ሰንደቅ ዓላማና ቤተክርስቲያን፡ የቄሳርን ለቄሳር!

flags_church
ምክንያተ ጽሕፈት

በአንዲት ኢትዮጵያውያን የሚኖሩባት የምዕራባውያን ሀገር ከተማ በቅርቡ የመጣውን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆኑ ጳጳሳት እርቅ ተከትሎ የጥምቀትን በዓል አጥቢያዎች ተለያይተው ማክበራቸው ቀርቶ “በአንድነት የማክበር ሀሳብ” በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ በዓሉን በአንድነት እናክብር ወይስ ላለፉት የተወሰኑ ዓመታት ልማድ እንደነበረው ተለያይተን እናክብር የሚል ውይይትም በካህናትም ሆነ በምዕመናን ዘንድ ጎልቶ ይሰማል፡፡ ሁሉም በየፊናው የየራሱን ሀሳብ ያቀርባል፡፡ በዚህ ሁኔታ ከቀረቡ ሀሳቦች ውስጥ አንዱ ባንዲራን ይመለከታል፡፡ አንዳንዱ “በጥምቀት በዓል መያዝ ያለበት ሀገራችን ኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት የተጠቀመችበት ልሙጡ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ ብቻ ነው፡፡ ኮከብ ያለበትን ባንዲራ የሚይዙ ካሉ ‘እንቃወማቸዋለን'”  ይላል፡፡ ሌላው ደግሞ “በጥምቀት በዓል መያዝ ያለበት የሀገራችን ኢትዮጵያ መደበኛ (ኦፊሴላዊ) ባንዲራ መሆን አለበት፡፡ ኮከብ የሌለበትን ባንዲራ የሚይዙ ካሉ ከእነርሱ ጋር ኅብረት የለንም፡፡” ይላል፡፡

ከዚህም በመነሳት መንፈሳዊ አንድነትን በሰንደቅ ዓላማ አረዳድ በመመዘን በዚህ ምድራዊ እይታ ከሚስማማቸው ጋር የሚውሉ፣ የማይስማማቸውን የሚያገሉ፣ አቅም ሲያገኙም የሚደበድቡ “የመንፈሳዊ በዓል አክባሪ ካህናትና ምዕመናን” አሉ፡፡ የሚገርመው እነዚህ ሁለት ቡድኖች የሚኖሩበትን ሀገር ባንዲራ ያለጭቅጭቅ ተሸክመው ሲዞሩ መዋላቸው ነው፡፡ የሚኖሩበት ሀገር ባንዲራም እንደ ሀገራችን ኢትዮጵያ ባንዲራ የፖለቲካዊ ትርክት ማሳያ መሆኑን አይረዱም፡፡ የምድራዊ ባንዲራ ጉዳይ “ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ” ብለን የምንዘምርበት፣ የሰማያት ምሥጢር የተገለጠበትን የጥምቀት በዓል ሲያውክ ማየት ያሳዝናል፡፡ በመንፈሳዊ አውደ ምህረት ምድራዊ ባንዲራን የልዩነት (ወይም የአንድነት) ምንጭ አድርጎ የመሳል አባዜ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ቤተክርስቲያንን መለካት ባለባት መንፈሳዊ ሚዛን ሳይሆን መለካት በሌለባት ፖለቲካዊ (ሀገራዊ) ሚዛን እንድትለካ ያደርጋል፡፡  

በአጠቃላይ ከቅርብ ዘመናት ወዲህ በሕንፃ ቤተክርስቲያን ላይ፣ የበዓላት አከባበርን ለማድመቅ፣ በአልባሳትና አንዳንዴ ደግሞ ንዋየ ቅድሳት ላይ ጥቅም ላይ የሚውሉ ቀለማትን ከፖለቲካዊ ሰንደቅ ዓላማ ጋር ማያያዝ እንዲሁም ሰንደቅ ዓላማን በንግሥ በዓላት ላይ መያዝ ለብዙዎች አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኗል፡፡ አንዳንዶቹ ባለማወቅ፣ ሌሎችም በድፍረት (ዓለማዊ ዓላማን ከመንፈሳዊ ዓላማ በማስቀደም) ቤተክርስቲያንን የፖለቲካ ፉክክር አውድ እያደረጉ ኅማማተ ክርስቶስን የምናስብበትን ከበሮ “የእኔ ነው” የሚሉትን ባንዲራ አልብሰው “መዝሙር ሲዘምሩ” ይታያሉ፡፡ ሌሎቹም ሥርዓተ ቅዳሴን የሚያክል ሰማያዊ አምልኮ በሚፈጸምበት ሰዓት በመጾር መስቀል ላይ የሚንጠለጠለውን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፈዋሽ ሕማም የሚታሰብበትን መግነዝ መታሰቢያ “የእኔ ነው” በሚሉት ባንዲራ ተክተው “ሲቀድሱ” ይታያሉ፡፡ ይህን መሰል አሰራር በአንዳንዶቹ ዘንድ “ሀገር ወዳድነት” የሚል ካባ ተደርቦበት “በመተዳደሪያ ደንብ” ውስጥ  ሳይቀር የተካተተባቸው ቦታዎች አሉ፡፡

