ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘጠነኛው አንቀጸ ብፁዓን “ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና (ማቴ 5:11-12)” በማለት ከመከራው መካፈል (ስለእርሱ መነቀፍ፣ መሳደድና ክፉ ስም መሰጠት) የክርስትና ሕይወት መገለጫዎች እንደሆኑ አስተምሯል። ወንጌላዊው ሉቃስም ይህንን ሲጽፍ “ሰዎች ስለሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ፣ ሲለዩአችሁም፣ ሲነቅፉአችሁም፣ ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ፥ ብፁዓን ናችሁ። እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና (ሉቃ 6:22-23)” በማለት መጠላትና መለየትም ጭምር እንደሚጠብቁን ተናግሯል።
ጌታችን ከዚህ በቀደሙት አንቀጾች “እነርሱ(they)“ እያለ በሩቅ (በጊዜ – እስከ ዓለም ፍጻሜ፣ በቦታ – እስከ ዓለም ዳርቻ) በሦስተኛ አካል (third person) ሲገልጻቸው ነበር። እዚህ ላይ ሲደርስ ግን “እናንተ (You)” ብሎ አቅርቦ በሁለተኛ አካል (second person) ተናገረ። በዚህም በተለይ በጊዜው በተራራው ስብከት የነበሩትን፣ በፍጻሜው ግን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚሰበሰቡትን ክርስቲያኖች ላይ አተኩሮ “እናንተ” ብሎ ተናገረ። በዚህ አንቀጽ በተለይም ስለስሜ (ስለሰው ልጅ) በማለት ስለእርሱ ስለሚነቀፉት፣ ስለሚሳደዱት፣ ስለሚጠሉት፣ ስለሚለዩት፣ ስለእርሱም በሐሰት ክፉውን ሁሉ ስለሚባሉት ደቀመዛሙርቱ ተናገረ። ጌታችን በዚህ አንቀጽ “በእኔም ምክንያት/ስለሰው ልጅ” በማለት መከራ የምንቀበልበት ምክንያት በእርሱ (ሰው በሆነ አምላክ) ማመናችን፣ እርሱን መከተላችን ወይም በአጭር አገላለጽ ክርስቲያን መሆናችን መሆኑን አስተምሯል። ይህም በቤተ ክርስቲያን ላይ ለሚመጣው መከራና በመከራም የሚገኘውን ክብር ያስተማረበት ልዩ አንቀጽ ነው።
በተለይም በዚህ አንቀጽ የቀደሙትን በመከራ ያለፉት ቅዱሳን ነቢያትን አነሳቸው። እኔ አስቀድሜ በላኳቸው በነቢያት ላይ እንዲህ ያደርጉባቸው ነበር፣ በእናንተም ላይ እንዲሁ ያደርጋሉ ማለቱ ነው። ነቢያትንም የላከው እርሱ ነው። ሐዋርያቱንም የሚልካቸው እርሱ ነው። ነቢያቱም ሐዋርያቱም ስለእርሱ መከራን ታግሰው ወደ ዘላለም ደስታ እንደሚገቡ ሲያስተምራቸው ይህንን አለ። የእግዚአብሔር መልእክተኞች የነበሩ ነቢያትን ማሳደድ ላኪውን እግዚአብሔርን ማሳደድ እንደሆነ ሁሉ ክርስቲያኖችን ማሳደድም ክርስቶስን ማሳደድ ነው። ክርስቲያኖች የክርስቶስ አካል ናቸውና። ይህንንም የሚያረጋግጥልን ጌታችን ለሳውል የተናገረው ቃል ነው። “በምድርም ላይ ወድቆ ሳለ፦ “ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ?” የሚለውን ድምፅ ሰማ። ሳውልም ጌታ ሆይ፥ ማን ነህ? አለው። እርሱም አለው፦ “አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል(ሐዋ 9:4-5)” አለው። እናስተውል! ጌታችን “ክርስቲያኖችን ለምን ታሳድዳለህ?” ሳይሆን ያለው “ለምን ታሳድደኛለህ?” ነው ያለው። ክርስቲያኖችን ማሳደድ እርሱን ማሳደድ ነውና።
ሲነቅፉአችሁ ብፁዓን ናችሁ።
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ከፊሪሳውያን የመጣ ብዙ መነቀፍን፣ መሰደብንና መዘበትን ታግሷል። በመስቀል ሰቅለውት ሁሉ “ሌሎችን አዳነ እስኪ ራሱን ያድን” እያሉ ይዘብቱበት ነበር። ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዴዎች ጭምር ያንኑ እያሉ ይነቅፉት ነበር (ማቴ 27:44)። እንግዲህ ክርስቶስን በመንቀፍና መከራን በማጽናት የተቀበለች ዓለም ክርስቲያኖችን በመወድስና በቀይ ምንጣፍ ልትቀበል አትችልም። የእውነተኛ ክርስትናም መርህ ይህ አይደለምና። ይልቁንም ጌታችን ሰዎች ሲያመሰግኑን ሲያወድሱንና ሲያደንቁን ወዮላችሁ በማለት ሲያስጠነቅቀን “ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላችሁ፥ ወዮላችሁ፤ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና (ሉቃ 6:26)” በማለት እንዳስተማረው ምስጋናን፣ ውዳሴንና አድናቆትን የምናገኝ ከሆነ ወዮልን፣ እጣ ፈንታችን ከሐሰተኞች አገልጋዮች ጋር ነውና። በእውነት የክርስቶስን ወንጌል ሰብከን ዕንቁ መምህራችን፣ የተዋሕዶ አርበኛ፣ ትሁቱ አገልጋይ እየተባልን በየሚዲያው የምንወደስ ከሆነ ወዮልን።