አንቀጸ ብፁዓን ፪- እውነተኛ ንስሐ: የሚያዝኑ (የሚያለቅሱ) ብፁዓን ናቸው።

የሚያዝኑ (የሚያለቅሱ) ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና። ማቴ 5:4 ሉቃ 6:21

የክርስትና ሕይወት የሐዘንና የለቅሶ ሕይወት ነውን? ደስታስ ኃጢአት ነውን? በፍጹም! ደስታ ኃጢአት አይደለም።. እንዲያውም  መጽሐፍ ቅዱስ ደስታን እንደ መንፈስ ፍሬ ይቆጥረዋል(ገላ 5፡22)። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ  “ነገር ግን እንደ ገና አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል፥ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም(ዮሐ. 16:22)” በማለት ስለመንፈሳዊ ደስታ አስተምሯቸዋል።  ሐዋርያው ​​ቅዱስ ጳውሎስም ስለዘላለማዊ ደስታ “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ (ፊልጵ 4፡4)” ብሏል። ጌታችንም በሰማያት ስለሚኖረው ደስታ ሲናገር “ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል” (ሉቃ 15:7) ብሏል። ሌላው መንፈሳዊ ደስታ ሌሎች ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ሲያድጉ ማየት ነው። ስለዚህም ደስታ ወንጌላዊው ዮሐንስ “ወንድሞች መጥተው አንተ በእውነት እንደምትሄድ ስለ እውነትህ ሲመሰክሩ እጅግ ደስ ብሎኛልና። ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም (3ኛ ዮሐ 2-4)” ብሏል።

ጌታችን ‘የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው’ ብሎ ያስተማረው ትምህርት ሥጋዊ ሐዘንን የሚመለከት አይደለም፣ መንፈሳዊውን እንጂ። ሥጋዊ ሐዘን እናት አባት፣ ወንድም እኅት ወይም ዘመድ ወይም ጓደኛ፣ ልጅ ወይም የትዳር አጋር የለኝም፣ ሞተብኝ፣ ተለየኝ ተብሎ ወይም ያሰቡት የለፉበት ነገር ሲጠፋ ወይም ሳይሳካ ሲቀር የሚታዘነው ሐዘን ነው። መንፈሳዊ ሐዘን ሰው ስለ በደሉና ኅጢአቱ፣ ስለሌሎች በደልና ኃጢአት፣ እንዲሁም የወልደ እግዚአብሔርን ሕማማቱን እያሰበ የሚያዝነው ሐዘን ነው። ይህም ሐዘን ብቻ ሳይሆን ወደ ንስሐ የሚያደርስ መፀፀት ነው። ሰው በምድር ላይ ሲኖር ስለኃጢአቱ በማዘንና በማልቀስ ወደ ንስሐ መድረስ አለበት። ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ”እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፥ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል (2ኛ ቆሮ 7:10)” በማለት ያስተማረው።

ጌታችን መስቀል ተሸክሞ ወደ ቀራኒዮ ሲወስዱት ያለቅሱለት ለነበሩት ሴቶች “እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች፥ ለእኔስ አታልቅሱልኝ፤ ዳሩ ግን መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች ያላጠቡ ጡቶችም ብፁዓን ናቸው የሚሉበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ (ሉቃ 23:28-29)” በማለት ነው ለራሳችን እንድናለቅስ የነገረን። ከሚያዝኑና ከሚያለቅሱ ጋርም አብረን እናለቅስ ዘንድ “ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ” የሚል ሐዋርያዊ መልእክት ተጽፎልናል (ሮሜ 12:15)። ሐዋርያው ያዕቆብም “እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ። ተጨነቁና እዘኑ አልቅሱም፤ ሳቃችሁ ወደ ኀዘን ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ። በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል (ያዕ 4:8-9)” በማለት ስለኃጢአታችን እንድናለቅስ አስተምሮናል። እንዲሁም “አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች፥ ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ (ያዕ 5:1)” በማለት በዕንባችን ከቅጣት ፍርድ እንድንድን አስተምሮናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ ብዙ ቅዱሳን ነቢያት፣ ሐዋርያት እንዲሁም ሌሎች ቅዱሳን ስለሕዝቡ፣ ስለ ነገሥታቱና ስለራሳቸውም ጭምር ብዙ አዝነዋል፣ አልቅሰዋልም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ስለሰው ልጆች አልቅሷል። ለምሳሌነት ያህል የሚከተሉት ተዳስሰዋል።

