ማኅሌቱንና ሰዓታቱን ስናደርስ ከቅኔ ማኅሌቱ በስተግራ፣ ከሊቃውንቱ በስተቀኝ በኩል፣ ከአምደ ወርቁ አሻቅቦ ማየት ከሚቻል ቦታ የሚንቆረቆርና ልብን የሚመስጥ ጥዑም ዜማ ይሰማል። በቅዳሴውም ሰዓት ከዚያው ስፍራ የመላእክትን ጣዕመ ዝማሬ የሚመስል ግዕዝና ዕዝሉን ዜማ ከቅዱስ ያሬድ በቀጥታ የተማረ ሰው የሚያወጣው አይነት ልዩ የሆነ ድምፅ ጎልቶ ይሰማል። ዲያቆናቱና የሰንበት ተማሪዎችም “ምነው በዚህ ዜማ ተሰጥኦ ብንማር!” ብለው ይናፍቃሉ። ምዕመናኑም “ምነው በዚህ ዜማና ድምፅ መዝሙር ብንሰማ!” ብለው ይመኛሉ። ይህ ድምፅ የቤተ ክርስቲያኒቱን የዜማ ሥርዓት የጠነቀቀ ከመሆኑም በላይ መጽሐፍ ‘ኅየንተ አበውኪ ተወልዱ ለኪ ደቂቅ፣ በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ’ እንዳለው ከዚህ ምድር ሳይሆን ከላይ የተሰጠ ልዩ ጸጋ መሆኑ ቅንጣት ያክል አያጠራጥርም። ይህ ድምፅ የማርታ ድምፅ ነው።
ማርታ ገና በሕፃንነቷ በሰባት ዓመቷ ነበር ወደ ሕፃናት ሰንበት ትምህርት ቤት የገባችው። በዚያም ብሩህ በሆነው በሕፃን አእምሮዋ ስትማርና ስትዘምር ለዓመታት ቆይታ ወደ ማዕከላውያን የሰንበት ትምህርት ቤት ክፍል ተሻገረች። ያንንም በሚገባ አጠናቃ በወጣቶች ሰንበት ትምህርት ቤት ተምራለች። ከዚህ ጎን ለጎንም ውዳሴ ማርያምን፣ መልክአ ማርያምን፣ መልክአ ኢየሱስን፣ ዳዊትን ትቀፅል ነበር። የቅዳሴና የሰዓታት ዜማዎችንም በሚገባ አጥንታለች። የሚያስተምሯት የኔታም ትጋቷንና ፍጥነቷን አይተው ልጄ “አይ አንቺ ወንድ ሆነሽ ቢሆን ኖሮ…” እያሉ ይቆጫቸው ነበር።
ማርታ ማኅሌቱንም ብዙ ጊዜ በማስተዋል ከመከታተሏ የተነሳ ተዋህዷታል። በዚህ ሁሉ ዘመን ሠርክ ጉባዔና የሰንበት ቅዳሴ ቀርታ አታውቅም። ትምህርት በሌለ ቀን ደግሞ ቅዳሴ ባለበት ሄዳ ታስቀደሳለች፣ ቅዱስ ቁርባንም ትቀበላለች። ማርታ ጎበዝ ተማሪ በመሆኗ ውጤት አምጥታ ወደ ዩኒቨርስቲ ገብታለች። በዚያም ለዓመታት በግቢ ጉባዔ ተምራለች፣ በመዝሙርና ኪነጥበብ ክፍልም አገልግላለች። ከዚያ ተመርቃ ስትወጣም በተመደበችበት ቦታ ሥራዋን በትጋት እያከናወነች በሰንበት ትምህርትና በማኅበራት አገልግላለች። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላም የድኅረ ምረቃን ግቢ ጉባዔ ተቀላቅላ በደንብ ተከታትላለች። ዘመናዊው ትምህርት የእንግሊዝኛ ቋንቋን አቀላጥፋ እንድትናገር አስችሏታል። ዛሬም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ባህር ማዶ አምርታ አንድ በምዕራቡ ዓለም በሚገኝ የወንጌል ሰባኪው የሆነውና እንደ እርሷ በትምህርት ምክንያት የሄደው ዲያቆን ናዖድ በሚያገለግልበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በትጋት ትከታተላለች። ነገር ግን ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ሰውን ማግኘትም አትፈልግም። በዚህም ምክንያት ስለማርታ ከመንፈሳዊ አገልግሎቷ ውጭ ስለግላዊ ሕይወቷ የሚያውቅ ማንም የለም።
የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ሥርዓት ዑደታዊና በየዓመቱ ተመልሶ የሚመጣ መሆኑ ለማርታ እጅግ ጠቅሟታል። ለምሳሌ በአንዱ ዓመት በደብረ ታቦር ቀን የተማረችውን ወንጌል በሚቀጥለው ዓመት ተመልሶ ሲመጣ ታጠናክረዋለች። እንደዚያ እያደረገች አምና በተማረችው ላይ የዘንድሮውን እየጨመረች ነው ዕውቀቷን ያካበተችው። የማኅሌቱን ቀለምም እንደዚሁ ልቧን ከፍታ በማዳመጥና በመሳተፍ ነው የተማረችው። ለነገሩ ከስንፍናና ከትኩረት ማነስ ካልሆነ በስተቀር አርባ ዓመት የደብረ ታቦርን ማኅሌት በሚገባ የተከታተለ ሰው እንዴት የኔታን አይሆንም?! በየሳምንቱ ቅዳሴ በመከታተል በአርባ ዓመታት ወስጥ ከሁለት ሺህ ጊዜ በላይ ያስቀደስ ሰው እንዴት መምሬን አይሆንም?! ማርታ ይህንን ዕድል በሚገባ በመጠቀም ነው ሁሉን የጠነቀቀችው።
ማርታ ባለችበት የፈረንጅ ሀገር ያሉ የኢትዮጵያውያን ልጆች መንፈሳዊ ትምህርትን ጉዳይ ስታስብ ያንገበግባታል። ልጆቹ በደንብ የሚናገሩት ቋንቋ እንግሊዝኛ ነው። ወላጅና ቤተ ክርስቲያን ግን መንፈሳዊ ትምህርትን እንዲማሩ የሚፈልጉት በወላጆቻቸው ቋንቋ ነው። ጥቂት ወንድሞች ልጆችን አማርኛ ቋንቋ ማስተማር ቢጀምሩም ፈደልና ቃላትን ብቻ መላልሰው ሲያስተምሩ አምስት አመት ደፍነዋል። ልጆቹ እንደተማሩ ለማስመሰል፣ ለታይታ ያህል፣ ለማኅበራዊ ሚዲያ ግብዓት ለማድረግ ሲባል ዩኒፎርም እንዲለብሱ ተደርገው በማይችሉት በአማርኛ ወይም በግዕዝ ቋንቋ (በእንግሊዝኛ ፊደላት ተጽፎላቸው) ከቅዳሴ በኋላ መዝሙር እንዲዘምሩ ይደረጋል። ማርታ “ልጆቹ ቋንቋ ይማሩ? ወይስ ሃይማኖታቸውን ይማሩ? ለምን ቀንበር እናከብድባቸዋለን?” እያለች ትጠይቃላች። “ለምን በሚገባቸው ቋንቋ አይማሩም?” ስትል ወላጆች “ቋንቋችንና ባህላችን ይጠፋል” ይላሉ። ሌላው ደግሞ “ማን በእንግሊዝኛ ያስተምራቸዋል?” ይላል። በዚህም የተነሳ ወላጆች ልጆቻቸውን ቤተ ክርስቲያን ይዘዋቸው ቢመጡም ቅዳሴውንም ስብከቱንም አይረዱትም። ከፍ ሲሉም ጭራሹንም ከቤተ ክርስቲያን ይቀራሉ። ለምን ሰንበት ቅዳሴ አትመጣም (አትመጪም) ብሎ ለሚጠይቃቸውም “Imagine standing still, forced to listen to a voice you can’t comprehend for more than three hours. It’s a slow, relentless form of mental torture” ብለው ይመልሳሉ።
