ቅዱሳን ሐዋርያት፡ ንጹሐን የሆኑ የሕግ ምንጮች

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ የጾመ ሐዋርያት መጨረሻ ላይ ሐምሌ 5 ቀን ጴጥሮስ ወጳውሎስ በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልካሙን የክርስትና ገድል ተጋድለው ሰማዕትነት የተቀበሉበትን ቀን በታላቅ መንፈሳዊ ሥርዓት ታከብራለች። በተመሳሳይ መልኩ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የሌሎችንም ቅዱሳን ሐዋርያት ዜና ገድላቸውን መዝግባ በመያዝ አገልግሎታቸውን ትዘክራለች፤ በጸሎታቸው፣ በምልጃቸው፣ በቃልኪዳናቸው ትማጸናለች፡፡ እኛም ኦርቶዶክሳውያን ሁላችን የቤተክርስቲያንን ፈለግ ተከትለን እንዲሁ እናደርጋለን፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት የቤተክርስቲያን አዕማድ ናቸው፡፡ በእነዚህ አስተምህሮና የመጻሕፍት ትርጓሜ ላይ የተመሠረተች ቤተክርስቲያንም ‹‹ሐዋርያዊት›› ትባላለች፡፡ በዚህ አጭር የአስተምህሮ ጦማርም የቤተክርስቲያን አዕማድ የተባሉ የቅዱስ ጴጥሮስና የቅዱስ ጳውሎስን ታሪክ ምሳሌነት በመጠቀም ስለ ሐዋርያት እንዲሁም የሐዋርያትን ሥልጣንና ኃላፊነት እስከ ዓለም ፍጻሜ ስለሚሸከሙ የቤተክርስቲያን ካህናት እንዳስሳለን፡፡

የሐዋርያትን ስያሜ በተመለከተ ቅዱስ ሉቃስ እንዲህ ሲል አስፍሮታል፡፡ ‹‹በእነዚያም ወራት ይጸልይ ዘንድ ወደ ተራራ ወጣ፡፡ ሌሊቱን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ፡፡ በነጋም ጊዜ ደቀመዛሙርቱን ጠራ፡፡ ከእነርሱም 12 መረጠ፡፡ ደግሞም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው (ሉቃ 6፡12-14)፡፡›› የሐዋርያት (የካህናት) ሲመት እንዴት መሆን እንዳለበት ሥርዓትን ሲሠራ በመጀመሪያ ወደ ተራራ ወጣ፡፡ ተራራ የተባለች ቤተክርስቲያን ናት፡፡ በዚያም ሲጸልይ አደረ፡፡ የሐዋርያት ሲመት ከእግዚአብሔር ነውና የእርሱን ፈቃድ መጠየቅ እንደሚገባ በዚህ አስተማረ፡፡ ከዚያም ከመምረጥ በፊት መጥራት ይቀድማልና ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፡፡ የተጠራ ሁሉ አይመረጥምና 12ቱን ብቻ መረጣቸው፡፡ በእርሱ በራሱ ፈቃድ መረጣቸው፡፡ ስማቸውንም ሐዋርያት ብሎ በክብር ሰየማቸው፡፡ ሐዋርያ የሚለው ቃል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለ12ቱ ደቀ መዛሙርት የሰጣቸው ስም (ስያሜ) ነው፡፡ ለመሆኑ ሐዋርያ ማለት ምን ማለት ነው? የአንድ ሐዋርያ ኃላፊነትስ ምንድን ነው? እኛስ ለእግዚአብሔር ሐዋርያት ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?

