“ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ::” ሉቃ 3፡21
እንኳን ለብርሀነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን!
የልደትና የጥምቀት ዘመን በጽርዕ ቋንቋ ኤጲፋኒ፣ በግእዝ ዘመነ አስተርእዮ፣ በአማርኛ የመገለጥ ዘመን ይባላል። ጥምቀት የሚለው ቃል “አጥመቀ” ከሚለው የግእዝ ቃል/ግሥ የተገኘ ሲሆን በቀጥታ ሲተረጎም በውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት፣ መነከር፣ መዘፈቅ፣ መጥለቅ ማለት ነው። በምሥጢር ትርጉሙ ግን ጥምቀት ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን አንዱ ሲሆን ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ተወልደን የሥላሴን ልጅነት የምናገኝበት፣ መንግሥተ ሰማያት የምንገባበት፣ ኃጢአታችን የሚደመሰስበትና ድኅነትን የምናገኝበት ዐቢይ ምሥጢር ነው። ጥምቀት በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ አምኖ ለሚቀበለው ሰው ሁሉ ከሥላሴ የጸጋ ልጅነት ለማግኘትና የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የተሰጠ ልዩ ክርስቲያናዊ የሕይወት መንገድ ነው።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጢባርዮስ ቄሳር (14-37 ዓ.ም) በነገሰ በ15ኛው ዓመት፣ በተወለደ በ30 ዓመቱ፣ በዕለተ ማክሰኞ ከሌሊቱ 10 ሰዓት፣ ዮር እና ዳኖስ የተባሉ ወንዞች በሚገናኙበት በተቀደሰው የዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡ ማቴ 3፡13-17 ማር 1፡9-11 ሉቃ 3፡ 21-22 ዮሐ 1፡29-34
የተጠመቀውም የዘካርያስና የኤልሳቤጥ ልጅ በሆነው፣ ገና የስድስት ወር ጽንስ ሳለ በማህፀን በሰገደለት፣ በበረሀ ባደገው፣ የመንገድ ጠራጊ በተባለው፣ የንስሐን ጥምቀት በዮርዳኖስ ሲያጠምቅ በነበረውና ኋላም በሄሮድስ ሰማዕትነትን በተቀበለው በደቀ መዝሙሩ በመጥምቀ መለኮት በቅዱስ ዮሐንስ እጅ ነው፡፡ ከውኃ ውስጥ ገብቶ በመውጣትም ተጠመቀ፡፡ ጌታችን የተጠመቀው ሕዝቡ ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ነበር፡፡ ይህም የራሱ ምክንያት አለው፡፡ ከሕዝቡ አስቀድሞ ተጠምቆ ቢሆን የኦሪት ጥምቀትን ተጠመቀ እንዳይባል፣ ከሕዝቡ መካከል ተጠምቆ ቢሆን ኦሪትና ሐዲስ ተቀላቅለዋል እንዳይባል፣ አዲስ ልጅነት ለምታስገኘዋ የአዲስ ኪዳን ጥምቀት አርአያ ሊሆን ሕዝቡ ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ እርሱ ደግሞ ተጠመቀ፡፡ ከሁሉ በላይ የሆነ ጌታ ከሕዝቡ በኋላ ተጠመቀ፡፡
ጌታችን ሲጠመቅ ሰማይ ተከፈተ (ያልተገለጠ ምስጢር ተገለጠ)፡፡ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል መጥቶ አረፈበት፡፡ አብም ከሰማያት ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወድደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት›› አለ፡፡ አምላክ በተጠመቀ ጊዜ ዮርዳኖስ ሸሸ፤ ተራሮችም እንደኮረብቶች ዘለሉ (መዝ 76፡16)፡፡
