አንቀጸ ብፁዓን ፬- ለጽድቅ መትጋት: ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና።

ጽድቅን መራብና መጠማት

ጌታችን በአራተኛው የአንቀጸ ብፁዓን ትምህርቱ “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ይጠግባሉና (ማቴ 5:6 ሉቃ 6:21)” በማለት አስተምሯል። ጽድቅ ማለት እውነት፣ እውነት ከሆነው ከእግዚአብሔርና እርሱ ከፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ ጋር የሚኖረን የተቀደሰ ሕይወት ነው። ይህም በምድር ላይ ስንኖር በእግዚአብሔር ፈቃድ ሕይወትን መምራት፣ ከዚያም ከእርሱና ከቅዱሳኑ ጋር በመንግሥተ ሰማያት የምንኖረው ሕይወት ነው። በመንፈሳዊው አስተምህሮ ጽድቅን መራብና መጠማት ማለት ጽድቅን ለማግኘት (ለመመገብ) በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በምፅዋት፣ በአገልግሎት መትጋት ማለት ነው። ይህም ሕግን መጠበቅን ብቻ ሳይሆን በፍጹም ልብ ለጽድቅ መትጋትንም ያጠቃልላል። በዚህች ጽሑፍ ‘ለጽድቅ መትጋት’ ስንል ጽድቅን በልባችን በጽኑ መሻትን፣ ጽድቅን ለማግኘት በአንደበታችን ተግቶ መጸለይን እና የጽድቅን ሥራ ለመፈጸም በሕይወታችን ዘመን ሁሉ መትጋትን ያጠቃልላል።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው ጌታችን “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ” በማለት የገለጸው መራብና መጠማት ከውስጥ የሚመነጩ ፍላጎቶች እንደሆኑ ሁሉ እውነተኛ የጽድቅ ፍላጎትም ሰውን ለመምሰል ወይም ከሰው ለመመሳሰል ብለን የምናሳየው ሳይሆን ከልባችንና ከሕሊናችን የሚመነጭ ጥልቅ ፍላጎት መሆን እንዳለበት ለማስገንዘብ ነው። “የሚራቡ እና የሚጠሙ” ብሎ ሁለቱንም የተናገረው ጽድቅ አስቸኳይና ከሁሉም በላይ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ሲያጠይቅ ነው። መራብና መጠማት በሙሉ አቅማችን ምግብና ውኃን እንድንፈልግ ከውስጥ እንደሚገፋን ሁሉ ጽድቅን መራብና መጠማትን በፍጹም ልባችንና በሙሉ ሀሳባችን ለጽድቅ ሥራ እንድንተጋ ያደርጋል። በተጨማሪም ሥጋዊ ሕይወት ያለ ምግብና ውኃ እንደማይጸናው ሁሉ መንፈሳዊ ሕይወትም ያለ ጽድቅ ሥራ የማይጸና መሆኑን ሲያስተምረን ነው። ስንራብ ምግብ እንደምንፈልገው፣ ስንጠማም ውኃን እንደምንሻው ሁሉ ጽድቅን መራብና መጠማት ጽድቅን አግኝቶ እንደ ምግብ ለመብላት፣ እንደ ውኃም ለመጠጣት፣ በእርሱም እርካታን አግኝቶ በመንፈሳዊ ሕይወት ለማደግ ያተጋናል። ይህም እግዚአብሔርን፣ ቅዱስ ቃሉን፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን፣ በቤቱ መኖርንና በእርሱ የሚገኝ በጎነትን፣ ሕጉንና መንገዱን እንዲሁም በፍጻሜውም እርሱ የሚያወርሰንን መንግሥተ ሰማያትን መራብና መጠማትን ያመለክታል። እያንዳንዳቸውን በዝርዝር እንመልከታቸው-

