ኒቆዲሞስ፡ የትህትና፣ የትጋትና የጽናት አብነት

የኒቆዲሞስ አብነትblue

በዲ/ን  ብሩክ ደሳለኝ (ዶ/ር)

በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን የበዓላት ቀኖና መሰረት ሰባተኛው የዐቢይ ጾም ሰንበት ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡ በግሪክ ቋንቋ ኒቆዲሞስ ማለት “አሸናፊ/ነት” ማለት ነው፡፡ በዚህ ሰንበት በዮሐ 3፡1-21 እንደተገለጸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ለተባለ የአይሁድ አለቃ ያስተማረው ትምህርት እንዲሁም የኒቆዲሞስ አስተማሪ ስብእና ይነበባል፣ ይተረጎማል፣ ይዜማል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓ የሰባተኛ ሣምንት መንፈሳዊ ድርሰቱ የኒቆዲሞስን በዓል አስመልክቶ ሲዘምር “ሖረ ኀቤሁ ዘስሙ ኒቆዲሞስ ወይቤሎ ለኢየሱስ ረቢ ሊቅ ንሕነ ነአምን ብከ ከመ እምኀበ አብ መጻእከ ከመ ትኩን መምህረ፤ ዕጓለ አንበሳ ሰከብከ ወኖምከ አንሥአኒ በትንሣኤከ ክርስቶስ/ኒቆዲሞስ የተባለው ሰው ወደ ጌታችን ኢየሱስ ሄደ፤ መምሕር ሆይ ልታስተምር ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ እንደመጣህ እናምንብሃለን አለው። የአንበሳ ደቦል ተኛህ፣ አንቀላፋህም፤ በትንሣኤህ አንሣኝ/ ብሏል፡፡ ይህም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ያስተማረውን ትምህርት የሚያመሰጥር ድንቅ ዜማ ነው፡፡ የዚህች አጭር የአስተምህሮ ጦማር ዓላማም ከኒቆዲሞስ ሕይወት መማር እንችል ዘንድ የኒቆዲሞስን ጠንካራ ስብእና እና መንፈሳዊነት የሚያሳዩ መገለጫዎችን መተንተንና እኛም አርዓያውን እነድንከተል መምከር ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከኒቆዲሞስ ሕይወት የምንማራቸው ቁም ነገሮችም እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

አትኅቶ ርዕስ (ራስን ዝቅ ማድረግ) – ኒቆዲሞስ መምህር ሲሆን ራሱን ዝቅ አድርጎ የተማረ የትህትና አርአያ ነው፡፡

ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ ብቻ ሳይሆን የፈሪሳውያን አለቃ፣ የኦሪት መምህር ብቻ ሳይሆን የኦሪት ምሁርም ነበር፡፡ በእርሱ ደረጃ የነበሩ ታላላቅ የአይሁድ ምሁራን መንፈሳዊ ስልጣናቸውና ሹመታቸው የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ረስተው በህዝቡ ላይ የሚመፃደቁ ነበሩ፡፡ በዘመናቸው እውቀትን የሚገልጥ እውነተኛ አምላክ፣ የካህናት አለቃ ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም ሲገለጥ የአይሁድ ምሁራን የጌታን መገለጥ አልወደዱትም፡፡ የእርሱ ትህትና የእነርሱን ትዕቢት የሚያጋልጥ ነበርና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሄዱትን ሁሉ ይነቅፉ ይከስሱ ነበር፡፡ ባለማወቅ ያደነደኑት የትዕቢት ልቦና ትህትናቸውን አጥፍቶባቸው ነበርና ዝቅ ብሎ በሰው ዘንድ በተናቁት በናዝሬትና በገሊላ እየተመላለሰ የሚያስተምር የዓለም ቤዛ የክርስቶስን ትምህርት እንዳይሰሙ ልባቸው ተዘግቶ ነበር፡፡ ጌታችንም የፈሪሳውያን ሀሳባቸው በግብዝነት የተሞላና ከንቱም እንደሆነ ነግሯቸዋል፡፡ ለደቀመዛሙርቱም ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ የሚበልጥ ሥራን እንዲሰሩ አስጠንቅቋቸዋል (ማቴ 5: 20 ማቴ 16:6)፡፡

