በዲ/ን ዮሐንስ ወርቁ
መግቢያ
አምላካችን እግዚአብሔር ዓለማትን የፈጠረበት ጥበቡ ቢተነተን አያልቅም። በባሕርይው ጥበበኛ የሆነ አምላክ ፈጣሪነቱ ከመጋቢነቱ፣ መጋቢነቱ ከአዳኝነቱ፣ አዳኝነቱ ከጠባቂነቱ ጋር የተገናዘበ ነው። ይህ የእግዚአብሔር ልዩ ጥበብ በሰው፣ በስነ ፍጥረትና በቅዱሳት መጻሕፍት አስረጅነት ይገለጣል፡፡ ከእነዚህም መካከል ምድር አንዷ ናት፡፡ በዚህች የአስተምህሮ ጦማር አዳምን ስላስገኘችው ምድርና የእርስዋንም አማናዊ ምሳሌነት እንመለከታለን፡፡
እግዚአብሔር ሁሉን ውብ አድርጎ ፈጠረው
እግዚአብሔር አምላካችን ከፍጥረት በፊት በባሕርይው እየተመሰገነ (በሰው ሰውኛ አገላለፅ) “ይኖር” ነበር። ፍጥረትን ካለመኖር ወደ መኖር ሲያመጣ ደግሞ ግሩም የሆነ መጋቢነቱን እና ከሀሊነቱን ፍጥረቱ ሲፈጠሩ ጀምረው በልዩ ልዩ መልክ መስክረዋል። ቅዱሳት መጻሕፍት ‘እግዚአብሔር በፍጥረቱ ለፍጥረቱ ይታወቃል’ እንዲሉ። ሁሉን ቻይ መሆኑ ደግሞ ገና ሲያስብ፣ ሀሳቡ ሰማይና ምድር ሆኖ በገሀድ ሲተረጎም፤ ቃል ከአንደበቱ ሲወጣ፣ ያ የተነገረው ቃል በተግባር ሲገለጥ ታውቋል/ይታወቃል። ብርሃን ይሁን ሲል ከዚያ በፊት ያልነበረው ብርሃን በቅፅበት ተገልጧል። (ዘፍ• 1:3)።ደግሞም ክቡራን፣ ቅዱሳን፣ ንጹሐን በሆኑ ዓለምን በያዙ እጆቹ የሰውን ልጅ ከምድር አፈር ወስዶ አበጃጀው። እንደ ሰዐልያን የራሱን መልክ በመስታወት ማየት ሳያስፈለገውም ወይም ረዳት ሳያሻው በአምሳሉና በአርአያው ሰውን ፈጠረ። ፍጥረትን የፈጠረበት መንገዱ እውነተኛ አምላክነቱን ብቻ ሳይሆን ለወደፊት ለሚሆኑ ነገሮችም አመልካች፤ ስለ ጥበቡና ጥበብ እርሱ እንደሆነ፤ ስለ ፍቅሩም ፤ ስለ ቸርነቱም ፤ ስለ ርህራሄው ባጠቃላይ ስለ ሥሉስ ቅዱስ ምስክር ናቸው። ታዲየ ያኔ ነበር በመጀመሪያዎቹ መጀመሪያ ከሁሉ በፊት አንድ ብሎ ሲፈጠር (በመጀመሪያ ጊዜን አመልካች ነውና ) ምድር የተፈጠረችው። ምድርም ያኔ እንከን አልነበራትም።
ምድር በሰው ልጅ ምክንያት ተረገመች
አዳም የተፈጠረባት ምድር እርግማን የለባትም ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ማለትም ለሰባት ዓመት በንጽህና ቆይታለች። አዳም አምላክነትን ሽቶ እስከበደለበትና እግዚአብሔርም እስከ ረገመው ቅጽበት ድረስ ንፁህ ሆና ቆይታለች። ምድር ከርግማኗ በፊት ያላት ታሪክ የሰውን ልጅ የሚመስል ነው፡፡ የሰው ልጅ ከውድቀቱ በፊት ጸጋ ነበረው። ምድርም በነበራት ጸጋ ሳትታረስ፣ ገበሬ ሳይደክምባት፣ ዘር ሳይዘራባት በትዕዛዘ እግዚአብሔር ብቻ ታበቅል ነበር። የመጀመሪያዎቹ ዕፅዋት ፣አዝዕርት፣ የሚበሉትና የማይበሉትም፣ ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉት ሁሉ ዝግጁ ሆነው ከምድር በቀሉ ። ምድርም በተሰጣት ጸጋ የሰውን ልጅ አገለገለች።