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ሲጽፍ “እኛ ስለ ክርስቶስ ሞኞች ነን እናንተ ግን በክርስቶስ ልባሞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን እናንተ ግን ኃይለኞች ናችሁ፤ እናንተ የከበራችሁ ናችሁ እኛ ግን የተዋረድን ነን። እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፥ እንጠማለን፥ እንራቆታለን፥ እንጐሰማለን፥ እንንከራተታለን፥ በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን፤ ሲሰድቡን እንመርቃለን፥ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፥ ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን፤ እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጥራጊ የሁሉም ጉድፍ ሆነናል (1ኛ ቆሮ 4:10-13)” በማለት ነው የተናገረው። ክርስትና ራስን ዝቅ አድርጎ ስለሌሎች መዳን መከራን መታገስ ነውና። ወዮ! የእግዚአብሔር ምርጥ ዕቃ የተባለ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ እኛ የዓለም ጥራጊ የሁሉም ጉድፍ ሆነናል ካለ በዚህ ኃጢአት በበዛበት ዓለም ያለን አገልጋዮች ራሳችንን ምን ማለት ይኖርብን ይሆን?! ወዮ! እኔ ሞኝ እናንተ ልባሞች፣ እኔ ደካማ እናንት ኃይለኞች፣ እኔ ወራዳ እናንተ ክቡራን ብሎ በልቡ የሚያምን አገልጋይስ ከወዴት ይገኝ ይሆን?! እንግዲህ ወደድንም ጠላንም ክርስትና እንዲህ ናት።
ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ በመከራ ውስጥ በማለፍ ስለሚገኘው ክብር ሲናገር “ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ (1ኛ ጴጥ 4:14)” ብሏል። ስለ ክርስቶስ ስም መነቀፍ ለክርስቲያኖች ክብር ነው። በእውነትም በክርስቶስ በማመናችን እርሱንም በመከተላችን ነቀፋን ተቀብለን የክብር መንፈስን ማግኘት ታላቅ ክብር ነው። ሐዋርያው ስለ ክርስትና ሕይወትም ሲያስተምር “በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችሁን የሚሳደቡ ሰዎች ክፉን እንደምታደርጉ በሚያሙበት ነገር እንዲያፍሩ በጎ ሕሊና ይኑራችሁ። የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ቢሆን፥ ክፉ ስለ ማድረግ ሳይሆን በጎ ስለ ማድረግ መከራን ብትቀበሉ ይሻላችኋልና (1ኛ ጴጥ 3:16-17)” በማለት በበጎ ሕሊና ስለ ክርስትና ሕይወታችን መከራን ብንቀበል እንደሚሻለን ተናግሯል።
ሲያሳድዱአችሁ ብፁዓን ናችሁ።
ጌታችን ሰለመንፈሳዊ አገልግሎት ተልዕኮዎች ባስተማረበት ትምህርቱ “ነገር ግን ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ በምኩራቦቻቸውም ይገርፉአችኋልና ከሰዎች ተጠበቁ፤ ለእነርሱና ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን፥ ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ። አሳልፈውም ይሰጧችኋል… በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ … በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ፤ … ባለቤቱን ብዔል ዜቡል ካሉት፥ ቤተሰዎቹንማ እንዴት አብዝተው አይሉአቸው! (ማቴ 10:16-25)” በማለት ክርስቶስን መስበክ በመከራና በፈተና የሚጸና ሕይወት መሆኑን አስተምሮናል። ይህንንም ፈጽሞ ሲያሳድዱን እንድንጸና አብነት ሆኖናል።
