ቤተ ክርስቲያን የክርስቲያኖች ኅብረት ናት። እያንዳንዱ ክርስቲያንም የቤተ ክርስቲያን አካ(ባ)ል ነው። በምድር ላይ ያለች ቤተ ክርስቲያን እንደ ተቋም የራሷ “ሕጋዊ ሰውነት” አላት። እያንዳንዱ ምዕመንም እንደ ግለሰብ ተፈጥሯዊ (ሕጋዊም) ሰውነት አለው። ቤተ ክርስቲያን እንደ ተቋም፣ እያንዳንዱ ምዕመንና አገልጋይ ደግሞ እንደ ቤተ ክርስቲያን አካል የሚግባቡበት ሥርዓት አለ። የቤተ ክርስቲያንም የዘወትር ድምፅ የሰውን ልጅ ለድኅነት መጥራት፣ በአገልግሎት ማትጋትና ለእግዚአብሔር መንግስት ማብቃት ላይ ያተኮረ ነው። የቤተ ክርስቲያን ድምፅ ለእግዚአብሔር የአምልኮ ምሥጋና፣ ለቅዱሳን የጸጋ ምሥጋና የሚቀርብበትና ለዓለሙ ሁሉ ድኅነት የሚጸለይበት ነው። የእርስዋ ድምፅ ቅዱሳን መላእክትን የሚያቀርብ፣ ርኩሳንን አጋንንትን ደግሞ የሚያርቅ፣ በሰው ልብና አዕምሮም ሰላምን የሚመላ ነው።
ይሁንና በየዘመናቱ የቤተ ክርስቲያንን ተቋማዊ ኃይል ለየራሳቸው ዓላማ ለመጠቀም የሚሞክሩ አካላት ነበሩ፣ አሉም። በተለይም ከቅርብ ዘመናት ወዲህ በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረትና በቤተ ክርስቲያን ስም የሚሰሙ አንዳንድ ድምፆች ከቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ድምፅ መገለጫዎች በእጅጉ ያፈነገጡ ናቸው። በተቀደሰው ዐውደ ምሕረት ምንም መንፈሳዊ ረብ የሌላቸውን ወይም ፍፁም ዓለማዊ የሆኑ ንግግሮችንና፣ ከዘፈን ብዙም ያልራቁ መዝሙራትን መስማት እየተለመደ መጥቷል። ብዙ ጸሐፊዎችም የራሳቸውን ሀሳብ በቤተ ክርስቲያን ስም ሲናገሩ መስማትና ማየት እየተለመደ መጥቷል። ቤተ ክርስቲያንን እንወክላለን የሚሉ ታዋቂ ግለሰቦች (ሰባክያን፣ ዘማርያንና ሌሎች አገልጋዮች)፣ ማኅበራት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያንን መደበኛ አስተዳደራዊ መዋቅር የሚወክሉ አካላት ከመንፈሳዊ ዓላማ ይልቅ ማኅበራዊ ተቀባይነት ላይ ያተኮሩ አቋሞቻቸውን “የቤተ ክርስቲያን” አስመስለው ያቀርባሉ። በዚህም የተነሳ ብዙ ምዕመናን “እውነተኛው የቤተ ክርስቲያን ድምፅ የትኛው ነው?” በማለት መጠየቅ ጀምረዋል። ብዙ ነገር የተቀላቀለበት ድምፅ በሚሰማበት በዚህ ዘመን እውነተኛውን የቤተ ክርስቲያን ድምፅ መለየትና ማወቅ እጅግ አስፈላጊ ነው። እኛም በዚህች የአስተምህሮ ጦማር ስለ እውነተኛው የቤተ ክርስቲያን ድምፅ እንዳስሳለን።
የካህናት መልእክት
የካህናት (የጳጳሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት) ንግግር እንዲሁም በመደበኛና በየማኅበራዊ ሚዲያ በቃልና በጽሑፍ የሚያስተላልፉት መልእክት “የግላቸው ነው ወይስ የቤተ ክርስቲያን?” የሚል ጥያቄ ሲነሳ እንሰማለን። አገልጋይ በሆኑባት ቤተ ክርስቲያን ሆነው የቤተ ክርስቲያንን የአገልግሎት ዐውድ ተጠቅመው (የአገልግሎት ልብስ ለብሰው እና/ወይም የቤተ ክርስቲያንን ዐውደ ምሕረት ተጠቅመው) ሃይማኖታዊ ነገርን (እውነተኛውን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ) ሲናገሩ ሰሚው አካል የቤተ ክርስቲያን መልእክት አድርጎ ይወስደዋል። ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ይህንን ያደርጉ ዘንድ በክህነት አገልግሎት ሾማቸዋለችና። የተሰጣቸውም ሹመት ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት ስለሆነ ይህንን በአግባቡ ሳይፈጽሙ ቢቀሩ በምድር የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፣ በሰማይ እግዚአብሔር ይጠይቃቸዋል።
ነገር ግን ካህናት መንፈሳዊ/ሃይማኖታዊ ባልሆነ ጉዳይ ላይ በየትኛውም መድረክ የሚሰጡት አስተያየትና የሚያንጸባርቁት አመለካከት ግን የግላቸው ነው። የሚጠየቁበትም በግላቸው ነው። ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ/ሃይማኖታዊ ባልሆነ ነገር ላይ ኃላፊነት አልሰጠቻቸውምና። መንፈሳዊ/ሃይማኖታዊ ያልሆነን ሀሳብ በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ካንፀባረቁም ሀሳቡ የቤተ ክርስቲያን አለመሆኑ ታውቆ እነርሱም የቤተ ክርስቲያንን ዐውደ ምሕረት ለዓለማዊ ነገር በማዋላቸው ይጠየቁበታል። እንዲሁም መንፈሳዊ ይዘት የሌለውን ሀሳብ በቤተ ክርስቲያን ስም (ዐውድ) ካስተላለፉም እንዲሁ ይጠየቁበታል። ምዕመናንም ይህንን ለይተው ያውቁ ዘንድ ይገባል። የካህናት ሹመት ለመንፈሳዊ ዓላማ እንጅ ለሌላ መዋል የለበትምና።
የንስሐ አባትና ልጅ ግንኙነት
አምላካችን እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን ካህናት ምዕመናንን እንዲጠብቁ፣ እንዲያገለግሉ መንፈሳዊ ኃላፊነት መስጠቱ በቅዱሳት መጻሕፍትና በቤተ ክርስቲያን ትውፊት የሚታወቅ ነው። ለዚህም አገልግሎት እንዲረዳ እያንዳንዱ ምዕመን አበ ነፍስ (የንስሐ አባት) ይኖረዋል። የንስሐ አባትና ልጅ ግንኙነት ዓላማው የምዕመናንን መንፈሳዊ ሕይወት ማጎልበት ነው። መንፈሳዊ ሕይወት ከዓለም የሚመጣ ፈተናን ማሸነፍ ስለሚፈልግ የንስሐ አባትና ልጅ ግንኙነት ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን መዳሰሱ የማይቀር ነው። በዚህ መንፈሳዊ ግንኙነት የሚደረጉ የካህናት ምክሮችና ቀኖናዊ ትዕዛዞች የቤተ ክርስቲያን ድምፅ፣ የቅዱሳት መጻሕፍት መተግበሪያ ናቸው። ስለሆነም ይህን መንፈሳዊ ግንኙነት ከመንፈሳዊ ዓላማ ውጭ መጠቀም የተቀደሰውን ማርከስ፣ ቤተ መቅደስን ማቆሸሽ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል። የንስሐ አባትና ልጅ መንፈሳዊ ትስስር በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ዙሪያ ላለ ለተበላሸ ገንዘብና ክብር ተኮር ስህተት መሸፈኛ መሆን የለበትም።
