ከቅዱስ ያሬድ በተገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የበዓላት ቀኖና መሰረት የዐቢይ ጾም አራተኛው ሰንበት “መጻጉዕ” ይባላል፡፡ መጻጉዕ ማለት “በሽተኛ” ማለት ነው፡ በዚህ ዕለት ጌታችን በቤተ ስዳ መጻጉዕን ማዳኑን ቤተክርስቲያን ትሰብካለች፡፡ ለ 38 ዓመታት ያህል የፈውስ ተስፈኛ ሆኖ በመጠመቂያው አጠገብ የኖረ መጻጉዕን በአልጋው ተኝቶ ሳለ ደዌው እንደጠናበት ፈውስ እንደዘገየበት አይቶ ‹‹አዎን›› እንደሚለው እያወቀ መጻጉዕን ‹‹ልትድን ትወዳለህን?” አለው። መጻጉዕም ‹‹ሰው የለኝም›› በማለት የመዳን ጉጉቱን ከወዳጅ አልባነቱ ጋር ገለጠ። ጌታም ‹‹ተንስና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው፡፡ ወዲያው አፈፍ ብሎ በፍጥነት ያን ሁሉ ዘመን የተሸከመችውን ጠንካራ አልጋ ተሸክሟት ሄደ (ዮሐ 5፡1-5)።
ጌታችን መጻጉዕን ‹‹ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ›› ያለው ስለ ሁለት ነገር ነው፡፡ አንደኛው ቅዱስ ኤስድሮስ እንዳለው አልጋው ጠንካራ የብረት አልጋ ነበረና ጽንዓ ተአምራቱን ለማሳየት ነው፡፡ ሁለተኛው ‹‹ታዲያ ቢያድነኝ በከንቱ መች ሆነና የገዛ አልጋዬን ትቼለት የመጣሁ ለመዳኔ ዋጋ የከፈልኩበት አይደለምን?›› እንዳይል መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ያለህን ይዘህ ሂድ እኔ ከአንተ አንዳች አልሻም›› ባሰኘ ቃል ‹‹አልጋህን ተሸክመህ ሂድ›› ብሎታል።
ይህ ሰንበት የሕሙማን ፈውስ መታሰቢያ ዕለት ነው። የሰንበቱም ስያሜ በዕለቱ የሚነበቡትን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢርና የጾመ ድጓውን ይትበሀል ተከትሎ የተሰየመ ነው፡፡ በመልእክታቱ የሚነበቡት (ገላ 5፡1 እና ያዕ 5፡14) ስለ ድውያን መፈወስ የሚያወሱ ናቸው፡፡ ከሐዋርያት ሥራ የሚነበውም እንዲሁ (ሐዋ 3፡1)፡፡ የዕለቱ ምስባክ እንዲሁ የድውያንን መፈወስ የሚሰብክ ሲሆን “እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ላይ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ ከበሽታው የተነሳ ይለውጥለታል፡፡ እኔስ “አቤቱ ይቅር በለኝ፤ አንተን በድያለሁና ለነፍሴ አስተስርይላት” አልሁ፡፡” ይላል (መዝ 40:3)
ጌታችን መጻጉዕን የፈወሰባት ቦታ ቤተ ሳይዳ ሳትሆን ቤተ ስዳ ናት፡፡
ቤተ ስዳ (Bethesda) በይሁዳ ግዛት ከሚገኙና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራቱን ከፈጸመባቸው ሥፍራዎች አንዷ ናት፡፡ ቤተ ሳይዳ (Bethesaida) ደግሞ በገሊላ አውራጃ የምትገኝ ከተማ ነበረች፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በይሁዳ ኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ ያለችዋን ቤተ ስዳን ‹‹በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ስዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። (ዮሐ 5፥2)›› ብሎ ሲገልጻት በገሊላ የምትገኘዋን ቤተ ሳይዳን ደግሞ ‹‹እነርሱም ከገሊላ ቤተ ሳይዳ ወደሚሆን ወደ ፊልጶስ መጥተው ጌታ ሆይ፥ ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን ብለው ለመኑት(ዮሐ 12፥21)›› ብሎ ገልጿታል፡፡