ነቢዩ ሳሙኤል: ንጉሥ ሳኦል እግዚአብሔር ያዘዘውን ባለመፈጸሙ እግዚአብሔር አዝኖበት ነበር። በዚህም የተነሳ የእግዚአብሔር ቃል “ሳኦል እኔን ከመከተል ተመልሶአልና፥ ትእዛዜንም አልፈጸመምና ስላነገሥሁት ተጸጸትሁ” ሲል ወደ ሳሙኤል መጣ። ሳሙኤልም ተቈጣ፤ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ (1ኛ ሳሙ 15:11)። ሳሙኤልም ወደ ሳኦል ሄዶ “በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል፤ ዓመፀኝነት እንደ ምዋርተኛ ኃጢአት፥ እልከኝነትም ጣዖትንና ተራፊምን እንደ ማምለክ ነው፤ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና እግዚአብሔር ንጉሥ እንዳትሆን ናቀህ (1ኛ ሳሙ 15:223)” በማለት ገሰፀው። ንጉሥ ሳኦልም ከልቡ ተጸጽቶ ባለመመለሱ “ሳሙኤልም እስከ ሞተበት ቀን ድረስ ሳኦልን ለማየት ዳግመኛ አልሄደም፥ ሳሙኤልም ለሳኦል አለቀሰ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ሳኦልን ስላነገሠ ተጸጸተ (1ኛ ሳሙ 15÷35)” በማለት መጽሐፍ ይነግረናል። በመጨረሻም እግዚአብሔር ሳሙኤልን “በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? በቀንድህ ዘይቱን ሞልተህ ሂድ፤ በልጆቹ መካከል ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተ ልሔም እልክሃለሁ” አለው። በዚህም ንግሥና ከሳኦል ተወሰደች፣ ለእሴይ ልጅ ለዳዊትም ተሰጠች።

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት: ክቡር ዳዊት ስለበደለው በደል፣ ስለደረሰበት ሐዘን፣ እንዲሁም ስለ እግዚአብሔር ምህረት አልቅሷል። ሳኦል ያሳድደው የነበረው ዳዊት አሳዳጁ ሳኦል በሞተ ጊዜ ጭምር አዝኗል፣ አልቅሷልም (2ኛ ሳሙ 1:12)። በዚህም ለወዳጅ ብቻ ሳይሆን ለጠላት ጭምር ማልቀስ እንደሚገባ አስተምሮናል። ልጁ አቤሴሎም ባመፀበት ጊዜ ዳዊት ተከናንቦ ያለ ጫማ እያለቀሰ ወደ ደብረ ዘይት ዐቀበት ወጣ፤ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተከናንበው እያለቀሱ ወጡ(2ኛ ሳሙ 15:30)። በአባቱ ዳዊት ላይ ያመፀው አቤሴሎምም ሲሞት ንጉሥ ዳዊት እጅግ አዘነ፥ በበሩም ላይ ወዳለችው ቤት ወጥቶ አለቀሰ፤ ሲሄድም:- ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ፥ ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ በአንተ ፋንታ ሞቼ ኖሮ ቢሆን፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ ይል ነበር (2ኛ ሳሙ 18:33)። ጺቅላግ በአማሌቃውያን ከተመታች በኋላ ዳዊትና ሰዎቹም ወደ ከተማ በመጡ ጊዜ፥ እነሆ፥ በእሳት ተቃጥላ፥ ሚስቶቻቸውም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም ተማርከው አገኙ። ዳዊት ከእርሱም ጋር የነበሩ ሕዝብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ለማልቀስ ኃይል እስኪያጡ ድረስ አለቀሱ(1ኛ ሳሙ 30÷3-5)። ንጉሥ ዳዊት ኦርዮንን በማስገደሉ፣ ሚስቱን ቤርሳቤህንም በመውሰዱ፣ ከቤርሳቤህ የተወለደው ልጁ በመሞቱም አልቅሷል (2ኛ ሳሙ 12:22)። በዚህ ሁሉ የተነሳም ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ሌሊቱን ሁሉ አልጋዬን አጥባለሁ፥ በዕንባዬም መኝታዬን አርሳለሁ (መዝ 6:6)፣ እንባዬ በቀንና በሌሊት ምግብ ሆነኝ (መዝ 42:3)፣ አመድን እንደ እህል ቅሜአለሁና፥ መጠጤንም ከእንባዬ ጋር ቀላቅያለሁና (መዝ 102:9)፣ ሕግህን አልጠበቁምና የውኃ ፈሳሽ ከዓይኖቼ ፈሰሰ (መዝ 119:136)” እያለ ስለራሱና ስለሕዝበ እስራኤል ስለኢየሩሳሌምም ያዝን ያለቅስ ነበር።

