በምስጢረ ሥጋዌ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችና ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ

ምስጢረ ሥጋዌ (አምላክ ሰው የሆነበት ምስጢር) ተረድተው ለሚያምኑት የመዳን መሠረት፣ በከንቱ ፍልስፍና ለሚጠራጠሩት ደግሞ የመሰናከያ አለት ነው፡፡ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “እርሱም በቃሉ ለሚጠራጠሩና የተፈጠሩበትን ለሚክዱ የዕንቅፋት ድንጋይና የማሰናከያ ዐለት ነው፡፡” (1ኛ ጴጥ. 2፡8) ያለው ለዚህ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ከጌታችን ልደት ጀምሮ በሐዋርያትም ዘመን ከዚያም በኋላ እኛ አስካለንበት ዘመን ድረስ ምስጢረ ሥጋዌ ላይ ብዙ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ጥያቄዎቹም ምስጢሩን በሚገባ ካለመረዳት ወይም በተሳሳተ መንገድ ከመረዳት የሚመነጩ ናቸው፡፡ በተለያየ ጊዜ የተነሱ መናፍቃን ያነሷቸውንና ሐዋርያዊት ጉባኤ በሆነች የቅድስት ቤተክርስቲያን አንድነት የተወገዙባቸውን (የተረቱባቸውን) አስተምህሮዎች ካለመረዳት ዛሬም ብዙ ወገኖች ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡ በዚህች የአስተምህሮ ጦማርም በምስጢረ ሥጋዌ ላይ የሚነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎች ተዳስሰዋል፡፡

ወደ ጥያቄዎቹ ከመግባታችን በፊት ስለመጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ነጥቦችን ማስተዋል የሚያስፈልግ መሆኑን እናስገነዝባለን፡፡ የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ አጻጻፍ ዘይቤ የሰዋስው፣ የጊዜ ቅደም ተከተልን፣ እንዲሁም የድርጊት ቅደም ተከተልን የማይጠንቅቅ  መሆኑን ነው፡፡ የወደፊት ጊዜን በኃላፊ ግስ መግለጽ የመጽሐፍ ቅዱስ አጻጻፍ ጠባይ ነው፡፡ ለምሳሌ በኢሳ 53፡1 ያለውን ብናይ ‹‹በእውነት ደዌያችንን ይቀበላል›› ማለት ሲገባው (ነቢዩ ከጌታችን አስቀድሞ የነበረ ነውና) ‹‹በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ›› ይላል፡፡ ቅዱስ ዳዊትም እንዲሁ ‹‹በቀሚሴ ዕጣ ይጣጣላሉ›› በማለት ፈንታ ‹‹ዕጣ ተጣጣሉ›› ብሏል፡፡ መዝ 21፡12 በሌላ በኩል ቅዱሳን ነቢያት መጻዕያትን እንደተፈጸሙ አድርገው መናገራቸው የእምነታቸውን ጽናትና የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ያስገነዝበናል፡፡ የቅዱሳት መጻሕፍት መተርጉማን አባቶቻችን “መጽሐፍ ምስጢር እንጂ ዘይቤ አይጠነቅቅም” የሚሉት ለዚህ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ዓላማ የእግዚአብሔርን ማዳን፣ የመንግስተ ሰማያትን ጉዞ ማሳወቅ፣ ማስረዳት እንጂ የቋንቋ ብሂል ማስተማር አይደለም፡፡

ስለሆነም ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉበትን ዓላማ፣ በአንዱ መጽሐፍ ያለው ምንባብ ከሌሎች መጻሕፍት ጋር ያለውን ትይይዝ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተጻፉ የቀደምት ሊቃውንትን ትርጓሜዎች አገናዝበን ልንተረጉም ይገባል እንጂ ማናችንም መጽሐፍ ቅዱስን በራሳችን ስሜት ልንተረጉመው አልተፈቀደልንም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ይህን በመጀመሪያ ዕወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፡፡ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፤ ዳሩ ግን ቅዱሳን ሰዎች ከእግዚአብሔር ተልከው በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ተናገሩ፡፡” (2ኛ ጴጥ. 1፡20-21) በማለት አስተምሮናልና፡፡ ማኅቶተ ቤተክርስቲያን፣ ንዋይ ኅሩይ የተባለ ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስም “በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ሕግ አገልጋዮች አደረገን፤ ፊደል ይገድላል፣ መንፈስ ግን ሕያው ያደርጋል፡፡” (2ኛ. ቆሮ. 3፡6) በማለት መክሮናል፡፡ ስለሆነም የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር እንደ አባቶቻችን ልቡናን ከፍ ከፍ በማድረግ፣ በትሁት ስብዕና፣ ከቀደሙት ሊቃውንት በመማር፣ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ሊሆን ልንመረምር ይገባል እንጂ ቃላትና ፊደላትን ብቻ በመከተል ሳያገናዝቡ የእምነት ድምዳሜ ላይ በመድረስ ሊሆን አይገባም፡፡ ፊደልን በመከተል መንገድ የሄዱት ሁሉም ጠፍተዋልና፡፡

ሁለተኛው ማስተዋል የሚያስፈልገው ነገር ከጥንት ዘመን በነበረው መጽሐፍ ቅዱስና በዘመናችን ባሉት በተለያዩ ቋንቋዎች የታተሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች መካከል አንዳንድ ቦታዎች ላይ የቃላትና የትርጉም ልዩነቶች መኖራቸውን ነው፡፡ ይህም ልዩነት (Translation Bias) በተርጓሚው፣ አስተርጓሚው ወይም በአሳታሚው ዝንባሌ/ተጽዕኖ የመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ቀደም ወዳሉት እትሞች ሄዶ ማረጋገጥ ተገቢ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ለምሳሌ በሮሜ 8፡34 (‹‹የሚማልደው››) በዕብ 7፡25 (‹‹ሊያማልድ››) በ1ኛ ዮሐ 2፡1 (‹‹ጠበቃ››) ያሉት ከቀደሙት የመጽሐፍ ቅዱሳት ቅጂዎች ጋር ያላቸውን የትርጉም ልዩነት ማስተዋል ይገባል፡፡

 አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ” (ማቴ 27፡46)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን በተሰቀለ ጊዜ “አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?” ማለቱን ይዘው በልዩ ልዩ ክህደት ራሳቸውን የሚጎዱ ወገኖቻችን አሉ፡፡ አንዳንዶቹ በፈቃዱ የተቀበለውን መከራ በግዳጅ የተቀበለ የሚመስላቸው አሉ፡፡ ሌሎቹም አምላክነቱን ለመካድ መነሻ ያደርጉታል፤ ሌላ አምላክ ያለው (የተፈጠረ) ይመስላቸዋል፡፡ ይሁንና ጌታችን መከራውን ስለ እኛ በፈቃዱ የተቀበለ ሲሆን ዓለማትን የፈጠረ የሁሉ አስገኝ እንጂ በማንም በማን የተፈጠረ አይደለም፡፡ ጌታችን ይህንን የተናገረው ስለ ሦስት ነገሮች ነው፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት ለአብነት ነው፡፡ በሃይማኖት ምክንያት መከራ ሲያጸኑባችሁ ‹‹አትተወን አበርታን›› እያላችሁ አምላካችሁን ተማጸኑ በችግር በሃዘናችሁም ጊዜ ጥሩኝ ሲለን ነው፡፡ ይህም ‹‹ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና›› ስላለ ነው (ማቴ 11፡29)፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ስለ አዳም ተገብቶ የተናገረው ነው፡፡ ተላልፎ ስለተሰጠለት ስለ አዳምና ስለልጆቹ የተናገረው ቃል ነው፡፡ ስለ አዳም ተገብቶ የአዳምን መከራ ተቀበለ የአዳምን ጩኸት ጮኸ፣ ሕመም የሚሰማማውን ሥጋ እንደለበሰ ለማመልከት ታመመ፣ የባሪያውን መልክ ይዞ በትህትና ሰው ሆኖ ተገልጧልና ራሱን አዋረደ እስከ መስቀል ሞትም እንኳ ሳይቀር ታዘዘ (ፊልጵ 2፡7) ይህ የለበሰው ስጋ ይራባል፣ ይጠማል፣ይታመማልና ጌታም በለበሰው ሥጋ የተቸነከረው ችንኳር ያሰቃያል፣ ያቆስላል ያማልና አምላኬ አምላኬ ብሎ አባቱን ተጣራ።

ሦስተኛቸው ምክንያት የትንቢት ቃል ይፈጸም ዘንድ የተናገረው ነው፡፡ በዙሪያው ተሰብስበው ለነበሩት አይሁድ ‹‹ይህ ለእኔ ተጽፏልና ሂዱና ሕግና ነቢያትን አንብቡ›› ሲል ነበረ አይሁድ የነቢያትንና የሙሴን መጻሕፍት ያውቁ ስለነበር ይህ የተነገረ ስለ እርሱ እንደሆነ እንዲያምኑ ነበር፡፡  ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ጌታችን ይህን ጸሎት በአዳም ተገብቶ “አምላኬ አምላኬ ተመልከተኝ ለምን ተውኸኝ?” (መዝሙር 21፡1) በማለት እንደሚጸልይ በትንቢት ተናግሮ ነበር፡፡ ጌታችን ይኽንን ጸሎት በሚጸልይበት ጊዜ አዳም የተሰጠውን ተስፋ እየጠበቀ “አምላኬ አምላኬ ተመልከተኝ ለምን ተውኸኝ?” ብሎ እየተማጸነ እንደነበር የቤተክርስቲያን መተርጉማን ያስረዳሉ፡፡ በሌላም መንገድ በማቴ 12፡29 ‹‹ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ እቃውን ሊነጥቀው እንዴት ይችላል?›› ብሎ እንደተናገረው ሰይጣንን ወደ እግረ መስቀሉ አቅርቦ ለማሰርና ምርኮኞችን ለማስመለስ ነው፡፡ ሰይጣን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተዋሕዶ ከልደቱ ጀምሮ ግራ ተጋብቶ ይኖር ነበር፡፡ አንድ ጊዜ በአምላክነት፣ ሌላ ጊዜ በሰውነት ሲገለጥ አምላክነቱን የተረዳ ሲመስለው ፈርቶ ይሸሽ ነበር፤ ሰውነቱን የተረዳ ሲመስለው ደፍሮ ሊፈትነው ይቀርብ ነበር፡፡ ሰይጣንን አስሮ በአካለ ነፍስ ሲኦልን የበረበረ ጌታችን “አምላኬ አምላኬ” ማለቱን ሲሰማ ሰይጣን ዕሩቅ ብዕሲ (ፍጡር) መስሎት እንደ ቀደሙት ነቢያት ሥጋውን በመቃብር ነፍሱን በሲኦል እገዛለሁ ብሎ ሲቀርብ በእሳት ዛንጅር አስሮ ቀጥቶታል፣ በሲኦል የነበሩ ነፍሳትንም ነጻ አድርጓል፡፡ (ቆላስይስ 2፡14-15) ስለሆነም አባቶቻችን ጌታችን “አምላኬ፣ አምላኬ” ማለቱ ለአቅርቦተ ሰይጣን (ሰይጣንን አቅርቦ ለማሰር) መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ እርሱ ፍጹም ሰው ነውና ‹‹አምላኬ አምላኬ አለ፣ ፍጹም አምላክ ነውና ‹‹ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ›› ሲል በቀኙ ለተሰቀለው ወንበዴ ተናገረው፡፡ በዚህም በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ መሆኑን አረጋገጠልን፡፡ ‹‹አምላኬ አምላኬ›› ብሎ ሁለት ጊዜ ‹‹አምላኬ›› ያለው ነፍስና ሥጋን፣ ለጻድቃንና ለኃጥአን፣ እንዲሁም ሕዝብና አሕዛብን ለመካስ የመጣ መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡

“ወደ አባቴ፣ ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬ ወደ አምላካችሁም አርጋለሁ” (ዮሐ 20፡17)

