ካለልክ መውደድና ለእርሱም መገዛትን ያመለክታል። በአማርኛ “አታመንዝር” ተብሎ የተተረጎመው ቃል በግእዙ “ኢትዘሙ” (ዝሙትን አትፈጽም) የሚል ነው። ሰው የሥጋ ፍላጎቱን መግታትና ራሱን መግዛት ሳይችል ሲቀር በዝሙት ይፈተናል፡፡ ከጋብቻ ውጪ የሚደረግ ማንኛውም አይነት ሩካቤ ሥጋ ማመንዘር (አመንዝራነት) ይባላል፡፡ ሰው አመንዝራ የሚባለው ከሕግ ሚስቱ(ባሏ) ውጭ ከሌላ ሰው ጋር ሩካቤ ሥጋ ያደረገ(ች) እንደሆነ ነው፡፡ ሴሰኝነት ደግሞ ከፍተኛ (ከልክ ያለፈ) የዝሙት ስሜትን ያመለክታል፡፡ ሴሰኝነት የሩካቤ ሥጋ ሱሰኝነት ነው። በአጽዋማት፣ በበዓላትም፣ እንዲሁም በሰንበት ያለዕረፍት ተራክቦን መፈፀም ሴሰኝነት ነው፡፡ ሰው ከትዳር አጋሩ ጋርም ቢሆን የሚያደርገው ሩካቤ ሥጋ የተወሰነ ጊዜ ከሌለው ሴሰኝነት ነው፡፡ መደፈር (Rape) ግን ከተጠቂዋ ፈቃድ ውጭ (አንዳንዴም በኃይል) የሚፈጸም ጥቃት ሲሆን (ለሚደፍረው) ከባድ ኃጢአትና ወንጀል ስለሆነ ከዝሙት የተለየ ነው። የተደፈረው አካል ግን ተጎጂ እንጂ ኃጢአተኛ አይሆንም (ዘዳ 22:25-27)።

በእምነት መነጽር በጥልቀት ለሚመለከትና ለሚያስተውል ሰው ማመንዘር ሁሉንም የክርስቲያናዊ ስነምግባር እሴቶች የሚንድ እጅግ ከባድ ኃጢአት ነው። ማመንዘር በቅዱስ ጋብቻ ከትዳር አጋር ጋር ተማምኖ ለመኖር የተገባውን የቅዱስ ጋብቻ ቃል ኪዳን ያፈርሳል። ማመንዘር የልብን፣ የአእምሮንና የሰውነትን ንጽሕና የሚያረክስ እጅግ ክፉ ኃጢአት ነው። ማመንዘር የትዳር አጋርን ፍቅር የሚነሳ፣ የእግዚአብሔር ስጦታ የሆኑ የልጆችን ተስፋ የሚያጨልም፣ የቤተሰብንና የማኅበረሰብን ክብር የሚያዋርድ አፀያፊ ኃጢአት ነው። የትዳር አጋር የሚገባውን ፍቅርና ክብር በመንፈግ አስተዋይነትንና ፍትሐዊነትን የሚያሳጣ የክህደት ተግባር ነው። ማመንዘር እግዚአብሔር የመሠረተውን ቅዱስ ጋብቻ የሚያፈርስና ለእርሱም ከመገዛት የሚያወጣ የአመፀኝነት ተግባር ነው። አመንዝራነት በነፃ ፈቃድ ለጋብቻ የተገባውን ቃል በማፍረስ በሰውና በእግዚአብሔር መታመንን የሚያሳጣ ድርጊት ነው። ማመንዘር ራስን ያለመግዛትና ለሥጋ ፍላጎት ብቻ መገዛትን የሚገልጥ ተግባር ነው። ማመንዘር እግዚአብሔር የፈቀደውን በመተው (የ)ሌላውን የሚያስመኝ ስግብግብነትም ነው። በጤናውም ዘርፍ ብናይ ዝሙት ለስነልቦና ችግር፣ ለተላላፊ በሽታዎች፣ ለፅንስ ማቋረጥ ወዘተ የሚያጋልጥ ነው። ስለዚህም ነው ጌታችን በሁለተኛው ሕገ ወንጌል ከዚህ ከባድ ኃጢአት ራሳችንን እንድንጠብቅ ያስተማረን።

ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል።

ሕግና ነቢያትን ፍጹም ሊያደርጋቸው የመጣው ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን “አታመንዝር” የሚለውን ሕግ ፍጹም ያደርገው ዘንድ “እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወደ ሴት (በዝሙት መንፈስ) ያየ ሁሉ (ለዝሙት) የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል (ማቴ 5:27-30)” በማለት ሁለተኛውን ሕገ ወንጌል ሠራልን። ይህንንም በማለት ማመንዘር በአካል ብቻ ሳይሆን በልብም የሚፈጸም ኃጢአት መሆኑን አስተማረን። ይህ የባልንጀራህን ሚስት አትመኝ ከሚለው የኦሪት ትዕዛዝ ጋርም የሚመሳሰል ነው (ዘጸ 20:17)። ስለዚህም ዝሙት በዐይን ያዩትን በልብ ከመመኘት ይጀምራልና በልብ መመኘት ኃጢአት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ “ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል፡፡ ምኞትም ከፀነሰች ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ከተፈጸመች ሞትን ትወልዳለች” (ያዕ 1: 14-15) እንዳለው ምኞት የኃጢአት ምንጭ ናትና።

