ደብረ ጽዮን ሀገረ እግዚአብሔር: የእግዚአብሔር ሀገሩ ወዴት ነው?

ምክንያተ ጽሕፈት

ሀገረ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ሀገር) የሚለው አገላለጽ በልዩ ልዩ አገባብ በቅዱሳት መጻሕፍትና በተያያዥ መንፈሳዊ ተዋስኦዎች በተደጋጋሚ እንደምንጠቀምበት ሁሉ ለፖለቲካዊ ቅኝትም የሚጠቀሙበት አሉ። በተለይም አንዳንዶች በተንኰል ወይም ጥልቅ በሆነ አላዋቂነት መንፈሳዊውን ከዓለማዊው በመቀላቀል ሲደበላልቁት ይስተዋላል። ሆነ ብለው የእግዚአብሔርን ቃል ለፖለቲካዊ ዓላማ የሚሸቅጡ ሰዎችና ተቋማት እግዚአብሔርን የእነርሱ ርዕዮት ማስፈጸሚያ አስመስለው ለጭካኔአቸውና ለክፋታቸው መደገፊያ ሲያደርጉት ማየት የተለመደ ፣ ነገር ግን የሚያሳዝን ግብር ነው። ለዚህም የታሪክ ማሳያነት የባርነት ስርዓት (system of human slavery) እና የቅኝ ግዛት ስርዓት (colonization) አቀንቃኝ የነበሩና የሆኑ ምዕራባውያን ተቋማትና ግለሰቦችን መጥቀስ እንችላለን። ችግሩ ግን በታሪክ ብቻ የቀረና የሚቀር እንዳልሆነ በዘመናችን ኢትዮጵያ በምናያቸው የተቀደሰውን አጣመው መንፈሳዊ ቃላትና አመክንዮ እየተጠቀሙ እግዚአብሔር የፈጠረውን ክቡር ሰው ለመግደልና ለመጨረስ ከሚጣደፉ ሰዎችና ተቋማት የጥቂት ዓመታት ክራሞት በማያሻማ ሁኔታ የተገነዘብነው አሳፋሪ ሀቅ ነው።

በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ “ሀገረ እግዚአብሔር” የሚል ሀረግ በስብከትና በኦርቶዶክሳዊ መዝሙራት ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚሰማ ቃል እየሆነ መጥቷል። ለዚህ ማሳያ ከሚሆኑ የቅርብ ጊዜ ልማዶች መካከል ለኢየሩሳሌም ሰማያዊት፣ ለቤተክርስቲያን እና ለእመቤታችን ድንግል ማርያም የሚዘመሩ መዝሙራትን ለሀገረ ኢትዮጵያ “የመዘመር” ብሂል ነው። ሊቁ ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ በተለይም በኅዳር ጽዮን በዓል በሚዜም ድንቅ መዝሙሩ “አይ ይእቲ ዛቲ እንተ ታስተርኢ እምርኁቅ ከመ ማኅቶት ብርህት ከመ ፀሐይ ሙሴኒ ርእያ ሀገር ቅድስት ዕዝራኒ ተናገራ ዳዊት ዘመራ“፡፡ ትርጉም፦ “ይህች እንደ መብራት ከሩቅ የምትታየው ማን ናት? ሙሴ ያያት ቅድስት ሀገር ዕዝራ የተናገረላት ዳዊት የዘመረላት፡፡” በማለት ያመሰጠረበትን ዝማሬ “ሙሴ ከርቀት ያያት፣ እዝራ የተናገረላት፣ ዳዊት የዘመረላት ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ናት” እያሉ “የሚዘምሩ” የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን ታዝበናል። ይህን መሰል የሳብ ግጥም ቅሰጣ “ኢትዮጵያዊነትን” የጭፍጨፋና የማስራብ መሣሪያ አድርገው እያቀረቡ በቤተክርስቲያን ስም ደርዝ የሌለው ጥላቻ ሲዘሩ በሚውሉ የጦርነት አጋፋሪ፣ አደባዳቢ ሚዲያዎች ያየነው ነው።

