ገብር ኄር፡ ካህናት ብቻቸውን ወደ ገነት አይገቡም!

በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን የበዓላት ቀኖና መሰረት የዐቢይ ጾም ስድስተኛው ሰንበት ገብር ኄር ይባላል፡፡ በዚህ ሳምንት የሚነበበውና የሚተረጎመው በማቴዎስ ወንጌል 25፡14-30 ድረስ የተጻፈው የገብር ኄርና ገብር ሐካይ (የእውነተኛ አገልጋይና የሐኬተኛ አገልጋይ) ምሳሌ (The Parable of Talents) ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24:1-42 የዳግም ምጽዓቱን ነገር ለደቀ መዛሙርቱ አስተማራቸው፡፡ የጌታችን ዳግም ምጽዓቱ ለፍርድ ነውና፣ የሚመጣበትም ቀንና ሰዓት በፍጡራን አይታወቅምና  በፍርድ ቀን በቀኙ መቆም እንድንችል ምን ማድረግ እንዳለብን ሲያስተምር እንዲህ አለ “ስለዚህ እናንተም ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና” ማቴ. 24፡44፡፡ ይህን ከተናገረ በኋላ በሁለት ምሳሌዎች መስሎ አስተማረ፡፡ እነዚህም የዐሥሩ ደናግልና የሦስቱ አገልጋዮች (የመክሊት) ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ሊቃውንት እንደሚያስተምሩን የመጀመሪያው ለምዕመናን ሁለተኛው ደግሞ በዋናነት ለካህናት ተግሳጽ የተጻፉ ምሳሌዎች ናቸው፡፡

እነዚህ ምሳሌዎች ምዕመናን ሃይማኖታቸውን ጠብቀው፣ ምግባራቸውን አቅንተው እንዲኖሩ፣ ካህናትም እንደምዕመናን ሃይማኖታቸውን ከመጠበቅና ምግባራቸውን ከማቅናት ባሻገር ሌሎችን እያስተማሩ በሃይማኖት በምግባር እንዲያጸኑ ለማበርታት የተጻፉ ናቸው፡፡ የዚህ ሣምንት የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ትኩረት መንገድ የሚሄድ ባለገንዘብ ሦስት አገልጋዮቹን ጠርቶ እንዲያተርፉበት መክሊት መስጠቱና ከእነርሱም ሁለቱ ገብር ኄር (እውነተኛ/ታማኝ አገልጋይ) በመሆን የገንዘቡ ባለቤት (ጌታቸው) ሲመጣ መመስገናቸው፣ የዘላለም ህይወት ምሳሌ የሆነ ክብር ማግኘታቸው፣ ሦስተኛው ግን ገብር ሐካይ (ሐኬተኛ/ሰነፍ አገልጋይ) በመሆኑ የገንዘቡ ባለቤት (ጌታው) ሲመጣ እንደገሰጸው፣ የዘላለም ሞት ምሳሌ ወደሆነ የስቃይ ቦታም እንደተጣለ ይተርካል (በማቴዎስ ወንጌል 25፡14-30)፡፡

ጌታችን በመክሊቱ ምሳሌ ያስተማረው ትምህርት ትርጉሙ እንዲህ ነው፡፡ ለሦስቱ አገልጋዮች ገንዘብ የሰጣቸው ባለገንዘብ የአምላካችን የእግዚአብሔር ምሳሌ ነው፡፡ ለሰዎች ሁሉ ጸጋን፣ ስጦታን  የሚሰጥ ጌታ ለአገልጋዮቹ እንደየአቅማቸው አምስት፣ ሁለትና አንድ መክሊት ሰጣቸው፡፡ መክሊት የተባለው የአገልግሎት ጸጋ ምሳሌ ነው፡፡ ጌታችን ለእያንዳንዱ እንደአቅሙ የአገልግሎት ጸጋ ይሰጣልና፡፡ አገልጋዮቹ ደግሞ የአገልግሎት ጸጋ የተቀበሉና ምዕመናንን በመንፈሳዊ ሥርዓት የሚያገለግሉ ካህናትና (እንደአገባቡ) በልዩ ልዩ ጸጋ የሚያገለግሉ ምዕመናን ምሳሌ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ስለዚህ ምሳሌ ሲያስረዳ (በጾመ ድጓ) ‹‹መኑ ውእቱ ገብር ኄር ወምእመን ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይ ወይሠይሞ ዲበ ኲሉ ንዋዩ ካዕበ ይቤሎ እግዚአብሔር ገብር ኄር ወምእመን ዘበውኁድ ምእመነ ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሠይመከ ባእ ውስተ ፍሥሐሁ ለእግዚእከ /ጌታው በመልካም ሥራ የሚያገኘው በሐብቱ ኹሉ ላይ የሚሾመው፤የታመነ በጎ አገልጋይ ማን ነው? ዳግመኛም እግዚአብሔር አንተ የታመንክ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ የታመንህ ስለኾንህ በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ይለዋል፡፡/›› ብሏል፡፡

ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው (እንደ አቅሙ) መክሊት ተሰጥቶታል፡፡ ጌታ ለአንዱ አምስት፣ ለአንዱ ሁለት፣ ለአንዱ አንድ መክሊት የሰጠው እንደየአቅማቸው ነው፡፡ አምስት ለሰጠው ሁለት፣ ሁለት ለሰጠው አንድ፣ አንድ ለሰጠው አምስት መስጠት ተስኖት ሳይሆን እንደችሎታቸው፣ እንደአቅማቸው ሰጣቸው፡፡ ጌታችን፣ ፈጣሪያችን፣ እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን እንደአቅማችን የአገልግሎት ጸጋ ሰጥቶናል፡፡ ሁለት የተሰጠው ለምን አምስት አልተሰጠኝም አይበል፣ ይልቁንስ በተሰጠው ይታመን፤ በተሰጠው ታምኖ ሲያገለግል ይጨመርለታልና፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “መንፈስ ቅዱስ አንድ ሲሆን ስጦታው ልዩ ልዩ ነው፡፡ ጌታም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ፡፡ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አሠራር አለ፡፡ ለሁሉም ጌታ እየረዳ በየዕድሉ እንደሚገባውና እንደሚጠቅመው ለእያንዳንዱ በግልጥ ይሰጠዋል፡፡ “(1ኛ ቆሮ. 12፡4-7) እንዳለ ሁሉም በተሰጠው ጸጋ መጠን እንዲያገለግል መክሊቱን ተቀብሏል፡፡

መክሊት የተሰጠን እንድናተርፍበት ነው፡፡ “አገልጋዮቹንም ጠርቶ ሊያተርፉበት ገንዘቡን ሰጣቸው” እንደተባለ የጸጋ ስጦታን የምንቀበለው እንድናተርፍበት ነው፡፡ ማትረፍ ማለት በሥጋዊ ንግድ እሳቤ ለግል የሚሆን ጥቅም ማግኘት ማለት ሳይሆን የተሰጠንን መንፈሳዊ እውቀት፣ ጸጋ ለሌሎች ማካፈል፣ በዚያም ከራሳችን አልፈን ለሌሎች የድኅነት ምክንያት መሆን ማለት ነው፡፡ የአገልግሎት መክሊት ለሥጋዊ ክብር የሚሰጥ አይደለም፡፡ በዘመናችን ግን የአገልግሎትን መክሊት ለሥጋዊ ጥቅም የሚያውሉ ሐኬተኛ አገልጋዮች በዝተዋል፡፡ እውነተኞቹ፣ ታማኞቹ አገልጋዮች (ገብር ኄር ) ግን መንፈሳዊ ትምህርት፣ መንፈሳዊ ጸጋ ሲሰጣቸው የራሳቸውን ክብርና ጥቅም ንቀው ሌሎች የእግዚአብሔርን ብርሃን እንዲያዩ፣ ለመንግስተ ሰማያት የሚያበቃ እምነትና ምግባር እንዲይዙ ለማድረግ ምክንያት ይሆናሉ፡፡

