ሆሳዕና: የምሥጋና ንጉሥ እርሱ ማነው?

በመጋቤ ምስጢር ቀሲስ ስንታየሁ አባተ

በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በድምቀትና በልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ በዓለ ሆሳዕና ነው። ሆሳዕና የሚለው “ሆሼዕናህ” ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ነው። ሆሳዕና “አድነና፣ አድነንኮ፣ እባክህ አድነን ወይም መድኃኒትነት፣ መድኃኒት መሆን ወይም መባል” የሚል ትርጉም ይይዛል። ሆሳዕና የጸበርት/የዘንባባ እሑድም ይባላል፡፡ በዓለ ሆሳዕና በቤተክርስቲያናችን ሊቃውንት ከዋዜማው ጀምሮ ሌሊቱን በማኅሌት እየዘመሩ የሚያመሰግኑበት ነው፡፡ ወደ ቅዳሴም ሲገባ ለየት ባለ ሁኔታ ዲያቆኑ ወደምዕራብ በር በማምራት “አርኅው ኆኃተ መኳንንት/መኳንንት ደጆችን ክፈቱ/” ሲል ካህኑም በውስጥ ሆኖ በዜማ “መኑ ውእቱ ዝንቱ ንጉሠ ስብሐት/የምሥጋና ንጉሥ እርሱ ማነው?/” ይላል፡፡ ይህንንም ከተቀባበሉ በኋላ ዲያቆኑ “እግዚአብሔር አምላከ ኃያላን ውእቱ ዝንቱ ንጉሠ ስብሐት/ይህ የምሥጋና ንጉሥ የኃያላን አምላክ እግዚአብሔር ነው/” ሲል ካህኑም “ይባእ ንጉሠ ስብሐት ይባእ አምላከ ምሕረት/የምሥጋና ንጉሥ ይግባ የምሕረት ንጉሥ ይግባ/” ይልና ዲያቆናቱ ወደ ውስጥ ዘልቀው ቅዳሴ ሥርዓቱ ይቀጥላል:: በዕለቱም ስለ ሆሳዕና በጥልቀት የሚናገረው የቅዱስ ጎርጎርዮስ (ኤጲስ ቆጶስ  ዘኑሲስ) ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ እጅግ ልዩ በሆነውም የሆሳዕና ዑደት ከዳዊት መዝሙር ምስባክ እየተሰበከ፣ ወንጌል እየተነበበ፣ ከጾመ ድጓውም እየተዜመ ይከበራል፡፡ ለሕዝቡም ዘንባባ ይታደላል፡፡ ጸሎተ ፍትሐትም ይከናወናል፡፡

ሆሳዕና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ። እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው። ትሑትም ሆኖ በአህያም በውርንጫይቱም ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል (ዘካ. ፱፣፱)” ተብሎ አስቀድሞ በነቢዩ ዘካርያስ የተነገረውን ትንቢት የፈጸመበት በአህያዪቱና በውርንጫይቱ ተቀምጦ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም የገባበትና ቤተ መቅደሱን ያጸዳበት ልዩ በዓል ነው። ሆሳዕና ከትንቢቱ በተጨማሪ ምሳሌውም የተገለጠበት ነው። በኦሪቱ የነበሩ ነቢያት ዘመኑ የጸብ የጦርነት ከሆነ በፈረስ ተቀምጠው ዘገር (ጦር) ነጥቀው ይታያሉ። በተቃራኒው ደግሞ ዘመኑ የሰላም የእርቅ የሆነ እንደሆን በአህያ ተቀመጠው መነሳንስ (ጭራ) ይዘው ይታያሉ። የሰላም ንጉስ የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረው ትንቢት ተፈጽሞ የተቆጠረው ሱባኤ አልቆ የተመሰለውም ምሳሌ እውን የሚሆንበት ዘመን ደረሰ፤ ሰላም እርቅ ድኅነት ሊፈጸምላችሁ ነው ሊለን በአህያና በውርንጫይቱ ተቀምጦ በብዙ አጀብ ታጅቦ በሆታ በእልልታ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ።