ሐዋርያ ማለት የተመረጠ (ምርጥ) ማለት ነው፡፡

ሐዋርያ ማለት በሰው ፈቃድ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ ሰውን ለማገልገል ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ለሚከናወነው መንፈሳዊ አገልግሎት የተመረጠ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያት አንተ ለዚህች አገልግሎት የመረጥከውን ሹም እንዳሉ (ሐዋ 1፡26) መራጩ እግዚአብሔር ነው፡፡ የሐዋርያነት ምርጫው በገንዘብ አይደለም፡፡ ሲሞን በገንዘቡ ሊመረጥ አስቦ ከነገንዘቡ ጠፍቷልና (ሐዋ 8፡18)፡፡ በዝምድናም አይደለም፡፡ መራጩ ሁሉንም እኩል የሚያይ ፍትሐዊ ንጉሥ ነውና፡፡ በእውቀት ብዛትም አይደለም፡፡ እውቀት ያስታብያልና፤ያልፋልምና (1ኛ ቆሮ 8፡1)፡፡ የሐዋርያነት ምርጫው በጸሎት (በእግዚአብሔር ፈቃድ) ነው እንጂ፡፡ ስለዚህ ሐዋርያት በጌታ ፈቃድ ተመረጡ፡፡ ሲመርጣቸውም በተራራው ሲጸልይ ያደረው ይህንን ሊያስተምር ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰምዖንን ከአሳ አጥማጅነት ጠርቶ ስሙን ወደ ጴጥሮስ (ዐለት) ቀይሮ በግብሩም ሰውን በወንጌል እንዲያጠምድ አድርጎታል፡፡ ሳውልን ደግሞ ከአሳዳጅነት ጠርቶ ስሙም ወደ ጳውሎስ (ብርሃን) ተቀይሮ የክርስቲያኖች አሳዳጅ የነበረው የቤተክርስቲያን አምድ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ባለትዳሩ ጴጥሮስን በአረጋዊነት፣ ድንግል የነበረውን ጳውሎስን በወጣትነት የጠራቸው ለሐዋርያነትም የመረጣቸው በእርሱ በራሱ ፈቃድ ነበር፡፡ አንዱ ኦሪትን ያላወቀ፣ ሌላው ኦሪትን የጠነቀቀ ቢሆኑም ሁለቱንም ለሐዲስ ኪዳን የሐዋርያነት አገልግሎት ጠራቸው፡፡

ሐዋርያ ማለት የተላከ (መልእክተኛ) ማለት ነው፡፡

ሐዋርያ ማለት እግዚአብሔር የላከው፤ የእርሱንም ወንጌል የሚመሰክር መልእክተኛ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያ የእግዚአብሔር በጎች ከጠፉበት እንዲፈልግ የተላከ መልእክተኛ ማለት ነው፡፡ እንደ በግ በተኩላ መካከል የተላከ፣ የዋህና ብልህ ሆኖ በጎችን ከተኩላዎች የሚታደግ መልእክተኛ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያ ለዓለሙ ሁሉ እስከ ዓለም ዳርቻ የተላከ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነው፡፡ ለእገሌ ወገን ወይም ለተወሰነ ልሳን ተናጋሪዎች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የተላከ መልክተኛ ማለት ነው፡፡ በሄደበትም ያላመኑትን እያስተማረ  እያጠመቀ ደቀ መዝሙር የሚያደርግ  መልክተኛ ነው (ማቴ 28፡28)፡፡ ጌታ በእርገቱ ዕለት ‹‹እስከምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ›› (ሐዋ 1፡8) እንዳለው እስከ ዓለም ዳርቻ ለተላከለት ዓላማ ምስክር የሚሆን ማለት ነው፡፡ የክርስቶስ ምስክር ማለትም የእርሱን ቃል የሚመሰክር ማለት ነው፡፡ ሰላምን የሚሰብክ፣ ሃይማኖትን የሚያጸና፣ ትውልድን የሚያንጽ የክርስቶስ መልእክተኛ እውነተኛ ሐዋርያ ይባላል፡፡ የሰይጣን መልእክተኞች ደግሞ የሐሰት ሐዋርያት ይባላሉ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ እውነተኛ ሐዋርያ (መልእክተኛ) ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እያስተማረ ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ ሲደርስ ሰዎች ማን እንደሚሉት ሐዋርያትን ጠየቃቸው። ሐዋርያትም “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፣ አንዳንዱ ኤልያስ ነው፥ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል” ሲሉ መለሱለት። ጌታችንም ‹‹ለመሆኑ እናንተስ ምን ትሉኛላችሁ›› ብሎ ስለ እርሱ ያላቸውን ግንዛቤ ጠየቃቸው።በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ›› ሲል መሰከረ። ጌታችን “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ አንተ ብፁዕ ነህ፤በሰማያትያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና። እኔምእልሃለሁ፥ አንተ ዐለት ነህ፥ በዚያች ዐለት ላይም ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፥የሲኦል በሮችም አይበረታቱባትም” (ማቴ. 16፡13-19)። ይህ እውነተኛ የጴጥሮስ ምስክርነት ለቤተክርስቲያን መሠረት ሆኗል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ስምንት ምዕራፎችን የያዘ ሁለት መልእክታትን ጽፎ ለክርስቲያኖች ሁሉ ምስክር ሆኗል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም እውነተኛ የወንጌል መልእክተኛ ነበር፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎቱንም የጀመረው ጌታ ካረገ በሰባት ዓመት በኋላ ነበር፡፡ በተለይም በወቅቱ አሕዛብ ይባሉ የነበሩትን በማስተማር ክርስትናን ያስፋፋ ታላቅ ሐዋርያ ነበር፡፡ አራት ታላላቅ ሐዋርያዊ ጉዞዎችን በማድረግ ወንጌልን በዘመኑ ሁሉ የመሰከረ የክርስቶስ ሐዋርያ ነበር፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አንድ መቶ ምዕራፎችን የያዙ አሥራ-አራት መልእክታትን ጽፏል። ይህን በማድረጉ የታሠረ የተንገላታ ነገር ግን ሁል ጊዜ ስለ ቤተክርስቲያን ሲያስብ የነበረ ታላቅ ሐዋርያ ነበር፡፡