በአስተዳደራዊ ሙስና የተበላሹ አጥቢያዎች ላይ ለቤተ ክርስቲያን ቀናኢ ሆነው በካህናትና በአስተዳዳሪዎች የሚፈፀሙ ሌብነቶችንና ሌሎች ክፋቶችን በልጅነት መብት የሚያጋልጡና ክፍተቶችን የሚጠቁሙ ምዕመናንና ካህናትን “በንስሐ አባት በማስመከር” ሰበብ “አርፋችሁ ብትቀመጡ ይሻላል” እያሉ የሚያስፈራሩ ንስሐ አባቶች “የቤተ ክርስቲያንን ድምፅ” እንወክላለን ሲሉ በእግዚአብሔር ቃል መቀለድ ይሆናል። አስተዳደራዊ ችግር በመረጃና በእውነት ተመስርቶ በሚደረግ ውይይት እንጂ መንፈሳዊ ስልጣንን ለነውር መሸፈኛ በማድረግ ሊፈታ አይችልምና። በተመሳሳይ መልኩ መንፈሳዊ መሠረት የሌለውን የራሳቸውን ፖለቲካዊና ታሪካዊ ምልከታ “በንስሐ አባት” ስልጣንና ግዝት በመሸፈን ምዕመናን ላይ የሚጭኑ ካህናትም ክህነታቸው የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ከሚያገለግል ሰማያዊ ስልጣን ተለይቶ ምድራዊ ርዕዮትን የሚያገለግል አርጤምሳዊ “ክህነት” በፈቃዳቸው እንደለወጡት ሊረዱ ይገባል።
የንስሐ አባትና ልጅ ግንኙነትን ጨምሮ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊና አስተዳደራዊ መዋቅር ለፖለቲካዊ ዓላማ መጠቀም አይገባም። አንዳንዶች በድብቅ፣ የባሰባቸው ደግሞ በግልፅ፣ የታመነውን የቤተ ክርስቲያን ድምፅ የፖለቲከኞች የምርጫ ማሸነፊያና ኢ-መደበኛ የአስተዳደራዊ ቅቡልነት ማስገኛ አድርገው ያስቡታል። እነዚህ ሃይማኖታዊ ፖለቲከኞች የቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የተለያየ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ምልከታ እንዳይኖራቸው ይፈልጋሉ። የእኔ ለሚሉት ፖለቲካዊ አቋም ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ ንስሐ አባት ያለው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር እንዲገብር ይፈልጋሉ። በዚህም የቤተ ክርስቲያንን ድምፅ በመንፈሳዊ ቃላት በተከሸነ፣ ፖለቲካዊ ግቡ ግን በታወቀ ዓለማዊ አስተሳሰብ ይለውጡታል። ይህም ቤተ ክርስቲያንን ልትወጣው ከማትችለው ቅርቃር ውስጥ ይከታታል።
ቅዱሳት መጻሕፍትን መሰረት አድርገን፣ ሃይማኖተ አበውን ተመልክተን፣ የቀደሙ ቅዱሳንን ሕይወት አብነት አድርገን፣ በቤተ ክርስቲያን የታወቁ ዓለም አቀፍ ጉባኤያት ላይ ከተብራሩ መንፈሳዊ አስተምህሮዎች አንፃር መርምረን የማናስረዳው እንቶ ፈንቶ ፖለቲካዊ እንጂ መንፈሳዊ አይደለም። ይህን መሰሉን በካይ ድምፅ “የቤተ ክርስቲያን ድምፅ” ብሎ ማቅረብ የቤተ ክርስቲያንን አምላክ መናቅ ካልሆነ ምን ይባላል? የምዕመናንን ቁጥርና የብሔር ስብጥር እየጠቀሱ “ተነስ ስንለው የሚነሳ፣ ተቀመጥ ስንለው የሚቀመጥ” ምዕመን አለ እያሉ ያለ ሀፍረት መናገር ለሀገርም ለቤተ ክርስቲያንም የማይጠቅም በዘመን ተፈትኖ የቀለለ የፊውዳላዊ ብዝበዛ ቅሪት ነው። ቤተ ክርስቲያን እንደ መምህሯ ኢየሱስ ክርስቶስ “በጎቼ ድምፄን ያውቃሉ፣ ይከተሉኝማል” የምትለው ያለመቀላቀል ለሚሰጡ ደገኛ አስተምህሮዎች እንጂ ለፖለቲካዊ ሃይማኖተኞች በሽንገላ የተሞላ ወለፈንድ አስተሳሰብ አይደለም።
የስብከትና የመዝሙር መልእክት
