ምስጢረ ቁርባን፡ የቤተክርስቲያን ምስጢራት አክሊል (ክፍል 2)

ምስጢረ ቁርባን በክርስቶስ ቤዛነት ያመንን ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ የምንሆንበት፣ ስርየተ ኃጢአትን የምናገኝበት፣ በመዳን ጉዞ ውስጥ ሰይጣንን ድል የምናደርግበት፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑ የሚታወቅበት፣ በእምነት ካልሆነ በቀር በፍጥረታዊ አዕምሮ የማይታወቅ ሰማያዊ ጸጋን የሚሰጥ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ የበጎ ነገር ጠላት ዲያብሎስ ምዕመናን በቀናች ሃይማኖት ጸንተው ከዚህ ጸጋ እንዳይካፈሉ በመናፍቃን እያደረ የማሳሳቻ ትምህርቶችን ያመጣል፡፡ ስለሆነም ምስጢረ ቁርባን እጅግ ብዙ ጥያቄዎች የሚነሱበት የቤተክርስቲያን ምስጢር ነው፡፡ ሰዎች በዚህ ምስጢር ላይ ጥያቄዎችን የሚያነሱት ስለ ምስጢሩ ካላቸው ግነዛቤ ማነስና ምስጢሩም ከሰው አዕምሮ በላይ ከመሆኑ የተነሳ ነው፡፡ በተጨማሪም ዘመኑ የወለዳቸው መናፍቃንም ራሳቸው ክደው ሌላውንም ለማስካድ በተለያየ መንገድ የሚረጩት የሐሰት ትምህርት በምዕመናን አዕምሮ ውስጥ ብዙ ጥያቄዎች እንዲፈጠሩ ያደርጋል፡፡ ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት በአስተምህሮ የጡመራ መድረክ በዚህ ርዕስ ክፍል አንድ ጦማር በምስጢረ ቁርባን ዙሪያ የሚነሱ 12 ዋና ዋና ጥያቄዎች ተዳስሰዋል፡፡ በዚህ በሁለተኛውና የመጨረሻው ክፍል ደግሞ ሌሎች በምስጢረ ቁርባን ላይ የሚነሱ 13 ተጨማሪ ጥያቄዎች ይዳሰሳሉ፡፡

13. ቅዱስ ቁርባንን በምንቀበልበት ጊዜ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?

ጌታችን በቃሉ እንዳስተማረን ቅዱስ ቁርባን ደካማ ስጋችን በእግዚአብሔር ፀጋ ከብሮ የሚኖርበት ድንቅ ምሥጢር ነው፡፡ በኃጢአት የደከመ ሰውነታችን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለመሆን፣ የክርስቶስን ሥጋና ደም ለመቀበል በንስሐ መታጠብ አለበት፡፡ ንስሐውም እንደ ሮማዊው መቶ አለቃ ፍፁም ራስን ዝቅ በማድረግ፣ በትህትና የሚፈጸም መሆን አለበት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቅፍርናፎም በገባ ጊዜ አንድ መቶ አለቃ ቀርቦ ልጁን እንዲያድንለት ለመነው፤ ጌታችን ወደ መቶ አለቃው ቤት ሄዶ ልጁን እንደሚፈውስለት በነገረው ሰዓት ትሁት፣ ተነሣሂ ልቦና ነበረው መቶ አለቃ “አቤቱ! አንተ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፡፡” (ማቴ. 8፡8) በማለቱ ጌታችን አመስግኖታል፡፡ እኛም የከበረ የክርስቶስ አካል ቤት በተባለ ሰውነታችን በቅዱስ ቁርባን አማካኝነት እንደሚገባ ሲነገረን እንደ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን በትዕቢት ሳይሆን እንደ መቶ አለቃው በትህትና፣ ኃጢአታችንን በመናዘዝ “አቤቱ! አንተ በእኔ በኃጢአት በከረሰ ሰውነት ልታድር አይገባህም፣ እንደ ቸርነትን አንጻኝ፣ ቀድሰኝ” ልንል ይገባል፡፡ ለዚህም እንዲረዳን በመንፈስ ቅዱስ የተቃኙ አባቶቻችን ወደ ቅዱስ ቁርባን ለመቅረብ የሚጸለዩ ልቦናን ከምድራዊ ሀሳብ ከፍ የሚያደርጉ፣ ትምህርተ ሃይማኖትን የጠነቀቁ ጸሎቶችን አዘጋጅተውልናል፡፡

