ሆሳዕና: የምሥጋና ንጉሥ እርሱ ማነው?

በመጋቤ ምስጢር ቀሲስ ስንታየሁ አባተ

በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በድምቀትና በልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ በዓለ ሆሳዕና ነው። ሆሳዕና የሚለው “ሆሼዕናህ” ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ነው። ሆሳዕና “አድነና፣ አድነንኮ፣ እባክህ አድነን ወይም መድኃኒትነት፣ መድኃኒት መሆን ወይም መባል” የሚል ትርጉም ይይዛል። ሆሳዕና የጸበርት/የዘንባባ እሑድም ይባላል፡፡ በዓለ ሆሳዕና በቤተክርስቲያናችን ሊቃውንት ከዋዜማው ጀምሮ ሌሊቱን በማኅሌት እየዘመሩ የሚያመሰግኑበት ነው፡፡ ወደ ቅዳሴም ሲገባ ለየት ባለ ሁኔታ ዲያቆኑ ወደምዕራብ በር በማምራት “አርኅው ኆኃተ መኳንንት/መኳንንት ደጆችን ክፈቱ/” ሲል ካህኑም በውስጥ ሆኖ በዜማ “መኑ ውእቱ ዝንቱ ንጉሠ ስብሐት/የምሥጋና ንጉሥ እርሱ ማነው?/” ይላል፡፡ ይህንንም ከተቀባበሉ በኋላ ዲያቆኑ “እግዚአብሔር አምላከ ኃያላን ውእቱ ዝንቱ ንጉሠ ስብሐት/ይህ የምሥጋና ንጉሥ የኃያላን አምላክ እግዚአብሔር ነው/” ሲል ካህኑም “ይባእ ንጉሠ ስብሐት ይባእ አምላከ ምሕረት/የምሥጋና ንጉሥ ይግባ የምሕረት ንጉሥ ይግባ/” ይልና ዲያቆናቱ ወደ ውስጥ ዘልቀው ቅዳሴ ሥርዓቱ ይቀጥላል:: በዕለቱም ስለ ሆሳዕና በጥልቀት የሚናገረው የቅዱስ ጎርጎርዮስ (ኤጲስ ቆጶስ  ዘኑሲስ) ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ እጅግ ልዩ በሆነውም የሆሳዕና ዑደት ከዳዊት መዝሙር ምስባክ እየተሰበከ፣ ወንጌል እየተነበበ፣ ከጾመ ድጓውም እየተዜመ ይከበራል፡፡ ለሕዝቡም ዘንባባ ይታደላል፡፡ ጸሎተ ፍትሐትም ይከናወናል፡፡

ሆሳዕና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ። እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው። ትሑትም ሆኖ በአህያም በውርንጫይቱም ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል (ዘካ. ፱፣፱)” ተብሎ አስቀድሞ በነቢዩ ዘካርያስ የተነገረውን ትንቢት የፈጸመበት በአህያዪቱና በውርንጫይቱ ተቀምጦ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባበትና ቤተ መቅደሱን ያጸዳበት ልዩ በዓል ነው። ሆሳዕና ከትንቢቱ በተጨማሪ ምሳሌውም የተገለጠበት ነው። በኦሪቱ የነበሩ ነቢያት ዘመኑ የጸብ የጦርነት ከሆነ በፈረስ ተቀምጠው ዘገር (ጦር) ነጥቀው ይታያሉ። በተቃራኒው ደግሞ ዘመኑ የሰላም የእርቅ የሆነ እንደሆን በአህያ ተቀመጠው መነሳንስ (ጭራ) ይዘው ይታያሉ። የሰላም ንጉስ የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረው ትንቢት ተፈጽሞ የተቆጠረው ሱባኤ አልቆ የተመሰለውም ምሳሌ እውን የሚሆንበት ዘመን ደረሰ፤ ሰላም እርቅ ድኅነት ሊፈጸምላችሁ ነው ሊለን በአህያና በውርንጫይቱ ተቀምጦ በብዙ አጀብ ታጅቦ በሆታ በእልልታ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ።

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲቀመጥባቸው የቀረቡት አህዮች በአንድ ሰው ግቢ ውስጥ ታስረው ነበር። ጌታችን ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ከደብረ ዘይት አጠገብ ወደምትገኘው ወደ ቤተ ፋጌ ላከ። “ወይቤሎሙ ሑሩ ሀገረ ዘቅድሜክሙ፤ ወይእተ ጊዜ ትረክቡ ዕድግተ ዕሥርተ ምስለ ዕዋላ፤ ፍትሕዎን ወአምጽእዎን ሊተ፤ በፊታችሁ ወዳለችው ሀገር መንደር ሂዱያን ጊዜም የታሠረች አህያ ከውርንጫዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፍቱና አምጡልኝ” ብሎ ላካቸው። እንደ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ትርጓሜም እነዚያ አህዮች ተሠርቀው የታሠሩ ነበሩ። እነዚህ አህዮች ባለቤታቸው ባልሆኑ ሰዎች ተሠርቀው እንደታሠሩ ሁሉ የሰው ልጆችም በምክረ ከይሲ ተታለው በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት አጉድለው ሕጉንም አፍርሰው ከተከለከሉት ዕፀ በለስ በመብላት ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በአጋንንት ቁራኝነት ታሥረው ይኖሩ ነበር።

በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት አምነን በሐዋርያት ሥልጣን ከማዕሠረ ኃጢአት የምንፈታበት ዘመን መድረሱን ሊነግረን ሐዋርያቱን ወደ አህዮቹ ላካቸው። ሐዋርያቱ ወንጌለ መንግሥትን አስተምረው አሳምነው በተሰጣቸው ሥልጣን በኃጢአት ማሠርያ የተያዘውን ዓለም እየፈቱ ወደ ክርስቶስ የሚያቀርቡ እውነተኞች መልእክተኞች ናቸው። አህዮቹን ፈትተው ሊያቀርቡለት ሲሞክሩም አንዳች የሚቃወማቸው ቢኖር “ወእመቦ ዘይቤለክሙ ምንተ ትገብሩ በሉ እግዚኦሙ ይፈቅዶሙ ወበጊዜሃ ይፌንወክሙ፤ ምን ታደርጋላችሁ? የሚላችሁ ቢኖርም ጌታቸው ይሻቸዋል በሉ፤ ያን ጊዜ ይሰዱአችኋል” ብሎ ነግሯቸው ነበርና እንደ ቃሉ አደረጉ።

አህያዪቱን ከነውርንጫዋ ካመጡላት በኋላ ልብሳቸውን እያወለቁ በላያቸው ጫኑ፤ በምትሄድበት መንገድም ልብሳቸውን አነጠፉ፤ የተቀሩትም የዛፍ ጫፍ እየቆረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር። የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ከፊት እየቀደሙ ከኋላው እየተከተሉ “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው። ሆሳዕና በአርያም” እያሉ እየጮሁ ያመሰግኑ ነበር። በእንዲህ ዓይነት ክብር በብዙ ሕዝብ ታጅቦ ከኢሩሳሌም እስከ ቤተ መቅደሱ ካለው ፲፮ ምዕራፍ ፲፬ቱን ምዕራፍ በእግሩ ፪ቱን በአህያዪቱ ተቀምጦ ሄዷል። በውርንጫዪቱ ተቀምጦ ደግሞ ቤተ መቅደሱን ሦስት ጊዜ ዞሯል። በእንዲህ ዓይነት ክብር መመስገኑ ሊቃነ ካህናቱን አላስደሰታቸውም ነበር። ከፍ ብለውም የሚያመሰግኑትን ሕጻናትን ጭምር ከማመስገን እንዲከለክላቸው ጠይቀውት ነበር። እርሱ ግን እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። “ለእመ አርመሙ እሎንቱ አእባን ይኬልሁ፤ እነዚህ [ሕፃናት] ዝም ቢሉ እነዚህ ድንጋዮች ያመሰግናሉ” ። በመጨረሻም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በዚያ የማይገባ ሥራ ይሠሩ የነበሩትን አውጥቶ ተአምራትን አደረገ። ይኽን ከላይ የተጠቀሰውን ታሪክ በማስተዋል ስንመረምረው እጅግ ጥልቅና ረቂቅ የሆኑ ምሥጢራትን እናገኛለን። አበው ሊቃውንት አምልተው አስፍተው ካስቀመጡልን ትምህርታቸውም በትንሹ ለማየት እንሞክራለን።

. አህያዋና ውርንጫዋ:  በዚህ ዓለም አህያ ለሸክም የሚያገለግል፣ የተናቀ፣ ነገር ግን ትሑት የሆነ እንስሳ ነው። ከዚህ በተጨማሪም አህያ እንደ በቅሎ ሰጋር እንደ ፈረስ ፈጣን አይደለም። በአህያ የተቀመጠ ሰውም አሳድዶ አይዝም፤ ጋልቦ ሮጦም አያመልጥም። ተሸክሞ እንኳን በዱላ እየተደበደበ አህያ ጌታውን በቅንነት ያገለግላል። ጌታችን በዚህች ትኁት በሆነችው አህያ መገለጡ በትኁታን ለማደሩ ምሳሌ ነው። ራሳቸውን ዝቅ ያደረጉትን እርሱ በረድኤት ያድርባቸዋል። በዘባነ ኪሩብ አድሮ የሚኖር ጌታ የአህያን ጀርባ መረጠ። እርሱን በሃይማኖት ለሚሹት፣ በሕግ በአምልኮ ለሚከተሉት የቅርብ አምላክ ነው። በጽኑ መከራ በሰቆቃና በስቃይ ውስጥ ሳይቀር በሃይማኖት ጸንተው ተስፋ የሚያድርጉትን ተስፋቸውን እውን ያደርግላቸዋል። ጌታችን የተቀመጠባቸው አህዮች አንደኛዪቱ ጭነት የለመደች ሁለተኛዪቱ ደግሞ ገና ያልለመደች ናት። እርሱ ግን በሁለቱም ተቀመጠባቸው። ጭነት የለመደችው ሕገ ኦሪትን መጠበቅ የለመዱ የእስራኤል ዘሥጋ፣ ውርንጫዪቱ ደግሞ የአሕዛብ ምሳሌ ናቸው። እነርሱ ገና ሕግ መጠበቅን አልለመዱም ነበርና ጌታችን ወድዶ ፈቅዶ ባደረገው ቤዛነት ሕዝብም አሕዛብም በእርሱ አምነው ማደርያዎቹ ሆነዋል።

. ልብስ: ደቀ መዛሙርቱ አህያዪቱን ከነውርንጫዋ ከታሰረችበት ቦታ ፈትተው እንዳመጡለት በዚያ የነበሩት ሰዎች ልብሳቸውን በአህያዪቱና በውርንጫዪቱ ጀርባ ጎዘጎዙ፤ አህያዪቱ ተራምዳ በምትሄድበት መንገድ ሁሉ ልብሳቸውን አነጠፉ። ይኽም ምሳሌ ነው። ልብስ የውስጥ ገመናን ከታች (ሸፋኝ) ነው። አንተ ገመናችንን ከታች ነህ ሲሉ ልብሳቸውን ጎዘጎዙለት። በሌላ በኩልም ልብስ ክብር ነው። ያስከብራል። ያንን የሚያስከብረውን ልብስ አነጠፉለት። ክብራችን አንተ ነህ ሲሉ ክብራቸውን ዝቅ አደረጉለት። የተናቀች የነበረችው አህያ ጌታችን ስለተቀመጠባት ክብር አገኘች። የሰዎች ልብስ እየተነጠፈላት በክብር ሄደች። እግዚአብሔር በረድኤት ሲያድርብን ይንቁን ያንገላቱን የነበሩት ሁሉ ያክብሩናል። ቅዱሳን በዚህ ዓለም ሲኖሩ ብዙ መከራ ተፈራርቆባቸዋል። ዓለም ትቢያና ጉድፍ አድርጓቸዋል። ይኹን እንጂ በሃይማኖታቸው ጽናት በምግባራቸው ቅናት እግዚአብሔር አድሮባቸው ሁሉ ያከብራቸዋል። አስጨናቂዎቻቸውን ሳይቀር ይገዙላቸዋል።