በዚህም የተነሳ ቤተ ክርስቲያን በብዛት የሚታዩት ሕፃናት፣ አዋቂዎችና አረጋውያን ናቸው። ጥቂት የማይባሉ ወጣቶችም በጓደኞቻቸው ግፊት ወደ ሱስ ይገባሉ። አንዳንዶችም ቁማር ይጀምራሉ። ይህን ማድረጋቸው ሲታወቅ ደግሞ የእኛ ማኅበረሰብ የማኅበራዊ ሚዲያ አጀንዳ ያደርጋቸዋል፣ ያገላቸዋልም። ይህም ለተለያየ የአእምሮ ሕመም ሊዳርጋቸው ይችላል። ከዚህ አንፃር ቤተ ክርስቲያን የወላድ መካን እንዳትሆን በእጅጉ ያሰጋታል። ነገር ግን የአብዛኛው ሰው ትኩረት ለቤተ ክርስቲያን መሥሪያ የሚሆን ቦታ መግዛት፣ ቦታውም ከተገዛ በኃላ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መሥራት፣ ከዚያም ለመሬትና ለሕንፃ የተወሰደውን ብድር መክፈል ላይ ነው። ለዚህም ገቢ ለማሰባሰብ አንድ ጊዜ ምግብ (እራት፣ ምሳ) ሌላ ጊዜ ጥበብ (ድራማ)፣ አንድ ጊዜ ጨረታ ሌላ ጊዜ ቶምቦላ፣ አንድ ጊዜ ስፖርት (ነጠላና ቀሚስ ለብሶ ሩጫ፣ ገመድ ጉተታ) ሌላ ጊዜ ፖስታና ትኬት በማዘጋጀትና በማደል ይደክማሉ። ሰባኪና ዘማሪም የሚጠራው ገቢን ታሳቢ ተደርጎ መሆኑ የታወቀ ነው። ትንሽ ሲብስ ደግሞ እያንዳንዱ ቤተሰብ በብዙ ሺዎች እንዲከፍል ይፈርዱበታል። “ይህ አሠራር ትክክል አይደለም!” የሚላቸውን ደግሞ “መክፈል ካልቻልህ…” እያሉ ያሸማቅቁታል። ይህ እንግዲህ ቢያንስ ሠላሳ ዓመታትን ይፈጃል። የልጆች ዕድሜ ደግሞ ቆሞ አይጠብቅም። የአዋቂዎችም ዕድሜ አላቂ ነው።
ዲያቆን ናዖድ ወንጌል እንዲሰብክ ተመድቦ በዐውደ ምሕረት ላይ ሲቆም በሴቶች በኩል ከፊት ለፊት ደምቃ የምትታየው ማርታ ናት። ናዖድ እርሷን ሲያይ “ዕድሜ ልኩን ወንጌል ሲማርና ሲያገለግል ለኖረ ሰው ምንድን ነው የምሰብከው?” የሚል ጥያቄ በአእምሮው ይመላለሳል። “ከብዙ መምህራን ሲማር ለኖረ ሰው እንዴት ነው የምሰብከው?” እያለም ራሱን ይጠይቃል። “አሁን እኔ ነኝ ወይስ ማርታ ናት እዚህ ዐውደ ምሕረት ላይ ቆሞ(ማ) ወንጌል ማስተማር ያለ(በ)ባት?” ብሎ ራሱን ይጠይቃል። “እኔ እዚህ ቆሜ ለማርታ ወንጌል መስበኬ ድፍረት ሲሆን ማርታ ግን እንደእኔ ካለ ጀማሪ ለመማር ቁጭ ማለቷ እንዴት ያለ ትህትና ነው?” እያለ ይብሰለሰላል። “እንደማርታ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በጥልቀት የተማሩ እኅቶችና እናቶች በዚህ በካበተ ዕውቀታቸው ቤተ ክርስቲያንን በተሻለ የሚያገለግሉት እንዴት ነው?” እያለም ራሱን ይጠይቃል። ቤተ ክርስቲያንም የእነማርታን ዕውቀት ለመጠቀም የሚያስችል የአገልግሎት ዘርፍ ባለመዘርጋቷም ይቆጫል።
ይነስም ይብዛም በየአጥቢያው እንደ ማርታ ያሉ ብዙ የአገልግሎት ጸጋ የተሰጣቸው፣ የዕውቀትና የክህሎት ሀብታም የሆኑ እናቶችና እኅቶች አሉ። ነገር ግን ሁሉም ነጭ ነጠላቸውን ተሸፋፍነውና የትንሣኤው ምስክር የሆኑ መላእክትን መስለው በትህትና ወጣት ሰባክያን በዐውደ ምሕረት ላይ ቆመው ‘ሲያስተምሩ’ እንደ ልድያ ልባቸውን ከፍተው ያደምጣሉ። እንዳንዶቹ ዝም ብለው በሰንበት ትምህርት ቤት ከወጣቶች ጋር ተቀላቅለው ይዘምራሉ። ሌሎቹ ደግሞ በትህትና ሆነው በመስተንግዶ ብቻ ያገለግላሉ። አንዳንድ አላዋቂዎችም ይህንን “መክሊታቸው ነው” እያሉ ይሳለቁባቸዋል። “ሴት ወደ ማጀት፣ ወንድ ወደ ችሎት” የሚለው አባባል ምዕተ ዓመታት እንዳለፈበት ማን በነገራቸው!? እጅግ ጥቂቶቹ በሰበካ ጉባዔ ቢመረጡም በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ያላቸው ድርሻ ግን ብዙ ጊዜ አነስተኛ ነው። በዚህም አእምሮአቸውን ከክፉ ሀሳብ ለመጠበቅ ሲሉ “ለማይለወጥ ነገር ምን አደከመኝ?” ብለው ራሳቸውን በማግለል ሌላ የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ያተኩራሉ። እጅግ የሚበዙት ማርታዎች ግን ቅዳሴ አስቀድሰው፣ ወንጌልም ከወጣቶች ‘ተምረው’ ወደ ቤታቸው የሚመለሱ ናቸው። ይህ እውነታ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ታላላቅ ከተሞችና በዝርወት ሀገር ባሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በሰፊው የሚታይ ነው። የዘመናችን ቤተክርስቲያን ከቀደመው ዘመን ትውልድ መጥፎ መጥፎውን መርጣ የያዘች ትመስላለች።