በአገላለጽ አውድም ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ሰዎች ይህ “ሀገረ እግዚአብሔር” የሚል አጠራር ለእስራኤል ወይም ለኢትዮጵያ ብቻ የሚሰጥ ይመስላቸዋል። በዝርወት ዓለም የሚኖሩባቸውን ሀገራት ጭምር የእግዚአብሔር እንዳልሆኑ አድርገው ይቆጥራሉ፣ በግብዝነትም ይሳደባሉ። በዚህም እግዚአብሔርን በፖለቲካዊ የሀገራት ድንበር ሊገድቡት ይሻሉ። በአንፃሩም ሌሎች ክርስቲያኖች “ሀገረ እግዚአብሔር” ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው? አንድን ሀገር ብቻ ለይታችሁ ‘ሀገረ እግዚአብሔር’ የምትሉት ዓለምን ሁሉ የፈጠረና በሁሉም ቦታ የሚኖር አምላክ የተለየ ሀገር አለውን?” እያሉ እየጠየቁ ይገኛሉ። በዚህች የአስተምህሮ ጦማር ቀላልና ቀጥተኛ የሆነውን የ”ሀገረ እግዚአብሔር ” መንፈሳዊ ትርጉም በመተንተን ቃሉን የሚቀስጡ፣ መንፈሳዊ ባልሆነ መንገድ ሆነ ብለው የሚያጣምሙ ሰዎችን ለክፉ ዓላማ የዋለና እየዋለ ያለ ትርክት መሰረት አልባነት ለማሳየት እንሞክራለን።

እግዚአብሔር ምሉዕ በኩለሄ ነው።

ሰማይና ምድርን እንዲሁም በምድርና በሰማይ ያሉትን ፍጥረታት ሁሉ የፈጠረ አምላካችን እግዚአብሔር በፍጥረት የመጨረሻው ቀንም ሰውን ፈጠረ (ዘፍ 1:26)፣ በምድር ያሉ ፍጥረታትን ሁሉ ይገዛም ዘንድ ሾመው። ሰውም በምድር ላይ እየበዛ ሲሄድ በተለያዩ ቦታዎች መኖር ጀመረ። በዘመናት ብዛትም የየራሳቸው ምድራዊ መንግሥትና አስተዳደር ያላቸው ሀገራት ተፈጠሩ። እነዚህ ሁሉ ሀገራት ሰዎች ድንበር ሠርተው የፈጠሯቸው ናቸው። በየሀገራቱም የየራሳቸው ባህል፣ ሃይማኖት ያላቸውና የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ሕዝቦች ይኖራሉ። ምድራዊ ሀገራትም በየዘመናቱ የአስተዳደር ወሰናቸውና ስማቸው እየተቀያየረ፣ ሰውም ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው እየተንቀሳቀሰ፣ የሕዝቡም አኗኗር እየዘመነ እስክ ዕለተ ምፅዓት ይቀጥላሉ።

እግዚአብሔር ግን ለዘመኑ ጥንት ወይም ፍጻሜ የሌለው አልፋና ኦሜጋ በቦታና በመጠን የማይወሰን በምልዓትና በርቀት ያለ ኃያልና ልዑል አምላክ ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያስተምሩን እግዚአብሔር “ምሉዕ በኩለሄ” ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ “እኔ የቅርብ አምላክ ነኝ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለሁም። ሰው በስውር ቢሸሸግ፥ እኔ አላየውምን? ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን? ይላል እግዚአብሔር። (ኤር 23፡ 23-24)” በማለት እግዚአብሔር በሰማይና በምድር የመላ መሆኑን ተናግሯል። ንጉሥ ሰሎሞንም “በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፥ ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ! (1ኛ ነገ 8፡27)” ብሎ እግዚአብሔርን የሚወስነው ነገር እንደሌለ ተናግሯል። ዳዊትም በመዝሙሩ “ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ፥ አንተ በዚያ አለህ። ወደ ሲኦልም ብወርድ፥ በዚያ አለህ (መዝ 138፡7)” ያለው ይህንኑ ያስረዳናል።

ታዲያ የእግዚአብሔር ሀገሩ ወዴት ነው?

