ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች ኅብረት፡ አንድነት ነው፡፡

ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች ኅብረት፡ የክርስቲያኖች አንድነት ነው፡፡

እንደ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አመሥጥሮ ቤተ ክርስቲያን ማለት “እግዚአብሔር ግዕዛን ካላቸው ፍጥረታት ጋር ያለው ግንኙነት ነው ይላሉ፡፡ ከዚህም የተነሣ የቤተ ክርስቲያንን ዕድሜ በሦስት ይከፍሉታል፥ አንደኛ የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን ሰው ከመፈጠሩ በፊት በዓለመ መላእክት የነበረችው የመላእክት አንድነት ናት፤በሊቃውንት አመሥጥሮ ሁለተኛዋ የቤተ ክርስቲያን ዕድሜ ከአቤል ጀምሮ እስከ ሐዲስ ኪዳን መግቢያ ድረስ የነበሩ ደጋግ ሰዎች አንድነት ነው፤ ሦስተኛዪቱ እና የመጨረሻዪቱ ግን በክርስቶስ ደም የተመሠረተችው የክርስቲያኖች አንድነት ናት፡፡ እርስዋም የጸጋና የጽድቅ ምንጭ ናት ከላይ የተወሱት ሁለቱ ግን ምሳሌነት ብቻ ነበራቸው፡፡” (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ገጽ 12) ከላይ እንደተገለጸው ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ በሚከተሉት ነጥቦች እርስዋን መስለው በዙሪያዋ ከከበብዋት ትለያለች፡፡

“ቤተ-“ ማለት ወገን ህብረት የሚለውን ትርጉምም ይይዛል፡፡ ለምሳሌ ቤተ እስራኤል፣ ቤተ ያዕቆብ ፣ቤተ አሮን ሲል የእስራኤል ወገን ፣የያዕቆብ ወገን፣ የአሮን ወገን እንደሚል ማለት ነውና፡፡ ማቴ 16÷18 18 ÷17 የሐዋ. 18 ÷22 20÷28 መዝ. 117፡3 በዘህም መሠረት ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያን ወገን ማለት ነው፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ (የምእመናን አንድነት ጉባኤ) የሚጠራበት ስም ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ይህም ስብስቡን ብቻ ሳይሆን በዋናነት በመካከላችን ያለውን ፍቅር ትስስር ህብረት አንድነት ነው የሚመለከተው፡፡ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ራስነት አንድ አካል የሆኑ የምእመናን አንድነት ናት፡፡

“እርሱም የአካለ ማሇት የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው . . .” ቆሊ. 1፡18፣24 “በየአብያተ ክርስቲያናትና ይህንንም ነገር በሰሙ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ፤” ይላል። የሐዋ 5፥11።በዚህ ምዕራፍና ቁጥር ላይ “አብያተ ክርስቲያናት” የተባሉት ማኅበረ ምዕመናን ናቸው። በሌላም ስፍራ፦ “በይሁዳ በሰማርያና በገሊላ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በሰላም ኖሩ፤ ሕዝቡም በመንፈስ ቅዱስ አጽናኝነት በዙ።” የሚል አለ። የሐዋ 9፡31 በቅዳሴም ላይ “ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተክርስቲያን አሐቲ ቅድስት ጉባዔ እንተ ሐዋርያት (አንዲት ቅድስት የሐዋርያት ጉባዔ ስለሆነች ቤተክርስቲያን ሰላም ጸልዩ)” የሚለው የሚያመለክተው ይህንን የክርስቲያኖችን ህብረት ነው፡፡

ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቶስ ማደሪያ፡ የክርስቲያኖች ሰውነት/ሕይወት ነው፡፡

“ቤት-“ ማለት “ማደሪያ” ማለት እንደሆነ ሁሉ ቤተክርስቲያን የሚለውም የክርስቶስ ማደሪያ ማለት ነው፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያን የክርስቶስ ማደሪያ ስለሆነ ቤተክርስቲያን ይባላል፡፡ ይህም በዋናነት የአንድ ክርስቲያንን ክርስቲያናዊ ሕይወትን ነው የሚመለከተው፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያን ሲባል የሚወክለው ምእመናንን ነው፡፡ ክርስቲያኖች የክርስቶስ ማደሪያዎች ናችውና፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቶስ ማደሪያ የሆኑ ክርስቲያኖችን /የክርስቲያኖችን ሰውነት/ የሚያመለክት ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።” 1ኛቆሮ. 3፡16-17 ገላ 1፡13  እንዲሁም የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና። 1ኛቆሮ.3÷9 በራዕየ ዮሐንስም እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል። ራዕ 3÷20 ይላል፡፡ እነዚህ የሚገልጹት እያንዳንዱ ክርስቲያን የክርስቶስ ማደሪያ (ቤተክርስቲያን) መሆኑን ነው፡፡

