ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ወይስ ታደርሳለች?

seba segel2

ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ቦታዎች ላይ የተጠቀሰች ሀገር ስትሆን በነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት በመዝሙር 67፡31 ላይ “መልእክተኞች ከግብፅ ይምጡ፤ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር  ትዘረጋለች” ተብሎ የተቀመጠው ግን በብዙዎች ዘንድ በሰፊው የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ የመዝሙር ክፍል በግዕዙ “ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር” የሚል ሲሆን በግዕዙና በአማርኛው ትርጉም መካከል ልዩነቶች እንዳሉ አንዳንድ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡

ቀደምት አበው እንዳስተማሩትና የግእዝ ቋንቋ ሊቃውንትም እንደሚያስረዱት “በጽሐ” የሚለው የግእዝ ቃል ቀጥታ የአማርኛ ትርጉሙ “ደረሰ” ማለት ነው፡፡ በዚህም መሠረት “ታበጽሕ” የሚለው ቃል “ታደርሳለች” የሚለውን ትርጉም ይይዛል ማለት ነው፡፡ በግዕዙ “ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር” የሚለውም ወደ አማርኛ ሲተረጎም “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ታደርሳለች” የሚል ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” የሚለው የአማርኛው ትርጉም ወደ ግዕዙ ቢመለስ ደግሞ “ኢትዮጵያ ትሰፍሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር” የሚል ይሆናል፡፡ በግዕዝ “ሰፍሐ” ማለት በአማርኛ “ዘረጋ” ማለት ነውና፡፡ “ትሰፍሕ” ማለት ደግሞ “ትዘረጋለች” ማለት ይሆናል፡፡ ይህም “…ይሰፍሑ ክነፊሆሙ…” ማለት “ክንፋቸውን ይዘረጋሉ” ማለት እንደሆነው ያለ ነው፡፡ስለዚህ “ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር” የሚለው “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” ከሚለው ይልቅ “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ታደርሳለች” የሚለው የአማርኛው ትርጉም የበለጠ ይስማማዋል፡፡

ይህንን ልዩነት  መተንተን ያስፈለገበት ዋነኛው ምክንያት “ታደርሳለች” እና “ትዘረጋለች” በሚሉት ቃላት መካከል ልዩነት ስላለና ልዩነቱም ከመጻሕፍት ምሥጢራት ጋር የሚያያዝ ስለሆነ ነው፡፡ እጅን መዘርጋት ማንም ሊዘረጋ ይችላል፡፡ለመቀበል ወይም ለመስጠት እጅን መዘርጋት አስፈላጊ ቢሆንም እጁን የዘረጋ ሁሉ ግን አይቀበልም ወይም አይሰጥም፡፡ ዘርግቶም ሊቀበልም ላይቀበልም ይችላልና፡፡ ዘርግቶ ሊሰጥም ላይሰጥም ይችላልና፡፡ እጁን የሚያደርስ ግን ወይ ይሰጣል ወይም ይቀበላል፤ አለበለዚያም ሰጥቶ ይቀበላል ወይም ተቀብሎም ይሰጣል፡፡ በጸሎት ጊዜ እጃችንን የምንዘረጋው በእምነት ሆነን ቸርና ለጋስ የሆነው አምላካችን የሚሰጠንን መልስና በረከት ለመቀበል መዘጋጀታችንን የሚያሳይ መሆኑን ነባቤ መለኮት የኑሲስ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ አስተምሯል፡፡

ይህቺ ቅድስት ሀገረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ግን ‹‹ታበጽሕ›› (ታደርሳለች) ተብሎ ነው የተነገረላት፡፡ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ ከሰብአ ሰገል አንዱ በመሆን ሥጦታን ለተወለደው አምላክ በማቅረብ በእውነት እጆቿን (ስጦታን ይዛ) ወደ እግዚአብሔር አድርሳለች፡፡ ይህም ከአምላኳ በነቢያት በኩል ለርሷ  የተሰጠና የተነገረላት ትንቢት ነው (መዝ 67:31)፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት ይህንን “በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ … የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤ የሳባና የዓረብ ነገሥታትም እጅ መንሻን ያቀርባሉ፤ የምድር ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል” ብሎ ገልጾታል፡፡ (መዝ. 71፡9-10)