ዲያቆን ናዖድ ግን ቁጭቱን በልቡ ቀብሮ አላስቀረውም። በመጀመሪያ እጅግ ለሚቀርባቸው አንድ አረጋዊ ካህን አካፈላቸው። እኚህ ካህን በአኃት አብያተ ክርስቲያናት ለብዙ ዓመታት ያገለገሉ ስለነበሩ የእናቶችን አገልግሎት በሚገባ ተረደተውታል። ቀስ ብለው እርሳቸው የሚያውቁትን እርሱም ሄዶ እንዲመለከት መከሩት። ናዖድም ጊዜ ሳያጠፋ ሄዶ ተመለከተ። እናቶች ልጆችን ልክ እንደ ዘመናዊ ትምህርት በየዕድሜያቸው ከፍለው በተመሳሳይ ሰዓት ስድስት መርኃ ግብሮችን ሲያካሂዱ፣ ከዚያም ቀጥለው መዝሙር ሲያስጠኑ በአይኑ ተመልክቶ ተደነቀ። በየሳምንችቱ ቅዳሜ ከሰዓትም ቆይታውን በዚያው አደረገ። ፋዘር ዮሴፍ ከሚባሉ ካህን ጋርም ሆኖ ከልጆች ትምህርት በተጨማሪም የእናቶችን ጉባዔም አየ። የልጆች ትምህርት ፕሮግራም የጀርባ አጥንት የእናቶች ጉባዔ ነው። በዚህ ጉባዔ የሚሳተፉ እናቶች ስልጠና ይወስዳሉ፣ በገንዘባቸው ይደግፋሉ፣ ራሳቸው ተገኝተው ልጆችን ያስተምራሉ፣ ያስተባብራሉ። ጉባዔው ይህንን ሥራ የሚያቅዱበት፣ አፈፃጸሙን የሚያስተባብሩበትና የሚከታተሉበት መድረክ ነው። ከዚህ ወጭ ሌላ ዓላማ የለውም። እናቶችም ይህንን ፕሮግራም ለመምራት ሙሉ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
የእናቶች ጉባዔ ሌላው ዓላማው በሀገር ቤት የተቸገሩ ሕፃናትና ልጆች መንፈሳዊና ዘመናዊ ትምህርትን እንዲማሩ በገንዘብ መርዳት ነው። ናዖድ እናቶች በሚያስተባብሯቸው ሌሎች ብዙ መርኃ ግብሮች ላይ ከተሳተፈ በኋላም ማርታንና ሌሎች ሁለት እናቶችን ወደዚያው ጋበዛቸው። ማርታም ሳታቅማማ ሄዳ ተመለከተች። በሚፈጽሙት አገልግሎት ተደነቀች፣ እርስዋ ይህንን ባለማድረጓ ከቁጭት የተነሳ ስቅስቅ ብላ አለቀሰች። በዚያ የነበሩ አንድ እናት ማልቀስዋን ተመልክተው ወደ እርስዋ ቀረቡና ማልቀስዋን እንድታቆም ጠየቋት፣ ወደ ቤተ መቅደሱም ወስደው ቀስ ብለው ለምን እንደምታለቅስ ጠየቋት። ማርታም በልቧ ያለውን ቁጭት አንድም ሳታስቀር ነገረቻቸው። “የእኛ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ልጆች አሏት። እነዚህ ልጆቿ ግን እንደ እናንተ እየሠሩ አይደለም። ስለዚህ የነገዋ ቤተ ክርስቲያኔን ሳስብ እንባዬ ይቀድመኛል” አለቻቸው።
እኝህ እናትም የልቧን ተረድተው ኖሯል የእነርሱን አጀማመር እንደዚህ አጫወቷት። እኛም ይህንን ሳንጀምር ከሃምሳ ዓመት በፊት እንደዛው ነበርን። ሁሉም ካህን ሁሉም ምዕመን በቋንቋችን የሚሰጠውን አገልግሎት እንጂ የልጆቹ ፍላጎት ግድ አይለውም ነበር። አንድ አባት ናቸው ልጆችን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተማር የጀመሩት። ሰውም “ልጆች የወላጆቻቸውን ቋንቋና ባህል እንዲረሱ ሊያደርጉብን ነው” ብለው ተቃወማቸው። እርሳቸው ግን እኔ ልጆቹን ነው የምሰማው ይሉ ነበር። ከዚያም ቅዳሴውን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተረጎሙት። ሰው ቅዳሴ መቅረት ጀመረ። ተቃውሞ መሆኑ ነው። እርሳቸው ግን ይህ ለልጆቹ ነው እንጂ ለአዋቂዎች አይደለም ይሉ ነበር። በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ አልፈው ጥቂት ወጣቶችን አፈሩ። እነዚያ ልጆች ናቸው እንግዲህ እየተቀባበሉ እዚህ ያደረሱት። እኔም የእርሳቸው ተማሪ ነበርኩ አሏት። ከዚያም ሁሉን እንድታይና እርስዋ ባለችበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንም ብትጀምረው በየጊዜው እየመጡ ልምዳቸውን እንደሚያካፍሏት ቃል ገቡላት።
ማርታ በተጋበዘችው መሠረት በአንዲቱ ሰንበት ቀን በማለዳ ከኦርቶዶክሳውያን አኃት አብያተ ክርስቲያናት ወደ አንዱ አጥቢያ ሄደች። በዚያን ቀን ጠዋት አራት ቅዳሴ ነበር። የመጀመሪያው ቅዳሴ በጠዋት ለሚመጡ ነው። ሁለተኛው ረፈድ አድርገው ለሚመጡ ነው። እነዚህ ሁለቱ ቅዳሴዎች በዋናው ቤተ ክርስቲያን በተለያየ መንበር በእንግሊዝኛ የሚከናወኑ ናቸው። ሦስተኛው ቅዳሴ በሀገራቸው ቋንቋ በሌላ መቅደስ ነው የሚቀደሰው። አራተኛው ደግሞ የልጆች (ልጆች ብቻ የሚሳተፉበት) ቅዳሴ ነው። ማርታ ይህንን ስታይ “በአንዲት እሑድ ጠዋት አራት ቅዳሴ ይቀደሳል ቢሉ ማን ያምናል!” ነበር ያለችው። እጅግ የገረማት ደግሞ ይህ ሁሉ ሥርዓቱን አንዳች ሳያፋልስ መከናወኑ ነው። የሰዓት አከባበሩም ነገር አስደናቂ ነው። ሁሉም ቅዳሴዎች በሁለት ሰዓት ውስጥ ተጠናቀው ሕዝቡን ያሰናብታሉ። ትምህርት የሚሰጠው ወንጌል ከተነበበ በኋላ እጅግ ቢበዛ ለአሥር ደቂቃ ነው። ሁሉም ምዕመን ከቅዱስ ቁርባኑ ይሳተፋል። አንዳች የሚቀር የለም። ከዚህ በኋላ ምንም አይነት ሌላ መርኃ ግብር የለም።
