«ዮም ፍሥሐ ኮነ በሰንበተ ክርስቲያን፤ እስመ ተንሥአ ክርስቶስ እሙታን»
በኦርቶዶካሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በታላቅ ድምቀት ከሚከበሩት ዐበይት በዓላት መካከል የትንሣኤ በዓል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ትንሣኤ (resurrection) የሚለው ቃል ‹‹ተንሥአ›› ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተወረሰ ሲሆን ትርጉሙም ‹‹መነሣት፣ አነሣሥ›› ማለት ነው። እስራኤል ዘሥጋ ያከብሩት የነበረው የፋሲካ (የመሻገሪያ) በዓል ከግብፅ ባርነት ቀንበር ወደ ነጻነት ምድር የተላለፉበት ከኀዘን ወደ ደስታ የተሸጋገሩበት በዓል ነበር። በሐዲስ ኪዳን የሚከበረው የክርስቶስ ትንሣኤ ግን እስራኤል ዘነፍስ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከሐሳር ወደ ክብር፣ ከጠላት ሰይጣን አገዛዝ ወደ ዘለዓለማዊ ነፃነት፣ ከአሮጌው ኪዳን ወደ አዲሱ ኪዳን፣ ከአደፈ፣ ከጐሰቆለ አሮጌ ሕይወት ወደ ሐዲስ ሕይወት የተሸጋገርንበት መንፈሳዊ የነጻነት በዓላችን ነው። «ትንሣኤ» ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በየመልኩ፣ በየዐይነቱ ሲያመሰጥሩት አምስት አይነት ትርጉም አለው፡፡ እነዚህም፡-
- ትንሣኤ ኅሊና፡ ተዘክሮተ እግዚአብሔር (እግዚአብሔርን ማሰብ)
- ትንሣኤ ልቡና፡ ቃለ እግዘብሔርን መስማትና በንስሐ እየታደሱ በሕይወት መኖር
- ትንሣኤ ሙታን፡ ለጊዜው የሙታን በሥጋ (በተአምራት) መነሣት ሲሆን ነገር ግን ድጋሚ ሞት ይከተለዋል
- ትንሣኤ ዘክርስቶስ፡ የክርስቶስ በገዛ የባሕርይ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣት
- ትንሣኤ ዘጉባኤ፡ ከዓለም ኅልፈት በኋላ ሰው ዅሉ እንደየሥራው ለጽድቅና ለኵነኔ በአንድነት የሚነሣው የዘለዓለም ትንሣኤ
ትንሣኤ ዘክርስቶስን በተመለከተ ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሞቱ ድል ነስቶ፣ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ በሥልጣኑ ከሞት የተነሣው መጋቢት 29 ቀን በ34 ዓ.ም እንደሆነ የቤተከርስቲያን ታሪክ ያስረዳል፡፡ የጌታችን ትንሣኤ አስቀድሞ በነቢያት ትንቢት የተነገረለትና ምሳሌም የተመሰለለት፣ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌውም ያስተማረለት፣ መላእክት ያበሰሩት፣ ሰዎችም መቃብሩን አይተው ያረጋገጡት፣ እርሱም ተገልጦ መነሳቱን ያረጋገጠበት ነው፡፡ በዚህች የአስተምህሮ አጭር ጽሑፍም እነዚህን የትንሣኤውን ምስጢር የሚገልጡ ክፍሎችን እንዳስሳለን፡፡
አስቀድሞ ስለትንሣኤው በትንቢት ተነገረ
ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት «ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተዋትም» ያለው የትንሳኤውን ምሥጢር በትንቢት ቃል ሲናገር ነው (መዝ 15፡10)፡፡ እንዲሁም ‹‹ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃህ እምንዋም። ወከመ ኃያል ኅዳገ ወይን። ወቀተሎ ፀሮ በድኅሬሁ።/እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፤ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው፤ ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ፤» ያለው የጌታን ትንሣኤ ያመለክታል (መዝ 77፡65)። ነቢዩ ሆሴዕም «ኑ÷ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና፤ እርሱም ይፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናል፤ እርሱም ይጠግነናል፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፤ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል (ሆሴ 6፡12)» ሲል የትንሣኤውን ምስጢር በትንቢት ተናግሯል፡፡ ነቢዩ ዮናስ በብሉይ ኪዳን የትንሣኤው ምሳሌ ነበር፡፡ ‹‹ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደነበረ እንዲሁ የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ) በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል፡፡» ብሎ ጌታችን ያስተማረውም ለዚህ ነው (ማቴ 12፡38-40)።
ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱም ስለትንሣኤው አስተማረ
ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ስለትንሳኤው ብዙ ጊዜ ለደቀመዛሙርቱና ለሕዝቡ እንዲሁም ለፈሪሳዊያን ጭምር አስተምሯቸዋል፡፡ ‹‹እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፥ ሊዘባበቱበትም ሊገርፉትም ሊሰቅሉትም ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል (ማቴ 20፡18-19)›› በማለት ስለትንሳኤው ተናግሯል፡፡ እንዲሁም ከሽማግሌዎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀመዛሙርቱ በግልጥ ነግሯቸዋል (ማቴ 16፡21)፡፡
በገሊላም ሲመላለሱ «ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው፤ ይገድሉትማል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፤» ብሏቸዋል (ማቴ 17፡20)፡፡ «ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና፤ ስለዚህ አብ ይወደኛል፡፡ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፡፡ ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ፡፡» በማለት አስቀድሞ ተናግሮታል (ዮሐ 10፡17)፡፡ ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅም “በሦስተኛውም ቀን ነፍሱን ከሥጋው ጋር አዋሐዳት” ያለው በገዛ ስልጣኑ መነሳቱን ሲገልጽ ነው፡፡የትንሳኤው በኩርና የሰውን ልጅም የሚያስነሳ እርሱ መሆኑን ሲናገርም ‹‹ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም (ዮሐ 11፡25-26) በማለት አረጋግጦልናል፡፡
ትንሣኤውን ቅዱሳን መላእክት ለሴቶች አበሰሩ
ልደቱ ለእረኞች በመልአክ እንደተበሰረ ትንሣኤውም በመልአክ ለሴቶች ተበሰረ፡፡ ይህም ‹‹ተነስቷል፤ በዚህም የለም›› የሚለው የመላእክት ብስራት በአራቱም ወንጌላት እንደሚከተለው ሰፍሯል፡፡
ቅዱስ ማቴዎስ፡ ‹‹መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው። እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። ፈጥናችሁም ሂዱና። ከሙታን ተነሣ፥ እነሆም፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው። እነሆም፥ ነገርኋችሁ።›› በማለት ገልጾታል (ማቴ 28፡5-10)፡፡
ቅዱስ ማርቆስ፡ ‹‹ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጎናጸፈ ጎልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ። እርሱ ግን። አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ። ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ለጴጥሮስም። ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ እንደ ነገራችሁ በዚያ ታዩታላችሁ ብላችሁ ንገሩአቸው አላቸው (ማር 16፡5) በማለት አስፍሮታል፡፡
ቅዱስ ሉቃስ፡ ‹‹እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው። ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም። የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደ ተናገረ አስቡ (ሉቃ 24፡4-9) ብሎ መልአኩ እንደነገራቸው አስፍሮልናል።
