ጌታችን አምለካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአምስተኛው አንቀጸ ብፁዓን “ምሕረትን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፥ ምሕረትን ያገኛሉና” (ማቴ 5:7) በማለት አስተምሯል። ምሕረት የርህራሄ (Compassion)፣ የቸርነት (Kindness) እና የይቅርባይነት (Forgiveness) ጥምር ናት። ርህራሄ ልባችን ለሰዎች ያለው ስሜት ሲሆን ሰዎችን መረዳትን፣ ለሰዎች ማዘንን፣ ሕመማቸውን የራሳችን ሕመም ማድረግንና ለመርዳት መነሳትን ያጠቃልላል። ቸርነት ደግሞ ያለንን (በእውነተኛ መንገድ ያገኘነውን) ሀብት፣ ዕውቀት፣ ጉልበትና የመሳሰሉትን ምንም ብድራትን ሳንሻ ለሌላቸው ማካፈልን ያመለክታል። ይቅር ባይነት ደግሞ ለበደለንና ይቅርታ ለማይገባው ይቅርታ ማድረግን፣ መጉዳት ወይም መቅጣት (ማስቀጣት) እየቻሉ መተውን ያመለክታል። ቸርነትና ይቅር ባይነት ከሩህሩህ ልብ ይመነጫሉ። ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምሕረት በሁለት እንደሚከፈል ያስተምሩናል፤ እነርሱም ምሕረት ሥጋዊና ምሕረት መንፈሳዊ ናቸው፡፡ ምሕረት ሥጋዊ ለተቸገረ ሰው የሚያስፈልገውን ነገር ማድረግ ነው፡፡ ምሕረት መንፈሳዊ ደግሞ አንድን ሰው ከኃጢአቱ ተመልሶ በንስሐ ሥርየትን ያገኝ ዘንድ መርዳት ነው፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን አየሱስ ክርስቶስ ድውያነ ሥጋን በተአምራት ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሰባት አደባባይ “ዐውደ ምሕረት” ተብላለች፣ ትርጉሙም “የምሕረት አደባባይ” ማለት ነው። ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ወንጌል የሚሰበክበት አደባባይ ወይም መድረክ በዚህ ስያሜ መጠራቱ ቤተ ክርስቲያን የምሕረት ዐውድ መሆኗን ለማሳየት ነው። አዎን! ክርስቶስ በደሙ የዋጃት ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ለሰዎች ምሕረትን የሚያደርጉባት፣ እግዚአብሔርም ለሰው ልጆች ምሕረትን የሚያድልባት ናት። የዛሬን አያድርገውና በቀደሙት አባቶቻችን ዘመንም እንዲሁ ዐውደ ምሕረት የምሕረት አደባባይ ሆና ተጠብቃለች። የምሕረት አምላክ እግዚአብሔር ዘመናችንን ሁሉ ምሕረትን የምናደርግበት፣ ምሕረትንም የምናገኝበት እንዲሆን ቅዱስ ፈቃዱ እንዲሆን እየተማጽንን በዚህች አምስተኛዋ የአንቀጸ ብፁዓን ጽሑፍ የእግዚአብሔርን መሐሪነት፣ የምሕረትን ኃይል፣ ምሕረትን በማድረግ አርአያ የሆኑንን ዋኖቻችንን እንዳስሳለን።
እግዚአብሔር የምሕረት አምላክ ነው።
እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ነው። ምሕረቱ የበዛ፣ ቁጣውም የዘገየ አምላክ ነው። ምሕረትን ማድረግ የእግዚአብሔር የባሕርዩ ነው። ለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያን “ይባእ ንጉሠ ስብሐት፣ ይባእ አምላከ ምሕረት” እያለች የምታመሰግነው። ምሕረትን ማድረግም እግዚአብሔርን መምሰል ነው። ስለዚህም ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት “እግዚአብሔር መሐሪና ይቅር ባይ ነው፥ ከቍጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ። ሁልጊዜም አይቀሥፍም፥ ለዘላለምም አይቈጣም። እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፥ እንደ በደላችንም አልከፈለንም። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ እግዚአብሔር ምሕረቱን በሚፈሩት ላይ አጠነከረ። ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፥ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ” (መዝ 103: 8-12) በማለት ተናግሯል። ነቢዩ ኤርምያስም “ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና” (ሰቆ ኤር 3:22) በማለት የምንኖረው በእግዚአብሔር ምሕረት የተነሳ እንደሆነና ለርህራሄውም ወሰን የሌለው መሆኑን ተናግሯል።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ “ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጠጋ ስለሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና” (ኤፌ 2:4-5) በማለት እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጠጋ መሆኑን አስተምሯል። እንዲሁም ለዕብራውያን ሰዎች “እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ” (ዕብ 4:16) በማለት ምሕረትን ለማግኘት ወደ እርሱ መቅረብ እንደሚገባ በመልእክቱ አስገንዝቦናል። ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል።” (1ኛ ጴጥ 1:3-5) በማለት ሁለተኛ ልደት ያገኘነው ከምሕረቱ ብዛት የተነሳ መሆኑን አስረግጦ ተናግሯል።