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲቀመጥባቸው የቀረቡት አህዮች በአንድ ሰው ግቢ ውስጥ ታስረው ነበር። ጌታችን ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ከደብረ ዘይት አጠገብ ወደምትገኘው ወደ ቤተ ፋጌ ላከ። “ወይቤሎሙ ሑሩ ሀገረ ዘቅድሜክሙ፤ ወይእተ ጊዜ ትረክቡ ዕድግተ ዕሥርተ ምስለ ዕዋላ፤ ፍትሕዎን ወአምጽእዎን ሊተ፤ በፊታችሁ ወዳለችው ሀገር መንደር ሂዱያን ጊዜም የታሠረች አህያ ከውርንጫዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፍቱና አምጡልኝ” ብሎ ላካቸው። እንደ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ትርጓሜም እነዚያ አህዮች ተሠርቀው የታሠሩ ነበሩ። እነዚህ አህዮች ባለቤታቸው ባልሆኑ ሰዎች ተሠርቀው እንደታሠሩ ሁሉ የሰው ልጆችም በምክረ ከይሲ ተታለው በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት አጉድለው ሕጉንም አፍርሰው ከተከለከሉት ዕፀ በለስ በመብላት ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በአጋንንት ቁራኝነት ታሥረው ይኖሩ ነበር።

በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት አምነን በሐዋርያት ሥልጣን ከማዕሠረ ኃጢአት የምንፈታበት ዘመን መድረሱን ሊነግረን ሐዋርያቱን ወደ አህዮቹ ላካቸው። ሐዋርያቱ ወንጌለ መንግሥትን አስተምረው አሳምነው በተሰጣቸው ሥልጣን በኃጢአት ማሠርያ የተያዘውን ዓለም እየፈቱ ወደ ክርስቶስ የሚያቀርቡ እውነተኞች መልእክተኞች ናቸው። አህዮቹን ፈትተው ሊያቀርቡለት ሲሞክሩም አንዳች የሚቃወማቸው ቢኖር “ወእመቦ ዘይቤለክሙ ምንተ ትገብሩ በሉ እግዚኦሙ ይፈቅዶሙ ወበጊዜሃ ይፌንወክሙ፤ ምን ታደርጋላችሁ? የሚላችሁ ቢኖርም ጌታቸው ይሻቸዋል በሉ፤ ያን ጊዜ ይሰዱአችኋል” ብሎ ነግሯቸው ነበርና እንደ ቃሉ አደረጉ።

አህያዪቱን ከነውርንጫዋ ካመጡላት በኋላ ልብሳቸውን እያወለቁ በላያቸው ጫኑ፤ በምትሄድበት መንገድም ልብሳቸውን አነጠፉ፤ የተቀሩትም የዛፍ ጫፍ እየቆረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር። የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ከፊት እየቀደሙ ከኋላው እየተከተሉ “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው። ሆሳዕና በአርያም” እያሉ እየጮሁ ያመሰግኑ ነበር። በእንዲህ ዓይነት ክብር በብዙ ሕዝብ ታጅቦ ከኢሩሳሌም እስከ ቤተ መቅደሱ ካለው ፲፮ ምዕራፍ ፲፬ቱን ምዕራፍ በእግሩ ፪ቱን በአህያዪቱ ተቀምጦ ሄዷል። በውርንጫዪቱ ተቀምጦ ደግሞ ቤተ መቅደሱን ሦስት ጊዜ ዞሯል። በእንዲህ ዓይነት ክብር መመስገኑ ሊቃነ ካህናቱን አላስደሰታቸውም ነበር። ከፍ ብለውም የሚያመሰግኑትን ሕጻናትን ጭምር ከማመስገን እንዲከለክላቸው ጠይቀውት ነበር። እርሱ ግን እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። “ለእመ አርመሙ እሎንቱ አእባን ይኬልሁ፤ እነዚህ [ሕፃናት] ዝም ቢሉ እነዚህ ድንጋዮች ያመሰግናሉ” ። በመጨረሻም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በዚያ የማይገባ ሥራ ይሠሩ የነበሩትን አውጥቶ ተአምራትን አደረገ። ይኽን ከላይ የተጠቀሰውን ታሪክ በማስተዋል ስንመረምረው እጅግ ጥልቅና ረቂቅ የሆኑ ምሥጢራትን እናገኛለን። አበው ሊቃውንት አምልተው አስፍተው ካስቀመጡልን ትምህርታቸውም በትንሹ ለማየት እንሞክራለን።