መክሊት የሰጠ ጌታ አገልጋዮቹን ሊቆጣጠር ይመጣል፡፡ “ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ ተመልሶ ተቆጣጠራቸው” እንዲል ጌታችን እግዚአብሔር አገልጋዮችን፣ እንደ አቅማችን የምናገለግል ሁላችንንም በተሰጠን መክሊት ምን እንዳተረፍንበት ሊቆጣጠረን ይመጣል፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለው ታማኝ አገልጋይ ሄዶ፣ ነግዶ፣ ወጥቶ ወርዶ ሌላ አምስት መክሊት አተረፈ፤ ሁለት የተሰጠውም እንዲሁ በድካም፣ በመታዘዝ ሌላ ሁለት አተረፈ፡፡ እነዚህ አገልጋዮች የተሰጣቸውን እንደችሎታቸው አትርፈዋልና መንግስተ ሰማያትን እንደሚወርሱ በሚያስረዳ ምሳሌ”አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” እየተባሉ ተመሰገኑ፡፡ በገብር ኄር ሰንበት በቅድስት ቤተክርስቲያናችን በጸሎተ ቅዳሴ በሚሰበከው ምስባክ “ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ፡፡ ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ፡፡ ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር ዐቢይ/አምላኬ ሆይ ፈቃድህን ለማድረግ መከርሁ፣ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው፡፡ በታላቅ ጉባኤ ጽድቅህን አወራሁ” (መዝ. 39፡8-9) እንደተባለ ገብር ኄር የተባሉ ደገኛ አገልጋዮች የጽድቅን አገልግሎት ሳይፈሩና ሳያፍሩ በታላቅ ጉባኤ (ፈተና በበዛበት ቦታ ሁሉ) ይናገራሉ፡፡

ሁለቱ ታማኝ አገልጋዮች በመክሊቱ ነግደው ስላተረፉ ተመሰገኑ፡፡ በክቡር ዳዊት መዝሙር እንደተጠቀሰው እውነተኛ አገልጋዮች እውነት የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል በግልጥ ያስተምራሉ፡፡ እውነትን ሲመሰክሩም “እኔን ካሳደዱ እናንተንም ያሳድዷችኋል” (ዮሐ. 15፡20) እንደተባለ ከአላውያን ባለስልጣናት፣ ከከሀድያን፣ ከሐሰተኛ መምህራን፣ ቤተክርስቲያንን መመዝበር ከሚፈልጉ ምንደኞች፣ በዘረኝነት ከታወሩ ሰዎችና ሌሎች ስደትና መከራ ይደርስባቸዋል፡፡ ይህን ታግሰው በአገልግሎታቸው ከጸኑ ለምህረትና ለሥርየተ ኃጢአት የበቁ ይሆናሉ፡፡ በአገልግሎታቸው ወራት ከንቱ ውዳሴንና ምስጋናን ንቀዋልና ጌታቸው ሲገለጥ ተመሰገኑ፤ በአገልግሎታቸው ወራት በእምነት በመውጣትና በመውረድ ደክመዋልና ጌታቸው ሲገለጥ ድካም ወደሌለበት ሰማያዊ ደስታ በቅዱሣን  መላእክት ታጅበው ገቡ፤ በአገልግሎታቸው ወራት በሰው ፊት ስለቀና አገልግሎታቸው ያለአግባብ ተሰድበዋልና ጌታቸው ሲገለጥ በአደባባይ አመሰገናቸው፡፡