የእግዚአብሔር መሐሪነት በመስቀል ላይ ታይቷል። አስቀድሞ በነቢዩ በኢሳይያስ “በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው። እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።” (ኢሳ 53:4-5) እንደተባለ እርሱ ስለእኛ መከራን ተቀብሎ ምሕረትን አድሎናል። በነቢዩ በሕዝቅኤልም አድሮ “በውኑ ኃጢአተኛ ይሞት ዘንድ እፈቅዳለሁን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዱስ ይመለስና በሕይወት ይኖር ዘንድ አይደለምን?” (ሕዝ 18:23) እንዳለው ከጥፋት መንገዳችን እንመለስ ዘንድ እርሱ በመስቀል ተሰቅሎ ምሕረትን አድርጓል። የሰውን ልጅ መመለስ እንጂ መጥፋትን የማይወደው አምላክ ሰብአ ነነዌ በጾምና በጸሎት በተመለሱ ጊዜ “እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ፤ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም።” (ዮናስ 3:10) ተብሎ እንደተገለጸው ምሕረትን አድጎላቸዋል። የዚህ ሁሉ መሐሪነቱ ፍጻሜ ግን ጌታችን በመስቀል ላይ እያለ ለሰቀሉት “አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” (ሉቃ 23:34) ማለቱ ነው። እርሱም “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም” (ዮሐ 15:13) ብሎ እንዳስተማረው ለሁላችን ነፍሱን አሳልፎ በመስጠት ወዶናል።
እግዚአብሔር በንስሐ የሚቀርቡትን ሁሉ ይምራቸዋል። ልቡም በንስሐ ለሚመለሱ ይራራል። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ብዙ ሕዝብ ባየ ጊዜ፥ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና” እንዳዘነላቸው (ማቴ 9:36) ለሁላችንም ያዝንልናል። ነቢዩ ናታን ለቅዱስ ዳዊት በደሉን በነገረው ጊዜ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ምሕረቱ ብዙ ነውና በእግዚአብሔር እጅ እንውደቅ፤ በሰው እጅ ግን አልውደቅ።” (2ኛ ሳሙ 24: 14) በማለት የእግዚአብሔርን መሐሪነት ተናግሯል። በእውነትም “እግዚአብሔር ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን፥ ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ ይወዳልና” (ሆሴዕ 6:6) እኛም ምሕረትን ገንዘብ ልናደርጋት ይገባል።
እግዚአብሔር ከልብ ለለመኑት ሁሉ ምሕረትን ያደርጋል።
ጌታችን በወንጌሉ “ለምኑ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል” (ማቴ 7:7-8) እንዳለው እርሱ ከልብ ለሚለምኑት ሁሉ ምሕረትን ይሰጣልና እኛም ዘወትር በጸሎታችን ኪሪያላይሶን፣ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ እያልን እንለምነዋለን። ልበ አምላክ ክቡር ዳዊትም “አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ። ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤ እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና። አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፥ በነገርህም ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ” (መዝ 51:1-4) በማለት እንደጸለየ እኛም እርሱን አብነት አድርግን እንጸልያለን። እንዲሁም “እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ፤ አንተን በመፍራት ወደ ቅድስናህ መቅደስ እሰግዳለሁ” (መዝ 5:7) እንዳለው እኛም ምሕረቱን ሽተን ወደ መቅደሱ ማልደን እንገሰግሳለን። ወንጌላዊው ሉቃስ “ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር።” (ሉቃ18:13) ብሎ እንደጻፈው እኛም በትሕትና እንጸልያለን። ታዲያ ምሕረትን እንደዚህ ስንፈልግ እኛም የበደሉንን ይቅር እያልን (ምሕረትን እያደረግን) ሊሆን ይገባል።
እግዚአብሔር ለተበደሉት፣ ለተጨቆኑትና ለተቸገሩት ምሕረትን ያደርጋል።
እግዚአብሔር ሕዝበ እስራኤል በግብፅ ባርነት ባሉ ጊዜ የሚደርስባቸውን መከራ አይቶ “በግብፅ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፥ ከአስገባሪዎቻቸውም የተነሣ ጩኸታቸውን ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም አውቄአለሁ፤ ከግብፃውያንም እጅ አድናቸው ዘንድ፥ ከዚያችም አገር ወተትና ማር ወደምታፈስሰው አገር ወደ ሰፊይቱና ወደ መልካሚቱ አገር ወደ ከነዓናውያንም ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ስፍራ አወጣቸው ዘንድ ወረድሁ።” (ዘጸ 3:7-8) እንዳለው ዛሬም የተበደሉትን የተጨቆኑትን በመከራ ያሉትን ያያል፣ ምሕረትንም ያደርግላቸዋል። ንጉሥ ዳዊትም “ስለ ድሆች መከራ፥ ስለ ችግረኞች ጩኸት እግዚአብሔር:- አሁን እነሣለሁ ይላል፤ መድኃኒትን አደርጋለሁ፥ በላዩም እገልጣለሁ።” (መዝ 12:5) እንዳለው እግዚአብሔር ለተቸገሩት ፈጥኖ ይደርስላቸዋል።
በተጨማሪም አባታችን ዳዊት “ለተበደሉት የሚፈርድ፥ ለተራቡ ምግብን የሚሰጥ ነው። እግዚአብሔር የታሰሩትን ይፈታል፤ እግዚአብሔር የወደቁትን ያነሣል፤ እግዚአብሔር ዕውሮችን ጥበበኞች ያደርጋቸዋል፤ እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወድዳል፤ እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፤ ድሀ አደጎችንና ባልቴቶችን ይቀበላል፤ የኃጢአተኞችንም መንገድ ያጠፋል።” (መዝ 146:7-9) እንዳለው እግዚአብሔር ለተበደለው ናቡቴ “አንተም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ገድለህ ወረስኸውን? ብለህ ንገረው። ደግሞም:- እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ስፍራ የአንተን ደም ደግሞ ውሾች ይልሱታል ብለህ ንገረው።” (1ኛ ነገ 21:19) በማለት ፈርዶለታል። መርዶክዮስ እንዲሰቀል መስቀልን ያዘጋጀው ሐማም ባዘጋጀው መስቀል እንዲሰቀል ተፈርዶበት ለምስኪኑ መርዶክዮስ ግን ምሕረት ተደርጎለታል (አስቴር 7:9-10) ።