ስለሆነም የሚቆርቡ ምዕመናን ከመቁረባቸው በፊት የሚጸለየውን ጸሎት ይጸልዩ ዘንድ ይገባል፡፡ ቅዱስ ቁርባንን ካህናት፣ ሕጻናት፣ ደናግል፣ ሕዝባዊያንና ምዕመናን ቤተክርስቲያን የሠራችላቸውን ቅደም ተከተል ጠብቀው ይቆርባሉ፡፡ ሥጋውን ካህኑ በእጁ ሲያቀብል ደሙን ንፍቅ ካህኑ በዕርፈ መስቀል ለካህናት እንዲሁም ዲያቆኑ ለምዕመናን በዕርፈ መስቀል ያቀብላል፡፡ ንፍቅ ካህን ሥጋውን አያቀብልም፡፡ ንፍቅ ዲያቆንም ደሙን ለማቀበል አይችልም፡፡  የአቆራረብ ቅደም ተከተላቸውም ቅድሚያ በመቅደስ ውስጥ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት፣ ቆሞሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት ሲቆርቡ በቅድስት ደግሞ የሚጠቡ ሕጻናት፣ ወንድ ልጆች፣ ሴቶች ልጆች፣ አዋቂ ወንዶችና አዋቂ ሴቶች ይቆርባሉ፡፡ በመጨረሻም ማየ መቁርር (የቅዳሴ ጠበል) ቅዱስ ቁርባንን ለተቀበሉ ወዲያውኑ ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚያም ከቁርባን በኋላ የሚጸለየውን ጸሎት ይጸልያሉ፡፡

14. ቅዱስ ቁርባን ከተቀበልን በኋላ ምን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል?

ቅድስት ቤተክርስቲያን የሰርግ ቤት ትባላለች፡፡ በሰርግ ቤት የሙሽራና የሙሽሪት ተዋሕዶ (አንድነት) እንደሚፈጸም በቅድስት ቤተክርስቲያንም የሙሽራው የክርስቶስና የሙሽራይቱ የቤተክርስቲያን ተዋሕዶ (አንድነት) ይነገርባታል፣ ይፈጸምባታል፡፡ (ኤፌ. 5፡21-33) የሰው ልጅ በልማዱ ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚሆንበት ጊዜ ራሱን ባማረ ልብስ ያስውባል (ታስውባለች)፡፡ በተለይም ደግሞ ወደ ሰርግ ቤት የተጠራ እንደሆነ ልዩና ያማረ ሰርግ ልብስ መልበስ ይገባል፡፡ በወንጌል ትርጓሜ የሰርግ ቤት የተባለች ቅድስት ቤተክርስቲያን ነች፡፡ የሰርጉ ማዕድም የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ፣ ክቡር ደም ነው፡፡ ጌታችን በወንጌል እንዳስተማረ ሙሽራው ባለበት የሰርግ ቤት የሰርግ ልብስ ሳይለብሱ በአልባሌ አለባበስ መገኘት ያስወቅሳል፣ ያስቀጣል፡፡ (ማቴ. 22፡11-13)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲህ የክርስቶስን አካል ወስዳችሁ የአመንዝራ አካል ታደርጉታላችሁን? አይገባም፡፡” (1ኛ ቆሮ. 6፡15) እንዳለ የክርስቲያን ሰውነት በክርስቶስ ሥጋና ደም የከበረ ነውና ሁልጊዜም በንጽሕና፣ ከኃጢአት በመራቅ መጠበቅ አለበት፡፡ በተለይም በቅዱስ ቁርባን ከክርስቶስ ጋር በምንዋሐድባቸው ዕለታት ከሌሎች ጊዜያት በበለጠ ጥንቃቄ ራሳችንን ከኃጢአት ልንጠብቅ ይገባል፡፡ ይህም ባሏን የምትጠብቅ ንጽሕት ሙሽራን ይመስላል፡፡ አንዲት ሴት ምንጊዜም ራሷን በንጽሕና መጠበቅ እንዳለባት ቢታወቅም ባሏን ለተዋሕዶ በምትጠብቅበት ዕለት ግን በተለየ ሁኔታ ራሷን ትጠብቃለች፡፡ እኛም ራሳችንን የክርስቶስ ሙሽራ አድርገን በንስሐ ተጸጽተን ሥጋውን ከበላን ደሙን ከጠጣን በኋላ ልናደርጋቸው የሚገቡንን ጥንቃቄዎች የክርስቶስ አካል ቅድስት ቤተክርስቲያን ደንግጋልናለች፡፡