ለተወለደው አምላክ በቤተልሔም ተገኝተው አምሐ ካቀረቡት ሦስት ነገስታት (ሰብአ ሰገል) መካከል አንዱ የሆነው ንጉሥ በዲዳስፋ (አንዳንድ ጸሐፊያን ባልዛር ወይም ባዜን ይሉታል) የኢትዮጵያ ንጉሥ እንደነበር የታሪክ ሊቃውንት ያስተምራሉ፡፡መልኩም ጥቁር እንደነበርና ከርቤን (አንዳንድ ጸሐፊያን ወርቅን ይላሉ) በአምላኩ በክርስቶስ ፊት እንዳቀረበ ይገልፃሉ፡፡ ዛሬም ድረስ ምዕራባውያን በሚሠሩት የልደት የፊልም፣ተውኔትና በሚሥሏቸው የሰብአሰገል ሥዕሎች ላይ አንዱን (ኢትዮጵያዊውን)ጥቁር አድርገው ይስሉታል፡፡ ይህም አምሐ ካቀረቡት ሦስት ነገስታት መካከል አንዱ ኢትዮጵያዊ እንደነበር ምዕራባውያን ሊቃውንትም ያውቁ እንደነበር ይጠቁማል፡፡ ኢትዮጵያ ክርስቶስን ያወቀችውና መባ በማቅረብ ልደቱን ያከበረችው ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ስለሆነ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቀዳማዊት ቤተ ክርስቲያን መባሉዋ ትክክል ነው፡፡ ብሉይ ኪዳንን በንግስተ ሳባ አማካኝነት የተቀበለች ኢትዮጵያ ተስፋ ልደቱን፣ የነቢያትን ሱባኤ የምታምንና የምትጠብቅ ስለነበረች ጌታ በተወለደ ጊዜ ከሰብአ ሰገል አንዱ የሆነው ኢትዮጵያዊ ንጉስና ሰራዊቱ ወደ ቤተልሔም የሄዱት የተቆጠረው ሱባኤ መፈጸሙን ተረድተው እንደነበር ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡

ለኢትዮጵያ ነገስታት ስጦታን መስጠት የተለመደ ነገር ነበር፡፡ ንግስተ ሳባ ስጦታን የክርስቶስ ምሳሌ ለነበረው ለእስራኤል ንጉሥ ለሰሎሞን አበርክታለች፡፡ይህም “ለንጉሡም መቶ ሀያ መክሊት ወርቅ እጅግም ብዙ ሽቱ የከበረም ዕንቍ ሰጠችው፤ የሳባ ንግሥት ለንጉሡ ለሰሎሞን እንደ ሰጠችው ያለ የሽቱ ብዛት ከዚያ ወዲያ አልመጣም ነበር” (1ኛ ነገ 10: 10) ተብሎ ተጽፏል፡፡ የአዲስ ኪዳን መጀመሪያ ላይ የነገሠውና ከሰብአ ሰገል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ንጉሥ ባልዛር (ባዜን) ደግሞ ለሰማያዊው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ከርቤን አበርክቷል፡፡

ወደ እግዚብሔር የተዘረጉት፣ እንዲሁም የደረሱት የኢትዮጵያ እጆች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ልጅዋ በስደት ሳሉ ተቀብለው አስተናግደዋቸዋል፡፡ በዚህም ብዙ በረከት አግኝተዋል፡፡ ሀገሪቱም ለቅድስት ድንግል ማርያም አስራት ተደርጋ ተሰጥታለች፡፡ ይህም ዛሬም ለእርስዋ ልዩ ፍቅር ያለው ሕዝበ ክርስቲያን እንዲኖር መሠረት ሆኗል፡፡