ነቢዩ ኢሳይያስ: ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም “እኔም ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው በመሆኔ፥ ከንፈሮቻቸውም በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመቀመጤ ዓይኖቼ የሠራዊትን ጌታ ንጉሡን እግዚአብሔርን ስለ አዩ ጠፍቻለሁና ወዮልኝ! አልሁ (ኢሳ 6:5)” በማለት ስለ ንስሐው ልቅሶ ተናግሯል። ስለሞዓብ መፍረስም “ስለዚህ በኢያዜር ልቅሶ ስለ ሴባማ ወይን ግንድ አለቅሳለሁ፤ ሐሴቦንና ኤልያሊ ሆይ፥ በዛፍሽ ፍሬና በወይንሽ መከር የጦር ጩኸት ወድቆአልና በእንባዬ አረካሻለሁ(ኢሳ 16:9)” በማለት ያለቅስ ነበር። ስለ ኢየሩሳሌም ጥፋትም “ስለዚህ ፊታችሁን ከእኔ ዘንድ አርቁ፤ መራራ ልቅሶ አለቅሳለሁ፤ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ጥፋት ታጽናኑኝ ዘንድ አትድከሙ አልሁ (ኢሳ 22:4)” እያለ ያለቅስ ነበር። ሕዝቅያስ ለሞት እስኪደርስ በታመመ ጊዜ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል አለው። ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። አቤቱ፥ በፊትህ በእውነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ። ሕዝቅያስም እጅግ አድርጎ አለቀሰ። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል መጣ። ሂድ፥ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው። የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፥ በዕድሜህ ላይ አሥራ አምስት ዓመት አጨምራለሁ። አንተንና ይህችንም ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፥ ይህችንም ከተማ እጋርዳታለሁ (ኢሳ 38:1-6) አለው።

ነቢዩ ኤርምያስ: ነቢዩ ኤርምያስ “በሕዝቤ ሴት ልጅ ስብራት እኔ ተሰብሬአለሁ ጠቍሬማለሁ (ኤር 8:21)” እያለ ስለሕዝቡ ያዝንና ያለቅስ ነበር። እንዲሁም “ተወግተው ስለ ሞቱ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ሰዎች ሌሊትና ቀን አለቅስ ዘንድ ራሴ ውኃ፥ ዓይኔም የእንባ ምንጭ በሆነልኝ! (ኤር 9:1)” በማለት እጅግ ያዝንና ያለቅስ ነበር። የሐዘኑንም ጽናት ሲናገር “ኅዘኔ የማይጽናና ነው፥ ልቤም በውስጤ ደክሞአል (ኤር 8:18)” በማለት ነበር። ሰቆቃወ ኤርምያስ በተባለው መጽሐፍም ነቢዩ ስለኢየሩሳሌም መፍረስ በስፋት በማንሳት ያለቀሰበትና ከእግዚአብሔርም ምህረትን የለመነበትን ጽፎልናል። በዚህም ሕዝብ ሲበድል፣ እግዚአብሔርም ሲቆጣ ክርስቲያኖች ስለራሳቸውና ስለሕዝቡ በደል በማልቀስ ይቅርታን ከእግዚአብሔር መለመን እንዳለባቸው ያስተምረናል።

