በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ማቴ 5:3 ሉቃ 6:20
በመንፈስ ድሃ መሆን ማለት ያለንን ሁሉ የእግዚአብሔርና ከእግዚአብሔር ነው ብሎ በማመን ከእኔ የሆነ አንዳች ነገር የለም በማለት በፍጹም ልባዊ ትህትና ራስን ባዶ (ድሃ) ማድረግ ነው። ይህም በሥጋ ያይደለ በመንፈስ (በነፍስ) ነው። ይህም አምላክ ለመሆን የተመኘ የአዳምን ኃጢአት (ዘፍ 3:5)፣ አምላክ ነኝ ብሎ የካደ የዲያብሎስን ኃጢአት (ኢሳ 14:14) ድል የምናደርግበት መንፈሳዊ ኃይል ነው። ልባዊ ትህትና የመንፈሳዊ ሕይወት ሥር ናት። ዛፍ ሥር ከሌለው አይጸናም፣ ፍሬም አያፈራልም፣ በሕይወትም አይቆይም። ልባዊ ትህትና የሌለው መንፈሳዊ ሕይወትም እንዲሁ ነው። ልባዊ ትህትና ለታይታና ለማስመሰል ሳይሆን ለራሳችን ብለን በእውነትና በተግባር ራስን ዝቅ ማድረግ ነው። ትህትና ‘ትሁት ነኝ’ ብለን በቃል የምንናገረው ወይም ትሁት መሆናችንን ለጊዜው ብቻ ትሁት መስለን የምናሳየው (አፍአዊ ትህትና) ሳይሆን በልባችን ሰርፆ በሕሊናችን ተቀርፆ በዘመናችን ሁሉ የምንኖረው ሕይወት ነው። ስለዚህም አስቀድሞ በነቢዩ ሚክያስ “ሰው ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፥ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፥ ከአምላክህም ጋር በትህትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን? (ሚክያስ 6:8)” በማለት እግዚአብሔር ፍጽምት በሆነች ልባዊ ትህትና እንድንጓዝ የሚፈልግ መሆኑን ተናግሯል።
ጌታችን በወንጌሉ ስለ ልባዊ ትህትና “ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ከፍ ይላል፣ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ዝቅ ይላል (ሉቃ 18:14)” በማለት ከፍ ለማለት ትህትና እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስተምሯል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በመልእክቱ “እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ (ሮሜ 12:3)… እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትህትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ (ሮሜ 12:16)” በማለት በትህትና እንድንተጋ አስተምሮናል። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ “ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትህትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሁታን ግን ጸጋን ይሰጣል። እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ(1ኛ ጴጥ 5:5-6)” በማለት ስለ ትህትና አስተምሯል። ምናልባት ‘ራስን ዝቅ ማድረግ’ ስንል ከየት፣ ምን ያህልና እንዴት ነው ራሳችንን ዝቅ የምናደርገው ብለን እንጠይቅ ይሆናል። ከዚህ በታች የቀረቡት አርአያዎቻችን በተግባር የተፈጸመ የትህትና ሕይወትን ያስረዱናል።
መምህረ ትህትና ኢየሱስ ክርስቶስ: ጌታችን ሁሉን የሚገዛ አምላክ ሲሆን “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። (ፊልጵ 2:5-8)” የተባለው ይህንን ትህትና የማዳን/የቤዛነት ስራውን በፈጸመበት የሥጋዌ መገለጥ በተግባር ያስተማረበት ነው። ይህ የእውነተኛ ትህትና ፍጹም አርአያ ነው። እርሱ በልዕልና የሚኖር እውነተኛ አምላክ፣ ሁሉን የፈጠረና ሁሉን ማድረግ የሚችል ሲሆን ሰውን ለማዳን ሲል ራሱን አዋርዶ ሰው ሆነ፣ ሰውም ሆኖ በሰው እጅ መከራን ተቀበለ። በመዋዕለ ስብከቱም “ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ(ማቴ 11:29)” በማለት ትህትናን ከእርሱ እንድንማር ነግሮናል። በበረት ተወልዶ፣ እንደ ደካማ ከሄሮድስ ፊት በመሸሸት ተሰድዶ፣ እንደ አላዋቂ ከእግረ መምህራን ተቀምጦ ተምሮ፣ በዕደ ዮሐንስ ተጠምቆ፣ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቦ፣ እንደ ወንበዴ በመስቀል ተሰቅሎ ትህትናን በተግባር አሳይቶናል።
