ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡

ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡

አዎን! ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ሐዋርያት ነበሩ፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን የመሠረተው በሐዋርያት መሠረትነት ላይ ነው “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ አንተ ብጹዕ ነህ . . . እኔም እልሃለሁ አንተ ዐለት ነህ በዚይች ዐለት ላይም ቤተ ክርስቲያኔን አሠራታለሁ የሲዖል በሮችም አይበረታቱባትም፡፡ የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ በምድር የምታስረው በሰማይ የታሰረ ይሆናል በምድርም የምትፈታው በሰማይ የተፈታ ይሆናል”ማቴዎስ 16 ፥ 15፡፡

ከትንሣኤው በኃላም “ሰላም ለእናንተ ይሁን አብ እኔን እንደላከኝ እንዲሁ እኔ እናንተን እልካችኃለሁ ይህንንም ብሎ እፍ አለባቸውና እንዲህም አላቸው መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኃቸው ይሰረይላቸዋል ይቅር ያላላችኃቸው ግን አይሰረይላቸውም” ዮሐንስ ወንጌል 20 ፥ 22፡፡

ከላይ በተገለጸው መሰረት ቤተ ክርስቲያንን የመምራትና የማስተዳደር ስልጣንን ሐዋርያት ከጌታ ተቀብለዋል፡፡ቅዱስ ጳውሎስም “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሄርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” የሐዋሪያት ሥራ 20 ፥ 28፡፡ በማለት ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ልትመራ እንደሚገባ አስገንዝቦናል ሲኖዶስ ማለት የጳጳሳት ጉባኤ መሆኑን ልብ ይልዋል፡፡ ቤተክርስቲያንም ሐዋርያዊት ናት ስንል ሐዋርያዊት የሆነችው በሦስት ነገሮች ነው፡፡

በሢመት ሀረግ፡- ከሐዋርያት አንስቶ ያልተቋረጠ የሢመት ሀረግ መኖሩ ቤተክርስቲያንን ሐዋርያዊት አድርጓታል፡፡ ጌታችን ለሐዋርያቱ የሰጠው የክህነት ስልጣን ሳይቋረጥ በቀጥታ እየተላለፈ መምጣቱ አንዱ የሐዋርያዊትነቷ መገለጫ ነው፡፡

በትውፊትና በምሥጢር፡-  ቤተክርስቲያን የሐዋርትን ትውፊት ተቀብላ መተግበሯ ሐዋርያዊት አድርጓታል፡፡ እንደ ሐዋርያት ሲኖዶስ አላት፡ እንደ ሐዋርት ታጠምቃለች፡ እንደ ሐዋርያት ትቀድሳለች፡ ሥጋና ደሙን ታቀብላለች፡፡ ሐዋርያት የሠሩትን እንደ ሐዋርያት አድርጋ ትሠራለች፡፡ ከሐዋርያት የተለየ ሥርዓት ሊኖራት አይችልም፡፡ ይህ የሐዋርያዊትነቷ ሌላው መገለጫ ነው፡፡

በመጻሕፍት ትርጓሜ፡- ሐዋርያዊ ክትትሉን የጠበቀ የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ስላላት ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡ ሐዋርያት እንደተረጎሙት አድርጋ ትተረጉማለች፡፡ ሐዋርያት እንዳስተማሩት አድርጋ ታስተምራለች፡፡ ሐዋርያት ያላስተማሩትን አታስተምርም፡፡ በዚህም ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት፡፡

ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ በቅዱስ ሲኖዶስ መመራት የጀመረችው ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ለመሆኑ ምሥክሩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ የመጀመሪያው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የተደረገበትን ምክንያት ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ግብረ ሐዋርያትን በገለጸበት ጽሑፉ ላይ እንዲህ ተርኮታል፡- አንዳንዶችም ከይሁዳ ወረዱና፥ እንደ ሙሴ ስርዓት ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም ብለው ወንድሞችን ያስተምሩ ነበር፡፡ በእነርሱና በጳውሎስ በበርናባስም መካከል ብዙ ጥልና ክርክር በሆነ ግዜ ስለዚህ ክርክር ጳውሎስና በርናባስ ከእነርሱም አንዳንዶች ሌሎች ሰዎች ወደ ሐዋርያት ወደ ቀሳውስቱም ወደ ኢየሩሳሌምም ይወጡ ዘንድ ተቆረጠ። . . .በሐዋርያት ያደረ ቅዱስ መንፈስ በቅዱስ ጳውሎስም ያደረ ሆኖ ሳለ ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ ሌሎች ሰዎችን ጨምረው ለምን? ወደ ሐዋርያት መሄድ አስፈለጋቸው? የሚለው መጠይቅና መልሰ የቤተ ክርስቲያን እርከናዊ መዋቅር ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ የነበረ መሆኑን ያስገነዝበናል ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ለተዋቀረው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የተገዙ መሆናቸውን ያሳያል ምክንያቱም ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቁና ያስተዳድሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳት አድርጎ የሾማቸው ናቸውና። ስለዚህ ለመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻው ወሳኝ አካል እነርሱ ነበሩ ይህ ሐዋርያዊ ውርስ ባላት የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንም የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ለዚህም ነው ሲኖዶሳዊት ያልሆነች ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት አይደለችም የምንለው፡፡

ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደ ምንረዳው የመጀመሪያው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ በሐዋርያው በቅዱስ ያዕቆብ ሊቀ መንበርነት ከ49 – 50 ዓ.ም ባለው ግዜ የተካሄደው ከላይ በተገለጸው መሠረት ከአሕዛብ ወገን ክርስትናን በተቀበሉና ከአይሁድ ወገን ክርስትናን በተቀበሉት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ለዚያ እልባት ለመስጠት ነበር ሐዋርያትም ግራ ቀኙን አድምጠው የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥተዋል።ሐዋርያትና ቀሳውስት ወንድሞችም በአንጾኪያና በሶርያ በኪልቅያም ለሚኖሩ ከአሕዛብ ወገን ለሆኑ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርባሉ፡፡ ያላዘዝናቸው ሰዎች ከእኛ ወጥተው ትገረዙ ዘንድና ሕግን ትጠብቁ ዘንድ ይገባችኃል ብለው ልባችሁን እያወኩ በቃል እንዳናወጡአችሁ ስለ ሰማን ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነፍሳችውን ከሰጡት ከምንወዳቸው ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር የተመረጡትን ሰዎች ወደ እናንተ እንልክ ዘንድ በአንድ ልብ ሆነን ፈቀድን፡፡ራሳቸውም ደግሞ በቃላቸው ያንኑ ይነግሩአችሁ ዘንድ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል፡፡ ለጣዖት ከተሠዋ ከደምም ከታነቀም ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናል ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ ጤና ይስጣችሁ፡፡ ” የሐዋርያት ሥራ 15 ፥ 22 – 29፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከምድረ ፍልስጤም ወደ ሌሎቹ የሮማ ግዛቶች ግዛትዋን እያሰፋች በመጣች ግዜም መዋቅርዋ፤ ሐዋርያዊ ሠንሰለቱ እንደተጠበቀ ነበር፤ ከቤተ አይሁድም ከቤተ አሕዛብም የመጡ ከሐዋርያት የሰሙ ከሐዋርያት የተማሩ ሐዋርያውያን አባቶች በሐዋርያት መንበር እየተተኩ ሠንሰለቱ ሳይበጠስ ቀጥሉዋል እንደ ኤሬኒዮስ ናኤጲፋንዮስ አገላለጽ በቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ላይ ከቅዱስ ጴጥሮስ ቀጥሎ ደቀ መዝሙሩ የነበረው ሊኖስ ሲሆን (የዚህ አባት ስም በ2ኛ ጢሞቲዎስ 4 ፥ 21 ላይ ተጠቅሱዋል) አውሳብዮስ ግን የቅዱስ ጴጥሮስ ወራሴ መንበር ቀሌምንጦስ ነው ይላል፡፡ በቅዱስ ማርቆስ መንበር ላይ ቅዱስ ማርቆስ አሰተምሮ ያሳመነው፣ ያጠመቀውና በክህነት የወለደው ጫማ ሰሪ የነበረው አናንያስ ነበር የተሰየመው ፤ የቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የነበረው ፖሊካርፕ እንዲሁም ሌሎችም ከሐዋርያት በቀጥታ ቤተ ክርስቲያንን የማስተዳደር ስልጣንን ተቀብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት የምንለው በሐዋርያው በቅዱስ ፊልጶስ አማካይነት በ34ዓ.ም ጥምቀትን ተቀበለች፥ በኃላም በአራተኛው ምዕተ ዓመት በሲኖዶስ ሕግ በቅዱስ ማርቆስ መንበር ሥር የተዋቀረች በመሆኑ ነው፡፡ የራስዋ መንበር ባለቤት የሆነችውም ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን በዓመጽ ተገንጥላ ሳይሆን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅደው መሠረት በሥርዓቱ ነው፡፡ ለዚህም አባቶቻችን አያሌ ዘመናት በትእግስት የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያንን ደጅ ጠንተዋል፡፡ይህም የሐዋርያዊ ውርስ ሠንሰለቱ እንዲጠበቅ የከፈሉት መሥዋዕትነት ነው፡፡