አንዳንድ ስብከቶች የምሕረት ዐውድ የሆነውን የቤተ ክርስቲያን አደባባይ የሁከት የሚያስመስሉ፣ ትህትናን ሳይሆን ድፍረትን የሚያበረታቱ፣ ልብን በወንጌል የሚያረሰርሱ ሳይሆን በቀልድ ልብን የሚያፈርሱ፣ ሩጫና መወራጨት የበዛባቸው፣ ፖለቲካንና ሃይማኖትን የደባለቁ፣ ምዕመናንን ሳይሆን አድናቂና ተከታይ ማፍራትን ግብ ያደረጉ ናቸው። በዚህም የተነሳ “የሰባክያን ስብከትና አስተያየት የግላቸው ሀሳብ ነው ወይስ የቤተ ክርስቲያን?” የሚለውን ጥያቄ ማጥራት ያስፈልጋል። በተለይም ግለሰባዊ እውቅና እና ቁሳዊ ጥቅምን ዋና ዓላማ አድርገው፣ በyoutube ‘የሚሰብኩ’ በበዙበት ዘመን ይህንን መጠየቅ ተገቢ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ እንዲያስተምሩላት ቤተ ክርስቲያን እውቅናና ፈቃድ የሰጠቻቸውና ለአገልግሎት የመደበቻቸው (ያሰማራቻቸው) ሰባክያንና በራሳቸው መንፈሳዊ ‘ተነሳሽነት’ የሚሰብኩ መምህራን እንዳሉ ማስተዋል ይገባል። ሁለቱም የሚጠበቅባቸው የክርስቶስን ወንጌል መስበክ ነው። እውነተኛውን ወንጌል እስከሰበኩ ድረስ ሁለቱም የቤተ ክርስቲያን ድምፅ ናቸው፣ እውነት በአስተዳደራዊ ስምሪት አይመዘንምና። ከዚህ የወጣ መልእክት (የቤተ ክርስቲያን ተብሎ ቢቀርብም እንኳን) ካስተላለፉ ግን ያ የግላቸው እንጂ የቤተ ክርስቲያን ድምፅ አይደለም። ይህንን ለይቶ ማወቅ የምዕመናን እና የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ድርሻ ነው።
በተመሳሳይም በዘማርያን መዝሙርና የተለያዩ ንግግሮች የሚተላለፉ መልእክቶች የግላቸው ናቸው ወይስ የቤተ ክርስቲያን? እነዚህ በብዛት የሰባኪውን ወይም የዘማሪውን ስም ይዘው የሚወጡና በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ያልጸደቁ ወይም ‘የቤተ ክርስቲያን አይደሉም’ ያልተባሉ ናቸው። ነገር ግን ሰባክያኑም ይሁን ዘማርያኑ በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት እስካገለገሉ ድረስ ወይም ቤተ ክርስቲያን ፈቃድ እስከሰጠቻቸው ድረስ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሰባክያንና ዘማርያን ተደርገው ይወሰዳሉ። መዝሙራትና የዘማርያን መልእክቶችም ቢሆኑ የቤተ ክርስቲያን ድምፅ የሚሆኑት “በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ሥርዓትና ደንብ የተዘጋጀ” የሚል ጽሑፍ ስለያዙ፣ ወይም ታዋቂ ዘማሪ ስለዘመራቸው፣ ታዋቂ ገጣሚ ግጥሙን ስላዘጋጀው፣ የታወቀ መዝሙር ቤት ስላተመውም ብቻ አይደለም። መዝሙራት የቤተ ክርስቲያን ድምፅ የሚሆኑት የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ፣ ሥርዓት፣ ትውፊትና አስተምህሮ የሚገልጹ ሆነው ሲገኙ ብቻ ነው።
በሚዲያ የሚንፀባረቁ ሀሳቦች
