የዋሆች ብፁዓን ናቸው። ማቴ 5:5
የዋህነት ምንድን ነው? የዋሆችስ እነማን ናቸው? የዋሆች ብፁዓን ናቸው የተባሉትስ ለምንድን ነው? አንዳንድ ወገኖች የዋህነትን የደካማነት፣ ያላዋቂነት፣ ወይም ያለመሰልጠን (የኋላቀርነት) መገለጫ አድርገው ይወስዱታል። ይህ ፍጹም ስሕተት ነው። ይልቁንስ የዋሆች አዋቂዎችና ጥበብን የተመሉ ናቸው። የዋህነት ራስን በመግዛት የተቃኘች የጥንካሬ፣ የብርታት፣ የብስለትና ብቃት መገለጫ ናት። ምንም እንኳን የዋህነት አንድ ውሕድ ምግባር ቢሆንም በሁለት መንገድ መንፈሳዊ የዋህነት እና ‘ስብዕናዊ’ የዋህነት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። መንፈሳዊ የዋህነት እግዚአብሔርን በመፍራትና በእርሱም በምትገኝ መንፈሳዊ ጥበብ ላይ የተመሠረተች ናት። ‘ስብዕናዊ’ የዋህነት ደግሞ ከሞራል ብቃት፣ ከስሜት ብስለት፣ ከማኅበራዊ ደረጃ፣ ወይም ከዕውቀትና ከክህሎት ልህቀት የሚመነጭ ነው። ይህም ሰዎች መሳሳታቸውን እያወቁ መታገስ፣ የሚያበሳጭ ነገር ሲፈጠር ራስን መቆጣጠር፣ ስልጣን እያለን ሌሎች እንዲመሩና እንዲናገሩ መፍቀድና እነርሱን ማድመጥ፣ ከእኛ የተሻለ ሀሳብ ያለው ሲገኝ መቀበልና የመሳሰሉትን ያካትታል። እግዚአብሔርን የማያምኑ ሰዎች ‘ስብዕናዊ’ የዋህነት ሊኖራቸው ይችላል። የዚህች ጽሑፍ ትኩረት መንፈሳዊ የዋህነት ላይ ስለሆነ ‘ስብዕናዊ’ የዋህነት በሰፊው አልተዳሰሰም።
ጌታችን በወንጌሉ “እነሆ፥ እኔ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ (ማቴ10:16)” ያለው ጥበብን የተመላች መንፈሳዊ የዋህነትን ገንዘብ እንድናደርግ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም በመልእክቱ “ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አኗኗሩ ሥራውን በጥበብ የዋህነት (Meekness of Wisdom) ያሳይ (ያዕ 3:13)” እንዳለ የዋሆች ጥበበኞች እንጂ ደካሞች አይደሉም። እንዲሁም ስለሰማያዊው ጥበብ ሲናገር “ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር (የዋህ)፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት” (ያዕ 3:17) በማለት ሰማያዊቷ ጥበብ የዋህነትን ገንዘብ ያደረገች መሆኗን አስተምሮናል። በጥበብ የተመላች መንፈሳዊ የዋህነትን ገንዘብ ያደረጉ ክርስቲያኖች በሚከተሉት ምግባሮቻቸው ይገለፃሉ።
የዋሆች በነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ያስቀድማሉ: ይህንንም የሚያድርጉት ለእግዚአብሔር ካላቸው ጥልቅ ፍቅርና በእርሱ ላይ ካላቸው መታመን የተነሳ ነው። ጠቢቡ ሰሎሞን “በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” (ምሳ 3:6) እንዳለው የዋሆች በመንገዳቸው (በሕይወታቸው) ሁሉ እግዚአብሔርን ያስቀድማሉ። ጌታችንም በወንጌሉ “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” (ማቴ 6:33) ብሎ እንዳስተማረው የዋሆች የእግዚአብሔርን መንግሥት ከሁሉ ያስቀድማሉ፣ ሌላው ነገር ሁሉ እንደሚጨመርላቸው ያምናሉ። በዚህ ፍጹም እምነታቸውም እግዚአብሔር የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ ሊያደርግላቸው የታመነ ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው” (ማቴ 11:6፣ ሉቃ 7:23) በማለት የተናገረው የእርሱን መድኃኒትነት በእውነትና በየዋህነት ለሚያምኑት ነው።