 

ቤተክርስቲያን ኲላዊት ናት፡፡

ቤተክርስቲያን ላዊት ናት፡፡

ቤተክርስቲያን ኲላዊት ናት ሲባል የሁሉ (አለም አቀፋዊት- Universal) እና ከሁሉ በላይ ናት ማለት ነው፡፡ ይህም በጸሎተ ሃይማኖት “እንተ ላዕለ ኩሉ” በሚለው ይታወቃል፡፡ ቤተክርስቲያን የሁሉ እንደሆነች ሁሉ ደግሞ ከሁሉ በላይ ናት፡፡ በደመ ክርስቶስ የተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የዚህ ወገን ናት የዚህ ወገን አይደለችም የማትባል በዘር፣ በቋንቋ፣ በጎጥና በቀለም እንዲሁም በቦታ የማትከፋፈል የሁሉና በሁሉ ያለች ናት፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን የሁሉም መሆንዋን እንዲህ ሲል ገልጾታል“አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና” ገላቲያን 3 ፥ 28፡፡

 

ቤተክርስቲያን የሁሉ ናት (አለም አቀፋዊት ናት) ስንል በአምስት ደረጃ ከፍለን ልናየው እንችላለን፡፡

በመልክአ ምድር (Geography)፡- ቤተክርስቲያን የዚህ ሀገር ወይም የዚህ አካባቢ ናት አይባልም፡፡ በክርስቶስ ያመነ የተጠመቀ ሁሉ (ከማንኛውም የዓለም ክፍል ቢመጣ) የሚገባባትና የሚኖርባት ቤት ናት እንጂ፡፡

በሰው ፀባይ (Personal attributes):- ቤተክርስቲያን የዚህ ዘር፣ የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ፣ የዚህ ጾታ ወይም የዚህ እድሜ ክልል ናት አይባልም፡፡ የሁሉም ናት እንጂ፡፡ በቤተክርስቲያን ሰው እምነቱ እንጂ ሰብአዊ ማንነቱ አይጠየቅም፡፡

በጊዜ/በዘመን (Time horizon)፡- ቤተክርስቲያን ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ለነበረው ትውልድ፣ አሁንም ላለው ትውልድ፣ ወደፊትም ለሚኖረው ትውልድ ናት፡፡ ቤተክርስቲያን የሁሉም ናት ሲባል የሁሉም ትውልድ ናት ማለትም ነው፡፡

በማዕረጋት (Hierarchical):- ቤተክርስቲያን የፓትያርኩም፡ የጳጳሳቱም፡ የቀሳውስቱም፡ የዲያቆናቱም፡ የምዕመናኑም ናት፡፡ ሁሉም በቤተክርስቲያን የየራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡

በሰማይና ምድር (Earth and Heaven)፡- ቤተክርስቲያን በአካለ ሥጋና በአካለ ነፍስ ያሉት አንድነት ስለሆነች የሁለቱም ናት፡፡ ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ስለሆነች የክርስቶስ ለሆነ ሁሉ ናት፡፡