እንዲሁም “ከዚህም ሁሉ በፊት እጃቸውን በላያችሁ ይጭናሉ ያሳድዱአችሁማል፤ ስለ ስሜም ወደ ምኵራብና ወደ ወኅኒ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ ወደ ነገሥታትና ወደ ገዥዎችም ይወስዱአችኋል፤ ይህም ለምስክርነት ይሆንላችኋል (ሉቃ 21:12-13)” በማለት መሳደድ፣ መታሠር፣ በዓለማዊ ፍርድ ቤት መቅረብ ክርስቶስን የመከተል በረከቶች እንደሆኑ አስተምሮናል። በዮሐንስ ወንጌልም “ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል። ባርያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው እንደ ሆኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ። ዳሩ ግን የላከኝን አያውቁምና ይህን ሁሉ ሰለ ስሜ ያደርጉባችኋል (ዮሐ 15:18-21)” በማለት የክርስትና ሕይወት ከዓለም ወጥቶ በዓለም መጠላት መሆኑን ተናግሯል።
ጌታችን ስለ ዘሪና ዘር ባስተማረበት ምሳሌም “እንዲሁም በጭንጫ ላይ የተዘሩት እነዚህ ናቸው፥ ቃሉንም ሰምተው ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፥ ለጊዜውም ነው እንጂ በእነርሱ ሥር የላቸውም፥ ኋላም በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላሉ (ማር 4:16-17)” በማለት ቃሉን ሰምተው ፈተና፣ መከራ፣ ስደት ሲመጣ የሚሰናከሉትን በጭንጫ ላይ በተዘራ ዘር መስሏቸዋል። ቃለ እግዚአብሔር በሕይወታችን ፍሬ ሊያፈራ የሚችለው ይህንን ጭንጫ (መከራ) ታግሰን ማለፍ ስንችል ነውና። ይህም በእያንዳንዳችን ሕይወት የሚመጣውን መከራና ስደት የሚመለከት ሲሆን ይህንን ተቋቁመን የቃሉን ዘር ወደ ፍሬ መለወጥ እንዳለብን የሚያስተምር ምሳሌ ነው።
ጌታችን በወንጌሉ “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ (ዮሐ 16:33)” በማለት እንደተናገረው የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖችም የክርስትና ታሪካቸው የመከራና የስደት ነበር። ወንጌላዊው ሉቃስ ይህንን ሲናገር “አይሁድ ግን የሚያመልኩትን የከበሩትንም ሴቶችና የከተማውን መኳንንት አወኩ፥ በጳውሎስና በበርናባስም ላይ ስደትን አስነሥተው ከአገራቸው አወጡአቸው። እነርሱ ግን የእግራቸውን ትቢያ አራግፈውባቸው ወደ ኢቆንዮን መጡ። በደቀ መዛሙርትም ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው (ሐዋ 13:50-52)” በማለት ቅዱሳን ሐዋርያት በመከራና በስደቱ ሰዓት ጌታችን እንዳስተማራቸው የእግራቸውን ትቢያ አራግፈው እንደወጡ ተናግሯል።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሥጋ የተወለዱ በመንፈስ የተወለዱትን እንደሚያሳድዱ ሲያስተምር “ነገር ግን እንደ ሥጋ የተወለደው እንደ መንፈስ የተወለደውን በዚያን ጊዜ እንዳሳደደው ዛሬም እንዲሁ ነው (ገላ 4:29)” ብሏል። እንዲሁም “በዚህ መከራ ማንም እንዳይናውጥ፥ ለዚህ እንደ ተመረጥን ራሳችሁ ታውቃላችሁና። በእውነት ከእናንተ ጋር ሳለን፥ መከራ እንቀበል ዘንድ እንዳለን አስቀድመን እንነግራችሁ ነበር፤ እንዲሁም ደግሞ ሆነ፥ ይህንም ታውቃላችሁ (1ኛ ተሰ 3:3-4)” በማለት የተመረጥነው መከራን ለመቀበል ነው እያለ ለተሰሎንቄ ሰዎች ያስተምር ነበር። አዎን የእውነተኛ አገልግሎት ሽልማቱ በምድር መከራ መቀበል ሲሆን በሰማይ ደግሞ የሕይወት አክሊል ነው። እኛ ግን ጥቂት አገልግለን ውዳሴን፣ ሹመትንና ሽልማትን የምንጠብቅ፥ ጥቂት ነቀፋ ሲመጣብን ደግሞ የምንደነብር የማኅበራዊ ሚዲያ ሠራዊታችንን የምናዘምት ምስኪኖች ነን።