የሰንደቅ ዓላማ ፉክክር ከፖለቲካና ከፖለቲከኞች አውድ አልፎ የሁሉም እናት ወደሆነች ቅድስት ቤተክርስቲያን አውደምህረት መምጣቱ በርካታ ችግሮችን እያስከተለ ይገኛል፡፡ አንዳንዶች በአንድ የሃይማኖት ተቋም ውስጥ ‘ሰንደቅ ዓላማ’ መጠቀም ለምን አስፈለገ ብለው ሲጠይቁ፣ ሌሎች ደግሞ ቤተክርስቲያንን የተወሰነ የፖለቲካ ወገንተኝነት ያለው ቡድን ለፖለቲካ ዓላማው እየተጠቀመባት ነው ብለው ይከሳሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ እነርሱ ይህንን ‘ሰንደቅ’ ዓላማ በቤተክርስቲያን የሚጠቀሙ ከሆነ እኛም እኛን የሚወክለንን ሰንደቅ ዓላማ እንጠቀማለን ሲሉ ይደመጣሉ፤ መጠቀምም ጀምረዋል፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ቤተክርስቲያንን የፖለቲካ ፉክክር አውድ ሊያደርጋት ይችላል፡፡ ከዚህም የተነሣ የበዓላትን መንፈሳዊ ዓላማ ከመረዳት ይልቅ መንፈሳዊ በዓላትን ለምድራዊ ፉክክር ማዋል የሚያስደስታቸው ሰዎች በማወቅም ባለማወቅም መንፈሳዊውን አውድ ለፖለቲካዊ ዓላማ ስለሚጠቀሙበት መንፈሳዊ አንድነትን እየተፈታተነ ይገኛል፡፡

በዚህች አጭር የአስተምህሮ ጦማር ሰንደቅ ዓላማን (ባንዲራን) እና የሰንደቅ ዓላማ ቀለማትን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎችን ከኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ አንጻር እንዳስሳለን፡፡ የሰንደቅ ዓላማ ዓለማዊ (ሀገራዊ) እና ፖለቲካዊ ትንታኔዎች እንዲሁም በሀገራዊ ክዋኔዎች የቤተክርስቲያን ተቋማዊ ሚና እና የምዕመኖቿ ግላዊ አበርክቶት የኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ትኩረት ስላልሆኑ በዚህ ጽሁፍ በትኩረት አልተዳሰሱም፡፡

ለመሆኑ ሰንደቅ ዓላማ ምንድን ነው?

ሰንደቅ ዓላማ (‘Flag’ in English, ‘Bandiera’ in Italian) ከጀርባው ትልቅና ጥልቅ መልዕክትን ያዘለና አንድን ሀገራዊ ወይም ፖለቲካዊ ወይም ድርጅታዊ አስተሳሰብ የሚወክል ምልክት ነው። በዚህም መሠረት ሀገራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ድርጅቶች የራሳቸው ባንዲራ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ሰንደቅ ዓላማ  “በአብዛኛው የተወሰኑና የተለያዩ ቀለማት ካሏቸው ቁሶች የሚዘጋጅ የአንድ ሀገር የነፃነት ምልክትና መለያ፣ የአንድ ሀገርና ሕዝብ የሉዓላዊነቱ ምልክት ወይም ትዕምርት” ነው፡፡ ስለዚህ ሰንደቅ ዓላማ ሀገራዊ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የሰንደቅ ዓላማ ታሪካዊ አጀማመርን ያጠኑ ሰዎች (vexillologists) እንደሚሉት የሰንደቅ ዓላማ አጀማመር በጦርነት ጊዜ ወዳጅን ከጠላት የመለየት ዓላማ ነበረው፡፡ በጊዜ ሂደት ሀገራት መደበኛ ቅርጽ ያለቸውን ባንዲራዎች በመወሰን የባህል፣ የፖለቲካ አቋምና የግዛት አንድነት መለያ አድርገው መውሰድ ጀመሩ፡፡ በዓለማችን ያሉ አብዛኞቹ ባንዲራዎች በብዛት ጥቅም ላይ መዋል የጀመሩት ከብሔራዊ መንግስታት (Nation States) ምስረታ ጋር ተያይዞ ነው፡፡

የየትኛውም ሀገር ወይም ድርጅት ወይም የኅብረተሰብ ክፍል የሚጠቀመው ባንዲራ ከዚያ አገር ሕዝብ ወይም የኅብረተሰብ ክፍል ማንነትና ከሚከተለው የፖለቲካ ሥርዓት፣ ታሪክ፣ አስተሳሰብ ወይም ዓላማ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ትርጓሜና ውክልና ይሰጠዋል። ስለዚህ ሰንደቅ ዓላማ የባለቤቱን አስተሳሰብ፣ አመለካከት ወይም ዓላማ ይወክላል ማለት ነው፡፡ የሰንደቅ ዓላማ ልዩነት የምልክቱ (የቀለሙ) ልዩነት ብቻ አይደለም፡፡ በዋናነት ከሰንደቅ ዓላማው ጀርባ ያለው ጥልቅ መልእክት/ዓላማ ልዩነት እንጂ፡፡ ከዚህ አንጻር አንድ ሰው/ማኅበረሰብ/ “ይህ ሰንደቅ ዓላማ ይገልፀኛል” ሲል ሰንደቅ ዓላማው ሀገራዊ አመለካከቴን፣ ፖለቲካዊ ፍልስፍናዬን፣ ታሪካዊ ማንነቴን፣ ከሌሎች ወገኖቼ ጋር ያለኝን መስተጋብር… ይገልፃል ማለቱ ነው፡፡ እንዲሁም “ይህ ሰንደቅ ዓላማ አይገልፀኝም” ሲል ከላይ የተጠቀሱትን የእኔነት መገለጫዎቼን አያንጸባርቅም ማለቱ ነው እንጂ ቀለሙ ጠቆረ ወይም ቀላ ወይም ነጣ ማለቱ ብቻ አይደለም፡፡

የኖኅ ቀስተ ደመና ከሰንደቅ ዓላማ ጋር ይገናኛልን?

