እንዴት እንዘምር?
በዲ/ን ብሩክ ደሳለኝ
ባለፉት ሦስት ተከታታይ ክፍል የመዝሙርን ምንነትና ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ምን መምሰል እንደሚገባው አውስተናል:: አስተምህሮ በዚህ አራተኛና የመጨረሻ ክፍል ኦርቶዶክሳዊ መዝሙርን እንዴት መዘመር እንዳለብን በመጠቆም ከአዘማመር ጋር በተያያዘ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋሉ ችግሮችን ታሳያለች፤ መፍትሔዎችንም ትጠቁማለች፡፡
መዝሙር ጸሎት ስለሆነ በማስተዋል በእምነት ልንዘምር ይገባል
መዝሙር ስንዘምር ዜማውን ብቻ በማሰላሰል ሳይሆን የመዝሙሩን ምስጢር አውቀን በእምነት ሊሆን ይገባል:: “አምናችኹም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ” እንደሚል (ማቴ ፳፩:፳፪):: ስንዘምር ልባችን ወደ ሌላ ሃሳብ ተወስዶ በሥጋዊ ስሜት የሚቀርብ ከሆነ የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ እንደማንሳት እንዲሁ በከንፈር ማክበር ብቻ ይሆንብናል (ዘጸ ፳:፯ ኢሳ ፳፱:፲፫):: ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል” (ሉቃ ፲፱:፳፭) እንዳለን ህሊናችን ወደ ሌላ ሃሳብ እንዳይወሰድ ልቡናችንን እየሰበሰብን መዝሙሩም የምእመናንን ልብ ለቃለ እግዚአብሔር የለሰለሰ እንዲሆን የሚያዘጋጅ መሆን አለበት:: መዝሙር ለመላእክትና በመንፈሳዊ ተጋድሎ ላሉ ምግባቸው እንደሆነ ሁሉ በፍጹም እምነት ሳናወላውል ልቡናን በመሰብሰብ ይህን ስጦታ የምንመገበው እግዚአብሔር አምላክ ድካማችንን አለማመናችንን እንዲረዳው በመማጸን ነው::
ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በእምነት ባለማወላወል ወደ እግዚአብሔር ብንቀርብ ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ ለምነን የምናጣው እንደሌለ ይነግረናል (ያዕ ፩:፮-፰):: ስለሆነም መዝሙር ስንዘምር በልማድ ቃላትን በመደጋገምና ለመርሃ ግብር ማሟያ ለይስሙላ ሳይሆን በእምነትና በተመስጦ መዘመር ይገባል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከአገልግሎታችን ሁሉ በላይ ዝማሬያችንን በእምነት ሲሆን ደስ ያሰኘዋል (ዕብ ፲፩:፮):: ለምሳሌ በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በዓል ሠለስቱ ደቂቅን ከእቶን እሳት እንዳዳናቸው እኛም ከበዓሉ በረከትን እንዲሰጠን ስንለምን (ስንዘምር) እንደ ሦስቱ ህጻናት ባለመጠራጠር በእምነት ለዚያም በሚያበቃ ተጋድሎ እንዲሆን ያስፈልጋል:: በሌላም የጌታችንን መድኃኒታችንን ስቅለት እያሰብን ስንዘምር ክርስቶስን በእውነት የተከተሉትን እያሰብን እኛም በጊዜውም ያለጊዜውም በመታመን በቀራንዮ የነበረውን በህሊናችን እየሳልን ነው (ገላ ፫:፩)::
መዝሙር መስዋዕት ስለሆነ በንጹህ ልብ ሊቀርብ ይገባል
ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መስዋዕት ስለሆነ በልዑል እግዚአብሔር ፊት የተወደደ መስዋዕት ሁኖ እንዲቀርብ ራስን ለንስሐ በማዘጋጀት ልቡናን በማንጻት ሕይወታችንን ልዑል እግዚአብሔር የሚቀበለው እንዲሆን በማድረግ ሊሆን ይገባል:: መዝሙረኛው ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።” እንዳለ የዝማሬ መስዋዕታችን ንጹሕ ልብን እንዲሰጠን የቀናውንም መንፈስ በልቡናችን እንዲያኖርልን በመማጸን ነው (መዝ ፶:፲-፲፯ ሉቃ ፲፰:፲-፲፬):: እግዚአብሔር ትሁትና የዋህ በሆነ በተሰበረ ልብ የሚቀርብን ዝማሬ ይመለከታል:: ከቃየልና አቤል መስዋዕት የምንማረው እግዚአብሔር አምላክ ወደ መስዋዕቱ እንደተመለከተና የአቤልን መስዋዕት ንጹህ መስዋዕት አድርጎ እንደተቀበለ ነው::