የቤተ ክርስቲያን ድምፅ ለምዕመናን ሊተላለፍ ከሚችሉባቸው መንገዶች አንዱ ሚዲያ ነው። ይሁንና የሚዲያ ብዙኅነት ባለበት ሁኔታ የቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ድምፅ የትኛው ነው የሚለውን መለየት ቀላል አይደለም። በተለይም ከቅርብ ዘመናት ወዲህ የተጀመረው በማኅበራዊ ሚዲያ የሚደረገው ሕዝብ የማነቃቃት እንቅስቃሴ ወደ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከገባ ወዲህ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ይገኛል። እነዚህ ግለሰቦች የሚያንጸባርቁት እጅግ ወገንተኛ የሆነና ፖለቲካ አዘል ስብከትና ስብከት የሚመስል ፖለቲካ ለምዕመናን መከፋፈል ዋነኛ ምክንያት እየሆነ መጥቷል። እነዚህ ግለሰቦች የሚያንጸባርቁትን ፖለቲካዊ አቋም የቤተ ክርስቲያን አድርጎ የሚወስድ ብዙ ምዕመን አለና። በተለይም ሕጋዊው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ይህንን እየሰማ እንዳልሰማ ዝም ሲል በሀሳቡ የተስማማ አድርጎ የመመልከት አዝማሚያ ይታያል። አንዳንዶቹም በልዩ ልዩ ተጽዕኖ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር እየጠመዘዙ ውሳኔ ሲያስወስኑና ሲያስቀይሩ ማየት እየተለመደ ነው። ይህም እየተደጋገመ ሲሄድ የቤተ ክርስቲያኒቱ እውነተኛ ድምፅ መስሎ ብዙ ምዕመናንን እያራቀ ይገኛል። ፖለቲካዊ ሃይማኖትን በግልፅ የሚያቀነቅኑ ሰዎችም አስተዳደሩንም ሆነ የምዕመናንን አስተሳሰብ በተፅዕኗቸው ስር ማድረጋቸው ስለማይቀር አደጋው እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ ላይሄድ ይችላል።
መታወቅ ያለበት እውነት ግን ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ተቋም መሆኗና ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ አቋም የሌላት የሁሉም ቤት መሆኗ ነው። ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም ካህን፣ ሰባኪ ወይም ዘማሪ ያስተማረችውና የምታስተምረው መንፈሳዊ አገልግሎትን ብቻ ነው። ቤተ ክርስቲያን ለማንም ፖለቲካዊ ትምህርትን አላስተማረችም፣ አታስተምርምም። ማንንም ‘ፖለቲካዊ አቋሜን’ አንጸባርቁልኝ ብላ ኃላፊነትን ለማንም አልሰጠችም። መንፈሳዊ እንጂ ፖለቲካዊ አቋም የላትምና። በተቃራኒ የፖለቲካ አመለካከት የተሰለፉትም ቢሆን ሁሉም ልጆችዋ ናቸው። ስለዚህ በማኅበራዊና በመደበኛ ሚዲያ በሃይማኖት ስም የሚንፀባረቁ ፖለቲካዊ አመለካከቶች የተናጋሪዎቹ ግለሰቦች (ቡድኖች) እንጂ የቤተ ክርስቲያን አለመሆናቸውን ለማስረገጥ እንወዳለን። ይሁንና እኛ “የቤተ ክርስቲያን አይደለም” ብለን በመርህ የምንበይነው አስተሳሰብና ተግባር ተጽዕኖው በጨመረ ቁጥር የሚያፈርሰው ቅጥር ይበዛል፣ በምድር ያለች ቤተ ክርስቲያንም በመናኛ የትርክት አረም ተውጣ ከተልዕኮዋ ትደናቀፋለች።
የቤተ ክርስቲያንን ድምፅ ከግለሰቦችና ቡድኖች ሀሳብ ለመለየትና ይህንንም የበለጠ ለመረዳት የአራት ነገሮችን ልዩነት በሚገባ መፈተሽና ማወቅ ያስፈልጋል።
እምነት (Faith)