ኒቆዲሞስ ግን ከእነዚህ ከፈሪሳዊያን መካከል የተገኘ ልዩ ምሁረ ኦሪት ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ራሱን ለእውነት ልቡን ለእምነት አዘጋጅቶ ከዅሉ ቀድሞ በሌሊት ክርስቶስን ፍለጋ የመጣ ከእነዚህ ፈሪሳዊያን ወገን ተለይቶ እንደ አባታችን አብርሃም ወደ ጽድቅ መንገድ የተጠራ ነው፡፡ ሹመት እያለው ሁሉ ሳይጎድልበት በዙርያው የነበሩት ከእኛ በላይ ማን አዋቂ አለ የሚሉ ከእውነት ጋር የተጣሉ ጌታችንን የሚያሳድዱ በእርሱም የሚቀኑና ጌታችንንም ለመግደልም ዕለት ዕለት የሚመክሩ ሁነው ሳለ ኒቆዲሞስ ግን እውነትን ለማወቅ እልቅናው ሳይታሰበው ከአካባቢው ጋር መመሳሰልን ሳይመርጥ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሊማር በሌሊት መጣ፡፡ መምህረ ትህትና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የኒቆዲሞስን ትህትናውን ተቀብሎ ለምን በቀን አትመጣም?” ሳይለው እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ትውልድ ሁሉ የሚማርበትን ረቂቁን ምስጢረ ጥምቀትን አስተማረው፡፡

አልዕሎ ልቡና (ልቡናን ከፍ ከፍ ማድረግ) – ኒቆዲሞስ ዳግመኛ የመወለድን ምስጢርን ለማወቅ ልቡናውን ከፍ ከፍ አደረገ፡፡

ለሥጋዊ ሕይወታችን እውቀት እንደሚያስገፈልገን ሁሉ ነፍስም ዕውቀት መንፈሳዊ ዕውቀት ያስፈልጋታል (ምሳ. 19፥2)፡፡ ኒቆዲሞስ በመጀመርያ የጥምቀትን ነገር ሲሰማ ለመቀበል ተቸግሮ ነበር፡፡ ጌታችን ግን የኒቆዲሞስን አመጣጥ በማየት ልቡናውንም ከፍ ከፍ ስላደረገ ምስጢረ ጥምቀትን ገለጸለት፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በሥርዓተ ቅዳሴ ምእመናንን በማነቃቃት ልቡናቸውን ከፍ እንዲያደርጉ “አልዕሉ አልባቢክሙ/ልቦናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ” ብሎ የሚያዘው ምእመናን የቅዱስ ሥጋውና የክቡር ደሙ ምስጢር እንዲገለጽልን፣ ከሥጋዊው መብል ሃሳብ ወደ ሰማያዊው መብል ልቡናችንን እንድናነሳ ሲያሳስብ ነው፡፡ ምእመናንም በጸሎተ ቅዳሴ ካህኑ የቅዱስ ኤጲፋንዮስን ትዕዛዝ ሲያሰማ “በአምላካችን በእግዚአብሔር ዘንድ አለን” በማለት እንመልሳለን።

መንፈሳዊ መረዳት የሚኖረንና በፈተናዎች ውስጥ ድል መንሳትን የምናገኘው ልቡናን ከፍ በማድረግ ከሁሉም የሚበልጠውን መንፈሳዊውን መንገድ በመከተል ነው፡፡ ግያዝ ከነብዩ ኤልሳዕ ጋር ሳለ ልቡናው ቁሳዊውን የሚመለከት እንጂ ሰማያዊውን ኃይል የተረዳ አልነበረም፡፡ ነብዩ ኤልሳዕ ግን ይህንን ምስጢር እንዲያይ ገለጸለት (2 ነገ 6:17)፡፡ እኛም ክርስቲያኖች በጸጋ የተሰጡንን ስጦታዎቻችንን እንድናውቅ ልቡናችንን ከፍ ከፍ አድርገን በመንፈሳዊ እውቀትና ልዕልና፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመረዳት፣ እንዴት በጽድቅ መመላለስ እንዲገባንና ስለምንወርሳት መንግስተ ሰማይ መማር ማወቅ ይገባናል፡፡ “ቅዱሱን ማወቅ ማስተዋል ነው” ተብሎ በምሳሌ መጽሐፍ እንደተጻፈ (ምሳ 9፥11) ኒቆዲሞስ ከፈሪሳውያን ህብረት ወጥቶ በትህትና ወንጌልን ለመማር በሃይማኖት ልቡናውን ለእግዚአብሔር ቃል አዘጋጀ፡፡ ለአብርሃም የግዝረትን ጸጋ የሰጠ ጌታ በትህትና ለቀረበው ኒቆዲሞስ የግዝረት ጸጋ ፍጻሜ የሆነች የልጅነት ጥምቀትን ነገር አስተምሮታል፡፡