ትጋት 1: እግዚአብሔርን መራብና መጠማት

ልበ አምላክ ዳዊት “እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም” (መዝ 34:8) በማለት መንፈሳውያን እግዚአብሔርን በማመን፣ እርሱም እንደሚወደን አውቀን ወደ እርሱ እንድንቀርብ አስተምሮናል። እግዚአብሔርም አስቀድሞ በነቢዩ ኤርምያስ “ሕዝቤ ሁለቱን ክፉ ነገሮች አድርገዋልና፤ እኔን የሕያውን ውኃ ምንጭ ትተውኛል፥ የተቀደዱትንም ጉድጓዶች፥ ውኃውን ይይዙ ዘንድ የማይችሉትን ጉድጓዶች፥ ለራሳቸው ቆፍረዋል” (ኤር 2:13) በማለት እርሱ የሕያው ውኃ ምንጭ መሆኑን ተናግሯል። ጽድቅን መጠማት ማለት ከዚህ ውኃ ለመጠጣት በጽኑ (በሀሳብም፣ በቃልም፣ በተግባርም) መሻት ማለት ነው። ክቡር ዳዊት “አምላኬ፥ አምላኬ፥ ወደ አንተ እገሠግሣለሁ፤ ነፍሴ አንተን ተጠማች፥ ሥጋዬ አንተን እንዴት ናፈቀች እንጨትና ውኃ በሌለበት በምድረ በዳ” (መዝ 63:1) በማለት ጽድቅን ስለመጠማት ተናግሯል። እንዲሁም “ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች። ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፤ መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ?” (መዝ 42:1-2) እያለም ጽድቅን መጠማቱን በመዝሙሩ ተናግሯል። ጽድቅን ማግኘትንም በተመለከተ “እንዲህ በሕይወቴ ዘመን አመሰግንሃለሁ፥ በአንተም ስም እጆቼን አነሣለሁ። ነፍሴ በቅቤና በስብ እንደሚጠግቡ ትጠግባለች፥ ከንፈሮቼም ስምህን በደስታ ያመሰግናሉ” (መዝ 63:4-5) ብሏል።

ትጋት 2: ቅዱስ ቃሉን መራብና መጠማት

ጽድቅን መራብና መጠማት አባታችን ዳዊት “ቃልህ ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ” (መዝ 119:103) እንዳለው ቃሉን መራብን፣ ለመመገብ (ለመስማትና እንደ ቃሉም ለመኖር) በጽኑ መፈለግን ያመለክታል።  ጽድቅን መራብና መጠማት ማለት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” (ማቴ 4:4) እንዳለው ዘወትር የእግዚአብሔርን ቃል መራብና መጠማት (ለመስማት መትጋት) ማለት ነው። እግዚአብሔር በነቢዩ አሞጽ አድሮ “እነሆ፥ በምድር ላይ ራብን የምሰድድበት ዘመን ይመጣል፥ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም” (አሞጽ 8:11-12) በማለት የተናገረው ቃሉን መራብና መጠማትን ያመለክታል። ቅዱስ ጴጥሮስም ቃለ እግዚአብሔር ወተት እንደሆነ ሲያስተምር  “እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፥ ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ” (1ኛ ጴጥ 2:1-3) ብሏል። ቃለ እግዚአብሔር ስንል እግዚአብሔር በቃልና በነቢያት በኩል የሰጣቸውን ሕግጋት፣ የአብ ቃል የተባለና ሥጋን የተዋሐደ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስን፣ እንዲሁም እርሱ ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው ያስተማረውን ሐዋርያትም የሰበኩትን ቅዱስ ወንጌልን ያጠቃልላል።

ትጋት 3: ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መራብና መጠማት

ጽድቅን መራብና መጠማት ማለት ጽድቅ የሚገኝበትን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መራብና መጠማት ነው። ጽድቅን መራብና መጠማት ስንል ጌታችን በወንጌሉ “እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ” (ዮሐ 4:14) ያለውን ውኃ መጠማትን፣ እንዲሁም “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም” (ዮሐ 6:35) ያለውን የሕይወት እንጀራ መራብን (ለመመገብ በጽኑ መሻትን) ያመለክታል። ይህም በምሳሌ ሲገለፅ እስራኤል ዘሥጋ ሲራቡ ሰማያዊ መናን እንደበሉት፣ ሲጠሙ ከአለት የፈለቀን ውኃ እንደጠጡት ያለ ሲሆን ይህ ግን ዘላለማዊ ሕይወትን የሚሰጥ፣ አማናዊ ነው።

ጌታችን በትምህርቱ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም። ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም።ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና።ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ” (ዮሐ 6:33-56) በማለት ይህንን በአጽንኦት ተናግሯል። ቅዱስ ዮሐንስም በራዕይ “እርሱም ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው ብለህ ጻፍ አለኝ። ደግሞም። ይህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃል ነው አለኝ” (ራዕ 19:9) ብሏል።