የሕፃናት፣ የልጆችና የወጣቶችን መንፈሳዊ ትምህርት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለመጀመር መሠራት የሚገባቸው ቅድመ ዝግጅቶች እንዳሉ ማርታና ናዖድ በሚገባ ተረድተዋል። ከእነዚህም መካከል የልጆችን ፍላጎቶች በሚገባ መረዳት፣ የወላጆችን ዘላቂ ተሳትፎ ማረጋገጥ፣ ቁርጠኝነት ያላቸው አገልጋዮችን ማዘጋጀት፣ የማስተማሪያ ቦታና ቁሳቁስ ማዘጋጀት ይገኙበታል። ለዚህም እንዲሆን ማርታና ናዖድ ዘመናዊ ዕውቀታቸውንና ክህሎታቸውን ተጠቅመው ሁሉንም አካላት አወያዩ፣ ይሁንታቸውንም አገኙ። እናቶችና እኅቶች ለማስተማር የተሻሉ መሆናቸውንም አረጋገጡ። ነገር ግን “እንግሊዝኛ ቋንቋን በሚገባ የሚናገሩ እናቶችን ማግኘት ይቻላል ወይ?” የሁሉም ጥያቄ ነበር።
በእውነት የእኛ ችግር ቋንቋውን ያለመቻል ነው ወይስ ደፍሮ ያለመናገር ችግር? ደግሞስ ለብዙ ዘመናት እዚህ ሀገር የኖረ ማኅበረሰብ እንዴት ቋንቋ ችግር ሊሆነበት ይችላል? ወይስ በአካል እዚህ በመንፈስ ሀገር ቤት ነው የምንኖረው? ሀገር ቤትስ ቢሆን እንግሊዝኛ ቋንቋን ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ የተማረ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና ዩኒቨርስቲ በእንግሊዝኛ የተማረ ሰው እንዴት እንግሊዝኛ መናገር ይቸግረዋል? የማርታ ጥያቄዎች ነበሩ። በሉ እናቶችንና እኅቶችን ሰብስቡልኝ አለች። በዘመናዊው ትምህርት ብዙ የተማሩ በሰነፎች ንትርክ ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን ርቀው የነበሩ፣ እዚሁ ሀገር ያደጉ ወጣቶች፣ ይባሱንም አማርኛ ቋንቋም የማይችሉ ሁሉ ይህን ሰምተው ተሰበሰቡ። ማርታ ውይይቱን በእንግሊዝኛ ቋንቋ አደረገችው። ሁሉም ያዳምጣሉ፣ አብዛኛቹ በደንብ መናገር ይችላሉ። ችግሩ ትንሽ የaccent ጉዳይ ብቻ ነው። እርሱ የሚያሳስብ ጉዳይ አይደለም።
በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩ ወላጆች በእውነቱ የሚታዘንላቸው እንጂ የሚታዘንባቸው አይደሉም። ብዙዎቹ ወደዚህ ሀገር ዕድሉን አግኝተው ከመምጣታቸው በፊት በስደት ብዙ ተፈትነዋል። እዚህ ከመጡም በኋላ ሀገሩን እና ባህሉን መልመድ ቀላል አይደለም። ባለው የኑሮ ውድነትም የተነሳ ብዙ ሰዓት መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ላይ ሀገር ቤት ያለ ዘመዳቸው እጃቸውን ይጠብቃል። እዚህ ሀገር መጥቶ ያላየውማ ገንዘብ ከዛፍ ላይ የሚሸመጠጥ እንጂ ተለፍቶ የሚገኝ አይመስለውም። ከዚህም አልፎ ቄሱም፣ ፖለቲከኛውም፣ አርቲስቱም፣ በጎ አድራጎት ሠራተኛውም ገንዘብ አምጡ ነው የሚላቸው። ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ እና ብዙ ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ቢሆኑም እንደ ገንዘብ ምንጭ ብቻ የሚያያቸው በዝቷል። ገንዘባቸውን እየሰጡ የሚገባቸው ክብርና ርህራሄ ሲሰጣቸው አይስተዋልም።
በዚህ ያሉት ካህናትም ቢሆኑ ከኑሮ ባሻገር ብዙ የአገልግሎት ጫና አለባቸው። ሁሉም በየራሱ አለቃ ሆኖ የተሰበሰበ አቅማቸውን እንዳይጠቀሙ የባህልና የፖለቲካ ዓላማ ይዞ ቤተክርስቲያን ውስጥ የመሸገው አስቸጋሪ ኃይል ስለሚያግዳቸው ብዙ አጥቢያዎች ጥቂት ካህናት ብቻ አላቸው፣ ‘ሰሞነኛ’ የሚባልም የለም። ካህናቱ ሁሌም ሰሞነኛ ናቸው። ከቤተ ልሔም እስከ ቀራኒዮ ያለውን የቅዳሴ አገልግሎት ሁሌ ይፈፅማሉ። ስብከቱንም ራሳቸው ናቸው የሚሰብኩት። በአጥቢያው ለሚገለገለው ምዕመን ሁሉ የንስሐ አባት ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያኑን የአስተዳደር ሥራ ይሠራሉ። እንደማንኛውም ስደተኛ ደግሞ ለሀገሩ እንግዳ ናቸው፣ የቋንቋውም ችግር አለ። በእነዚህ ምክንያቶች ልጆችን ብቻቸውን እንዲያስተምሩ መጠበቅ ፍትሃዊ አይሆንም። ነገር ግን የራሳቸው ድርሻ እንደሚኖራቸው እሙን ነው። ይህን ማድረግ የሚችሉትም ማርታዎችንና ናዖዶችን በማክበርና በማቅረብ እንጂ በሁሉም አገልግሎት ላይ የግል ተጽዕኗቸውን ለማሳየት በእንግሊዝኛ ለሚማሩ ሕፃናት የሠላሳ ደቂቃ ተረትና ምሳሌ እያንዛዙ አገልግሎቱን በማወክ መሆን የለበትም።
በምዕራቡ ዓለም ያለው የወላጆችና የልጆች መስተጋብር ውስብስብ ነው። የኑሮ ውጥረት ለልጆች በቂ ጊዜ ለመስጠት አያስችልም። በዚህ ላይ የባህልና የቋንቋ ልዩነቱ ልጆችና ወላጆችን አራርቋል። ዘመናዊው ትምህርትም ሀገር ቤት ካለው የተለየ ስለሆነ ወላጆች ልጆቻቸውን ብዙም ማገዝ አይችሉም። ስለዚህም ወላጆች ልጆቻቸውን በሚመኙት መጠን መርዳት ባለመቻላቸው እየተሳቀቁ፣ ልጆች ደግሞ በሰለጠነው ሀገር በመማራቸው የተሻሉ እየመሰላቸውና ወላጆቻቸውን እየናቁ ክፍተት ሰፍቷል። ይህንን ክፍተት ለማጥበብ ልጆችን መንፈሳዊ ትምህርትን ማስተማር የግድ ይላል። በተጨማሪም ወላጆች ለልጆቻቸው ሲሉ የከፈሉትንና እየከፈሉ ያሉትን መስዋእትነት ልጆች እንዲረዱት የሚያደርግ አሠራር ያስፈልጋል።
በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩ ምዕመናን በፖለቲካ አመለካከትና በብሔር መስመር የመከፋፈል ሰለባዎች ናቸው። ሁሉም በየፊናው ቤተ ክርስቲያን እየመሠረተ አጥቢያዎች ጥቂት ምዕመናን ነው ያላቸው። ለዚህም ፖለቲከኞችና ፖለቲከኛ ካህናት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው። አጥቢያዎችም የክፍፍሉን እሳት ስለሚሞቁ ከመቀራረብ ይልቅ መራራቅን ይመርጣሉ። በዚህም የተነሳ ልጆቻቸው አብረው ኳስ እንኳን እንዳይጫወቱ ያደረጉበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ይህ ሥር የሰደደ ችግር በሌላ አጥቢያዎች ያሉ ልጆች መጥተው እንዳይማሩ ሊያደርጋቸው ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ለልጆች መንፈሳዊ ሕይወት የወላጆች አርአያነት እጅግ አስፈላጊ ነው። አንዳንድ ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚታየው አላስፈላጊ ፍትጊያ እንደሚያስፈራቸውና በዚያ ቢቆዩ እነርሱም እንዳይገቡበት ይሰጋሉ። ልጆቹ It is scary and frustrating! ይላሉ። ታዲያ ወላጆች ራሳቸው በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ እንኳን ሳይቀር የማይስማሙ ከሆነ እንዴት ለልጆቻቸው መልካም አርአያ ሊሆኑ ይችላሉ? አርአያ ከሆኑም በመጥፎ መልኩ ነው። ይህም ልጆች ለቤተ ክርስቲያን ያላቸው አመለካከት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያደርጋል። ስለዚህም ለልጆች ብቻ ሳይሆን ወላጆቻቸውንም ስለክርስቲያናዊ ቤተሰብ ሕይወት ማስተማር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ማርታ፣ ናዖድና ናዖድን የሚወዱት አረጋዊ ካህን ሆነው ሱባዔ ገብተው ፈጣሪያቸውን ከጠየቁ በኋላ በማርታ መሪነት አገልግሎታቸውን ለመጀመር በተሠራው ጥናት ግኝቶች ላይ የተመሠረተ እቅድ አውጥተው ለሰበካ ጉባዔው ለማቅረብ ወሰኑ። ዕቅዳቸውን ጽፈው ከሰበካ ጉባዔው ጋር ለመወያየት እየሄዱ ሳለ ማርታ ናዖድንና አረጋዊ ካህኑን “ቆይ አንድ ጊዜ!” ብላ በሴቶች በር በኩል ወዳለው አጸድ ሥር ወሰደቻቻው። አለቻቸውም አባቴና ወንድሜ ጥሩ ዕቅድ አውጥተናል። ነገር ግን ይህን ዕቅድ እንዳለ ለሰበካ ጉባዔው ብናቀርበው “ሀሳቡ ጥሩ ነው፣ ግን ትግበራው ከባድ ነው” በሚል ምክንያት ሳይጀመር ሊቀር ይችላል። ከዚህ ይልቅ ‘በመጀመሪያ ሰበካ ጉባዔው በአንድነት ሄዶ እኛ ያየነውን እንዲያይ እናድርግ፣ ከዚያ የሚሆነውን አብረን እናያለን’ አለቻቸው። ሄደውም ዕቅድ እንዲያቀርቡ ሲጠብቋቸው አብረው ሄደው እንደ ሐዋርያው ናትናዔል እነርሱ ያዩትን እንዲያዩ ጋበዟቸው።
የደብሩ አስተዳዳሪ ያዩትን ማመን አቃታቸው! የደብሩ ሰበካ ጉባዔ ጸሐፊም “እስከዛሬ የት ነበርን?” አሉ። የሰበካ ጉባዔው አባላትም ሕሊናቸው ወቀሳቸው። ሁሉም ይህንን አገልግሎት ሳንውል ሳናድር መጀመር አለብን በሚለው ሳይነጋገሩ ተስማሙ። በዚያው ቅጽበት ዋናው ኃላፊነት ወደ ሰበካ ጉባዔው ዞረ። አዲስ ዕቅድ አውጥተን መሥራት ባንችል እንዴት ሌሎች የሚያደርጉትን አይተን፣ ከእነርሱም ተምረን ያንን መተግበር ያቅተናል? ከአኃት አብያተ ክርስቲያናትና ከሌሎች አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ጋር ያለን ግንኙነት ከውድድር መንፈስ ወጥቶ የትብብር መንፈስን የሚላበሰው መቼ ነው? ዛሬም ከሃምሳ ዓመት በኋላ የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ‘ጨቁናን ነበር’ የሚል እኮ አይጠፋም። የምንናገረውና የምንጽፈው የቤተ ክርስቲያናችን ታሪክና የብዙ ቅዱሳን አገልግሎት የተፈጸመው በነዚያ ዘመናት መሆኑን ለማስተዋል የሚፈቅድ ፍትሐዊ አእምሮ ግን ብዙ አይስተዋልም። ሆኖም ዋናው ጉዳይ ዛሬ እነርሱ ምን እየሠሩ ነው? እኛስ ከእነርሱ ምን እንማራለን? የሚለው ነጥብ ነው።
