በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን
አነ ውእቱ ኖላዊ ኄር – ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ። ዮሐ 10፡11
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የበዓላት ቀኖና መሠረት ከህዳር 15 እስከ ጌታችን ልደት (ታህሳስ 28/29) ድረስ ያለው ወቅት በዘመነ ብሉይ የነበሩ ቅዱሳን ነቢያት የጌታን ልደት በተስፋ እየጠበቁ የገቡትን ሱባኤ፣ የጾሟቸውን አጽዋማት በማሰብ ልዩ ልዩ ክብረ በዓላት ይከበራሉ። ለእያንዳንዱ በዓልም የተለየ የቅዱሳት መጻሕፍት ንባብና ትርጓሜ፣ የተለየ የምስጋና መዝሙር ይዘመራል። በጾመ ነቢያት ውስጥ ያሉት የመጨረሻዎቹ ሦስት ሣምንታት በተለየ መልኩ ይከበራሉ። ወቅቱም ትንቢተ ነቢያትን በማሰብ ዘመነ ስብከት ይባላል። የነቢያት የስብከታቸው ማዕከል የክርስቶስ ሰው የመሆን ተስፋ ነውና።
የዘመነ ስብከት የመጀመሪያው ሣምንት ስብከት ይባላል፤ ሁለተኛው ሣምንት ብርሃን ይባላል፤ ሦስተኛው ሳምንት ኖላዊ ይባላል። ኖላዊ ማለት ጠባቂ ማለት ሲሆን ቅዱሳን ነቢያት እውነተኛው ጠባቂ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ይገለጣል ብለው በትንቢት መናገራቸውና ኢየሱስ ክርስቶስም ቸር ጠባቂ መሆኑን እያሰበች ቤተክርስቲያን የምትዘምርበት፣ የምታመሰግንበትና የምታስተምርበት ዕለት በመሆኑ ኖላዊ ተብሎ ተሰይሟል። በዚህ ዕለት ጌታችን በወንጌሉ እርሱ ቸር ጠባቂ እንደሆነ ያስተማረበት ዮሐ 10፡1-22 ያለው የወንጌል ክፍል ይነበባል፣ ከተያያዥ የቅዱሳት መጻሕፍት ምስጢራት ጋርም ይሰበካል፣ ይተረጎማል።
የዚህ የጌታችን ትምህርት መነሻ ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ወደ በጎች ስፍራ በበሩ የማይገባ በሌላም በኩል የሚገባ ሌባ፥ ወንበዴም ነው፤ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች ጠባቂ ነው። ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰሙታል፥ የራሱንም በጎች በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ አውጥቶም ያሰማራቸዋል። ሁሉንም አውጥቶ ባሰማራቸው ጊዜ በፊት በፊታቸው ይሄዳል፥ በጎቹም ቃሉን ያውቃሉና ይከተሉታል፤ ከሌላው ግን ይሸሹታል እንጂ አይከተሉትም፥ የሌላውን ቃሉን አያውቁምና(ዮሐ 10፡1-5)። ›› የሚለው ነው።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ‹‹ቸር ጠባቂ›› የተባውን ትምህርት ስለ ሦስት ምክንያቶች አስተምሯል። የቸር ጠባቂ መገለጫዎችን ለይቶ ለማሳወቅ፤ የቸር ጠባቂና የምንደኛን ልዩነት ለማስረዳትና ቸር ጠባቂ እርሱ መሆኑን ለመግለጽ ያስተማረው ነው። በትምህርቱም ሰባት የቸር ጠባቂ መገለጫዎችን አስቀምጧል። እነዚህም፡-
ቸር ጠባቂ በበሩ ይገባል፤ በበሩም ይወጣል።