ጻድቁ ኢዮብ: በፈተና የጸናው ጻድቁ ኢዮብ “ምድር ሆይ፥ ደሜን አትክደኚ፥ ለጩኸቴም ማረፊያ አይሁን (ኢዮ 16:18)” በማለት በንጹሕ ልብ ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር። እግዚአብሔር በፈተና እንዲጸና ፈቅዷልና ፈተናው ሲበዛበት ጻዲቁ ኢዮብ “እነሆ፥ ስለ ተደረገብኝ ግፍ ብጮኽ ማንም አይመልስልኝም፤ አሰምቼም ብጠራ ፍርድ የለኝም (ኢዮ 19:7)” ብሏል።  እንዲሁም “እግዚአብሔር ባጠፋውና ነፍሱን በለየ ጊዜ፥ የዝንጉ ሰው ተስፋው ምንድር ነው? በውኑ መከራ በመጣበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ጩኸቱን ይሰማልን? (ኢዮ 27:8-9)” በማለት ሰው በሕይወት ሳለ ማልቀስ እንዳለበት ተናግሯል። እግዚአብሔር መከራን ይታገስ ዘንድ ፈቅዷልና ጻድቁ ኢዮብ ፈተናው በበዛበትና የእግዚአብሔርንም ዝማታ ባየ ጊዜ “ወደ አንተ ጮኽሁ፥ አልመለስህልኝም፤ ተነሣሁ፥ አልተመለከትኸኝም (ኢዮ 30:20)” በማለት ወደ እግዚአብሔር ይጮህ እንደነበር ተናግሯል። ስለራሱ ብቻ ያይደለ ስለሌሎችም ያለቅስ እንደነበር “ጭንቅ ቀን ላገኘው ሰው አላለቀስሁምን? ለችግረኛስ ነፍሴ አላዘነችምን? (ኢዮ 30:25)” በማለት ተናግሯል።

ቅድስት ማርያም እንተ ዕረት (ባለሽቶዋ): ማርያም እንተ ዕፍረት ከጌታችን በስተኋላው በእግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፥ በራስ ጠጕርዋም ታብሰው እግሩንም ትስመው ሽቱም ትቀባው ነበረች (ሉቃ 7:38)። በዚህም ኃጢአቷ ተሰርዮላታል። በሉቃስ ወንጌል እንደተጻፈው ከፈሪሳውያንም አንዱ ከእርሱ ጋር ይበላ ዘንድ ለመነው፤ በፈሪሳዊው ቤትም ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ። እነሆም በዚያች ከተማ ኃጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት፤ በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደ ተቀመጠ ባወቀች ጊዜ፥ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ አመጣች። በስተ ኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፥ በራስ ጠጕርዋም ታብሰው እግሩንም ትስመው ሽቱም ትቀባው ነበረች። የጠራው ፈሪሳዊም አይቶ:- ይህስ ነቢይ ቢሆን፥ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፥ ኃጢአተኛ ናትና ብሎ በልቡ አሰበ። ኢየሱስም መልሶ:- ስምዖን ሆይ፥ የምነግርህ ነገር አለኝ አለው። እርሱም:- መምህር ሆይ፥ ተናገር አለ።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በምሳሌ እንዲህ አለው። ለአንድ አበዳሪ ሁለት ተበዳሪዎች ነበሩት በአንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት በሁለተኛውም አምሳ። የሚከፍሉትም ቢያጡ ለሁለቱም ተወላቸው። እንግዲህ ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው ማንኛው ነው? ስምዖንም መልሶ:- ብዙ የተወለቱ ይመስለኛል አለ። እርሱም:- በእውነት ፈረድህ አለው። ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው። ይህችን ሴት ታያለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፥ ውኃ ስንኳ ለእግሬ አላቀረብህልኝም፤ እርስዋ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች በጠጕርዋም አበሰች። አንተ አልሳምኸኝም፤ እርስዋ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም። አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች። ስለዚህ እልሃለሁ፥ እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል። እርስዋንም:- ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል አላት። ሉቃ 7:36-48