እኛም በዝማሬያችን በአንድ ልብ በንጹህ ህሊና ቁመት ዝማሬያችንንም መስዋዕት አድርገን ከማቅረብ አስቀድሞ ይህን እግዚአብሔር አምላክ እንደሚፈልግ መዘንጋት የለብንም (ሐዋ ፬:፴፬):: ይህም እግዚአብሔር አምላክ ፊቱን ወደኛ እንዲመልስ የሚያደርግ ጸጋንም የሚያሰጥ ነው (፩ጴጥ ፭:፭):: በግርግር በሁከት በመገፋፋት በመለያየት በድፍረት በራስ ሃሳብ/ፈቃድ በመወሰድ ጸጋ አይገኝም (ዕብ ፲፪:፳፰-፳፱ ፪ቆሮ ፲፫:፭ ሚክ ፮:፮-፰ ሮሜ ፮:፩):: “ለአንዱ ተስፋችሁ እንደ መጠራታችሁ መጠን አንድ አካልና አንድ መንፈስ ትሆኑ ዘንድ እማልዳችኃለሁ” (ኤፌ ፬:፬):: ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሰውነታችንን በአገልግሎታችን ወቅት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርገን ልናቀርብ በዝማሬያችንም ወቅት መዘመራችንን ብቻ ሳይሆን የእኛን ልብ የሚመረምር አምላክ ፊት እንደቆምን በማስተዋል ሊሆን እንዲገባ ያሰተምረናል (ሮሜ ፩፪:፩-፭)::
መዝሙር እግዚአብሔር የሚወደው ንጹህ መስዋዕት ሁኖ ሳለ አንዳንድ መዝሙር ተብለው በሚዘመሩት ዝማሬዎች ፉከራ ያለባቸው የራሳችንን ድካም ኃጢአት የምንመለከትበት ሳይሆን ሌሎችን ብቻ የምንኮንንበት ወይም “የእኛ ይሻላል ከሌላ” የሚል ስሜት ባለበት ሲቀርብ በልዑል አምላክ ፊት መቆማችንን የዘነጋን ያደርገናል:: ክርስትና የራስን በደል እያሰቡ ለሌላውም መልካምን የምንመኝበት ልቡናን ከፍ ከፍ በማድረግ (በመንፈሳዊ ዝግጅት) የምንኖረው ሕይወት እንጂ በሕይወታችን ስንዝል በሚሰማን ጊዜያዊ ስሜት ወድቀን ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መስዋዕትን ሳይሆን ስሜታችንን ብናንጎራጉር ራሳችንን እናታልላለን:: ቅዱሳት መጻሕፍት የሚያስተምሩን ‘እዘምራለሁ ንጹሕ መንገዱንም አስተውላለሁ” (መዝ ፻:፪) “በስፍራ ሁሉ ያለቍጣና ያለክፉ አሳብ የተቀደሱትን እጆች እያነሱ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ” (፩ጢሞ ፪:፰) የሚለውን ነው:: ስለሆነም መዝሙራችን ከተነሳሂ ልቡና የሚወጣ፣ ተናጋሪውንም አድማጩንም ወደ ንስሃ የሚመራ መሆን አለበት፡፡
በአንዳንዶች ዘንድ ልማድ እንደሆነው በክርስቶስ ጸጋ ያገኘነውን የመዳን ሕይወት በራሳችን የተለየ ችሎታ ያገኘነው አስመስለን በመዝሙራችን ሌሎችን ማቃለል አይገባም፡፡ ይልቁንስ እንደ አባቶቻችን በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የየራሳችንን መዳን እንፈጽም ዘንድ በምስጋናና ራስን ዝቅ በማድረግ እግዚአብሔርን ልናመሰግን፣ ትምህርተ ሃይማኖትን ልንመሰክር ይገባል፡፡ ትህትናችን ግን ባለማወቅ መጻሕፍትን የሚተረጉሙ ሰዎች እንደሚመስላቸው ክርስቶስን የሚቃወሙትን፣ ቤተክርስቲያንን የሚያቃልሉትን፣ የሚዘርፉትን የሚያበረታታ ወይም “የማይሞቀው፣ የማይበርደው” መሆን የለበትም፡፡ መዝሙራችን ትምህርት ነውና ሰውን በሚያንጽ መልኩ፣ በፍቅር አንድ በሆነ መንፈስ በንጽህና የሚገባውን ክብር እየሰጠን ከተመላለስን በመካከላችን እንዲገኝ አምላካችን ለቃሉ የታመነ አምላክ ነው።
ዘማርያን (መዘምራን) የሚባሉት እነማን ናቸው?