ቸር ጠባቂ ወደ በጎች በረት በበሩ ብቻ ይገባል፤ በበሩም ብቻ ይወጣል። በጎቹን ከበረታቸው አውጥቶ ሊያሰማራ በግልፅ በበሩ ይገባል፤ ይዟቸውም በግልፅ (በብርሃን) በበሩ ይወጣል። የሌሊት ጠባቂውም ይከፍትለታል። ሌባ ግን አጥር ጥሶ ቅጥር አፍርሶ ይገባል እንጂ በበሩ አይገባም፤ እንደዚያውም ይወጣል። በጨለማ ይገባል እንጂ በግልፅ (በብርሃን) አይገባም። ምንደኛ መምህርም እንደዚሁ እምነትን አጉድሎ ሥርዓትን አፍርሶ ወደ ቤተክርስቲያን በተንኮል ይገባል።
የበጎች በር የተባለውም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በእርሱ ያላመነ (በበሩ ያልገባ) እውነተኛ ጠባቂ ሊሆን አይችልምና። እምነትን ሥርዓትን ያልጠበቀ እውነተኛ ጠባቂ ሊሆን አይችልም። በበሩ የገባ (ተመስክሮለት የመጣ) በበሩም መግባትን ያስተማረን ጠባቂ እርሱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የክርስቶስን አርዓያ የተከተሉ ደገኛ መምህራንም በበሩ ይገባሉ፤ በበሩ ይወጣሉ።
ቸር ጠባቂ በጎቹን ያውቃቸዋል፤ እነርሱም ያውቁታል።
ቸር ጠባቂ በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል። እነርሱም ድምፁን ይሰሙታል፤ ያውቁታልም። በትክክለኛው ስማቸው (ግብራቸውን በሚገልፅ) ይጠራቸዋል። እነርሱም ድምፁን ስለሚያውቁ ይሰሙታል። ቃሉን (አስተምህሮውን) ያዉቁታል። ወንበዴ ግን የበጎቹን ስም ከቶ አያውቅም፤። በጎቹም ድምፁን አያውቁትም። እንደ ይሁዳ ዘገሊላ እንደ ቴዎዳስ ዘግብፅ ያሉት እንደዚህ ሐሰተኛ ጠባቂዎች ነበሩ (ሐዋ 5፡33-39)። አስተምህሮአቸው ከእግዚአብሔር ስላልሆነ ለጊዜው ተከታይ ቢያገኙም ምዕመናን አልሰሟቸውም። እነርሱም ጊዜአቸው ሲደርስ ጠፍተዋል። በጎቹን የሚያውቅ እነርሱም ድምፁን የሚያውቁት እውነተኛ እረኛችን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ‹‹ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ፥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ፥ አድምጥ፤ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፥ ተገለጥ (መዝ 79፡1)።›› እንደተባለ የቤተክርስቲያን ጠባቂዋ እርሱ ነው። የክርስቶስን አርዓያ የተከተሉ ደገኛ መምህራንም በጎች የተባሉ ምዕመናንን ሐዋርያዊ ትምህርትን እያስተማሩ በምግባር በሃይማኖት ያጸኗቸዋል።
ቸር ጠባቂ በጎቹን ይመራቸዋል፤ እነርሱም ይከተሉታል።
ቸር ጠባቂ በበጎቹ ፊት ፊት ይሄዳል። እነርሱም እርሱን እየተከተሉት ይሄዳሉ። እርሱ ቀድሞ በጎቹ ይከተሉታል። ወደ መሰማርያችውም ይመራቸዋል። አንድ በግ ቢቀርበት ወይም ቢጠፋበት እንኳን ሌሎቹን ትቶ የጠፋውን ይፈልጋል (ሉቃ 15፡2ሌባ ግን ከበጎቹ ኋላ ኋላ ይሄዳል፤ በጎቹንም ሊሠርቅ ከኋላ ሆኖ በጎቹን በአይነ ቁራኛ እየተመለከተ ይከተላል። በጎቹ ቢጠፉም አይገደውም፤ ሊሠርቅ እንጂ ሊመራቸው አልመጣምና። እኛን ወደ ለመለመ መስክ የሚመራን እኛም ድምፁን ሰምተን የምንከተለው እውነተኛ ጠባቂያችን እርሱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