ትግሃ ሌሊት (በሌሊት መትጋት) – ኒቆዲሞስ ቀን እየሠራ በሌሊት ወደ ጌታ በመሄድ ለትጋት አብነት ሆነን፡፡

ኒቆዲሞስ ወደ መድኃኔዓለም ለመማር የሄደው በሌሊት ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ በሚታሰብበት የዐቢይ ጾም ሰንበት በጸሎተ ቅዳሴ የሚዜመው የክቡር ዳዊት መዝሙር  “ሐወፅከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ፡፡ አመከርከኒ ወኢተረክበ ዐመፃ በላዕሌየ፡፡ ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ ዕጓለ እመሕያው/በሌሊት ጎበኘኸኝ፤ ልቤንም ፈተንኸው፣ ፈተንኸኝ፣ ዐመፅም አልተገኘብኝም፡፡ የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር” (መዝ. 16፡3)ይህን የሚያስረዳ ነው፡፡ ሌሊት በባህሪው ሕሊናን ለመሰብሰብ በተመስጦ ለመማር የሚመች ነው፡፡ ክርስትናም በተጋድሎ ሕይወት በመትጋት ሥጋን በቀንና ሌሊት ለነፍስ እንዲገዛ በማድረግ የሚኖር ሕይወት ነው፡፡ ጌታችን ሐዋርያቱን “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ” ባለው መሠረት ቤተክርስቲያንም በቀንና በሌሊት በኪዳኑ በቅዳሴው በማህሌቱ እግዚአብሔርን ታመሰግናለች፡፡ የቅዱሳን አባቶቻችን (አባ ቢሾይ) በሌሊት ጸሎት እንቅልፍ እንዳያስቸግራቸው ፀጉራቸውን ከዛፍ ቅርንጫፍ በማሰር ይተጉ ነበር፡፡ ለኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ ወደ ጌታችን መምጣት ልጅነትን ለምናገኝበት የምስጢረ ጥምቀት ትምህርት እንደተገለጠለት እኛም በሌሊት በነግህ ጸሎት በመትጋት ረቂቅ የሆነውን መንፈሳዊ እውቀት ሰማያዊ ምስጢር ይገለጥልናል፡፡

በዘመናችን ከቀድሞ ይልቅ ፈተና የሚገጥመን በሌሊት ከመትጋት ይልቅ አርአያነት በጎደለው ሕይወት ውስጥ ስንገኝ ነው፡፡ “ሌሊት ጌታን ለማመስገን የተፈጠረ ድንቅ ጊዜ ነው” እንዳለ ሊቁ ማር ይስሐቅ ራስን በቀንም በሌሊት ከሚመጣ ፈተና መጠበቅ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር የሙሴን አገልጋይ የነዌን ልጅ ኢያሱን እንደተናገረው በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ማንም እንዳይረታው፣ ከሙሴ ጋር እንደነበረ ከእርሱ ጋር እንዲኖር “ለአባቶቻቸው እሰጣቸዋለሁ” ብሎ የማለላቸውን ምድር እንዲወርስ በሚሔድበት ሁሉ እንዲከናወንለት ወደ ቀኝም ወደ ግራም እንዳይል ሃሳቡም እንዲቀና የምጽሐፉን ሕግ ከአፉ እንዳይለይ እንዲጠብቀውም በቀንም በሌሊትም ማሰብ እንደሚገባ ይነግረናል (ኢያ 1:1-8):: ቅዱስ ይስሐቅ ሶርያዊ “ከመኝታህ በፊት የምታደርገውን ጸሎት ትተህ እንድትተኛ መንፈስህ ሲገፋፋህ እሺ ብለህ አትቀበለው፡፡ እንዲያውም መዝሙረ ዳዊትን ጨምርና ሌሊቱን በሙሉ ስትጸልይ እደር’ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት “በሌሊት በቤተ መቅደስ ውስጥ እጆቻችሁን አንሡ፥ እግዚአብሔርንም ባርኩ።” መዝ 134:1-3 እንዳለ እኛም ከዚህ የፈተና ዓለም ለማምለጥ በኦርቶዶክሳዊ ሰውነት እንድንጸና በትጋት ወደ ቤተ ክርስቲያን በቀንና በሌሊት ልንገሰግስ በኪዳኑ በማኅሌቱ በቅዳሴው ጸሎት ልንሳተፍ ያስፈልጋል፡፡