ዝሙት የተገለጠ የሥጋ ሥራ ነው (ገላ 5:19-212)። የዝሙት ኃጢአት በድንገት የሚፈፀም ሳይሆን ስሜትን፣ ልብን፣ ሀሳብን፣ ፈቃድን፣ አንደበትንና ግብርን ሁሉ የሚያሳትፍ ሂደት ነው። በመጀመሪያ በዐይን መመልከት እና ወይም በጆሮ መስማት፣ ቀጥሎ በልብ መሻት (መመኘት)፣ ከዚያ በአእምሮ ማሰብ (ማቀድ)፣ ከዚያ በነፃ ፈቃድ ለመተግበር መወሰን፣ በመጨረሻም በድርጊት መፈፀም ናቸው። መመልከትና መስማት (የስሜት ሕዋሳቶቻችን) የዝሙት ሀሳብ ወደ ሰውነታችን የሚገባበት በር ነው። ስለዚህ ነው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ዐይን ከሰውነት ሁሉ ቀድማ ዝሙትን ትፈፅማለች” በማለት ያስተማረው። ልብ ደግሞ የገባውን ሀሳብ ወደ ምኞት ይቀይረዋል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህንን ሲገልፅ “ዝሙት በልብ ውስጥ ትፀነሳለች” በማለት አስተምሯል። ወደ አእምሮ ሲሄድ አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ነው። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ “ስለዚህ አእምሮ ስዕልን ይስልና ለስሜት ፈቃድን ይሰጣል” ብሏል። ፈቃድ ደግሞ ውሳኔን ያሳልፋል። አንደበትን የሚናገረው፣ ሰውነት የሚፈፅመው ልብ፣ አእምሮና ፈቃድ የተቀበሉትን ነው። ስለዚህም ዝሙት መላ ሰውነትን (ስሜትን፣ ልብን፣ አእምሮን፣ ፈቃድን፣ አንደበትንና አካልን) የሚያረክስ ኃጢአት ነው። ይህንን ለመከላከል የዝሙት ሀሳብ አስቀድሞ ወደ እኛ እንዳይገባ መከላከል ይገባናል። ከገባም በጾም፣ በጸሎትና በንስሐ ሰንሰለቱን መበጣጠስ ይኖርብናል።

ጌታችን በወንጌሉ ኃጢአት በልብ ካለ ክፉ ሀሳብ እንደሚጀምር ሲያስተምር “ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና (ማቴ 15÷19)” በማለት ተናግሯል። ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስም ይህንኑ “ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ መጐምጀት፥ ክፋት፥ ተንኰል፥ መዳራት፥ ምቀኝነት፥ ስድብ፥ ትዕቢት፥ ስንፍና ናቸውና፤ ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል ሰውን ያረክሰዋል (ማር 7:21)” በማለት ጽፎልናል። ጠቢቡ ሰሎሞንም “አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና (ምሳሌ 4:23)” በማለት ልባችንን ከዝሙት ሀሳብ እንድጠብቅ አስተምሮናል። ስለዚህ ይህች ደገኛ ሕገ ወንጌል አታመንዝር (በአካል) የምትለዋን ሕገ ኦሪት በልብም (በሀልዮ)፣ በቃልም (በነቢብ)፣ በተግባርም (በግብር) አታመንዝር በማለት ፍጽምት አድርጋታለች።

የትዕግስት ምሳሌ የሆነው ኢዮብ “ከዐይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፤ እንግዲህስ ቆንጆይቱን እንዴት እመለከታለሁ? (ኢዮብ 31:1)” እንዳለው ዐይናችንን ለዝሙት ከሚዳርጉ ነገሮች መጠበቅ አለብን። እንዲሁም “ልቤ ወደ ሌላይቱ ሴት ጎምጅቶ እንደ ሆነ፥ በባልንጀራዬም ደጅ አድብቼ እንደ ሆነ፥ ሚስቴ ለሌላ ሰው ትፍጭ፥ ሌሎችም በእርስዋ ላይ ይጎንበሱ። ይህ ክፉ አበሳ፥ ፈራጆችም የሚቀጡበት በደል ነውና፤ ይህ እስከ ጥፋት ድረስ የሚበላ እሳት፥ ቡቃያዬንም ሁሉ የሚነቅል ነውና (ኢዮብ 31:9-12)” በማለት የዝሙትን አስከፊነት መስክሯል። ነቢዩ ሚልክያስም “ለፍርድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በመተተኞችና በአመንዝሮች፥ … ፈጣን ምስክር እሆንባቸዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር (ሚል 3:5)” በማለት ተናግሯል።