የሰቡትና የወፈሩት አንዳንድ በጎች፣ ምስኪኖችንና የከሱትን በጎች እየገፉ ከበረት ሲያስወጡአቸው፣ በቀንዳቸው ሲወጉአቸው፣ ሲያቆስሉአቸው፣ ሲያደሙአቸው፣ የሚጠጡትን ውኃ ሲያደፈርሱባቸው፣ ምግባቸውን ሲረግጡባቸው እያዩ ከመቀመጫቸው ላለመነሳት ዝም ብለው እንደሚያዩ ምንደኞች ያይደለ እውነተኛ እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የክርስቶስን አርዓያ የተከተሉ ደገኛ መምህራንም በጎች የተባሉ ምዕመናንን በእውነተኛ ትምህርት ይጠብቋቸዋል። ምንደኛ የሆኑ ክፉ መምህራን ግን በጎች የተባሉ ምዕመናንን አቁስለውና አድምተው ከበረት ያወጧቸዋል፤ በሌሎች ፈተናዎች ምዕመናንን ከመጠበቅ ቸል ይላሉ።
ቸር ጠባቂ በጎቹን ይጠብቃል፤ ይንከባከባቸዋልም።
ቸር ጠባቂ በጎቹን ከክፉ ሁሉ ይጠብቃል፤ የሚያስፈልጋቸውንም ነገር ሁሉ ያውቃል። ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማቸዋል። የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል (ኢሳ 40፡11)። ጭቃውን ሳይጠየፍ ይሸከማቸዋል፤ ይንከባከባቸዋል (ሉቃ 15፡6)። ምንደኛ የሆነ እረኛ ግን የራሱን ፍላጎት እንጂ የበጎቹን ፍላጎት አያውቅም፤ እነርሱም አያውቁትም። በጎቹን ይበትናቸዋል፤ በጎቹን ይጠቀምባቸዋል እንጂ አይጠብቃቸውም፤ አይጠቅማቸውምም። ጠፍተን ሳለ የፈለገን የሚንከባከበንና የሚመግበን ቸር ጠባቂያችን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
እንደ ምንደኛ (ቅጥረኛ) በጎቹን በማሰማራት ፈንታ ወደ እረፍት መስክ ራሱን ያላሰማራ፤ በአደራና በጠባቂነት የተሰጣቸውን በጎች እያረዱ እየበሉ አውሬ በላቸው እንደሚሉ ቅጥረኞች ያይደለ፤ በጎች እሰከሚበርዳቸው ድረስ ያለ አግባብ ፀጉራቸውን እንደሚሸልቱ ቅጥረኛ ያልሆነ፤ ታማሚ በጎችን እንዳላከሙ፤ ደካሞችን እንዳላዳኑ፤ ሰባራዎችን እንዳልጠገኑ፤ የጠፉትን በጎች ወደ መንጋው በመመለስ ፈንታ ወሬያቸውን በመሰለቅ በወንበራቸው ተቀምጠው እንዳልሰበሰቡ እረኞች ያይደለ የጠፉትን የሚሰበስብ የቤተክርስቲያን ጠባቂዋ እርሱ ነው።
ቸር ጠባቂ ለበጎቹ መልካም መሰማርያን ያዘጋጃል፤ ያሰማራቸዋልም።
ቸር ጠባቂ በጎቹን በመልካም ስፍራ ለማሰማራት መሰማርያን ያዘጋጃል። ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ የሚያሳጣኝም የለም፤ በለመለመ መስክ ይመራኛል(መዝ 22፡1)።›› እንዳለው ቸር ጠባቂ በጎቹን በለመለመ መስክ ያሰማራቸዋል። ‹‹በሙሴና በአሮን እጅ ህዝብህን እንደ በጎች መራሀቸው›› መዝ 76፡20 እንደተባለም በበጎ ይመራል። የለመለመ መሰማርያ የተባለም የቤተክርስቲያን መንፈሳዊ የአገልግሎት ዘርፍ ነው።
ምንደኛ ግን ራሱን ያሰማራል። በትንቢተ ሕዝቅኤል በምዕራፍ 43 ቁጥር 2 ላይ እንደተገለፀው ክፉ እረኛ ራሱን በበጎቹ መካከል ያሰማራል። ጠቦቶቹንም ያርዳቸዋል፤ ይበላቸዋልም። ‹‹ጮማውን ትበላላችሁ፤ ጠጉሩንም ትለብሳላችሁ፤ የወፈሩትንም ታርዳላችሁ፤ በጎቹን ግን አታሰማሩም (ሕዝ 34፡23)።›› እንዳለ መሰማርያውንና ውኃውን ይረግጣል፤ ያፈርሳልም። ለራሱና ለራሱ ብቻ መሰማርያን ያዘጋጃል። ለእኛ ግን ለነፍስም ለሥጋም የሚሆን መሰማርያን የሚያዘጋጅልን እርሱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ቸር ጠባቂ በጎቹን ያበዛል።