. የዘንባባ ዝንጣፊ:  ጌታችን በሚያልፍባቸው የኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ያጀቡት ሰዎች የዘንባባ ዝንጣፊ የዛፍም ጫፍ እየቆረጡ በመያዝ ያመሰግኑት ነበር። ይኽም የደስታ የድል አድራጊነት ምሳሌ ነው። አብርሃም ይስሃቅን፣ ይስሃቅ ያዕቆብን በወለዱ ጊዜ፣ እስራኤል ከግብፅ በወጡበት ወቅት፣ ዮዲት ሆሎፎርኒስን በገደለች ጊዜ ዘንባባ ቆርጠው ይዘው እግዚአብሔርን አመስግነዋል። ክርስቶስ በታላቅ ግርማ ወደ ኢየሩሳሌም እየገባ ስለነበር ደስታቸውን አዕጹቀ በቀልት ይዘው ዘመሩ። በላያቸን ለዘመናት ነግሦ የነበረውን ዲያብሎስንና ሥራዎቹን ሞትንና ሙስና መቃብርን ድል ሊነሣ ጌታ መጥቷልና ደስ እያላቸው ዘንባባ ይዘው አመሰገኑት። ከፊት ከኋላ ያሉትም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “ሆሳዕና ለወልደ ዳዊት፤ ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፤ ለዳዊት ልጅ መድኃኒት መባል ይገባዋል፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው” እያሉ ዘመሩ። ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት ከልደተ ክርስቶስ አስቀድሞ በትንቢት መንፈስ “እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይኽቺ ናት፣ በእርስዋ ደስ ይበለን፣ ሐሴትም እናድርግባት። አቤቱ እባክህ አሁን አድን፣ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና። በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው”  (መዝ. ፻፲፯፣፳፬ – ፳፮) ብሎ እንደዘመረው አመሰገኑት።

. ጌታችን በቤተ መቅደስ: በብዙ ምስጋናና እልልታ ይልቁንም ሽንገላ ከሌለበት ከሕፃናት አፍ የሚፈልቀው ምስጋና እየቀረበለት በልዩ ግርማ ጌታችን በኢየሩሳሌም አደባባይ አቋርጦ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ። በቤተ መቅደሱ የጠበቀው ነገር ግን እርሱ ለቤቱ የፈቀደው ቅድስናና ክብር አልነበረም። አህዮቹን ከታሠሩበት አስፈትቶ ይዞ ወደ ቤተ መቅደሱ በመጣበት ሰዓት ለክብሩ የማይገባ የተፈቱትን አህዮች ወደ ኋላቸው የሚመልሳቸው ሥጋዊ ሥራ እየተፈጸመበት የሥጋ ገበያ ቦታ ሆኖ ነው ቤተ መቅደሱን ያገኘው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህች ምድር በሥጋ ተገልጦ እየተመላለሰ ባገለገለባቸው ዓመታት ውስጥ ከተቆጣባቸው ጥቂት ጊዜያት አንዱ በሆሳዕና ዕለት ወደ ቤተ መቅደሱ ሲገባ ነው። የጸሎት ቤት የሆነችውን የእግዚአብሔር ቤት  አይሁድ የገበያ ቦታ የቅሚያና የዝርፊያ አደባባይ አደረጓት። በዚህም ትሑቱ ጌታ ተቆጣ። በዚያ ይሸጡ ይለውጡ የነበሩትን አስወጣቸው። ወንበራቸውን ገለበጠው። ቤቱን ቀደሰው። “ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል” እንዲል ቅዱስ ዳዊት። አነፃው፤ ለየው፤ አከበረው፤ ወደ ቀድሞ ክብሩ መለሰው። ይኽን ቤት ነገረ ምፅአቱን ለደቀ መዛሙርቱ ባስተማረበት ወቅት ትቶት ሄዶ ነበር። “ጌታችን ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሄደ” እንዲል ቅዱስ ማቴዎስ። የሆሳዕና ዕለት ግን ለሐዲስ ኪዳን አገልግሎት እንዲሆን ነጋዴዎቹን አጭበርባሪዎቹን አውጥቶ አጽድቶ ሰጠን። በዚያም በተቀደሰው ቤተ መቅደስ “በቤተ መቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ መጡ፤ አዳናቸውም” ተብሎ እንደ ተጻፈው። ማቴ ፳፩፣ ፲፬።

ዛሬስ ጌታችን በየአጥቢያችን ወዳለው ቤተ መቅደስ ቢመጣ ወይም ቤተ መቅደስ ወደ ተባለው ሰውነታችን ቢመጣ ይኽን ቤተ መቅደሱን በተገቢው ክብሩ ያገኘው ይሆን?” የገበያ ስፍራ ያልሆነ፣ ከንብረት እስከ ሰው ያልተሸጠበት ቤተ መቅደስ ይኖር ይሆን? የጸሎት ቤት የነበረው ቤቱ እንደዚያን ዘመን ዛሬም ከጸሎት ቤትነት ይልቅ የነገር፣ የክርክር፣ የፖለቲካ፣ የክስ፣ የወንጀል ሁሉ መፈጸሚያ አልሆነምን? ሙስና የነገሠባቸው “አገልጋዮች” በሚፈጽሙት ኢ-ክርስቲያናዊ በደል ምዕመናን ከቤተ መቅደሱ ተገኝተው ጸሎት ማድረግ ተስኗቸው እየተሰቃዩ፣ እያዘኑና እያለቀሱ የሚገኙባቸው ቤተ መቅደሶች የሉንምን? ያኛውን ቤተ መቅደስ ያጸዳው የገሊላ አውራጃ ከምትሆን ከናዝሬት የወጣው ጌታ ነበር። አሁን ግን ያ ጌታ ከሰማይ በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት በቅዱሳን መላእክት ታጅቦ ይመጣል። አንደበት ሁሉ በፊቱ ዝም ይላል። እርሱም ዝም አይልም።

. የሊቃነ ካህናትና የጸሐፍት መቆጣት:  የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ ክቡር በሆነ ምስጋና መመስገን፣ የቤተ መቅደሱ በክርስቶስ መጽዳትና ወደ ቀደመ ክብሩ መመለስ ሊቃነ ካህናትንና ጸሐፍቱን አላስደሰታቸውም። በክፋትና በተንኮል ካባ እንደተጀቦኑ ጻድቃን መስለው ለዘመናት ትሑትና የዋህ የሆነውን ሕዝበ እግዚአብሔር ሲያታልሉ የነበሩት እነዚህ አካላት በጽድቁ ክፋታቸውን የሚገልጥባቸው የክርስቶስ በክብር መገለጥ እንዲሁም መመስገን አስቆጣቸው። የእርሱ መገለጥና መመስገን እነርሱን የሚያሳንስ ክፋታቸውን የሚገልጥ መሆኑን ተረዱት። ጌታችን በወንጌል “ሥራው ክፉ የሆነ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ክፉም ስለሆነ ሥራው እንዳይገለጠበት ወደ ብርሃን አይመጣም (ዮሐ. ፫፣፳)” እንዳለው ሆነባቸው።

የክፉዎች የመጨረሻው ክፋታቸው ክፉ መሥራታቸው ብቻ ሳይሆን በጎ የሚሠሩትን ሰዎች በዓይናቸው እንኳን ለማየት አለመፈለጋቸው ነው። የቅኖች ደግነት፣ የመልካሞች በጎ ሥራ፣ የትሑታን የተሰበረ መንፈስ ይረብሻቸዋል። ማንነታቸውን ያጎላዋል። እናም ጌታችን ሲመሰገን መስማት አለፈለጉም። ግን እኮ አመስግኑ ያላቸው የለ። አላመሰገናችሁም ብሎ የወቀሳቸውም የለ። ሕሊናቸው ቢረብሻቸው “ሕጻናቱን ዝም አሰኝ” ብለው ለክርስቶስ ነገሩት።

የእነዚህ ደቀ መዛሙርት ዛሬም አሉ። እግዚአብሔር ሲመሰገን፣ ሰው ንስሐ ሲገባ፣ ወንጌል የሚያስተምሩ እውነተኛ መምህራን ሲበዙ፣ ሰላም ሲሰፍን፣ አንድነት ሲጸና፣ ሕገ እግዚአብሔርን የሚያከብሩ ሰዎች ሲገኙ፣ ደናግላን በድንግልናቸው ሲጸኑ፣ በትዳር ያሉ ትዳራቸውን ሲያከብሩ፣ የመነኮሱ ቆባቸውን አክብረው ሲይዙ፣ የደኸየው ሠርቶ ሲያገኝ ወዘተ… ማየትና መስማት የማይፈልጉ አሉ። ሁሉም እንደነርሱ ሲሆን ማየት ይፈልጋሉ። ዓለም ሳይፈጠር ባሕርይው ባሕርይውን እያመሰገነ ምስጋናው ሳይቋረጥ የኖረውን ጌታችንን ሕጻናት “ለምን አመሰገኑህ?” ብለው ያላዋቂ ጥያቄ ጠየቁት። በዚያ ስፍራ ያሉ ዝም ቢሉ ምስጋናው የሚቋርጥ መሰላቸው። እርሱ ግን “ለእመ አርመሙ እሎንቱ አእባን ይኬልሁ፤ እነዚህ [ሕፃናት] ዝም ቢሉ እነዚህ ድንጋዮች ያመሰግናሉ” አላቸው።

. ትቶአቸው ሄደ: የታሰሩትን ፈትቶ ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ፣ ቤተ መቅደሱንም ባርኮ ፈውስ በረከት አሳድሮበት፣ ተመስግኖበት ለዘላለምም የሚመሰገንበት መሆኑን ለተቃወሙት አስረድቶ ሲያበቃ “ትቶአቸው ከከተማው ወደ ቢታንያ ሄደ። በዚያም አደረ” እንዲል ሊቃነ ካህናቱንና ጸሓፍቱን ትቶአቸው ሄደ። ክህነታቸው አለፈች። ያላቸውን ክብር፣ ሀብት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቅንና ትሑት ልቡና ለነበራቸው ለሐዋርያት ተሰጠች። እግዚአብሔር በተለያዩ መንገዶች ክብሩን አምላክነቱን ይገልጥልናል። የልቡናችንን በር ያንኳካል። በቃሉ ይጠራናል። ተገቢውን ምላሽ በጊዜው ካልሰጠነው ትቶን ያልፋል። እነርሱን ጌታችን ትቶአቸው ሄዷልና በ፸ ዓ.ም ጥጦስ ከሮም ዘምቶ ቤተ መቅደሳቸውን አፍርሶ እነርሱንም መትቶ ሀገሪቱን ወና አደረጋት። እኛንስ ዛሬ ቢመጣ ወደ እኛ የሚያስገባው ከእኛም ጋር እንዲያድር የሚያደርገው በጎ መዓዛ ያለው ምግባር ይኖረን ይሆን?

በአጠቃላይ:- በዓለ ሆሳዕና ደቀ መዛሙርት የታሰሩትን ለመፍታት የተላኩበት፣ አህዮችም ከእስራታቸው የተፈቱበት፣ አዋቂዎች ሲለጎሙ ሕጻናት ያመሰገኑበት፣ ጌታችን ቤተ መቅደሱን ያጸዳበት፣ እናውቃለን ባዮችን ግን ትቶ የሄደበት በዓል ነው። በዚህን ቀን አህዮቹ ከጌታችን የተላኩላቸውን ፈቺዎቻቸውን (ደቀ መዛሙርቱን) አላስቸገሯቸውም። እንደ ልቧ መቦረቅ የምትወድ ውርንጫ እንኳን አደብ ገዝታ ፈቺዎቿን ተከትላ ሄደች። እኛስ? ከታሰርንበት የክፋትና የኃጢአት ሁሉ ማሰርያ መች ይሆን የምንፈታው? ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላኩልንን እውነተኞቹን አባቶቻችን ካህናቱን እናውቃቸው ይሆን? ለእግዚአብሔር ክብር ሳይሆን ለራሳቸው ጥቅም በቤቱ ያሉትን የእግዚአብሔር አገልጋዮች የሚመስሉ ግን እግዚአብሔርን የማያውቁትን “አገልጋዮችን” እናውቃቸው ይሆን? እንግዲህ እንደዚያን ዕለት ሰዎች ልብሳችንን ሳይሆን ልባችንን፣ የዛፍ ቅርንጫፍ ሳይሆን ራሳችንን በጌታችንና የእርሱ እውነተኛ አገልጋዮች በሆኑ በቅዱሳኑ ፊት ዝቅ እናድርግ። ለዚህም የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሁሉ ተራዳኢነት አይለየን። አሜን።

 

ኒቆዲሞስ፡ የትህትና፣ የትጋትና የጽናት አብነት

የኒቆዲሞስ አብነትblue

በዲ/ን  ብሩክ ደሳለኝ (ዶ/ር)

በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን የበዓላት ቀኖና መሰረት ሰባተኛው የዐቢይ ጾም ሰንበት ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡ በግሪክ ቋንቋ ኒቆዲሞስ ማለት “አሸናፊ/ነት” ማለት ነው፡፡ በዚህ ሰንበት በዮሐ 3፡1-21 እንደተገለጸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ለተባለ የአይሁድ አለቃ ያስተማረው ትምህርት እንዲሁም የኒቆዲሞስ አስተማሪ ስብእና ይነበባል፣ ይተረጎማል፣ ይዜማል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓ የሰባተኛ ሣምንት መንፈሳዊ ድርሰቱ የኒቆዲሞስን በዓል አስመልክቶ ሲዘምር “ሖረ ኀቤሁ ዘስሙ ኒቆዲሞስ ወይቤሎ ለኢየሱስ ረቢ ሊቅ ንሕነ ነአምን ብከ ከመ እምኀበ አብ መጻእከ ከመ ትኩን መምህረ፤ ዕጓለ አንበሳ ሰከብከ ወኖምከ አንሥአኒ በትንሣኤከ ክርስቶስ/ኒቆዲሞስ የተባለው ሰው ወደ ጌታችን ኢየሱስ ሄደ፤ መምሕር ሆይ ልታስተምር ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ እንደመጣህ እናምንብሃለን አለው። የአንበሳ ደቦል ተኛህ፣ አንቀላፋህም፤ በትንሣኤህ አንሣኝ/ ብሏል፡፡ ይህም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ያስተማረውን ትምህርት የሚያመሰጥር ድንቅ ዜማ ነው፡፡ የዚህች አጭር የአስተምህሮ ጦማር ዓላማም ከኒቆዲሞስ ሕይወት መማር እንችል ዘንድ የኒቆዲሞስን ጠንካራ ስብእና እና መንፈሳዊነት የሚያሳዩ መገለጫዎችን መተንተንና እኛም አርዓያውን እነድንከተል መምከር ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከኒቆዲሞስ ሕይወት የምንማራቸው ቁም ነገሮችም እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

አትኅቶ ርዕስ (ራስን ዝቅ ማድረግ) – ኒቆዲሞስ መምህር ሲሆን ራሱን ዝቅ አድርጎ የተማረ የትህትና አርአያ ነው፡፡

ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ ብቻ ሳይሆን የፈሪሳውያን አለቃ፣ የኦሪት መምህር ብቻ ሳይሆን የኦሪት ምሁርም ነበር፡፡ በእርሱ ደረጃ የነበሩ ታላላቅ የአይሁድ ምሁራን መንፈሳዊ ስልጣናቸውና ሹመታቸው የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ረስተው በህዝቡ ላይ የሚመፃደቁ ነበሩ፡፡ በዘመናቸው እውቀትን የሚገልጥ እውነተኛ አምላክ፣ የካህናት አለቃ ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም ሲገለጥ የአይሁድ ምሁራን የጌታን መገለጥ አልወደዱትም፡፡ የእርሱ ትህትና የእነርሱን ትዕቢት የሚያጋልጥ ነበርና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሄዱትን ሁሉ ይነቅፉ ይከስሱ ነበር፡፡ ባለማወቅ ያደነደኑት የትዕቢት ልቦና ትህትናቸውን አጥፍቶባቸው ነበርና ዝቅ ብሎ በሰው ዘንድ በተናቁት በናዝሬትና በገሊላ እየተመላለሰ የሚያስተምር የዓለም ቤዛ የክርስቶስን ትምህርት እንዳይሰሙ ልባቸው ተዘግቶ ነበር፡፡ ጌታችንም የፈሪሳውያን ሀሳባቸው በግብዝነት የተሞላና ከንቱም እንደሆነ ነግሯቸዋል፡፡ ለደቀመዛሙርቱም ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ የሚበልጥ ሥራን እንዲሰሩ አስጠንቅቋቸዋል (ማቴ 5: 20 ማቴ 16:6)፡፡

ኒቆዲሞስ ግን ከእነዚህ ከፈሪሳዊያን መካከል የተገኘ ልዩ ምሁረ ኦሪት ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ራሱን ለእውነት ልቡን ለእምነት አዘጋጅቶ ከዅሉ ቀድሞ በሌሊት ክርስቶስን ፍለጋ የመጣ ከእነዚህ ፈሪሳዊያን ወገን ተለይቶ እንደ አባታችን አብርሃም ወደ ጽድቅ መንገድ የተጠራ ነው፡፡ ሹመት እያለው ሁሉ ሳይጎድልበት በዙርያው የነበሩት ከእኛ በላይ ማን አዋቂ አለ የሚሉ ከእውነት ጋር የተጣሉ ጌታችንን የሚያሳድዱ በእርሱም የሚቀኑና ጌታችንንም ለመግደልም ዕለት ዕለት የሚመክሩ ሁነው ሳለ ኒቆዲሞስ ግን እውነትን ለማወቅ እልቅናው ሳይታሰበው ከአካባቢው ጋር መመሳሰልን ሳይመርጥ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሊማር በሌሊት መጣ፡፡ መምህረ ትህትና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የኒቆዲሞስን ትህትናውን ተቀብሎ ለምን በቀን አትመጣም?” ሳይለው እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ትውልድ ሁሉ የሚማርበትን ረቂቁን ምስጢረ ጥምቀትን አስተማረው፡፡

አልዕሎ ልቡና (ልቡናን ከፍ ከፍ ማድረግ) – ኒቆዲሞስ ዳግመኛ የመወለድን ምስጢርን ለማወቅ ልቡናውን ከፍ ከፍ አደረገ፡፡

ለሥጋዊ ሕይወታችን እውቀት እንደሚያስገፈልገን ሁሉ ነፍስም ዕውቀት መንፈሳዊ ዕውቀት ያስፈልጋታል (ምሳ. 19፥2)፡፡ ኒቆዲሞስ በመጀመርያ የጥምቀትን ነገር ሲሰማ ለመቀበል ተቸግሮ ነበር፡፡ ጌታችን ግን የኒቆዲሞስን አመጣጥ በማየት ልቡናውንም ከፍ ከፍ ስላደረገ ምስጢረ ጥምቀትን ገለጸለት፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በሥርዓተ ቅዳሴ ምእመናንን በማነቃቃት ልቡናቸውን ከፍ እንዲያደርጉ “አልዕሉ አልባቢክሙ/ልቦናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ” ብሎ የሚያዘው ምእመናን የቅዱስ ሥጋውና የክቡር ደሙ ምስጢር እንዲገለጽልን፣ ከሥጋዊው መብል ሃሳብ ወደ ሰማያዊው መብል ልቡናችንን እንድናነሳ ሲያሳስብ ነው፡፡ ምእመናንም በጸሎተ ቅዳሴ ካህኑ የቅዱስ ኤጲፋንዮስን ትዕዛዝ ሲያሰማ “በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ አለን” በማለት እንመልሳለን።

መንፈሳዊ መረዳት የሚኖረንና በፈተናዎች ውስጥ ድል መንሳትን የምናገኘው ልቡናን ከፍ በማድረግ ከሁሉም የሚበልጠውን መንፈሳዊውን መንገድ በመከተል ነው፡፡ ግያዝ ከነብዩ ኤልሳዕ ጋር ሳለ ልቡናው ቁሳዊውን የሚመለከት እንጂ ሰማያዊውን ኃይል የተረዳ አልነበረም፡፡ ነብዩ ኤልሳዕ ግን ይህንን ምስጢር እንዲያይ ገለጸለት (2 ነገ 6:17)፡፡ እኛም ክርስቲያኖች በጸጋ የተሰጡንን ስጦታዎቻችንን እንድናውቅ ልቡናችንን ከፍ ከፍ አድርገን በመንፈሳዊ እውቀትና ልዕልና፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመረዳት፣ እንዴት በጽድቅ መመላለስ እንዲገባንና ስለምንወርሳት መንግስተ ሰማይ መማር ማወቅ ይገባናል፡፡ “ቅዱሱን ማወቅ ማስተዋል ነው” ተብሎ በምሳሌ መጽሐፍ እንደተጻፈ (ምሳ 9፥11) ኒቆዲሞስ ከፈሪሳውያን ህብረት ወጥቶ በትህትና ወንጌልን ለመማር በሃይማኖት ልቡናውን ለእግዚአብሔር ቃል አዘጋጀ፡፡ ለአብርሃም የግዝረትን ጸጋ የሰጠ ጌታ በትህትና ለቀረበው ኒቆዲሞስ የግዝረት ጸጋ ፍጻሜ የሆነች የልጅነት ጥምቀትን ነገር አስተምሮታል፡፡

ትግሃ ሌሊት (በሌሊት መትጋት) – ኒቆዲሞስ ቀን እየሠራ በሌሊት ወደ ጌታ በመሄድ ለትጋት አብነት ሆነን፡፡

ኒቆዲሞስ ወደ መድኃኔዓለም ለመማር የሄደው በሌሊት ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ በሚታሰብበት የዐቢይ ጾም ሰንበት በጸሎተ ቅዳሴ የሚዜመው የክቡር ዳዊት መዝሙር  “ሐወፅከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ፡፡ አመከርከኒ ወኢተረክበ ዐመፃ በላዕሌየ፡፡ ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ ዕጓለ እመሕያው/በሌሊት ጎበኘኸኝ፤ ልቤንም ፈተንኸው፣ ፈተንኸኝ፣ ዐመፅም አልተገኘብኝም፡፡ የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር” (መዝ. 16፡3)ይህን የሚያስረዳ ነው፡፡ ሌሊት በባህሪው ሕሊናን ለመሰብሰብ በተመስጦ ለመማር የሚመች ነው፡፡ ክርስትናም በተጋድሎ ሕይወት በመትጋት ሥጋን በቀንና ሌሊት ለነፍስ እንዲገዛ በማድረግ የሚኖር ሕይወት ነው፡፡ ጌታችን ሐዋርያቱን “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ” ባለው መሠረት ቤተክርስቲያንም በቀንና በሌሊት በኪዳኑ በቅዳሴው በማህሌቱ እግዚአብሔርን ታመሰግናለች፡፡ የቅዱሳን አባቶቻችን (አባ ቢሾይ) በሌሊት ጸሎት እንቅልፍ እንዳያስቸግራቸው ፀጉራቸውን ከዛፍ ቅርንጫፍ በማሰር ይተጉ ነበር፡፡ ለኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ ወደ ጌታችን መምጣት ልጅነትን ለምናገኝበት የምስጢረ ጥምቀት ትምህርት እንደተገለጠለት እኛም በሌሊት በነግህ ጸሎት በመትጋት ረቂቅ የሆነውን መንፈሳዊ እውቀት ሰማያዊ ምስጢር ይገለጥልናል፡፡

በዘመናችን ከቀድሞ ይልቅ ፈተና የሚገጥመን በሌሊት ከመትጋት ይልቅ አርአያነት በጎደለው ሕይወት ውስጥ ስንገኝ ነው፡፡ “ሌሊት ጌታን ለማመስገን የተፈጠረ ድንቅ ጊዜ ነው” እንዳለ ሊቁ ማር ይስሐቅ ራስን በቀንም በሌሊት ከሚመጣ ፈተና መጠበቅ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር የሙሴን አገልጋይ የነዌን ልጅ ኢያሱን እንደተናገረው በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ማንም እንዳይረታው፣ ከሙሴ ጋር እንደነበረ ከእርሱ ጋር እንዲኖር “ለአባቶቻቸው እሰጣቸዋለሁ” ብሎ የማለላቸውን ምድር እንዲወርስ በሚሔድበት ሁሉ እንዲከናወንለት ወደ ቀኝም ወደ ግራም እንዳይል ሃሳቡም እንዲቀና የምጽሐፉን ሕግ ከአፉ እንዳይለይ እንዲጠብቀውም በቀንም በሌሊትም ማሰብ እንደሚገባ ይነግረናል (ኢያ 1:1-8):: ቅዱስ ይስሐቅ ሶርያዊ “ከመኝታህ በፊት የምታደርገውን ጸሎት ትተህ እንድትተኛ መንፈስህ ሲገፋፋህ እሺ ብለህ አትቀበለው፡፡ እንዲያውም መዝሙረ ዳዊትን ጨምርና ሌሊቱን በሙሉ ስትጸልይ እደር’ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት “በሌሊት በቤተ መቅደስ ውስጥ እጆቻችሁን አንሡ፥ እግዚአብሔርንም ባርኩ።” መዝ 134:1-3 እንዳለ እኛም ከዚህ የፈተና ዓለም ለማምለጥ በኦርቶዶክሳዊ ሰውነት እንድንጸና በትጋት ወደ ቤተ ክርስቲያን በቀንና በሌሊት ልንገሰግስ በኪዳኑ በማኅሌቱ በቅዳሴው ጸሎት ልንሳተፍ ያስፈልጋል፡፡

