ስቅለት፡ ሕይወትን የሠራውን ከበደለኞች ጋር ሰቀሉት!

seklet

ሰሙነ ሕማማት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  የሰውን ልጅ ከዲያብሎስ ባርነት ነፃ ለማውጣት በፈቃዱ የተቀበላቸው ጸዋትወ መከራዎች የሚታሰቡበት ሳምንት ነው፡፡ የሰሙነ ሕማማት ዕለታት የዓመተ ኩነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች ክርስቶስ የዋለልንን ውለታ እያሰብን እጅግ የምናዝንበት፣ የምናለቅስበት፣ የምንሰግድበት ከሌሎች ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ አምላካችንን የምንማጸንበት፤ ጧት ማታ ደጅ የምንጠናበት፤ የክርስቶስን ተስፋ ትንሣኤ ከመቼውም ጊዜ በላይ በእምነትና በተስፋ የምንጠብቅበት  በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ልዩ ተምሣሌታዊ ምስጢራትና አዘክሮ የሚፈጸምበት ሳምንት ነው፡፡ በዚህ  ሳምንት ያሉ እያንዳንዳቸው ቀናት ስያሜና ከስያሜው ጋር የተያያዘ ምስጢር አላቸው፡፡ ይህም፡-

  1. ሰኞ: አንጽሆተ ቤተመቅደስ፣ መርገመ በለስ
  2. ማክሰኞ:  የጥያቄ ቀን፣ የትምህርት ቀን
  3. ረቡዕ:    የምክር ቀን፣መልካም መዓዛ ያለው ቀን፣ የእንባ ቀን
  4. ሐሙስ:   ጸሎተ ሐሙስ፣ ሕፅበተ ሐሙስ፣ የምስጢር_ቀን፣ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ፣ የነፃነት ሐሙስ
  5. ዓርብ:    የስቅለት ዓርብ፤ የድኅነት ቀን፣ መልካም ዓርብ
  6. ቅዳሜ:    ቅዳም ሥዑር፣ ለምለም ቅዳሜ፣ ቅዱስ ቅዳሜ

ከእነዚህ ሁሉ ግን ዓርብ የስቅለት (crucifixion) ቀን እጅግ ልዩ ናት፡፡ የስቅለት ዕለት የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ “የድኅነት ቀን” ወይም ‹‹መልካም ዓርብ›› ይባላል፡፡ ጌታችን ከተያዘባት ሰዓት አንሥቶ አይሁድ ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አደሩ፡፡ ሲነጋ ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ አደባባይ አስረው ወሰዱት (ማቴ. 27፥1-57)፡፡ ይህን አጥፍቶአል የሚሉት ነገር ሳይኖራቸው ጌታችንን ለፍርድ ያቀረቡት አይሁድ ጲላጦስ እነርሱ ወደ ተሰባሰቡበት ቦታ ወጥቶ ‹‹ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁበት በደል ምንድን ነው?›› ሲል በጠየቃቸው ጊዜ በቂ ምላሽ አላቀረቡም፡፡

በግብረ ሕማማት‹‹የማይሞት መለኮት ስለ እኛ የሞትን ጽዋ ተቀብሎ በሰውነቱ ሞተ! ወዮ ለዚህ አንክሮ ይገባል፡፡›› እንደተባለ ስለኛ በፈቃዱ ይሞት ዘንድ ፈቃዱ ነበርና በአይሁድ ጭካኔ ምክንያትነት ሞት ተፈረደበት፡፡ ይህ የስቅለት ዕለት ሙሉ ምስጢሩና ሥርዓቱ በግብረ ሕማማቱ በስፋትና በጥልቀት እንደሰፈረው ነው፡፡ በዚህች አጭር ጽሑፍ የተወሰኑ ነጥቦችን ለማንሳት ያህል ይህ የስቅለት ቀን የሚከተሉት የተከናወኑበት ነው፡፡

