አንቀጸ ብፁዓን ፮ – ንጹሕ ልቡና: ልበ ንጹሐን ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና።

ጌታችን በስድስተኛው አንቀጸ ብፁዓን “ብፁዓን ንጹሓነ ልብ፥ እስመ እሙንቱ ይሬእይዎ ለእግዚአብሔር /ልበ ንጹሐን ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና/” (ማቴ 5:8) በማለት አስተምሯል። ልብ በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ታላቅ ቦታ አለው። ልብ አጠቃላይ ውስጣዊ ሕይወትን (Internal life) የሚያመለክት ነው። ይህም ሀሳብን፣ ፍላጎትን፣ ስሜትና ፈቃድን ያጠቃልላል። ጠቢቡ ሰሎሞን “ልጄ ሆይ፥ ልብህን ስጠኝ፥ ዓይኖችህም መንገዴን ይውደዱ” (ምሳሌ 23:26) ሲል በእግዚአብሔር ፈቃድ ተጓዝ ማለቱ ነው። እንዲሁም “አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና” (ምሳሌ 4:23) ሲል ውስጣዊ (መንፈሳዊ) ሕይወትህን ጠብቅ ማለቱ ነው። ጌታችንም በወንጌሉ “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና መልካም ሰው ከልብ መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከልብ ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል።” (ሉቃ 6:45) ማለቱ ሰው በሕይወቱ ከኖረው (ከልምዱ) ተነስቶ ይናገራል ማለቱ ነው። እንዲሁም “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው።” (ማቴ 15:8) ሲል ይህ ሕዝብ በቃላት (በንግግር) ያከብረኛል፣ በተግባር የሚኖረው ሕይወት ግን ከእኔ ርቋል ማለቱ ነው። ሐዋርያው ያዕቆብም “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ።”(ያዕ 4:8) በማለት እግዚአብሔር እንዲቀርበን ልብ የተባለ ውስጣዊ ሕይወታችንን እንድናጠራ አስተምሮናል።

ንጹሕ ልብ ማለት ከኃጢአት የራቀ፣ በፍቅር፣ በቅንነት እና በታማኝነት ለእግዚአብሔር የተሰጠ ሕይወት ማለት ነው። ከሰው ልጅ ሁሉ ለንጹሕ ልብ (Purity of Heart) ፍጹም ምሳሌ የምትሆነው ቤዛዊተ ዓለም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። እርስዋ በሀልዮ፣ በነቢብ እና በገቢር ንጽሕት ናት። ስለዚህም “ንጽሕተ ንጹሐን” እንላታለን። ንጽሐ ሥጋን፣ ንጽሐ ነፍስን፣ ንጽሐ ልብን የያዘች ናትና። በዚህም የልዑል ማደሪያ ሆናለች። ፍጡራን ሊያዩት የማይቻላቸው ንጹሐ ባህርይ አምላክ ከእርስዋ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆነ። ስለዚህም ነው አባቶቻችን “ንጽሕተ ንጹሐን ከዊና ከመታቦት ዘዶር ዘሲና፣ ውስተ ቤተ መቅደስ ነበረት በድንግልና፣ ሲሳያ ሕብስተ መና ወስቴሃኒ ስቴ ፅሙና (ከንጹሐንም ንጹሕ ሁና በሲና እንደ ነበረችው ታቦት በድንግልና በቤተ መቅደስ ውስጥ ኖረች ምግቧም ሕብስተ መና መጠጧም የፀጥታ መጠጥ ነበር)” በማለት ያመሰገኗት። ቅዱስ ድዮስቆሮስም በቅዳሴው “በፈቃደ አቡሁ ወረደ፣ኀበ ማርያም ተአንገደ፤ በድንግልናሃ ንጹሕ እግዚአብሔር ተወልደ። በጎለ እንስሳ ተወድየ፣ አምኃ ንግሡ ተወፈየ፤ ወከመ ሕጻናት በከየ፣ እንዘ ይስእል እምአጥባተ እሙ ሲሳየ (በአባቱ ፈቃድ ወረደ፣ በማርያም ዘንድ፣ እንግዳ ሆነ፣ እግዚአብሔር በንጹሕ ድንግልናዋ ተወለደ። በእንስሳት በረት ተጨመረ፣ የንግሡንም እጅ መንሻ፡ ተቀበለ፣ ከእናቱ ጡቶች ምግብን እየለመነ እንደ ሕጻናት አለቀሰ)” በማለት ስለንጽሕናዋ ተናግሯል። በቀረው በምድር ላይ በኖረችባቸው ዓመታትም በንጽሕና ኖራለች። ከዚህ ቀጥሎ የልብ ንጹሕነት ዋና ዋና መገለጫዎችን እንዳስሳለን።

፩: ራስን በንስሐ ንጹሕ ማድረግ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል።” (ሮሜ 3:23) እንዳለው ሁላችን ኃጢአትን ሠርተናል፣ ንጹሕ የሆነ ልብም የለንም። ንጹሕ መሆን የሚገኘው ቅዱስ ዳዊት  “አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።” (መዝ 51:10) ብሎ እንደለመነው በንስሐ ነው። በእውነተኛ ንስሐ ለሚመለሱ ሁሉ እግዚአብሔር አዲስ (ንጹሕ) ልብ ይሰጣል።  በነቢዩ ሕዝቅኤል “የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስም ለእናንተ አድርጉ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ ምን ትሞታላችሁ? የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ።” (ሕዝ 18: 31-32) እንዳለው ንስሐ የሚገቡ አዲስ ልብን ለራሳቸው ያደርጋሉ። በተጨማሪም “ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ። አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ።” (ሕዝ 36: 25-27) እንዳለው በንስሐ ለሚታጠቡ አዲስ (ንጹሕ) ልብን ይሰጣቸዋል። በንስሐ የታጠበ ንጹሕ ልብን የያዙ ብፁዓን ናቸው፣ እግዚአብሔርን ያዩታልና።

፪: ራስን ከኃጢአት መጠበቅ

አካላዊ ንጽሕናችንን ለመጠበቅ ዕለት ዕለት መታጠብ እንደሚያስፈልገን ሁሉ የልብ ንጽሕናም ሁል ጊዜ የምንጠብቀው እንጂ የአንድ ወይም ሁለት ጊዜ ንስሐ መግባት ብቻ አይደለም። አስቀድመን እንደገለጽነው በንጹሕ ልብ እግዚአብሔርን መውደድ ይመላበታል። ስለዚህ የዚህን ዓለም ነገር ለመውደድ ቦታ የለውም። ስለዚህም ነው ሐዋርያው ያዕቆብ “አመንዝሮች ሆይ፥ ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል።” (ያዕ 4:4) በማለት ዓለምን መውደድ ከእግዚአብሔር መለየት መሆኑን የተናገረው። አዎን! ልበ ንጹሕነት ዓለምንና በዓለም ያለውን ሁሉ በመተው እግዚአብሔርን መከተል ነው። ጌታችንም በትምህርቱ “ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።” (ማቴ 10:37-38) በማለት የተናገረው ሰው ንጹሕ ልብን ይዞ በሕይወቱ ሁሉ እርሱን ይከተል ዘንድ ነው። ስለዚህ ነገር ልበ ንጹሐን ከሆኑት ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችንን “እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን?” ብሎ በጠየቀው ጊዜ “እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ።” (ማቴ 19:27-28) በማለት ነበር ቃል ኪዳን የሰጠው። እውነት ነው ሁሉን በመተው የተከተሉት ልበ ንጹሐን እግዚአብሔርን ያዩታል፤ በክብር ዙፋንም ይቀመጣሉ።

: ሕይወትን በፍቅር መምራት

ንጹሕ ልብ ስንል ከኃጢአትና ከበደል የጸዳ፣ ከጥርጥር የራቀ፣ ፍቅርን ግን የተመላ ልብ (ውስጣዊ ሕይወት) ማለታችን ነው። ንጹሕ ቤት ማለት ባዶ ቤት ማለት እንዳልሆነ ሁሉ ንጹሕ ልብ ማለትም ከኃጢአት የጸዳ ብቻ ሳይሆን ፍቅርን የተመላ ማለት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ፍቅር የሁሉ ነገር መሠረትና ፍጻሜ እንደሆነ ሲናገር “ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።” (1ኛ ቆሮ 13:3) እንዳለው ንጹሕ ልብ ማለት በፍቅር የተመላ ልብ ማለት ነው። ጌታችንም ሁለቱን ታላላቅ ሕግጋት ሲገልጽ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም። ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።” (ማቴ 22:37-38) በማለት የተናገረው በልባችን (በሕይወታችን) እነዚህ ሁለቱን የፍቅር ሕግጋት እንድንኖራቸው ነው።

አዎን በፍቅረ እግዚአብሔርና በፍቅረ ቢጽ መጽናት ብፁዕነት ነው። ጌታችን በወንጌሉ “ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው” (ሉቃ 11:28) በማለት የተናገረውም በንጹሕ ልብ ሰምተው፣ በንጹሕ ልብ ለሚተገብሩት ነው። እንዲሁም በዮሐንስ ወንጌል “ብትወዱኝ ትዕዛዛቴን ጠብቁ” (ዮሐ 14:15) እና “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት።” (ዮሐ 15:12) በማለት ያስተማረው ንጹሕ ልብ ባዶ ሳይሆን ፍቅር የመላበት መሆኑን የሚያመለክት ነው። ዮሐንስም በራዕዩ “የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው።” (ራዕ 1:3) እንዲሁም “እነሆም፥ በቶሎ እመጣለሁ። የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው አለኝ።” (ራዕ 22:7) በማለት የተናገረው ልበ ንጹሐን ቃሉን የሚሰሙትና የሚጠብቁት መሆናቸውን ያስረዳናል። ልባቸውን በንጹሕ ፍቅር (በፍቅረ እግዚአብሔርና በፍቅረ ቢጽ) እንዲመላ ያደረጉ ብፁዓን ናቸው፣ እግዚአብሔርን ያዩታልና።

: ሕይወትን በጽድቅ መምራት

አባታችን ዳዊት በመዝሙሩ “ወደ እግዚአብሔር ተራራ ማን ይወጣል? በቅድስናውስ ስፍራ ማን ይቆማል? እጆቹ የነጹ፥ ልቡም ንጹሕ የሆነ፥ ነፍሱን ለከንቱ ያላነሣ፥ ለባልንጀራውም በሽንገላ ያልማለ። እርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከትን ከመድኃኒቱ አምላክም ምሕረትን ይቀበላል።’ (መዝ 24:3-5) እንዳለው በቅድስናው ስፍራ ለመቆም ልብን ንጹሕ አድርጎ ለጽድቅ መትጋት ያስፈልጋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል።” (2ኛ ጢሞ 2:22) ብሎ ለመንፈስ ልጁ ለጢሞቴዎስ እንዳስተማረው ልበ ንጹሕነት ጽድቅን መከተል ነው። እንዲሁም “የትእዛዝ ፍጻሜ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር ነው።” (1ኛ ጢሞ 1:5) እንዳለው ጽድቅ ከንጹሕ ልብ የሚወጣ ነው። ወንጌላዊው ዮሐንስም “በእርሱ የሚኖር ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፤ ኃጢአትን የሚያደርግ ሁሉ አላየውም አላወቀውምም። ልጆች ሆይ፥ ማንም አያስታችሁ፤ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው።” (1ኛ ዮሐ 3:6-7) በማለት እንዳስተማረው ልበ ንጹሕነት ጽድቅን በማድረግ ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ነው።

፭: እግዚአብሔርን መምሰል

እግዚአብሔር ንጹሐ ባሕርይ ነው። ሥራውም ንጹሕ ነው። ንጉሥ ዳዊት “የአምላኬ መንገድ ፍጹም ነው፥ የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፥ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው።” (መዝ 18:30) እንዳለው የእግዚአብሔር ቃል ንጹሕ ነው። ንጹሕ ልብን መያዝ ንጹሕ ቃልን በመናገር እግዚአብሔርን መምሰል ነው፣ ከክፉ ሀሳብም መራቅ ነው። የከበረ ዳዊት “ልቤ መልካም ነገርን አፈለቀ፥ እኔ ሥራዬን ለንጉሥ እነግራለሁ፤ አንደበቴ እንደ ፈጣን ጸሓፊ ብርዕ ነው” (መዝ 45:1) በማለት እንደተናገረውም ንጹሕ ልብ ምሥጋናን ጨምሮ ሌሎች መንፈሳዊ ሕይወትን የሚያለመልሙ መልካም ነገሮችን ያፈልቃል። እግዚአብሔር ታጋሽ አምላክ ነው። ልበ ንጹሕነትም ትዕግስትን ገንዘብ ማድረግ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “እናንተ የቆሮንቶስ ሰዎች ሆይ፥ አፋችን ለእናንተ ተከፍቶአል ልባችንም ሰፍቶላችኋል፤ በእኛ አልጠበባችሁም በሆዳችሁ ግን ጠቦባችኋል፤ ልጆቼ እንደ መሆናችሁ ግን እላችኋለሁ፥ እናንተ ደግሞ ብድራት መልሳችሁልን ተስፋፉ።” (6:11-13) በማለት እንዳስተማረው ንጹሕ ልብ ሰፊ ነው፣ ሁሉንም ይታገሳል። ስለዚህ ክቡር ዳዊት “እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፥ እንደ በደላችንም አልከፈለንም። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ እግዚአብሔር ምሕረቱን በሚፈሩት ላይ አጠነከረ። ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፥ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ።” (መዝ 103: 10-12) እንዳለው እግዚአብሔርን የምንመስል ሁሉ ትዕግስትን ገንዘብ ልናደርግ ይገባናል። ጌታችንም በትምህርቱ “በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።” (ማቴ 5:45) እንዳለው ልበ ንጹሕነት እርሱን መምሰል ነው።

፮: የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሆን

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።” (1ኛ ቆሮ 3:16) በማለት እንዳስተማረው የክርስቲያኖች ልብ የእግዚአብሔር መቅደስ ነው። ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም ስለዚህ “ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት።” (1ኛ ጴጥ 3፥15) በማለት አስተምሯል። እንዲሁም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል። ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።” (1ኛ ቆሮ 6:18-20) በማለት የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሆነውን ልባቸውን እንዲያከብሩ አስተምሯል። በተጨማሪም “ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና እንዲሁም እግዚአብሔር ተናገረ እንዲህ ሲል:- በእነርሱ እኖራለሁ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፥ አምላካቸውም እሆናለሁ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።” (2ኛ ቆሮ 6: 16-17) ብሎ እንዳስተማረው በልባችን መቅደስ እግዚአብሔር ያድራል። በኤፌሶን መልእክቱም “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ።” (ኤፌ 2:20-22) በማለት ይህንን ልባችንን በንጽሕና እንድሠራው አስተምሮናል።

፯: ከቅዱሳት ምሥጢራት መሳተፍ

ልበ ንጹሕነት ራስን ከቅዱስ ምሥጢር ማሳተፍ ነው። ፍጹም የኃጢአት ስርየትና ለቅድስና መታተም የሚገኘው በእርሱ ነውና። ወደዚህ ምሥጢር ከመቅረባችን በፊት ግን ልባችንን በንስሐ ልናነጻው ይገባናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን ደግሞ አንሥቶ። ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ በጠጣችሁት ጊዜ ሁሉ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት። ሰው ግን ራሱን ይፈትን፥ እንዲሁም ከእንጀራው ይብላ ከጽዋውም ይጠጣ፤ ሳይገባው የሚበላና የሚጠጣ የጌታን ሥጋ ስለማይለይ ለራሱ ፍርድ ይበላልና፥ ይጠጣልምና።” (1ኛ ቆሮ 11:25-29) በማለት ልባችንን ንጹሕ በማድረግ ከዚህ ምሥጢር እንድንሳተፍ አስተምሮናል። እንዲሁም “ከአጋንንትም ጋር ማኅበረተኞች እንድትሆኑ አልወድም። የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም።” (1ኛ ቆሮ 10:19-21) በማለት ወደ ቅዱስ ምሥጢር ስንቀርብ በንጽሕና መሆን እንዳለበት አስገንዝቦናል። በቅዳሴውም ካህኑ “ንጹሕ የሆነ ከቁርባኑ ይቀበል፣ ንጹሕ ያልሆነ ግን አይቀበል” በማለት የሚያውጀው ይህንን አብነት በማድረግ ነው። ከዚህ ቅዱስ ምስጢር ስንሳተፍ ፍጹምና ዘላላማዊ የሆነ የልብ ንጽሕናን እናገኛለን።

እግዚአብሔርን ያዩታልና: እግዚአብሔርን የምናየው እንዴት ነው?

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም።” (1ኛ ጢሞ 6:16) እንዳለው እግዚአብሔርን በመለኮቱ በዓይን ያየው የለም፣ ሊያየውም የሚችል የለም። በሥጋ ዓይናችን እንኳን እግዚአብሔርን ይቅርና የፀሐይንም ክበብ ሙሉ በሙሉ ማየት አይቻለንም። ረቂቅ የሆኑ ፍጥረታትንም ማየት አይቻለንም። ጌታችን በተራራው ስብከቱ “ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና” በማለት ያስተማረው እግዚአብሔር የሚታየው በሥጋ ዓይን ሳይሆን በንጹሕ ልብ ስለሆነ ነው። በዮሐንስ ወንጌልም “የማያዩ እንዲያዩ የሚያዩም እንዳያዩ እኔ ወደዚህ ዓለም ለፍርድ መጣሁ።” (ዮሐ 9:39) በማለት ያስተማረው ስለ መንፈሳዊው እይታ (ዓይነ ልቡና) ነው። ሁሉም በሥጋ ዓይናቸው ቢያዩትም፣ ድምፁንም በጆሮአቸው ቢሰሙትም እናውቃለን ብለው የሚታበዩት ፈሪሳውያን እርሱን ባለማመናቸው ሲፈረድባቸው፣ ልባቸውን ክፍተው የሰሙትና ያመኑት ትሁታን ሐዋርያት ግን ከራሳቸውም አልፈው ለዓለም ብርሃን ሆነዋል።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው በምድር ላይ ያሉ ነገሮችን የምናየው በሥጋ ዓይናችን እንደሆነ ሁሉ እግዚአብሔርን የምናየው በልባችን (በዓይነ ልቡናችን) ነው። ነገሮችን አጥርተን ለማየት የሥጋ ዓይናችን ጤነኛ (ንጹሕ) መሆን እንደሚያስፈልገው ሁሉ እግዚአብሔርንም ለማየት ልባችን ከኃጢአት ንጹሕ መሆን ይኖርበታል። በዓይን ውስጥ ያለ ጉድፍ እይታችንን እንደሚከልለው ሁሉ በልባችን ውስጥ ያለ ኃጢአትም እግዚአብሔርን እንዳናይ የልባችንን ብርሃን ይከልላል። ልበ ንጹሐን የጽድቅን ሥራ በመሥራት ልባቸውን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያደርጉታል፣ በልባቸውም ይቀድሱታል። በዚህም ዕለት ዕለት በጸሎታቸው ያነጋግሩታል፣ በልባቸው አድሮም ጽድቅን ሲያሠራቸው ያዩታል። እኛም ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን በልባችን ያየነውና የምናየው በሚከተሉት መንገዶች ነው።

በኢየሱስ ክርስቶስ: ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።” (ዮሐ 1:18) በማለት እንደጻፈው እግዚአብሔርን ያየው የለም። እግዚአብሔርን ያየነው በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ከሐዋርያት አንዱ የሆነው ፊልጶስ “ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል” ባለ ጊዜ ጌታችን “አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ። አብን አሳየን ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል።  እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ባይሆንስ ስለ ራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ።” (ዮሐ 14: 8-11) በማለት አንድነቱን አረጋግጦልናል። ስለዚህም ነው እግዚአብሔርን አይተነዋል የምንለው። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ፣ እግዚአብሔር ነውና።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በመልእክቱ “እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው። የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው። ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል።” (ቆላ 1:15) ያለው እግዚአብሔርን ያየነው በኢየሱስ ክርስቶስ ስለሆነ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም “ይኸውም ለሕዝብ ሁሉ አይደለም ነገር ግን በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተመረጡ ምስክሮች ለሆንን ለእኛ ነው እንጂ፤ ከሙታንም ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን።” (ሐዋ 10:41) በማለት መስክሯል። በዘመኑ የነበሩት በዓይናቸው አይተውታል፣ በእግራቸውም በግብራቸውም ተከትለውታል፣ በጆሮአቸውም ሰምተውታል፣ የሰሙትንም በልባቸውም አኑረውታል፣ አብረውትም በልተዋል። እኛ ደግሞ ይህንን አምነን፣ ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን ተቀብለን እንደ እነርሱ እንሆናለን።

በሕይወታችን ባደረገልን ነገር: እግዚአብሔርን በሕይወታችን ባደረገልን ነገሮች ውስጥ በልባችን እናየዋለን። የተደረጉልን ነገሮች በራሳቸው የሆኑ ሳይሆኑ በእግዚአብሔር የተደረጉልን መሆናቸውን ስናስተውልና ስናምን እግዚአብሔርን በልባችን እናየዋለን። ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት “እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም፤ በእርሱ የሚታመን ሰው ምስጉን ነው።” (መዝ 34:8) በማለት የዘመረው ይህንን ቸርነቱን በማሰብ ነው። ጠቢቡ ሰሎሞንም “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል።” (ምሳሌ 3:5-6) እንዳለው ሕይወታችንን የሚያቀናልን እግዚአብሔር ነው። በነቢዩ ኢሳይያስም “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።” (ኢሳ 41:10) እንዳለው በሕይወታችን የሚረዳን እርሱ ነው። በነቢዩ ኤርምያስም “ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም።” (ኤር 29:11) እንዳለው እርሱ የሚያስብልን የሰላም ሀሳብ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።” (ሮሜ 12:2) በማለት ይህንን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ፈትነን እንድናውቅ አስተምሯል። የእርሱን ፈቃድ ስናውቅ ያደረገልንንም ስናስተውል እግዚአብሔርን በልባችን እናየዋለን።

በመንፈሳዊ መገለጥ/መረዳት: ጌታችን በፊሊጶስ ቂሳርያ ሐዋርያቱን “እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?” ሲላቸው ስምዖን ጴጥሮስም “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” አለ።  “ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፥ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።” (ማቴ 16:15-19) ለቅዱስ ጴጥሮስ ይህንን ምስጢረ ተዋሕዶ በልቡ የገለጠለት እግዚአብሔር ነው። ጌታችን በሌላው ትምህርቱም “ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል።” (ዮሐ 16:13) በማለት መንፈስ ቅዱስ ነገረ እግዚአብሔርን በልባችን እንደሚገልጥልን ተናግሯል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚህ “ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደ ታወቅሁ አውቃለሁ።” (1ኛ ቆሮ 13:12) ብሏል። በተጨማሪም “የክብር አባት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እርሱን በማወቅ የጥበብንና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ እለምናለሁ። ይህም የልባችሁ ዓይኖች ሲበሩ የመጥራቱ ተስፋ ምን እንዲሆን በቅዱሳንም ዘንድ ያለው የርስት ክብር ባለ ጠግነት ምን እንዲሆን ለምናምን ከሁሉ የሚበልጥ የኃይሉ ታላቅነት ምን እንዲሆን ታውቁ ዘንድ ነው፤ ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤ ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው።” (ኤፌ 1:17-22) በማለት አስተምሯል። እንዲሁም “እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም።” (1ኛ ቆሮ 2:12) ብሏል።

በፍጥረቱ: እግዚአብሔርን በፍጥረቱ እናየዋለን። ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት “አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ እጅግ ተመሰገነ፥ ምስጋናህ በሰማዮች ላይ ከፍ ከፍ ብሎአልና።  ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ ስለ ጠላትህ፥ ጠላትንና ቂመኛን ለማጥፋት  የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችን ባየሁ ጊዜ፥ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን፥ ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?” (መዝ 8: 1-4) በማለት የእግዚአብሔርን ግሩም ፍጥረታት እያነሳ ዘምሯል። እንዲሁም “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል።” (መዝ 19:1) እያለ ፍጥረታቱ የእግዚአብሔርን ክብር እንደሚመሰክሩ ተናግሯል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና።” (ሮሜ 1:20) በማለት ፍጥረታት የእግዚአብሔር ክብር መገለጫዎች እንደሆኑ አስተምሯል።

በራዕይ በማየት/በመስማት: ብዙ ቅዱሳን ሰዎች እግዚአብሔርን በራዕይ አይተዋል፣ ድምፁንም ሰምተዋል። የኤሊ ልጆች እግዚአብሔርን በበደሉ ጊዜ እግዚአብሔር ልበ ንጹሕ የነበረውን ሳሙኤልን ጠርቶ ተናግሮት ነበር። መጽሐፍ ሁለት ጊዜ ጠርቶት ለሦስተኛ ጊዜ የጠራውን ሲገልጽ “እግዚአብሔርም መጥቶ ቆመ፥ እንደ ቀድሞውም:- ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም። ባሪያህ ይሰማልና ተናገር አለው።” (1 ሳሙ 3:1-14) ይላል። ሳውልም ከደማስቆ መንገድ ሲጠራ የእግዚአብሔርን ድምጽ ሰምቶ ነበር። ይህንንም ሲመሰክር “ስሄድም ወደ ደማስቆ በቀረብሁ ጊዜ፥ ቀትር ሲሆን ድንገት ከሰማይ ታላቅ ብርሃን በዙሪያዬ አንጸባረቀ፤በምድርም ላይ ወድቄ። ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ።እኔም መልሼ። ጌታ ሆይ፥ አንተ ማን ነህ? አልሁ። እርሱም። አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ እኔ ነኝ አለኝ። ከእኔ ጋር የነበሩትም ብርሃኑን አይተው ፈሩ፥ የሚናገረኝን የእርሱን ድምፅ ግን አልሰሙም ።”(ሐዋ 22:6-9) ብሏል።

በፈተና ውስጥ: ልበ አምላክ የተባለ ዳዊት “አጥንቶቼ ሁሉ እንዲህ ይሉሃል:- አቤቱ፥ እንደ አንተ ማን ነው? ችግረኛን ከሚቀማው እጅ፥ ችግረኛንና ድሀውንም ከሚነጥቀው እጅ ታድነዋለህ።” (መዝ 35:10) በማለት እንደተናገረው እግዚአብሔርን ድሆችን ሲረዳ፣ ችግረኞችን ከመከራ ሲታደግ እናየዋለን።  እንዲሁም “ቅዱስ ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ይላልና:- ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፥ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና።” (ሐዋ 2:25) ተብሎ እንደተነገረው እግዚአብሔር እንደ አባታችን ዳዊት ላሉ ልበ ንጹሐን በፊታቸው ነው፣ ከፈተና ሲታደጋቸው ያዩታልም።

በሌሎች ሰዎች ሕይወት: እግዚአብሔርን በሌሎች ሰዎች ሕይወት ውስጥ እናየዋለን። ለምሳሌ እግዚአብሔር በጻድቁ ኢዮብ ሕይወት ውስጥ በግልጽ ታይቷል። ልበ ንጹሕ የነበረውን ኢዮብን ሊፈትን ለመጣው ሰይጣንም እግዚአብሔር እንደተናገረው መጽሐፍ ሲገልጽ “እግዚአብሔርም ሰይጣንን:- ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም:- ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ። እግዚአብሔርም ሰይጣንን። በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም አለው። ሰይጣንም ለእግዚአብሔር እንዲህ ብሎ መለሰለት። በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን? እርሱንና ቤቱን በዙሪያውም ያሉትን ሁሉ አላጠርህለትምን? የእጁን ሥራ ባርከህለታል፥ ከብቱም በምድር ላይ በዝቶአል። ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳብስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል። እግዚአብሔርም ሰይጣንን። እነሆ ለእርሱ ያለው ሁሉ በእጅህ ነው፥ ነገር ግን በእርሱ ላይ እጅህን አትዘርጋ አለው። ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ።” (ኢዮብ 1:7-12) ይላል።

ለነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ በመድረስ: ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩት ዐሥር የቅድስና መዓርጋት አሉ። እነዚህም በሦስት ምድብ ይካተታሉ። የመጀመሪያው ንጽሐ ሥጋ ሲሆን መዓርገ ጽማዌ (በዓለም ያለውን አለመስማት፣ በእዝነ ልቡና የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ መስማት)፣  መዓርገ ልባዌ (ቃሉን ልብ ማድረግ፣ ማስተዋልና ዕውቀትን ገንዘብ ማድረግ) እና መዓርገ ጣዕመ ዝማሬን (እንደ መላእክት በመዘመር ቀንና ሌሊት እግዚአብሔርን ማመስገንን) ይይዛል። ሁለተኛው ደግሞ ንጽሐ ነፍስ ሲሆን መዓርገ አንብዕ (ክርስቶስ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር ሲል የከፈለውን መሥዋዕትነት እንዲሁም የሰውን ልጅ በደል እያሰቡ ማንባት)፣ መዓርገ ኵነኔ (ሥጋዊ ፈቃድ ለነፍስ ፈቃድ ማስገዛት)፣ መዓርገ ፍቅር (ፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅር ቢጽ በመያዝ ሁሉንም መውደድ) እና መዓርገ ሑሰትን (እንደ እግር ፀሐይ (የፀሐይ ብርሃን) ካሰቡበት ሁሉ መገኘት እና በሌላ ቦታ የሚሠራውን በአንድ ቦታ ሆኖ ማየት መቻል) ያካትታል። ሦስተኛው ንጽሐ ልቡና ሲሆን መዓርገ ንጻሬ መላእክት (መላእክትን የማየት ብቃት ወይም ደረጃ)፣ መዓርገ ተሰጥሞ (የብርሃን ውቅያኖስ በሆነ የእግዚአብሔር ጸጋ ውስጥ መስጠም) እና መዓርገ ከዊነ እሳትን (የሰውነታት በብርሃን መከበብ፤ ከእግር እስከ ራስ እሳት መምሰል) /ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ(ቅድስት ሥላሴን ማየትረጃ፤ በተዋሕዶ ከመላእክት ጋር እግዚአብሔርን ማመስገን)/ ይይዛል። በመጨረሻው መዓርገ ቅድስና የደረሱት እግዚአብሔርን ያዩታል፣ ከመላእክት ጋርም በአንድነት ያመሰግኑታል።

በትንሣኤ ዘጉባዔ: በመጨረሻው ቀንም እግዚአብሔር በግርማ መለኮት በክበበ ትስብዕት ለፍርድ ሲመጣ ሁሉም ያዩታል። ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ “እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ።” (ራዕ 1:7) በማለት እንደጻፈው በዚያን ጊዜ የወጉት ጭምር ያዩታል። በዚያን ጊዜ ያለው እግዚአብሔርን ማየት ግን በነቢዩ ሆሴዕ “ተራሮችንም። ክደኑን፥ ኮረብቶችንም ውደቁብን።” (ሆሴዕ 10:8) የሚያስብል እጅግ የሚያስፈራ ነው። “በእውነት በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነውና።” (ዕብ 10:31) በዚያን ጊዜ በፊቱ መቆም እጅግ ያስጨንቃል። አዎን በመጨረሻ ሁላችንም እግዚአብሔርን እናየዋለን። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “ጌታ ግን መንፈስ ነው፤ የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ። እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን ።” (2ኛ ቆሮ 3:17-18) በማለት እንዳስተማረው ዛሬ በመንፈስ የምናየውን ያኔ በግልጽ እናየዋለን። ከትንሣኤ ዘጉባኤ በኋላም “ጻድቃን እንደመላእክት ልበ ንጹሐን ሆነው በእግዚአብሔር መንግሥት ለዘላለም ይኖራሉ።” (ማቴ 22:30)

እግዚአብሔር የተገለጠላቸው ሰዎች እነማን ናቸው?

እግዚአብሔርን በመለኮታዊ ባህርዩ በዓይን ያየው የለም። ልጁ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተወልዶ ነገረን እንጂ። በዚህም በተዋሕዶ የተወለደውን ክርስቶስን አይተው፣ አግኝተው የተከተሉት ልበ ንጹሐን ሐዋርያት “የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው።” (ማቴ 13:16) እንዲሁም “የምታዩትን የሚያዩ ዓይኖች ብፁዓን ናቸው።”  (ሉቃ 10:23) ተብለዋል። እግዚአብሔር በሥጋ ከመገለጡ በተጨማሪ በብዙ ዘመናት ለቅዱሳን አበው፣ ለቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በተለያየ ሁኔታ ተገልጦላቸዋል። የሚከተሉትን እንደ አብነት ማየት ይቻላል።

አዳምና ሔዋን: አዳምና ሔዋን ልበ ንጹሐን እያሉ (ከመሳሳታቸው በፊት) ከእግዚአብሔር ጋር ይኖሩ ነበር። “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው።” (ዘፍ 2:7-8)። “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው። እግዚአብሔር አምላክም ሰውን እንዲህ ብሎ አዘዘው። ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።” (ዘፍ 2:15-18) “እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው። እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት።” (ዘፍ 2:21-22) ከበደሉ በኋላ ግን እግዚአብሔርን ያገኙት ፍርድን ሲሰጣቸው ነው (ዘፍ 3:1-8)።

አባታችን አብርሃም: “በቀትርም ጊዜ እርሱ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ የአድባር ዛፍ ተገለጠለት። ዓይኑንም አነሣና እነሆ፥ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ፤ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ፥ ወደ ምድርም ሰገደ፥ እንዲህም አለ። አቤቱ፥ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ፤ ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፥ እግራችሁን ታጠቡ፥ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፤ ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፥ ልባችሁንም ደግፋ ከዚያም በኋላ ትሄዳላችሁ፤ ስለዚህ ወደ ባሪያችሁ መጥታችኋልና። እነርሱም። እንዳልህ አድርግ አሉት።” (ዘፍ 18:1-15)

ጻድቁ ኢዮብ: “ምነው አሁን ቃሌ ቢጻፍ! ምነው በመጽሐፍ ውስጥ ቢታተም! ምነው በብረት ብርና በእርሳስ በዓለቱ ላይ ለዘላለም ቢቀረጽ! እኔን ግን የሚቤዠኝ ሕያው እንደ ሆነ፥ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም፥ ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ። እኔ ራሴ አየዋለሁ፥ ዓይኖቼም ይመለከቱታል፥ ከእኔም ሌላ አይደለም። ልቤ በመናፈቅ ዝሎአል (ኢዮብ 19:23-27)።” “ኢዮብም መለሰ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው። ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደ ሆንህ፥ አሳብህም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ። ያለ እውቀት ምክርን የሚሰውር ማን ነው? ስለዚህ እኔ የማላስተውለውን፥ የማላውቀውንም ድንቅ ነገር ተናግሬአለሁ። እባክህ፥ ስማኝ እኔም ልናገር፤ እጠይቅህማለሁ፥ አንተም ተናገረኝ። መስማትንስ በጆሮ በመስማት ሰምቼ ነበር፤ አሁን ግን ዓይኔ አየችህ፤ ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ፤ በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬ እጸጸታለሁ።” (ኢዮብ 42:1-6)

አባታችን ያዕቆብ: “ያዕቆብም ከቤርሳቤህ ወጥቶ ወደ ካራን ሄደ። ወደ አንድ ስፍራም ደረሰ፥ ፀሐይም ጠልቃ ነበርና ከዚያ አደረ፤ በዚያም ስፍራ ድንጋይ አነሣ፥ ከራሱም በታች ተንተርሶ በዚያ ስፍራ ተኛ። ሕልምም አለመ፤ እነሆም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ፥ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ፥ እነሆም የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበት ይወርዱበት ነበር። እነሆም፥ እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር፥ እንዲህም አለ። የአባትህ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁ፤ ዘርህም እንደ ምድር አሸዋ ይሆናል፤ እስከ ምዕራብና እስከ ምሥራቅ እስከ ሰሜንና እስከ ደቡብ ትስፋፋለህ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በአንተ በዘርህም ይባረካሉ። እነሆም እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ በምትሄድባትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፥ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና። ያዕቆብም ከእንቅልፉ ተነሥቶ። በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ነው፤ እኔ አላወቅሁም ነበር አለ። ፈራ፥ እንዲህም አለ። ይህ ስፍራ እንዴት ያስፈራ፤ ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህም የሰማይ ደጅ ነው።ዘፍ 28:10-17 ያዕቆብም፦ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፥ ሰውነቴም ድና ቀረች ሲል የዚያን ቦታ ስም ጵኒኤል ብሎ ጠራው።” (ዘፍ 32:30)

ሊቀ ነቢያት ሙሴ: “እግዚአብሔርም ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ፊት ለፊት ከሙሴ ጋር ይነጋገር ነበር። ሙሴም ወደ ሰፈሩ ይመለስ ነበር፤ ነገር ግን ሎሌው ብላቴና የነዌ ልጅ ኢያሱ ከድንኳኑ አይለይም ነበር። ሙሴም እግዚአብሔርን። እነሆ አንተ። ይህን ሕዝብ አውጣ ትለኛለህ፤ ከእኔም ጋር የምትልከውን አላስታወቅኸኝም። አንተም። በስምህ አወቅሁህ፥ ደግሞም በእኔ ፊት ሞገስን አገኘህ አልኸኝ። አሁንም በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ፥ አውቅህ ዘንድ በፊትህም ሞገስን አገኝ ዘንድ መንገድህን እባክህ አሳየኝ፤ ይህም ሕዝብ ሕዝብህ እንደ ሆነ ተመልከት አለው። እግዚአብሔርም። እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፥ አሳርፍህማለሁ አለው። እርሱም። አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ፥ ከዚህ አታውጣን። በምድርም ፊት ካለው ሕዝብ ሁሉ እኔና ሕዝብህ የተለየን እንሆን ዘንድ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህ፥ እኔና ሕዝብህ በአንተ ዘንድ ሞገስ ማግኘታችን በምን ይታወቃል? አለው።” (ዘጸ 33:11-16) “ሙሴም አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወጡ፤ ፤ የእስራኤልንም አምላክ አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ሰማይ መልክ የሚያበራ እንደ ብሩህ ሰንፔር ድንጋይ የሚመስል ወለል ነበረ።” ዘጸ (24:9-11)

ነቢዩ ሚክያስ: “ሚክያስም አለ። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። እግዚአብሔርም ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን የሚያታልል ማን ነው? አለ። አንዱም እንደዚህ፥ ሌላውም እንደዚያ ያለ ነገር ተናገረ። መንፈስም መጣ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ። እኔ አታልለዋለሁ አለ። እግዚአብሔርም በምን? አለው። እርሱም ወጥቼ በነቢያቱ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ አለ። እግዚአብሔርም ታታልለዋለህ፤ ይቀናሃል፤ ውጣ፥ እንዲህም አድርግ አለ። አሁንም፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ አፍ ሐሰተኛ መንፈስን አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በአንተ ላይ ክፉ ተናግሮብሃል።” (2ኛ ዜና 18:18-22)

ክቡር ዳዊት: “ንጉሡ ዳዊትም ገባ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ። ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ?” (2ኛ ሳሙ 7:18) “ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ፤ በቀኜ ነውና አልታወክም። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው ምላሴም ሐሴት አደረገች፤ ሥጋዬም ደግሞ በተስፋ ታድራለች፤ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም። የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን አጠገብኸኝ፥ በቀኝህም የዘላለም ፍሥሐ አለ።” (መዝ 16:8)

ንጉሥ ሰሎሞን: “ገባዖን ዋና የኮረብታ መስገጃ ነበረችና ንጉሡ ይሠዋ ዘንድ ወደዚያ ሄደ፤ ሰሎሞንም በዚያ መሠዊያ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። እግዚአብሔርም በገባዖን ለሰሎሞን በሌሊት በሕልም ተገለጠለት፤ እግዚአብሔርም። ምን እንድሰጥህ ለምን አለ። ሰሎሞንም አለ። እርሱ በፊትህ በእውነትና በጽድቅ በልብም ቅንነት ከአንተ ጋር እንደ ሄደ፥ ከባሪያህ ከአባቴ ከዳዊት ጋር ታላቅ ቸርነት አድርገሃል፤ ዛሬ እንደ ሆነም በዙፋኑ ላይ የሚቀመጥ ልጅ ሰጥተህ ታላቁን ቸርነትህን አቆይተህለታል። አሁንም፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እኔን ባሪያህን በአባቴ በዳዊት ፋንታ አንግሠኸኛል፤ እኔም መውጫንና መግቢያን የማላውቅ ታናሽ ብላቴና ነኝ። ባሪያህም ያለው አንተ በመረጥኸው ሕዝብህ ስለ ብዛቱም ይቈጠርና ይመጠን ዘንድ በማይቻል በታላቅ ሕዝብ መካከል ነው።ስለዚህም በሕዝብህ ላይ መፍረድ ይችል ዘንድ፥ መልካሙንና ክፉውንም ይለይ ዘንድ ለባሪያህ አስተዋይ ልቡና ስጠው፤ አለዚያማ በዚህ በታላቅ ሕዝብህ ላይ ይፈድ ዘንድ ማን ይችላል? ሰሎሞንም ይህን ነገር ስለ ለመነ፥ ነገሩ እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው።” (1ኛ ነገ 3:4-10)

“ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤት፥ የንጉሡን ቤትና ሰሎሞን የወደደውን የልቡን አሳብ ሁሉ ሠርቶ በፈጸመ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በገባዖን ለሰሎሞን እንደ ተገለጠለት ዳግመኛ ተገለጠለት። እግዚአብሔርም አለው። በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ ለዘላለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ። ዳዊትም አባትህ በየዋህ ልብና በቅንነት እንደ ሄደ አንተ ደግሞ በፊቴ ብትሄድ፥ ያዘዝሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ሥርዓቴንም ፍርዴንም ብትጠብቅ፥ እኔ። ከእስራኤል ዙፋን ከዘርህ ሰው አታጣም ብዬ ለአባትህ ለዳዊት እንደ ተናገርሁ፥ የመንግሥትህን ዙፋን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጸናለሁ።ኋላም ተገልጦለት የሠራውን ቤተ መቅደስ ባርኮለታል፣ ቃል ኪዳንም ሰጥቶታል።” (1ኛ ነገ 9:1-5)

ነቢዩ ኢሳይያስ: “ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፥ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር። ሱራፌልም ከእርሱ በላይ ቆመው ነበር፥ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፥ በሁለቱም ክንፍ ይበር ነበር። አንዱም ለአንዱ። ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር። የመድረኩም መሠረት ከጭዋኺው ድምፅ የተነሣ ተናወጠ፥ ቤቱንም ጢስ ሞላበት። እኔም። ከንፈሮቼ የረከሱብኝ ሰው በመሆኔ፥ ከንፈሮቻቸውም በረከሱባቸው ሕዝብ መካከል በመቀመጤ ዓይኖቼ የሠራዊትን ጌታ ንጉሡን እግዚአብሔርን ስለ አዩ ጠፍቻለሁና ወዮልኝ! አልሁ። ከሱራፌልም አንዱ እየበረረ ወደ እኔ መጣ፥ በእጁም ከመሠዊያው በጕጠት የወሰደው ፍም ነበረ። አፌንም ዳሰሰበትና። እነሆ፥ ይህ ከንፈሮችህን ነክቶአል፤ በደልህም ከአንተ ተወገደ፥ ኃጢአትህም ተሰረየልህ አለኝ።” (ኢሳ 6:1-7)

ነቢዩ ሕዝቅኤል: “በሠላሳኛው ዓመት በአራተኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን በኮቦር ወንዝ በምርኮኞች መካከል ሳለሁ ሰማያት ተከፈቱ፥ የእግዚአብሔርንም ራእይ አየሁ።” (ሕዝ 1:1) “በራሳቸውም በላይ ካለው ጠፈር በላይ የሰንፔር ድንጋይ የሚመስል የዙፋን አምሳያ ነበረ፤ በዙፋኑም አምሳያ ላይ እንደ ሰው መልክ አምሳያ ነበረ። ከወገቡም አምሳያ ወደ ላይ የሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ አየሁ፤ ከወገቡም አምሳያ ወደ ታች እንደ እሳት ምስያ አየሁ፤ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ። በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደ ቀስተ ደመና አምሳያ፥ እንዲሁ በዙሪያው ያለ ፀዳል አምሳያ ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበረ። ባየሁም ጊዜ በግምባሬ ተደፋሁ፥ የሚናገርንም ድምፅ ሰማሁ።” (ሕዝ 1:26-28) “እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ በኪሩቤል ራስ ላይ ባለው ጠፈር በላያቸው እንደ ሰንፔር ድንጋይ ያለ እንደ ዙፋን የሚመስል መልክ ተገለጠ። በፍታም የለበሰውን ሰው። በመንኰራኵሮች መካከል ከኪሩብ በታች ግባ፥ ከኪሩቤልም መካከል ካለው እሳት ፍም እጆችህን ሙላ በከተማይቱም ላይ በትናት ብሎ ተናገረው። እኔም እያየሁ ገባ።” (ሕዝ 10:1-2)

ነቢዩ ዳንኤል: “ዙፋኖችም እስኪዘረጉ ድረስ አየሁ፥ በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ፥ የራሱም ጠጕር እንደ ጥሩ ጥጥ ነበረ፤ ዙፋኑም የእሳት ነበልባል ነበረ፥ መንኰራኵሮቹም የሚነድድ እሳት ነበሩ። የእሳትም ፈሳሽ ከፊቱ ይፈልቅና ይወጣ ነበር፤ ሺህ ጊዜ ሺህ ያገለግሉት ነበር፥ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር፤ ፍርድም ሆነ፥ መጻሕፍትም ተገለጡ። የዚያን ጊዜም ቀንዱ ይናገረው ከነበረው ከታላቁ ቃል ድምፅ የተነሣ አየሁ፤ አውሬይቱም እስክትገደል፥ አካልዋም እስኪጠፋ ድረስ፥ በእሳትም ለመቃጠል እስክትሰጥ ድረስ አየሁ። ከቀሩትም አራዊት ግዛታቸው ተወሰደ፤ የሕይወታቸው ዕድሜ ግን እስከ ዘመንና እስከ ጊዜ ድረስ ረዘመ። በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።” (ዳን 7:9-14)

ነቢዮ አሞጽ: “እንዲህም አሳየኝ፤ እነሆም፥ ጌታ ቱንቢውን ይዞ በቱንቢ በተሠራ ቅጥር ላይ ቆሞ ነበር። እግዚአብሔርም አሞጽ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም ቱንቢ ነው አልሁ። ጌታም እነሆ፥ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ቱንቢ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ደግሞ አላልፋቸውም፤ የይስሐቅም የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፥ የእስራኤልም መቅደሶች ባድማ ይሆናሉ፤ በኢዮርብዓምም ቤት ላይ በሰይፍ እነሣለሁ አለ።” (አሞጽ 7:7-9) “ጌታን በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አየሁት፤ እርሱም እንዲህ አለ። መድረኮቹ ይናወጡ ዘንድ ጕልላቶቹን ምታ፥ በራሳቸውም ሁሉ ላይ ሰባብራቸው፤ እኔም ከእነርሱ የቀሩትን በሰይፍ እገድላለሁ፤ የሚሸሽ አያመልጥም፥ የሚያመልጥም አይድንም። ወደ ሲኦል ቢወርዱ እጄ ከዚያ ታወጣቸዋለች፤ ወደ ሰማይም ቢወጡ ከዚያ አወርዳቸዋለሁ፤ በቀርሜሎስም ራስ ውስጥ ቢሸሸጉ ፈልጌ ከዚያ አወጣቸዋለሁ፤ በጥልቅ ባሕርም ውስጥ ከዓይኔ ቢደበቁ ከዚያ እባቡን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይነድፋቸዋል፤ በጠላቶቻቸውም ፊት ተማርከው ቢሄዱ ከዚያ ሰይፍን አዝዛለሁ፥ እርሱም ይገድላቸዋል፤ ዓይኔንም በእነርሱ ላይ ለክፋት እንጂ ለመልካም አላደርግም።” (አሞጽ 9:1-5)

ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ያዕቆና ዮሐንስ: “ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ። እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነሆም፥ ከደመናው። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር። ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸውና። ተነሡ አትፍሩም አላቸው። ዓይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም።” (ማቴ 17:1-8)

ቅዱስ እስጢፋኖስ: አዎን ልበ ንጹሐን እግዚአብሔርን የሚያዩት ጥርጥር በሌለባት በጽንእት እምነታቸው ነው። በአይሁድ ፊት በጽንእት እምነት ቆሞ የነበረው ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ አይሁድ ሲወግሩት መንፈስ ቅዱስንም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና “እነሆ፥ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ (ሐዋ  7:54-60)። ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ “ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው። መንፈስ:- አዎን፥ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል ብለህ ጻፍ የሚል ድምፅ ሰማሁ።” (ራዕ 14:13) እንዳለው እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ በእምነታቸው ሰማዕትነትን የሚቀበሉ እግዚአብሔርን ያዩታል፣ በክብርም ይቀበላቸዋል።

ቅዱስ ጳውሎስ: “ትምክህት የሚያስፈልግ ነው፤ አይጠቅምም ነገር ግን ከጌታ ወዳለው ራእይና መገለጥ እመጣለሁ። ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም ወይም ከሥጋ ውጭ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ። እንዲህ ያለውንም ሰው አውቃለሁ፥ በሥጋ እንደ ሆነ ወይም ያለ ሥጋ እንደ ሆነ አላውቅም፥ እግዚአብሔር ያውቃል፤ ወደ ገነት ተነጠቀ፥ ሰውም ሊናገር የማይገባውን የማይነገረውን ቃል ሰማ። እንደዚህ ስላለው እመካለሁ፥ ስለ ራሴ ግን ከድካሜ በቀር አልመካም። ልመካ ብወድስ ሞኝ አልሆንም፥ እውነትን እላለሁና፤ ነገር ግን ማንም ከሚያይ ከእኔም ከሚሰማ የምበልጥ አድርጎ እንዳይቆጥረኝ ትቼአለሁ።” (2ኛ ቆሮ 12:1-6)

ቅዱስ ዮሐንስ: “ከዚያ በኋላም አየሁ፥ እነሆም በሰማይ የተከፈተ ደጅ፥ እንደ መለከትም ሆኖ ሲናገረኝ የሰማሁት ፊተኛው ድምፅ:- ወደዚህ ውጣና ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚያስፈልገውን ነገር አሳይሃለሁ አለ። ወዲያው በመንፈስ ነበርሁ፤ እነሆም፥ ዙፋን በሰማይ ቆሞአል በዙፋኑም ላይ ተቀማጭ ነበረ፤ ተቀምጦም የነበረው በመልኩ የኢያስጲድንና የሰርዲኖን ዕንቍ ይመስል ነበር። በመልኩም መረግድን የመሰለ ቀስተ ደመና በዙፋኑ ዙሪያ ነበረ። በዙፋኑ ዙሪያም ሀያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፥ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሀያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር።” (ራዕ 4:1-4)

ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው

ከሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ ሌሎቹ ሐዋርያት የጌታችንን ትንሣኤ ሲነግሩት “እጄን በተወጋ ጎኑ አስገብቼ ካላየሁ አላምንም” ብሎ ነበር። ጌታችን ዳግመኛ ተገልጦ “ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን” አለው። ቶማስም “ጌታዬ አምላኬም” ብሎ መለሰለት። ኢየሱስም “ስላየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” አለው (ዮሐ 20:27-29)። አዎን በጆሮአቸው ብቻ የእርሱን ወንጌል ሰምተው በዓይናቸው ያዩት ያህል እምነታቸው ታላቅ ሆኖ የሚገኙ ክቡራን ንዑዳን ናቸው። ስለዚህም ነው ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም “የማይደፈር ግሩም ነው፤ በእኛ ዘንድ ግን ትሁት ነው፤ የማይገኝ ልዑል ነው፤ በእኛ ዘንድ ግን አርአያ ገብርን ነሳ፤ የማይዳሰስ እሳት ነው፤ እኛ ግን አየነው ዳሰስነው ከእርሱም ጋር በላን ጠጣን” በማለት ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር እንደነበረ አድርጎ በፍጹም እምነት የተናገረው። ዛሬም ልባቸው (ውስጣዊ ሕይወታቸው) ንጹሕ የሆነ እግዚአብሔርን በእምነታቸው ዘወትር በጸሎታቸው ያዩታል። በሥራው ሲረዳቸው፣ ከፈተናም ሲጠብቃቸው ዘወትር ያዩታል። በመጨረሻም ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላቸውን መንግሥት ሲሰጣቸው ያዩታል፣ ለዘላለምም አብረውት ሲያመሰግኑት ይኖራሉ። ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና።

እግዚአብሔር መንፈስ ነውና የምናመልከውም በመንፈስና በእውነት ልናመልከው ያስፈልጋል (ዮሐ 4:24)። በእውነትና በንጽሕና ስንፈልገው ሥራውን እናስተውላለን፣ በልባችንም እናየዋለን። ልባችን በግብዝነት ከተሞላ ግን ለፈሪሳውያን “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።” (ማቴ 23:39) በማለት እንደተናገረው የምናየው በመጨረሻው ቀን ሲፈረድብን ብቻ ይሆናል። የሰው ልጆች ሆይ÷ የምንሄድበት መንገድ በሥጋዊ እይታ ንጹሕ ሊመስለን ይችል ይሆናል። የመንገዳችን ንጹሕነት በእውነት የሚመዘነው ግን ልብና ኩላሊትን በሚመረምረው በእግዚአብሔር (ቃል) ነው (ምሳ 16:2)። ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን ቃሉን በእምነት መነጽርነት እየመረመርን በተማርነውና በተረዳነው በእምነትና በምግባር ልንጸና ይገባል። የሰው ልጅ ልቡን ንጹሕ ማድረግ የሚችለው ቃሉን በማወቅና በመጠበቅ ነውና (መዝ 119:9) ቃሉን በመጠበቅ ልባችንን ንጹሕ አድርገን እግዚአብሔርን ለማየት፣ ክብሩንም ለመውረስ የተዘጋጀን ልንሆን ይገባናል። ስለዚህም ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ በቅዳሴው “ሀበነ እግዚኦ አዕይንተ አዕምሮ ወትረ ኪያከ ይርአያ። ወአዕዛንነሂ ቃለ ዘባህቲትከ ይስምአ /አቤቱ ዘወትር አንተን የሚመለከቱ የልቡናን ዓይን ስጠን። ጆሮዎቻችንም ያንተን ቃል ብቻ ይስሙ/” እንዳለው ለእኛም እርሱን የሚያዩ የልቡና ዓይኖችን ይስጠን። አሜን!

Leave a comment