ምድርን ያስረገማት ከርሷ የተገኘው ሰው እንደ ሆነ ግልጽ ነው። በምሥጢሩ የተረገመችው ምድር የአዳምን ዘር ወክላ ነው ። ስለዚህ የተረገመችው ምድር ሰውን ስትወክል በአንጻሩ ቡርክት የሆነችውን ምድር እግዚአብሔር ምድርን ለመቤዠት በልዩ ጥበቡ በመረጣት፣ በጠበቃት በቅድስት ድንግል ማርያም እንመስላታለን። ምድር መረገሟ አዳም ደክሞ ወጥቶ ወርዶ የሚያስፈልገውን ማግኝት ስላለበት ነው። ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ትዕዛዝ ብቻ ሳይሆን የወጣው እግዚአብሔርነትን ተመኝቷልና። መልካምነት በፈጣሪ ለፍጡራን የተሰጠ ነው። ስለዚያም ነው የሰው ልጅ በተፈጥሮው የሌለውን ባሕርይ ሲያበቅል ያንን ማረም ያለበት። ምድር እሾህና አሜከላ አብቅይ የተባለችው ስትረገም ነው። አዳምም ክፉ ጠባዮችን መያዝ የጀመረው ከውድቀት በኋላ ነው ። ከዚያ በፊት የሚኖረው በገነት ነበር፡፡ እንደርሱ ሰው ከሆነችው፣ በአስተሳሰብም በምግባርም ከምትመስለው ያውም አካሉ ከሆነችው ከሔዋን ጋር ብቻ ሳይሆን ከእንስሳትም ጋር በሰላም ይኖር ነበር።
ምድር አዳም በበደለ ጊዜ ዝምታን መርጣ ነበር፡፡ ብቻዋን አይደለም ከዕፀ በለሷም ጋር ነው እንጂ። ወንጀል ሲፈፀም እያየ ዝም ያለ የወንጀሉ ተባባሪ እንደሆነ ዓለማዊው ሕግም ያስተምራል። በዕለተ ዓርብ የአምላካችን ቅዱስ ሥጋው በተቆረሰና ክቡር ደሙ በፈሰሰና የምድርን እርግማን ባስቀረላት ጊዜ የአስቆሮቱን ይሁዳ ራሱን ሊያጠፋ ሲል ዛፏ ስትገስፀው ተመልክተናል። እንግዲህ ግዕዛን የሌላቸው ፍጥረታት እንኳ በተዓምራት ሰዎችን ከተሳሳተ ጎዳና የሚመልሱ ከሆነ እኛም ሰዎች ወደተሳሳተ መንገድ እየሄዱ ስናይ ዝም ልንል እንዳማይገባን ያመለክተናል። ታዲያ ከዚያ በፊት ግን ሰውን ከምድር ካበጃጀው በኋላ እግዚአብሔር አምላክ እጅግ መልካም መሆኑን ፍጹም በማይታበልና ሰማይን እና ምድርን ባፀናበት ቃሉ በእውነት ያለ ሐሰት ተናግሯል። እግዚአብሔርን ያስደሰተው የእጅ ሥራ የተገኝበትም ከመልካሚቱ ያውም መልካምነቷ በሰማይና በምድር ፈጣሪ ከተመሰከረላት ከምድር ነው። የመጀመሪያዋ ምድር ፍሬ ግን ማለትም አዳም ለዓለም ሁሉ መርገምን፤ ሞትን፤ ከእግዚአብሔር ጋር መጣላትን ያመጣ አመፀኛ ነበረ።
ምድር ለዓይን ውብ ሆና፣ በአበቦች አጊጣ ፣ በአረንጓዴ እና ረጃጅም ዕፅዋት ፣ እንዲሁም በተለያዩ ቀለሞች የተሞሸሩ ዛፎች፣ መልከአ ምድርን ያማከሉና ከተራራ እሰከ ስምጥ ሸለቆ በዓይን ተቃኝቶ በልቦና ክንፍነት ተቃኝቶ የመንፈስ ምግብ ሆኖ እርካታን በመስጠት ረገድ ቀዳማዊ ናት። ከርግማኗ በፊት መከባበር እና ታዛዥነት የሰፈነባት ቦታ ነበረች። ይህም ማለት የሰው ልጅ በጸጋ ነግሶ ስለነበር ሁሉም ይገዙለት ነበር። ከርግማኗ በኋላ እርሷ ስትቀየር በርሷ ላይም የሚኖሩት ተቀየሩ። ረሀብ ቸነፈር በዛ፤ ሰው እና እንስሳትም አብረው መኖር ተሳናቸው። መከባበር፣ ታዛዥነትም፣ በአጠቃላይ ፍቅር ከምድር ጠፋ። በአንጻሩ ደግሞ ሰይጣናዊ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ተስፋፉ።
ምድርና የሰው ልጅ ልቡና