ይኽንንም ቃል ይዘው ክብር ይግባውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የሚጠራጠሩ፣ ልዩ ልዩ ክህደትንም የሚናገሩ አሉ፡፡ይሁንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ቃል የተናገረው ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላ ሲሆን ይህም ፍጹም በተዋሕዶ ሰው መሆኑን ለማጠየቅ ነው። ተዋሕደው ያሉ ሥጋና መለኮት ከትንሣኤም በኋላ ለአፍታም እንዳልተለያዩ ሊያስረዳን ‹‹ወደ አምላኬ›› ብሎ ተናግሯል። አንድም “በተዋሕዶ ለነሳሁት ሥጋ ፈጣሪው ወደሚሆን” አምላክ ዐርጋለው የሚል ትርጉም ይኖረዋል። ወደ አምላኬ አለ፤ ምክንያቱም መለኮት የፈጠረውን ሥጋ ንብረቱ አድርጓልና፡፡ አንድም የተዋሐደውን ሥጋ በመቃብር ጥሎት እንዳልተነሳ ለማጠየቅ ፤ ቀጥሎም አምላካችሁ አለ፤ በጥንተ ተፈጥሮ ሁላችንን ይፈጥረናልና ነው፡፡

እንደዛ ባይሆን ‹‹ወደ አምላካችን›› ብሎ በተናገረ ነበር። ወደ አባታችንና አምላካችን ብሎ በአንድነት ቃል ቢገልጸው ኖሮ እርሱም ሆነ እኛ ከአንድ ወገን መሆናችንን ያስረዳ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ለመለየት ወደ አባቴና አባታችሁ ፤ ቀጥሎም አምላኬና አምላካችሁ አለን እንጅ:: ስለዚህ ይህ ቃል የሚያመለክተው ክርስቶስ በተዋሕዶ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መሆኑን ነው።  እርሱ ‹‹ወደ አባቴ›› ያለውም ለእርሱ የባህርይ አባቱ መሆኑን ሲገልጽ ነው፡፡ ቀጥሎም ‹‹ወደ አባታችሁ›› ያለው ደግሞ ለእኛ የፈጠረን አባታችን መሆኑን ሲያመለክት ነው፡፡ ሁለቱን ለመለየት ‹‹ወደ አባታቸን›› ሳይሆን ‹‹ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ›› አለ፡፡ ሊቁ አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህንን ሲያስረዳ እንዲህ አለ “ዳግመኛም በተነሣ ጊዜ ከዚህ ከአዳም ባሕርይ ሰው መሆኑን አስረዳ ፈጽሞ ከእርሱ ወደአልተለየው ወደአብም ከማረጉ አስቀድሞ ለደቀ መዛሙርቱ አምላኬ አምላካችሁ አለ፤ ይህን በሰሙ ጊዜ ይህን የተናገረ ሥጋ ብቻ እንዳይመስላቸው ሰው የሆነ እርሱ እግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ አቡየ ብሎ ከዚህ በኋላ አምላኪየ አለ እንጂ፡፡…ከእኔ ጋር አንድ አካል አንድ ባሕርይ ላደረግኹት ለሥጋ ሥርዓት እንደሚገባ እንዲህ አባቴን አምላኪየ ብዬ ጠራሁት ይላል፡፡” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ 68፡12-13) ቅዱስ ኤጲፋንዮስም ይህንን ቃል ሲተረጉም እንዲህ አለ፡- “የባሕርይ ልጁ ስለሆነ አቡየ (አባቴ) አለ፤ ለደቀመዛሙርቱ ስለሰጣቸው ልጅነትም አቡክሙ (አባታችሁ) አለ፤ ባሕርየ ትስብእትን ስለሚመስል ባሕርየ አርድእት አምላኪየ አለ ይኸውም ፈጣሪያችሁ ማለት ነው” (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤጲፋንዮስ 54፡8)

“ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና” (ዕብ.7:25)

ይህ ንባብ በብዙ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጅዎች ይገኛል፡፡ ከግዕዙ የተተረጎመው ግን እንዲህ ይላል “ለእነዚያስ ብዙዎች ካህናት ነበሩአቸው፤ ሞት ይሽራቸው፣ እንዲኖሩም አያሰናብታቸውም ነበርና፡፡ እርሱ ግን ለዘለዓለም ይኖራል፤ ክህነቱ አይሻርምና፡፡ ዘወትር በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሊያድናቸው ይቻለዋል፤ ለዘለዓለምም ሕያው ነውና ያስታርቃቸዋል፡፡” (ዕብ. 7፡24-25) ነገር ግን ፊደል ለሚያጠፋቸው፣ ላጠፋቸው ወገኖች ትምህርት ይሆን ዘንድ በአማርኛ ትርጉም የሚገኘውን “ሊያማልድ በሕይወት ይኖራል” የሚለውን መነሻ አድርገን እናስረዳለን፡፡

እነርሱም (ሌዋውያን ካህናት) ሞት ስላለባቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው ፡ ክርስቶስ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ (እግዚአብሔር ስለሆነ) የማይለወጥ ክህነት አለው (ዕብ 7፡24) ፡ ስለእነሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ፡ ስለዚህም ደግሞ በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈፅሞ ሊያድናቸው ይችላል (ዕብ 7፡25)፡፡ ‹‹ስለእነርሱ ሊያማልድ ዘወትር በህይወት ይኖራል›› መባሉ ስለክርስቶስ ኃይል የመስዋእቱ ኃይል ከፍ እንዳለ መናገሩ ነው፡፡ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መናፍቃኑ ለምንፍቅና ትምህርታቸው እንዲመቻቸው ‹‹ስለ እነርሱ ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል›› ብለው ያጣሙት እንጂ ቆየት ብሎ በታተመው መጽሐፍ ቅዱስ (1960) ላይ ግን ‹‹ክህነቱ አይሻርምና ዘወትር በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሊያድናቸው ይቻለዋል ለዘላለም ሕያው ነውና ያስታርቃቸዋል›› ነው የሚለው (ዕብ 7፡24-25)