የዋሆች ያለኝ ይበቃኛል ይላሉ: የዋሆች ሁሉ ነገር ከእግዚአብሔር እንደተሰጠ ስለሚረዱ ያለኝ ይበቃኛል ይላሉ፣ የሌላውንም አይመኙም። ቅዱስ ጳውሎስ “ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” (ፊል 4:11-12) ያለውን የኑሯቸው መመሪያ አድርገው ስግብግብነትንና አልጠግብ ባይነትን አርቀው ባላቸው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በደስታ ይኖራሉ። እንዲሁም “ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል” (1ኛ ጢሞ 6:6-8) ያለውን ገንዘብ ያደርጋሉ። በተጨማሪም “አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን፥ ያላችሁም ይብቃችሁ፤ እርሱ ራሱ። አልለቅህም ከቶም አልተውህም ብሎአልና” (ዕብ 13:5) የተባለውንም የህይወት መርህ ያደርጋሉ።
የዋሆች አይበቀሉም: የዋሆች ማንም ቢበድላቸው አይበቀሉም፣ እግዚአብሔርንም ተበቀልልን ብለው አይጠይቁም፣ ለበደላቸውም ምህረትን ይጠይቃሉ እንጂ። የዋሆች ሰው ቢበድላቸው “እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ” (ዘጸ 14:14) የሚለውን አምላካዊ ቃል እያሰቡ ዝም ይላሉ እንጂ አይበቀሉም። የተወደደ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ “ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና” (ሮሜ 12:19) እንዳለውም ሁሉን ለእግዚአብሔር ይሰጣሉ። ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ “ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና” (1ኛ ጴጥ 3:9) በማለት እንዳስተማረው እንዲሁም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ማንም ለሌላው በክፉ ፈንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፥ ነገር ግን ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ለሁሉም መልካሙን ለማድረግ ትጉ” (1ኛ ተሰ 5:15) እንዳለው የዋሆች ክፉውን በክፉ አይመልሱም፣ በመልካም እንጂ። የዋህነትን በተግባር ያስተማረን ጌታችንም “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ” (1ኛ ጴጥ 2:23)።
የዋሆች ሌሎችን ያስቀድማሉ: የዋሆች ለሌሎች ካላቸው ልባዊ ፍቅር የተነሳ ከራሳቸው ይልቅ ሌሎችን ያስቀድማሉ፣ ለማንም ሸክም ወይም ዕዳ አይሆኑም። ይልቁንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም እንዲሁም የክርስቶስን ሕግ ፈጽሙ” (ገላ 6:2) ብሎ እንዳስተማረው የሌላውን ሸክም ይሸከማሉ። “በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ” (ሮሜ 12:10) እንደተባለም ሁሉንም ሰው ያከብራሉ። ቅዱስ ጳውሎስ “እኛም ኃይለኞች የሆንን የደካሞችን ድካም እንድንሸከም ራሳችንንም ደስ እንዳናሰኝ ይገባናል። እያንዳንዳችን እንድናንጸው እርሱን ለመጥቀም ባልንጀራችንን ደስ እናሰኝ” (ሮሜ 15:1-2) እንዳለውም ከራሳቸው ይልቅ የባልንጀራቸውን ደስታ ይሻሉ። እንዲሁም “ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ” (ፊልጵ 2:3-4) እንደተባለውም የዋሆች ለራሳቸው ሳይሆን ለባልንጀራቸው የሚጠቅመውን ያደርጋሉ።