የንጉስ ዳዊት ትህትና: ልበ አምላክ ክቡር ዳዊት በጊዜው የእስራኤል ንጉሥ ሲሆን በሥጋ ብዙ ሀብትና ስልጣን ነበረው። ነገር ግን ራሱን በመንፈስ ድሃ አድርጎ “እኔ ችግረኛና ምስኪን ነኝ (መዝ 40:17)” አለ። እርሱ እግዚአብሔር እንደ ልቤ የሚሆን የዕሴይን ልጅ አገኘሁ (1ኛ ሳሙ 13:14 ሐዋ 13:22) በማለት የመሰከረለት ክቡር ዳዊት በፍጹም ትህትና “እኔ ግን ትል ነኝ ሰውም አይደለሁም፤ የሰው ማላገጫ በሕዝብም ዘንድ የተናቅሁ ነኝ (መዝ 22:6)” አለ። እግዚአብሔር “ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል (1ኛ ሳሙ 16:7)” ብሎ ያነገሠው ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “እኔ ትል ነኝ” ካለ እኛ በኃጢአትና በበደል የምንኖር፣ በማስመሰልና ለታይታ የምናገለግል ሰዎች ምን ልንል ይሆን?! በእግዚአብሔር ፊት የከበረው ዳዊት በዚያ ትህትናም ሆኖ “አቤቱ፥ ልቤ አይታበይብኝ፥ ዓይኖቼም ከፍ ከፍ አይበሉብኝ፤ ከትልልቆች ጋር፥ ከእኔም ይበልጥ ከሚከበሩ ጋር አልሄድሁም። ነፍሴን አሳረፍኋት፥ የእናቱንም ጡት እንዳስተውት ዝም አሰኘኋት፤ ነፍሴ የእናቱን ጡት እንዳስተውት በእኔ ውስጥ ናት (መዝ 131:1-2)” ይል ነበር። በዚህም ሕይወቱ የትህትና ምሳሌ ሆኖናል።
የኒቆዲሞስ ትህትና: ኒቆዲሞስ መምህር ሲሆን ራሱን ዝቅ አድርጎ የተማረ የትህትና አርአያ ነው (ዮሐ 3:1-14)፡፡ ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ ብቻ ሳይሆን የፈሪሳውያን አለቃ፣ የኦሪት መምህር ብቻ ሳይሆን የኦሪት ምሁርም ነበር፡፡ በእርሱ ደረጃ የነበሩ ታላላቅ የአይሁድ ምሁራን መንፈሳዊ ስልጣናቸውና ሹመታቸው የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን ረስተው በህዝቡ ላይ የሚመፃደቁ ነበሩ፡፡ በዘመናቸው እውቀትን የሚገልጥ እውነተኛ አምላክ፣ የካህናት አለቃ ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤዛ ዓለም ሲገለጥ የአይሁድ ምሁራን የጌታን መገለጥ አልወደዱትም፡፡ የእርሱ ትህትና የእነርሱን ትዕቢት የሚያጋልጥ ነበርና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሄዱትን ሁሉ ይነቅፉ ይከስሱ ነበር፡፡ ባለማወቅ ያደነደኑት የትዕቢት ልቦና ትህትናን አጥፍቶባቸው ነበርና ዝቅ ብሎ በሰው ዘንድ በተናቁት በናዝሬትና በገሊላ እየተመላለሰ የሚያስተምር የዓለም ቤዛ የክርስቶስን ትምህርት እንዳይሰሙ ልባቸው ተዘግቶ ነበር፡፡ ጌታችንም የፈሪሳውያን ሀሳባቸው በግብዝነት የተሞላና ከንቱም እንደሆነ ነግሯቸዋል፡፡ ለደቀመዛሙርቱም ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ የሚበልጥ ሥራን እንዲሰሩ አስጠንቅቋቸዋል (ማቴ 5: 20 ማቴ 16:6)፡፡ መምህረ ትህትና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የኒቆዲሞስን ትህትናውን ተቀብሎ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ትውልድ ሁሉ የሚማርበትን ረቂቁን ምስጢረ ጥምቀትን አስተማረው፡፡