ጌታችን ራሱ መስዋዕት አቅራቢ፣ ራሱ መስዋዕት፣ ራሱ መስዋዕት ተቀባይ ሆኖ አንድ ጊዜ ብቻ ራሱን ባቀረበው መስዋዕት ለዘላለም ኃጢዓታችንን ያስተሰርይልናል፡፡ አንድ ጊዜ በመስቀል ላይ ያፈሰሰው ደም ያለፈውንም ሆነ የሚመጣውን ትውልድ ለዘላለም ያስታርቀዋል እንጂ እንደ ኦሪቱ ሥርዓት ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ‹‹ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም›› ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጓልና፡፡ ስለዚህ እኛም ፍጹም ድኅነትን ያገኘነው አንድ ጊዜ በሠራልን የክህነት ስራ ነው፡፡ ‹‹በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድራዊ ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷል›› (ቆላ 1፡19) ተብሎ እንደተጻፈ ይህ የሠራልን የክህነቱ ሥራው ነው፡፡ ‹‹ዘወትር ሲያስታርቀን የሚኖረው አሁንም ያማልደናል›› ካልን ግን ክርስቶስ ዕለት ዕለት ኃጢአት በሠራን ቁጥር መሞት አለበት ማለት ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲያብራራ ‹‹ነገር ግን የሆነው ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን (ከባሕርይ አባቱ ከአብ፣ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ) ጋር በሥልጣን፣ በአገዛዝ፣ በሕልውና አንድ ስለሆኑ) የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር (የሦስትነትና የአንድነት ስማቸው) ነው አንድም ኢየሱስ ራሱ እግዚአብሔር ነው፣) እግዚአብሔር ‹‹በክርስቶስ ሆኖ›› (ሥጋን ለብሶ ሰው ሆኖ) ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበር›› (ኀላፊ ቃል) በደላቸውንም አይቆጥርባቸውም ነበር በእኛም የማስታረቅን ቃል አኖረ እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማድ ስለ ክርስቶስ መልዕክተኞች ነን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቀ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን እናማልዳለን› ብሏል› (2ቆሮ 5፡18-21)፡፡

“ስለእኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” (ሮሜ 8፡34)

ይህ ጥቅስ መናፍቃኑ ለራሳቸው እንዲመች አድርገው የተረጎሙት ነው፡፡ ትክክለኛው ትርጓሜ ‹‹እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች የሚነቅፋቸው ማን ነው? የሚፈርድስ ማን ነው? የሞተው ይልቁንም ከሙታን ተለይቶ የተነሣው በእግዚአብሔርም ቀኝ የተቀመጠው ደግሞ ስለ እኛ የሚፈርደው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ሮሜ 8፡33-35)፡፡›› የሚለው ነው፡፡ በ1946 ዓ.ም. እና በ2000 ዓ.ም. በታተሙት የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጅዎች “ስለ እኛ የሚፈርደው” ይላል እንጂ “ስለ እኛ የሚማልደው” አይልም፡፡ ይሁንና በ1980 የታተመው ቅጅ “ስለ እኛ የሚማልደው” በማለት ከአውድ ውጭ የተረጎመውን ይዘው ፊደላውያን ሰዎች መሰረታዊ የቤተክርስቲያን መሰረተ እምነትን ለማዛባት ይደክማሉ፡፡

እነዚህ ሰዎች የዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና ትርጓሜ ለመረዳት የሚሞክሩት በጥሬ ንባብ እንጂ የንባቡን ዓላማ ለመረዳት እንኳ ጥረት አያደርጉም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሰዎች ለመከራከር የሚያነሱትን ቃል የተናገረበትን አውድ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በሮሜ መልእክቱ 8፡31-39 ቅዱስ ጳውሎስ አንቀጸ ሰማዕታትን እያስተማረ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሰማዕታት መከራ ሲቀበሉ ሊሰቀቁ እንደማይገባ፣ ይልቁንም ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት አድርገው መከራን ሊቀበሉ እንደሚገባ ያስተማረበት ክፍል ነው፡፡ የሰማዕታትን ዋጋ ሲያስረዳም “እንግዲህ እርሱ ራሱ ካጸደቀ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች የሚቃወማቸው ማን ነው?” በማለት ይጠይቃል፡፡ ለዚህ መልሱን ሲሰጥ፡- “የሚፈርድስ ማን ነው?” በማለት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈራጅነት (ስለ ሥሙ መከራ ለሚቀበሉ ሰማዕታት እንደሚፈርድላቸው ያስረዳል፡፡  “የሞተው ይልቁንም ከሙታን ተለይቶ የተነሣው በእግዚአብሔርም ቀኝ የተቀመጠው ደግሞ ስለ እኛ የሚፈርደው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡” በማለትም አስረግጦ ይናገራል፡፡ ከዚህ ሁሉ ንባብ አንዲት ቃልን የሚፈርደው ከሚል የሚማልደው ወደሚል ንባብ የሚቀይሩ ሰዎች ያልተረዱት መሰረታዊ ሀሳብ የንባቡ አውድ ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ቁጥር 35 ላይ “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ነውን? ኀዘን ነውን? ስደት ነውን? ራብ ነውን? መራቆት ነውን? ጭንቀት ነውን? ሾተል ነውን? መጽሐፍ እንዳለ ‘ስለ አንተ ዘወትር ይገድሉናል፤ እንደሚታረዱ በጎችም ሆነናል፡፡” የሚለው የሚያስረዳን የሰማዕታትን ዋጋ ነው፡፡ ሰማዕታት መከራ በተቀበሉ ሰዓት የሚፈርድላቸው (ዋጋቸውን የሚሰጣቸው) እንጂ የሚያማልዳቸው አምላክ እንዳላቸው መጽሐፍ ቅዱስ አያስተምረንም፡፡ ለማሳያ ያክል በዮሐንስ ራዕይ 6፡9-10 የተጻፈውን ነገረ ሰማዕታት ማየት እንችላለን፡፡ “አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የተገደሉትን ሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያው በታች አየሁ፡፡ በታላቅ ድምፅም እየጮሁ ‘ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ስለ ደማችንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም?’ አሉ፡፡” እንግዲህ እናስተውል ሰማዕትነትን የተቀበሉ ሰዎች ቅዱስና እውነተኛ ፈራጅ ከሆነ ከጌታቸው ከኢየሱስ ዘንድ ፍርድን ይጠብቃሉ እንጂ ዋጋ ከፋዩን ጌታ አማላጅ አይሉትም፡፡ ስለሆነም ሰይጣን በመናፍቃን አድሮ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያለ አውዳቸው ንባባቸውን ሲቆነጻጽል ልንታለል አይገባም፡፡