እምነት በሰማነውና በተረዳነው አምነን የምንቀበለው፣ የምንጠብቀውና ተስፋ የምናደርገው ነው። የቀደሙት ቅዱሳን አባቶች ያስቀመጡልንን እውነት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት መርምረን የምናምነው ነው። እምነት የቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃነት ካልሆነ በቀር ሳይንሳዊ መረጃ አያስፈልገውም። እምነትም የአንድ ሰው ብቻ ስላልሆነ ተለይቶ ይታወቃል። ከቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የሚጠበቀውና ቤተ ክርስቲያንም በመጻሕፍቷ ዘግባ ያስቀመጠችውም ይኸው እውነት ነው። ምንጭ የሚጠቀስለት፣ በቂ ማስረጃ የሚቀርብለት፣ ሊቃውንትም የተማሩትና የሚያስተምሩት ይህንን ነው። የቤተ ክርስቲያን የዘወትር ድምፅም ሰው ያላመነ እንዲያምን፣ ያመነም በእምነቱ ጸንቶ ክርስቲያናዊ ስነ-ምግባራትን ፈጽሞና ከምሥጢራት ተካፋይ ሆኖ ለእግዚአብሔር መንግስት እንዲበቃ ማደረግ ነው። እምነትን በተመለከተ የቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ድምፅ በቅዱሳት መጻሕፍት የተመሰከረ፣ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በተሰጠ የሊቃውንት ትርጓሜ የታወቀ፣ በታወቁ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት በሚገባ ተመርምሮ የተደነገገ ነው። ስለሆነም የቤተ ክርስቲያንን እውነተኛ ድምፅ ለማወቅ ምንጫችንን እስካወቅን ድረስ ከባድ አይደለም።
ተጨባጭ እውነታ (Fact)
እውነታ ደግሞ መሬት ላይ በተጨባጭ የተከሰተና የታየ ወይም ሊታይ የሚችል ነገር ነው። ነባራዊ ማረጋገጫ የሚቀርብለት ተጨባጭ ክንውን ወይም ነገር ነው። ሰዎች አይተው፣ ዳስሰው ወይም ሌሎች መንገዶችን ተጠቅመው ሊያረጋግጡት የሚችሉት ነገር ነው። እውነታ ስለሆነ የማይለወጥ ታሪክም ነው። እዚህ ላይ የመረጃ እጥረት ወይም ሆን ብሎ እውነታውን የመካድ ነገር ካልሆነ በቀር በሰዎች መካከል ልዩነት የለም። ነገር ግን ለአንድ በገሀዱ ዓለም ለተከሰተ እውነታ የሚሰጠው መንፈሳዊ ትርጉም ብዙ ችግር ይታይበታል። ይህም በምዕመናን ዘንድ ብዙ ብዥታንና መለያየትን ሲፈጥር ይስተዋላል። እውነታው የታወቀ ቢሆንም ለዚያ እውነታ የሚሰጠው ትርጉም ግን አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔርን ሳይቀር “የክፉ ነገር ተባባሪ” ወይም አድሎ የሚያደርግ አምላክ የሚያስመስል ነው።
ምልከታ (Opinion)
ምልከታ የሚባለው ሰዎች በአንድ ሀሳብ፣ ድርጊት፣ እውነታ ወይም ነገር ላይ የሚኖራቸው አስተሳሰብ፣ አተያይና አመለካከት ነው። ይህም እንደየግለሰቡ የሚለያይ ሲሆን ወጥ ይሁን አይባልም። እያንዳንዱ ሰው ባለው ዕውቀት፣ አመለካከትና ልምድ የየራሱ ምልከታ ይኖረዋል። ምልከታ ማረጋገጫ ላያስፈልገው ይችላል። በእምነት መድረክ ምልከታን መስበክ አይገባም። ምልከታን በእምነት መድረክ ማቅረብ ግድ በሚሆንባቸው ጊዜያት ደግሞ በጥንቃቄ ከእምነትና እውነታ ጋር ሳይቀላቅሉ ማቅረብ ይገባል። ምክንያቱም እያንዳንዱ ግለሰብ በአንድ ነገር ላይ የተለያየ ምልከታ አለውና። ይህ ምልከታ ትክክል ነው ይህ ደግሞ ትክክል አይደለም ብሎ መበየንም አስቸጋሪ ስለሆነና ምልከታዎችም ተለዋዋጭ ስለሆኑ ምልከታዎች የእምነት መገለጫዎች ሊሆኑ አይችሉም። እምነትንም፣ እውነትንም ምልከታንም ጨፍልቆ “የእኔ ብቻ ትክክል ነው” ማለት ከእምነትም ከእውነትም የተፋታ አደገኛ አስተሳሰብ ነው።
