አሜን እና እልል: ለማንና ለምን?

የ‹‹አሜን›› ነገር:-

ድሮ ድሮ (ያው ድሮ ቀረ እንጂ) ሽማግሌ ወይም ካህን ሲመርቅ ሌላው (ተመራቂው) ‹‹አሜን!›› ይል ነበር፡፡ መራቂው ከተመራቂው ወይ በዕድሜ ወይ በማዕረግ ከፍ የሚልም ነበር፡፡ ተመራቂውም ምርቃቱን በጥሞና ካዳመጠ በኋላ ነበር ‹‹አሜን›› የሚለው፡፡ ምርቃቱም ተመራቂውን ‹‹አሜን›› የሚያስብል፣ ተመራቂውም ‹‹አሜን›› የሚባለውን ታላቅ ቃል በአግባቡ የሚጠቀም ነበር፡፡ በዚያን ዘመን አንድ ሰው ‹‹አሜን›› ሲል ‹‹እንደተባለው ይሁን፣ ይደረግ›› ማለቱ ነበር፡፡ አሜን ‹‹የተረጋገጠና  የታመነ›› ከሚል የዕብራይስጥ ቃል የወጣ ሲሆን እንደየአገባቡ ትርጉሙ ‹‹ይሁን›› ‹‹በእውነት›› ‹‹መልካም›› ማለት ነው፡፡  ክርስቶስም እውነት ስለሆነ ‹‹አሜን›› ተብሏል፡፡ ራዕ 3፡14

በብሉይ ኪዳን (ዘዳ 27፡15-26) እንደተገለጸው ሌዋውያን ከፍ ባለች ድምፅ የተለያዩ ኃጢአትና ሕግን መተላላፍ አይነቶች እየጠሩ እነዚህን ያደረገ ‹‹ርጉም ይሁን›› ሲሉ ሕዝቡ ሁሉ ‹‹አሜን›› እንዲሉ እግዚአብሔር ለሙሴ ትዕዛዝ ሰጥቶት ነበር፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም (መዝ 41፡13) ‹‹ከዘላለም እስከ ዘላለም የእስራኤል አምላክ እግዚአሔር ይባረክ። አሜን አሜን።›› ብሎ ‹‹አሜን›› የሚባለው በምን አይነት ቦታ እንደሆነ አሳይቶናል፡፡ ሐዋርያትም ‹‹አሜን›› የሚለውን ቃል በየመልእክታቱ/መጻሕፍቱ ማጠናቀቂያ ላይ በብዙ ቦታዎች ተጠቅመውታል፡፡ (2ኛ ጢሞ 4፡22 ዕብ 13፡25 ራዕ 22፡21) ከእነዚህ ተጨማሪ ለእግዚአብሔር የአምልኮ ምስጋናን የሚገልፁ ታላላቅ ዓረፍተ ነገሮች መጨረሻ ላይ ‹‹አሜን›› የሚለውን ቃል እናገኛለን፡፡ ራዕ 1፡6 7፡12 19፡4 ነህያም እግዚአብሔርን ሲያመሰግን ሕዝቡ ‹‹አሜን አሜን›› ብለው መልሰዋል፡፡ ነህ 8፡6 ካህኑም ሲመርቅ ‹‹አሜን›› ማለት እንደሚያስፈልግ እንዲሁ ተጽፏል፡፡ ዘኁ 5፡22

ቤተክርስቲያናችንም ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አብነት በማድረግ በቅዳሴና በሌሎችም የጸሎት መጻሕፍት ‹‹አሜን›› የሚባልበትን ሥርዓት ሠርታለች፡፡ በየትኛው ቦታ ምዕመናኑ አሜን ማለት እንዳለባቸው፣ ስንት ጊዜ አሜን ማለት እንዳለባቸው፣ በንባብ ወይም በዜማ አሜን እንደሚባል ጭምር በመጻሕፍቱ አስቀምጣለች፡፡