ሐዋርያ ማለት የሚከተል (ተከታይ) ማለት ነው፡፡

በሌላም በኩል ሐዋርያ ማለት ተከታይ ማለት ነው፡፡ ክርስቶስን የሚከተል የክርስቶስ ሐዋርያ ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ‹‹ተከተሉኝ›› ብሎ እንደጠራቸው ሁሉ ሐዋርያ ማለት ተከታይ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያት ጌታን የተከተሉት በሁለት መንገድ ነው፡፡ የመጀመሪያው በመዋዕለ ሥጋዌ (በሥጋው ወራት) በእግር ተከትለውታል፡፡ ከዋለበት እየዋሉ ካደረበት እያደሩ ከእግሩ ሥር ቁጭ ብለው እየተማሩ በእግር ተከትለውታል፡፡ ሁሉን ትተው ተከትለውታል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በግብር (በሕይወትና በአገልግሎት) መከተል ነው፡፡ እርሱ እንደጾመ እየጾሙ፣ ዞሮ እንዳስተማረ ዞረው እያስተማሩ፣ መከራን እንደታገሰ መከራን እየታገሱ ተከትለውታል፡፡

ሁሉን ትቶ እግዚአብሔርን የሚከተል በመጨረሻ ታላቅ ዋጋ አለው (ማቴ 19፡27)፡፡ በሕይወቱና በአገልግሎቱ ሁሉ እግዚአብሔርን የሚያስቀድም፣ እንደ እግዚአብሔር ሕግ የሚመራ ሐዋርያ ነው፡፡ ‹‹ፍለጋውን ትከተሉ ዘንድ ምልክትን ሊተውላችሁ እርሱ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአል›› (1ና ጴጥ 2፡21) እንደተባለው እውነተኞቹ ሐዋርያት ክርስቶስን መስለውታል፤ ተከትለውታልም፡፡ እውነተኛ ሐዋርያ ክፉ ምኞትን የማይከተል፣ የዓለምን ጣዕም የማይከተል ሊሆን ይገባዋል፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድና የዓለምን ጣዕም አብሮ መከተልም አይቻልም፡፡ ሐዋርያ ገንዘብንም አይከተልም፡፡ ሐዋርያ አርአያ ሆኖ ሌሎችን ወደ እግዚአብሔር የሚመራ መንፈሳዊ መሪም ጭምር ነው፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታን ሲከተል ጌታችን በደብረታቦር ብርሃነ መለኮቱን ገልጾለታል፡፡ በደብረ ዘይት ተራራም ነገረ ምጽአቱን ሰምቶ፣ በጸሎተ ሐሙስም በጌታ እግሩን የታጠበ ሐዋርያ ነው፡፡ ጌታችን በተያዘባት በዚያች ሌሊት ግን ጌታን አላውቀውም ብሎ ሦስት ጊዜ ክዶታል፡፡ ነገር ግን አምርሮ በማልቀሱ ጌታችን ወደ ቀደመ ክብሩ መልሶት በጥብርያዶስ አደራን ተቀበለ፡፡ በበዓለ ሃምሳም በአንድ ትምህርት ሦስት ሺ ሰዎችን አሳምኖ ተጠምቀዋል፡፡ ጌታችንን አምኖ የሚከተል ቢወድቅም እንኳን በንስሐ ተነስቶ ይደምቃል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ጌታን ተከተለ፡፡ በግብር በአገልግሎት ተከተለው፡፡ ጌታችን ዞሮ እንዳስተማረ ቅዱስ ጳውሎስም ዞሮ አስተምሯል፡፡ እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተ ደግሞ እኔን ምሰሉ ያለው እርሱ ክርስቶስን በሕይወት ስለተከተለው ነው፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችንን ‹‹ሁሉን ትተን ተከተልንህ፣ እንግዲህ ምን እናገኛለን?›› ሲል በጠየቀ ጊዜ ጌታም “የተከተላችሁኝ እናንተ በዳግም ልደት በ12ቱ ዙፋን ትቀመጣላችሁ፤በ12ቱም ነገደ እሥራኤል ትፈርዳላችሁ። ስለስሜም ቤትን፣ ወይም ወንድሞችን፣ ወይም እኅቶችን፣ ወይም አባትን፣ ወይም እናትን፣ ወይም ሚስትን፣ ወይም ልጆችን፣ ወይም ርስቱን የተወ መቶ እጥፍ ዋጋ ያገኛል” ብሎ መመለሱ እውነተኞቹ ሐዋርያት ያላቸውን ታላቅ ክብር ያሳያል (ማቴ. 19፡27-28)።