ትጋት 4: በእግዚአብሔር ቤት መኖርን መራብና መጠማት

ጽድቅን መራብና መጠማት ማለት ሰማያዊ ሕይወትን መናፈቅ (የሰማያዊ ሕይወት ፍቅር) ነው። ይህም በእግዚአብሔር ቤት (በጸሎት) የምንኖረው መንፈሳዊ ሕይወት ነው። ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት “የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ ማደሪያዎችህ እንደምን የተወደዱ ናቸው! ነፍሴ የእግዚአብሔርን አደባባዮች ትወድዳለች ትናፍቅማለች፤ ልቤም ሥጋዬም በሕያው አምላክ ደስ ተሰኘ” (መዝ 84:1-2) በማለት በእግዚአብሔር ቤት ለመኖር መራቡን ገልጿል።  ሕይወት ወደሚገኝበት ወደ እግዚአብሔር ቤት መሄድም እንዴት ደስ እንደሚያሰኝ ሲናገር “ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሄድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ” (መዝ 122:1) ብሏል። በእውነትም “በእግዚአብሔር ቤት የሚኖሩ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው፤ ለዓለምና ለዘላለምም እርሱን ሲያመሰግኑ ይኖራሉ” (መዝ 84:5)።

በእግዚአብሔር ቤት እንደ እርሱ ፈቃድ መኖር ከሁሉም ነገር የሚበልጥ ነው። አባታችን ዳዊት ስለዚህ ሲናገር “ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች፤ በኃጥኣን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ” (መዝ 84:10) ብሏል። በእግዚአብሔር ቤት መኖርን የተራበውና የተጠማው ዳዊት የለመነው ይህንኑ ነው እንዲህ በማለት “እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ” (መዝ 27:4)። ቅዱስ ጳውሎስም ለልጁ ለጢሞቴዎስ “በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው” (1ኛ ጢሞ 3፡15) በማለት በእግዚአብሔር ቤት እንዲኖር መክሮታል።

ትጋት 5: የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማድረግን መራብና መጠማት

ጽድቅን መራብና መጠማት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ መትጋት ነው። ጌታችን በሰማርያ ሲያልፍ ደቀመዛሙርቱ ምግብ ገዝተው ካመጡ በኋላ ‘መምህር ሆይ ብላ’ ሲሉት “እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ” አላቸው። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ የሚበላው አንዳች ሰው አምጥቶለት ይሆንን? ተባባሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” (ዮሐ 4:32-34) አላቸው። እርሱ አርአያ የሆነን ክርስቲያኖችም ምግባችን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማድረግ መንፈሳዊ አገልግሎትንም መፈጸም ሊሆን ይገባል። ዕለት ዕለት መራብና መጠማት ያለብንም ይህንን ነው።

በሌላም በኩል ጽድቅን መራብ ማለት ለጽድቅ በሚያበቃ አገልግሎት መትጋት ነው። ጌታችንም ለጽድቅ አገልግሎት የሚተጉ ብፁዓን መሆናቸውን ሲናገር “ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው” (ማቴ 24:46 ሉቃ 12:43) በማለት አስተምሯል። እንዲሁም “ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ታጥቆ በማዕድ ያስቀምጣቸዋል ቀርቦም ያገለግላቸዋል። ከሌሊቱም በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንዲሁ ቢያገኛቸው፥ እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው” (ሉቃ 12:37-38) በማለት በአገልግሎት የሚተጉ፣ ሲተጉም የሚያገኛቸው ብፁዓን ናቸው ብሏል።

