እንኳን ለዘመነ አስተርእዮ በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን፡፡
በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን የበዓላት ቀኖና መሠረት ከልደተ ክርስቶስ እስከ ዐቢይ ፆም መግቢያ ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ አስተርእዮ (የመገለጥ ዘመን) በመባል ይታወቃል፡፡ ዘመነ አስተርእዮ አራት ዓበይት በዓላትን ማለትም የጌታችን ልደት፣ የጌታችን ጥምቀት፣ የቃና ዘገሊላ ተዓምርና የእመቤታችን ዕረፍት ያጠቃልላል፡፡ ዘመን የማይቆጠርለት፣ ይህን ያህላል፣ ይህን ይመስላል የማይባል ጌታ ከድንግል በሥጋ ተወልዶ ስለተገለጠ፣ ለዘመናት በእምነት ካልበሰሉ ምዕመናን አዕምሮ ተሰውሮ የነበረ የሥላሴ ኀልወት (ምስጢረ ሥላሴ) በጌታ ጥምቀት በዮርዳኖስ ወንዝ በገሃድ ስለታየ፣ በሥጋ ማርያም የተገለጠ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለ30 ዓመታት በግልጥ ሳያስተምር በየጥቂቱ አድጎ በቃና ዘገሊላ አምላክነቱን ስለገለጠ፣ ቤተክርስቲያናችን ይህንን ወቅት ዘመነ አስተርእዮ ትለዋለች፡፡
የጌታችን ጥምቀት በዘመነ አስተርእዮ ከሚከበሩት የአደባባይ በዓላት ውስጥ ቀዳሚው ነው፡፡ ጥምቀትን ስናከብር ሁሉም እንደተሰጠው ጸጋ በደስታ በማመስገን መሆን ይኖርበታል፡፡ በልዩ ልዩ ባህል ሆ! በማለት ታቦትን አክብሮ ማጀብ ከዘመነ ብሉይ ጀምሮ የነበረ ትውፊት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ “የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ሰፈር በገባች ጊዜ እስራኤል ሁሉ ታላቅ እልልታ አደረጉ፤ ምድሪቱም አስተጋባች” (1ኛ ሳሙ. 4፡5) “ዳዊትና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ በዜማ መሣሪያዎች በበገናና በመሰንቆ፣ በከበሮና በነጋሪት፣ በጸናጽልና በዕንዚራ በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር” (2ኛ ሳሙ. 6፡5) “ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ ሆ እያሉ ቀንደ መለከትም እየነፉ የእግዚአብሔርን ታቦት አመጡ” (2ኛ ሳሙ. 6፡15) መዝሙር መዘመር ያልለመድን ምዕመናን እንደየባህላችን ሆ! እያልን ታቦታቱን ብናከብር እንከብርበታለን፡፡
ከዚያም ባሻገር እንደ እናቶች ልማድ በቅንቀና “እሰይ ስለቴ ሰመረ፣ ነይ ነይ እምዬ ማርያምና የመሳሰለውን በመዘመር ብናገለግል ዋጋ እናገኝበታለን፡፡ እነዚህ ሁለቱ ከመደበኛ የቤተክርስቲያን አገልጋይ ካህናትና ሰንበት ተማሪዎች ውጭ ያሉ ምዕመናን ሲያደርጓቸው ደስ ያሰኛል፡፡ እስራኤል ዘሥጋ እንደየችሎታቸው ከንጉሥ እስከ ጭፍራ በታቦቱ ፊት እንደየአቅማቸው አመሰገኑ እንጅ ምስጋናን ለሌዋውያን ብቻ ትተው አምላካቸውን በሚመሰግኑበት ቀን ተመልካች አልሆኑም፡፡ እንደዚሁም ጥምቀት ሁሉም በየችሎታው እግዚአብሔርን የሚያመሰግንበት እንጅ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ልብሰ ተክህኖና የሰንበት ትምህርት ቤት ዩኒፎርም ለብሰው ለተመልካች የሚያቀርቡበት አውድ አይደለም፤ መሆንም የለበትም፡፡ መዝሙር ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ምስጋና ነው እንጂ ለታደመው ሰው የሚቀርብ ትርኢት ስላልሆነ ሁሉም እንደየጸጋው ፈጣሪውን ሊያመሰግን ይገባዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ መደበኛ መዘምራን ከሌላው ምዕመን የበለጠ ኃላፊነት እንዳለባቸው ሊያስተውሉ ይገባል፡፡ የአንዲት ሀገር ሹመኞች የሚያደርጉት በጎ ሥራ ሀገርን የሚያስመሰግን፣ ያልተገባ ስራቸውም ሀገርን የሚያስነቅፍ እንደሆነ ሁሉ ሳይገባው በቤቱ ለአገልግሎት የተጠራ ሁሉ አገልግሎቱን በጥንቃቄ ሊፈፅም ይገባዋል፡፡ የባህል ሆታዎችንና ቅንቀናዎችን ለሚያምርባቸው ለምዕመናን ሲሆኑ የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያን ደግሞ በአቅማቸው የቤተክርስቲያንን ቀኖና ተከትለው ወቅታዊ የዘመነ አስተርዕዮ መዝሙራትን በመዘመር በዓሉን ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የዘመነ አስተርእዮ መዝሙራት ለዘመነ አስተርዮ የሚስማሙና የቤተክርስቲያንን ጥልቅ ምስጢራት የያዙ መሆናቸውን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ “ባለቤቱ ያቃለለውን አሞሌ የሚያከብረው የለም” እንደሚባለው አገልጋዮች የቤተክርስቲያንን ሥርዓት ሳይጠብቁ ሌላ ሲያቃልለው ለማስጠበቅ “ዘራፍ!” ማለት ብቻ ሞኝነት ይሆናል፡፡
በዘመናችን ግን አንዳንዶች አገልጋዮች ባለማወቅ፣ አንዳንዶች የሚደምቅላቸው ስለማይመስላቸው፣ ሌሎች ደግሞ የሲዲ ሽያጭና የሞቅ ሞቅ ጫጫታ ህሊናቸውን አውሮት በጥምቀት ዕለት ከበዓሉ ምስጢር ጋር የማይያያዙ፣ የቤተክርስቲያንን ወግና ሥርዓት የሚያደበዝዙ የሽያጭ “መዝሙራትን” ሲያቀርቡ ማየት እየተለመደ ነው፡፡ ይህን መርህ አልባ አዳማቂነት በተቻለ መጠን ለመቀነስ ይቻል ዘንድ የዘመነ አስተርዕዮ መዝሙራትን ከነትርጉማቸው ምዕመናን እንዲያውቋቸው ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ በጥምቀት ሰሞን የሚዘመሩት የጥምቀት መዝሙራት ብቻ ሳይሆኑ፣ ልደቱን፣ ጥምቀቱን፣ የቃና ዘገሊላ ተዓምራቱን የሚያዘክሩ ናቸው፤ ምስጢራቸው የተያያዘ ነውና፡፡ የመዝሙሮቹን ምስጢር የተረዳ ሰው የቤተክርስቲያን የሆነውን አምሃ ትቶ የግለሰቦችንና የቡድኖችን ጨዋታ ሲፈልግ አይውልም፡፡
ስለሆነም ሁላችንም አቅም በፈቀደ መጠን የዘመነ አስተርእዮ መዝሙራትን በመዘመር፣ ይህን ማድረግ የማንችል ደግሞ ባህላዊ ሆታዎችን ወይም ቅንቀናወችን እያቀረብን ብናከብረው መልካም ይሆናል፡፡ ሌዋውያንን እንዲመስሉ የሚጠበቅባቸው መደበኛ አገልጋዮች (ሰንበት ት/ቤትን ጨምሮ) ሆ! ሲሉ አልለመድንም፣ አልተማርንም፣ አባቶቻችንም አላሳዩንም፡፡ ስለሆነም መደበኛ አገልጋዮች በደመቀበት ከመዋል አባቶቻችን እንዳስተማሩን ያሬዳዊ የሆኑትን የዘመነ አስተርእዮ መዝሙራትን በአንድነት በመዘመር የቅዱስ ያሬድ በረከት እንዳያመልጠን እንትጋ፡፡ የተባረከ ዘመነ አስተርዕዮ ለሁላችን፡፡
ይህ የአስተምህሮ ጦማር እይታ ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ የታያችሁን አካፍሉ፡፡ “ኩሎ አመክሩ፤ ወዘሰናየ አጽንዑ/ሁሉን መርምሩ፤ መልካም የሆነውን ያዙ” እንደተባለ ከመረመርን በኋላ መልካም የሆነውን እንይዛለን፡፡ ምርመራችንም በእውነት፣በቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርት፣ በቤተክርስቲያን ቀኖናና ትውፊት መመራት አለበት እንጅ በመርህ የለሽ አዳማቂነት መቃኘት የለበትም፡፡
ስብሃት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር
(Email: tewahdo@astemhro.com)