ሐዋርያ ማለት የሚጠብቅ (ጠባቂ) ማለት ነው፡፡

ሐዋርያ ማለት ጠባቂ ማለት ነው፡፡ የጌታውን በጎች፣ ጠቦቶች፣ ግልገሎች የሚጠብቅ ማለት ነው፡፡ ሐዋርያ ጌታ በደሙ የዋጃትን ቤተክርስቲያንን የሚጠብቅ ታማኝ አገልጋይ ማለት ነው (ሐዋ 23፡20)፡፡ ተኩላ ሲመጣ በጎቹን ትቶ የማይሸሽ፣ ከተኩላም ጋር ተመሳጥሮ በጎቹን አሳልፎ የማይሰጥ፣ ራሱን ስለ በጎቹ አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ እውነተኛ ሐዋርያ ነው (ዮሐ 10፡11)፡፡ ሐዋርያ የእግዚአብሔርን በጎች ቃለ እግዚአብሔርንና የክርስቶስን ሥጋ ወደሙን እየመገበ የሚንከባከብና መንፈሳዊ ሕይወታቸውን የሚያሳድግ ነው፡፡ እውነተኛ ሐዋርያ በጎቹ በኃጢአት ቢታሰሩ በንስሐ የሚያስፈታ ታማኝ አገልጋይ ነው፡፡ እውነተኛ ሐዋርያ በጎቹን በስማቸው የሚያውቃቸው፤ በጎቹም ድምፁን የሚያውቁት ጠባቂ ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቸር ጠባቂ እንደሆነ (ዮሐ 10፡11) የእርሱም ሐዋርያት ቸር ጠባቂዎች ነበሩ፡፡ የጠባቂነቱን ኃላፊነት በቅዱስ ጴጥሮስ አማካኝነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ‹‹ምሳ ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ግልገሎቼን አሰማራ አለው።  ደግሞ ሁለተኛ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ጠቦቶቼን ጠብቅ አለው። ሦስተኛ ጊዜ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። ሦስተኛ። ትወደኛለህን? ስላለው ጴጥሮስ አዘነና። ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ኢየሱስም። በጎቼን አሰማራ። (ዮሐ 21፡15-17)