. አህያዋና ውርንጫዋ:  በዚህ ዓለም አህያ ለሸክም የሚያገለግል፣ የተናቀ፣ ነገር ግን ትሑት የሆነ እንስሳ ነው። ከዚህ በተጨማሪም አህያ እንደ በቅሎ ሰጋር እንደ ፈረስ ፈጣን አይደለም። በአህያ የተቀመጠ ሰውም አሳድዶ አይዝም፤ ጋልቦ ሮጦም አያመልጥም። ተሸክሞ እንኳን በዱላ እየተደበደበ አህያ ጌታውን በቅንነት ያገለግላል። ጌታችን በዚህች ትኁት በሆነችው አህያ መገለጡ በትኁታን ለማደሩ ምሳሌ ነው። ራሳቸውን ዝቅ ያደረጉትን እርሱ በረድኤት ያድርባቸዋል። በዘባነ ኪሩብ አድሮ የሚኖር ጌታ የአህያን ጀርባ መረጠ። እርሱን በሃይማኖት ለሚሹት፣ በሕግ በአምልኮ ለሚከተሉት የቅርብ አምላክ ነው። በጽኑ መከራ በሰቆቃና በስቃይ ውስጥ ሳይቀር በሃይማኖት ጸንተው ተስፋ የሚያድርጉትን ተስፋቸውን እውን ያደርግላቸዋል። ጌታችን የተቀመጠባቸው አህዮች አንደኛዪቱ ጭነት የለመደች ሁለተኛዪቱ ደግሞ ገና ያልለመደች ናት። እርሱ ግን በሁለቱም ተቀመጠባቸው። ጭነት የለመደችው ሕገ ኦሪትን መጠበቅ የለመዱ የእስራኤል ዘሥጋ፣ ውርንጫዪቱ ደግሞ የአሕዛብ ምሳሌ ናቸው። እነርሱ ገና ሕግ መጠበቅን አልለመዱም ነበርና ጌታችን ወድዶ ፈቅዶ ባደረገው ቤዛነት ሕዝብም አሕዛብም በእርሱ አምነው ማደርያዎቹ ሆነዋል።

. ልብስ: ደቀ መዛሙርቱ አህያዪቱን ከነውርንጫዋ ከታሰረችበት ቦታ ፈትተው እንዳመጡለት በዚያ የነበሩት ሰዎች ልብሳቸውን በአህያዪቱና በውርንጫዪቱ ጀርባ ጎዘጎዙ፤ አህያዪቱ ተራምዳ በምትሄድበት መንገድ ሁሉ ልብሳቸውን አነጠፉ። ይኽም ምሳሌ ነው። ልብስ የውስጥ ገመናን ከታች (ሸፋኝ) ነው። አንተ ገመናችንን ከታች ነህ ሲሉ ልብሳቸውን ጎዘጎዙለት። በሌላ በኩልም ልብስ ክብር ነው። ያስከብራል። ያንን የሚያስከብረውን ልብስ አነጠፉለት። ክብራችን አንተ ነህ ሲሉ ክብራቸውን ዝቅ አደረጉለት። የተናቀች የነበረችው አህያ ጌታችን ስለተቀመጠባት ክብር አገኘች። የሰዎች ልብስ እየተነጠፈላት በክብር ሄደች። እግዚአብሔር በረድኤት ሲያድርብን ይንቁን ያንገላቱን የነበሩት ሁሉ ያክብሩናል። ቅዱሳን በዚህ ዓለም ሲኖሩ ብዙ መከራ ተፈራርቆባቸዋል። ዓለም ትቢያና ጉድፍ አድርጓቸዋል። ይኹን እንጂ በሃይማኖታቸው ጽናት በምግባራቸው ቅናት እግዚአብሔር አድሮባቸው ሁሉ ያከብራቸዋል። አስጨናቂዎቻቸውን ሳይቀር ይገዙላቸዋል።