ቤተ ስዳና ቤተ ሳይዳ የተለያዩ ቦታዎች ከመሆናቸው በተጨማሪ የስማቸውም ትርጉምም እንዲሁ የተለያየ ነው፡፡ ቤተ ስዳ ማለት ‹‹ቤተ ሣህል (የጸጋ/የምህረት ቤት)›› ማለት ሲሆን፣ በግሪኩ ቤተ ዛታ ወይም ቅልንብትራ ትባላለች፡፡ ቤተ ስዳ ባለ አምስት በር መመላለሻ አምስት ዓይነት ድውያን ፈውስን ከመጠመቂያው ውኃ ሲጠባበቁ የሚኖሩባት የጌታችን ማዳን የተገለጠባት ሥፍራ ናት። የእግዚአብሔር መልአክ ውኃውን ሲባርክ/ሲያናውጥ ቀድሞ የገባ የሚነጻባት በዕለቱ ከአንድ በቀር ለሌላው ፈውስ የማይደገምባት ቦታ ነበረች። ለዚህም ነው ይህች ስፍራ መጠመቂያና መመላለሻ ያላት በመሆኗ የምህረት ቤት የተባለቸው፡፡ እንደስሟ ትርጓሜ ‹‹ቤተ ስዳ›› የተባለችበትም ምክንያት የሰሎሞን ቤተ መቅደስ አጠገቧ የሚገኝ ሲሆን ለቤተመቅደሱ መስዋእት የሚሆኑ በጎች ሁሉ በዚህ መጠመቂያ ሳይጠመቁ ወደ መስዋእቱ መሰዊያ ቦታ አይቀርቡ ስለነበረ ነው (ዘሌ 9፡2)። ጌታችን በቤተ ስዳ መዳንን ይጠባበቅ የነበረውን መጻጉዕን ፈውሷል፡፡
በቤተ ስዳ መጠመቂያ ይፈጸም የነበረው ድኅነት ምሳሌው እንዲህ ነው፡፡ ውኃውን ያናውጥ (ይባርክ) የነበረው መልአክ የቀሳውስት ምሳሌ፣ ውኃው የጥምቀት ምሳሌ፣ አምስቱ መመላለሻ (እርከን) የአምስቱ አዕማደ ምስጢር፣ የአምስቱ ድውያንና የአምስቱ ፆታ ምዕመናን ምሳሌ ናቸው፡፡ ቤተ ስዳ በዕለተ ቀዳሚት የሚፈወሰው አንድ ሰው ብቻ ነበር፡፡ አንድ ብቻ መሆኑ አለመቅረቱን ሲያሳይ አለመደገሙ ደግሞ ፍጹም እንዳልነበረ ያሳያል፡፡
በአንጻሩ ቤተ ሳይዳ ማለት ደግሞ “የማጥመጃ ቤት” ወይም ‹‹የዓሳ ቤት›› የሚል ትርጉም ያላትና በተለይ ከሐዋርያቱ አሳ አጥማጆቹ ወንድማማቾች እና ቅዱስ ፊልጶስ የነበሩባት መንደር ነበረች (ዮሐ·1፡45)። ይህች ከተማ ‹‹የዓሳ ቤት›› የተባለችውም ከገሊላ ባህር ዳር የምትገኝ ስለሆነችና ዓሳ የሚያሰግሩ ሰዎች የሚነግዱባት ስለሆነበረች ነው። በዚህ በሞቀ ንግዷ የተነሳ ከተማዋ የተሰበከላትን ወንጌል ለመስማት ባለመቻሏ ጌታችን በተናገረው ትንቢት መሰረት ከሌላዋ ከተማ ከኮራዚን ጋር አብረው ጠፍተዋል (ማቴ 11፣21)፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ሳይዳም ድውያንን ፈውሷል (ማር 8፡22-25)፡፡
መጻጉዕ ግን ያዳነውን ረሳ፤ በሐሰትም መሰከረበት፤ ወደቀደመ “ደዌውም” ተመለሰ፡፡
መጻጉዕ ቀድሞ በቤተ ስዳ እያለ የነበረበትን ያንን ሁሉ ጭንቅ ኋላ በሊቶስጥሮስ አደባባይ ሲቆም ረሳው፡፡ ይህ ምስኪን መጻጒዕ “ሰው የለኝም” ብሎ የደረሰለትን ሰው ረሳ፡፡ ያዳነው ማን እንደሆነ ሲጠየቅ እንኳ አላወቀም። ወንጌላዊውም ‹‹የዳነው ያዳነውን አላወቀውም›› ( ዮሐ.5፥13) ይለዋል። በምኩራብ አግኝቶት ያዳነውን እንዳወቀውም ሄዶ ለአይሁድ ያዳነኝ እርሱ “ጌታ ኢየሱስ ነው” ብሎ ነገራቸው፡፡
ጌታችን መጻጉን ‹‹ልትድን ትወዳለህን›› ያለው አስፈቅዶ ለማዳን እንዲሁም በዕለተ ዓርብ ‹‹አድነኝ ሳልለው አድኖኝ›› እንዳይል ሲሆን መጻጉዕ ግን ‹‹ሰው የለኝም›› ያለው ያድነኛል ብሎ ሳይሆን ‹‹ወደ መጠመቂያው ያደርሰኛል›› ወይም ‹‹ከሚከተሉት አንዱን አዝዞ ወደ መጠመቂያው እንዲያደርሰኝ ያደርጋል›› ብሎ ነበር፡፡