ቸር ጠባቂ በበረት ያሉትንና በውጭ ያሉትን በጎች አንድ ለማድረግ ይተጋል። በውጭ ያሉትን በጎች ወደ በረት ለማስገባት ሌትና ቀን ይሠራል። ይህንንም መርህ በማድረግ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን ለዓለም በመስበክ በጎችን አብዝተዋል። ቅጥረኛ ግን በውጭ ያሉት በጎች በዚያው ቢቀሩ አይገደውም። በበረት ያሉትንም ጭምር በመከፋፈል ከበረት አስወጥቶ ይበትናል። እርሱ ስለራሱ ጥቅም እንጂ ስለበጎቹ ምንም የማይገደው ምንደኛ ነውና። ነገር ግን ‹‹የማሰማሪያዬን በጎች ለሚያጠፉና ለሚበትኑ እረኞች ወዮላቸው (ኤር 23፡1)።›› እንደተባለ በመጨረሻው ቀን መጠየቁ አይቀርም። እኛ ግን የጠፉትን የሚፈልግ፣ ያሉትን የሚያፀና እውነተኛ ጠባቂያችን እርሱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብለን እናምናለን።
ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት ‹‹እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳና ድብ ይመጣ ነበር፥ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር። በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር፥ ከአፉም አስጥለው ነበር፤ በተነሣብኝም ጊዜ ጕሮሮውን ይዤ እመታውና እገድለው ነበር (1ኛ ሳሙ 17፡34)። ›› እንዳለው ከዲያብሎስ ጉሮሮ ከአንበሳም መንጋጋ ያዳነን እውነተኛው ጠባቂያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ቸር ጠባቂ ስለበጎቹ መስዋእት ይሆናል።
ቸር ጠባቂ ራሱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል። ተኩላ ሲመጣ ጥሎ አይሸሽም፤ ከበጎቹ ቀድሞ ይዋጋል እንጂ። ‹‹ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከማኖር ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም (ዮሐ 15፡13)።›› እንደተባለ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ መስዋእት ይሆናል። ምንደኛ ግን በጎቹን ስለ ራሱ አሳልፎ ይሰጣል። ተኩላ ሲመጣም በጎቹን ጥሎ ይሸሻል፤ በጎቹም ለምድር አራዊት መብል ይሆናሉ።