የዋሆች ለራሳቸው ምድራዊ ክብርን አይሹም: የዋሆች በምድር ላይ በሚያደርጉት ሁሉ እግዚአብሔር እንዲመሰገንበት እንጂ ለራሳቸው ክብርን አይሹም። ከራሳቸው ክብርም ይልቅ በሌላው ክብር ይደሰታሉ። ጌታችን በወንጌሉ “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፥ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል” (ማቴ 23:12) ብሎ እንዳስተማረው ክብራቸው በሰማይ እንደሆነ ስለሚያውቁ ከምድራዊ ከንቱ ውዳሴ ራሳቸውን ይጠብቃሉ። ጠቢቡ ሰሎሞንም “ብዙ ማር መብላት መልካም አይደለም፤ እንዲሁም የራስን ክብር መፈለግ አያስከብርም” (ምሳሌ 25:27) እንዳለው የዋሆች የራሳቸውን ክብር አይፈልጉም። የየዋህነት አርአያ የሆነው ጌታችን “ከሰው ክብርን አልቀበልም” (ዮሐ 5:41) እንዲሁም “እኔ ግን የራሴን ክብር አልፈልግም፤ የሚፈልግ የሚፈርድም አለ” (ዮሐ 8:50) በማለት ምሳሌነቱን አስተምሮናልና። በተጨማሪም “ከራሱ የሚናገር የራሱን ክብር ይፈልጋል፤ የላከውን ክብር የሚፈልግ ግን እርሱ እውነተኛ ነው በእርሱም ዓመፃ የለበትም” (ዮሐ 7:18) በማለትና “እኔ ራሴን ባከብር ክብሬ ከንቱ ነው፤ የሚያከብረኝ እናንተ አምላካችን የምትሉት አባቴ ነው” (ዮሐ 8:54) በማለት ምሳሌ ሆኖናል።
የየዋህነት ምሳሌዎች
በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪት፣ በሕገ ወንጌል ዘመናት እጅግ ብዙ የዋሀን የእግዚአብሔር ሰዎች ነበሩ፣ አሉም። ለዚህች ጽሑፍ ያህል የሚከተሉትን ምሳሌዎች አቅርበናል። ይህም የየዋህነትን ጽንሰ ሀሳብ ለማስረዳት ያህል እንጂ ሁሉንም በጥበብ የዋህነት ያደረጓቸውን የጽድቅ ሥራዎች ለመዘርዘር አይደለም።
ጻድቁ አቤል: “አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ።ከብዙ ቀን በኋላም አቤል ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ። ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። በዚህም ምክንያት ቃየን አቤልን ገደለው” (ዘፍ 4: 1-25)። የአቤል የዋህነት አንድም ለእግዚአብሔር የሚገባውን መስዋዕት ማቅረቡ ነው። ሁለተኛም በየዋህነት በግፍ መገደሉ ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አቤል ሲናገር “ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችኋል” በማለት ነበር(ማቴ 23:35)። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ስለ አቤል የዋህነት ሲናገር “አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ፥ በዚህም፥ እግዚአብሔር ስለ ስጦታው ሲመሰክር፥ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ሞቶም ሳለ በመሥዋዕቱ እስከ አሁን ይናገራል” ብሏል (ዕብ 11:4)። ሊቁ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም እመቤታችንን “በግፍ የተገደለ የአቤል የዋህነት አንቺ ነሽ” በማለት እመቤታችንን በአቤል የዋህነት መስሏታል።