በፍርድ በሙግት ጠብና ክርክር አይታጣምና ከዚያ ለመራቅ ከቆረቡ በኋላ በዚያው ዕለት ወደ ፍርድ ቤት መሄድና መሟገት ክልክል ነው፡፡ ከመንፈሳዊ ሀሳብ ይልቅ ለስጋዊ ደስታ የተመቸ ነውና በዚሁ ዕለት ለባለትዳሮች ሩካቤ፣ አብዝቶ መብላትና መጠጣት አየይገበባመም፡፡ ጥፍር መቁረጥ፣ ጸጉር መላጨት፣ በውኃ መታጠብና ከልብስ መራቆት ክልክል ነው፡፡ ግብፃውያን ክርስቲያኖች በቆረቡበት ዕለት በባዶ እግር አይሄዱም፡፡ እንቅፋት እንዳያገኛቸውና እግራቸው እንዳይደማ ነው፡፡ እንዲሁም ከቁርባን በኋላ የጸሎት መጻሕፍትን ያነባሉ፡፡ ተረፈ ዕለቱንም ከሰዎች ጋር ባለመገናኘት፣ በሰላምና ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ያሳልፋሉ፡፡

ከቆረቡ በኋላ በተለይም ከጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ እንቅፋት (መሰናክል) እክል ቢያጋጥመን ለምሳሌ. ነስር፣ እንቅፋት፣ ትውከት፣ ወደ አፍ የሚገባ ትንኝ፣ ዝንብ… ቢያጋጥመን፤ ንስሃ ልንገባና ያጋጠሙንን እክሎች በሙሉ ለካህን (ለንስሃ አባታችን) ልንናገር ይገባል፡፡የተሰጠንን ንስሃም ሳንፈጽም ዳግም መቁረብ አይፈቀድም (አይገባም)፡፡ ሩቅ መንገድ መሔድ፣ መስገድ፣ አይገባም፡፡ ይህም ምስጢሩ በሥጋ ወደሙ ድካም የለበትምና፡፡ አንድም በመንግስተ ሰማይ ከገቡ በኋላ ድካም የለምና አንድም ድኀነት በሥጋና በደሙ ሳይሆን በትሩፋት ነው እንዳያሰኝ ነው፡፡

15. ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስለምስጢረ ቁርባን የምታምነው እምነት ከሌሎች የሚለየው እንዴት ነው?

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስለምስጢረ ቁርባን የምታምነው እምነት አማናዊ ለውጥ (Definitive change) ሲሆን ይህም ‹ፍጹም በሆነ አምላካዊ ምስጢር ኅብስቱ ተለውጦ አማናዊ የክርስቶስ ሥጋ፣ ጽዋውም ተለውጦ አማናዊ የክርስቶስ ደም ይሆናል›› የሚል ነው፡፡ ይህም የሰው አእምሮ ተመራምሮ የማይደርስበት አምላካዊ ምስጢር ነው፡፡ ከተለወጠም በኋላ ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሐደው ሥጋና ደም ይሆናል፡፡ ይህንንም ተቀብለን ከክርስቶስ ጋር አንድ አካል እንሆናለን፡፡ የካቶሊክ እምነት ደግሞ ‹‹ተፈጥሮአዊ በሆነ ለውጥ (Transubstantiation) የኅብስቱና የወይኑ ተፈጥሮ ወደ ሥጋና ደም ይቀየራል›› የሚል ነው፡፡ በእነርሱ እምነት ለውጡ በውጫዊ ገጽታውና በውስጣዊ ይዘቱ ላይ አይታይም፡፡ ተቀይሮም ሙሉ ክርስቶስን (ሥጋ፣ ደም፣ ነፍስና መለኮት ያለው) ይሆናል ብለው ያምናሉ፡፡ በሌላ በኩል ሉተራንስ ብሎ ራሱን የሚጠራው ዋናው የፕሮቴስታንት ክንፍ ስለ ቁርባን የሚያራምደው እምነት ‹‹ምስጢራዊ ኅብረት (Sacramental Union)›› ይባላል፡፡ ይህም የክርስቶስ ሥጋና ደም ከኅብስቱና ከወይኑ ጋር አብሮ በኅብረት ይገኛል የሚል ሲሆን የሚቀበሉትም ሥጋውና ደሙን እንዲሁም ኅብስቱንና ወይኑን አብረው ይቀበላሉ ብለው ያምናሉ፡፡

