ምስጢረ ቁርባን፡ የቤተክርስቲያን ምስጢራት አክሊል (ክፍል 1)

ምስጢረ ቁርባን ከአምስቱ አዕማደ ምስጢራት አንዱ ነው፡፡ ሃይማኖታቸው የቀናና እውነተኛ የሃይማኖትን መንገድ ያቀኑ ቀደምት አበው (ሠለስቱ ምዕት) “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት (ከሁሉ በላይ በምትሆን የሐዋርያት ጉባዔ በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን)” ብለው የሃይማኖትን ድንጋጌ ያስቀመጡት በቅድስት ቤተክርስቲያን ምስጢረ ምስጢራት (የምሥጢራት ሁሉ ማጽኛ ማኅተም) የተባለው ምስጢረ ቁርባን ስለሚፈጸምባት ነው፡፡ ይህም ምስጢር የሌሎች ምስጢራተ ቤተክርስቲያን መክብባቸውና መፈጸሚያቸው ነው፡፡ የሰው ልጆች ድኅነትን (የዘላለም ሕይወትን) የምናገኝበት፣ በክርስቶስ ቤዛነት ያገኘነውን ነፃነት በሥጋዊ ድካም በኃጢአት ስናሳድፈው ደግሞ ለዘለዓለም ሕያው ከሆነ መስዋዕት በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ እየተካፈልን፣ በድቅድቅ ጨለማ የተመሰለ ኃጢአትን ድል አድርገን ለሰርጉ ቤት ለመንግስተ ሰማያት የተገባን የምንሆንበት ምሥጢር ነው፡፡

በሁለት ተከታታይ የአስተምህሮ ጦማሮች ምስጢረ ቁርባንን የሚመለከቱ ዋና ዋና ጥያቄዎችን አጠር ካለ ማብራሪያ ጋር እናቀርባለን፡፡

1. የምስጢረ ቁርባን ትርጉም ምንድን ነው?

ቁርባን ቃሉ የሱርስትና የግሪክ ሲሆን ትርጉሙ በቁሙ መንፈሳዊ አምኃ (ስጦታ)፣ መስዋዕት፣ መባዕ፣ ለአምላክ የሚቀርብ የሚሰጥ ገንዘብ ማለት ነው፡፡ ግብጾች ዩክሪስት ይሉታል፡፡ ይህም ቃል የግሪክ ሲሆን ትርጉሙ ‹‹ምስጋና ማቅረብ›› ማለት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹የጌታ እራት››፣ ‹‹ምስጢራዊው እራት››፣ ‹‹አንድ የመሆን ምስጢር›› ይሉታል፡፡ ቁርባን የሚለውን ቃል በስፋት ስንመለከተው ሰው ለአምላኩ (ለፈጣሪው) የሚያቀርበውን አምኃ በሙሉ የሚያካትት ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው ግን ስለ አማናዊው ስጦታ ስለኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ነው፡፡ ከሰው ለእግዚአብሔር የቀረበ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ለሰው ሁሉ የተሰጠ የዘላለም ሕይወትን የምንካፈልበት አምላካዊ ጥበብ ነው፡፡ ሰው ለመስዋዕት የሚሆነውን ቀላል ነገር ያቀርባል፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ የሰውን መታዘዝና እምነት አይቶ የሚያልፈውን ወደማያልፈው፣ ምድራዊውን ወደ ሰማያዊው፣ ጊዜያዊውን ወደዘላለማዊው ይለውጣል፡፡ ይህም ምስጢረ ቁርባን በመባል ይታወቃል፡፡

ከአባታችን አዳም ጀምሮ የነበሩ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን በኃጢአታቸው ከእግዚአብሔር በተለዩ ጊዜ ሁሉ በግና ላምን የመሳሰሉ እንስሳትን በእምነት መስዋዕት አድርገው ያቀርቡ ነበር፤ እግዚአብሔርም መስዋዕታቸውን እየተቀበለ ይታረቃቸው ነበር፡፡ በሕገ ልቡናና በሕገ ኦሪት የነበሩት ሁሉ በዚህ ሥርዓት አልፈዋል፡፡ አበ ብዙሐን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ለመሰዋት ወደ ሞሪያ ተራራ በሚወስደው ሰዓት የክርስቶስ ምሳሌ የሆነ ይስሐቅ አባቱን አብርሃምን የጠየቀው ጥያቄና በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘው የአብርሃም ምላሽ በብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን መስዋዕት መካከል ያለውን መሰረታዊ ልዩነት ያስረዳናል፡፡ በዘመነ ብሉይ መስዋዕቱ ምድራዊ፣ አቅራቢውም ምድራዊ ነው፡፡ ይስሐቅ እንደተለመደው የመስዋዕት በግ እንዳልተያዘ ባየ ጊዜ “አባቴ ሆይ…እሳቱና እንጨቱ ይኸው…የመሥዋዕቱ በግ ግን ወዴት አለ?” በማለት ጠይቆት ነበር፡፡ በአብርሃም ህሊና የመሥዋዕቱ በግ ይስሐቅ ነበር፡፡ ይሁንና መንፈስ ቅዱስ እንዳቀበለው “ልጄ ሆይ የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል፡፡” በማለት መለሰለት፡፡ (ዘፍ. 22፡7-8) ለጊዜው እግዚአብሔር ያዘጋጀው (አብርሃምም ይስሐቅም የማያውቁት) ንጹሕ የመሥዋዕት በግ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ ከሰማይ ወረደ፣ በይስሐቅም ቤዛ መሥዋዕት ሆኖ ቀረበ፡፡ (ዘፍ. 22፡13) ይህ በይስሐቅ ፈንታ የተሰዋው ንጹሕ በግ የዓለም መድኃኒት የኢየሱስ ክርስቶስ ምሣሌ ነበር፡፡