ጻድቁ ዮሴፍ: ጻድቁ ዮሴፍ በየዋህነት ያየውን ሕልም ለወንድሞቹ በመናገሩ ምክንያት ወንድሞቹ በጉድጓድ ጥለውታል፣ ኋላም ከጉድጓድ አውጥተው ለግብፅ ነጋዴዎች ሽጠውታል። በጥበባዊ የዋህነት እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ ያስቀድም ነበር። በዚህም በግብፅ ለታላቅ ስልጣን በቅቷል። የጲጢፋራ ሚስት በዝሙት ብትፈትነው በእግዚአብሔር ፊት ይህንን አላደርግም በማለቱ በሐሰት ክስ ለእሥራት ተዳርጓል። ነገር ግን በዚያም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለነበር የፈርኦንን ሕልም በመፍታቱ ወደ ክብሩ ተመልሷል። ግብፅንም ከረሃብ አድኗል። በእስራኤል ረሃብ በሆነ ጊዜም የሸጡት ወንድሞቹ ወደ ግብፅ ሲመጡ በየዋህነት ተቀብሏቸዋል። በዚህም በየዋህነቱ ለሁላችን አርአያ ሆኖናል (ዘፍ 37-39)።
ሊቀ ነቢያት ሙሴ: በብሉይ ኪዳን የየዋህነት ምሳሌ ከሆኑት ደጋግ አበው አንዱ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ነው። ለዚህ ነው መጽሐፍ “ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ የዋህ ሰው ነበረ” (ዘኍ 12:3) ያለው። ከእስራኤል የተወለደውና በፈርዖን ቤተመንግሥት ያደገው ሙሴ እግዚአብሔር እስራኤልን እንዲመራ በጠራው ጊዜ “ወደ ፈርዖን የምሄድ የእስራኤልንም ልጆች ከግብፅ የማወጣ እኔ ማን ነኝ?” (ዘጸ 3:11) በማለት ራሱን ዝቅ ያደረገ የዋህ ነበር። በዚህም እግዚአብሔርን አስቀድሞ እስራኤልን መርቷል። ሕዝበ እስራኤል በድለው እግዚአብሔር በተቆጣቸው ጊዜ “ወዮ! እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋል፥ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፤ አሁን ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ” (ዘጸ 32:31)” በማለት ከራሱ ክብር ይልቅ የሕዝበ እስራኤልን ድኅነት የጠየቀ የዋህ ሰው ነበር። በየዋህነቱ ባቀረበው ምልጃም የእግዚአብሔር ቸርነት ምክንያት ሆኖ ወገኖቹ እስራኤልን ከመከራ ስጋ ታድጓቸዋል።
ሩት: ሩት የተወለደችበትን፣ ያደገበችበትንና ለወግ ለማዕረግ የበቃበችበትን ሞዓብን በመተው “ወደምትሄጅበት እሄዳለሁና፥ በምታድሪበትም አድራለሁና እንድተውሽ ከአንቺም ዘንድ እንድመለስ አታስቸግሪኝ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፥ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል፤ በምትሞችበትም ስፍራ እሞታለሁ፥ በዚያም እቀበራለሁ፤ ከሞት በቀር አንቺንና እኔን አንዳች ቢለየን እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ እንዲሁም ይጨምርብኝ”(ሩት 1:16-17) በማለት ኑኃሚንን ተከትላ ወደ ቤተልሔም የሄደች የዋህት ሴት ናት። በዚህም የዋህነቷ እግዚአብሔር ሌላውን የዋህ ቦዔዝን ሰጥቷት (ሩት 3:9) የእሴይን አባት ኢዮቤድን ወልዳለች።በዚህም የተነሳ በማቴዎስ ወንጌል የመጀመሪያ ምዕራፍ በተዘረዘረው የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ ሀረግ ለመቆጠር በቅታለች።