አቋም (Position)
አቋም ማለት አንድ ሰው፣ ቡድን ወይም ተቋም ካሉት አማራጭ ሀሳቦች፣ መንገዶች መርምሮ አንዱን መርጦ ሲስማማበት፣ ሲያምንበትና ለተፈጻሚነቱም ይሁንታ ሲሰጠው አቋም ያዘ ይባላል። ይህም የግለሰቡን ወይም የተቋሙን የወደፊት አቅጣጫ የሚጠቁም ነው። እንደ አስፈላጊነቱም በየጊዜው እየተገመገመ ሊሻሻል ይችላል። አንድ አማራጭ መንገድ የቤተ ክርስቲያን አቋም የሚሆነው የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር የሚያምንበት፣ የተስማማበትና ያጸደቀው ሲሆን ነው። ይህም በአጥቢያ ደረጃ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ (ተወካዩ ሰበካ ጉባዔ)፣ በሀገረ ስብከት የሀገረ ስብከቱ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ (በሊቀ ጳጳሱ የሚመራ) እና በሀገር አቀፍ ቅዱስ ሲኖዶሱ ያመነበት፣ የተስማማበትና ያጸደቀው ሲሆን የቤተ ክርስቲያን አቋም ይሆናል። በመንፈሳውያን ማኅበራትና ሰንበት ትምህርት ቤቶችም ቢሆን የየማኅበራቱ አመራር ወይም እነርሱን የሚወክል አካል የሚያንጸባርቀው አቋም የዚያ ማኅበር ነው። ማኅበራት የቤተ ክርስቲያን አካል እንደመሆናቸው አቋማቸውም ከቤተ ክርስቲያን ጋር መገናኘቱ የግድ ነው።
የተቀላቀሉ ድምፆች
በዘመናችን በብዛት የሚሰማው ድምፅ የተቀላቀለ ነው። ሃይማኖትን ከባሕል (የማኅበረሰብ ልማድ)፣ ሃይማኖትን ከፖለቲካ (ከሀገር አንድነት)፣ ሃይማኖትን ከቢዝነስ (ገንዘብና ርካሽ ታዋቂነት) የቀላቀለ ድምፅ መስማት የተለመደ ነው። እንዲህ አይነቱ ድምፅ ብዙ ምዕመናንን ያደናግራል። የትኛው መንፈሳዊ፣ የትኛው ዓለማዊ መሆኑን መለየት ያስቸግራል። በተለይም መንፈሳዊውን አስተምህሮ ብቻ የሚያቀርቡ አገልጋዮች እያነሱ መሄዳቸው፣ ያሉትም በቂ መድረክ አለማግኘታቸው ችግሩን አስከፊ አድርጎታል። እንደዚህ አይነት ውጥንቅጥ በበዛበት ዘመን ምዕመናንን ስንዴውን ከእንክርዳድ ለይተው እንዲሰሙ ማስቻል ይገባል። ከዚህም አንፃር ምዕመናን መንፈሳዊው አስተምህሮ ላይ የሚያተኩሩ መምህራንን አስተሳሰብ፣ እንዲያውቁና እነርሱንም እንዲሰሙ ማድረግ ይጠበቃል። በሌላም በኩል ብዙ ነገር የሚቀላቅሉትን ትኩረት በመንፈግ እንዲስተካከሉ ማገዝ ያስፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥንታውያን መጻሕፍት ማንበብ፣ ከሊቃውንቱና በገዳማት ከሚኖሩት አባቶች መማር የተሻለ መፍትሔ ይሆናል እንላለን። ለባሕል የበላይነት፣ ለፖለቲካዊ ትርፍ፣ ለገንዘብ ክብርና እውቅና ሲባል የሚቀላቀሉ በካይ አረሞችን በጥንቃቄ መለየትና የቤተ ክርስቲያንን እውነተኛ ድምፅ እንዳያደበዝዙ ማድረግ የሚቻለው የድምፆቹን ምንጮች እውነተኛነት በመለየትና መንፈሳዊ ያልሆነ ዓላማ ያላቸውን ንቆ በመተው፣ ባለመከተል ነው እንላለን።