የቀራጩ ሰው ትህትና: ጌታችን ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፥ እንዲህ ሲል፥ ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፥ አንዱ ፈሪሳዊ ሁለተኛውም ቀራጭ። ፈሪሳዊም ቆሞ በልቡ ይህን ሲጸልይ:- እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤ በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጦማለሁ፥ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት አወጣለሁ አለ። ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን:- አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር። እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል (ሉቃ 18:9-14)። በመቅደስ ሲጸልይ የነበረው ቀራጭ ራሱን በመንፈስ ድሃ (ትሁት) በማድረግ በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን። አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር። በትህትና ያቀረበው ጸሎትም ተሰምቶለት፣ ኃጢአቱም ተሰርዮለት ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ (ሉቃ 18:11-14)።
የፈያታዊ ዘየማን (ጥጦስ) ትህትና: ከጌታችን በቀኝ የተሰቀለው ሽፍታ በፍጹም ትህትና “ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው” በማለቱ ድኅነትን አግኝቷል (ሉቃ 23:41)። ከተሰቀሉት ከክፉ አድራጊዎቹም አንዱ:- አንተስ ክርስቶስ አይደለህምን? ራስህንም እኛንም አድን ብሎ ሰደበው። ሁለተኛው ግን መልሶ:- አንተ እንደዚህ ባለ ፍርድ ሳለህ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም ብሎ ገሠጸው። ኢየሱስንም:- ጌታ ሆይ፥ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው። ኢየሱስም፥ እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው (ሉቃ 23:39-43)። ይህ ሰው በዚያች ሰዓት ‘እግዚአብሔርን አትፈራውምን’ ብሎ ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዳለው ተናገረ። ‘እኛ ስላደረግነው በደል ይህ ይገባናል/’ ብሎ ራሱን ዝቅ አደረገ። ‘ይህ ግን ምንም ክፋት አላደረገም’ ብሎ ጌታችንን አከበረ። ከዚያም ‘በመንግሥትህ አስበኝ’ ብሎ የጌታችንን አምላክነት በመመስከር ለራሱም ድኅነት ያሰጠችውን ጸሎት አቀረበ።
የከነናዊቷ ሴት ትህትና: እነሆም፥ ከነናዊት ሴት ከዚያ አገር ወጥታ:- ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረኝ፤ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዞአታል ብላ ጮኸች። እርሱ ግን አንዳች አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው:- በኋላችን ትጮኻለችና አሰናብታት እያሉ ለመኑት። እርሱም መልሶ:- ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም አለ። እርስዋ ግን መጥታ፥ ጌታ ሆይ፥ እርዳኝ እያለች ሰገደችለት። እርሱ ግን መልሶ:- የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም አለ። እርስዋም። አዎን ጌታ ሆይ፤ ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ አለች። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ፥ አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ አላት። ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች(ማቴ 15:22-28)። ይህች ሴት “አዎን ጌታ ሆይ፤ ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” በማለት ራሷን በመንፈስ ድሃ በማድረጓ ጌታችን “አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ” ብሏታል። ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ድናለች። የመንፈስ ድህነት እንደዚህ አይነት ልባዊ ትህትና ነው። ለዚህ ነው ሐዋርያው ያዕቆብ “በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል (ያዕ 4:10)” በማለት ያስተማረው።