ስምዐ ጽድቅ (የእውነት ምስክርነት) – ኒቆዲሞስ ማንንም ሳይፈራ እውነትን በመመስከር ከሳሾችን አሳፈራቸው፡፡ 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እኔ ለእውነት ለመመስከር መጥቻለሁ›› በማለት እውነትን እንድንመሰክር አብነት ሆኖናል (ዮሐ.18፥37)፡፡ በተጨማሪም ‹‹በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፡፡ በሰው ፊት የሚክደኝን ሁሉ ደግሞ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ›› ሲል ስለ ሃይማኖታችን እውነትን መመስከር እንደሚገባን አስተምሮናል (ማቴ.10፥32-33)፡፡ እንዲሁም ለኒቆዲሞስ ሲያስተምረውም ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን›› በማለት ለእውነት መመስከር እንደሚገባ አስገንዝቦታል (ዮሐ 3፡11)፡፡ይህንን ቃል ከራሱ ጋር በማዋሀድ የአይሁድ የፋሲካ በዓል በቀረበበት ወቅት ጻፎችና የካህናት አለቆች ጌታን ለመያዝ፣ የሙሴን ሕግም አጣምመው ሊያስፈርዱበት በሚጥሩበት ጊዜ ኒቆዲሞስ የእውነት ምስክርነቱን አረጋገጠ፡፡ የሙሴ ፈጣሪ መሆኑን ባለማወቃቸው ምክንያት የካህናት አለቆች ተሰብስበው ክርስቶስን ለመያዝ ሲመካከሩ ከሙሴ መጽሐፍ ሕግ ጠቅሶ ሊቃውንተ ኦሪትን አፍ ያስያዛቸው እርሱ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ሳይስማሙ ወደየቤታቸው እንዲበታተኑ ምክንያት የሆነ ታላቅ ሰው ነው፡፡ 

ዮሐንስ ወንጌላዊ ይህንን የኒቆዲሞስን ምስክርነት “ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው። እነርሱም መለሱና፡- አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ አሉት። እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ሄደ።” በማለት ገልጾታል (ዮሐ 7-50-52)፡፡ ኒቆዲሞስ ያለፍርሐትና ያለ ሀፍረት በካህናቱ ፊት እውነትን መስክሯል፡፡ እውነትንና ፀሐይን ፈርቶ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ካህናቱን መጽሐፍ ጠቅሶ እውነትን ተናግሮ አሳፍሯቸዋል፡፡ በመሪዎች ፊት በታላላቅ ሰዎች ፊት እውነትን መመስከር ክርስትናችን የሚያስገድደን ቁም ነገር ነው (ሉቃ 12፡ 8)፡፡ ቤተክርስቲያን “ሰማዕታት” እያለች የምትዘክራቸው ቅዱሣን በሙሉ ለእውነት ብለው ራሳቸውን ለክርስቶስ አሳልፈው የሰጡ ናቸው፡፡ በፍርሐትና በሀፍረት በይሉኝታና በሀዘኔታ እውነትን አለመመስከር በክርስቶስ ፊት ያስጠይቃል እንጅ አያስመሰግንም (ማቴ 10፡32)፡፡ ሐዋርያው “ለእውነት እንጅ በእውነት ላይ ምንም ማድረግ አንችልም” እንዳለ እኛም እንደ ኒቆዲሞስ የእውነት ምስክሮች እንሁን (2ቆሮ 13፡8)፡፡

ጽንዐ ሃይማኖት (በሃይማኖት መጽናት) –  ኒቆዲሞስ እስከ መጨረሻው በመጽናት ለታላቅ ክብር በቃ፡፡

 በጌታችን ትምህርት ተስበው ተዓምራቱን በማየት ከተከተሉት ሰዎች ውስጥ በቀራንዮ የተገኙት ጥቂት ናቸው፡፡ ከእነዚህ አንዱ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ ቀራንዮ የምግበ ነፍስ ቦታ ናትና ኒቆዲሞስም ፈተናን ሳይሰቀቅ እስከ መጨረሻው የጸና ፃድቅ ነው፡፡ የክርስትና አገልግሎት ሲመቸን የምንሳተፍበት ፈተና ሲበዛ የምንሸሽበት አይደለም፡፡ ክርስትና በጅምር የሚቀር ሳይሆን እውነትን ሳንፈራ በመመስከር በተጋድሎ የምናሳልፍበት ለፈጸሙትም የድል አክሊል የሚያገኙበት ሕይወት ነው (2ጢሞ 4:8)፡፡ ምሳሌ ከሚሆኑን ቅዱሳን አንዱ አባታችን ቅዱስ እንጦንስ በፍጹም መንፈሳዊ ተጋድሎ ለ35 ዓመታት ከዚህ ዓለም ተድላና ደስታ በመራቅ እንዲሁም በአህዛብ መካከል ክርስትናን በመግለጽ የጽናት ታላቅ አስተማሪ ነው::

ኒቆዲሞስም ከጌታችን በተማረው ትምህርት ጸንቶ ለመኖር የበቃ አባት ነው፡፡ የሃይማኖቱ ጽናትም በተግባር የተፈተነ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ የአርማትያስ ሰው ከሚሆን ከዮሴፍ ጋር በመሆን የአይሁድን ድንፋታ ሳይፈራ “እሱን ያገኘ ያገኘኛል” ሳይል በድፍረት የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውን በንጹሕ የተልባ እግር በፍታ ገንዞ በአዲስ መቃብር፣ በጌቴሴማኒ የቀበረ ሰው ነው (ዮሐ 19፥ 38)፡፡ ኒቆዲሞስ ከሐዲስ ኪዳን ካህናት ቀድሞ የጌታችንን ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሀደው ክቡር ሥጋ ለመገነዝ የበቃ አባት ነው፡፡ የጌታችንን ክቡር ሥጋ ገንዘው ሲቀብሩም በጸናች የተዋህዶ እምነት ጌታ እንደገለጠላቸው “ቅዱስ እግዚአብሔር፣ ቅዱስ ኃያል፣ ቅዱስ ህያው ዘኢይመውት” የሚለውን ቤተክርስቲያናችን እስከ ዕለተ ምጽአት የክርስቶስን ሥጋና ደም ስትባርክ የምትጠቀምበትን ጸሎት እስከ ፍፃሜው እየጸለዩ ነበር፡፡ በዚህም ኒቆዲሞስ ከሐዲስ ኪዳን ካህናት ቀድሞ ምስጢረ ጥምቀትን ከጌታ እንደተማረ፣ የሐዲስ ኪዳንን የምስጢራት አክሊል ምስጢረ ቁርባንንም እንዲሁ ተማረ፡፡ ይህንንም በሚመለከት ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ አብሮት ይቀድስ የነበረውን ንፍቅ ካህን በባረከበት አንቀጽ “በዚህ ምስጢር እየተራዳኝ ከእኔ ጋር ያለ ይህንን ካህን እርሱንም እኔንም ሥጋህን እንደገነዙት እንደ ዮሴፍና እንደ ኒቆዲሞስ አድርገን” (ቅዳሴ ማርያም ቁጥር 115) ብሏል፡፡

እኛም እንደ ኒቆዲሞስ፡-

  1. በዕውቀታችን፣ በስልጣናችን፣ በሀብታችን፣ ባለን ማንነት ሳንታበይ ራሳችንን ዝቅ በማድረግ የእውነተኛ አባቶችን ትምህርት፣ ምክርና ተግሳፅ ልናዳምጥ በተግባርም ልናውለው ይገባናል፡፡
  2. የያዝነውን እውነተኛ እምነት በማጠንከር በሃይማኖት ልብ የቤተክርስቲያንን ምስጢራት በትህትና ለመሳተፍ ልቡናችንን ከፍ ከፍ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
  3. ምድራዊ አመክንዮ ሳያሰናክለን በቀንና በሌሊት ወደ አማናዊት የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ለምስጋና መሄድ ይኖርብናል፡፡
  4. እውነትን በማድረግ ሕይወት የሚገኝበትን ቃለ እግዚአብሔርን ያለኃፍረትና ያለፍርሀት ልንመሰክር ያስፈልጋል፡፡
  5. ክርስትና ምድራዊ ስጦታና ተዓምራት በሚገለጥበት በገሊላ ባህር አጠገብ ብቻ ሳይሆን መከራና ስቃይ ባለበት በቀራንዮም መገኘትን ይጠይቃልና በፈተናና በመከራ ጊዜም ቢሆን በእምነት ልንጸና የበለጠም በመታመን ልናገለግል ይገባል፡፡

ከኒቆዲሞስ ሕይወት ተምረን በሃይማኖት እንድንጸና የአባቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

ገብር ኄር፡ ካህናት ብቻቸውን ወደ ገነት አይገቡም!

በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን የበዓላት ቀኖና መሰረት የዐቢይ ጾም ስድስተኛው ሰንበት ገብር ኄር ይባላል፡፡ በዚህ ሳምንት የሚነበበውና የሚተረጎመው በማቴዎስ ወንጌል 25፡14-30 ድረስ የተጻፈው የገብር ኄርና ገብር ሐካይ (የእውነተኛ አገልጋይና የሐኬተኛ አገልጋይ) ምሳሌ (The Parable of Talents) ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24:1-42 የዳግም ምጽዓቱን ነገር ለደቀ መዛሙርቱ አስተማራቸው፡፡ የጌታችን ዳግም ምጽዓቱ ለፍርድ ነውና፣ የሚመጣበትም ቀንና ሰዓት በፍጡራን አይታወቅምና  በፍርድ ቀን በቀኙ መቆም እንድንችል ምን ማድረግ እንዳለብን ሲያስተምር እንዲህ አለ “ስለዚህ እናንተም ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና” ማቴ. 24፡44፡፡ ይህን ከተናገረ በኋላ በሁለት ምሳሌዎች መስሎ አስተማረ፡፡ እነዚህም የዐሥሩ ደናግልና የሦስቱ አገልጋዮች (የመክሊት) ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ሊቃውንት እንደሚያስተምሩን የመጀመሪያው ለምዕመናን ሁለተኛው ደግሞ በዋናነት ለካህናት ተግሳጽ የተጻፉ ምሳሌዎች ናቸው፡፡

እነዚህ ምሳሌዎች ምዕመናን ሃይማኖታቸውን ጠብቀው፣ ምግባራቸውን አቅንተው እንዲኖሩ፣ ካህናትም እንደምዕመናን ሃይማኖታቸውን ከመጠበቅና ምግባራቸውን ከማቅናት ባሻገር ሌሎችን እያስተማሩ በሃይማኖት በምግባር እንዲያጸኑ ለማበርታት የተጻፉ ናቸው፡፡ የዚህ ሣምንት የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ትኩረት መንገድ የሚሄድ ባለገንዘብ ሦስት አገልጋዮቹን ጠርቶ እንዲያተርፉበት መክሊት መስጠቱና ከእነርሱም ሁለቱ ገብር ኄር (እውነተኛ/ታማኝ አገልጋይ) በመሆን የገንዘቡ ባለቤት (ጌታቸው) ሲመጣ መመስገናቸው፣ የዘላለም ህይወት ምሳሌ የሆነ ክብር ማግኘታቸው፣ ሦስተኛው ግን ገብር ሐካይ (ሐኬተኛ/ሰነፍ አገልጋይ) በመሆኑ የገንዘቡ ባለቤት (ጌታው) ሲመጣ እንደገሰጸው፣ የዘላለም ሞት ምሳሌ ወደሆነ የስቃይ ቦታም እንደተጣለ ይተርካል (በማቴዎስ ወንጌል 25፡14-30)፡፡