ሐዋርያ ማለት እንደራሴ (ተወካይ) ማለት ነው፡፡

ሐዋርያ ማለት በምድር ላይ ያለ የክርስቶስ እንደራሴ ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ካረገ በኋላ በምድር ላይ ያሉ ተወካዮች (ምስክሮች) ሐዋርያት ናቸው፡፡ ሐዋርያት የማሰር የመፍታት ስልጣንን የተሰጣቸው የክርስቶስ እንደራሴዎች ናቸው (ማቴ 18፡18)፡፡ እናንተን የተቀበለ እኔን ይቀበላል ያለውም ለዚህ ነው፡፡ በርኩሳን መናፍስት ላይ ስልጣንን የሰጣቸውም የእርሱ እንደራሴዎች ስለሆኑ ነው (ማቴ 10፡1)፡፡ ሕሙማንን በተአምራት እንዲፈውሱ ስልጣን የሰጣቸው፤ በደዌ የገባውን በተአምራት በክህደት የገባውን በትምህርት እንዲያስወጡ ስልጣንን የሰጣቸው፤ ሰውና እግዚአብሔርን የሚያስታርቅ ስልጣንን የሰጣቸው፤ በመጨረሻው ቀን (ባስተባሩት ወንጌል) የመፍረድ ስልጣን የሰጣቸው (ማቴ 19፡28) የእርሱ ተወካዮች ስለሆኑ ነው፡፡ ይህም ስልጣን ለሠሩበት ክብርን ያስገኘ ለማይሠበት ደግሞ የሚያስጠይቅ ነው፡፡

ሐዋርያት ጌታ በሰጣቸው ስልጣን ብዙ ተአምራት አድርገዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በየስፍራው ሁሉ ሲዞር በልዳ ወደሚኖሩ ቅዱሳን ደግሞ ወርዶ በዚያም ከስምንት ዓመት ጀምሮ በአልጋ ላይ ተኝቶ የነበረውን ኤንያ የሚሉትን አንድ ሰው ፈውሶታል (ሐዋ.9፡32-33)።  በኢዮጴም ጣቢታ የሚሉአት አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፥ ትርጓሜውም ዶርቃ ማለት ነው፤ እርስዋም መልካም ነገር የሞላባት ምጽዋትም የምታደርግ ነበረች። በዚያም ወራት ታመመችና ሞተች፤ ጴጥሮስም ሁሉን ወደ ውጭ አስወጥቶ ተንበርክኮም ጸለየ፥ ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ። ጣቢታ ሆይ፥ ተነሺ አላት። እርስዋም ዓይኖችዋን ከፈተች ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ተቀመጠች። እጁንም ለእርስዋ ሰጥቶ አስነሣት፤ ቅዱሳንንና መበለቶችንም ጠራ ሕያውም ሆና በፊታቸው አቆማት። (ሐዋ. 9፡36-41)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ታላላቅ ተአምራቶችና ድንቅ ያደርግ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፥ ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር (ሐዋ. 19፡11-13)። አውጤኪስ የሚሉትም አንድ ጎበዝ በመስኮት ተቀምጦ ታላቅ እንቅልፍ አንቀላፍቶ ነበር፤ ጳውሎስም ነገርን ባስረዘመ ጊዜ እንቅልፍ ከብዶት ከሦስተኛው ደርብ ወደ ታች ወደቀ፥ ሞቶም አነሡት። ጳውሎስም ወርዶ በላዩ ወደቀ፥ አቅፎም። ነፍሱ አለችበትና አትንጫጩ አላቸው። ወጥቶም እንጀራ ቆርሶም በላ፤ ብዙ ጊዜም እስኪነጋ ድረስ ተነጋገረ እንዲህም ሄደ። ብላቴናውንም ደኅና ሆኖ ወሰዱት እጅግም ተጽናኑ። (ሐዋ. 20፡7-12)

የቅዱሳን ሐዋርያት ክብር

ክርስትና ፈተናና መከራ የበዛበት ስለሆነ እውነተኛ ሐዋርያ ማለት በዚህ መከራ ውስጥ የሚጋደልና እርሱ ለክብር በቅቶ ሌሎችንም ለክብር የሚያበቃ ማለት ነው፡፡ የሐዋርያት አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ መከራን እንደተቀበለ እነርሱንም በምድር ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነገር ግን አይዞአችሁ ብሎ ተስፋን እንዲሰንቁ አስቀድሞ ነግሯቸዋል፡፡ ወንጌልን ስላስተማሩ የጨለማ ሥራ ይሠሩ የነበሩ ሥራቸው እንዳይገለጥባቸው ‹‹ብርሃንን ለማጥፋት›› ሲሉ ሐዋርያት ላይ መከራ አጽንተውባቸዋል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ በእሥር ተንገላተዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በድንጋይም ተወግሯል፡፡ እነዚህ ሁለቱ የቤተክርስቲያን አዕማድ የሆኑት ሐዋርያት ያረፉትም በሰማዕትነት ነው፡፡ ሁለቱም ያረፉት በ67 ዓ.ም. ኔሮን ቄሣር በቅድስት በቤተክርስቲያን ላይ መራር ትእዛዝን ባስተላለፈበት ዘመን ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ቁልቁል ተዘቅዝቆ በመሰቀል፥ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ በ74 ዓመት ዕድሜው በሮም ከተማ በኦስትያ መንገድ አንገቱን ተሰይፎ ክብረ ሰማዕትነት ተሸልመዋል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ አስቀድሞ ስለዚህ የሰማዕትነት ክብር ሲናገር ‹‹በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል። መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም (2ኛ ጢሞ 4፡6-8)›› ብሏል፡፡ ቤተክርስቲያናችንም እነዚህን ሐዋርያት ሁል ጊዜ ታስባቸዋለች፡፡ ቤተክርስቲያን የሐዋርያትን ክብር የምታስበው በሐዋርያት ጾምና በበዓለ ሐዋርያት ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ ባለው ቅዳሴ ነው፡፡ በቅዳሴው ሁሉ ከሐዋርያት መልእክት ሁለት እንዲሁም ከሐዋርያት ሥራ የዕለቱን ክፍል እያነበበች መልእክታቸውንና አገልግሎታቸውን ታስባለች፡፡ ለምሳሌ ከቅዳሴው የሚከተለውን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስ ሠናየ መልእክት ፈዋሴ ዱያን ዘነሣእከ አክሊለ ሰአል ወጸሊ በእንቲአነ ያድኅን ነፍሳተነ በብዝኃ ሣህሉ ወምሕረቱ በእንተ ስሙ ቅዱስ” (ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስ መልእክትኽ የበጀ ያማረ ድውያንን የምታድን አክሊልን የተቀበልክ ሆይ በይቅርታውና በቸርነቱ ብዛት ስለ ቅዱስም ስሙ ሰውነታችንን ያድን ዘንድ ስለኛ ለምን ጸልይም)

ተውህቦ መራኁት ለአቡነ ጴጥሮስ ፣ ወድንግልና ለዮሐንስ ወመልእክት ለአቡነ ጳውሎስ እስመ ውእቱ ብርሃና ለቤተ ክርስቲያን” (ለአባታችን ለጴጥሮስ መክፈቻ ፣ ለዮሐንስም ድንግልና ፣ ለአባታችን ለጳውሎስም የቤተ ክርስቲያን ብርሃኗ ርሱ ነውና መልእክት ተሰጠው)›› (መጽሐፈ ቅዳሴ)፡፡

 ቤተክርስቲያናችን ለቅዱሳን ሐዋርያት ያላትን ክብር ከምትገልጽባቸው መካከል አንዱ የሐዋርያትሥራ ከመነበቡ በፊት ካህኑ “ንጹሐን ከሚኾኑ ከሕግ ምንጮች የተገኘ ጥሩ ምንጭ፣ ይኸውም የሐዋርያት የሥራቸው ነገር ነው፤”ብሎ የሚያውጀው ይገኝበታል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት እንደዚህ ንጹሐን የሚሆኑ የሕግ ምንጮች፤ አገልግሎታቸውም ጥሩ ምንጭ ነው፡፡