በተመሳሳይ የሊቃውንት ጉባኤ ባሳተመው ግዕዝና አማርኛ ወይም ነጠላ ትርጉም አዲስ ኪዳን እንደሚከተለው ተገልጧል፡፡ ‹‹ወመኑ ውእቱ እንከ ዘይትዋቀሦሙ ለኅሩያነ እግዚአብሔር ለእመ ለሊሁ ያጸድቅ፡፡ ወመኑ ዘይኬንን ክርስቶስ ኢየሱስ ሞተ ወተንስአ እምውታን ወሀሎ ይነብር በየማነ እግዚአብሔር ወይትዋቀሥ በእንቲአነ›› (ሮሜ 8፡33-34) ትርጉሙም ‹‹እርሱ ካጸደቀ እንግዲህ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች የሚቃወማቸው ማነው? የሚፈርድ ማን ነው? ክርስቶስ ኢየሱስ ሞተ፣ ከሙታንም ተለይቶ ተነሣ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጧል፣ ስለ እኛም ይፈርዳል›› ይላል፡፡

ይህንን ለራሳቸው እንዲመች አድርገው የተረጎሙትን ጥቅስ በመጠቀም አንዳንዶች ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ያማልደናል›› ይላሉ፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም፡፡›› (ዮሐ 16፡26) በማለት እውነቱን ተናግሯል፡፡ እንዲሁም ‹‹አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል። ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም።›› (ዮሐ 5፡21-23) በማለት እውነተኛ ፈራጅ እርሱ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

‹‹ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን››” (1ኛ ዮሐ፡2፡1)

‹‹ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን›› (1ኛ ዮሐ 2፡1)። ይኸንን ኃይለ ቃል የምናገኘው በተለመደው መጽሐፍ ቅዱስ በሐዋርያው በቅዱስ ዮሐንስ መልእክት ላይ ነው። ይህ ሐዋርያ በመጀመሪያቱ መልእክቱ ምዕራፍ አንድ ከቍጥር አንድ ጀምሮ እንዲህ ይላል፡፡ “ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን፤ በዓይኖቻችንም ያየነውን፥ እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ፥ አይተንማል፥እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም፥ ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራችኋለን። ”ካለ በኋላ፥በምዕ 2፡1 “ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፥ እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤” ብሎአል። እንዲህ የሚለው በስፋት በሁሉ ዘንድ የተሰራጨው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡

ነገር ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በራሷ ሊቃውንት አስመርምራ፥ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና፥የራሷን መጽ ሐፍ ቅዱስ በ2000 ዓ.ም. በማሳተሟ ችግሩ ተቀርፎአል። እንደተለመደው ይኸንን ገጸ ንባብ፥ለአማርኛው ጥንት ከሆነው ግዕዝ ጋር እናገናዝበዋለን። “ደቂ ቅየ ዘንተ እጽሕፍ ለክሙ ከመ ኢተአብሱ፤ልጆቼ ሆይ፥እንዳትበድሉ ይህን እጽፍላችኋለሁ” በማለት የጻፈበትን ምክንያት ካስረዳ በኋላ፡-“ወእመኒ ቦ ዘአበሰ ጰራቅሊጦስ ብነ ኀበ አብ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ጻድቅ ውእቱ ይኅድግ ለነ ኃጣውኢነ፤ የሚበድልም ቢኖር ከአብ ዘንድ ጰራቅሊጦስ አለን፥ኢየሱስ ክርስቶስም ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ጻድቅ ነው፤(በድሎ ንስሐ የገባ ሰው ቢኖር ኃጢአታች ንን የሚያስተሠርይልን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ዘንድ የሚልክልን ጰራቅሊጦስ አለን፥ እርሱ ኃጢ አታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ቸር አምላክ ነው)፥ይላል።በመሆኑም፡-“ኢየሱስ ጠበቃ፤” የሚል ንባብም ትርጓሜም የለውም።

“ከእኔ አብ ይበልጣል” (ዮሐ 14፡28)

ጌታ ኢየሱስ ይህንን ያለበት ምክንያት ሥጋን በመልበሱ ህማም፣ ሞት፣ ግርፋት፣ ስቃይ፣ የመስቀል መከራ ስለሚደርስበት ነው ፡፡ አብ ግን ሥጋን ስላለበሰ ህማም፣ ሞት፣ መከራ፣ ስቃይ አያውቀውም /አይደርስበትም/ የለበትም፡፡ በዚህ ምክንያት አብ ከኔ ይበልጣል በዚህ ሰአት እኔ ወደመከራ ግርፋት ስቃይ መሄዴ ነው፤ ወደ አባቴ መሄዴ መልካም ነው፤ እሱ ዘንድ መከራ የለም ግርፋት የለም ስቃይ የለም ሥጋን በመልበሴ በሚደርስብኝ መከራ ምክንያት አብ ከኔ ይበልጣል አለ፡፡ እርሱ ከባሕርይ አባቱ ከአብና ከባህርይ ሕይወቱ ከወልድ ጋር አንድ መሆኑን ሲናገር ግን ‹‹እኔና አብ አንድ ነን›› ብሏል (ዮሐ 10፡30)፡፡

ጌታችን ሥጋን በመዋሐዱ ምክንያት እንኳን ከአብ ከመላእክትም አንሶ እንደነበር ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ይነግረናል፡፡ ዕብ 2፡9 ‹‹ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ፥ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስን ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና የምስጋናን ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን።›› መላእክት ሥጋን ባለመልበሳቸው/ሰው  ባለመሆናቸው/የሚደርስባቸው መከራ እና ስቃይ ባለመኖሩ የመላእክት ፈጣሪ ከመላእክት አንሶ ነበር ተብሎ ተፃፈ ፡፡ ራሱን ባዶ አድርጎ ‹‹በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ፡፡›› ፊልጵስዩስ 2፡6