ቤተክርስቲያን

“ቤተክርስቲያን” የሚለው የግዕዝ ቃል ሲሆን “ቤት-” እና “ክርስቲያን” ከሚሉት ቃላት የተቀመረ ነው፡፡ ይህም በግሪክ አቅሌስያ (Ecclesia) ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ቤት የሚለው ቃል ወገን፤ ነገድ፤ ዘር፤ ትውልድ፤ ጉባኤ፤ ማኅበር ማለት እንደሆነ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡(ኪ.ወ.ክ ገጽ 268) የያዕቆብ ወገን ቤተ ያዕቆብ (ቤተ እስራኤል)፤የዳዊት ወገን ቤተ ዳዊት እንዲባል በመንፈሳዊና በምሥጥራዊ ልደት ከክርስቶስ የተወለዱ ምእመናንም ቤተ ክርስቲያን ይባላሉ፤ ቤተ ክርስቶስ (የክርስቶስ ወገን) እንደ ማለት ነው፡፡ ዳሩ ግን በዘመናችን ስምና ግብር ለየቅል ሆነው በተቃራኒ ያሉት ወገኖች ሳይቀሩ ስሙን መጠሪያ አድርገው አናስተውላለን፤ ዘመናችን አማናዊቱ ቤተ ክርስቲያን ስምዋን ወስደው በሚጠሩ አስመሳዮች የተወረረችበት ወቅት በመሆኑ እውነተኛዋን ለይቶ ማወቅ ግድ ይላል፡፡ ብዙ መምህራን ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል ሦስት ትርጉም አለው ብለው ያስተምራሉ፡፡ ትርጉሙን በጥልቀት ለተመለከተው ግን አራት ነገሮችን ይገልፃል፡፡ ይቀጥላል፡፡

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ

የዚህ ስያሜ ትርጉምና ትር

  1. ኦርቶዶክስ (Orthodox)

“ኦርቶዶክስ” የሚለው ቃል የግሪክ ቃል ሲሆን የተቀናበረው “ኦርቶ” እና “ዶክስ” ከሚሉት ሁለት ቃላት ነው፡፡ትርጉማቸውም ኦርቶ ማለት ቀጥተኛ: ትክክለኛ ማለት ሲሆን ዶክስ ማለት ደግሞ እምነት/ሃይማኖት ማለት ነው፡፡ በአንድነት ሲሆኑ ኦርቶዶክስ ማለት ቀጥተኛ፡ ትክክለኛ እምነት/ሃይማኖት ማለት ነው፡፡

ኦርቶዶክስ የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት ላይ የዋለው በ325 ዓ.ም በኒቅያ ጉባዔ ነው፡፡ በኒቅያ “ወልድ ፍጡር ነው” የሚለውን የአርዮስን የክህደት ትምህርት ለማውገዝና ሃይማኖታቸውን ለማፅናት የተሰበሰቡ ሃይማኖታቸው የቀና 318ቱ ሊቃውንት ይህን ቃል የተጠቀሙት  ሐዋርያት  ያስተማሯት ሃይማኖት ቀጥተኛና ትክክለኛ ናት ለማለት ነው፡፡ ሌሎች እንደ አርዮስ ክህደት ያሉት በየዘመኑ የሚነሱት ልዩ ልዩ አዳዲስ ትምህርቶች የምንፍቅና መሆናቸውን ለማረጋገጥ ይህችን ሃይማኖት ኦርቶዶክስ  ብለዋታል፡፡

