የእውነተኛይቱ ቤተክርስቲያን መገለጫዎች
እንደ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አመሥጥሮ ቤተ ክርስቲያን ማለት “እግዚአብሔር ግዕዛን ካላቸው ፍጥረታት ጋር ያለው ግንኙነት ነው ይላሉ፡፡ ከዚህም የተነሣ የቤተ ክርስቲያንን ዕድሜ በሦስት ይከፍሉታል፥ አንደኛ የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን ሰው ከመፈጠሩ በፊት በዓለመ መላእክት የነበረችው የመላእክት አንድነት ናት፤በሊቃውንት አመሥጥሮ ሁለተኛዋ የቤተ ክርስቲያን ዕድሜ ከአቤል ጀምሮ እስከ ሐዲስ ኪዳን መግቢያ ድረስ የነበሩ ደጋግ ሰዎች አንድነት ነው፤ ሦስተኛዪቱ እና የመጨረሻዪቱ ግን በክርስቶስ ደም የተመሠረተችው የክርስቲያኖች አንድነት ናት፡፡ እርስዋም የጸጋና የጽድቅ ምንጭ ናት ከላይ የተወሱት ሁለቱ ግን ምሳሌነት ብቻ ነበራቸው፡፡” (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ገጽ 12) ከላይ እንደተገለጸው ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ በሚከተሉት ነጥቦች እርስዋን መስለው በዙሪያዋ ከከበብዋት ትለያለች፡፡
የቤተክርስቲያን መገለጫዎች የሚባሉት በኒቅያ ጉባዔ በተደነገገው የሃይማኖት መሠረት (Creed) ላይ “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባዔ ዘሐዋርያት (ከሁሉም በላይ በምትሆን የሐዋርያት ጉባዔ አንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን)” የሚለው ነው፡፡ እንዲት ቤተ ክርስቲያንን ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ የሚያሰኛት በ381 ዓ.ም በቁስጥንጥንያ የተሰበሰቡት 150 ኤጲስ ቆጶሳት (ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን) በቀኖና ሃይማኖታቸው ላይ እንደገለጡት አንዲት(one ) ቅድስት (Holy) ኩላዊት (የሁሉና በሁሉ ያለች(universal )) እና ሐዋርያዊት (Apostolic succession) ስትሆን ብቻ ነው፡፡ ከእነዚህ ከአራቱ አንዱን ያጎደለች የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ልትሆን አትችልም አይደለችምም፡፡