እግዚአብሔር በኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎችን በክፋታቸው ምክንያት በንፍር ውኃ ካጠፋቸው በኋላ ዳግመኛ የሰውን ልጅ በንፍር ውኃ ላያጠፋ ቃል ኪዳንን ሰጥቶታል፡፡ መጽሐፍ ይህንን ቃል ኪዳን ሲገልጽ “እግዚአብሔርም ለኖኅና ለልጆቹ እንዲህ ብሎ ተናገረ። እኔም እነሆ ቃል ኪዳኔን ከእናንተና በኋላ ከሚመጣው ከዘራችሁ ጋር አቆማለሁ፤ ከእናንተ ጋር ላሉትም ሕያው ነፍስ ላላቸው ሁሉ … ይሆናል። ቃል ኪዳኔንም ለእናንተ አቆማለሁ፤ ሥጋ ያለውም ሁሉ ዳግመኛ በጥፋት ውኃ አይጠፋም፤ ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም። እግዚአብሔርም አለ፡- በእኔና በእናንተ መካከል … ለዘላለም የማደርገው የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው፤ ቀስቴን በደመና አድርጌአለሁ፥ የቃል ኪዳኑም ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል። በምድር ላይ ደመናን በጋረድሁ ጊዜ ቀስቲቱ በደመናው ትታያለች… ሥጋ ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም። ቀስቲቱም በደመና ትሆናለች፤ በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው በሕያው ነፍስ ሁሉ መካከል ያለውን የዘላለም ቃል ኪዳን ለማሰብ አያታለሁ። እግዚአብሔርም ኖኅን፡- በእኔና በምድር ላይ በሚኖር ሥጋ ባለው ሁሉ መካከል ያቆምሁት የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው አለው።” በማለት አስፍሮታል (ዘፍ 9፡8-17)፡፡

እግዚአብሔር ይህንን ቀስተ ደመና ነው የቃል ኪዳኑ ምልክት ያደረገው፡፡ ቃልኪዳኑም ዘላለማዊ ሲሆን እግዚአብሔር ዳግመኛ የሰውን ልጅ በንፍር ውኃ ላለማጥፋት የሰጠው ቃል ኪዳን ነው፡፡ ለሰው ብቻ ያይደለ ሥጋ ለለበሰ ፍጡር ሁሉ የተሰጠ ቃል ኪዳን ነው፡፡ ምልክቱም በእግዚአብሔርና በሰው መካከል በደመና ላይ የሚታይ ምልክት ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህንን ምልክት በደመና ላይ እንዲሆን ያደረበት የራሱ ምሥጢር አለው፡፡ የዚህ ምልክት ፍጻሜ ለሰው ልጅ ምክንያተ ድኂን የሆነችው ድንግል ማርያም ናት፡፡ ከልጇ ጽኑ ቃል ኪዳን የተቀበለች የአምላክ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም በኖኅ መርከብ እንደምትመሰል ሁሉ በኖኅ የቃል ኪዳን ምልክት በሆነችው በኖኅ ቀስተ ደመና ትመሰላለችና፡፡

እግዚአብሔር ይህንን የቀስተ ደመና ምልክት ለኖኅ ማሳየቱ ለጊዜው ከእንግዲህ ወዲህ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋና ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ የተፈጠረ ሰውን በንፍር ውሃ አላጠፋውም ሲለው ሲሆን ፍጻሜው ግን ደመና የቅድስት ድንግል ማርያም፤ ሕብረ ቀለማቱ የሰው ባሕርያት ምሳሌ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ይህንን የቃል ኪዳን ምልክት ማሳየቱ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቼ ተወልጄ ሰውን ከመርገም ውሃ (ከሲኦል) አድነዋለሁ ሲል ነው፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ይህን በማስመልከት በሰላምታ መጽሐፉ ላይ “ከልቅሶ ደመና የጥፋት ውሃ ዳግመኛ በምድር ፊት ላይ እንዳይዘንብ የኖኅ የመሐላው ምልክት የሆንሽ የተመሰገንሽ ማርያም ሰላምታ ላንቺ ይገባሻል” በማለት ድንቅ ምስጢርን አመስጥሯል፡፡ ሌሎች ቅዱሳን አባቶችም አማናዊት ቀስተ ደመና የድኅነት ምልክት የሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም መሆኗን መስክረውላታል፡፡ ይህ የቀስተደመና ምልክትም በሰማያዊው የእግዚአብሔር ዙፋን ጭምር መታየቱን መጻሕፍት ያስረዳሉ (ሕዝ 1:28 ራዕይ 4:3)።

ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴ ቀለማት (Pan-African Colours) (በብዙ ሀገራት ባንዲራ ላይ የሚገኘው) መነሻው የቀስተ ደመና ምልክት መሆኑ ቢታወቅም በሁለቱ መካከል መሠረታዊ ልዩነቶች እንዳሉ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ቀስተ ደመና በእግዚአብሔርና በሰው (በዓለም ላይ ያለው ሰው ሁሉ) መካከል ያለው ቃል ኪዳን ምልክት ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማ ግን የሀገር ፖለቲካዊ ምልክት ነው፡፡ ቀስተ ደመና በሰውና በእግዚአብሔር መካከል በደመና ላይ የሚታይ ምልክት ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማ ግን በጨርቅ ወይም መሰል ቁስ ላይ ተደርጎ የሚሰቀል ነው፡፡ ቀስተ ደመና ከሰባት የማያንሱ ቀለማት አሉት፡፡ በቀስተ ደመና ላይ ያሉት ቀለማት አቀማመጥም እንዲሁ ከሰንደቅ ዓላማ የተለየ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን የቃል ኪዳን ምልክት መነሻ ያደረጉ የብዙ ሀገራት ሰንቅ ዓላማዎች እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ይህ የቀስተ ደመና ቀለማት ያለው ምልክት የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን የሚደግፉና የሚፈጽሙ አካላት ምልክት ሆኗል፡፡ ይህ ቢሆንም ግን የቃል ኪዳን ምልክትነቱ የጸና ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ዓላማዋ “ነዋ ወንጌለ መንግስት/የመንግስት ወንጌል እነሆ” የሚለውን አምላካዊ ቃል መመሪያ በማድረግ ለሰው ልጅ ሁሉ ወንጌልን በመስበክ ለዘላለም ሕይወት ማብቃት ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” (1ኛ ቆሮ 1፡23) እንዳለው የቤተክርስቲያን ዓላማ ክርስቶስን መስበክ ነው፡፡ ይህንን ዓላማዋ ያደረገች ቤተክርስቲያን ማንኛውንም ምድራዊ አስተሳሰብ፣ አመለካከት ወይም ዓላማ በሚያንጸባርቅ ምልክት ልትገለጽ አይገባም፡፡ ስለዚህ ምድራዊ ዓላማ ያላቸው ሰዎች የራሳቸውን ዓላማ የሚገልጽ ምልክት ወደ ቤተክርስቲያን በማስገባት ከመንፈሳዊ ዓላማዋ ፈቀቅ እንድንል እንዲያደርጉ መፍቀድ አይገባም፡፡