ሦስተኛው አገልጋይ ግን ሰነፍ ስለነበር የተሰጠውን መክሊት ሥራ ሳይሠራበት ቀበረው፡ የተሰጠውን የአገልግሎት ጸጋ እንደ አቅሙ ከመጠቀም ይልቅ የመናፍቃንን ክርክርና ሥም ማጥፋት፣ የዓለምን ፈተና፣ የሥጋውን ምኞት መቋቋም አቅቶት መክሊቱን ቀበረው፡፡ ጌታው ሲጠይቀው ግን የተገለጠ ድካሙን ከማስተዋል ይልቅ በሀሰት ቃል ጌታውን ወቀሰው፡፡ ሰነፍ አገልጋዮች ሁሌም እንዲህ ናቸው፤ ለስንፍናቸው ሌሎችን ተጠያቂ ያደርጋሉ እንጅ ወደራሳቸው ተመልክተው ስህተታቸውን አያርሙም፡፡ ጌታም ቅዱሳን መላእክቱን “ይህን መክሊት ከእርሱ ተቀብላችሁ ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት፡፡ ላለው ሁሉ ይሰጡታልና፤ ይጨምሩለታልም፤ ለሌለው ግን ያንኑ ያለውን ይወስዱበታል፡፡”  (ማቴ 25፡28-29) በማለት ተናገረ፡፡ “ላለው ይሰጡታል፣ ለሌለው ይወስዱበታል” የሚለውን አገላለጽ በጥራዝ ነጠቅ አረዳድ መልእክቱን ሳይረዱ የሚተቹ ሰዎች አሉ፡፡ ይህ ቃል በዋናነት የተነገረው ስለመንፈሳዊ ጸጋ፣ ስለመንፈሳዊ አገልግሎት እንጅ ስለምድራዊ ንግድና ትርፍ አለመሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡ ያላተረፈ ካህን፣ ያላተረፈ መምህር፣ ያላተረፈ አገልጋይ ፍጻሜው የዘላለም ሞት መሆኑንም ጌታ በዚህ ሰው ላይ በተናገረው ተረዳን፡፡ “ክፉውን አገልጋይ ግን ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወደ አለ ጨለማ አውጡት፡፡” (ማቴ. 25፡30)

በተሰጠው መክሊት ሠርቶ ያላተረፈበት ተፈረደበት፡፡ ለራሱ በተሰጠው መክሊት ያላተረፈ፣ መክሊቱን የቀበረው አገልጋይ በጌታ ከተፈረደበት የሌሎችን የእውነተኛ አገልጋዮችን የአገልግሎት ጸጋ (መክሊት) አላዋቂነትና ምቀኝነት በወለደው እልህ የሚቀብሩ፣ የጽድቅ አገልግሎትንም የሚያደናቅፉ መናፍቃን፣ ምንደኞችና ዘረኞች በጌታ ፊት ሲቀርቡ ምን ይመልሱ ይሆን?! እንግዲህ እናስተውል! የጽድቅን አገልግሎት ለመቅበር የሚሯሯጡ ምንደኞች መጠቀሚያ መሆን የለብንም፡፡ በመክሊቱ ምሳሌ የተጠቀሰው ሐኬተኛ (ሰነፍ) አገልጋይ ገብር ኄር ከተባሉት ከሁለቱ የታመኑ አገልጋዮች ተለይቶ ለመንግስተ ሰማያት ክብር  የበቃ፣ የተዘጋጀ ያልሆነው በተሰጠው መክሊት ወጥቶ ወርዶ ስላላተረፈ (ስላልሰራበት ነው)፡፡ ካህናት ከሌሎች ምዕመናን በተለየ ተጨማሪ ግዴታ አለባቸው፡፡ ያን ግዴታቸውን እንደአቅማቸው ሳይለግሙ ከተወጡ ክብራቸው በመንግስተሰማያት ከምዕመናን ሁሉ የተለየ እንደሆነ አባቶቻችን አስተምረውናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በመንግስተሰማያት ከአንዱ ኮከብ ክብር የሌላው ኮከብ ክብር እንደሚበልጥ ያስተማረው ይህን ያስረዳናል (1ኛ ቆሮ. 15፡41)፡፡  ይሁንና ካህናት ግዴታቸውን ካልተወጡ፣ ከሃይማኖት የወጡትን፣ በምግባር የደከሙትን ካላበረቱ፣ በአገልግሎታቸውም እንደ ታማኝ አገልጋይ በቅንነት ካላተረፉ ወደ መንግስተ ሰማያት አይገቡም፡፡ ክብራቸው ከምዕመናን እንደሚበልጥ ሁሉ ግዴታቸውም እንዲሁ ይበልጣልና፡፡