የተግባር ሰው የሆነችው ማርታ ሳትውል ሳታድር በዕቅዱ መሠረት የቅዱሳት አንስትን የአገልግሎት ማኅበር አቋቋመች። በዚህም ውስጥ ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ጋር በመተባበር የእንግሊዝኛ ቋንቋን በተሻለ ሁኔታ የሚናገሩ እናቶች ተመርጠው የሕፃናት፣ የልጆችና የወጣቶች ትምህርት ላይ ስልጠና እንዲወስዱ አደረገች። ሦስት ሦስት እናቶች ሆነውም ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን በትምህርት ሥርዓቱ መሠረት ልጆችን በየክፍላቸውና በየዕድሜያቸው ለይተው ለየብቻቸው እንዲያስተምሩ መደበች። ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ስድስተኛ ክፍል ያሉት በአንድ መደብ፣ ከስድስተኛ እስከ አሥራ ሁለተኛ ያሉት በሌላ መደብ እንዲማሩ ሆነ። ከቦታ እጥረትም የተነሳ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ፣ በሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ፣ በሰበካ ጉባዔው ጽሕፈት ቤት፣ በደጀ ሰላም፣ እንዲሁም በአስተዳዳሪው ቢሮ ማስተማር ተጀመረ። እናቶች ልጆቻቸውን ይዘው ይመጣሉ። ልጆቻቸው ሲማሩ እነርሱ በማስተማር ያገለግላሉ። ማርታም ከትምህርቱ በኋላ ያሬዳዊ መዝሙራትን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ታስጠናለች። ድምጿን ለመስማት ሁሉም ስለሚጓጓ በዚህ መርኃግብር ጠጠር መጣያ ቦታ አይገኝም። አንዳንድ ሰነፎች ግን ‘ሴት ልታስተምር አይገባም’ የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስ ቃል ለማደናቀፊያ ያለ ዐውዱ ቢጠቅሱም ሰሚ ስላላገኙ ይህን መንፈሳዊ አገልግሎት ሊገቱት አልቻሉም።
ማርታ የትምህርቱ መጀመር ቢያስደስታትም ልጆች ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣት ናፍቀው፣ መቼ ሰዓቱ በደረሰና በሄድን ብለው ወላጆቻቸውን እንዲጎተጉቱ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ታምናለች። ትምህርት ብቻ ከሆነ ልጆች ሊሰላቹ ይችላሉና። ስለዚህ በቅዱሳት አንስት ማኅበር በኩል እናቶችን አስተባብራ ዘመናዊ የልጆች መጫወቻና አነስተኛ የስፖርት ማዕከል በዚያው በአጥቢያው እንዲሠራ አደረገች። ከትምህርት በኋላ ልጆች ይጫወታሉ፣ ስፖርታዊ ውድድሮችንም በዚያ ያካሂዳሉ። በዚህም አላበቃም። ማርታ የልጆች ትምህርት ንድፈ ሀሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባር መታገዝ አለበት የሚል ጽኑ አቋም ስላላት ልጆችና ወጣቶች ገዳማትን እንዲጎበኙ፣ ድሆችን እንዲረዱ፣ ሌሎች ወጣቶችንም እንዲያስተምሩ የተለያዩ መርኃግብሮች ተቀርፀው የትምህርት አካል ተደረጉ። ወንድሞችም ከእነማርታ ተምረው አገልግሎቱን ለማገዝ የአርድዕትን የአገልግሎት ማኅበር መሠረቱ። የእነማርታንም አገልግሎት አጠናከሩት። ካህናቱም ጎን ለጎን የአብነት ትምህርቱን ለማጠናከር አመቺ ሁኔታ ተፈጠረላቸው።
አዲሱን ትምህርት ልጆቹ በጣም ወደውታል። ለምንስ አይወዱት?! ትምህርቱ በጣም አሳታፊ ነው፣ የሚያሰለች አንዳች ነገር የለውም። የተሻለ ተሳትፎ ለሚያደርጉ ልዩ ልዩ ሽልማት ይሰጣል። የሁሉም ልጆች የልደት ቀን ከትምህርት በኋላ በደማቅ ሁኔታ ይከበራል። የተለያዩ የስፖርትና የክህሎት ውድድሮች ይዘጋጃሉ። አንዳንዴም ወደ ዘመናዊ የመጫወቻ ቦታዎች ይወሰዳሉ። ለበዓላት ለልጆች ልዩ ልዩ ስጦታዎች ይሰጣሉ። ለገና በዓልም አገልጋዮች እናቶች ስጦታ ይዘው እያንዳንዱን ልጅ ቤት ድረስ ሄደው እንኳን አደረሳችሁ ይላሉ። ይህንንም የሚያደርጉት በቅዱሳት አንስት የአገልግሎት ማኅበር የሚያዋጡትን ገንዘብ በመጠቀም ነው።
የእነማርታ ትምህርት ዲጂታል ሚዲያውንም ለማስተባበሪያነት በሚገባ ይጠቀማል። ከቅዳሜው ሰንበት ትምህርት ቤት በተጓዳኝ ሁል ጊዜ ማክሰኞና ረቡዕ ማታ ልጆችን በዲጂታል ሚዲያ መጽሐፍ ቅዱስን ያስተምራሉ። ነገር ግን መርኃግብሮቹ በማኅበራዊ ሚዲያ አይተላለፉም፣ ምክንያቱም ማርታ “ልጆቹን ልናስተምር እንጂ የማኅበራዊ ሚዲያ ግብዓት ልናደርጋቸው አይገባም!” ስለምትል። ስለዚህ ሁሉም መደበኛ መርኃ ግብሮች ከካሜራ የጸዱ ናቸው። ጸጋው ያላቸው አገልጋዮችም የልጆች መማሪያ መጻሕፍትን ያዘጋጁ ነበር። ተሰጥኦው የነበራቸው ደግሞ ኪነ ጥበብንም ያክሉበት ነበር። ሰነፎች “ይህን ሁሉ ትምህርት ማን ያስቀጥለዋል?” ብለው ይጠይቃሉ። ማርታ ግን መልሷ አጭር ነው። ልጆቹ ራሳቸው ያስቀጥሉታል ትላለች። “እንዴት?” ሲሏት ጊዮርጊስ ሐቢብን ጠይቁት ትላለች። ጊዮርጊስ ሐቢብ ወጣቶችን አስተማረ። የእርሱ ተማሪዎች እስከ ጵጵስና ደርሰው ለቤተ ክርስቲያኒቱ አለኝታ እንደሆኗት የማርታ ልጆችም ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ሴቶቹ በቅዱሳት አንስት፣ ወንዶቹ በአርድዕት የአገልግሎት ማኅበር ገብተው ተተኪ ይሆናሉ። ከዚህ በላይ ቀጣይነቱ የተረጋገጠ መንፈሳዊ አገልግሎት ምን አለ? ከዚህስ በላይ ለቤተ ክርስቲያንና ለትውልድ አለኝታ መሆን እንዴት ይቻላል?