የባርክኤል ልጅ ኤሊሁ: ሦስቱ ሽማግሌዎች ጻድቁ ኢዮብን ሲናገሩት በየዋህነት ዝም ብሎ ሲያዳምጥ የነበረው የባርክኤል ልጅ ኤሊሁ እነርሱ ሲሳሳቱ ግን ዝም ብሎ አልቀጠለም። መጽሐፍም የዋህነቱን ሲገልጽ “ኢዮብም ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና እነዚያ ሦስቱ ሰዎች መመለስን ተዉ። ከራም ወገን የሆነ የቡዛዊው የባርክኤል ልጅ የኤሊሁ ቍጣ ነደደ፤ ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና ኢዮብን ተቈጣው። ደግሞም በኢዮብ ፈረዱበት እንጂ የሚገባ መልስ ስላላገኙ በሦስቱ ባልንጀሮቹ ላይ ተቈጣ። ኤሊሁ ግን ከእርሱ ይልቅ ሽማግሌዎች ነበሩና ከኢዮብ ጋር መናገርን ጠብቆ ነበር። ኤሊሁም በነዚህ በሦስቱ ሰዎች አፍ መልስ እንደሌለ ባየ ጊዜ ቍጣው ነደደ” (ኢዮብ 32:1-5) ይላል።
“የቡዛዊውም የባርክኤል ልጅ ኤሊሁ ተናገረ እንዲህም አለ። እኔ በዕድሜ ታናሽ ነኝ፥ እናንተ ግን ሽማግሌዎች ናችሁ፤ ስለዚህም ሰጋሁ፤ እውቀቴን እገልጥላችሁ ዘንድ ፈራሁ። እንደዚህም አልሁ። ዓመታት በተናገሩ ነበር፥ የዓመታትም ብዛት ጥበብን ባስተማረች ነበር። ነገር ግን በሰው ውስጥ መንፈስ አለ፥ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ማስተዋልን ይሰጣል። በዕድሜ ያረጁ ጠቢባን አይደሉም፥ ሽማግሌዎችም ፍርድን አያስተውሉም.. እነሆ፥ ቃላችሁን በትዕግሥት ጠበቅሁ፤ የምትናገሩትን ነገር እስክትመረምሩ ድረስ፤ ብልሃታችሁን አዳመጥሁ። እንዲሁም ልብ አደረግሁ፤ እነሆም፥ በእናንተ መካከል ኢዮብን ያስረዳ፥ ወይም ለቃሉ የመለሰ የለም። እናንተም። ጥበብን አግኝተናል፤ እግዚአብሔር ነው እንጂ ሰው አያሸንፈውም እንዳትሉ ተጠንቀቁ። እርሱ ግን ቃሉን በእኔ ላይ አልተናገረም፤ እኔም በንግግራችሁ አልመልስለትም። እነርሱ ደነገጡ፥ ዳግመኛም አልመለሱም፤ የሚናገሩትንም አጡ”። (ኢዮብ 32:6-15) የኤሊሁ የዋህነት በትዕግስትና ራስን በመግዛት በማዳመጥ ጊዜው ሲደርስም እውነቱን በመግለጥ ታውቃለች።
ቅድስት ድንግል ማርያም: የዋህት ርግብ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም የየዋህነት አማናዊት ምሳሌ ናት። እርስዋ መልአኩ ባበሰራት ጊዜ ምንም ሳታመነታ “እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” (ሉቃ 1:38) በማለት የተቀበለች የዋህ ናት። በምድር ላይ ሳለች በልጇ የሚደረገውን ተአምር ሁሉ እየተመለከተች ሳትታበይ በልብዋ የምትጠብቅ የዋህ ነበረች (ሉቃ 2:19፣ 51)። በቃና ዘገሊላ ሠርግ ቤትም “የሚላችሁን አድርጉ” በማለት ፍጹም የሆነ የዋህነትን ያሳየች እናታችን ናት (ዮሐ 2:5)። ብዙዎች ጥለው በሸሹ ጊዜም እስከመጨረሻው ድረስ ተከትላው መስቀል ስር ስታለቅስ አታልቅሺ ያላትና ለሁላችንም እናት ትሆን ዘንድ የተሰጠችን ለፍጥረታት ሁሉ የምትራራ የዋህት ርግብ ናት (ዮሐ 19:26-27)።