ትጋት 6: እውነትንና ፍትህን መራብና መጠማት

ጽድቅ እውነትና ፍትሕ ናት። ጽድቅን መራብና መጠማት ስንልም እውነትንና ፍትሕን በጽኑ መሻትን፣ ስለ እውነትና ፍትሕ ተግቶ መጸለይን እንዲሁም የእውነትና የፍትሕ ሥራን መሥራትን ያመለክታል። የክርስትና ሕይወት ለእውነትና ለፍትሕ መኖር ነው። ክርስቶስ እውነት ነውና (ዮሐ 14:6)። መጽሐፍ “እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፤ የታመነ አምላክ፥ ክፋትም የሌለበት፥ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው” (ዘዳ 32:4) እንዳለው እግዚአብሔር የእውነትና የፍትሕ አምላክ ነው። እርሱን የምናመልክም በእውነትና በፍትሕ ልንኖር ይገባል። ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት “የእግዚአብሔር ቃል ቅን ነውና ሥራውም ሁሉ በእምነት ነውና። ጽድቅንና ፍርድን ይወድዳል፤ የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች። በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ” (መዝ 33:4-6) እንዲሁም “የዙፋንህ መሠረት ጽድቅና ፍርድ ነው፤ ምሕረትና እውነት በፊትህ ይሄዳሉ” (መዝ 89:14) በማለት እንደተናገረው እግዚአብሔር የእውነት (የጽድቅ) እና የፍርድ (የፍትሕ) አምላክ ነውና እርሱን የምናምን እኛም ለእውነትና ለፍትሕ ልንተጋ ይገባናል። እንዲሁም በነቢዩ ኤርምያስ አድሮ “ፍርድንና ጽድቅን አድርጉ” (ኤር 22:3) ይለናል። በነቢዩ አሞጽም አድሮ “ፍርድ እንደ ውኃ፥ ጽድቅም እንደማይደርቅ ፈሳሽ ይፍሰስ” (አሞጽ 5:24) እንዳለው ጽድቅንና ፍትሕን ለማድረግ መትጋት ይኖርብናል።

ትጋት 7: መንግሥተ ሰማያትን መራብና መጠማት

ጽድቅን መራብና መጠማት ሲባል ዋናውና ፍጻሜው መንግሥተ ሰማያትን መሻት ነው። ጌታችንም በወንጌሉ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ” (ማቴ 6:33) ያለው ከሁሉም ማስቀደም ያለብን መንግሥቱን መፈለግን እንዲሆን ነው። እንዲሁም “ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?” (ማር 8:36) በማለት ያስተማረውም የሰው ልጅ ነፍሱን ማዳንን (ለመንግሥተ ሰማያት መብቃትን) ዓላማው እንዲያደርግ ነው። በዮሐንስ ወንጌል “በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ። ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፥ እንዲሁ እናንተ ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም። እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ። ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፥ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል። በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል ይደርቅማል፤ እነርሱንም ሰብስበው ወደ እሳት ይጥሉአቸዋል፥ ያቃጥሉአቸውማል። በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል” (ዮሐ 15:4-7) በማለት እንዳስተማረው ፍጻሜያችን የምትሆነው መንግሥተ ሰማያትን የምናገኘው በእርሱ ስንኖር ብቻ ነው።

ይጠግባሉና

ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው። ምክንያቱም ትክክለኛውንና ከሁሉ የሚበልጠውን ነገር ፈልገዋልና፣ እርሱንም ለማግኘት ተግተዋልና። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ‘ተጠማሁ’ ያለው ከሰው ልጆች አንዳች እንኳን የጽድቅ ሥራ ባለማግኘቱ ነበር (ዮሐ 19:28)። የሰው ልጆች ግን “ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ” (መዝ 69:21) እንደተባለ የጽድቅን ሥራ ሳይሆን እንደሆምጣጤ የሚመር የኃጢአትን ግብር ብቻ ይዘው ተገኙ። ይህም እግዚአብሔር ከሰው ልጆች የጽድቅን ሥራ እንደሚጠማ (እንደሚሻ)፣ የጽድቅ ሥራ ከሰው ልጆች ሲያገኝም ደስ እንደሚለው ያመለክታል። መጽሐፍ “እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና” (2ኛ ዜና 16:9) እንዳለው እግዚአብሔር ጻድቃንን ይመለከታል። ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት “የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና (መዝ 34:15)” እንዳለው እርሱ ዓይኖቹና ጆሮዎች ወደ ጻድቃን ናቸው። ጠቢቡ ሰሎሞንም “የእግዚአብሔር ዓይኖች በስፍራ ሁሉ ናቸው፤ ክፉዎችንና ደጎችን ይመለከታሉ” (ምሳሌ 15:3) በማለት እንዳስተማረን እርሱ ጽድቅን የሚራቡትን ይመለከታል። ደጉ አባታችን አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም የቁርባን ምስጋናው እግዚአብሔር ከሰው ወገን ጽድቅን ፈልጎ የምድር “ዳርቻዎችንም ሁሉ በእውነት ተመለከተ። ተነገረ አሻተተም እንደ አንቺ ያለ አላገኘም፣ የአንቺን መዓዛ ወደደ፣ ደም ግባትሽንም ወደደ፣ የሚወደውን ልጁንም ወደአንቺ ሰደደ።” (ቅዳሴ ማርያም ቁጥር 24) በማለት የጸለየው ጸሎት፣ ያመሰገነው ምስጋና ጌታችን ሁልጊዜም ከሰው ልጆች በእምነትና በጎ ምግባር የሚገለጥ የጽድቅን በጎ መዓዛ እንደሚፈልግ ያስገነዝበናል።