ጌታችን በመክሊቱ ምሳሌ ያስተማረው ትምህርት ትርጉሙ እንዲህ ነው፡፡ ለሦስቱ አገልጋዮች ገንዘብ የሰጣቸው ባለገንዘብ የአምላካችን የእግዚአብሔር ምሳሌ ነው፡፡ ለሰዎች ሁሉ ጸጋን፣ ስጦታን  የሚሰጥ ጌታ ለአገልጋዮቹ እንደየአቅማቸው አምስት፣ ሁለትና አንድ መክሊት ሰጣቸው፡፡ መክሊት የተባለው የአገልግሎት ጸጋ ምሳሌ ነው፡፡ ጌታችን ለእያንዳንዱ እንደአቅሙ የአገልግሎት ጸጋ ይሰጣልና፡፡ አገልጋዮቹ ደግሞ የአገልግሎት ጸጋ የተቀበሉና ምዕመናንን በመንፈሳዊ ሥርዓት የሚያገለግሉ ካህናትና (እንደአገባቡ) በልዩ ልዩ ጸጋ የሚያገለግሉ ምዕመናን ምሳሌ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ስለዚህ ምሳሌ ሲያስረዳ (በጾመ ድጓ) ‹‹መኑ ውእቱ ገብር ኄር ወምእመን ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይ ወይሠይሞ ዲበ ኲሉ ንዋዩ ካዕበ ይቤሎ እግዚአብሔር ገብር ኄር ወምእመን ዘበውኁድ ምእመነ ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሠይመከ ባእ ውስተ ፍሥሐሁ ለእግዚእከ /ጌታው በመልካም ሥራ የሚያገኘው በሐብቱ ኹሉ ላይ የሚሾመው፤የታመነ በጎ አገልጋይ ማን ነው? ዳግመኛም እግዚአብሔር አንተ የታመንክ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ የታመንህ ስለኾንህ በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ይለዋል፡፡/›› ብሏል፡፡

ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው (እንደ አቅሙ) መክሊት ተሰጥቶታል፡፡ ጌታ ለአንዱ አምስት፣ ለአንዱ ሁለት፣ ለአንዱ አንድ መክሊት የሰጠው እንደየአቅማቸው ነው፡፡ አምስት ለሰጠው ሁለት፣ ሁለት ለሰጠው አንድ፣ አንድ ለሰጠው አምስት መስጠት ተስኖት ሳይሆን እንደችሎታቸው፣ እንደአቅማቸው ሰጣቸው፡፡ ጌታችን፣ ፈጣሪያችን፣ እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን እንደአቅማችን የአገልግሎት ጸጋ ሰጥቶናል፡፡ ሁለት የተሰጠው ለምን አምስት አልተሰጠኝም አይበል፣ ይልቁንስ በተሰጠው ይታመን፤ በተሰጠው ታምኖ ሲያገለግል ይጨመርለታልና፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “መንፈስ ቅዱስ አንድ ሲሆን ስጦታው ልዩ ልዩ ነው፡፡ ጌታም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ፡፡ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አሠራር አለ፡፡ ለሁሉም ጌታ እየረዳ በየዕድሉ እንደሚገባውና እንደሚጠቅመው ለእያንዳንዱ በግልጥ ይሰጠዋል፡፡ “(1ኛ ቆሮ. 12፡4-7) እንዳለ ሁሉም በተሰጠው ጸጋ መጠን እንዲያገለግል መክሊቱን ተቀብሏል፡፡

መክሊት የተሰጠን እንድናተርፍበት ነው፡፡ “አገልጋዮቹንም ጠርቶ ሊያተርፉበት ገንዘቡን ሰጣቸው” እንደተባለ የጸጋ ስጦታን የምንቀበለው እንድናተርፍበት ነው፡፡ ማትረፍ ማለት በሥጋዊ ንግድ እሳቤ ለግል የሚሆን ጥቅም ማግኘት ማለት ሳይሆን የተሰጠንን መንፈሳዊ እውቀት፣ ጸጋ ለሌሎች ማካፈል፣ በዚያም ከራሳችን አልፈን ለሌሎች የድኅነት ምክንያት መሆን ማለት ነው፡፡ የአገልግሎት መክሊት ለሥጋዊ ክብር የሚሰጥ አይደለም፡፡ በዘመናችን ግን የአገልግሎትን መክሊት ለሥጋዊ ጥቅም የሚያውሉ ሐኬተኛ አገልጋዮች በዝተዋል፡፡ እውነተኞቹ፣ ታማኞቹ አገልጋዮች (ገብር ኄር ) ግን መንፈሳዊ ትምህርት፣ መንፈሳዊ ጸጋ ሲሰጣቸው የራሳቸውን ክብርና ጥቅም ንቀው ሌሎች የእግዚአብሔርን ብርሃን እንዲያዩ፣ ለመንግስተ ሰማያት የሚያበቃ እምነትና ምግባር እንዲይዙ ለማድረግ ምክንያት ይሆናሉ፡፡

መክሊት የሰጠ ጌታ አገልጋዮቹን ሊቆጣጠር ይመጣል፡፡ “ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ ተመልሶ ተቆጣጠራቸው” እንዲል ጌታችን እግዚአብሔር አገልጋዮችን፣ እንደ አቅማችን የምናገለግል ሁላችንንም በተሰጠን መክሊት ምን እንዳተረፍንበት ሊቆጣጠረን ይመጣል፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለው ታማኝ አገልጋይ ሄዶ፣ ነግዶ፣ ወጥቶ ወርዶ ሌላ አምስት መክሊት አተረፈ፤ ሁለት የተሰጠውም እንዲሁ በድካም፣ በመታዘዝ ሌላ ሁለት አተረፈ፡፡ እነዚህ አገልጋዮች የተሰጣቸውን እንደችሎታቸው አትርፈዋልና መንግስተ ሰማያትን እንደሚወርሱ በሚያስረዳ ምሳሌ”አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” እየተባሉ ተመሰገኑ፡፡ በገብር ኄር ሰንበት በቅድስት ቤተክርስቲያናችን በጸሎተ ቅዳሴ በሚሰበከው ምስባክ “ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ፡፡ ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ፡፡ ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር ዐቢይ/አምላኬ ሆይ ፈቃድህን ለማድረግ መከርሁ፣ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው፡፡ በታላቅ ጉባኤ ጽድቅህን አወራሁ” (መዝ. 39፡8-9) እንደተባለ ገብር ኄር የተባሉ ደገኛ አገልጋዮች የጽድቅን አገልግሎት ሳይፈሩና ሳያፍሩ በታላቅ ጉባኤ (ፈተና በበዛበት ቦታ ሁሉ) ይናገራሉ፡፡

ሁለቱ ታማኝ አገልጋዮች በመክሊቱ ነግደው ስላተረፉ ተመሰገኑ፡፡ በክቡር ዳዊት መዝሙር እንደተጠቀሰው እውነተኛ አገልጋዮች እውነት የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል በግልጥ ያስተምራሉ፡፡ እውነትን ሲመሰክሩም “እኔን ካሳደዱ እናንተንም ያሳድዷችኋል” (ዮሐ. 15፡20) እንደተባለ ከአላውያን ባለስልጣናት፣ ከከሀድያን፣ ከሐሰተኛ መምህራን፣ ቤተክርስቲያንን መመዝበር ከሚፈልጉ ምንደኞች፣ በዘረኝነት ከታወሩ ሰዎችና ሌሎች ስደትና መከራ ይደርስባቸዋል፡፡ ይህን ታግሰው በአገልግሎታቸው ከጸኑ ለምህረትና ለሥርየተ ኃጢአት የበቁ ይሆናሉ፡፡ በአገልግሎታቸው ወራት ከንቱ ውዳሴንና ምስጋናን ንቀዋልና ጌታቸው ሲገለጥ ተመሰገኑ፤ በአገልግሎታቸው ወራት በእምነት በመውጣትና በመውረድ ደክመዋልና ጌታቸው ሲገለጥ ድካም ወደሌለበት ሰማያዊ ደስታ በቅዱሣን  መላእክት ታጅበው ገቡ፤ በአገልግሎታቸው ወራት በሰው ፊት ስለቀና አገልግሎታቸው ያለአግባብ ተሰድበዋልና ጌታቸው ሲገለጥ በአደባባይ አመሰገናቸው፡፡

ሦስተኛው አገልጋይ ግን ሰነፍ ስለነበር የተሰጠውን መክሊት ሥራ ሳይሠራበት ቀበረው፡ የተሰጠውን የአገልግሎት ጸጋ እንደ አቅሙ ከመጠቀም ይልቅ የመናፍቃንን ክርክርና ሥም ማጥፋት፣ የዓለምን ፈተና፣ የሥጋውን ምኞት መቋቋም አቅቶት መክሊቱን ቀበረው፡፡ ጌታው ሲጠይቀው ግን የተገለጠ ድካሙን ከማስተዋል ይልቅ በሀሰት ቃል ጌታውን ወቀሰው፡፡ ሰነፍ አገልጋዮች ሁሌም እንዲህ ናቸው፤ ለስንፍናቸው ሌሎችን ተጠያቂ ያደርጋሉ እንጅ ወደራሳቸው ተመልክተው ስህተታቸውን አያርሙም፡፡ ጌታም ቅዱሳን መላእክቱን “ይህን መክሊት ከእርሱ ተቀብላችሁ ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት፡፡ ላለው ሁሉ ይሰጡታልና፤ ይጨምሩለታልም፤ ለሌለው ግን ያንኑ ያለውን ይወስዱበታል፡፡”  (ማቴ 25፡28-29) በማለት ተናገረ፡፡ “ላለው ይሰጡታል፣ ለሌለው ይወስዱበታል” የሚለውን አገላለጽ በጥራዝ ነጠቅ አረዳድ መልእክቱን ሳይረዱ የሚተቹ ሰዎች አሉ፡፡ ይህ ቃል በዋናነት የተነገረው ስለመንፈሳዊ ጸጋ፣ ስለመንፈሳዊ አገልግሎት እንጅ ስለምድራዊ ንግድና ትርፍ አለመሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡ ያላተረፈ ካህን፣ ያላተረፈ መምህር፣ ያላተረፈ አገልጋይ ፍጻሜው የዘላለም ሞት መሆኑንም ጌታ በዚህ ሰው ላይ በተናገረው ተረዳን፡፡ “ክፉውን አገልጋይ ግን ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወደ አለ ጨለማ አውጡት፡፡” (ማቴ. 25፡30)

በተሰጠው መክሊት ሠርቶ ያላተረፈበት ተፈረደበት፡፡ ለራሱ በተሰጠው መክሊት ያላተረፈ፣ መክሊቱን የቀበረው አገልጋይ በጌታ ከተፈረደበት የሌሎችን የእውነተኛ አገልጋዮችን የአገልግሎት ጸጋ (መክሊት) አላዋቂነትና ምቀኝነት በወለደው እልህ የሚቀብሩ፣ የጽድቅ አገልግሎትንም የሚያደናቅፉ መናፍቃን፣ ምንደኞችና ዘረኞች በጌታ ፊት ሲቀርቡ ምን ይመልሱ ይሆን?! እንግዲህ እናስተውል! የጽድቅን አገልግሎት ለመቅበር የሚሯሯጡ ምንደኞች መጠቀሚያ መሆን የለብንም፡፡ በመክሊቱ ምሳሌ የተጠቀሰው ሐኬተኛ (ሰነፍ) አገልጋይ ገብር ኄር ከተባሉት ከሁለቱ የታመኑ አገልጋዮች ተለይቶ ለመንግስተ ሰማያት ክብር  የበቃ፣ የተዘጋጀ ያልሆነው በተሰጠው መክሊት ወጥቶ ወርዶ ስላላተረፈ (ስላልሰራበት ነው)፡፡ ካህናት ከሌሎች ምዕመናን በተለየ ተጨማሪ ግዴታ አለባቸው፡፡ ያን ግዴታቸውን እንደአቅማቸው ሳይለግሙ ከተወጡ ክብራቸው በመንግስተሰማያት ከምዕመናን ሁሉ የተለየ እንደሆነ አባቶቻችን አስተምረውናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በመንግስተሰማያት ከአንዱ ኮከብ ክብር የሌላው ኮከብ ክብር እንደሚበልጥ ያስተማረው ይህን ያስረዳናል (1ኛ ቆሮ. 15፡41)፡፡  ይሁንና ካህናት ግዴታቸውን ካልተወጡ፣ ከሃይማኖት የወጡትን፣ በምግባር የደከሙትን ካላበረቱ፣ በአገልግሎታቸውም እንደ ታማኝ አገልጋይ በቅንነት ካላተረፉ ወደ መንግስተ ሰማያት አይገቡም፡፡ ክብራቸው ከምዕመናን እንደሚበልጥ ሁሉ ግዴታቸውም እንዲሁ ይበልጣልና፡፡