ሰዎች በእርሱ ስም ይጠመቃሉ፡፡ እርሱስ በማን ስም ተጠመቀ? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ስለሆነ መጥምቁ ዮሐንስ እንዴት ብሎ ማጥመቅ እንደሚችል ግራ ገብቶት ‹‹ሌላውን ሰው በአንተ ስም አጠምቃለሁ፤ አንተን በማን ስም አጠምቃለሁ?›› ብሎ ጠይቆት ነበር፡፡ ጌታም ‹‹ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሀብ ተሣሀለነ፤ አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከፄዴቅ (የቡሩክ የእግዚአብሔር ልጅ፣ የብርሀን መገኛ ይቅር በለን፡፡ አንተ እንደመልከፄዴቅ ለዓለም ካህን ነህ፡፡)›› ብለህ አጥምቀኝ እንዳለው እንደዚሁ ብሎ አጥምቆታል፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ሲሆን ለምን መጠመቅ አስፈለገው? በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተገለፀው ጌታችን ስለ አምስት ምክንያቶች ተጠምቋል፡፡
- ጥምቀትን ለመመስረት (ለመባረክ)
‹‹ሰው ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግስት አይገባምና (ዮሐ 3፡5)›› ጥምቀትን ለመንግስተ ሰማያት መግቢያ በር አድርጎ ሊመሠርት ተጠመቀ፡፡ ‹‹ያላመነ ያልተጠመቀ አይድንምና ማር 16፡16›› ጥምቀትን የድኅነት መሠረት አድርጎ ሠራት፡፡ ‹‹በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ሥም አጥምቁ የምትል ትዕዛዝ ሰጥቷልና ማቴ 28፡19›› እርሱ ተጠምቆ እናንተም ተጠመቁ አለን፡፡ በአጠቃላይ ምስጢረ ጥምቀትን ሊመሠርታትና ራሱ ተጠምቆ አርአያ ለመሆን ተጠመቀ፡፡
ምስጢረ ጥምቀትን እንደዚህ አድርጎ መሠረታት፡፡ ሁላችን ለመጠመቅ ወደ ቤተክርስቲያን እንሄድ ዘንድ ሊያስተምር በመጀመሪያ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄደ፡፡ እኛም ወደ ካህናት ሄደን እንድንጠመቅ አርአያ ለመሆን እርሱ አምላክ ሲሆን ወደ ፍጡሩ ወደ ዮሐንስ ለመጠመቅ ሄደ:: ሁላችን በውኃ እንድንጠመቅ እርሱም በውኃ ተጠመቀ፡፡ ጥምቀት ለእኛም የክርስትና መግቢያ በር እንድትሆንልን ጥምቀትን የሥራው ሁሉ መጀመሪያ አደረጋት፡፡ እኛም ስንጠመቅ መንፈስ ቅዱስ እንደሚወርድልን ለማጠየቅ እርሱ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ ወረደ፡፡ እኛ በሥላሴ ስም እንድንጠመቅ ምስጢረ ሥላሴ በዮርዳኖስ ተገለጠ፡፡ ጥምቀት አንዲትና የማትደገም ምስጢር ናትና እርሱም አንድ ጊዜ ብቻ ተጠመቀ፡፡
‹‹…እንደ ምህረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው ጥምቀትና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን፡፡ ቲቶ 3፡4›› እንዳለ፤ እንዲሁም ‹‹የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም እነዚህ ሦስቱ ናቸው፤ ሦስቱም አንድ ናቸው 1ኛ ዮሐ 5፡8፡፡›› እንደተባለ እኛ ተጠምቀን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ፣ ከማኅጸነ ዮርዳኖስ ተወልደን ልጆቹ እንሆን ዘንድ ጥምቀትን ሠራልን፡፡ በእርሱ ጥምቀት አማካይነት ጥምቀት ከሰማይ መሆኗን፤ በእግዚአብሔር ፈቃድ የምትደረግ መሆኗን አሳየን፡፡ ጥምቀታችንንም በጥምቀቱ ባረከልን፡፡
- የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት እንዲገለጥ
በጌታችን ጥምቀት አምላክ በዮርዳኖስ በአንድነት በሦስትነት ተገልጧል፡፡ አብ በሰማያት ሆኖ በመመስከር ‹‹የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት›› በማለት እውነተኛ አባት፤ አውነተኛ ልጅ መሆኑን፤ ቅድመ ዓለም ከአብ የተወለደ የባህርይ ልጅ መሆኑን፤ በተዋሕዶ የከበረ መሆኑን፤ ‹‹ልጄ›› ብሎ አረጋገጠልን፡፡ ወልድ በማዕከለ ባህር ሥጋን ተዋሕዶ ቆሞ፤ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው ሆኖ፤ እንደሰው ተጠምቆ (ሥጋን ተዋሕዷልና)፤ የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ፤ ይመጣል ተብሎ ትንቢት የተነገረለትን ሆኖ በመጠመቅ ተገለፀ፡፡መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በርግብ አምሳል መጥቶ በራሱ ላይ አርፎ፤ ረቂቅ ነውና ለሰው እንዲታይ በርግብ አምሳል ሆኖ ተገለፀ። በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አምነን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንድንጠመቅ ይህንን ምስጢር በዮርዳኖስ ገለጠልን። እግዚአብሔር አብ በደመና ሆኖ ስለ ባህርይ ልጁ በመመስከር፣ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ፊት በትህትና በመቆም፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በነጭ ርግብ አምሳል በመውረድ ከኢአማንያን ተሰውሮ የነበረ የሥላሴ ኀልወት ታወቀ፣ አስተርዕዮ ሆነ፡፡
- ትህትናን ለማስተማር
የጌታችን የትህትናው ነገር እጅግ ድንቅ ነው፡፡ እርሱ ፈጣሪ ሲሆን ራሱ በፈጠረው ፍጡር በዮሐንስ እጅ ተጠምቀ:: አንዳች ኃጢአት ሳይኖርበት ለሰው ልጅ ሲል ጽድቅን ለመፈፀም ተጠምቀ:: ሰማያዊው ንጉሥ በምድራዊው ሰው ተጠምቀ:: እሳትነት ያለው መለኮትን ያለመለየት የተዋሐደ ሥጋ ፍፁም ሰው ሆኖ ተጠምቀ:: በእሳትና በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው እርሱ በውኃ ተጠምቀ:: ፍጡራን በስሙ የሚጠመቁት እርሱ በፍጡር እጅ ተጠምቀ:: ፈጣሪ የሆነው ራሱ በፈጠረው ውኃ ተጠምቀ:: ኃጢአት የሌለበትና የሰውን ልጅን ኃጢአት የሚያስወግድ እርሱ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከኃጢአተኞች ጋር አብሮ ተጠመቀ (ተቆጠረ):: ይህንን ሁሉ ያደረገው ትህትናን ለማስተማር ነው፡፡ “ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝና” እንዳለ፡፡ ማቴ 11፡29
- ትንቢቱና ምሳሌው እንዲፈፀም
ጌታችን በዮሐንስ ሊጠመቅ ሲመጣ አምላክነቱን በመንፈስ ቅዱስ የተረዳ ዮሐንስ “እኔ በአንተ ልጠመቅ እሻለሁ፤ አንተ ወደ እኔ ትመጣለህን?” ብሎ በከለከለው ጊዜ መምህረ ትህትና ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹አሁንስ ተው፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናልና›› ብሎ መልሶለታል፡፡ ጽድቅን መፈጸም ብሎ ጌታ ከገለፃቸው ውስጥ አንዱ ትንቢተ ነቢያትን መፈጸም ነበርና በዮርዳኖስ በመጠመቅ የነቢያትን ትንቢት ፈጸመ፡፡ ‹‹አንቺ ባህር የሸሸሽ፣ አንተም ዮርዳኖስ ወደ ኋላህ የተመለስህ ምን ሆናችሁ ነው? እናንተም ተራሮች፣ እንደ ኮርማዎች፣ ኮረብቶችስ እንደ በጎች ጠቦቶች ለምን ዘለላችሁ? ከያዕቆብ አምላክ ፊት፣ ከእግዚአብሔር ፊት ምድር ተናወጠች፡፡ መዝ 113፡3›› የተባለውና እንዲሁም ‹‹አቤቱ ውኆች አዪህ፤ ውኆች አይተው ፈሩ፤ የውኆች ጥልቆች ተነዋወጡ፣ ውኆቻቸውም ጮሁ፡፡ መዝ 76፡16 ተብሎ በነቢያት የተነገረው ይፈፀም ዘንድ በዮርዳኖስ ተጠመቀ፡፡
በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቁም በብሉይ ኪዳን ብዙ ምሳሌዎች ያሉት ሲሆን የሚከተሉትን ለአብነት ያህል መመልከት ይቻላል፡፡
- ዮርዳኖስ መነሻው አንድ ሲሆን ከዚያ በደሴት የተከፈለ፤ ኋላም የሚገናኝ ነው፡፡የሰው ዘሩ አንድ አዳም ነው፡፡ ኋላ ሕዝብና አሕዛብ ተብሎ በግዝረትና በቁልፈት ተከፈለ፡፡ በክርስቶስ ጥምቀት ህዝብና አህዛብ አንድ ሆኑ፡፡
- አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ሲሄድ መልከፄድቅ ኅብስተ በረከት ጽዋዐ አኮቴት ይዞተ ቀብሎታል፡፡አብርሀም የምዕመናን፣ መልከፄድቅ የካህናት፣ ዮርዳኖስ የጥምቀት፣ኅብስቱና ጽዋው የሥጋ ወደሙ ምሳሌ ናቸው፡፡