በቤተክርስቲያናችን በቀዳሚነት በዝማሬ የሚታወቁት ቅዱሳን መላእክት ናቸው፡፡ እነርሱ ያለማቋረጥ “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ” እያሉ በማይሰለች ልሳን፣ በማይጠገብ ዜማ አምላካችንን በሰማያት እንደሚያመሰግኑ ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክሩልናል (ኢሳ ፮:፩-፬)፡፡ በሰማያዊ ልሳን ከቅዱሳን መላእክት ጋር እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት የሰማይ መንግስት ምሳሌ በሆነች ምድራዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን ሁሉ ዘማርያን፣ አመስጋኞች ናቸው፡፡ በተለየ ሁኔታ የቤተክርስቲያንን ዜማና አዘማመር የተማሩ ሊቃውንት መዘምራን ይባላሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሰንበት ት/ቤትና በልዩ ልዩ መንፈሳውያን ማኅበራት መዝሙር የሚዘምሩ ምዕመናን በሰንበት ት/ቤት ወጣት መዘምራን ይባላሉ፡፡ እንደዚሁም ኦርቶዶክሳዊ ዝማሬን በካሴትና በሲዲ እያዘጋጁ ለመንፈሳዊ ዓላማ የሚያውሉ ምዕመናንም እንዲሁ እየተለመደ ነው፡፡
ኦርቶዶክሳዊ ዘማሪነት ቀሚስ ከመልበስ፣ ፖስተር ከማሰራት፣ ድምጽን በካሴትና በሲዲ ከማስቀረጽ፣ ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ እነዚህ እንግዳ መገለጫዎች አንዳንድ አገልጋዮች ዘማሪነትን የገንዘብ ማግኛ ሙያ በማድረጋቸው ምክንያት ራሳቸውን ከሌላው ማኅበረ ምዕመናን ለመለየት የሚጠቀሙባቸው የንግድ ምልክቶች (trade marks) እንጅ ኦርቶዶክሳዊ ውርስ ያላቸው አይደሉም፡፡ በተለይም ዘማሪ በመባል ታዋቂነትን በማትረፍ (celebrity culture) ኦርቶዶክሳዊ መዝሙርን ብቻ ሳይሆን ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮንም ለሚቆሙለት ልዩ ልዩ ጥቅም፣ ክህደትና ምንፍቅና ሲሉ በመበረዝ ምዕመናንን ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች ከቤተክርስቲያን ማኅበር እየለዩ የሚያስኮበልሉ በበዙበት በዚህ ዘመን የዘማሪነት ግብር ትክክለኛ መገለጫዎችን መለየት ካልቻልን ለምዕመናንም በተገቢው መልኩ ካላስረዳን ታሪኩን የማያውቅ ትውልድ እንደማፍራት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ገንዘብን መውደድ የኃጢአት ሁሉ ስር እንደሆነና ይህንን የተመኙ ከሃይማኖት እንደወጡና ራሳቸውን በብዙ ስቃይ እንደወጉ ይመክረናል (፩ጢሞ ፮:፲ ቆላ ፫:፩-፫)::