የሐኬተኛው አገልጋይ ታሪክ የሚያረጋግጥልን ካህናት ብቻቸውን ወደ ገነት መግባት እንደማይችሉ ነው፡፡  በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ አንድ ሰው ለመዳን እምነት (ሃይማኖት) ከምግባር አስተባብሮ መያዝ አለበት፡፡ ያለሃይማኖት የሚሰራ ምግባር፣ ኑፋቄ ባለበት እምነት የሚሰራ ምግባር ለድኅነት አያበቃም፡፡ ድኅነት በጸጋ ያገኘናት፣ የምናገኛት እንጅ በድካማችን ተመክተን የምናገኛት አይደለችምና፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ቅዱስ ያዕቆብ “ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው” (ያዕ. 2፡26) እንዳለ ያለምግባር በሃይማኖት (በእምነት) ብቻ መዳን አይቻልም፡፡ አምስቱ ደናግል እምነት የተባለ መብራት ነበራቸው፤ ምግባር የተባለ ዘይት ግን ስላልያዙ ከመንግስተሰማያት በአፍአ ቀርተዋል፡፡ ቤተክርስቲያንን የሚያገለግሉ መምህራን፣ ካህናት ከመምህርነታቸው፣ ከክህነታቸው በፊት እንደ አምስቱ ልባም ደናግላን ሃይማኖትን ከምግባር አስተባብረው የያዙ መሆን አለባቸው፡፡ ምዕመን ሳይሆኑ ካህን፣ መምህር መሆን አይቻልም፡፡ እውነተኛ አገልጋዮች የሚባሉትም ከመምህርነታቸውም ሆነ ከክህነታቸው በፊት እውነተኛ ምዕመናን የሆኑት ናቸው፡፡

አረጋዊው የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ይህን በተመለከተ ሲያስተምሩ እንዲህ ብለዋል፡- “ምዕመናን እድለኛ ናቸው፤ ወደገነት ብቻቸውን መግባት ይችላሉ፡፡ ካህናት ግን ብቻቸውን ወደገነት መግባት አይችሉም፡፡” የገብር ሐካይ (የሐኬተኛው አገልጋይ) ታሪክ የሚያረጋግጥልን ይህንኑ ነው፡፡ ካህናት እምነታቸውን ቀብረው መኖር አይገባቸውም፡፡ ከቀበሩት ግን፣ ሌሎችን ካላፈሩበት፣ ካላስተማሩበት ከመንግስተ ሰማያት በአፍአ ይቀራሉ፡፡ የካህናት፣ የመምህራን መክሊት ለራሳቸው ለመዳን ብቻ አይደለም፡፡ አገልግሎታቸውን ፈጸሙ የሚባለው የራሳቸውን መዳን ፈጽመው ለሌሎችም መትረፍ ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ ለዚያ ነው ብጹዕ አባታችን “ካህናት ግን ብቻቸውን ወደገነት መግባት አይችሉም፡፡” በማለት አመስጥረው ያስተማሩት፡፡

የዘመናችን ሐኬተኛ አገልጋዮች ራሳቸው የማያደርጉትን ለሌሎች አድርጉ የሚሉት  ናቸው፡፡  በየዘመናቱ የሚነሱ ምንደኞች አገልግሎትን ለእምነት፣ በእምነት ሳይሆን ከእምነት ተለይተው እንደሥራና ግዴታ ወይም እንደ የገቢና የዕውቅና ምንጭ ያዩታል፡፡ እነርሱ ሳያምኑ ሌሎችን ለማሳመን ይሞክራሉ፣ እነርሱ ንስሐ ሳይገቡ ሌሎችን ንስሐ ግቡ ብለው ያስተምራሉ፤  እነርሱ ሳይሰግዱ (ይልቁንም በጸሎተ ቅዳሴ እንኳ ሰው ሁሉ ሲሰግድ እነርሱ ግን ከእምነት በተለየ ልቦና መስገድ ሲችሉ በትዕቢትና በትዕዝርት በምዕመናን ፊት እየተቀመጡ) ሌሎችን ስገዱ ብለው ያስተምራሉ፤ እነርሱ ሳይጾሙ በአጽዋማትም በአደባባይ ቤተክርስቲያንን የሚያስነቅፍ ነውር እያደረጉ ሌሎችን ጹሙ ብለው ያስተምራሉ፤ እነርሱ ሳይመጸውቱ፣ አስራቱን ሳያወጡ ሌሎችን ምጽዋት ስጡ፣ አስራት አውጡ እያሉ ያስተምራሉ፤ ምጽዋትን ቢሰጡ እንኳ ሰው እንዲያውቅላቸው በአደባባይ ነጋሪት እያስጎሰሙ ይሰጣሉ፤ ይህን የሚያደርጉትም ለጽድቅ ብለው ሳይሆን በሰዎች ለመመስገን ነው፤ ምዕመናንን ከከንቱ ውዳሴ እንዲርቁ ያስተምራሉ እነርሱ ግን በራሳቸው የታይታ ስጦታ ብቻ ሳይሆን ሌሎች በሰጡት ስጦታ እንኳ በከንቱ ውዳሴ ይሸነጋገላሉ፡፡ እውነተኛ ካህናት ግን ከክህነታቸው፣ ከመምህርነታቸው በፊት እውነተኛ ምዕመናን ናቸው፣ ከማስመሰልና ከሽንገላ የተለዩ ናቸው፣ አገልግሎታቸውም ለነቀፋ አይመችም፡፡

አገልጋዮች የድካማቸውን ዋጋ ከባለቤቱ ይቀበላሉ እንጂ ትርፉም ይሁን ዋናው የእነርሱ አይደለም፡፡ ዛሬ እኛ ከመክሊቱ ምሳሌ የምንማረው ለአገልግሎት ስንዘጋጅ ለአገልግሎታችን የሚያስፈልገንን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጠን፣ የእያንዳችን የአገልግሎት ጸጋ የተለያየ መሆኑን፣ የምናገለግለው የእርሱን ፈቃድ እንጂ የራሳችንን ፍላጎት መሆን እንደሌለበት፣ መንፈሳዊ አገልግሎት የጽድቅ ዋጋን የሚያሰጥ መሆኑንና እንዲሁም ተጠያቂነት ያለበት መሆኑን ነው፡፡ የገንዘቡ ባለቤት (እግዚአብሔር) የሰጣቸውን መክሊት (ዋናውን) እና ሠርተው የጨመሩትን  መክሊት(ትርፉን) እንደተቆጣጠራቸው አገልጋዮችም የተሰጣቸው ጸጋም ይሁን በአገልግሎታቸው ያተረፉት የእርሱ የባለቤቱ መሆኑን መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡

የመክሊቱ ምሳሌ የተጻፈው እምነት ለሌላቸውና አገልግሎትን “እንደ ሥራ” ብቻ ለሚያዩ ሳይሆን እንደየአቅማቸው እምነትና ምግባርን አስተባብረው ይዘው ለሌሎች ለመትረፍ የአገልግሎት ጸጋ ለተቀበሉት ነው፡፡  ይህም በአንብሮተ ዕድ ለተሾሙ በተለየ አገልግሎት የእግዚአብሔርን ቤተመቅደስ ለሚያገለግሉ፣ የሰማይ መላእክት አምሳል ለሆኑ ካህናት ብቻ ሳይሆን በየደረጃው በሰንበት ት/ቤት፣ በሰበካ ጉባኤ፣ በልዩ ልዩ መንፈሳውያን ማኅበራት፣ በሰፈርና በቤተሰብ የሚያገለግሉትንም ይጨምራል፡፡ ስለሆነም ሁላችንም ደካማ አገልጋዮቹ እምነትን ከምግባር አስተባብረን፣ በተሰጠን መክሊት አትርፈን ለሌሎች የመዳን ምክንያት እንድንሆን፣ የራሳችንንም መዳን በእምነት እንድንፈጽም የቅዱሳንና ቅዱሳት አባቶቻችንና እናቶቻችን አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

 

 

ደብረ ዘይት፡ ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንጠብቃለን!

የዐቢይ ጾም አምስተኛው ሰንበት “ደብረ ዘይት” ይባላል፡፡ ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ዛፍ ያለበት ተራራ ማለት ነው፡፡ ቦታው ከኢየሩሳሌም በስተምስራቅ የሚገኝ የወይራ ዛፍ የበዛበት ተራራ ሲሆን ስሙም ከወይራ ዛፉ የተነሳ “ደብረ ዘይት (የወይራ ዛፍ ተራራ) (Mount of Olives)” ተብሏል። በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የደብረ ዘይት በዓል የጌታችን ዳግም ምጽአት፣ የዓለም ፍጻሜ ጉዳይ የሚሰበክበት እና የሚተነተንበት በዓል ነው፡፡ ይህም የተደረገው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረዘይት ተራራ ላይ ሳለ ለቅዱሳን ደቀመዛሙርቱ ስለ ዓለም ፍጻሜ እና ስለ ዳግም ምጽአቱ ስላስተማራቸዉ በጌታችን ትምህርት መሰረት ነገረ ምጽአቱን (የመምጣቱን ነገር) እንድናስታዉስ ወይም እያሰብን እንድንዘጋጅ ለማድረግ ነዉ።

ደብረ ዘይት ጌታችን በደብረ ዘይት ተራራ ‹‹የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ ምንድን ነው?›› ብለው ሐዋርያቱ ለጠየቁት ታላቅ ጥያቄ በስፋትና በጥልቀት  ትምህርት የሰጠበት ክፍል የሚሰበክበት ዕለት ነው፡፡ ጌታችን ስለ ምጽአቱ ያስተማረው (ማቴ 24፡1-36)፣ በ40ኛውም ቀን ያረገው (ሐዋ 1:12)፣ ዳግመኛም ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው (ዘካ 14፡4) በዚሁ በደብረ ዘይት ተራራ ነው፡፡ ጌታችን ስለ ዳግም ምጽአቱ ባስተማረው ትምህርት ዘመኑ ሲቃረብ የተለያዩ ተፈጥሮአዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ምልክቶች እንዲሚከሰቱ ተናግሯል፡፡ የሚመጣበትን ዕለቱንና ሰዓቱን ሳይሆን ምልክቶችን ነገረን፡፡ እነዚህም ምልክቶች አብዛኞቹ በዘመናችን እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ምልክቶች ሲታዩ ምን ማድረግ እንደሚገባንም ሲያስተምር ሰባት ዋና ዋና ማስጠንቀቂያ አዘል ምክሮችን ሰጥቶናል፡፡ እነዚህም፡-

ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ይነሳሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉና እንዳለው እኛም ከሐሰተኞች ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ ሐሰተኞች በእርሱ ስም ወይም በቅዱሳን ስም የበግ ለምድ ለብሰው በጎችን ለመንጠቅ ሲመጡ እኛም በእነርሱ እንዳንነጠቅ እንድንጠነቀቅ ይህንን ማስጠንቀቂያ ሰጠን፡፡ እነዚህም ሐሰተኞች ጥቂት ሳይሆኑ ብዙዎች፣ አንድ ጊዜ ተነስተው የሚጠፉ ሳይሆን በየዘመናቱ መልካቸውን እየቀያየሩ የሚነሱ ናቸው፡፡ ተዓምራትን በማድረግ፣ የእግዚአብሔር ሰዎች በመምሰል ይመጣሉ፡፡ ነገር ግን አሰራራቸው በቃለ እግዚአብሔር ሚዛንነት ሲታይ ሀሰተኛነታቸው ይገለጣል፡፡

በሐሰተኞች ወሬ ልባችሁ አይታወክ፡፡ ማንም ክርስቶስ በዚህ አለ ወይም በዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፡፡ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሳሉና፡፡ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳን እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ፡፡ አስቀድሜ ነገርኳችሁ፤ በበረሀ ነው ቢሏችሁ አትውጡ፤ በእልፍኝም ነው ቢሏችሁ አትመኑ በማለት የትንቢቱ መፈጸሚያ እንዳንሆን እንድንጠበቅ አስጠንቅቆናል፡፡ በሐሰተኛ ወሬና ተዓምራት ምዕመናንን ከእውነተኛ እምነት ለማስወጣት ሐሰተኞች ይደክማሉ፡፡ እኛ ግን በሐሰተኞች ማጭበርበር ሳንደናገር እውነት የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይዘን የክርስቶስን መገለጥ በተስፋ እንድንጠብቅ ታዘናል፡፡