ቤተክርስቲያን የሁሉም ናት ሲባል በቃ የሁሉ ናት ተብሎ የሚያበቃ አይደለም፡፡ የሁሉም ናት ማለት ሁሉም በቤተክርስቲያን የየራሱ የአገልግሎት ድርሻ አለው ማለት ነው፡፡ ፈተና ቢያጋጥማትም የሚመለከተው ሁሉንም ነው ማለት ነው፡፡

ቤተክርስቲያን ቅድስት ናት፡፡

ቤተክርስቲያን ቅድስት ናት፡፡

ክርስቶስ በቅዱስ ደሙ መሥርቷታል፤ አንጽቷታል፤ ቀድሷታልና ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት ኤፌሶን 5 ፥ 26፡፡የቤተ ክርስቲያን ቅድስና የተገኘው ቅድስና የባሕርይ ገንዘቡ ከሆነው ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ ወደ እርስዋ የገቡ ርኩሳን ይቀደሳሉ እንጂ በውስጥዋ ያሉ ሰዎች በኃጢአት በክህደት ቢረክሱ እርስዋ አትረክስም፡፡ ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ባለው መሠረት በእርሱ ያመኑ በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር የተጠለሉ ሁሉ ቅድስናን ገንዘብ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ቤተክርስቲያን ቅድስት (የተለየች) ናት ስንል ስለ አራት ነገሮችን ያመለክታል፡፡

አንደኛ፡ በደሙ የመሠረታት ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ነውና ቤተክርስቲያን ቅድስት ናት፡፡ 1ጴጥ 1፡15-16 ሐዋ 23፡20 ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካሉ ናትና ቅድስት ናት፡፡ እርሱም መሠረቷ አካሏና ጉልላቷ ስለሆነ ቅድስት ናት፡፡

ሁለተኛ፡-ቤተክርስቲያን የቅድስና ሥራ (አገልግሎት) የሚፈጸምባት የጸሎት ቤት ናትና ቅድስት (የተለየች) ናት፡፡ የተለየችው ለቅድስና ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ በቅድስት ቤተክርስቲያን የቅድስና ያልሆነ ሥራ መሥራት አይገባም፡፡

ሦስተኛ፡- ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ያመኑ የሰው ልጆች ምሥጢራትን ተካፍለው (ተጠምቀው ንስሐ ገብተው ሥጋና ደሙን ተቀብለው) ቅድስና ያገኙባታልና ቅድስት ናት፡፡ የቅድስና መገኛ ስፍራ ናትና ቅድስት ናት፡፡

አራተኛ፡- ቤተክርስቲያን ቅድስት የሆነችው የሰማያዊት ኢየሩሳሌም ምሳሌ ናትና ቅድስት ናት፡፡ ወደ ሰማያዊት መንግስት የምታደርስ በምድር ላይ ያለች የክርስቲያኖች ቤት ናትና ቅድስት ናት፡፡ በምድር ላይ ለእግዚአብሔር የተለየች ቅድስት ናት፡፡

አንዳንድ ወገኖች ብዙ ኃጢአት የሚሠሩና በደልን የሚፈፅሙ ሰዎች በቤተክርስቲያን ስላሉ ቤተክርስቲያን የምትረክስ (ቅድስናዋ የሚቀንስ) ይመስላቸዋል፡፡ እውነታው ግን እነዚህ ሰዎች በጊዜው በንስሐ ካልተለመሱ ራሳቸው ይረክሳሉ እንጂ ቤተክርስቲያን አትረክስም፡፡ የቤተክርስቲያን ቅድስናዋ ዘላለማዊና የማይለወጥ ስለሆነ አትረክስም፡፡ ሰው ቢያከብራት ራሱ ይከብራል፡፡ ባያከብራት ደግሞ ራሱ ይረክሳል፡፡ ይህም በአፍኒንና በፊንሐስ እንዲሁም በሐናና በሳጲራ እንደሆነው ነው፡፡ ሐዋ 5፡1 1ኛ ሳሙ 2፡12 ለምሳሌ በቆሻሻ ላይ የፀሐይ ብርሀን ቢወጣበት ቆሻሻው ይሸታል እንጂ የፀሐይ ብርሀኑ ምንም አይሆንም፡፡ የቤተክርስቲያን ቅድስናም ልክ እንደ ፀሐይ ብርሀን ነው፡፡