ሰነፎች ግን ማርታን “ልጆቻችንን በእንግሊዝኛ እያስተማረች አማርኛ እንዳይችሉ አደረገቻቸው፣ ባህላችንን ልታጠፋብን የተላከች ናት” እያሉ ያሟታል። አንዳንዶችም “የቅብጥ ተላላኪ ናት” እያሉ ስሟን ያጠፋሉ። ሌሎችም “እኛኮ ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ጋር በቀኖና እንለያያለን፣ ልጆቻችንን ከዚያ የተቀዳ ትምህርት እያስተማረች ተሃድሶ ልታደርጋቸው ነው” እያሉ ውስጥ ውስጡን ያጉተመትማሉ። የራሳቸው እንጂ የልጆች ጉዳይ የማይገዳቸው አንዳንድ አገልጋዮችም “ከእንግዲህማ ቅዳሴውም ሁሉም አገልግሎት በእንግሊዝኛ ይሆናል፣ እኛም ላናስፈልግ እንችላለን” በማለት ስጋታቸውን አሰምተዋል። እውነተኞቹ እናቶች ግን “ልጆቻችንን የታደገችልን እርሷ ናት” ይላሉ። በእርስዋም ምክንያት ልጆቻችንን ማስተማር ችለናል ብለው ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ። ልጆቹ ደግሞ እጅግ በጣም ይወዷታል፣ “Mother Martha/እናታችን ማርታ” ይሏታል። እርስዋም ልክ እንደ አዋቂ አክብራ ነው የምታናግራቸው። ፈገግታም ስለማይለያት ልጆች የልባቸውን ሁሉ በነጻነት ይነግሯታል።
ማርታ በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ምንም ብትባል መልስ አትሰጥም። በሃይማኖቷ በኩል ለሚመጣባት ስም ማጥፋት ግን እንዲህ ስትል ትመልሳላች። እኛ ልጆችን ለማስተማር ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት የተማርነው የማስተማሪያ ስልቱን እንጂ ልጆቹ የሚማሩትን የትምህርት ይዘት አይደለም። የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርት ቀጥታ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ነው የተረጎምነው ትላቸዋለች። መዝሙሩንም ዜማውን ሳይለቅ በእንግሊዝኛ ነው ያዘጋጅንላቸው እያለች ታብራራለች። የቤተ ክርስቲያን ትምህርት በግዕዝና በአማርኛ ሲሆን ትክክል፣ በእንግሊዝኛ ሲተረጎም ‘ተሃድሶ’ ሊያሰኝ አይችልም በማለት ተረጋግታ ታስረዳቸዋለች። እንዲያው ቢሆንስ በዶግማ አንድ ከሆንነው ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ይዘቱንስ መማር ምን ነውር አለው? ይልቁንም ሆነ ብለው በዶግማ ከምንለያየው ከሩስያ ቤተ ክርስቲያን ጋር ልዩነት የሌለን አስመስለው የሚያቀርቡትን የዘመናችን ነጋድያንና ፖለቲካዊ ሃይማኖተኞች፣ መጻሕፍቶቻቸውን ወደ አማርኛ ተርጉመው የሚያስተምሩትን ወድንሞቻችሁን እንዴት ዝም አላችኋቸው? በማለት መልስ ታሳጣቸዋለች።
በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ አልፎ የእነማርታ አገልግሎት እንደ ማርታ ያሉ እናቶች ልጆችንና ወጣቶችን በማስተማር የነገዎቹን የቤተ ክርስቲያን ተረካቢዎች በመቅረፅ ረገድ ታላቅ ሚና እንዳላቸው አስመሰከረ። ማርታና እንደ ማርታ ያሉ ጸጋው የበዛላቸው እናቶች የትምህርትና የተለያዩ ፕሮግራሞችን በማስተባበር መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን መፈጸም የሚችሉ መሆናቸውን አረጋገጠ። ማርታና እንደ ማርታ ያሉ እናቶች የልጆችን፣ የእኅቶችና የእናቶችን ዘርፍ በመምራት ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊያን እንድታብብ ማድረግ ቻለ። ይህ አገልግሎት ማርታና እንደ ማርታ ያሉ እናቶች በኅትመት ሚዲያዎች፣ በማኅበራዊና በመደበኛ ሚዲያዎች፣ እንዲሁም በሌሎች የዲጂታልና የድረ መረብ መገናኛ ዘዴዎች ቃለ እግዚአብሔርን በማዳረስ የቤተ ክርስቲያንን የመንፈሳዊ አገልግሎት አድማስ ማስፋት መቻላቸውን በተግባር አሳየ። ማርታና እንደ ማርታ ያሉ እናቶች በዕድሜ ዘመናቸው የተማሩትንና የኖሩትን መንፈሳዊ ሕይወት በመጽሐፍ መልክ በመሰነድና በኪነ ጥበብ በመቀመር ለቤተ ክርስቲያን ቋሚ ምስክርን በማስቀመጥ አለኝታ ሆኗት። ማርታ ግን ዘወትር ይህ በአንድ አጥቢያ ብቻ መወሰን የለበትም፣ ሁሉም አጥቢያዎች እንዲህ ሊሠሩ ይገባል ትላለች።
የእነማርታ የዓመታት ድካም ፍሬ አፍርቷል። ትምህርት ጨርሰው ሥራ የጀመሩ ወጣቶች የማስተማሩን እና የማስተባበሩን አገልግሎት ከእነማርታ ተረክበዋል። አቀላጥፈውም እየመሩት ነው። የአብነት ትምህርቱን የተማሩት ደግሞ ክህነት ተቀብለው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ቅዳሴውን እየቀደሱ ነው። ወንጌልም በሁለቱም ቋንቋዎች ይሰበካል። ከብዙ ዘመናት ድካም በኋላ የእግዚአብሔርም ቅዱስ ፈቃድ ሆኖ ቤተ ክርስቲያን ተተኪ ወጣቶችን አፍርታለች። ቤተ ክርስቲያን የወላድ መካን ልትሆን ትችላለች የሚለው የማርታና የሌሎች አገልጋዮች ስጋት ተወግዷል። አሁን እነማርታ ደርሻቸው ወጣቶቹን ማማከር ነው። ለዚህም የአማካሪዎች ጉባዔ መሥርተዋል።