ስለሆነም ዘማሪነትን ከንግድና ከታዋቂነት ገጽታ ግንባታ (celebrity culture) በእውቀትና በብልሃት መለየትና የሰይጣንን ተንኮል ማፍረስ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ከሚረዱን አሰራሮች መካከል አንዱ መዝሙራት በግለሰብ ባለቤትነት ከሚወጡ ይልቅ በሰንበት ት/ቤቶችና በማኅበራት እንዲወጡ በማድረግ ማንም የእኔነት ይዞ እንዳይመካባቸውና መውደቂያ እንቅፋትም እንዳይሆኑበት ማገዝ ይቻላል፡፡ እንደሚታወቀው ቅዱሳን መላእክትም ሆኑ አባቶቻችን መዘምራን መዝሙርን ለአምልኮና ለምስጋና በማኅበር ይዘምራሉ እንጂ አንድን ሰው በሚያገን ወይም ተከታዩን በሚያሰናክል መልኩ አይደለም፡፡ ይህ ማለት ግን አገልጋይ ዘማርያን በግል መዘመራቸው በራሱ ችግር ነው ማለት እንዳልሆነ ማስተዋል ይገባል፡፡ ዓላማውን ተረድተው፣ የቤተክርስቲያንን ትምህርትና ሥርዓት ጠብቀው፣ ለግል እውቅናና ጥቅም ሳይሆን ለቤተክርስቲያን ልዕልና የሚዘምሩትን በህሊና ዳኝነት እየተመራን ልናግዛቸው፣ ልናበረታታቸው ይገባል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ በመዝሙር የሚያገለግሉ ሁሉ የቤተክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት አክብረው የሚያስከብሩ በሕይወታቸውም አርአያነት ያላቸው ሊሆኑ ይገባል:: አገልግሎቱን የሚሰጡ ለጸሎት የሚተጉ በሥርዓተ ቅዳሴ የሚሳተፉ ሕይወታቸው የሚያስተምር አለባበሳቸውና በሰውነታቸው ላይ የሚያኖሩት ጌጣ ጌጦች ግራ የሚያጋባ መሆን የለበትም:: ዛሬ ላይ እንደልማድ ተወስዶ በተለያየ ማህበራዊ ዝግጅቶች ላይ ዘማርያን ለሰማያዊው ዝማሬ ለታላቁ አገልግሎት ከተጠራን በኋላ ቀድመን ስንመላለስበት በነበረው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደመከረን እንደክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ቤተ ክርስቲያንን በሚያስነቅፍ ሕይወት በዘፈኑ በስካሩ በጸብ በማይጠቅም የክርክር ሕይወት ልንታይ አይገባም (ቆላ ፪:፰ ያዕ ፫:፩ ሮሜ ፪:፳፩):: ሰይጣን ከመውደቁ በፊት አገልግሎቱ ምስጋና ነበር:: የሰው ልጅም እርሱ በለቀቀው አገልግሎት እንዳይሰማራ ሰማያዊ ከሆነው መዝሙር ይልቅ ሥጋዊ ስሜትን በሚጋብዝ ከስጦታችን ውጭ እንድንመላለስ ያለበረከት ያለዋጋ እንድንቀር በልቡናችን እንክርዳድን ይዘራል:: “አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን በኋላም የካዱትን እንደገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው” (ሮሜ ፮:፬-፮)::
አዘማመራችን የሚያስነቅፍ መሆን የለበትም
ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎትን ያለሥርዓት መፈጸም እንደማይገባ ታስተምራለች፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓት ማለት በመጻህፍት የተጻፈ ብቻ ማለት አይደለም፡፡ በጽሑፍ ከተቀመጡ ሥርዓቶች ባሻገር በልማድ የዳበሩ ሕግጋት አሉ፡፡ ከአዘማመር እንቅስቃሴያችን ጋር የተያያዙ ችግሮች የሚፈጸሙት መዘምራን በግል ወይም በጋራ በሚዘምሩበት ወቅት ነው፡፡ ለምሳሌ ዓይን ጨፍኖ መዘመር፣ ያለ ልክ መጮህ፣ ከመጠን በላይ መዝለል፣ ከሚገባ በላይ እንቅስቃሴን ያካትታል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለፍጥረታት ሥርዓትን እንደሰራላቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የቆሮንቶስ ሰዎችን ያለሥርዓት በመሄዳቸው እንደገሰጻቸው እኛም እግዚአብሔር የሥርዓት አምላክ እንደሆነና በቤተክርስቲያን የሚከናወኑ አምልኮታዊ ሥርዓቶች አሰላለፋችንና እንቅስቃሴያችን እግዚአብሔር የሥርዓት አምላክ መሆኑን በመረዳት ወንጌልን የሚሰብክ በአገባብና በሥርዓት ሊሆን ይገባል (፩ቆሮ ፲፬:፵ መዝ ፻፵፪:፮ መዝ ፭:፫ ፩ቆሮ ፲፬:፵)::