ይህ የተወደደ ሐዋርያ በክርስቶስ በሚመጣ መሳደድ ደስ እንደሚለው ሲናገር “ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና (2ኛ ቆሮ 12:10)” ብሏል። ይህንን የሚያነብ ሰው እንዴት ሰው መከራን እየተቀበለ፣ እየተንገላታ፣ እየተጨነቀ ደስ ሊለው ይችላል ብሎ ሊያስብ ይችላል። በሥጋዊ አስተሳሰብ ይህ ሊሆን አይችልም። በመንፈሳዊ እይታ ግን መከራ የክብር ምንጭ ስለሆነችና ስለክርስቶስ መከራን መቀበልም ታላቅ ክብርን የሚያስገኝ ስለሆነ ያስደስታል። በሌላው ትምህርቱም ሐዋርያው “የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፥ መርቁ እንጂ አትርገሙ (ሮሜ 12:14)” ማለቱ በሥጋዊ አእምሮ ሲታስብ ግርታን ይፈጥራል። በሥጋዊ አስተሳሰብ ሰው የሚያሳድዱትን ይፋረዳል እንጂ አይመርቅም። በክርስትና ግን ዋናው ጠላታችን ዲያብሎስ ስለሆነ ለሚያሳድዱን እንጸልያለን እንጂ አንፈርድባቸውም። እነርሱም እንደ እኛ ይድኑ ዘንድ ይገባልና።
በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።
አይሁድ ጌታችንን ሳይቀር በሐሰት “ሳምራዊ እንደ ሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ በማለታችን እኛ መልካም እንል የለምን?” (ዮሐ 8:48) ብለውታል። አጋንንትን በኃይሉ ባወጣም “በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል” (ሉቃ 11:15) ብለዋል። እንዲሁም እየበላና እየጠጣ በመጣ “እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ” (ማቴ 11:19) ብለውታል። ጌታችንን ይዘው በሊቀ ካህኑ ፊት ባቀረቡት ጊዜም በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ “ተሳድቦአል እንግዲህ ወዲህ ምስክሮች ስለ ምን ያስፈልገናል? እነሆ፥ ስድቡን አሁን ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል? አለ። እነርሱም “ሞት ይገባዋል ብለው” መለሱ (ማቴ 26:65)። ጌታችን ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በምኩራባቸው ያስተምራቸው ነበር፤ እንዲህም አሉ “ይህን ጥበብና ተአምራት ይህ ከወዴት አገኘው? ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን?እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን? እንኪያስ ይህን ሁሉ ከወዴት አገኘው?” ተሰናከሉበትም። ኢየሱስ ግን። ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ቤቱ በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው(ማቴ 13:54-57)።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ሲያስተምር አንዳንዶቹ “ይህ ለፍላፊ ምን ሊናገር ይወዳል?” ይሉ ነበር። ሌሎችም የኢየሱስንና የትንሣኤውን ወንጌል ስለ ሰበከላቸው “አዲሶችን አማልክት የሚያወራ ይመስላል” ይሉ ነበር (ሐዋ 17:18-19)። ቅዱስ ጳውሎስ ስለራሱ ሲመልስ ፊስጦስ በታላቅ ድምፅ “ጳውሎስ ሆይ፥ አብድሃል እኮ፤ ብዙ ትምህርትህ ወደ እብደት ያዞርሃል” (ሐዋ 26:24) ብሎታል። ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ “በክፉ ወሬና በመልካም ወሬ ራሳችንን እናማጥናለን፤ አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን፤ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፤ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፤ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፤ኀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፤ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለ ጠጎች እናደርጋለን፤ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው (2ኛ ቆሮ 6:8-10)” በማለት አስተምሯል።