የቅዱስ ጳውሎስ ትህትና: ቅዱስ ጳውሎስ የእግዚአብሔር ምርጥ ዕቃ የተባለ ሐዋርያ ሲሆን እርሱ ግን ራሱን “ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ (1ኛ ቆሮ 15:8)” በማለት ራሱን ዝቅ ያደርግ ነበር። እንዲሁም “እኔም ራሴ ጳውሎስ፥ በእናንተ ዘንድ ፊት ለፊት ሳለሁ ትሁት የሆንሁ፥ ከእናንተ ግን ብርቅ የምደፍራችሁ፥ በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እመክራችኋለሁ (2ኛ ቆሮ 10:1)” በማለትም ስለ ትህትናው ተናግሯል። በዚሁ መልእክቱም “እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፥ እንጠማለን፥ እንራቆታለን፥ እንጐሰማለን፥ እንንከራተታለን፥ በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን (ሥራው ድንኳን መስፋት ነበር ሐዋ 18:3)፤ ሲሰድቡን እንመርቃለን፥ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፥ ክፉ ሲናገሩን እንማልዳለን፤ እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጥራጊ የሁሉም ጉድፍ ሆነናል (1ኛ ቆሮ 4:11-13)” በማለት ትህትናውን አሳይቶናል። መታበይንም ከእርሱ እንዳራቀ ሲናገር “እንደዚህ ስላለው እመካለሁ፥ ስለ ራሴ ግን ከድካሜ በቀር አልመካም። ልመካ ብወድስ ሞኝ አልሆንም፥ እውነትን እላለሁና፤ ነገር ግን ማንም ከሚያይ ከእኔም ከሚሰማ የምበልጥ አድርጎ እንዳይቆጥረኝ ትቼአለሁ። ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው (2ኛ ቆሮ 12: 5-7)” ብሏል።
እግዚአብሔር ትሁታንን ከፍ ያደርጋል፣ ትዕቢተኞችን ግን ያዋርዳል
ሐዋርያው ያዕቆብ በመልእክቱ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሁታን ግን ጸጋን ይሰጣል (ያዕ 4:6)” በማለት ትዕቢት በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ፣ ትህትና ደግሞ የተወደደ እንደሆነ ጽፎልናል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በጸሎቷ እንደተናገረችው “በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤ ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤ ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል፤ ትሁታንንም ከፍ አድርጎአል፤(ሉቃ 1:48-52)” በማለት እግዚአብሔር በልባቸው ሀሳብ የሚኮሩ ትዕቢተኞችን እንደሚያዋርድ ትሁታንን ግን ከፍ እንደሚያደርግ ተናግራለች። ጌታችንም ለደቀ መዛሙርቱ “ጻፎችና ፈሪሳውያን ለሰው እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ስለዚህ አሽንክታባቸውን ያሰፋሉ ዘርፉንም ያስረዝማሉ፥ በምሳም የከበሬታ ስፍራ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥ በገበያም ሰላምታና። መምህር ሆይ መምህር ሆይ ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ። እናንተ ግን:- መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ። አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም። አባት ብላችሁ አትጥሩ። ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና። ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ። ከእናንተም የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፥ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል (ማቴ 23:5-12)” በማለት ራስን ከፍ ማድረግ እንደሚያዋርድ አስተምሯል።