“የክርስቶስ ራስ እግዚአብሔር ነው” (1ኛ ቆሮ 11፡3)

ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ “ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስ ወንድ፥ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ።” በዚህ ጦማር የምንመለከተው የዚህን ጥቅስ የመጨረሻውን ሐረግ ” የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደሆነ ልታውቁ እወዳለሁ” የሚለው ላይ በማተኮር ነው፡፡ ይህንንም በመያዝ አንዳንዶች ክርስቶስ ከእግዚአብሔር የሚያንስ አስመስለው ይናገራሉና፡፡ እውነታው ግን እንደሚከተለው ነው፡፡

የሴት ራስ ወንድ ነው ሲል የሴት መገኛ ወንድ ነው ማለቱ ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው (ዘፍ 2:21)›› እንዳለው። ሴት ከወንድ ተገኘች እንጂ ወንድ አልፈጠራትም፡፡ ወንድ የሴት እራስ ነው የተባለው መገኛዋ ስለሆነ ነው፡፡ ስለሆነም ራስ የአካል መገኛና ተመሳሳይ፤ አንድ ባህሪ ወይም መሰረት ነው፡፡ የሴት መሰረቷ (መገኛዋ) ወንድ ነው፡ ይሁን እንጂ ሴት በወንድ አልተፈጠረችም፡፡ ነገር ግን የወንድ እና የሴት አፈጣጠር መቀዳደም ነበረበት፡፡

የክርስቶስ ራስ እግዚአብሔር ነው ሲል ደግሞ የወልድ መገኛ እግዚአብሔር አብ ነው ማለቱ ነው፡፡ ‹‹ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ደግሞ ዓለምን እተወዋለሁ ወደ አብም እሄዳለሁ (ዮሐ 16:28)›› እንዳለው። ወልድ ከእግዚአብሔር ወጥቶ መጣ እንጂ በእግዚአብሔር አብ አልተፈጠረም፡፡ የሴት መገኛዋ ወንድ ቢሆንም ሴት በወንድ እንዳልተፈጠረች ሁሉ  የወልድ መገኛው ወይም መሰረቱ እግዚአብሔር አብ ቢሆንም ወልድ በእግዚአብሔር አብ አልተፈጠረም፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ናቸውና፡፡

“በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው” (1ኛ ጢሞ 2፡5)

‹‹አንድ እግዚአብሔር አለና በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው (1ኛ ጢሞ. 2፡5)›› የሚለውን ቃል ይዘው ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ አማላጃችን ነው›› የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ሐዋርያው የተናገረው ቃል ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ግን እንደሚከተለው ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ አንቀጽ ላይ መግለጽ የፈለገው አንድ እግዚአብሔር አለና ማለቱ በስልጣን፣ በአገዛዝ፣ በፈቃድ አንድ የሆነ እግዚአብሔር (የዓለም ጌታ) አለ ማለቱ ነው፡፡ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ማለቱ በአንድነት እግዚአብሔር ተብለው ከሚጠሩት ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው(ማዕከላዊ) የሆነው ማለቱ ነው፡፡ አንድ አለ ብሎ መካከለኛው አንድ ብቻ መሆኑን መግለፁ በተለየ አካሉ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው የሆነው ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡

ምክንያቱም እግዚአብሔር አብ መካከለኛ አይባልም፡፡ ለምን ቢባል ፍፁም አምላክ ብቻ ነው እንጂ ፍፁም ሰው አልሆነም፡፡ ወደፊትም አይሆንምና፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም መካከለኛ አይባልም ምክንያቱም ፍፁም አምላክ ብቻ ነው እንጂ ፍፁም ሰው አልሆነም፡፡ ወደፊትም አይሆንምና፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን መካከለኛ ይባላል ምክንያቱም ፍፁም አምላክ ሆኖ ሳለ አምላክነቱን ሳይለቅ ፍፁም ሰው ሆኗልና፡፡ አምላክነትን ሰውነትንም የያዘ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባህሪ አንድ ባህሪ በተዋህዶ የከበረ ነው፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛው ሲል ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው የሆነው ማለቱ ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ኢየሱስ ክርስቶስን መካከለኛ ነው ካለ በኋላ ወረድ ብሎ ከቁጥር 6 – 7 እንዲህ ይላል፡፡ ራሱን ለሁሉ ቤዛ ሰጠ ይህም በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበረ በማለት ጌታ በሥጋ ማርያም ተገልፆ በምድር ይመላለስበት በነበረበት በገዛ ዘመኑ ማለትም በሥጋው ወራት ስለሁላችን ራሱን ቤዛ አድርጎ እንደሰጠ ሐዋርያው ተናገረ፡፡በሌላም ቦታ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት ሲገልጽ እንዲህ አለ፡፡ ዕብ. 9፡15 የፊተኛው ኪዳን ሲፀና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለሆነ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው፡፡ የተጠሩት ሰዎች የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ ማለትም መንግስተ ሰማያት ትወርሳላችሁ የዘላለምን ሕይወት ታገኛላችሁ የሚለውን የተስፋ ቃል እንዲይዙ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው፡፡ ማለትም የዘላለም የተስፋን ቃል(አዲሱን ኪዳን) የተቀበልነው በፍጡር ሳይሆን በፈጣሪ መካከለኛነት ወይም በኢየሱስ ክርስቶስ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው ሆኖ ነው ማለቱ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው በመሆን አዲሱን ኪዳን ለሰው ልጆች የሰጠ በመሆኑ ማዕከላዊ (መካከለኛ) ተብሏል፡፡

“እርሱን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሳው” (ሐዋ 2፡32)