ቅዱስ ጴጥሮስ: ጌታውን ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ የካደው ቅዱስ ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ በማልቀሱ ምህረትን አግኝቷል (ሉቃ 22:62)። በሉቃስ ወንጌል እንደምናነበው ጌታም:- ስምዖን ስምዖን ሆይ፥ እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና አለ። እርሱም:- ጌታ ሆይ፥ ወደ ወኅኒም ወደ ሞትም ከአንተ ጋር ለመሄድ የተዘጋጀሁ ነኝ አለው። እርሱ ግን። ጴጥሮስ ሆይ፥ እልሃለሁ፥ እንዳታውቀኝ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዛሬ ዶሮ አይጮኽም አለው (ሉቃ 22: 31-34)። አየሱስንም አይሁድ ይዘውም ወሰዱት ወደ ሊቀ ካህናት ቤትም አገቡት፤ ጴጥሮስም ርቆ ይከተለው ነበር። በግቢ መካከልም እሳት አንድደው በአንድነት ተቀምጠው ሳሉ ጴጥሮስ በመካከላቸው ተቀመጠ። በብርሃኑም በኩል ተቀምጦ ሳለ አንዲት ሴት አየችውና ትኵር ብላ:- ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ አለች። እርሱ ግን:- አንቺ ሴት፥ አላውቀውም ብሎ ካደ። ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሌላው አይቶት:- አንተ ደግሞ ከእነርሱ ወገን ነህ አለው። ጴጥሮስ ግን:- አንተ ሰው፥ እኔ አይደለሁም አለ። አንድ ሰዓትም የሚያህል ቆይቶ ሌላው አስረግጦ:- እርሱ የገሊላ ሰው ነውና በእውነት ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ አለ። ጴጥሮስ ግን:- አንተ ሰው፥ የምትለውን አላውቅም አለ። ያን ጊዜም ገና ሲናገር ዶሮ ጮኸ። ጌታም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም። ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እንዳለው የጌታ ቃል ትዝ አለው። ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ (ሉቃ 22:54- 62)።