ክቡር ዳዊትም እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን እንደሚያዋርድ ትሁታንን ግን እንደሚያከብር ሲናገር “አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህና፥ የትዕቢተኞችን ዓይን ግን ታዋርዳለህ (መዝ 18:27)” ብሏል። እንዲሁም “እግዚአብሔር ትሁታንን በፍርድ ይመራል፥ ለትሁታንም መንገድን ያስተምራቸዋል (መዝ 25:9)” ብሏል። በተጨማሪም “ትሁታን ግን ምድርን ይወርሳሉ፥ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል (መዝ 37:11)” በማለት ዘምሯል። በእውነት እግዚአብሔር የዋሃንን ያነሣል፥ ኃጢአተኞችን ግን እስከ ምድር ድረስ ያዋርዳል (መዝ 147:6)። በእርግጥም እግዚአብሔር የወደቁትን ያነሣል፤ ዕውሮችን ጥበበኞች ያደርጋቸዋል፤ ጻድቃንን ይወድዳል (መዝ 146:8)። እግዚአብሔር የዋሃንንም በማዳኑ ከፍ ከፍ ያደርጋል(መዝ 149:4)። እግዚአብሔር ከፍ ያለ ነውና፥ ወደ ችግረኞችም ይመለከታልና፤ ትዕቢተኞችንም ከሩቅ ያውቃል(መዝ 138:6)። ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ እንደተናገረውም ሰውም ሁሉ ይዋረዳል፥ የሰውም ኵራት ይወድቃል፥ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ብቻ ከፍ ከፍ ይላል(ኢሳ 2:17)። ንጉሡ ናቡከደነፆርም “አሁንም እኔ ናቡከደነፆር የሰማይን ንጉሥ አመሰግናለሁ፥ ታላቅም አደርገዋለሁ፥ አከብረውማለሁ። ሥራው ሁሉ እውነት፥ መንገዱም ፍርድ ነውና፥ በትዕቢትም የሚሄዱትን ያዋርድ ዘንድ ይችላልና (ዳን 4:37)” በማለት እግዚአብሔር ትሁታንን ከፍ እንደሚያደርግ ትዕቢተኞችን ግን እንደሚያዋርድ ጽፏል።
ጠቢቡ ሰሎሞንም በመጽሐፈ ምሳሌ ትዕቢት እንደምታዋርድ፣ ትህትና ግን ከፍ እንደምታደርግ ብዙ ተናግሯል። እግዚአብሔር ለትሁታን ሞገስን እንደሚሰጥ ሲናገር “በፌዘኞች እርሱ ያፌዛል፥ ለትሁታን ግን ሞገስን ይሰጣል (ምሳ 3:34)” ብሏል። ትዕቢትንም ውርደት እንደሚከተላት ሲያስተምረን “ትዕቢት ከመጣች ውርደት ትመጣለች፤ በትሁታን ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች (ምሳ 11:2)” ብሏል። ክብር በትህትና እንደምትገለጥም ያስረዳው “እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ ትምህርት ነው፤ ትህትናም ክብረትን ትቀድማለች (ምሳ 15:33)” በማለት ነው። እንዲሁም ውድቀት ትዕቢትን እንደምትከተላት ሲናገር “ሰው ሳይወድቅ በፊት ልቡ ከፍ ከፍ ይላል፥ ትህትናም ክብረትን ትቀድማለች (ምሳ 18:12)” ብሏል። የትህትናን ዋጋ በተናገረበት ክፍልም “ትህትናና እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት ክብር ሕይወትም ነው (ምሳ 22:4)” በማለት አስተምሮናል። እንዲሁም ሰው ራሱን ከማወደስ ይርቅ ዘንድ “ሌላ ያመስግንህ እንጂ አፍህ አይደለም፤ ባዕድ ሰው እንጂ ከንፈርህ አይደለም(ምሳ 27:2)” በማለት ይመክረናል። ራስን በመንፈስ ድሃ ማድረግ ያለውን ዋጋ ሲያስገነዝበንም “ሰውን ትዕቢቱ ያዋርደዋል፤ መንፈሱን የሚያዋርድ ግን ክብርን ይቀበላል (ምሳ 29:23)” ብሏል።
መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
እግዚአብሔር ራሳቸውን በመንፈስ ድሃ ላደረጉ ሰዎች የሚሰጣቸው ዘላለማዊ ሕይወትን (መንግሥተ ሰማያትን) ነው። ስለዚህ ነው ጌታችን በወንጌሉ “ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና (ማቴ 6: 19-21)” በማለት ያስተማረው። ራሳቸውን በመንፈስ ድሃ ያደረጉ ትሁታን አላፊና ጠፊ የሆነውን በታይታ የሚገኘውን ታዋቂነትና ዝና ሳይሆን በጾም፣ በጸሎትና በምጽዋት በሰማይ መዝገብን (ጽድቅን) ያከማቻሉ። ለዚህም ምስክር ይሆን ዘንድ አልዓዛር በምድር ሳለ ራሱን በመንፈስ ድሃ በማድረጉ በሰማይ ከአብርሃም እቅፍ ተቀምጦ ታይቷል። ነዌ ግን በባለጠግነትና በትዕቢት ስለኖረ ተፈርዶበታል (ሉቃ 16:19-31)። አልዓዛርን ለጽድቅ ያደረሰው የሥጋዊ ድህነቱ ሳይሆን ትህትናው ነው። ነዌንም ለቅጣት የዳረገው ምድራዊ ባለጠግነቱ ሳይሆን ትዕቢቱ ነበር።