በዘመናችን የቋንቋ አጠቃቀምም  ኦርቶዶክሳዊ መንገድ (orthodox) ማለት ቀጥተኛ (የተለመደ የታወቀ) የችግር አፈታት ሲሆን ኢ-ኦርቶዶክሳዊ (unorthodox) ማለት ደግሞ ከተለመደው ከታወቀው ወጣ ያለ የችግር አፈታት ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ይህን ቃል አንዳንዶች ግትርነትን ወይም ለለውጥ ያልተዘጋጀ የሚለውን ለመግለፅም ሲጠቀሙበት ይታያል፡፡ ይህ ግን በሂደት የመጣ የትርጉም መዛባት ተደርጎ ሊወስድ ይችላል፡፡

  1. ተዋህዶ (Miaphysite)

ተዋሕዶ የሚለው ቃል ከልሣነ ግእዝ የመነጨ ቃል ነው፡፡ ትርጒሙም  “አንድ ሆኖ” ማለት ነው። በዚህ ትርጉም ውስጥ አንድ የሆኑት መለኮታዊና ሰብዓዊ ባሕርይ (መለኮትና ትስብዕት) ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት የተዋሕዶ ትርጓሜ በአጭሩ “ወልድ ዋሕድ” የሚለው ነው፡፡ ክርስቶስ ሰው የሆነው ያለሚጠት (ያለመመለስ)፣ ያለ ውላጤ (ያለ መለወጥ)፣ ያለ ቱሳኤ (ያለ መቀላቀል)፣ ያለትድምርት (ያለ መደመር)፣ ያለ ቡዓዴ (ያለመለያየት)፣ ያለ ኅድረት (ያለ ማደር) ነው፡፡ ክርስቶስ  ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ፣ ከሁለት አካል አንድ አካል የሆነው  በተዋህዶ ነው፡፡  ስለዚህ ተዋሕዶ የሚለው ቃል ክርስቶስ ሰው የሆነበትን ምስጢር የሚገልፅ ታላቅ ቃል ነው፡፡ ክርስቶስ ሰው የሆነው በ ተ ዋ ሕ ዶ ነው!

  1. ኦርቶዶክስ ተዋህዶ (Orthodox Miaphysite)

ኦርቶዶክስ ተዋህዶ  ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋህዶ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ፣ ከሁለት አካል አንድ አካል ሆነ (ሥግው ቃል ነው) ብላ የምታምን ቀጥተኛና ትክክለኛ እምነት/ሃይማኖት ማለት ነው፡፡ ይህም ነቢያት የተናገሩትን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ያስተማረውን፣  ሐዋርያት የሰበኩትን፣ ሊቃውንት ያመሠጠሩትን አስተምህሮ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ከሐዋርያት (ከመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች) በቀጥታ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈች ከእኛ ትውልድ ስለደረሰች ቀጥተኛ ናት፡፡ ያልተበረዘች ያልተለወጠች ያልተከለሰች ስለሆነችም ትክክለኛዋ እርሷ ናት፡፡

በማቴ 16፡16-18 ላይ “ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፡- ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ። እነርሱም፡- አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት። እርሱም፡- እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፡- አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።” ይላል፡፡

ተዋሕዶ (ወልድ ዋሕድ) የሚለው ይህንን የጴጥሮስን እምነት የሚያመለክት ነው፡፡ ጌታችን እንዳረጋገጠው ይህች የጴጥሮስ እምነት ዓለት ናት፡፡ ቤተክርስቲያናችንም በቀጥታ በዚህ እምነት/ዓለት ላይ የተመሠረተች ስለሆነች ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ትባለለች፡፡ ይህች ዓለት የምትለወጥ/የምትታደስ አይደለችም፡፡ ቤት ሲታደስ እንኳን መሠረቱ አይታደስም፡፡ ሃይማኖት መሠረት ነው፡፡ ምግባር ደግሞ ግድግዳና ጣሪያ ነው፡፡ ቤት ቢያረጅ ጣሪያና ግድግዳው እንጂ መሠረቱ አይታደስም፡፡ መሠረቱን ለማደስ መሞከር ቤቱን ሙሉ በሙሉ አፍርሶ እንደገና መሥራት ነው፡፡ ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ “ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (1ኛ ቆሮ 3:11)።” ይላል፡፡ በዚህ መሠረትነት ላይ የጸናች ሃይማኖት ሰውን ታድሳለች እንጂ እርሷ አትታደስም፡፡

  1. የተዋህዶ ምሳሌዎች (Examples of Miaphysite)