እኛና ቅዱሳን ሐዋርያት

በዘመናችን ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚተጉ (በተለይ በክህነቱ) ሐዋርያት ናቸው፡፡ እነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ እነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ እነ አቡነ አረጋዊ የእኛ ሐዋርያት ነበሩ፡፡ ስልጣን ከኃላፊነትና ከተጠያቂነት ጋር የተሰጠው ለዚህም የሚተጋ እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊ አገልጋይ ዛሬም እንደ ጥንቱ ሐዋርያ ነው፡፡ ይህን ስልጣን የሰጣቸው አምላካችን እግዚአብሔር ስለሆነ ስልጣናቸውንና እነርሱን ልናከብር ይገባል፡፡ እግዚአብሔር አክብሮአቸዋልና፤ በማክበራችንም እንከብርበታለንና ማክበር ይኖርብናል፡፡ በዚህች ምድር ላይ ላሉ እውነተኞች የክርስቶስ ሐዋርያት ልንጸልይላቸውም ይገባል፡፡ የሃይማኖትን መንገድ ያቀኑ ዘንድ፤ ፈተና ይርቅላቸው ዘንድ በጸሎታችን ልናግዛቸው ይገባል፡፡ ቤተክርስቲያንም ይህ ጸሎት በቅዳሴው ጸሎት እንዲካተት ያደረገችው ለዚህ ነው፡፡ በአፀደ ገነት ያሉት ሐዋርያት በረከታቸው  እንዲደርሰን መታሰቢያቸውን ማድረግ፣ በምድር ያሉት ደግሞ ቡራኬያቸው እንዲደርሰንና በሄድበት ሁሉ እንዲጠብቀን ጸሎታቸውን መሻት ያስፈልገናል፡፡ የአገልግሎታቸውንም ዋጋ ማስተዋል ይገባናል፡፡ በህፃንነት ብንጠመቅ በካህን፣ በወጣትነት ተክሊል ብናደርግ በካህን፣ ከዚህ ዓለም በሞት ብንለይ ጸሎተ ፍትሐት የሚደርስልን በካህን፣ የኃጢአት ሥርየት የምናገኘው በካህን፣ ሥጋውንና ደሙን ብንቀበል በካህን፣ በደዌ ብንያዝ መንፈሳዊ ሕክምና የምናገኘው በካህን ነውና የሐዋርያት አገልግሎት በሕይወታችን ያላቸው ዋጋ ታላቅ ነው፡፡

ሐዋርያዊት የሆነችው ቤተክርስቲያናችን ቅዱሳን ሐዋርያትን የምትዘክረው ስለብዙ ምክንያቶች ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የምታመልከው አምላክ መርጧቸው ተከትለውታልና እነርሱን ማከበር እርሱንም ማክበር ስለሆነ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ቅዱሳን ሐዋርያት ራሳቸው የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ሆነው የሐዲስ ቤተክርስቲያንን በምድር ላይ የመሠረቱት እነርሱ ናቸውና ቤተክርስቲያንም ራሷ የሐዋርያት ጉባዔ ናትና ሐዋርያትን ዘወትር ትዘክራቸዋለች፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ቤተክርስቲያን በአስተምህሮ የቅዱሳን ሐዋርያትን የመጻሕፍት ትርጓሜ፣ በክህነት አገልግሎት ከሐዋርያት በቀጥታ የመጣ የሲመት ሀረግ ስላላትና ራስዋም ሐዋርያዊት ስለሆነች ሐዋርያትን ትዘክራቸዋለች፡፡ አራተኛው ምክንያት ደግሞ በቤቱና በቅጥሩ የማያልፍ ስም ስለተሰጣቸው፣ በአስራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ እስከመፍረድ የሚደርስ ክብርና ስልጣን ስለተሰጣቸው በረከታቸው ይደርሰን ዘንድ እንዘክራቸዋለን፡፡ በመጨረሻም ወንጌል፣ ክርስትናና ቤተክርስቲያን 2ሺ ዘመናት አልፈው ከእኛ ዘመን የደረሱት በየዘመናቱ በነበሩት የሐዋርያት አገልግሎት ነው፤ በገሊላና በአካባቢዋ ብቻ ተሰብካ የነበረችው ወንጌል እስከ ዓለም ዳርቻ የደረሰችው በሐዋርያት አገልግሎት ነው፤ ብዙ ጻድቃን ሰማዕታት ሊቃውንትን ያፈራነው የሐዋርያት አገልግሎት ወደ ሕዝብ በመድረሱ ነው፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን ሐዋርያት እነርሱ እየቀለጡ ለእኛ ያበሩልን ስለሆኑ የክርስትናችንን ነገር ስናስብ እነርሱን ዘወትር እንዘክራቸዋለን፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን ሐዋርያት በረከት አይለየን፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s