እግዚአብሔር ለደካሞች፣ ለተናቁት፣ ረዳት ለሌላቸው ምሕረትን ያደርጋል።
ቅዱስ ሉቃስ በወንጌል እንደፃፈልን በዘመኑ ከተናቁት ወገን የሆነው ቀራጭ “በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን። አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር።በዚህም ከፈሪሳዊው ይልቅ ምሕረትን አግኝቶ ወደ ቤቱ ተመለሰ።” (ሉቃ 18:13-14) እግዚአብሔር ለተናቁት ምሕረትን ያደርጋልና። ጌታችን ዘኬዎስን በዛፍ ላይ ወጥቶ ባየው ጊዜ “ዘኬዎስ ሆይ፥ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ አለው። ፈጥኖም ወረደ በደስታም ተቀበለው። ሁሉም አይተው:- ከኃጢአተኛ ሰው ጋር ሊውል ገባ ብለው አንጐራጐሩ። ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታን:- ጌታ ሆይ፥ ካለኝ ሁሉ እኵሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደ ሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ አለው። ኢየሱስም:- እርሱ ደግሞ የአብርሃም ልጅ ነውና ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል።” (ሉቃ 19:5-9) በማለት ምሕረትን አደረገለት። ረዳት የሌለው መጻጉዕም “ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” (ዮሐ 5:7) ባለው ጊዜ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ በማለት ምሕረትን አድርጎለታል።
የምሕረት ኃይል
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በትምህርቱ “ምሕረትን ማድረግ ታላቅ ጥበብ ስትሆን ለሚያደርጓትም ጋሻ ናት። እርስዋ የእግዚአብሔር ባልንጀራ ናት። ሁልጊዜ በአጠገቡ ቆማ እርሱ የወደደውን ትባርካለች። በእኛ ዘንድ በፍጹም መናቅ የለባትም። በንጽሕናዋ ለሚያደርጓት ሁሉ ታላቅ ነጻነትን ታጎናጽፋለች። ምሕረት ለተጣሉን፣ ለበደሉን ስትደረግ ደግሞ ታላቅ ኃይል ይኖራታል። እርስዋ ሰንሰለትን ትበጥሳለች፣ እሳትን ታጠፋለች፣ ትሉን ትገድላለች፣ ጥርስ ማፋጨትንም ታስወግዳለች። በእርስዋ የገነት ደጆች በቀላሉ ይከፈታሉ። በአጭሩ ምሕረትን ማድረግ ሰው እግዚአብሔርን እንዲመስል የምታደርግ ንግሥት ናት” በማለት ምሕረትን ማድረግ ሰው እግዚአብሔርን የሚመስልባት ታላቅ ጥበብ መሆኗን ተናግሯል (Chrysostom, J. Commentary on James 2:13)። እኛም ይህንን አብነት በማድረግ ዋና ዋና የሚባሉትን የምሕረት ባሕርያት ቅዱሳት መጻሕፍትን ዋቢ በማድረግ እንደሚከተለው አቅርበናል።
የምሕረት ኃይል 1: ምሕረትን ማድረግ እግዚአብሔርን የምንመስልባት ትሩፋት ናት።
እውነተኛ ክርስቲያኖች ክርስቶስን መምሰል አለብን (1ኛ ቆሮ 10:1)። ምሕረትን ማድረግ አምላካችን ክርስቶስን ልንመስልባቸው ከሚገቡ ትሩፋቶች አንዷ ናት። እግዚአብሔር ሩህሩህ፣ ቸርና ይቅር ባይ ነው። ጌታችን በወንጌሉ ምሕረትን በማድረግ እርሱን እንድንመስል “አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ ርኅሩኆች ሁኑ” (ሉቃ 6:36) በማለት አስተምሮናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።” (ኤፌሶን 4:32) በማለት ምሕረትን በማድረግ የክርስቶስን አርአያነት እንድንከተል አስተምሮናል። እግዚአብሔር ለእኛ ምሕረትን ያደረገልን ምሕረት የሚገባን ሆኖ አይደለም። ሐዋርያው ስለዚህ ሲያስተምር “እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም።” (ቲቶ 3:5) ብሏል። ስለዚህ እኛም ምሕረትን ስናደርግ ያለ ልዩነት እንደዚህ በፍጹም ርህራሄ ሊሆን ይገባል። ልበ አምላክ ዳዊትም “ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ” (መዝ 18:25) በማለት ምሕረትን ማድረግ ከሌላ ሰውም የምንማራት መሆኗን ተናግሯል።
የምሕረት ኃይል 2: ምሕረትን ማድረግ በልባችን ያለው ፍቅር መገለጫ ናት።
እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ሰው የሆነው የሰው ልጅ ምሕረትን ያገኝ ዘንድ ነው። ምሕረትን ማድረግ ለሰው ልጆችም ያለንን ፍቅር የምንገልጥባት ትሩፋት ናት። ባልንጀራችንን መውደዳችን በምን ይገለጣል ብንል በቃል ‘እውድኃለሁ’ ወይም ‘እወድሻለሁ’ በማለት አይደለም። ከልብ በመነጨ ርህራሄ፣ ቸርነትና ይቅር ባይነት እንጂ። ምሕረትን ማድረግ ምሕረት እንዲደረግልን ታደርጋለች። ይህ መውደድ ደግሞ የሚወዱንን ብቻ ሳይሆን የሚጠሉንን ጭምር መሆን እንዳለበት ጌታችን አስተምሮናል (ማቴ 5:45-47)። እርሱ ለሚሰቅሉት ጭምር ምሕረትን እንዳደረገ እኛም ያላንዳች ልዩነት ለሰው ልጆች ሁሉ ምሕረትን በማድረግ እርሱን ልንመስል ይገባናል። “ፍቅር ቸርነትን ያደርጋልና” (1ኛ ቆሮ 13:4)።
ጌታችንም ስለእውነተኛው ፍቅር ሲያስተምር “ሰዎችም ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው። የሚወዱአችሁንማ ብትወዱ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ የሚወዱአቸውን ይወዳሉና። መልካምም ለሚያደርጉላችሁ መልካም ብታደርጉ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ ያን ያደርጋሉና። እንድትወስዱባቸው ተስፋ ለምታደርጉአቸው ብታበድሩ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ በትክክል እንዲቀበሉ ለኃጢአተኞች ያበድራሉ። ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ ምንም ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፥ ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል፥ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፥ እርሱ ለማያመሰግኑ ለክፉዎችም ቸር ነውና።” (ሉቃ 6:31-35) በማለት ያስተማረው ምሕረትን ማድረግ የፍቅር መገለጫ መሆኗን ሲያረጋግጥልን ነው።