የነፍስና የሥጋ ተዋህዶ፡- ነፍስና ሥጋ ተዋህደው አንድ ሰው ይባላል እንጂ ሁለት አይባልም፡፡

የብረትና የእሳት ተዋህዶ፡- ብረት በእሳት ሲግል የጋለ ብረት እንጂ ይህ ብረት ነው፣ ይህ ደግሞ እሳት ነው ተብሎ አይለይም፡፡

የሲና ሐመልማል፡- እሳቱ ሐመልማሉን ሳያቃጥለው፣ ሐመልማሉም እሳቱን ሳያጠፋው በአንድነት (በተዐቅቦ) መታየታቸው የተዋህዶ ምሳሌ ነው (ዘፀ 3፡2)፡፡

  1. ይህንን አስተምህሮ የተቀበሉት (Miaphysite churches)

የተዋህዶን (Miaphysite) አስተምህሮ የተቀበሉት ኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት ይባለሉ፡፡ እነዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን (Ethiopian Orthodox Tewahedo Church)፡ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን (Eritrean Orthodox Tewahedo Church)፡ የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን (Coptic Orthodox church)፡ የአርመንያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን (Armenian Orthodox Church)፡ የሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንና (Syrian Orthodox Church) የህንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን (Indian Orthodox church) ናቸው፡፡ እነዚህ  ጉባዔ ኬልቄዶንን የማይቀበሉ የምሥራቅ ኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት በዶግማቸው አንድ ናቸው፡፡

አንዳንድ ወገኖች “ኦርቶዶክስ የሚል ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም::” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ነገር ግን በትንቢት “በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም፥ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደ ሆነች እወቁ፥ በእርስዋም ላይ ሂዱ፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ እነርሱ ግን። አንሄድባትም አሉ (ኤር 6፡16)።” ይላል፡፡ በአዲስ ኪዳንም “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው (ዕብ 13፡8)።” ይህ የሚያሳየው አንዲት ቀጥተኛ መንገድ/ሃይማኖት እንዳለች ነው፡፡ እርሷም ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ናት፡፡ ይህን ስንልም በመረጃና በማስረጃ ነው፡፡ አስተምህሮ በቀጣይ እነዚህን መረጃዎችና ማስረጃዎች በቀጣይ ለአንባቢያን ታቀርባለች፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

 

 

 

 

አንዲት እምነት/ሃይማኖት

እምነት ምንድን ነው? ሃይማኖትስ?

እምነት ማለት “ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው፡፡ ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደተዘጋጁ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን (ዕብ 11፡1-3)፡፡” ለምሳሌ መንግስተ ሰማያትን (የዘላለም ሕይወትን) ተስፋ እናደርጋለን፡፡እምነትም ይህንን ተስፋ ያረጋግጥልናል፡፡ የእግዚአብሔርን (የሰማዩን) መንግስት አላየነውም፡፡ እምነት ይህንን ያላየነውን ነገር ያስረዳናል፡፡ ሳይንስ ይህንን ሊያደርግ አይቻለውም፡፡  እምነት በፍጹም እውነት (absolute truth) ላይ እንጂ እንደ ሳይንስ በአንጻራዊ እውነት (relative truth) ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡

ሃይማኖት ማለት ደግሞ እምነትና አምልኮን በአንድ ላይ አጣምሮ የያዘ  የእምነትና የአምልኮ ሥርዓት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔርን አምነን የምናመልክበት ሥርዓት (system) ሃይማኖት ይባላል፡፡ የዚህም አስተምህሮ ትምህርተ ሃይማኖት ይባላል፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔርን እናምናለን፡ እርሱንም እናመልካለን፡፡ እርሱን ምን ብለን እንደምናምንና እንዴት እንደምናመልክ (የአምልኮ ሥርዓት እንደምንፈጽም) የሚገልጽ ሃይማኖት ነው፡፡ ስለዚህ የእምነት መገለጫው ሃይማኖት ነው፡፡

አንዲት ሃይማኖት/እምነት ማለት ምን ማለት ነው? ኤፌ 45.