ከዓመታት በኋላ ከሰንበታቱ በአንዲቱ ቀን ማርታ ያለወትሮዋ ለቅዳሴ አልመጣችም። ያ መረዋ ድምፅ በቅዳሴ ሰዓት አለመኖሩ አንድ ታላቅ ነገር እንደጎደለ ያሳብቃል። ወዳጆቿም በስልኳ ላይ ቢደውሉም ዝግ ነው። ወደ መኖሪያዋ ቢሄዱም ያላትን የቤት መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ ለድሆች መጽውታ መሄዷ ተነገራቸው። ብዙዎች ማርታ በሙያዋ ሠርታ የምታገኘውን ሁሉ ለመንፈሳዊ አገልግሎት እያደረገች ትዳርም ቤትም እንደሌላትና በድንግልና ፀንታ አንድ ክፍል ብቻ ተከራይታ ትኖር የነበረች ቅድስት ሴት እንደነበረች የተረዱት የዚያን ዕለት ነበር። ሁሉም በሆነው ነገር ደነገጠ። ነገር ግን በራሷ ውሳኔ እርሷ ብቻ ወደምታውቀው ቦታ ርቃ መሄዷን ተረድተዋል። አንዳንዱ ገዳም ገብታ ሊሆን ይችላል ይላል። ሌላውም ወደ ሀገሯ ተመልሳ ሊሆን ይችላል ይላል። ግማሹም ሌላ ቦታ ለሥራ ሄዳ ሊሆን ይችላል ይላል። ሁሉም ግን ‘ሊሆን ይችላል’ ነበር። ብዙ ሰው ግን ‘እባክህ ፈጣሪ ሆይ እናታችን ማርታን ጠብቅልን’ እያለ ይጸልይ ነበር።
ቀሲስ ናዖድም ይህንን ሲሰማ ደነገጠ። የቅዱሳት አንስት የአገልግሎት ማኅበር አባላትም ምናልባት ለመረጃ ከሆነ ብለው ወደ ዲጂታል መገናኛቸው ፕላትፎርም ሲገቡ ማርታ ለመጨረሻ ጊዜ የለጠፈችው የአንዲትን ቅድስት ስዕል ነው። ይህች ቅድስት አርሴማ አይደለችም፣ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራም አይደለችም፣ ወለተ ጴጥሮስም አይደለችም። ከማኅበሩ አባላት ይህችን ቅድስት የሚያውቃት ጠፋ። ቀሲስ ናዖድ የዚህችን ቅድስት ስዕል ይዞ ማርታ ወደምታዘወትርበት ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ወደ አንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሄደ። ‘ይህች ቅድስት ማናት?’ ብሎ ሲጠይቃቸውም ቅድስት ዲሚያና ትባላለች አሉት። እርስዋም በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአርባ ደናግላን ጋር ሰማዕትነትን የተቀበለች ናት አሉት። በተጨማሪም በሀገራቸው በስሟ የተሰየመ የደናግላን ገዳም እንዳለም ነገሩት። ማርታም (ትርሲተ ማርያም) በተለያዩ ጊዜያት ገዳሙን እንደጎበኘች ጠቆሙት። “ትርሲተ ማርያም ሆይ በጸሎትሽ አስቢን!” የሚለው የቀሲስ ናዖድ ጸሎት ነበር።
ማስገንዘቢያ
የማርታ ታሪክ ምናባዊ መቼት በዝርዎት ዓለም ያለችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን መሆኗ የተገለፀ ነው። ይህን ያደረግነው በተግባር ከተማርንበት የአኃት አብያተ ክርስቲያናት የመንፈሳዊ አገልግሎት ልማድ አንፃር በዝርወት ዓለም (diaspora) የኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን አጥቢያዎች በቀላሉ ሊቀስሙት የሚገባ ውጤታማ የአገልግሎት መስመር ነው ብለን በማመን ነው። የማርታ አይነት አገልግሎት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ፣ ሰንበት ትምህርት ቤት ባለበት ሁሉ የሚያስፈልግና የሚገባ ነው። የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሕይወት የሚኖረው በወንዶች አገልጋዮችና በመደበኛ ካህናት ብቻ ሲወሰን ሳይሆን ወንዶችም ሴቶችም፣ ካህናትም ምዕመናንም እንደየጸጋቸው ሲሳተፉበት ብቻ መሆኑን የቤተክርስቲያን የቀድሞ ታሪክና የአሁን ሁኔታ ያስረዳናል። ስለሆነም ማርታዎች የበዙባት፣ አገልግሎታቸውም ከጸበል ጸዲቅ አቅራቢነት የተሻገረባትን ቤተክርስቲያን እውን ለማድረግ በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በአጥቢያ ቤተክርስቲያን፣ በሀገረ ስብከትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ማለም፣ መትጋትና መሥራት ይገባል እንላለን። ለዚህ ለሚተጉት ማርታዎችና ናዖዶች ሁሉ አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር የቅዱሳት አንእስትን፣ የቅዱሳን አርድእትን ጸጋና በረከት ያድልልን። አሜን።