ነገር ግን በመጥፎ ግብራችን (በእውነት) ብንከሰስ ግን በሰማይ ዋጋ አይኖረንም። መልካም ባለማሰብ፣ አንደበታችንን ባለመግታት፣ በማምታታት፣ ኃጢአትን በማድረግ ወይም በስንፍና ምክንያት ብንከሰስ የሥራችን ውጤት ነው እንጂ ጽድቅ አይደለም። ጌታችን በዚህ አንቀጸ ብፁዓን ያስተማረው እውነትን በመናገራቸው፣ ክርስቶስን በመስበካቸው በሐሰት የሚነቀፉትን፣ የሚሰደቡትን፣ የሚከሰሱትን ነው። እኛማ በደካማ ምግባራችን ብንከሰስ፣ ብንወቀስ ለበደልነው በደል፣ ላጠፋነው ጥፋት ቅጣት እንጂ ጽድቅ አይደለም። ይህንን በበዳላችን ምክንያት የመጣብንን ቅጣት ወንጌልን እየጠቀስን “ስለእውነት መከራ እየተቀበልን ነው” እያልን ራሳችንን እና ሌሎችን ማታለል የለብንም።
ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ።
ጌታችን በስሙ ለሚነቀፉ፣ ለሚሳደዱና ክፉውን ሁሉ ለሚባሉ ታላቅ ተስፋን ሰጥቷቸዋል። ይህም “ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነው” የሚል ነው። በእውነትም በሰማያት ታላቅ ዋጋ የተባለ የዘላለም ሕይወትን ማግኘት እጅግ ታላቅ ነው። ከዚህ የሚበልጥ ነገር የለምና። በዚህም “ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ” በማለት በክርስቶስ በማመናችን በመነቀፍ፣ በመሳደድና በመጠላት ውስጥ አልፈን የምናገኘው ዋጋ የሚያስደስት መሆኑን ተናገሯል። ከዚያም ቀጥሎ “ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና” በማለት ስለስሙ መከራን የሚቀበሉ ቁጥራቸውና ዕድል ፈንታቸው ከቀደሙት ነቢያት ክብር ጋር መሆኑን ተናግሯል።
ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ መንፈስ ቅዱስን ተመልቶ ሊወግሩት ለመጡት አይሁድ “ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድሞ የተናገሩትን ገደሉአቸው፤ በመላእክት ሥርዓት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም አሁን እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ገደላችሁትም (ሐዋ 7:52)” በማለት አይሁድ ስለክርስቶስ ትንቢት የተናገሩትን ቅዱሳን ነቢያት ሁሉ ያሳድዱና ይገድሉ እንደነበር፣ ኋላም ዘመኑ ሲደርስ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደውን ክርስቶስን በመስቀል እንደ ገደሉት ይነግራቸው ነበር። ክርስቲያኖችም ወደ ክብር የሚደርሱት በመከራ ውስጥ በማለፍ የቀደሙት ነቢያትን እንዲሁም ክርስቶስን በመከራ ሲመስሉት መሆኑን ሲያጠይቅ ይህንን ተናግሮ እርሱም ሰማዕትነትን ተቀብሎ የማታልፈውን ክብር አግኝቷል።
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስም በመከራ ስለሚገኘው ክብር ሲናገር “ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤ ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ። ስለክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ። ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጒዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤ ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር። (1ኛ ጴጥ 4:12-16)” በማለት ወርቅ ወርቅነቱ የሚታወቀው በእሳት ሲፈተን እንደሆነ ሁሉ ክርስትናም የሚጸናው በመከራ ሲፈተን እንደሆነ በመግለጽ በዚህም በሚገኘው ክብር ደስ ሊለን እንደሚገባ አስተምሯል። ንዑድ ክቡር የሚሆን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን (ሮሜ 8:17)” በማለት የመከራ መቀበልን ታላቅ ዋጋ ተናግሯል።
ብርሃነ ዓላም ቅዱስ ጳውሎስ በፊሊጵስዮስ መልእክቱ “እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ (ፊልጵ 3:10)” በማለት በክርስቶስ መከራ መካፈልን ይናፍቅ ነበር። በሰማያት ታላቅ ዋጋ የሚገኘው በመከራው በመካፈል ነውና። ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም የሆነው ክርስቶስ በደሴተ ፍጥሞ በግዞት ለነበረው ለወንጌላዊው ዮሐንስ በራዕይ “ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ፥ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፥ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ (ራእይ 2:10)” እንዳለው ስለክርስቶስ መከራን መቀበል ለሕይወት አክሊል የሚያበቃ ነው። የክርስትና ሕይወት የመጨረሻ ግብም የሕይወት አክሊልን ማግኘት ስለሆነ ሁላችንም ለዚህ ልንተጋ ይገባል።
ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።
የቀደሙት ነቢያት ስለእግዚአብሔር አስተምረው በመከራ ውስጥ ያለፉ ሰማዕታት ነበሩ። ጌታችንም ስለእነዚህ ነቢያት ሲናገር “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም። እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል። እላችኋለሁና፥ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም (ማቴ 23:37)” በማለት አስቀድሞ የላካቸው ነቢያት የገጠማቸው መወገርና መገደል እንደነበር ተናግሯል።
ጌታችን በዕለተ ዕርገቱ ለሐዋርያቱ “በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ (ሐዋ 1:8)” ብሏቸዋል። በዚህም መሠረት ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጴጥሮስ “እንግዲህ እኔ፥ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ የክርስቶስም መከራ ምስክር ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ፥ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤ በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፤ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ (1ኛ ጴጥ 5:1-4)” በማለት ይህ ምስክርነት በቃል ብቻ ያይደለ በክርስቶስ መከራ ተካፋይ በመሆንም ጭምር እንደሆነ አስተምሯል።
በተጨማሪም ይህ ሐዋርያ በመልእክቱ “ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን። ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፥ በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ (2ኛ ጴጥ 1:4-8)” በማለት ለክብር የምንበቃበትን ስነምግባር አስተምሯል። እንዲሁም “ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፥ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል። የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና (1ኛ ጴጥ 2:20-21)” በማለት ከመከራው ተካፍለን ታላቁን ዋጋ እንድናገኝ አስተምሮናል።
አሰርገዋ ለቤተ ክርስቲያን በደመ ሰማዕታት
ቀደምት አበው በፍትሐ ነገሥት “ስለጌታችን ስምና ስለቀናች ሃይማኖት ስለእግዚአብሔርም ፍቅር ዐላውያን በቅጣት የሚያስቃዩትን ክርስቲያናዊ ቸል አትበሉ። በእውነት ወዛችሁ ተንጠፍጥፎ ካገኛችሁት ገንዛባችሁ ኃይልን ያገኝበት ዘንድ የሚሻውን በእነርሱ ዘንድ ዕረፍትን ያገኝ ዘንድ ስለዋጋቸው ለሚጠብቁት ጭፍራዎች የሚሰጣቸውን ላኩለት እንጂ። ወውእቱ ሰማዕት ቅዱስ ወእኅሁ ለክርስቶስ፤ ወወልደ ልዑል፤ ወማኅደረ መንፈስ ቅዱስ፤ ወሰማዕተ ሕማሙ ለክርስቶስ፤ ወሱታፌ ለእርእያ ስብሐቲሁ / ይኸውም ቅዱስ ሰማዕት የክርስቶስ ወንድም፤ የልዑል ልጅ፤ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ፤ የክርስቶስ የመከራው ምስክር፤ የጌትነቱ እርእያ ተባባሪ ነው/ (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 20 ቁ 745)” በማለት እንደጻፉልን ስለክርስቶስ መከራ የሚቀበሉትን የክርስቶስ የመከራው ምስክሮች ብለን እናከብራቸዋለን።።