በመንፈሳዊ አስተምህሮ “ሀገር” የሚለው ቃል ለእግዚአብሔር ሲውል ማደሪያ፣ መኖሪያ ማለት ነው። በዚህም መሠረት “ሀገረ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ሀገር)” ስንልም የእግዚአብሔር ማደሪያ፣ መኖሪያ፣ እግዚአብሔር በተለየ ሁኔታ የሚኖርበት ወይም የሚገለጥበት ቦታ ማለታችን ነው። በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት የእግዚአብሔር ሀገር ተብላ በንባብም፣ በምሳሌም፣ በምስጢርም የምትገለጸው ደብረ ጽዮን ናት። ይህችም በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር የተገለጠባት፣ ቃል ኪዳን የሰጠባት፣ የተመሰገነባት በምድር ላይ ያለች ልዩ ቦታ ነች። በሐዲስ ኪዳንም ለመዳናችን መሠረት የሆኑ ዐበይት ምሥጢራት የተፈጸሙባት ቦታ ናት። ነገር ግን ከምድራዊ ቦታነት (መካንነት) የተለየ መንፈሳዊ ትርጉም ያላት መሆኗ ይታወቃል። በዚህም ሰው የሆነ አምላካችን ክርስቶስን ላስገኘችልን ቅድስት ድንግል ማርያምና ሕይወት ለምናገኝባት ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን አማናዊ ምሳሌ ሆናለች። በሰማያት ላለችው የእግዚአብሔር መንግሥትም አምሳል ሆናለች። ከዚህ በመቀጠልም ጽዮን እውነተኛ ሀገረ እግዚአብሔር መሆኗን የሚያስረዳውን የቅዱሳት መጻሕፍትን አስተምህሮ እናቀርባለን።

ደብረ ጽዮን ሀገረ እግዚአብሔር ናት

እግዚአብሔር አስቀድሞ ብሉይ ኪዳንን (ሕገ ኦሪትን) ኋላም ሐዲስ ኪዳንን (ሕገ ወንጌልን) ለሰው ልጅ ሁሉ ለመስጠት የመረጣቸው እስራኤላውያን ሕዝበ እግዚአብሔር ተብለው ተጠርተዋል። እግዚአብሔርም እንዴት እንደመረጣቸው ሲናገር “ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፤ በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መረጠህ። እግዚአብሔርም የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፤ እናንተ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ጥቂቶች ነበራችሁና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ ወደዳችሁ ለአባቶቻችሁም የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ፥ ስለዚህ እግዚአብሔር በጽኑ እጅ አወጣችሁ፥ ከባርነትም ቤት ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ አዳናችሁ። (ዘዳ 7:6-9)” ብሏል።

በእውነትም እግዚአብሔር በምድር ላይ እንደ እስራኤል ሕዝብ ተአምራትን ያደረገለት የለም። ለዚህም ነው መጽሐፍ “ለእርሱ ለራሱ እንዲሆን ሕዝብን ይቤዥ ዘንድ ለእርሱ ለራሱም ስም ያደርግ ዘንድ፥ በአሕዛብና በአምላኮቻቸውም ፊት ከግብጽ በተቤዠው ሕዝብ ፊት ተአምራትንና ድንቅን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ሄደለት እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ምን ሕዝብ አለ? (2ኛ ሳሙ 7:23)” ያለው። ለዓለም ሁሉ የመዳን መንገድ አድርጓቸዋልና እስራኤልን የካህናት መንግሥት አላቸው – “አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤ እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ። (ዘፀ 19:5-6)” ቅዱስ ጴጥሮስም እስራኤል የተመረጡ እንደነበሩ ሲገልፅ “እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ (1ኛ ጴጥ 2:9)” በማለት ጽፏል። ጌታችንም በዚያ ተወልዶ አድኖናል።

