የቤተክርስቲያን ምስጢራዊ ትርጉም

“ቤተክርስቲያን” የሚለው የግዕዝ ቃል ሲሆን “ቤት-” እና “ክርስቲያን” ከሚሉት ቃላት የተቀመረ ነው፡፡ ይህም በግሪክ አቅሌስያ (Ecclesia) ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ቤት የሚለው ቃል ወገን፤ ነገድ፤ ዘር፤ ትውልድ፤ ጉባኤ፤ ማኅበር ማለት እንደሆነ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡(ኪ.ወ.ክ ገጽ 268) የያዕቆብ ወገን ቤተ ያዕቆብ (ቤተ እስራኤል)፤የዳዊት ወገን ቤተ ዳዊት እንዲባል በመንፈሳዊና በምሥጥራዊ ልደት ከክርስቶስ የተወለዱ ምእመናንም ቤተ ክርስቲያን ይባላሉ፤ ቤተ ክርስቶስ (የክርስቶስ ወገን) እንደ ማለት ነው፡፡ ዳሩ ግን በዘመናችን ስምና ግብር ለየቅል ሆነው በተቃራኒ ያሉት ወገኖች ሳይቀሩ ስሙን መጠሪያ አድርገው አናስተውላለን፤ ዘመናችን አማናዊቱ ቤተ ክርስቲያን ስምዋን ወስደው በሚጠሩ አስመሳዮች የተወረረችበት ወቅት በመሆኑ እውነተኛዋን ለይቶ ማወቅ ግድ ይላል፡፡ ብዙ መምህራን ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል ሦስት ትርጉም አለው ብለው ያስተምራሉ፡፡ ትርጉሙን በጥልቀት ለተመለከተው ግን አራት ነገሮችን ይገልፃል፡፡ ይቀጥላል፡፡

ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቶስ ማደሪያ፡ የክርስቲያኖች ሰውነት/ሕይወት ነው፡፡

“ቤት-“ ማለት “ማደሪያ” ማለት እንደሆነ ሁሉ ቤተክርስቲያን የሚለውም የክርስቶስ ማደሪያ ማለት ነው፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያን የክርስቶስ ማደሪያ ስለሆነ ቤተክርስቲያን ይባላል፡፡ ይህም በዋናነት የአንድ ክርስቲያንን ክርስቲያናዊ ሕይወትን ነው የሚመለከተው፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያን ሲባል የሚወክለው ምእመናንን ነው፡፡ ክርስቲያኖች የክርስቶስ ማደሪያዎች ናችውና፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቶስ ማደሪያ የሆኑ ክርስቲያኖችን /የክርስቲያኖችን ሰውነት/ የሚያመለክት ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።” 1ኛቆሮ. 3፡16-17 ገላ 1፡13  እንዲሁም የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና። 1ኛቆሮ.3÷9 በራዕየ ዮሐንስም እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል። ራዕ 3÷20 ይላል፡፡ እነዚህ የሚገልጹት እያንዳንዱ ክርስቲያን የክርስቶስ ማደሪያ (ቤተክርስቲያን) መሆኑን ነው፡፡

ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች ኅብረት፡ የክርስቲያኖች አንድነት ነው፡፡

እንደ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አመሥጥሮ ቤተ ክርስቲያን ማለት “እግዚአብሔር ግዕዛን ካላቸው ፍጥረታት ጋር ያለው ግንኙነት ነው ይላሉ፡፡ ከዚህም የተነሣ የቤተ ክርስቲያንን ዕድሜ በሦስት ይከፍሉታል፥ አንደኛ የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን ሰው ከመፈጠሩ በፊት በዓለመ መላእክት የነበረችው የመላእክት አንድነት ናት፤በሊቃውንት አመሥጥሮ ሁለተኛዋ የቤተ ክርስቲያን ዕድሜ ከአቤል ጀምሮ እስከ ሐዲስ ኪዳን መግቢያ ድረስ የነበሩ ደጋግ ሰዎች አንድነት ነው፤ ሦስተኛዪቱ እና የመጨረሻዪቱ ግን በክርስቶስ ደም የተመሠረተችው የክርስቲያኖች አንድነት ናት፡፡ እርስዋም የጸጋና የጽድቅ ምንጭ ናት ከላይ የተወሱት ሁለቱ ግን ምሳሌነት ብቻ ነበራቸው፡፡” (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ገጽ 12) ከላይ እንደተገለጸው ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ በሚከተሉት ነጥቦች እርስዋን መስለው በዙሪያዋ ከከበብዋት ትለያለች፡፡