ቤተክርስቲያን አንዲት ናት፡፡

ቤተክርስቲያን አንዲት ናት፡፡

ቤተክርስቲያን አንዲት (አሐቲ) ናት፡፡ ሁለት ወይም ሦስት ወይም ከዚያ በላይ አትሆንም፡፡ ከአንድም አታንስም፡፡ አይጨመርባትም፡ አይቀንስባትምም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ …”በዚህ አለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እመሠርታለሁ” አለ እንጂ “ቤተክርስቲያኖቼን” አላለም፡፡ ማቴ 16፡18 በአንድ መሠረት ላይ አንዱ መሥራች የመሠረታት ስለሆነች ቤተክርስቲያን አንዲት ናት፡፡

ቤተክርስቲያን አንዲት ናት ሲባል በእርሷ ያለውን አንድነትም ያመለክታል፡፡ በቤተክርስቲያን ሦስት አይነት አንድነት አለ፡፡ የመጀመሪያው በምድር ላይ የምንኖር ክርስቲያኖች (እርስ በእርሳችን) ያለን አንድነት ነው፡፡ ሁለተኛው በአካለ ሥጋ ያለን ክርስቲያኖችና በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን ያለን አንድነት ነው፡፡ ሦስተኛው አንድነት ሁላችንም (በአካለ ሥጋ ያለን ክርስቲያኖችና በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን) ከእግዚአብሔር ጋር ያለን አንድነት ነው፡፡ ይህ አንድነት ነው እንግዲህ ቤተክርስቲያንን አንዲት ያደረጋት፡፡

እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ እንዳለ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ የባሕርይ አምላክነት ያመኑ ክርስቲያኖችም በእርሱ ላይ የበቀሉ ቅርንጫፎች ናቸውና እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሊሆኑ ይገባል፡፡ “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አለምንም . . . አንተ አባት ሆይ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ . . . እኛም አንድ እንደሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ” ዮሐንስ ወንጌል 17 ፥ 20 – 23፡፡ ከሚለው የጌታ አነጋገር የምንረዳው ይህን አንድነት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “ለአንዱ ተስፋችሁ እንደ መጠራታችሁ መጠን አንድ አካልና አንድ መንፈስ ትሆኑ ዘንድ እማልዳችኃለሁ፥ ጌታ አንድ ነው ሃይማኖትም አንዲት ናት ጥምቀትም አንዲት ናት” ኤፌሶን 4 ፥ 4 – 5። በማለት ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ እንዲት መሆንዋን አስገንዝቡዋል፡፡ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን በእብነ በረድ ትሠራ በጭቃ፤ በሀገር ቤት ትመስረት በውጭ ሀገር እምነትዋ ሥርዓትዋ አንድ ነው፡፡

ቤተክርስቲያን አንዲት ናት ሲባል በዋናነት የሚመለከተው ከአንዱ ክርስቶስ ጋር ያለንን ውህደት ነው እንጂ አስተዳደራዊ ጉዳይ አይደለም፡፡ አንድነታችን የአንዱ ግንድ የክርስቶስ ቅርንጫፎች መሆናችንና በአንዱ በክርስቶስ ሥጋና ደም የምንድን መሆናችን ነው፡፡ ዮሐ 15፡1-10 በዚህ በአንዱ መሠረትነት ላይ የተመሠረተች ስለሆነች ቤተክርስቲያን አንዲት ናት፡፡

የእውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን መገለጫዎች

እውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን መገለጫዎች

እንደ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አመሥጥሮ ቤተ ክርስቲያን ማለት “እግዚአብሔር ግዕዛን ካላቸው ፍጥረታት ጋር ያለው ግንኙነት ነው ይላሉ፡፡ ከዚህም የተነሣ የቤተ ክርስቲያንን ዕድሜ በሦስት ይከፍሉታል፥ አንደኛ የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን ሰው ከመፈጠሩ በፊት በዓለመ መላእክት የነበረችው የመላእክት አንድነት ናት፤በሊቃውንት አመሥጥሮ ሁለተኛዋ የቤተ ክርስቲያን ዕድሜ ከአቤል ጀምሮ እስከ ሐዲስ ኪዳን መግቢያ ድረስ የነበሩ ደጋግ ሰዎች አንድነት ነው፤ ሦስተኛዪቱ እና የመጨረሻዪቱ ግን በክርስቶስ ደም የተመሠረተችው የክርስቲያኖች አንድነት ናት፡፡ እርስዋም የጸጋና የጽድቅ ምንጭ ናት ከላይ የተወሱት ሁለቱ ግን ምሳሌነት ብቻ ነበራቸው፡፡” (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ገጽ 12) ከላይ እንደተገለጸው ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ በሚከተሉት ነጥቦች እርስዋን መስለው በዙሪያዋ ከከበብዋት ትለያለች፡፡