ከቦታዎችም ሁሉ ደብረ ጽዮንን ልዩ አድርጎ መርጧታል። ጽዮን የሚለው ቃል ቀጥታ ትርጉሙ የእግዚአብሔር መንግሥት (Kingdom of God) ማለት ሲሆን በብሉይ ኪዳን የጽዮን ተራራ፣ የዳዊት ከተማ፣ መላው ኢየሩሳሌም እንዲሁም ሕዝበ እስራኤልን ለማመልከት ውሏል። አባታችን አብርሃም በዚህች ተራራ (አስቀድሞ የሞሪያም ተራራ ትባል ነበር) ልጁ ይስሐቅን ለመስዋዕትነት አቅርቧል። ያዕቆብም በዚህች ተራራ ህልምን አይቶ የሰማይ ደጅ ብሏታል። ልበ አምላክ የተባለ ንጉሥ ዳዊትም መናገሻው አድርጓታል። በመዝሙሩም 38 ጊዜ አንስቶ ዘምሮላታል። ጠቢቡ ሰሎሞንም በዚህች ተራራ ላይ በእግዚአብሔር የተወደደ ቤተ መቅደሱን ሠርቷል (2ኛ ዜና 3:1)። በዚህም ይህች ተራራ በምድር ላይ ካሉ ቦታዎች ሁሉ ተለይታ የእግዚአብሔር ማደሪያ ተብላለች። ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ በትንቢቱ “እነሆ፥ እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ለእስራኤል በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክትና ተአምራት ነን። (ኢሳ 8:18)” በማለት የጽዮን ተራራ የእግዚአብሔር መኖሪያው (ሀገሩ) መሆኗን ተናግሯል። ልበ አምላክ ክቡር ዳዊትም በመዝሙሩ “አስቀድመህ የፈጠርሃትን ማኅበርህን፥ የተቤዤሃትንም የርስትህን በትር፥ በእርስዋ ያደርህባትን የጽዮንን ተራራ አስብ። (መዝ 74:2)” ሲል የጽዮን ተራራ የእግዚአብሔር ማደሪያው መሆኗን ተናግሯል። እንዲሁም እርስዋ የእግዚአብሔር ለዘለዓለም ማረፊያው መሆኗን ሲናገር “እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ እንዲህ ብሎ። ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት፤ መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ። (መዝ 132: 13-14)” በማለት እውነተኛዋ የእግዚአብሔር ማደሪያው መሆኗን አስረድቶናል።

ሰማያዊቷ ደብረ ጽዮን ሀገረ እግዚአብሔር ናት

የእግዚአብሔር መኖሪያው በሰማይ (በልዕልና) ነው። ለዚህ ነው ሊቀ ነቢያት ሙሴ “ከቅዱስ ማደሪያህ ከሰማይ ጐብኝ፥ ሕዝብህንም እስራኤልን ለአባቶቻችን እንደ ማልህላቸው የሰጠኸንንም ወተትና ማር የምታፈስሰውን አገር ባርክ። (ዘዳ 26:15)” በማለት ጸሎትን ለእግዚአብሔር ያቀረበው። ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም “ለዘላለም የሚኖር ስሙም ቅዱስ የሆነ፥ ከፍ ያለው ልዑል እንዲህ ይላል። የተዋረዱትን ሰዎች መንፈስ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠውንም ልብ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠና የተዋረደ መንፈስ ካለው ጋር በከፍታና በተቀደሰ ስፍራ እቀመጣለሁ። (አሳ 57:15)” በማለት እግዚአብሔር በተቀደሰና በልዕልና ስፍራ እንደሚኖር ጽፏል። ይህችም ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ወይም ደብረ ጽዮን ቅድስት ትባላለች።

ጌታችንም እንዴት መጸለይ እንደሚገባን ሲያስተምረን “እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ። በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፥ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን… (ማቴ 6:9-10)” በማለት የጸሎትን ሥርዓት ሲሠራ በሰማያት (በልዕልና) የምትኖር ብለን እንድንጠራው ነግሮናል። እኛም ሁላችን ተስፋ የምናደርጋት መንግሥተ ሰማያት እግዚአብሔር በክብር የሚኖርባት ሀገሩ ናት። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ለፊልጵስዮስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ “እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን (ፊልጵ 3:20)” በማለት እኛም ዘላለማዊ ሀገራችን በሰማይ ከእርሱ ዘንድ እንደሆነ በግልፅ አስተምሯል።

ይህችም የእግዚአብሔር መንግሥት ሰማያዊት ጽዮን ተብላለች። ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ “አየሁም፥ እነሆም፥ በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፥ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ። እንደ ብዙ ውኃም ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅን ሰማሁ፥ ደርዳሪዎችም በገና እንደሚደረድሩ ያለ ድምፅ ሰማሁ። በዙፋኑም ፊት በአራቱም እንስሶችና በሽማግሌዎቹ ፊት አዲስ ቅኔ ዘመሩ፤ ከምድርም ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራት ሺህ በቀር ያን ቅኔ ሊማር ለማንም አልተቻለውም። ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው፥ ድንግሎች ናቸውና። በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው። ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው። በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም (ራዕ 14:1-5″ በማለት እውነተኛዋ በሰማይ ያለችው የእግዚአብሔርን መንግሥት ደብረ ጽዮን ብሏታል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ለዕብራውያን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ “ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል (ዕብ 12:22-24)።” በማለት የጽዮን ተራራ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም፣ የሕያው እግዚአብሔር ከተማ፣ ጻድቃንም የሚኖሩባት መሆኗን በማያሻማ መልኩ ገልጿታል። ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም ” እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ እየዘመሩም ወደ ጽዮን ይመጣሉ፤ የዘላለም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ሐሤትንና ደስታን ያገኛሉ፥ ኀዘንና ትካዜም ይሸሻሉ። (ኢሳ 35:10)” በማለት ሰማያዊቷና የማታልፈው ከተማ እርሷ መሆኗን ተናግሯል። መዝሙረኛው ዳዊትም ይህንኑ ሲገልፅ “እግዚአብሔር ከጽዮን ይባርክህ፤ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፥ የኢየሩሳሌምን መልካምነትዋን ታያለህ። (መዝ 128:5)” በማለት በሰማያት የእግዚአብሔር ሀገሩ መሆኗን ገልጿል።

አማናዊት ጽዮን ድንግል ማርያም ሀገረ እግዚአብሔር ናት።

ጌታችን የሰውን ልጅ ለማዳን በልዩ የተዋሕዶ ምሥጢር ሰው በሆነ ጊዜ ለዘጠኝ ወር ማደሪያው ያደረጋት የእግዚአብሔር ሀገሩ (ማደሪያው) ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ወደ ካራን ሲሄድ ያያት ሰውና እግዚአብሔርን ያገናኘች መሰላል የእግዚአብሔር ማደሪያው እርሷ ናት። መጽሐፍ “እነሆም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ፥ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ፥ እነሆም የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበት ይወርዱበት ነበር። እነሆም፥ እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር። … ያዕቆብም ከእንቅልፉ ተነሥቶ። በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ነው.. ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህም የሰማይ ደጅ ነው። (ዘፍ 28:10-27)” እንዳለው እርሷ የእግዚአብሔር ሀገሩ ናት። አባቶቻችንም በሰዓታት ጸሎት “ዛቲ ይእቲ ጽዮን ሐዳስ ሀገረ አምላክነ ዘኃደረ ላዕሌሃ ፍሥሓ ኵሎሙ ነቢያት ቅዱሳን (የአምላካችን ማደሪያው አዲሲቷ ጽዮን ፤ የቅዱሳን ነቢያት የትንቢታቸው ፍጻሜ ደስታቸው አንቺ ነሽ)” የሚሏት ሀገር እግዚአብሔር እርሷ ስለሆነች ነው።

በብሉይ ኪዳን ለድንግል ማርያም ምሳሌ የነበረችው ጽዮን የእግዚአብሔር ማደሪያው ተብላለች። የእግዚአብሔርን የሰውን ልጅ የማዳን ጥበብ በትንቢተ መነጽር አይቶ የተናገረው እንደ ልቤ የተባለው ዳዊት በሌላው መዝሙሩም “በጽዮን ለሚኖር ለእግዚአብሔር ዘምሩ፥ በአሕዛብም መካከል አደራረጉን ንገሩ” (መዝ 9:11) እንዲሁም “እግዚአብሔር በይሁዳ ታወቀ፥ ስሙም በእስራኤል ታላቅ ነው። ስፍራው በሳሌም፥ ማደሪያውም በጽዮን ነው። (መዝ 76:2)” በማለት ጽዮን ማደሪያው እንደሆነች በመዝሙሩ ዘምሮታል። በተጨማሪም “መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው፤ ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ፥ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወድዳቸዋል። የእግዚአብሔር ሀገር/ከተማ ሆይ፥ በአንቺ የተከበረ ነገር ይባላል…ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፥ በውስጥዋም ሰው ተወለደ፤ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት። (መዝ 87:3-5)” በማለት በሐዲስ ኪዳን ማኅደረ መለኮት ለሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያም በምሳሌ ተናግሯል። ቅድስት ድንግል ማርያም በእውነትም የእግዚአብሔር ሀገሩ፣ የእግዚአብሔር ከተማው ናት። በእርስዋ ድንቅ፣ የተከበረው በልዩ ጥበቡ ሥጋን ተዋሕዶ ሰውን ያዳነበት ምሥጢር ሲነገር ይኖራል። ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስም የብሥራቱንና የፅንሰቱን ነገር በተናገረበት ወንጌሉ “መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት። መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል። (ሉቃ 1:34-35)” በማለት አስቀድሞ በትንቢት የተነገረው ሀገረ እግዚአብሔር የመሆኗ ምሥጢር መፈጸሙን ጽፎታል።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሀገረ እግዚአብሔር ናት።

በዘመነ ኦሪት እግዚአብሔር በቃል ኪዳኑ ታቦት (በታቦተ ጽዮን) ላይ አድሮ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሙሴን፣ ኋላም ሊቀ ካህኑን ያናግር እንደነበር በሰፊው ተጽፏል። ኋላም “በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ። (ዘጸ 25:8)” ባላቸው መሠረት መቅደስን ሠርተዋል። የኦሪቱ ሥርዓተ መስዋዕት በዚህ መልኩ ቀጥሎ ከዘመናት በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን በጽዮን ተራራ ላይ ሠርቷል። እግዚአብሔርን ለሰሎሞን ቃል ኪዳንን ሲሰጠው “ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት፥ የንጉሡን ቤትና ሰሎሞን የወደደውን የልቡን አሳብ ሁሉ ሠርቶ በፈጸመ ጊዜ እግዚአብሔር በገባዖን ለሰሎሞን እንደ ተገለጠለት ዳግመኛ ተገለጠለት። እግዚአብሔርም አለው። በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ። (1ኛ ነገሥት 9: 1-3)” በማለት ቤተ መቅደሱ የእርሱ ማደሪያ መሆኑን ቃል ገብቶለታል።

ከቃል ኪዳኑ ጋርም እግዚአብሔር በመቅደሱ የሚያድረው ትዕዛዙን ሲጠብቁ ብቻ መሆኑን ሲነግረው “እናንተና ልጆቻችሁ ግን እኔን ከመከትል ብትመለሱ፥ የሰጠኋችሁንም ትእዛዜንና ሥርዓቴን ባትጠብቁ፥ ሄዳችሁም ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ፥ ብትሰግዱላቸውም፥ እስራኤልን ከሰጠኋቸው ምድር አጠፋቸዋለሁ፤ ለስሜም የቀደስሁትን ይህን ቤት ከፊቴ እጥለዋለሁ፤ እስራኤልም በአሕዛብ ሁሉ መካከል ምሳሌና ተረት ይሆናሉ። ከፍ ከፍ ብሎ የነበረውም ይህ ቤት ባድማ ይሆናል፤ በዚያም የሚያልፍ ሁሉ እያፍዋጨ። እግዚአብሔር በዚህ አገርና በዚህ ቤት ስለምን እንዲህ አደረገ? ብሎ ይደነቃል። (1ኛ ነገሥት 9: 6-8)” ብሏል። ይህም እስራኤል ከእግዚአብሔር ትዕዛዝ በወጡ ጊዜ ተፈፅሟል።

በሐዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር ማደሪያው አማናዊቷ ጽዮን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት። በዚህም አምሳለ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ትባላለች። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ብሎ ቤተ ክርስቲያን የራሱ ቤት (ማደሪያ) መሆኗን ተናግሯል (ማቴ 21:13)። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ለልጁ ጢሞቴዎስ በጻፈው መልእክቱ “በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዐምድና መሠረት፣ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው (1ኛ ጢሞ 4:15)” በማለት ቤተ ክርስቲያን አማናዊት የእግዚአብሔር ማደሪያ (ሀገር) መሆኗን በማያሻማ መልኩ አስተምሯል። እንዲሁም ለኤፌሶን ሰዎች “እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም። በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ። (ኤፌ 2:19-22)” ሲል ቤተ ክርስቲያን (የክርስቲያኖች ኅብረት) የእግዚአብሔር መኖሪያ መሆኗን አረጋግጦልናል።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎተ ሐሙስ ሥርዓተ ቁርባንን የሠራው በጽዮን ነው። የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን በሚባለው በዓለ ጰራቅሊጦስ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉት በዚሁ በጽርሐ ጽዮን ነው። ይህም እርሱ ባወቀው በሐዲስ ኪዳን ለምትኖረው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሠረት ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ያረፈችው በዚሁ በጽዮን ነው። ቆይቶም ሐዋርያት የጽዮንን ቤተ ክርስቲያን በዚያው ሠርተዋል። የጽዮን ተራራ በብሉይ ኪዳን ቤተ መቅደሱንና ሕዝበ እስራኤልን ሲገልፅ ዋና ከተማዋ ምድራዊቷ ኢየሩሳሌም ነበረች። በሐዲስ ኪዳን ግን የጽዮን ተራራ ቤተ ክርስቲያንና በክርስቶስ ደም የተዋጁ ክርስቲያኖችን ስትገልፅ መናገሻቸው በሰማይ ያለቸው አዲሲቷ ኢየሩሳሌም ናት።

የክርስቲያኖች ልብ ሀገረ እግዚአብሔር ነው።

የክርስቲያኖች ልብ (ሰውነት) የእግዚአብሔር ማደሪያ ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ “ጻድቅ አባት ሆይ፥ ዓለም አላወቀህም፥ እኔ ግን አወቅሁህ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ አወቁ፤ እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፥ ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ (ዮሐ 17:26)” በማለት ካወቁትና ካመኑት ጋር እንደሚሆን ሕያው ቃል ኪዳን ሰጥቶናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚህ ሲጽፍ “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? (1ኛ ቆሮ 3:16)” በማለት ለቆሮንቶስ ሰዎች አስተምሯል። በተጨማሪም የእግዚአብሔር ማደሪያ በሆነው ሥጋችን እግዚአብሔርን ማክበር እንደሚገባን ሲናገር “ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ። (1ኛ ቆሮ 6:20)” ብሏል። እንዲሁም ለኤፌሶን ሰዎች “በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር እንደ ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን ይስጣችሁ፤ የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ (ኤፌ 3:17)” በማለት የክርስቲያኖች ልብ በእምነት የእግዚአብሔር መኖሪያ መሆኑን አስተምሯል።

ቅዱስ ዮሐንስም በራዕዩ “እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል (ራዕ 21:3)” በማለት የጻፈው የእግዚአብሔር መኖሪያው በሰዎች መካከል መሆኑን ያስረግጥልናል። እንዲሁም ጌታችን “እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል። (ራዕ 3:20)” በማለት ሰውነታችን (ልባችን) በእምነት የእግዚአብሔር ማደሪያ መሆኑን ያስተምረናል። እንግዲህ ሰውነታችን (ልባችን) የእግዚአብሔር ማደሪያ ከሆነ እንዴት ቅዱስ መሆን እንደሚገባው ልናስተውል ያስፈልጋል። በሐዲስ ኪዳንም ድኅነት የሚገኘው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በሚኖረን እምነት መሆኑን የተናገሩት ሐዋርያትም “እነሆ፥ የተመረጠና የከበረን የማዕዘን ራስ ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ በእርሱም የሚያምን አያፍርም ተብሎ ተጽፎአልና። (1ኛ ጴጥ 2:6)” እንዲሁም “እነሆ፥ በጽዮን የእንቅፋት ድንጋይና የማሰናከያ ዓለት አኖራለሁ በእርሱም የሚያምን አያፍርም ተብሎ እንደ ተጻፈ በእንቅፋት ድንጋይ ተሰናከሉ። (ሮሜ 9:33)” በማለት ጌታችን በጽዮን የማዳኑን ሥራ መፈጸሙንና ለሚያምኑበት የዘላለም ሕይወት፣ ይህን እውነት አይተውና ሰምተው ላላመኑት ደግሞ ፍርድ እንደሚሆንባቸው ሰብከዋል።

ሀገረ እግዚአብሔር” ለምድራዊ ሀገራት

በመንፈሳዊው አስተምህሮ ሀገረ እግዚአብሔር የሚለው ቃል ትርጉም ከላይ እንደተገለጠው ቢሆንም ምን ያህል ምዕመናንና መምህራን ይህ መረዳት እንዳላቸው መመርመር ያስፈልጋል። በወፍ በረር ጥናት “የእግዚአብሔር ሀገር ማን ናት?” የሚል መጠይቅ ብናቀርብ የብዙዎች መረዳት ከቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ ሳይሆን self-serving ከሆነ አስተሳሰብ መሆኑን መረዳት አይከብድም። ይህም ብዙውን ጊዜ የራሳቸውን ምድራዊ ሀገር ወይም አካባቢ ለመግልጽ ነው።

ሰዎች “ሀገረ እግዚአብሔር” የሚለውን አገላለጽ ለምድራዊ ሀገራት የሚጠቀሙት በሁለት መንገድ ነው። የመጀመሪያ በሃይማኖታዊ እይታ ሲሆን ሁሉተኛው ደግሞ በተፈጥሮ ውበት ነው። በሃይማኖታዊ እይታ በአንድ ሀገር የሚኖር ሕዝብ ሃይማኖተኛና እግዚአብሔርን የሚያመልክ መሆኑን ለመግለጽ፣ ቦታው እግዚአብሔር በልዩ ሁኔታ የሚመለክበትና ብዙ ቅዱሳት መካናት የሚገኙበት መሆኑን ለማሳየት፣ እግዚአብሔርም ሕዝቡንና ሀገሩን በተለየ ሁኔታ በበረከት እንደጎበኘው ለመግለጽ እንዲሁም ብዙ ቅዱሳን የጸለዩበት መሆኑን ለማመልከት ይጠቀሙበታል።

ከተፈጥሮ ውበት አንጻርም አንድ ሀገር ወይም ቦታ ምንም የሰው ጥበብ ሳይታከልበት በተፈጥሮ ያገኘውን እጅግ ግሩምና አስደናቂ የሆኑ የተፈጥሮ ገፅታዎችን ለመግለጽ ‘ሀገረ እግዚአብሔር’ (God’s own country) ይሉታል። እግዚአብሔር ልዩ አድርጎ የፈጠረው ማለታቸው ነው። Blake Shelton የሚባል አሜሪካዊ God’s country (የእግዚአብሔር ሀገር) በሚል ርዕስ ሙዚቃ የሠራላት Oklahoma state ናት። በተጨማሪም Australia, Brazil, England, India, New Zealand, United States እና Zimbabwe ተፈጥሯዊ ውበትን ለመግለፅ God’s own country የሚለውን ሀረግ ተጠቅመዋል።

ማጠቃለያ

የተቀደሰችው ደብረ ጽዮን በእውነትም ሀገረ እግዚአብሔር ናት። በምድር እግዚአብሔር በእርስዋ ላይ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅ፣ ለያዕቆብ፣ ለዳዊት፣ ለሰሎሞንና ለሌሎችም ቀደምት አበው ቃል ኪዳንን ሰጥቷል። በዚህች ተራራ ላይ ቤተ መቅደሱ ተሠርቷል። እግዚአብሔርም በቅድስናው ሲቀደስ ኖሯል። ስለዚህም በምድር ላይ ካሉ ቦታዎች ሁሉ ሀገረ እግዚአብሔር የተባለችውና ልትባልም የሚገባት የዳዊት ከተማ ጽዮንን፣ ምድራዊቷ ኢየሩሳሌምንና ሕዝብ እስራኤልን በአንድነት የምትገልጸው ደብረ ጽዮን ናት። የተቀደሰችው ደብረ ጽዮን በሐዲስ ኪዳንም ምክንያተ ድኂን ለሆነችውና ጌታን ለወለደችልን ቅድስት ድንግል ማርያምና የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ለምትመግበን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አማናዊ ምሳሌ ሆናለች። ስለዚህ በሐዲስ ኪዳን ላለን ክርስቲያኖችም የእግዚአብሔር ማደሪያው አማናዊት ጽዮን የተባለችው ድንግል ማርያምና የሰማያዊቷ ጽዮን አምሳል የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት። ፍጽምት እና ዘላለማዊ የሆነችው የእግዚአብሔር ሀገር ግን ሰማያዊቷ ጽዮን የተባለችው የእግዚአብሔር መንግሥት ናት። ሁላችንም በምድር ባለችው ጽዮን በቤተ ክርስቲያን ጸንተን በሰማያት ያለችውን ደብረ ጽዮን ቅድስትን ተስፋ እናደርጋለን። ስለ ሀገረ እግዚአብሔር በራሳቸው መረዳት እየተረኩ የእግዚአብሔርን ህዝብ የሚጨርሱ የተረገሙ ቀሳጥያንን የምንለይበትን ጥበብ ስጋዊ፣ ጥበብ መንፈሳዊ ያድለን። አምላካችን እግዚአብሔር ክብርት በምሆን በደብረ ጽዮን ነፃ በምታወጣ በሰማያዊት ኢየሩሳሌም ይሰብስበን። አሜን ።

Leave a comment