በቤተክርስቲያናችን ልማድ በማኅሌትና በመዝሙር ወቅት ስሜታዊ የሚሆኑ አገልጋዮች ቢኖሩ እንኳ የቤተክርስቲያን አባቶች ጸናጽሉን በመጠቀም ምልክት እየሰጡ ያስቆሟቸዋል እንጅ ለነቀፋ አሳልፈው አይሰጧቸውም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያለአውዳቸው የሚጠቅሱ የሚቆነጻጽሉ ሰዎች ክቡር ዳዊት በታቦተ ጽዮን ፊት ራስን በመናቅ ከዘመረው መዝሙር ጋር በማስመሰል የዋሃንን ለማሳት ይሞክራሉ፡፡ ሰይጣን ሁልጊዜም ስህተቱን በቃለ እግዚአብሔር የተደገፈ ለማስመሰል እንደሚጥር ይታወቃል፡፡ እኛ ግን እናስተውል፣ ተመስጦና ራስን መናቅ ከስሜታዊነት ጋር አይገናኙም፡፡ ይልቁንም ተመስጦና ስሜታዊነት ተቃራኒዎች ናቸው፡፡ ክቡር ዳዊት በተመስጦ፣ ራስን ዝቅ በማድረግ ዘመረ እንጅ ስሜታዊ አልነበረም፡፡ መዝሙር ስንዘምር ሊኖረን የሚገባው ተመስጦ ብንችል አባታችን ቅዱስ ያሬድ በንጉሡ በአጼ ገብረመስቀል ፊት ሲዘምር በጦር መወጋትን እንኳ እስከማይሰማው ድረስ የተመሰጠውን ተመስጦ ሊመስል ይገባል፡፡
ስንዘምር ሰዎች ምን ይሉናል ብለን ለራሳችን ክብር ከተጨነቅን ለክቡር ዳዊት የተሰጠ ቡራኬ ይቀርብናል፡፡ በዝማሬያችን እግዚአብሔር አምላክ የብርሃን አምላክ ነው ስንል ዓይናችንን ወደ እርሱ በማቅናት (በመጨፈን ሳይሆን መዝ ፻፵፪:፮) በእንቅስቃሰያችንም መገፋቱን መከራ መቀበሉን ስንመሰክር መንፈሳዊ ዋጋም አለን:: ምድራዊ ሥርዓት ልዩ አሰላለፍና ክብር ካለው ለሰማይና ምድር ፈጣሪ የሚቀርበው መላው እንቅስቃሴያችን የድምጽ አወጣጣችን እንደአንድ ልብ መካሪ አንድ ሃሳብ ተናጋሪ ተጨንቀን ተጠበን ሊሆን ይገባል:: በዚህም እግዚአብሔር አምላክ የአቤልን መስዋዕት እንደተመለከተ የእኛንም በመዝሙር የምስጋና መስዋዕት ይቀበልልናል::
በመዝሙር ወቅት የዜማ መሣርያዎች አጠቃቀማችንና አያያዛችን እንዲሁም መዝሙሩን ከጨረስን በኋላ ስናስቀምጣቸው እንዲሁ በሥርዓቱ መሆን አለበት፡፡ በካህናት የማህሌት ዝማሬን ስንመለከት ካህናቱ ከበሮውን ሲመቱ እንዲሁ በዘፈቀደ ሳይሆን ምስጢርን ጠብቀው ሲጀምር በእርጋታ ምሳሌነቱም አይሁድ ጌታችንን እያፌዙ ለመምታታቸው ዝማሬው ተሸጋግሮ በፍጥነት ሲመታም ሰንበት እንዳይገባባቸው በዚህም ጲላጦስም ምክንያትን አግኝቶ እንዳያድነው በማለት ያንገላቱበት ምሳሌ ነው:: “በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ። በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ” እንዲል (ቆላ ፫:፲፮)። የከበሮ ሰፊው አፍ (ገጽ) የመለኮት ምሳሌ ነው ስላልን ስናስቀምጥም አስተማሪነት እንዲኖረው ወደ ላይ መሆን አለበት:: ይህም ለሚመለከተው እንቅስቃሴያችን ድርጊታችን በመላው ሥርዓታችን ወንጌል የክርስቶስ መስቀል ሁኖ የተዋህዶን ምስጢር አስረጅ ለእኛም ለእግዚአብሔር ተብሎ የተለየን የዜማ መሳርያ የሚገባውን ክብር መስጠታችን ዋጋን የሚያሰጠን ነው::