ወደ እግዚአብሔር ተዘርግተው ወደ እርሱም የደረሱት የኢትዮጵያ እጆች ክርስትናንም ተቀብለው ተመልሰዋል፡፡ በሐዋርያት ሥራ 8፡26 ላይ እንደተገለጸው የንግሥት ህንደኬ ጃንደረባ የነበረው ባኮስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ሲመለስ በሐዋርያው ፊሊጶስ ተጠምቆ ክርስትናን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል፡፡ በቅዱስ ፍሬምናጦስ በኩል ወደ እስክንድርያ የተዘረጋው ከዚያም የደረሰው የኢትዮጵያ እጅ ምስጢረ ክህነትን ይዞ ተመልሷል፡፡በአፄ ዳዊት ዘመንም የተዘረጉት የኢትዮጵያ እጆች ግማደ መስቀሉን ይዘው ተመልሰዋል፡፡ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “መልእክተኞች ከግብፅ ይምጡ፤ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር  ትዘረጋለች” እንዳለ ኢትዮጵያ ሐዋርያዊ የክህነት ውርስን ከግብፅ መልእክተኞች፣ በወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ መንበር ከተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳት ተቀብላ፣ በሐዋርያዊ አስተምህሮም ተባብራ (አንድ ሆና) ስለኖረች፣ ስለምትኖር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ውርስ ተገለጠ፣ ልበ አምላክ የተባለ የንጉስ ዳዊት ትንቢትም ተፈጸመ፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” ያለውን ሊቃውንት ሲያብራሩት ኢትዮጵያ (የመጽሐፍ ቅዱሷ) እጆቿን ወደ እግዚአብሔር የምትዘረጋው አንድም ጸሎትን፣ ምሥጋናን፣ ስጦታን፣ መስዋዕትን ለማድረስ ሲሆን ሁለትኛም በዚሁ ፈንታ ጸጋን፣ ምህረትን፣ ቸርነትንና በረከትን ከእግዚአብሔር ዘንድ ለመቀበል ነው። ይህ አማናዊ ቃል መንፈሳዊ ትንቢት እንጂ “ሀገራዊ መፈክር” አይደለም። እጅን መዘርጋትም ቢሆን በትህትና የሚፈጸም አገልግሎት እንጂ በየአደባባዩ “ምንም አንሆንም” እያሉ ለመታበይ የሚውል መፈክር አይደለም። በየመዝሙሩም ይህንን ቃል ስንጠቀም የእግዚአብሔርን ቸርነት በማሰብ እንጂ “አንድ ጊዜ እጇን ትዘረጋለች ተብሎ ተጽፏልና ማንም አይነካንም” ብሎ በመመካት ሊሆን አይገባም። ይልቁንም በትህትና ልብ ስንጸልይ የምናስበውና ተስፋ የምናደርገው የትንቢት ቃል እንጂ በጸሎት ሳንተጋ እንደዚያ ስለተባለ ብቻ የሚፈጸምልን አድርገን መታበይ የለብንም።

ቃሉንም ከመንፈሳዊ አውድ ውጭ መውሰድ አይገባም። ኢትዮጵያ እጆቿን የምትዘረጋው ከመከራና ከፈተና ለመጠበቅ ቢሆንም “የዓለም ገዥ (ልዕለ ኃያል) ሀገር ለመሆን ነው” ብሎ ማሰብ ግን መንፈሳዊነት የጎደለው አካሄድ ነው። ከኢኮኖሚ አንጻርም ቢታይ እግዚአብሔር ለሚለምኑት ሁሉ በረከትን የሚሰጥ ቢሆንም ኢትዮጵያን ብቻ በበረከት አትረፍርፎ ሌላውን ዓለም የሚነፍግ አይደለም። በመንፈሳዊውም በየአደባባዩ “እጆቿን ትዘረጋለች” ስላልን ብቻ “የዓለም ብርሃን ትሆናለች” ማለት አይደለም። እውነተኛውን የክርስቶስ ወንጌል ለዓለም የሚሰብኩ ሐዋርያት ሲኖሯት ነው የዓለም ብርሃን የምትሆነው። ዛሬ ግን እንኳን ለዓለም ቀርቶ ሀገር ውስጥ ላሉት የተለያየ ቋንቋ ለሚናገሩ ወገኖች እንኳን ወንጌል በበቂ ሁኔታ አልተሰበከም፣ ብዙ የተሰበከለትም የገዛ ወንድሙን ከመበደል አልታቀበም።

የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብና ትርጉም እንዲሁም ታሪክን ለራሳቸው ዓላማ የሚበርዙ ልዩ ልዩ መናፍቃን፣ ፖለቲከኞችና ሌሎች ግለሰቦች የክቡር ዳዊትን ትንቢት ያለአውዱ እየጠቀሱ አንዳንዶችን ግራ ሊያጋቡ ቢሞክሩም ከላይ በተጠቀሱት ታሪካዊና፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃወች የንጉስ ዳዊት ትንቢት ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ብሎም ለኢትዮጵያ ምልክት ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የተነገሩ መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ ዛሬም በጸሎትና በምስጋና የሚዘረጉት የኢትዮጵያ እጆች ወደ እግዚአብሔር ደርሰው ረድኤትን፣ በረከትንና ድኀነትን የዘላለም ሕይወትን ለሕዝቦቿ ይዘው ይመለሳሉ፡፡ ሰማያዊ ጸጋ በምድራዊ ምቾትና ባለጸግነት የሚመዘን አይደለምና፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s