የዚህ መነሻው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት” ብሎ ያስተማረው ነው (ኤፌ 4፡4-5)፡፡ ይህንን የጻፈበትም ዓላማ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ይተጉ ዘንድ (በመካከላቸው መለያየትን ያስወግዱ ዘንድ) ነበር።  በዚህ አገላለጽ መሠረት አንዲት ሃይማኖት ማለት የሚከተሉትን ትርጉሞች እንሚይዝ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡

1. አንዲት ሃይማኖት ማለት በአንድ አምላክ ማመን ነው፡፡

የአዳም አምላክ የአብርሀምም አምላክ ነው፡፡ ያው የአብርሀም አምላክ የይስሐቅም የያዕቆብም የሙሴም የዳዊትም የጴጥሮስም የእኛም አምላክ ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ያመነውን አምላክ እርሱ እንዳመነው አድርገን ካመንን እርሱ እንዳመለከውም አድርገን ካመለክን ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በሃይማኖት አንድ ነን፡፡ ልጆቻችንም እንደዚህ ካመኑ እንደዚህም ካመለኩ አንዲት ሃይማኖት ተጠብቃ ኖረች ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አንዲት ሃይማኖት ማለት በአንድ (በቁጥርም በባህሪም) አምላክ ማመንንና እርሱንም በአንድ አይነት አምልኮ ማምለክ ነው፡፡በብሉይም በሐዲስም ያለው አምላክ አንድ ነው፡፡ ሐዋርያው አንዲት ሃይማኖት ያለው ስለአንዱ አምላክ የሚሰብክ መሆኑን ለማስረገጥና ክርስትናም ቀደም ከነበረው ሃይማኖት በገሃድ በመገለጥ የቀጠለ ነው እንጅ ክርስትና አዲስ መጥ ሃይማኖት አይደለም ለማለት ነው፡፡

2. አንዲት ሃይማኖት ማለት በአንዲት ጥምቀት መወለድ ነው፡፡

የሃይማኖት መግቢያ በር በአንድ አምላክ አምኖ መጠመቅ ነው፡፡ ጥምቀትም ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ መወለድና የክርስቶስን ቤተሰብን መቀላቀል ነው፡፡ እያንዳዳችን የምንጠመቃት ጥምቀት አንዲት (በቁጥር) ናት፡፡ አትደገምም፡፡ ልጅ ከተባልንና ወደ እቅፉ ከገባን በኋላ ደግሞ ሌላ ስም ስለማይሰጠን ፣ ዳግመኛ ልጅነትም ስለማይኖር ፣ ጥምቀታችን አንዲት ብቻ ናት እንላለን ፡፡  ሁላችንም የተጠመቅናት የልጅነት ጥምቀት ዓላማዋ አንድ ነው፡፡ ይህም ልጅነትን ማግኘት ነው፡፡ በመጠመቃችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድነትን ፣ ኀብረትን እንፈጥራለን ፤ ሞትና ትንሣዔውን እንጋራለን ፤ መንፈሳዊ የጸጋ ልጅነትንም እናገኛለን ፡፡  ያ የልጅነት ጸጋም አንድ ነው (አይለያይም)፡፡ ስለዚህ ይህችን አንዲት ጥምቀት ተጠምቆ ልጅነትን አግኝቶ ከአንድ ከክርስቶስ ቤተሰብ የተቀላቀለ አንዲት ሃይማኖት ነው የሚከተለው ለማለት አንዲት ሃይማኖት አለ፡፡

3. አንዲት ሃይማኖት ማለት በአንድና ለአንድ ተስፋ መጠራት ነው፡፡

በአንድ አምላክ አምኖ አንዲት ጥምቀትን የተጠመቀ የሚጠባበቀው አንድ ተስፋ ነው፡፡ እርሱም ተስፋ መንግስተ ሰማያት (የዘላለም ሕይወትን) ነው፡፡ ለአንዱ ሌላ ለሌላው ሌላ ተስፋ የለም፡፡ አንድ ተስፋ እንጂ፡፡ ለአንድ ተስፋ የተጠራ በተላያየ ሃይማኖት ሊሆን አይችልም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ስለአንዲት ተስፋ ሰብከውላቸው ያመኑ ክርስቲያኖች አንድ ሃይማኖት ነበሩ፡፡ ጴጥሮስ ለተገረዙት ፣ ጳውሎስ ደግሞ ለአሕዛብ ቢያስተምርም ፣ ሃይማኖታችን አሁንም አንዲት ናት ፡፡ ስለዚህ ነው አንዲት ሃይማኖት ያለው፡፡