“ቤተ-“ ማለት ወገን ህብረት የሚለውን ትርጉምም ይይዛል፡፡ ለምሳሌ ቤተ እስራኤል፣ ቤተ ያዕቆብ ፣ቤተ አሮን ሲል የእስራኤል ወገን ፣የያዕቆብ ወገን፣ የአሮን ወገን እንደሚል ማለት ነውና፡፡ ማቴ 16÷18 18 ÷17 የሐዋ. 18 ÷22 20÷28 መዝ. 117፡3 በዘህም መሠረት ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያን ወገን ማለት ነው፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ (የምእመናን አንድነት ጉባኤ) የሚጠራበት ስም ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ይህም ስብስቡን ብቻ ሳይሆን በዋናነት በመካከላችን ያለውን ፍቅር ትስስር ህብረት አንድነት ነው የሚመለከተው፡፡ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ራስነት አንድ አካል የሆኑ የምእመናን አንድነት ናት፡፡

“እርሱም የአካለ ማሇት የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው . . .” ቆሊ. 1፡18፣24 “በየአብያተ ክርስቲያናትና ይህንንም ነገር በሰሙ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ፤” ይላል። የሐዋ 5፥11።በዚህ ምዕራፍና ቁጥር ላይ “አብያተ ክርስቲያናት” የተባሉት ማኅበረ ምዕመናን ናቸው። በሌላም ስፍራ፦ “በይሁዳ በሰማርያና በገሊላ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በሰላም ኖሩ፤ ሕዝቡም በመንፈስ ቅዱስ አጽናኝነት በዙ።” የሚል አለ። የሐዋ 9፡31 በቅዳሴም ላይ “ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተክርስቲያን አሐቲ ቅድስት ጉባዔ እንተ ሐዋርያት (አንዲት ቅድስት የሐዋርያት ጉባዔ ስለሆነች ቤተክርስቲያን ሰላም ጸልዩ)” የሚለው የሚያመለክተው ይህንን የክርስቲያኖችን ህብረት ነው፡፡

ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች መኖሪያ፡ የእግዚአብሔር ቤት ነው፡፡

ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች መኖሪያ፡ የእግዚአብሔር ቤት ነው፡፡ቤት ማለት መኖሪያ ማለት እንደሆነ ሁሉ ቤተክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች ቤት/መኖሪያ የእግዚአብሔር ቤት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ “ቤተ-ልሔም” የሚለው ቤተ ህብስት፣ የህብስት ቤት፣ የእንጀራ ቤት ማለት እንደሆነ ማለት ነው፡፡ “…እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንኩት እርሷንም እሻለሁ…በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ…እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ…መቅደሱንም እመለከት ዘንድ…(መዝሙር 27፡4)” ቤተክርስቲያን ማለት አምልኮተ እግዚአብሔር የምንፈጽምበት ሕንፃ ቤተክርስቲያንንና በውስጡ ያሉትን ንዋየ ቅድሳት፣ የሚፈፀሙትን ምሠጢራትና ያለውን አገልግሎት ጨምሮ ነው፡፡

 እዚህ ላይ ህንፃ ቤተክርስቲያን ስንል አገልግሎቱንም ጭምር የሚያመለክት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ይህም የክርስቲያኖች መሰብሰቢያ መገናኛ፤ ክርስቲያኖች በአንድነት ተሰብስበው የሚጸልዩበት ሥጋ ወደሙ የሚቀበሉበት የሚሰግዱበት ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት የጸሎት ቤት ማለት ነው፡፡ ኢሳ. 56÷7 ኤር.7÷10-11 ማቴ.21÷13 ማር. 11÷17 ሉቃ. 19÷46 በሌላም ስፍራ «እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደቤትህ እገባለሁ፥ አንተን በመፍራት በቤተ መቅደስህ እሰግዳለሁ።» እንዲል መዝ 5፡7 እንዲሁም «አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ፥ ጆሮዎቼም ያደምጣሉ። አሁንም ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ፤ ቀድሻለሁም፤ ዓይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ።» ብሏል። 2ኛ ዜና 7፥15(ኢሳ. 56፡7፤ ኤር. 6፡10-16፤ ማቴ. 21፡13፤ ማር. 11፡17፤ ሉቃ. 19፡46 ) ጌታም “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች` በማለት የቤተመቅደስን አስፈላጊነት ነግሮናል፡፡ “ቤቴ” ወዳላት ቤተመቅደስ በመሄድ ክርስቶስን ዛረም እናመልካልን፡፡ እዚህ ላይ “ቤቴ” ሲል ባለቤትነቱ የእርሱ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ሐዋርያትም ወደ ቤተመቅደስ አዘውትረው ይሄዱ እንደነበር መጽሐፍ ይናገራል (ሐዋ 3፡1) የጸሎት ቤት ናትና፡፡

ቤተክርስቲያን ማለት መዋቅርና አሠራር ያለው መንፈሳዊ ተቋምም ነው፡፡

ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል የቤተክርስቲያንን “ተቋማዊ ሰውነት” የሚያሳይም ነው፡፡ ይህም ከላይ የተጠቀሱትን ሁሉ የሚያጠቃልል ሲሆን የተቋሙን አጠቃላይ መዋቅርና መንፈሳዊ አሠራሩንም ያመለክታል፡፡ ለምሳሌ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን” ወይም “የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን” ሲባል በአጠቃላይ ያለውን ቤተክርስቲያን እንደ ተቋም የሚገልጽ ነው፡፡ ይህም ከፓትርያርኩ እስከ እያንዳንዱ ምዕመን፣ ከቤተክህነቱ እስከ እያንዳንዱ አጥቢያ ቤተክርስቲያን፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ አስተዳደር ያለውን የሚያጠቃልል ነው፡፡ በዚህ ትርጉም ከጥንት ጀምሮ የነበረችውን፣ አሁንም ያለችውን ወደፊትም የምትኖረውን ቤተክርስቲያን የሚገልጽ መሆኑን እንረዳለን (ማቴ 16፡18 ኤፌ 5፡23-27)፡፡

አንዳንድ ወገኖች “ቤተክርስቲያን” የሚለው ቃል “ሕንፃውንና ተቋሙን” አይመለከትም ይላሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ቤተክርስቲያን ማለት እያንዳንዱ ክርስቲያንና የክርስቲያኖች ህብረት መሆኑን ግን ይቀበላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን አራቱንም ትርጉሞች ነው የሚያሳየን፡፡ እዚህ ላይ ማስተዋል የሚያስፈልግ ነገር አለ፡፡ እያንዳንዱን ሰው ክርስትናን እንዲቀበል ጠብቆትም እንዲኖር ለማድረግ (ቤተክርስቲያን እንዲሆን) ቢያንስ የሆነ መንፈሳዊ አደረጃጀትና አሠራር ያስፈልጋል፡፡ ክርስቲያኖችም በአንድነት በህብረት እንዲገኙ ቦታና አስተባባሪዎች እንዲሁም የእግዚአብሔርን ቃል የሚያስተምሩ መምህራን ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህ መምህራንም የሚማሩበት/የሚሠለጥኑበት ትምህርት ቤት ያስፈልጋል፡፡ እኛ እንግዲህ ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል ትርጉም ሕንፃውንና ተቋሙንም ያጠቃልላል ስንል መጻሕፍት የገለጹትን እውነት፣ ሊቃውንት ያስተማሩትን ምሥጢር በማገናዘብና ከሌሎቹ ሁለቱ ትርጉሞች ጋር የማይነጣጠሉ ስለሆኑም ጭምር ነው፡፡

በሌላ ምሳሌ “ቤተሰብ” ማለት የአንድ ቤት ሰዎች፡ በአንድ ባለቤት የሚተዳደሩ እና በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ማለት ነው፡፡ በቤተሰብ ውስጥ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል፣ የአባላቱም አንድነት/ቤተሰባዊነት፣ የሚኖሩበት ቤትና የቤተሰቡ አስተዳደር/አመራር (ቤተሰብ ተቋም ነውና) አሉ፡፡ ቤተክርስቲያንም ማለት አንዲሁ ነው፡፡ በመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን (የማርቆስ እናት ቤት) አራቱም የቤተክርስቲያን ትርጉሞች ተገልፀዋል፡፡ እያንዳንዳቸው ሐዋርያት፣ የሐዋርያትም አንድነት፣ የተሰበሰቡባት ቤትና ከሌላው ዓለም ተለይተው ክርስቲያን መባላቸው አራቱን ትርጉሞች ያስረዳል፡፡

Leave a comment