በአንጻሩ ተሃድሶአውያኑ ደግሞ ‹‹በመንፈስ መገኘት (Spiritual Presence)›› የሚል አስተምህሮ አላቸው፡፡ ይህም በቁርባኑ ላይ ክርስቶስ በአካል አይገኝበትም፤ በመንፈስ እንጂ የሚል ነው፡፡ ስለዚህም በኅብስቱና በወይኑም የሚካሄድ የተፈጥሮ/ይዘት ለውጥ የለም ብለው የሚያምኑ ሲሆን ከቁርባኑ ጋር ያለው መንፈስም የሚቀበሉትን ክርስቲያኖችን ከክርስቶስ ጋር ያገናኛቸዋል ይላሉ፡፡ ሌላው በቁርባን ላይ ያለው እምነት የተለያዩ አዳዲስ የእምነት ድርጅቶች የሚያራምዱት ‹‹መታሰቢያነት (Memorialism)›› የሚለው ነው፡፡ ይህም ኅብስቱና ወይኑ የክርስቶስ ሥጋና ደም መታሰቢያ ምልክቶች ብቻ ናቸው የሚል ትምህርት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ኅብስቱንና ወይኑን የሚቀበል የክርስቶስን መታሰቢያ ያደርጋል የሚሉ ሲሆን ክርስቶስ በክርስቲያኖቹ ኅሊና እንጂ በኅብስቱና በወይኑ አይገኝም ብለውም ያስተምራሉ፡፡ በእነርሱ እምነት የቁርባን ሥርዓቱ ምልክትና መታሰቢያ ብቻ ነው፡፡ በመጨረሻም ቁርባን የሚባለው የእግዚአብሔር ቃል እንጂ የሚበላና የሚጠጣ አይደለም (Real Absence) የሚል አስተሳሰብ ያላቸው ወገኖችም አሉ፡፡ እኛ ግን አምላካችን ክርስቶስ ያስተማረውንና የሠራልንን የምስጢረ ቁርባን ሥርዓት መሠረት አድርገን በአማናዊው የክርስቶስ ሥጋና ደም (ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሐደው) እናምናለን፡፡

16. ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ለምን ለየብቻ ይዘጋጃል?

ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ለየብቻ እንጂ ተቀላቅሎ አይዘጋጅም፡፡ ይህም የጌታችንን የምስጢረ ቁርባን ትምህርትና የሠራውን ሥርዓት መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ጌታችን “ሥጋዬን የሚበላ” ሲል ቅዱስ ሥጋውን እንድንበላ፣ ከዚያም “ደሜን የሚጠጣ” ሲል ደሙን እንድንጠጣ መናገሩ ነው፡፡ እንዲሁም “ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነው” ብሎ ለይቶ የተናገረው ተለያይቶ እንዲዘጋጅ ነው፡፡ ሥርዓተ ቁርባንን በሠራባት በጸሎተ ሐሙስም በመጀመሪያ ኅብስቱን አንስቶ ባረከና ቆርሶ ሰጣቸው፤ ከዚም ጽዋውን አንስቶ አመስግኖ ስጣቸው፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ለየብቻ ተዘጋጅቶ በመጀመሪያ ቅዱስ ሥጋውን ቀጥሎ ክቡር ደሙን እንቀበላለን፡፡

17.  ሳይገባው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን የሚቀበል ቅጣቱ ምንድን ነው?

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው ሳይገባው (ሳይዘጋጅ) የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም የሚቀበል ዕዳ አለበት፡፡  ካህኑ እንዳወጀው ተጠያቂው ራሱ በድፍረት የተቀበለው ሰው ነው፡፡ የካህኑ አዋጅ የሚጠቅመው “ባለማወቅ ነው የተቀበልኩት” እንዳንልም ነው፡፡ እዚያው ካህኑ ተናግሮታልና፡፡ ይህንን የካህኑን ቃል ተዳፍሮ የሚቀበል ግን ዲያቆኑ እንደተናገረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያሳዝናል፡፡ “ስለበረከት ፈንታ መርገምን ስለኃጢአት ሥርየት ፈንታ ገሃነመ እሳትን ይቀበላል” የድፍረት ኃጢአት ከሁሉ የከፋ ነውና፡፡

18. ጌታችን ሥጋውና ክቡር ደሙን “ለመታሰቢያ አድርጉት” ያለው ምን ማለት ነው?