. የዘንባባ ዝንጣፊ:  ጌታችን በሚያልፍባቸው የኢየሩሳሌም ጎዳናዎች ያጀቡት ሰዎች የዘንባባ ዝንጣፊ የዛፍም ጫፍ እየቆረጡ በመያዝ ያመሰግኑት ነበር። ይኽም የደስታ የድል አድራጊነት ምሳሌ ነው። አብርሃም ይስሃቅን፣ ይስሃቅ ያዕቆብን በወለዱ ጊዜ፣ እስራኤል ከግብፅ በወጡበት ወቅት፣ ዮዲት ሆሎፎርኒስን በገደለች ጊዜ ዘንባባ ቆርጠው ይዘው እግዚአብሔርን አመስግነዋል። ክርስቶስ በታላቅ ግርማ ወደ ኢየሩሳሌም እየገባ ስለነበር ደስታቸውን አዕጹቀ በቀልት ይዘው ዘመሩ። በላያቸን ለዘመናት ነግሦ የነበረውን ዲያብሎስንና ሥራዎቹን ሞትንና ሙስና መቃብርን ድል ሊነሣ ጌታ መጥቷልና ደስ እያላቸው ዘንባባ ይዘው አመሰገኑት። ከፊት ከኋላ ያሉትም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “ሆሳዕና ለወልደ ዳዊት፤ ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፤ ለዳዊት ልጅ መድኃኒት መባል ይገባዋል፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው” እያሉ ዘመሩ። ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት ከልደተ ክርስቶስ አስቀድሞ በትንቢት መንፈስ “እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይኽቺ ናት፣ በእርስዋ ደስ ይበለን፣ ሐሴትም እናድርግባት። አቤቱ እባክህ አሁን አድን፣ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና። በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው”  (መዝ. ፻፲፯፣፳፬ – ፳፮) ብሎ እንደዘመረው አመሰገኑት።

. ጌታችን በቤተ መቅደስ: በብዙ ምስጋናና እልልታ ይልቁንም ሽንገላ ከሌለበት ከሕፃናት አፍ የሚፈልቀው ምስጋና እየቀረበለት በልዩ ግርማ ጌታችን በኢየሩሳሌም አደባባይ አቋርጦ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ። በቤተ መቅደሱ የጠበቀው ነገር ግን እርሱ ለቤቱ የፈቀደው ቅድስናና ክብር አልነበረም። አህዮቹን ከታሠሩበት አስፈትቶ ይዞ ወደ ቤተ መቅደሱ በመጣበት ሰዓት ለክብሩ የማይገባ የተፈቱትን አህዮች ወደ ኋላቸው የሚመልሳቸው ሥጋዊ ሥራ እየተፈጸመበት የሥጋ ገበያ ቦታ ሆኖ ነው ቤተ መቅደሱን ያገኘው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህች ምድር በሥጋ ተገልጦ እየተመላለሰ ባገለገለባቸው ዓመታት ውስጥ ከተቆጣባቸው ጥቂት ጊዜያት አንዱ በሆሳዕና ዕለት ወደ ቤተ መቅደሱ ሲገባ ነው። የጸሎት ቤት የሆነችውን የእግዚአብሔር ቤት  አይሁድ የገበያ ቦታ የቅሚያና የዝርፊያ አደባባይ አደረጓት። በዚህም ትሑቱ ጌታ ተቆጣ። በዚያ ይሸጡ ይለውጡ የነበሩትን አስወጣቸው። ወንበራቸውን ገለበጠው። ቤቱን ቀደሰው። “ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል” እንዲል ቅዱስ ዳዊት። አነፃው፤ ለየው፤ አከበረው፤ ወደ ቀድሞ ክብሩ መለሰው። ይኽን ቤት ነገረ ምፅአቱን ለደቀ መዛሙርቱ ባስተማረበት ወቅት ትቶት ሄዶ ነበር። “ጌታችን ኢየሱስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሄደ” እንዲል ቅዱስ ማቴዎስ። የሆሳዕና ዕለት ግን ለሐዲስ ኪዳን አገልግሎት እንዲሆን ነጋዴዎቹን አጭበርባሪዎቹን አውጥቶ አጽድቶ ሰጠን። በዚያም በተቀደሰው ቤተ መቅደስ “በቤተ መቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ መጡ፤ አዳናቸውም” ተብሎ እንደ ተጻፈው። ማቴ ፳፩፣ ፲፬።