እግዚአብሔር የሚለው የመለኮት መጠርያ ሲሆን እግዚአብሔር አብ እግዚአብሔር ወልድ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተብሎ ይጠራል፡፡ ለዚህም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማረጋገጫው ቀዳሚሁ ቃል ውእቱ ወውእቱ ቃል ኀበ እግዚአብሔር ውእቱ ቃል ወዝንቱ እምቀዲሙ ኀበ እግዚአብሔር ውእቱ (ዮሐ 1፡2)፡፡ ስለዚህ ሥላሴ በፈቃድ አንድ በመሆናቸው አንዲት በሆኑት በአብ በራሱ እና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ተነሳ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር በመሆኑ ተነሳ ተብሎ ይተረጎማል ይታመናል፡፡ ትንቢቱም የሚያረጋግጥልን ይህንኑ ነው (ወተንስአ እግዚአብሔር ከመዘንቃህ እምንዋም ወከመ ኃያል ወህዳገ ወይን ወቀተለፀሮ በድህሬሁ) እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነሳ እንደሚነቃ ተነሳ የወይን ስካር እንደተወ እንደ ኃያልም ሰው ጠላቶቹን በኋላው መታ መዝ( 77፡65)።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት እኔ በሶስተኛው ቀን አነሳዋለሁ›› ያለው በራሱ መለኮታዊ ስልጣን እንደሚነሳ ሲናገር ነው (ዩሐ.ወ 2፥19)። በተጨማሪም «ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራታለሁ…. እኔ በፍቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም ላኖራት ስልጣን አለኝ ደግሞ ላነሳት ስልጣን አለኝ» (ዮሐ 10፥17) ብሏል። ስለዚህን ክርስቶስ የሞትን ማሰሪያ የሚያጠፋ መለኮታዊ ኃይል ያለው አምላክ ስለሆነ ሌላ አስነሺ አላስፈለገውም።

“በእግዚአብሔር ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው” (ራዕይ 3፡14)

የዚህ አነጋገር ትርጓሜ ፍጥረታት ከመፈጠራቸው በፊት ያለው የነበረው ለማለት ነው፡፡ የቀድሞው ትርጓሜ ‹‹እርሱ እግዚአብሔር ከፈጠረው ሁሉ አስቀድሞ የነበረው›› ሲል ጽፎታል፡፡ እንግዲህ ከፍጥረት ሁሉ ቀድሞ የነበረ ነው ማለትና መጀመሪያ ተፈጠረ ማለት የሰማይና የምድር ያህል በአነጋገርም ሆነ በሀሳብ የተራራቁ ናቸው፡፡ ፈጣሪ ኢየሱስ ክርስቶስ ከፈጠረው ፍጥረት ቀድሞ መኖሩ የተረጋገጠ ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርነቱ ከፈጠረው ፍጥረት ሁሉ አስቀድሞ የነበረው እርሱ እግዚአብሔር ወልድ (ኢየሱስ ክርስቶስ) እንዲህ አለ ብለህ ጻፍለት አለ እንጂ የእግዚአብሔር የመጀመሪያ ፍጥረቱ አላለም፡፡

“እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ” (ኤፌ 4፡24)

በእግዚአብሔር ምሳሌ (አርአያ) የተፈጠረው ቀዳማዊ አዳም እንጂ ሁለተኛው አዳም የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በመልካችን እንደምሳሌችን እንፍጠር በማለት አዳምን ፈጠረ፡፡ ዘፍ 1፡26 ይህ በንጽሕና በቅድስና በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረው አዳም ትዕዛዘ እግዚአብሔርን በመጣሱ ተዋረደ ጎሰቆለ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለወደቀው አዳም ክሶ የቀደመ ክብሩን ንጽሕናውን ቅድስናውን መለሰለት፡፡ በጥንተ ተፈጥሮ የፈጠረን አምላክ በሐዲስ ተፈጥሮ ፈጠረን፤ በኃጢአት ያረጀው የአዳም ባህርይ በክርስቶስ መስዋዕትነት ታደሰ፡፡ ይህንን ሲያስረዳና ዳግመኛ ወደ ኃጢአት እንዳንመለስ ሲመክረን እግዚአብሔር ያደሰውን አዲሱን ሰውነት ልበሱት በእውነት በቅንነት በንጽሕናም አለ፡፡

“ያቺን ሰዓት ልጅም ቢሆን አያውቃትም” (ማቴ 24፡36)

ከፍጡራን ሲለየው ነው እንጂ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ሲለየው አይደለም፡፡ ልብ ቃልና እስትንፋስ ያለው አንድ ሰው በልቡ አስቦት አውቆት ለመናገር ጊዜው ባለመድረሱ ሰዓት እየጠበቀለት ሰውሮ የያዘውን ነገር በቃል ሳይናገረው ቢቆይ ቢጠየቅም ዛሬ አልናገረውም ቢል አያውቀውም እንደማይባል ወልድም ያቺ ዕለት ያቺ ሰዓት የምትገለጽበት ጊዜው እስኪደርስ በልቤ በአብ ሰውሬ አቆያታለሁ እንጂ ዛሬ በቃልነቴ አውጥቼ አልናገራትም ማለቱ ነው እንጂ የማያውቃት ሆኖ አይደለም፡፡ ባያውቃትማ ምልክቶቹን ባልተናገረም ነበር፡፡ ነገር ግን ቢያውቃትም ቀኒቱን ለሰው ልጆች ሊገልጻት አልፈለገም፡፡ ይህም ቀኑ ሩቅ ነው ብለው ችላ እንዳይሉ ቅርብ ነው ብለው የዚህ ዓለም ኃላፊነታቸውን እንዳይዘነጉ ያደረገው ነው፡፡

አንድም ወልድ ቅድመ ተዋሕዶ የነበረ አላዋቂ ሥጋን እንደተዋሐደ ለማጠየቅ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አልአዛርን ከሞት እያስነሳ የት ቀበራችሁት እያለ ይጠይቅ ነበር (ዮሐ 11)፡፡ አስራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የነበረች ሴት ስትነካው ማነው የነካኝ እያለ ኃይል ከውስጤ ወጥቷል (ሉቃ 8፡43) ይል ነበር፡፡ ይህን የተናገረው ‹‹ቅድመ ተዋሕዶ አላዋቂ የነበረውን ሥጋ በእውነት እንደተዋሐደ ለማስረዳት ሲል›› ነው፡፡