አንዳንድ ወገኖች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ መያዝ/መጠቀም/ ቤተክርስቲያኒቱ “የኢትዮጵያ” መሆኗን ለመግለጽ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን” በሚለው ስያሜ ውስጥ “የኢትዮጵያ” የሚለው ቃል የቤተክርስቲያኒቱን “ሕጋዊ ሰውነትን፣ አስተዳደራዊ መዋቅርን፣ ታሪካዊ መሠረትን፣ ትውፊታዊ አመጣጥን…” የሚያሳይ እንጂ መንፈሳዊ ወሰንን ወይም ሃይማኖታዊ ባለቤትነትን የሚያመለክት አይደለም፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም” (ማቴ 16፡18) እንዳለ እንዲሁም ቅዱስ ጳውሎስ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ….”(ሐዋ 20፡28) ብሎ እንደመሰከረው ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ቤተክርስቲያን፣ የጸሎት ቤት፣ የክርስቲያኖች ቤት ናትና አምኖ ለመገልገልና ለማገልገል ለመጣ ሁሉ ናት፡፡ ከዚህ አንጻር እንደየፖለቲካው አስተሳሰብ በየዘመናቱ የሚቀያየሩ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ምልክቶች መንፈሳዊ ማንነቷና ምንነቷን ሊገልጹ አይችሉም፡፡

ቤተክርስቲያን ግዕዛን ያላቸው ፍጥረታት (ሰውና መላእክት) ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ኅብረት ናት፡፡ ስለዚህ ቀድሞ በዓለመ መላእክት ቀጥሎም በብሉይ ኪዳን ነበረች፡፡ የሐዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ደግሞ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ከመሠረታት ጀምሮ በሐዋርያት ስብከት በዓለም ላይ ከአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንስቶ የነበረች፣ ያለችና እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ የምትኖር ናት፡፡ ሰንደቅ ዓላማን አሁን ባለው መልኩ መጠቀም የቅርብ ዘመን ታሪክና ከብሔራዊ መንግስታት መመስረት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካለንበት ዘመን ድረስ የብዙ ሀገራት ሰንደቅ ዓላማ ለብዙ ጊዜያት ለውጥ ተደርጎበታል፡፡ ለወደፊትም እንደአስፈላጊነቱ ለውጥ ሊደረግበት ይችላል፡፡ ቤተክርስቲያን ግን ትናንትናም ዛሬም ነገም “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬና ነገ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ያው ነው” እንደተባለ እርሱን ስትሰብክ ትኖራለች እንጂ አትለዋወጥም፡፡

የሰው ልጅ ሙሉ ነጻነት ያለው ፍጡር ስለሆነ በተረዳውና ባወቀው መጠን በነፃ ፈቃዱ የፈለገውን ሃይማኖት የመከተል፣ የፈለገውን ፖለቲካዊ አመለካከት የማራመድ መብት አለው፡፡ ስለዚህም ሰው በሚከተለው ሃይማኖት የተነሳ ሃይማኖታዊ ማንነት፤ በሚኖርበት ሀገር ዜግነት፤ በሚያራምደው ፖለቲካዊ አቋም ደግሞ ፖለቲካዊ ማንነት አለው፡፡ እነዚህን ማንነቶች አስማምቶ መኖር የእያንዳንዱ ሰው ድርሻ ነው፡፡ አማናዊት ቤተክርስቲያን ግን ፖለቲካዊ ወገንተኝነት የላትም፡፡ “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች” እንደተባለ ሁሉም የሚጸልይባት፣ ከአምላኩ ጋር የሚገናኝባት፣ የእግዚአብሔር ቤት ናት፡፡

ዓለም አቀፋዊት ቤተክርስቲያን ሀገራዊ/አካባቢያዊ ምልክት ይገልጻታልን?

ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ሰማያዊት ከመሆኗም ባሻገር ኩላዊት (በሁሉ ያለች፣ ዓለም አቀፋዊት) ናት፡፡ ይህም ሲባል በየትኛውም ሀገር ለሚኖር፣ የትኛውንም ቋንቋ የሚናገር ሰው ተምሮ፣ አምኖና ተጠምቆ የቤተክርስቲያኒቱ አካል፣ የክርስቶስ አካል ሆኖ ከምስጢራት ይካፈላል ማለት ነው፡፡ ሰው በቤተክርስቲያን እምነቱ እንጂ ማንነቱን ወይም ሀገሩን አይጠየቅም፡፡ ሰው አምኖ ከተጠመቀ በኋላ ማንነቱ ክርስቲያን (የክርስቶስ አካል) ሀገሩም በሰማይ ነውና (ፊል 3፡20)፡፡  እንግዲህ በዓለም ላይ ሁሉ ላለችና ለሰው ልጆች ሁሉ መዳን የሚሆነውን ቅዱስ ወንጌልን ለምትሰብክ ቤተክርስቲያን የተወሰነ ሕዝብ ወይም ሀገር ወይም ቡድን የሚጠቀምበት ምድራዊ ዓላማን በሚገልጽ ምልክት እንዴት ልትወከል ትችላለች? ስለዚህ ብዙ ውስንነት ያለውንና የቤተክርስቲያንን ኩላዊነት የማይገልጽ ማንኛውንም ዓይነት ምድራዊ ምልክት በቤተክርስቲያን እንጠቀም ማለት ከቤተክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ዓላማ ጋር አብሮ የማይሄድ ከመሆኑ ባሻገር የቤተክርስቲያኒቱን ዓለም አቀፋዊነትም እንኳን የማይገልጽ ነው፡፡ ዓለም አቀፋዊት ናት ተብሎም ምድራዊ የሆኑ ዓለም አቀፋዊ ምልክቶች አይደረጉላትም፡፡

ታዲያ ቤተክርስቲያን ዓርማ/ምልክት ምንድን ነው?

