የዐቢይ ጾም አምስተኛው ሰንበት “ደብረ ዘይት” ይባላል፡፡ ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ዛፍ ያለበት ተራራ ማለት ነው፡፡ ቦታው ከኢየሩሳሌም በስተምስራቅ የሚገኝ የወይራ ዛፍ የበዛበት ተራራ ሲሆን ስሙም ከወይራ ዛፉ የተነሳ “ደብረ ዘይት (የወይራ ዛፍ ተራራ) (Mount of Olives)” ተብሏል። በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የደብረ ዘይት በዓል የጌታችን ዳግም ምጽአት፣ የዓለም ፍጻሜ ጉዳይ የሚሰበክበት እና የሚተነተንበት በዓል ነው፡፡ ይህም የተደረገው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረዘይት ተራራ ላይ ሳለ ለቅዱሳን ደቀመዛሙርቱ ስለ ዓለም ፍጻሜ እና ስለ ዳግም ምጽአቱ ስላስተማራቸዉ በጌታችን ትምህርት መሰረት ነገረ ምጽአቱን (የመምጣቱን ነገር) እንድናስታዉስ ወይም እያሰብን እንድንዘጋጅ ለማድረግ ነዉ።
ደብረ ዘይት ጌታችን በደብረ ዘይት ተራራ ‹‹የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱ ምንድን ነው?›› ብለው ሐዋርያቱ ለጠየቁት ታላቅ ጥያቄ በስፋትና በጥልቀት ትምህርት የሰጠበት ክፍል የሚሰበክበት ዕለት ነው፡፡ ጌታችን ስለ ምጽአቱ ያስተማረው (ማቴ 24፡1-36)፣ በ40ኛውም ቀን ያረገው (ሐዋ 1:12)፣ ዳግመኛም ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው (ዘካ 14፡4) በዚሁ በደብረ ዘይት ተራራ ነው፡፡ ጌታችን ስለ ዳግም ምጽአቱ ባስተማረው ትምህርት ዘመኑ ሲቃረብ የተለያዩ ተፈጥሮአዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ምልክቶች እንዲሚከሰቱ ተናግሯል፡፡ የሚመጣበትን ዕለቱንና ሰዓቱን ሳይሆን ምልክቶችን ነገረን፡፡ እነዚህም ምልክቶች አብዛኞቹ በዘመናችን እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ምልክቶች ሲታዩ ምን ማድረግ እንደሚገባንም ሲያስተምር ሰባት ዋና ዋና ማስጠንቀቂያ አዘል ምክሮችን ሰጥቶናል፡፡ እነዚህም፡-
ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ይነሳሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉና እንዳለው እኛም ከሐሰተኞች ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ ሐሰተኞች በእርሱ ስም ወይም በቅዱሳን ስም የበግ ለምድ ለብሰው በጎችን ለመንጠቅ ሲመጡ እኛም በእነርሱ እንዳንነጠቅ እንድንጠነቀቅ ይህንን ማስጠንቀቂያ ሰጠን፡፡ እነዚህም ሐሰተኞች ጥቂት ሳይሆኑ ብዙዎች፣ አንድ ጊዜ ተነስተው የሚጠፉ ሳይሆን በየዘመናቱ መልካቸውን እየቀያየሩ የሚነሱ ናቸው፡፡ ተዓምራትን በማድረግ፣ የእግዚአብሔር ሰዎች በመምሰል ይመጣሉ፡፡ ነገር ግን አሰራራቸው በቃለ እግዚአብሔር ሚዛንነት ሲታይ ሀሰተኛነታቸው ይገለጣል፡፡