የቤተክርስቲያን መገለጫዎች የሚባሉት በኒቅያ ጉባዔ በተደነገገው የሃይማኖት መሠረት (Creed) ላይ “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባዔ ዘሐዋርያት (ከሁሉም በላይ በምትሆን የሐዋርያት ጉባዔ አንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን)” የሚለው ነው፡፡ እንዲት ቤተ ክርስቲያንን ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ የሚያሰኛት በ381 ዓ.ም በቁስጥንጥንያ የተሰበሰቡት 150 ኤጲስ ቆጶሳት (ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን) በቀኖና ሃይማኖታቸው ላይ እንደገለጡት አንዲት(one ) ቅድስት (Holy) ኩላዊት (የሁሉና በሁሉ ያለች(universal )) እና ሐዋርያዊት (Apostolic succession) ስትሆን ብቻ ነው፡፡ ከእነዚህ ከአራቱ አንዱን ያጎደለች የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ልትሆን አትችልም አይደለችምም፡፡

ቤተክርስቲያን ማለት መዋቅርና አሠራር ያለው መንፈሳዊ ተቋም ነው፡፡

ቤተክርስቲያን ማለት መዋቅርና አራር ያለው መንፈሳዊ ተቋምም ነው፡፡

ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል የቤተክርስቲያንን “ተቋማዊ ሰውነት” የሚያሳይም ነው፡፡ ይህም ከላይ የተጠቀሱትን ሁሉ የሚያጠቃልል ሲሆን የተቋሙን አጠቃላይ መዋቅርና መንፈሳዊ አሠራሩንም ያመለክታል፡፡ ለምሳሌ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን” ወይም “የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን” ሲባል በአጠቃላይ ያለውን ቤተክርስቲያን እንደ ተቋም የሚገልጽ ነው፡፡ ይህም ከፓትርያርኩ እስከ እያንዳንዱ ምዕመን፣ ከቤተክህነቱ እስከ እያንዳንዱ አጥቢያ ቤተክርስቲያን፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ አስተዳደር ያለውን የሚያጠቃልል ነው፡፡ በዚህ ትርጉም ከጥንት ጀምሮ የነበረችውን፣ አሁንም ያለችውን ወደፊትም የምትኖረውን ቤተክርስቲያን የሚገልጽ መሆኑን እንረዳለን (ማቴ 16፡18 ኤፌ 5፡23-27)፡፡

አንዳንድ ወገኖች “ቤተክርስቲያን” የሚለው ቃል “ሕንፃውንና ተቋሙን” አይመለከትም ይላሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ቤተክርስቲያን ማለት እያንዳንዱ ክርስቲያንና የክርስቲያኖች ህብረት መሆኑን ግን ይቀበላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን አራቱንም ትርጉሞች ነው የሚያሳየን፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋል የሚያስፈልግ ነገር አለ፡፡ እያንዳንዱን ሰው ክርስትናን እንዲቀበል ጠብቆትም እንዲኖር ለማድረግ (ቤተክርስቲያን እንዲሆን) ቢያንስ የሆነ መንፈሳዊ አደረጃጀትና አሠራር ያስፈልጋል፡፡ ክርስቲያኖችም በአንድነት በህብረት እንዲገኙ ቦታና አስተባባሪዎች እንዲሁም የእግዚአብሔርን ቃል የሚያስተምሩ መምህራን ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህ መምህራንም የሚማሩበት/የሚሠለጥኑበት ትምህርት ቤት ያስፈልጋል፡፡ እኛ እንግዲህ ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል ትርጉም ሕንፃውንና ተቋሙንም ያጠቃልላል ስንል መጻሕፍት የገለጹትን እውነት፣ ሊቃውንት ያስተማሩትን ምሥጢር በማገናዘብና ከሌሎቹ ሁለቱ ትርጉሞች ጋር የማይነጣጠሉ ስለሆኑም ጭምር ነው፡፡