ሕፃናት: ሕፃናት የዋሆች ናቸው። ጌታችንም እንደ ሕፃናት የዋሆች እንድንሆን አስተምሯል። ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ “በዚያች ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው:- በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን? አሉት ሕፃንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ እንዲህም አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ፥ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው” (ማቴ 18: 1-4) በማለት ይህንን አማናዊ ተምሳሌትነት ጽፎልናል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: በሐዲስ ኪዳን የየዋህነት ፍጹም ምሳሌ የሆነን የቅዱሳን ሁሉ አክሊላቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህንንም በወንጌሉ “ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” (ማቴ 11:29) በማለት ነበር የተናገረው። አስቀድሞ በነቢዩ ዘካርያስ “ለጽዮን ልጅ፥ እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት” (ዘካ 9:9 ማቴ 21:4) የተባለለት እርሱ ፍፁም የዋህ፣ የየዋህነትም ምሳሌ ነው። ስለዚህም ቅዱስ ጴጥሮስ “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና።እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ” (1 ጴጥ 2:23) በማለት የእርሱን የዋህነት መስክሯል። ቅዱስ ጳውሎስም “በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እመክራችኋለሁ” (2ኛ ቆሮ 10:1) በማለት የየዋህነት አርአያ እርሱ መሆኑን ተናግሯል።
ምድርን ይወርሳሉና
ቀደምት አበው “የዋሆች ብፁዓን ናቸው ፣ ምድርን ይወርሳሉና” (ማቴ 5:5) የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ የአንቀጸ ብፁዓን ትምህርት “ምድርን ይወርሳሉና” የሚለውን በተመለከተ በአራት መንገዶች አብራርተውና አመስጥረው አስተምረዋል።
አዲሲቷ ምድርን: የዋህነት ጥበብ ናት፣ ጻድቃን መንግሥተ ሰማያትን የሚወርሱባት ጥበብ። እግዚአብሔር ለየዋሆች ምድርን (መንግሥተ ሰማያትን) ያወርሳቸዋል። ስለዚህም ነው “የዋሆች ብፁዓን ናቸው” በማለት የተናገረው። ልበ አምላክ የተባለ ዳዊትም “ገሮች (የዋሆች) ግን ምድርን ይወርሳሉ፥ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል (መዝ 37:11)” በማለት የተናገረው ስለመንግሥተ ሰማያት ነው። በምድር ካለው ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን አስቀድመው መንግሥቱን ሽተዋልና እርሱም ምድርን ሊያወርሳቸው የታመነ ነው። ክቡር ዳዊት ስለዚያች ምድር “የእግዚአብሔርን ቸርነት በሕያዋን ምድር አይ ዘንድ አምናለሁ” (መዝ 27:1 በማለት በእምነት ናፍቋታል። በተመሳሳይም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” (2ኛ ጴጥ 3:13) እያለ እርሷን እንጠብቅ ዘንድ አሳስቦናል። የዋሆች የሚወርሷት ምድር፣ የምንኖርባት ምድር ካለፈች በኋላ የምትኖረው አዲስ ምድር ናት። ስለዚህች ምድርም ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም” (ራእይ 21:1) በማለት ጌታችን የተናገረው ስለአዲሲቷ ምድር መሆኑን ገልጾልናል።