ዛሬ ዛሬ ግን ‹‹አሜን›› የሚለው ቃል በአደባባይም ይሁን በአውደምህረት፣ በመገናኛ ብዙኃንም ይሁን በማህበራዊ ሚዲያ ብዙ ‹‹ተጠቃሚ›› አግኝቷል፡፡ ነገር ግን የአጠቃቀሙ ጉዳይ በዝግመታዊ ለውጥ (Evolutionary change) ይሁን በአብዮታዊ ለውጥ (Revolutionary change) በማይታወቅ ሁኔታ ወደ ሌላ አዝማሚያ ተሸጋግሮአል፡፡ ብዙዎች ይህንን ጉዳይ የምዕራባዊያኑ ተፅዕኖ ወይም ዘመናዊነት ነው ቢሉትም የቃሉ አጠቃቀም ግን በአግባቡ መሆን እንዳለበት ይስማማሉ፡፡ አሜንን በአግባቡ እንጠቀም የሚለው ሀሳብ የአሜን ቁጠባ ሳይሆን መልእክትን በሚገባ ለማስተላለፍ ከሚል ዓላማ የመነጨ ነው፡፡ ‹‹አሜን›› የሚለውን ቃል የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ መንገዶች ‹‹ሲጠቀሙበት›› ይታያል፡፡ ከእነዚህም መካከል ለምሳሌ ያህል የሚከተሉት ቀርበዋል፡፡

የተፅዕኖ አሜን፡ የዚህ አይነቱ ‹‹አሜን›› አሜን አስባዩ በመድረክ ላይ ቆሞ ‹‹አሜን በሉ!›› ሲል ወይም በማህበራዊው ሚዲያ ‹‹እገሌን የሚወድ አሜን ይበል›› ሲል የሚባል ‹‹አሜን›› ነው፡፡ ለመሆኑ ሰው የሰማውን/ያየውን ነገር ሲያምንበት አሜን ይበል እንጂ ስለምንድን ነው በግድ ‹‹አሜን በሉ›› የሚባለው? ይህ የሚያሳየው ‹‹አሜን በሉ›› የሚለው ግለሰብ አሜን የሚያስብል ነገር ማቅረብ ስላልቻለ ‹‹አስገድዶ›› አሜን ለማስባልና ሕዝቡ ‹‹አሜን ይልለታል›› ለመባል የሚደረግ ከንቱ ድካም ነው፡፡

የብዜት አሜን፡- የዚህ አይነቱ አሜን ደግሞ አሜንን ብዙ ጊዜ በተከታታይ (ሌላ ቃል በመካከል ሳያስገቡ) ‹‹አሜን አሜን አሜን አሜን አሜን ….›› በማለት ወይም ‹‹አሜን (በቁጥር ይህንን ያህል ጊዜ በል)›› በማለት የሚነገር ወይም የሚፃፍ ሲሆን ብዛቱም እንደ አሜን ባዩና አስባዩ ስሜት የሚወሰን ይሆናል፡፡ በአሜን ብዛት የሚበዛ በረከት ወይም አንድ/ሦሰት ጊዜ ብቻ አሜን በማለት የሚቀር በረከት ይኖር ይሆን እንዴ? ወይስ ለወደፊት ‹‹ይህንን ያህል ጊዜ አሜን በሉ›› የሚል ህግ ያስፈልግ ይሆን?

የትኩረት አሜን፡- የዚህ አይነቱ ‹‹አሜን›› ደግሞ አሜን በሚለው ቃል ውስጥ ያሉ ፊደላትን በማጥበቅ ወይም በማርዘም ወይም ሌላ ድምፅ በመስጠት የሚባል ሲሆን ዓላማውም ክረትን ወይም ርዝመትን በመፍጠር ትኩረትን መሳብ ነው፡፡ አምኤኤኤን (Ameeen)፣ አሜንንንን (Amennnnn)፣ አሜ…..ን (Ame….en) የሚሉት የዚህ አይነቱ ‹‹አሜን›› ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ‹‹አሜን›› በማለት ፈንታም ከሌላው ተውሶ ‹‹ኤሜን!›› ማለትም ከዚህ ይካተታል፡፡ አሜን የሚለውን በተገቢው ዜማ ማለት እንደተጠበቀ ሆኖ የዚህ አይነቱ አዲስ የመጣ የአሜን አክራሪነት ግን በአግባቡ ሊጤንና ሊጠና የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡

የቅብብል አሜን፡- ይህ ደግሞ ተናጋሪው አንድ ቃል/ሀረግ በተናገረ ቁጥር ሌላው ሰው ለእያንዳንዱ ቃል/ሀረግ አጸፋ ‹‹አሜን›› የሚልበት ነው፡፡ በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ ‹‹አሜን›› የሚለውም ሰው ምን እንደተባለ እንኳን በአግባቡ ሳይሰማ ‹‹አሜን›› ማለትን እንደ ሥርዓተ ነጥብ (punctuation) ብቻ ይጠቀመዋል፡፡ ‹‹አሜን›› የሚባልለትም ሰው በአሜን ታጅቦ ንግግሩን ይዘልቀዋል፡፡ የእንደዚህ አይነቱ አሜን ‹‹ተጠቃሚዎች›› ካልሆኑ በቀር የዚህ አይነቱን ‹‹አሜን›› ጠቀሜታ የሚያውቅ የለም፡፡