የድኅነትን ነገር መቀለጃ የሚያደርጉ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ምስጢር ከእምነት በተለየ ደካማ ፍጥረታዊ አዕምሮ ለመረዳት የሚሞክሩ የወንጌል ጠላቶች በወንጌል ያልተጻፈውን አንብበው፣ የተጻፈውን አዛብተው እውነተኛ የክርስቶስ ሥጋና ደም “መታሰቢያ ብቻ” ነው በማለት የማይገባቸውን ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ጌታችን ኅብስቱን ባርኮ ሲሰጣቸው ‹‹ይህ ሥጋዬ›› ነው በማለት ነው እንጂ መታሰቢያ ነው በማለት አይደለም፡፡ ጽዋውንም አንስቶ አመስግኖ ሲሰጣቸው ‹‹ይህ ደሜ ነው›› አላቸው እንጂ መታሰቢያ ነው አላለም፡፡ ሐዋርያት የእምነታችው ጽናት የሚደነቀው ኅብስቱን እያዩት ‹‹ሥጋዬ ነው›› ወይኑንም እያዩት ‹‹ደሜ ነው›› ቢላቸው የሚሳነው ነገር እንደሌለና በግብር አምላካዊ ‹‹አማናዊ ሥጋና ደም›› እንደሚሆን ያለጥርጥር መቀበላቸው ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ለመታሰቢያዬ አድርጉት›› ያለው ዘወትር ምዕመናን ለምስጋና ለመስዋዕት (ሊቆርቡ) በተሰበሰቡ ጊዜ ሞቱን ግርፋቱን ትንሣኤውንና ዕርገቱን እንዲያስታውሱ ለማሳሰብ ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይህንን የሐዋርያትን ትምህርት ሳታፋልስ፣ ሳትጨምርና ሳትቀንስ በቅዳሴ ጊዜ ‹‹ንዜኑ ሞተከ እግዚኦ ወትንሣኤከ ቅድስት/አቤቱ ሞትህንና ቅድስት ትንሣኤህን እንናገራለን›› እያለች ማንሳቷ ለዚህ ጽኑ ምስክር ነው፡፡ ጌታችን ለመታሰቢያዬ አድርጉት ሲል ‹‹ቅዱስ ቁርባንን በተቀበላችሁ ጊዜ የተደረገላችሁን ሰማያዊ ፍቅር አስቡ›› ማለቱ ነው እንጂ ‹‹ቁርባን መታሰቢያ ነው›› ማለቱ አይደለም፡፡ መታሰቢያዬ አድርጉት ማለትና መታሰቢያ ነው ማለት የተለያየ ነው፡፡ ደካማ አዕምሮ ባላቸው ሰዎች አነባበብ ከተወሰደ “መታሰቢያ” የሚል ስያሜ ያላቸው ሰዎች “እውነተኛ አይደሉም” ይባል ይሆን? መታሰቢያ ብቻ ቢሆን ኖሮ ሳይገባው የተቀበለ ሁሉ ዕዳ አለበት አይባልም ነበር፡፡ ብዙዎች ታመዋል፣ አንቀላፍተዋል የተባለው መታሰቢያ የሆነውን ሳይገባቸው ስለተቀበሉ ይሆንን? ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ለመታሰቢያዬ አድርጉት›› የሚለውን ሲያብራራ ‹‹ይህንን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፣ ይህንንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስሚኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና›› በማለት ገልጾታል፡፡ 1ኛ ቆሮ 11፡25-26

19. ካህናት አባቶች ለምን ሥጋውና ክቡር ደሙን ይሸፍኑታል?

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት የጌታችን ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ይሸፈናል፡፡ ይህም ቅዱስ ዮሐንስ የጌታችንን ስዕል ለጢባርዮስ ቄሳር ሲሥል በመጀመሪያ ጌታችንን ልክ እንደተሰቀለ አድርጎ ራቁቱን ነበር የሳለው፡፡ ዮሐንስ የሳለው የጌታችን ሥዕልም አፍ አውጥቶ “በመጀመሪያ አይሁድ በኢየሩሳሌም ራቁቴን ሰቀሉኝ፣ አሁን ደግሞ አንተ ድጋሚ በሮም ራቁቴን ትሰቅለኝን?” ብሎ ተናገረው፡፡ ዮሐንስም እጅግ ደንግጦ ‹‹እንዴት አድርጌ ልሳልህ?›› ብሎ የሳለውን ሥዕል ቢጠይቀው ሥዕሉም “ከለሜዳ አልብሰህ ሳለኝ” አለው፡፡ ዮሐንስም እንዳለው ከለሜዳ አልብሶ ሳለው፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ በከለሜዳ ምሳሌ ይሸፈናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ የፈጣሪያቸውን እርቃን ላለማሳየት ፀሐይ ጨልማ ጨረቃም ደም ለብሳ ነበር፡፡ ይህንንም አብነት በማድረግ ካህናት ሥጋና ደሙን ይሸፍኑታል፡፡

20. ስለምን ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን ደጋግመን እንድንቀበል አስፈለገ? ስንት ጊዜስ እንቁረብ?