የምሕረት ኃይል 3: ምሕረትን ማድረግ በፍርድ ቀን የምንጠየቀው ነው።
ጌታችን “ነገር ግን ግብዣ ባደረግህ ጊዜ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንም ዕውሮችንም ጥራ፤ የሚመልሱት ብድራት የላቸውምና ብፁዕ ትሆናለህ፤ በጻድቃን ትንሣኤ ይመለስልሃልና” እንዳለው (ሉቃ 14:13-15) ቸርነትን ማድረግ በፍርድ ቀን የምንጠየቅበት ነው። ጻድቃን ቸርነትን ስለደረጉ ዓላም ሳይፈጠር ወደተዘጋጀችላቸው መንግሥት ይገባሉ። ስለዚህም “ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል። እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና። ጻድቃንም መልሰው ይሉታል። ጌታ ሆይ፥ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን? ንጉሡም መልሶ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል።” (25:34-40) በማለት አስተምሯል።
በግራው ያሉት ኃጥአን ደግሞ ቸርነትን ባለማድረጋቸው ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደተዘጋጀው የዘላለም እሳት ይጣላሉ። ስለዚህም ጌታችን “በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል። እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና። እነርሱ ደግሞ ይመልሱና። ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም? ይሉታል። ያን ጊዜ እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም ብሎ ይመልስላቸዋል። እነዚያም ወደ ዘላለም ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።” (ማቴ 25:41-46) በማለት ነግሮናል።
የምሕረት ኃይል 4: ምሕረትን የሚያደርግ ምሕረትን ያገኛል።
ምሕረትን የሚያደርግ የእግዚአብሔርን መሐሪነት በምግባር ይሰብካል። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትምህርቱ “በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፥ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል።” (ማቴ 7:2) እንዳለው ምሕረትን የሚያደርጉ ምሕረትን ያገኛሉ። በዚያው ትምህርቱም “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና።” (ማቴ 7:12) በማለት ምሕረት እንዲደረግልን የምንወድ ሁሉ እኛም ለሌሎች ምሕረትን ማድረግ እንዳለብን አስተምሮናል። ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት “ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፤ እግዚአብሔር በክፉ ቀን ያድነዋል። እግዚአብሔር ይጠብቀዋል፥ ሕያውም ያደርገዋል፥ በምድር ላይም ያስመሰግነዋል፥ በጠላቶቹም እጅ አያሳልፈውም።” (መዝ 41:1) ብሎ እንደተናገረው ምሕረትን ለማግኘት ምሕረትን (ቸርነትን) ማድረግ ይገባል።
ጌታችን ጸሎትን ባስተማረበት ትምህርቱ “እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን” በማለት ጸልዩ ካለ በኋላ “ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና፤ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።” (ማቴ 6:12, 14-15) በማለት ምሕረትን ማድረግ ምሕረትን ለማግኘት አስፈላጊ መሆኗን አስተምሮናል። እንዲሁም “እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፥ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፥ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፥ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ።” (ማቴ 5:23-24) በማለት ምሕረት ከመስዋዕት እንደምትቀድም አስተምሮናል።
እንዲሁም “ለጸሎትም በቆማችሁ ጊዜ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት። እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።” (ማር 11:25-26) በማለት አስተምሮናል። ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ ጌታችን ቀርቦ፦ “ጌታ ሆይ፥ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን?” ሲለው ጌታችን “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም” (ማቴ 18:21-22) በማለት ይቅርባይነታችን ምን ያህል ጊዜ መሆን እንዳለበትም (በውስን ቁጥር እንደማይገደብ) ጭምር አስተምሮናል።
ለፈሪሳውያንም “ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤ ነገር ግን ሄዳችሁ ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደ ሆነ ተማሩ፤ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና አላቸው።” (ማቴ 9:12-13) በማለት ምሕረት ከመስዋዕት እንደምትቀድም ተናግሯል። “ምሕረትን ለማያደርግ ምሕረት የሌለበት ፍርድ ይሆናልና፤ ምሕረትም በፍርድ ላይ ይሰለጥናል።” (ያዕቆ 2:13) እንደተባለም ምሕረትን የማያደርግ ምሕረትን አያገኝም።
ቅዱስ አውግስቲንም ይህን አንቀጸ ብፁዓን ባስተማረበት ትምህርቱ “አንተ ሀብት ያለህ ቢመስልህም ግን ዘላለማዊ ሕይወት ያስፈልግሀል። የሚለምንህ ሰውን ድምፅ ትሰማለህ፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት አንተም ትለምናለህ። አንተ ለሚለምንህ ሰው እንዳደረግክለት እግዚአብሔርም እንደዚያው ያደርግልሃል” ብሏል። ይህም “የኔ ቢጤ” የሚለውን አገላላጽ ያጠይቃል። ከልብ ላስተዋለው “የኔ ቢጤ” ማለት “ልክ እንደ እኔ ያለ ድሃ” ማለት ሲሆን “እኔም በምድር (ለጊዜው) ጥቂት ሀብት ቢኖረኝም ድሃ ነኝ” የሚል ልባዊ ትህትናን የሚገልጽ ስያሜ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው “የሚምሩ ብፁዓን ናቸው ይማራሉና” የሚለው የሰው ልጅ የሚያደርገው ምሕረትና እግዚአብሔር ለእርሱ የሚያደርግለት የሚወዳደር አይደለም። የሁለቱ ልዩነት በፍጹምነትና በስንፍና መካከል ያልውን ርቀት ይመስላል። የሰው ልጅ የሚያደርገው ምሕረት እጅግ ጥቂት ነው። የእግዚአብሔር ምሕረት ግን እንዲህ ነው ተብሎ የሚወሰን አይደለም። እንግዲህ የሰው ልጅ ጥቂት ምሕረትን አድርጎ እጅግ ብዙ ምሕረትን ከእግዚአብሔር ያገኛል ማለት ነው።
የምሕረት ኃይል 5: ምሕረትን የማያደርግ ምሕረትን አያገኝም፣ የተደረገለት ምሕረትም ይወሰድበታል።
ጠቢቡ ሰሎሞን “የድሀውን ጩኸት እንዳይሰማ ጆሮውን የሚደፍን ሰው፥ እርሱ ራሱ ይጮኻል አይሰማለትምም።” (ምሳ 21:13) በማለት እንደተናገረው ምሕረትን (ቸርነትን) የማያደርግ ሰው ራሱም ምሕረትን (ቸርነትን) የሚያደርግለት አያገኝም። ነዌ ለዓላዛር ቸርነትን ባለማድረጉ ለቅጣት ተዳርጓል (ሉቃ 16:19-31)። ይህ ብቻ ሳይሆን ምሕረትን ያላደረገ ሰው አስቀድሞ የተደረገለት ምሕረት ሳይቀር ይወሰድበታል። እግዚአብሔር ምሕረት የሚያደርግልን እኛም ለባልጀራችን እንደዚያው እንድናደርግ ነውና። ጌታችን ይህንን በምሳሌ ሲያስተምር “ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ባሮቹን ሊቈጣጠር የወደደን ንጉሥ ትመስላለች። መቈጣጠርም በጀመረ ጊዜ፥ እልፍ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። የሚከፍለውም ቢያጣ፥ እርሱና ሚስቱ ልጆቹም ያለውም ሁሉ እንዲሸጥና ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ። ስለዚህ ባሪያው ወድቆ ሰገደለትና:- ጌታ ሆይ፥ ታገሠኝ፥ ሁሉንም እከፍልሃለሁ አለው። የዚያም ባሪያ ጌታ አዘነለትና ለቀቀው፥ ዕዳውንም ተወለት። ነገር ግን ያ ባሪያ ወጥቶ ከባልንጀሮቹ ከባሮቹ መቶ ዲናር ዕዳ ያለበትን አንዱን አገኘና ዕዳህን ክፈለኝ ብሎ ያዘና አነቀው። ስለዚህ ባልንጀራው ባሪያ ወድቆ:- ታገሠኝ፥ ሁሉንም እከፍልሃለሁ ብሎ ለመነው። እርሱም አልወደደም፥ ግን ሄዶ ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ በወኅኒ አኖረው። ባልንጀሮቹ የሆኑ ባሮችም ያደረገውን አይተው እጅግ አዘኑ፥ መጥተውም የሆነውን ሁሉ ለጌታቸው ገለጡ። ከዚያ ወዲያ ጌታው ጠርቶ:- አንተ ክፉ ባሪያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው። ጌታውም ተቈጣና ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ ለሚሣቅዩት አሳልፎ ሰጠው። ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፥ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል።” (ማቴ 18:23-35) በማለት ገልጾታል።
የምሕረት ኃይል 6: ምሕረትን ማድረግ ሳምራዊው ከሌዋዊውም ከካህኑም እንዲመረጥ አድርጎታል።
ጌታችን ለተቸገሩት ቸርነትን ማድረግ እንደሚገባ ይህም ወደ ታላቅ መመረጥ እንደሚያደርስ በምሳሌ ሲያስተምር “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ። ድንገትም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ አይቶትም አዘነለት፥ ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቍስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፥ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደርያ ወሰደው ጠበቀውም። በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና። ጠብቀው፥ ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ አለው። እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል? እርሱም። ምሕረት ያደረገለት አለ። ኢየሱስም ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ አለው።” (ሉቃ 10:30-37) ብሏል። እንግዲህ ሳምራዊው ከካህኑም ከሌዋዊውም ይልቅ በእግዚአብሔር እንዲመረጥ ያደረገው ቸርነትን ማድረጉ ነው። ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ “ከእነርሱ ጋር እንደ ታሰረ ሆናችሁ እስሮችን አስቡ፥ የተጨነቁትንም ራሳችሁ ደግሞ በሥጋ እንዳለ ሆናችሁ አስቡ።” (ዕብ 13:3) በማለት ራሳችንን በተቸገሩት ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ቦታ አድርገን መመልከት እንዳለብን አሳስቦናል።
የምሕረት ኃይል 7: ምሕረትን የተመላች ልብ ለኃጢአተኞች ትራራለች።
ኃጢአታቸው ምንም ያህል ቢበዛ፣ ውድቀታቸውም ምንም ያህል ቢከፋ ምሕረትን የተመላች ልብ ለኃጢአተኞች ትራራለች። ጻፎችና ፈሪሳውያንም በምንዝር የተያዘችን ሴት ወደ እርሱ ባመጡና እንድትወገር እንዲፈርድ መላልሰው በጠየቁት ጊዜ በምድር ላይ በጣቶቹ ጽፎ “ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት” ነበር ያላቸው። እነርሱም ኃጢአታቸውን እያሰቡ ወጥተው በሄዱ ጊዜ “እኔም አልፈርድብሽም፤ ሂጂ ከአሁንም ጀምሮ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ።” (ዮሐ 8:11) ነበር ያላት። በዚህም እኛ እንደፈሪሳውያን ከሳሽ እና ፈራጅ ሳይሆን እንደ ጌታችን ምሕረትን የምንወድ እንድንሆን አርአያ ሆኖናል።
ወንጌላዊው ሉቃስ እንደጻፈው “ከፈሪሳውያንም አንዱ ስምዖን ጌታችንን ከእርሱ ጋር ይበላ ዘንድ ለመነው፤ ጌታችንም በስምዖን ቤት ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ። እነሆም በዚያች ከተማ ኃጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት፤ በስምዖን ቤት በማዕድ እንደ ተቀመጠ ባወቀች ጊዜ፥ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ አመጣች። በስተ ኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፥ በራስ ጠጕርዋም ታብሰው እግሩንም ትስመው ሽቱም ትቀባው ነበረች። የጠራው ስምዖንም አይቶ:- ይህስ ነቢይ ቢሆን፥ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፥ ኃጢአተኛ ናትና ብሎ በልቡ አሰበ። ጌታችንም:- ስምዖን ሆይ፥ የምነግርህ ነገር አለኝ አለው። ስምዖንም:- መምህር ሆይ፥ ተናገር አለው። ጌታችንም:- ለአንድ አበዳሪ ሁለት ተበዳሪዎች ነበሩት በአንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት በሁለተኛውም አምሳ። የሚከፍሉትም ቢያጡ ለሁለቱም ተወላቸው። እንግዲህ ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው ማንኛው ነው? ስምዖንም መልሶ:- ብዙ የተወለቱ ይመስለኛል አለ። እርሱም:- በእውነት ፈረድህ አለው። ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው:-ይህችን ሴት ታያለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፥ ውኃ ስንኳ ለእግሬ አላቀረብህልኝም፤ እርስዋ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች በጠጕርዋም አበሰች። አንተ አልሳምኸኝም፤ እርስዋ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም። አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች። ስለዚህ እልሃለሁ፥ እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል። እርስዋንም:- ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል አላት፤ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ አላት።” (ሉቃ 7:36-50)። እናንተም እንደዚሁ አድርጉ ሲል ይህንን አደረገ።
አማናዊ ምሳሌዎች
ቅዱስ ዮሴፍ: ጻዲቁ ዮሴፍ በግብፅ ምድር ታላቅ ባለስልጣን ሲሆን በጉድጓድ ለጣሉት ወደ ግብፅ ለባርነት ለሸጡት ወንድሞቹ ይቅርታና ቸርነትን አድርጓል። በመከራ ያለፈባቸውን ዘመናት ሳያስብ ይቅርታ አድርጎላቸዋል። በእጄ ወድቀዋልና ብድራቸውን ልመልስ ሳይል ቸርነትን አድርጎላቸዋል። በረሀብም እንዳይሞቱ ከግብፅ ለምግብ የሚሆን እህልን በመስጠት ነፍሳቸውን ታድጓል። የበደሉትንም ሁሉ ይቅር ብሎ ከነቤተሰቦቻቸው በግብፅ መጥተው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል (ዘፍ 50:21)።
ሊቀ ነቢያት ሙሴ: እግዚአብሔርን ለበደሉት ሕዝበ እስራኤል ምሕረትን ለምኗል። በእግዚአብሔር ፊትም ሰግዶ “አቤቱ በፊትህስ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ፥ ይህ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነውና ጌታዬ በመካከላችን ይሂድ፤ ጠማማነታችንንና ኃጢአታችንንም ይቅር በለን፥ ለርስትህም ተቀበለን (ዘፀ 34:9)” በማለት ምሕረትን ይለምን ነበር። እግዚአብሔርንም እርሱንም ለበደሉት ሕዝበ እስራኤል “ወዮ! እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋል፥ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፤ አሁን ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ።” (ዘፀ 32:32) እያለ ምሕረትን ለምኗል።
ሞአባዊቷ ሩት: ባለቤትዋንና ሁለት ልጆችዋን ያጣችውን ኑኃሚንን በመንከባከብ ተከትላትም ወደ ቤተ ልሄም በመሄድ ምሕረትን አድርጋለች። ሩት የኑኃሚንን ሐዘን ሐዘኗ በማድረግ አገሯን ሞአብን በመተው አብራት ወደ ቤተ ልሔም ሄዳለች። በዚህም ከራስዋ ይልቅ ለኑኃሚን ቅድሚያ ሰጥታለች። ኑኃሚን ሂጂ ስትላት፣ ዖርፋም ስትሄድ እርስዋ ግን እስከመጨረሻው ታምናለች። ሩት ምንም ሳይኖራት ታላቅ ምሕረትን ያደረገች ታላቅ ሴት ናት። በዚህም “እግዚአብሔር እንደ ሥራሽ ይስጥሽ፤ ከክንፉም በታች መጠጊያ እንድታገኚ በመጣሽበት በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ ደመወዝሽ ፍጹም ይሁን።” (ሩት 2:12) ለመባል በቅታለች፣ ተደርጎላታልም።
ሰራፕታዊቷ ሴት: በእስራኤል ታላቅ ረሀብ በነበረ ጊዜ “አምላክህ ሕያው እግዚአብሔርን! በማድጋ ካለው ከእፍኝ ዱቄት፥ በማሰሮም ካለው ከጥቂት ዘይት በቀር እንጀራ የለኝም፤ እነሆም፥ ገብቼ ለእኔና ለልጄ እጋግረው ዘንድ በልተነውም እንሞት ዘንድ ጥቂት እንጨት እሰበስባለሁ” በማለት ያለቻትን ጥቂት ምግብ ለነቢዩ ኤልሳዕ ያካፈለችና በረከትን ያገኘች እናት ናት (1ኛ ነገሥት 17:7-16)። ጌታችንም በትምህርቱ “ነገር ግን እውነት እላችኋለሁ፥ በኤልያስ ዘመን ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ሰማይ ተዘግቶ ሳለ በምድር ሁሉ ብርቱ ራብ በነበረ ጊዜ፥ በእስራኤል ብዙ መበለቶች ነበሩ፤ ኤልያስም በሲዶና አገር ወዳለች ወደ ሰራፕታ ወደ አንዲት መበለት እንጂ ከእነርሱ ወደ አንዲቱ አልተላከም።” (ሉቃ 4:26) በማለት ስለዚህች ሴት ተናግሯል።
ደሀዋ መበለት: ጌታችን በሚያስተምርበት ወቅት አንዲት ድሀ መበለት መጥታ አንድ ሳንቲም የሚያህሉ ሁለት ናስ ጣለች። ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፥ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ይህች ድሀ መበለት አብልጣ ጣለች፤ ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና፥ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ ጣለች።” (ማር 12:42-44) ቅዱስ ሉቃስም ይህንኑ “ዓይኑንም አንሥቶ መባቸውን በመዝገብ የሚጥሉ ባለ ጠጎችን አየ። አንዲትም ድሀ መበለት ሁለት ሳንቲም በዚያ ስትጥል አየና፡ እንዲህ አለ፦ “እውነት እላችኋለሁ፥ ይህች ድሀ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች፤ እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ እግዚአብሔር መዝገብ ጥለዋልና፤ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ ጣለች።” (ሉቃ 21:1-4) በማለት ጽፎልናል። የዚህች መበለት ምፅዋት በመጽሐፈ ስንክሳር ላይ ከ260 ጊዜ በላይ ለተጠቀሰው “ጌታ ሆይ ከብልጽግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።” ለሚለው የመማጸኛ ጸሎት መሠረት ሆኗል።
ጣቢታ/ዶርቃ: “በኢዮጴም ጣቢታ መልካም ነገር የሞላባት ምጽዋትም የምታደርግ ነበረች። በዚያም ወራት ታመመችና ሞተች፤ አጥበውም በሰገነት አኖሩአት። ልዳም ለኢዮጴ ቅርብ ናትና ደቀ መዛሙርት ጴጥሮስ በዚያ እንዳለ ሰምተው፥ ወደ እነርሱ ከመምጣት እንዳይዘገይ እየለመኑ ሁለት ሰዎች ወደ እርሱ ላኩ። ጴጥሮስም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር መጣ፤ በደረሰም ጊዜ በሰገነት አወጡት መበለቶችም ሁሉ እያለቀሱ ዶርቃ ከእነርሱ ጋር ሳለች ያደረገቻቸውን ቀሚሶችንና ልብሶችን ሁሉ እያሳዩት በፊቱ ቆሙ። ጴጥሮስም ሁሉን ወደ ውጭ አስወጥቶ ተንበርክኮም ጸለየ፥ ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ። ጣቢታ ሆይ፥ ተነሺ አላት። እርስዋም ዓይኖችዋን ከፈተች ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ተቀመጠች። እጁንም ለእርስዋ ሰጥቶ አስነሣት፤ ቅዱሳንንና መበለቶችንም ጠራ ሕያውም ሆና በፊታቸው አቆማት።” (ሐዋ 9:36-43)።
አንባ አብራም: ቁጥሩ በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከነበሩ ቅዱሳን ወገን ነው። ብዙ የምሕረት ሥራዎችን ያደረገ ቅዱስ ሲሆን ለምሳሌ ያህል ሁለቱን ብቻ እንጠቅሳለን። አንባ አብራም ኤጲስ ቆጶስነት እንደተሾመ መንበረ ጵጵስናውን ቤት ለሌላቸው፣ ወላጅ አልባ ሕፃናት፣ ድሆች እና እንግዶች መጠጊያ አደረገው። አንዲት ቀን አንዲት ድሀ ሴት ወደ እርሱ መጣች። አንባ አብራም ሊሰጣት የሚችለው ምንም ገንዘብ አልነበረውም። ነገር ግን አንድ ሰው የሰጠው አዲስ መጎናጸፊያ ነበረው። ገንዘብ የለኝም ብሎ ለሴትየዋ ይቅርታ ጠይቋት መጎናጸፊያውን ሸጣ ብሩን እንድትጠቀምበት ሰጣት። ሴትዮዋ መጎናጸፊያውን ወስዳ ልትሸጥ ወደ ገበያ ሄደች። እዚያም የመጎናጸፊያው ባለቤት አይቷት ከእርሷ ገዝቶ ለአንባ አብራም መለሰው። መጎናጸፊያውን ለአንባ አብራም ከመስጠቱ በፊት “አባቴ መጎናጸፊያውን በዚህ ክረምት ለምን አልተጠቀምክም?” አለው። አንባ አብራም መልሶ፡- “መጎናጸፊያው ከላይ አለ” በማለት መጎናጸፊያው ከእግዚአብሔር ጋር እንደሆነ ነገረው። ሰውየውም መልሶ የገዛውን መጎናጸፊያ ሰጠው። አንባ አብራምም “ለሴትየዋ የሚገባውን ዋጋ ከፍለሃታል ወይ?” አለው። ሰውየውም “አዎን” አለ።
በግብዝነት የምትደረግ ምሕረት ወደ ጽድቅ አታደርሰንም!
ምሕረትን ከልባችን ምንም ጥቅምን ሳንሻ ልናደርጋት እንደሚገባ ከላይ ተገልጿል። በዘመናችን የበቀሉ አንዳንድ አስመሳዮች ግን ድሆችን መርዳትን ራሳቸውና ድርጅቶቻቸውን ለማስተዋወቅና ከዚህም የራሳቸውን ጥቅም ለማካበት ይጠቀሙበታል። ይህ አሳፋሪ ድርጊት ነው። ሌላው ቢቀር ለድሆች ግላዊነት (privacy) ምንም ሳያስቡ የሚዲያ ማስታወቂያ ያደርጓቸዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።” (1ኛ ቆሮ 13:3) እንዳለው ያለ ፍቅር የሚደረግ ቸርነት ዋጋን አያስገኝም። ጌታችን በወንጌሉ “ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ምጽዋታችሁን በፊታቸው እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ ያለዚያ በሰማያት ባለው አባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም። እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ፥ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ በመንገድም እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ምጽዋት ስታደርግ ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።” (ማቴ 6:1-4) በማለት ከእንደዚህ አይነቱ ግብዝነት እንድንርቅ አስተምሮናል። ግብዞችንም “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር።” (ማቴ 23:23) በማለት ገስጿል።
እንግዲህ እናስተውል ሰማያዊቷ ጥበብ “ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት፥ በኋላም ታራቂ፥ ገር፥ እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት፥ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት።” (ያዕቆብ 3:17) እንደተባለው እንደዚህ አይነት ግብዝነት የለባትም። ይሁን እንጂ ለውዳሴ ከንቱ የምትደረግ ቸርነት ምንም ቸርነትን ሳያደርጉ ቆሞ ከመተቸት ግን ትሻላለች። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሚያስተምርበት ወቅት አንድ ሰው ወደ እርሱ ቀርቦ ምፅዋትን እሰጣለሁ፣ ምስጋናንም (ውዳሴ ከንቱን) እሻለሁ፣ ካልተመሰገንሁ አልሰጥም ባለው ጊዜ እንዲሰጥ ፈቅዶለታል። ይህም ትምህርቱ ‘ምንም ካለመዝራት ዘርቶ አረም ቢወርሰው ይሻላል’ በሚለው ምሳሌ ተብራርቷል። ዘር ከተዘራ በኋላ ወይ አረሙ ይታረማል፣ ባይታረምም እንኳን ለዘር የምትሆን ጥቂት ፍሬ ከአረሙ መካከል ትገኛለች። በውዳሴ ከንቱ የሚዘራም እንዲሁ ነው። በሂደት ቸርነትን አድራጊው ልቡ በንስሐ ተመልሶ ውዳሴ ከንቱን ሊርቃት ይችላልና። ውጭ ቆሞ የሚተች ግን ልቡናውን ወደ ርህራሄ መመለስ ይከብደዋል። ይህ ማለት ግን ውዳሴ ከንቱን እናበረታታ ማለት ሳይሆን ቢያንስ መስጠትን እንለማመድ ለማለት የተሰጠ ምክር ነው።
መደምደሚያ
ምሕረትን ማድረግ በንድፈ ሀሳብ (theory) ደረጃ የምናውቃት ብቻ ሳይሆን በአቅማችን ልናደርጋት የሚገባን ትሩፋት መሆን አለባት። ሌሎች እንዲያደርጓት የምንመክራት ብቻ ሳይሆን ራሳችን ገንዘብ አድርገናት ለሌሎች ምሳሌ የምንሆንባት ናት። ምሕረት በእምነት፣ በተስፋ እና በፍቅር የምናደርጋት እንጂ በዚህ ዓለም ታይቶ ለሚጠፋ ርካሽ ተወዳጅነት የምናደርጋት business strategy አይደለችም። እኛ ለምናደርጋት ምሕረት ምሳሌ ማድረግ ያለብንም እውነተኛውን የምሕረት አምላክ ክርስቶስን እና እርሱን የተከተሉትን ቅዱሳንን እንጂ ታዋቂ ሰዎችን አይደለም። ቸርነትንም የምናደርገው በልባችን ካለ ርህራሄ እንጂ በማስታወቂያ ብዛት ወይም በሰዎች ውትወታ መሆን የለበትም። ቤተ ክርስቲያንም እንደ ተቋም የድሆች መጠጊያነቷ የሚገለጠው ቸርነትን በማድረግ ጭምር እንጂ ቸርነትን አድርጉ ብሎ በማስተማር ብቻ አይደለም።
አባቶቻችን ስለ ምጽዋት ሲያስተምሩ “ምጽዋትን ማድረግ ለእግዚአብሔር እንደማበደር ነው።” ይላሉ (ምሳሌ 19:17)። እርሱም ብድራቱን በብዙ እጥፍ አድርጎ ይመልሳልና። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም “ምፅዋት መስጠት ተአምር ከመሥራት ይበልጣል። በክርስቶስ ስም ሙት ከማስነሳት በክርስቶስ ስም የተራበን ማብላት ይበልጣል። ተአምር ስትሠራ አንተ የፈጣሪ ተበዳሪ ትሆናለህ። ምፅዋት ስት ሰጥ ግን አንተ ለፈጣሪ እያበደርክ ነው” በማለት ገልጾታል። ይህም ጌታችን በወንጌሉ “ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና።” (ማቴ 6:19-21) ያለውን መሠረት ያደረገ ትምህርት ነው። እንግዲህ ልባችን በሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንዲሆን መዝገባችንን በሰማያት በእግዚአብሔር ዘንድ እናድርግ። እግዚአብሔር የሚያየው የምፅዋታችንን አይነትና ብዛት ሳይሆን የልባችንን ርህራሄ ነው። የምንሰጠው ባይኖረን “እግዚአብሔር ይስጥልን” ብንል የልባችንን ርህራሄ አይቶ እርሱ ይሰጥልናል። ለተቸገረ ሁሉ ለመስጠት ስለማንችል ጊዜ የማይሰጥ ችግር ያለባቸውን እናስቀድም። ቸርነትን ማድረግ ከቤታችን፣ ከቤተ ክርስቲያናችን፣ ከጎረቤቶቻችን እንጀምር። በፍትሐ ነገሥቱ (አንቀጽ 11 ቁጥር 452) ላይ “መድን በሌለበት ቦታ ገንዘብህን አትበትን” እንደተባለ ቸርነትን የምናደርገው ለሰው በሚጠቅም ነገር ላይ ሊሆን ይገባል። ይህም እግዚአብሔር ለሰው የሚጠቅመውን፣ የሚበጀውን እንደሚያደርግለት ነው።
እንግዲህ “ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው።” (ምሳ 3:3) እንደተባለ ምሕረትን እናገኝ ዘንድ እኛም ጭካኔን አስወግደን ለበደሉን ምሕረት ማድረግን፣ ለተቸገሩት ቸርነት ማድረግን ገንዘብ እናድርግ። የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፣ ይማራሉና የሚለው የተስፋ ቃል ዘላለማዊ ነውና። ልበ አምላክ ክቡር ዳዊትም በመዝሙሩ “ቸርነትህና ምሕረትህ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ይከተሉኛል፥ በእግዚአሔርም ቤት ለዘላለም እኖራለሁ።” (መዝ 23:6) እንዳለው የእግዚአብሔር ምሕረት እንድትከተለን ምሕረት ማድረግን ገንዘብ እናድርግ። ዘወትርም “በረከተ እዴከ ቅድስት እንተ ምልዕተ ምሕረት ኪያሃ ንሴፎ ኩልነ፤ እምኩሉ ምግባረ አኩይ አግኀሰነ ወውስተ ከሉ ምግባረ ሰናይ ደምረነ፤ ቡሩክ ዘወሀበነ ሥጋሁ ቅዱስ ወደሙ ክቡረ /ምሕረትን የተመላች ክብርት የምትሆን የአጅህን በረከት ሁላችን ተስፋ አናደርጋለን፤ ከክፉ ሥራ ሁሉ ኣርቀን፤ በበጎውም ሥራ ሁሉ አንድ አድርገን፤ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙንም የሰጠን ብሩክ ነው/ (መጽሐፈ ቅዳሴ)” እያልን የእግዚአብሔርን ምሕረት እንጠይቅ። የለመኑትን የማይነሳ የነገሩትን የማይረሳ አምላክ ምሕረት ማድረግን በልባችን ያኑርልን፣ ምሕረቱንም ያብዛልን። አሜን!