ዛሬስ ጌታችን በየአጥቢያችን ወዳለው ቤተ መቅደስ ቢመጣ ወይም ቤተ መቅደስ ወደ ተባለው ሰውነታችን ቢመጣ ይኽን ቤተ መቅደሱን በተገቢው ክብሩ ያገኘው ይሆን?” የገበያ ስፍራ ያልሆነ፣ ከንብረት እስከ ሰው ያልተሸጠበት ቤተ መቅደስ ይኖር ይሆን? የጸሎት ቤት የነበረው ቤቱ እንደዚያን ዘመን ዛሬም ከጸሎት ቤትነት ይልቅ የነገር፣ የክርክር፣ የፖለቲካ፣ የክስ፣ የወንጀል ሁሉ መፈጸሚያ አልሆነምን? ሙስና የነገሠባቸው “አገልጋዮች” በሚፈጽሙት ኢ-ክርስቲያናዊ በደል ምዕመናን ከቤተ መቅደሱ ተገኝተው ጸሎት ማድረግ ተስኗቸው እየተሰቃዩ፣ እያዘኑና እያለቀሱ የሚገኙባቸው ቤተ መቅደሶች የሉንምን? ያኛውን ቤተ መቅደስ ያጸዳው የገሊላ አውራጃ ከምትሆን ከናዝሬት የወጣው ጌታ ነበር። አሁን ግን ያ ጌታ ከሰማይ በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት በቅዱሳን መላእክት ታጅቦ ይመጣል። አንደበት ሁሉ በፊቱ ዝም ይላል። እርሱም ዝም አይልም።

. የሊቃነ ካህናትና የጸሐፍት መቆጣት:  የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ ክቡር በሆነ ምስጋና መመስገን፣ የቤተ መቅደሱ በክርስቶስ መጽዳትና ወደ ቀደመ ክብሩ መመለስ ሊቃነ ካህናትንና ጸሐፍቱን አላስደሰታቸውም። በክፋትና በተንኮል ካባ እንደተጀቦኑ ጻድቃን መስለው ለዘመናት ትሑትና የዋህ የሆነውን ሕዝበ እግዚአብሔር ሲያታልሉ የነበሩት እነዚህ አካላት በጽድቁ ክፋታቸውን የሚገልጥባቸው የክርስቶስ በክብር መገለጥ እንዲሁም መመስገን አስቆጣቸው። የእርሱ መገለጥና መመስገን እነርሱን የሚያሳንስ ክፋታቸውን የሚገልጥ መሆኑን ተረዱት። ጌታችን በወንጌል “ሥራው ክፉ የሆነ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ክፉም ስለሆነ ሥራው እንዳይገለጠበት ወደ ብርሃን አይመጣም (ዮሐ. ፫፣፳)” እንዳለው ሆነባቸው።

የክፉዎች የመጨረሻው ክፋታቸው ክፉ መሥራታቸው ብቻ ሳይሆን በጎ የሚሠሩትን ሰዎች በዓይናቸው እንኳን ለማየት አለመፈለጋቸው ነው። የቅኖች ደግነት፣ የመልካሞች በጎ ሥራ፣ የትሑታን የተሰበረ መንፈስ ይረብሻቸዋል። ማንነታቸውን ያጎላዋል። እናም ጌታችን ሲመሰገን መስማት አለፈለጉም። ግን እኮ አመስግኑ ያላቸው የለ። አላመሰገናችሁም ብሎ የወቀሳቸውም የለ። ሕሊናቸው ቢረብሻቸው “ሕጻናቱን ዝም አሰኝ” ብለው ለክርስቶስ ነገሩት።