ምስጢረ ቁርባን የሚደገም ምስጢር ስለሆነ አንድ ክርስቲያን በሕይወቱ ይህን ያህል ጊዜ ይቁረብ ባይባልም በየጊዜው ግን ንስሐ እየገባ ከመምህረ ንስሐው ጋርም እየተማከረ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሊቀበል ይገባዋል፡፡ ሁሉም ክርስቲያን ሲጠመቅ ቅዱስ ቁርባንን ቢቀበልም ከተጠመቀ በኋላ ለሚሠራው ኃጢአት ማስተስረያ ንስሐ ገብቶ ቅዱስ ቁርባንን መቀበል ያስፈልገዋል፡፡ ባለትዳሮችም በተክሊል ሥርዓታቸው ወቅት ቅዱስ ቁርባንን ቢቀበሉም በትዳር ሕይወታቸውም በየወቅቱ ከመምህረ ንስሐቸው ጋር እየተመካከሩ ንስሐ እየገቡ ቅዱስ ቁርባንን ይቀበላሉ፡፡ ሰው በንስሐ ታጥቦ ቅዱስ ቁርባንን ከተቀበለም በኋላ መልሶ ኃጢአትን ይሠራልና ምስጢረ ቁርባንን ደጋግሞ ይፈጽማል፡፡ ይህንን ያህል ጊዜ ባይባልም በዓመት ውስጥ ክርስቲያኖች ቢያንስ በታላላቅ በዓላት (ልደት፣ ጥምቀት፣ ትንሣኤ…..) መቁረብ ይኖርባቸዋል፡፡

21. ሐዋርያት የቆረቡት ከምግብ በኋላ ምሽት ላይ ሆኖ ሳለ ለምን እኛ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል እንጾማለን?

የዚህ ጥያቄ መንፈስ “ከሐዋርያት ጋር ፉክክር” ያለ ያስመስላል፡፡ በመሠረቱ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንደሚያስተምሩት ‹‹የጸሎተ ሐሙስ ዕለት አስቀድመው የፋሲካውን በግ ከበሉ በኋላ በግብር አምላካዊ አስቀድመው የበሉትን አጥፍቶ ለበረከት ካመጡለት ከኅብስቱና ከወይኑ ከፍሎ “ይህ ሥጋዬ ነው፣ ይህ ደሜ ነው” ብሎ ለውጦ ትኩስ ሥጋ ትኩስ ደም አድረጎ አቁርቧቸዋል›› በማለት አመስጥረው ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሐደው አድርጎ እንደሰጠን አስተምረውናል፡፡ በወንጌል እንደተጻፈ ቅዱስ ዮሴፍ ዘአርማትያስ ጌታችን እንዲቀበርበት የመረጠው መቃብር “በውስጡ ሰው ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበር፡፡” (ዮሐ. 19፡41)  እኛ ደግሞ ስንቆርብ የምንቀበለው ዮሴፍና ኒቆዲሞስ እንደገነዙት ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሐደውን የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም እንደሆነ ቅድስት ቤተክርስቲያን ታስተምራለች፡፡ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በአዲስ መቃብር ጌታችንን እንደቀበሩት ከቅዱስ ቁርባን የሚቀበሉ ምዕመናንንም አፋቸውን ምሬት እስኪሰማቸው (ሆዳቸው ባዶ እስኪሆን) ለ18 ሰዓታት በመፆም እንዲቆርቡ ቅዱሳን አባቶቻችን ሥርዓትን ደንግገውልናል፡፡

22. መስዋዕት የሚባለው ራሱን ቤዛ አድርጎ የተሰቀለው መድኃኔዓለም ወይስ ቅዱስ ቁርባን?

የዚህ ዓይነት ጥያቄ የሚመነጨው በኢየሱስ ክርስቶስና በቅዱስ ቁርባን መካከል ያለውን ግንኙነት ካለመረዳት ነው፡፡ ሥጋ ወደሙን ከኢየሱስ ክርስቶስ ለይቶ ማየት ደግሞ ምስጢረ ተዋሕዶን ያለመረዳት ነው፡፡ በመሠረቱ በሥጋ ወደሙና በጌታችን መካከል ስላለው ግንኙነት ያስተማረን ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እንዲህ ሲል ‹‹እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፡፡ ጽዋውንም አንስቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፡- ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ ስለብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈሰ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው፡፡›› ማቴ 26፡ 26 ታዲያ ራሱ ጌታችን የነገረንን ትተን የሰዎችን ፍልስፍናና ተረት እንቀበልን? እኛስ የምንቀበለው ቅዱስ ቁርባን ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ሆኖ የተገለጠ የመድኃኔዓለም የኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊ መሥዋዕት መሆኑን በፍጹም ሃይማኖት እንቀበላን፡፡ ይህ ግን የምንመገበው የተሰዋው አንድ ጊዜ ነው፡፡ አሁንም የምንሳተፈው ከዚያው አንድ ጊዜ በርሱ በራሱ ከቀረበው ሆኖ አምነው በመቅረብ ግን ዘወትር ለሚመገቡትም የዘላለም ሕይወትን የሚያስገኝ ነው፡፡

23. ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰው የነሳውን ሥጋ እንዴት ‹‹እንዴት የአምላክ ሥጋ የአምላክ ደም›› እንለዋለን?