በግብር የሚገለጥ የዝሙት ኃጢአት

የቅድስና መንገድ ግልፅ ነው። ይህም እስከ ጋብቻ ዐቂበ ርእስን (ራስን መጠበቅን) ገንዘብ ማድረግ፣ ከዚያ ቅዱስ ጋብቻን መመሥረት ወይም የምንኩስና ሕይወትን (እውነተኛ ምንኩስናን ማለታችን እንደሆነ ልብ ይሏል) መያዝ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየበዛ የመጣው ትዳርም ሳይመሠርቱ፣ ሳይመነኩሱም ዝም ብሎ መኖር ለዝሙት ኃጢአት የሚያጋልጥ መንገድ ነው። ‘መነኩሴ ነኝ’ እያሉም በከተማ እየኖሩ፣ ሀብት እያፈሩ፣ የቀሚስ ፋሽን እያቀያየሩ፣ በየመዝናኛው እየተንሸራሸሩ፣ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተገማሸሩ በልብም፣ በሀሳብም፣ በግብርም ማመንዘር የኃጢአት መንገድ እንጂ የክርስትና ሥርዓት አይደለም። የአመንዝራነት ኃጢአት ከጋብቻ አንጻር በብዙ መንገድ ሊገለፅ ይችላል። ቅድመ ጋብቻ (ከጋብቻ በፊት) የሚፈፀም ማንኛውም ሩካቤ ሥጋ አመንዝራነት ነው። ይህ ከእጮኛ ጋር የሚፈፀመውንም ያካትታል። እጮኛ የትዳር አጋር አይደለ(ች)ምና። በሕግ ከተፈፀመ ጋብቻ ውጭ የሚፈፀም ማንኛውም ጾታዊ ግንኙነትም አመንዝራነት ነው። በጋብቻ ፈንታ (ማግባትን ትቶ) በየጊዜው የሥጋን ፍላጎት ለማርካት ብቻ የሚደረግ ተራክቦም አመንዝራነት ነው። ያለዝሙት ምክንያት የትዳር አጋርን መፍታት የተፈታው(ችው)ን ማግባትም አመንዝራነት ነው። ግብረ አውናንን መፈፀምም እንዲሁ የዝሙት ኃጢአት ነው።

የዝሙት ኃጢአት የሚፈፀምባቸው መንገዶችም እንዲሁ ብዙ ናቸው። በርቀት በቴክኖሎጂ (Digital/virtual) የዝሙት ስሜትን የሚቀሰቅስ መልእክት (message)፣ ምስል (Photos, emojis)፣ ምስል ወድምፅ (Videos) በመለዋወጥ ከሚፈፀም የዝሙት ኃጢአት ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባናል። በምልክት (non-verbal) ከሚገለጥ የዝሙትን ሀሳብ በአእምሮ ውስጥ ከሚፈጥር ተዋስኦም (conversation) ራሳችንን መጠበቅ አለብን። የዝሙት ፍላጎትን በሚያነቃቁ ቃላት (verbal) ከሚፈፀመውም አንደበታችንን ልንገታ ይገባናል። ከሩካቤ ሥጋ በመለስ ያሉ የአካል መነካካት (ለምሳሌ እጅ ለእጅ ተያይዞ መሄድ፣ መደባበስ፣ መሳሳም፣ መተቃቀፍ ወዘተ) ቀጣዩን ደረጃ ይይዛሉ። እነዚህ ሁሉ አድገው በአካል ወደሚፈፀመው ሩካቤ ሥጋ (physical acts) ያደርሳሉና ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባናል።

የአመንዝራነት ኃጢአት ውጤቱ የከፋ ነው።

ዝሙት ሰውን ከእግዚአብሔር የሚለይ፣ ከራስ ማንነት ጋር የሚያጣላ፣ ከቅድስና የሚያርቅ፣ ለቅጣት የሚዳርግ የስነምግባር ውድቀትና የስብእና ውርደት ነው። የሰዶምና የገሞራ ሰዎች ለመጥፋታቸው ምክንያት የአመንዝራነት ኃጢአት ነበር (ዘፍ 19:4-5 ይሁዳ 1:7)። ሴኬም የያዕቆብ ልጅ የነበረችውን ዲናን በማስነወሩ በወንድሞቿ ተገድሏል፣ ይኖርባት የነበረችው ከተማም ጠፍታለች (ዘፍ 34:1-17)። የብንያም ነገድ የነበሩት የጊብዓ ሰዎች በሌዋዊው ቁባት ላይ በፈፀሙት አመንዝራነትና ነፍስ ገዳይነት በጦርነት ተቀጥተዋል (መሳ 19-21)። በመገናኛውም ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉት ሴቶች ጋር ዝሙትን የፈፀሙት የኤሊ ልጆች (አፍኒንና ፊንሐስ) በሞት ተቀጥተዋል (1ኛ ሳሙ 2:22 4:11)። በእነርሱ ኃጢአት ምክንያት የእስራኤል ወታደሮች በጦርነት ተሸንፈው ታቦተ ጽዮንም ተማርካለች። አባታቸው ኤሊም ከወንበሩ ወድቆ ሞቷል። ንጉሥ ዳዊት ከኦሪዮን ሚስት ቤርሳቤህ ጋር የፈፀመው ዝሙት መነሻው በዐይኑ አይቶ በልቡ መመኘቱ ነበር (1ኛ ሳሙ 11:4)። በዚህም ምክንያት ቤርሳቤህ በመፅነሷ ባሏ ኦርዮንን አስገድሎታል። ከቤርሳቤህ የተወለደው የዳዊት ልጅም ታሞ ሞቷል። በኋላም እግዚአብሔር ነቢዩ ናታንን ልኮ ገስፆታል። በዚህም በንስሐ ተመልሷል።