ዛሬስ የኛ ልቦናችን የትኛይቱን ምድር ይመስላል? ከርግማን በፊት የነበረችውን? እንደዛ ከሆነ ልባችን ቅን ነገሮችን ያስባልን? ይፈፅማልን? የመንፈስ ፍሬ የተባሉት ይበቅሉበታልን? ፍሬስ ያፈራልን? ፍቅር ካለን ሳንመርጥ የሚወዱንን እና የሚጠሉንን እንወዳለንን?፥ ትህትና ካለን ፈሪሀ እግዚአብሔር ካለን፣ ባጠቃላይ መልካም ነገሮችን በተግባር ተግባሪዎች ከሆንን፣ በኛ ምክንያት እግዚአብሔር ከተመሰገነ መልካሚቱን ምድር መምሰላችን ጥያቄ የለውም።
እስቲ በህሊናችን ክቡር እና ምስጉን ወደ ሆነው አምላካችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የቤዛነት ሥራ እንመልከት፡፡ በተለይም በዕለተ ዓርብ የተቀበለውን መከራዎች እናስብ። አስራ አራቱን ምዕራፎች አብረነው መስቀሉን ተሸክመን እንከተለው። በዚህም ጉዞ ላይ የጌታችንን ቃል “ከእኔ ተማሩ” የምትለውን አንስተን በእነዚህ ምዕራፎች ከሆነው አንድ ታሪክ ወስደን ከጌታችን የምንማራቸውን ምግባራት እንመልከት።
ለመጀመሪያ ጊዜ ጌታችን መስቀሉን እንደ ተሸከመ ወደቀ ። መስቀል የሚሸከምበት ይቅር እና ልብስ እንኳን የማያስለብስ ትኩስ የግርፋት ቁስል ጀርባውን አቁስለውት ነበር ። ያውም ያለ ርህራሄ፤ የግርፋቱን ቁጥር በማምታታት ነበር የገረፋት። እርሱ እየቆሰለ እኛን ከቁስለ ሥጋ እና ቁስለ ነፍስ ነው የፈወሰን። ይህ ታዲያ በደዌ ነፍስ ወይም በደዌ ሥጋ፤ በሕማመ ነፍስ ወይም በሕማመ ሥጋ ፤ በሀዘን፤ በጭንቀት የወደቁትን ልናነሳ እንዲገባን ያስረዳናል። እነሱ ወደኛ ሲመጡ ብቻ ሳይሆን ከጌታችን እንደተማርነው እኛ ፈልገን ሄደን ዋጋ ከፍለን ልንረዳቸውና ከጎናቸው ልንቆም ይገባናል። ያኔ በእውነት የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደሆን ሥራችን ይመሰክርልናል። ክርስቲያን ተብለን ለመጠራትም የተገባን እንሆናለን።
የመኪና መንጃ ፈቃድ ሳንይዝ ያልተፈቀደልንን የወታደር መኪና ስናሽከረክር በሕግ አስከባሪ ብንያዝ ስለ መንጃ ፈቃዱ ብቻ ሳይሆን ወታደር ሳንሆን የወታደር ተሽከርካሪ ስለ መያዛችንም ጭምር ልንቀጣ እንችላለን። ክርስቲያን ተብለን ክርስትና ህይወትንም ካልኖርንበት፤ ህጉን ስለጣስን ብቻ ሳይሆን ስላልኖርነበትም እንቀጣለን። ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስን ብንመለከት ከክርስቶስ የተማረውን እንደበረዶ የድንጋይ ናዳ ባወረዱበት ጊዜ እርሱ ግን የሥላሴን ምስጢር ሲመለከት በአንደበቱ የሚወግሩትን አልከሰሰም ። እንዲከሳቸው ከበቂ በላይ ምክንያት ቢኖረውም በደዌ ነፍስ ስለታመሙ ራራላቸው። ጌታችንን አሰበ። ከእኔ ተማሩ ያለውንም አስታወሰና ልክ እንደ አምላኩ ቀና ብሎ “አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁም እና ይቅርበላቸው” አለ። የሚያደርጉትን የማያውቁ ሕፃናት ሆነው አይደለም። ይልቁንም የሰበከላቸውን ስላላስተዋሉና ደዌ ነፍስ እያዩ እንዳያዩ ስለከለከላቸው ነው እንጂ።
ካህናት አበው አስተምረውን ወንጌልን ዘርተውብን የወንጌልን ፍሬ ሳናፈራ በእርሱ ፈንታ እሾህ አሜከላ የተባለውን ዘረኝነት፣ ሴሰኝነት፣ አድመኛነት፣ ዘማዊነት፣ ሰካራምነት፣ አጫሽነት፣ ዘፋኝነት፣ ምንፍቅና እና የመሳሰለውን ካፈራን ልባችን የቆመበትን እንመርምረው። ያላፈራው ምናልባት እሾህ በቅሎበት ይሆን? እሾህ በተፈጥሮው የሚዋጋ የሚያደማ ነውና ሰዎችን በንግግራችን ወይም በድርጊቶቻችን አድምተናቸው ይሆን? እንዲህ ከሆነ ይቅርታ በመጠየቅ ልናክማቸው ተገቢ ነው። ትህትና መገለጫው ራስን ዝቅ ማድረግ ለይቅርታ መፋጠንም ነው። ትህትና ከምድር ወደ ሰማይ የሚያሻግር መሰላል ነው። ትዕቢት ግን ከላይ ወደታች የሚጥል ነው። ሰይጣንን ሲጥለው ተመልክተናልና። ከምናያቸው ወንድሞቻችን ጋር በፍቅር ስንኖር ከእግዚአብሔር ጋር በእምነት ለመኖር ጉልበት ይሆነናል። በእግዚአብሔርም ዘንድ ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅርና ሃይማኖት ያለ ነቀፋ ተቀባይነት ይኖረዋል። ከአምላካችን ጋር በንስሐ እንታረቅና እግዚአብሔር በኛ ላይ ደስ ይበለው።
የመጀመሪያቱ ምድር፡ ድንግል ማርያም
የእመቤታችን ወዳጅ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በማክሰኞ ውዳሴ ማርያም (ውዳሴ ማርያም ዘሰሉስ) “አንቲ ውእቱ ገራህት ዘኢተዘርአ ውስቴታ ዘርዕ፣ ወጽአ እምኔኪ ፍሬ ሕይወት/ዘር ያልተዘራባት [የመጀመሪያይቱ የማክሰኞ] እርሻ አንቺ ነሽ፣ የሕይወት ፍሬ ከአንቺ ወጣ” በማለት የመጀሪያይቱን ምድር አማናዊ ምሳሌነት ተርጉሞልናል። ዳግማዊው አዳም የተወለደባት መርገመ ስጋ ወነፍስ ያልነካት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም እንደቀደመችው ምድር ንጽህት ናት፣ ርግማን የለባትም። የመጀመሪያዋ ምድር ንጽህናዋ በኋለኛው ዘመን ዳግማዊ አዳምን ከወለደችው ምንም እንከን ከሌለባት ከድንግል ማርያም ጋር ያመሳስላታል። ዳግማዊው አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ፤ የአርአያነቱና የቤዛነቱን ሥራ ሠርቶ አዳምን ወደቀደመ ክብሩ መልሶታል። ይህ የእመብርሃን የሆዷ ፍሬ ለዓለም ሁሉ ድህነትን፣ በረከትን ያደለ ነው፤ ከራሱ ጋር ያስታረቀን ነው፤ እርሱ እግዚአብሔር ነውና።
አዳምን ሲፈጥረው አራት ባሕርያተ ሥጋ እና ሶስት ባሕርያተ ነፍስን አዋሕዶ ነበር። ከአራቱ ባሕርያት አንዱ አፈር ነበር፡፡ ይህም አፈር የተገኘው ምድር ከመረገሟ በፊት ነበር። ዉሀም የእግዚአብሔር መንፈስ አድሮበት ስለ ነበር ቅዱስ ነው። ነፋስም እና እሳትም የተቀደሱ ነበሩ። እግዚአብሔር ሰለ ፈጠረው ፍጥረት መልካም ነው ብሏልና። ነገር ግን ሰውን ከፈጠረው በኋላ እጅግ መልካም ነው ብሎ ምን ያክል እንዳስደሰተው ተናግሯል። ይህ እግዚአብሔርን ያስደሰተው ምስጢር በአዳም ውስጥ ያያት ዳግማዊ አዳምን የምትሽከም ዳግማዊት ሰማይ፣ ንጽሕት፣ ቅድስት ድንግል በክልኤ የሆነች ድንግል ማርያምን፣ የአምላክን ሥጋዌ (ሰው መሆን) ስላየ ነው። ይህ አዳም ቢበድልም ምክንያተ ድኅነት የምትሆን በውስጡ ስላዘጋጃት እግዚአብሔር ደስ አለው። ምድርም ለዚህ ምስጢር ምሳሌ ትሆን ዘንድ ሁለቱን ገጽታዎች ከርግማኗ በፊት የነበራትን ጸጋ እና ጸጋውን ካጣች በኃላ ያላትን ገጽታ አሳየች።