ስምዐ ጽድቅ (የእውነት ምስክርነት) – ኒቆዲሞስ ማንንም ሳይፈራ እውነትን በመመስከር ከሳሾችን አሳፈራቸው፡፡ 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹እኔ ለእውነት ለመመስከር መጥቻለሁ›› በማለት እውነትን እንድንመሰክር አብነት ሆኖናል (ዮሐ.18፥37)፡፡ በተጨማሪም ‹‹በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፡፡ በሰው ፊት የሚክደኝን ሁሉ ደግሞ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ›› ሲል ስለ ሃይማኖታችን እውነትን መመስከር እንደሚገባን አስተምሮናል (ማቴ.10፥32-33)፡፡ እንዲሁም ለኒቆዲሞስ ሲያስተምረውም ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን›› በማለት ለእውነት መመስከር እንደሚገባ አስገንዝቦታል (ዮሐ 3፡11)፡፡ይህንን ቃል ከራሱ ጋር በማዋሀድ የአይሁድ የፋሲካ በዓል በቀረበበት ወቅት ጻፎችና የካህናት አለቆች ጌታን ለመያዝ፣ የሙሴን ሕግም አጣምመው ሊያስፈርዱበት በሚጥሩበት ጊዜ ኒቆዲሞስ የእውነት ምስክርነቱን አረጋገጠ፡፡ የሙሴ ፈጣሪ መሆኑን ባለማወቃቸው ምክንያት የካህናት አለቆች ተሰብስበው ክርስቶስን ለመያዝ ሲመካከሩ ከሙሴ መጽሐፍ ሕግ ጠቅሶ ሊቃውንተ ኦሪትን አፍ ያስያዛቸው እርሱ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ሳይስማሙ ወደየቤታቸው እንዲበታተኑ ምክንያት የሆነ ታላቅ ሰው ነው፡፡ 

ዮሐንስ ወንጌላዊ ይህንን የኒቆዲሞስን ምስክርነት “ከእነርሱ አንዱ በሌሊት ቀድሞ ወደ እርሱ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ ሕጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን? አላቸው። እነርሱም መለሱና፡- አንተም ደግሞ ከገሊላ ነህን? ነቢይ ከገሊላ እንዳይነሣ መርምርና እይ አሉት። እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ሄደ።” በማለት ገልጾታል (ዮሐ 7-50-52)፡፡ ኒቆዲሞስ ያለፍርሐትና ያለ ሀፍረት በካህናቱ ፊት እውነትን መስክሯል፡፡ እውነትንና ፀሐይን ፈርቶ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ካህናቱን መጽሐፍ ጠቅሶ እውነትን ተናግሮ አሳፍሯቸዋል፡፡ በመሪዎች ፊት በታላላቅ ሰዎች ፊት እውነትን መመስከር ክርስትናችን የሚያስገድደን ቁም ነገር ነው (ሉቃ 12፡ 8)፡፡ ቤተክርስቲያን “ሰማዕታት” እያለች የምትዘክራቸው ቅዱሣን በሙሉ ለእውነት ብለው ራሳቸውን ለክርስቶስ አሳልፈው የሰጡ ናቸው፡፡ በፍርሐትና በሀፍረት በይሉኝታና በሀዘኔታ እውነትን አለመመስከር በክርስቶስ ፊት ያስጠይቃል እንጅ አያስመሰግንም (ማቴ 10፡32)፡፡ ሐዋርያው “ለእውነት እንጅ በእውነት ላይ ምንም ማድረግ አንችልም” እንዳለ እኛም እንደ ኒቆዲሞስ የእውነት ምስክሮች እንሁን (2ቆሮ 13፡8)፡፡

ጽንዐ ሃይማኖት (በሃይማኖት መጽናት) –  ኒቆዲሞስ እስከ መጨረሻው በመጽናት ለታላቅ ክብር በቃ፡፡

 በጌታችን ትምህርት ተስበው ተዓምራቱን በማየት ከተከተሉት ሰዎች ውስጥ በቀራንዮ የተገኙት ጥቂት ናቸው፡፡ ከእነዚህ አንዱ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ ቀራንዮ የምግበ ነፍስ ቦታ ናትና ኒቆዲሞስም ፈተናን ሳይሰቀቅ እስከ መጨረሻው የጸና ፃድቅ ነው፡፡ የክርስትና አገልግሎት ሲመቸን የምንሳተፍበት ፈተና ሲበዛ የምንሸሽበት አይደለም፡፡ ክርስትና በጅምር የሚቀር ሳይሆን እውነትን ሳንፈራ በመመስከር በተጋድሎ የምናሳልፍበት ለፈጸሙትም የድል አክሊል የሚያገኙበት ሕይወት ነው (2ጢሞ 4:8)፡፡ ምሳሌ ከሚሆኑን ቅዱሳን አንዱ አባታችን ቅዱስ እንጦንስ በፍጹም መንፈሳዊ ተጋድሎ ለ35 ዓመታት ከዚህ ዓለም ተድላና ደስታ በመራቅ እንዲሁም በአህዛብ መካከል ክርስትናን በመግለጽ የጽናት ታላቅ አስተማሪ ነው::