ሶምሶንን የመሰለ የእስራኤል ኃያል ሰው ለውርደትና ለምርኮ የዳረገው ከደሊላ ጋር የነበረው ያልተገባ ግንኙነት ነበር (መሳ 16:1)። እኅቱ ትዕማርን የደፈረው የዳዊት ልጅ አምኖን በወንድሙ በአቤሴሎም ተገድሏል (2ኛ ሳሙ 13)። አምኖን በአይኑ ብቻ ውበትን አይቶ፣ የክፉ ሰውም ምክር ሰምቶ በእኅቱ ላይ ታላቅ በደልን ፈፅሟል። ትዕማር ካስነወራት በኋላ ከእርሱ ጋር እንድትሆን ብትለምነውም እንኳ በሠራተኛው ከቤት አስወጥቷታል። በፊት ከወደዳት መውደድ ይልቅ በኋላ የጠላት ጥል በልጧልና። እርሷም የደናግላን ልብሷን ቀድዳ እያለቀሰች ወጥታ ወደ ወንድሟ አቤሴሎም ሄደች። ከሁለት ዓመት በኋላ አምኖን በአቤሴሎም ወታደሮች ተገደለ። የዝሙት ጦስ መጨረሻው እንዲህ የከፋ ነው።

ሶስናን ለዝሙት ተመኝተዋት ያሰቡት ባለመሳካቱ በሐሰት ፍርድ እንድትወገር ያስፈረዱባት ሁለቱ መምህራን (ረበናት) እግዚአብሔር በነቢዩ ዳንኤል በኩል እውነቱ እንዲገለጥ በማድረጉ ራሳቸው ተወግረው ሞተዋል (መጽሐፈ ሶስና)። ንጉሥ ሄሮድስም (Herod Antipas) የወንድሙን የፊሊጶስን ሚስት በመውሰዱ በመጥምቁ ዮሐንስ ተገስጿል (ማር 6:18)። በዚህም ከዝሙት ጋር በተያያዘ ምክንያት መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐስን አስገድሎታል። በዚህም በጦርነት ተሸንፎ፣ ከስልጣኑ ተሽሮ፣ በሀገር ክህደት ወንጀል ተከሶ፣ ከሀገሩ ጭምር ተሰዶ በዚያው ሞቷል። ዛሬም ዝሙትን የሚሠሩ በምድር ላይ ሳሉ ለማኅበራዊ ቀውስ፣ ለአእምሮ ሕመም፣ ለስነልቦና መናጋት፣ ለበሽታና ለመሳሰሉት ችግሮች ይጋለጣሉ። ዝሙት ሁሉ የሚታጣበት አንዳችም የማይገኝበት ከባድ ኃጢአት ነው።

ነገር ግን እግዚአብሔር ኃጢአትን እንጂ ኃጢአተኛን አይጠላም። በኢያሪኮ ትኖር የነበረችው ጋለሞታዋ ረዓብ በእምነቷ ከክርስቶስ የዘር ሀረግ ለመቆጠር በቅታለች (ኢያሱ 2:1)። የሆሴዕ ሚስት የነበረችው የዴቤላይምን ልጅ ጎሜር ሌላ ሰው ብታገባም እግዚአብሔር ግን በምህረቱ መልሷታል (ሆሴ 3)። በዚህም የእስራኤል አለመታመን፣ የእግዚአብሔር የበዛ ምህረት ታውቋል። አምስት ባሎችን አግብታ የነበረችውን ሳምራዊቷን ሴት ጌታችን በያዕቆብ ጉድጓድ አጠገብ ማንነቱን ገልፆላታል (ዮሐ 4:18)። ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ስታመነዝር አግኝተናታል ብለው ወደ እርሱ ያመጧትን ሴት ጌታችን ከሳሾቿ የየራሳቸው ኃጢአት ወቅሷቸው ከሄዱ በኋላ በምሕረት አሰናብቷታል (ዮሐ 8:3-11)።

ቀኝ ዐይንህም ብታሰናክልህ አውጥተህቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ቆርጠህ ከአንተ ጣላት

ጌታችን ስለዚህች ሕገ ወንጌል ሲያስተምር “ቀኝ ዐይንህም ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻልሃልና። ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ቆርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻላልና (ማቴ 5:27-30)” በማለት ከዝሙት ኃጢአት እንድንርቅ አስጠንቅቆናል። ይህ ዘይቤያዊ አገላለጽ ሲሆን መንፈሳዊውን እንጂ አካላዊ ዐይንን የሚመለከት አይደለም። ጌታችን ቀኝ ዐይን እና ቀኝ እጅ ያለው ቀኝ ዐይን ቀጥተኛው ዐይን ቀኝ እጅም ዋነኛው እጅ ስለሆኑ ለኃጢአት ምክንያት የሆነ ማንኛውም (ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለውም ቢሆን) መተው እንዳለብን ለማመልከት ነው። ቃሉን በቀጥታ ወስደው ዐይናቸውን አውጥተው የጣሉ (ሰምዖን ጫማ ሰፊው)፣ እጃቸውንም ቆርጠው የጣሉ (አባ መርቲያኖስ፣ አባ አትናቴዎስ ዘአንጾኪያ) በምንኩስና ሕይወት የነበሩ አባቶች አሉ። ይህ ዘይቤያዊ ምሳሌ በሦስት መልኩ ይተረጎማል።