‹‹ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ። ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል። ጠባቂ ያይደለ፥ በጎቹም ገንዘቡ ያልሆኑ ምንደኛ ግን ቅጥረኛ ግን ተኵላ ሲመጣ ባየ ጊዜ በጎቹን ትቶ ይሸሻል፤ ተኵላም መጥቶ በጎቹን ይነጥቃቸዋል፤ ይበትናቸዋልም። ምንደኛስ ይሸሻል፤ ስለ በጎቹም አያዝንም፤ ምንደኛ ነውና። ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፥ የእኔ የሆኑትን መንጋዎቼን አውቃለሁ፡፡ የእኔ የሆኑትም ያውቁኛል፡፡ አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን አውቀዋለሁ፤ ለበጎች ቤዛ አድርጌ ሰውነቴን አሳልፌ እሰጣለሁ (ዮሐ 10፡11-15)።›› እንዳለ ነፍሱን ስለ በጎቹ አሳልፎ የሰጠ እውነተኛ ጠባቂያችን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ እንደተናገረው ቸር ጠባቂ እርሱ ነው፤ በዘላለም ኪዳን ደም ለበጎቹ ትልቅ ጠባቂ የሆነው እርሱ ነው (ዕብ 13፡20)። የነፍሳችን ጠባቂ የሆነው እርሱ ነው (1ኛ ጴጥ 2፡23)። የእስራኤል ዘነፍስ ጠባቂ የሆነውም እርሱ ነው (መዝ 79፡1)። እውነተኛም ጠባቂ እርሱ ነው (ዮሐ 10፡7)።
በጎችን የመጠበቅ ኃላፊነትና ተጠያቂነት
በጎችን የመጠበቅ ኃላፊነት ከተጠያቂነት ጋር አብሮ ለጠባቂዎች (ለሐዋርያትና ከሐዋርያት ቀጥሎ እስከ ዕለተ ምጽዓት ለሚነሱ እውነተኛ መምህራን) ተሰጥቷል። ‹‹ግልገሎቼን አሰማራ፤ ጠቦቶቼን ጠብቅ፤ በጎቼን አሰማራ።›› ብሎ የመጠበቅ ኃላፊነትን በጴጥሮስ በኩል ለሐዋርት ሰጥቷል (ዮሐ 21፡15-17)። ‹‹በጎቼን ከጠባቂዎች እጅ እፈልጋለሁ›› ብሎም በጎችን የመጠበቅ አገልግሎት ተጠያቂነትም እንዳለበት ተናግሯል (ሕዝ 34፡10)። በጎች (ምዕመናን) የክርስቶስ ተከታዮች እንጂ የእረኞቹ ተከታዮች አይደሉም፤ ጠባቂዎችም ባለአደራዎች እንጂ የበጎቹ ባለቤቶች አይደሉምና።
ዛሬስ የጠባቂዎች ድርሻ ምንድን ነው?
ጌታችን እንዳስተማረው የጠባቂዎች (የካህናትና የመምህራን) ድርሻ የሚከተሉትን ያጠቃልላል።
- በበሩ መግባት፡- በተዋሕዶ ላይ መመሥረት፣ በሥርዓት መመራት፣ በእምነት መኖር
- በጎቹን ማወቅ፡- በግና ተኩላን ለይቶ ማወቅ፣ የራስንና የሌላውን ለይቶ ማወቅ፣ ለበጎቹም ግልፅ መሆን
- በጎቹን መጠበቅ፡- በጎችን ነቅቶ መጠበቅ (እንዳይነጠቁ)፣ ባክነው እንዳይጠፉ መንከባከብ
- መሠማርያውን ማዘጋጀት፡- የሚያስፈልጋቸውን ትምህርት፣ ተግሳፅና ምክር መስጠት
- በመልካም ስፍራ ማሰማራት፡- ከፊት ሆኖ በመምራት (በማገልገል) ለሥጋ ወደሙ ማብቃት
- አንድነትን ማጠናከር፡- ከውጭ ያሉትን በማምጣትና ከውስጥ ያሉትን በማፅናት አንድነትን ማጠናከር
- መስዋዕትነትን መክፈል፡- እውነትን በመመስከር መልካም አርአያ መሆን
የበጎች (የተጠባቂዎች) ድርሻስ ምንድን ነው?
በጌታችን ትምህርት መሠረት በጎች (ተጠባቂዎች) ጠባቂያቸውን በሚገባ ድምፁን ማወቅና እርሱንም መከተል፣ እውነተኛ ጠባቂ ያልሆነውን (ክፉውን እረኛ ወይም ምንደኛውን) መለየትና ከእርሱም መራቅ፣ ዛሬ እውነተኛ የሆነው ጠባቂያቸው ወደ ምንደኛነት ቢቀየር እንኳን ቶሎ ነቅቶ መለየት መቻልና ራሳቸውንም መጠበቅ ይኖርባቸዋል። እውነተኛና ቸር ጠባቂያችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም በጎች ያድርገን፤ አርአያ የሚሆኑ ደገኞች ጠባቂዎችንም አያሳጣን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር