አሠርቱ ትዕዛዛት: በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያላቸውና ሊኖራቸው የሚገባው ተፈጻሚነት

መግቢያ

አሠርቱ ትዕዛዛት በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ለሊቀ ነቢያት ሙሴ የሰጣቸው ሕግጋት ሲሆኑ በሐዲስ ኪዳንም “እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፣ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም።” (ማቴ 5:17) በሚለው በጌታችን በኢየሱስ ክርሰቶስ ቃል የጸኑ ናቸው። ትዕዛዛቱ አሥር መሆናቸው የፍጹምነት ምሳሌ ሲሆን በሁለት ጽላቶች ላይ መጻፋቸው ሁለቱን መሠረታዊ ሕግጋት ማለትም ፍቅረ እግዚአብሔርን እና ፍቅረ ቢጽን የሚያመለክቱ መሆናቸውን ያጠይቃል። እግዚአብሔር ራሱ ትዕዛዛቱን ከአንድም ሁለት ጊዜ ባጣቶቹ መጻፉ ትዕዛዛቱ ምን ያህል ታላቅና አስፈላጊ መሆናቸውን ያሳየናል። ስለዚህም እነዚህ ትዕዛዛት ሁሉም ክርስቲያን ሊጠብቃቸው የሚገባ ሕግጋትና የሌሎች ሕግጋትም መሠረቶች ናቸው። በገሀዱ ዓለም የእነዚህ ትዕዛዛት አፈጻጸም ግልጽ ቢሆንም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያላቸው ተፈጻሚነትን በግልጽ የሚያስረዳ ትምህርት ያስፈልጋል። ምዕመናንም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባላቸው ተሳትፎ እንዴት ሕግጋተ እግዚአብሔርን መጠበቅ እንዳለባቸው የሚተነትን ትምህርት ያስፈልጋል ብለን በማመን በዚህች የአስተምህሮ ጽሑፍ ከመንፈሳውያን መጻሕፍት ያገኘናቸውንና ከመምህራን የተማርናቸውን መነሻ በማድረግ አሠርቱ ትዕዛዛት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያላቸውን (ሊኖራቸው የሚገባውን) ተፈጻሚነት አብራርተናል። ለዚህም ትዕዛዛቱን በቅደም ተከተል በመዘርዘር ከማኅበራዊ ሚዲያ አውድ አኳያ ተንትነን አቅርበነዋል።

1. ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ። ዘጸ 20፡2-6 ዘዳ 5፡6-10

ይህ ትዕዛዝ ከእግዚአብሔር ሌላ (ራስን ጨምሮ) ማንኛውንም ዓይነት ነገር ማምለክን ይከለክላል። በዘመነ ብሉይ “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም (ዘጸ 20:3-6)” እንደተባለ ይህ ትዕዛዝ በተለይም ጣኦት ማምለክና የተቀረጸ ምስልን መከልከል ላይ ያተኩር ነበር። በዘመነ ሐዲስ ደግሞ ዘመናዊ ጣኦታት የሚባሉትን ገንዘብን፣ ስልጣንን፣ ራስን፣ የምናፈቅረውን ሰው፣ የግል ጥቅምን፣ አመለካከትን እና የመሳሰሉትን ማምለክን ይከለክላል። ጌታችን በገዳመ ቆሮንቶስ “ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል” ያለው (ማቴ 4:10) ይህንን የሚገልጽ ነው። ሕግ አዋቂውም በጠየቀው ጊዜ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህ በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት” (ማቴ 22:37 ዘዳ 6:5) ያለው ይህንን ትዕዛዝና ሌሎቹንም አምልኮተ እግዚአብሔርን (ፍቅረ እግዚአብሔርን) የሚመለከቱትን ትዕዛዛት የሚያጠቃልል ነው። ይህም የመጀመሪያውና ዋነኛው ሕግ ሲሆን የሚፈጸመውም እግዚአብሔርን ብቻ በማምለክ ነው።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚኖረው ተፈጻሚነት: ማኅበራዊ ሚዲያን በአግባቡ ካልተጠቀምክ ዘመናዊ ጣኦት ሊሆንብህ ይችላል። ማኅበራዊ ሚዲያ ያገነናቸውን ታዋቂዎችንና ዝነኞችን (public figures) አታምልክ – በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ታዋቂና ዝነኛ የሆኑ አገልጋዮችን/ሰዎችን እንደ ፍጹም አትውሰድ። ስሜን ያጠፋሉ ብለህም ከፈጣሪ ይልቅ እነርሱን አትፍራ። የእነርሱን ሀሳብ፣ አለባበስ፣ አነጋገር እና እንቅስቃሴ ልዩ ምሳሌ አድርገህ አትውሰድ። ለማኅበራዊ ሚዲያ ቀመሮች (Statistics) አትገዛ – የማኅበራዊ ሚዲያ ቀመሮችን (like, share, comment, subscribe) የዕውቀት፣ የተጽዕኖ ፈጣሪነት፣ የተሰሚነትና የማንነት መግለጫ አድርገህ አትውሰድ። በማድነቅ አባዜ አትያዝ – በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የምታያቸውን ማራኪ ፎቶዎች፣ ቪዲዮዎች ወይም ንግግሮችን በማድነቅና በማጋራት አትጠመድ። ጸሎት ይልቅ ማኅበራዊ ሚዲያን አታስቀድም – ከልክ በላይ ማኅበራዊ ሚዲያን መከታተል፣ የጸሎትና ራስህን የምታይበትን ጊዜ ለዚህ ማዋል፣ ማኅበራዊ ሚዲያን ከእግዚአብሔር ማስቀደምን ያስከትላልና ከዚህ ተጠበቅ። በቡድናዊነት አስተሳሰብ አትያዝ – ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስለራሳቸው አብዝተው የሚሰብኩ ቡድኖች (groups) ውስጥ መግባትና ለእነርሱም ታማኝ መሆን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ። ከማኅበራዊ ሚዲያ የሚገኝ ታይታንና አድናቆትን አትከተል – ራስህን እና ስኬቶችህን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ልዩ አድርጎ በማቅረብ መወደድን እና አድናቆትን ከሌሎች አትጠብቅ። ማኅበራዊ ሚዲያን የጥበብ ምንጭ አድርገህ አትውሰድ – ከመንፈሳዊ ትምህርትና ጥበብ ይልቅ በተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ አነቃቂ ንግግር ተናጋሪዎች (motivational speakers)፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች (Activists) እና ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሚገኙ ሀሳቦች ላይ ተመርኩዘህ ሕይወትህን ለመምራት አትሞክር።

2. የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ። ዘጸ 20፡7 ዘዳ 5፡11

የእግዚአብሔር ስም ታላቅና እጅግ የከበረ ነው። እኛም የተፈጠርነው ስሙን ለመቀደስ ነው። እኛ ብንበድለውም እርሱ ግን ራሱ ተወልዶ አርአያና ቤዛ ሆኖ አድኖናል። ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት “አቤቱ፥ ስለዚህ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ ለስምህም እዘምራለሁ (መዝ 18:49)” በማለት የሰው ልጅ ድርሻ ስሙን ማመስገን እንደሆነ ተናግሯል። ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም ስለስሙ ታላቅነት ሲናገር “ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” (ኢሳ 9:6) ብሏል። በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ይህ ስም የዳንበትና የምንድንበት ስም ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ “መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።” (ሐዋ 4:12) በማለት ስሙ መዳኛችን መሆኑን መስክሮልናል። ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚህ ሲናገር “በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።” (ፊል 2:9-11) በማለት ስሙ ያለውን ክብር አስተምሯል። ጌታችንም በተራራው ስብከት “ከቶ አትማሉ፤ … ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው።” (ማቴ 5:24) ያለው ይህንን ሕግ ፍጹም ሲያድርገው ነው።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚኖረው ተፈጻሚነት: በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የአምላክህን ስም በከንቱ አትጠቀም – የእግዚአብሔርን ስም በየልጥፍ (post) እና በየኮመንት በከንቱ መጥራት (ለምሳሌ በረባ ባልረባው Oh My God (OMG) ማለት) ይህንን ትዕዛዝ መተላለፍ ሊሆን ይችላል። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በእግዚአብሔር ስም አትነግድ – ላይክና ሼር ወይም የገንዘብ ልገሳ ለማግኘት ወይም ተከታይ ለማብዛት ብለህ የእግዚአብሔር ስም ያለበትን የሐሰት መረጃ አታጋራ። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በእግዚአብሔር ስም አትቀልድ – የእግዚአብሔርን ስም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በቀልዶች፣ በስላቅ ወዘተ ውስጥ አትጠቀም። ለእግዚአብሔር ክብር የማይሰጥን ነገር አትውደድ፣ አታጋራ – ለእግዚአብሔርና እርሱ ላከበራቸው ቅዱሳን የሚገባቸውን ክብር የማይሰጥ ፖስት ወይም ቪዲዮ ማጋራትም በዚያው ተግባር መተባበር ነው። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የእግዚአብሔርን ቃል ከመንፈሳዊ አውድ ውጭ አትጠቀም – መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶችን ወይም ሌሎች ሃይማኖታዊ ቃላትን ከመንፈሳዊ አውድ ውጭ ለመቀለድ ወይም ለማሳሳት መጠቀም ይህንን ትዕዛዝ መተላለፍ ነው። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የእግዚአብሔርን ስም እየጠራህ አታጭበርብር – በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መንፈሳዊ በመምሰል የእግዚአብሔርን ስም እየጠሩ ማጭበርበር ወይም ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን መሞከር በእግዚአብሔር ስም ማታለል ነው። በማኅበራዊ ሚዲያ በሌሎች ሰዎች እምነት ላይ አትሳለቅ – ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት መተቸት ወይም በእምነታቸው መሳለቅ ይህንን ትዕዛዝ መሻር ነው።

3. ሰንበትን አክብር፣ ቀድሰውም። ዘጸ 20፡8-11 ዘዳ 5፡12-15

በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ። ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤ ሰባተኛው ቀን ግን እግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ ከብትህም፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ፤ እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም።(ዘጸ 20:8-11)” በማለት ሕዝበ እስራኤል ቀዳሚት ሰንበትን እንዲቀድሷት ትዕዛዘን ሰጥቷል። ሰንበትን ማክበርም በእግዚአብሔርና በእስራኤል ልጆች ዘንድ የዘላለም ምልክት ነው (ዘጸ 31:16)። በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ጌታችን ሙስና መቃብርን ድል አድርጎ ትንሣኤውን የገለጠባትን ሰንበተ ክርስቲያንን እንቀድሳታለን። የምንቀድሳትም እርሱ እንዳስተማረን ከሌሎቹ ዕለታት በተለየ መልኩ የአምልኮና የቅድስና ሥራን በመፈጸም ራሳችንን በመቀደስ ነው። ማር 2:27 ሉቃ 6:1-11 ሉቃ 13:11-17 ዮሐ 5:1-18

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚኖረው ተፈጻሚነት: ሰንበትን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አታሳልፍ – በሰንበት ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ማመስገን፣ መባረክ፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል፣ ቃሉን መማርና ሌሎችንም የቅድስና ሥራዎች መሥራት ይገባሀል። በዚህች ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መጠመድ ሰንበትን በሚገባህ መንገድ እንዳታከብር ሊያደርግህ። በሰንበት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አትለጥፍ – በሰንበት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጽሑፎችንና ቪዲዮችን ማጋራት ሌሎች ወንድሞቻችና እህቶቻችን ሰንበትን በሚገባው መንገድ እንዳይቀድሷትና እንዳይቀደሱባት ሊያደርጋቸው ስለሚችል የማኅበራዊ ሚዲያ ውሎህ ከዚህ አኳያ ለሌሎች በማሰብ ሊሆን ይገባል። ማኅበራዊ ሚዲያ በሚያሳድርብህ ተጽዕኖ ምክንያት ሰንበትን ለሥራ አታውላት – በሥራ ሰዓት ማኅበራዊ ሚዲያን መመልከት በሳምንቱ መጨረሻ የሥራ ጫና ፈጥሮብህ ሰንበትን በሥራ እንድታሳልፍ ሊያስገድድህ ይችላል። በተቀደሰችው በሰንበት ዕለት ለኃጢአት የሚጋብዝ ይዘት ያላቸውን ነገሮች አትመልከት – በዚህች ዕለት ማኅበራዊ ሚዲያን scroll ማድረግ ብዙ የሚረብሹ፣ አዕምሯችንን ለኃጢአት ሀሳብ የሚጋብዙና የዕረፍት ቀናችንን የሚያበላሹ ነገሮችን እንድትመለከት ያደርግሀል። በሰንበት ማኅበራዊ ሚዲያን መጠቀም ካለብህ ለመንፈሳዊ ጉዳይ ብቻ ይሁን – ምናልባት አንዳንዶች በሰንበት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መልካም ነገርን መሥራት ይቻላል ብለው ሊሞግቱህ ይችላሉ። እውነት ነው አስቀድሞ የታቀደ፣ የተወሰነና የተመጠነ ሥራን መሥራት አያስነቅፍም።

4. አባትህንና እናትህን አክብር። ዘጸ 20፡12 ዘዳ 5፡16

ይህ ትዕዛዝ አባትና እናትን እንዲሁም ሌሎች ሰዎችን ሁሉ ማክበር እንዲሚገባን ያዛል። ለዚህ ትዕዛዝ በተለይ “እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም” የሚል ቃል ተከትሎታል (ዘጸ 20:12)። እኛ የወላጆቻችን የነፍስና የሥጋ ክፋይ ስለሆንንና ማኅበራዊ ማንነታችንም የተቀረፀው በእነርሱ ስለሆነ እነርሱን ማክበር መንፈሳዊም ሰብአዊም ግዴታችን ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሰውን ማክበር የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ከምንገልጥባቸው ምግባራት አንዱ ነው። እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰውን አክብሮ በምሳሌው ፈጠረው፣ በፍጥረታት ላይ ሁሉ ገዢ አደረገው (ዘፍ 1:26-27)። ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። (መዝ 139:14) እንዳለው የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ድንቅ ፍጥረት ነው። ጌታችንም የባሕርይ አባቱን አብን እና እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምን አክብሮ ይህንን ትዕዛዝ እንድንፈጽም አርአያ ሆኖናል። ቅዱስ ጳውሎስም “ስለዚህ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እንደ ተቀበላችሁ እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ። (ሮሜ 15:7)” በማለት ክርስቶስ እንዳከበረን እርስ በእርሳችን ልንከባበር እንደሚገባ አስተምሯል። እንዲሁም “እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው። (ኤፌ 6:4)” በማለት መክሮናል። ጠቢቡ ሰሎሞንም “ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ምክር ስማ፥ የእናንትህንም ሕግ አትተው፤ ለራስህ የሞገስ ዘውድ ለአንገትህም ድሪ ይሆንልሃልና። (ምሳሌ 1:8-9)” በማለት ስለዚህ ትዕዛዝ ተናግሯል። ከዚህ በተጨማሪ ሌላውን ሰው ማክበር የስልጣኔ መገለጫም መሆኑን ልናስተውል ይገባል። ሌላውን ስናከብር ራሳችንም እንከበራለንና።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚኖረው ተፈጻሚነት: በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በአባቶችና በእናቶች ላይ አትቀልድ፣ አትሳለቅ – የአባትና እናቶቻችን እምነት፣ ቁመና፣ አኗኗርና የመሳሰሉት ላይ የሚቀልድ፣ የሚሳለቅ ይዘት ያለውን መለጠፍ ወይም ማጋራት፣ ወይም የወላጆችን ሚና የሚያሳንስ ነገር አትናገር፣ አትጻፍ። የአባትህና የእናትህን ግላዊ ጉዳይ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አታውጣ – ከወላጆችህ ጋር ያለህን ግላዊና ቤተሰባዊ ጉዳይ የእነርሱን ክብር በሚነካ መልኩ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አታውጣ። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወላጆችን እሴቶች አክብር – የወላጆችህን ማኅበራዊ ዕሴቶች ጋር የሚቃረኑ ነገሮችን ወይም እነርሱ የሚቃወሟቸውን ነገሮች አትለጥፍ። ከወላጆችህ የተደበቀ የማኅበራዊ ሚድያ ሕይወት አይኑርህ – በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያለህን ጠባይ ከወላጆችህ አትደብቅ። ወላጆችህን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አትተች – ስለ ወላጆችህ የተሳሳቱ ወይም የተጋነኑ ታሪኮችን አታጋራ፣ የራስህን ድክመት በወላጆችህ ላይ በማላከክ እነርሱን በማኅበራዊ ሚዲያ አትውቀስ። ወላጆችህ ይልቅ ማኅበራዊ ሚዲያን አታስቀድም – ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በመጠመድ ለወላጆችህ ማድረግ ያለብህን ሳታደርግ፣ መስጠት ያለብህን ትኩረት ሳትሰጥ እንዳትቀር ተጠንቀቅ። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የመንፈስ አባቶች ካህናትንም አክብር – የመንፈስ ቅዱስ አባቶችህን የማያከብር ወይም ስም የሚያጠፋ ነገር አትናገር፣ አትጻፍ፣ አታጋራ።

5. አትግደል። ዘጸ 20፡13 ዘዳ 5፡17

አትግደል የሚለው ትዕዛዝ የራስንም ይሁን የሌላ ሰው ነፍስን ማጥፋትን ይከለክላል። ጌታችን በወንጌሉ ይህንን ትዕዛዝ ፍጹም ሲያደርገው “ለቀደሙት። አትግደል እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል። (ማቴ 5:21-22)” በማለት ማንኛውንም በሰው ላይ መቆጣት፣ መሳደብና ሌሎች ሰውን ከሚጎዱ ነገሮችን ሁሉ እንድንከለከል ሕገ ወንጌልን አጽንቶልናል። ሰዎች ክፉ ነገር ቢያደርጉብን እንኳን “ጌታችን ክፉውን በክፉ አትቃወሙ (ማቴ 5:39)” ብሎ እንዳስተማረን መልካምን በማድረግ የክፋትን ዑደት ማስቆም ይገባናል። እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ምን ያህል አክብሮ እንደፈጠረው፣ ቢበድለውም አንድያ ልጁን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ እንደወደደው የሚያውቅ ክርስቲያን የሰውን ልጅ ሁሉ መውደድ ነው ያለበት። ከዚህ በተቃራኒ ሰውን የሚጎዳ ሀሳብ ማሰብ፣ ሰውን የሚጎዳ ቃልን መናገር፣ ሰውን የሚጎዳ ድርጊትን መፈጸም ወይም ሌሎች ሰውን የሚጎዳ ነገር እንዲያስቡ፣ እንዲናገሩና እንዲፈጽሙ ማድረግ ይህንን ትዕዛዝ መተላለፍ ነው። ጉዳትም ሲባል አካላዊ (Physical)፣ ስነ-ልቦናዊ (Psychological)፣ አዕምሮአዊ (mental)፣ ስሜታዊ (emotional) እና ማኅበራዊ (Social) ጉዳቶችን ሁሉ ያካትታል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚኖረው ተፈጻሚነት: በማኅበራዊ ሚዲያ በሰዎች ላይ ጥቃት አትፈጽም (ጥቃት እንዲፈጸምባቸው የሚያደርግ መረጃ አታቅርብ) – አንድን ሰው ዒላማ ያደረገ ስድብ፣ ማስፈራሪያና ዛቻ፣ የሰውን ክብር የሚነካ፣ ስም የሚያጠፋ፣ ምግባርን የሚያጎድፍ፣ ማኅበራዊ ተቀባይነትን የሚጎዳ መረጃን በማኅበራዊ ሚዲያ አታሰራጭ። ማንኛውንም የጥላቻ ይዘት ያለውን ነገር በማኅበራዊ ሚዲያ አትለጥፍ፣ አትውደድ፣ አታጋራ – ሰውን ከሰው፣ ማኅበረሰብን ከማኅበረሰብ የሚያጣላና የሚያጋጭ ጽሑፍን፣ ፎቶን ወይም ቪዲዮን፤ ሰውን በብሔሩ፣ በሃይማኖቱ፣ በጾታው ወይም በአመለካከቱ የሚያንቋሽሹ ወይም የሚያሳንሱ ነገሮችን አትለጥፍ፣ አታጋራ፣ አትውደድ። በተቻለህ መጠን እንዲህ ዓይነት ይዘት ያለው ነገር ከማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ይወገድ ዘንድ ሪፖርት አድርግ። ማንኛውንም አይነት ሰዎች ራሳቸውን እንዲጎዱ የሚገፋፋ ነገር አትለጥፍ፣ አታጋራ – ሰው ራሱን እንዲጎዳ ወይም ራሱን እንዲያጠፋ የሚያነሳሱ ወይም የሚገፋፉ ነገሮችን አትለጥፍ፣ አታጋራ፣ አትውደድ። ሰው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ራሱን የመጉዳት አዝማሚያ ሲያሳይ አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ ዝም ብለህ አትለፍ።

ማንኛውንም የሰውን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ነገር አትለጥፍ፣ አታጋራ – በሰዎች ላይ ፍርሃትንና መረበሽን የሚያስከትል ሐሰተኛ ወይም ያልተረጋገጠ መረጃን ወይም የሰውን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል የጤና ምክር (ለምሳሌ ውጤታማነቱ ያልተረጋገጠ መድኃኒትን መረጃ በማጋራት፣ መድኃኒት መውሰድ እንዲያቋርጡ የሚያደርግ) በማኅበራዊ ሚደያ ላይ አታቅርብ። ግጭትን የሚያባብስ መረጃ አታቅርብ፣ አታጋራ – ግጭትን ወይም መገዳደልን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ወይም ፎቶዎችን መለጠፍ፣ በቀጥታ ጽሑፍ ወይም በኮመንት መገዳደልን እንደ ጀግንነት ማወድስ፣ አንደኛውን ወገን በድርጊቱ እንዲገፋበት ማበረታታት ወይም ድጋፍ መስጠት እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በቀልን የሚደግፍ ወይም የሚያበረታታ ነገርን ማቅረብ አትግደል የሚለውን ሕግ መተላለፍ ነው። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሰውን ስሜት አትጉዳ – የሰዎችን ጉዳት ወይም ሐዘን እንደተራ ነገር መቁጠር፣ በሰው ጉዳትና ሐዘንም መሳለቅ፣ ለተናገርነውም ሰውን የሚጎዳ ነገር ኃላፊነት አለመውሰድ አትግደል የሚለውን ሕግ መተላለፍ ነው።

6. አታመንዝር። ዘጸ 20፡14 ዘዳ 5፡18

ይህ ትዕዛዝ ዝሙትን ይከለክላል፣ ለተቀደሰው ትዳር መታመንን ይደነግጋል። ዝሙት የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ በተባለ ሰውነት ላይ የሚፈጸም የርኩሰት ኃጢአት ነው። ዝሙት እግዚአብሔር አስቀድሞ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጥሮ የመሠረተውን ተቋም (ቤተሰብ) የሚያፈርስ ኃጠአት ነው። ጌታችንም “አታመንዝር እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል። (ማቴ 5:27-28)” በማለት ሕጉን ፍጹም አድርጎታል። በዚህም ማንኛዋንም ሴት (ያገባችም ያላገባችም) በዝሙት ሀሳብ ማየት፣ ለዝሙትም መመኘት ይህን ሕግ መተላለፍ ነው። ሐዋርያው ያዕቆብ “ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች (ያዕ 1:15)” እንዳለው ዓይቶ መመኘት ኃጠአት ነው። ቅዱስ ጴጥሮስም ስለዚህ “ምንዝር የሞላባቸው ኃጢአትንም የማይተዉ ዓይኖች አሉአቸው፤ የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፤ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው። (2ኛ ጴጥ 2:14)” በማለት የምኞት ኃጠአትን ገልጾታል። በተጨማሪም ጌታችን “ሚስቱን የሚፈታት ሁሉ የፍችዋን ጽሕፈት ይስጣት ተባለ። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል። (ማቴ 5:31-32)” በማለት ይህንን ትዕዛዝ ፍጹም አድርጎታል። ቅዱስ ጳውሎስም “አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ … የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።(1ኛ ቆሮ 6:9-10)” ብሏል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚኖረው ተፈጻሚነት: በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሰው ይህንን ትዕዛዝ በስሜታዊ አለመታመን (emotional infidelity)፣ ተገቢ ባልሆኑ ግንኙነቶችና ትዳርን በሚጎዱ ጠባዮች ሊተላለፍ ይችላል፣ ወይም ትዳሩን ሊጎዳ ይችላል። ስለዚህ በማኅበራዊ ሚዲያ ያልተገባ ጾታዊ ግንኙነትን(virtual affair) አትፍጠር – በማኅበራዊ ሚድያ ከሌላ ሰው ጋር መልእክት በተደጋጋሚ በመላላክ፣ በኮመንት በመደናነቅ፣ ፎቶና ቪዲዮ በመለዋወጥ ወይም በድምጽ በማውራት ትዳርን ወይም እጮኝነትን የሚጎዳ የማኅበራዊ ሚዲያ ግንኙነት ከሌላ ሰው ጋር አትፍጠር። የተጋለጠ ጾታዊ ይዘት ያላቸውን ፎቶዎችን/ቪዲዮችን አትመልከት፣ አታጋራ – ልቅ የሆኑ ፎቶዎችን ከማየት፣ ቪዲዮዎችን ከመመልከት፣ ጽሑፎችን ከማንበብ እንዲሁም ለሌሎች ከማጋራት ተቆጠብ። ግላዊ የሰውነት ክፍሎችን የሚያሳዩ፣ ወይም ልቅ የሆነ ጾታዊ ግንኙነቶችን የሚያሳዮ ነገሮችን ደጋግሞ ከመመልከት፣ ላይክ ከማድረግ፣ አስተያየት ከመስጠት ተቆጠብ። ከትዳር አጋርህ የተደበቀ የማኅበራዊ ሚዲያ ሕይወት አይኑርህ – በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የምትለዋወጣቸውን መልእክቶች ወይም የምትለጥፋቸውን ነገሮች ከትዳር አጋርህ አትደብቅ (በማጥፋት ወይም ሌላ አካውንት በመጠቀም ሊሆን ይችላል)። ይህ ሲታወቅ ጥርጣሬን በመፍጠር ትዳርህን ያፈርሳልና።

ከትዳር/እጮኝነት ውጭ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የምታያቸውን ሰዎች ለጾታዊ ግንኙነት አትመኝ – የሌሎች ሰዎችን ፎቶዎች ወይም ተክለሰውነት ወይም ውበት በአስተያየት ‘እንዴት ቆንጆ ነሽ፣ እንዴት ታምሪያለሽ፣ የኔ ቆንጆ፣ የኔ ሸበላ ወዘተ’ በማለት ከማድነቅና የፍቅር (የልብ ምልክት) ከመጠቀም ተቆጠብ። አመንዝራነትን የሚያበረታታ ይዘት ያለው ነገር አትውደድ፣ አታጋራ – ከትዳር በፊት ወይም ከትዳር ውጭ የሚደረጉ ግንኙነቶችን የሚያበረታታ ይዘት ያላቸውን ነገሮች አትውደድ ወይም አታጋራ። በአመንዝራነት ምክንያት ትዳር ሲፈርስ እንደተለመደና እንደተራ ነገር አትቁጠር፣ እንደዚህ ዓይነት አንድምታ ያለውን ነገርም አታጋራ። ከብዙ ሰው ጋር ጾታዊ ግንኙነት የሚያደርጉ ሰዎችን የሚያወድስን መረጃ አትውደድ ወይም አታጋራ። ማኅበራዊ ሚዲያን ከትዳር ውጣ ውረዶች ማምለጫ አታድርግ – በትዳርህ ውስጥ ፈተና ሲያጋጥም ከትዳር አጋርህ ጋር ተነጋግሮ ከመፍታት ይልቅ የትዳር አጋርህን ወደ ጎን ትተህ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያለን ሰው ለማማከር ወይም አስተያየትና ድጋፍ ለማግኘት፣ ወይም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ብዙ ጊዜ በማሳለፍ የትዳር አጋርን ፍላጎቶች ለመርሳት አትሞክር።

7. አትስረቅ። ዘጸ 20፡15 ዘዳ 5፡19

ይህ ትዕዛዝ የራስ ያልሆነውን ማንኛውንም ነገር መውሰድን ይከለክላል። ቅዱስ ጳውሎስ በግልጽ “ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም (1ኛ ቆሮ 6:10)” በማለት መስረቅ ታላቅ ኃጢአት መሆኑን ተናግሯል። ሰዎች በዚህ ምድር ላይ ሲኖሩ ሠርተው ያፈሩትን ማንኛውንም ዓይነት ንብረት መስረቅ የሌሎች ሰዎችን መብትንና የግል ንብረትን አለማክበር ነው። መስረቅ ያልሠሩትን ያልደከሙበትን ይልቁንም ሌላ ሰው የደከመበትን መውሰድ ነው። ስድስት ቀን ሥራ ለተባለ ክርስቲያን እግዚአብሔር የሰጠውን ከመስጠት ይልቅ የሌሎችን ንብረት ወደ መስረቅ ከሄደ ታላቅ የመንፈሳዊነትና የሞራል ውድቀት ላይ ነው ማለት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ “የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፥ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም። (ኤፌ 4:28)” ያለው ይህንን የሚመለከት ነው። ጌታችንም ሌባ ሊሰርቅ የሚመጣው በሌሊት እንደሆነ በመግለጽ ሌብነት የጨለማ ሥራ መሆኑን አስተምሯል (ማቴ 24:43)። አትስረቅ የሚለው ሕገ እግዚአብሔር በምድር ላይ ላሉ የግል የንብረት ባለቤትነት ሕጎች ሁሉ መሠረት ነው። ስለዚህም በማንኛውም ምድራዊ ሕግ መስረቅ ወንጀልም ጭምር ነው።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚኖረው ተፈጻሚነት: በማህበራዊ አውታረ መረቦች ውስጥ መስረቅ በአካላዊ ነገሮች ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም፣ ወደ አእምሯዊ ንብረት፣ እምነት እና ታማኝነት ይዘልቃል። በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመን ይህን ትዕዛዝ በሚከተሉት መንገዶች ልንተላለፍ እንችላለን። የአእምሮአዊ ንብረት አትስረቅ – የሌላ ሰውን ጽሑፎች፣ ፎቶዎች ወይም ቪዲዮዎች ምንጭ ሳትጠቅስ ወይም ፍቃድ ሳታገኝ አትጠቀም። በቅጂ መብት የተያዘውን ሙዚቃ፣ ምስሎችን ወይም ሌላ ሚዲያን በልጥፎች ወይም ቪዲዮዎች አትጠቀም። በሰዎች ሥራ የባለቤትነት መብትን አትጠይቅ። ትኩረትን፣ ተከታዮችን ወይም ትርፍ ለማግኘት ብለህ የሌላ ሰውን ሥራ እንደራስህ አድርገህ አታቅርብ። የሰዎችን ግላዊነት (privacy) አትጣስ – የሰውን የግል መረጃ (ለምሳሌ አድራሻ፣ ስልክ ቁጥር ወይም የግል መልዕክቶች) ያለፈቃድ አታጋራ፡፡ በህገ፡ወጥ መንገድ የሌላ ሰውን የማኅበራዊ ሚዲያ መለያ ለማግኘት ወይም ግላዊ መረጃቸውን ተጠቅመህ የራስህን መረጃ ለመለጠፍ አታስብ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ገንዘብ የማጭበርበር ድርጊት አትፈጽም – በማኅበራዊ ሚድያ ላይ የሐሰት የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻዎችን በማድረግ፣ ትክክለኛ ያልሆኑ ማስታወቂያዎችን በማስተላለፍ ወይም የሐሰት ምርቶችን ወይም አገልግሎቶችን በመሸጥ ገንዘብ ለማግኘት አትሞክር። የሰዎችን ሀሳብ አትስረቅ – ለሰዎች ሀሳብ ወይም አስተዋጽኦ እውቅና ስጥ፣ የሰውን ሀሳብ ወይም የፈጠራ ውጤት ተገቢው እውቅና ሳትሰጥ አትጠቀም። የመረጃዎችንና የማስረጃዎችን ይዘት አታዛባ – ጥልቅ ሐሰተኛ (deep fake) እና የተስተካከሉ ቪዲዮዎችን ወይም ምስሎችን (doctored) ወይም የሐሰት ትርክቶችን አታሰራጭ። ትኩረትን ለመሳብ ብለህ የሐሰት ወይም የተሰረቁ አርዕስተ ዜናዎችን ወይም ምስሎችን አትጠቀም። የሐሰት መለያዎችን በመጠቀም ተከታይ አታፍራ – ምንጩን ሳትጠቅስ የሰውን የሥራ ውጤት በመጠቀም ለመደነቅ፣ ተከታይ ለማብዛት ወይም ገቢን ለማሳደግ አትሞከር፣ የሐሰት መለያዎችን በመጠቀም ወይም በማስመሰል ተከታዮችን ለማፍራት አትሞክር። ጊዜን አትስረቅ – የሥራ ሰዓትህን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አታባክን፣ ሰዎችም የሥራ ሰዓታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ እንዲያባክኑ ምክንያት አትሁን።

8. በሐሰት አትመስክር። ዘጸ 20፡16 ዘዳ 5፡20

ይህ ትዕዛዝ ማንኛውንም አይነት ሐሰት (ውሸት) መናገርን ይከለክላል። መጽሐፍ “እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፤ የታመነ አምላክ፥ ክፋትም የሌለበት፥ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው (32:4)” እንዳለ እግዚአብሔር እውነት፣እውነተኛ ነው። ጌታችንም ያመኑትን አይሁድ “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል አላቸው (ዮሐ 8:32) በማለት እንዲሁም “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም (ዮሐ 14:6)” በማለት እውነት መሆኑን ተናግሯል። አይሁድን ግን “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና (ዮሐ 8:44)” በማለት ሐሰት መናገር ከዲያብሎስ ጋር መተባበር መሆኑን ጭምር አስተምሯል። ጠቢቡ ሰሎሞንም “እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች…በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ። (ምሳ 6:16-19) ብሏል። በተጨማሪም “ውሸተኛ ከንፈር በእግዚአብሔር ዘንድ አሰጸያፊ ነው፤ እውነትን የሚያደርጉ ግን በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው (ምሳ 12:22)” በማለት ሐሰት የመናገርን መጥፎነት ተናግሯል። ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ “… የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው (ራዕ 21:8) ውሻዎችና አስማተኞች ሴሰኛዎችም ነፍሰ ገዳዮችም ጣዖትንም የሚያመልኩት ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ (ራዕ 22:15)” ሐሰት መናገር የሚያደርሰውን ዘላለማዊ ቅጣት ተናግሯል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚኖረው ተፈጻሚነት: በማኅበራዊ ሚዲያ የሐሰት መረጃን አታሰራጭ – ያልተረጋገጡ ወይም የውሸት ዜናዎችን፣ አሉባልታዎችን ወይም የሴራ ፅንሰ ሀሳቦችን አትለጥፍ። ትኩረትን ለመሳብ ብለህ ስሜት ቀስቃሽ ወይም አሳሳች አርዕስተ ዜናዎችን አታጋራ። በማኅበራዊ ሚዲያ የሰውን ስም አታጥፋ – ስለ ሰው የሐሰት ውንጀላ አታቅርብ፣ ሐሜትን አታሰራጭ፡፡ እውነትን ሳታረጋግጥ ስለሌሎች ወሬ ከመለጠፍ ወይም ከማጋራት ተቆጠብ። የራስህን ወይም የሌሎችን መረጃ አታዛባ– የውሸት አካውንት በመፍጠር ሌሎችን ሌላ ሰው መስለህ ለማታለል አትሞክር። የተለየ አርትዖትን፣የተቀነባበሩ ፎቶዎችን፣ ቪዲዮዎችን ወይም ጥቅሶችን በመጠቀም ሌሎችን በሐሰት ለመሳል ወይም ለማሳየት አትሞክር። ለግል ጥቅም ብለህ አትዋሽ – የፈጠራ ታሪኮችን በማጋራት ትኩረትን ወይም አድናቆትን ለማግኘት፣ ሐሰተኛ መረጃን በመጠቀም ሀብት ለማግኘት አትሞክር። ውሸትን አታበረታታ፣ አታጉላ – እውነት እንዳልሆኑ የምታውቃቸውን ልጥፎችን በመውደድ፣ በማጋራት ወይም አስተያየት በመስጠት ለሐሰት መስፋፋት አስተዋፅዖ አታድርግ። በማንም ሰው ላይ ሐሰተኛ መረጃን አትጠቀም – በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የአንድን ሰው ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት ወይም ለመውንጀል ብለህ የሐሰት መረጃዎችን አትጠቀም። ሐሰተኛ መረጃን ከማረም ቸል አትበል – የተሳሳተ መረጃ ስታይ በዝምታ አትለፍ፣ ቢያንስ የተሳሳተ መሆኑን አሳውቅ።

9. የባልንጀራህን ቤት አትመኝ። ዘጸ 20፡17 ዘዳ 5፡21

ይህ ትዕዛዝ የራስ ያልሆነ ማንኛውንም ነገር ሁሉ መመኘትን ይከለክላል። በዚህም የውስጥ በልብ/ሀሳብና ፍላጎት ላይ የሚያተኩር ትዕዛዝ ነው። ትዕዛዙም “የባልንጀራህን (የሌላን ሰው) ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ሎሌውንም ገረዱንም በሬውንም አህያውንም ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ። (ዘጸ 20:17)” ይላል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል። (2ኛ ጢሞ 2:17)” ብሎ እንዳስተማረው የዝሙት መነሻው ክፉ ምኞት ነው። የስርቆትም መነሻው የራስ ያልሆነን ነገር መመኘት ነው። የመግደልም መነሻው በቀልን መፈለግ ነው። ስለዚህ ይህ ትዕዛዝ በሥራ ለሚገለጥ ኃጠአት ሁሉ መነሻ ነው። ለሁላችን የሚያስፈልገንን ሁሉ የሚሰጠን አምላክ እያለ እኛም ከተሰጠን ለሌላው መስጠት ሲገባን የእኛ ያልሆነውን መመኘት ስግብግብነት ነው። እንዲህ ያለው ፍላጎት ደግሞ ማብቂያ ስለሌለው ከእግዚአብሔር የሚለይ ኃጢአት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው(1ኛ ጢሞ 6:6)” በማለት ለልጁ ጢሞቴዎስ ያስተማረው፣ ቅዱስ ጴጥሮስም “በመጠን ኑሩ” (1ኛ ጴጥ 5:8) ሲል የተናገረን ከዚህ ማብቂያ ከሌለው የሰው ልጅ ፍላጎት ጋር ከተያያዘው የምኞት ኃጢአት እንድንጠበቅ ነው።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚኖረው ተፈጻሚነት: በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በምትመለከተው የሌሎች ሰዎች ሕይወት አትቅና።: ባልንጀሮችህ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሚያጋሯቸው የቁሳዊ ነገሮች ፎቶዎችና ቪዲዮዎች እየተመለከትህ አትጎምዥ። ባልንጀሮችህ ስኬቶቻቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያካፍሉ አድናቆትን ሲያገኙ ስታይ አትበሳጭ፣ በስውርም አትተች። የራስህን መልክ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከምታየው የሌሎች መልክ ወይም ውበት እያነጻጸርክ በእነርሱ መልክ ወይም ውበት አትቅና። ባልንጀሮችህ የሚጎበኟቸውን ቦታዎች፣ የሚያገኟቸውን ሰዎች፣ የሚሳተፉባቸውን ስብሰባዎች ወይም የሚያገኟቸውን ሽልማቶች አይተህ አትቅና። ራስህን መስለህ ኑር እንጂ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የምትመለከተውን የሌሎችን ስኬት በመኮረጅ ወይም በመድገም አድናቆትን ለማግኘት አትሞክር። ባልንጀሮችህ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያላቸውን የተከታይ ብዛት ወይም የሚያገኙትን አድናቆት፣ዝናና ታዋቂነት በመመልከት ራስህን ከእነርሱ ጋር በማነጻጸር የባዶነት ስጋት ውስጥ አትግባ።

10. ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ። ዘሌ 19:18

ይህ ጌታችን ከተናገራቸው ዋነኛ ትዕዛዛት ሁለተኛው ነው (ማቴ 22:39)። በሰዎች መካከል ያለውን መስተጋብር የሚመለከቱ ትዕዛዛት ሁሉ በዚህች በሁለተኛይቱ ዋነኛ ትዕዛዝ ይጠቃለላሉ። ባልንጀራ የሚባለውም ማንኛውም ሰው ነው። ለዚህም ነው ጌታችን “ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ (ማቴ 5:43-48)” በማለት ያስተማረው። “እንደራስህ ውደድ” ያለውም ራሳችንን በምንወደው ልክ እንድንወድ፣ ለእኛ ይደረግልን ዘንድ የምንወደውን ሁሉ ለሌሎችም እንድናደርግ ነው (ማቴ 7:12)።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚኖረው ተፈጻሚነት: ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የምትጽፈውን/የምትለጥፈውን የሚመለከት ሰው ሁሉ ባልንጀራህ ነውና ማኅበራዊ ሚዲያን በኃላፊነትና በፍቅር (ለሌላው ሰውም በማሰብ) ተጠቀም። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማንኛውንም ዓይነት አንተን ወይም ባልንጀራህን የሚጎዳ ነገር ከመመልከት፣ ከመለጠፍ፣ ከማጋራት ተቆጠብ። ከተቻለህ የባልንጀራህን እና የራስህን መንፈሳዊ ሕይወት የሚያንጽ ነገር ብቻ አተኩር። እውነትነቱ ያልተረጋገጠ ወይም ሐሰት መረጃን አትለጥፍ፣ አታጋራ። ባልንጀራህ ቢበድልህ ጉዳዩን ከእርሱ ጋር ፍታው እንጂ ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ አታምጣ። ባልንጀራህን ቢያጠፋ ለብቻው ምከረው እንጂ ጥፋቱን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አታውራ። ጊዜህን በታቀደና በተመጠነ ሁኔታ ብቻ ማኅበራዊ ሚዲያን ተጠቀም። ሰዎችንና ግላዊነታቸውን አክብር። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ራስህን ሆነህ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር። ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጥቃት ቢያደርሱብህ እንኳን ለእግዚአብሔር ሰጥተህ እለፍ እንጂ ክፉውን በክፉ አትመልስ። በተጨማሪም ሰውን የሚጎዳ ነገር ሲያጋጥምህ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት አድርግ እንጂ በዝምታ አትለፍ። እንዲህ በማድረግህ ለማኅበራዊ ሚዲያ ሰላም የራስህን አስተዋጽኦ ታበረክታለህ።

መደምደሚያ

ቀደምት ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ቅዱሳት መጻሕፍትን በየአውዱ በማብራራት በየዘመኑ ለሚነሱ ጥያቄዎች የተደራጀ የአንድምታ ትንተና በመስጠት ይታወቃሉ። ማኅበራዊ ሚዲያ የዘመናችን ተጽዕኖ ፈጣሪ የቴክኖሎጂ ውጤት በመሆኑ የምዕመናንን ግላዊ መንፈሳዊ ሕይወትም ሆነ በልዩ ልዩ ማኀበራት ያላቸውንና የሚኖራቸውን ሱታፌ በገሀዱ ዓለም ካለው የአሠርቱ ትዕዛዛት አረዳድና አፈጻጸም ጋር በማገናዘብ መረዳትና መተንተን የዘመናችን ሊቃውንት ትኩረት ሊሆን ይገባል ብለን እናምናለን። በዚህች የአስተምህሮ ጦማር ከማኀበራዊ ሚዲያ አንጻር የተተነተኑትን ሕግጋተ እግዚአብሔር ከእያንዳንዳችን የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም አንጻር ስንመረምረው ድካማችንና አለመታዘዛችን ይገለጥልናል። አቤቱ እንደ ቸርነትህ ማረን።