የመጀመሪያው ዐይን የሰውነት መብራት ስለሆነች ማንኛውም ሀሳብና ምኞት በልባችን የሚመነጨው ከምናየው ስለሆነ ከማየት የሚመነጭ ክፉ ሀሳብና ምኞትን አውጥታችሁ ጣሉ ሲል ነው። ለዐይናችን የሚያምር፣ ልብን የሚማርክ ነገርም ቢሆን ወደ ኃጢአት የሚመራን (የሚያሰናክለን) ከሆነ ጨክናችሁ ተውት ሲል ነው። ይህ በዘመናችን በተለይም በዲጂታል ሚዲያ የሚታዩትን ለሥጋዊ ዐይን የሚማርኩ፣ መንፈሳዊ ሕይወትን ግን የሚሸረሽሩ ነገሮችን ይመለከታል። እጅም ሥራ የምንሠራበት የግብር መገለጫ ስለሆነ ለኃጢአትና በእርሱም ምክንያት ለሚመጣ ሞት የሚዳርግ ክፉ ሥራን/ምግባርን ቆርጣችሁ ጣሉ ሲል ነው። ለሥጋ የሚጠቅመን፣ ለኑሯችንም መሠረት፣ ገንዘብ የሚያስገኝም ሥራ ቢሆን ወደ ኃጢአት የሚመራን (የሚያሰናክለን) ከሆነ ጨክናችሁ ተውት ሲል ነው።

ሁለተኛው ባልንጀርነትን (ጓደኝነትን) የሚመለከት ነው። የሚመክሩን፣ መንገድ የሚያሳዩን ሰዎች በቀኝ ዐይን ይመሰላሉ። ‘እገሌ ቀኝ ዐይኔ ነው’ ስንል ብዙ ነገሮችን የሚያሳየኝ፣ የሚመራኝ እርሱ ነው ማለታችን ነው። በኑሯችን የሚያግዙን፣ የሚረዱን ሰዎች ደግሞ በቀኝ እጅ ይመሰላሉ። ‘እገሊት ቀኝ እጄ ናት’ ስንል ፈጥና የምትረዳኝ፣ የምፈልገውን እንድፈጽም የምታግዘኝ ናት ማለታችን ነው። ጌታችን በዚህ ምሳሌ ያስተማረን በቀኝ ዐይን የተመሰሉ የሚመክሯችሁና የሚመሯችሁ ሰዎች የሚያሰናክሏችሁ ከሆነ ከእነርሱ ራቁ ሲል ነው። በቀኝ እጅ የተመሰሉ የሚረዷችሁ ሰዎችም የሚያሰናክሏችሁ ከሆነ ተዋቸው ሲል ነው። የዘላለም ሕይወት ከእነዚህ ሁሉ ትበልጥባችኋለች ሲለን ነው።

ሦስተኛው ዐይን የዕውቀት፣ የጥበብ ምሳሌ ናት። እጅ ደግሞ የኃይል (የጉልበት፣ የስልጣን፣ የገንዘብ) ምሳሌ ናት። ጌታችን በዚህ ትምህርቱ ሥጋዊ ዕውቀትና ጥበብ ከመንፈሳዊ ሕይወት የምታሰናክልህ ከሆነ አውጥተህ ጣላት ማለቱ ነው። ምንም ያህል የምትጠቅምህ ብትሆን ይህችን ዕውቀትና ጥበብ ይዘህ ገሃነም ከምትገባ እርሷን ጥለህ ሕይወትህን ብታተርፍ ይሻላል ማለቱ ነው። እንዲሁም በምድር ላይ ያለህ ኃይል (ጉልበት፣ ስልጣን፣ ገንዘብ) ምንም ያህል የምትወደው ቢሆን ከዘላለም ሕይወት የሚያጎድልህ ከሆነ ተወው ሲለን ነው። እነዚህ የኃጢአት ምንጭ የሆኑትን ጨክነን አውጥተን ወይም ቆርጠን እንደንጥል ያስተማረን ይህች ሕገ ወንጌል በእውነትም ፍጽምት ናት።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህንን ከቀዶ ሕክምና ጋር በማነፃፀር አስተምሯል። አንድ ሰው እግሩ ታማሚ ቢሆንና በመድኃኒት መዳን ካልቻለ በሽታው ወደ ሌላው የሰውነት ክፍል እንዳይዛመትና ሕመምተኛውን ከሞት ለማትረፍ ሲባል የሕመምተኛው ይሁንታ ተጠይቆ እግሩ በቀዶ ሕክምና እንዲቆረጥ ይደረጋል። ይህም ሕመምተኛው ሙሉ ሰውነቱን ይዞ ከሚሞት እግሩን አጥቶ ቢተርፍ ይሻላል ከሚል እሳቤ ነው። ይህ ምድራዊ ቀዶ ሕክምና ነው። ጌታችን ያስተማረው ደግሞ ስለ መንፈሳዊ ቀዶ ሕክምና ነው። በሥጋዊ ሕይወታችን ያለ ማንኛውም ነገር መንፈሳዊ ሕይወታችንን የሚያሰናክል ከሆነ ጨክነን እንተወው ዘንድ በዚህ ምሳሌ አስተምሮናል።