አንድ ሊቅ ይህን ‹‹ታሞ የተነሳ ፈጣውን ረሳ›› የተባለለት መጻጒዕ እና በሐሰት የተከሰሰውን ይቅር ባይ አምላኩን እያደነቀ በጉባዔ ቃናው እንዲህ ተቀኘ፡፡ ” ይትዐረቅ ምስለ ብእሲት ደዌሁ፤ ሠላሳ አዝማነ እስመ ነበረት ምስሌሁ” (ትርጉም፡ መጻጒዕ ከሚስቱ ከደዌ ጋር ይታረቅ ፤ ሠላሳ ዓመታት ከእርሱ ጋር ኑራለችና)፡፡ ለብዙ ዓመታት አብረው የኖሩ ባልና ሚስት ሲፋቱ ከናፍቆት የተነሳ መለያየቱ እንደሚከብዳቸውና ተመልሰው እንደሚታረቁ ሁሉ ‹‹ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ አትበድል›› ተብሎ ከጌታ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው መጻጉዕም ያዳነውን ጌታ በጥፊ መትቶ ዳግመኛ ወደ 38 ዓመት “የአልጋ ወዳጁ” ደዌ ተመልሶ ከእርስዋም ጋር መታረቁን የቅኔው ምስጢር ያስተምረናል። ጌትችን ከደዌው ነጻ አወጣው፤ እርሱ ግን ከደዌው ተለያይቶ መኖር ከብዶት ተመልሶ ታረቃት፡፡ኋላም በአውደ ምኩናን የሐሰት ክስ የቀረበበትን ጌታችንንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቀድሞ ወደ መጠመቂያው እንኳ ለመቅረብ አቅም ያልነበረው ዛሬ ግን አልጋ ለመሸከም በበቃውና ያለ ተረፈ ደዌ በጸናው ኃይሉ የጌታውን ጉንጮች በጥፊ የመምታት ጉልበትና ድፍረት አገኘ ። አምላከ ምሕረት የክብር ጌታ ቀድሞ ‹‹ከዚህ የጠናው” ስለ ደዌ ሥጋ ፈንታ ደዌ ነፍስ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል” (ዮሐ 5፡14) ያለውን ዘንግቶ ደዌ ዘኃጢአትን ጠርቶ ተወዳጃት፤ በዕለተ ዓርብ የጌታውን ጉንጮች የጸፉች እጁም ደርቃ ቀርታለች፡፡
የዐቢይ ጾም አራተኛው ሰንበት እኛም የታመሙትን መጎብኘት እንዳለብን የምንማርበት ነው፡፡
ይህ ሳምንት “መጻጉዕ” ጌታችን ድውያንን ስለመፈወሱ የሚነገርበትና እኛም ባለን አቅም በነፍስ በሥጋ የተቸገሩትን ሁሉ መርዳትና ማገዝ እንዳለብን የምንማርበት ሳምንት ነው፡፡ ሕሙማንን መጠየቅ፣ የታሰሩትን መጎብኘትና ማስፈታት፣ የተራቡትን ማብላት፣ የተጠሙትን ማጠጣት፣ የታረዙትን ማልበስ ያዘኑትን ማረጋጋት ከጌታችን የተማርናቸው ክርስቲያናዊ ምግባራት ናቸው፡፡ ይህንን በማስተዋል የሚያስፈልገንን ሁሉ የሰጠንንና ከክፉ ነገር የጠበቀንን አምላክ ውለታውን እያሰብን ልናመሰግነው ይገባል፡፡ መጻጒዕ መጀመሪያ የነበረበት ደዌ ሥጋ ነበር፣ ይህንንም ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አራቀለት/አዳነው፡፡ ይሁንና በጌታችን ስቅለት ከአይሁድ ጋር በመተባበሩ፣ ያዳነውን ባለማመኑ ግን ደዌ ነፍስ አገኘው፡፡ እኛም እንደ መጻጒዕ ደዌ ነፍስ እንዳያገኘን ያዳነንን አምላካችንን ልናውቀው፣ ልናምነው፣ በህጉና በትዕዛዙም ልንሄድ ያስፈልጋል፡፡ ያን ጊዜ ከደዌ ነፍስ እንድናለን፡፡ ያንን ተስፋ ያልነበረውን በሽተኛ ከደዌ ሥጋው ፈውሶ ሕይወትን የሰጠው አምላክ፣ እኛንም በውስጥ በአፍአ ካለብን ደዌ ሥጋና ደዌ ነፍስ እንዲፈውሰን፤ ቁስለ ኃጢአታችንን እንዲያደርቅልን፣ በሕይወትና በጤና እንዲጠብቀን የእርሱ የጌታችን ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