በመዋዕለ ሥጋዌው ራሱን ድሃ ያደረገው የድሆች መጠጊያ የድኅነት ምንጭ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አንድ ሰው፥ ጌታ ሆይ፥ ወደ ምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ ሲለው “ለቀበሮዎች ጕድጓድ ለሰማይም ወፎች መስፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም (ሉቃ 9:58)” ነበር ያለው። ሰማይንና ምድርን የፈጠረ ጌታ ለሰው ልጅ ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለ። ነገር ግን ስለ መንግሥተ ሰማያት ሲናገር “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ (ዮሐ 14:2-3)” ነው ያለው። አዎን የእርሱን አርአያነት ተከትለው ራሳቸውን በመንፈስ ድሃ ላደረጉ እርሱ መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳቸዋል። አስቀድሞም እግዚአብሔር ለጠቢቡ ሰሎሞን ቃል ኪዳን ሲሰጥ “በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው (በትህትና) ቢጸልዩ፥ ፊቴንም ቢፈግሉ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፥ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፥ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ (2ኛ ዜና 7:14)” ብሏል።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ፥ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙምና፤ ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት፥ በምድሪቱም እንግዶችና መጻተኞች እንዲሆኑ ታመኑ። አሁን ግን የሚበልጠውን እርሱም ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም፥ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና (ዕብ 11:13-16)” በማለት በምድር ራሳቸውን መጻተኞች (ድሆች) ላደረጉ እግዚአብሔር በሰማያት ከተማን እንዳዘጋጀላቸው አስተምሯል። ወንጌላዊው ዮሐንስ በመልእክቱ “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም። ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል (1ኛ ዮሐ 2:15-17)” በማለት በሰማያት ዘላለማዊ ሀብትን የሚያስገኘው የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸም እንደሆነ ተናግሯል።
ጌታችንም “እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ቤትን ወይም ወላጆችን ወይም ወንድሞችን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን የተወ፥ በዚህ ዘመን ብዙ እጥፍ በሚመጣውም ዓለም የዘላለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም አላቸው (ሉቃ 18:30)” በማለት ስለክርስትናቸው ሁሉን የተው መንግሥተ ሰማያትን እንደሚወርሱ አረጋግጧል። ለዚህም ምስክር የሚሆነን ራሱን በመንፈስ ድሃ አድርጎ “አቤቱ በመንግሥትህ አስበኝ” ያለው በቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ “ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ” መባሉ ነው (ሉቃ 23:42)። እርሱ በትህትና የሚያምኑትንና የሚያገለግሉትን የዘላለም ሕይወትን ያወርሳቸው ዘንድ የታመነ ነው። ስለዚህ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትህትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ (ቆላ 3:12)” በማለት እንዳስተማረው ትህትናን ልንለብስ ይገባናል፣ እርሱን ካልለበስን እርቃናችን ይታያልና። እንዲሁም “በትህትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ (ኤፌ 4:2-3)” እንዳለው ትህትናን ገንዘብ እናድርግ።
ትህትናና መንፈሳዊ አገልግሎት
መንፈሳዊ አገልግሎት የትህትና አገልግሎት ነው። አገልጋዮች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ የሚያደርጉበት አገልግሎት ነው። አገልግሎቱም ዋጋ የሚያስገኘው በትህትና ሲሆን ብቻ ነው። ጌታችን ይህንን የትህትና አገልግሎት በተግባር ሲያስተምር የደቀ መዛሙርቱን እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፥ እንዲህም አላቸው። “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ። እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም። መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም። ይህን ብታውቁ፥ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ” (ዮሐ 13:12-17)። ብፁዓን ትህትናን የሚያውቋት ብቻ ሳይሆኑ አውቀው የሚያደርጓት ናትና።
ትህትናና ራስን መግለጽ
በመጽሐፍ ቅዱስ በብዛት የተገለጸው ትህትና መንፈሳዊ ትህትና ነው። ይህም የጽድቅ ሥራን የሚመለከት ነው። በሥጋዊ ሥራም ትህትና አስፈላጊ ነው። ሆኖም መንፈሳዊ ትህትናን እና በሥጋዊ ዕውቀትና ሙያ ራስን መግለጽን ማምታታት የለብንም። እውነተኛ ትህትና ራስን ማሳነስ (መጣል) አይደለም። እውነተኛ ትህትና ራስን በሚገባ በማወቅ ራስ ላይ ከማተኮር ይልቅ ለእግዚአብሔርና ለሌሎች ሰዎች ክብርን መስጠት ነው። ራስን እና ስኬትን በእውነትና በሚገባው መጠን (የረዳን እግዚአብሔር መሆኑን በማስተዋል) መግለጽ ትህትና ማጣት አይደለም። ይልቁንስ ካለን ዕውቀትና ክህሎት በላይ አድርገን (አጋነን) ራሳችንን እንዳንገልጽ መጠንቀቅ አለብን። ውድድር በበዛበት ዓለም ስንኖር ራሳችንን በሆንነው ልክ መግለጽ ተዓማኒነት (honesty) እንጂ ትዕቢት አይደለም። ትዕቢት የሚሆነው እኛ የሆንነውን በራሳችን ችሎታና ጥበብ እንደሆነ እያሰብን ራሳችንን ከፍ አድርገን፣ ሌሎችን ደግሞ ከራሳችን አሳንሰን ማሰብ ወይም መመልከት ስንጀምር ነው። ስለዚህ ነው ጠቢቡ ሰሎሞን “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል። በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፤ እግዚአብሔርን ፍራ፥ ከክፋትም ራቅ (ምሳ 3:5-7)” በማለት የጻፈልን።
በአጠቃላይ ልባዊ ትህትና ሁሉን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን በማመንና በእርሱም በመታመን፣ ከራሳችን ፍላጎት ይልቅ ለሌሎች ቅድሚያና ክብር በመስጠት፣ ትኩረታችንን በመንፈሳዊ አገልግሎትና እግዚአብሔርን በማመስገን ላይ የምናደርግበት ሕይወት ነው። እውነተኛ ትህትናም ራስን ማወቅ እንጂ በራስ አለመተማመን አለመሆኑን ልንረዳ ይገባል። በተጨማሪም እውነተኛ ትህትና በአፍአ ትሁት መስለን ነገር ግን በልባችን ትዕቢትን ሸሽገን የምንኖረው የማስመሰልና የድራማ ሕይወት አለመሆኑን ልንረዳ ይገባል። ያለ ልባዊ ትህትና ክርስቶስን መምሰል አይቻልም። በአንጻሩም በትዕቢት መኖር በትዕቢቱ ብዛት የወደቀ ዲያብሎስን መምሰል ነው። ያለ ትህትና ክርስትናም ቅድስናም የለም። የወንጌል መልእክት የቅዱሳን ሕይወት ሁሉ የሚያስተምረን ትህትናን ነው። በትዕቢት የወደቀ እንጂ የጸደቀ የለም። ይህንን እውነት አስተውለን ልባዊ ትህትናን በሕይወታችን ሁሉ ገንዘብ ልናደርግ ይገባል እንላለን። በመንፈስ ድሆች ሆነን በማስመሰል ሳይሆን በእውነት በእግዚአብሔር ፊት፣ እንዲሁም በዓለማዊ መመዘኛ ታላቅም ሆነ ታናሽ በሚባሉ ሰዎች ፊት በትህትና ተመላልሰን፣ የትሁታን አምላክ እግዚአብሔር በምትመጣ መንግስቱ ከሚያከብራቸው ቅዱሳን ጋር እንዲደምረን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። አሜን።