በሌላ ምሳሌ “ቤተሰብ” ማለት የአንድ ቤት ሰዎች፡ በአንድ ባለቤት የሚተዳደሩ እና በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ማለት ነው፡፡ በቤተሰብ ውስጥ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል፣ የአባላቱም አንድነት/ቤተሰባዊነት፣ የሚኖሩበት ቤትና የቤተሰቡ አስተዳደር/አመራር (ቤተሰብ ተቋም ነውና) አሉ፡፡ ቤተክርስቲያንም ማለት አንዲሁ ነው፡፡ በመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን (የማርቆስ እናት ቤት) አራቱም የቤተክርስቲያን ትርጉሞች ተገልፀዋል፡፡ እያንዳንዳቸው ሐዋርያት፣ የሐዋርያትም አንድነት፣ የተሰበሰቡባት ቤትና ከሌላው ዓለም ተለይተው ክርስቲያን መባላቸው አራቱን ትርጉሞች ያስረዳል፡፡

ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች መኖሪያ፡ የእግዚአብሔር ቤት ነው፡፡

ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች መኖሪያ፡ የእግዚአብሔር ቤት ነው፡፡ቤት ማለት መኖሪያ ማለት እንደሆነ ሁሉ ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች ቤት/መኖሪያ የእግዚአብሔር ቤት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ “ቤተ-ልሔም” የሚለው ቤተ ህብስት፣ የህብስት ቤት፣ የእንጀራ ቤት ማለት እንደሆነ ማለት ነው፡፡ “…እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንኩት እርሷንም እሻለሁ…በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ…እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ…መቅደሱንም እመለከት ዘንድ…(መዝሙር 27፡4)” ቤተክርስቲያን ማለት አምልኮተ እግዚአብሔር የምንፈጽምበት ሕንፃ ቤተክርስቲያንንና በውስጡ ያሉትን ንዋየ ቅድሳት፣ የሚፈፀሙትን ምሠጢራትና ያለውን አገልግሎት ጨምሮ ነው፡፡

 እዚህ ላይ ህንፃ ቤተክርስቲያን ስንል አገልግሎቱንም ጭምር የሚያመለክት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ይህም የክርስቲያኖች መሰብሰቢያ መገናኛ፤ ክርስቲያኖች በአንድነት ተሰብስበው የሚጸልዩበት ሥጋ ወደሙ የሚቀበሉበት የሚሰግዱበት ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት የጸሎት ቤት ማለት ነው፡፡ ኢሳ. 56÷7 ኤር.7÷10-11 ማቴ.21÷13 ማር. 11÷17 ሉቃ. 19÷46 በሌላም ስፍራ «እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደቤትህ እገባለሁ፥ አንተን በመፍራት በቤተ መቅደስህ እሰግዳለሁ።» እንዲል መዝ 5፡7 እንዲሁም «አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ፥ ጆሮዎቼም ያደምጣሉ። አሁንም ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ፤ ቀድሻለሁም፤ ዓይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ።» ብሏል። 2ኛ ዜና 7፥15(ኢሳ. 56፡7፤ ኤር. 6፡10-16፤ ማቴ. 21፡13፤ ማር. 11፡17፤ ሉቃ. 19፡46 ) ጌታም “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች` በማለት የቤተመቅደስን አስፈላጊነት ነግሮናል፡፡ “ቤቴ” ወዳላት ቤተመቅደስ በመሄድ ክርስቶስን ዛረም እናመልካልን፡፡ እዚህ ላይ “ቤቴ” ሲል ባለቤትነቱ የእርሱ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ሐዋርያትም ወደ ቤተመቅደስ አዘውትረው ይሄዱ እንደነበር መጽሐፍ ይናገራል (ሐዋ 3፡1) የጸሎት ቤት ናትና፡፡