ማጠቃለያ
የቤተ ክርስቲያን ደወል (መረዋ) ድምፅ ምዕመናንን ወደ ቤተ ክርስቲያን ይጠራል። የአገልጋዮች ድምፅም እንዲሁ ሊሆን ይገባል። የቤተ ክርስቲያን ቅዳሴዋ፣ ማኅሌቷ፣ ሰዓታቷ ሰውን በተመስጦ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኙ ናቸው። ቤተ ክርስቲያን የምትታወቀው በእነዚህ ድምፆች ነው። ቅዱሳን ሐዋርያትና ቀደምት ቅዱሳን አበው የሰበኩት ወንጌልና የጻፏቸው መልእክታት እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ድምፆች ናቸው። ከሁሉም በላይ ክርስቶስ በምድር ላይ ያደረገውን ተአምርና ያስተማረውን ትምህርትን የሚመስከር ድምፅ የቤተ ክርስቲያን ድምፅ ነው። ጌታችን በወንጌል በጎቼ ድምፄን ያውቁታል እንዳለ እውነተኛው የቤተ ክርስቲያን ድምፅ በይዘቱና በዓላማው ይታወቃል።
እያንዳንዱ ምዕመን የሚያምንበትና የሚያንጸባርቀው ሀሳብ የየራሱ ነው። በተቋም ደረጃ የቤተ ክርስቲያን አመራር የሚያንጸባርቀው ሀሳብ የተቋሙ ተደርጎ ይወሰዳል። በተቋሙ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች በግላቸው ወይም ተቋማቸውን ወክለው ሀሳብ ሊያንጸባርቁ ይችላሉ። ተቋሙ በውክልና ሲልካቸው ወይም የተቋሙን ደንብና መድረክ ተጠቅመው ወይም የተቋሙን መገናኛ ዘዴዎች ተጠቅመው ሲናገሩ የተቋሙ ሀሳብ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ነገር ግን በራሳቸው ተነሳሽነት ያለ ተቋሙ ይሁንታ (ተቋሙ ተናገሩልኝ ሳይላቸው) ሲናገሩ ግን የግል ሀሳባቸው ተደርጎ ይወሰዳል። እንዲሁም ሲናገሩ የተቋማቸው ሀሳብ አለመሆኑን ገልጠው ከተናገሩ፣ የተቋሙን ሥራ ከሚሠሩበት ዐውድ ውጭ በሆነ ሁኔታ ሲናገሩ ወይም ተቋሙ የኔ ሀሳብ አይደለም ካለ የግላቸው ሀሳብ ተደርጎ ይወሰዳል። ይሁንና ግለሰቡ የተቋሙ አባ(ካ)ል እስከሆነ ድረስ ግለሰቦች የሚያንጸባርቁት ሀሳብ በተቋሙ ውስጥ ካሉት ሀሳቦች እንደ አንዱ ተደርጎ ይወሰዳል።
ስለሆነም የቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ልዕልና የሚገደን ሁላችንም እግዚአብሔር በገዛ ደሙ የዋጃት፣ ቅዱሳን አበውና እማት ሰማዕትነት የተቀበሉባት ቤተ ክርስቲያን በተበከሉ ድምፆች እንዳትወከል የሚጠበቅብንን ግዴታ በአግባቡ መወጣት ይኖርብናል። እውነተኛው የቤተ ክርስቲያንን ድምፅ በመንፈሳዊ ይዘቱና በመንፈሳዊ ዓላማው ለይተን ልናውቅ ይገባል። ተናጋሪውንና የተነገረበትን ዐውድ ብቻ ይዘን መንፈሳዊ ነው ማለት የማንችልበት ክፉ ዘመን ላይ ደርሰናልና። የቤተ ክርስቲያን አምላክ እግዚአብሔር እውነተኛና መንፈሳዊ የሆነውን የቤተ ክርስቲያን ድምፅ ሸንጋይና የኃጢአት መደላድል ከሆነው የአስመሳይ ግለሰቦችና ተቋማት በካይ ድምፅ የምንለይበትን ጥበብ መንፈሳዊ እንዲያድለን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። አሜን።