ይህችን የምንኖርባትን ምድር: የዋሆች በዚህች ምድር ላይ ሲኖሩ በሁሉም ሰው ይወደዳሉ፣ የእግዚአብሔር በረከትም ይበዛላቸዋል። በዚህም መንፈሳዊና ሥጋዊ ሀብታትን ያድላቸዋል። በዚህች ምድር ላይ ሲኖሩም የሚቸግራቸው ነገር አይኖርም። መንግሥቱን አስቀድመው ሽተዋልና ሁሉም ይጨመርላቸዋልና። በዚህም ይህችን የምንኖርባትን ምድር ይወርሳሉ። አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ፣ ዮሴፍ እና ሌሎች ብዙ አባቶች የዋሆች ስለነበሩ የእግዚአብሔር በረከት በዚህች ምድር ላይ ተጨምሮላቸዋል። ሊቀ ነብያት ሙሴ የዋህ ስለነበር ሕዝበ እስራኤልን እንዲመራ እግዚአብሔር መርጦታል። ቦኤዝም የዋህ ስለነበር እግዚአብሔር በበረከት ጎብኝቶታል። በሰው ፊት ታናሽ የነበረ ዳዊትንም እንዲሁ የእስራኤል ንጉሥ አድርጎታል።
ሰውነታቸውን: ምድር የሰውነት ምሳሌ ነው፣ ሰው ከምድር ተፈጥሯልና። የዋሆች ሥጋቸውን ለነፍሳቸው በማስገዛት የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያደርጉታል። በዚህም ምድር (አፈር) የተባለ ሥጋቸውን ይወርሱታል። ወርሰውም ለጽድቅ ሥራ እንዲተጋ ያደርጉታል። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ “ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን” (1ኛ ጴጥ 3:15) በማለት ያስተማረውን የዋሆች ሰውነታቸውን ለነፍሳቸው በማስገዛት ይተገብሩታል። ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ “በትሁታንና በየዋሀን ልብ የጥበብ መንፈስ ያድራል” እንዳለው የዋሀን ልባቸውን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ያደርጉታል።
በኃጢአት የሚኖሩትን: ምድር የኃጥአን ምሳሌም ናት። አንድም ኃጥአን ምድራዊ ሕይወታቸው ላይ ያተኩራሉና። በሌላም መልኩ ምድር ኃጢአት የሚሠራባት ቦታ ናትና። የዋሆች በጥበብ በቃልና በተግባር ክርስትናን እየሰበኩ ኃጥአንን ከክፉ ሥራ ወደ እውነት (ክርስቶስ) በመማረክ ይወርሷቸዋል፣ ማለትም የጽድቅ አገልጋይ የእግዚአብሔር ልጆች ያደርጓቸዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በገላቲያ መልእክቱ “ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ” (ገላ 6:1) በማለት እንዳስተማረው የዋሆች በኃጢአት የሚኖር ወገናቸውን አቅንተው የእግዚአብሔር ልጅ ያደርጉታል።
ስለየዋህነት የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት
“ሁሉም ትሩፋቶች መልካም ናቸው። ከሁሉም ግን የዋህነት የተለየ ነው። የዋህነት ሰውን ከአራዊት ለይቶ ከቅዱሳን መላእክት ጋር እንዲመሳሰል የሚያደርግ ትሩፋት ነው። ስለዚህም ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ የዋህነት አምልቶና አስፍቶ በቃል ያስተማረው። በቃል ማስተማርም ብቻ አይደለም በተግባርም ያሳየን።” (Homily 61 on Gospel of John)
“እንግዲህ ክርስቶስን ከመሰላችሁ ዲያብሎስ ፊት ለፊት ሊያያችሁ አይችልም። የክርስቶስን መልክ ያውቃልና፣ የክርስቶስን የጦር መሳሪያዎችንም ያውቃል፣ በዚህም ክፉኛ ተጎድቷል። እነዚህም ትህትናና የዋህነት ናቸው። ምክንያቱም ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ ዲያብሎስን ድል የነሳው እርሱ ክርስቶስ መሆኑን በማስታወቅ አልነበረም። ነገር ግን በነዚህ ቃላት አጥምዶ በትህትናና የዋህነት አሳደደው እንጂ።” (Homily 78 on Gospel of John)