ዝሙት የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሆነውን ሰውነታችንን ታረክሳለች።

በወቅቱ ከጣኦት አምልኮ ጋር በተያያዘ የዝሙት ኃጢአት በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍቶባት በነበረችው ቆሮንቶስ ያስተምር የነበረው ቅዱስ ጳውሎስ በዚያ የነበሩ ክርስቲያኖች ከዝሙት እንዲርቁ በሰፊው አስተምሯል። በመጀመሪያ ሰውነታቸው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆነ (1ኛ ቆሮ 3:16) አስገንዝቧቸዋል። ከዚያም ከሴሰኞች ጋር እንዳይተባበሩ “ከሴሰኞች ጋር እንዳትተባበሩ በመልእክቴ ጻፍሁላችሁ። በጠቅላላው የዚህን ዓለም ሴሰኞችን፥ ወይም ገንዘብን የሚመኙትን ነጣቂዎችንም፥ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩትን አላልሁም፤ ይህስ ቢሆን ከዓለም ልትወጡ ይገባችሁ ነበር። አሁን ግን ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ ሴሰኛ ወይም ገንዘብን የሚመኝ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካር ወይም ነጣቂ ቢሆን ከእርሱ ጋር እንዳትተባበሩ እጽፍላችኋለሁ፤ እንደነዚህ ካለው ጋር መብል እንኳን አትብሉ (1ኛ ቆሮ 5÷9-11)” በማለት አስጠንቅቋቸዋል።

በመቀጠልም ሴሰኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ “አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም (1ኛ ቆሮ 6:9-10)” በማለት አስተምሯቸዋል። አስከትሎም “ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደ ሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን? አይገባም። ወይስ ከጋለሞታ ጋር የሚተባበር አንድ ሥጋ እንዲሆን አታውቁምን? ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ ተብሎአልና…ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል (1ኛ ቆሮ. 6:16-18)” በማለት ዝሙት የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሆነ ሰውነታችንን የሚያረክስ ክፉ ኃጢአት መሆኑን በማስረዳት ክርስቶስ በዋጋ የገዛውን ሰውነታቸውን (1ኛ ቆሮ 6:20) ከዝሙት ርኩሰት እንዲጠብቁ አስተምሯቸዋል። ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው፡ ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራሷ ባል ይኑራት (1ኛ ቆሮ 7:2) ብሎም የቅዱስ ጋብቻ ሥርዓትን አስተምሯል።

ሐዋርያው እንዳስተማረን ሴሰኞችንና አመንዝሮችን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል (ዕብ 13:4)። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሆነውን ሰውነታችንን በዝሙት ኃጢአት ስናረክሰው ከእግዚአብሔር እንለያለን። እርሱ ቅዱስ ነውና በረከሰው መቅደስ አያድርም። በኃጢአት በረከሰ ሰውነት ሊያድር የሚችለው የረከሰውና የርኩሰት አባት የሆነው ዲያብሎስ ነው። ዝሙት አስከፊ ኃጢአት ነው የምንለው ሰውነታችንን የቅድስና አባት ከሆነው ከእግዚአብሔር ማደሪያነት ለይቶ የርኩሰት አባት ለሆነው ዲያብሎስ ማደሪያ ስለሚያደርግ ነው። ፈጥነን በንስሐ ካልተመለስን የርኩሰት አባት የሆነው ዲያብሎስ በኃጢአት ላይ ኃጢአትን እንድንጨምርና ተስፋ እንድንቆርጥ ያደርገናል።

ለዝሙት ኃጢአት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ

የማኅበረሰባችን መንፈሳዊ ሕይወት ብልሹነት መገለጫ የሆኑ የአርት (Art) ውጤቶች ለዝሙት ኃጢአት አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ። በልብ ወለድ ድርሰቶች፣ በቀልዶች (ኮሜዲ ሥራዎች)፣ በተከታታይ ድራማዎች፣ በፊልም ውጤቶች፣ በስዕል ውጤቶች ወዘተ ደራሲያኑ የሚያስገቧቸው “የፍቅር ታሪኮች” አብዛኞቹ የሚቀርቡበት መንገድ ሰውን ለዝሙት ሀሳብ የሚያጋልጥ ነው። ተደራሲያኑም ይህንን አይነቱን የድርሰት ወጤት ከመውደዳቸው የተነሳ እንደዚህ አይነት ታሪክን ያልያዙ ድርሰቶች አድማጭ ተመልካች ያጣሉ። ይህም የዝሙትን ሀሳብ የሚያጋቡ የአርት ውጤቶች እንዲበዙ ምክንያት ሆኗል። ይህንን ለመለወጥ የአርት ባለሙያዎች ክርስቲያናዊ ሕይወትን የማይጎዳ ሥራ ብቻ ቢሠሩ፤ አንባቢያን፣ አድማጮችና ተመልካቾች ደግሞ የሚያንጸውን ብቻ መርጠው ቢጠቀሙ መልካም ነው።

አንዳንድ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ያፈነገጡ ክንውኖችም የራሳቸውን አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። ከእነዚህም ውስጥ እርቃንን የሚያሳይ ጠበል የማጥመቅ ሂደት፣ በአገልግሎት ሰበብ የእኅቶችን ሰውነት መንካት፣ በአንድ ቤት ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮች ብቻቸውን መገኘት፣ ከልክ ያለፈ ቅርርብ ያለበት የወንድና የሴት አገልጋዮች የአገልግሎት ስምሪት፣ ጥንቃቄ የጎደላቸው የመንፈሳዊ ጉዞ መርሃግብሮች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን በምሽት በሆቴል ሰርግ የማጀብ መርሃ ግብሮች፣ የምሽትና የአዳር ጉባዔዎች፣ ወዘተ ይገኙበታል። ለአገልግሎት ወደ ክፍለ ሀገር ለሚጓዙ እኅቶች የተለየና ለአደጋ የማያጋልጥ ማረፊያ ያለማዘጋጀትና ከወንዶች ጋር አንድ ቤት እንዲያድሩ ማድረግም የሚፈጥረውን ችግር መረዳት ይገባል። በሰንበት ትምህርት ቤት ያለም ሥርዓት አልባ ግንኙነት ወደ ዝሙት ኃጢአት በመምራቱና ወጣቶች በትምህርታቸው ደካማ እንዲሆኑ በማድረጉ ምክንያት ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ የሚከለክሉበትም ሁኔታም አዲስ አይደለም። ይህ የምዕመናንን ሕይወት የቤተ ክርስቲያንንም አገልግሎት የሚያደናቅፍ ነው።