ይስሐቅና አብርሃም ለጊዜው ሳይረዱት በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት ሳይረዱት የመሰከሩለት እውነተኛው፣ እግዚአብሔር ያዘጋጀው  (ሰውን ለማዳን በባሕርያችን የተገለጠ) የመሥዋዕት በግ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን የነቢያት ፍጻሜ፣ የሐዋርያት መጀመሪያ የሆነ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ መስክሮልናል፡፡ “ዮሐንስ ወደ እርሱ ሲመጣ ጌታችን ኢየሱስን አይቶ እንዲህ አለ ‘እነሆ የዓለሙን ኀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ፡፡ ከእኔ በፊት የነበረ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል ብዬ ስለ እርሱ የነገርኋችሁ ይህ ነው፤ እርሱ ከእኔ አስቀድሞ ነበርና፡፡” (ዮሐ. 1፡29-30) ስለ ሆነም የሐዲስ ኪዳን እውነተኛ መሥዋዕት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ መሥዋዕትነቱም በይስሐቅ ፈንታ እንደቀረበው በግ ለአንድ ሰው ወይም ለጥቂቶች ሳይሆን ለዓለም ሁሉ ነው፡፡ መሥዋዕት የሆነውም እንደ ብሉይ ኪዳን መሥዋዕት በተደጋጋሚ ሳይሆን አንድ ጊዜ ነው፡፡ መሥዋዕቱም፣ መሥዋዕት አቅራቢውም፣ መሥዋዕት ተቀባዩም እርሱ ራሱ ሰው የሆነ አምላክ፣ ልዩ ሊቀ ካሕናት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ምሥጢረ ቁርባን ማለት ከዚህ በታች በተብራራው መሰረት አንድ ጊዜ ስለ ዓለም ሁሉ ቤዛ መሥዋዕት ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም አካሉ እንሆን ዘንድ የምንካፈልበት፣ ከክርስቶስ ለቤተክርስቲያን የተሰጠ የጸጋዎች ሁሉ አክሊል ነው፡፡  ደጉ አባታችን አባ ሕርያቆስ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት በተናገረው የቅዳሴ ማርያም አንቀጽ ይህንን ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፡- “ዛሬ በዚህች ቀን በፍቅርና በትሕትና ግሩም በሚሆን በዚህ ምሥጢር ፊት እቆማለሁ፡፡ በዚህም ማዕድና ቁርባን ፊት፡፡ መንፈሳቸውን ያረከሱ ሰዎች ከርሱ ሊቀምሱ የማይቻላቸው በእውነት ቁርባን ነው፡፡ በበግ በጊደርና በላም ደም እንደ ነበረው እንደ ቀደሙት አባቶች መሥዋዕት አይደለም፤ እሳት ነው እንጂ፡፡ ፈቃዱን ለሚሠሩ ልቡናቸውን ላቀኑ ሰዎች የሚያድን እሳት ነው፡፡ ስሙን ለሚክዱ ለዓመፀኞች ሰዎች የሚበላ እሳት ነው፡፡” (ቅዳሴ ማርያም ቁጥር 5-7)

በእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት (በምስጢረ ስላሴ) አምነው በክርስቶስ ደም የተዋጁና በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተጠመቁ ምዕመናን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም በመቀበል ምስጢረ ቁርባንን ይፈጽማሉ፡፡ ጌታም በቃሉ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው›› (ዮሐ 6፡54) ብሎ እንደተናገ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን የሚቀበሉ ምዕመናን የዘላለም ሕይወት አላቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ሳይገባው ይህንን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት›› (1ኛ ቆር 11፡26) ብሎ እንደገለጸው የምስጢረ ቁርባን ተካፋይ የሆነ ሁሉ ስለ ቅዱስ ቁርባን ትርጉም፣ አስፈላጊነት፣ አፈጻጸም …ወዘተ ማመንና ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡

2. የሐዲስ ኪዳን ቁርባን በማን እና እንዴት ተመሠረተ?