ቤተክርስቲያንም ሆነች ክርስቲያኖች የእምነት ምልክታቸው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ድኅነት ሲል የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ነው፡፡ ይህም ምልክት ብቻ ሳይሆን ኃይልም ጭምር ነው፡፡ ቅዱስ መስቀል በቤተክርስቲያኒቱ ሕንፃና በካህናቱ እጅ፣ በምዕመናኑ አንገት እንዲሁም በንዋየ ቅድሳት ላይ ያለ ክርስቶስ ስለመዳናችን የከፈለልንን ቤዛነት የምናስብበት ነው፡፡ ይህ የክርስትናችን ሃይማኖታዊ ምልክት ነው፡፡ ክርስትናችንን የሚገልጽ ከዚህ የሚበልጥ ምልክት የለንም፡፡ ምድራዊያን መንግስታት፣ ምድራዊ አስተሳሰብ፣ ምድራዊ ምልክቶችም ያልፋሉ፡፡ ቤተክርስቲያን ግን ዘላለማዊት ናት፡፡ ዘላለማዊት የሆነች ቤተክርስቲያን የሚያልፍ ምልክት ሊኖራት አይችልምና ዘላለማዊ ምልክቷ ቅዱስ መሰቀል ነው፡፡

በሌላም በኩል ቤተክርስቲያን በአካለ ሥጋ ያሉ ክርስቲያኖችና በአፀደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን ኅብረት ናት፡፡ የእነዚህ አንድነት ሁለቱም የክርስቶስ አካል መሆናቸው ነው፡፡ የክርስቶስ አካል የሆኑትም በስሙ አምነው፣ ከጎኑ በፈሰሰው ማየ ገቦ ተጠምቀው፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለው፣ ስለ ስሙ መስክረው፣ በስሙ መከራን ተቀብለው (ምግባር ትሩፋትን ሠርተው) ነው፡፡ ሰለዚህ የአንድነታቸው ምልክት ክርስቶስ የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ነው እንጂ ሌላ ምድራዊ ዓላማ ያለው ምልክት ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ አንጻር የክርስቲያኖች አንድነታችን መገለጫው በአንድ አምላክ ማመናችን፣ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት መዋጀታችን፣ በአንዱ በመንፈስ ቅዱስ መክበራችን፣ ለአንድ ተስፋ (ለመንግስተ ሰማያት) መጠራታችን፣ አንዲት ጥምቀትን መጠመቃችን፣ በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ከክርስቶስ ጋር አንድ አካል መሆናችንና ለቅዱሳን አንድ ጊዜ በተሰጠች ሃይማኖት በማመናችን ነው፡፡ የኑሮ ዘይቤ፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ፖለቲካዊ ፍልስፍና፣ ምድራዊ ሙያ/ጥበብ፣ ሰንደቅ ዓላማ…ወዘተ የምድራዊ አኗኗራችን ነፀብራቆች ናቸው እንጂ የክርስቲያናዊ አንድነት መስፈርቶች አይደሉም፡፡

አንድ መንፈሳዊ ተቋም ሰንደቅ ዓላማ ሊኖረው ይችላልን?

አንድ መንፈሳዊ ተቋም እንደ ማንኛውም ተቋም የራሱን መንፈሳዊና ሰማያዊ ዓላማ የሚገልጽ ምልክት ሊኖረው ይችላል፡፡ ይህም በመንፈሳዊ ተቋሙ የበላይ አካል የጸደቀና በተከታዮቹም የታመነበት ሊሆን ይገባል፡፡ ይህም መንፈሳዊ ዓላማን የሚገልጽና ለማንኛውም ዓይነት ምድራዊ ዓላማ ያልወገነ መሆን ይኖርበታል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴ ቀለማት ያለው ከጥንት ጀምሮ በቤተክርስቲያኒቱ የነበረ ምልክታችን ስለሆነ ዛሬ ላይ አንዳንድ ወገኖች ለፖለቲካ ዓላማ ቢጠቀሙበትም እኛ ጠብቀን ልናቆይ ያስፈልጋል ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ የባንዲራው ቀለማት መንፈሳዊ ታሪክና መነሻ እንዳላቸው ግልጽ ነው፡፡ ይሁንና እዚህ ላይ ግልጽ ማድረግ የሚያስፈልግ ዐቢይ ነገር አለ፡፡ ይህም በምልክቱና ምልክቱ በሚወክለው ዓላማ መካከል ያለው ልዩነት ነው፡፡ በቤተክርስቲያኒቱ ያሉ ሰዎች የቤተክርስቲያኒቱን ማንኛውንም ምልክት ለምድራዊ ዓላማ የሚጠቀሙ ከሆነ መንፈሳዊነታቸውን ያደበዝዘዋል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ማንኛውንም ምድራዊ ምልክት ለመንፈሳዊ ዓላማ የሚጠቀሙ ከሆነ ዓለማዊነታቸውን ያጎላዋል፡፡

ሃይማኖታዊ መሠረት ያላቸው ፖለቲካዊ ምልክቶችስ እንዴት ይታያሉ?