ወንጌላዊ ዮሐንስ: ፍቁረ እግዚእ የተባለው ዮሐንስ ወንጌላዊ ጌታችንን እስከ መስቀል ከተከተሉት ጥቂት ሰዎች አንዱ ነው። በዚህም ጌታችን እናቱን ድንግል ማርያምን ለእናትነት በአደራ ሰጥቶታል። እርሱም ይህንን በወንጌሉ ሲጽፍ “ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር። ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን። አንቺ ሴት፥ እነሆ ልጅሽ አላት። ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን። እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት (ዮሐ 19: 25-27)” በማለት ገልፆታል። በዚህም ወንጌላዊ ዮሐንስ የወልደ እግዚአብሔርን መከራውን እያሰበ እስከ ዕለተ ዕረፍቱ ድረስ አልቅሷል። የጌታን ጸዋትወ መከራ አይቶ ፊቱ በኃዘን ተቋጥሮ ይኖር ስለ ነበር ቁጹረ ገጽ (ፊቱ በኃዘን የተቋጠረ) ይባላል፡፡ እንዲሁም በራዕዩ “በዙፋኑ ላይም በተቀመጠው በቀኝ እጁ ላይ በውስጥና በኋላ የተጻፈበት በሰባትም ማኅተም የተዘጋ መጽሐፍን አየሁ። ብርቱም መልአክ:- መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ማኅተሞቹንም ይፈታ ዘንድ የሚገባው ማን ነው? ብሎ በታላቅ ድምፅ ሲያውጅ አየሁ። በሰማይም ቢሆን በምድርም ላይ ቢሆን ከምድርም በታች ቢሆን መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው ማንም አልተቻለውም። መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው የሚገባው ማንም ስላልተገኘ እጅግ አለቀስሁ። ከሽማግሌዎቹም አንዱ:- አታልቅስ፤ እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ሰባቱንም ማኅተም ይፈታ ዘንድ ድል ነሥቶአል አለኝ (ራዕ 5:1-5)” የሰውን ልጅ የሚያድነው በጠፋ ጊዜ ማልቀሱን ነግሮናል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ስለ አልዓዛር ሞት ሲናገር “ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ። ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ (አልዓዛር) ባልሞተም ነበር አለችው። ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ ከእርስዋም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤ ወዴት አኖራችሁት? አለም። እነርሱም። ጌታ ሆይ፥ መጥተህ እይ አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ (ዮሐ 11:32-35)” ብሏል። ፍጹም ሰው (በነፍስና በሥጋ) መሆኑን ሲያጠይቅ አለቀሰ። በሐዘን ያሉትን እግዚአብሔር እንደሚያጽናና ሲያሳየን አብሮ አለቀሰ። በመንፈስ የሚዘሩ በሐዘን መዝራት እንዳለባቸው ሲያስተምር አብሯቸው አለቀሰ። ፍጹም አምላክ መሆኑን ሲያስረዳን ደግሞ አልዓዛር አስነስቶ አሳየን።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለራስ ብቻ ያይደለ ስለሌላውም ኃጢአት ማልቀስ እንዳለብን ሲያስተምረን ከተማይቱን (ኢየሩሳሌምን) አይቶ አልቅሶላታል። ወንጌላዊው ሉቃስ ይህንን “ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፥ እንዲህ እያለ:- ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል። ወራት ይመጣብሻልና፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና (ሉቃ 19:41-44)” በማለት ጽፎልናል። በዚህም ጌታችን ስለሕዝብ ኃጢአት ማዘንና ማልቀስን እንደሚገባ በተግባር አርአያ ሆኖናል።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህች ምድር ላይ በሥጋ ሳለ ስለሁላችን በደል እንባን አፍስሶ እንደነበር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር “እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው (ዕብ 5:7-10)” ብሏል። እንግዲህ በደል የሌለበት እርሱ ስለእኛ በደል እንባን ካፈሰሰ እኛ እርሱን የበደልነው ስለራሳችን በደል ምንኛ ማልቀስ ይገባን ይሆን?!

መፅናናትን ያገኛሉና።

ነቢዩ ኢዩኤል “አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ (ኢዩ 2:12)” ከበደላችን በልቅሶ እንድንመለስ ተናግሯል። በተጨማሪም ጠቢቡ ሰሎሞን “ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል፤ እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፥ ሕያውም የሆነ በልቡ ያኖረዋልና። ከሳቅ ኀዘን ይሻላል፥ ከፊት ኀዘን የተነሣ ልብ ደስ ይሰኛልና (መክ 7:2-3)” በማለት የእውነተኛ ንስሐን ጥቅም በአጽንዖት ግልጿል። በምድር ሳሉ ስለ በደላቸው አልቅሰው ንስሐ ያልገቡ ግን በሰማይ ያለቅሳሉ። ጌታችን ስለዚህ  “የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል (ማቴ 13:41-42)” በማለት አስጠንቅቆናል።