ቅዱስ ዮሐንስ፡ መግደላዊት ማርያም ሁለቱን መላእክት እንዳየችና ከእነርሱም ጋር እንደተነጋገረች ሲገልጽ ‹‹ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች። እነርሱም። አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? አሉአት (ዮሐ 20፡10-13)›› ብሏል።
ደቀ መዛሙርቱም መቃብሩን አይተው መነሳቱን አረጋገጡ
ሁለቱ ደቀ መዛሙርት የትንሣኤውን ዜና ከሴቶች ከሰሙ በኋላ ወደ መቃብሩ በመግባት የጌታችንን መነሳት አረጋግጠዋል፡፡ ይህንን ወንጌላዊው ዮሐንስ ‹‹ስለዚህ ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና አስቀድሞ ከመቃብሩ ደረሰ፤ ዝቅም ብሎ ቢመለከት የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ነገር ግን አልገባም። ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ደግሞም በራሱ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ። በዚያን ጊዜ አስቀድሞ ወደ መቃብር የመጣውም ሌላው ደቀ መዝሙር ደግሞ ገባ፥ አየም፥ አመነም (ዮሐ 20፡3-8)›› ሲል ገልጾታል፡፡ ቅዱስ ሉቃስም ይህንን የጴጥሮስን ወደ መቃብር ገብቶ የጌታን ትንሳኤ ማረጋገጡን ሲገልጽ ‹‹ጴጥሮስ ግን ተነሥቶ ወደ መቃብር ሮጠ፤ በዚያም ዝቅ ብሎ ሲመለከት የተልባ እግር ልብስን ብቻ አየ፤ በሆነውም ነገር እየተደነቀ ወደ ቤቱ ሄደ (ሉቃ 24፡12)›› ብሏል።
ጌታችን ራሱ ተገልጦ ትንሣኤውን አረጋግጦልናል
ከትንሣኤ በኋላ ጌታችን በተለያየ ጊዜ ተገልጧል፡፡ አስቀድሞ ለማርያም መግደላዊት በመቃብሩ ስፍራ ተልጦላታል፡፡ እርሷም ያየችውን ለደቀ መዛሙርቱ ተናግራለች (ዮሐ 20፡14-17) ፡፡ ወደ ኤማሁስ ይሄዱ ለነበሩት ሁለቱ ደቀመዛሙርትም መንገደኛ መስሎ ተገጦላቸዋል (ሉቃ 24፡13-31)፡፡ አሥራ አንዱና ከእነርሱ ጋር የነበሩትም በተሰበሰቡበት ተገልጦ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይሁን›› ካላቸው በኋላ ከተጠበሰ ዓሣ አንድ ቁራጭ፥ ከማር ወለላም ሰጥተውት፤ ተቀብሎም በፊታቸው በልቷል፤ አስትምሯቸዋልም (ሉቃ 24፡ 42-43)፡፡ በማዕድ ተቀምጠው ሳለም ለአሥራ አንዱ ተገለጧል፤ተነሥቶም ያዩትን የተነገራቸውን ስላላመኑአቸው አለማመናቸውንና የልባቸውን ጥንካሬ እንደነቀፈ ተጽፏል (ማር 16፡14)። ዮሐንስ ወንጌላዊ እንደጻፈው ጌታችን ለደቀመዛሙርቱ ሁለት ጊዜ (የመጀመሪያው ጊዜ ቶማስ በሌለበት) በተዘጋ ቤት ተገልጦላቸዋል (ዮሐ 20፡19-31)፡፡ከዚያም በጥብርያዶስ ባሕር አጠገብ ተገልጦላቸዋል (ዮሐ 21፡1-25)፡፡ እነዚህ ለማሳያነት ቢገለጹም ጌታችን ከትንሣኤ በኋላ እስከ ዕርገቱ ድረስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የተገለጠባቸው ጊዜያቶች ግን እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡
እነዚህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታዎች መሰረት በማድረግ ከዐበይት በዓላት አንዱ የሆነው የትንሣኤ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡ ይህም ከጥንት አበው የነበረውን የአከባበር ሥርዓት የተከተለ ነው፡፡ የትንሣኤ በዓል መከበር የጀመረው በቅዱሳን ሐዋርያትና በሰብዐ አርድእት፣ ኋላም በየጊዜው የተነሡ ምእመናን ማክበር ቀጠሉ፡፡ ድምቀቱና የአከባበር ሥርዐቱ ይበዛ ይቀንስ እንደሆን እንጂ መከበሩ ግን ተቋርጦ አያውቅም፡፡ የትንሣኤ በዓል የሚከበረው ‹‹ዘመነ ትንሣኤ›› የሚባሉትን ከትንሣኤ እሑድ ቀጥለው ያሉትን ሰባቱን ቀናት ጭምር ይዞ ነው፡፡ እነዚህም ዕለታት የየራሳቸው ምስጢራዊ ስያሜ አላቸው፡፡
- ሰኞ፡ ፀአተ ሲኦል ማዕዶት (ጌታችን በሞትና ትንሣኤው ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ ወደ ገነት ለማስገባቱ መታሰቢያ)
- ማክሰኞ፡ ቶማስ (በቶማስ ጥያቄ መሠረት በሳምንቱ ጌታችን በድጋሚ ስለተገለጸ ለዚህ መገለጹ መታሰቢያ)
- ረቡዕ፡ አልዓዛር (ከሞተና ከተቀበረ አራት ቀን በኋላ ከመቃብር ጠርቶ ላሥነሣው፣ አላዓዛር መታሰቢያ)