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ነፍስን የነሣው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ረቂቅ የሆነው መለኮት የሰውን ሥጋና ነፍስ ፍጹም ስለተዋሐደና በተዋሕዶ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ስለሆነ የሥጋ ገንዘብ የመለኮት ሆነ፤ የመለኮትም ገንዘብ ለሥጋ ሆነ፡፡ ቃል ሥጋ ሆኖአልና፡፡  ስለዚህ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነፍስ ስለተለየው እንደሚፈርስ፣ እንደሚበሰብስ የፍጡር አካል አይደለምና፡፡ ‹‹የአምላክ ሥጋ የአምላክ ደም›› እንለዋለን፡፡

24. “ኢየሱስ ይፈርዳል፣ ሥጋውና ደሙ ያማልደናል” የሚሉትስ እንዴት ይታያል?

በፕሮቴስታንታዊ አስተምህሮ የደነዘዙ ሰዎች ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከማዳን፣ ከቤዛነት ስራው ፍጻሜ በኋላም “አማላጅ”  እንደሆነ አድርገው ይናገራሉ፣ ያስተምራሉ፡፡ ለዚህም እንዲረዳቸው የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብና ያበላሻሉ፣ ትርጓሜውን ይለውጣሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ከሚታወቁባቸው አስተምሮዎቻቸው መካከል ቀደምት አበው ያቆዩዋቸውን አዋልድ መጻሕፍት በውኃ ቀጠነ መተቸት  አንዱ ነው፡፡ ምንም እንኳ አዋልድ መጻሕፍትን የሚጠሉና የሚንቁ ቢሆኑም “ሰይጣን ላመሉ መጽሐፍ ቅዱስን ይጠቅሳልና” እነርሱም ለክህደታቸው የሚመች ከመሰላቸው የአዋልድ መጻሕፍትንም አጣምመው ለመጠቀም ይሞክራሉ፡፡ በዚህ አግባብ ከሚጠቅሷቸው ደገኛ የቤተክርስቲያን መጻሕፍት አንዱ ቅዳሴ ሐዋርያት ነው፡፡ “ኢየሱስ ያማልዳል” የሚለውን አዘምነው “ኢየሱስ በዙፋኑ ተቀምጦ እንደሚፈርድ እናውቃለን፤ያማልዳል የምንለው በሥጋውና በደሙ(በቅዱስ ቍርባን) ነው” ይላሉ

ለዚህም የሚጠቅሱት ንባቡን እንጂ ትርጓሜውን ሳይመለከቱ “ስለ እኔ በቀራንዮ የፈሰሰ ንጹሕ የሚሆን የመሢሕም ደም እነሆ ስለ እኔ ይጮኻል፤ ይህ የሚናገር ደም የእኔን የባሪያህን ኃጢአት የሚያስተሰርይ ይሁን” የሚለውን ነው። ይህ ገጸ ንባብ የሚገኘው በቅዳሴ ሐዋርያት ቍጥር 106 ላይ ነው። የቅዳሴው አንድምታ ትርጓሜ ግን “የሚጮህ የሚካሰስ ዋጋ እንደሚያሰጥ ዋጋዬን (የዘለዓለም ሕይወትን) ይሰጠኛል ማለት ነው” ብሎ ምሥጢራዊ መልእክቱን ነግሮናል። ምክንያቱም ጌታችን “ሥጋዬን የሚበላ፥ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው”ብሎናልና ነው (ዮሐ 6፡53)።  በቅዳሴው “የሚጮህ ደም የሚናገር ደም”ተብሎ የተነገረው ሥጋውና ደሙ (ቅዱስ ቍርባን) ነፍስ የተለየው መለኮት ግን የተዋሐደው ሕያውና ዘለዓለማዊ መሆኑን ለመመስከር ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ “በሥጋ ሞተ በመንፈስ (በመለኮት) ግን ሕያው ሆነ (ነፍስ ሥጋን እንደተለየችው ሕያው መለኮት አልተለየውም)” ያለው ይኼንን ነው (1ኛ ጴጥ 3፡18)።  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡-የክርስቶስ ሥጋውና ደሙ መለኮት የተዋሐደው መሆኑን ሲመሰክር “የእግዚአብሔር ደም” ብሎአል (የሐዋ፡20፡28)።