- ከሕዝብ ወገን የሆነው ኢዮብ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ድኗል፡፡ ከአሕዛብ ወገን የሆነውም ሶርያዊው ንዕማን በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ድኗል፡፡የሕዝብም የአሕዛብም ወገኖች በጥምቀት ይድናሉና፡፡
- እስራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረው ምድረ ርስት ገብተዋል፡፡ነቢዩ ኤልያስም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደገነት አርጓል፡፡ ምዕመናንም አምነው ተጠምቀው ገነት መንግስተ ሰማያት ይገባሉና፡፡
- ዮርዳኖስ በክረምት አይሞላም፡፡ በበጋም አይጎድልም፡፡ በጥምቀትም የሚገኝ ልጅነት ጽኑ ነው፣ አይነዋወጽምም፡፡
- የአዳምንና የሔዋንን (የሰው ልጆችን) የዕዳ ደብዳቤ ሊያጠፋ
አዳምና ሔዋን ዕፀ በለስን በልተው ከተሳሳቱ በኋላ ዲያብሎስ የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ መከራ አፀናባቸው፡፡ በመከራቸውም ጊዜ ‹‹ስመ ግብርናችሁን ጽፋችሁ ብትሰጡኝ መከራችሁን አቀልላችሁ ነበር›› አላቸው፡፡ ‹‹አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ (አዳም የዲያብሎስ ባሪያ ነው) ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ (ሔዋን የዲያብሎስ አገልጋይ ናት)››ብለው ጽፈው ሰጡት (ይሁንብን አሉ)፡፡ እርሱም በሁለት እብነ ሩካብ ጽፎ አንዱን በዮርዳኖስ አንዱንም በሲኦል ጥሎታል፡፡ በዮርዳኖስ ያለውን ጌታ ሲጠመቅ እንደሰውነቱ ረግጦ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶላቸዋል፡፡ በሲኦል ያለውን ደግሞ በዕለተ ዓርብ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ሲያወጣ አጥፍቶላቸዋል፡፡ ጌታችን በዮርዳኖስ መጠመቁ አንደኛው ምክንያት ይህንን የዕዳ ደብዳቤ ለማጥፋት ነው፡፡
ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን በጥምቀት ዕለት ፡-
ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን በጥምቀት ዕለት “ሖረ ኢየሱስ እምገሊላ ኀበ ዮርዳኖስ” (ኢየሱስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄደ) ስትል ታቦታቱን ከመንበራቸው አንስታ ወደ ጥምቀተ ባህሩ በድምቀት ትወስዳለች፡፡ “…ቆመ ማዕከለ ባህር…” (በባህር ውስጥ ቆመ) እያለች በመዘመር የጌታን ጥምቀት ታከብረዋለች፡፡ “…ተጠምቀ በማየ ዮርዳኖስ…. በዕደ ዮሐንስ…” (በዮርዳኖስ ውኃ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ) እያለች ታመሰግነዋለች፡፡ “ባህርኒ ርዕየት ወጎየት….” (ባህር አየች፤ ሸሸችም ) እያለችም የነቢያትን ትንቢት ፍፃሜ ትሰብካለች፡፡
በጥምቀተ ባህር ያለውን ውኃ በመባረክ ምዕመናንንም በተባረከው ውኃ በመርጨት ከበዓሉ በረከት እንዲቀበሉ ታደርጋለች፡፡ ይህ ዳግመኛ ጥምቀት አይደለም፡፡ በዚህ ዕለት በዋናነት በዮርዳኖስ የተጠመቀው አምላክ የሚመሰገንበት ቀን ነው፡፡ ለእርሱም በማህሌት፣ በመዝሙር፣ በቅዳሴ ምስጋና የሚቀርብበት ቀን ነው፡፡ የጥምቀት በዓል ሁላችንም የምንባረክበትና በረከትን የምናገኝበት ዕለት ነው፡፡ ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
የመጀመሪያው ምእራፍ መስመር 10 ላይ “ድኅነትን” የሚለው ቃል ይስተካከል. ድኅነትን ሳይሆን ደህንነትን በሚለው ይስተካከል.
LikeLike