በዓለማችን ላይ ካሉ ሀገራት አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በሰንደቅ ዓላማቸው ላይ ሃይማኖታዊ መሠረት ያላቸው ምልክቶች አሏቸው፡፡ ጥቂት የማይባሉ ሀገሮችም በብሔራዊ መዝሙራቸው ውስጥ እንዲሁ “ሃይማኖታዊ ቃላት” አሏቸው፡፡ ይህም ሆኖ ግን የሰንደቅ ዓላማዎቹና የብሔራዊ መዝሙራቱ ዓላማ ፖለቲካዊ እንጂ ሃይማኖታዊ አይደለም፡፡ ስለዚህ የሀገራት መንግስታት ሃይማኖታዊ መነሻ ያለውን ምልክት ለሀገራዊ (ፖለቲካዊ) ዓላማ ሲጠቀሙበት የሚወስዱት ምልክቱን እንጂ ዓላማውን እንዳልሆነ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ ለምሳሌ የመስቀል ምልክት ያለባቸው ሰንደቅ ዓላማዎች ያላቸው ሀገራት አሉ፡፡ ይህ ማለት ግን የእነዚህ ሀገራት መንግስታት “ሃይማኖታዊ ዓላማ” ያላቸው ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ምናልባት አብዛኛው ሕዝባቸው ክርስቲያን ይሆናል ወይም የክርስትና ታሪክ ያለው ሕዝብ ይሆናል እንጂ፡፡

በእነዚህ ሀገራት ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ለመስቀል ምልክት የሚሰጡት ሃይማኖታዊ ትርጉምና የሚጠቀሙበት መንፈሳዊ ዓላማ እነዚህ መንግስታት ለመስቀሉ ምልክት ከሚሰጡት ፖለቲካዊ ትርጉምና ከሚጠቀሙበት ፖለቲካዊ ዓላማ የተለየ ነው፡፡ ይህንንም ማስተዋል ይገባል፡፡ በእነዚህ ሀገራት ያሉ አብያተ ክርስቲያናት የመስቀሉን ምልክት መንግስት ለፖለቲካ ዓላማ ተጠቅሞበታል ብለው ሃይማኖታዊ አገልግሎቱን አይተውም፡፡ መንፈሳዊ ትርጉሙን ጠብቀው ሃይማኖታዊ ዓላማውንም ጠንቅቀው ለመንፈሳዊ አገልግሎታቸው ይጠቀሙበታል እንጂ፡፡ ነገር ግን ሃይማኖታዊ ትርጉሙንና ሃይማኖታዊ ዓላማውን እንዲሁም መንፈሳዊ አጠቃቀሙን ለምእመናኑ በሚገባ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ፖለቲከኞቹም ቢሆኑ ፖለቲካዊ ትርጉሙን፣ ፖለቲካዊ ዓላማውንና ፖለቲካዊ አጠቃቀሙን ያሳውቃሉ፡፡ ምንም እንኳን ምልክቱ ተመሳሳይ ቢሆንም የተለያየ ትርጉም፣ ዓላማና አጠቃቀም ስላላቸው ሃይማኖትና ፖለቲካ የተለያዩ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡

ታዲያ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ምልክቶችን እንዴት እንለይ?

ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ምልክቶችን በዋናነት የምንለያቸው በቅርጻቸው፣ በመጠናቸው ወይም በቀለማቸው ሳይሆን ባላቸው ትርጉምና በሚወክሉት ዓላማ ነው፡፡ እነዚህ በግልፅ አለመለየታቸው ምዕመናን በመንፈሳዊ በዓላት ሳይቀር በመንፈሳዊ አስተምህሮ አንድ ከመሆን ይልቅ በምድራዊ ባንዲራ እየተቧደኑ ለመዘላለፍ ዳርጓቸዋል፡፡ ይህንን ክፍተትም ፖለቲከኞችና ሌሎች የቤተክርስቲያን መከፈል የሚያስደስታቸው ሰዎች ይጠቀሙበታል፡፡ ካህናትና ምዕመናን ተብለው በመንፈሳዊ አውደ ምህረት የሚሰበሰቡ ብዙ ግብዝ ሰዎችም በመንፈሳዊ ዓላማ ከሚመስላቸው ሰው ይልቅ በፖለቲካዊ ትንታኔና በሰንደቅ ዓላማዊ አንድነት የሚመስሏቸውን ሰዎች ሲያቀርቡ ይስተዋላል፡፡ በዚህም ሳናውቀው ሰቃልያነ እግዚእ አይሁድን እንመስላለን፡፡ እነርሱ አባቶቻቸው ከተውላቸው የነቢያት ተስፋ ይልቅ ለሚጠተ እስራኤል በመጨነቅ “ደሙ በእኛና በልጅ ልጆቻችን ላይ ይሁን” ብለው መድኃኒታቸውን የሰቀሉት በእግዚአብሔር ቤት ለሰማያዊ (ለመንፈሳዊ) ዓላማ ከመጨነቅ ይልቅ በምድራዊ ትብታብ ስለተያዙ ነበር፡፡ስለዚህ “የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር” (ማቴ 22፡21) እንደተባለ መንፈሳዊ/ሃይማኖታዊ ትርጉምና ዓላማ ያለውን ምልክት ለመንፈሳዊ አገልግሎት፣ ፖለቲካዊ ትርጉምና ዓላማ ያለውን ምልክት ደግሞ ለቆመለት ዓላማ ማዋል ይገባል፡፡ የሀገራዊ ምልክቶች ፖለቲካዊ ትርጉም፣ ፖለቲካዊ ዓላማና ፖለቲካዊ አጠቃቀም ለፖለቲከኞች ነው፡፡ የሃይማኖታዊ ምልክቶች መንፈሳዊ ትርጉም፣ ሃይማኖታዊ ዓላማና ክርስቲያናዊ አጠቃቀም ደግሞ ለሃይማኖት ሰዎች ነው፡፡ በአንድ ሳንቲም ላይ ‘የቄሳር’ እና ‘የእግዚአብሔር’ የሚል ጽሕፈት ቢኖርም ጌታችን “የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” እንዳለ ምልክቶች ቢመሳሳሉ እንኳን መንፈሳዊ ትርጉምን፣ ዓላማንና አጠቃቀምን ለቤተክርስቲያን፤ ፖለቲካዊ ትርጉምን፣ ዓላማንና አጠቃቀምን ደግሞ ለፖለቲከኞች መስጠት ይገባል፡፡ በፖለቲካው ንቁ ተሳትፎ ያላቸው ክርስቲያኖችም ቢሆኑ ፖለቲካውን በፖለቲካው አውድ፤ ሃይማኖታቸውን ደግሞ በመንፈሳዊው አውድ ማንጸባረቅ ይገባቸዋል፡፡ የተራራቀ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው የአንዲት ቤተክርስቲያን ልጆችም ቢሆኑ ይህን አመለካከታቸውን በቤተክርስቲያን ከሚኖራቸው ክርስቲያናዊ አንድነት ጋር ማያያዝ የለባቸውም፡፡ ከዚህ በተረፈ ፖለቲካዊ ዓላማ፣ ትርጉምና ትንታኔ ላለው ማንኛውም ምልክት ሃይማኖታዊ ካባ መደረብ አያስፈልግም፡፡ በዚህም ምክንያት የሚመጣው አላስፈላጊ ንትርክም ለቤተክርስቲያን ዕዳ እንጅ ጥቅም አይኖረውም፡፡