ምስጢረ ቁርባንን የመሠረተው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ ‹‹ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራውን አንስቶ ባረከ፤ ቆርሶም ለደቀመዛሙርቱ ሰጠና እንካችሁ ብሎ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፡፡ ጽዋውንም አንስቶ አመስግኖ ሰጣቸው፡፡ ሁላችሁም ከእርሱ ጠጡ፤ ስለብዙዎች የኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፡፡›› (ማቴ 26፡26) በማለት የምስጢረ ቁርባንን አመሠራረት ጽፎታል፡፡ አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን ሲቀርቡ የነበሩ መስዋዕቶችን ሁሉ ምሳሌው አድርጎ በማሳለፍ የራሱን መስዋዕትነት ካቀረበ በኋላ ቀድሞ የነበሩትን ነፍሳት ብቻ ሳይሆን ከዚያም በኋላ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድርስ የሚመጡትን ሁሉ አንድ ጊዜ ባቀረበው መስዋዕት የሚያድን ስለሆነ ምስጢሩ ይፈጸም ዘንድ ከሞቱ አስቀድሞ አስተማረ፡፡ ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ የወልደ እጓላ እመሕያው ክርስቶስን ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም፡፡ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው›› በማለት እስከዓለም ፍጻሜ የሰው ልጅ ሌላ መስዋዕት ሳያስፈልገው በአምላካችን ሥጋና ደም ሕይወት እንደሚያገኝ አስተማረ፡፡ የምስጢረ ቁርባንን ትምህርት በወቅቱ የነበሩ አይሁድ ሰምተው ምስጢሩ አልገባቸው ሲል ‹‹ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይቻላል›› በማለት ጠይቀው ነበር፡፡ ደቀመዛሙርቱም ትምህርቱ ከብዷቸው ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ ግን ምስጢሩን ተረድተው ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡ (ሐዋ 2፡43፣ 1ኛ ቆሮ 11፡20)

3. ከምስጢረ ቁርባን በመሳተፍ የሚገኘው ጸጋ ምንድን ነው?

የጌታችንን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ስንቀበል የምናገኘው በረከትና ጸጋ ስፍር ቁጥር ባይኖረውም እንኳን የሚከተሉትን በዓበይትነት ማግኘት እንችላለን፡፡

ቅዱስ ቁርባን የዘላለም ሕይወት ያሰጠናል፡፡ ጌታችን በማይታበል አማናዊ ቃሉ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ›› በማለት እንደተናገረ የተቀበልነው ቅዱስ ቁርባን የሕያው አምላክ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም ነውና የዘላለም ሕይወት ባለቤት መሆናችንን ያረጋግጣል፡፡ ዳግመኛም ቅርጫፍ ከግንዱ እስካልተለየ ድረስ ልምላሜ፣ ጽጌና ፍሬ ሕይወት ለዘላለም እንዲኖረው ሁሉ ክርስቲያኖችም ጉንደ ሐረገ ወይን ከሆነው ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አለመለየታችንና በሕይወት መኖራችንን ቅዱስ ቁርባን ስንቀበል እናረጋግጣለን፡፡ (ዮሐ 6፡53፣ ሮሜ 11፡21-24) ሕያዋን የሚያደርጉንም በውስጣችን ያደረው (የተዋሐደን) ሥጋ ክርስቶስና ደመ ክርስቶስ ናቸው፡፡ እርሱ የማይሞት የማይለወጥ ነውና ‹‹ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ›› በማለት አረጋግጦልናል፡፡ (ዮሐ 6፡56)

ቅዱስ ቁርባን ሥርየተ ኃጢአትን ያስገኛል፡፡ አባቶቻችን ‹‹ሰው ሆኖ የማይበድል እንጨት ሆኖ የማይነድ የለም፤ ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም›› እንዲሉ ደካማና ስሑት የሚሆን ሰብአዊ ባሕርያችን ወደ ስህተት ጎዳና ሲነዳንና ኃጢአት ሲያገኘን በደላችንን ለካህን ተናዝዘን፣ ቀኖና ተቀብለንና ንስሐችንን ጨርሰን በካህኑ ፈቃጅነት ቅዱስ ቁርባንን ስንቀበል የቀደመ ኃጢአት በደላችን ሁሉ እሳት ላይ እንደወደቀ ቅቤ ቀልጦ ጠፍቶ ነጻ ያደርገናል፡፡ ‹‹ከጥምቀት በፊት የተሠራ ኃጢአት በጥምቀት ይሰረያል፤ ከጥምቀት በኋላ የተሠራ ኃጢአት በንስሐና በሥጋ ወደሙ ይሰረያል›› እንዳለ ፊልክስዮስ፡፡  የጌታ ሥጋና ደም ሥርየተ ኃጢአትን ያሰጣልና፡፡ ‹‹ ስለብዙዎች የኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፡፡›› (ማቴ. 26፡28) ብሎ ባለቤቱ ራሱ አስረድቶናል፡፡ እንግዲህ እናስተውል ሥጋውን ከመቁረሱ ደሙን ከማፍሰሱ በፊት በአንጻረ ሕብስትና ጽዋ ሥጋውንና ደሙን ባርኮ ሰጥቶናል፡፡ ይህም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የክርስቶስ አካል የሆነች ቅድስት ቤተክርስቲያን ኃጢአትን የሚያስተሰርይ የጌታን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ለምዕመናን የምትሰጥበት ሰማያዊ ሥርዓት ነው፡፡ የከበረ ሐዋርያ ቅዱስ ዮሐንስ “ልጆቼ ሆይ እንዳትበድሉ ይህን እጽፍላችኋለሁ፤ የሚበድልም ቢኖር ከአብ ዘንድ ጰራቅሊጦስ አለን፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ኃጢአታችንን ያስተሰርይልን ዘንድ ጻድቅ ነው፡፡” (1ኛ ዮሐ. 2፡1) በማለት እንደመከረን በደካማ ባሕርይ እግዚአብሔርን የሚያሳዝን በደል ብንፈጽም በንስሐ ተመልሰን የእግዚአብሔርን ማዳን የምናገኝበት ህያው ቃል ኪዳን የእግዚአብሔር የቸርነቱ መገለጫ የሆነ ቅዱስ ቁርባን ነው፡፡ ማንኛውም ሰው በሃይማኖት ሆኖ ቅዱስ ቁርባንን ቢቀበል ሥርየተ ኃጢአትን ያገኛል፡፡ ከኃጢአት ቁራኝነት ነጻ ሆኖ ኅብረቱ ከሰማያውያን ቅዱሳን ጋር ይሆናል፡፡ ‹‹ኅብስቱ አንድ እንደሆነ እንዲሁም እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ አካል ነን፡፡ ሁላችንም ከአንድ ኅብስት እንቀበላለንና›› በማለት ንዋየ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ ያረጋግጥልናል፡፡ (1ኛ ቆሮ 10፡17)