በሐሰተኞች ወሬ ልባችሁ አይታወክ፡፡ ማንም ክርስቶስ በዚህ አለ ወይም በዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፡፡ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሳሉና፡፡ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳን እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ፡፡ አስቀድሜ ነገርኳችሁ፤ በበረሀ ነው ቢሏችሁ አትውጡ፤ በእልፍኝም ነው ቢሏችሁ አትመኑ በማለት የትንቢቱ መፈጸሚያ እንዳንሆን እንድንጠበቅ አስጠንቅቆናል፡፡ በሐሰተኛ ወሬና ተዓምራት ምዕመናንን ከእውነተኛ እምነት ለማስወጣት ሐሰተኞች ይደክማሉ፡፡ እኛ ግን በሐሰተኞች ማጭበርበር ሳንደናገር እውነት የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይዘን የክርስቶስን መገለጥ በተስፋ እንድንጠብቅ ታዘናል፡፡
ትንቢቱ ሊፈጸም የግድ ነውና አትደንግጡ፡፡ የታየው ምልክቱ እንጂ መጨረሻው አይደለምና አትደንግጡ፡፡ ጦርንም የጦርንም ወሬ ስትሰሙ፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግስትም በመንግስት ላይ ሲነሳ ስታዩ፣ ረሀብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ ሲሆን አትደንግጡ፡፡ ይህ መጀመሪያው እንጂ መጨረሻው አይደለምና! ይህም ሁሉ ሊሆን የግድ ነውና አትደንግጡ፡፡ አለመደንገጥ ነገሮችን በጥሞና ለመመርመር ይጠቅማልና ‹‹አትደንግጡ›› አለን፡፡ መደንገጥ፣ መረበሽ መፍትሔ አይሆንምና፤ እነሆ አስቀድሞ ተነግሮናልና ምልክቶቹ ሲፈጸሙ መደንገጥ የለብንም፡፡ ትንቢቶች የሚፈጸሙት ጌታ ነገሮችን ቀድሞ ስለወሰናቸው ሳይሆን ቀድሞ ስላወቃቸው መሆኑን እናስተውል፡፡ ስለሆነም በትንቢት የተነገሩ ክፉ ነገሮች ሁሉ ሲፈጸሙ ማድረግ የሚገባንን ከማድረግ ይልቅ በሰነፍ እይታ “ምን ይደረግ?! ያው ትንቢቱ መፈጸሙ አይቀርም” ብለን ራሳችንን በማስነፍ የክፋት ተባባሪ መሆን አለብን ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንስ እንደ ደጋግ አባቶቻችንና እናቶቻችን የአቅማችንን አድርገን እንደበጎ አገልጋይ በጌታ ምጽአት ለመመስገን፣ ክብርን ለማግኘት እንትጋ፡፡
የጥፋትን ርኩሰት በተቀደስው ስፍራ ስታዩ ቀኑ እንደቀረበ አስተውሉ፡፡ ምልክቶቹ ሲታዩ ጊዜው እንደደረሰ አስተውሉ፡፡ ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፡፡ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቆጠቁጥ ያን ጊዜ በጋ እንደቀረበ ታውቃላችሁ፡፡ እንዲሁ እነዚህ ምልክቶች ሁሉ ሲታዩ በደጅ እንደቀረበ እወቁ፡፡ በደጅ ያለ ቶሎ መግባት ይችላልና ይህንን አለ፡፡ ምልክቶቹ ሲታዩ መስማትና ማየት ብቻ ሳይሆን ማስተዋልም እንደሚገባ ይህንን አስተማረን፡፡ የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰው ስፍራ ስናይ እንድናስተውል፣ በንስሐም እንድንመለስ ታዘናል እንጅ “ምን ይደረግ?! የዘመኑ ፍጻሜ ስለሆነ ለውጥ ማምጣት አንችልም” በሚል የስህተት ምክንያት ራሳችንን እያታለልን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰው ስፍራ መፈጸም፣ የሚፈጽሙትንም መተባበር በጌታችን ግራ ቆመው ከሚፈረድባቸው ወገን ያደርገናልና በተቀደሰው ስፍራ፣ በመንፈሳዊ አገልግሎት ከጥፋት ርኩሰት ልንርቅ፣ የቀረቡትንም በትምህርትና በተግሳጽ ከጥፋት ልናርቃቸው ይገባል፡፡