ፍኖተ መስቀልጌታችን 15ቱን ምዕራፎች መከራ እየተቀበለ የተጓዘበት ነው፡፡

ጌታ በጲላጦስ ፊት ከቆመበት ቦታ ጀምሮ እስከ መካነ ትንሣኤው ድረስ በዕለተ ዓርብ የሆነው ዐሥራ አምስት የመከራ መስቀል መንገድ ምዕራፎች (ፍኖተ መስቀል) አሉ፡፡ እነዚህም የጲላጦስ ዐደባባይ (ለፍርድ የቆመበት)፣ የተገረፈበት፣ በመጀመሪያ የወደቀበት ቦታ፣ እመቤታችን እያለቀሰች ልጇን ያገኘችበት ቦታ፣ ቀሬናዊ ስምዖን የጌታን መስቀል የተሸከመበት ቦታ፣  ቤሮና /ስራጵታ/ በመሐረብ የጌታን ፊት የጠረገችበት ቦታ፣ የጎልጎታ መቃረቢያ፣ የጌታችንን ሥቃይ ሴቶች አይተው ያለቀሱበት ቦታ፣ መስቀል ይዞ የወደቀበት፣ ልብሱን የገፈፉበት፣ጌታን የቸነከሩበት፣ የተሰቀለበት ቦታ፣ ቅዱስ ሥጋውን ያወረዱበት ቦታ፣ ቅዱስ ሥጋውን የገነዙበት ቦታ፣ ቅዱስ ሥጋው የተቀበረበት ቦታ ናቸው፡፡ እነዚህም ምዕራፎች የጌታችንን መከራና የማዳኑን ሥራ ሲያሳስቡን ይኖራሉ፡፡

ሕማማተ መስቀልጌታችን 13ቱን ሕማማተ መስቀል የተቀበለበት ዕለት ነው፡፡

ዕለተ ዓርብ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መተላለፋችን የቆሰለበት፣ ስለ በደላችንም የደቀቀበት፣ ስለ ሁላችን ኃጢአት ራሱን መስዋዕት ያደረገበት፤ በእርሱም ቁስል እኛ የተፈወስንበት፤ በሞቱም የሞት ስልጣን የተሻረበት ዕለት ነው፡፡ የሕይወት ባለቤት፣ የሕያዋን ሁሉ አምላክ በፈቃዱ በሥጋ ሞቷልና የሞትን ስልጣን አጠፋልን፡፡ ይህ ዕለት አስራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል የተቀበለበት፣ እኛም እነዚህን እያሰብን የምንሰግድበት፣ በተደረገልን ቤዛነት እየተደነቅን ፍቅራችንን አምልኮታችንን የምንገልጥበት ዕለት ነው፡፡ የበረቱ ቅዱሳን ሙሉ ሕይወታቸውን፣ ትዳራቸውን ደስታቸውን ትተው ዕለት ዕለት የሚያስቡትን መከራ መስቀል፣ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችንም በየዕለቱ የምታስበውን፣ የምታዘክረውን መከራ መስቀል እኛ ደካሞች ደግሞ ቢያንስ ለአንድ ሣምንት በልዩ ሁኔታ የምናስብበት ልዩ ወቅት ነው፡፡ በዚህ ልዩ ወቅት ስለበደላችን እያነባን መድኃኒት የሆነንን የክርስቶስን 13ቱን ሕማማተ መስቀል እናስባለን፡፡ እነዚህም 13ቱ ሕማማተ መስቀል የሚባሉት፡ አስሮተ ድኅሪት (ወደኋላ መታሰር)፣ ተስሕቦ በሐብል (በገመድ መሳብ)፣ ወዲቅ ውስተ ምድር (በምድር ላይ መውደቅ)፣ ተከይዶ በእግረ አይሁድ (በእግረ አይሁድ መረገጥ)፣ ተገፍዖ ማዕከለ ዓምድ (ከምሶሶ ጋር መላተም)፣ ተጽፍዖ መልታሕት (በጥፊ መመታት)፣ ተቀሰፎ ዘባን (ጀርባን በጅራፍ መገረፍ)፣ ተኰርዖተ ርእስ (ራስን በዱላ መመታት)፣ አክሊለ ሦክ (የሾህ አክሊል መድፋት)፣ ፀዊረ መስቀል (መስቀል መሸከም)፣ ተቀንዎ በቅንዎት (ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ ሮዳስና አዴራ በተባሉት ችንካሮች መቸንከር)፣ ተሰቅሎ በዕፅ (በመስቀል ላይ መሰቀል) እና ሰትየ ሐሞት (መራራ ሐሞትን መጠጣት) ናቸው፡፡ በስቅለት ዕለት ለእኛ ሲል እነዚህን ሕማማተ መስቀል መቀበሉን እያሰብን የአምልኮ ስግደት እንሰግድለታለን፡፡