ስለዚህ ምን እናድርግ?

እያንዳንዱን አጥቢያ ቤተክርስቲያን ጨምሮ ቤተክርስቲያን እንደ ተቋም በባንዲራ ወገንተኝነት መተብተብ የለባትም፡፡ በዓላቶቿም በምድራዊ ቀለማት የሚደምቁ የፌሽታ ቦታዎች አይደሉም፡፡ ይሁንና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ብዙ ምዕመናን የባንዲራ ቀለማትን መጠቀም እንደሚወዱ ይታወቃል፡፡ ለዚህ መፍትሄው አንዱን መውቀስ፣ ሌላውን ማወደስ ሳይሆን ምዕመናን በየግላቸው የሚፈልጓቸው ቀለማትና አርማዎች የየራሳቸው ምርጫዎች እንጂ ቤተክርስቲያንን የሚወክሉ፣ አስተምህሮዋን የሚገልጹ አስመስሎ አለማቅረብ ነው፡፡ ምዕመናንን ይሄን ልበሱ፣ ይሄን አውልቁ የሚል አላስፈላጊ ንትርክም ቤተክርስቲያንን ጠላት ዲያብሎስ እንደሚመኘው የንትርክ አውድማ ያደርጋታል እንጂ ረብ የለውም፡፡ ይልቁንስ መንፈሳውያን መሪዎችና መምህራን በመንፈሳዊ ቦታ ምድራዊ የፖለቲካ ፉክክር እንዲፈጠር ያደረገውን መሰረታዊ ችግራቸውን መፍታት አለባቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቤት፣ የቤተክርስቲያን አውደ ምህረት፣ መንፈሳዊ በዓላት የከበረ ወንጌል የሚነገርባቸው፣ ለመንግስተ ሰማያት የሚያበቃ ምግባር የሚከብርባቸው እንጂ ሰዎች የወደዱትን የሚያሞግሱባቸው፣ የጠሉትን የሚኮንኑባቸው ምድራዊ አደባባዮች አይደሉም፡፡ ካህናትና መምህራን ትኩረታቸውን ቤተክርስቲያንን ወደሚወክለው አስተምህሮ በማድረግ ከጸኑ በጊዜ ሂደት ቤተክርስቲያን የምድራዊ ሰንደቆችና አርማዎች መፎካከሪያ ያደረጋትን መጤ አረም ማሸነፍና ለሁሉም ያለልዩነት መንፈሳዊ ዘርን መዝራቷን ትቀጥላለች፡፡

ክርስቲያናዊ አንድነታችን በእምነት መሠረቶቻችን ላይ የታነጸ መሆን አለበት እንጂ በሰንደቅ ዓላማ ወይም በፖለቲካዊ አመለካከት ልዩነት የተነሳ የሚፈረካከስ የአሸዋ ክምር መሆን የለበትም፡፡ በመንፈሳዊ በዓላትና ጉባኤያት ላይ የባንዲራ ፉክክር ማድረግ እንደ አይሁድ ሰማያዊ ተስፋን በምድራዊ፣ ውል አልባ የፖለቲካ ፍላጎት መተካት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቤተክርስቲያንን ያከስራታል እንጂ አይጠቅማትም፡፡ መንፈሳዊ አውዶች በምድራዊ ልዩነት በታጀበ ፉክክራዊ የሰንደቅ ዓላማ እሽቅድምድም ሲሞሉ ለጊዜው በስሜታዊነት የሚሰበሰቡ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ይሁንና የመሰባሰባቸው ምክንያት ፖለቲካዊ እንጂ መንፈሳዊ አይደለም፡፡ በመንፈሳዊ ቦታ ከመንፈሳዊ ሀሳብ ይልቅ ባንዲራ ማውለብለብን እና ለሚወዷቸው ፖለቲከኞች ደርዝ የሌለው ውዳሴ ማቅረብን ቁም ነገር አድርገው የሚያስቡ መለካውያን (ፈጻምያነ ፈቃደ ንጉስ፣ የቤተክርስቲያንን አስተምህሮ ለመሪዎች ጥቅም ሲሉ የሚበርዙ አድርባይ አገልጋዮች) እንደሚሉት ቤተክርስቲያንን የሚወዷት ከሆነ ከዚህ መሰል አላስፈላጊና መንፈሳዊ ረብ የሌለው እሽቅድምድም መራቅ ይገባቸዋል፡፡ ቤተክርስቲያን በምታምንበት፣ በምትታመንበት ሰማያዊ ሰንደቅ፣ በቅዱስ መስቀል እንጂ በምድራዊ ምልክት አትወከልምና፡፡

ስብሃት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር፡፡ አሜን፡፡

 

7 thoughts on “ሰንደቅ ዓላማና ቤተክርስቲያን፡ የቄሳርን ለቄሳር!