አንዳንድ በዘመናዊነትና በውበት ዲዛይን ሰበብ በማኅበረሰብ ውስጥ የሚገቡ ከክርስትና ስነምግባር ያፈነገጡ አለባበሶችና የመዋቢያ ዘዴዎችም ለዝሙት ኃጢአት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። ሰው በፈለገው መዋብ መብት ቢኖረውም ሌላውን እንዳያሰናክል ግን መጠንቀቅ ይኖርበታል። ይህ ጉዳይ የመብት ጥያቄ ሳይሆን በመንፈሳዊ ሕይወት ደካማ የሆነ ወገናችን እንዳይሰናከልብን (እንዳይፈተንብን) ኃላፊነት የመውሰድና ጥንቃቄ የማድረግ ጉዳይ ነው። “እኔ ስለሰው ምናገባኝ? የራሱ ጉዳይ ነው” ማለት ከክርስቲያን አይጠበቅም። ሰው በልቡ እንዲያመነዝር ምክንያት ከመሆን ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባናልና። ይህ በአንዳንድ አገልጋዮች ዘንድም የሚስተዋል ሲሆን ታዳሚው ከቃለ እግዚአብሔር ይልቅ ተክለ ሰውነትና ሰው ሠራሽ ውበት ላይ በማተኮር በልቡና በሀሳቡ እንዲያመነዝር ምክንያት ሊሆን ይችላል።

በከፍተኛ ድህነት ምክንያት መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚሆን የሥራ አማራጭ በማጣት ዝሙትን መተዳደሪያቸው ባደረጉ ወገኖቻችን ላይ ከመፍረድ ይልቅ ለዚያ አስከፊ ሕይወት የዳረጋቸው ችግር ላይ በማተኮር ከዚያ ሕይወት እንዲወጡ መርዳት ይጠበቅብናል። ሌላ የሕይወት አማራጭንም እንዲከተሉ የምንችለውን ማድረግ ይገባናል። ይልቁንም ሀብትን አግኝተው የትዳር አጋራቸውን ቤታቸው አስቀምጠው በገንዘባቸው የዝሙት ኃጢአትን የሚሽምቱትን ወገኖች ከዚህ ኃጢአት እንዲወጡ ማስተማር ይኖርብናል። በገንዘባቸውም የጽድቅን ሥራ እንዲሠሩበት ማስቻል ይኖርብናል። በአንዳንድ በመካከለኛ ዕድሜ ያሉ ሰዎች ዘንድም ትዳርን ትቶ (ትዳርን አፍርሶ) ወደ ወጣቶች የመሄድ ነገር አለ። ከ40 እስከ 60 ዓመት ዕድሜ ውስጥ ሊያጋጥም የሚችለው ‘የመካከለኛ ዕድሜ ቀውስ‘ (Midlife Crisis) ለዚህ አስተዋጽኦ ስለሚያደርግ ክርስቲያኖች ይህንን አውቀን ራሳችንን ለሕገ እግዚአብሔር በማስገዛት ከዝሙት ኃጢአት ልንጠበቅ ይገባናል።

በተጨማሪም አንዳንድ ስሑት አስተሳሰቦች ለዝሙት መስፋፋት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። በአንዳንድ ወጣቶች ዘንድ ክብረ ንጽሕናን ጠብቆ መቆየት እንደ ኋላቀርነት (“ፋራነት”) ይታያል። አንዳንዶችም ቅድመ ጋብቻ ሩካቤ ሥጋ መፈፀምን የእጮኝነት (የመጠናናት) አንዱ አካል እያደረጉት መጥተዋል። በሌሎች ዘንድም ከአንድ በላይ ጓደኛ (Partner) መያዝ የተፈላጊነት መለኪያ ተደርጎ ይታሰባል። በአንዳንዶች ዘንድም ዝሙትን የሚያክል ከባድ ኃጢአት መፈፀም ቀለል ተደርጎ መታየቱ ወይም የተለመደ ተደርጎ መቆጠሩ ለዝሙት ኃጢአት መስፋፋት ምክንያት ሆኗል። አንዳንድ “ዘማዊ” አባባሎችና ባህላዊ ጨዋታዎችም እንዲሁ። ያልተገቡ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ መጥፎ ባልንጀርነት፣ ከትዳር አጋር ውጭ ከሌላ ሰው ጋር ያልተመጠነ ቅርርብ (Intimacy) መፍጠር፣ ዝሙት ቀስቃሽ ፊልሞች፣ የአልኮል መጠጥና የመሳሰሉትም በዝሙት ኃጢአት ለመውደቅ አስተዋጽኦ ስለሚያደርጉ ከእነዚህ ራሳችንን መጠበቅ ይኖርብናል።

ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም በራሱ ኃጢአት ባይሆንም ለዝሙት ኃጢአት ግን መግቢያ በር ሊሆን ይችላል። ማኅበራዊ ሚዲያ የመልእክት መለዋወጥን ምስጢራዊነትን ስለሚጠብቅ ለድብቅ ግንኙነት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ማኅበራዊ ሚዲያ ከብዙ ሰዎች ጋር ስለሚያገናኝ አይቶ የመመኘት ኃጢአትን ያሰፋል። ማኅበራዊ ሚዲያ ቀስ በቀስ ከሌሎች ሰዎች ጋር ስሜታዊ መሳሳብን ስለሚፈጥር ለትዳር መታመንን ይፈትናል። በማኅበራዊ ሚዲያ የተዋቡና ለአይን የሚማርኩ ሰዎችን ማየት፣ ዝሙት ነክ መልእክቶችንና ጽሑፎችን ማንበብ፣ ቪዲዮዎችን መመልከት መንፈሳዊ ሕይወትን ይፈትናል። በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት የሚፈፀም “ማኅበራዊ ስርቆት (Social cheating)” ትዳርን ሊያፈርስ ይችላል። ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን ለመጠበቅ ለማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ገደብ ልናበጅለት ይገባል። የምንከተላቸውን ሰዎች፣ የምንለዋወጠውን መልእክት፣ የምናነበውንና የምንጽፈውን፣ የምንመለከተውን ለይተን ልናውቅ ይገባናል። የማኅበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴያችንንም ለትዳር አጋራችንና ለቤተሰባችን ግልፅ ማድረግ ይኖርብናል።

መደምደሚያ

ከጋብቻ በፊት፣ ከጋብቻ ውጭ የሚደረጉ ግንኙነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዙ መምጣታቸው ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው። ይህም የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩትም ስለዝሙት አስከፊነት በበቂ ሁኔታ አለማስተማራችን ዋነኛው ምክንያት ነው። ዝሙት የወጣቶችን ሕይወት የሚያበላሽ፣ የተቀደሰውን ትዳር የሚያፈርስ፣ ለበሽታ የሚዳርግ፣ ከእግዚአብሔር መንግሥትም የሚለይ ክፉ ኃጢአት መሆኑን አጠንክረን ማስተማር ይገባናል። “አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? (ሮሜ 2:22)” የሚለውን የሐዋርያውን ተግሳፅ ቸል ብለው የራሳቸውን የሥጋ ፍላጎት መግታት ሲገባቸው እኅቶቻችንን የሚደፍሩትን ለበደላቸው በሕግ እንዲቀጡ (እኅቶቻችንም ፍትሕ እንዲያገኙ)፣ ለፈጸሙት ኃጢአትም በንስሐም እንዲመለሱ ማድረግ ይገባናል። ከምንም በላይ ልጆቻችን ግብረ ገብነትን ተምረው እንዲያድጉና ለዝሙት ሀሳብ ምንጭ ከሚሆኑ የሚዲያ ወጤቶች እንዲርቁ በማድረግ ዛሬ በአገልጋዮች ጭምር እየተፈጸመ የሚገኘው እንዲህ አይነቱ አስከፊ ተግባር እንዳይቀጥል መከላከል ይገባናል።

በማኅበራዊና በመደበኛው ሚዲያ እንዲሁም በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች የዝሙት ተግባርን ቀርፀው የሚያስተላልፉ፣ ለዝሙት የሚያነሳሱ አለባበሶችን፣ ንግግሮችንና እንቅስቃሴዎችን ሰንደው የሚያስተላልፉ አካላት በበዙበት በዚህ ዘመን ዐይናችንንና ጆሮአችንን ከእነዚህ ሁሉ ልንጠብቅ ይገባናል። ‘መሥራት እንጂ ማየት ችግር የለውም’ እያልን ራሳችንን ማታለል የለብንም። ‘ራሳችንን መቆጣጠር ስለምንችል ብናይ ችግር የለውም’ ብለንም መታበይ የለብንም። በዐይን የገባ ኃጢአት በልብ ተፀንሶ አድጎ በገቢር ይወለዳልና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኵሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ… አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኵስ ወይም የሚመኝ እርሱም ጣዖትን የሚያመልክ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም (ኤፌ 5:3-5)” በማለት እንዳስተማረው የዝሙት ነገር በእኛ ዘንድ ሊሰማ አይገባም።

በአጠቃላይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፥ እነዚህም ዝሙትና ርኵሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣኦትንም ማምለክ የሆነ መጎምጀት ነው (ቆላ 3:5)” በማለት እንደጻፈልን ምኞታችንን በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደትና ቃለ እግዚአብሔርን በመስማት ልንገድል ይገባናል። ይህ ካልሆነና ንስሐ ካልገባን ግን በቲያጥሮን ለነበረችው ኤልዛቤልን “ዳሩ ግን ነቢይ ነኝ የምትለውን ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ንስሐም እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት ከዝሙትዋም ንስሐ እንድትገባ አልወደደችም። እነሆ፥ በአልጋ ላይ እጥላታለሁ፥ ከእርስዋም ጋር የሚያመነዝሩትን ከሥራዋ ንስሐ ባይገቡ በታላቅ መከራ እጥላቸዋለሁ (ራእይ 2:20-22)” የተባለው ይጠብቀናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “በደለኞችንም ይልቁንም በርኩስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርቀድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል (2ኛ ጴጥ. 2:9–10)” በማለት የተናገረው የፍርድ ቀን ሳይመጣ ንስሐ ልንገባ ይገባል። ይቆየን።

Leave a comment