4. አንዲት ሃይማኖት ማለት አንድ አካል መሆን ነው፡፡

አንዲት ሃይማኖት ማለት አንድ አካል አንድ መንፈስ መሆን ነው፡፡ ሐዋርያው ይህንን ሲገልፅ “አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና… አካል ብዙ ብልቶች እንጂ አንድ ብልት አይደለምና…እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ።  (1ቆሮ 12፡27)።” ጌታም “እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ ዮሐ 15፡5።” እንዳለ በአንዱ ግንድ ላይ የተመሠረትን ነን፡፡ የተለያየ ጸጋ ቢኖረንም የአንዱ የክርስቶስ አካል ስለሆንን አንድ ሃይማኖት ነን እንጂ ብዙ ሃይማኖቶች አይደለንም፡፡

5. አንዲት ሃይማኖት ማለት በአንድ መንፈስ መመራት ነው፡፡

ክርስቶስ ካረገ በኋላ ቤተክርስቲያንን የሚመራት በሐዋርያት ላይ የወረደው መንፈስ ቅዱስ ነው (ሐዋ 2፡1)፡፡ ዛሬም ቤተክርስቲያንን በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል የሚመራት መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ”ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል እንዲል (1ቆሮ 12፡27)።”  በአንድ መንፈስ ቅዱስ የምንመራ አንድ እምነት አንድም ሃይማኖት እንጂ ብዙ እምነት ወይም ብዙ ሃይማኖት ሊኖረን አይችልም፡፡ ስለዚህም አንዲት ሃይማኖት ማለት አንድ መንፈስ ቅዱስ የሚመራት ማለት ነው፡፡

6. አንዲት ሃይማኖት ማለት አንድ ጊዜ የተሰጠች ማለትም ነው፡፡

ሃይማኖት አንድ ጊዜ የተሰጠች አንዲት ናት፡፡ ይህንንም “ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ (ይሁዳ 1፡3)።” ይህችም ሃይማኖት ኢየሱስ ክርስቶስ ራስ ሆኗት በአለት ላይ የመሠረታት ናት (ማቴ 16፡16)፡፡ በዚህ መሠረት ሃይማኖት ደግማ ደጋግማ የምትሰጥ አይደለችም፡፡ ለሐዋርያት የተሰጠችው ያችው ሃይማኖት ናት ዛሬም በእኛ ዘመን መኖር ያለባት፡፡ በዚህም መሠረት ሃይማኖት የምትጠበቅ (conservative) እንጂ በየጊዜው የምትሻሻል (progressive) አይደለችም፡፡ ስለዚህ ሃይማኖት አንዲት ናት፡፡

7. አንዲት ሃይማኖት ማለት አንዱን ክርስቶስን መምሰል ማለት ነው፡፡

ከአንዱ ከክርስቶስ እርሱን (ክርስቶስን) መምሰል እንዳለብን ተምረናልና ሃይማኖት አንዲት ናት፡፡ ስለዚህ ነገር ሐዋርያው “ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? … ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን (ሮሜ 6፡4-5)” ብሏል፡፡  ጌታችንም “መምህራችሁ፣ ሊቃችሁ፣ አባታችሁ አንድ ነው (ማቴ 23፡8)፡፡” ብሎ አስተምሯል፡፡ እኛ ክርስቶስን መምሰል እንዳለብንም ሲናገር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተ እኔን ምሰሉ (1ኛ ቆሮ 11፡1)” ብሏል፡፡ ጌታችንም “ከእኔ ተማሩ (ማቴ 11፡29)” “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ (1ኛ ጴጥ 1፡16)” ብሎ ገልጾታል፡፡  እንግዲህ በሃይማኖት መኖር ማለት አንዱን ክርስቶስን መምሰል ከሆነ ሃይማኖትም አንዲት ናት ማለት ነው፡፡

አንዲት እምነት ወይስ አንዲት ሃይማኖት?