ቅዱስ ቁርባን የኃጢአት ልም ሆኖ ያገለግለናል፡፡ ክርስቲያን የጌታን ሥጋና ደም ሲቀበል የኃጢአት ልጓም ያገኛል፡፡ ሥጋው ለኃጢአት የሚጓጓና የሚሰነካከል እንዳይሆን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ይጠብቀዋል፡፡ በሥጋውና በደሙ የተዋሐደው አምላክ ኃጢአትን ተደፋፍሮ እንዳይሠራ ይወቅሰዋል፡፡ የኃጢአት ውጤት ሞት መሆኑን ያሳስበዋል፡፡ በአጠቃላይ ወደ ቅድስናና ጽድቅ የሚመራ መንፈሰ እግዚአብሔር ስለተዋሐደን ለጽድቅ ሥራ የምንተጋ ለኃጢአት የምንሰቀቅ እንሆናለን፡፡ በቅዱስ ቁርባን ጸጋ እግዚአብሔርን ስለምንታደል ኃጢአትን እንጸየፈዋለን፡፡ ምክንያቱም በመንፈሳዊ ዕውቀት የምናድግበትና በጸጋ መንፈስ ቅዱስ የምንበለጽግበት ምግበ ሕይወት አግኝተናልና ነው፡፡ ‹‹የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፡፡ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፡፡ በእኔ የሚያምን ሁል ጊዜ ከቶ አይጠማም….ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜ እውነተኛ መጠጥ ነውና›› (ዮሐ 6፡35-45) እንዲል፡፡

4. ምስጢረ ቁርባን ስለምን የምስጢራት ሁሉ መክብባቸው/አክሊል ተባለ?

ቅዱስ ቁርባን ለሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን አክሊል ነው፡፡ እንዲያውም ምስጢረ ምስጢራት ይባላል፡፡ ምክንያቱም አንድ ተጠማቂ ተጠምቆ እንደወጣ ቅዱስ ቁርባን መቀበል አለበት፡፡ አንድ ተነሳሒ ቀኖናውን ሲጨርስ በካህኑ ፈቃድ ንስሐውን በቅዱስ ቁርባን ያትመዋል፡፡ በቅዱስ ጋብቻ ለመኖር የወሰኑ ተጋቢዎች ከሥርዓተ ተክሊል በኋላ አስቀድሰው ቅዱስ ቁርባንን ይቀበላሉ፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ቅዱስ ቁርባን የምስጢራት ምስጢር መባሉ ትክክል ነው፡፡ ቅዱስ ቁርባን የምስጢራተ ቤተክርስቲያን ሁሉ የበላያቸው፣ መክብባቸውና መፈጸሚያቸው የሆነበት ምክንያት ጌታ የሰውን ልጅ ለማዳን በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ ሥጋውን በመቁረስ ደሙንም በማፍሰስ ካሳ የከፈለበትን፣ የማዳን ሥራውን የፈጸመበትን ሁኔታ የሚያረጋግጥና የሚመሰክር ከመሆኑ ጋር ምዕመናን ከሥጋውና ከደሙ ተካፋይ እንዲሆኑ በማብቃት የሕይወትን ጸጋ እንዲቀበሉ ስለሚያደርግ ነው፡፡ ስለዚህም ሌሎቹ ምስጢራት ሁሉ በቅዱስ ቁርባን አማካኝነት የምስጢራቸውን ትርጉምና ፍጻሜ ያገኛሉ፡፡

5. ክርስቶስ ሥጋውንና ደሙን ለምን በምግብና መጠጥ (በሚበላና በሚጠጣ) አደረገው?

ምግብና መጠጥ ከሰውነታችን እንደሚዋሐድ ሥጋውንና ደሙን ስንቀበል በእውነት እንደሚዋሐደን ለማስረዳት፤ በጸጋ ተዋሕጃችኋሁ ሲለን ሥጋውና ደሙን በሚበላና በሚጠጣ አደረገው፡፡ አንድም መብልና መጠጥ ያፋቅራል፤ ስጋና ደሙ ያፋቅራልና፤ ቅዱስ ቁርባንም የክርስቶስን ፍቅር በልቦና ያሳድራልና አንድም እርሱ ለእኛ ያለውን ፍቅር ሲገልጥልን ሥጋውና ደሙን በሚበላና በሚጠጣ አደረገው፡፡ እንዲሁም ምግብ ለሥጋችን ኃይል እንደሚሆነን ሥጋውና ደሙም ለነፍሳችን መንፈሳዊ ኃይል እንዲሰጠን ሥጋውና ደሙን በሚበላና በሚጠጣ አደረገው፡፡ በተጨማሪም በመብል የጠፋው ዓለም በመብል እንዲድን፤ አዳምና ሄዋን በምግብ የእግዚአብሔር ልጅነታቸውን እንዳስወሰዱ ፤ በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ልጅነታችንን ሊመልስልን ሥጋውና ደሙን በሚበላና በሚጠጣ አደረገው። (ዘፍ 3 ፥ 1 ። ዮሐ 6 ፥ 49) ከዚህም በላይ የተራበና የተጠማ ሰው ብር፣ ወርቅ ከሚሰጡት ይልቅ መብልና መጠጥ የሰጠውን እንደሚወድ ጌታም ፍቅሩን ሲገልጥልን የነፍስ ርሃባችንን ሊያስወግድ ሥጋና ደሙን በምግብና በመጠጥ አደረገው፡፡ ምግብና መጠጥ በቀላሉ ከሰውነታችን እንደሚዋሐድ እንዲሁ ጌታም በቀናች ሃይማኖት በመልካም ምግባር ሆነን ሥጋውን ብንበላ ደሙንም ብንጠጣ ከጌታችን ሕያውነት የተነሳ ለዘለዓለም ሕያው ሆነን በክብር እንደምንኖር ጌታችን አስተምሮናል፡፡ (ዮሐ. 6፡58)

6. የቅዱስ ቁርባን የብሉይ ኪዳን ምሳሌዎች ምንድን ናቸው?

የአብርሃም መሥዋዕት፡ አባታችን አብርሃም በልጁ ይስሐቅ ፈንታ የሰዋው በግ ለአማናዊው (ለእውነተኛው) የእግዚአብሔር በግ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀጥተኛ ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም በጉን በይስሐቅ ፈንታ እንደሰዋ ሁሉ ክርስቶስም ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ መስዋዕት (ምትክ) ሆኖ ተሰውቷል፡፡ የበጉ ቀንድ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ እንደተገኘ ጌታም ከእመቤታችን በነሳው ሥጋ ተገኝቷል፡፡ አብርሃም በሰዋው በግ እርሱና ዘሮቹ በሙሉ እንደተባረኩ፣ በጌታም መስዋዕትነት አዳምና ልጆቹ ተባርከዋል፡፡ ዘፍ 22፡1-9

መሥዋዕተ መልከጼዴቅ፡ መልከ ጼዴቅ ከአብርሃም በፊት የነበረ የእግዚአብሔር ካህን ነው፡፡ዘፍ 14፡18-21 ዕብ 7፡1 ከመልከጼዴቅ በኋላ የተነሡ ሌዋውያን ካህናት መሥዋዕትን የሚያዘጋጁት ከእንስሳት ነበር፡፡ ዕብ 10፡4 መልከጼዴቅ ግን የሐዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ራስ የክርስቶስ ምሣሌ ነበርና እንደ ሐዲስ ኪዳን ሥርዓት በንጹህ ስንዴና ወይን ያስታኩት ነበር፡፡ ይህንንም መሥዋዕት አድርጎ ያቀርብ ነበር፡፡ ‹‹የእንስሳትን መስዋዕት አትሰዋ፤ ነገር ግን መስዋዕትህ በእግዚአብሔር ፊት ከንጹሕ የስንዴ ኅብስትና ከንጹሕ የወይን ፍሬ ይሁን›› እንዳለ ቀለሜንጦስ፡፡ መሥዋዕተ መልከጼዴቅ ለቅዱስ ቁርባን ምሳሌው ነበር፡፡ የመልከ ጼዴቅ ክህነትም ለኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ ክህነት ምሳሌ ነበር፡፡

የደብተራ ኦሪት ቁርባንና መሥዋዕት፡ ከ430 ዓመታት በኋላ ከግብፅ የወጡት እስራኤላውያን መሥዋዕትን እንዲያቀርቡ ታዘው ነበር፡፡ ዘሌ 12፡3-11 ይህ የበግ መሥዋዕት የሚቀርብበት የእስራኤል ፋሲካ የሥጋ ወደሙ ምሳሌ ነበር፡፡በዕብራይስጥ ፋሲካ ማለት ‹‹አለፈ›› ማለት ነው፡፡ያለፈውም ቀሳፊው መልአክ ነው፡፡ በሐዲስ ኪዳን ክርስቶስ ‹‹ፋሲካችን›› ተብሏል፡፡ 1ኛ ቆሮ 5፡7 ‹‹በዓለ ትንሣኤ ፋሲካነ እስመ ሥርዓቱ ለእስራኤል ውእቱ›› እንዲል፡፡

እስራኤል ከሞተ በኩር የዳኑበት በግ፡ ሕዝበ እስራኤል በእግዚአብሔር ኃይል በሙሴ መሪነት ከፈርዖን መዳፍ ነጻ የወጡት በግብፃውያን ላይ በታዘዘው ሞተ በኩር ምክንያት ነበር፡፡ ይህ ሞተ በኩር የእስራኤልን ልጆች እንዳያገኛቸው ‹‹ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ጠቦት እንዲያዘጋጁ፣ እስከ 14ኛው ቀንም እንዲጠብቁት፣ሲመሽም እንዲያርዱት፣ ከደሙም ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጉበኑን እንዲቀቡት፣ በእሳት የተሠበሰውን ሥጋውንና ቂጣውን እንጀራ እንዲበሉ፣ የቀረውንም እንዲያቃጥሉት›› ታዘው ነበር፡፡  ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ጠቦት ምክንያተ ኃጢአት የሌለበት የንጹሐ ባሕርይ አምላክ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ የበጉን ጥብሱን ብቻ እንደተመገቡ በእሳት የተመሰለ መለኮት የተዋሐደውን ሥጋ ለምንቀበል ለእኛ አብነት ለመሆን የምንበላውና የምንጠጣው ሥጋና ደም ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሐደው ነውና፡፡ ዘጸ 12፡46

ለእስራኤል የወረደው መና፡ ለእስራኤል ልጆች በምድረ በዳ ከደመና የወረደላቸው መና ጌታ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ ለሰው ልጆች ሲል የቆረሰው ሥጋና ያፈሰሰው ደም ምሳሌ ነው፡፡ መናው የተገኘው ከደመና እንደሆነ ሁሉ ጌታም ሥጋና ነፍስን የነሳው ከቅድስት ድንግል ማርያም ነው፡፡ ስለዚህ ደመናው ጌታ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ ሰው የሆነባት የድንግል ማርያም ምሳሌ ነው፡፡ ጌታም በዘመነ ስብከቱ ‹‹የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፡፡ አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም፤ ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው….እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምስጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው›› በማለት ለእስራኤል የወረደው መና የሥጋውና የደሙ ምሳሌ መሆኑን አስተምሯል፡፡ ዮሐ 6፡49-51

7. ቅዱስ ቁርባን ለምን ከስንዴና ከወይን ይዘጋጃል?

ከአዝዕርት ስንዴ ከፍራፍሬ ደግሞ ወይን ለጌታ ሥጋና ደም መመረጣቸው ምሳሌ፣ ትንቢትና ምስጢር አለው፡፡ ምሳሌው ክህነቱ ለወልደ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ ክህነት ምሳሌ ሆኖ የተጠቀሰው መልከጼዴቅ በስንዴና በወይን ይሰዋ ነበር፡፡ ይህም ምሳሌነቱ ለጌታ ሥጋና ደም ነው፡፡ ዘፍ 14፡18 ትንቢቱ ደግሞ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ‹‹በልቤ ደስታ ጨመርኩ፤ ከስንዴ ፍሬና ከወይን ከዘይትም ይልቅ በዛ›› በማለት የተናገረው ነው፡፡ መዝ 4፡7 ምስጢሩ ደግሞ ስንዴ ስብን ይመስላል፤ ወይን ደግሞ ትኩስ ደምን ይመስላል፡፡ ስለዚህ በሚመስል ነገር መስጠቱ ነው፡፡

8. መሥዋዕቱ ከቤተልሔም ተነስቶ ወደ ቤተመቅደስ መግባቱ የምን ምሳሌ ነው?

መሥዋዕቱ የሚዘጋጀው በቤተክርስቲያን ቅጥር (አጥር) ውስጥ በስተምሥራቅ በኩል በሚገኘው ‹‹ቤተልሔም›› ውስጥ ነው፡፡ ይህም ጌታችን በተወለደበት ከተማ ስም የተሰየመ ሲሆን ቤተመቅደሱ ደግሞ አምሳለ ቀራኒዮ ነው፡፡ ጌታችን የማዳን ሥራውን በቤተልሔም ጀምሮ በቀራኒዮ አደባባይ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ‹‹ተፈፀመ›› በማለት አድኖናልና የቅዱስ ቁርባን መስዋዕትም በቤተልሔም ተዘጋጅቶ ወደ ቤተመቅደስ ገብቶ ይቀርባል፡፡ ይህም ጌታን ከልደቱ እስከ ስቅለቱ ያደረገው የማዳን ጉዞ ምሳሌ ነው፡፡

9. ኅብስቱና ወይኑ ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደም የሚለወጥበት ሥርዓት ምንድን ነው?

ምስጢረ ቁርባን የሚከናወንበት ጸሎተ ቅዳሴ እጅግ የከበረና ለክርስቲያኖች ሁሉ በረከትን የሚያሰጥ ነው፡፡ በጸሎተ ቅዳሴው ውስጥ ካህኑ እንደ ሥርዓቱ እየጸለየ በኅብስትና በወይኑ ላይ ቡራኬ ያደርጋል፡፡ ጸሎተ ቅዳሴውንም ሲጸልይ “አቤቱ ወደዚህ ኅብስትና ወደዚህ ወይን መንፈስ ቅዱስንና ኃይልን እንድትልክ እንለምንኃለን፣ የጌታችንን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውንና ደሙን ያደርገው ዘንድ” የሚለዉን ጸሎት እየጸለየ ቀዳሹ ካህን ሕብስቱንና ወይኑን ይባርካል፡፡ ይህን የሚጸለይበት ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል (በመንፈስ ቅዱስ ሥራ)ኅብስቱ የክርስቶስ ሥጋ፣ ወይኑ የክርስቶስ ደም ይሆናል፡፡ ይህም ጸሎት ይረስዮ ይባላል፡፡ (ኅብስቱንና ወይኑን የክርስቶስ ሥጋውንና ደሙን ያድርገው ማለት ነው)፡፡

ይህም በቅዳሴ ሐዋርያትና በቅዳሴ እግዚእ ነው ያለው፣ በሌሎቹ ቅዳሴዎችም ይህን የመሰለ ጸሎት አለ፣ ከዚህ ቀጥሎ አያይዞ ካህኑ እየመራ፣ ሕዝቡ እየተከተለ “ሀበነ ንኀበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ ወፈውሰነ በዝንቱ ጵርስፎራ…” እያሉ ይጸልዩበታል፡፡ ቀጥሎ ጸሎተ ፈትቶ አለ፣ ቄሱ ያን እየጸለየ እንደ ሥርዓቱ ሥጋውን ይፈትተዋል፡፡ ይህንንም ሲፈጽም ካህኑ እየመራ ሕዝቡ እየተቀበሉ አርባ አንድ ጊዜ እግዚኦታ (እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ) ያደርሱበታል፡፡ ቀጥሎ ካህኑ “አአምን፣ አአምን፣ አአምን፣ ወእትአመን …እያለ ሥጋውን በደሙ” “ቡሩክ እግዚአብሔር አብ…ወብሩክ ወልድ ዋሕድ…ወቡሩክ መንፈስ ቅዱስ…”እያለ ደሙን በሥጋው ሦስት፣ ሦስት፣ ጊዜ ይባርከዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በቅድሚያ ቀዳሾች ካህናት (ቅዱስ ሥጋውን ከሠራዒው ካህን፣ ክቡር ደሙን ከንፍቁ ካህን እጅ በዕርፈ መስቀል)፣ ቀጥሎ ሕዝቡ (ቅዱስ ሥጋውን ከሠራዒው ካህን፣ ክቡር ደሙን ከዲያቆኑ በዕርፈ መስቀል) እንቀበላለን፡፡

10. ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን ሊቀበል የሚገባው ማነው? ሕጻናትና ለአዛውንቶች ብቻ ናቸውን?

ለብዙዎች የክርስቶስ ሥጋና ደም ለሕፃናት፣ ለአረጋውያንና በደዊ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ለተያዙ ብቻ የተሰጠ ይመስላቸዋል፡፡ ይህ ግን ፍጹም ስሕተት ነው፡፡ ሥጋ ወደሙ የዘላለም ሕይወትን የሚያድል፣ ሥርየተ ኃጢአትን የሚሰጥና ከዳግም ድቀት የሚጠብቅ ነው ካልን ይህ ጸጋና በረከት ደግሞ ዕድሜ፣ዘር፣ ቀለምና ጾታ ሳይለይ በስሙ ለሚያምኑ የሰው ልጆች ሁሉ የሚያስፈልግ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ጌታችን ኅብስቱን ከ13 ፈትቶ አንዱን ራሱ ተቀብሎ የቀረውን ያቀበላቸው 13ቱን ሕማማተ መስቀል ተቀብዬ አድናችኋለሁ ሲላቸው ነው፡፡ ሥጋዬን በልታችሁ ደሜን ጠጥታችሁ መንግስተ ሰማያት ትገባላችሁ ቢላቸው ከአይሁድ ትምህርት የተነሳ የሰው ሥጋ እንዴት ይበላል ብለው ይፈሩ ነበርና አብነት ሲሆናቸው ቆርቦ አቆረባቸው፡፡

በማዕከለ ምድር በቀራኒዮ አደባባይ በመልዕልተ መስቀል ላይ የተሰዋው የመድኃኒት በግ ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ትምህርቱ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ለሚያምንበት ሁሉ የተሰጠ ምግበ ሕይወት መሆኑን አስተምሯል፡፡ የአዳም ዘር የሆነ ሁሉ መንግስተ እግዚአብሔርን ይወርስ ዘንድ ከዚህ መንፈሳዊ አምኃ (ስጦታ) መካፈል ግዴታው ነው፡፡ ሰው አስቀድሞ የሚቀበለው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ አማናዊ መሆኑን አምኖ ራሱን ሲመረምር፣ ንስሐ ሲገባና ከመምህረ ንስሐው ጋር ተማክሮ በሃይማኖትና በአትሕቶ ርዕስ ቢቀርብ ከቅዱስ ቁርባኑ አይከለከልም፡፡ 1ኛ ቆሮ 11፡29 ስለዚህ በክርስቶስ የባህርይ አምላክነት ያመነ፣ ሃይማኖታዊ ምስጢር የገባው፣ ንስሐ የገባና የተሰጠውንም ቀኖና በሚገባ የፈጸመ ሰው ዕድሜና ጾታ ሳይለይ ከምስጢረ ቁርባን መካፈል ይችላል፡፡

11. ከምስጢረ ቁርባን ለመሳተፍ ምን ዝግጅት ያስፈልጋል?