ኒቆዲሞስም ከጌታችን በተማረው ትምህርት ጸንቶ ለመኖር የበቃ አባት ነው፡፡ የሃይማኖቱ ጽናትም በተግባር የተፈተነ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ የአርማትያስ ሰው ከሚሆን ከዮሴፍ ጋር በመሆን የአይሁድን ድንፋታ ሳይፈራ “እሱን ያገኘ ያገኘኛል” ሳይል በድፍረት የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውን በንጹሕ የተልባ እግር በፍታ ገንዞ በአዲስ መቃብር፣ በጌቴሴማኒ የቀበረ ሰው ነው (ዮሐ 19፥ 38)፡፡ ኒቆዲሞስ ከሐዲስ ኪዳን ካህናት ቀድሞ የጌታችንን ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሀደው ክቡር ሥጋ ለመገነዝ የበቃ አባት ነው፡፡ የጌታችንን ክቡር ሥጋ ገንዘው ሲቀብሩም በጸናች የተዋህዶ እምነት ጌታ እንደገለጠላቸው “ቅዱስ እግዚአብሔር፣ ቅዱስ ኃያል፣ ቅዱስ ህያው ዘኢይመውት” የሚለውን ቤተክርስቲያናችን እስከ ዕለተ ምጽአት የክርስቶስን ሥጋና ደም ስትባርክ የምትጠቀምበትን ጸሎት እስከ ፍፃሜው እየጸለዩ ነበር፡፡ በዚህም ኒቆዲሞስ ከሐዲስ ኪዳን ካህናት ቀድሞ ምስጢረ ጥምቀትን ከጌታ እንደተማረ፣ የሐዲስ ኪዳንን የምስጢራት አክሊል ምስጢረ ቁርባንንም እንዲሁ ተማረ፡፡ ይህንንም በሚመለከት ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ አብሮት ይቀድስ የነበረውን ንፍቅ ካህን በባረከበት አንቀጽ “በዚህ ምስጢር እየተራዳኝ ከእኔ ጋር ያለ ይህንን ካህን እርሱንም እኔንም ሥጋህን እንደገነዙት እንደ ዮሴፍና እንደ ኒቆዲሞስ አድርገን” (ቅዳሴ ማርያም ቁጥር 115) ብሏል፡፡

እኛም እንደ ኒቆዲሞስ፡-

  1. በዕውቀታችን፣ በስልጣናችን፣ በሀብታችን፣ ባለን ማንነት ሳንታበይ ራሳችንን ዝቅ በማድረግ የእውነተኛ አባቶችን ትምህርት፣ ምክርና ተግሳፅ ልናዳምጥ በተግባርም ልናውለው ይገባናል፡፡
  2. የያዝነውን እውነተኛ እምነት በማጠንከር በሃይማኖት ልብ የቤተክርስቲያንን ምስጢራት በትህትና ለመሳተፍ ልቡናችንን ከፍ ከፍ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
  3. ምድራዊ አመክንዮ ሳያሰናክለን በቀንና በሌሊት ወደ አማናዊት የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ለምስጋና መሄድ ይኖርብናል፡፡
  4. እውነትን በማድረግ ሕይወት የሚገኝበትን ቃለ እግዚአብሔርን ያለኃፍረትና ያለፍርሀት ልንመሰክር ያስፈልጋል፡፡
  5. ክርስትና ምድራዊ ስጦታና ተዓምራት በሚገለጥበት በገሊላ ባህር አጠገብ ብቻ ሳይሆን መከራና ስቃይ ባለበት በቀራንዮም መገኘትን ይጠይቃልና በፈተናና በመከራ ጊዜም ቢሆን በእምነት ልንጸና የበለጠም በመታመን ልናገለግል ይገባል፡፡

ከኒቆዲሞስ ሕይወት ተምረን በሃይማኖት እንድንጸና የአባቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s