አንዳንዶች “በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ‘አንድ ሃይማኖት’ ቢልም በሌሎች ቋንቋዎች ግን ‘አንድ እምነት’ ነው የሚለው ስለዚህ አንድ እምነት ያላቸው የተለያዩ ሃይማኖቶች ሊኖሩ ይችላሉ::” ብለው ይከራከራሉ፡፡ ነገር ግን ከላይ እንደተገለጸው ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር በእምነት ብቻ ሳይሆን በአምልኮም አንድ መሆን ማለትም እርሱ  ያመነውን ማመን: እንዳመነው አድርጎ ማመን እርሱም እንዳመለከው አድርጎ ማምለክ ነው ፍጹም ሊያደርግ የሚችለው፡፡ የአንዲት እምነት መገለጫዋ አንዲት ሃይማኖት ናት፡፡ የተለያየ እምነት እንጂ አንዲት እምነት በተለያየ ሃይማኖት አትገለጥም፡፡  አንዲት እምነት የምትገለፀው በአንዲት ሃየማኖት ነው፡፡ ይህም መገለጫው በአንድ አምላክ ማመለክ፣ አንዲት ጥምቀት መጠመቅ፣ ለአንድም ተስፋ መጠራት  ናቸው፡፡ ስለዚህ እምነትም ሃይማኖትም አንዲት ናት፡፡

ይህ እውነተኛይቱን እምነትና እውነተኛይቱን ሃይማኖት (በተረዳ ነገር ያወቅናትን) የሚመለከት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሌሎች እምነቶች እንደነበሩና እንደሚኖሩ  ግን በሐዋርያትም ዘመንም የታወቀ ነበር፡፡ 1ኛ ዮሐ 4፡1-3

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አስተምህሮ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ከሁሉ አስቀድመን ምስጋና የባህሪው ለሆነው አምላካችን ምስጋናን እናቀርባለን፡፡ በሥራችንም ሁሉ ይረዳን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ እንዲሆንልንም ዘወትር በፊቱ እንቆማለን፡፡

አስተምህሮ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ የጡመራ መድረክ ዛሬ ህዳር 21 ቀን 2010 ዓ.ም ተመሠረተች፡፡ የጡመራ መድረኳ ስያሜ ‘አስተምህሮ’ እንደመሆኑ በዚህ የመጀመሪያው ጡመራችን አስተምህሮ የሚለውን ቃል ትርጉም በአጭሩ እንመለከታለን፡፡ አስተምህሮ የሚለው ቃል ሁለት ዓይነት ትርጉም አለው፡፡

አንደኛ፤ አስተምህሮ ማለት የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት ማለት ሲሆን ይህም የትምህርቱን ይዘት፣ የይዘቱንም ምንጭ፣ የትምህርቱን አሰጣጥ ስልት፣ የመምህራኑና የተማሪዎቹን መስተጋብር ወዘተ… ያጠቃልላል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ከሚገለፅባቸው መንገዶች መካከልም የአደባባይ ስበከት (ለምዕመናን የሚሰበከው)፣ የወንበር ትምህርት (በአብነት ትምህርት ቤት የሚሰጠው) ፣ ልዩ ስልጠናና (በኮርስ መልክ የሚሰጠው ትምህርት) በመገናኛ ብዙሀን (በጋዜጣ በመጽሔት በድረ ገፅ) የሚሰጡት ትምህርቶች ይገኙበታል፡፡

ሁለተኛ፤ መሀረ ማለት ይቅር አለ ማለት ሲሆን፤  አስተምህሮ ማለት ይቅርታ መጠየቅ /ምልጃ/ ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስለ ልጆቿ ይቅርታ የምትጠይቅበት፤ ምዕመናንንም ስለ በደላቸው ይቅርታ የሚጠይቁበት፤ ስለዚህም በስፋት ትምህርት የሚሰጥበት ዘመንም ዘመነ አስተምህሮ ይባላል፡፡ በቤተ ክርስተያናችን የዘመን አቆጣጠር /አከፋፈል/ መሠረት ከኀዳር 6 ጀምሮ እስከ ታኀሣሥ 13 ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ አስተምህሮ ይባላል፡፡

አስተምህሮም በይዘቷ በመጀመሪያው ላይ በማተኮር ለአንባቢያን ይበጃሉ ይጠቅማሉ ያልናቸውን ትምህርቶችንና ወቅታዊ መረጃዎችን የምናደርስባት አዲስ የጡመራ መድረክ ናት፡፡ በዘመነ አስተምህሮ ስለተመሠረተችም ስያሜዋን “አስተምህሮ” ብለናታል፡፡ ለሁላችንም መልካም የአገልግሎት ዘመን እንዲሆንልን በጸሎታችሁ እንድታስቡንና ገንቢ አስተያየታችሁንም በማጋራቱ በኩል እንዳትለዩንም በትህትና እንጠቃለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር