አንቀጸ ብፁዓን ፯ – ፍጹም ሰላም: ሰላምን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።

ጌታችን በሰባተኛው አንቀጸ ብፁዓን “ብፁዓን ገባርያነ ሰላም፥ እስመ እሙንቱ ውሉደ እግዚአብሔር ይሰመዩ /ሰላምን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና/።” (ማቴ 5:9)” በማለት አስተምሯል። ሰላም ማለት ጸጥታ፣ እርጋታ፣ እረፍት፣ እርካታ ማለት ሲሆን በፍቅር፣ በአንድነትና በስምምነት ላይ የተመሠረተ ከእግዚአብሔር፣ ከራሳችን እና ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት ያመለክታል። በመጀመሪያ ጌዲዮን “እግዚአብሔር ሰላም ነው” (መሳ 6:24) እንዳለው እግዚአብሔር የሰላም አምላክ ነው። ሰላም አንዱ የመንፈስ ፍሬ ሲሆን መሠረቱ ፍቅር ነው (ገላ 5:22)። ቅዱስ ወንጌልም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የላከው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም የሰበከው የሰላም መልእክት ስለሆነ “የሰላም ወንጌል” ይባላል ( ሐዋ 10:36 ኤፌ 6:15)። ስለዚህም ገባርያነ ሰላም (Peacemakers) ወይም “ሰላምን የሚያደርጉ” በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደዱ የወንጌል ፍሬዎች ናቸው። ገባርያነ ሰላም በሰውና በእግዚአብሔር መካከል፣ በሰዎች መካከልና በልባቸው ከሚኖረው እግዚአብሔር ጋር፣ እንዲሁም በራሳቸው ነፍስና ሥጋ መካከል ሰላም እንዲሰፍን ይሠራሉ።

ገባርያነ ሰላም በሰዎችና በእግዚአብሔር መካከል ሰላምን የሚያሰፍኑት በመጀመሪያ በራሳቸውና በእግዚአብሔር መካከል ሰላምን አድርገው ከዚያም ሰዎች በእምነት እንዲጸኑ፣ በንስሐ እንዲመለሱና የእግዚአብሔር እንዲሆኑ በማድረግ ነው። ስለዚህ ጉዳይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን።” (2ኛ ቆሮ 5:18-20) በማለት አስተምሯል። ይህም ሰውን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበው የቅዱሳን አማላጅነት ነው።

ገባርያነ ሰላም በመጀመሪያ ራሳቸው ከሰው ጋር ሰላምን ያደርጋሉ። ከሰው ጋር ሰላምን ሳያደርጉ በሰዎች መካከል ሰላምን ማድረግ አይቻልምና። ከዚያም በሰዎች መካከል ሰላምን የሚያደርጉት በሦስት ደረጃ ነው። በመጀመሪያ ምንም አይነት አለመግባባትን ወይም ጥልን ባለመፍጠር (እንዳይፈጠር በማድረግ) ወይም ባለማባባስ ነው። ሁለተኛም ያለመግባባት ወይም የጥል ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት አስተዋጽኦ በማበርከት ነው። በመጨረሻም በሰዎች መካከል ፍቅር እንዲነግሥ በማስቻል ነው። በሰዎች መካከል የሚኖረው ሰላም በብዙ ደረጃ የሚታይ ነው። ይህም በግለሰቦች(በሁለት ሰዎች) መካከል፣ በቤተሰብ መካከል፣ በማኅበር (ማኅበረሰብ) መካከል፣ በሀገራት መካከል ሊሆን ይችላል።

ገባርያነ ሰላም በውስጣቸው በነፍስና በሥጋ መካከል ሰላምን የሚያደርጉት የራሳቸውን ሕሊና በማዳመጥ የሥጋቸው ፍላጎት ከመንፈሳዊ ሕይወታቸው ጋር እንዳይጋጭ በማድረግ ነው። ይህም የሚፈጸመው የሥጋን ፈቃድ ለነፍስ በማስገዛት ነው። የሥጋን ፈቃድ ለነፍስ ማስገዛት የሚቻለው ደግሞ በጾም፣ በጸሎት፣ በምጽዋትና በስግደት በመጽናት ነው። ቅዱስ ያሬድ  ስለጾም “ጾም ትፌውስ ቊስለ ነፍስ፤ ወታጸምም ኵሎ ፍትወታተ ዘሥጋ፤ ትሜህሮሙ ጽሙና ለወራዙት/ ጾም የነፍስን ቊስል ትፈውሳለች፤ የሥጋን ፍትወታት ሁሉ ታጠፋለች፤ ለወጣቶችም ትሕትናን ታስተምራለች” ያለው ይህንን ያስረዳናል። ይህ ውስጣዊ ሰላም የሚጸናው በእግዚአብሔር በመታመን፣ የሚያስጨንቀንንም ሁሉ በእርሱ ላይ በመጣል ነው (መዝ 4:8 1ኛ ጴጥ 5:7)። በዚህች ጽሑፍ ገባርያነ ሰላም እንዴት ለሰላም እንደሚተጉና በዚህም የእግዚአብሔር ልጆች ስለመባላቸው እንዳስሳለን።

በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ሰላምን ማድረግ

ዓለም ለሰላም የምትሠራበት መንገድና ክርስትና ሰላምን የምታደርግበት መንገድ ይለያያል። ዓለም የምታተኩረው በሰዎች መካከል ያለው ሰላም ላይ ሲሆን ይህንንም የምትፈጽመው በሰዎች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር በማድረግ፣ ግጭቶች ሲፈጠሩ በሳይንሳዊ፣ በባሕላዊና በሕጋዊ መንገድ በመፍታትና ጸጥታን በማስጠበቅ ነው። በክርስትና አስተምህሮ ግን የሰላም መሠረቱ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለው መልካም ግንኙነት ነው። በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለው ሰላም ስንል በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለው የፍጡርና የፈጣሪ፣ የልጅና የአባት፣ የአምላኪና የተመላኪ፣ የጸሎት አድራጊና የጸሎት ተቀባይ፣ የሕግ ጠባቂና የፈራጅ መልካም ግንኙነት ማለታችን ነው። በፍጡራንና በፈጣሪ መካከል የነበረው መልካም ግንኙነትን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጥል ያመራው ዲያብሎስ አምላክነትን በተመኘና አምላክ ነኝ ባለ ጊዜ ነበር።

በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለው ሰላም መሠረቱ ፍቅረ እግዚአብሔር ሲሆን ይህ ሰላም የሚናጋው የሰው ልጅ ኃጢአትን ሲሠራ ነው። በሰው ልጅና በእግዚአብሔር መካከልም ጥል የተፈጠረው የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ተላልፎ ኃጢአትን ባደረገና (ዕፀ በለስን በበላ) ከገነት በተባረረ ጊዜ ነበር። ይህም በሰው ልጆችና በእግዚአብሔር መካከል የጥል ግድግዳ እንዲፈጠር አድርጓል (ዕብ 9:3 10:19)። በዚህም በኦሪት ሥርዓት የነበረው የሚቃጠል መስዋዕት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ስለሚሆነው ሰላም ምሳሌ ነበር (ዘሌ 6:8-13)። የሚቀርበውም የደም መስዋዕት ሲሆን ለእግዚአብሔር ብቻ ነበር (ዕብ 9:22 ሮሜ 6:23)። ይህ ሁሉ መስዋዕት ጊዚያዊ ኃጢአትን ቢያስተሰርይም በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ ማፍረስ ግን አልተቻለውም (ዕብ 10:4)።

በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ ፈርሶ ሰላም የሠፈነው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በከፈለው ቤዛነት ነው። በዚህም የሐዲስ ኪዳን መካከለኛ፣ ሰው የሆነ አምላክ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከራሱ ጋር አስታርቆን በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ሰላምን አድርጓል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ መዳናችን ሲናገር “ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን።” (ሮሜ 5:10) ነው ያለው። እንዲሁም “አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።” (ኤፌ 2:13-16) በማለት ጌታችን የጥል ግድግዳውን በማፍረስ ሰላማችን መሆኑን አስተምሯል። በተጨማሪም “እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና።” (ቆላ 1:20) በማለት በደሙ ሰላምን እንዳደረገ አስተምሯል። ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርም ዘሰንበተ ክርስቲያን ላይ “ወኮነ ዓራቄ ለሐዲስ ኪዳን በውኂዘ ደሙ ቅዱስ አንጽሆሙ ለመሃይምናን ወለሕዝብ ንጹሐን/ለሐዲስ ኪዳንም አስታራቂ ሆነ በከበረ ደሙ መፍሰስ ያመኑትንና ንፁሓን የሆኑትን ህዝብ አነፃቸው/” ያለው ይህንን ያጠይቃል።

ስለዚህም በደሙ ፈሳሽነት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ሰላምን ያወረደውን ወልደ እግዚአብሔር ወልደ ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስን ዘወትር እናመሰግነዋለን። እርሱ የሰላም አለቃ ነውና (ኢሳ 9:6) “የሰላም ንጉሥ ሆይ ሰላምህን ስጠን።” እያልን እንጸልያለን። ቅዱሳን መላእክትም በእርሱ ልደት “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ / ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ።” (ሉቃ 2:14) በማለት የዘመሩት በእርሱ መወለድ ሰላም ስለሆነልን ነው። እርሱ ሰላምን ከማድረጉ በፊት በእርግማን እንኖር ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገር “በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን።” (ኤፌ 2:3) ብሏል። ቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊም “ወአርትአ እገሪነ ውስተ ፍኖተ ሰላም /እግሮቻችንን ወደ ሰላም መንገድ አቀናልን (ውዳሴ ማርያም ዘቀዳሚት ሰንበት)'” እንዳለው በእርሱ ቤዛነት ወደ ሰላም መንገድ ደርሰናል።

በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ለነበረው የጥል ግድግዳ መፍረስ ከክርስቶስ መወለድና የቤዛነት አገልግሎት በቀር ሌላ ተስፋ አልነበረም። ጌታችንም ስለዚህ “ጻድቅ አባት ሆይ፥ ዓለም አላወቀህም፥ እኔ ግን አወቅሁህ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ አወቁ፤ እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፥ ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ።” (ዮሐ 17:25-26) ብሏል። ሐዋርያው ያዕቆብም “ኃጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን፥ የኃጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ።” ( ያዕ 5:20) እንዳለው ሰውን ከኃጢአት በንስሐ መመለስ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ሰላምን መፍጠር ነው። ስለዚህም ከሁሉም በላይ እግዚአብሔር አምላከ ሰላም (የሰላም አምላክ) ተብሎ ይጠራል (ሮሜ 15:33 16:20 ፊልጵ 4:9 ዕብ 13:20 )።

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠን ሰላም ዓለም ሊሰጠን ከሚችለው እጅግ የተለየ ሰላም ነው። እርሱም “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም።” (ዮሐ 14:27) እንዳለው እርሱ የሚሰጠን ሰላም ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር በሰላም የሚያኖር ማንም ሊወስድብን የማይችል የውስጥ ሰላም ነው። ይህ ሰላም እጅግ ጥልቅና በሰው አእምሮ እንዲህ ነው ተብሎ ሊነገር የማይችል መሆኑን ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር “አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊል 4:7) በማለት ገልጾታል። ጌታችንም “በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” (ዮሐ 16:33) በማለት እንደተናገረው ይህን እውነተኛ ሰላም የምናገኘው ከእርሱ ጋር ስንኖር ነው። በፈተናም ብንሆን በዚህ ሰላም ዓለምን እናሸንፋለን። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክታቱ አብዝቶ ስለሰላም ሲጽፍ “እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ።” (ሮሜ 5:1) እንዲሁም “በአንድ አካልም የተጠራችሁለት ደግሞ የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፣ የምታመሰግኑም ሁኑ።” (ቆላ 3:15) በማለት ሰላምን እንድንይዝ፣ የክርስቶስ ሰላምም ልባችን እንዲገዛ አስተምሮናል።

በሌላ በኩል ጌታችን በወንጌሉ “በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም።” (ማቴ 10:34) በማለት ለደቀመዛሙርቱ ተናግሯል። እውነት ነው እርሱ የመጣው በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ዘላለማዊ ሰላምን ለማስፈን ነው እንጂ አይሁድ እንዳሰቡት ፖለቲካዊ ስልጣንን በመያዝ በዓለም ላይ ሁሉ ጦርነትንና ግጭትን ለማስቀረትና ምድራዊ ሰላምን ለማምጣት ወይም ከሮማውያን ቅኝ ግዛት ነፃ ለማውጣት አይደለም። እርሱ የመጣው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል።” (ዕብ 4:12) በማለት እንደገለጸው ሰይፍ የተባለ የእግዚአብሔርን ቃል (ወንጌልን) ሊያስተምረን ነው። በዚህም በሚያምኑትና በሚቃወሙት መካከል ልዩነት ሆኗል። ይህም የሚያምኑት ሰይፍ በተባለ በቅዱስ ቃሉ ሲዋጉ የሚቃወሙት ደግሞ መከራን እንደሚያጸኑባቸው የሚያስረዳ ነው።

በሰዎች መካከል ሰላምን ማድረግ

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰዎች መካከል ሰላምን አስፍኗል። በተለይም በዘመኑ በነበሩት በአይሁድና በአሕዛብ፣ እንዲሁም በአይሁድና በሰማርያ መካከል ሰላምን አድርጓል። የመንግሥት ልጆች ነን ከሚሉት ይልቅ ከአሕዛብ ወገን ለሆነውና “ቃል ብቻ ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል” ላለው መቶ አለቃ “እውነት እላችኋለሁ፥ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም።” (ማቴ 8:10 ሉቃ 7:9) በማለት የአሕዛብን እምነታቸውን አድንቋል፣ የወንጌልንም የምስራች ሰብኮላቸዋል። በሰማርያም ወንጌልን ሰብኮ (ዮሐ 4:40-43  ሉቃ 10:33) ሐዋርያቱንም በዚያ እስከዓለም ዳርቻም እንዲሰብኩ አዟቸዋል (ሐዋ 1:8 ማር 16:15 ማቴ 28:19)። በመካከላቸው ጥል የነበረው ሄሮድስና ጲላጦስ ሳይቀሩ በክርስቶስ ለመፍረድ ሲሉ በመካከላቸው (ጊዜያዊ) ሰላም (ወዳጅነት) ተፈጥሯል (ሉቃ 23:11-12)።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ። አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል…እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም።” (ኤፌ 2:12-13, 19) በማለት አሕዛብም በወንጌል ካመኑት እስራኤል ጋር በክርስቶስ አንድ መሆናቸውን አስተምሯል።

ጌታችን ከሰዎች ጋር በሰላም እንኖር ዘንድ አስተምሮናል። “ዓይን ስለ ዓይን ጥርስም ስለ ጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ። ለሚለምንህ ስጥ፥ ከአንተም ይበደር ዘንድ ከሚወደው ፈቀቅ አትበል።ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና” (ማቴ 5:38-45) በማለት ለሰላም ዋጋ መክፈል እንደሚገባን ጭምር አስተምሮናል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና። ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።” (ሮሜ 12:16-21) በማለት ከሰዎች ጋር ሁሉ በሰላም እንድንኖር አስተምሯል። እርሱም አናሲሞስ እና ፊሊሞና በባልጀርነት እንዲያገለግሉ በመካከላቸው ሰላምን አድርጓል (ፊልሞና 1:16-17)።

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በሌሎች መልእክታቱም ሰለሰላም ብዙ አስተምሯል። ለቆሮንቶስ ሰዎች “እግዚአብሔር ግን በሰላም ጠርቶናል።” (1ኛ ቆሮ 7:15) በማለት በሰላም ስለመጠራታቸው ሲናገር ለሮሜ ሰዎች ደግሞ “እንግዲያስ ሰላም የሚቆምበትን እርስ በርሳችንም የምንታነጽበትን እንከተል።” (ሮሜ 14:19) በማለት ሰላም የሚጸናበትን እንዲከተሉ መክሯል። እንዲሁም ለዕብራውያን ሰዎች “ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና።” (ዕብ 12:14) በማለት ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን እንዲከተሉ አስተምሯል። ለቆሮንቶስ ሰዎችም “ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ። ወንድሞቼ ሆይ፥ በመካከላችሁ ክርክር እንዳለ ስለ እናንተ የቀሎዔ ቤተ ሰዎች አስታውቀውኛልና።” (1ኛ ቆሮ 1:10-11) በማለት መለያየትን እንዲያስወግዱ አስተምሯል።

በብሉይ ኪዳን በዳዊትና በናባል መካከል ቁጣ በተነሳ ጊዜ በትጋቷ ሰላምን ያወረደች አቢጊያ የሰላም ፈጣሪዎች ጥሩ ምሳሌ ናት (1ኛ ሳሙ 25: 1)። አቢጊያ አእምሮዋ ታላቅ መልኳም የተዋበ ነበረች። ባለቤቷ ናባል ግን ባለጌ ነበር። ዳዊት መልእክተኞች እንዲባርኩት በላከበት ጊዜ ናባል በትዕቢት “ዳዊት ማን ነው? የእሴይስ ልጅ ማን ነው? እያንዳንዳቸው ከጌቶቻቸው የኰበለሉ ባሪያዎች ዛሬ ብዙዎች ናቸው። እንጀራዬንና የወይን ጠጄን ለሸላቾቼም ያረድሁትን ሥጋ ወስጄ ከወዴት እንደ ሆኑ ለማላውቃቸው ሰዎች እሰጣለሁን?” ብሎ ለዳዊት መልእክተኞች መለሰላቸው። የዳዊትም ቁጣ በናባል ላይ በነደደ ጊዜ አቢጊያ መጣች። ዳዊትን ባየች ጊዜ ከአህያዋ ላይ ፈጥና ወረደች፥ በዳዊትም ፊት በግምባርዋ ወደቀች፥ በምድርም ላይ እጅ ነሣች። በእግሩም ላይ ወደቀች፥ እንዲህም አለች። ጌታዬ ሆይ፥ ወደ ደም እንዳትገባ፥ እጅህም ራስህን እንዳታድን የከለከለህ እግዚአብሔር ነው፤ … የእግዚአብሔርን ጦርነት ስለምትዋጋ እግዚአብሔር በእውነት ለጌታዬ የታመነ ቤት ይሠራልና የእኔን የባሪያህን ኃጢአት፥ እባክህ፥ ይቅር በል፤ … እግዚአብሔርም ለጌታዬ የተናገረውን ቸርነት ሁሉ ባደረገልህ ጊዜ፥ በእስራኤልም ላይ አለቃ አድርጎ ባስነሣህ ጊዜ፥ አንተ በከንቱ ደም እንዳላፈሰስህ፥ በገዛ እጅህም እንዳልተካስህ ይህ ዕንቅፋትና የሕሊና ጸጸት በጌታዬ አይሆንልህም፤ እግዚአብሔርም ለጌታዬ በጎ ባደረገልህ ጊዜ፥ ባሪያህን አስብ።” ዳዊትም እግዚአብሔርንም እርስዋንም አምስግኖ ሸኛት።

በነፍስና በሥጋ መካከል ሰላምን ማድረግ

ውስጣዊ ሰላም (Internal peace) በነፍስና በሥጋ መካከል የሚኖረው ሰላም ነው። ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር ሰላምን ያደረገ ሰው ውስጣዊ ሰላም ይኖረዋል። ይህም የህሊናና የልብ ሰላም ነው። ቅዱስ ጳውሎስ “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ።” (ፊል 4:6) እንዳለው ውስጣዊ ሰላም የሚገኘው በእግዚአብሔር በማመንና በመተማመን የሚያስጨንቀንን ነገር ሁሉ ለእርሱ በጸሎት በማመልከት ነው፣ እርሱ ሊረዳን የታመነ ነውና። እንዲሁም ቅዱስ ጴጥሮስ “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።” (1ኛ ጴጥ 5:7) በማለት እንዳንጨነቅና የውስጥ ሰላማችን እንዳይናጋ አስተምሮናል። በነቢዩ ኢሳይያስ “በአንተ ታምናለችና በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ በፍጹም በሰላም ትጠብቃታለህ።” (ኢሳ 26:3) እንደተባለም በእርሱ የምትታመን ነፍስን በሰላም ይጠብቃታል።

ለውስጥ ሰላም መናጋት አንዱ ምክንያት ፍርሃት ነው። ይህም ከተለያዩ የፍርሃት ምንጮች ሊመጣ ይችላል። ክርስቲያን “ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ።” (ማቴ 10:28) እንደተባለው መፍራት ያለበት እግዚአብሔርን ብቻ ነው። በነቢዩ ኢሳይያስም “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።” (ኢሳ 41:10) እንደተባለው ክርስቲያን በእግዚአብሔር ድጋፍ መታመን እንጂ መፍራት የለበትም። ሐዋርያው “እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና” (2ኛ ጢሞ 1:7) እንዳለው በእግዚአብሔር የሚታመን አይፈራም። ልበ አምላክ ዳዊትም “በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ እነርሱ ያጸናኑኛል።” (መዝ 23:4) በማለት በእግዚአብሔር ያመነ ሰው የሚያስፈራው ምንም ነገር እንደሌለ ተናግሯል። ጌታም ሌሊት በራእይ ጳውሎስን “እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ ማንም ክፉ ሊያደርግብህ የሚነሣብህ የለምና አትፍራ፥ ነገር ግን ተናገር ዝምም አትበል፤ በዚህ ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና።” (ሐዋ 18:9-10) እንዳለው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ የሚያስፈራን አንዳች ነገር የለም።

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ።” (1ኛ ወደ ተሰ 5:23) እንዳለው በመንፈሳችን፣ በነፍሳችንና በሥጋችን መካከል ያለውን ሰላም የሚጠብቀው የሰላም አምላክ እግዚአብሔር ነውና በእርሱ እንታመን። እንዲሁም “ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም።” (ገላ 5:16-17) በማለት በሥጋና በነፍስ መካከል ያለውን ግጭት አስተምሯል።

በቅዱሳት መጻሕፍትና በትርጓሜያቸው መካከል ሰላምን ማድረግ

የእስክንድርያው ቅዱስ ቄርሎስ “ሰላምን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” የሚለውን የጌታችንን ትምህርት ሲያብራራ በቅዱሳት መጻሕፍትና በትርጓሜያቸው መካከል ሰላምን የሚያደርጉትንም እንደሚመለከት ተናግሯል። በሕግና በነቢያት መጻሕፍት መካከል፣ በሐዲስና በብሉይ መካከል፣ በአራቱ ወንጌላት መካከል፣ በመልእክታትና በወንጌል መካከል ያለውን ትርጓሜ ምስጢርን በማደላደል አስማምተው የሚያስተምሩ ሊቃውንት ብፁዓን ናቸው። በኒቂያ፣ በኤፌሶን፣ በቁስጥንጥንያ ጉባዔያት የመጻሕፍትን ትርጓሜ በማስታረቅ ሃይማኖትን ያቀኑ ቅዱሳን አበው ገባርያነ ሰላም ናቸው። እንዲሁም በንባብ ተመሳስለው በትርጓሜና በምስጢር ግን የሚለያዩትን ወገኖች በማቀራረብ በሚያመሳስሏቸው ጉዳዮች ላይ እንዲተባበሩ፣ በሚያለያዩባቸው ጉዳዮች ላይ ተከባብረው እንዲኖሩ በማድረግ ሰላምን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው። የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን በግብር መስለውታልና የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉ።

የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና

የእግዚአብሔር ልጅ መባል በእውነት ታላቅ መመረጥ ነው፣ ልጅ ወራሽ ነውና(ሮሜ 8:17)። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።” (ዮሐ 1:12-13) እንዳለው የእግዚአብሔር ልጆች በስሙ የሚያምኑና ከእግዚአብሔር የተወለዱ ናቸው። እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ከእግዚአብሔር የተወለዱትን ይወዳሉ። ወንጌላዊው ዮሐንስ ስለዚህ “ክርስቶስ ነው ብሎ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፥ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል። እግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድ በዚህ እናውቃለን።” (1ኛ ዮሐ 5:1-2) ብሏል። እግዚአብሔር ለልጆቹ የሰጠው ተስፋም ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥተው ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርሱ ነው (ሮሜ 8:21)።

የእግዚአብሔር ልጆች በመንፈስ ቅዱስ የሚመሩ፣ ስለክርስቶስ የሚመጣባቸውን መከራን የማይፈሩ የክብሩም ወራሾች ናቸው። ስለዚህ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ “በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፥ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።” (ሮሜ 8:14-17) ብሏል። በተጨማሪም “በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፥ ስለዚህም በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል።” (ፊል 2:15-16) በማለት የእግዚአብሔር ልጆች ለዓለም ብርሃን መሆናቸውን ተናግሯል።

የእግዚአብሔር ልጆች የሚታወቁት በእውነተኛ ፍቅር ነው። ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ “የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፥ እንዲሁም ነን። ስለዚህ ምክንያት ዓለም እርሱን ስላላወቀው እኛን አያውቀንም። ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን።” (1ኛ ዮሐ 3:1-2) በማለት የእግዚአብሔር ልጆች በፍቅር አባታቸውን እንደሚመስሉ አስተምሯል። እንዲሁም “የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።” (1ኛ ዮሐ 3:10) በማለት አረጋግጦታል።

ከላይ እንደተብራራው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን የጥል ግድግዳ አፍርሶ ሰላምን አውጇል። በሰዎች መካከልም ሰላምን አስፍኗል። በነፍስና በሥጋ መካከልም በእርሱ መወለድ ሰላም ሆኗል። የእርሱን አርአያነት ተከትለው ፍቅርን በመስበክ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ሰላምን የሚያጸኑ፣ ሰው ከኃጢአት ተጠብቆ ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቆ እንዲኖር የሚተጉ፣ እንዲሁም ሰው ከኃጢአቱ በንስሐ ተመልሶ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቆ በሰላም እንዲኖር የሚተጉ ብፁዓን ናቸው። ኢየሱስ ክርስቶስን አርአያ አድርገው በምግባራቸው በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ሰላም እንዲጸና ተግተዋልና የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉ።

በአርአያ ሥላሴ በተፈጠሩ ሰዎች መካከል ፍቅር እንድትጸና የሚተጉ፣ በሰዎች መካከል አለመግባባትና ጥል ሲፈጠር ይህንን ለመፍታት የሚተጉ፣ ጥል ወደ ፍቅር፣ አለመግባባትም ወደ መተባባር እንዲሸጋገር የሚሠሩ፣ ራሳቸውም ከሰዎች ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር የሚተጉ ብፁዓን ናቸው። ሰውን ከሰው፣ ሰውንም ከእግዚአብሔር አስታርቀዋልና። በዚህም ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን መስለውታልና የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉ። በፈቃደ ነፍስና በፈቃደ ሥጋ መካከል ያለውን ቅራኔ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው በማስገዛት ውስጣዊ ሰላማቸውን ያረጋገጡ፣ የሚያስጨንቃቸውን ነገር ሁሉ በፍጹም እምነት በእግዚአብሔር ላይ የጣሉ፣ መታመኛቸውን እግዚአብሔርን አድርገው ሥጋዊ ፍርሃትን ከራሳቸው ያራቁ ብፁዓን ናቸው። ጽድቅንና ፍትህን ገንዘብ አድርገዋልና የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉ። እርሱ የእውነትና የፍትሕ አምላክ ነውና። እንግዲህ “የጽድቅም ፍሬ ሰላምን በሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል።” (ያዕ 3:18) እንደተባለ ለሰላም ተግተን የእግዚአብሔር ልጆች እንባል ዘንድ ያስፈልጋል።

ሰላምና ቤተ ክርስቲያን

ሰላምን ማድረግ የቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ነው። ቤተ ክርስቲያን ሰው ከእግዚአብሔር ጋር በንስሐ የሚታረቅባት፣ ከእግዚአብሔር ጋርም በፍቅር የሚኖርባት የእግዚአብሔር ቤት ናት። በሰዎች መካከልም ፍቅር እንዲነግሥ የምታስተምር፣ ይቅር ባይነትንም የምትሰብክ መንፈሳዊ ተቋም ናት። በዚህም በሰዎች መካከል ሰላም እንዲሰፍን የራስዋን አስተዋጽኦ ታበረክታለች። በተጨማሪም ሰው ሥጋውን ለነፍሱ እንዲያስገዛ በማድረግ ውስጣዊ ሰላምን ታሰፍናለች። በቅዳሴው፣ በኪዳኑ እና በሌሎች ጸሎቶች ሁሉ ዘወትር ለሰላም ትጸልያለች። ስለሰላም የሚጸለይ “መስተበቁዕ በእንተ ሰላም” የሚባል የጸሎት ክፍልም አላት። ይህም ከፈጣሪዋና ከቅዱሳን ነቢያት፣ ከቅዱሳን ሐዋርያት፣ ከቅዱሳን ሊቃውንት የተማረችው ነው። ለምሳሌ ያህል የሚከተሉት ስለሰላም የሚደረጉ የጸሎት ክፍሎች በአጭሩ ቀርበዋል።

ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ትንሣኤ ሰላም መሆኑን ስትመሰክር “ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን፤ በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን፤ አሠሮ ለሰይጣን፤ አግዐዞ ለአዳም፤ ሰላም እምይዕዜሰ፤ ኮነ፤ ፍስሐ ወሰላም/ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ዲያብሎስን አሰረው አዳምን ነጻ አወጣው ሰላም ስለዚህም ከእንግዲህ ወዲህ ፍጹም ሰላምና ደስታ ሆነ” ትላለች። ካህኑም በቅዳሴ ጊዜ “ንስአሎ እንከ ከመ ይዕቀበነ በዛቲ ዕለት ቅድስት ኲሎ መዋዕለ ሕይወትነ ወበኲሉ ሰላም አኃዜ ኲሉ እግዚአብሔር አምላክነ/ አሁንም ክብረት በምትሆን በዚች ዕለት በሕይወታችን ዘመን ሁሉ በፍጹም ሰላም ሁሉን የሚይዝ አምላካችን እግዚአብሔር ይጠብቀን ዘንድ እንለምነው” በማለት ስለሁላችን ሰላም ይጸልያል።

ጌታችን ከትንሣኤው በኋላ ለደቀመዛሙርቱ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” (ዮሐ 20:21) በማለት ሰላሙን እንደሰጣቸው ዛሬም ቤተ ክርስቲያናችን በቅዳሴው ጸሎት በካህኑ 12 ጊዜ “ሰላም ለኩልክሙ (ሰላም ለሁላችሁ ይሁን)” እያለች ምዕመናንን የእግዚአብሔርን ሰላም እንዲያገኙ ትጸልያለች። ምዕመናንም “ምስለ መንፈስከ (ከመንፈስህ ጋራ)” ብለው እውነተኛው ሰላም እንዲደርሳቸው ይጸልያሉ። ይህም ሰላመ እግዚአብሔር ለክርስትና ሕይወታችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ከምናይባቸው ጸሎቶች አንዱ ነው። ጌታችን በዚህች ምድር ላይ በሚያስተምርበት ጊዜ ድውያንን ከፈወሰ፣ ኃጢአታቸውንም ተሰርዮላችኋል ካላቸው በኋላ “ልጄ ሆይ:- በሰለም ሂድ(ጂ)” ነበር የሚላቸው (ማር 5:34 ሉቃ 7:50 8:48)። ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ይህንን አብነት አድርጋ ምዕመናንን ከቅዳሴ ጸሎት በኋላ “እትው በሰላም (በሰላም ወደየቤታችሁ ግቡ)” ትላለች።

ቤተ ክርስቲያን በነቢዩ ኤርምያስ “ሰላምን ፈልጉ ስለ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ” (ኤር 29:7) የተባለውን መሠረት አድርጋ በቅዳሴው ሁል ጊዜ ስለሰላም ልዩ ትኩረት ሰጥታ ትጸልያለች። በቅዳሴው ካህኑ ስለቤተ ክርስቲያን ሰላምም “አቤቱ ሐዋርያት የሰበሰቡዋትን አንዲት የምትሆን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሰላም አስብ” በማለት ጸሎትን ያቀርባል። ዲያቆኑም “ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን አሐቲ ቅድስት ጉባኤ እንተ ሐዋርያት ርትዕት በኀበ እግዚአብሔር /ሐዋርያት ለሰበሰቡዋት በእግዚአብሔር ዘንድ ስለቀናች ክብርት ስለምትሆን አንዲት ቤተ ክርስቲያን ሰላም ጸልዩ/” በማለት ሁሉም ስለቤተ ክርስቲያን ሰላም እንዲጸልዩ ያውጃል። እንዲሁም ዲያቆኑ “ጸልዩ በኀበ ዛቲ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ወማኅበረነ በውስቴታ” ሲልም ሕዝቡ “ማኅበረነ ባርክ ዕቀብ በሰላም/ማኅበራችንን ባርክ በሰላምም ጠብቅ/” ይላሉ።

በተጨማሪም በቅዳሴው “ወመላእከ ኩላ ምድረ ሰላመከ እንተ እምሰማያት እንተ ባቲ ሠራዊተ ሰማያት ይሴብሑ እንዘ ይብሉ ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ /የሰማይ ሠራዊት እንዲህ እያሉ አንተን የሚያመሰግኑባትን ከሰማይ የተገኘች ሰላምን በምድር ላይ ሁሉ መላህ፤ በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባል በምድርም ሰላም የሰው ፈቃድ/” እያለች እንደ መላእክቱ ታመሰግነዋለች። በዲያቆኑም “ጸልዩ በእንተ ሰላም ፍጽምት ወፍቅር ተአምኁ በበይናቲክሙ በአምኃ ቅድሳት /ፍጽምት ስለምትሆን ሰላምና ፍቅር ጸልዩ፣ እርስ በርሳችሁ በተለየች ሰላምታ እጅ ተነሳሱ/” የሚለው ሲታወጅ ካህናት ከካህናት ጋር፣ ዲያቆናት ከዲያቆናት ጋር፣ ሕዝቡም ከሕዝቡ ጋር፣ ሴቶችም ከሴቶች ጋር እጅ ይነሳሳሉ።

በእንተ ቅድሳት በሚባለው የቅዳሴ ጸሎትም ስለሰላም “አንድ ስለምታደርግ ሥጋውና ደሙ እግዚአብሔር በይቅርታው አንድ ያደርገን ዘንድ ሰላምን እንማልዳለን” በማለት ትጸልያለች። በተጨማሪም ስለሀገር ሰላም ስትጸልይ “በዘመኑ ሁሉ ፍጹም ሰላምን እግዚአብሔር ይሰጣት ዘንድ ስለሀገራችን ኢትዮጵያ እንማልዳለን” ትላለች። የዚህ የጸሎት ክፍል ማጠቃለያ ላይም “በጸሎት የምንለምንና የምንማልድ ሁላችንንም በሰላም በመንፈስ ይጠብቀን ፍቅርንም ይስጠን ዓይነ ልቡናችንን ያብራልን ፈቃዱም ሆኖ ጸሎታችንን ይቀበል ዘንድ ቀርበን እግዚአብሔርን እንለምነው” እያለች እግዚአብሔርን ትማጸናለች። በሌላው የቅዳሴ ክፍልም “እግዚኦ ሰላመከ ሀባ ለሀገር ወጽድቀከኒ ለቤተክርስቲያን /አቤቱ ጌታ ሆይ ሰላምህን ለሀገር ፤ እውነትህንም ለቤተ ክርስቲያን ስጥ/” እያለች ስለሀገር ሰላም ትጸልያለች።

ሊቁ አባ ድዮስቆሮስ “የፍቅር ባለቤት የሰላም ንጉሥ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ሰላምህን ስጠን፣ ሰላምህን አጽናልን፣ ኃጢአታችንንም ይቅር በለን፣ በሰላም ወደ ቤታችን ሄደን እንገባ ዘንድ የበቃን አድርገን።” (ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ) በማለት በደረሰው የቅዳሴ ክፍልም ስለሰላም ፈጣሪዋን ትማጸናለች። እንዲሁም ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ከመታደሉ በፊት “..በሰላም ወበፍቅረ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰብሑ ወዘምሩ/በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ፍቅር አመስግኑ፣ ዘምሩም” በማለት ሁሉም እንዲያመሰግን ታውጃለች። በቅዳሴው ማጠናቀቂያም “አሜን እግዚአብሔር ይባርከነ ለአግብርቲሁ በሰላም/አሜን እግዚአብሔር እኛን አገልጋዮችን በሰላም ይባርከን” እያልን የሰላምን በረከት እንለምናለን።

ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን አምላከ ሰላም ትለዋለች። ስለዚህም ነው በጸሎቷ “አምላከ ሰላም ተራድአነ” የምትለው። መሠረትና ጉልላት የሆናትን ኢየሱስ ክርስቶስንም “አየሱስ ክርስቶስ ንጉሠ ሰላም ወተራኅርኆ (መልክአ ኢየሱስ ለቃልከ)” እያለች ታመሰግነዋለች። ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ላይ “ወገብረ ሰላመ ማእከሌነ /በመካከላችን ሰላምን አደረገ/ ካለ በኋላ ሰላምን ያደረገበትን መንገድና ኃይል ሲናገርም “በመስቀሉ ወበትንሣኤሁ ቅድስት” በማለት ሰላምን ያገኘነው በእርሱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን አስረድቷል። ይህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በመስቀሉ ላይ ባፈሰሰው ደም ሰላምን አደረገ፤ በምድርና በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷልና።” (ቈላ.1:19) በማለት ያስተማረውን የሚያጠይቅ ነው። ጸሎተ ኪዳንም የሚጀመረው “ሰላመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወፍቅራ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ፣ ሞገሰ መስቀሉ ወሀብተ ረድኤቱ የሃሉ ምስለ ኵልነ ሕዝበ ክርስቲያን ለዓለመ ዓለም” በማለት ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር እንዲሆን በመጸለይ ነው።

ቤተ ክርስቲያን አምላኳን ኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ያሬድ በድጓ “ትእምርተ ሰላምነ ወልድ ተወልደ ለነ፤ የሰላማችን ሰንደቅ ዓላማ የሆነው ወልድ ወይም ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ለኛ ተወለደልን” እንዳለው አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም በሰዓታት ጽሎት  “ትእምርተ ሰላምነ ዘኪያሁ ንትአመን፥ አረፍተ መድኃኒትነ በዘቦቱ ናሰምክ፥ ዕብነ ሕይወት ርእሰ ማእዘንት ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ /የምንታመንበት የሰላማችን ምልክት፥ የምንደገፍበት የድኅነታችን ግድግዳ፥ የሕይወት ዓለት የማዕዘንም ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው/” እንዳለው የሰላማችን ሰንደቅ (ምልክት) እያለች ታመሰግነዋለች።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሰላም አምላክ ብላ የምትጠራው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናቱን ቅድስት ድንግል ማርያምን “ማኅደረ ሰላም (የሰላም ማደሪያ)” ብላ ትጠራታለች። ቤተ ክርስቲያን በጸሎቷ “ማኅደረ ሰላምነ ቅድስት ደብተራ እሞሙ ለሰማዕት ወእኅቶሙ ለመላእክት ንዑ ንሰግድ ኵልነ ኀበ ማርያም እምነ /የሰላማችን ማደሪያ ልዩ ድንኳን፤ የሰማዕታት እናታቸው የመላእክት እኅታቸው ወደ እናታችን ማርያም የጸጋ ስግደት እንሰግድ ዘንድ ኑ/” በማለት ቅድስት ድንግል ማርያም የሰላም ማደሪያ መሆኗን እያሳሰበች ትማጸናለች። እርስዋ የሰላማችን (የኢየሱስ ክርስቶስ) ማደሪያ ናትና። ከእርስዋም በመወለዱ ያጣነውን ሰላም አግኝተናልና። ከዚህ በተጨማሪም በሰዓታቱ “ሰላማዊት ሰላም ለኪ፤ መንፈሳዊት ርግብ ወንሰግድ ለኪ” እያለች ታወድሳታላች። እንዲሁም ቅዱሳን ሐዋርያትንም “ሐዋርያተ ሰላም (የሰላም ሐዋርያት)” እያለች ታስባቸዋለች። ለዚህም ማሳያ የሚሆነን ለብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ሰማዕትነት የተቀበሉበትን ቀን በማኅሌት “ሐዋርያተ ሰላም ክቡራነ ስም፤ ሥረዩ ኃጢአተ ዓለም፤ በእንተ ኢየሱስ ክርስቶስ ወበእንተ ድንግል እም” እና “ሐዋርያተ ሰላም ብርሃናተ ዓለም፤ አሥራበ ምሕረት ከዓው እምአርያም” እያለች የምታመሰግንበት ዝማሬ ነው።

በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያን በምዕራብ በኩል ያለውን ደጅ “ደጀ ሰላም(የሰላም ደጅ)” ትለዋለች። ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመግባቱ በፊት የበደለው ሰው ካለ ይቅር ብሎ የሚገባበት ደጅ ነውና። የአድባራትንም ስያሜ ላይ “ደብረ ሰላም (የሰላም ደብር)፣ መካነ ሰላም (የሰላም ቦታ)” በማለት ትገልፃቸዋለች። እውነተኛ ሰላም የሚገኝባቸው ናቸውና። ለቅዱሳን መላእክትም መልአከ ሰላም (የሰላም መልእክተኛ) የሚለውን ገላጭ ትጠቀማለች፣ የሰላምን ዜና ለሰው ልጆች ያደርሳሉና። ለካህናት የመዓርግ ስሞችም “መልአከ ሰላም“(የሰላም መልእክተኛ/አለቃ)፣ ላዕከ ሰላም ብላ ትሰይማለች። ካህናት ሰውን ከእግዚአብሔር በንስሐ የሚያስታርቁ፣ ሰውንም ከሰው የሚያስታርቁ፣ ነፍስንም ከሥጋ በትምህርት የሚያስታርቁ ናቸውና ይህንን ስያሜ ትሰጣለች። ቤተ ክርስቲያን ይህንን ሁሉ የምታደርገው ሰላምን የምትሠራ መንፈሳዊ ተቋም ስለሆነች ነው።

ሰላምን ማድረግ በዘመናችን

ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት “ሰላምን ሻት ተከተላትም።” (መዝ 34:14) እንዳለው ዛሬም በዘመናችን ለሰላም የሚጸልዩ፣ ለሰላም የሚተጉ ደጋግ አበው፣ እማት፣ አኃውና አኃት አሉ። ለዚህም ያልተወንን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ የሚታየው መነቃቀፍ፣ መገፋፋት፣ መነታረክና አልፎም መሰዳደብን ማየት ልብን ይሰብራል። እነዚህ ከራስ ወዳድነትና ለሌላው ደንታ የለኝም ከሚል አመለካከት የሚመነጩ አተካራዎች በመካከላችን ያለውን ልዩነት እያሰፉት ሄደዋል። አብረን ከመኖር ይልቅ “ባንደራረስ ይሻላል” ወደሚል ድምዳሜም እየመሩን ነው። በተለይም ቤተ ክርስቲያንን እንወክላለን የሚሉ አካላት የቤተ ክርስቲያንን ስም ለብሰው የሚያስተላልፏቸው መልእክቶች የቤተ ክርስቲያንን ሰላም እየጎዱ ይገኛሉ። በተለይም በዝርወት ዓለም “ቤተ ክርስቲያን መሄድ ሰላምን ይነሳል፣ አለመሄድ ደግሞ ሰላምን ይሰጣል” እስኪባል ድረስ በጥቃቅን ነገሮች እየተጨቃጨቅን የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን በእኛ ሰላም ማጣት ምክንያት ሰዎች እንዲርቋት አድርገናታል።

አስቀድሞ በነቢዩ ኤርምያስ “ሰላም ሳይሆን፥ ሰላም ሰላም ይላሉ” (ኤር 6:14) እንደተባለ ልባችን ሰላም አጥቶ በአፋችን ሰላም ሰላም እንባባላለን። ይባስ ብሎም ለዓለሙ ሁሉ ሰላም የምትጸልየው ቤተ ክርስቲያን ፍትሕን ከዓለማዊ ፍርድ ቤት፣ ሰላምን ከፖሊስና ከሌሎች የፀጥታ አካላት እንድትጠይቅ እያደርግናት ነው። ይህንን ለማየት በተለይም በምዕራቡ ዓላም ባለችው በቤተ ክርስቲያን ሕንፃና መሬት ምክንያት የሚፈጠሩ ግጭቶችንና ክሶችን ማየት በቂ ነው። ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ፣ የሁሉም ክርስቲያን ማምለኪያ ቦታ ተብላ ከተሠራች በኋላ የእኛና የእናንተ እያልን እንጣላባታለን። ይህ የሚያመለክተው ቤተ ክርስቲያንን እንደ ንብረት (Property) ብቻ የቆጠርን መሆናችንን ነው። ከአንድ አባት የተወለዱ ወንድሞችና እህቶችን ከቤተ ክርስቲያን በግድ አስወጥተን ጸሎት ብናቀርብ ጸሎታችንን እግዚአብሔር የሚቀበለው ይመስለናል? “አስቀድመህ ከወንድምህ ጋር ታረቅ” (ማቴ 5:24) የሚለውን ቃል ልናስተውል ይገባናል።

በቤተ ክርስቲያን የብዙ ዘመናት ታሪክ የምናውቀው ዓላውያንና መናፍቃን በቤተ ክርስቲያን ላይ መከራን ሲያደርሱ፣ ክርስቲያኖችንም ሲያሳድዱ ነው። በዘመናችን የሚታየው ግን ወንድም ለወንድሙ የተለያየ ስም እየሰጠ ሲያሳድድ፣ በማሳደዱም ‘ጀግና፣ አርበኛ፣ የቁርጥ ቀን ልጅ’ ተብሎ ሲሸለም ነው። እንደዚህ ሰላምን የሚያጠፉትን እያገነንን፣ ወንድሞችም ከቤተ ክርስቲያን ሲወጡ እንደ ስኬት እየቆጠርን እንዴት ሰላም ሊመጣ ይችላል? አርዮስ እንኳን ከቤተ ክርስቲያን በመለየቱ የቀደሙት አባቶች እያዘኑና እያለቀሱ “አንድ የሰውነት ክፍል እንደመቁረጥ ያህል ከባድ ነው” በማለት የገለጹትን እንዴት ማስታወስ አቃተን? በተጨማሪም በሌላ ቤተ እምነትም ያሉ ወንድሞችና እኅቶችን ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን መመለስ የሚቻለው በፍቅርና በትምህርት ብቻ መሆኑ እየታወቀ ከዚህ በተቃራኒ ጠላት ተደርገው እንዲታዩና የበለጠ እንዲርቁን የሚያደርግ ስብከት እየተሰጠ እንዴት ሰላምን እንሰብካለን እንላለን?

በክርስትና አስተምህሮ መሠረት ሰላም በፍቅር አብሮ በመኖር እንጂ አንዱን ወገን በማሳደድ ወይም በማጥፋት ሊገኝ አይችልም። የቀደሙት አባቶቻችን ያስተማሩትም በፍቅር አብሮ በመኖር የሚገኘው ሰላምን ነው። መስበክም ያለብን የዚህ ፍቅር አርአያ የሆነው የሰላም አምላክ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ክርስቶስ ያን ሁሉ መከራ ሲያደርሱበት እንኳን አንዳች ክፉ ቃልን አልተናገረም፣ ሐዋርያትም መከራን ሲቀበሉ አንዳችም የስድብ ቃልን አልተናገሩም፣ ፍቅርን አስተማሩ እንጂ። ዛሬ ግን እኛ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “የሰላምንም መንገድ አያውቁም” (ሮሜ 3:18) እንዳላቸው አይሁድ የምናስበው፣ የምንጽፈውና የምንናገረው ስለሌላ ሰው ነቀፋ፣ ትችትና ስድብ ነው። ጊዜያችንን በጭቅጭቅና በንትርክ እየጨረስን ቤተ ክርስቲያንን ሳይቀር የመታገያ መድረክ አድርገናታል። እንደዚህ እያደረግን ለሰላማዊ አገልግሎት ጊዜ ከየት እናገኛለን? የሚሠራ ሰውን በሕይወቱ ሳለ ስናብጠለጥለው ኖረን ሕይወቱ ሲያልፍ ብቻ ጠብቀን ጥሩ ጥሩ ነገር መናገር ብቻውን ሰላም አያመጣም። በሕይወት ሳለን ብንፋቀር ብዙ እናተርፋለን። እንደቀደሙት አባቶች የሰላም ሐዋርያ መሆን ባንችል እንኳን ሰላም ከማደፍረስ መቆጠብ እንዴት አቃተን?

የሚያስታርቁ፣ የሚያስተራርቁ

በግዕዙ ገባርያነ ሰላም (Peacemakers) የሚለው በአማርኛው የሚያስታርቁ ወይም የሚያስተራርቁ ተብሎ ተተርጉሟል። ይህ የአማርኛ ትርጉም “ገባርያነ ሰላም” የሚለውን የግዕዙን ሀረግ ሙሉ በሙሉ ይገልጸዋል ለማለት አያስደፍርም። ምክንያቱም ማስታረቅ የገባርያነ ሰላም ዋና አገልግሎት ቢሆንም የገባርያነ ሰላም (Peacemakers) ድርሻ ግን ማስታረቅ ብቻ አይደለምና። የገባርያነ ሰላም ድርሻ አስቀድሞ ፍቅርን በማጽናት ሰላምን ማጎልበትን፣ ሰላም ሲጠፋ በማስታረቅ ሰላምን መመለስን፣ ከእርቅ በኋላም ሰላም እንዳይደፈርስ መትጋትን ያጠቃልላል። ይህንን የተሻለ ይገልጸዋል ብለን ያመነው “ሰላምን ማድረግ” የሚለውን ነው። ሰላምን ማድረግ ማስታረቅን ጨምሮ ሌሎችን ለሰላም መሥፈን የሚከናወኑ አገልግሎቶችን ሁሉ ያካትታልና። የግዕዙ “ገባርያነ ሰላም” ለሚለውም ቀጥተኛ ትርጉሙና የተሻለ የሚስማማው ቃል “ሰላምን የሚያደርጉ” የሚለው ነው ብለን እናምናለን። ምናልባት እዚህ ላይ “ሰላም የሚሠራ ነገር ነው ወይ?” የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። አዎን ሰላም መረዳትን፣ ልባዊ ፈቃደኝነትን፣ መንፈሳዊ ቁርጠኝነትን የሚፈልግ ስለሆነ ይህንን ማድረግ የሚቻለው በጸሎትና በሥራ (በአገልግሎት) ብቻ ነው።

ማጠቃለያ

ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ ሐዋርያዊ ተልዕኮን ሲያስተምራቸው “ወደ ቤትም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤ ቤቱም የሚገባው ቢሆን (በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር) ሰላማችሁ ይድረስለት፤ ባይገባው ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ።” (ማቴ 10:13 ሉቃ 10:6) በማለት ነበር። እግዚአብሔር የላከውን (መልእክቱንም መልእክተኛውንም) የሚቀበል ሰላመ እግዚአብሔርን (በረከትን) ያገኛልና ይህን አለ። ይህንን ሰላም የሚያገኝ ሰው ከሌላው ወንድሙ ጋርም ሰላም ይኖረዋል፣ ከወንድሞቹ ጋር የመንፈስን አንድነት ይፈጥራልና።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ “በሰላም ማሠርያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።” (ኤፌ 4፥3) በማለት ያስተማረው የመንፈስ አንድነት ማሠሪያው ሰላም ስለሆነ ነው። በመካከላችን ያለው የመንፈስ አንድነት የሚጸናው በሰላም ስናመልክ፣ በሰላም ስናገለግል፣ በሰላም ስንኖር ነውና ይህን አለ። ጌታችንም በወንጌሉ “በነፍሳችሁ ጨው ይኑርባችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ሰላም ይኑራችሁ።” (ማር 9:50) ብሎ ያስተማረው በመካከላችን ያለው ሰላም ለክርስትና ሕይወትና የመንፈስ አንድነት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ለማመልከት ነው።

በመጨረሻም ሰላምን ማድረግ በሚል ዐቢይ ርዕስ ያዘጋጀናትን ጽሑፍ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመልእክቶቹ ማጠቃለያ ባደረጋቸው ቃላት እንደመድማለን። ይህ የተወደደ ሐዋርያ “የሰላምም ጌታ ራሱ በሁሉ መንገድ ዘወትር ሰላምን ይስጣችሁ።” (2ኛ ተሰ 3:16) እንዳለው የሰላም አምላክ ሰላሙን ይስጠን። እንዲሁም “በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ደኅና ሁኑ፣ ፍጹማን ሁኑ፥ ምክሬን ስሙ፥ በአንድ ልብ ሁኑ፥ በሰላም ኑሩ፥ የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።” (2ኛ ቆሮ 13:11) እንዳለው በሰላም እንኖር ዘንድ የፍቅርና የሰላም ንጉሥ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላሙን ይስጠን፣ ሰላሙንም ያጽናልን። አሜን።

Leave a comment