እንኳንስ ሥጋ ወደሙን የሚቀበል ክርስቲያን ይቅርና ወደ አንድ ምድራዊ ንጉሥ (ባለ ጸጋ) ግብዣ የተጠራ ሰው አቅሙ የፈቀደለትን ያህል ተዘጋጅቶ ነው የሚሄደው፡፡ ለሰማያዊው ንጉሥ ለኢየሱስ ክርስቶስ ግብዣማ አብልጠን ልንዘጋጅ ይገባል፡፡ ማቴ 21፡16 ‹‹ንጉሥ የተቀመጡትን ለማየት በገባ ጊዜ በዚያ የሰርግ ልብስ ያልለበሰ ሰው አየና ወዳጄ ሆይ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ አለው፤ እርሱም ዝም አለ›› ይለናልና እኛም ጥያቄው ምላሽ እንዳናጣ ልንዘጋጅ ያስፈልጋል፡፡

ስንዘጋጅም ወደ ልባችን የኃጢአት ሐሳብ እንዳያስገቡ አካለዊ ስሜቶቻችንን ሁሉ መግዛት፣ አካልን መታጠብና አቅም የፈቀደውን ንጹሕና ጽዱ (ነጭ) ልብስ መልበስ (ራዕ 6፡11)፣ ቁርባን በሚቀበሉበት ዋዜማ ቀለል ያለ ምግብ መመገብና ለ18 ሰዓታት ከምግበ ሥጋ መከልከል፣ በትዳር ለሚኖሩ ከቁርባን በፊት ለ3 ቀናት ከቁርባን በኋላ ለ2 ቀናት ከሩካቤ መከልከል፣ ለወንዶች ህልመ ሌሊት (ዝንየት) ለሴቶች ደግሞ የወር አበባ (ወይም በማንኛውም ምክንያት የሚደማ/የሚፈስ፣ ቁስል) ያላገኛቸው፣ ሴቶች ወንድ ቢወልዱ 40 ቀን ሴት ቢወልዱ ደግሞ 80ቀን የሞላቸው፣ በሚቆርቡበት ዕለት ቅዳሴ ሲጀመር ጀምሮ ተገኝቶ ማስቀድስ ናቸው፡፡

12. “ከበደላችሁ ንጹሕ ነኝ!” የሚለው የካህኑ አዋጅ ለምን አስፈለገ?

በቅዳሴ ውስጥ ካህኑ “ንጹሕ የሆነ ከቁርባኑ ይቀበል፤ ንጹሕ ያልሆነ ግን አይቀበል፤ ለሰይጣንና ለመልእክተኞቹ በተዘጋጀው በመለኮት እሳት እንዳይቃጠል፤ በልቡናው ቂምን የያዘ ልዩ አሳብም ያለበት ቢኖር አይቅረብ፤ እጄን ከአፍአዊ ደም ንጹሕ እንዳደረግሁ እንዲሁም ከሁላችሁ ደም ንጹሕ ነኝ፡፡ ደፍራችሁ ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደም ብትቀርቡ ከእርሱ ለመቀበላችሁ መተላለፍ የለብኝም በደላችሁ በራሳችሁ ይመለሳል እንጅ፡፡ በንጽሕና ሆናችሁ ባትቀርቡ እኔ ከበደላችሁ ንጹሕ ነኝ” ብሎ እጁን ይታጠባል፡፡ ዲያቆኑም ተቀብሎ “ይህን የቄሱን ቃል ያቃለለ ወይም የሳቀና የተነጋገረ ወይም በቤተክርስቲያን በክፋት የቆመ ቢኖር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዳሳዘነው በእርሱም እንደተነሣሣ ይወቅ ይረዳ ስለበረከት ፈንታ መርገምን ስለኃጢአት ሥርየት ፈንታ ገሃነመ እሳትን ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላል” ይላል፡፡

ይህ አዋጅ የሚታወጀው ከቅዱስ ሥጋና ከክቡር ደሙ ርቀን እንድንቆም ወይም ተመልካቾች ብቻ እንድንሆን ተፈልጎ ወይም እንዳንቆርብ ለማስፈራራት ተብሎ አይደለም፡፡ ንስሓ ገብተን፣ በምክረ ካህን ተዘጋጅተን በንጽሕና ሆነን እንድንቀበል ነው ለማሳሰብ ነው እንጅ፡፡ የጌታችን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ከኃጢአት በንስሐ ሳይነጹ በድፍረት ቢቀበሉት ቅጣትን ያመጣልና፡፡ ጠላት ዲያብሎስ ግን ይህንን የካህኑን አዋጅ እያሳሰበና እንደማስፈራሪያ እንድናየው እያደረገ “ሥጋ ወደሙን ለመቀበል የበቃህ/ሽ አይደለህ/ሽም” ብሎ ከሥጋ ወደሙ እንድንርቅ ያደርገናል፡፡ የዚህ አዋጅ ዋና መልእክት ንስሓ ገብታችሁ፣ ከንስሓ አባታችሁ ጋር ተማክራችሁ ቅረቡ የሚል ነው፡፡

ክፍል 2 ይቀጥላል፡፡

3 thoughts on “ምስጢረ ቁርባን፡ የቤተክርስቲያን ምስጢራት አክሊል (ክፍል 1)

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s