እግዚአብሔርን ለማግኘት ከእርሱም ጋር ለመኖር የሚራቡና የሚጠሙ (ከልብ የሚፈልጉት) ግን ያገኙታል። ስለዚህ እግዚአብሔር በማይታበል ቃሉ “ነገር ግን ከዚያ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትሻላችሁ፤ በልብህም ሁሉ በነፍስህም ሁሉ የፈለግኸው እንደ ሆነ ታገኘዋለህ” (ዘዳ 4:29) ብሏል። በነቢዩ ኤርምያስም አድሮ “እናንተ ትሹኛላችሁ፥ በፍጹም ልባችሁም ከሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ” (ኤር 29:13) በማለት በፍጹም ልባቸው የሚፈልጉት እንደሚያገኙት ተናግሯል። ተግተው የሚሹትም እንደሚያገኙት ሲናገር “እኔ የሚወድዱኝን እወድዳለሁ፥ ተግተው የሚሹኝም ያገኙኛል” (ምሳሌ 8:17) ብሏል። ቅዱስ ቃሉን ለሚራቡና ለሚጠሙም በእውነተኞቹ መምህራነ ወንጌል በኩል ያጠግባቸዋል። ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለሚራቡና ለሚጠሙም በካህናት በኩል ያጠግባቸዋል። በቤቱ (በጸሎት) መኖርን ለሚራቡም በቤቱ ያጸናቸዋል። እንደፈቃዱ መኖርን የሚራቡና የሚጠሙትንም በሃይማኖት በምግባር ያንጻቸዋል። ‘ይጠግባሉና’ ብሎ የሰጠን ቃል ኪዳን ፍጹም ዘላለማዊ ነውና።

“ይጠግባሉና” የሚለው ቃል የእግዚአብሔር ወሰን የሌለው ቸርነትንም ይገልፃል። እግዚአብሔር ሲሰጠን በብዛትና በምልዓት ነው። ጌታችን በወንጌሉ “እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ” (ዮሐ 10:10) በማለት እንዳስተማረን እርሱ የሚያስፈልገንን ያውቃልና አብዝቶ ይሰጠናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል” (ፊልጵ 4:19) እንዳለው እግዚአብሔር ጽድቅን ሲሰጥ በምልዓት ነው። እንዲሁም “እንግዲህ በእኛ እንደሚሠራው ኃይል መጠን ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ ይቻለዋል” (ኤፌ 3:20) እንደተባለ ከምንለምነው ወይም ከምናስበው በላይ አብዝቶ ሊሰጠን የታመነ ነው። ስለዚህም ጽድቅን ለሚራቡና ለሚጠሙ በሚያስፈልጋቸው ልክ ይሰጣቸዋል፣ ይጠግባሉም።

አማናዊ ምሳሌዎች

ለጽድቅ በመትጋት ቅዱሳን ነቢያት፣ ሐዋርያት አበው፣ ጻድቃንና ሰማዕታት እንዲሁም ሌሎች ብዙ ቅዱሳን ምሳሌዎች አሉን። ጌታችንም በሥጋው ወራት ጽድቅን ሁሉ በማድረግ አርአያ ሆኖናል። ለዚህ ጽሑፍ ብቻ ስንል የሚከተሉትን ጥቂት ምሳሌዎች ከአጭር ማብራሪያ ጋር አቅርበናል።

አባታችን አብርሃም: አባታችን አብርሃም እግዚአብሔርን በመፈለግ ተግቶ አገኘው። “በእግዚአብሔር አመነ፥ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት” (ዘፍ 15:6) እንዲል። ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲህ በሥጋ አባታችን የሆነ አብርሃም ምን አገኘ እንላለን? አብርሃም በሥራ ጸድቆ ቢሆን የሚመካበት አለውና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ዘንድ አይደለም። መጽሐፍስ ምን አለ? አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት” (ሮሜ 4:1-3) በማለት አስተምሯል። በተጨማሪም “እንዲሁ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ። መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ። እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ” (ገላ 3:6-9) ብሏል። በተብራራው መልእክቱም “አብርሃም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ፥ ወዴትም እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጣ። ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖሮ፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር፥ እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፤ መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና። ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደ ሆነ ስለ ቈጠረች፥ ሣራ ራስዋ ደግሞ ዕድሜዋ እንኳ ካለፈ በኋላ ዘርን ለመፅነስ ኃይልን በእምነት አገኘች። ስለዚህ ደግሞ በብዛታቸው እንደ ሰማይ ኮከብ እንደማይቈጠርም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የነበሩት የሞተን ሰው እንኳ ከመሰለው ከአንዱ ተወለዱ” (ዕብ 11:8-12)።

ክቡር ዳዊት: ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት ጽድቅን የተጠማ እንደነበር በመዝሙሩ ተናግሯል። ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ላይ “ለእስራኤል የነገሠ ዳዊት ጠላቶቹ በተነሱበት ጊዜ ከቤተልሔም ምንጭ ዉሃ ይጠጣ ዘንድ ወደደ። የጭፍሮቹ አለቆች ፈጥነዉ ተነሡና በጠላቶች ከተማ ተዋግተዉ ሊጠጣ የወደደዉን አመጡለት፡፡ ጻድቅ ዳዊት ግን ጨክነዉ ሰዉነታቸዉን ስለ እርሱ ለጦርነት ለሞት አሳልፈዉ እንደሰጡ ባየ ጊዜ ያን ዉሃ አፈሰሰ ከእርሱም አልጠጣም። ከዚህ በኋላ ለዘላለም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።” (2ኛ ሳሙ 23:15-17 1ኛ ዜና 11:17-19 ሐሙስ ወዳሴ ማርያም ቁ 6)” በማለት እንደጻፈልን አባታችን ዳዊት ውኃውን ባለመጠጣት ከእርሱ የውኃ ጥም ይልቅ ጭፍሮቹ የከፈሉትን መስዋዕትነት ዋጋ ሰጥቷል። ከምድራዊው ውኃ ጥም ይልቅ ጽድቅን በማስቀደም ከራሱ ፍላጎት ይልቅ ትህትናን፣ አክብሮትንና ለጭፍሮቹ ያለውን ፍቅር ገልጦበታል። ያመጡለት ውኃም “ደም” ስለነበር አፍስሶታል። ይህም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። ሊቃውንትም ይህንን ሲተረጉሙ ይህ ጌታችን ደሙን የማፍሰሱ ምሳሌ ነው ብለዋል።

አረጋዊ ስምዖን: አረጋዊ ሰምዖን ለጽድቅ የሚተጋ ስለነበር በምድር ላይ ብዙ ዘመናትን ኖሮ ጸሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስን አይቷል፣ በእጆቹም አቅፎታል። ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ስለዚህ “እነሆም፥ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል ሰው ነበረ፥ ይህም ሰው የእስራኤልን መጽናናት ይጠባበቅ ነበር፤ ጻድቅና ትጉህም ነበረ፥ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበረ። በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር።  በመንፈስም ወደ መቅደስ ወጣ፤ ወላጆቹም እንደ ሕጉ ልማድ ያደርጉለት ዘንድ ሕፃኑን ኢየሱስን በአስገቡት ጊዜ፥ እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀፈው እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ።  ጌታ ሆይ፥ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው። ዮሴፍና እናቱም ስለ እርሱ በተባለው ነገር ይደነቁ ነበር። ስምዖንም ባረካቸው እናቱን ማርያምንም። እነሆ፥ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ፥ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፥ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል አላት።” (ሉቃ 2:25-35) በማለት አብራርቶ ጽፎልናል።

ነቢዪት ሐና: ነቢዪት ሐና ዕድሜዋን ሙሉ በጾምና በጸሎት ለጽድቅ የተጋች ታላቅ ሴት ነበረች። በዚህም ጸሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስን በቤተ መቅደስ አግኝታዋለች፣ አመስግናዋለችም። ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ስለዚህች ታላቅ ነቢዪት ሲጽፍ “ከአሴር ወገንም የምትሆን የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች፤ እርስዋም ከድንግልናዋ ጀምራ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ኖረች፤ እርስዋም ሰማኒያ አራት ዓመት ያህል መበለት ሆና በጣም አርጅታ ነበር፤ በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ አትለይም ነበር በዚያችም ሰዓት ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር” (ሉቃ 2:36-38) በማለት ነው የገለጻት። በእውነትም ቀንና ሌሊት በቤተ መቅድስ ሆና ለጽድቅ የተጋች ነበረች። በዚህም ለቅዱሳት አንስት ሁሉ ምሳሌ ሆናለች።

ቆርነሌዎስ ጻድቅ: በዚህ ዘመን ያለን ክርስቲያኖች ለጽድቅ እንተጋ ዘንድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ሌላው ጻድቅ ቆርነሌዎስ ነው። ታሪኩም እንደሚከተለው ነው። “በቂሣርያም ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የሚሉት አንድ ሰው ነበረ። እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ ለሕዝብም እጅግ ምጽዋት የሚያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ የሚጸልይ ነበረ። ከቀኑም ዘጠኝ ሰዓት ያህል “ቆርኔሌዎስ ሆይ” የሚለው የእግዚአብሔር መልአክ ወደ እርሱ ሲገባ በራእይ በግልጥ አየው። እርሱም ትኵር ብሎ ሲመለከተው ደንግጦ:- ጌታ ሆይ፥ ምንድር ነው? አለ። መልአኩም አለው:- ጸሎትህና ምጽዋትህ በእግዚአብሔር ፊት ለመታሰቢያ እንዲሆን አረገ። አሁንም ወደ ኢዮጴ ሰዎችን ልከህ ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን አስመጣ አለው” (ሐዋ 10:1-5)። “የቆርነሌዎስ መልእክተኞችም ወደ ጴጥሮስ ሄደው:- ጻድቅ ሰው እግዚአብሔርንም የሚፈራ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ የተመሰከረለት የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ወደ ቤቱ ያስመጣህ ዘንድ ከአንተም ቃልን ይሰማ ዘንድ ከቅዱስ መልአክ ተረዳ አሉት።” (ሐዋ 10:22) ወደ ቆርነሌዎስ ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተገናኝቶ ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት (ሐዋ 10:25)።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ለአርአያነትና ለቤዛነት የሰውን ሥጋ ተዋሕዶ የተገለጠው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፀሐየ ጽድቅ፣ ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ነው። ነገር ግን እኛ ጽድቅን እንድንራብና እንድንጠማ በቃልና በተግባር አስተምሮን ፍጹም ምሳሌ ሆኖናል። በቃል “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው” ብሎ አስተምሮናል። በምድር ላይ በሚያስተምርበት ጊዜም የጽድቅን ሥራ ሁሉ ፈጽሟል። በከብቶች በረት ተወልዶ ትህትናን አስተምሯል፣ ወደ ግብፅ ተሰዶ ስደትን ባርኮልናል፣ በገዳመ ቆሮንቶስ ጾሞ ጾምን ቀድሶልናል፣ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ጥምቀትን መሥርቶልናል፣ ከድሆችና ከቀራጮች ጋር እየዋለ ወንጌልን ሰብኳል፣ ድውያነ ሥጋን በተዓምራት ድውያነ ነፍስን በትምህርት ፈውሷል፣ ለቤተ መቅደሱም በመቅናት በወንበዴዎች ላይ ጅራፍን አንስቷል፣ በመጨረሻም በመስቀል ተሰቅሎ ሥጋውን እና ደሙን ሰጥቶናል፣ በሦስተኛው ቀን ተነስቶም ለእኛ ትንሣኤ በኩር ሆኖናል። እርሱ ጽድቀን ለተራቡና ለተጠሙ ጽድቅን የሚያጠግባቸው ሲሆን እኛ ለጽድቅ ሥራ እንድንተጋ ፍጹም ምሳሌ (Supreme example) ሆኖናል።

ስለጽድቅ መራብና መጠማት

ይህ አራተኛው አንቀጸ ብፁዓን በአንዳንድ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጎሞች ‘ስለጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙ’ በማለት ተገልጿል። ይህም “ጽድቅን ለማግኘት ብለው የሚጾሙ – ከሥጋዊ ምግብና መጠጥ (ውኃ) የሚራቡና የሚጠሙ” የሚል ትርጉምን ሊሰጥ ይችላል። ተያይዞም “ይጠግባሉና” የሚለውም ለዚህ ሲሆን አሻሚ ትርጉም ሊሰጥ ይችላል። ስለጽድቅ መራብና መጠማት ያለውን ታላቅ ዋጋ ብንረዳም “ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ” የሚለው የሌሎች ኦሪየንታል አብያተ ክርስቲያናትም አስተምህሮ ስለሆነና የተሻለም ስለሚገልጽ እርሱን ተጠቅመናል። ጽድቅን መራብና መጠማት ስለጽድቅ መራብንና መጠማትንም ያጠቃልላል። ምክንያቱን ሰው ጽድቅን ሲራብና ሲጠማ ጽድቅን ለማግኘት የሚጠይቀውን ተጋድሎ ያደርጋል፣ ይህም ስለጽድቅ ብሎ መራብንና መጠማትን ይጨምራል።

ከዚህ የተነሳ የቤተ ክርስቲያን መምህራን ስለጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙ የሚለውን ትርጉም ከጾም ጋር አያይዘው ያስተምራሉ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና” (ሮሜ 14:19) በማለት እንዳስተማረው የእግዚአብሔር መንግሥት መብልና መጠጥ አይደለችም። እንዲሁም “መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላም ምንም አይጎድለንም ብንበላም ምንም አይተርፈንም” (1ኛ ቆሮ 8:8) በማለት የጾምን ዋጋ ተናግሯል። በተጨማሪም “መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል (1ኛ ቆሮ 6:13)” በማለት መጾም የጽድቅ ሥራ መሆኑን አስተምሯል። ስለዚህም ስለጽቅድ መራብና መጠማት ጽድቅን የመራብና የመጠማት አንድ አካል ነው።

መደምደሚያ

የቤተ ክርስቲያን ዋና ዓላማ የሰው ልጆችን ለጽድቅ ማብቃት ነውና የክርስትና ሕይወት ግብም ጽድቅን ማግኘት ነው። ይህም የሚፈጸመው ለጽድቅ በመትጋት ነው። ጌታችን በወንጌሉ “ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። ወይስ ከእናንተ፥ ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ሰው ነው? ዓሣስ ቢለምነው እባብን ይሰጠዋልን? እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው?” (ማቴ 7:7-11) በማለት እንዳስተማረው ጽድቅን ለሚለምኑ ይሰጣቸዋል፣ ጽድቅን የሚፈልጉ ጽድቅን ያገኛሉ፣ የጽድቅን በር የሚያንኳኩም ይከፈትላቸዋል።

ለጽድቅ የመትጋት የመጀመሪያው እርምጃ ከኃጢአት መንጻት ነው። ጤነኛ ያልሆነ ሰው የምግብ ፍላጎቱ እንደሚቀንሰውና የመራብና የመጠማት ስሜት እንደማይሰማው ሁሉ በኃጢአት የሚኖር ሰውም ጽድቅን የመራብና የመጠማቱ ነገር አነስተኛ ነው። የታመመ ሰው ምግብ ቢመገብም አይስማማውም። በኃጢአት ያለ ሰውም እንዲሁ ነው። የታመመ ሰው ሕመሙ ሲሻለው የምግብ ፍላጎቱ እንደሚመለሰው ሁሉ ኃጢአተኛ ሰውም ኃጢአቱን በንስሐ ሲያጥበው ጽድቅን ይራባል፣ ይጠማልም። ስለዚህም ጽድቅን ለመራብና ለመጠማት ከኃጢአት መለየት ያስፈልጋል። ለተራበና ለተጠማ ሰው በቀጥታ የሚያስፈልገው ምግብና ውኃ እንደሆነው ሁሉ (ያዕቆ 2:15-16) ጽድቅን ለተራበና ለተጠማም የሚያስፈልገው ለጽድቅ መትጋት ነው። የመትጋታችንም ዓላማ ጽድቅን ለማግኘት ብቻ ሊሆን ይገባዋል። ከኃጢአታችን ነጽተን፣ ጽድቅን በመራብና በመጠማት ለጽድቅ ተግተን ጽድቅን ለማግኘት ያብቃን! አሜን

1 thought on “አንቀጸ ብፁዓን ፬- ለጽድቅ መትጋት: ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና።

Leave a comment