ስለኃጢአታቸውና ስለበደላቸው ለሚያዝኑና ለሚያለቅሱ ሰዎች እግዚአብሔር ንስሐቸውን ሊቀበል የታመነ ነው። ይቅርታን በማድረግ፣ ምሕረትንም በመስጠት እንዲጽናኑ ያደርጋቸዋል። ስለሌሎች በደልና ኃጢአት የሚያዝኑና የሚያለቅሱትንም ሰምቶ በንስሐ ይመለሱ ዘንድ የሚራዳ መንፈስን ያድላል። ልበ አምላክ የተባለ ክቡር ዳዊት እግዚአብሔርን በበደለ ጊዜ በሐዘንና በለቅሶ ንስሐ በመግባቱ እግዚአብሔር ምሕረትን ስለሰጠው ተጽናንቷል (2ኛ ሳሙ 11÷12)። ቅዱስ ጴጥሮስም ምርር ብሎ በማልቀሱ (ሉቃ 22÷54-62) ጌታችን ንስሐውን ተቀብሎት ተጽናንቷል። ኋላም በጎቼን አሰማራ የሚል አምላካዊ ትዕዛዘን ተቀብሎ (ዮሐ 21:17 በሮም አድባባይ ሰማዕትነትን እስከመቀበል ድረስ ታምኗል። ማርያም እንተ ዕፍረትም በዕንባዋና በጸጉሯ የጌታችንን እግር በማጠቧ ኃጢአቷ ሁሉ ተሰርዮላት ተጽናንታለች።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ “ዓመፃቸው የተሰረየላቸው ኃጢአታቸውም የተከደነላቸው ብፁዓን ናቸው፤ ጌታ ኃጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ብፁዕ ነው (ሮሜ 4:7-8)” በማለት አስቀድሞ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “መተላለፉ የቀረችለት ኃጢአቱም የተከደነችለት ምስጉን ነው። እግዚአብሔር በደልን የማይቈጥርበት በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት ሰው ምስጉን ነው (መዝ 32:1-2)” በማለት የተናገረውን አስተምሯል። እውነት ነው በኃጢአት ስርየት የሚገኝ በረከትና ደስታ ታላቅ ነው።  ጌታችንም “እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል (ሉቃ 15: 7-10)” በማለት ንስሐ መግባት በሰማይ መላእክት ዘንድ ሳይቀር ታላቅ ደስታ መሆኑን ተናግሯል።

ንስሐ የሚገቡና በንስሐ ሕይወት የሚኖሩ ሰዎችን ብፅዕና ቅዱስ ዮሐንስ በራዕይ “ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆችዋም ወደ ከተማይቱም እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው (ራዕ 22:14)” በማለት ነው የገለጸው። እንዲሁም በኃጢአት ምክንያት በመጨረሻው ቀን ራቁታችንን እንዳንቀር ሲያሳስብ “እነሆ፥ እንደ ሌባ ሆኜ እመጣለሁ፤ ራቁቱን እንዳይሄድ እፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው (ራዕ 16:15)” ብሏል። እንዲሁም “እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ (ራዕ 21:3-4)” በማለት በምድር የሚያለቅሱ በመጨረሻው ዘመን እንባቸው እንደሚታበስ፣ ኃዘናቸውም እንደምትረሳ በራዕዩ አስፍሮልናል።

የበደለኛን መመለስ እንጂ የቀደመ በደል የማይቆጥር የምህረትና የይቅርታ ባለቤት አምላካችን እግዚአብሔር ስለ ኀጢአታችን፣ ስለ በደላችን ተጸጽተን የምናለቅሰውን የእውነተኛ ንስሐ እንባ እንዲያድለን፣ በርህራሄው በአባትነቱም ፍጹም መጽናናት ለሚገኝባት ለመንግስተ ሰማያት የተገባን ያደርገን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። አሜን።

Leave a comment