- ሐሙስ፡ የአዳም ሐሙስ (የአዳም ተስፋው ተፈጽሞለት ከነልጅ ልጆቹ ወደቀደመ የገነት ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ)
- ዓርብ፡ ቤተክርስቲያን (በክርስቶስ ደም ተዋጅታ በተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታላቅ መታሰቢያ)
- ቀዳሚት፡ አንስት (እስከ ቀራንዮ ለተከተሉት፣ በሌሊቱ ወደ መቃብሩ ለገሠገሱት ቅዱሳት አንስት መታሰቢያ)
- እሑድ፡ ዳግም ትንሣኤ (የትንሣኤው ምስጢር ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት) ዮሐ 20፡24
የክርስቶስ ትንሣኤ ለእኛ ታላቅ ትርጉም አለው፡፡ በእርሱ ትንሣኤ ታላቅ ጸጋ አግኝተናልና። በእርሱ ትንሣኤ ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋግረናል፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን ወጥተናል። ምድራዊያን የነበርን ሰማያዊያን፣ ሙታን የነበርን ሕያዋን፣ ሥጋዊያን የነበርን መንፈሳዊያን ሆነናል፡፡ በእርሱ ትንሣኤ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ «ሞት ሆይ÷ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ÷ ድል መንሣትህ የት አለ?» ማለት ችለናል (1ኛቆሮ 10፡55)፡፡ “ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፥ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና (1ኛ ተሰ 4፡14)” እንደተባለ በእርሱ ትንሣኤ ማመናችን ለድኅነታችን መሰረት ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንቶስ መልእክቱ ‹‹አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል። ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና። ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና (1ኛ ቆሮ 15፡20-22)›› እንደተባለው የእርሱ ትንሳኤ ለእኛ ትንሳኤ በኩር ነው፡፡ እንዲሁም “ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለንና (ሮሜ 6፡5)” እንዳለው ክርስቶስ በትንሣኤው ለእኛም ትንሣኤ መሰረት ሆኖናል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም፡- ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፣ እድፈትም ለሌለበት፣ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ (1ኛ ጴጥ 1፡3)›› እንዳለው የጌታችን ትንሣኤ ለማያልፍ ርስት ዳግመኛ የተወለድንበት ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ ቅዱስ ጳውሎስም ይህንን ታላቅ የትንሣኤ ጸጋ አስመልክቶ «በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳ የን ዘንድ ከእርሱ ጋር አስነሣን፤ በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊው ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን(ኤፌ 2፡6-7)» ብሏል።
ዛሬ የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ (ትንሣኤ ዘክርስቶስን) ስናከብር ትንሣኤ ኅሊና የተባለ በእርሱ ላይ ያለንን እምነትና በእርሱም መታመናችንን በማጽናት፣ ትንሣኤ ልቡና የተባለ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማትና በንስሐ ሕይወት እየታደሱ መኖርን ገንዘብ በማድረግ፣ እርሱ ሕይወታችንና ትንሣኤያችን መሆኑን በማስተዋልና ትንሣኤ ዘጉባዔ ለተባለው ከዓለም ኅልፈት በኋላ ሰው ሁሉ እንደየሥራው ለጽድቅና ለኵነኔ በአንድነት በሚነሣበት የዘለዓለም ትንሣኤ በቀኙ የሚያቆመንን እምነትና ምግባር አስተባብረን በመያዝ ራሳችንን እያዘጋጀን ሊሆን ይገባል፡፡ ይህንንም እናደርግ ዘንድ የትንሣኤውን ብርሃን ያሳየን አምላካችን እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን፡፡ አሜን፡፡