እስከመጨረሻው የጸና ይድናልና እስከመጨረሻው ጽኑ፡፡ ለመከራ አሳልፈው ሲሰጧችሁ፣ ሲገድሏችሁ፣ ስለ ስሜም የተጠላችሁ ስትሆኑ በእምነታችሁ ጽኑ፡፡ ብዙዎች ሲሰናከሉ፣ እርስ በእርሳቸውም አሳልፈው ሲሰጣጡ፣ ከአመጻም ብዛት የተነሳ ፍቅር ስትቀዘቅዝ በእምነታችሁ ጽኑ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹በጊዜውም ያለጊዜውም ጽና›› ያለው ለዚህ ነው (2ኛ ጢሞ 4፡2)፡፡ በዚህ ወቅት መከራን መታገስ፣ አስፈላጊም ሆኖ ሲገኝ መስዋዕትነትን በመክፈል ጽናትን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ እስከ መጨረሻው በጽድቅ አገልግሎት የሚጸና በጌታ ምጽዓት የክብር ትንሣኤ ይነሳልና፡፡
ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፡፡ ክረምት የቡቃያ እንጂ የፍሬ ዘመን አይደለምና በሃይማኖት ብቻ ሳላችሁ ምግባርን ሳትሠሩ ሞት እንዳይታዘዝባችሁ ጸልዩ፡፡ ሰንበትም ዕለተ ዕረፍት ናትና በዕረፍት ሳላችሁ ሞት እንዳይታዘዝባችሁ ጸልዩ፡፡ በሃይማኖት ሳላችሁ ምግባር ሳይኖራችሁ ብትወሰዱ መጨረሻችሁ መከራ ይሆናልና ጸልዩ፡፡ ክረምትና ሰንበት ለሽሽት አይመችም መንገድና አቅጣጫ የሚያሳይ የለምና፡፡ ሽሽቱም ተራራ ወደተባሉት ወደ ረድኤተ እግዚአብሔር፣ ወደ ቤተክርስቲያንና በምልጃቸው ወደሚረዱን ቅዱሳን ነው፡፡ መንፈሳዊ ምግባራትን መስራት የማንችልበት ጊዜ ሳይመጣ፣ በጉብዝናችን ወራት እምነታችንን አጽንተን፣ ጠብቀን፣ በጎ ምግባራትን ሰርተን ጌታችን ሲገለጥ በምግባራቸው ከሚያመሰግናቸው ቅዱሳን ጋር እንድንቆም ልንተጋ ያስፈልጋል፡፡
የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም እና ለአርዓያነት በተገለጠ ጊዜ አመጣጡ በአጭር ቁመት እና በጠባብ ደረት ተወስኖ በትህትና ነበር፡፡ ዳግመኛ የሚመጣው ግን በግርማ መለኮት በክበበ ትስብዕት ነው፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ብሎ አስተማረን፡፡ ያቺን ቀን ከእርሱ በቀር የሚያወቃት የለም፡፡ በኖኅ ዘመን እንደነበረው የእርሱም መምጣት እንደዚያ ይሆናል፡፡ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ በነቃና ቤቱን በጠበቀ ቤቱም ሊቆፈር ባልተወው ነበር፡፡ ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና፡፡ ይህ ቀን ስለማይታወቅ ሁል ጊዜ በንስሐ እና በሥጋ ወደሙ ተዘጋጅተን ልንኖር ይገባናል፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ የጌታችን ምጽአት የሚዘገይ እንዳልሆነ ሲያስረዳ ‹‹ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል (2ኛ ጴጥ 3፡9)›› ብሏል፡፡
ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በትንቢት “እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመጽእ፤ ወአምላክነሂ ኢያረምም። እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል፤ አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም።” መዝ. 49፡3 እንዳለ ጌታችን በብዙ ክብርና በብዙ ኃይል ከሰማይ መላእክት ጋር ግልጥ ሆኖ ይመጣል። በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል (2ኛ ጴጥ 3፡10)። በዚያን ጊዜ ከመጀመሪያዉ ሰዉ ከአዳም ጀምሮ እስከ መጨረሻዉ ሰዉ ድረስ ሁላችንም በሕይወተ ሥጋ በነበርንበት ጊዜያችን የሠራነዉን ሥራ ይዘን በፊቱ እንቀርባለን (2ቆሮ. 5፡10)። ጌታችንም በጎ የሠሩትን ቅዱሳን በቀኙ፤ ክፉ የሠሩትን ኃጥአንን በግራዉ ያቆማቸዉና ፍርዱን ያስተላልፋል (ማቴ. 25፡31 እስከ ፍጻሜ)። የወጉትም ያዩታል እንደተባለ (ራዕ 1፡7)፣ በዚያን ጊዜ በእርሱ ላይ የፈረዱበት፣ በቅዱሳንም ላይ መከራን ያጸኑ ሞትንም የፈረዱ ሁሉ ለፍርድ ይቀርባሉ፡፡ ሁሉን ትተው የተከተሉት፣ ስለ እርሱ መከራን የተቀበሉ፣ ሞትም የተፈረደባቸው ደግሞ በፍርድ ወንበር ተቀምጠው ይፈርዳሉ (ማቴ 19፡28)፡፡
በየዓመቱ የደብረ ዘይትን በዓል ስናከብር የተለየ አጽንኦት ሰጥተን ማስተዋል ያለብን ጌታችን ዳግመኛ የሚመጣው ለጻድቃን የዘላለም ሕይወትን፣ ለኃጥአን ደግሞ ፍርድን ሊሰጥ መሆኑን ነው፡፡ የመምጣቱና የዓለም መጨረሻ ምልክቶች ሲከሰቱ እንድንጠነቀቅ፣ እንዳንደነግጥ፣ እንድንጸና፣ እንድንጸልይ፣ እንድንጠበቅ፣ እንድናስተውልና እንድንዘጋጅ ራሱ ባለቤቱ መክሮናል፡፡ ከእርሱ ከባለቤቱ በላይ ማድረግ ያለብንን ሊመክረን የሚችል የለም፡፡ አስቀድሞ ለፍቅር በፍቅር የመጣው በመጨረሻው ቀን ለፍርድ ሲመጣ እንዳናፍር፣ ዕድል ፈንታችንም የዘላለም ሕይወት እንዲሆን እነዚህም ምክሮች ልንጠቀምባቸው ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ “ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን፡፡ ስለዚህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፥ የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ (2ኛ ጴጥ 3፡13)።” እንዳለው እነዚህን ምክሮች የሕይወታችን መርህ አድርገን ይህችን ተስፋ ልንጠባበቅ ይገባል፡፡
ዛሬ ትላንት ሳይሆን፣ ነገም ዛሬ ሳይሆን እኛ እያንዳንዳችን ራሳችንን መጠየቅ ያለብን መሠረታዊ ጥያቄ መሆን ያለበት “የእርሱ መምጣት ለእኛስ ምን ይሆን?” የሚለው ነው፡፡ የዘላለም ሕይወት ወይስ የዘላለም ቅጣት? የእርሱ መምጫው የዓለም ፍጻሜ የእኛም መጠሪያችን ቀን ሲቀርብ ምልክቶችም ሲታዩ እነዚህን ምክሮች ልንፈጽም ይገባናል፡፡ እኛ እርስ በእርሳችን መፋቀር ሲጠበቅብን ስንነቃቀፍ፣ ስለፍቅር እየተናገርን ጠብን ስንዘራ፣ የጽድቅ አውድ በሆነው በእግዚአብሔር ቤት እንቶ ፈንቶ ስናወራ፣ ታሪክ እያወራን አንዳች ሳንሠራ፣ ስለ አንድነት እየተናገርን በየደቂቃው ስንለያይ፣ በሐሰተኞች ወሬና በአስማተኞች ተንኮል ስንነዳ፣ ከውጭ ያሉትን ወደ እግዚአብሔር ቤት ማምጣት ሲጠበቅብን ከውስጥ ያሉትን ስናባርር ለንስሐ የተሰጠን ዘመን ሳንጠቀምበት አልቆ ከፊቱ ቀርበን እንዳይፈረድብን ዛሬውኑ ሕይወታችንን በቃሉ እንቃኛት፡፡ ወደ እርሱም እንቅረብ፡፡ እርሱም ሲመጣ ‹‹ኑ የአባቴ ቡሩካን›› እንዲለን በሕይወታችን እነዚህን ምክሮች ገንዘብ እናድርግ፡፡
የሕይወትን ቃል ያሰማልን!
LikeLike