ከምድር ባሕሪያት አንዱ የተዘራባትን ማብቀል ሲሆን ያም የተዘራው ዘርን ሳትቀይር እርሱን ትተካለች። ብርቱካን ቢተክሉባት ሎሚ አታበቅልም። ያው ብርቱካኑን አብቅላ ብርቱካን ታፈራለች እንጂ። በቀናች ሃይማኖት የተጓዙትን የእነርሱን መልካም ፍሬ ብንዘራበት መልካም ዘር ይበቅላል። ከዚህም ባሻገር ምድር ከሃያ ሁለቱ ፍጥረታት አንዱ ብትሆንም ለሁሉም ማዕከላዊ ናት። ሰለ ሰማይ ሲነገር ምድር ሳትነሳ አታልፍም። ምክንያቱም በሰማይ ባለው ዙፋን ለተቀመጠው ንጉሥ መረገጫውም ናትና። የሰማይ ልዕልናም ለምድር ነውና።
ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ስለአምላካችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲነገር ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ይነገራል። አማናዊት ምድር በዘር የሚተላለፈው እርግማን ያልነካት፣ በጥበበ እግዚአብሔር የተጠበቀች ናት። አባቶች እንደሚሉት “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንነ ገሞራንም በመሰልነ ነበር።” (ኢሳ• 1:9) ብሎ ነቢየ ልዑል ኢሳይያስ የተናገረላት ንጹህ ዘር ድንግል ማርያም ናት። ለዚህም ነበር ያ የውርስ ኃጢአት የነካቸው የተቀበሉት ጸጋ ሙሉ እንዳልሆነ ሲነገርላቸው ድንግል ማርያምን ግን ምድራዊ ሳይሆን ሰማያዊ መልአክ የሌሎች ጸጋ በጎደለበት ዘመን “ጸጋን የተመላሽ ሆይ” ብሎ ያበሰራት። ልክ እንደ መልካሚቷ ምድር እሾህ ያላበቀለች እንዲያውም በተግባር ይቅርና በሀሳብ ደረጃ እንኳን ኃጢአትን ያላሰበች ፍጽምት የባሕርያችን መመኪያ ናት።
የመጀመሪያይቱ ምድር በፈቃደ እግዚአብሔር የመግቦቱ መገለጫ፣ የርህራሄው ማሳያ ነበረች። ዘር ሳይዘራባት በጸጋ እግዚአብሔር የቀደመ ሰው አዳምን እንዲሁም ለዓለም ሁሉ የሚበቃ ፍሬን አስገኝታለችና። ምሳሌ ከሚመሰልለት ማነሱ የታወቀ ነውና የዳግማዊ አዳም የክርስቶስ መገኛ፣ ለዓለም ሁሉ ድኅነት የሚበቃ የቅዱስ ሥጋው፣ የክቡር ደሙ ምንጭ የባሕርያችን መመኪያ ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላለማዊ መግቦት መገለጫ ናት። ስለ ርኅራሄዋ በጥም የተመታው ውሻ ይመሰክራል። የሰውን ጭንቀት ስለመረዳቷ ዶኪማስን መጠየቁ ይበቃል። የዘመናችንም ዶኪማሶች እልፍ ነን። የእርሷን ፍቅሯን በሚገባው መጠን ብንረዳ “ዶኪማስ ሆይ ያንተን ምስክርነት አንሻም እኛው ራሳችን እንመስክርላታለን” ባልን ነበር። ሁለተኛይቱ ምድር የዓለምን መድኅን ክርስቶስን አስገኝታ የመጀመሪያውን አዳም ወደቀደመው ክብሩ ለመመለስ ምክንያተ ድኅነት ሆናለች። ዓለማትን የፈጠረ ጌታ ማደሪያ የሆነች፣ የሁሉን መጋቢ የድንግልና ወተቷን የመገበች፣ እርግማን እንዳልነካት የመጀመሪያይቱ ምድር የጸጋ ሁሉ ምንጭ የሆነች የእመቤታችን በረከቷ፣ አማላጅነቷ ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን።
አሜን፡ቃለ፡ሂወት ያስማልን
LikeLike