አንድም አብ ለልጁ በመስጠት አውቋታል፡፡ ወልድ ግን በሥራ አላወቃትም ሲል እንዲህ አለ፡፡ ይህም ማለት የዓለም ፍጻሜ ዕለቱና ሰዓቱ በአብ ልብነት ትታወቃለች እንጂ በወልድ ቃልነት አልተነገረችም፤ ምጽአተ ክርስቶስ ትሁን ትፈጸም አልተባለችም ሲል ነው፡፡  አንድም ወልድ ብቻውን ያለ አብ አያውቃትም ሲል ነው፡፡ ከአብ ተለይቶ እንደማያውቃት ከልቡ የተሰወረች አለመሆንዋን፤ቀኒቱ በአብም ዘንድ የምትታወቅ መሆንዋን ለመግለጽ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም ያውቃታል፡፡ 1ኛ ቆሮ 2፡10 የጌታ መምጫ ቀን በሥላሴ ዘንድ ብቻ መታወቅዋን መግለጹንና ከዚህ ውጭ ግን ከሰማይ መላእክትም ሆነ ከምድራዊያን ወገኖች የተሰወረች መሆንዋን ገልጾልናል፡፡

“ወልድም ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል” (1ኛ ቆሮ 15፡24-28)

ይህንን ይዘው ‹‹ወልድ ለአብ ይገዛል›› የሚሉ አሉ፡፡ ነገር ግን የዚህ ቃል ትርጉም እነርሱ እንደሚሉት ሳይሆን እንደሚከተለው ነው፡፡ሁሉን ካስገዛለት (ሥልጣን ከሰጠው) ከወልድ ሞት እንዲያንስ ይታወቃል፡፡ ሞት ከሁሉ በሁሉ ላይ እንዲሰለጥን ያደረገው ወልድ ነውና፡፡ ከሰው ደግሞ ሞት እንዲያንስ ይታወቃል፤በዕለተ ምጽአት ሞት ይሻራል፡፡ ሁሉ ሞትን ድል አድርገው ይነሳሉና፡፡ ለሞት ሁሉ በተገዛለት ጊዜ ያን ጊዜ ወልድም ሁሉን እንዲገዛ ስልጣን ሰጥቶት ለነበረው ለሞት ተገዝቷል፡፡ በዕለተ ዓርብ ጌታ ስለ ሰው ልጆች ለነበረው ለሞት ተገዝቷል፡፡ በዕለተ ዓርብ ጌታ ለሰው ልጆች ብሎ እንደሞተ ሲገልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ በገዛ ፈቃዱ ሞተ እንጂ እንደሌሎች ሰዎች በግድ የሞተ አይደለም፡፡ ራሱ ወዶ ፈቅዶ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አደረ እንጂ፡፡ ይህም ወዶ ፈቅዶ ያደረገው መሆኑን ጳውሎስ ሲገልጽ ‹‹ሁሉን ላስገዛለት ተገዢ ይሆናል›› አለ፡፡ እንዲገዛ ስልጣን ለሰጠው ለሞት ወዶ ፈቅዶ ራሱን ሰጠ ማለት ነው፡፡

“ስለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም” (ማር 10፡18)

ጌታችን ራሱን ‹‹ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ›› ብሏል (ዮሐ 10፡11)፡፡ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ከሌለ፤ እርሱ ደግሞ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በባህርይ በመለኮት አንድ ካልሆነ እንዴት ‹‹ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ ሊል ቻለ?›› ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም ያለው ጠያቂው ምስጋናን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሽቶ (ቸር ብለው ቸር ይለኛል ብሎ ነበርና መጣጡ) ነበርና ‹‹ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር የለም›› በማለት የእርሱን ቸር መሆን ሲገልጽ ከእግዚአብሔር በቀር ሰው ቸር ሊባል አይገባውም ብሎ መለሰለት፡፡ በዚህም ሰውየው በልቡ አስቦ የመጣውን እንዳወቀበት ገልጾለታል፡፡ በተጨማሪም በሉቃስ 11፡27 ላይ  ‹‹ይህንም ሲናገር፥ ከሕዝቡ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ፥ የተሸከመችህ ማኅፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው አለችው። እርሱ ግን፥ አዎን፥ ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው አለ›› የሚለው ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

በምስጢረ ሥጋዌ ላይ የተነሱና የሚነሱ እጅግ ብዙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ያለመንፈስ ቅዱስ መሪነት በሥጋዊ አዕምሮ በራሱ እየተረጎመ የሚሄድ ሁሉ በየዘመናቱ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት በክርስቲያኖች ላይ ውዥንብር ለመፍጠር ይሞክራል፡፡ ከዚህ ለመጠበቅ እውነተኛውን የሐዋርያትና የሊቃውንተ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ አስቀድሞ መማርና ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራዊያን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ ‹‹የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፥ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው፣ ልዩ ልዩ በሆነ እንግዳ ትምህርት አትወሰዱ።›› (ዕብ 13-7-8) እንዳለው ከጌታችን እግር ሥር ቁጭ ብለው የተማሩት ዋኖቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ለዓለም ሁሉ ያስተማሩት እውነተኛው የወንጌል ቃል እያለ በየዘመናቱ የተነሱ መናፍቃን አስርገው ባስገቡት የስህተት ትምህርት ልንወሰድ አይገባም፡፡ ስለዚህም ሐዋርያዊት የሆነችው ቤተክርስቲያን የምታስተምረውን አምላክ ሰው የሆነበትን ምስጢረ ተዋሕዶ ጠንቅቆ በማወቅና በማመን ለሌሎችም ማስተማር ይገባል፡፡ የጌታችን ተዋሕዶ ምሥጢር በእምነት እንደደከሙት የመሰናከያ አለት ሳይሆን የመዳን መሰረት እንዲሆንልን ስለ መድኃኒታችን የምናምነውን፣ የምንናገረውን እንወቅ። የቤተክርስቲያን አምላክ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ያድለን።

ወስብሃት ለእግዚአብሔር

1 thought on “በምስጢረ ሥጋዌ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችና ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ

  1. በጣም ነው የማመሰግነው የምፈልገውን እጥር ምጥን ባለ መልኩ ቁልጭ ብሎ የቀረበ ሆኖ አግኝቼዋለሁ

    Like

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s