“አፍህ ከወርቅ ወይም ከከበረ ዕንቍ የተሠራ ቢሆን እንኳ በየዋህነት ጌጥ እንደተሠራ አንደበት ሊያበራ አይችልም።” (Homily 78 on Gospel of John)
“ከየዋህነት የበለጠ ኃይል የለም። እሳት በውኃ እንደሚጠፋ እንዲሁ በቁጣ የተመላ አእምሮ በየዋህነት ይበርዳል። በየዋህነት ሌሎች የትሩፋት ሥራዎችን እንተገብራለን፣ የወንድማችንን ቁጣ እናበርዳለን፣ የወንድማችንን አእምሮንም ከጭንቀት እንታደጋለን።” (Homily 2, 15 on Gospel of John)
“ከእነዚህ ትዕዛዞች የበለጠ ምን ሊከብድ ይችላል? መከራ መቀበል ብቻውን በቂ አይደለም። ነገርግን እንደ እርግብ ተፈጥሮ በምንቀበለው መከራ ልንቆጣ አይገባም። ቁጣ የሚጠፋው በቁጣ ሳይሆን በየዋህነት ነውና።” (Homily 33 on Gospel of Matthew)
ሐሰተኛና አስመሳይ የዋህነት
እውነተኛ የዋህነትን ከሐሰተኛና ከአስመሳይ የዋህነት ለይተን ማወቅ ይገባናል። እውነተኛ የዋህነት ከብስለት ወይም ከጥንካሬ የሚመነጭ ሲሆን ሐሰተኛ የዋህነት ከፍርሃት (fear)፣ በራስ ካለመተማመን (insecurity) ወይም መበለጥን ከመቀበል (submission) የሚመነጭ ነው። ይህም እነዚህ ሁኔታዎች ሲቀየሩ ወደ ትዕቢት፣ ራስወዳድነትና ማን አለብኝነት የሚቀየር የዋህነት ነው። አስመሳይ የዋህነት ደግሞ ከልብ ያልሆነ ነገር ግን መታወቅን፣ ውዳሴ ከንቱን፣ ስልጣን፣ ገንዘብ፣ ዕውቀት ወይም ሌላ ጥቅምን ማግኘትን ወይም በቆይታ ሰውን መጉዳትን ብቻ ግብ ያደረገ የዋህነት ነው። በዚህ ዓይነቱ ራስን በመደበቅ ከሚደረግ የዋህነት ልንርቅ ይገባል፣ በአስመሳይ የዋህነትም ልንታለል አይገባም።
እውነተኛ የዋህነት የትህትና (humility)፣ የበጎነትና የትዕግስት (gentleness) እና ራስን የመግዛት (self-control) ጥምር ውጤት ናት። ይህችም የመንፈስ ፍሬ ተብለው ከተገለጹት ውስጥ አንዷ ናት (ገላ 5:22)። ስለዚህም የዋህነት በጸሎት የምታድግ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብና ቃለ እግዚአብሔርን በመስማት የምትጎለብት፣ የመንፈስ ቅዱስን መሪነት ገንዘብ በማድረግ የምትጸና መንፈሳዊ እሴት ናት። የዋህነት በክርስትና ሕይወታችን ክርስቶስን የምንመስልባት፣ የቅዱሳንን ሕይወት የምንኖርባት ክርስቲያናዊ ትሩፋት ናት። ስለዚህ ነው “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን (መንግሥተ ሰማያትን) ይወርሳሉና” በማለት ጌታችን ያስተማረው። መንግሥተ ሰማያት በብልጠት ሳይሆን በጥበብ የዋህነት የምትወረስ ናትና። ስለሆነም ንጉሥ ዳዊት “እግዚአብሔር በልባቸው የዋሃን ለሆኑ ቅርብ ነው፥ በመንፈስ ትሑታን የሆኑትንም ያድናቸዋል” (መዝ 33:18) እንዳለው እግዚአብሔር እንዲቀርበን በልባችን የዋሆች ልንሆን ይገባናል። የየዋሀን፣ የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር የልባችንን ክፋት አርቆ በየዋህነት ዘለዓለማዊ ህይወትን ከሚወርሱ ኅሩያን ጋር እንዲደምረን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። አሜን።