 1. ቤተክርስቲያንን ከፖለቲካ ለማሸሽ ባንዲራዋን መግፈፍ ተገቢ ነው? ከፖለቲካ በፊት ይዛው የነበረችው ባንዲራ ያለውን መንፈሳዊ ትርጉም ከፖለቲካ እንደሚለይ ማስተማር ሲገባ ባንዲራና ቤተክርስቲያን ያላቸውን መንፈሳዊ ትስስር መካድ?
  ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ‘መንፈሳዊ ወሰንን ወይም ሃይማኖታዊ ባለቤትነትን የሚያመለክት አይደለም”ማለትስ በመጽሃፍ ቅዱስ፣ በክብረ ነገስት፣ በልዩ ልዩ ዓዋልድ መጻህፍት ያላት ልዩ ቃልኪዳን የፖለቲካ ልዩነት ያመጣውን ለመሸሽ ሲባል ወደዓስተዳደራዊና ታሪካዊ ምንጭነት መቀየር ዓይሆንም? ሃገሪቱ የራሧ የሆነ መንፈሳዊ ማንነት የሌላት ናት ማለት ነው?
  በየገጠርና ገዳማቱ ባንዲራ ለብሰው የሚሄዱት መንፈሳዊ ትርጉም የላቸውም? የምታደርጉትን ዓታውቁም እኛ እናውቃለን ማለት ዓይሆንም?
  የቤተክርስቲያኒቱን ሃገራዊ መሰርትዋን እያፈረሱ ዓለማቀፍ ቅርጽ ለመስጠት መሞከር ስሩን እየነቀሉ ቅርንጫፉን ውሃ ማጠጣት ዓይሆንም?
  ለመሆኑስ ከዚያ ሁሉ የሃይማኖት መጽሃፉዋ መጽሃፍ ቅዱስ ብቻ የሁሉም መጻህፍት የበላይ ያደረገው የውጭ ተጽእኖ እንጅ ሌላ ሃይማኖታዊ ምክኛት ዓለን? መጽሃፍ ቅዱስን ብቻ እየጠቀሱ ሌሎች የቤተክርስቲያኗ መጻህፍትን መርሳት ወይም መቃረን በተዋህዶ ላይ በደል መፈጸም ዓይሆንም? ይሄ የክህደት ዓስተምህሮ ዓይደለም? : …“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን” በሚለው ስያሜ ውስጥ “የኢትዮጵያ” የሚለው ቃል የቤተክርስቲያኒቱን “ሕጋዊ ሰውነትን፣ አስተዳደራዊ መዋቅርን፣ ታሪካዊ መሠረትን፣ ትውፊታዊ አመጣጥን…” የሚያሳይ እንጂ መንፈሳዊ ወሰንን ወይም ሃይማኖታዊ ባለቤትነትን የሚያመለክት አይደለም፡፡”…ከዚህ በላይ ስር መንቀል ምን ዓለ?

  Like

 2. ስለ አስተያየትዎ እናመሰግናለን፡፡ በዚህ ጦማር ‹‹መንፈሳዊ ወሰን›› የሚለው አገላለጽ የቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አስተምህሮ በሀገራት ድንበር የሚታጠር አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ከኢትዮጵያ ውጭም አለች፡፡ ክርስትናም ወደ ሀገራችን የገባው ከውጭ ነው፡፡ ለ1500 ዓመታትም ከግብፅ ቤተክርስቲያን ጋር ነበርን፡፡ ስለዚህ ይህ የታወቀ እውነት ነው፡፡

  ሌላው ‹‹ሃይማኖታዊ ባለቤት›› የሚለው ነው፡፡ ይህ ሀረግ የቤተክርስቲያን ባለቤቷ (የመሠረታት፣ የሚጠብቃት) እግዚአብሔር መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ለዚህም ‹‹…የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ›› የሚለውን ማየት ይበቃል፡፡ እንግዲህ ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ካልሆነች የማን ልትሆን ነው?

  Like

 3. Pingback: “ቤተክርስቲያን መመሥረት”: ስሁትና ከፋፋይ ልማዶች ይታረሙ! – አስተምህሮ

 4. የጥል ግድግዳ በፈረሰበት ዘመን የጥል ግድግዳ የሚገነባ የመለያየት አባት ርኩስ መንፈስ ይወገድ።ከመለያየት የሚያተርፍ እርሱ ብቻ ነው

  Like

 5. ሁል ጊዜም በአእምሮዬ ይመላለስ ለነበረ ትልቅ ጥያቄ በሚገባ አብራርቶ መልስ የሰጠ ፅሑፍ ነው ! ከዚህ በፊት በተለያዩ አጋጣሚዎች ያውቃሉ ብዬ የማስባቸውን ሰዎች ሁሉ ብጠይቅም አሳማኝና አጥጋቢ መልስ አግኝቼ አላውቅም ነበር። ብዙዎች ሶስቱን ቀለማት ከባለ ሰባት ቀለሙ ቀስተ ደመና ጋር እያገናኙት ሌላ ጥያቄን የሚያስከትል መልስ ይሰጡኝ ነበር።

  Like

 6. የቀስተደመና ቀለማት ሰባት ስለመሆናቸው ማስረጃችሁ ምንድነው? ሳይንስ ነው እንዳትሉ ዶግማ አይደለም ይለዋወጣል፣ የዛሬ 400 ዓመት 7 ስለተባለ ያንን ይዞ መሮጥ አያዋጣም። እናም ዛሬ ከ100 በላይ ቀለማት በቀስተደመና ውስጥ እንዳሉ ተደርሷል። ወይ በቤተክርስቲያን ትምህርት ተመርኮዙ ወይም እሱን ትታችሁ ሳይንሱ ላይ ተለጠፉ። አትወላውሉ።

  Like

 7. Pingback: ዘመናዊ ጣዖታትና የጣዖት አምልኮ በቤተ ክርስቲያን | አስተምህሮ ዘተዋሕዶ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s