የሐኬተኛው አገልጋይ ታሪክ የሚያረጋግጥልን ካህናት ብቻቸውን ወደ ገነት መግባት እንደማይችሉ ነው፡፡  በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ አንድ ሰው ለመዳን እምነት (ሃይማኖት) ከምግባር አስተባብሮ መያዝ አለበት፡፡ ያለሃይማኖት የሚሰራ ምግባር፣ ኑፋቄ ባለበት እምነት የሚሰራ ምግባር ለድኅነት አያበቃም፡፡ ድኅነት በጸጋ ያገኘናት፣ የምናገኛት እንጅ በድካማችን ተመክተን የምናገኛት አይደለችምና፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ቅዱስ ያዕቆብ “ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው” (ያዕ. 2፡26) እንዳለ ያለምግባር በሃይማኖት (በእምነት) ብቻ መዳን አይቻልም፡፡ አምስቱ ደናግል እምነት የተባለ መብራት ነበራቸው፤ ምግባር የተባለ ዘይት ግን ስላልያዙ ከመንግስተሰማያት በአፍአ ቀርተዋል፡፡ ቤተክርስቲያንን የሚያገለግሉ መምህራን፣ ካህናት ከመምህርነታቸው፣ ከክህነታቸው በፊት እንደ አምስቱ ልባም ደናግላን ሃይማኖትን ከምግባር አስተባብረው የያዙ መሆን አለባቸው፡፡ ምዕመን ሳይሆኑ ካህን፣ መምህር መሆን አይቻልም፡፡ እውነተኛ አገልጋዮች የሚባሉትም ከመምህርነታቸውም ሆነ ከክህነታቸው በፊት እውነተኛ ምዕመናን የሆኑት ናቸው፡፡

አረጋዊው የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ይህን በተመለከተ ሲያስተምሩ እንዲህ ብለዋል፡- “ምዕመናን እድለኛ ናቸው፤ ወደገነት ብቻቸውን መግባት ይችላሉ፡፡ ካህናት ግን ብቻቸውን ወደገነት መግባት አይችሉም፡፡” የገብር ሐካይ (የሐኬተኛው አገልጋይ) ታሪክ የሚያረጋግጥልን ይህንኑ ነው፡፡ ካህናት እምነታቸውን ቀብረው መኖር አይገባቸውም፡፡ ከቀበሩት ግን፣ ሌሎችን ካላፈሩበት፣ ካላስተማሩበት ከመንግስተ ሰማያት በአፍአ ይቀራሉ፡፡ የካህናት፣ የመምህራን መክሊት ለራሳቸው ለመዳን ብቻ አይደለም፡፡ አገልግሎታቸውን ፈጸሙ የሚባለው የራሳቸውን መዳን ፈጽመው ለሌሎችም መትረፍ ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ ለዚያ ነው ብጹዕ አባታችን “ካህናት ግን ብቻቸውን ወደገነት መግባት አይችሉም፡፡” በማለት አመስጥረው ያስተማሩት፡፡