ትንቢቱ ሊፈጸም የግድ ነውና አትደንግጡ፡፡ የታየው ምልክቱ እንጂ መጨረሻው አይደለምና አትደንግጡ፡፡ ጦርንም የጦርንም ወሬ ስትሰሙ፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግስትም በመንግስት ላይ ሲነሳ ስታዩ፣ ረሀብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ ሲሆን አትደንግጡ፡፡ ይህ መጀመሪያው እንጂ መጨረሻው አይደለምና! ይህም ሁሉ ሊሆን የግድ ነውና አትደንግጡ፡፡ አለመደንገጥ ነገሮችን በጥሞና ለመመርመር ይጠቅማልና ‹‹አትደንግጡ›› አለን፡፡ መደንገጥ፣ መረበሽ መፍትሔ አይሆንምና፤ እነሆ አስቀድሞ ተነግሮናልና ምልክቶቹ ሲፈጸሙ መደንገጥ የለብንም፡፡ ትንቢቶች የሚፈጸሙት ጌታ ነገሮችን ቀድሞ ስለወሰናቸው ሳይሆን ቀድሞ ስላወቃቸው መሆኑን እናስተውል፡፡ ስለሆነም በትንቢት የተነገሩ ክፉ ነገሮች ሁሉ ሲፈጸሙ ማድረግ የሚገባንን ከማድረግ ይልቅ በሰነፍ እይታ “ምን ይደረግ?! ያው ትንቢቱ መፈጸሙ አይቀርም” ብለን ራሳችንን በማስነፍ የክፋት ተባባሪ መሆን አለብን ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንስ እንደ ደጋግ አባቶቻችንና እናቶቻችን የአቅማችንን አድርገን እንደበጎ አገልጋይ በጌታ ምጽአት ለመመስገን፣ ክብርን ለማግኘት እንትጋ፡፡

የጥፋትን ርኩሰት በተቀደስው ስፍራ ስታዩ ቀኑ እንደቀረበ አስተውሉ፡፡ ምልክቶቹ ሲታዩ ጊዜው እንደደረሰ አስተውሉ፡፡ ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፡፡ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቆጠቁጥ ያን ጊዜ በጋ እንደቀረበ ታውቃላችሁ፡፡ እንዲሁ እነዚህ ምልክቶች ሁሉ ሲታዩ በደጅ እንደቀረበ እወቁ፡፡ በደጅ ያለ ቶሎ መግባት ይችላልና ይህንን አለ፡፡ ምልክቶቹ ሲታዩ መስማትና ማየት ብቻ ሳይሆን ማስተዋልም እንደሚገባ ይህንን አስተማረን፡፡ የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰው ስፍራ ስናይ እንድናስተውል፣ በንስሐም እንድንመለስ ታዘናል እንጅ “ምን ይደረግ?! የዘመኑ ፍጻሜ ስለሆነ ለውጥ ማምጣት አንችልም” በሚል የስህተት ምክንያት ራሳችንን እያታለልን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰው ስፍራ መፈጸም፣ የሚፈጽሙትንም መተባበር በጌታችን ግራ ቆመው ከሚፈረድባቸው ወገን ያደርገናልና በተቀደሰው ስፍራ፣ በመንፈሳዊ አገልግሎት ከጥፋት ርኩሰት ልንርቅ፣ የቀረቡትንም በትምህርትና በተግሳጽ ከጥፋት ልናርቃቸው ይገባል፡፡

እስከመጨረሻው የጸና ይድናልና እስከመጨረሻው ጽኑ፡፡ ለመከራ አሳልፈው ሲሰጧችሁ፣ ሲገድሏችሁ፣ ስለ ስሜም የተጠላችሁ ስትሆኑ በእምነታችሁ ጽኑ፡፡ ብዙዎች ሲሰናከሉ፣ እርስ በእርሳቸውም አሳልፈው ሲሰጣጡ፣ ከአመጻም ብዛት የተነሳ ፍቅር ስትቀዘቅዝ በእምነታችሁ ጽኑ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹በጊዜውም ያለጊዜውም ጽና›› ያለው ለዚህ ነው (2ኛ ጢሞ 4፡2)፡፡ በዚህ ወቅት መከራን መታገስ፣ አስፈላጊም ሆኖ ሲገኝ መስዋዕትነትን በመክፈል ጽናትን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ እስከ መጨረሻው በጽድቅ አገልግሎት የሚጸና በጌታ ምጽዓት የክብር ትንሣኤ ይነሳልና፡፡

ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፡፡ ክረምት የቡቃያ እንጂ የፍሬ ዘመን አይደለምና በሃይማኖት ብቻ ሳላችሁ ምግባርን ሳትሠሩ ሞት እንዳይታዘዝባችሁ ጸልዩ፡፡ ሰንበትም ዕለተ ዕረፍት ናትና በዕረፍት ሳላችሁ ሞት እንዳይታዘዝባችሁ ጸልዩ፡፡ በሃይማኖት ሳላችሁ ምግባር ሳይኖራችሁ ብትወሰዱ መጨረሻችሁ መከራ ይሆናልና ጸልዩ፡፡ ክረምትና ሰንበት ለሽሽት አይመችም መንገድና አቅጣጫ የሚያሳይ የለምና፡፡ ሽሽቱም ተራራ ወደተባሉት ወደ ረድኤተ እግዚአብሔር፣ ወደ ቤተክርስቲያንና በምልጃቸው ወደሚረዱን ቅዱሳን ነው፡፡ መንፈሳዊ ምግባራትን መስራት የማንችልበት ጊዜ ሳይመጣ፣ በጉብዝናችን ወራት እምነታችንን አጽንተን፣ ጠብቀን፣ በጎ ምግባራትን ሰርተን ጌታችን ሲገለጥ በምግባራቸው ከሚያመሰግናቸው ቅዱሳን ጋር እንድንቆም ልንተጋ ያስፈልጋል፡፡

የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም እና ለአርዓያነት በተገለጠ ጊዜ አመጣጡ በአጭር ቁመት እና በጠባብ ደረት ተወስኖ በትህትና ነበር፡፡ ዳግመኛ የሚመጣው ግን በግርማ መለኮት በክበበ ትስብዕት ነው፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ብሎ አስተማረን፡፡ ያቺን ቀን ከእርሱ በቀር የሚያወቃት የለም፡፡ በኖኅ ዘመን እንደነበረው የእርሱም መምጣት እንደዚያ ይሆናል፡፡ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ በነቃና ቤቱን በጠበቀ ቤቱም ሊቆፈር ባልተወው ነበር፡፡ ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና፡፡ ይህ ቀን ስለማይታወቅ ሁል ጊዜ በንስሐ እና በሥጋ ወደሙ ተዘጋጅተን ልንኖር ይገባናል፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ የጌታችን ምጽአት የሚዘገይ እንዳልሆነ ሲያስረዳ ‹‹ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል (2ኛ ጴጥ 3፡9)›› ብሏል፡፡

ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በትንቢት “እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመጽእ፤ ወአምላክነሂ ኢያረምም። እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል፤ አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም።” መዝ. 49፡3 እንዳለ ጌታችን በብዙ ክብርና በብዙ ኃይል ከሰማይ መላእክት ጋር ግልጥ ሆኖ ይመጣል። በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል (2ኛ ጴጥ 3፡10)። በዚያን ጊዜ ከመጀመሪያዉ ሰዉ ከአዳም ጀምሮ እስከ መጨረሻዉ ሰዉ ድረስ ሁላችንም በሕይወተ ሥጋ በነበርንበት ጊዜያችን የሠራነዉን ሥራ ይዘን በፊቱ እንቀርባለን (2ቆሮ. 5፡10)። ጌታችንም በጎ የሠሩትን ቅዱሳን በቀኙ፤ ክፉ የሠሩትን ኃጥአንን በግራዉ ያቆማቸዉና ፍርዱን ያስተላልፋል (ማቴ. 25፡31 እስከ ፍጻሜ)። የወጉትም ያዩታል እንደተባለ (ራዕ 1፡7)፣ በዚያን ጊዜ በእርሱ ላይ የፈረዱበት፣ በቅዱሳንም ላይ መከራን ያጸኑ ሞትንም የፈረዱ ሁሉ ለፍርድ ይቀርባሉ፡፡ ሁሉን ትተው የተከተሉት፣ ስለ እርሱ መከራን የተቀበሉ፣ ሞትም የተፈረደባቸው ደግሞ በፍርድ ወንበር ተቀምጠው ይፈርዳሉ (ማቴ 19፡28)፡፡

በየዓመቱ የደብረ ዘይትን በዓል ስናከብር የተለየ አጽንኦት ሰጥተን ማስተዋል ያለብን ጌታችን ዳግመኛ የሚመጣው ለጻድቃን የዘላለም ሕይወትን፣ ለኃጥአን ደግሞ ፍርድን ሊሰጥ መሆኑን ነው፡፡ የመምጣቱና የዓለም መጨረሻ ምልክቶች ሲከሰቱ እንድንጠነቀቅ፣ እንዳንደነግጥ፣ እንድንጸና፣ እንድንጸልይ፣ እንድንጠበቅ፣ እንድናስተውልና እንድንዘጋጅ ራሱ ባለቤቱ መክሮናል፡፡ ከእርሱ ከባለቤቱ በላይ ማድረግ ያለብንን ሊመክረን የሚችል የለም፡፡ አስቀድሞ ለፍቅር በፍቅር የመጣው በመጨረሻው ቀን ለፍርድ ሲመጣ እንዳናፍር፣ ዕድል ፈንታችንም የዘላለም ሕይወት እንዲሆን እነዚህም ምክሮች ልንጠቀምባቸው ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ “ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን፡፡ ስለዚህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፥ የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ (2ኛ ጴጥ 3፡13)።” እንዳለው እነዚህን ምክሮች የሕይወታችን መርህ አድርገን ይህችን ተስፋ ልንጠባበቅ ይገባል፡፡

ዛሬ ትላንት ሳይሆን፣ ነገም ዛሬ ሳይሆን እኛ እያንዳንዳችን ራሳችንን መጠየቅ ያለብን መሠረታዊ ጥያቄ መሆን ያለበት “የእርሱ መምጣት ለእኛስ ምን ይሆን?” የሚለው ነው፡፡ የዘላለም ሕይወት ወይስ የዘላለም ቅጣት? የእርሱ መምጫው የዓለም ፍጻሜ የእኛም መጠሪያችን ቀን ሲቀርብ ምልክቶችም ሲታዩ እነዚህን ምክሮች ልንፈጽም ይገባናል፡፡ እኛ እርስ በእርሳችን መፋቀር ሲጠበቅብን ስንነቃቀፍ፣ ስለፍቅር እየተናገርን ጠብን ስንዘራ፣ የጽድቅ አውድ በሆነው በእግዚአብሔር ቤት እንቶ ፈንቶ ስናወራ፣ ታሪክ እያወራን አንዳች ሳንሠራ፣ ስለ አንድነት እየተናገርን በየደቂቃው ስንለያይ፣ በሐሰተኞች ወሬና በአስማተኞች ተንኮል ስንነዳ፣ ከውጭ ያሉትን ወደ እግዚአብሔር ቤት ማምጣት ሲጠበቅብን ከውስጥ ያሉትን ስናባርር ለንስሐ የተሰጠን ዘመን ሳንጠቀምበት አልቆ ከፊቱ ቀርበን እንዳይፈረድብን ዛሬውኑ ሕይወታችንን በቃሉ እንቃኛት፡፡ ወደ እርሱም እንቅረብ፡፡ እርሱም ሲመጣ ‹‹ኑ የአባቴ ቡሩካን›› እንዲለን በሕይወታችን እነዚህን ምክሮች ገንዘብ እናድርግ፡፡

መጻጉዕ: የዳነው ያዳነውን አላወቀውም!