እንዲሁም በዚሁ በአንቀጸ ሰማዕታት “ወእለሂ ይሰድድዎሙ በእንተ ሃይማኖት ወይጒይዩ እምሀገር ውስተ ሀገር በእንተ ትእዛዘ እግዚእነ ተወከፍዎሙ ወአዕርፍዎሙ። ወርብኅዎሙ፣ ወአክብርዎሙ ከመ ሰማዕታት/ ስለሃይማኖት የሚያሳድዷቸውን፣ ስለ ጌታችን ትእዛዝ ከአገር ወደ አገር የሚሸሹትን ተቀበሏቸው አሳርፏቸውም፣ ጥቀሟቸውም፣ እንደ ሰማዕታትም አድርጋችሁ አክብሯቸው/(ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 20 ቁ 749)” እንዳሉት ስለክርስቶስ መከራን የሚቀበሉትን እንደሰማዕታት አድርገን እንድናከብራቸው ታዝ ዘናል። እነርሱን የሚረዳ፣ የሚያከብር ብጹዕ ነውና። ስለዚህ እኛ ሰማዕት መሆን ባንችል እንኳን እነርሱን አክብረን መክበር ይጠበቅብናል።
ቅዱስ ዮሐንስም በራዕዩ “አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ፦ “ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?” አሉ። ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፥ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው (ራእይ 6:9-11)” በማለት በክርስቶስ መከራ የተካፈሉ ነፍሳት ነጭ ልብስ (የዘላለም ክብር) እንደተሰጣቸው ጽፎልናል። ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና ሐሴትን አድርጉ የተባለው ይህ የዘላለም ሕይወት ነው።
ብርሃነ ዓላም ቅዱስ ጳውሎስ በፊሊጵስዮስ መልእክቱ “ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ። በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህ ስለ ክስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤ በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና (ፊል 1:27-30)” በማለት በክርስቶስ መከራ መካፈል የመዳናችን ምልክት መሆኑን አስተምሮናል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም “መከራ የሌለበትን ዘመን ፈጽሞ አትመኙ፤ የምታተርፉት ነገር የለምና” ክርስቲያን የሚያተርፈው በክርስቶስ መከራ በመካፈል መሆኑን ተናግሯል።
ቅዱስ ያሬድ ማኅሌታይ “በከመ አሰርገዎሙ ለሰማይ በከዋክብት፤ ወለምድርኒ በሥነ ጽጌያት፤ ከማሁ አሰርገዋ ለቤተ ክርስቲያን በደመ ሰማዕታት /ሰማያትን በከዋክብት ያስጌጠ፤ ምድርንም በአበባ የሸለመ፤ ቤተ ክርስቲያንንም በሰማዕታቱ ደም አስጌጣት” እንዳለው በክርስቶስ መከራ ተካፋይ ሆነው የክርስቶስ ምስክር የሆኑት ሰማዕታት የቤተ ክርስቲያን ጌጦች ናቸው። እኛም በክርስቶስ መከራ መካፈል ይገባናል እንጂ የሰማዕታትን ገድል በመተረክና በመስማት ብቻ ተወስነን መቅረት የለብንም። ቅዱስ ያሬድ “ሰማዕትኒ ያሰረግዋ ለቤተ ክርስቲያን በገድሎሙ/ሰማዕታት በገድላቸው ቤተ ክርስቲያንን አሸበረቋት” እንዳለው ገድላቸው ጌጥ ቢሆነንም ምሳሌም ጭምር መሆኑ መረሳት የለበትም።
ሰማዕታት በክርስቶስ መከራ በመካፈል እርሱ ዓለምን እንዳሸነፈው እነርሱም ይህንን ዓለም ድል አድርገዋል። ሊቁ አባ ሕርያቆስም “ያብዕክሙ ሀበ ሀለዉ ማኅበረ ነቢያት ቅዱሳን፤ ወማኅበረ ሐዋርያት ሰባክያን፤ ወማኅበረ ሰማዕት መዋዕያን። ወማኅበረ ጻድቃን ቡሩካን፤ ወማኅበረ ካህናት ስዩማን፤ ወማኅበረ መላእክት ትጉሃን። ወማኅበረ ደናግል ወመነኮሳት ፍጹማን።/የቅዱሳን ነብያት ማኅበር፥ ያስተማሩ የሐዋርያት ማኅበር፥ ድል የነሱ የሰማዕታት ማኅበር፥ ቡሩካን የሚሆኑ የጻድቃን ማኅበር፥ የተሾሙ የካህናት ማኅበር፥ ትጉኀን የሚሆኑ የመላእክት ማኅበር፥ ፍጹማን ደናግል መነኮሳት ወዳሉበት ያግባችሁ (ቅዳሴ ማርያም ቁ 159)” እንዳለው እግዚአብሔር ከእነዚህ በክርስቶስ መከራ ተካፋይ ሆነው ድል ከነሱ ከሰማዕታት ማኅበር ይደምረን። አሜን።
ማስታወሻ: አንዳንድ መምህራን ይህንን አንቀጽ ከቀደመው ማለትም “ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” ከሚለው ጋር አብረው ያስተምራሉ። ነገር ግን የቀደመው አንቀጽ ስለጽድቅ ሲሆን ይህ ደግሞ በተለይ በክርስቶስ ስም ስለሆነና የተሰጠው ተስፋም ስለሚለያይ ለይተን ዘጠነኛ አድርገን አቅርበነዋል።