የ‹‹እልል›› ነገር:-

ከአሜን ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው የ‹‹እልል›› ነገር ነው፡፡ ‹‹እልል›› ወይም ‹‹እልልታ›› የደስታ ጩኸት፣ ደስታን የተሞላ ድምፅ ማለት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ሰዎች ለእግዚአብሔር ክብር በእልልታ ይዘምሩ ነበር፡፡ ዛሬም እልልታ የደስታ/የምስጋና መግለጫ እንደመሆኑ መጠን በመዝሙር ወይም ሌሎች ደስ የሚያሰኙ ነገሮች ሲነገሩ እናቶችና እህቶች ‹‹እልል›› ይላሉ፡፡ ይህም በመጽሐፍ  ‹‹አሕዛብ ሁላችሁ፥ እጆቻችሁን አጨብጭቡ፥ በደስታ ቃልም ለእግዚአብሔር እልል በሉ።…አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ። መዝ 47፡1-5›› ተብሎ እንደተገለጸው በማስተዋል እስከተደረገ ድረስ አግባብ ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔርን ክቡር ዳዊት ‹‹ እግዚአብሔርን…. እልልታ ባለው ጸናጽል አመስግኑት፡፡ መዝ 150፡5›› ብሎ የዘመረው ይህንን እንድናስተውል ነው፡፡  ‹‹እልል›› ለንግሥና ለመዝሙርም፣ ለሠርግና ለዘፈንም አገልግሎት ይውላል፡፡

‹‹እልልታ›› እናቶችና እህቶች በራሳቸው ተነሳሽነት የሚሉት ነው እንጂ በሌላ አካል ግፊት አይደለም፡፡ አሁን አሁን የሚታየው ግን በመድረክ የቆመው (በሚዲያ የሚፅፈው) ሰው ‹‹እልል በሉ›› እያለ ወይም ራሱ ‹‹እልልልል…..›› እያለ እልል የሚያስብልበት ሁኔታ ነው፡፡ ‹‹እልል›› የምንል ሰዎች በማስተዋል አምነንበትና ከልባችን ‹‹እልል›› ስንል ምስጋና ይሆናል፡፡ ‹‹እልል በሉ›› ስለተባለ ወይም ሌላው እልል ስላለ ብቻ እልል ማለት ግን ውስጣችን ጥያቄ እንዲፈጥር ያደርጋል፡፡

ጥቂት ማሳሰቢያ፡-

መምህራንና ዘማርያን ነን የምትሉ ወይም በመድረክና በየማህበራዊ ሚዲያው ለመናገር የምትፈጥኑ ‹‹አሜን›› እና ‹‹እልል›› የማለት ወይም ያለማለትን ነፃነትን ለምዕመናን ብትተውት ምናለበት? በተፅዕኖ ‹‹አሜን›› ወይም ‹‹እልል›› አስብላችሁ የምታተርፉትስ ነገር ምንድን ነው? አሁን አሁንማ ህዝቡ የምትፈልጉትን ስላወቀ ‹‹አሜን/እልል በሉ›› ሳትሉ ቀድሞ ‹‹አሜን/እልል›› ይላል፡፡ ይህ ግን እናንተ ‹‹እልል በሉ!›› እንጂ እያላችሁ ከምትሳቀቁ ብሎ አስቀድሞ መፍትሔ ለመስጠት መሆኑን መረዳት ይኖርባችኋል፡፡ ዓለማችሁ ንግግራችሁ ወይም መዝሙራችሁ እንዲደምቅ  ወይም ተቀባይነት እንዲያገኝ ከሆነ እልልታ ምስጋና እንጂ ማድመቂያ አይደለም፡፡ ‹‹አሜን›› እና ‹‹እልል›› አስባይ ሰዎች በየመድረኩ ሲበዙ ሳይገባው (‘ገ’ ላልቶ ይነበብ) ‹‹አሜን›› እና ‹‹እልል›› የሚል ህዝብ ይበዛል፡፡ ጉባዔያትና የሜዲያ ገፆችም ከእውቀት የራቁ የእልል የአሜን አስባዮችና ባዮች መድረክ ይሆናሉ፡፡

 

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s