ከቅዱስ ያሬድ በተገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የበዓላት ቀኖና መሰረት የዐቢይ ጾም አራተኛው ሰንበት “መጻጉዕ” ይባላል፡፡ መጻጉዕ ማለት “በሽተኛ” ማለት ነው፡ በዚህ ዕለት ጌታችን በቤተ ስዳ መጻጉዕን ማዳኑን ቤተክርስቲያን ትሰብካለች፡፡ ለ 38 ዓመታት ያህል የፈውስ ተስፈኛ ሆኖ በመጠመቂያው አጠገብ የኖረ መጻጉዕን በአልጋው ተኝቶ ሳለ ደዌው እንደጠናበት ፈውስ እንደዘገየበት አይቶ ‹‹አዎን›› እንደሚለው እያወቀ መጻጉዕን ‹‹ልትድን ትወዳለህን?” አለው። መጻጉዕም ‹‹ሰው የለኝም›› በማለት የመዳን ጉጉቱን ከወዳጅ አልባነቱ ጋር ገለጠ። ጌታም ‹‹ተንስና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው፡፡ ወዲያው አፈፍ ብሎ በፍጥነት ያን ሁሉ ዘመን የተሸከመችውን ጠንካራ አልጋ ተሸክሟት ሄደ (ዮሐ 5፡1-5)።

ጌታችን መጻጉዕን ‹‹ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ›› ያለው ስለ ሁለት ነገር ነው፡፡ አንደኛው ቅዱስ ኤስድሮስ እንዳለው አልጋው ጠንካራ የብረት አልጋ ነበረና ጽንዓ ተአምራቱን ለማሳየት ነው፡፡ ሁለተኛው ‹‹ታዲያ ቢያድነኝ በከንቱ መች ሆነና የገዛ አልጋዬን ትቼለት የመጣሁ ለመዳኔ ዋጋ የከፈልኩበት አይደለምን?›› እንዳይል መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ያለህን ይዘህ ሂድ እኔ ከአንተ አንዳች አልሻም›› ባሰኘ ቃል ‹‹አልጋህን ተሸክመህ ሂድ›› ብሎታል።

ይህ ሰንበት የሕሙማን ፈውስ መታሰቢያ ዕለት ነው። የሰንበቱም ስያሜ በዕለቱ የሚነበቡትን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢርና የጾመ ድጓውን ይትበሀል ተከትሎ የተሰየመ ነው፡፡ በመልእክታቱ የሚነበቡት (ገላ 5፡1 እና ያዕ 5፡14) ስለ ድውያን መፈወስ የሚያወሱ ናቸው፡፡ ከሐዋርያት ሥራ የሚነበውም እንዲሁ (ሐዋ 3፡1)፡፡ የዕለቱ ምስባክ እንዲሁ የድውያንን መፈወስ የሚሰብክ ሲሆን “እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ላይ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ ከበሽታው የተነሳ ይለውጥለታል፡፡ እኔስ  “አቤቱ ይቅር በለኝ፤ አንተን በድያለሁና ለነፍሴ አስተስርይላት” አልሁ፡፡” ይላል (መዝ 40:3)

ጌታችን መጻጉዕን የፈወሰባት ቦታ ቤተ ሳይዳ ሳትሆን ቤተ ስዳ ናት፡፡

ቤተ ስዳ (Bethesda)  በይሁዳ ግዛት ከሚገኙና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራቱን ከፈጸመባቸው ሥፍራዎች አንዷ ናት፡፡ ቤተ ሳይዳ (Bethesaida) ደግሞ በገሊላ አውራጃ የምትገኝ ከተማ ነበረች፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በይሁዳ ኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ ያለችዋን ቤተ ስዳን ‹‹በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ስዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። (ዮሐ 5፥2)›› ብሎ ሲገልጻት በገሊላ የምትገኘዋን ቤተ ሳይዳን ደግሞ ‹‹እነርሱም ከገሊላ ቤተ ሳይዳ ወደሚሆን ወደ ፊልጶስ መጥተው ጌታ ሆይ፥ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን ብለው ለመኑት(ዮሐ 12፥21)›› ብሎ ገልጿታል፡፡

ቤተ ስዳና ቤተ ሳይዳ የተለያዩ ቦታዎች ከመሆናቸው በተጨማሪ የስማቸውም ትርጉምም እንዲሁ የተለያየ ነው፡፡ ቤተ ስዳ ማለት ‹‹ቤተ ሣህል (የጸጋ/የምህረት ቤት)›› ማለት ሲሆን፣ በግሪኩ ቤተ ዛታ ወይም ቅልንብትራ ትባላለች፡፡ ቤተ ስዳ ባለ አምስት በር መመላለሻ አምስት ዓይነት ድውያን ፈውስን ከመጠመቂያው ውኃ ሲጠባበቁ የሚኖሩባት የጌታችን ማዳን የተገለጠባት ሥፍራ ናት።  የእግዚአብሔር መልአክ ውኃውን ሲባርክ/ሲያናውጥ ቀድሞ የገባ የሚነጻባት በዕለቱ ከአንድ በቀር ለሌላው ፈውስ የማይደገምባት ቦታ ነበረች። ለዚህም ነው ይህች ስፍራ መጠመቂያና መመላለሻ ያላት በመሆኗ የምህረት ቤት የተባለቸው፡፡ እንደስሟ ትርጓሜ ‹‹ቤተ ስዳ›› የተባለችበትም ምክንያት የሰሎሞን ቤተ መቅደስ አጠገቧ የሚገኝ ሲሆን ለቤተመቅደሱ መስዋእት የሚሆኑ በጎች ሁሉ በዚህ መጠመቂያ ሳይጠመቁ ወደ መስዋእቱ መሰዊያ ቦታ አይቀርቡ ስለነበረ ነው (ዘሌ 9፡2)። ጌታችን በቤተ ስዳ መዳንን ይጠባበቅ የነበረውን መጻጉዕን ፈውሷል፡፡

በቤተ ስዳ መጠመቂያ ይፈጸም የነበረው ድኅነት ምሳሌው እንዲህ ነው፡፡ ውኃውን ያናውጥ (ይባርክ) የነበረው መልአክ የቀሳውስት ምሳሌ፣ ውኃው የጥምቀት ምሳሌ፣ አምስቱ መመላለሻ (እርከን) የአምስቱ አዕማደ ምስጢር፣ የአምስቱ ድውያንና የአምስቱ ፆታ ምዕመናን ምሳሌ ናቸው፡፡ ቤተ ስዳ በዕለተ ቀዳሚት የሚፈወሰው አንድ ሰው ብቻ ነበር፡፡ አንድ ብቻ መሆኑ አለመቅረቱን ሲያሳይ አለመደገሙ ደግሞ ፍጹም እንዳልነበረ ያሳያል፡፡

በአንጻሩ ቤተ ሳይዳ ማለት ደግሞ “የማጥመጃ ቤት” ወይም ‹‹የዓሳ ቤት›› የሚል ትርጉም ያላትና በተለይ ከሐዋርያቱ አሳ አጥማጆቹ ወንድማማቾች እና ቅዱስ ፊልጶስ የነበሩባት መንደር ነበረች (ዮሐ·1፡45)። ይህች ከተማ ‹‹የዓሳ ቤት›› የተባለችውም ከገሊላ ባህር ዳር የምትገኝ ስለሆነችና ዓሳ የሚያሰግሩ ሰዎች የሚነግዱባት ስለሆነበረች ነው። በዚህ በሞቀ ንግዷ የተነሳ ከተማዋ የተሰበከላትን ወንጌል ለመስማት ባለመቻሏ ጌታችን በተናገረው ትንቢት መሰረት ከሌላዋ ከተማ ከኮራዚን ጋር አብረው ጠፍተዋል (ማቴ 11፣21)፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ሳይዳም ድውያንን ፈውሷል (ማር 8፡22-25)፡፡

መጻጉዕ ግን ያዳነውን ረሳ፤ በሐሰትም መሰከረበት፤ ወደቀደመ “ደዌውም” ተመለሰ፡፡

መጻጉዕ ቀድሞ በቤተ ስዳ እያለ የነበረበትን ያንን ሁሉ ጭንቅ ኋላ በሊቶስጥሮስ አደባባይ ሲቆም ረሳው፡፡ ይህ ምስኪን መጻጒዕ “ሰው የለኝም” ብሎ የደረሰለትን ሰው ረሳ፡፡ ያዳነው ማን እንደሆነ ሲጠየቅ እንኳ አላወቀም። ወንጌላዊውም ‹‹የዳነው ያዳነውን አላወቀውም›› ( ዮሐ.5፥13) ይለዋል። በምኩራብ አግኝቶት ያዳነውን እንዳወቀውም ሄዶ ለአይሁድ ያዳነኝ እርሱ “ጌታ ኢየሱስ ነው” ብሎ ነገራቸው፡፡

ጌታችን መጻጉን ‹‹ልትድን ትወዳለህን›› ያለው አስፈቅዶ ለማዳን እንዲሁም በዕለተ ዓርብ ‹‹አድነኝ ሳልለው አድኖኝ›› እንዳይል ሲሆን መጻጉዕ ግን ‹‹ሰው የለኝም›› ያለው ያድነኛል ብሎ ሳይሆን ‹‹ወደ መጠመቂያው ያደርሰኛል›› ወይም ‹‹ከሚከተሉት አንዱን አዝዞ ወደ መጠመቂያው እንዲያደርሰኝ ያደርጋል›› ብሎ ነበር፡፡

አንድ ሊቅ ይህን ‹‹ታሞ የተነሳ ፈጣውን ረሳ›› የተባለለት መጻጒዕ እና በሐሰት የተከሰሰውን ይቅር ባይ አምላኩን እያደነቀ በጉባዔ ቃናው እንዲህ ተቀኘ፡፡ ” ይትዐረቅ ምስለ ብእሲት ደዌሁ፤ ሠላሳ አዝማነ እስመ ነበረት ምስሌሁ” (ትርጉም፡ መጻጒዕ ከሚስቱ ከደዌ ጋር ይታረቅ ፤ ሠላሳ ዓመታት ከእርሱ ጋር ኑራለችና)፡፡ ለብዙ ዓመታት አብረው የኖሩ ባልና ሚስት ሲፋቱ ከናፍቆት የተነሳ መለያየቱ እንደሚከብዳቸውና ተመልሰው እንደሚታረቁ ሁሉ ‹‹ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ አትበድል›› ተብሎ ከጌታ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው መጻጉዕም ያዳነውን ጌታ በጥፊ መትቶ ዳግመኛ ወደ 38 ዓመት “የአልጋ ወዳጁ” ደዌ ተመልሶ ከእርስዋም ጋር መታረቁን የቅኔው ምስጢር ያስተምረናል። ጌትችን ከደዌው ነጻ አወጣው፤ እርሱ ግን ከደዌው ተለያይቶ መኖር ከብዶት ተመልሶ ታረቃት፡፡ኋላም በአውደ ምኩናን የሐሰት ክስ የቀረበበትን ጌታችንንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቀድሞ ወደ መጠመቂያው እንኳ ለመቅረብ አቅም ያልነበረው ዛሬ ግን አልጋ ለመሸከም በበቃውና ያለ ተረፈ ደዌ በጸናው ኃይሉ የጌታውን ጉንጮች በጥፊ የመምታት ጉልበትና ድፍረት አገኘ ። አምላከ ምሕረት የክብር ጌታ ቀድሞ ‹‹ከዚህ የጠናው” ስለ ደዌ ሥጋ ፈንታ ደዌ ነፍስ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል” (ዮሐ 5፡14) ያለውን ዘንግቶ ደዌ ዘኃጢአትን ጠርቶ ተወዳጃት፤ በዕለተ ዓርብ የጌታውን ጉንጮች የጸፉች እጁም ደርቃ ቀርታለች፡፡

የዐቢይ ጾም አራተኛው ሰንበት እኛም የታመሙትን መጎብኘት እንዳለብን የምንማርበት ነው፡፡

ይህ ሳምንት “መጻጉዕ” ጌታችን ድውያንን ስለመፈወሱ የሚነገርበትና እኛም ባለን አቅም በነፍስ በሥጋ የተቸገሩትን ሁሉ መርዳትና ማገዝ እንዳለብን የምንማርበት ሳምንት ነው፡፡ ሕሙማንን መጠየቅ፣ የታሰሩትን መጎብኘትና ማስፈታት፣ የተራቡትን ማብላት፣ የተጠሙትን ማጠጣት፣ የታረዙትን ማልበስ ያዘኑትን ማረጋጋት ከጌታችን የተማርናቸው ክርስቲያናዊ ምግባራት ናቸው፡፡ ይህንን በማስተዋል የሚያስፈልገንን ሁሉ የሰጠንንና ከክፉ ነገር የጠበቀንን አምላክ ውለታውን እያሰብን ልናመሰግነው ይገባል፡፡ መጻጒዕ መጀመሪያ የነበረበት ደዌ ሥጋ ነበር፣ ይህንንም ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አራቀለት/አዳነው፡፡ ይሁንና በጌታችን ስቅለት ከአይሁድ ጋር በመተባበሩ፣ ያዳነውን ባለማመኑ ግን ደዌ ነፍስ አገኘው፡፡ እኛም እንደ መጻጒዕ ደዌ ነፍስ እንዳያገኘን ያዳነንን አምላካችንን ልናውቀው፣ ልናምነው፣ በህጉና በትዕዛዙም ልንሄድ ያስፈልጋል፡፡ ያን ጊዜ ከደዌ ነፍስ እንድናለን፡፡ ያንን ተስፋ ያልነበረውን በሽተኛ ከደዌ ሥጋው ፈውሶ ሕይወትን የሰጠው አምላክ፣ እኛንም በውስጥ በአፍአ ካለብን ደዌ ሥጋና ደዌ ነፍስ እንዲፈውሰን፤ ቁስለ ኃጢአታችንን እንዲያደርቅልን፣ በሕይወትና በጤና እንዲጠብቀን የእርሱ የጌታችን ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