የእነዚህ ደቀ መዛሙርት ዛሬም አሉ። እግዚአብሔር ሲመሰገን፣ ሰው ንስሐ ሲገባ፣ ወንጌል የሚያስተምሩ እውነተኛ መምህራን ሲበዙ፣ ሰላም ሲሰፍን፣ አንድነት ሲጸና፣ ሕገ እግዚአብሔርን የሚያከብሩ ሰዎች ሲገኙ፣ ደናግላን በድንግልናቸው ሲጸኑ፣ በትዳር ያሉ ትዳራቸውን ሲያከብሩ፣ የመነኮሱ ቆባቸውን አክብረው ሲይዙ፣ የደኸየው ሠርቶ ሲያገኝ ወዘተ… ማየትና መስማት የማይፈልጉ አሉ። ሁሉም እንደነርሱ ሲሆን ማየት ይፈልጋሉ። ዓለም ሳይፈጠር ባሕርይው ባሕርይውን እያመሰገነ ምስጋናው ሳይቋረጥ የኖረውን ጌታችንን ሕጻናት “ለምን አመሰገኑህ?” ብለው ያላዋቂ ጥያቄ ጠየቁት። በዚያ ስፍራ ያሉ ዝም ቢሉ ምስጋናው የሚቋርጥ መሰላቸው። እርሱ ግን “ለእመ አርመሙ እሎንቱ አእባን ይኬልሁ፤ እነዚህ [ሕፃናት] ዝም ቢሉ እነዚህ ድንጋዮች ያመሰግናሉ” አላቸው።

. ትቶአቸው ሄደ: የታሰሩትን ፈትቶ ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ፣ ቤተ መቅደሱንም ባርኮ ፈውስ በረከት አሳድሮበት፣ ተመስግኖበት ለዘላለምም የሚመሰገንበት መሆኑን ለተቃወሙት አስረድቶ ሲያበቃ “ትቶአቸው ከከተማው ወደ ቢታንያ ሄደ። በዚያም አደረ” እንዲል ሊቃነ ካህናቱንና ጸሓፍቱን ትቶአቸው ሄደ። ክህነታቸው አለፈች። ያላቸውን ክብር፣ ሀብት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቅንና ትሑት ልቡና ለነበራቸው ለሐዋርያት ተሰጠች። እግዚአብሔር በተለያዩ መንገዶች ክብሩን አምላክነቱን ይገልጥልናል። የልቡናችንን በር ያንኳካል። በቃሉ ይጠራናል። ተገቢውን ምላሽ በጊዜው ካልሰጠነው ትቶን ያልፋል። እነርሱን ጌታችን ትቶአቸው ሄዷልና በ፸ ዓ.ም ጥጦስ ከሮም ዘምቶ ቤተ መቅደሳቸውን አፍርሶ እነርሱንም መትቶ ሀገሪቱን ወና አደረጋት። እኛንስ ዛሬ ቢመጣ ወደ እኛ የሚያስገባው ከእኛም ጋር እንዲያድር የሚያደርገው በጎ መዓዛ ያለው ምግባር ይኖረን ይሆን?

በአጠቃላይ:- በዓለ ሆሳዕና ደቀ መዛሙርት የታሰሩትን ለመፍታት የተላኩበት፣ አህዮችም ከእስራታቸው የተፈቱበት፣ አዋቂዎች ሲለጎሙ ሕጻናት ያመሰገኑበት፣ ጌታችን ቤተ መቅደሱን ያጸዳበት፣ እናውቃለን ባዮችን ግን ትቶ የሄደበት በዓል ነው። በዚህን ቀን አህዮቹ ከጌታችን የተላኩላቸውን ፈቺዎቻቸውን (ደቀ መዛሙርቱን) አላስቸገሯቸውም። እንደ ልቧ መቦረቅ የምትወድ ውርንጫ እንኳን አደብ ገዝታ ፈቺዎቿን ተከትላ ሄደች። እኛስ? ከታሰርንበት የክፋትና የኃጢአት ሁሉ ማሰርያ መች ይሆን የምንፈታው? ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላኩልንን እውነተኞቹን አባቶቻችን ካህናቱን እናውቃቸው ይሆን? ለእግዚአብሔር ክብር ሳይሆን ለራሳቸው ጥቅም በቤቱ ያሉትን የእግዚአብሔር አገልጋዮች የሚመስሉ ግን እግዚአብሔርን የማያውቁትን “አገልጋዮችን” እናውቃቸው ይሆን? እንግዲህ እንደዚያን ዕለት ሰዎች ልብሳችንን ሳይሆን ልባችንን፣ የዛፍ ቅርንጫፍ ሳይሆን ራሳችንን በጌታችንና የእርሱ እውነተኛ አገልጋዮች በሆኑ በቅዱሳኑ ፊት ዝቅ እናድርግ። ለዚህም የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሁሉ ተራዳኢነት አይለየን። አሜን።

 

1 thought on “ሆሳዕና: የምሥጋና ንጉሥ እርሱ ማነው?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s