ለመሆኑ “ኢየሱስ ይፈርዳል፥ ሥጋውና ደሙ ያማልዳል፤” ማለት ምን ማለት ነው? በእርሱና በሥጋ ወደሙ መካከል ልዩነት አለ እንዴ? እርሱ ሌላ፥ሥጋውና ደሙ ደግሞ ሌላ ነው? እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ አንዱን ክርስቶስ ለሁለት ከፍለው (በተዋህዶ ከሁለት አካል አንድ አካል፥ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ የሆነውን አንዱን ክርስቶስ ሁለት ባሕርይ አድርገው) በሥጋው ወደ ሠርግ ቤት ተጠራ፤ በመለኮቱ ደግሞ በተአምር ውኃውን ወደ ወይን ጠጅነት ለወጠ” እንደሚሉ ውጉዛን ካቶሊካውያን መሆን ነው። ምክንያቱም ወደ ሠርግ ቤት የተጠራውም ተአምር ያደረገውም ከተዋህዶ በኋላ መለየት የሌለበት አንዱ ክርስቶስ ነው። እኛም የምንቆርበው በተዋህዶተ መለኮት የከበረውን፥ የአንዱን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋና ደም ነው፤ እርሱም የዘለዓለምን ሕይወት የሚሰጥ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡-“የምንቆርበው ቅዱስ ቍርባንበዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ ከተቆረሰው የክርስቶስ ሥጋና ደም ጋር አንድ ነው” ያለው ለዚህ ነው። 1ኛ ቆሮ 11፡29

25. ሰዎችን ሥጋውንና ደሙን እንዳይቀበሉ የሚያደርጓቸው ምክንያቶችና መፍትሔዎቻቸው ምንድን ናቸው?

ክርስቲያኖችን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እንዳይቀበሉ የሚያደርጓቸው ብዙ ምክንቶች ቢጠቀሱም ባለመቀበል የቀረውን ዋጋ ግን ሊመልሱት አይችሉም፡፡ ብዙውን ጊዜ የሚጠቀሱት ምክንያቶች ስለቅዱስ ቁርባን በሚገባ አለመረዳት፣ መቅሰፍት ያመጣብኛል ብሎ መፍራት፣ ከኃጢአት አልተለየሁም (አልበቃሁም) ማለት፣ ከቆረብኩ በኋላ መልሼ ኃጢአት እሠራለሁ ማለት፣ እንዲሁም ስሸመግል እቀበላለሁ ማለት እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ኢየሱስም በሰማ ጊዜ አላቸው። የታመሙ እንጂ ጤነኞች ባለ መድኃኒትን አይሹትም። ነገር ግን ሂዱ እወቁትም ይህ ምንድር ነው ኃጥአንን ወደ ንስሓ ልጠራ መጣሁ እንጂ ጻድቃንን ለመጥራት አልመጣሁምና” (ማቴ.9:12-13) እንደተባለው ይህ መድኃኒት ለታመሙት ነውና ከምክንያተኝነት ወጥተን ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን ልንቀበል ይገባል፡፡

ክርስቲያን ስለ ምስጢረ ቁርባን የሚማረውና የሚያውቀው በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ ራሱን እንዲያዘጋጅና ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብሎ የዘላለም ሕይወትን እንዲወርስ ነው፡፡ “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው” እንደተባለ ሥጋውን የሚበላ ደሙንም የሚጠጣ በክርስቶስ ይኖራል፡፡ ሥጋውን ያልበላ ደሙንም ያልጠጣ ግን ለዘለዓለም የዘላለም ሕይወትን አያይም፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል እንጂ ላለመቀበል ምክንያትን ማቅረብ የዘላለም ሕይወትን አያሰጥምና ሁሉም ክርስቲያን ንስሐ እየገባ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሊቀበል ይገባዋል፡፡ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ቤዛ ያደረገ፣ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ያዳነን፣ በዕለተ አርብ በቀራንዮ አደባባይ ራሱን ከአዳም ጀምሮ እስከ ዓለም ፍጻሜ ላሉ ሰዎች ሁሉ ቤዛ፣ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበ፣ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በቤተክርስቲያን  መሥዋእት ህልው ሆኖ የሚኖር፣ በደላችንን የሚያጠፋ፣ መሥዋዕታችንን የሚቀበል ልዩ የሐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን በዘላለም ሕይወት ለመኖር ርስታችን መንግስተ ሰማያትን እንወርስ ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ አሜን፡፡

1 thought on “ምስጢረ ቁርባን፡ የቤተክርስቲያን ምስጢራት አክሊል (ክፍል 2)

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s