በአጠቃላይ በዝማሬያችን የሌላውን ተመስጦ በማይነካ አንድ ወጥ በሆነ የእንቅስቃሴ ስልት በሙሉ ስሜታችን ይህን ታላቅ ምስጢር እያስተዋልን የመዝሙሩን ባለቤት ልዑል እግዚአብሔር መዝሙሩን በአንደበታችን እንዳኖረልን ተገንዝበን ልንዘምር ይገባል (ያዕ ፩:፰):: ሌላው በመዝሙር አገልግሎት ልናስተውል የሚገባን የምንዘምረው መዝሙር ወቅቱን የጠበቀ መሆኑን ነው:: ቤተክርስቲያን ሁሉ ነገሯ ሥርዓት ነውና ዓመቱን በዘመናት ከፍላ ለምስጋናም የሚስማማውን ሰርታ አዘጋጅታለች:: በሃይማኖት ጸሎታችን አንዲት ቤተክርስቲያን ብለን እንደመሰከርን ወቅቱን ጠብቀን ከዕለቱ ጋር የሚስማማውን ብንዘምር የአባታችንን ቤት ያወቅን ለእናታችን ቤተ ክርስቲያንም ታዛዦች ነን::
ማጠቃለያ
ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መስዋዕት እንጂ ለሰዎች የሚቀርብ ‘ዝግጀት’ አይደለም፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አምላክ የሥርዓት አምላክ ነውና ለእርሱም የሚቀርብ መዝሙር በሥርዓት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ቤተክርስቲያንም በሁሉ አገልግሎታችን እና ተሳትፎአችን መንፈሳዊ ዋጋ እንዲያሰጠን ዓመቱን በዘመናት ከፍላ በዝማሬያችንም ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት ባደረገና የቅዱሳን አባቶችን አሰረ ፍኖት በተከተለ አካሄድ ሰማያዊውን የዜማ ስልት ተከትለን አስተማሪነት ባለው ምስጋና እንድናመሰግን ሥርዓትን ሠርታልናለች:: እኛም በሁለንተናችን ትምህርቷን መስለን ለቤተክርስቲያንም ሥርዓት የመገዛት መንፈሳዊ ግዴታ አለብን:: በግልም ሆነ በማኅበር ስንዘምር ልናስተውላቸው የሚገቡንን እያስተዋልን፤ ዝማሬያችንም ፍጹም ለልዑል እግዚአብሔር የሚቀርብ ስለሆነ ‘መታዘዝ ከመስዋዕት ይበልጣልና’ በፍጹም ትህትናና በእምነት፤ ለቤተ ክርስቲያንም ሥርዓት በመታዘዝና ዋጋ የሚያሰጠን እንደሚሆን በማሰብ ሊሆን ይገባል:: የመዝሙሩ የምስጢር፣ ቅንብር እና የእንቅስቃሴ ስልት ምስጢሩን የጠነቀቀና ወቅቱን የጠበቀ ሆኖ የዝማሬም ሥርዓታችን ከቤተክርስቲያን ሥርዓት አንጻር በጾም በበዓላት በዘመናት መደብ ሰጥታ እንዳቆየችልን ሁሉ ሊዘመሩ የሚገባቸውን ዝማሬዎች እንደሥርዓቱ ልንከተላቸው ይገባል:: ለዚህም ሰንበት ትምህርት ቤቶች ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን የተከተለ የመዝሙር ሥርዓት እንዲኖር ትልቁን አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ::
ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን!
Pingback: ዘማሪ ማስመጣት፡ በሐዋርያዊ ጉዞ ላይ የዘማርያን ሚና – አስተምህሮ