አጽርሐ መስቀልጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ ሰባቱን አጽርሐ መስቀል የተናገረበት ነው፡፡

ይህ ዕለት ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ ሰባቱን አጽርሐ መስቀል (የፍቅር ቃላት) የተናገረበት ዕለት ነው፡፡ እነዚህም ቃላት በየራሳቸው ጥልቅ ምስጢር ያላቸው ሲሆኑ የማዳኑ ሥራም አካል ናቸው፡፡ ሰባቱ ቃላትም:  ኤሎሄ ኤሎሄ ኤልማስላማ ሰበቅታኒ/አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ (ማቴ.27፤46)፣ አማን ዕብለከ እሙን ፈድፋደ ከመ ዮም ትሄሉ ምስሌየ ውስተ ገነት (እውነት እውነት እልሃለሁ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ)(ሉቃ.23፤43)፣ አባ አማሐፅን ነፍስየ ውስተ እዴከ (አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ) (ሉቃ.23፤46)፣ አባ ሥረይ ሎሙ እስመ በዘኢየአምሩ ይገብሩ (አባት ሆይየሚያደርጉትን አየውቁምና ይቅር በላቸው) (ሉቃ.2334)፣ ነዋ ወልድኪ ወነያ እምከ (እናትህ እነኋት፤ እነሆ ልጅሽ) (ዮሐ.19፤26-27)፣ ጸማዕኩ (ተጠማሁ) (ዮሐ.19፤30) እና ተፈጸመ ኩሉ (ተፈጸመ) (ዮሐ.19፤30) የሚሉት ናቸው፡፡ እነዚህን ሰባቱን በመስቀል ላይ ሆኖ ተናግሮ እራሱን ወደቀኝ ዘንበል አድርጎ ነፍሱን ከሥጋው በገዛ ሥላጣኑ ለየ፡፡ በስቅለት ዕለት እነዚህ በንባብና በዜማ እያልን እንሰግድለታለን፡፡

የስቅለት ተአምራትበሰማይና በምድር ሰባት ተአምራት የተከናወኑበት ነው፡፡

በዕለተ ዓርብ በሰማይ ሦስት ተአምራት ተከናውነዋል፡፡ እነዚህም የፀሐይ መጨለም፣ የጨረቃ ደም መልበስ፣ የክዋክብት መርገፍ ናቸው፡፡ ይህም የሆነው በመስቀል ላይ ያለውን የአምላካቸውን እርቃን ላለማሳየት ነው፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ይህንን ‹‹ፀሐይ ፀልመ ወወርኅ ደመ ኮነ ወክዋክብት ወድቁ ፍጡነ ከመ አይርአዩ ዕርቃኖ ለዘአልበሶሙ ብርሃነ›› ሲል ገልጾታል፡፡ እንዲሁም በምድር አራት ተአምራት ታይተዋል፡፡ እነዚህም የቤተ መቅደስ መጋረጃ መቀደድ፣ የዐለቶች መሰንጠቅ፣ የመቃብሮች መከፈት፣ የሙታን በአጸደ ሥጋ መነሳት ናቸው (ማቴ.27፤45-46)፡፡ እነዚህ ተአምራት በመስቀል ላይ የተሰቀለው ወልደ እግዚአብሔር መሆኑን ለሰው ልጆች ያረጋገጡ ምልክቶች ነበሩ፡፡ እነዚህን ተዓምራት አይተው በጌታችን ያመኑ ነበሩ፡፡ ከሰቃዮቹ ወገን የሆኑት እንኳ በትህትናው፣ በተዓምራቱ ተማርከው አምነው ምስክሮቹ (ሰማዕታት) ሆነዋል፡፡

ዕርቀ ሰላምሰባቱ መስተፃርራን (ጠበኞች) የታረቁበት ዕለት ነው፡፡

በዚህ ዕለት ሰባት መስተፃርራን (ጠበኞች) ታረቁ፤ ተስማሙ፡፡ እነዚህም፡- ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሕዝብና አሕዛብ፣ ነፍስና ሥጋ ናቸው (ኤፌ. 2፥10 ቈላ. 1፥20)፡፡ የስቅለት ቀን የገነት በር የተከፈተበት በአንጻሩ ደግሞ ሲኦል የተበረበረበችበት ነው፡፡ በአዳም በደል ምክንያት አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ተዘግታ የነበረችው ገነት የተከፈተችበት፣ በአንጻሩ ደግሞ ሰልጥና የነበረችው ሲኦል የተበረበረችበት፣ ነፍሳት ከሲኦል ወጥተው ወደ ገነት የገቡበት ነው፡፡ የስቅለት ዕለት የገነት መዘጋት ያበቃበት፣ የሲኦልም መሰልጠን ያከተመበት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ «ጥልን በመስቀሉ ገደለ» ሲል የገለጸው (ኤፌ. 2፥16) በእነዚህ መካከል የነበረው ጥል ማብቃቱንና ፍጹም ሰላም መስፈኑን ያሳያል፡፡

የሰው ልጅ ድኅነትየሰው ልጅ ከዲያብሎስ እሥራት የተፈታበት ዕለት ነው፡፡

የስቅለት ዓርብ የሰው ልጆች በዘር ኃጢአት /ቁራኝነት/ ይኖሩበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመበት ፍጹም ድኅነት ያገኙባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ የስቅለት ዓርብ የሲኦል አበጋዝ ዲያብሎስ በንፋስ አውታር የታሠረበትና ስልጣኑ የተሻረበት፣ በአንጻሩ ደግሞ ታስሮ የነበረው አዳም የተፈታበትና ወደ ገነት የተመለሰበት ናት፡፡ በመጀመሪያ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲፈረድበት ወንጀለኛ የነበረው በርባን ተፈታ፡፡ ጌታችን በሥጋው ሲሞት ደግሞ አዳምና ልጆቹ በሙሉ ተፈቱ፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ “በምድር ላይ ኃጢአትን አሳፈረ፤ መርገምን በመስቀል ላይ ሻረ፤ ሞተ ነፍስን በሲዖል አጠፋ፤ ፈርሶ በስብሶ መቅረትን በመቃብር አፈራረሰ” እንዳለ፡፡ እንዲሁም ቅዱስ ጴጥሮስ “ሞተ በሥጋ ወሐይወ በመንፈስ ወወረደ ኀበ እለ ሙቅሕታ ትነብር ነፍሶሙ ወሰበከ ሎሙ ግዕዛነ” በሥጋ ሞተ በመንፈስ /በመለኮት/ ግን ሕያው ነው እርሱም ደግሞ ሄደ በወህኒ /በሲዖል/ ለነበሩ ነፍሳት ነጻነትን ሰበከላቸው” (1ጴጥ.3፡18) እንዳለው ጌታችን በሲኦል እስራት የነበሩትን ነፍሳት ነፃ አወጣቸው፡፡

የመስቀል ስጦታዎችየምንጠመቅበት ማየ ገቦ፣ የምንድንበት ሥጋውና ደሙን እንዲሁም የምታማልድ እናት የተሰጠንበት ነው፡፡

በዘጠኝ ሰዓት ጌታችን በውኃው ተጠምቀን፣ ደሙን ተቀብለን የእግዚአብሔር ልጆች እንኾን ዘንድ ከቀኝ ጎድኑ ጥሩ ውኃ፣ ትኩስ ደም አፈሰሰልን (ዮሐ. 19፥34)፡፡ ዕለተ ዓርብ ተጠምቀን ድኅነት የምናገኝበት ውኃ ከጎኑ የፈሰሰበት፣ የዘላለም ሕይወት የምናገኝበት ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን ያገኘንበት ዕለት ነው፡፡ ‹‹ በነገው ዕለት ስለ ዓለም የሚቆረሰው ሥጋዬ የሚፈሰው ደሜ ይህ ነው›› እንዳለ (ማቴ 27፡27)፡፡ ቤተክርስቲያንም የተዋጀችው በዚሁ በዕለተ ዓርብ በፈሰሰው ደሙ ነው፡፡ በዚህ ዕለት አርማችን መስቀሉ፣ ማኅተማችን ደሙ፣ ሕይወታችን እርሱ ሆነዋል፡፡ ሥጋውንና ደሙን በመስቀሉ ላይ አግኝተናል፡፡ ከመስቀሉ ሥር ድንግል ማርያም በዮሐንስ አማካኝነት እናት እንድትሆነን፣ እኛም ልጅ እንድንሆን የተሰጠንበት ቀን ነው፡፡ እናቱ እናት እንድትሆነን በይፋ የተሰጠንበት ቀን ነው፡፡ ‹‹እነኋት እናትህ፤ እነሆ ልጅሽ›› (ዮሐ 19፡36) ብሎ ሰጠን፡፡ ርህርህት እናት ከመሰቀል ሥር በዕለተ ዓርብ አግኝተናል፡፡

በአጠቃላይ የስቅለት ዓርብ ጌታችን የቤዛነቱን ሥራ የፈጸመበት ነው፡፡ በቤተልሔም የተጀመረው የሰውን ልጅ የማዳኑ ሥራ የተጠናቀቀበት፣ ጌታም ስለ ሰው ልጆች ፍቅር ሲል በቀራኒዮ አደባባይ ራሱን አሳልፎ በመስጠት የቤዛነቱን ሥራ የሠራበት ዕለት ነው፡፡ ዕለተ ዓርብ “እግዚአብሔር አንድያ ልጁን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና” የተባለው የተፈጸመበት ነው፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን በመስቀል ላይ ‹‹ተፈጸመ›› ያለው (ዮሐ 19፡30)፡፡ እኛም በዚህ ታላቅ ዕለት ጌታችን ስለ እኛ የተቀበለውን መከራ እያሰብን፣ ስለ ኃጢአታችንም እያዘንንና እያለቀስን፣ ስለ ማዳኑም ሥራ ምስጋናን እያቀረብን ስንሰግድ እንውላለን፡፡ እንደ ፈያታዊ ዘየማን ‹‹አቤቱ በመንግስትህ በመጣህ ጊዜ አስበን›› እያልን እንማፀናለን፡፡ እርሱም ዳግመኛ በመጣ ጊዜ እንዲያስበን የጾማችንን ፍጻሜ በቅዱስ ሥጋው በክቡር ደሙ ማኅተምነት ማተም ይኖርብናል፡፡ ለዚህም የእርሱ ቸርነት የቅድስት ድንግል እመቤታችን አማላጅነት አይለየን፡፡ አሜን፡፡

 

1 thought on “ስቅለት፡ ሕይወትን የሠራውን ከበደለኞች ጋር ሰቀሉት!

  1. በእውነት ኢንተርኔት ከፍቼ አላስፈላጊ ነገሮችን ከማንበብ አውጥቶኛል፡፡
    ቃለ ህይወት ያሰማልን፡፡
    ወቅታዊ ነገሮችን ከስር ከስር ስቀሉልን፡፡ በተረፈ መድኀኔዓለም ያበርታችሁ!!!

    Like

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s