የዘመናችን ሐኬተኛ አገልጋዮች ራሳቸው የማያደርጉትን ለሌሎች አድርጉ የሚሉት  ናቸው፡፡  በየዘመናቱ የሚነሱ ምንደኞች አገልግሎትን ለእምነት፣ በእምነት ሳይሆን ከእምነት ተለይተው እንደሥራና ግዴታ ወይም እንደ የገቢና የዕውቅና ምንጭ ያዩታል፡፡ እነርሱ ሳያምኑ ሌሎችን ለማሳመን ይሞክራሉ፣ እነርሱ ንስሐ ሳይገቡ ሌሎችን ንስሐ ግቡ ብለው ያስተምራሉ፤  እነርሱ ሳይሰግዱ (ይልቁንም በጸሎተ ቅዳሴ እንኳ ሰው ሁሉ ሲሰግድ እነርሱ ግን ከእምነት በተለየ ልቦና መስገድ ሲችሉ በትዕቢትና በትዕዝርት በምዕመናን ፊት እየተቀመጡ) ሌሎችን ስገዱ ብለው ያስተምራሉ፤ እነርሱ ሳይጾሙ በአጽዋማትም በአደባባይ ቤተክርስቲያንን የሚያስነቅፍ ነውር እያደረጉ ሌሎችን ጹሙ ብለው ያስተምራሉ፤ እነርሱ ሳይመጸውቱ፣ አስራቱን ሳያወጡ ሌሎችን ምጽዋት ስጡ፣ አስራት አውጡ እያሉ ያስተምራሉ፤ ምጽዋትን ቢሰጡ እንኳ ሰው እንዲያውቅላቸው በአደባባይ ነጋሪት እያስጎሰሙ ይሰጣሉ፤ ይህን የሚያደርጉትም ለጽድቅ ብለው ሳይሆን በሰዎች ለመመስገን ነው፤ ምዕመናንን ከከንቱ ውዳሴ እንዲርቁ ያስተምራሉ እነርሱ ግን በራሳቸው የታይታ ስጦታ ብቻ ሳይሆን ሌሎች በሰጡት ስጦታ እንኳ በከንቱ ውዳሴ ይሸነጋገላሉ፡፡ እውነተኛ ካህናት ግን ከክህነታቸው፣ ከመምህርነታቸው በፊት እውነተኛ ምዕመናን ናቸው፣ ከማስመሰልና ከሽንገላ የተለዩ ናቸው፣ አገልግሎታቸውም ለነቀፋ አይመችም፡፡

አገልጋዮች የድካማቸውን ዋጋ ከባለቤቱ ይቀበላሉ እንጂ ትርፉም ይሁን ዋናው የእነርሱ አይደለም፡፡ ዛሬ እኛ ከመክሊቱ ምሳሌ የምንማረው ለአገልግሎት ስንዘጋጅ ለአገልግሎታችን የሚያስፈልገንን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጠን፣ የእያንዳችን የአገልግሎት ጸጋ የተለያየ መሆኑን፣ የምናገለግለው የእርሱን ፈቃድ እንጂ የራሳችንን ፍላጎት መሆን እንደሌለበት፣ መንፈሳዊ አገልግሎት የጽድቅ ዋጋን የሚያሰጥ መሆኑንና እንዲሁም ተጠያቂነት ያለበት መሆኑን ነው፡፡ የገንዘቡ ባለቤት (እግዚአብሔር) የሰጣቸውን መክሊት (ዋናውን) እና ሠርተው የጨመሩትን  መክሊት(ትርፉን) እንደተቆጣጠራቸው አገልጋዮችም የተሰጣቸው ጸጋም ይሁን በአገልግሎታቸው ያተረፉት የእርሱ የባለቤቱ መሆኑን መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡

የመክሊቱ ምሳሌ የተጻፈው እምነት ለሌላቸውና አገልግሎትን “እንደ ሥራ” ብቻ ለሚያዩ ሳይሆን እንደየአቅማቸው እምነትና ምግባርን አስተባብረው ይዘው ለሌሎች ለመትረፍ የአገልግሎት ጸጋ ለተቀበሉት ነው፡፡  ይህም በአንብሮተ ዕድ ለተሾሙ በተለየ አገልግሎት የእግዚአብሔርን ቤተመቅደስ ለሚያገለግሉ፣ የሰማይ መላእክት አምሳል ለሆኑ ካህናት ብቻ ሳይሆን በየደረጃው በሰንበት ት/ቤት፣ በሰበካ ጉባኤ፣ በልዩ ልዩ መንፈሳውያን ማኅበራት፣ በሰፈርና በቤተሰብ የሚያገለግሉትንም ይጨምራል፡፡ ስለሆነም ሁላችንም ደካማ አገልጋዮቹ እምነትን ከምግባር አስተባብረን፣ በተሰጠን መክሊት አትርፈን ለሌሎች የመዳን ምክንያት እንድንሆን፣ የራሳችንንም መዳን በእምነት እንድንፈጽም የቅዱሳንና ቅዱሳት አባቶቻችንና እናቶቻችን አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

 

 

1 thought on “ገብር ኄር፡ ካህናት ብቻቸውን ወደ ገነት አይገቡም!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s